Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 December 2012 10:49

ኢንተርፕረነርሽፕና የሽልማት መድረኮች Featured

Written by 
Rate this item
(4 votes)

“ማስታወሻ” በሚል ርዕስ በደራሲና ጋዜጠኛ ዘነበ ወላ ተዘጋጅቶ በ1993 ዓ.ም በታተመውና የደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን የሕይወትና የሥራ ታሪክ በሚያስቃኘው መጽሐፍ “ነጂና ተነጂ” በሚለው ምዕራፍ ላይ፣ ስለ ቀድሞ ዘመን ሥራ ፈጣሪ ኢትዮጵያዊያኖች የሚነገር ታሪክ አለ፡፡ አንደኛው የደራሲ ስብሐት ጓደኛ ነው፤ አቶ ደረጀ ይልማ ይባላል፡፡ ለገንዘብ ግድ የለውም፡፡ ከፈለገም በቀላሉ ሠርቶ ያገኘዋል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ይችላል፡፡ 

ስብሐት ገብረእግዚአብሔር በማስታወቂያ ሚኒስቴር፣ በዓሉ ግርማ በመነን መጽሔት በሚሰሩበት ወቅት አቶ ደረጀ ይጠራቸውና “ቢዝነስ እናቋቁም” ይላቸዋል፡፡ ምን እንዳላቸው አልገባቸውም፡፡ ስላልገባቸው ግን አልተዋቸውም፡፡ ሁለቱን ጓደኞቹን ባለ ድርሻ በማድረግ “ዓለም የሕዝብ ግንኙነት” የሚል የቢዝነስ ተቋም መሠረተ፡፡ ለሥራው የሚያስፈልገው ገንዘብስ ከየት ይምጣ? ብሎ ሲያስብ መልሱ ብዙ አላደከመውም፡፡ በአገራችን የብሔራዊ ሎተሪ ሥራን የጀመሩት አቶ ኢቦን የቢዝነስ ባለ ድርሻ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን በጋራ ለተቋቋመው ቢዝነስ ሥራም አስገኘ፡፡ የብሔራዊ ሎተሪን መጽሔት እንዲያዘጋጁ ተሰጣቸውና ሰርተው አስረከቡ፡፡ 
“ዓለም የሕዝብ ግንኙነት” በብድር በተገኘ 15 ሺህ ብር ነበር ሥራውን የጀመረው፡፡ ዕዳቸውን በአጭር ጊዜ መክፈል ቻሉ፡፡ በዘመኑ በአዲስ አበባ ከተማ ታዋቂ ለነበረው ቢስ ካምፓኒ ማስታወቂያ እስከመስራት ደረጃም ከፍ አሉ፡፡ የቢዝነስ ሀሳብ ሲቀርብላቸው ግር ብሏቸው የነበሩት ስብሐት ገ/እግዚአብሔርና በዓሉ ግርማ፤ ገንዘብ በቀላሉ ሊሰራም ሆነ ሊገኝ የሚችል መሆኑን አዩ፡፡ በዚህ መልኩ ከአዲስ ዕውቀት ጋር ያገናኛቸው ጓደኛቸው አቶ ደረጀ ይልማ፣ በሥራ ፈጠራ የተለየ ተሰጥኦ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ሊያስተዋውቃቸው ሞከረ፡፡ ደራሲ ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ከአቶ ደረጀ ይልማ የሰማሁት ነው ብሎ ለዘነበ ወላ ያጫወተው አንድ ታሪክ በ “ማስታወሻ” ውስጥ እንዲህ ይነበባል፡-
“ፖለቲከኛ፣ ነጋዴ፣ ሸሌ እርስ በእርስ እንደሚቀናናው ሁሉ የቢዝነስ ሰውም እንደዚያው ነው፡፡ ደረጀ ግን እርሱ በፍፁም የቢዝነስ ሰው ያልሆነ ያህል ሌሎችን ሲያደንቅ እሰማዋለሁ፡፡ አንዴ ምን አለኝ መሰለህ? “ተመልከት ይህንን ገብረየስ ቤኛን፡፡ እርሱን የሚያህል የቢዝነስ ሰው የትም ብትሄድ አታገኝም፡፡ እየው ይቀጥላል፡፡ ማንም ምንም የማያስቆመው ሰው ሆኖ ታገኘዋለህ” አለኝ፡፡ ይሄ በጃንሆይ ጊዜ ነበር፡፡ ቀጠለ፡፡ ደርግም መጣ፡፡ ገብረየስን ማንም አላቆመውም፣ በአሁንም ዘመን እንደቀጠለ ነው፡፡
ይህንን ታሪክ ለጽሑፌ መግቢያ እንድጠቀምበት ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ የተከናወኑ ሁለት ዝግጅቶች ናቸው፡፡
ኢንተርፕነርሽፕ ወይም ሥራ ፈጠራን ማዕከል ያደረጉ ሁለት የተለያዩ መድረኮች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተሰናድተዋል፡፡ የመጀመርያው ህዳር 4 ቀን 2005 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነሮች ሳምንት በአገራችን ለሁለተኛ ጊዜ ሲከበር፣በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተከናወነው ሥነ ስርዓት፣በዕለቱ በብቸኛ ተሸላሚነት የተመረጡት ቀኛዝማች ተካ ኤገና ነበሩ፡፡
ሁለተኛው መድረክ ቅዳሜ ታህሳስ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በሸራተን አዲስ የተከናወነው ነው፡፡ ለ4ኛው የንግድ ስራ ተሰጥኦ ውድድር በ698 ተሳታፊዎች ተጀምሮ ለሠርተፊኬት የበቁ 40 የመጨረሻ ተወዳዳሪዎችና ከነዚህም ውስጥ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብሩን በእኩል የተካፈሉት 10 ተመራጮች ማንነት ይፋ ሆኗል፡፡
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በኢንተርፕረነርሽፕ ዙሪያ ሁለት ታላላቅ ዝግጅቶች መሰናዳታቸው ብዙ አዎንታዊ ነገሮችን ያመለክታል፡፡ ቀዳሚው ለኢንተርፕነርሽፕ በሕዝብና በመንግሥት ደረጃ እየተሰጠው ያለው ዕውቅና ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንተርፕነርሽፐ በሕዝብ የተገዛ ወይም ማንም የእኔ የማይለው ጽንሰ ሐሳብ መሆኑን ከሚያመላክቱት መሐል ቃሉ የቋንቋችን አካል ሆኖ ብዙ ሰው እየተጠቀመበት መሆኑ ነው፡፡ እንደማንኛውም የዓለም ቋንቋዎች፤ አማርኛም ከሌሎች ወስዶ የራሱ ያደረጋቸው ብዙ ቃላት አሉት፡፡ ኢንተርፕነርሽፕንም፤ በተመሳሳይ መልኩ በውሰት ወስዶ የራሱ እያደረጋቸው ካሉ ቃላት መሐል መካተቱ ግልጽ እየሆነ መጥቷል፡፡ በቀጣይ በሚታተሙ የአማርኛ መዛግብት ቃላት የመካተት ዕድሉም የሰፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ኢንተርፕነሮች ሁሉ ባለሀብት ቢሆኑም ሁሉም ባለሀብቶች ግን ኢንተርፕረነሮች አይደሉም ይባላል፡፡ ስለዚህ ኢንተርፕረነር ማነው? ከቢዝነስ ሰው ጋር አንድነትና ልዩነቱ ምንድነው? ግለሰባዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ ተቋማዊና መንግስታዊ ኢንተርፕነርሽፕ አንዱ ከሌላው ጋር ምን ያመሳስለዋል? ምንስ ያለያየዋል? ኢንተርፕረነርሽፕ ከየት ተነስቶ የት ደርሷል? በአገራችንስ ያለው ታሪክ ምን ይመስላል? የሚሉት ጥያቄዎች እያነጋገሩ፣ እያወያዩ እየተፃፈባቸው ይገኛል፡፡ አሁን በመንግሥትና በሕዝብ ዕውቅና የተሰጠው ኢንተርፕነርሽፕ ስያሜውና ስልጠናዎቹ በአገራችን መታወቅ ከጀመረ ቅርብ ቢሆንም ኢንተርፕረነሪያል ተሰጥኦ፣ ባሕርያትና አሰራርን የሚከተሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የቢዝነስ ሰዎች እንደነበሩ አንዱ ማሳያ “ነጂና ተነጂ” ከሚለው ምዕራፍ ወስደን ያየነው ታሪክ ነው፡፡ ኢንተርፕረነሮች ሥራ በመፍጠር፣ ካፒታል በማሳደግ፣ ያልታዩ ነገሮችን በማመላከት የመሪነት ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን በእርሻው ዘርፍ ባከናወኑት ታላቅ ተግባር ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት ድርጅት ከተሸለሙት አንዱ የነበሩት ቀኛዝማች ተካ ኤገና፤ በአገራችን ለሁለተኛ ጊዜ በተከበረው የኢንተርፕረነርስ ሳምንት የዘርፉን ሽልማት ማግኘት የቻሉት የመሪነት፣ የቀጣይነት፣ እጅ ያለመስጠት፣ ያለመሸነፍ፣ … ማንነታቸው ከትላንት ወደ ዛሬ መሻገር ስለቻለ ነው፡፡
በንጉሡ ዘመን ማደግ ጀምሮ የነበረው ሥራ ፈጠራ፣እንዳይስፋፋና እንዲከስም ምክንያት ሆኗል ተብሎ የሚከሰሰው የደርግ መንግሥት፤ በአንድ ወቅት በቡናው ዘርፍ ባደረጉት ምርምር አዲስ ነገር አግኝተዋል ብሎ ዕውቅና ለሰጣቸው ሰው የመኪና ሽልማት አበርክቷል፡፡ በ4ኛው የንግድ ስራ ተሰጥኦ ውድድር በአንደኝነት የተመረጡት አቶ አህመድ ሀሰን ስኳርም ለአሸናፊነት ያበቃቸው ከቡና ጋራ የተያያዘ የፈጠራ ስራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ለእርሻው ዘርፍ መለወጥ፣ መሻሻልና ማደግ ጠቃሚ የሆነ ሥራ መስራት የቻሉ ግለሰቦች በንጉሡም፣ በደርግም፣ በኢሕአዴግም ዘመን መሸለም ከቻሉ ታዲያ ሁሉም መንግሥታት ለአገርና ሕዝብ የተመኙት ለውጥና ዕድገት ፈጥኖ ያልተዳረሰበት ምክንያት ምንድነው? ችግሩ የቱ ጋ ነው ያለው? የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡
መልሱም ግልጽና ቀላል ነው፡ አገሪቱ አልላቀቃት ያለ ከዜሮ የመጀመር አባዜና የቀጣይነት ችግር ነው፤ የሚታሰበው ዕድገትና ለውጥ እንዳይገኝ እንቅፋት ሆኖ ዛሬ ላይ የተደረሰው፡፡
አሁን ለሥራ ፈጠራ ወይም ለኢንተርፕረነርሽፕ በሕዝብና በመንግሥት የተሰጠው ዕውቅና አዎንታዊ ተግባር ከመሆኑም ባሻገር፣ ለቀጣይነቱ የሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ብዙ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከሁሉም በላይ መቅደም ያለበት ግን ሽልማት የሚሰጠው ተቋም ማንነትና ሕጋዊ አደረጃጀት ጉዳይ ነው፡፡ ለአራት ዙር ለተካሄደው የንግድ ስራ ተሰጥኦ ውድድር ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የስፖንሰር አድራጊዎች አስተዋጽኦ የጎላበት ነበር፡፡
ታህሳስ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በሸራተን አዲስ በተከናወነው ሥነ ስርዓት ደግም የኮንስትራክሽንና ከተማ ልማት ሚኒስቴር “የሚቀጥለውን ውድድር በተሳትፎም ሆነ በሽልማቱ ከአሁን የተሻለ አድርገን እንሰራዋለን” ብሏል፡፡
እንደዚህ ዓይነት ውድድሮችና ሽልማቶች አስተማማኝ መሠረት ከሌላቸው ቀጣይነታቸው አጠራጣሪ ይሆናል፡፡
የገንዘብ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ አካላት ስለተገኙ ብቻ ቀጣይነቱን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ከሕጋዊ አደረጃጀት በተጨማሪ ኃላፊነትና ተጠያቂነትን ይፈልጋል፡፡

Read 10130 times