Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 17 September 2011 10:01

የአስናቀች ወርቁ ሥርዓተ ቀብር ተከናወነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከያንያን ከሞቷ ይልቅ በመጨረሻ ሕይወቷ አዝነዋል
በክራር ዜማዎቿ ይበልጥ የምትታወቀውና ሐሙስ ማለዳ በ78 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው አንጋፋ አርቲስት አስናቀች ወርቁ ሥርዓተ ቀብር ትናንት ተከናወነ፡፡ በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ሥላሴ ደብር እኩለ ቀን ላይ በተከናወነው ሥርዓተ ቀብር የሙያ አጋሮቿ፣ አድናቂዎቿና ቤተሰቦቿ ተገኝተዋል፡፡ ከቀብር ሥነሥርአቱ በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በተከናወነላት የመታሰቢያ ዝግጅት የተገኙ አርቲስቶች ከሞቷ ይልቅ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ በነበረው የመጨረሻ ሕይወቷ አዝነዋል፡፡ በዝግጅቱ የመጨረሻ ዘመኗ የሕመምና የሰቆቃ ነበር ብለዋል፡፡ አንጋፋዋ አርቲስት ሰላማዊት ገብረሥላሴ ..ሞተች አይባልም እረፍት ነው ሕመም ቆይቶባታል.. ብላለች፡፡

ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ አንጋፋ አርቲስትም የምትኖርበትን ቤት ኪራይ ተጨማሪ ሕመም ሆኖባት እንደከረመ በምሬት ተናግረዋል፡፡ አርቲስት ደበሽ ተመስገን በተለይ ጋዜጠኞች ..አርቲስት.. አትበሏት እሷ ከዚያም በላይ ነች.. በማለት የሙዚቃ መሳርይ ተጫዋችነቷን፣ ድምፃዊነቷን፣ ተዋናይነቷን፣ ተወዛዋዥነቷን ወዘተ የጠቀሰ ሲሆን የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሐት ሁሉንም የኢትዮጵያ ቅኝቶች መጫወቷን አውስቷል፡፡ ..ኢትዮጵያውያን ሴቶች ተገፍተዋል የምንለው በኪነጥበባትም ጭምር ነው.. ያለው አርቲስትና ጋዜጠኛ ሱራፌል ወንድሙ አስናቀች ግን ተእኖውን ጥሳ በመውጣት አርአያ መሆኗን ተናግሯል፡፡ ከትልቅ ስኬት ላይ መድረሷን አስምሮ የተናገረው አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ ትልቅ ዝግጅት በሥሟ ለማቅረብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበርን በመወከል በስፍራው የተገኘው ደራሲ አፈወርቅ በቀለ ..ያለፈችበት ሕይወት ያሳዝናል፤ ይኼ የአብዛኛው ኪነጥበብ ባለሙያዎች እጣ ነው.. በማለት የግል አስተያቱን የሰጠ ሲሆን በማከልም በሽኝቷ ሥለ አስናቀች ብዙ መናገር የሚችሉ ባለሙያዎች አለመገኘታቸውንና የመንግስት ተወካዮች ባለመኖራቸው ጭምር ማዘኑን ገልፆ በማህበር ተወካይነቱ ዘላቂ ማስታወሻ እንደሚያስፈልጋት ተናግሯል፡፡ ..አስናቀች ወርቁ.. በሚል ርእስ አንጋፋው አርቲስት ጌታቸው ደባልቄ በ1995 ዓ.ም ገደማ መሐፍ የተፃፈላት አስናቀች ወርቁ፣   ..የክራሯ ንግስት.. በመባል የምትታወቅ ሲሆን የመጀመሪያ ክራሯን የገዛችው በያኔው ስሌት በ25 ሳንቲም ነው፡፡
..አልበር እንዳሞራ..፣ ..የፍቅር ጮራ.. (1945 ዓ.ም) ..እንደ ኢየሩሳሌም.. ..ሳብዬ.. በሚሉት ክራር ቅኝት ዘፈኖቿ የምትታወቀው አስናቀኝ ..ሥጋ ያጣ መንፈስ.. በተሰኘ የቪዲዮ ፊልም ትወናዋም በመድረክ ትያትሮቿ ትታወቃለች፡፡

 

Read 3567 times Last modified on Saturday, 17 September 2011 10:05