የዘንድሮ  ህዳር አክሱም ጽዮን ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ የታደምኩት በመንፈሳዊ ጉዞ ታቅፌ ወይም ተደራጅቼ ሳይሆን ከስራዬ ጋር በተፈጠረልኝ መገጣጠም ነበር፡፡ እኔም እድሌን እያመሰገንኩ ዓመት በአሉን ታድሜ አመሻሽ ላይ ሻይ ቡና ለማለት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ደመቅመቅ ወዳለችው አክሱም ከተማ ጎራ ብለን በአንድ ካፌ በረንዳ ላይ ስናወጋ፣ አንድ መጽሀፍ አዟሪ ሽፋኑ ላይ በእድሜ የገፉ አዛውንት የስላቅ ፈገግታ እያሳዩ የተነሱትን ፎቶ የያዘ የትግርኛ መጽሀፍ እንካችሁ አለን፡፡ እኔም “ቀልድታትን አሽሙራትን ምህረይ ወሊሃንስ” የሚለውን መጽሀፍ ገዝቼ እንደ ዋዛ ማንበብ ጀመርኩ።
መጽሀፉ፤ መምሬ ወልደ ዮሃንስ ወልደ አብዝጊ የተባሉ አክሱም ውስጥ     “እብዱ ሰው” በሚል ቅጽል ስም ሲጠሩ በዕድሜ ዘመናቸው የተናገሯቸው፤ የቀለዷቸውና ያሸሞሯቸውን ንግግሮች የያዘ ሲሆን (ሰው ባትም እንደ አለቃ ገብረሃና ሰፊ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ናቸው) በሰለሞን ገ/ህይወት ተዘጋጅቶ በ2006 ዓ.ም ለንባብ የበቃ መፅሃፍ ነው፡፡
የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በመጽሀፉ ዙሪያ ሙያዊ ሂስ ለማቅረብ ሳይሆን በመጽሀፉ መግቢያ ላይ የተጻፈውን እጅግ ልብ የሚነካና አሳዛኝ የመምሬ ወልደ ዩሃንስ አጠቃላይ የህይወት ውጣ ውረድ ለማስቃኘት እንዲሁም ከመጽሀፉ ውስጥ አንባቢ ቢሰማቸው ብዬ ያመንኩባቸውን የተወሰኑ ዋዛና ቁምነገሮችን ማካፈል ነው፡፡ በተጨማሪም አዘጋጁ ይህን መጽሃፍ ወደ አማርኛ ተርጉሞ ለሌሎች አንባብያን እንዲደርስ ወንድማዊ ምክሬን ለመለገስ በማሰቤም ጭምር ነው። ወደ ታሪኩ ስንገባ ታዲያ!
ምህረይ ወልደ ዩሃንስ ወልደ አብዝጊ፤ ህዳር 3 ቀን 1917 ዓ.ም በአክሱም ዞን ናእዴር አዴት በተባለ ወረዳ፣ ጎዲቖ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ተወለዱ የሚለን ጸሀፊው፤ በመቀጠልም እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ እስከ ጎጃም ድረስ በመሄድ ጥልቅ የቤተክህነት ትምህርት ተከታትለው በመምጣት በአዴት መድኀኒዓለም ቤተክርስቲያን ሲቀድሱ መኖራቸውን ይነግረናል።
እኚህ አዋቂ ሰው ትዳር መስርተው ሶስት ልጆችን ወልደው፣ እንደ ማንኛውም የገጠር አርሶ አደር ኑሯቸውን በግብርና ላይ መስርተው ሲኖሩ በነበረበት ወቅት፣ በ1951 ዓ.ም በትግራይ “ዘመነ አንበጣ” እየተባለ የሚታወቀው የአንበጣ ወረርሽኝ በአዝመራው ላይ የነበረውን ቡቃያ አዝርእት በማጥቃት እንኳንስ ለሰው ልጅ ለከብቶች እንኳን ገለባ ሳይተው እንዳልነበረ አደረገው፡፡ በዚህ ጊዜም  ምህረይ ወልደ ዩሀንስ እንዲህ አሉ ይባላል፤ “አቤቱ ጌታዬ! መቼም የአንተ ፍጥረት ሆነን አንበጣን ለምን ፈጠርክ አንልም፡፡ አንበጣስ ቢሆን የአንተው ፍጥረት አይደል? ከሆነልህ አንበጦቹን ወደ ንብ ቀይርልንና ማር እንኳን ቢሰጡን። አምላኬ!! ለኛ ቀርቶ ለከብቶቻችን የሚሆን ገለባ እንኳን ሳያስቀሩ አንበጦቹ ቅርጥፍጥፍ አድርገው ሲያወድሙት መቼስ ምን እንበል?” አሉ ይባላል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን የምህረይ ህይወትን የሚቀይር ክስተት አስከትሎ መጣ ይለናል ጸሐፊው፡፡ ምን አስከተለ? የሚል ጥያቄ ማንሳት መቼም ተገቢ ነው፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ከአንበጣ መንጋው አደጋ በኋላም ምህረይ ይቀድሱበት በነበረው ቤተክርስቲያን ቅዳሴው ተጠናቆ ገድለ እዮብን አንብበው እንዲህ አሉ፤ “ተመስገን ነው የሚባለው ጎበዝ? ተመስገን በሉ፡፡ እዮብ ያ ሁሉ መከራ ወርዶበት ተመስገን ነው ያለው፡፡ ተመስገን በማለቱም አምላክ ዳግም ፈጠረው፡፡ የሆነው ሆኖ ፈጣሪ ተመስገን ነው የሚፈልገውና ተመስገን በሉ፡፡” በወቅቱ በቤተክርስቲያን የሚካሄደው ምህላ ከወትሮው የተለየ ነበር፡፡ ህጻን አዋቂ፤ አሮጊት ሽማግሌ ሳይቀር በጉልበቱ ተንበርክኮ ምህላ ለእግዚአብሔር ያቀርባል። ይህን የታዘቡት ምህረይም፤ “እናንተ ሰዎች ይህን ምህላ ለአባቶቻችንና ለእናቶቻችን እንተውላቸው፡፡ እናንተ ወጣቶች ግን እስኪ አምላክን እናግዘው፡፡ ስደት እንሂድና ችግሩን እናሳልፍ፡፡ በጓዳ ያለውን እህል እየቆሉ በልተውም ቢሆን እድሜያቸውን ቢገፉ ትተልናቸው እንሂድ። አምላክ ጸሎታችንንና ምህላችንን ቢሰማ እንኳን ዝናብ እንጂ ገብስ አያዘንብልንም፡፡ በዚህ በጋ ወቅት ዝናብ ቢያዘንብ እንኳን ችለው የሚጠመዱ በሬዎች የሉንም፡፡” ብለው አቅም ያላቸውንና እንችላለን የሚሉ ሰዎችን ጨምረው ስደት ሆነ፡፡ ወዴት? ተስፋ ወደ አሳደሩበት ፀለምት፡፡ ሸቅለውም ሆነ ለምነው የቤተሰቦቻቸውን እስትንፋስ ለማራዘም ትንሽዬ መኮትኮቻቸውን ይዘው በመንገድ ከገበሬ በቤት እየለመኑ፤ ስር እየማሱና እየተመገቡ መሪሩን የበረሃ ጉዞ ያለ በቂ እህልና ውሃ ተያያዙት፡፡ ያ የበረሃ ጉዞ ግን እንደታሰበው ቀላል አልነበረም፡፡ ሁለቱን ልጆቻቸውን የትኩሳት ህመም አሸነፋቸውና እጅ ሰጡ፡፡ የአንዱን ልጅ ስም ጠርተው አልቅሰው ሳያበቁ ሁለተኛው ልጅ ተከተለ፡፡
ግማሽ እድሜያቸውን እያወደሱና እየቀደሱ ያገለገሉትን ፈጣሪ ቀና ብለው ተማጸኑ፡፡ ከወሰደ የማይመልስ ፈጣሪ ግን ምላሽ አልሰጠም፡፡ ዝም! በቃ ዝም! አምላክ እንደ እዮብ ሊፈትነኝ ሳይሆን አይቀርም ብለው የሚወዷት ሚስታቸውንና አንድ ልጃቸውን እየተመለከቱ፤ “ተመስገን እንጂ ሌላ ምን ይባላል አምላኬ?”  አሉ፡፡ ይህን የሰሙ ሚስታቸው “ምን አሉ?” ሲሏቸው “ተመስገን ነው ያልኩት” ሲሉ ሚስትየው አከታትለው አጓሩ፡፡ “ሆይ … ሆይ” በማለት፡፡  
ምህረይ ሁለቱን ልጆቻቸውን ቀብረው እንደ ሰማይ ኮከብ የራቀችው ጸለመት ላይ ለመድረስ በዚያ በበርሃ ዳዴ ሆነ፡፡ ዳዴ ብቻ፡፡ የሰሜን ምዕራብ የትግራይ በረሃን እየወደቁ እየተነሱ መጓዝ ሆነ ምርጫው፡፡ የባለቤታቸው ጉልበት በሃዘንና በረሃብ መላወስ እያቃተው ሙክክ ብሎ ቀረ፡፡ ግንባራቸው በላብ ተጠምቆ፣ በረሃብና በውሃ ጥም የደረቀ ጉሮሮአቸውን ሊያረጥቡ ፈለጉ መሰለኝ “ውሃ፤ ውሃ፤ ው…ሃ እባክህ ውሃ ስጠኝ” እያሉ ማንቋረር ጀመሩ፡፡ የውሃ ጠብታ በሌለበት በረሃ ውሃ እያሉ፣ ውሃ ሆነው የልጆቻቸውን ዱካ ተከትለው አሸለቡ፡፡
ምህረይ ወልደ ዩሀንስ ምን ይበሉ? ምንስ ሊሉ ይችላሉ? ጸለምት ገብተው የሰዎችን እርሻ ኮትኩተው የቤተሰቦቻቸውን እስትንፋስ ለማትረፍ የያዟት መቆፈሪያ የሁለት ልጆቻቸውና የባለቤታቸው ጉድጓድ መቆፈሪ ሆነች፡፡ በቃ ወደ ሰማይ አንጋጠው ፈጣሪን ተመለከቱ፡፡ እልህ ይሁን ብስጭት ባሸነፈው አንደበት “አልክ!? አልክ አይደለም? ካልክስ ደስ ይበልህ! ተመስገን!” አሉ፡፡ በእጃቸው የያዙትን መቆፈሪያ “አሁንስ ማን ቀረሽ ይሆን?” ብለው አርቀው አሽቀንጥረው ወረወሯት፡፡ የተረፈ አንድ ልጃቸውን ይዘው፣ ቁጣ ጉልበት አበደራቸው መሰለኝ፣ ከሩጫ በማይተናነስ እርምጃ ከሚስታቸው መቃብር ሽሽት ሆነ፡፡ ከሞት ሽሽት!!
ልጃቸውን አዝለው ከፊት ለፊታቸው የተገተረውን ተራራ መቧጠጡን ተያያዙት። አሰጋገራቸው የተራራው ጫፍ ላይ ወጥተው ፈጣሪን ሊሟገቱ ይመስላል፡፡ ተራራው ጫፍ ላይ ሳይደርሱ ግን ጀምበር አዘቀዘቀች፡፡ ታዲያ ይህ ሁኔታ በፈጠረላቸው አጋጣሚ ከተራራው ወገብ ላይ በሩቁ በገዳመ ጰንጠልዮን የመነኑ ባህታውያን የያዙት እሳት ብልጭ ብልጭ ሲል ታያቸው፡፡ ተመስገንን ዘንግተው የነበሩት ምህረይ፣ በዚያች የእሳት ብልጭታ ምክንያት ተመስገንን አስታውሰው፤ “ተመስገን… ተመስገን… ተመስገን .. አምላኬ” አሉ፡፡ መጾም መጸለይ ሰርክ ተግባራቸው የሆነው ምህረይ፣ እንኮኮ አድርገው ላዘሉት ልጃቸው አንዳች የሚበላ ነገር አቅምሰው እድሜውን ማራዘም ነበረባቸው፡፡ እንደ ዝንጀሮ በአራት እግራቸው ተራራውን እየቧጠጡ ገዳሙ ጋር ሲደርሱ፣ እንደርሳቸው ስደት የወጡ ወጣቶች የተጋገረ ቂጣ ሲበሉ አገኟቸው፡፡ ቂጣው እንዳያልቅ የሰጉት ምህረይ፣ ያለ ቀልባቸው “እባካችሁ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ ለልጄ የሚሆን ትንሽ አስተርፉልኝ” እያሉ መማጸናቸውን ያዙ፡፡ አንድ ባህታዊ ቀበል አድርገው “ይበሉ እንጂ ጌታዬ የሚበላ ሞልቷል ይልቅ ለጁን ያውርዱትና እህል አቅምሱት” ሲሏቸው ድንግጥ ብለው “ተመስገን … ተመስገን … ጌታዬ!” ብለው ልጃቸውን ከጀርባቸው ላይ ዳሰስ ቢያደርጉት እስትንፋስ አልቦ ሆኖ ድርቅ ብሏል፡፡ ለዘላለም አንቀላፍቷል፡፡
ምህረይ ከዚህ በኋላ ፈጣሪን ተመስገን ይበሉት ይውቀሱት የሚያስታውሱት ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊገቡባት አስበዋት የነበረችው ጸለምት ከተማ ለብቻቸው ገብተው “እኚህ ወፈፍ የሚያደርጋቸው ሰውዬ መጡ” እያለ የከተማው ህዝብ ይናገር እንደነበር ብቻ ነው የሚያስታውሱት፡፡
ከረጅም ጊዜ በኋላ ዘመን ሲቀየር እብድ እየተባልኩ ጸለምት ከምኖር ወደ ሚያከብረኝ ህዝብ ሄጄ የቤተሰቤን ማለቅ አርድቼ፣ ደብሬን እያገለገልኩ ብኖር ይሻለኛል ብለው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ተመለሱ፡፡ ወደ ቀዬአቸው ሲገቡ ግን ያዩት ነገር አስደንጋጭ ሆነ፡፡ መኖሪያ ቤታቸው ፈርሶ፣ በማሽላና በጤፍ አዝርእት ተሸፍኖ፣ የአንድ ቤተሰብ አባላት አጨዳ ሲያካሂዱ አገኟቸው፡፡ በውስጣቸው “እውነትም ሰው እንደሚለው ሳላብድ አልቀረሁም?” ብለው አንዲት ቃል ግን ሳይተነፍሱ አረፍ አሉ፡፡ በወቅቱ አዴት ከተማ ውስጥ እዳጋ ሰሉስ በሚባል ቦታ መሬታቸውን የወሰደው ሰው ከሹመኛ ዳኛ ጋር እየተሳሳቀ ሲያወራ ያገኙትና ሞግተው እንደማይረቱት ተገንዝበው አማራጭ ስላልነበራቸው፣ ወደ ፍርድ ቤቱ ሰሌንና አነስተኛ እራፊ አቡጀዲ ለብሰው ቀረቡ፡፡ ዳኛው ተገርሞ፤ “ምህረይ ለምንድን ነው ሰሌን ለብሰው የመጡት?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ምህረይም ተስፋ በቆረጠ አንደበት፤ “ሞቴ ካልቀረ ብትገንዙኝ ብዬ ነው የመጣሁት” ሲሉ ችሎቱ በሳቅ ተሞላ፡፡ ቀጠለ፡፡ ምህረይም “ከእንግዲህ የተረፈኝ ምህረይ! እንዲህ አሉ የሚል ተረት ብቻ እንጂ ፍትህ አላገኝም” ብለው ወደ ጎዳና ወጡ፡
አክሱም ከተማ ከሃውልቱ ስር እንዲሁም በሽሬ ጎዳናዎች ላይ ብርድና ጸሃይ ሲፈራረቁባቸው ኡኡታቸውን ማሰማት ቀጠሉ፡፡ ሰዎች ከመሬት ተነስተው የሚጮሁ እየመሰላቸው አበዱ ሲሏቸው መሳቅ፤ መዝፈንና ማፏጨት እለታዊ ተግባራቸው ሆነ፡፡
ምህረይ ወልደ ዩሃንስ “እብድ” የሚል ተቀጽላ ስም ተሰጥቷቸው፣ እርሳቸውም እብድነታቸውን በጸጋ ተቀብለው አዝናኝና አሸሟሪ ንግግራቸውን ለሰው እያካፈሉ መኖር ጀመሩ፡፡ በጣም የሚገርመው የታሪካቸው ክፍል ደግሞ ቀን እብድ እየተባሉ ከተማ ውስጥ ሲዞሩ ውለው ለሊት በቤተክርስቲያን ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ ማደራቸው ነበር፡፡ ወደ ሞታቸው አቅራቢያ ወዳጆቻቸው በቆርቆሮ ቤት ሰርተው፣ ልብሳቸውንም ቀይረውላቸው ያኖሯቸው ነበር፡፡ በዚያች ቆርቆሮ ቤት ውስጥ ለአንድ ዓመት ከስምንት ወር ተቀምጠው፣ እግራቸው ላይ በወጣች ቁስል ምክንያት ህመም በርትቶባቸው ህዳር 28 ቀን 1998 ዓ.ም በ81 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
የእኚህን ታላቅ ሰው ቅኝት ከመቋጨቴ በፊት ለዛሬ አንድ ሁለት የተናገሯቸውን አሽሙሮች ላካፍላችሁ፡፡
ማበድ መልካም
ምህረይ ወልደ ዩሃንስ ብዙ ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት እየሄዱ ወንጀለኞች የፈጸሟቸውን የወንጀል ተግባራት ሲሰሙ ይውሉ ነበር፡፡ ታዲያ ባንዱ ቀን አንድ ጤነኛ ተብሎ የሚታመን ሰው የፈጸመው ወንጀል በጣም አስገርሟቸው ነው መሰለኝ በመንገድ ላይ “ማበድ መልካም!! ማበድ መልካም!! ማበድ መልካም!!” እያሉ ከተማዋን ሲዞሩ ዋሉ፡፡
ሁኔታቸው የገረመው አንድ ሰው አስቆማቸውና፤ “ምህረይ፤ እንዴት ብሎ ነው ማበድ መልካም የሚሆነው? ምን እያሉ ነው?” ብሎ ሲጠይቃቸው፤ “አብደህ እየው ልጄ!! አብደህ እየው ልጄ! አብጄ ነው መልካም መሆኑን የተረዳሁት” ብለውት አለፉ።
“ለኔ ብለው”
ምህረይ አክሱም ማሪያም ቤተክርስቲያንን እየሳሙ ሳለ አንድ አራጣ አበዳሪ ያዩና፤ “እስኪ ብር ይስጡኝ?” ይሏቸዋል፡፡ እኚህ አራጣ አበዳሪ ታዲያ ቆጣ ብለው “ዛሬ ማሪያም አይደለችም እንዴ! ስለማሪያም ብለው ይለምኑና እንስጥዎት፡፡ ምንድን ነው እንዳስቀመጡት ገንዘብ ብር ስጡኝ ማለት!!” ይሏቸዋል፡፡
ምህረይ ወልደ ዩሃንስ ቀበል አድርገው፡- “አቤት … አቤት … መጽደቂያ ሊያደርጉኝ ፈልገው ነው? ከፈለጉ ለኔ ብለው ይስጡኝ፡፡ ካልፈቀዱ ደግሞ ይቅርብኝ፡፡” ብለዋቸው ሄደ፡፡ (አራጣ አበዳሪ አይጸድቅም ስለሚባል)
“እኩልነት”
ምህረይ ወልደ ዩሃንስ የሚወዱትን ቢራ ተጋብዘው እየጠጡ እያለ፣ አንድ ታጋይ ቀረብ ይልና እንዲህ ይላቸዋል፡-
ታጋዩ፡- “ምህረይ፤ አሁን ነው ድሮ የጾታ እኩልነት የተረጋገጠው?”
ምህረይ - “ድሮ ነበር እንጂ እኩልነት የነበረው፤ አሁን የታለ” ይሉታል፡፡
ታጋዩ ተገርሞ፡- “እንዴት?” ይላቸዋል፡፡
ምህረይ ቀበል አድርገው፤ “ዛሬማ ወንዶች ለብቻችን እየተገረዝን ምን እኩልነት አለ ብለህ ነው?” አሉት ይባላል፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 31 January 2015 13:17

የምርጥ ውሻ አጭር ታሪክ

ሰዎች ነን አይደል?! እንዴት አወቃችሁ?
አቦ ግራ አትጋቡ በናታችሁ! … እስቲ አንድ ነገር ላይ እንኳን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ በናታችሁ! ሰዎች ነን። እንዴት አወቃችሁ? … ሥነ ልቦና አለን፤ ብትሉኝ መልስ ነው። ሥነ ልቦናን ያጠኑ ብዙ ተመራማሪዎች ተደርድረው ታገኛላችሁ፤ “ጉግል” ላይ ብትገቡ፡፡ ይኼ ሁሉ ጥናት ስለኛ ነው እስክትሉ ድረስ፡፡ ፓቭሎቭ፣ እስኪነር፣ ሀርሎ፣ ሀድሰን፣ ኔሰን፣ ኮህለር … ዳርዊንም እንደ ስነ ልቦና ተመራማሪ ያደርገዋል፤ ሸንቆጥ ሲያደርገው፡፡
ሩሲያዊው ፓቭሎቭ ስለ ሰዎች ያጠናው በውሻ ስነ ልቦና አማካይነት ስለሆነ … ውሻ የሆኑ ሰዎች ፓቭሎቭ ጂኒየሳቸው ነው፡፡ ማነው ውሻ? እንዳትሉኝ፡፡ ቀስ ብለን አብረን እንየው፡፡ (“ማነው ማነው ያለኝ?! እሱ ራሱ ማነው? ሰው ከመሆን ወዲያ ማንነት ምንድነው” የምትለዋን የፍሬዘር አድማሱን ባለ ሁለት መስመር ግጥም “አንድ አለኝ” በሉና በልባችሁ ያዙ፡፡ መጣጥፌ ሲጠናቀቅ ሂሳቡን እንተሳሰባለን)
ውሻ ለምግብ ነው የሚኖረው፡፡ መንግስት ለስልጣን እንደሚኖረው፡፡ ፖሊስ ወንጀለኛ ለመያዝ እንደሚኖረው፡፡ ነጋዴ ለገንዘብ፣ ገጣሚ ለጭብጨባ፣ ሰባኪ ተሰባኪ ለማብዛት፣ አትሌት ለሜዳሊያ፣ እነ እንትና … መፅሐፍ ግርጌ የታተመ ዋጋ ለመፋቅ፣ ወላድ ወልዳ ለማሳደግ ወይ ያሳደገችው እንዲጦራት፣ ፈሪ የሚያስፈራራውን ጀግና አጫርቶ ለመምረጥ፣ ባሪያ አሳዳሪ ባሪያን ለመርገጥ፣ ካፌ ቡና ለመሸጥ፣ “ቀልደኛ” ለመቀለድ፣ አክሱም ታላቅ ታሪኩን ለጎብኚ ለመናገር፣ ምርጫ ለመወዛገብ … እኔ ደግሞ አዲስ ነገር የፃፍኩ መስሎኝ ለመደሰት … ወዘተ የምንኖርለት አላማ አለን፡፡
ፓቭሎቭ ያረጋገጠው ፅንሰ ሀሳብ ለሁሉም ሰዎች ቢሰራ ኖሮ ህይወት ጉጉት አልባ በሆነች ነበር፡፡ ግን ፓቭሎቭ ሊገልፃቸው የማይችል እንደ ጸደቀ ጥላሁን አይነት ሰዎች ምድር አልፋ አልፋ ትፈጥራለች፡፡ ፀደቀ ጥላሁን ባይኖር ሰው ውሻ ስላለመሆኑ ለማሰብ በተለይ እኔን በከበደኝ ነበር፡፡
ጸደቀ ጥላሁን የሚባለውን ሰው ከማወቄ በፊት፣ የሰው ልጆች ለማበረታቻ ሲሉ የሚኖሩ ይመስለኝ ነበር፡፡ ኮሜዲያን የሚስቅለት ከሌለ ቀልድ እንደማይፈጥር ነበር የማስበው፡፡  ማተሚያ ከሌለ ደራሲ እንደማይኖር፡፡ ሌብነት ከድህነት እንደሚመነጭ ነበር የሚመስለኝ፡፡ ጥሩ ተማሪ በብዙ የ“ራይት” ማበረታቻ የሚፈጠር፣ ደደብ ተማሪ በብዙ “ኤክስ” ምልክት ተጠፍጥፎ መሰራቱን ነበር የማውቀው፡፡ ግን ፀደቀ ጥላሁን … (ፀ.ጥ)ን ከተመለከትኩ በኋላ ሀሳቤን ከእናካቴው ቀየርኩ፡፡
ፀደቀ እንደነገረኝ ከሆነ … በፓቭሎቭ ፅንሰ ሀሳብ የማይሰራ ፍጥረት መሆኑን የደረሰበት ገና በልጅነቱ ነው፡፡ ገና መዋለ ህጻናት በነበረበት ወቅት፡፡ ወይዘሮ አልማዝ ክፍት ጫማ ተጫምታ በእንግሊዝኛ የሃይማኖት ዘፈኖች በምታስተምራቸው ወቅት፡፡ ፀደቀ ዘፈኑን የሚዘፍነው ከረሜላ ሽልማት እንዲያገኝ ብሎ አልነበረም፡፡ ደግሞ ከተማሪዎቿ ሁሉ እሱ በሚያወጣው ዜማ ብቻ ነበር ወይዘሮዋ የምትረካው፡፡ ፀደቀ ግን አስተማሪዋ በረካች ቁጥር የምትሰጠው ከረሜላ ወዲያው ሰለቸው፡፡ መዘመር ጥሩ ነገር፣ አስተማሪዋ እንደፈቀደችው መጮህ ደግሞ የሚያሸልም ጀግንነት መሆኑ ነው፡፡ ለጀግናው የሚበረከተው ሜዳይ ደግሞ ከረሜላ፡፡  
ከረሜላው ለሌሎቹ ህፃናት፣ አጥንት ለውሻ እንደሆነው ነው፡፡ ውሻ በእየለቱ አጥንት ቢሰጠው አይሰለቸውም፡፡ ከፀ.ጥ በስተቀር ሌሎቹ ህጻናት እንደዚያ ናቸው፡፡ የወይዘሮ አልማዝ የመዝሙር ክፍለ ጊዜ ሊጀመር መሆኑን የሚያበስር ደውል ገና ከመደወሉ የህፃናቱ አፍ እና አገጭ በአዝረበረቡት ለሀጭ ይርሳል፡፡ ከፀደቀ ጥላሁን አገጭ በስተቀር፡፡
ፀደቀ እንደሚናገረው ከሆነ፣ ህፃናቱ ለሀጭ ሲያዝረበርቡ ፀደቀ እንባ … ጨው ጨው እያለው ወደ ጉንጩ ይወርድበት ነበር፡፡ በማበረታቻው መደጋገም ምክኒያት ማበረታቻው መቀጣጫ እየመሰለው በመምጣቱ … ከፓብሎቭ ፅንሰ ሀሳብ ያፈነገጠ ብቸኛው ቡችላ ሆነ፣ በለጋ እድሜው፡፡
እንደነገረኝ .. ወይዘሮ አልማዝም ማበረታቻ እንዲሰጣት ስትል ነው በከረሜላ ብዛት እፁብ ድንቅ የሃይማኖት መዝሙሮች ታስዘምራቸው (ታዘፍናቸው) የነበረው፡፡ በየወሩ መጨረሻ፣ የደመወዝ ደወል ሲሰማ… ወይዘሮ አልማዝም ህፃናቱ የእሷን ኮቴ በየቀኑ ሲሰሙ እንደሚሆኑት ትሆናለች፡፡ ከወር አንዱም ቀን ብቻ ቢሆንም የምታበቅለው እና የምትቆላው ጅራት አላት፡፡
በከረሜላ ፋንታ ፀደቀ ጥላሁን የተሻለ ማበረታቻ (ሳያስበው) የሆነለት እንዲያውም የአባቱ ኩርኩም ነበር፡፡ ኩርኩም መጀመሪያ ጊዜ የቀመሰ እለት በማልቀስ ፋንታ ሳቀ፡፡ አባቱ የሱን ጭንቅላት በመምታቱ ሲፀፀት ደግሞ ሳቁ ወደ ጉጉት ተቀየረ፡፡ በአባቱ ላይ ስልጣን ያገኘ መሰለው፡፡
በትምህርት ከፍ እያለ ሲሄድ ኩርኩም ከአባቱ ብቻ በአጋጣሚ የሚገኝ ነገር ሳይሆን ከሁሉም አቅጣጭ በሁሉም ሰዓት ጭንቅላቱ ላይ መንጠር ሲበዛ እንደ ከረሜላው ኩርኩሙም አንገሸገሸው፡፡ ኳስ ጨዋታ ጀመረ፡፡ ኳስ መጫወት ሲጀምር ከረሜላዋ ቅርፅ ቀይራ መጣች፡፡ ከረሜላዋ ጎል ሆነች፡፡ የከረሜላዋ ጣዕም ጎል ከገባ በኋላ ጓደኞቹ ሲያዝሉት፣ ጀርባው ላይ ሲንጠለጠሉበት … ሰው ሁሉ ሲጮህለት ጣዕሟ ይሰማው ነበር፡፡ ግን ፀደቀ ውሻ አይደለም፡፡ ዘጠነኛ ክፍል ሲገባ … ከእግር ኳስ ጨዋታ የሚገኘው ጐል ጣዕሙ እጅ እጅ እያለው መጣ፡፡ ብዙ ጎል አገባ ግን ሰለቸው፡፡ ማበረታቻው ጭብጨባ ብቻ መሆኑ ጉጉቱን ገደለበት፡፡ የተሻለ ተጫዋች ከእሱ በልጦ ቢያገኝ እንኳን ለፉክክር ሲል እግር ኳሱን በቀጠለው ነበር፡፡
ፀ.ጥ ውሻ አይደለም፡፡ ሁሌ በአንድ አይነት ጉጉት ሊረካ አይችልም፡፡ እሱ እንደነገረኝ ከረሜላን፣ ኩርኩም፣ ጎልን፣ ለሀጭ ማዝረብረብን (ጉጉትን)፣ እና እንባ ማውረድን በአንድ ላይ የያዘ ነገር ያየው … አስረኛ ክፍል ሳለ ከአንዲት የሀብታም ልጅ ጋር ፎንቃ በጠለፈው ወቅት ነበር፡፡ ልጅቱ በጣም ቆንጆ ናት፤ ብሎኛል፡፡ ቀና ብሎ እሷን ለማየት አቅም አጣ፡፡ እግር ኳስ ሜዳ ላይ እሱን ከሌሎቹ ተጫዋቾች እንድትለየው ብዙ ግብ አገባ፡፡ ጭራሽ የናቀችው መሰለው፡፡ ትምህርት ብቻ ነው የምትወደው፡፡ ከደብተር አንገቷን ቀና አታደርግም፡፡ ቀና ስታደርግ ደግሞ አስተማሪውን ለማድመጥ ብቻ ነው፡፡ በአስተማሪው እና በሷ መሀል ጉጉቱን እንደ ኳስ አጣጥፎ ማስገባት ፈለገ፡፡ ኳሷን እንደ ልጅቱ፤ አስተማሪውን እንደ ተቀናቃኝ ቡድን አየ፡፡ በኳስ ብቃቱ ልጅቱን መንጠቅ ፈለገ፡፡
የኳስ ብቃቱን ወደ ጥናት ለወጠው፡፡ የልጅቷ ፍቅር ለትምህርቱ ማበረታቻ ሆነው፡፡ ፀደቀ ለእሷ ሲል አራት ነጥብ አግኝቶ ዩኒቨርሲቲ ገባ፡፡
ሲገባ ልጅቱ አብራው አልመጣችም፡፡ ሌላ አቅጣጫ ቀይራ ከትምህርት ውጭ ወደ ሆነ ህይወት አምርታለች፡፡ በሷ ምትክ ሌላ ሴት ወደደችው። የወደዳት ወደ ሌላ፣ ያላሰባት ወደሱ ጐል ገባች፡፡ ፍቅር ብሎ ቀመሰ፡፡ በፍቅር እውነትም ከረሜላን፣ ኩርኩምን፣ ጎልን፣ እንባን ይመስላል፡፡ ግን እሱም ሰለቸው፡፡ ፀደቀ ጥላሁን (ፀ.ጥ) ውሻ አይደለም፡፡ በወደደችው ሴት ላይ ሌላ ወደደ … በማበረታቻ ላይ ማበረታቻ ደራረበ፡፡ ግን በመጨረሻ ማበረታቻው ለምን እንዳስፈለገው ግራ ገባው … በተለይ ሀይስኩል ሆኖ የወደዳት ልጅ ኮንኮርድ የሚባል ሆቴል እየሰራች አግኝቷት ያለምንም ውድድር አብሯት ካደረ በኋላ … ለቀላል ዓላማ ከባድ መስዋዕትነት መክፈሉ ተሰማው። ትምህርቱን ያጠበቀው እሷ ጋ ለመድረስ ነበር … ትምህርቱን እንዲያጠብቅ አድርጋ ያጓጓችውን ከረሜላ… ቀበቶውን በማላላት ብቻ በእጁ አስገባት። … ከረሜላ፣ ጎል፣ ፍቅርም የተጋጠ አጥንት መስለው አስጠሉት፡፡
ዲግሪ ሲሰጣቸው እየታያቸው ለሀጫቸው ከሚዝረበረብ ተማሪዎች እኩል መሆን የፀደቀን ማንነት እንደማይገልፅ ያምን ነበር፡፡ አስተማሪ የደረደረውን መልቀም … የተለቀመውን መልሶ አስተማሪ “አምጣ” ሲል መትፋትም ባርነት መሰለው፡፡ ትምህርቱን ብቻ ለማጣጣም ስለሰለቸ ድርሰት ማንበብ ጀመረ፡፡ ሴሚስተሩን በሙሉ አንጋፋ ደራሲያንን ያለማቋረጥ ሲለበልብ ከረመ፡፡
የመፅሐፍ ስም ሲጠራ ለሀጩ ከቁጥጥር ውጭ የሚሆንበት የንባብ ሱሰኛ ለመሆን ጥቂት ሲቀረው አሁንም ሰለቸው፡፡ ሲሰለቸው ራሱን ማንቃት የሚችለው ሌላ ጉጉት በመፍጠር ብቻ ነው፡፡
“ግጥም መፃፍ” የሚል ጉጉት አደረበት፡፡ ግጥም ከከረሜላም፣ ከኩርኩምም፣ ከጎል ማግባትም፣ ሴትን ከማፍቀርም .. የበለጠች ሆና አገኛት፡፡ እምነቱን ባገኘበት ወቅት እምነቱ ወረት ስለመሆኑ ማንም ነግሮ ሊያሳምነው አይችልም፡፡ ፀደቀ ጥላሁን ውሻ እንዳልሆነ ያውቃላ!
ጥሩ ገጣሚ መሆን ግን ቀላል አልሆነለትም። ብዙ ለቀለቀ፣ በብዕሩ የሚዝረከረከው ለሀጭ በዛ።  … ጉጉቱ ተትረፈረፈ እንጂ የጓጓለትን ሊጨብጥ አልቻለም፡፡ እድሜ ልኩን የሰው ግጥም እና የሰው ድርሰት ሲያነብ መኖር እጣ ፈንታው እንደሆነም ተቀብሎ ጉጉቱን ማስረዝም አልፈለገም፡፡ በሰው ልጅ የሚወረወርለትን አጥንት መጋጥ እጄ ብሎ ተቀብሎ አያውቅም፡፡
የራሱን ስጋ መጋጥ መጀመር ነበረበት፡፡ የራሱን ስጋ ግጦ እውነተኛ ግጥም ማፍለቅ፡፡ እውነተኛ ግጥም ከተገኘ ለሌሎቹ እንዲግጡ አውጥቶ ይሰጣቸዋል፡፡ እንዴ የሱን ስጋ እና ደም ወይንም መንፈስ በግጥም መልክ አንብበው ከቀመሱ … እንደ ፓብሎቭ ውሻ የሱን ስም ሲሰሙ አእምሯቸው ውስጥ ይደውልባቸዋል፡፡ ለሀጭ በማዝረብረብ ዲሀይድሬት አድርገው ሊሞቱ ሁሉ ይችላሉ፤ ብሎ ሳይጓጓ አልቀረም፡፡
“ህይወትን መኖር አለብኝ” ብሎ የወሰነው ግጥም  ለመግጠም እንዲችል ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የሚደወልለትን የዲግሪ ምርቃት መጥሪያ ችላ ብሎ ሌላ የማይጠበቅ፣ የሚያስፈራ መጥሪያ ጆሮው አደመጠ፡፡
ወቅቱ ኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተቀሰቀሰበት ጊዜ ነው፡፡ ትምህርቱን ያለ መልቀቂያ በአንድ አጭር ውሳኔ ሶስተኛ ዓመት ላይ አቋርጦ ወደ ባድመ አመራ፡፡ ወደ ገጣሚነት ለማምራት መጀመሪያ ጦር ሜዳን መግጠም እንደሚያሻው፣ ጀብዱ መጀመሪያ መስራት እንዳለበት ወስኗል፡፡
ፀደቀ ከጦርነቱ ተመልሶ ሲመጣ በድሽቃ ጥይት ደረቱ ላይ ተመትቶ ነበር፡፡ መሞት ቢኖርበትም በሆነ ተአምር እንደተረፈ ነግሮኛል፡፡ “ከሄደበት ከተመለሰ በኋላ ብዙ ማውራት ተወ” ይላሉ በፊት የሚያውቁት። የፍልሚያ ማዕረግ ሁሉ አግኝቷል፤ በጦርሜዳ የሆነ ከፍተኛ ጀብዱ ሳይፈፅም አልቀረም። ግን ምን እንደፈፀመ አይናገርም፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ጉጉት የሌለው ወጣት ሆኖ ተመለሰ፡፡ ጉጉት ያሳጣው ነገር ምን እንደሆነ እኔም ሆነ እሱ አናውቅም። እኔ የማወቅ ጉጉት ቢኖረኝም እሱ ግን ስለራሱ ማንነት መጥፋት ምክንያት ለማወቅ እንኳን ምንም ተነሳሽነት አልነበረውም፡፡
በፓቭሎቭ ፅንሰ ሀሳብም ሆነ በራሱ የማይሰራ የሰው ዓይነት ሆነ፡፡ የራሱም ሆነ የሌሎች ውሾች ፍላጎት የማይቀሰቅሰው ሆኖ ደነዘዘ፡፡ ትምህርቱንም መልሶ አልቀጠለም፡፡ ኩርኩምም ሆነ ከረሜላ ጣዕም አይሰጡትም፡፡
ከጦርነት መልስ ግጥምን በቀላል መፃፍ እንደቻለ ቢያውቅ ግጥምም እንደሌላው ነገር ሁሉ ከመከራ ውስጥ የሚገኝ ከንቱ ነገር ሆነበት፡፡ መፃፍ ሳይጀምር በፊት አቋረጠው፡፡ በውስጡ ያቆጠቆጡትን ስንኞች በመጠጥ አጥቦ ወደ ውስጥ ዋጣቸው፡፡ ውጦ አስቀራቸው፤ ራሱ ሰከረባቸው፡፡ ሰክሮ አድሮ ወይም ከርሞ መልሶ አልነቃም፡፡ እንደተኛ ቀረ። ፀደቀ ጥላሁን ፀ.ጥ ማለት ጀመረ፡፡ ለእኔ ያዋየኝ ታሪክ ከአንደበቱ ሳይሆን ከአኳህዋኑ የወጣ ነው። ልብ ብዬ ስመለከተው ለካ እሱም ውሻ ነው፡፡ ተጠቅልሎ … ያለ ዕድሜው አርጅቶ በተኛበት … አጭር  ታሪኩን በገላው ላይ የከተበ ውሻ፡፡ እኔም እኮ ውሻ ነኝ… የምርጥ ውሻ ገድል ሳይ ይገባኛል፡፡ ገድሉን አሁን እንዳነበባችሁት ፃፍኩት፡፡ ፀ.ጥ ያለ ውሻ ታሪክ እንደ ፓቭሎቭ ደወል ድርሰት ለመጫር ያነሳሳኛል፡፡ ብዕሬ ለሀጩን እንዲዘራ ያነሳሳዋል፡፡ ብዕሬ ቀለሙን መዝራት ሲጀምር  … የሆነ አጥንት ያለው መረቅ እንደመጣ እረዳለሁ፡፡
“ፀደቀ ተክሌ ውሻ አይደለም” ያልኩት ተሳስቼ ነው፡፡ ተራው ነገደ ውሻ በሚረካበት ደወል የማይረካ ውሻ ነው ማለቴ ነው፡፡ ተራው ውሻ ለሆዱ ነው የሚኖረው፡፡ ከተራው ውሻ የተለየ ሁሉ ለገንዘብ፣ ለክብር፣ ለጎል፣ ለጭብጨባ፣ ለሴት… ሳይሆን ለሌላ…ለሆነ እፁብ ድንቅ መሳይ ህልውና ይኖራል። ከውጭ ሳይሆን በውሻ ነፍሱ ውስጥ ለሚሰማት የራሱ የነፃነት ደወል፡፡
ደወሉን ተከትሎ ጉጉቱን አስቀድሞ ይወጣል። … እኔ ራሴ አዲስ ነገር የፃፍኩ ሲመስለኝ… ብዕሬ ከእኔ ቀድሞ ወደ ህልሜ ለመድረስ እንደሚሮጠው … በስተመጨረሻ ግን ብዕርም በሰገባው፣ ህልምም በእንቅልፍ እረፍቱን ያገኛል።  የፀደቀ ተክሌ ሳይሆን ለሌላ ለሆነ የሁላችንም የተሻልን ነን የምንል አመፀኛ ውሾች ታሪክ ነው፡፡
እንደ ፓቭሎቭ ፅንሰ ሀሳብ፡- አዎ ሰዎች ነን፤ የህይወት ደወልን .. በጉጉት የምንከተል እና ተከትለን ከሄድንበት ርቀት አንፃር የማይመጥን ትንሽ መቃብር ውስጥ የምንሞት… የሰውነት ህልማችንን የማንክድ ውሾች ነን፡፡   


Published in ጥበብ

“የደመና መንገድ” ሒስ-ቀመስ ንባብ

   ዛሬ ወጣት ደራስያን ተጠራርተው አንዱ የሌላዉን ሲያነብ፥ እንዲሁም በማኅበራዊ ድረገፅ ሲተነፍሱ ሁሉም ማለት ይቻላል ግጥም ይቀላቸዋል። ለመጽሐፋቸው ሽፋን ተጠበው የግጥም ስብስብ ያሳትሙና በምረቃው ዕለት ተውበው ይፈካሉ። ልክ በአሉ ግርማ በ“ከአድማስ ባሻገር” ሽቅርቅሩን አበራ ወርቁን ሲገልጠው የውጭ ገፅታው እየማረከ ብብቱና የእግር ጥፍሮቹ መቸክ እንደደነቀው፤ ከታተሙት አያሌ የግጥም ስብስቦች ጥቂት ብቻ ናቸው ትኩረት ተሻምተው በጥሞና ከአዕምሯችን ለመወራጨት የበቁት። ሆኖም ብዙ ወጣቶች ገጠመኛቸውን በልቦለድ ለመግራት አይደፍሩም። ለምን? ብቁ አንባቢ ስለአልሆኑ ይሆን? ምናባቸው ተኮማትሮ የሚያደሩት ትረካ አቅም ነጥፎበት ይሆን? ማኅበረሰቡን ለማጥናት ችላ  ብለው ይሆን?  በአማርኛ ስንኝ አባብሎ ቤት ለመምታት ዜማው ስለማይፈትን፥ በተራ ግጥም ገፅ ማጨናነቅ ማንም ሊለማመድበት ይችላል፤ ይህን መለማመጃ ሰብስቦ -ገጣሚ ለመባል ብቻ- መሽቀዳደም ይጐዳል። መሽቀዳደም ካልቀረ ያኔ በአፍላ እድሜው ባለቅኔ ሰሎሞን ደሬሳ ለ“ልጅነት” ስብስቡ -እሽቅድምድም- በማለት የጣፈውን መግቢያ ቢመጥን ዘመን በተሻገረ። ደግነቱ አልፎ አልፎ የሚያስደምም ግጥሞች የተፍታቱበት መጽሐፍ ለማንበብ እንታደላለን። ምናልባት ልዩ የፈጠራ ውጤት አሳትመው እምብዛም ሳይዳረስ ቀርቶ ተጋርደው እውቅና የተነፈጉም ይኖራሉ። ለአጭር ልቦለድ ገፅ መድቦ ሳያስተጓጉል በየሳምንቱ የሚያስነብበን ብቸኛው የህትመት ዉጤት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በመሆኑ ይመሰገናል፤ ወጣቱ ክህሎቱን የሚያስተዋውቅበት መድረክ ተነፍጓልና በሙሉ አፍ አይጽፍም-አያነብም ብሎ መደምደም ያስተዛዝባል። ከወጣቱ መካከል የግሉን ፈር እየቀደደ፥ ጥሞናውና አስተውሎቱ - በትረካም በግጥምም- ነዝረው በስለው ብዙ ተከታይ የመለመለው አሌክስ አብረሃም ነው። “ዶ/ር አሸብር” እና “አገር፥ እናት፥ ፍቅር” መጻሕፍቱን ስናነብ የምናብና የአስተውሎቱን ጥልቀት መካድ አንችልም።
ይታገሱ ጌትነት በሁለት የግጥም ስብስቦቹ ይታወቃል፤ “ጥቁር ነጥብ” እና “ደጅ የዋለ ልብ”። ሰሞኑን ይህን ዘውግ ተራምዶ አስራ ሁለት አጭር ልቦለዶች ነቅሶ“የደመና መንገድ” በሚል ርዕስ ጥሞናችንን ለማስገር ሞክሯል። በእርግጥ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በግጥም እየመሰጠን፥ ድንበር ሳይገድበው ወደ አጭር ልቦለድ ሲሸጋገርተጠቅልሎ የተዘረጋለት ጥበባዊ ውበት ኅብረ ቀለሙ አልደበዘዘም፤ ሽግግሩ የሰመረ ነበር። በአንፃሩ የይታገሱ ጌትነት ጥረት እንደ ማለፊያ ሙከራ ይቆጠራል እንጂ ገና ይቀረዋል። በስንኝ ሳይቀነበብ በዐረፍተ ነገር የህይወትን ውጣ ውረድ፥ የኑሮን ፈገግታና ኩርፊያ ለማጠላለፍ መድፈሩ የድረገፁን ወጣት ልቦለድን ለመከየን ያነቃቀዋል በማለት እንጂ በደምሳሳው ሲነበብ ከፊል ልቦለዶቹ ናቸው ኮስታራ ሒስ የሚያባብሉት። የሽፋኑ ጭምት ቀለም የመንፈስ ስክነት ቢረብበትም ለትረካ ብቻ ሳይሆን ለቅኔ እምቅነት ምስልም ነው። የሁለት ላባዎች ጥምረት - መድጋገፍን ይሆናል - ነፋስ እየገረፈ ደመና ውስጥ ሲያንሳፍፋቸው፥ የአይን ብሌን የመሰል ዘለላ እንባ ወይም ጤዛ ያሳስባል።
የድንቅ አጭር ልቦለዱ የ“አባ እብዱ” ገጠመኝ እግዜርን አስቆጭቶት ከሰማየ ሰማያት ሾልኮ ከላባው ላይ መግቻውን ያገኘ የእንባ ዘለላ ይመስላል፤ በበለጠ ግን ጤዛን ይወክላል። እንደ Dogen Zenji ጥልቅ አባባል፤ “The whole moon and the entire sky are refelected in one dewdrop on the grass.” ነው። ድፍን ሰማይና ሙሉ ጨረቃ ሳር ላይ በሰከነ ጠብታ ጤዛ ይንፀባረቃሉ፤ ትንሽ ጥበት የተንጣለለ ስፋትን ማቀፉ - ነፀብራቅ ቢሆንም - ይመስጣል። የይታገሱ ትረካዎች ያንሰራሩት የህይወትን አታካች ስፋት ለማጠንፈፍም ይሆናል - አንድምታው። የጀርባ ሽፋን ግን በአገኘሁ አዳነ የደራሲው ፎቶ-ንድፍ የሆነ ጥበብ ቢነሰነስበትም፥ ከሶስት ትረካዎች ቅንጭብጫቢ ተለብዶበት የማንበብ ጉጉት አይቀሰቅስም፤ ስለ ልቦለዶቹ አጠቃላይ መንፈስና አቅም የሚመጥን ማራኪ አስተያየት ይበጀው ነበር።
ያጐጠጐጠች ወጣት ወሲብን ለመተዋወቅ፥ የገላዋን ግለት እየተሻሸች ገና ካልጐረመሰ ልጅ ጋር መዋዛት ስትጀምር፥ አካላዊና ሥነልቦናዊ አንድምታዎች ይወሩናል። የመቃብር ሀውልት ለመመረቅ የመጡ ሃዘንተኞች ፈንጠር ብለው ቆመዋል። የሟች ባለቤት ተንበርክካ በለሆሳስ ትናገራለች፤ “ፍቅሬ... አንተ የቤቴ ሻማ ነበርክ።” ለቤታችን “አጥፊዋ፥ አፍራሿ ነበርክ” በማለት የዕድሜዋን ግማሽ ተከትላው በስስቱ ጦስ መባከኗ ይቆጫታል። ካህኑ ማሳረግያቸውን ሲሰጡ የሟች ውብ እህት ከመቃብር ተደፍታ ትወዛወዛለች። “የጉድለታችን ሙላት፥ ገመና ከታቻችን አንተ ነበርክ” በማለት ቸርነቱን ታሞካሻለች። አንድ ግለሰብ ለእናቱና እህቱ ሳይሰስት እያንቀባረረ፥ ሚስትና ልጁን በእጦት ለማሰቃየት መብቃቱ በተፃራሪ ተግባር እየተናደእንደ ሰው መኖርና መሞቱ ያጠያይቃል። የንሰሃ አባት ቀኖና ለመስጠት ባደመጡት ምስጢርና ገመና ተሰቅቀው እስከ መቀወስ የሚያበቃቸው ትረካ ስለ ምን ማኅበራዊ ጉዳይ ይሆን? እግዜርን እስከ ማሸማቀቅ ምን ሀይል ገፈተራቸው? በቡና ቤት ሴት አስተናጋጅ ውበት ልቡ የቀለጠው ተራኪ መረቡን ዘርግቶ ሲያጠምዳት፣ እሷን ብቻ ሳይሆን ግሳንግሷንም ሲያፍስ የሚከሰት ጉድ አለ። አንድ ባለስልጣን በትግል ወቅት ወንድነቱ ስለፈዘዘ፥ ይህን ሀቅ ባለቤቱ እየኖረች ስታመናጭቀውና ስትንጫጫበት ብቻ ሳያበቃ፥ ለሀገር ጉዳይ ተጠሪ ናቸውና የመኝታ ክፍል ብሶት በስብሰባ አዳራሽ ተገምሶ ሲዘረገፍ መዘዙ ያስሸብራል። አባወራ ህይወቱ ሲያልፍ ህጋዊ ባለቤቱ ነኝ ብላ ልጅ ጐትታ የመጣች ሴትና የአምስት አመት ጐረቤቱ ነበርኩ ባዩ፥ ልጅና ትዳር አልነበረውም በማለት ከአንድ ዶክተር ጠባብ ክፍል ይከራከራሉ። በዚህ በማያውቁት ጐቦኛ ሃኪም፣ በደላሎች የተፈረመ፣ አንዱ የሌላዉን ጥያቄ የሚገስ ማስረጃ አላቸው። የህሊና እና የህይወት አቅጣጫ ጉዳይ ይሸረብበታል። አንድ እህል ከአፉ ከዞረ ሶስት ቀናት የሞላው ግለሰብ፥ ድሮም ኩሩነት የመሰለ ግትርነት በስራና ኑሮ ቢያደናቅፈውም፣ የዛሬን ፈተና እንዴት ይወጣል? ሥነልቦናዊ ቀውስ ነው ወይስ ጅልነት?
ውብ የምታማልል የዩኒቨርስቲ ተማሪ፣ ጭኗ አካባቢ እስከ ብልቷ የተዘረጋው ጠባሳ ለፍቅር፥ ለወንድ ጉዳይ ከራሷ እያሟገታት ስትማቅቅ ገመናዋና የተባዕት ጓደኛዋ ጥያቄ እንዴት መልስ ያገኛሉ? ሴት ለቁንጅናዋ ብትስገበገብም ከህፃንነት ጀምሮ ለከፈለችው መስዋዕት ማን ነው ተጠያቂ? ሁለት ጐሳዎች በድሎት ተንቀባረው እየተደጋገፉ፣ ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን እያጣጣሙ ሲኖሩ ፀጉረ ልውጦች ጀልባ ቀዝፈው ከቀያቸው ይደርሳሉ። ከስልጣኔ ሲያስተዋውቋቸው እድገትና ፀብ፥ ስቃይና ጦርነት እንዴት የሰው እጣ ፈንታ ለመሆን በቁ? በጥንት ዘመን ነፋስ እያለኸለኸ ስለፍቅር ከተፈጥሮ  ንጉሥ ከአዳም ምክር ይጠይቃል፤ ሲነጋገሩ ያደመጠች በቀቀን አዳም ፍቅር አለማወቁን ለገነት ፍጥረታት ናኘችው። ያ ማኅበረሰብ ሲታመስ አዳም ምን ይገጥመው ይሆን? ወይዘሮ የሹምነሽ ሴተኛ አዳሪ ሆነው ኑሮን ሲቋቋሙ፥ የዶሮ ዐይን በመሰለ ጠላ ሙያቸው ሲወደደ፥ ተመልካችን በምታፈዝ ቆንጆ ልጅ ተማምነው እና የልጅ ልጅ ሲያሳድጉ ህይወት ምን ቋጥሮላቸው ይሆን? በተጋፈጡት ፈተና ምክንያት እርጅና እና እጦት ያጋልጣቸው ይሆን? ሄሚንግወይ የቀረፀው የሰማንያ አመቱ አዛውንት ለተከታታይ አርባ ቀናት አሳ ማጥመድ ባይቀናቸውም ጅልባቸውን ቀዝፈው እንደገና ብቻቸውን ባህሩን ይደፍሩታል። የወይዘሮ የሹምነሽ ታሪክ ስናነብ በ”ሽማግሌውና ባህሩ” የገዘፈው ሳንትያጐ ትዝ ይለናል፤ ሁለቱም ኑሮ ቢገጫጫቸውም አልተሸነፉም። እጅጉን ውብ የሆነች በአፍላ ዕድሜዋ የጥቂት ወንዶች የፍቅር ግፊት ችላ ብላ ታቅባ ብትኖርም እየበሰለች ስታድግ ከአንድ ወጣት ጋር ጥልቅ ፍቅር ይወራታል።  እየተፈላለጉ ስሜታቸው እንዳይፈልቅ ፍቅራቸው በዝምታ ይታፈናል። ከሀገር ማዶ የተሰደደው ፍቅረኛዋ ከአመታት በኋላ ሲመለስና ሲቀጣጠሩ፥ ትናንት-ዛሬ ተማስሎ የወጣትነት ዕድሜ እየሟሸሸ ከራስ ጋር ሲያላትም ምን ይከሰት ይሆን?
የይታገሱ ጌትነት “የደመና መንገድ”  ሲነበብ እንዲህ ከተወሳሰበ የኑሮ ፍጥጫ ጣዕምና መራራነት አንዴ ተመስጠን አንዴ እያዛጋን እንቋደስለታለን። እንደ ታሪክ እንደ የልቦለድ ሤራ -plot- አስራ ሁለት የህይወት ቅርድዶች የወንድ፥ የሴት፥ የፍቅርና የሀገር ጉዳይ እየሆኑ የጭብጥ ድግግሞሽ ሳይኖር ተተርከዋል። ደራሲው ከገፀባህሪ ውስጣዊ አሳሳል እና ከሁነቶች ገለጣ በበለጠ ያተኮረው ለሤራ አወቃቀር መሆኑን ማጤን አያዳግትም። ልብ አንጠልጥሎ እንዴት ያበቃ ይሆን አሰኝቶ በመተረኩ ለብዙ አንባቢያን ይጥማቸዉ ይሆናል። በአማርኛ ሥነጽሁፍ አዳም ረታ፥ እንዳለጌታ ከበደ፥ ዓለማየሁ ገላጋይና በዕውቀቱ ሥዩም በአጭር ልቦለድ አፃፃፍ በመርቀቃቸው ይህን ዘውግ ከሰቀሉበት ከፍታ ለመታከክ አዳጋች ነው። የይታገሱ የአፃፃፍ አካሄድ ነባር የአተራረክ ስልት - የነታደሰ ሊበን ትረካዎች - ያስታውሰናል። ደራሲ አማረ ማሞ በማስተማሪያ መጽሐፋቸው አንድ አጭር ልቦለድ መግቢያ፥ መካከል እና መቋጫ ሊኖረው ይገባል ያሉት ለይታገሱ እንደ መመሪያ ሆነው። ከአንድ ሁለቱ በስተቀር የተቀሩት ከዚህ አፃፃፍ ዑደት ውስጥ ተቀንብበዋል። በአመዛኙ ድርጊት ላይ ስለአተኮረ፣ እንደ እንዳለጌታ ከበደ ትረካዎች በጥቃቅን ሁነቶች መሳጭ ቅኔያዊ ገለፃ አልወረዙም። በአጨራረስ አስገራሚነት እንደ “ጤዛ”፥ ከአጋጣሚ አጠራጣሪነት እንደ “የደመና መንገድ”፥ አንድን አብይ ልቦለድ በአስተዋፅኦ -synopsis- አሳጥሮ መተረክ እንደ “አምላክን ማጠፋት” ፥ ብሎም ብዙ ተወግቶለት ለተሰለቸ -cliché- በለጋ አንድምታ ለማፍካት የተሞከረበት እንደ ”አዳም ፍቅረ ቢሱ“ ለሤራቸው ይነበባሉ እንጂ ከውስጣችን ስርገው ለመብላላት አቅም ይጥራቸዋል።
ለኔ የማጣጣም ግንዛቤ ያመቹኝ አምስት ናቸው። “አጨዳ”፥ “አባ እብዱ”፥ “ሬሳው”፥ “በመቃብሩ ግርጌ የፈሰሱ እንባዎች” እና “የልብ ኩራት” የሚሉት። ከስብስቡ አስራ ሁለት ርዕሶች እንደ ርዕስ ምስጢር ሸሽጐ ለትርጓሜ ጨረሮች የቋጠረው “የደመና መንገድ” ሲሆን በይበልጥ ግን “የገለባ ምሽግ” ቅኔያዊ ነዉ። የስብስቡ ርዕስ “የደመና መንገድ” የሁሉንም ጭብጥ ለመወከል ቢዳዳውም -ምስሉ ያልተገታ ጉዞ ነዉና- ደመና የጋተው ዝናብ፣ አካባቢን ለማራስና ለማፅዳት ያንዣብባል። ደመና ተተርትሮ ለበጐ የመፍሰሱ ያክል ለአደጋ -የኖህን ውሃ ባይመጥንም- የማጥፋት ሃይል አለው። ይህ ለስብስቡ የተመረጠው ርዕስ በአንዲት ውብ ሴት፥ ሰላሳ አምስተኛ የልደቷን ቀን ባንኳኳው የብቸኝነት ስጋት ዋልታ ዙሪያ ይጠነጠናል።
”ለሁሉም እደርስበታለሁ ብላ የጨቆነችው ወጣትነቷ፥ ያፈነችው ስሜቷ፥ ተከርችሞ የከተተችው ሙቀቷ እያደር ሲቀዘቅዝ ነው ወጣትነትን እየራቀችው መሆኑን የተረዳችው። ቆንጆ ናት! ልቅም ያለች ቆንጆ፥ አይደለም ወንድን ሴትን ምራቅ ታስውጣለች።
ከዕድሜዋ ዐሥር አስራ አምስት ዓመት ቀንሳ ብትናገር የሚጠረጥራት የለም። ሆኖም ውስጧ ከስሜት ወጥቶ በምክንያት ሲመራ እያየችው ራሷን እንደ ወጣት ለማሰብ ትቸገራለች። አብረዋት የተማሩ ጓደኞቿን ከእኩያ ልጆቻቸው ጋራ ስታገኛቸዉ ጥርሷ የሳቀ ቢመስልም ራሷን ግን እየነከሰ ነው የሚያደባያት። [ገፅ 104]
ሁለተኛ ድግሪ የጨበጠች ራሷን በደሞዝ የምታስተዳድር፥ ገና ዩኒቨርስቲ ስትገባ ከመንዘላዘል እንድትታቀብ ለአባቷ ምክር የተገዛች፥ ውበቷ ያልቀዘዘ እንስት ናት። በአንድ ወቅት ፍቅር ይዟት ነበር። “ግን ትንፍሽም ሳትል ኮሽም ሳይል ግቢውን ለቀው እስከወጡበት ጊዜ አብረው ቆይተዋል፤ በስመ የክፍል ልጅ።” እሱ እንደተመረቀ ከአገር ለመውጣት ሲንደረደር “የጆበነችው ስሜቷ... አይጥ እንደዋለበት ዱባ ብርቅስቅሱ ወጣ። ሀዘኗን መቋቋም አልቻለችም።”ለሴቶች አርአያ ለመሆን የሚዘመርላት ጠንካራ ሴት እንደ ተራ እንስት፥ እንዳልተማረች ሄዋን፥ ውበትና ዕውቀት ተከማችተውባት ሳለ ፍቅር ተነፍጋ በብቸኝነት መቦርበሯ ያደናግራል። እሷ ይህን በኑሮ ጥድፊያ የተደቀነባትን ቀላል የኅላዌ ዕንቆቅልሽ በጥሞና ልትፈታው አቅም ሳያንሳት እንዲህ መዋዠቋና መርበትበቷ፥ መረቧን ዘርግታ ተባዕት ማጥመድና መግራት ተሳናት ማለት አይመጥናትም። የወሲብ ስሜቷ የቀዘቀዘ፣ ከወንድ ለመዳራት እንደሚያዳግታት ቢጠቆም አካላዊና ሥነልቦናዊ ምክንያት በሆናት ነበር። ጤነኛ እና ንቁ ሆና መንከራተቷ ደራሲው ያለበሳት ባህርይ እንጂ ማንነቷ የሚፈቅደው ቁዘማ አይደለም። ልቦለዱ ተጨማሪ ታሪክ በመቋጠሩ ሳይሰለች ይነበባል፤ አጨራረሱም ከዳር ያልተበተነ ስለሆነ በምናባችን ስለ ልጅቷ መለወጥ የምናክለው እሳቦት ይቀሰቀሳል።
የመቼት ስፋትና የጭብጥ ግዙፍነት በአጭር ልቦለድ ለመገራት ያዳግታሉ። ለዚህም ነው “አምላክን ማጥፋት” እና “ድፍን ወርቅ” እንደ መጐተት ያዘገሙት። ደራሲ Reymon Carver ፈጠራ ድርሰትን አጢኖ ያስተዋለዉ ነጥብ ጠቃሚ ነዉ። “ስለ ተራ ቁሳቁስ እና ሁነቶች በቀላል ግን እቅጩን በሚገልጥ ቋንቋ መተረክ ይቻላል። ወንበር፥ መስኮት፥ ማንኪያ፥የጆሮ ጌጥ ... የመሳሰሉ ቅራቅንቦ ለመሳጭ አጭር ልቦለድ ሆነ ግጥም መፍለቅያም ናቸው” ብሏል።
በአማርኛ ሥነፅሑፍ አዳም ረታ “ኮሳንኩስ” በሚል አውራ ርዕስ ስር ስለ ሊጥ፥ ሻሽ፥ ኩል፥ ልፎ፥ ወተት... በመቶ አርባ ስምንት ገፅ እጅጉን መሳጭ ስምንት ትረካዎች አስነብቦናል።ዓለማየሁ ገላጋይ በ“ኩርቢት”-ጋያ፥ የትንባሆ መጠጫ-ቁሳቁስ ተነካክቶ ድንቅ መፅሐፍ አስነብቦናል። የደራሲው ክህሎት የሚወስነው የጥበብደረጃ እንጂ የጭብጥ መደንደን እና መክሳት አያሳስብም። ይታገሱ በቋንቋ ችሎታው በተለይም በነፍስ ወከፍ ቃላት ምርጫው አይታማም፤ ሲፈልግ በዘይቤም ትረካዉን ያስዉባል። “ወዝ ያጣው ገጿ እንዳረጀ የግራር ዛፍ ቅርፊት ድርቅ በላል።” ፥“ወንዱ ሁሉ ምን የቅንዝር እሳት እንደለቀቀበት ወይም ደግሞ የትኛው ደብተራ አዝኖላት እጸ-መስኅብ እንደቀባት ሳታውቅ ደንበኞቿ ዕረፍት ነስተዋት ነበር።”፥ “በአዲስ አበባ ቆንጆ እንደ ሰርዶ የትም ይበቅላል ባክህ” ፥“ኑሮን ራሱን ሰብስበው የተሸከሙ ይመስል ወገባቸው ጐበጠ።”... ደራሲው በዘይቤ መርቀቅ ብቻ ሳይሆን ሰባት አጭር ልቦለዶቹን በግጥም ነው የጀመራቸዉ -epigraph- ገጣሚ ስለሆነ አባዜው እየጐተጐተው ወይም ለትረካው ምጥቀት አልያም ማደናገሪያ ናቸው ለማለት በሌላ ወረቀት ጥናት ይሻል። የዚህ ሒስ-ቀመስ ንባቤ ርዕስ ከይታገሱ “እርጥብ ማኅጸን” ትረካ የተዋስኳቸው ስንኞች ናቸው፤ ይነዝራሉ።
“የደመና መንገድ” በአጻጻፍ ጥበብ የተጠበቀው ያክል አለመሆኑ ያወያያል እንጂ ከጭብጥ አንፃር የታመሱበት ርዕሰ ጉዳዮች ጥያቄ ይቀፈቅፋሉ። እግዜር የምድርን ሰቆቃ ችላ ማለቱ፥ የግለሰብ የዋህነትና ክፋት፥ ህይወት ስትጨረማመት፥ ለፍቅርና ለወሲብ መብሰክሰክም መቆዘምም ስነልቦናዊና አካላዊ ትርምሱን ተንገዳግዶ መኖር የመሰሉ ሁነቶች ተተርከዋል። ዝነኛው ደራሲ O. Henry ጥቂት ፀሀፍት የሚቀበሉት ምክር አለዉ። “I will give you the whole secret to start story writing. Here it is . Rule number one, write stories that please yourself. There is no rule number 2” ልቦለድ ለመከየን የሚያበቃህ ድፍን ምስጢሩን ልንገርህ። ድንጋጌ ቁጥር አንድ፥ አንተን የሚያስደስቱ ትረካዎች መፃፍ አለብህ። ቁጠር ሁለቱ ድንጋጌ ብሎ መርሆ የለም ባይ ነዉ። ወሳኝ ነጥብ ቢሆንም የማይወዱትን ልቦለድ የሚቀሽሩ አሉ። ይታገሱ ጌትነት ብዕሩን ከስነግጥም ነቅሎ አጭር ልቦለድ ልብ ላይ በመሰካቱ፣ ወጣት ደራሲያን ይህን ዘውግ ተመስጠው እንዲፅፉበት ያደፋፍራል። ይታገሱም ለጣቂ ስብስቡ ጥልቅና ውብ እንዲሚሆንለት ጥቆማዎች አሉ፤ በፈጠራ ድርሰት መጠመድና የኑሮን ማዕበል መቅዘፍ ያመሳስላቸዋል።  

Published in ጥበብ

     የጽሑፌ ዓላማ ዮሐንስ ሰ. “የአማርኛ ግጥሞች ትንታኔ በተለያዩ ምሁራን” በሚል ርዕስ በዚሁ ጋዜጣ ላይ ቅዳሜ ጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም (የዛሬ ሳምንት መሆኑ ነው) በጥበብ አምድ ስር ባቀረቡት ጽሑፍ ላነሷቸውና “ስህተት ናቸው” ለምላቸው አንዳንድ ሀሳቦች ምላሽ መስጠት ነው፡፡
ዮሐንስ ሰ. በዚሁ ጋዜጣ ላይ ያቀረቧቸውን በርካታ ጽሑፎቻቸውን አንብቤአለሁ፡፡ በተለይም በሀገራችን ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ነባራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያቀርቧቸውን በአመክንዮ የተሞሉ ጽሑፎቻቸውን አደንቃለሁ፡፡ እያሰለሱ በጽሑፎቻቸው የሚያነሱዋቸውን ሸንቋጭና አወያይ ሀሳቦችም ጭምር፡፡
ዮሐንስ የዛሬ ሳምንት “የአማርኛ ግጥሞች ትንታኔ በተለያዩ ምሁራን” በሚል ርዕስ ያስነበቡን ጽሑፍ ግን በብዙ መልኩ “ዝርው፣ አቅጣጫውን የሳተና በመደናገር የተመላ ነው፡፡” ያም ሆኖ ግን ጸሐፊው ቢያንስ በሁለት ምክንያቶች ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አንደኛው ምክንያት፤ በዩኒቨርስቲ በቋንቋና ስነጽሑፍ ትምህርት ክፍል ብቻ ተወስኖ የቆየውን ስነግጥምን እጅጉን ቴክኒካል እስከሆኑት ጓዞቹ ወደ ጋዜጣ አምድ በማምጣታቸው ሲሆን ሁለተኛው ጉዳይም፣ በዘመን የተራራቁትን የአምስት ምሁራን ሰፊ ጥናቶች በማንበብ ተገነዘብኩት ያሉትን ነጥቦች በተቆርቋሪነት ለአንባቢያን በማቅረባቸው ነው፡፡ የዮሐንስን ጽሑፍ ድክመቶች የሚያሳዩትን ነጥቦች ከማንሳቴ በፊት በአማርኛ ስነግጥም ዙሪያ ስለተደረጉ ጥናቶች አጠቃላይ ምስልን ሊሰጡ የሚችሉ ነጥቦችን በጥቂቱ ላንሳ፡፡
የአማርኛን ስነግጥም በአይነት በመክፈል ለመመደብ ሙከራ የተደረገባቸው ቀዳሚ ጥናቶች ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጥናት ያማርኛ ሰዋሰው (1948) በሚል ርዕስ በመርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ የተደረገው ነው፡፡ ሁለተኛው ጥናት ደግሞ ያማርኛ ግጥምና ቅኔ ማስተማሪያ (1954) በሚል አለማየሁ ሞገስ ያደረጉት ሲሆን ሶስተኛውም “የአማርኛ ግጥም ዓይነቱ፣ ሥረቱ፣ ሥርዓቱ” (1963) በሚል ርዕስ መንግስቱ ለማ ያደረጉት ነው፡፡
ከመንግስቱ ጥናት በኋላ የተለያዩ የስነጽሑፍ አጥኚዎች በተለያየ ወቅት ግጥምን በአጠቃላይ፣ ወይንም አንድን የግጥም አካል በመውሰድ (ለምሳሌ ደረጄ ገብሬ “ምት በስነግጥም ውስጥ” (1976)፣ እንዲሁም ዘሪሁን አስፋው በየስነ ፅሑፍ መሰረታውያን (1992)) የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉ ቢሆንም በተለየ ግጥምን በአይነት ለመክፈል የተካሄደ ጥናት ለረጅም ጊዜ ሳይካሄድ ቆይቶአል፡፡ ሆኖም ከበርካታ ዓመታት በኋላ “የአማርኛ ግጥም አይነቶች” በሚል ርዕስ ተሾመ ይመር አበባው በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጥናት መጽሔት ላይ አንድ ጥናት አሳተሙ፡፡ የተሾመ ጥናት ዓላማው የአማርኛን ስነግጥም በአይነት መክፈል ሲሆን ይህ ጥናት ርዕሰ ጉዳዩን ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ አካዳሚያዊ ውይይት ያመጣ ነው፡፡
የተሾመ ጥናት ከታተመ ከ3 ዓመታት በኋላ ብርሃኑ ገበየሁ “ምጣኔ በአማርኛ ስነግጥም” ተሾመ ይመር አበባው፣ 1997 ‘የአማርኛ ግጥም አይቶች’” በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ይህ የብርሃኑ ጥናት የተሾመ ጥናት ላይ የተመሰረተና ተሾመ ያነሷቸውን ሀሳቦች በመቃወም የቀረበ ገምጋሚ ጥናት ነው፡፡ ከብርሃኑ በኋላም እንዲሁ “የአማርኛ ግጥም ባህርዩ፣ መደቡና ውበቱ” (2003?) በሚል ርዕስ አምሀ አስፋው ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡ የአምሀ ጥናትም የአማርኛን ግጥሞች ባህርይ በኮምፒዩተር ቀመር ለማጥናት የሞከረ ነው፡፡
እነዚህ አምስት አጥኚዎች በጥናቶቻቸው የአማርኛን ግጥሞች “በአይነት” ለመክፈል የሞከሩ ቢሆኑም ምሁራኑ በተገበሯቸው መስፈርቶችም ሆነ ባደረጓቸው ትንታኔዎች ልዩነት የሚታዩባቸው ናቸው። በመሆኑም ምሁራኑ ጥናቶቻቸውን ሲያደርጉ ከእነሱ ቀድሞ የተሰሩ ጥናቶችን በመመርመር፣ ጥንካሬና ድክመቶቻቸውን በማሳየት በመሆኑ ከየቆሙበት አንጻርና ከተነሱበት ዓላማ አንጻር በራሳቸው የሚሉት እጅግ ሰፊ ጉዳይ አሏቸው፡፡
ይህንን ካልኩ ዘንድ በእነዚህ ጥናቶች ላይ የተነሱ ሀሳቦችን መሰረት አድርጎ የራሱ (በእኔ ግምት የተሳሳተ) ማጠቃለያ ላይ ወደደረሰው ዮሐንስ ሰ. ጽሑፍ በማለፍ የጽሑፉ ድክመት የምላቸውን ጉዳዮች ላንሳ፡፡
ዮሐንስ በጽሑፋቸው የሳቱት ቀዳሚው ነጥብ፣ በአንድ የእውቀት ዲስፒሊን ውስጥ (በተለይ በማኅበረሰብ ሳይንስ /social science/ ያሉ ምሁራን በሚያጠኑትና በሚያስተምሩት እውቀት ዙሪያ አመክንዮአዊ /logical or reasonable/ በሆነ መልኩ መለያየታቸው ተፈጥሮአዊና የሚጠበቅ መሆኑን መዘንጋታቸው ነው፡፡ ይህ ነጥብ ዮሐንስን አቅጣጫ ያሳታቸውና ለደረሱበት የተሳሳተ ማጠቃለያ የዳረጋቸው አቢይ ምክንያት ይመስለኛል፡፡
እንደምናውቀው በየትኛውም ዲስፒሊን ውስጥ ያለ እውቀት በነበረበትና ባለበት ቆሞ የማይቀር፣ ይልቁንም የሚቀየርና በየጊዜው እየተጨመረበት የሚያድግ ነው፡፡ በመሆኑም እንኳንስ በተለያዩ ዘመናት የተነሱ ተመራማሪዎች ቀርቶ በአንድ ዘመንም ሆነ ስፍራ ያሉ ተመራማሪዎችም በሚያነሱዋቸው ልዩ ልዩ የእውቀት እሳቤዎች፣ የጽንሰሀሳብ ፍቺዎችና ትወራዎች (Theories)… ላይ ልዩነት ማሳየታቸው በጥናትና ምርምር ውስጥ ተፈጥሮአዊ፣ የሚጠበቅና ጠቃሚ ጉዳይ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ የእኛ ሀገር ከፍተኛ የትምህርት ስርዓት እዚህ ደረጃ ላይ አልደረሰም እንጂ የትምህርት ስርዓታቸው እጅጉን በመጠቀው በሰለጠኑት ሀገሮች በማኅበረሰብ ሳይንስ ስር ለሚጠኑ የተለያዩ ዲስፒሊኖች የተለያዩ “School of thoughts” ጭምር አሉ፡፡
ለምሳሌ ስነጽሑፍን የሚያስተምሩ በአንድ ሀገር የሚገኙ ሁለት ዩኒቨርስቲዎች ሁለት የተለያዩ ስነጽሑፋዊ ፍልስፍናዎችን መሰረት ያደረጉ የስነጽሑፍ ትምህርቶችን እስከመስጠት ይደርሳሉ። ልብ እንበል ዩኒቨርስቲዎቹ በአንድ ሀገር ያሉ ሲሆኑ የሚያስተምሩትም አንድ አይነት ዲስፒሊንን ነው። ግን እውቀቱን ማንጸሪያቸው/መመልከቻቸው ሊለያይ ይችላል፡፡ እንግዲህ ይህ ጉዳይ እጅጉን ጠቃሚና ብዙ የጥናትና ምርምር ሂደቶችን አልፎ የሚደረስበት ነው፡፡ ሲመስለኝ የሂደቶቹም መጀመሪያ የአጥኚዎቹ የሀሳብና ፍልስፍና ልዩነት ነው፡፡ በመሆኑም ዮሐንስ ሰ. ጥናቶቻቸውን ከሞላ ጎደል የዳሰሷቸው አምስት ምሁራን (መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ፣ አለማየሁ ሞገስ፣ መንግስቱ ለማ፣ ተሾመ ይመር እና ብርሃኑ ገበየሁ) በአማርኛ ግጥሞች ላይ ያላቸው የሀሳብ ልዩነት በጥናትና ምርምር ባህል ውስጥ የሚጠበቅና “ተፈጥሮአዊ” እንዲሁም ጠቃሚና መስኩን የሚያሳድገው ነው፡፡
ዮሐንስ ግን ይህንን የተገነዘቡት አይመስልም፡፡ ይልቁንም በምሁራኑ መካከል ያለው የሀሳብና ትንታኔ ልዩነት (ምንም እንኳን ራሳቸው ዮሐንስ የልዩነቶቹን መነሻና ምክንያት በቅጡ ባይረዱትም) ሊሆን የማይገባውና ይልቁንም አደናጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ጸሐፊው የጽሑፌ ትኩረት ነው ያሉትን ጉዳይ ላንሳ፡፡
“…እንደ ማስተማሪያ የሚቆጠሩት የአምስቱ ምሁራን አስተሳሰቦች ምን ያህል እርስ በርስ የማይጣጣሙና የቱን ያህል ዝብርቅርቅ ሃሳቦችን እንደሚፈጥሩ ማሳየት ነው የፈለግሁት። ከዚህ ጋር አብሮ የሚመጣው ሌላው ጥያቄ፣ “በዩኒቨርስቲ የቋንቋና የስነፅሁፍ ተማሪዎች በስነግጥም ዙሪያ ዝብርቅርቅ ሃሳቦችን እየተጋቱ እንዴት ቅጥ ያለው እውቀት ሊገበዩ ይችላሉ?” የሚል ነው።”
ከገለጻው እንደምንረዳው፤ የዮሐንስ ጽሑፍ ማጠንጠኛ ወይንም የመጻፉ ሰበብ ሁለት ተያያዥ ነጥቦች ናቸው፡፡ አንዱ በምሁራኑ ስራዎች መካከል የሀሳብ ልዩነት መኖሩ የፈጠረው መገረም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዚህ ልዩነት ምክንያት የትምህርት ክፍሉ ተማሪዎች የተለያዩ ምልከታዎችን (በሳቸው አባባል “ዝብርቅርቅ ሃሳቦችን እየተጋቱ”) መማራቸው “ተደናገሩት እንጂ ምኑን ተማሩት” የሚል ጥያቄና ስጋት መፍጠሩ ነው፡፡  
በምሁራኑ መካከል ያለው የሀሳብ ልዩነት በጥናትና ምርምር ባህል ውስጥ የሚጠበቅና ጠቃሚ መሆኑን ከላይ ያወሳሁ በመሆኑ፣ ወደ ሁለተኛው የጸሐፊው ጥያቄ የሚመስል መልስ ልለፍ፡፡ ይኸውም ዮሐንስን ያሳሰባቸው የክፍለ ትምህርቱ ተማሪዎች የሚቀስሙት እውቀት ተገቢነት ጉዳይ ነው፡፡
ግምቴ ትክክል ከሆነ ዮሐንስ በዩኒቨርስቲ የቋንቋና ስነጽሑፍ ትምህርት ስለሚሰጥበት አግባብና ሂደት መረጃው ያላቸው አይመስልም። በየትኛውም የትምህርት መስክ ውስጥ በአንድ እውቀት ላይ መሰረታዊ (fundamentals) የሆኑና በኋላ የትምህርት ደረጃውን ማደግ ተከትሎ የሚሰጡ የሰፉና የረቀቁ እውቀቶች አሉ፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ የተማሪነታቸው ወቅቶች በአብዛኛው እንዲቀስሙ የሚደረጉት መሰረታዊ የሆኑ እውቀቶችን ነው፡፡ በመሆኑም የስነ ግጥምንም ሆነ ሌሎች የስነጽሑፍ ኮርሶችን የሚወስዱ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች እንዲጨብጡ የሚደረገው የስነግጥምን ምንነትና ባህርያት፣ መዋቅሮችና መሰል መሰረታዊ እውቀቶችን ነው፡፡ እነዚህን መሰረታዊ ጽንሰ ሀሳቦች ሊያስተምሩ የሚችሉ በክፍለ ትምህርቱ የጸደቁና መሰረታዊ በመሆናቸውም  በአብዛኛው መምህራኑ የሚስማሙባቸው “መጻሕፍት” አሉ። በመሆኑም የወዳጄ ዮሐንስ ስጋት ምናልባትም ከመረጃ አለመኖር የመነጨ ይመስለኛል፡፡
ሆኖም ግን የትምህርት ደረጃው ወደ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ሲያድግ፣ በሌሎች የእውቀት ጥናት ዘርፎች እንደሚሆነው ሁሉ፣ እነዚህ መሰረታዊ እውቀቶች ሊፈርሱ (ሊጠፉ አላልኩም፡፡) ግድ ነው፡፡ የእውቀት ዘርፉ የማህበረሰብ ሳይንስ እንደመሆኑ መጠን ነገሮች የሚለኩትና የሚመዘኑት ባላቸው ተጠየቃዊነት፣ አጥኚዎቹ በሚያቀርቡቸው ማጠየቂያዎች ወዘተ… ነው፡፡ ዮሐንስ መሰረት ያደረጓቸው ምሁራን ጥናቶች በአብዛኛው የሚፈተሹት በእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ላይ ነው፡፡ በእነዚህ የትምህርት ደረጃዎች ደግሞ ተማሪው ማጠየቂያዎችን ማቅረብ እስከቻለ ድረስ የፈለገውን ፍልስፍና እና ትወራ የመከተል፣ ከቻለም የራሱን የመፍጠር ፈቃድ ያለው በመሆኑ በዚህ ደረጃ በምሁራኑ መካከል ያለው የሀሳብ ልዩነት ተፈላጊና ጠቃሚ እንጂ ወዳጄ ዮሐንስ እንዳሉት “ዝብርቅርቅ ሀሳቦችን” የሚግት አይደለም፡፡
ሁለተኛው የጸሐፊው ስህተት መንታ መልክ ያለው ነው፡፡ ቀዳሚው ዮሐንስ ምሁራኑ የደረሱበት የሀሳብና ትንታኔ ልዩነት ላይ ለመድረስ መነሻ ያደረጓቸውን መሰረቶች አለመረዳታቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ራሳቸው ዮሐንስ የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦችን ማቀላቀላቸው ነው፡፡
ጸሐፊው ምሁራኑ ለደረሱባቸው የሀሳብ ልዩነቶች መነሻ ያደረጉዋቸውን ጉዳዮች በቅጡ የተረዱት አይመስልም፡፡ ይህንንም ባለመረዳታቸውም የማይጠበቀውን ሲጠብቁና የጠበቁትን በማጣታቸውም ምሁራኑን ተሳስተዋል ሲሉ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ “እዮሐ አበባዬ ቤት” የሚባለውን የግጥም “ስልት” መንግስቱ ለማ፣ አለማየሁ ሞገስና መርስኤ ሀዘን ወልደ ቂርቆስ በተለያየ መልኩም ቢሆን መቀበላቸውን የሚገልጹት ዮሐንስ፤ ተሾመ ይመርን “…የግጥም አይነቶችን በአዲስ መልክ በመዘርዘር ሲያቀርቡ፣ “እዮሐ አበባዬ” ከየትኛው ምድብ እንደሚካተት አላስረዱም፡፡” በማለት፣ እንዲሁም ብርሃኑ ገበየሁ “…ስለግጥም የምጣኔ አይነቶች ብዙ ቢናገሩም፣ “እዮሐ አበባዬ” የሚል አንድም ቦታ ሳይጠቅሱ አልፈዋል፡፡” (መስመሩ የእኔ ነው) በማለት ሁለቱን አጥኚዎች ይወቅሳሉ፡፡ (ወዳጄ ዮሐንስ የግጥም ምጣኔ አይነቶችን እና የግጥም አይነቶችን መቀላቀልዎትን ልብ ይበሉ፡፡)
እንግዲህ ዮሐንስ “እዮሐ አበባዬ ቤት” በቀዳሚዎቹ አጥኚዎች (በመንግስቱ፣ አለማየሁና መርስኤ ሀዘን) የተነሳ በመሆኑ ተከታዮቹ ሁለት አጥኚዎችም የግድ ሊቀበሉት ይገባል እያሉን ነው፡፡ እውነት ለመናገር በጥናትና ምርምር አውድ ውስጥ ይህንን መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል፡፡ ሲጀመር ምሁራኑ ለየምጣኔዎቹ ስያሜ ሲሰጡ ምክንያቶች አሏቸው፡፡
ለምሳሌ “መርስኤ ሀዘንና አለማየሁ ሞገስ ግጥሞችን ለመመደብ በመስፈርትነት የተገለገሉት የግጥሙን መከወኛ አውድ፣ መዋቅሩንና እና ስልታዊ ገጽታውን እንዲሁም የግጥሙን ይዘት ነው፡፡ ለስያሜም በማህበረሰቡ ውስጥ ያሉ ቃላትን ተጠቅመዋል፡፡ መንግስቱ ደግሞ ግጥሞችን ለመክፈል በሐረግ ውስጥ የሚገኙ ቀለማትን መቁጠርን ተገልግለዋል፡፡
“ምጣኔ በአማርኛ ስነግጥም ተሾመ ይመር አበባው፣ 1997 “የአማርኛ ግጥም አይነቶች” በተባለው ጥናታቸው በስንኝ ስድስት ቀለማት ያሉትን የግጥም ምጣኔ አይነት “ከበደ ቤት” ብለው የሰየሙበት ብርሃኑ ገበየሁም፣ ይህንን ያደረጉበትን ምክንያት በግርጌ ማስታወሻቸው ላይ እንዲህ በማለት ይገልጻሉ፡፡
“ከዘመናዊ የአማርኛ ገጣሚያን ባለ ስድስት ቀለማት ስንኞችን በተደጋጋሚ መገልገላቸውን ለማስረገጥ የምደፍረው ከበደ ሚካኤልን ነው፡፡… ስለዚህ ለታላላቆቹ ገጣሚዎቻችን የሚገባቸውን አክብሮትና ሞገስ ከመስጠት፣ እንዲሁም፣ ሰዎቹንና ስራዎቻቸውን ከአዲሱና ከመጪው ትውልድ ከማስተዋወቅ አንፃር ስልቱ ከበደ ቤት ተብሎ መሰየሙ አግባብነት ያለው ይመስለኛል፡፡ አግባብነቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ለፀጋዬ ገብረመድህንና ለዮሐንስ አድማሱም ጭምር ነው፡፡” (ገጽ-91)
ከስፍራ ውስንነት አንጻር በቁንጽልም ቢሆን ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት ምሁራኑ የግጥም አይነቶችንም እንበል የግጥም ምጣኔ አይነቶችን ለመክፈል፣ እንዲሁም ስያሜዎችን ለመስጠት ልክና ተገቢ ነው ብለው የሚያምኑባቸውን ምክንያቶችና መንገዶች ተከትለዋል፡፡ (የሁሉም ምሁራን ጥናቶች እንከን አልባ ናቸው እያልኩ አይደለም፤ ጊዜና አጋጣሚው ከፈቀደ ሌላ ጊዜ እመለስባቸዋለሁ፡፡) እነዚህ ምክንያቶች ስህተት ናቸው ብሎ መተቸትና የተሻለ ነው የሚሉትን ማቅረብ የሚገባ ቢሆንም፣ ዮሐንስ ግን ያደረጉት ይህንን ሳይሆን (በተለይ የብርሃኑን ጥናት) በደፈናው ልክ አይደሉም ብሎ መቃወምን ነው፡፡ አንድ ስለስነግጥም ምንነትና ባህሪያት መሰረታዊ የሆነ እውቀት ያለው ሰው እንደሚረዳው፤ የግጥም አይነቶች እና የግጥም ምጣኔ አይነቶች የሚባሉት ቃላት የሁለት የተለያዩ ጽንሰ ሀሳቦች መጠሪያዎች ናቸው፡፡ (እርግጥ ነው ምሁራኑም ጭምር ይህንን ሲቀላቅሉት ይታያል) ብዙዎችን የሚያስማማው ይሄ ቢሆንም ዮሐንስ ግን (ከላይ ከጽሑፋቸው ላይ በቀጥታ የጠቀስኩትን አንቀጽና ያሰመርኩባቸውን ሐረጋት ተመልከቱ) ሁለቱን የተለያዩ ቃላት ሲያጣርሱና ያለ አግባቡ አንዱን ለሌላው መጠሪያነት ሲያውሉት ይታያል፡፡
ሌላውና ምናልባትም አሳዛኙ የወዳጄ ዮሐንስ ስህተት ጥናቶቻቸውን በቅጡ ሳይመረምሩ  ብርሃኑ ገበየሁን አብዝተው መውቀሳቸው ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
“አሳዛኙ ነገር፣ መንግስቱና ፀጋዬ ወደፊት ያራመዱት የግጥም ስልትና የምት ትንታኔ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተረሳ፣ በተለይ ደግሞ በብርሃኑ ገበየሁ ጨርሶ ትርጉም አልባ እንዲሆን ተደርጓል ማለት ይቻላል - ምት የተመሳሳይ ድምፆች ድግግሞሽ ነው ብለዋል (የአማርኛ ስነግጥም ገፅ 206)። በአንድ ስንኝ ውስጥ ‘ሮ’ እና ‘ሎ’ የሚሉ ሳብዕ ድምፆች መኖራቸው እንደ ዋና የምት ምሳሌ ማቅረባቸው፣ የምትን እሳቤ እጅጉን በሩቁ እንደሳቱት ያረጋግጣል።… ብርሃኑ ገበየሁ፣ የምት እሳቤን ብቻ ሳይሆን ከመነሻው የቀለም ምንነት ላይ ከዚያም የስንኝ ምንነት ላይ ከፍተኛ የግንዛቤ ችግር እንዳለባቸው መፅሐፋቸው ውስጥ በተደጋጋሚ ይታያል።”
ከገለጻው እንደምንረዳው፣ “አንድ እውቀትና የሚያቅፋቸው እሳቤዎች ቀዳሚዎቹ አጥኚዎች ያሰመሩትን መንገድ መልቀቅ የለበትም” በማለት የሚያምኑት ዮሐንስ፤ “መንግስቱና ፀጋዬ ያራመዱት የግጥም ስልትና የምት ትንታኔ በብርሃኑ ገበየሁ ጨርሶ ትርጉም አልባ እንዲሆን ተደርጎአል” ይላሉ፡፡ ከዚያም አልፈው ብርሃኑ ገበየሁ የምትን፣ የቀለምን እና የስንኝን ምንነት ፍፁም እንዳልተገነዘቡት ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ግን ብርሃኑ ገበየሁ አስቀድመን በጠቀስነው ጥናታቸውም ሆነ “የአማርኛ ሥነግጥም” (1999) በተባለው መጽሐፋቸው ሦስቱንም ጽንሰ ሀሳቦች የሚተረጉሙ ብያኔዎችን በግልጽ አስፍረዋል፡፡ ያሰፈሩትን ልጥቀስ፡፡
ምት፦ “የተመሳሳይ ወይም አቻ ድምጾችና የድምጽ ቅንብሮች (ቃላት፣ ሐረጋት፣ ስንኞች) በተወሰነ መዋቅራዊ ቦታ ላይ ተደጋግሞ መምጣት ምት ይባላል፡፡” (ብርሃኑ ከዚህ ቀጥሎ ያሉትን ዮሐንስ ልብ አላሉትም) “ምት በሚከሰትባቸው መዋቅራዊ ቅምጠቶች ከሁለት አቅጣጫ ሊታይ ይችላል፤ ውስጠ-ምት እና ቤት መምቻ ተብሎ፡፡” በስንኝ መዋቅር ውስጥ ውስጠ ምት በልዩ ልዩ ብልሀቶች ሊበጅ ይችላል፡፡ አንደኛው ብልሃት በነጠላ ስንኝ ውስጥ አንድ ድምጻዊ ምስል ደጋግሞ በመምጣት ተለይቶ የሚሰማ ምት በማስገኘት ነው፡፡” (ገጽ-205)
እንግዲህ ብርሃኑ ይህንን መሰረት አድርገው ነው የዮሐንስ አድማሱን ግጥም በምሳሌነት በማምጣት ትንታኔያቸውን ያቀረቡትና በሁለተኛው ስንኝ ላይ የሚገኙትን “ሮ” እና “ሎ” የተባሉትን ሁለት ድምጾች ለ“ውስጠ-ምት” አይነት አስረጂ ያደረጉት፡፡ የብርሃኑን መነሻና አቅጣጫ በቅጡ ያልተረዱት ዮሐንስ ግን ጫፉን ብቻ በመያዝ ብርሃኑን አላዋቂ አድርገዋቸዋል። ወደ ሌሎቹ ጽንሰ ሀሳቦች ልለፍ፡-
ቀለም፦ “በሥነግጥም ጥናት ቀለም የኪናዊ ንግግር ክዋኔን አደረጃጀት መጠን መስፈሪያ ደቂቅ አሀድ ነው፡፡ ስለዚህም፣ ትኩረቱ በግብር በተከወኑ፣ በተወሰኑና በታወቁ ንግግሮች ውስጥ ባሉ የድምጾች ቅንብር ላይ ነው፡፡… ሥነግጥማዊ ቀለም በቃል መዋቅር ላይ አይወሰንም፣ ከቃል ዝቅ ያሉም ከፍ ያሉም ተግባቦታዊ ገጽታዎችን ይመለከታል፡፡” (ገጽ-229)
ስንኝ፦ “ስንኝ በጠባብ ፍቺው አንድ የግጥም መስመር ማለት ነው፡፡… ስንኝ በሰፊ ፍቺው ግጥም ማለት ነው፡፡…” (ገጽ-187)
እንግዲህ የግጥም አካላት የሆኑትን ጽንሰ ሀሳቦችን በዚህ መልኩ የበየኑትን ብርሃኑን ነው ዮሐንስ “ግንዛቤ የላቸውም” የሚሏቸው፡፡ የአማርኛ ስነግጥም ጉዳይ እጅግ ሰፊና በጋዜጣ አምድ ሊቋጩ የሚችል ባለመሆኑ፣ አንድ እጅጉን የተደመምኩበትን የወዳጄ ዮሐንስን ጽሑፍ “ክፍተት” አንስቼ ላብቃ፡፡
የአምስቱን የስነጽሑፍ ምሁራን ትንታኔዎች በማውሳት (በተለይ የብርሃኑን) ስህተት መሆናቸውን የሚገልጸው የዮሐንስ ጽሑፍ፤ ይህንን ከማለት ባለፈ ምሁራኑ የትኛው ጉዳይ ላይ እንደተሳሳቱ፣ የተሳሳቱባቸውን ምክንያቶች፣ እንዲሁም ልክ ነው የሚለውን ሀሳብ ለይቶ ያላሰፈረ ነው፡፡ ይህም የምሁራኑን ሀሳቦች በደፈናው ተሳስቷል ከማለት ባለፈ፣ ስህተት ያለውን በግልጽ በመንቀስ፣ ልክ ነው የሚለውን የራሱን ሀሳብ የማያሳይ በመሆኑ ጽሑፉን ውሃ የማይቋጥር አድርጎታል፡፡  
መልካም ሰንበት!!

Published in ጥበብ
Saturday, 31 January 2015 13:14

የቁልቁለት መንገድ

      ኤደን ወልዳ ተኝታለች፡፡ አራስ ቤት ሆና ሰላም ልታገኝ ግን አልቻለችም፡፡ በህይወትዋ ውስጥ የተከሰቱ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ የምትወዳቸውም የማትወዳቸውም፡፡ ታዲያ ታሪክዋ ታሪክ ብቻ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ወደ ኋላ ይስቧታል፡፡ ወደ ድሮ ይጎትቷታል፡፡
ከናትናኤል ጋር ተጋብተዋል፡፡ ተጋብተዋል ግን አልተግባቡም፡፡ ትወደዋለች ግን ትፈራዋለች። ታፈቅረዋለች ግን ታፍረዋለች። ለዚህ የዳረጋት ታሪክዋ ነው፡፡ ከናትናኤል ጋር ህይወትዋ ውስጥ አራት ሰው አለ፡፡ ከመጀመሪያው ስንጀምር፡-
የመጀመሪያው ሰው
ሱራፌል ይባላል፡፡ የታክሲ ሹፌር ነው፡፡ አንድ ቀን ከካሳንቺስ ወደ ፒያሳ ስትጓዝ የቆመላት ታክሲ ውስጥ ገባች፡፡ ቆንጆ ናት፡፡ ቁንጅናዋ የትኛውንም ወንድ እንደ ማግኔት ከሩቅ ይስባል። ሱራፌል ቆንጆ ሴት አይቶ የማያልፍ ዓይነት ሰው ነው፡፡ ቆንጆና እሸት አይታለፍም ከሚሉት ውስጥ ነው፡፡
“መነፅርሽ በጣም ያምራል!” አላት
“አመሰግናለሁ!”
“ምነው እኔስ አላምርም ወይ ነው ያልሽኝ?”
“ኧረ ታምሪያለሽ … መነፅሩ ራሱ ያማረው እኮ ያንቺ ፊት ውበት ተጋብቶበት ነው … እመብርሃንን!”
 ፈገግ ብላ “አመሰግናለሁ!” አለች በድጋሚ
“ምስጋና ኪስ አይገባም ሲባል አልሰማሽም?”
ዝም አለችው፡፡
“እግዜርን ግን በጣም ልታመሰግኚው ይገባሻል።”
“ለምን?”
“ይህቺን የመሰለች .. መልአክ የምትመስል ሴት አድርጎ ስለፈጠረሽ፡፡”
እንደ መሽኮርመም አለች፡፡ ወሬ ተጀመረ፡፡ ተግባቡ፡፡ ከመውረድዋ በፊት
“ስልክሽን አንዴ ታውሺኝ?!” አላት፤ በግራ እጅዋ ወደያዘችው ስልክዋ እጁን እየዘረጋ፡፡
“ለምን?”
“ስልኬ ባላንስ የለውም፤ የሆነ ቦታ ሚስኮል ላደርግ ፈልጌ ነው”
ሰጠችው፡፡ ተቀበላት፡፡ በስልኳ ወደ ስልኩ ደወለ፡፡ ስልክ ቁጥርዋን ስልኩ ላይ መዘገበ፡፡ አመስግኖ ስልክዋን መለሰላት፡፡
“ለምኑ ነው የምታመሰግነኝ?” አለችው
“ቀኔ ብሩህ እንዲሆን ስለረዳሽኝ አመሰግናለሁ!”
ደረሰች፡፡ ወረደች፡፡ በስልክ ግንኙነታቸው     ቀጠለ፡፡ በየቀ ይደውላል፡፡ በየቀኔ ታወራዋለች። አንዴ ተገናኙ፡፡ ሁለቴ ተገናኙ፡፡ ሶስቴ ተገናኙ። አራቴ ተገናኙ፡፡ በመጨረሻ ፍቅረኛሞች ሆኑ ተገኙ። ያልሆኑትና ያላደረጉት ነገር የለም፡፡
ተዋደዱ፡፡ ተሻሹ፡፡ ተሳሳሙ፡፡ ምን ቀረ? ምንም!
ሁለተኛው ሰው
ተመስገን ይባላል፡፡ መካኒክ ነው፡፡ የራሱ ጋራጅ ቤት አለው፡፡ በድርጅቱ በር ስታልፍ አያት፡፡
“አንድ ጊዜ እንድናወራ ትፈቅጂልኛለሽ?” አላት መንገድ ላይ አስቁሟት፡፡
“ስለ ምን?”
“ዝም ብለን ስለ አንዳንድ ነገር ብናወራ ደስ ይለኝ ነበር”
“አይመቸኝም!” ብላ ጥላው ልትሄድ ስትል እጅዋን አፈፍ አድርጎ እያስቆማት፤
“ይቅርታ…ከድፍረት አትቁጠሪብኝና የግድ ዛሬ መሆን የለበትም፤ የሆነ የሚመችሽ ቀን ሻይ ቡና እያልን ብናወራ ደስ ይለኝ ነበር፡፡” አላት፡፡
“ወንድሜ … እኔና አንተን የሚያገናኘን ምንም የጋራ ነገር ያለንም፡፡ ስለዚህ …”
ተለያት፡፡
በሚቀጥለው ቀን አስቁሞ ትንሽ አወራት፡፡ በሚቀጥለው ቀንም ትንሽ አወራት፡፡ በኋላ ላይ ካፌ ገብቶ ለመጨዋወት ፈቀደች፡፡ ገቡ፡፡ አወሩ።
“ፍቅር ያዘኝ” አለ፡፡
ግንኙነት ጀመሩ፡፡ ተሳሳሙ፡፡ ተቃቀፉ፡፡ አንሶላ ተጋፈፉ፡፡
ሶስተኛው ሰው
ስምኦን ይባላል፡፡ መሀንዲስ ነው፡፡ መሀንዲስ ብቻ ሳይሆን የሰፈርዋ ልጅም ነው፡፡ የወንድ ቆንጆ ነው፡፡ ከጓደኞችዋ ጋር “ቆንጆው ልጅ” እየተባባሉ ያወራሉ፡፡
“ቆንጆው ልጅ መጣ …”
“ቆንጆው ልጅ አለፈ …”
“ቆንጆው ልጅ ሰላም አለኝ …”
“ቆንጆው ልጅ …”
“ቆንጆው ልጅ …”
ተግባቡ፡፡ አብረው ጊዜ ማሳለፍ ጀመሩ። አብሮ ፊልም ማየት መጣ፡፡ ተላመዱ፡፡ ተዋደዱ። ፍቅር ደራ፡፡ ክርና መርፌ ሆኑ፡፡
ሦስቱን ወንዶች የተዋወቀችውና ግንኙነት የጀመረችው በአንድ ዓመት ውስጥ ነው። በወራት ልዩነት! ሱራፌል የሚያውቀው ከእሱ ጋር ብቻ እንደሆነችና እንደምትወደው ነው። ተመስገን የሚያውቀው ከ‘ሱ ሌላ ወንድ ቀና ብላ የማታይ እና እንደሚወዳት ሁሉ አብዝታ የምትወደው መሆኗን ነው፡፡ ስምኦን የሚያውቀው እሱ ብቸኛው ፍቅረኛዋ እንደሆነና ሌላ ወንድ እንደማታውቅ ነው፡፡
አንዱ ሰኞ ከተቀጠረ፤ ሌላኛው ማክሰኞ ይቀጠራል፡፡ አንዱ እሮብ ካገኛት፤ ሌላው ሀሙስ ያገኛታል፡፡ ከአንዱ ጋር መልካም ቅዳሜ፤ ከሌላው ጋር ቆንጆ እሁድ ታሳልፋለች። አንዳንዴም አንዱን ጠዋት ሌላውን ከሰዓት ታገኛለች፡፡ አንዱን ረፋድ ላይ፤ ሌላውን አመሻሽ ላይ! አንዱን ቀትር ላይ፤ ሌላውን ማታ! (ማታ ላይ)… ስትጀምረው እንደ ቀልድ ነው፡፡ ሲቆይ ግን ህይወትዋ ሆነ፡፡
አንድ ለሶስት
አንዲት ሴት በሶስት ወንዶች ተይዛለች፡፡
ጨዋታው አንድ ለሶስት ሆኗል፡፡
ከአንዱ ጋር ረጅም ሰዓት ስልክዋ ስለሚያዝ ሌሎቹ መንጨርጨራቸው አልቀረም። ሚስጥሩን አውቀው ሳይሆን እንዲሁ ጠርጥረው። አለ አይደል?! … እንዲሁ!
“ወንድ ልጅ ሞኝ ነው፡፡” ብሎ የለ ዘፋኙ?! ሶስቱም እውነቱን አላወቁም፡፡ ሶስቱም ፍቅር ውስጥ ናቸው፡፡ ሶስቱም ይደውላሉ፡፡ ሶስቱም ያገኝዋታል። ከሶስቱም ጋር አንሶላ ትጋፈፋለች፡፡ “ወንድ ልጅ ሞኝ ነው …” … ፍቅር አልያዛትም፡፡ ሶስቱንም ግን ትወደዋለች፤ ወይም የወደደቻቸው ይመስላታል። ብቻዋን ስትሆን ተሰልፈው ተራ በተራ በፊትዋ  ያልፋሉ፡፡
ሱራፌል ጨዋታውና ቀልዱ ይማርካል። ከሌሎች በተለየ ከእሱ ጋር እንደ ስኳር ድንች የሚጣፍጥ ትዝታ አላት፡፡ መቼም የማትረሳቸው! ከእሱ ጋር ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ትንፋሽ  ለትንፋሽ የተማማገችው፤ ሩካቤ ስጋ የፈፀመችው፡፡ እሱ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ አካሉን ከአካልዋ ያዋሃደውና ያዋደደው፡፡ ድንግልናዋን የገረሰሰ ወንድ ነው። የወንድ ጀግና! ማንም ያልሄደበትን መንገድ የሄደ። ስለዚህ አሻራውን ውስጥዋ ትቷል፡፡ ሌሎች በተሄደው መንገድ ላይ ነው የሄዱት፡፡ አሻራቸው አካልዋ ላይ አልታተመም፤ ቢታተምም ግን እንደ‘ሱ በደማቁና በትልቁ ሳይሆን በስሱና በትንሹ ነው።
…ተመስገን ቁምነገረኛነቱ ይደንቃታል። በጣም ሲበዛ ቁምነገረኛ ነው፡፡ ለቁም ነገር እንደሚፈልጋት ይነግራታል፡፡ የወሬው ጭብጥ ትዳር ነው፡፡
“አገባሻለሁ!” ይላታል
“አገባሽና ልጅ ትወልጂልኛለሽ … ከዚያ በደስታ ልጃችንን እያሳደግን በደስታ አብረን እንኖራለን፡፡”
“እሺ!” ትለዋለች፡፡
“ግን ስንት ልጅ ነው የምንወልደው?”
“ስምንት፤ … ዘጠኝ፤ … አስር፤ … አስራሁለት ወይም አስራ አራት … ኧረ ከዛም በላይ!”
ልጅ ይወዳል፡፡ እና ብዙ ቢወልድ ደስ ይለዋል፡፡
እሷ ግን ትለዋለች፤
“ኧረ ባክህ … እኔ ዝም ብዬ ልጅ ስቀፈቅፍ ልኖርልህ ነው?”
“እሺ ታዲያ ስንት እንውለድ?” ይላታል፤ ፍም የመሰለውን ጉንጭዋን በእጁ እየቆነጠጠ፡፡
“ሁለት!” ትለዋለች
“እንዴ … ሁለትማ ያንሳል … አይሆንም … አይሆንም …”
ልጅ አሁኑኑ የሚመጣ ይመስል በሚወልዱት ልጅ መጠን ላይ ይከራከራሉ፡፡ እየተከራከሩና እየተጨቃጨቁ ረጅም ጊዜ ይቆያሉ፡፡ በተገናኙ ቁጥር ባይሆንም አልፎ አልፎ ንትርኩ አይቀርም፡፡
ስምኦን አለባበሱ ይመቻታል፡፡ ዘናጭ ነው። ዘመናዊ ልብሶች ይለብሳል፡፡ ዘመናዊ ጫማዎች ይጫማል፡፡
አንዳንዴ ዲዛይነር ሁሉ ይመስላታል፡፡ እንደሚገነባው ህንፃ ዲዛይን፤ ለ‘ራሱም ዲዛይን ያወጣል፡፡ ወይም ይመስላል፡፡ ቤት መስራት፤ ህንፃ መገንባት ብቻ ሳይሆን ‘ራሱን መስራት፤ ማንነቱን መገንባትም ይችልበታል፡፡ እና እሱን ማየት ደስ ይላታል፡፡ አታፍርበትም፡፡ ከሰው ጋር ስታስተዋውቀው ኩራት ይሰማታል፡፡ የትም ይዛው ትገኛለች፡፡ ከሦስቱ ፍቅረኞችዋ ጓደኞችዋ የሚያወቁት እሱን ብቻ ነው፡፡ ሌሎቹ በሚስጥር የተያዙ ናቸው፡፡ ሌላው ከስምኦን የምትወደው አሳሳሙን ነው፡፡ ሲስማት ልብዋ ጥፍት ይላል፡፡
እየሳማትና እየሳመችው እጁ ላይ እንደ ጨው ትሟሟለች፡፡ ከየት እንደሚያመጣው አታውቅም። ግን ይችልበታል፡፡ አሳሳሙን ጥበባዊ ያደርገዋል። ዛሬ የሳማትን አሳሳም፤ ነገ ላይደግም ይችላል። ብቻ ግን ባገኛትና በሳማት ቁጥር ሌላ ዓለም ውስጥ ያስገባታል፡፡ አየር ላይ ትንሳፈፋለች፡፡ መሬት ትርቃለች፡፡ ሰማይ ይቀርባታል፡፡ ጨረቃዋን መንካትና መጨበጥ፣ ፀሐይዋን መዳበስና መዳሰስ ይቃጣታል፡፡
*   *   *
በድርጊትዋ ደስተኛ አይደለችም፡፡ እንደዚህ መሆን፤ እንደዚህ መኖር አትፈልግም። ሳታስበውና ሳትዘጋጅ የገባችበት ህይወት ነው። ራስዋን ትንቃለች፡፡ በ‘ራስዋ እፍረት ይሰማትና ስቅቅ ትላለች፡፡  እስከመቼ ነው እንደዚህ የምቀጥለው? ብላ ታስባለች፡፡ አታላይ፣ አምታች፣ ውሸታም መሆንዋ አንገት ያስደፋታል።
አንድ ለሶስት!
መወሰን ግን አቃታት፡፡ ከሶስቱ ሁለቱን ምን አድርጋ፤ እንዴት ሆና መገላገል እንዳለበት ግራ ገባት፡፡ ሶስቱን ማወዳደሩና ከሶስቱ አንዱን መምረጡ ራሱ ‘ራሱን የቻለ የቤት ስራ ነው። ማን ይቅር? … ማን ይሸኝ? … ድንግልናዋን የገረሰሰው፤ ሁሌ የሚያስቃትና የሚያዝናናት ሱራፌል፤ ወይስ እንደ ሚስቱ የሚንከባከባት፤ በስጦታ የሚያንበሸብሻትና ሚስት ሊያደርጋት የሚመኘውን ተመስገን  ወይስ በአለባበሱ የሚማርካትና በአሳሳሙ ልብዋን የሚያጠፋው ስምኦን ወይስ … ማን?!
መወሰን እንዳቃታት ወራት ነጎዱ፡፡ ዓመቱ መጣ። መጨረሻ ላይ ያላሰበችው ነገር ተከሰተ። ወርሃዊ ደሞዝዋ ሳይመጣ ቀረ፡፡ የወር አበባዋ የውሃ ሽታ ሆነ፡፡ ኤደን አረገዘች፡፡ ከማን እንዳረገዘች ልታውቅ አልቻለም፡፡ በዚያን ሰሞን ከሶስቱም ጋር አንሶላ ትጋፋ ነበር፡፡ ልጁ የማን ነው? የሱራፌል? … የተመስገን? … የስምኦን? … ወይስ የሶስቱም ወይስ የሌላ የአራተኛ ሰው ወይስ የማን?!
ልታስወርድ አልፈለገችም፡፡ ማስወረድ ሀጢያት ነው ብላ ልትወልደው ወሰነች። ጓደኞችዋ ፅንሱ ቀን ሳይገፋና ሳያድግ ቶሎ እንዲወጣ እናድርገው ቢልዋት፤ የሰው ነፍስ አላጠፋም ብላ በውሳኔዋ ፀናች፡፡ … ሱራፌል ጋ ሄደች፡፡
“ፀንሻለሁ!” አለችው፡፡
“ስትቀልጂ መሆን አለበት” አለ፤ ኮስተር ብሎ፡፡
“የምን ቀልድ ነው የምታወራው፤ ካንተ ልጅ አርግዤያለሁ እኮ ነው የምልህ …” አለችው፡፡
“እኔ የማውቀው ነገር የለም! … የልጁን አባት ሄደሽ እዚያ የምትፈልጊበት ፈልጊ” ብሎ ሸኛት፡፡
ተመስገን ጋ ሄደች፡፡
“አርግዣለሁ! ልጁ የአንተ ነው” አለችው፡፡
“ጥሩ ነው … አንድ ላይ እንጠቃለላለን” አላት፡፡
“ቤተሰቦቼ ጋ ሽማግሌ ላክ” አለችው፡፡
“የምን ሽማግሌ መላክ ነው … ነይና ቤቴ ግቢ፤ ሽማግሌውን ባይሆን በኋላ ለእርቅ እንልካለን እንጂ አሁን አያስፈልግም…”
አልተዋጠላትም፡፡ እንዲደገስ ትፈልጋለች። የሰርግዋን ዕለት መኖርና ማየት ትፈልጋለች፡፡ በክብር ሽማግሌ ተልኮ፤ የቤተቦችዋን ይሁንታ አግኝቶ፤ ቬሎ ለብሳ፤ ተደግሶ፤ ተሰርጎ “የኛ ሙሽራ …” እንድትባል ፈለገች፡፡ ተመስገን ይሄን አላደርግም አለ፡፡
ስምኦን ጋ ሄደች፡፡
“ልጅህን በሆዴ ይዣለሁ!” አለችው፡፡
“የኔ ስለመሆኑ ማረጋገጫሽ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት፡፡
“እንዴ … አታምነኝም?” አለችው ዓይንዋን ቅልስልስ አድርጋ፡፡
“ማመን አለማመን አይደለም፡፡ ሳልደብቅ የምነገርሽ አንድ ነገር አለ፡፡ እኔ በዚህ ዕድሜዬ ልጅ እንዲኖረኝ አልፈልግም፡፡ ገና የራሴን ልጅነትም ያልጨረስኩ ሰው ነኝ፡፡ እና የልጁን አባት ሄደሽ ሌላ ቦታ ብትፈልጊ መልካም ነው፡፡” ብሎ ተሰናበታት፡፡
ኤደን ግራ ገባት፡፡ ኤደን ተጨነቀች፡፡ ኤደን የምትገባበት ጠፋት፡፡ ወደ ሰማይ ብትመነጠቅ በወደደች፡፡ መሬት አፍዋን ከፍታ ብትውጣት በተደሰተች፡፡ ሁሉም አልሆነም፡፡ “ሁሉም ነበረን፤ ግን ሁሉንም አጣን” ዓይነት ሆነ፡፡ ማስወረዱን “ፈፅሞ የማላደርገው ነገር ነው!” ብላ ደመደመች። ዘጠኝ ወር ጠብቃ በእናት በአባትዋ ቤት ልጅዋን ወለደች፡፡ ወንድ ልጅ ከነቃጭሉ ዱብ!…
*   *   *
ወራት ነጎዱ፡፡ ዓመታት አለፉ፡፡ ልጅዋ ድክድክ ከማለትም አልፎ በእግሩ መሄድ ጀመረ፡፡  ከናትናኤል ጋ ተዋወቁ፡፡ ወደዳት! ሊጋቡም ወሰኑ፡፡ ሽማግሌ ተላከ፡፡ ቤተሰብ በክብር ሰጠው፡፡ የሰርጉ ቀን ሲቃረብ ሽር ጉድ ተጧጧፈ፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተጠሩ። ተደገሰ፡፡ የሰርጉ ዕለት ሙሽራውና ሚዜዎቹ መጥተው ይዘዋት ወጡ፡፡ ጉዞ ወደሱ ቤት ሆነ፡፡
ናትናኤል ስለ ኤደን የኋላ ታሪክ ብዙ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ስለምንም አላነሳችበትም። በትዋን ዓይቶ ወደዳት፡፡ እና ቸኩሎ አገባት፡፡ አብረው እየኖሩ ሳሉ ከዕለታት ባንዱ ጉዱን ሰማ፡፡ ኤደን ልጅ አላት! ተናደደ፡፡
“እንዴት ሳትነግሪኝ” አለ፡፡ ተርበተበተች፡፡ ከውሃ እንደ ወጣ እንቁራሪት ሆነች፡፡
“ማነው የነገረህ?” አለችው፡፡
“ማን እንደነገረኝ ማወቅ ምን ያደርግልሻል?” አላት፡፡
“ተደብቆ የሚቀር መስሎሽ ነበር?” ብሎ ጮኸባት፡፡
ከዚያን ቀን ጀምሮ የናትናኤል ባህሪ ተለወጠ። ትቀፈው ጀመር፡፡ ባያያት ደስ ይለዋል። ባይሰማት ደስ ይለዋል፡፡ አንድ ማዕድ ላይ አብረው ባይቀርቡ ደስ ይለዋል። አንድ አልጋ ላይ አብረው ባይተኙ ደስ ይለዋል። ይህ ስሜት በሱ ውስጥ እየገነነ ስር እየሰደደ በመሄድ ላይ ባለበት ወቅት ኤደን ማርገዝዋን አወቀች፡፡ ከወራት በኋላም ሴት ልጅ ወለደች፡፡ ብትወልድም የናትናኤል ባህሪ አልተስተካከለም። እንደ እንቁ ያያትና እንደ እንቁላል ይንከባከባት እንዳልነበረ ለዓይኑም ጠላት፡፡ ከስራ እንደወጣ ወደ ቤት አይገባም፡፡ ሌላ ቦታ አምሽቶ ለመኝታ ብቻ ነው የሚገባው፡፡ ከቤት መብላትም አቆመ። ሰራተኛዋ እራት ስታቀርብለት “በልቻለሁ!” ነው መልሱ፡፡ በአጋጣሚ በምሳ ሰዓት መጥቶ እንደሆነ ምሳ ስታቀርብለትም “በልቻለሁ!” ይላታል፡፡ ቁርስ  ስታቀርብለትም “አሁን አላሰኘኝም” ብሎ ይወጣል። ቤቱና ናትናኤል ሆድና ጀርባ ሆኑ፡፡
ኤደንም ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ እንደገባት በተኛችበት ስትተክዝ ውላ፤ ስትቆዝም ታድራለች፤ እራስዋ ኤደን!

Published in ልብ-ወለድ

የአንዲት ሴተኛ አዳሪ ኢትዮጵያዊትን የዕለት ማስታወሻ የሚተርከውና በአርታኢ ፍፁም ብርሃኔ የተዘጋጀው “ሮዛ ቁጥር ሁለት” መፅሃፍ ገበያ ላይ ዋለ፡፡
ነዋሪነቱ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ የሆነው የመፅሃፉ አርታኢ የባለታሪኳን ዳያሪዎች አሰባስቦ ለህትመት ለማብቃት አንድ ዓመት እንደወሰደበት ግልጿል፡፡ በዚህ መፅሃፍ የመጀመሪያው ክፍል ከአንድ ዓመት በፊት የታተመ ሲሆን ከ45ሺ በላይ ሰዎች እንዳነበቡትና መፅሃፉን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም በዝግጅት ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡  

በአቢሲኒያ ኢንተርቴይንመንት እየተዘጋጀ በኤፍኤም 96.3 ላይ ሲሰራጭ የቆየው የቀጥታ የስልክ መስመር የድምፅ ውድድር ዛሬ ይጠናቀቃል፡፡
ለመጨረሻ ውድድር የቀረቡ አምስት ተወዳዳሪዎች በቀጥታ ከስቱዲዮ የሚያካሂዱትን የድምፅ ውድድር ለመዳኘት ታዋቂ የሙዚቃ አቀናባሪዎችና ድምፃውያን በስፍራው ይገኛሉ፡፡ በውድድሩ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡት ተወዳዳሪዎች የግጥም፣ የዜማና የሙዚቃ ቅንብር ሙሉ ወጪያቸው ተችሎ ነጠላ ዜማ እንዲሰሩ እንደሚደረግ የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ አቶ አባተ ማንደፍሮ ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
አቢሲኒያ ኢንተርቴይንመንት እስከ አሁን ድረስ በአምስት ዙሮች ባደረገው የቀጥታ ስልክ መስመር የድምጽ ውድድር በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከ350 በላይ ጀማሪ ድምጻውያን እንደተካፈሉ አቶ አባተ ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙ የተጀመረበት 4ኛ ዓመት በዚሁ ዕለት እንደሚከበርም ገልጿል፡፡

በድምፃዊ ዳንኤል ዘውዱ የተሰራው “የዝና” የተሰኘና ነባር ዘፈኖች የተካተቱበት የሙዚቃ አልበም በገበያ ላይ ዋለ፡፡
በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን የተስፋዬ ወርቅነህን ተወዳጅ ዜማዎች ሪሚክስ በማድረግና በድጋሚ በመስራት በገበያ ላይ ያዋለው ድምፃዊ ዳንኤል ዘውዱ ለዘፈኖቹ ግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተገቢውን ክፍያ መፈፀሙንና የቅጂ መብቱን ጠብቆ መስራቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡
የዘፈኖቹ ግጥሞች የተወሰነ ማሻሻያዎች እንደተደረጉባቸውና በታዋቂ የሙዚቃ አቀናባሪዎች መሰራታቸውንም ድምፃዊው ተናግሯል፡፡  

ላለፉት ሃምሳ አመታት ተስለው የተጠራቀሙ የሰዓሊ ወርቁ ጐሹ የስዕል ስራዎች ለዕይታየ ማቀርቡበት “ላይት” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ የፊታችን አርብ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ሙዚየም አርት ጋለሪ ይከፈታል፡፡
በዚህ አውደ ርዕይ እጅግ በርካታ የስዕል ስራዎች የሚቀርቡ ሲሆን የተለያዩ ጉዳዮችን እንደሚዳስሱም ተገልጿል፡፡
አውደ ርዕዩ እስከ ፌቡራሪ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ለጐብኚዎች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም አዘጋጁ ጐሹ አርት ጋለሪ ከላከው መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡


ቫይረሱ በትንፋሽ መተላለፍ ሊጀምር እንደሚችል ተሰግቷል

በምዕራብ አፍሪካ አገራት ተከስቶ ከ22 ሺህ በላይ ሰዎችን ያጠቃውና ወደ 9 ሺህ የሚደርሱትንም ለህልፈት የዳረገው የኢቦላ ቫይረስ፣ ባህሪውን እየለወጠ እንደሚገኝና ለውጡ ቫይረሱን ከሰው ወደ ሰው በቀላሉ መዛመት እንደሚያስችለው ለማወቅ  ጥናት እየተካሄደ  መሆኑን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የፈረንሳዩን ፓስተር ኢንስቲቲዩት ተመራማሪዎች ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ቫይረሱ የቀድሞ ባህሪውን እየለወጠ እንደሚገኝ የተረጋገጠ ሲሆን ተመራማሪዎቹ የቫይረሱ የባህሪ ለውጥ የከፋ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን ለማወቅ  በጊኒ፣ በቫይረሱ በተጠቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የደም ናሙና ላይ ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
የተመራማሪ ቡድኑ አባል የሆኑት ዶክተር አናቫይ ሳኩንታቢ እንዳሉት፤ የኢቦላ ቫይረስ በሚገርም ሁኔታ የተፈጥሮ ባህሪውን እየቀየረ እንደሚገኝ በጥናታቸው አረጋግጠዋል፡፡ ቫይረሶች በጊዜ ሂደት የተፈጥሮ ባህሪያቸውን መቀየራቸው የተለመደ ክስተት ነው ያሉት ዶክተሩ፣ ኢቦላም እንደ ኤች አይቪ ኤድስና ኢንፍሉዌንዛ ቫይረሶች ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ የባህሪ ለውጥ የማካሄድ ተፈጥሯዊ ባህሪ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ይህም ቫይረሱ ከሁኔታዎች ጋር የመላመድ አቅሙን ከፍ እንደሚያደርገውና የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት እንደፈጠረ አክለው ገልጸዋል፡፡
ቫይረሱ በርካታ ሰዎችን እያጠቃና የባህሪ ለውጡን እየቀጠለ ከሄደ፣ በትንፋሽ የመተላለፍ ዕድል ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ ይህም ሆኖ ግን ለጊዜው ቫይረሱ በትንፋሽ እየተላለፈ እንደሚገኝ የሚያረጋግጥ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአለም ባንክ ፕሬዚደንት ጂም ያንግ ኪም፤ አለማችን በቀጣይ ሊከሰቱ ለሚችሉ ኢቦላን የመሳሰሉ ገዳይ በሽታዎች ይህ ነው የሚባል ዝግጅት አለማድረጓንና ይህም ከፍተኛ ጥፋት ሊያስከትል እንደሚችል አስታወቁ፡፡
መንግስታት፣ የእርዳታ ድርጅቶች፣ አለማቀፍ ተቋማትና ኩባንያዎች ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የገዳይ በሽታዎች ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት ይገባቸዋል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በምዕራብ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ ጥፋት ካደረሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በመማር አለም ከወዲሁ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ
Page 1 of 18