ሃዋሣ ከተማ ላይ የተካሄደው 1ኛው ኃይሌ ገ/ስላሴ ስኬታማ አጀማር እንደነበረው ተገለፀ፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በሃዋሣ የግማሽ ማራቶንና የጎዳና ላይ ሩጫዎችን ያካሄደው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የማራቶኑን በአስደናቂ ዝግጅት በማካሄድ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የአትሌቲክስ ውድድሮች አዘጋጅ ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከሚያካሂዳቸው የሞሃ ማራቶን እና የአበበ ቢቂላ ማራቶን ነበሩ፡፡ በግል ተቋም በታሪክ የመጀመርያው የማራቶን ውድድር አንደኛው የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን” ነው፡፡ ማራቶኑ በሌሎች የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድሮች ታጅቦ የተካሄደ ሲሆን የህፃናት የ2ኪ.ሜ የጐዳና ውድድር፣ የ5 ኪ.ሜ ህዝብ አሳታፊ ሩጫ እና የግማሽ ማራቶን ውድድሮች ናቸው፡፡ የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በሃዋሣ ከተማ አውራ ጐዳናዎች የተደረገው በተገቢው የማራቶን ርቀት ሲሆን በአይ. ኤ. ኤ. ኤ ፍ ባለሙያ ሂውጅ ጆንስ በሰራው ልኬት ማረጋገጫ እና ዕውቅና አግኝቶ ነው፡፡
ማራቶኑን በማዘጋጀት በተለይ ሶስት አካላት በአጋርነት ሰርተዋል፡፡ በማርኬቲንግ እና በፕሮሞሽን እንቅስቃሴዎች በባለቤትነት የመራው የአሜሪካው ሞራይ ማውንተን ስፖርትስ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የውድድሩን ዝግጅት እና ኦፕሬሽን አከናውኗል፡፡ አዋዜ ቱርስ ደግሞ ከውድድሩ ጋር በተያያዘ በተለይ የውጭ አገር ተሳታፊዎች በማቀላጠፍ ተሳትፏል፡፡ ኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶንን የማዘጋጀት ሃሳብን የተወጠነው በአሜሪካው የአትሌቲክስ ውድድሮች አዘጋጅነት በሚታወቀው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ነበር፡፡ የሮክን ሮል ማራቶን እና ታዋቂውን የግራንድ ፕሪ ውድድር ካርልስባድ የማዘጋጀት ልምድ አለው
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለፀው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ሃሳቡን ያመነጨው በአሜሪካ እና በአውሮፓ ከሚካሄዱ ውድድሮች የተለየ ማራቶን መዘጋጀት አለበት በሚል ነው፡፡ ስለዚህም ታላላቅ የረጅም ርቀት ሯጮችን በማፍራት ወደ የሚታወቁት ሁለቱ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ኬንያና ኢትዮጵያ ተተኮረባቸው። ከኃይሌ ገብረስላሴ ጋር በነበራቸው ትውውቅ ኢትዮጵያ ተመረጠች፡፡
ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ለታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዝግጅት ክፍያ በመፈፀም ፤ለውድድሩ የሚያስፈልገውን ወጭን በመበጀት፤ ስፖንሰሮችና ባለ ድርሻ አካላትን በማስተባበር፤ የውጭ ተሳታፊዎችን በመማረክ እና አጠቃላይ የማስተዋወቅ እና የፕሮሞሽን ተግባራትን በዋና አጋርነት ሰርቷል፡፡ አቶ ኤርሚያስ አየለ እንደገለፀው የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶንን ለማሰናዳት በውድድሩ ዙርያ የተሰባሰቡ አጋሮች ለአንድ አመት ሰርተዋል፡፡ ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ አማካኝነት ስለየኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶንን በታላላቆቹ የኒውዮርክ፤ ቺካጎ እና የበርሊን ማራቶኖች በክፍያ በሚገኝ ቦታ ቢልቦርዶችን በመስቀል ማስተዋወቅ ተደርጓል፡፡ ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ የዚህን ውድድር አጠቃላይ ወጪ የሸፈነ ሲሆን እስከ 2 ሚሊዮን ብር ወጭ አድርጓል፡፡ ይህንኑ ማራቶንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ እንቅስቃሴ 200ሺ ዶላር ማግኘት ተችሏል፡፡ ይህ የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ በሞራይ ስፖርትስ አማካኝነት የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ከልብ ጋር በተያያዘ የጤና ችግር ድጋፍ ለሚሹ እና ለተቸገሩ ህፃናት እርዳታ ለሚሰጠው ለእንጦጦ ፋውንዴሽን የተበረከተ ነው። የሃዋሳው ውድድር የዓለም ማራቶን ሪከርድ ለሁለት ጊዜያት በሰበረው ታላቁ የማራቶን ሯጭ ኃይሌ ገ/ስላሴ በመሰየሙ በርካታ የውጭ አገር ስፖርተኞች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ውድድሩ ላይ እንዲሳተፉ ምክንያት ነበር፡፡ ለማራቶኑ ድረገፅ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ትኩረትም የጠቀመ አሰያየምም ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ላለፉት 4 ዓመታት በሃዋሣ ከተማ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች የግማሽ ማራቶን ውድድሮችን ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ይህ ልምዱ በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ዝግጅት የተቀላጠፉ ስራዎች እንዲከናወኑ አግዟል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ለውድድሩ የተመረጡት አውራ ጎዳናዎች ሜዳማ መሆናቸውና አቀበትና ቁልቁለት ስላልበዛባቸው ለአትሌቶች የተመቹ ነበሩ፡፡ የአየሩ ሁኔታ ግን በሙቀት ሳቢያ ትንሽ አስቸጋሪ ስለነበር የውድድሩ አዘጋጆች ማራቶኑ በማለዳ እንዲካሄድ አድርገዋል፡፡ የማራቶን ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ ተዘጋጅቶ፣ በአማረ ሁኔታ ተስተናግዶ እና በሰለማዊና በአስደናቂ የውድድር መንፈስ ታጅቦ መጠናቀቁን አቶ ኤርምያስ አየለ ይገልፃል፡፡ ስኬታማ አጀማመር እንዳደረግን ያረጋገጥነው ሐዋሣ ከተማ ለማራቶን የምትመች መሆኗን ስላመለከትን በርካታ ተሳታፊዎች ከውጭ መጥተው በመወዳደራቸው፤ ሁሉም ተሳታፊዎች በማራቶኑ የተሰማቸውን እርካታ በ99 በመቶ በመግለፃቸው፤ የማራቶን ርቀቱን በ7 ሰዓት ጨርሶ የገባ ተወዳዳሪ እንኳን ሩጫውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደተደሰተበት ማሳወቁ እንዲሁም በአጠቃላይ ክንውኑ ስፖርትና ቱሪዝምን በማስተሳሰር በታየበት ውጤት እንደነበርም አብራርቷል፡፡
በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን እና በ5ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው እና በግማሽ ማራቶን ውድድር ለመሳተፍ ከውጭ አገር የመጡ ስፖርተኞች ብዛት እስከ 150 መድረሳቸው መሆኑ ለውድድሩ ጥሩ አጀማመር መገለጫ የሚሆን ነው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ፤ ከእነዚህ የውጭ አገር ተሳታፊዎች 50ዎቹ በማራቶን እንዲሁም 32 ያህል በግማሽ ማራቶን በመወዳደር ደስተኞች ናቸው ብሏል። የማራቶን ውድድሩ ከተዘጋጀባቸው አላማዎች ዋንኛው ለአገር ውስጥ አትሌቶች የውድድር እድል ለመፍጠር ነው፤ በውድድሩ ላይ ከ40 በላይ ክለቦች አትሌቶቻቸውን አሳትፈዋል፤ የግል ተወዳዳሪዎች ምቹ መስፈርት በማውጣት እንዲካፈሉ ተደረጓል ማራኪ የገንዘብ ሽልማት በማቅረብም ለውድድሩ ትኩረት ተፈጥራል፡፡ በውድድሩ ለሚሳተፉ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በሽልማት እና በስጦታ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር መሰጠቱን የገለፀው አቶ ኤርሚያስ፤ በወንዶች የማራቶን ርቀቱን ከ2 ሰዓት 12 ደቂቃ በታች ለሚገባ 100ሺ ብር እንዲሁም በሴቶች 2 ሰዓት ከ30 ደቂቃ በታች ለምትገባ 100ሺ ብር የቦነስ ሽልማት ቀርቦ ነበር ብሏል፡፡ በውድድሩ ላይ ያሸነፉ አትሌቶች አዘጋጆቹ ምርጥ ሰዓት ያላቸውን አትሌቶች አብዝተው ቢያሳትፉ እና አሯሯጮችን ቢመድቡ የተሻለ ነበር በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ በሌላው የዓለም ክፍል አትሌቶችን ለተሳትፎ በመክፈል እና የሚከፈላቸውን አሯሯጮች በመቅጠር ይሰራል። በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በዚህ መንገድ የመስራት እቅድ ያልበረን ኢትዮጵያ የሯጮች አገር እንደመሆኗ ጥሩ ተወዳዳሪ ማግኘት ስለማንቸገር ነው ያለው አቶ ኤርሚያስ፤ በዚህ ውድድር ላይ ተሳትፈው እስከ 30ኛ ደረጃ የሚያገኙ አትሌቶች በሌላው አለም ጥሩ የማራቶን ተወዳዳሪ ሊሆኑ መቻላቸውን መታሰብ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡
የመጀመርያው አሸናፊ መሆኔ ትልቅ ታሪክ ነው
አትሌት ጉዲሳ ሸንተማ
ባለፈው ሰሞን አንደኛውን የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ከማሸነፉ በፊት አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ በትልልቅ የማራቶን ውድድሮች ሰፊ ዓለም አቀፍ ልምድም ነበረው፡፡ በ2006 እ.ኤአ በበርሊን ማራቶን ኃይሌለ ተከትሎ በመግባት በ2ኛ ደረጃ ሲያጠናቅቅ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ከ47 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ በመሸፈን ነበር፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ በፓሪስ ማራቶንና፣ በዱባይ ማራቶን ተወዳድሮ በተመሳሳይ 4ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ ማራቶኑን በጥሩ ሁኔታ በመቆጣጠር ተወዳድርያለሁ ብሎ ለስፖርት አድማስ የተናገረው አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ የኃይሌ ገ/ስለሴ ማራቶንን የመጀመርያው አሸናፊ መሆኔ ትልቅ ታሪክ ነው ሲል ተሳትፎውን ለሽልማት በመጓተት ሳይሆን፣ በኃይሌ መሰየሙንና እንደተምሳሌት ስለሚመለከተው በከፍተኛ ደስታ ተቀብሎታል፡፡ የመሮጫ ጐዳናው ዳገትና ቁልቁለት ያልበዛበት በመሆኑ ምቹ ነበር የሚለው አትሌት ጉዲሣ ፣ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ካደረግኳቸው የማራቶን ውድድሮች ጋር ሲነፃፀር ለየት የሚለው እና አስቸጋሪነቱ ከተማዋ ሞቃታማ በመሆኑ ብቻ ነው ብሏል፡፡ አሯሯጮች ቢኖሩ የተሻለ ሰዓት ማስመዝገብ ይቻል ነበር ያለው አትሌት ጉዲሣ ሸንተማ በቀጣይ እንዲስተካከል እጠብቃለሁ ብሏል፡፡ በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ሳሸንፍ ያስመዘገብኩት ሰዓት በሌሎች የዓለም አገራት ከሚካሄዱ ትልልቅ ማራቶኖች በአንዱ ቢሆን 2 ሰዓት 06 በታች እንደገባሁ የሚቆጠር ነውም ብሏል፡፡
በአገሬ ህዝብ ፊት ባደረግኩት ውድድር ተደስቻለሁ አትሌት አልማዝ ነገደ
በሴቶች ምድብ የመጀመርያው የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን አሸናፊ ለመሆን የበቃችው አትሌት አልማዝ ነገደ ናት፡፡ ርቀቱን በ2 ሰዓት ከ39 ደቂቃ ከ50 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ለመሸፈን ነው፡፡ በአገሬ ህዝብ ፊት ያደረግኩት ውድድር ነው ብላ ተደስታለች፡፡ አልማዝ ማራቶንን ለመጀመሪያ ጊዜ አምና የቡካሬስት ማራቶን በመሳተፍ ሲሆን አሸናፊ ነበረች፡፡ ዘንድሮ ደግሞ በአሜሪካ በተካሄዱ የግማሽ ማራቶን እና የጐዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ምርጥ ሰዓቶችን በማስመዝገብ ተሳክቶላታል፡፡
የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን አሸናፊነት ትልቅ መነቃቃት እንደፈጠረላት የተናገረችው አልማዝ፤ መሮጫው ጎዳና ሜዳማ እና አስፋልት መሆኑ ውድድሩን ደስ የሚል ውድድር አድርጐታል ብላለች ጥሩ ሰዓት ያላቸው አትሌቶች በብዛት አለመሳተፋቸውና አሯሯጭ አለመኖሩ የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ ለነበራት ፍላጎት ተፅእኖ የፈጠረ ነበር፡፡ ማራቶኑ በአገር ውስጥ መዘጋጀቱ ውድድር ለሚፈልጉ አትሌቶች ጥሩ እድል መሆኑን የገለፀችው አትሌት አልማዝ ነገደ፤ ተመሳሳይ የማራቶን ውድድሮች በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች በብዛት መካሄዳቸው ለተተኪ አትሌቶች ሰፊ የውድድር እድል ስለሚጠቅሙ ያስፈልጋሉ ብላለች፡፡ በሃዋሣው የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ተሳትፌ ያገኘሁት ውጤት በዓለም አቀፍ ውድድሮች ለመሳተፍ ይጠቅመኛልም ብላለች፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ወደ ሌላ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯል ሪቻርድ ኔሩካር
ታዋቂው እንግሊዛዊ አትሌት እና የአትሌቲክስ ባለሙያ ሪቻርድ ኔሩካር የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን ወደ ሌላ የእድገት ምዕራፍ አሸጋግሯል ይላል፡፡ ከዓመታት በፊት በታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅነት የሠራ ነው እና አሁን ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ አድርጎ ከተቋሙ ጋር መስራቱን የቀጠለው በኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ስኬታማነት ታላቁ ሩጫ ኢትዮጵያ በልምዱ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡ በማራቶን ውድድሩ 82 ተወዳዳሪዎች ከ16 የተለያዩ አገራት ለመምጣታቸው የአሜሪካው ሞራይ ማውንቴን ስፖርትስ ያደረገው እንቅስቃሴ ወሳኝ እንደነበር ሪቻርድ ኔሩካር፤ ተናግሯል፡፡ በማራቶን ውድድር በመሳተፍ የሚዝናኑ ስፖርተኞችን ከውጭ አገራት በማሰባሰብ የመጀመርያው ኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን ስኬታማ ነበር ያለው ሪቻርድ፣ የውድድሩ ድባብ ጥሩ እንደነበር፣ የትራፊክ ፖሊስ፣ የፖሊስ አባላትና የከተማው ህዝብ ለውድድሩ የተቃና ሂደት የሰጡት ትብብር የሚመሰገን ብሏል፡፡ ውድድሩን በቀጣይነት ለማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድ ተገኝቷል፡፡ የኃይሌ ገ/ስላሴ ማራቶን በማዘጋጀት ቱሪዝምንና ስፖርትን በማስተሳሰር ውጤታማ ለመሆን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለ ድርጅት ትልቁን የማራቶን ውድድር በማዘጋጀት የሚከብድ ነበር ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ ውድድሮችን በማዘጋጀት ያለውን የ13 ዓመታት ልምድ በመጠቀም ሰርቶ አቅሙን በመፈተሹ ወደፊትም በመላው ዓለም ከሚገኙ በአትሌቲክስ ውድድር አዘጋጅነት ከሚሰሩ ተቋማት እና ድርጅቶች ጋር በመተባበር ውድድሩን በየዓመቱ ለማካሄድ የሚያስችል አጀማመር ነው በማለት ለስፖርት አድማስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ሃዋሣ የማራቶን ውድድር ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ምናልባትም ብቸኛዋ ምቹ እና ተመራጭጥ ከተማ ናት ያለው ሪቻርድ ኔሩካር ወደፊት ምናልባትም ከ5 ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ሌላ የማራቶን ውድድር ለማዘጋጀት ይሞከራል ብሏል፡፡

ሴቶች በአለም ዙሪያ ጽንስን ማቋረጥ የጀመሩት እንዲህ እንደዛሬው በሳይንሳዊው መንገድ ሳይሆን በግላቸው የየራሳቸውን ጥረት በማድረግ እንደሆነ አንዳንድ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡ቀደም ባለው ጊዜ ሴቶች እርስ በእርሳቸው በመረዳዳት አንዱዋ የአንዱዋን ጽንስ ለማቋረጥ ባህላዊ ዘዴዎችን በህገወጥ መንገድ ሲጠቀሙ እ.ኤ.አ እስከ 1800/ድረስ እንደቀጠሉ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡ ነገር ግን በጊዜው ጽዳቱ እና ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ጽንስን የማቋረጥ ሂደት ብዙ ሴቶችን ለህልፈት ይዳርግ ስለነበር በአንዳንድ የአለማችን ክፍሎች ትኩረትን አግኝቶ ህገወጥ ጽንስን ማቋረጥ እንዲቆም የተቻለውን ያህል ጥረት ተደርጎ አል፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደየሀገራቱ አሰራር በተለያየ ጊዜ ቢሆንም በአብዛኛው የአለማችን ክፍሎች ጽንስን ማቋረጥ በህጋዊ መንገድ እንዲሆን ተደርጎአል፡፡ ኢትዮጵያም በ1996 ዓ/ም ጽንስን ማቋረጥ በህግ እንዲደገፍ የራስዋን ድንጋጌ አውጥታለች።
African network for medical abortion የሚባል ድርጅት በአሁኑ ወቅት በጽንስ ማቋረጥ ዙሪያ በአፍሪካ በጋራ ስራ ለመስራት የተቋቋመ ሲሆን የዚህ ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪም ዶ/ር እስክንድር ከበደ በአ.አ. ዩኒቨርሲቲ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ከፍል ትምህርት ክፍል ሀላፊ ናቸው፡፡ ዶ/ር እስክንድር ከበደ የኢሶግ ቦርድ ዋና ጸሐፊና የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
African network for medical abortion (ANMA) የሚባለው ድርጅት ምን የሚሰራ ነው?
Medical Abortion ማለት ምን ማለት ነው?
ከሚሉት በመነሳት ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ዶ/ር እስክንድር ከበደ ማብራሪያቸውን ለዚህ አምድ ሰጥተውል፡፡
ጥ/ Medical Abortion (ሜዲካል አቦርሽን) ሲባል ምንን የሚያመለክት ነው?
መ/ Medical Abortion ሜዲካል አቦርሽን ማለት ውርጃ በህጋዊው መንገድ ጥራቱን እና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ መፈጽም ካለበት ቀደም ባለው ጊዜ በተለያዩ የህክምና መሳሪያዎች ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት ወደ መድሀኒት በመለወጥ ጽንስን ማቋረጥ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ልጅ ራቅ ካለው ዘመን ጀምሮ መድሀኒትን ለጽንስ ማቋረጫነት መጠቀም የጀመረ ቢሆንም እንኩዋን ውጤታማ በሆነና በተሳካ መንገድ በህክምና ባለሙያዎች በመሰጠት ስራ ላይ የዋለው ከሀያ አምስት አመታት ወዲህ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ውጤታማ የሆነው መድሀኒትም የተገኘው በፈረንሳይ አገር ተመራማሪዎች ሲሆን እሱም እ.ኤ.አ በ1970 እና 80/ዎቹ አካባቢ የተሰራ ነው፡፡ በሕክምናው ዘርፍም የመጀመሪያው ሙከራ የተደረገው በጄኔቭ እ.ኤ.አ በ1981 ዓ/ም ነው፡፡ በ1988 ፈረንሳይ መድሀኒቱን ፈቃድ በመስጠት የመጀመሪያ ሀገር በመሆን ጥቅም ላይ ያዋለች ሲሆን ከዚያም በተለያዩ ሀገራት እየተስፋፋ መጥቶ በኢትዮጵያም በ2008/ ዓ/ም ፈቃድ አግኝቶአል። በአሁኑ ጊዜም ከ40/የሚበልጡ ሀገሮች መድሀኒቱን የሚጠቀሙበት ሲሆን የአለም የጤና ድርጅትም እ.ኤ.አ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ መድሀኒቶቹን ለጽንስ ማቋረጫነት እንዲያገለግሉ ሀሳብ ያጋራል፡፡ መድሀኒቶቹ Misopostol and mifepristone በመባል ይታወቃሉ፡፡
ጥ/ African network for medical abortion … ANMA ምን የሚሰራ ድርጅት ነው?
መ/ African network for medical abortion በምህጻረ ቃሉ ANMA ¾ሚባለው እ.ኤ.አ በ2010/ዓ/ም ሊዝበን ላይ በተደረገ አለምአቀፍ ስብሰባ ጽንስን በማቅዋረጥ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች በተለየ መልኩ የሜዲካልን አቦርሽን በስፋት ስራ ላይ እንዲውል በማስተማር በኩል እንዲሰራ ለተቋቋመው ድርጅት አካል የሆነ በአፍሪካ የተቁዋቁዋመ ድርጅት ነው፡፡ ANMA የመጀመሪያው ስራው ያደረገው በአለም የጤና ድርጅት የተነደፈው መመሪያ ላይ በመሳተፍ ሐኪሞችን በማሰልጠን እንዲሁም በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ሀገራት ሜዲካል አቦርሽንን እንደአማራጭ እንዲጠቀሙበት ማስተዋወቅና መድሀ ኒቱም ፈቃድ ተሰጥቶት እንዲመዘገብና በየሀገሩም ስራ ላይ እንዲውል ማድረግ ነው፡፡
ጥ/ በኢትዮጵያ በANMA አሰራር ምን ለማድረግ ታስቦአል?
መ/ በኢትዮጵያ አስቀድሞውኑም ጽንስን በማቋረጥ ረገድ ህግን ከማውጣት እና ከመተግበር ጀምሮ ብዙ የተሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጽንስን ከማቋረጥ ጋር በተያያዘ ይከሰቱ የነበሩ የህይወትም ሆነ የአካል ጉዳቶች በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ ነገር ገን አሁንም ሙሉ በሙሉ ችግሩ ተቀርፎአል ማለት ስለማይቻል በቀጣይነት የሚሰሩ ስራዎች በእቅድ ተይዘዋል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በመቀጠል ለማድረግ የታሰበው የህክምና ባለሙያዎችን በአዲሱ የአለም የጤና ድርጅት መመሪያ ጋይድ መሰረት ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር ጋር በመተባበር ማሰልጠን ነው፡፡ በሁለተኛም ደረጃ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ የተለያዩ ተቋማት የስራ መደራረብ እንዳይኖር ወይንም አንዱ የሚ ሰራውን ሌላው እንዳይደግመው እና ህብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር እንዲኖር ለማስተዋወቅ ታስቦአል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሜዲካል አቦርሽን ላይ ያልታዩ ወይንም ያልታወቁ ነገሮች ካሉ ለማሳየት የሚያስችል ጥናት ማድረግ ከእቅዶች መካከል ናቸው፡፡
ጥ/ Medical Abortion ሜዲካል አቦርሽን በሀገራችን ስራ ላይ ውሎአልን?
መ/ Medical Abortion (ሜዲካል አቦርሽን በሀገራችን እ.ኤ.አ ከ2008/ዓ/ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለ አሰራር ነው፡፡ በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የሚሰሩ ድርጅቶች በህግ ለተፈቀደ የውርጃ አገልግሎት እንዲሁም በመንግስት የጤና ተቀዋማት ውስጥ በመድሀኒት መጠቀምን ተግ ባራዊ እያደረጉት ነው፡፡ እንዲያውም በዘርፉ እንደ አንድ አስገራሚ ሁኔታ የታየው ተጠ ቃሚዎች ውርጃን በሕክምና መሳሪያ ከሚሰራላቸው ይልቅ በመድሀኒት እንዲሆን በአብ ዛኛው ምርጫ ቸው በማድረጋቸው ነው። በአለፈው አመት በተደረገው ጥናት እንደተረ ጋገጠው በአሁኑ ሰአት ውርጃ እንዲሰራላቸው ከሚመጡ ሴቶች የምክር አገል ግሎት በሚሰጣቸው ጊዜ በመድ ሀኒቱ መጠቀምን የሚሹት ወደ 70% ደርሰዋል። ስለሆነም ውርጃን በመሳሪያ አማካ ኝነት መስራትን በጣም ቀንሶታል፡፡ በእርግጥ አን ዳንድ ቦታ ዎች የአቅርቦት እጥረት የሚታይ ሲሆን ይህም በጊዜ ሂደት ከሚሻሻሉት መካከል ነው፡፡
ጥ/ በመድሀኒት አማካኝነት ጽንስን ማቋረጥ እስከ ስንተኛው ወር ድረስ ይቻላል?
መ/ መድሀኒቶቹ Misopostol and mifepristone የተባሉ ሁለት መድሀኒቶች ናቸው፡፡ ሁለቱን መድሀኒቶች በአንድ ላይ በምንጠቀምበት ጊዜ እርግዝናው ከመጨረሻው የወር አበባ እስከ 49/ ቀን ወይንም እስከ 7/ ሳምንት ድረስ ከሆነ 95% ለሚሆነ ሴቶች ውጤታማ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህንን መድሀኒት የወሰዱ ሴቶች ወደ ሆስፒታልም ሳይመለሱ ልክ እንደየወር አበባ ቀስ በቀስ እየተቆጣጠሩ ሊወገድ ይችላል፡፡ ነገር ግን 5% የሚሆኑት ሴቶች ውርጃው በትክክል ሂደቱን ላያሟላና በማህጸን ውስጥ ሊቀር ስለሚችል በተቀ ጠሩበት ቀን ወደ ጤና ባለሙያው በመቅረብ በመሳሪያ የታገዘ አገልግሎትን እንዲያገኙ ግድ ይሆናል፡፡
ጥ/ ከ49/ ቀን ወይንም ከሰባት ሳምንት በሁዋላስ ውርጃው በምን መልክ ይሆናል?
መ/ በሀገራችን ህግ መሰረት ውርጃ የሚባለው እስከ 28ኛው ሳምንት ድረስ ነው፡፡ ነገር ግን ቀኑ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ተጉዋዳኝ ችግሮቹ እየበዙ ስለሚሄዱ ውርጃን ማካሄድ አይመከርም፡፡ ሆኖም ባልታወቁ ምክንያቶች ችግር ደርሶ ከሆነ ፣ወይንም በተፈጥሮአዊ ሁኔታ ውርጃውን ማድረግ ግድ ከሆነ፣ ህጉ እየፈቀደላቸው አገልግሎቱን ሳያገኙ ቀርተው ከሆነ በትልልቅ ሆስፒታሎች እና ስልጠናውን በወሰዱ ሐኪሞች አማካ ኝነት ብቻ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡ ከዚህ ውጭ የእርግዝናወ ጊዜ ከፍ ያለ ጽንስና ለማቋረጥ በክሊኒኮች ወይንም በጤና ጣቢያዎች አገልግሎቱ ሊሰጥ አይችልም፡፡ በእርግጥ Misopostol and mifepristone የተባሉት መድሀኒቶች በዚህ ደረጃ ላሉ እርግዝናዎች ለጊዜው አገልግሎት ባይ ሰጡም አንዳንድ መረጃዎች እንደሚገልጹት ግን በመሳሪያ ከሚሰጠው አገልግሎት ይልቅ በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ነው፡፡ በአጠቃላይም በአፍሪካው ኔትወርክ አማካኝነት ለመስራት የታሰበው በተለያዩ ቦታዎች በተንጠባጠበ እና በተደጋጋሚ የሚሰሩትን ስራ ዎች በተቀናጀ መልክ ከፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስር እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በአንድነት በትብብር ለመስራት መድረኩን ለመፍ ጠር ነው፡፡ በዚህም ተጠቃሚው ህብረተሰብ የሰመረ አገልግሎትን ያገኛል የሚል እምነት አለን፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ፣አላን ጉትማቸር እና አለምአቀፉ የቤተሰብ መምሪያ እኤአ/ በ2009 ዓ/ም ያወጡት መረጃ ጽንስን ማቁዋረጥ በአለማችን ምን ገጽታ እንዳለው ያሳያል፡፡
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ምክንያት በየአመቱ ከሰባ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ የሚደርሱ እናቶች በአለም ይሞታሉ፡፡
ከጠቅላላው የእናቶች ሞት ከ13-20% የሚሆኑት የሚከሰቱት በህገወጥ ጽንስ ማቋረጥ ነው፡፡
በአለም ከሚፈጸሙት ጽንስ ማቋረጦች 1/3ኛው በህገወጥ መንገድ ነው፡፡
በየአመቱ ሀያ ሚሊዮን ህገወጥ ጽንስ ማቋረጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ይፈጸማል፡፡ 90 ሕገወጥ ጽንስ ማቋረጥ የሚተገበረው ባልለሙት አገራት ነው፡፡

Published in ላንተና ላንቺ

በአውሮፓ እና በአሜሪካ ነዋሪ በሆኑ ታዋቂ የቀድሞ እና የአሁን ዘመን ተጨዋቾች ቡድኖች በሚደረጉ የወዳጅነት ጨዋታዎች ገቢ ማሰባሰቢያ ልዩ የእግር ኳስ ፌስቲቫል መዘጋጀቱ ታወቀ፡፡ ነዋሪነታቸውን በቦስተን ያደረጉት እና በአዲስ አበባ የተጨዋቾችና ደጋፊዎች ማህበር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ዳዊት ጌታቸው ለስፖርት አድማስ እንደገለፁት የእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ጥር 11 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚካሄድ ይሆናል፡፡ ፌስቲቫሉ በአሜሪካ እና በአውሮፓ ካሉት የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበራት ጋር በትብብር በመስራት ተዘጋጅቷል፡፡ ለእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ወደ አዲስ አበባ ከሚመጡት ታዋቂ የቀድሞ ተጨዋቾች መካከል እነ ካሳዬ አራጌ፤ አብዲ ሰኢድ፤ አቦነህ እና አብርሃም ብስራት ይገኙበታል፡፡ የእግር ኳስ ፌስቲቫሉ በችግር ላይ ያሉ እና የተጎዱ ተጨዋቾችን ለመርዳት፤ የታመሙትን ለማሳከም እና የእግር ኳስ ተጨዋቾች ስፖርቱን በጡረታ ከመለየታቸው በፊት የተሻለ ህይወት እንዲኖራቸው የማስተማር ዓላማዎችን በማነገብ እንደጠንቀሳቀስም ተገልጿል፡፡ ከእግር ኳስ ፌስቲቫሉ ጋር በተያያዘ በሚገኝ የስታድዬም ገቢ፣ ከተለያዩ ኩባንያዎች በሚገኝ የስፖንሰሺፕ ድጋፍ እንዲሁም ከማህበራቱ አባላት አመታዊ መዋጮ በሚገኝ አስተዋፅኦ የተጨዋቾች መረዳጃ ፋውንዴሽን ለመመስረት እንደታሰበም አቶ ዳዊት ጌታቸው ለስፖርት አድማስ ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ፤ በአውሮፓ እና በአዲስ አበባ ያሉት የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበራት በሚያደርጓቸው ትብብሮች ባለፉት ጊዜያት ለቀድሞ ተጨዋቾች የገንዘብ እርዳታዎችን፤ የህክምና ድጋፎች እና ለተሻለ ህይወት የሚያበቁ እገዛዎች በማከናወን ሲሰራ መቆየቱን አቶ ዳዊት ጌታቸው ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት በፊት ኬንያ ውስጥ በከፋ ችግር ላይ የነበረው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ተጨዋች አብዱልከሪም ወደ አሜሪካ በመውሰድ በተሻለ ህይወት ቀሪ እድሜዉን እንዲያሳልፍ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተጨዋች እና ምክትል አሰልጣኝ የነበረውን አስራት አዱኛ ከአውሮፓው ማህበር ጋር በመተባበር ወደ ስዊዘርላንድ ተወስዶ በተሻለ ኑሮ ውስጥ ገብቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ አንዳንድ ተጨዋቾች የህክምና ድጋፎች እና የገንዘብ ድግግሞሽ ተከናውነዋል፡፡ በተለይ የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የነበረችው ብዙአየሁ ጀምበሩ አስቀድሞ ለክራንች ዳርጓት ከነበረውን ጉዳት በቂ ህክምና አግኝታ አገግማለች፡፡ በተመሳሳይ ሰለሞን አወቀ፣ ሰለሞን ገ/አማኑኤል እና ሲሳይ ተሰማ ለተባሉ የቀድሞ ተጨዋቾች ተመሳሳይ የህክምና ድጋፎችም መደረጉን አቶ ዳዊት ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
አዲሱን የአዲስ አበባ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበርን የቀድሞ የፖሊስ እና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች የሆኑት ንጉሴ ገብሬ በፕሬዝዳትነት እየመሩት ናቸው፡፡ በዚሁ ማህበር የቀድሞ የምድር ጦር ክለብ አጥቂ መስመር ተሰላፊ በሃብቱ ገብረማርያም በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሁም አቶ ተስፋዬ ከበደ በዋና ፀሃፊነት እየሰሩ ሲሆን የስራ አስፈፃሚ አባል በመሆን ቀድሞ የመድን ክለብ ተጨዋች የሆኑት ጌቱ መልካ እንዲሁም የአየር መንገድ ክለብ ተጨዋች የነበሩት አቶ ፍትሃነገስት በርሄ በህዝብ ግንኙነት ሃላፊነት ያገለግሉበታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በአሜሪካ ያለው የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበር በቅርቡ በአዲስ የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ እንደተዋቀረ ታውቋል፡፡ አቶ ዳዊት አስመላሽ በአሜሪካው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በተሰጣቸው ሃላፊነት መሰረት ምርጫውን በአግባቡ እንዲከናወን ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ዳዊት ጌታቸው ናቸው፡፡ በአሜሪካ ያለው የእግር ኳስ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ማህበርን ለመምራት በተመረጠው አዲስ ኮሚቴ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድንና የክለብ ተጨዋች አቶ አብዲ ሰኢድ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ የእርሻ ሰብል ክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች የሆኑት መንግስቱ ሁሴን በምክትል ፕሬዝዳንትነት፤ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለረጅም ጊዜ በግብ ጠባቂነት የተጫወተው አቶ ታደሰ ተክለፃዲቅ በዋና ፀሃፊነት እየመሩት ናቸው፡፡

“ሁሉም አይስላንዳዊ መጽሐፍ ይወልዳል”
የሴቶች የፖለቲካ ፓርቲ ያላት ብቸኛ አገር ናት
በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ጥንካሬ ከዓለም ሁለተኛ
በአንድ ፓርቲ ተመርታ አታውቅም - በጥምር ፓርቲዎች እንጂ

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ “አይስላንድ የደራሲያን ሀገር” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሁፍ፣ ዋናውን ርዕሰ ጉዳይ ከማስረዳቴ በፊት ሀገሪቱን በሚገባ ለማወቅም ሆነ ለጠቅላላ እውቀት ይረዳሉ ያልኳቸውን የተለያዩ ጉዳዮች አቅርቤአለሁ፡፡ ይህ የዛሬው ጽሁፍ ካለፈው ሳምንት የቀጠለና የማጠቃለያ ጽሁፍ ነው፡፡
አይስላንድን በተመለከተ አለም አቀፉ ሚዲያ ሊያወራው የሚችለው ክፉም ሆነ በጐ ዜና እምብዛም አግኝቶ አያውቅም፡፡ ለአለም አቀፉ ሚዲያም ሆነ ለአብዛኛው የአለም ህዝብ አይስላንድ በቅዝቅዜና በበረዶ ግግር መካከል የምታንቀላፋ አንዲት ለሰሜን ዋልታ የቀረበች አውሮፓዊት ሀገር ማለት ናት፡፡ ከተጫናት ቅዝቃዜ መካከል አውጥቶና ላዩዋ ላይ የተጋገረውን በረዶ አራግፎ፣ በጥሞና ላያት ግን አይስላንድ የበርካታ አስገራሚ ታሪኮች ባለቤት የሆነች ሀገር ናት፡፡
የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚዎች፤ “የአለማችን የፖለቲካ መድረክ እስከዛሬም ድረስ እጅግ በአብዛኛው ወንዶች በመሪ ተዋናይነት የሚተውኑበት መድረክ ነው” ይላሉ፡፡ አይስላንዳውያንን ግን በዚህ ሀሳብ ጨርሶ አይስማሙም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አይስላንዳውያን ባይስማሙ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን ቢባል? በአለማችን ውስጥ በሴቶች የተመሠረቱና በሴቶች የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉዋት ብቸኛዋ ሀገር አይስላንድ ብቻ ናት፡፡ ዛሬ በምድረ አይስላንድ በማንኛውም አይነትና ሁኔታ የሚመሠረቱ ፓርቲዎች፣ አርባ በመቶ የሚሆነውን ኮታቸውን ለሴቶች የመመደብ ግዴታ አለባቸው፡፡ እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም አይስላንዳውያን ባካሄዱት ብሔራዊ ምርጫ፣ ወይዘሮ ቪግዲስ ፊንቦጋዶቲርን ፕሬዚዳንታቸው አድርገው መርጠዋቸዋል፡፡ በዚህም በአለም በቀጥተኛ ህዝባዊ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ፕሬዚዳንት የመረጡ ዜጐችና ሀገር ተብለው በአለም የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለመመዝገብ በቅተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም ዮሀና ሲጐሮአርዶቲር፤ የአይስላንድ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን ጨበጡ፡፡ በዚህም አይስላንዳውያን ተጨማሪ የፖለቲካ ታሪክ ለመስራት በቁ፡፡ አይስላንድ ግብረ-ሠዶማዊነቷን በግልጽ ያወጀችን ፖለቲከኛ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጋ የሾመች በአለም የመጀመሪያዋ ሀገር ሆነች፡፡ በ2011 ዓ.ም የወጣ አለም አቀፍ ጥናት፤ በዲሞክራሲ ተቋማት ጥንካሬ አይስላንድን ከመላው አለም በሁለተኛ ደረጃ ሲያስቀምጣት፤ በመንግስቷ ግልጽነት ደግሞ ከአለም ሀገራት በአስራ ሶስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷን መስክሮላታል፡፡
ምርጫን በተመለከተ ጨርሶ ቀልድ የማያውቁ ዜጐች በድፍን አለም ውስጥ አሉ ከተባሉ አይስላንዳውያን ብቻ ናቸው፡፡ ብሔራዊ ምርጫ ሲደረግ የአይስላንዳውያን ዝቅተኛው ተሳትፎ በአማካይ 81.4 በመቶ ነው፡፡ በድፍን አለሙ እግር እስኪቀጥን ድረስ ሲያስሱ ቢኖሩ፤ እንደ አይስላንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሉ ከፍተኛ የህዝብ አመኔታ ያላቸው ፓርቲዎች ማግኘት ጨርሶ አይቻልም፡፡
አይስላንድ በሪፐብሊክነት ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ በተካሄዱት ህዝባዊ ምርጫዎች አንድም የፖለቲካ ፓርቲ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ ብቻውን መንግስት ለመመስረት አለመቻሉ ከአይስላንድ አስገራሚ የፖለቲካ ታሪኮች አንደኛው ነው፡፡ እስከዛሬም ድረስ አይስላንድ የምትገዛው ወይም የምትተዳደረው በተለያዩ ፓርቲዎች በሚቋቋሙ የጥምር መንግስት ነው፡፡
የአለምን የመከላከያ ሠራዊት ሁኔታ የሚከታተሉ ባለሙያዎች፤ ስለ አይስላንድ የመከላከያ ሰራዊት ሁኔታ የሚያወሩት በመገረም ነው፡፡ አይስላንድ ኔቶ እየተባለ በአጭር ስሙ የሚታወቀው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገር ናት፡፡ ይህ ጉዳይ በየትኛውም መመዘኛ ቢሆን ምንም የሚያስገርም ነገር የለውም፡፡ አስገራሚው ጉዳይ አይስላንድ የኔቶ አባል ሀገር የሆነችው አንድ መቶ እንኳ የማይሞሉ ቀላል የነፍስ ወከፍ መሳሪያ የታጠቁ ጠረፍ ጠባቂዎች በስተቀር አንድም የመከላከያ ጦር ሰራዊት ሳይኖራት መሆኑ ነው፡፡
ይህን ወታደራዊ ሁኔታ በማጤን የአይስላንድ የአየር ክልል “ማርያም ትጠብቀው!” ተብሎ የተተወ ነው ብላችሁ ልትገምቱ ትችላላችሁ፡፡ እውነታው ግን እንደዚህ አይደለም፡፡ የኔቶ አባል ሀገራት የጦር ሀይል የወራ ተራ እየገቡ የአይስላንድን የአየር ክልል ይጠብቃሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የአይስላንድን የአየር ክልል የሚጠብቀው የጣሊያን የአየር ሀይል ነው፡፡
የአለም አቀፍ ፖለቲካ ነገር ሲነሳ አይስላንዳውያን በ1986 ዓ.ም በዋና ከተማቸው ሬይካቪክ ታላቅ ጉባኤ በማዘጋጀት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገንና የሶቪየት ህብረቱ መሪ ሚካይል ጐርቫቾቭ የኒውክሊየር ጦር መሳሪያ ስምምነት እንዲፈራረሙ በማድረግ፣ ለአለም ሰላም የበኩላቸውን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን በኩራት ይናገራሉ፡፡
የአለም ሰላምን በተመለከተ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች፤ አይስላንድ ከአለም ሀገራት መካከል እጅግ ዝቅተኛ ወንጀል የሚፈፀምባት፣ እጅግ ከፍተኛ የፖለቲካና ማህበራዊ መረጋጋት ያለባት ሰላማዊ ሀገር እንደሆነች ይጠቁማሉ፡፡
ኢኮኖሚዋን በተመለከተ ያላት ታሪክም ጉደኛ ነው፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በፊት አይስላንድ ከአውሮፓ እጅግ ደሀ ሀገራት አንዷ ነበረች፡፡ አሁን ይሄ እንደ ተረት ወይም እንደ ጥንት ታሪክ የሚነገር ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬ በአለም እጅግ ፍሬያማና ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ አመታዊ ገቢ አላቸው ከሚባሉት ሀገራት አንዷ አይስላንድ ናት፡፡ የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከሁለት አመት በፊት ባወጣው ሪፖርት፤ የአይስላንድ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 54ሺ858 ዶላር መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡
እንግዲህ ልብ በሉ፡፡ እስካሁን የቃኘነው አይስላንድ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በወታደራዊና፣ በአለም አቀፍ ግንኙነት ካሏት አሪፍ አሪፍ ታሪኮች በመጠኑ የተጨለፈ ነው፡፡ ከአገሪቱ ታሪኮች ከሁሉም የሚልቀውና አለምን ምንጊዜም አጀብ የሚያሰኘው ታሪኳ ግን በስነ ጽሁፍ ረገድ ያላት ታሪክ ነው፡፡ ይሄን ታሪኳን በአንድ አረፍተ ነገር መግለጽ ካስፈለገ “አይስላንድ ድንቅ የስነ ጽሁፍና የደራሲያን ሀገር!”
በየትኛውም አይነት አጋጣሚም ሆነ ምክንያት ወደ አይስላንድ እግሩ የጣለውና በጣት ከሚቆጠሩ አይስላንዳውያን ጋር “እንዴት ነህ? እንዴት ነሽ?” መባባል የቻለ ማንኛውም ሰው፤ በምንም ተአምር ቢሆን ሊያጋጥመው የማይችለው ሰው ቢኖር ደራሲ አይስላንዳዊ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከቶ እንዴት ይሆናል፣ ብትሉ ነገሩ ቀላል ነው፡፡ ከአስር አይስላንዳውያን ውስጥ ቢያንስ አንዱ ወይም አንዷ መጽሐፍ ጽፎ ወይም ጽፋ ያሳተመ ወይም ያሳተመች ስለሆነ ነው፡፡
በዋና ከተማዋ ሬዳካቪክም ሆነ በሌሎች የአይስላንድ ከተሞች ዞር ዞር ብትሉ ቆጥራችሁ የማትዘልቁት የመጽሀፍት መሸጫ ሱቆችና አሳታሚ ኩባንያዎችን ታገኛላችሁ፡፡ በእነዚህ የመጽሀፍት መሸጫ ሱቆችና አሳታሚ ኩባንያዎች ግድግዳ ላይ ለአፍታ ያህል አይናችሁን ጣል ካደረጋችሁ ደግሞ በአይስላንዲክ ቋንቋ “አድ ጋንጋ ሜድ ቡክ አይ ማጋነም!” የሚል ጥቅስ በብዛት ተጽፎ ታገኛላችሁ፡፡ ትርጉሙ “ሁሉም አይስላንዳዊ መጽሀፍ ይወልዳል፡፡” ወይም በሁሉም አይስላንዳዊ ሆድ ውስጥ መጽሀፍ አለ፡፡” ማለት ነው፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ይህን የአይስላንዳውያን ጥቅስ ማንም አሌ ብሎ ሊሞግተው የማይችለው ሀቅ ነው፡፡ ከጠቅላላው የአይስላንድ ዜጐች ውስጥ አስር በመቶ የሚሆኑት በዘመናቸው ቢያንስ አንድ መጽሀፍ ጽፈው ያሳተሙ ናቸው፡፡ በነፍስ ወከፍ ሲሠላ ከአይስላንዳውያን በስተቀር በርካታ መጽሀፎችን መፃፍና ማሳተም የቻሉ የሌላ ሀገር ዜጐችን ለሞት መድሀኒት ብላችሁ እንኳ በድፍን አለሙ ዞራችሁ ብትፈልጉ እስከወዲያኛው አታገኙም፡፡ መጽሀፎችን ገዝቶ በማንበብ ረገድም አይስላንዳውያን በመላው አለም አቻ የላቸውም፡፡ የስነ ጽሁፍ ህትመቶችን ወደ ሀገራቸው በማስመጣትም አይስላንዳውያን የአለም ቁንጮ ናቸው፡፡
አይስላንዳውያን ደራሲያን ብቻ አይደሉም። የሌሎች ሀገራት ደራሲያንን የስነጽሁፍ ስራዎች በመተርጐም በኩልም የሚስተካከላቸው አንድ ሀገር እንኳ አለማችን ማግኘት አልቻለችም። በነፍስ ወከፍ ሲሰላ እጅግ ከፍተኛ የመጽሀፍ መሸጫ መደብር በመያዝ አይስላንድን በልጦ የአለም ቁንጮ መሆን የቻለ አንድም ሌላ ሀገር እስከዛሬ ድረስ ሊገኝ አልቻለም፡፡
በሬይካቪክ ከተሞች ባሉ የህዝብ መናፈሻ ቦታዎች ውስጥ ያሉ ሁሉም መቀመጫዎች ስማርት ፎን ያላቸው ሰዎች የተለያዩ የመጽሀፍት ትረካዎችን ማዳመጥ እንዲችሉ ተደርገው በእውቅ የተሰሩ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ዩኔስኮ ከተማዋን ሬይካቪክን “የስነጽሁፍ ከተማ” ብሎ ለመሰየም በእጩነት መዝግቦ ይዟታል፡፡
በአይስላንድ እንግዳ የሆነና ፀጉሩን ለመቆረጥ ወደ ፀጉር ቤት ጐራ ያለ ማንኛውም ሰው በመጀመሪያም ሆነ በመጨረሻ የሚቀረብለት ጥያቄ፣ እንደኛ ሀገር ፀጉር ቤቶች የአርሴናል ወይም የማንቸስተር ጉዳይ ሳይሆን ስለ አነበባቸው መጽሀፍቶችና በሀገሩ ስለታተሙ አዳዲስ መጽሀፍቶች ብቻ ነው፡፡
አይስላንድ በአለም ደረጃ የታወቁ ደራሲያንን ማፍራት ችላለች፡፡ ከእነዚህ እውቅ አይስላንዳዊ ደራሲዎች ውስጥ በ1955 ዓ.ም በስነጽሁፍ የኖቤል ሽልማት ያገኘው ደራሲ ሀልዶር ላክስነስ ይገኝበታል፡፡ ሲቲን ስቲይናር የተባለው አይስላንዳዊ ደግሞ የሀያኛው ክፍለ ዘመንን መቆጣጠር የቻለ የዘመናዊ ቅኔ ባላባት ነበር፡፡
በመጨረሻ ጉዳያችንን ለማጠቃለል አንድ ጥያቄ እናቅርብ:- “አይስላንድ ከሌሎች ሀገራት በተለየ ዘመን የጠገበ የስነጽሁፍ ታሪክ ባለቤትና የአለማችን ቁንጮ የስነጽሁፍና የደራሲያን ሀገር ልትሆን የቻለችበት ምክንያት ለመሆኑ ምንድን ነው?” ወጣቱ አይስላንዳዊ ቢዬን ሲጉርድሰን ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ፤ “ሀገራችን አይስላንድ የታሪክ ተራኪዎች ሀገር ናት፡፡ ሲመሽና ቅዝቃዜው ሲበረታ ሰብሰብ ብለን ታሪክ ከመተረክና ሲተረክ ከማዳመጥ በቀር ሌላ ስራ እኮ የለንም!” ለጊዜው ከዚህ የተሻለ መልስ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡

Published in ከአለም ዙሪያ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን “መጽሐፈ ቅዳሴ” ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተተረጎመ፡፡ ለብዙ ዘመናት “መጽሐፈ ቅዳሴ”ን በግእዝ እና በአማርኛ ስትጠቀምበት የቆየችው ቤተክርስትያኗ፤መፅሃፉን በኦሮምኛ ማስተርጎም የጀመረችው በ1999 ዓ.ም እንደሆነ ታውቋል፡፡ የመጽሐፉ መተርጎም በኦሮሚያ ክልል ላሉ አብያተ ክርስትያናት በኦሮምኛ ለመቀደስ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡ የቤተክርስትያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ እያካሄደ ባለው የጥቅምት ምልዐተ ጉባዔው ትኩረት ከሰጣቸው ዋና አጀንዳዎቹ አንዱ ስብከተ ወንጌልን ማዳረስ እንደሆነ የገለፁት ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ የመጽሐፉ  ሕትመት እንዲቀላጠፍ ትዕዛዝ እንዳስተላለፉም  ለማወቅ ተችሏል፡፡ “መጫፈ ቂዳሴ” በሚል ርዕስ የተተረጎመው የኦሮምኛ መጽሐፉ፤በቅርቡ ዝግጅቱን የተቀላቀሉትን ብፁዕ አቡነ ዮሴፍን ጨምሮ፣ በርካታ ጳጳሳት ተሳትፈውበታል፡፡ መጽሐፉ በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት እየታተመ ሲሆን በዚህ ሳምንት ከተጠናቀቀ በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ መዝጊያ ላይ ሊመረቅ እንደሚችል ታውቋል፡፡ 

በሻሻመኔ ከተማ እና አካባቢዋ ኪነጥበብ አፍቃሪዎች የተቋቋመው ከ “አድማስ ፊት” ማሕበር 44ኛ ዝግጅቱን ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት በሻሸመኔ ሁለገብ አዳራሽ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡ በ “ወንዶች ጉዳይ” እና “ሜድ ኢን ቻይና” ፊልሞች የሚታወቁት አርቲስት መስፍን ኃይለኢየሱስ እና አርቲስት ቴዎድሮስ ስዩም በፊልም ዙርያ ያላቸውን ልምድ ለታዳሚው ያጋራሉ፡፡ ከሐዋሳ “60 ሻማ” እና “መቅረዝ” የኪነጥበብ ማሕበራት፣ የአርሲነጌሌ ኪነጥበብ ማሕበርና የአጎራባች ከተሞች ኪነጥበብ አፍቃሪዎች ሥራቸውን በሚያቀርቡበትና በሚታደሙበት ዝግጅት በኢትዮጵያ አይዶል ተሸለሚ የሆነው “ሬንጀርስ” እና “ኮንታ የባሕል ቡድን” ውዝዋዜ የሚያቀርቡ ሲሆን የበላ ልበልሃና የግጥም ዝግጅቶች እንደሚኖሩ ታውቋል፡፡ የመግቢያው ዋጋ 10 ብር ሲሆን ከትኬት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለእንግዶች መሸኛ እንደሚውል ማሕበሩ ገልጿል፡፡ 

Saturday, 26 October 2013 14:19

“ሀ-ሞት”

የግጥም መድበል ለንባብ በቃ
በገጣሚ ሄኖክ ሥጦታው የተፃፉ ግጥሞች የተሰባሰቡበት “ሀ-ሞት” የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ በቃ፡፡ 78 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ ለሀገር ውስጥ በ25 ብር ለውጭ ሀገራት ደግሞ በ15 ዶላር እየተሸጠ ነው፡፡ ሄኖክ ከአሁን ቀደም “ነቁጥ” የሚል የግጥም መጽሐፍ ማሳተሙ ይታወሳል፡፡

            “አንተ አስተካክለህ ጥራው እኛ እንነዳዋለን” … የሚለውን ዘመነኛ የቀልድ መቋጫ ሳትሰሙ የቀራችሁ አይመስለኝም፤ ሳትሰሙ ከቀራችሁ የሚያሰማችሁ ቀልደኛ ፈልጉና ለመስማት ያብቃችሁ፡፡
“የጐጊንን ስዕል ፓሪስ ሙዚየም ገብቼ ተመልክቼዋለሁ” … አላችሁ እንበል አንድ ኋላቀር የሚመስል ሰው፡፡ እናንተስ ለፉክክር መች ታንሱና! … ኋላ አልቀረሁም የሚል የእውቀት ቃርሚያ ወኔ ይቀሰቅሳችሁና … ልታርሙት ትጀምራላችሁ። ‘ጐጊን’ … አይደለም ‘ፕሮናውንስ’ ሲደረግ … ‘ጐጋ’ ነው” ትሉታላችሁ፤ ፈርጠም ደልደል ብላችሁ፡፡ አጠራሩ ላይ እናንተ ትክክል ብትሆኑም … እናንተ አስተካክላችሁ/አሳምራችሁ የጠራችሁትን ሰዓሊ ታራሚው (ፋራ) በፓሪስ (ሉቭር) ሚውዚየም በአካል ተገኝቶ፣ ከሰዓሊው ስራ ጋር ፊት-ለፊት ተፋጥጦ ተመልክቶል፡፡
“እናንተ (አዋቂዎቹ) አስተካክላችሁ ጥሩት፤ እኔ ግን ተመልክቼዋለሁ” ቢላችሁ መሳቂያው … (በአጠራር ስህተት ምክንያት) እሱ ሳይሆን እናንተ ናችሁ፡፡ ግን ጥንቃቄ ማድረግ ያሻል … ጥንቃቄው የሚያሻው ለመመርመር ሲባል ነው፡ ማን ላይ ነው መሳቅ ያለበት? እናንተ አሳምራችሁ መጥራት በቻላችሁት ላይ ነው፤ ወይንስ እናንተ አሳምሮ በመጥራት የምታውቁትን ሠዓሊ እሱ አበላሽቶ ጠርቶ ግን በተጨባጭ ፓሪስ ሄዶ የተመለከተው ላይ ነው መሳቅ ያለበት? ይህ ቀልድ መሰል ጉዳይ … ብዙ ከቀልድ በላይ የሆኑ እውነቶችን የሚመለከት ስለመሰለኝ፤ በተለያየ እይታዎቼ እየተጠቀምኩ ብጐረጉረው … አሳ ሳይሆን ዘንዶ ብቅ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ብቅ ያለው ነገር፤ ማን ላይ መሳቅ እንዳለበት አመልካች መሆኑን አምናለሁ፡፡ አምኜም እጐረጉራለሁ፡፡
ድርጊቱን መፈፀም መቻል ነው ግብ? ወይንስ የድርጊቱን ትርጉም ማወቅ? … የድርጊቱን ትርጉም ያወቀ … አብሮ አሳምሮ ድርጊቱን መፈፀም ይኖርበታል። በአሜሪካን የሲቪል ራይት እንቅስቃሴ ትኩሳት ዘመን … ለግለቱ ምክንያት የነበሩ የነፃነት ትግል አፋፋሚዎች ትዝ ይሉናል፡፡ አንደኛው ለምሳሌ፤ የቤተ መቅደስ አገልጋዩ ማርቲን ሉተር ኪንግ ጂኒየር ነው ወይንም ነበር፡፡ ዶክተር እና ቄስ ነው፡፡ “ህልም አለኝ” በሚል መነባነቡ ብቻ ሳይሆን ባደረገው የነፃነት ጥሪው እና በፈጠረው መነቃቃት ይታወቃል፡፡ ይህ ጥሪው ነው በስተመጨረሻ ወደ ሞቱ የመራው፡፡ ከሞቱ በፊት የጀግንነት ተግባር ፈፀመ፡፡ ከሞቱ በኋላ ጀግና ተባለ፡፡ በተግባሩ ሰአት ህልመኛ ነበር የሚመስለው፡፡
ይህንን ባለ ህልም የነበረ ሰው፤ ወደ ቅድሙ የቀልድ ቅፅር ይዘነው እንዝለቅ፡፡ ቅድም፤ “አንተ አስተካክለህ ጥራው፤ እኛ እንነዳዋለን” የተባለው መኪና፤ በማርቲን ሉተር ኪንግ አንፃር ስንለካው … ዶክተሩ ቄስ “አስተካክሎ ህልምን የሚጠራ ሲሆን” …. አስተካክሎ እሱ የጠራውን ህልም እነሱ ወደ ተግባር የህይወት መኪና ቀይረውት እየሾፈሩ ዘንድሮ በመኖር ላይ ይገኛሉ፡፡ “አንተ ህልምን አስተካክለህ ጥራው፤ እኛ በእውን እንኖርበታለን” ቢሉት እሱ ላይ ይሳቅበት ይሆን? ያለ ህልም ወደ ተግባር የደረሰ ደንቆሮ “ዋናው ድርጊት ነው” ብሎ በህልም አለም ዝግመቱ ላይ በሞት በተቀጨው … ቄስ/ዶክተር ላይ ሊስቀበት ይችላል፡፡ ግን አሁንም መሳቅ ያለበት በማን ላይ ነው? የሚለው ጥያቄዬ በግልፅ አልተፈታልኝም፡፡ ተጨማሪ ምሳሌዎች እንደ መጐርጐሪያ ልጠቀም፡፡
ምሳሌውን ከእዛው ዘመን ግድም ልውሰደው። ከአሜሪካ የሲቪል ራይት እንቅስቃሴ ትኩሳት ዘመን ግድም፡፡ ይኼኛውም ሰው ታጋይ ነው። የሚታገለውም ለተጨቆነው የጥቁሮች መብት ነው፡፡ ስሙ ኤልድሪጅ ክሊቨር ይባላል፡፡ የ“ብላክ ፖንተርስ” የንቅናቄ ፓርቲ የኮሚኒኬሽን ሚኒስቴር ነበር፡፡
ኤልድሪጅ የተናገረውን ከመጥቀስ በፊት የንቅናቄያቸውን ባህሪ ልግለፅ፡፡ ንቅናቄያቸውን እንደ ቄሱ ዶክተር በስብከት አልነበረም ወደ ተግባር ለመቀየር የፈለጉት፡፡ በነጭ ፖሊስ የሚደርስባቸውን ጭካኔ ለመቋቋም የራሳቸውን የጥቁር ፖሊሶች በመመልመል አስታጠቁ፡፡ “ነጭን ህዝብ መጠበቅ ያለበት ነጭ ፖሊስ ነው፤ ጥቁርን ደግሞ እንዲጠብቅ ጥቁር ፖሊሶች ያስፈልጉናል” ብለው ወሰኑ፡፡ ንቅናቄው የተወለደበት ስቴት ሉዊዚያና በመሆኑ፤ በሉዊዚያና የወቅቱ ህግ ደግሞ፤ ማንም ነዋሪ ራሱን ለመጠበቅ መሳሪያ መታጠቅ ይችላል የሚል ነበር፡፡ “አንተ ህልምህን አልም፤ እኛ ከተግባር አድርገነዋል” ብለው ወደ ትጥቅ ተግባራቸው ገቡ፡፡
ከእነሱ በቀደሙ አርአያዎቻቸው ላይ የሳቁ አይመስለኝም፡፡ … ግዴለም፤ እነሱም ባይስቁ እንኳን የእነሱ ተግባር ራሱ የእነ ማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም (“ህልም አለኝ”ነታቸው) ላይ ሳቁበት እንበል፡፡ … የሳቅ የጨዋታ ህግ በተደነገገው መሰረት … ቀድሞ የተሳቀበት ሳይሆን መጨረሻ የተሳቀለት ላይ ነው አሸናፊ፡፡ በተሸነፈው ላይ ያሳቀበት አሸናፊው ነው፡፡
በማርቲን ሉተር ኪንግ ህልም ላይ “የብላክ ፓንተሮቹ” ተግባር ተሳለቀ ቢባል እንኳን … ስላቁ ግን የመጨረሻ አልሆነም፡፡
መሳሪያ የመታጠቅ መብታቸው (በእነ ሮናልድ ሬገን (ያኔ ሴኔተር ነበር) አማካኝነት ተነፈጋቸው። በዛ ላይ የኮሚኒስት አፈ ቀላጤ ብሎ የአሜሪካ መንግስት ጠላት አድርጐ ፈረጃቸው፡፡ ይባስ ሲል፤ የጥቃት እርምጃ ሊወስዱ ተዘጋጅተዋል በሚል በመሉ ተሰብስበው እስር ቤት ተጨመሩ፡፡ … በእዚህ ደረጃ የመጨረሻው ሳቅ በእነሱ ተግባር ላይ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ የእነሱ ተግባር አስቂኝ ሲሆን የማርቲን ሉተር ህልም በሳል ተባለ፤ “አንተ ህልሙን አሳምረህ እይ፤ እኛ በተግባር አድርገነዋል” የሚለው የአራዳ እንቅስቃሴያቸው የጨቅላ ህልም ሆነና ቁጭ አለ፡፡ ሲስቅ በነበረው ሲሳቅበት በጨዋታው ህግ ተሸነፈ ይባላል፡፡  
ቅድም እመለስበታለሁ ያልኩት የብላክ ፓንተር ኮሚውኒኬሽን ሚኒስትር የነበረው ኤልድሪጅ ክሊቨር፤ ወደ ንቅናቄው ከመግባቱ በፊት … የንቅናቄውን ግብ ተጠይቆ ሲመልስ (Soul On Ice የተባለ ድንቅ መፅሐፉ ላይ ሰፍሯል)፡- “To put a black finger on the Nuclear trigger” ብሎ ነበር። የተግባር እንቅስቃሴያቸው ግብ አሁን ፕሬዚዳንት ኦባማ የተቀመጠበት የስልጣን ቦታ ገስግሶ መድረስ ነበረ፡፡ ግን አልደረሱም፡፡ የደረሱት ዘብጥያ ነው፡፡
ኦባማ ስልጣን ላይ የመጀመሪያው የአሜሪካ የጥቁር ፕሬዚዳንት ሆኖ የተሾመ ቀን የ Black Panters ህልም የነበረውን (ጥቁር ዝርያን በኑክሊየር መተኮሻው ቃታ ላይ ስልጣን እንዲኖረው ማድረግ (ቃታውን መቆጣጠር) ኦባማ በተግባር አከናወነው።
ኦባማ፤ “እናንተ ስለ መቆጣጠር አሳምራችሁ ተናገሩ … እኔ ግን ተቆጣጥሬዋለሁ” ቢል ስለ ብላክ ፓንተሮች ህልም … የሳቅ ጨዋታው አሸናፊ መሆኑ ቅንጣት አያጠራጥርም፡፡ who’s got the last laugh now?! … ግን ኦባማ እንደዛ የሚያስብ አይመስለኝም። እኔ እና እናንተ ነን እንደዛ እያሰብን እርስ በርስ የምንሳሳቅ፡፡ የሳቀ … ሲሳቅበት ያለቅሳል። “የሚስቁ አያውቁም፤ የሚያውቁ አይስቁም” ላኦ ትዙ ባይልም፤ እኔ ያላለውን ለሳቅ አስተሳሰቤ ስል ወረስኩት፡፡
ሁለት ሆቴል ያለው ባለ ሀብት፤ ንግድ እና ኢኮኖሚን አሳምሮ በመተንተን ከሚፈላሰፍ ባለሞያ ጋር ቢገናኝ “አንተ አሳምረህ ተንትን፤ እኔ አንተ የምትተነትነውን ብር እቆጥረዋለሁ” ቢለው ሳቁ የሚያደላው ወደ ባለ ሀብት ተብዬው ነው፡፡
አሳምሮ ብርን በማውራት ከሚኖረው ባለሞያ የሚሰጠውን ትንተና፣ ህልም ወይንም እርማት መቀበል ካልቻለ … የሚቆጥረው ብር እና ተግባሩ ተጨብጦ አይቀርም፤ በሂደት ሀብቱ ህልም ይሆንበታል፡፡ የጨበጠውን እውነታ ያጣዋል። የሳቀበት ተንታኝ መልሶ በተተነተነ ማስረጃ ይስቅበታል፡፡
ይሄንን ሁሉ ወደ መፃፍ ያመራሁት “ፐርሼ” ተብላ የምትጠራውን የልዕለ ቅንጦት መኪና ገዝቶ እየነዳ … ስሟን እና የመኪናዋን ምንነት እና የገዛውን እሴት ትርጉም ከተራው የመኪና ጐሳ አንፃር … እሴቷን ሳያውቅ በገንዘብ ለመፎካከር ብቻ ገዝቷት፣ የመኪናዋን ስምም ሆነ ከጀርባዋ ስላለው የእሴት ዳራ ሳይገደው፣ ከሚኒባስ ታክሲ ባልተለየ አያያዙ ሲያንገላታት የታዘበ አዋቂ ነኝ ባይ “ስሟ … እንደዛ ሳይሆን እንደዚህ ነው! …” ወዘተ ብሎ ሊያታክረው ሲል “አንተ ስሟን አስተካክለህ ጥራ፤ እኔ ግን እነዳታለሁ” አለው፡፡ ተሳቀለት፡፡ ግን ጥያቄው፤ ከተሳቀለት በኋላ በስተመጨረሻ፣ የኋላ ኋላ የሚስቅበት ማነው? “Who’s got the last laugh now?!” የሚል ነው፡፡
ወደ ፓሪስ ሚዩዚየም ሄዶ “ጐጊንን” ተመልክቼ መጣሁ ማለቱ እንዲያውስ ስምም ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑን በማወቁ ነው፡፡ ትልቅ ስልጣኔ ሀገር ላይ ኋላ ቀር የሆነ አመለካከቱን ይዞ ገብቶ … ሲኖር ቆይቶ ሲመለስ “እንትንን አየኸው ወይ?” ሲባል “አንተ አስተካክለህ ጥራው፤ እኔ ግን ኖሬበታለሁ” ካለ መሳቅ ያለበት አስቃለሁ ያለው ላይ ነው፡፡ ፓሪስ ሄዶ ከኢትዮጵያ የተለየ ነገር ማየት ያልቻለ … ኢትዮጵያ ሆኖ ስለ ፓሪስ እና አሜሪካ ከሚያስበው ህልመኛ በላይ ያስቃል። ለእኔ ያስቃል ያልኩት ነገር ግን ሌላውን የሚያስቅብኝ ሊሆን ይችላል፡፡
ጥያቄው የበስተመጨረሻው ሳቅ የሚሳቀው በማን ነው? የሚሳቅበትስ ማን ላይ ነው? የሚል ነው … ተግባር ያለ ህልም … ህልምም ያለ ተግባር የለም … ያለ እውቀት የሚመጣ ተግባር … እና ወደ ተግባር የማያመራ እውቀት … ሁለቱም አስቂኝ ናቸው፡፡

Published in ጥበብ

የሠዓሊ ዳንኤል ታዬ ሥዕሎች ዛሬ እንደሚሸጡ የአርቲስቱ ስቱዲዮ አስታወቀ። ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለ6 ሰዓታት ብቻ የሚዘልቀው ሽያጭ፤አርቲስቱ ያሳለፈውን የጥበብ ጉዞ የሚያስቃኝበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ስዕሎቹ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው የዳንኤል ታዬ ስቱዲዮ በቀላል ዋጋ መቸብቸባቸው የጥበቡን ዋጋ ያሳንሰዋል ሲሉ የተናገሩ ሠዐሊዎች፤ሁኔታው እንዳሳዘናቸው ገልፀዋል፡፡ ለአርቲስቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በበኩላቸው፤ከሽያጩ የሚገኘው ገቢ የአርቲስቱን ጤና ለመንከባከብ እንደሚውል ተናግረዋል፡፡


ሁሉም ድንጋይ ድንጋይ አይደለም
በሰዋዊነት ሲመነዘር፣
ከሰው የሚሻል ድንጋይ አለ፤ ከድንጋይ
እንደሚሻለው የሰው ዘር …
አዋላጅ ሲገኝ… ድንጋይ እትብት አለው
ሶስት ሺ ዘመንን የሚያስር፣
ብልህ ሲጠርበው… ድንጋይ ፍትሕ አለው
የሀገርን እውነት የሚያበጥር፡-
ወላይታን ከትግራይ የሚያዋቅር፣
አማራን ከኦሮሞ የሚያፋቅር፣
ጠያቂ ሲኖር ድንጋይ እውቀት ነው፤ በመላው
ሀገር የሚስተጋባ፣
አዋቂ ካየው ድንጋይ እምነት ነው፤ ሁሉንም
አማኝ የሚያተባ!
እስላም ከክርስቲያን የሚያጋባ፣
በቅዱስ ሳይንስ የሚያግባባ…!
ጠቢብ ሲያየው ድንጋይ ብርሃን ነው፤ የሀገርን
ጨለማ የሚያበራ፣
መራሄ ሲገኝ ድንጋይ ሀር አለው፤ የሀገርን
ድር የሚያደራ፣
አፋርን ከቤልሻንጉል የሚያጋራ፣
ሶማሌን ከሀረሬ የሚያዋራ፣
ደቡብን ከጋንቤላ የሚያዳራ…!
ትርጁማን ሲገኝ፣ ድንጋይ ቋንቋ አለው
አፍሪካን በአንድ የሚያናግር፣
እንኳንስ ለአቢሲኒያው ውላጅ፣ ኩሽን
ከሴማዊው ለሚማግር፣
የትውልድ ሁሉ ልሳን ነው፤ እንደ
አማርኛችን ቅይጥ እግር!
ካልክማ ድንጋዩ እንጀራ ነው፤ ሀገርን
አስምቶ ለሚጋግር…!
(ስለዚህ ወዳጄ…)
በድንጋይ የሚመካ ሰው ነው፣ ያውም
ብልህ አእምሮን የታደለ፣
ግዑዙን አለትን ጠርቦ፣ ‹‹ድንጋይነት››ን
የገደለ!
ከ‹‹ሙት›› ድንጋይ ላይ፣ ሕይወት የዘራ
ህያው ቅሪቱን ያኖረ፣
እንደ አክሱማዊው ምንጅላቴ ፣አለት
በጥበብ ያነጠረ፣
ሀገርን ከአለት የፈጠረ፡፡
ሀገርም በድንጋይ ባይመካ፣ ከድንጋይ
ህላዌን ያስቆጠረ፣
የንጉስ ረምሀይ ሀውልት ሳለ
የተሟሸ ታሪኩን ያኖረ፣
ሰዋዊነትን ከድንጋይ ውስጥ፣ በጥበብ ጨምቆ
የቀመረ…!
የባዜን መቃብር ዕየታየ፤ የዘመን መንፈስ
እንዳረገዘ፣
ካሌብ የቀረጸው የድንጋይ ጣሪያ፣ ዛሬም እኛን
እያፈዘዘ…!
“በድንጋይ አትመኩ!” ማለት ምንድን ነው?
በውቀትና በውነት ለሚዳኝ ሰው፣
የሀገርን መቅን ከማድረቅ ውጭ፣ ጥበብን
በነገር ሳናድሰው…!
ያልገባን ታሪክ ሁሉ፣ ከንቱ ወንጅለን
ከምንገረጣ፣
የሀገርን ሰንደቅ አርማ፣ ከሀውልቱ አናት ላይ
ሳናወጣ፣
የጦቢያን ድንበር የምንኩልበት፣ ቁራጭ
ድንጋይ እንዳናጣ፣
የዕይታ አድማሳችንን አስፍተን፣ ከጠባቧ ኩሬ
እንውጣ!
የመርገም ዶሴያችን ይቀበር፣ ሥልጣኔያችንም
ይምጣ ...

ለጌታው፣ ጅምሩ ‹‹ሊቅ›› ማስታወሻ
(ጥቅምት 1፣ 1999፤ አክሱም፣ የሐ ሆቴል)

Published in የግጥም ጥግ
Page 1 of 16