• ለዛሬ የፀጋዬን ግጥሞች አንድ ሰባት ሰበዝ መዝዤ ልያቸው፡፡
  • ፀጋዬ በቦታዎች ላይ - ምነው አምቦ፣ አድዋ፣ ማይጨው፣ ሐረር፣ ወዘተ
  • ፀጋዬ በጀግንነትና በብሔራዊ ስሜት ላይ - የመቅደላ ስንብት፣ ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት፣ አበበ እንጂ ሞተ አትበሉ
  • ፀጋዬ በፍቅር ላይ - መሸ ደሞ አምባ ልውጣ፣ ትዝታ፣ ጌራ፣ ተወኝ፣
  • ፀጋዬ በፍልስፍና ውስጥ - ክልስ አባ ልበ - እግረኛ፣ መተማን በህልም፣
  • ፀጋዬ ማህበራዊ ጉዳይ ላይ - ማነው ምንትስ
  • ፀጋዬ - አገሬውን፣ ገጠሩን፣ ብሔረሰቡን የሚያይበት ዐይን - የምታውቀኝ የማላቅህ፣ አቴቴ ዱብራ ኦሮሞ
  • ፀጋዬ የማሕበረሰብን ዝቅጠት ለመከላከል ሲፅፍ - አባቴስ ወንድ ወለድኩ ይበል፣ እንዳይነግርህ አንዳች ዕውነት
  • ፀጋዬ በማናየው አቅጣጫ ላይ፣ ህግን መጣስ ይችላል - እንቅልፍ ነው እሚያስወስድህ፣ መትፋት የስነውራል
  • የፀጋዬ አፃፃፍ ከጠቅላላ ወደ ዝርዝር የመግባት ባህሪ አለው፡፡ በቦታ ላይ በሰፊው ጽፏል፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸውን ላቆያቸውና ከመጨረሻው ልጀምር፡፡

ለምሣሌ ድሬዳዋን በጅምላ ጆግራፊዋን፣ የያዘችውን ህዝብ፣ መልክና ውበቷን ያሳየናል
…ዲሬ - ዳዋ - ድሬ ዳዎ
የምሥራቅ አድባር ጥላዋ
ላገር ጎሣ ድምር - ጽዋ
ኅብረ - ጠባይ ማጥለያዋ
ድሬ - ዳዋ ውስጠ - ደማቅ
ሽፍንፍን እንደአባድር - ጨርቅ፣ ብልጭልጭ እንደሩቅ ምሥራቅ
ከዚያ በዝርዝር ድሬዳዋ ጉያ ውስጥ ይገባል
…በየጉድባሽ ጫት ሲሰጣ
ጣይ ያደከመው ወፈፌሽ፣ አራራ ጥሎት ሲንጣጣ
ብሌኑ እንደጐሽ - ግት ፈጦ
ጉድ ከየአንደበቱ ፈልቆ….
“ብሌኑ እንደ ጎሽ - ግት ፈጦ” የሚለውን ምስለታ ተመልከቱ፡፡ በእግሩ መካከል ነጩ ብቻ የፈጠጠ ያጋተ ጡትና ዐይኑ የፈጠጠ ባለሐራራ ነው የሚያመሳስልልን፡፡
አሥመራ
አዘቦን ዳግም አየሁዋት
ሌሎቹ በቦታ ላይ የተቀኘባቸው ሥራዎች ናቸው፡፡
ጋሽ ፀጋዬ አህጉራዊም አለም አቀፋዊም ብዕር አለው
ጋሽ ፀጋዬ በእንግሊዝኛም ይገጥማል፡፡ በዚያም የአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ብዕሩን አሳይቷል፡፡ እንደ ኤዞፕ፣ ዘ ኤይዝ ሐርሞኒና የአፍሪካ ህብረት መዝሙር፣ እንዲሁም ፕሮሎግ ቱ አፍሪካን ኮንሳይንስ የሚሉትን ግጥሞች ለአብነት ብጠቅስ ይበቃል፡፡
“This is the land of the 8th harmony
In the rainbow: Black
It is the dark side of the moon
Brought to light.”
በቁሙ ብተረጉመው እንዲህ የሚል ይሆናል:-
ጥቁር
የስምንተኛው ብርሃን ህብር
ይህ የቀስተ - ደመና ምድር
የጨረቃ ጭልም ወገን፣ ወደ ብርሃን ሲከተር
እንጂ ሌላም አደል ጥቁር!
ጥቁር
“አባይ” በሚለው ግጥሙ ውስጥም ይህንኑ ባህሪ እናያለን፡፡
…አባይ የጥቁር ዘር ብሥራት
የኢትዮጵያ ደም የኩሽ እናት
የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር እስከ ካርናክ
…አባይ የአቴስ የጡቶች ግት
ለዓለም የሥልጣኔ እምብርት” ይለዋል
ስለፍቅርም ይቀኝ ነበር ጋሽ ፀጋዬ - በእንግሊዝኛ፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻ ከፃፋቸው ውስጥ Gladiator’s Love
Gladiator’s Love
Though the stars no more glitter
And the cloud does no more rain
Though the moon shall not be borne
Yet your love is not in vain
Though I bid fare-well to life
Where you too are included,
Breaking the law of nature
Your loving has intruded.
ቀለል ለማድረግ ብዬ በወል ተርጉሜዋለሁ፡-
    ከዋክብት አይበሩም
ዳመናው አይዘንብም
ጨረቃ በቅቷታል ዳግሚያ አትወለድም
ያንቺ ፍቅር ብቻ አለው አንድ አብነት
ፍጥረት ሲለዋወጥ ፀንቶ የመቆየት፡፡
አንቺንም ጨምሬ ሁሉን ለመለየት
ኑሮዬን ደህና ሁን ብዬ ስሰናበት
ፍቅርሽ ግላዲያተር ማን ያዘኛል ያለ
አንቺንም ሸኝቼ፣
የዓለም ህግ ጥሶ፣ ይሄው አብሮኝ አለ!!
Prologue to African conscience ሌላው የእንግሊዝኛ ግጥሙ ነው፡፡ ቀንጭቤ ላቅርብላችሁ ከነትርጉሙ
…It looks right
It looks left
It forgets to look into its own self:
The broken yoke threatens to return
Only, this time
In the luring shape
Of luxury and golden chains
That frees the body
And enslaves the mind.
    የአፍሪካ ህሊና
ወደቀኝም ያያል
ወደ ግራም ያያል
ግና ራሱን ውስጡን ማየቱን ዘንግቷል
የሰበርነው አስኳል መልሶ ሊመጣ
አሁን በሌላ መልክ ታይቷል ሲቀናጣ
ግና የአሁነኛው
ለቅንጦት ለአዱኛ፣ ለወርቅ ሰንሰለት፣ እንድናደገድግ
ነው አንዳች ወህኒ ውስጥ የሚያስረን ከራር ድግ፤
ገላን ነፃ አውጥቶ፣ አንጐል ባሪያ እሚያረግ
ለጋሽ ፀጋዬ “እንደ” የሚለው የተማስሎ ቃል - ትልቁ ብቃቱና ኃይሉ ነው እላለሁ፡፡ ልዩ ምስል ይቀር
ፅበታል፡፡ “እንደ” ብሎ በተማስሎ መጠቀም ይችልበታል፡፡
ለአብነት ጥቂት ላሳያችሁ:-
ከአይ መርካቶ
    የከበረ እንደመረዋ፣ ረብጣ አፍኖት ሲያስገመግም
    የከሰረ እንደፈላስፋ፣ በቁም ቅዠት ሲያልጐመጉም
    ከቃል ቃተተ
    ቃላችንን ካስጐሰበትን፣ እንደሥራ-ቤት ልፈፋ
እንደቀፈፋ አቆማዳ፣ ምሥጢር ካፎቱ ከሰፋ
እንደባለጌ መቀነት፣ ውሉ በልፊያ እየገፋ
እንደአቃቢት ግብር ውሃ፣ ገበና የትም ሲደፋ፣…
ጋሽ ፀጋዬ ባለሁለት ወይም ሦስት ፊደል ቃል መጠቀሙ ሌላው ልዩ ችሎታው ነው ቁጥብ ያደርገዋል፡፡
ከርዕሶች እንጀምር
ክልስ አባ ልበ እግረኛ
በቃኝ
ቦረን
አዋሽ
ምንም አልል
ምንም አልል
ልሳኔን ሲያስነሳ ሲያስጥል
ቃላቴን ሲቃኝ ሲያጋግል
ክል ሲል ትር ድም፤ ሲል

ማዳመጥ
ማስታመም እንጂ፣ ሌላ ምንም ምንም አልል
እነዚህን ባለሁለትና ሦስት ፊደል ቃላት ልብ ይሏል፡፡
ከአዋሽ
    …መጫ ቋጥሮ ሸዋ ፀንሶ፣ ሰባት ቤት     ጉራጌ አርግዞ
    ከዳዳ ምንጭ አሩሲ እምብርት፣ ከነ     ቅሪቱ  ተጉዞ
    ከአላባ ጣፋ ሼህ ሁሴን፣ አዳል ሞቲ     ሽሉን ይዞ
    ከከረዩ ማታ ሐራ፣ ከኢቱ እስከ አፋር አምጦ…
(ይቀጥላል)

Published in ጥበብ

       ገጣሚነት አማረኝ ተብሎ የሚገኝ ተሰጦእ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ ግጥም ለመግጠም ከፈለክ ልክ እንደማኪያቶ ወይም እንደ ጥሬ ስጋ ውል እስኪልህ ጠብቅ፡፡ በአይንህ ላይ ከዞረ ለደቂቃ እንዳትዘናጋ፡፡ አምሮትህን ለማውጣት ፈጥነህ ሁለት እና ሶስት ስንኞችን እንደኒሻን ደርድር፡፡ ለጥቀህ በጣም ለሚቀርቡህ ባልንጀሮችህ ተቀኝላቸው፡፡ ስንኝ ድርደራው እንደተዋጣልህ በስሜት ተውጠው ያበስሩሃል፡፡ አንተም በተራህ የእነ እርሱን ግጥም ለማወደስ አይንህን ማሸት ይከብድሃል፡፡ እነርሱም ባለቅኔ ይሉሃል፣ አንተም ባለቅኔ ትላቸዋለህ፡፡
እርስ በእርስ መጠፋፋቱ ይህን ጊዜ ይጀምራሉ፡፡ በዚህ መሰሉ አጥፍቶ ጠፊ ቁርኝት በገጣሚነት እየተፈረጁ ሰልፉን የተቀላቀሉት ስንቶቹ ናቸው፡፡ የገጣሚያኑ ተፈጥሯዊ ባህሪ መመሳሰልን ስንመለከት ደግሞ የምንጫቸውን አንድነት ከወደ አንድ አቅጣጫ እንደሆነ ሳንጠራጠር እንድንቀበል ያደርገናል፡፡ ግጥሞቻቸው መርዘም የተሰናቸው ጉርድ ባለ ሁለት እና ሶስት ስንኝ ያቀፉ ከግልብ ህሳቤ የሚፈልቁ የቃላት ኮተቶች እንደሆኑ ማንኛውም አንባቢ በጨረፍታ ገርምሞ ብይን ሊሰጥባቸው ይችላል፡፡
ሳያነቡ የሚገጥሙ “ብፁሃን” ናቸው
ንባብ፣ ተመስጠን የተራቆቱ የግጥም ስንኞች ምንጫቸው ደመነፍስ ነው፡፡ በእዚህ አባዜ የተተበተቡ ገጣሚያን “ብፅህናን” ታድለዋል፡፡ አሀዱ ሳይሉ የሚሰልሱ፣ ማንበብን የፆሙ በክሸፈት የሚገድፉ መናኞች ናቸው፡፡ እነዚህን ገጣሚያን ለመንካት የምትገዳደር ከሆነ ያልጠበከው ቀስት ከእየአቅጣጫው ይወነጨፍብሃል፡፡ እድለኛ ከሆንክ ደረትህ ከመነደል ይተርፋል፡፡ ትግሉ ይሰለችና እና አንተም በተራህ ብፅህናን ለማግኘት ከተኮናኝ እጣ ለመትረፍ በደመነፍስ መግጠም ትጀምራለህ፡፡ ደጋግመህ መግጠምህ የልብ ለብ እንዲሰማህ እያደረገህ ነው፤ ፉጨቱ… ጭብጨባው… ሙቀቱ… ከልክ በላይ ሆኖብህ እያጠወለወለህ ነው፡፡ በአጃቢዎችህ ውትወታ በሞቅታ የጫርካቸውን ዝባዝንኬዎች አሰባስበህ በመፅሀፍ ቢጤ ታበጃጅ እና ገበያውን ትቀላቀላለህ፡፡ በተራህ አትራፊ ነጋዴ ለመሆን ላይ ታች ትታትራለህ፡፡ ሼልፍህን የሞላውን መፅሀፍ ለማንበብ ስትነሳ አይተኸው የማታውቀው ድብርት እላይህ ላይ ሲከመርብህ ይሰማሃል፡፡ ምግብማ ሞልቲል አፒታይት ጠፋ እንጂ በሚል ማደናገሪያ ዜማ ትግሉን ለመሸንገል ትሞክራለህ፡፡
ቀና በል
ግድየለም ቀና በል፣ አላንበብኩም ብለህ እንዳትቆዝም፣ ለምን አንገትህን ትደልህ፣ ይህ ለማንም አይበጅም፡፡ ጭምትነትህ ባይተዋርነትህ ከቀዬው አድባር ጋር ቁርሾ ያስገባሀል፡፡ ወጣ ወጣ በል፣ ቀና ቀና፣ ደረትህን ገልበጥ አድርገህ ለሀገሩ አይን አዋጅ ሁንበት፡፡ ለማን ደስ ይበለው ብለህ ነው፡፡ ተጠበብ፣ ጉርድ ግጥሞችን ሞጫጭር፡፡ ከጉርድያን አደባባይ ላይ ተመር፡፡ የአጨበጨብክላቸው ለመቼ ሊሆንህ ነው፡፡ እነርሱም ያጨበጭቡ እንጂ፡፡ ጠቢብነትን ፈላስፊነትህን ለማሳየት አንድ ሁት ቃል አምጥ፡፡
ቀና በል ወዳጄ፣ የሸፍጡን ምድር ለመቀላቀል ጉርዱን፣ ድንክዬውን አንግብ፡፡ ደግሞም ማህላህን እንዳታብል፡፡ ለጉርዳያን ከምትሰጠው ከብር ጠብታ እንቋን ልታጓድል አይገባህም፡፡ ክንዴ ዛለ ብለህ ለጭብጨባ ብትቦዝን ቆሌያቸው ቅያሜ ይገባወል፡፡ የሸፍጥን ምድር ተጠቀምበት፣ ከአሻህ እግርህን ሰደድ፣ ከልካይ የሌለው አጥር አልባ፣ ወይ መስክ ነው እና፡፡ ባሰኘህ ላይ መቀኘት ትችላለህ፣ ያሻህን ቤት ድፋ፣ ለአንተ ሻማ ሊያበሩ አቅፍ ድግፍ አድርገው ሊያሞቱህ የተዘጋጁ ታማኝ ባልንጀሮችህ ምሰጋና ይግባቸው እና፡፡
ደግሞም ምርጫ አለህ
ሽንገላን፣ ውዳሴን ተጠይፈህ በራስህ አለም መመሰጥ፡፡ ከደራው ከሞቀው ግርግር መሀል መሰወር፣፣ ምርቃት፣ ድግስን ለተሰብሳቢዎቹ ለጉርዳያን መተው፡፡ በሸፍጥ ግዛት ለሚቦርቁት ግለቦች ከንፈርህን መምጠጥ፡፡ ጥበብን እንደ ሸቀጥ እንደ አስቤዛ ጠቅልለው ከኮሮጃቸው ወስጥ ለሚዶሉት ገጣሚያን አንዲት ዘለላ የአዞ እምባ ማንጠባጠብ፡፡ የእምቧየ ካብ ሰብእናቸው የበለጠ እንዲቆለል አንድ እምቧይ መወርወር፡፡ ደግመህ መወርወር፡፡ ቁልሉ እን እንዲጋነን፡፡ ተጋኖ እንዲናድ፡፡ ደጋግመህ እምቧይ መወርወር፡፡
እምቧዩን ስትወረውር ፎቶውን ገን አደራ
ፎቶውን አትንካ… ታሪክ ይከውኑበት፣ የፎቶን ታሪክ ነጋሪነት ለማውሳት ከጉርዳዊያን ቀድሞ አንደበቱን የሚያላውስ አፈቀላጤ አየኖርም፡፡ በምስላቸው በታሪክ ሲዘክሩ እንደሚኖሩ ከማንም በላይ አማናዊያን ናቸው፡፡ ፎቶውን፣ ታፔላውን ከፍ ከፍ ለማድረግ ዳተኛ ሆነው አያውቁም፡፡
በመዳፍ ልክ የተከረከመችውን የመፅሃፍ ጀርባ እኩሌታ ግዛቱ ያደረገው ምስላቸው በኩራት ይገረመማል፡፡ በፎቶው ግርጌ ላይ ከአንጀት ወዳጅ የፈሰሰ የውዳሴ ዝናብ አለ፣ “ባለ… ንስር… ገጣሚ” … “ዘመኑን… የቀደመ… ጥበበኛ” …ለውዳሴው…ቃላት ተንጠፍጥረው… ተንጠፍጥፈው… ከአንጀት ጠብ አይሉም፡፡
በእርግጥም ፎቶው ከስሙ፣ ፈረሱ ከጋሪው ቀድሟል
ድሮ ድሮ መልካም ስም ከመቃብር በላይ ይኖር ነበር፡፡ አሁን ግን መልካም ፎቶ ከመቃብር በላይ ይነግሳል ተብሎ ተገልብጧል፡፡ እውነት ነው ከጥበብ ጋር ደም የተቃቡ ግራዞች በክብር ቆመዋል፡፡ ነውራቸውን በገፅታቸው ሊያድበሰብሱ ይሞክራሉ፡፡ ጥበብን ከፍነው ከከተቱበት መቃብር አናት ላይ መለመላቸውን የሚያሳይ ፎቶ አለ፡፡ ፎቶው ለመሰሎቹ ወናፍ ነው፡፡ ጥበብን ገድሉ የሚሸልል ወናፍ፣ በግዳይ ላይ መፎከር ይሉሃል እንዲህ ነው፡፡
ወዳጄ ግን ከፉከራው ይልቅ ማህላውን ማጥበቁን መረጠ
በሽታን ደብቆ ከፈውስ ላለመራቅ፣ ድብብቆሽ፣ አኩኩሉው እንዲያበቃ ለማሃላ የአጅ መዳፉን አነሳ፡፡ የታይታ የሸንግላን፣ ውዳሴን እንትፍ አለ፡፡
 ከጉርዳዊ ዜግነት ተባራሪ ስደተኛ መሆንን መርጧል፡፡ በጉርድ ስንኝ አለሙን ከእጅ መዳፉ ላይ አኑሮ ኬረዳሽ ብሎ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የከፋ ሀጢያትን በንሰሃ ለመሻር ፈተና እንደሆነ ቢያውቅም ያቅሙን ግን ከመሞከር ወደኋላ አላለም፡፡ በመናኛ ጉርድ ስንኝ መመሰጥ በሁከት፣ በጫጫታ፣ በገበያ መሀል ለማሸለብ እንደሞመከር ይቆጠራል፡፡
ከመመሰጥ ጋር አንድነት በሌላቸው ስንኞች መደንዘዝ በእኔ ይብቃ ብሏል፡፡
አንዴም ጨምሮ አስረግጦ ተናገረ
“በእርግጥም ከሸፈትን የተከናነቡ ጉርድ ስንኞችን ጥቂት ንዋይ የቋጠረ ሁለ እንዳሻው የሚያነሳቸው የሚያፈርጣቸው የሱስ አረንቋዎች እንደሆኑ… ጠንቅቄ… አውቃለሁ፡፡ በጥበብ በድን ላይ የተጐለቱ የመቃብር አበባ መሆናቸውን ለማረጋገጥ እማኝ አያስፈልገኝም… በመሃላ እንደተጋባሁዋቸው በመሃላ ልፋታቸው… ይኸው እጄን አንስቻለሁ፡፡ አምሮቴን ገሸሽ አድርጌ… ከራሴ ጋር ለመምከር ወስኜያለሁ” ወዳጄ እንዲህ አምርሮ ከሸፈት ከተጣባቸው ጉርድ ስንኞች ጋር በአንድ ገበታ ላለመቀመጥ ምሎ ተገዘተ፡፡

Published in ጥበብ

ጀግንነት፣ ለጌጥ የተቀባነው የታይታ ቅባት ሳይሆን፣ በደም በአጥንታችን ውስጥ በእውን የሚላወስ የህልውና ሃብታችን ነው፡፡ ጀግና ያገር አለኝታ ነው፡፡ ጀግንነት ደግሞ አላፊውን አካል ለሌሎች መስዋዕት ማድረግ የማያልፍ ክቡር ዘለዓለማዊ ግብር፡፡  
ጀግንት ባህላችን በመሆኑ ሃገራችን በረጅም የመንግስትነትና የአገርነት ታሪኳ አንድ ጊዜ እንኳ በባዕዳን ቀንበር ስር ውላ እንዳታድር አስችሏል፡፡ ይህም ከአፍሪካ ብቸኛዋ አገር ያደርጋታል፡፡ የመጣውን ሁሉ አፈር ድሜ እያስጋጡ የመለሱት ጀግኖቻችን፤ በወገናቸው ዘንድ የተለየ ክብርና ሞገስ አላቸው፡፡ በየጊዜው በሚነሱት ትውልዶች ይወደሳሉ፤ ይሞገሳሉ፤ ይከበራሉም፡፡ ከማወደሻ መንገዶች አንዱ ቀርቶ ነው፡፡
አብዛኛው የአገራችን ሰው፣ ሆዱን ነገር ሲያምረው አልያም፣ ጥቃት ሲመረው፣ መጀመሪያ ማንጎራጎርን ይመርጣል፡፡ ከዚያ ነው ወደ ድርጊት የሚገባው እንዲህ እያለ፤
ብችለው ብችለው - አንገቴ ደረሰ
እክ ብለው ወጣ - ደም እየለበሰ፡፡
ኧረ ተው አንተ ሰው - አትለፍ በደጄ
እንደ ማታ መብራት - ትጠፋለህ በእጄ፡፡
ኧረ ተው አንተ ሰው - መካር የለህም ወይ?
ምላጩን ከሳቡት - እርሳስ አይደለም ወይ?  
ተው በሉት ያንን ሰው - ያን አመሉን ይተው፣
ደርሶ መወዘቱን - ሰው በጎላላቸው፡፡
ሰው መግደል እንደ እግዜር …
ዱር መግባት እንደ አውሬ - መቼ ይቸግራል፣
ከጓደኛ ጋራ - መጫወት ይቀራል፡፡
ካባቱ ባድማ - የተኛውን በሬ፣
ጎስጉሰው ጎስጉሰው - አደረጉት አውሬ …
ጀግና፣ ሲፈጥረው ስግብግብ አይደለም፡፡ ይልቁንስ አርቆ አሳቢና ትዕግስተኛ በመሆኑ ሳይነኩት አይነካም፡፡ ከሰው ቤት ገብቶም አይፈተፍትም፡፡ እንዲህ ያሉት ሲያጋጥሙት አላርፍ ብለው እረፍት ሲነሱት ያንጎራጉራል፡፡
እዩልኝ ያንን ሰው - ሳልጥለው ሲጥለኝ፣
አያሌ ጊዜው ነው - ትግል  ከከጀለኝ፡፡
ኧረ ተው ተመለስ - እባክህ ተመከር፣
እንደ እመጫት አልጋ - በደም ሳትነከር፡፡
ኧረ ተው ተመለስ - እሱ ነው ድንበሩ፣
ጎበዝ የዋለበት - አይጠፋም መስመሩ
እያለ ጠመንጃውን እየወለወለ እንደፍቅረኛው የሆዱን ያወያያታል፡፡ እኒህ አይነት የቀረርቶ ግጥሞች የጀግናው ትዕግስት መሟጠጡንና የመጨረሻ ውሳኔ ላይ መድረሱን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡
ከሁሉም ይልቅ ጀግናው በግጥሞቹ… አትንኩኝ አትድረሱብኝ፣ ድንበሬን አክብሩ፣” እያለ ፀብ እንዳልተጠማ የሚገልፀው ጀግና፣ ይህ ካልሆነ ግን እንደ እመጫት አልጋ በደም እነክራችኋለሁ፣ የጀግና  ወሰኑ ታሪክ ሊረሳ የሚችል አይደለም” ይለናል፡፡
“የሰውየውን ቤት - ሰውየው ከፈተው፣
ለወንድም ወንድ አለ - ኧረ ተው ኧረ ተው፡፡
ኧረ ተው አንተ ሰው - ስሮጥ አታባረኝ፣
አንተም አበዛኸው - እኔንም መረረኝ፡፡
ኧረ ይህ የጅል ልጅ - ምንኛ ሰለለኝ፣
ቤት እሰራለሁ ስል - ሰምቶኛል መሰለኝ፡፡”
ጀግናው እንዲህ የሚያንጎራጉረው፣ በቅናት የናወዘው ጎረቤቱ እየተጎነተለ አላስቀምጠው ሲል፣ ቢታገሰው እንኳ ትዕግስቱን እንደ ፍርሃት እየቆረጠበት - እንደ ሙጀሌ ቁስል እየነዘነዘ መውጫ መግቢያ ሲያሳጣው ብሶቱን ለመግለፅ ነው፡፡
“ትዕግስትና ጥረት ለድል ያበቃሉ” እንደሚባለው ጀግናው ትዕግስቱ ተንጠፍጥፋ እስከምታልቅ ድረስ ጠላቱን እና ጥላቻውን ችሎ ሲያስል ቆይቶ፣ የኋላ ኋላ አማራጭ አለው? ያንገሸግሸዋል፡፡
የምሰማው ወሬ ምንድነው ሽክሹክታው?
አንበሳው ቤት ጦጣ አይገባም ነውር ነው፡፡
ይብላው ውሃ ይብላው አሞራው፣
የጎበዝ አዝመራ ይበቃል ገቦው፡፡
እምብዛ ዝምታ ለበግም አልበጃት፣
አምሳ ሆና ቆማ አንድ ነብር ፈጃት፡፡
እኔስ ትቸው ነበር ደሞ ከፋው ሆዴን፣
እስኪ ልነሳና ላብጀው መንገዴን፡፡
እስኪ ልነሳና ልጓዝ ወደ ደኔ፣
መቸም በእናንተ ቤት ሰው አይደለሁ እኔ…
ጀግናው ከእንግዲህ የሚመልሰው የለም፡፡
 ሲል እንደ ሰው ሆኖ መኖር ቢፈልግም በምቀኞቹ ጉንተላ የአውሬነት ኑሮውን ሊያያዝ ወደ ጫካ ለመግባት መገደዱን ይናገራል፡፡
እንዲህ ዳምኖ - የዘነበ እንደሆን፣
ማን በተለመው ላይ - ማን ይዘራ ይሆን?
እንዴት በላው - እንዴት ጣለው ጣለው፣
ይቸግር የለም ወይ - ደም መላሽ እንዳለው፡፡
ዘንድሮ አለ ነገር አለ ነገር፣
ቁልቁለቱን ወርደን ወንዙን ስንሻገር፡፡
ቁልቁለቱን ወርደን ወንዙን ስንሻገር፣
እስኪ እንደ ቀደሙ ነካካኝ በነገር …
ጀግናው እነዚህን የቀረርቶ ስንኞች የሚያንጎራጉረው ጣቱን ከምላጬ ላይ አርጎ “ከእንግዲህ በኋላ የሚለየን ይህ ብቻ ነው” በሚል ዓይነት ነው፡፡ ጀግና የመታገሱን ያህል ሲያመር አያድረስ ነው፡፡
እጀታው ወደቀ - ወልቆ ከምሳሩ፣
ይሻል  የነበረው - ተዋዶ መኖሩ፡፡
በሬውን ረዳው - ቤቱንም አቃጥለው - አስቀምጠው ባመድ፣
ሲጨንቀው ሲጠበው - ያረግሃል ዘመድ …
ሰላምን በዋዛ የሚመለከቷትና ትርጉሟ የማይገባቸው ደናቁርት ሲያጋጥሙት ምን ያድርግ?
ጀግና ጥቃትን ከሞት በላይ ይፈራዋል፤ ይጠላዋልም፡፡ ይህን የሚገልጥበት ቋንቋው ያው ቀረርቶ ነው፡፡
ጎራዴህን መዘህ - አርገው ገለል ገለል፣
ሞት አይቀርምና - በጀርባ መንጋለል፡፡
ዓባይ ጣና ሞልቶ - እሳት ይዞረዋል፣
ሊጠፋ ነው እንጅ - መች ይሻገረዋል፡፡
ዓባይ ጣና ሞልቶ - በደረቁ ላጨኝ፣
ራሴን ሳያመኝ - መደፈሬን ቆጨኝ
የጀግና ስንኞች ናቸው - ለህመሙ ሳይሆን ለክብሩ የሚጨነቅ መሆኑን ያስረገጡ፡፡ አዎ! ውርደትን ለማያውቅ ህዝብ እርግጥም መዋረድን ያህል በሽታ ሊኖር አይችልም፡፡
ደህና ጎበዝና - ነብር አንድ ናቸው፣
ደርሰው ሰው አይነኩም -ካልደረሱባቸው፡፡
ኧረ ጀግና ይሙት - ፈሪ ይኑር ቢሻው፣
አተላ መሸከም - ይችላል ትከሻው፡፡
ጉልፍ ጉልፍ አርጎ - ሞቶ አገኘሁት፣
ሰው እያየው መሸሽ - ነውር ሆኖበት፡፡
ሰንጋ አረጀ ብለው - ጋማውን ጭራውን - ቢጎነዳድቡት፣
አመሉን አይተውም - ኮርቻ ሲጭኑት
አንበሳው ተኝቶ - ላም ተራመዳችው፣
አውቆ ቢያሳልፉት ሞኝ አደረገችው፡፡
አንበሳው ተገርሞ - ታስሯል በመጫኛ፣
የቆረጠ እንደሆን - ወይ እሱ ወይ እኛ፡፡
ከመነሻ እስከ መድረሻ ከእያንዳንዱ ስንኝ እንዲታዘብ ነው፤ ጀግና ደርሶ ሰው አይነካም፡፡ ሲነኩትም ቶሎ ደሙ አይፈላም፡፡ የፀብን መጨረሻ ያውቀዋል እናም አይቸኩልም፡፡ ነገር ግን ፈሪ መሆን የሚያስከትለውን ውርደት ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ለዚህም ነው ከውርደት ይልቅ ሞቱን የሚያስቀድመው፡፡
በጀግና ቤት መሸሽ ብሎ ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ስሙ ዘልዓለም እንዳይሞት ብቻ ተጨንቆ ጠላቱን አስጨንቆ፣ ግንባሩን ለጠላት ጥይት ይሰጣል፡፡ የመጨረሻ ብቸኛ ምርጫውም ይህ ብቻ ነው፡፡ ሸሸ መባል ሞት ብቻ ሳይሆን የሞት ሞት ነውና!
ጀግና በግጥሞች ብርሃንም ሆነ በማታ ጨለማ በአፍላነት እድሜውም ሆነ በጉልምስናው ዘመኑ፣ ከተፈጥሮው አይዛነፍም፡፡ ሰንጋ ፈረስን ይመስላል፡፡ ሰንጋ ፈረስ ባለሙያ ነው፡፡ “ከእንግዲህ አርጅቷል፣ ዋጋ የለውም” ብለው የተፈጥሮ ጌጡን ጋማውንና ጭራውን - ቢሸልቱት እንኳ ኮርቻ በጫኑት ጊዜ ከተፈጥሮው የማያዛንፍ አመሉ ይመጣበትና መቅበጥበጥ ይጀምራል፡፡ ጀግናም ጥቃትን የሚሸከምበት ትከሻ ስለሌለው መቅበጥበጡ መቁነጥነጡ አይቀሬ ነው - ጥቃትን ለማጥቃት፡፡
በለው በእናት አልቢን - አስሂደው በዋንዛ፣
በእናት አገርና በሚስት የለም ዋዛ፡፡
ተቀመጥ ጠላቴ - ወዳጄ መስለህ፣
አውድማ ለቅልቄ - እስካበራይህ፡፡
ከዘና ነው ከዘና ነው ዕርቁ፣
አውድማው ይለቅለት - በሮችም አይራቁ፡፡
አይረባ ዘጭ ዘጭ - እየገባህ ታረቅ፣
ገሳ ዝናብ እንጅ - አያድንም መብረቅ፣
ምከሩት ያንን ሰው - ያን አጉል ደንቆሮ፣
እሳት ሊበላው ነው - በገዛ እጁ ጭሮ፡፡
ሁሉም “ልክ” አለውና፣ የተጋፈጠው የጀግና ልጅ ትዕግስት፣ ጠላቶቹን የሚያነድ ወላፈኑ የሚጋረፍ ምህረት የለሽ እሳት ይሆናል፡፡ ጀግና ታጋሽ ነው ሲባል ዘልዓለም ይታገሳል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉንም ችሎ ይታገሳል ማለትም አይደለም፡፡ ከምንም በላይ በሃገሩ ከመጡበት ትዕግስት ብሎ ነገር፣ መቻል ብሎ ቀልድ አያስቅም፡፡ በልፍስፍስ ዕርቅም አያምንም፡፡ ዕርቅ ከሆነ ዕውነተኛ ሰላምን የሚያመጣ እንጅ ለይምሰል ብቻ ከሚያደርግ የውሸት እርቅ፣ ጭልጥ ያለ ጠብ ይመረጣል - በጀግና ዘንድ፡፡ ብዙ የታገሰ ጀግና ጠላቱን መክሮና አስመክሮ አልሰማህ ሲለው ደግሞ በጠንካራ ክንዱ አደባይቶ ማንነቱን ያስመሰክራል፡፡ በዚህ ጊዜ በጉራ ተኮፍሶ የነበረው ጠላት የተነፈሰ ፊኛ መስሎ ተጣጥፎ ከወደቀበት ውርደት ሳይነሳ፣ የጀግና ስም በተነሳ ቁጥር ሲቃዥና ሲወራጭ ማደር ይጀምራል፡፡ ለዚህም
“በነብሩ መኝታ - ፍየል ተገኝቶበት፣
ሲበረግግ ያድራል በልሙ እየመጣበት”
እየተባለ ለጀግናው ድልና ጠላቱ ለተከናነበው የጨለማ ህይወት ይገጠምለታል፡፡ ጀግና በጀግንነቱ እንደተከበረ እንደታፈረ፤ ፈሪ በፈሪነቱ እንደተናቀ እንደተዋረደ ይኖራል፡፡

Published in ጥበብ

ከ“ያልታተመው መግቢያ” ግለ - ታሪክ መጽሐፌ የተወሰደ)

ማርጋሬት ሚሼል መጽሐፏን ጽፋ ለመጨረስ አሥር ዓመት ፈጅቶባታል - ከ1926 -1936 ዓ.ም!! ይኼውም ታማ የአልጋ ቁራኛ ሆና በነበረበት ጊዜ ነው፡፡
እኔም የማርጋሬት ሚሼልን Gone With The Wind “ነገም ሌላ ቀን ነው” ብዬ ለመተርጐምና ለማሳተም አሥር ዓመት ፈጅቶብኛል - ከ1980-1990፡፡ የማርጋሬት ህመምና የኔ ህመም ባይመሳሰልም ሁለታችንም ህመምተኞች መሆናችን ያቀራርበናል፡፡ እሷ ቁርጭምጭሚቷን ታማ የአልጋ ቁራኛ፡፡ እኔ ደሞ የሀገር ህመም ታምሜ የእሥር ቁራኛ!
መጽሐፉን እተረጐምኩበት ቦታ ለመድረስ ብዙ ተጉዣለሁ፡፡ ብዙ ደክሜያለሁ፡፡ እንዴት? ለምን? የት? መቼ? ከማጋር? እነሆኝ:-
ጐን ዊዝ ዘ ዊንድ (ነገም ሌላ ቀን ነው) የተተረጐመበት ቦታ ከላይ ጣራ ቢኖረው ኖሮ ዋሻ ይመስላል፡፡ ብዙ የሚውጥ፣ ጥቂት የሚተፋ የድንጋይ ዋሻ፡፡ ግርግዳው ግንብ፣ ጣራው ግንበ፣ ወለሉ ሲሚንቶ፡፡ የዋሻው ኮሪዶር የታደለ ሲሚንቶ ነው፡፡ በየቀኑ በኦሞ ይፈተጋል፡፡ ነፃ ጉልበት ይፈስስበታል፡፡ ቁጥሩ የማይታወቅ ውሃ በባሊ ይቸለስበታል፡፡ ስለዚህ ማንም የዚያ ዋሻ አባል ያልሆነ የውጪ ዓለም ሰው ከሚገምተው በላይ ንፁህ ነው፡፡ ነዋሪው ህዝብ ሲተባበርና ሲረዳዳ ለጉድ ነው፡፡ ፕሮግራም አውጥቶ ተራ ገብቶ ግቢዬ የሚለውን የዋሻውን ኮሪዶር ከሚገባው በላይ ያፀዳዋል፡፡ ምናልባትም የውጪውን ዓለም ቤቱን ከሚያፀዳበት ሺ ጊዜ በበለጠ፡፡ ለራሱ ጤንነት ሲል ነዋ!
የዋሻው ሆድ - ዕቃ በርካታ ሰዎችን በውስጣቸው ያጐሩ ዘጠኝ ክፍሎችን ይዟል፡፡ በተዛነፉ አራተ ባንድ ፎት አምስት በአንድ ፊት፡፡ ክፍሎቹ የብረት መዝጊያ አላቸው፡፡ የብረቶቹ መዝጊያዎች እክፍሉ ውስጥ ያሉትን ሰዎች በደምብ ይጠብቃሉ፡፡ ብረት ናቸዋ መዝጊያዎቹን ደግሞ የሚጠብቁ በጣሪያ የለሹ የዋሻ ኮሪደር አናት ላይ ካናት ጥግ እና ጥግ ሆነው ቁልቁል ያፈጠጡ የብረት አፈሙዞች አሉ፡፡ የብረቶቹ አፈ - ሙዞች የብረቶቹን መዝጊያዎች ማንም እንዳይነካቸው ይጠብቁዋቸዋል፡፡ አፈ - ሙዞቹ ጠንካሮች በመሆናቸው አስተማማኝ ናቸው፡፡ ግን እነሱም ቢሆኑ ጠባቂ አላቸው፡፡ የያዙዋቸው እጆች በደምብ ይጠብቋቸዋል!! የእጆቹ ባለቤቶች ኮስተር ኮስተር ያሉ ጭካኔን የተካኑ፤ በየጊዜው የሚለዋወጡ የቀንና የሌሊት ተረኛ ሰዎች ናቸው፡፡ ለጠባቂው ሁሉ ጠባቂ አለው - አለቃ፡፡ እንግዲህ የብረቶቹ አለቃ ሰው፣ የሰው አለቃ ደግሞ ሌላ ሰው ነው፡፡ ከዚያም በላይ፣ ከዚያም በላይ በላይ የሆነ የበላይ ሰው አለ፡፡ ለጠባቂው ሁሉ ጠባቂ አለው!! እንዲህ እንዲህ እያለ ፍጥረቱ ሁሉ ሲጠባበቅ ይኖራል!
ከእነዚያ እዋሻው ክፍሎች ውስጥ ከታጐሩት ሰዎች፣ እሥረኞች፣ ማህል እንደብረቱ መዝጊያ ብረት ልብ ያላቸው አሉ፡፡ ከጥጥ የተሠራ ይመስል የሚሳሳ፣ የሚባዘት፣ የሚዳወር የሚበጫጨቅ፣ ልብ ያላቸውም አሉ፡፡ ከጥጡ እስከ ብረቱ ልብ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ያ የብረት መዝጊያ በዓይነ ቁራኛ ይጠብቃቸዋል፡፡ ለአንዳቸውም አልራራ ባይ ነው፡፡ አልፎ አልፎ መርጦ ከሚያስወጣቸው በቀር፡፡ አንዳንዴ ገርበብ ብሎ ይከፈትና ትንሽ አየር ይመፀውታቸዋል፡፡ (የእስረኞች የስር ስነ- ስርዓት ኃላፊ የሚባል አለ፡፡ አየር ያከራያል ለ5 ደቂቃ 5 ብር ያስከፍላል፡፡ ፍቃድ የሌለው የአየር ነጋዴ ወን! ወደፊት እናየዋለን የክፍሉ በር) ሲያሰኘው በደምብ ብርግድ ብሎ ይከፈትና በሙሉ ሣምባቸው አየር እንዲተነፍሱ ይፈቅድላቸዋል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጠባቂው ከከፋው፣ ወይም የጠባቂው ጠባቂ ከከፋው ወይም ሌላኛው ጠባቂ የሚኖርበት ሠፈር ሰላም ካልሆነ፣ ያ የብረት መዝጊያ ጥርቅም ብሎ ይዘጋና አትተንፍሱ! አትናፈሱ! አትጠጉኝ! ዋ ዛሬ ሁልሺም ቀንሽ ደርሷል! ይላል፡፡ ለምሳሌ ከከርቸሌ እስረኛ ካመለጠ በቃ አለቀልን ብረት መዝጊያው አንድ ሁለት ቀን ተከረቸመ ማለት ነው፡፡ ብረት መዝጊያው አንዳንዴ ተዓምር ይሠራል፡፡ ጠባቂዎቹን በጥበብ ከጣራው ያወርዳቸውና እክፍሉ ውስጥ አስገብቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ እነሱም ይታሰራሉ፡፡ ከእሥረኛ ይቀላቅላቸዋል፡፡ ጠባቂውን ተጠባቂ ያደርገዋል! እሥረኛ ዜጋ!
የእሥር ቤት ማህበራዊ ኑሮ
በየክፍሉ የሚኖሩት ዜጐች የራሳቸው የአኗኗር ዘዴ አላቸው፡፡ ማኅበራዊ ኑሮ ይባላል፡፡ የዛው ዋሻ መከራና ረሀብ የፈጠሩት ኑሮ ነው፡፡ በየትኛው ዘመን እንደተመሠረተ ባይታወቅም የመጀመሪያዎቹ ከቤቱ ከዋሻው ጋር የተሠሩት እሥረኞች የፈጠሩት ሳይሆን አይቀርም የሚል ጠንካራ ግምት አለ፡፡ አብሮ ይበላል፡፡ አብሮ ይጠጣል፡፡ አብሮ ይተኛል፡፡ አብሮ ይወጋል፡፡ አብሮ ይነጋል፡፡ አብሮ ይገፋል፡፡ በለስ ካልቀናም አብሮ ይሞታል፡፡ ማኅበራዊ ህይወትና ማኅበራዊ ሞት የዚያ ዋሻ ዜጐች ተገደው የፈቀዱት ደምብ ነው፡፡ ከአብሮ መኖሩ ጋር ሀሳብን ለመክፈል ሲባል መጨዋወትና መዝናናት አይቀርም፡፡ የስቃዩ ዋሻ ከአብራኩ ፌሽታን የሚወልድበት ጊዜ አለ፡፡ ከምጥ በኋላ እልል ማለትን ሰው ያውቅበት የለ? ታዲያ ሲዝናኑ የውጪውን ዓለምም ይረሱታል፡፡ ህልማቸውም ቅዠታቸውም ከዋሻ ህይወታቸው ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ህልምም ይታሠራል! ያሰኛል! ለካ እዋሻው ሆድቃ ሲገቡ ብዙ ነገር ይረሳል፡፡ ቤት ንብረት ይረሳል፡፡ ሠርግና ቀብር ይረሳል፡፡ የቅርብ የሥጋ ዘመድም ቢሆን፤ በየቀኑ ስንቅ ባያመጣ ኖሮ መረሳት አይቀርለትም ነበር! ከሁሉ ነገር ይልቅ፣ ከሰውም ይልቅ ዜጐቹ ሁሉ የማይረሱት የታሠሩበትን ጉዳይ ነው፡፡ እራስ አይረሳማ! ከራስ በላይ ንፋስ ወይም ከራስ በላይ ጠባቂ ነው እንግዲህ በዜጐቹ አኗኗር ውስጥ ካሉት ህግጋት ውስጥ የኢኮኖሚ ህግጋት፣ የአመጋገብ ህግጋት፣ የጤና አጠባበቅ ህግጋትና የመዝናናት ህግጋት አሉ፡፡ ሁሉም ህግጋት ደህና ፀሐፊ ቢያገኙ ወደል ወደል መጽሐፍ ይወጣቸዋል፡፡ እኔ ለመግቢያ ያህል የመዝናናቱን ነገር ባጭሩ አነሳዋለሁ፡፡
በየክፍሉ የሚኖሩት ዜጐች የመዝናኛ ተጠሪ የሚባል አንድ አንድ ሰው ይመርጣሉ፡፡ በዛ ዘመን እንደዛሬው የግቢ መዝናኛ ኮሚቴ አልነበረም፡፡ የግቢ መዝናኛ ኮሚቴ አሁን በቅርቡ የተፈጠረ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ የምናወራው የአንዱን ክፍል ተጠሪ ጉዳይ ብቻ ይሆናል፡፡ የመዝናኛ ተጠሪው ዋንኛ ኃላፊነቱ አዲስ ሰው ሲመጣ በዘልማድ በየፖሊስ ጣቢያው እሥር ቤት “የሻማ” እየተባለ የሚጠራውን ከውጪው አለም (ከሞላ ጐደል ከተመቸ ኑሮ የመጣ ነው ተብሎ የሚታመነውን አዲስ ገቢ (ያው ለወጉ) “እንኳን ደህና መጣህ!” ለማለት የቤቱን ሰው ይሰበስብና ሁለት ዓይነት ጥያቄዎችን ይጠይቀዋል፡፡ አንዱ የኢኮኖሚ፡፡ አንደኛው የመዝናኛ፡፡ የኢኮኖሚ የሚባለው እነዚያ ከአንድ ወር እስከ አራት አምስት ዓመት ዋሻው ውስጥ የቆዩ ዜጐች ይበሉት ምግብ፣ ይለብሱት ልብስ፣ ይጠጡት ሻይ የሌላቸው በመሆናቸው ካዲሱ ዜጋ ጥቂት የኢኮኖሚ ምፅዋት ብናገኝ ብለው እጅህ ከምን? የሚሉበት ዘመናዊ ልመና ግን ከህልውና ሊነጠል የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ አዲሱ ሰው የዜግነት መታወቂያውን ለማግኘት ለነባሮቹ ዜጐች አቅሙ የፈቀደውን ለመርዳት ቃል ይገባል፡፡ የደነገጠ ዘመድ ወዳጅ ገንዘብ ሲልክለት የቃሉን ይፈጽማል፡፡ ሌላኛው ጉዳይ መዝናኛ የሚባለው ሲሆን አዲሱ ዜጋ ከኢኮኖሚው ጥያቄ ባላነሰ ሁኔታ ማሟላት ያለበት ግዴታ ነው፡፡ ወይ መዝፈን ወይ መቀለድ አሊያም ሰውን ጥቂት ያጫውታል፣ ያዝናናል የሚለውን ነገር መናገር ነው፡፡ የራሱንም አስገራሚ የህይወት አጋጣሚ ቢሆን፡፡ ይህን ሲፈጽም ሙሉ ዜጋ ይሆናል፡፡ የውጪውን ዓለም ዜግነቱን ሽሮ የዋሻውን ዓለም ዜግነት ያገኛል፡፡ ማለት ነው የመኖሪያ ፍቃዱን ይወስዳል፡፡ የመታሠር መብቱን ያስከብራል፡፡ የመታሠር ሊቼንሳውን ይረከባል፡፡
ከዚያ ወዲያ ነፃነት የሚባል፣ አገር፣ እንደልብ መሆን፣ የሚባል ነገር የት አግኝቶት፡፡ ዓለምን በሰላም ጭብጥ ኩርምት ብሎ ይገፋል፡፡ ያ ምልዕተ - እሥረኛ ገበያ ቀዝቅዞ ወደዋሻው የሚገባ ሰው ሲጠፋ አዲስ ወሬ የሚያመጣለት፣ አዲስ ፊት የሚያሳየው፣ አዲስ እርጥባን የሚለግስለት ትኩስ ዜጋ ያጣ ጊዜ፤ አቤት ያለ ዐይን ማፍጠጥ! አቤት ያለ ድብርት! አቤት የሰው ረሀብ! አቤት መሰላቸት! ደግነቱ ዜጋ ሆዬ ከረጅም ጊዜ ልምዱ በመነሳት እርስ በርስ ተፋጠን ከምንሰለቻች ጨዋታ እንፍጠር! ከምንደበር መላ መትተን ጊዜ እንግፋ ይላል! ለዚህ እንግዲህ ቴያትር ያዘጋጃል (ባይፈቀድም ውስጥ ውስጡን ተስማምቶ ድምፁን አጥፍቶ ይሠራዋል) ግሩም ቴያትር ያውም ድምጽ አጥፍቶ ተሠርቶ!
የዳማ፣ የቼዝ፣ የዶሚኖ ውድድር ማዘጋጀትም ተለምዷል! ቢንጐ ያጫውታል በየክበቡ አዲሳባ እንደሚታየው  የተሟላ አይደለም፡፡ ኑሮ ካሉት ፍሪጅም ይሞቃል፡፡ እዚህም በሲጋራ ካርቶን ሠንጠረዡን ሠርቶ የብርቱካን ልጣጩን ቆራርጦ የሠንጠረዡን ቁጥሮች በልጣጭ እየደፈነ ቢንጐውን ይከሰሳል! ኧረ ብዙ ጨዋታ ይፈጥራል! ሞገደኛ እሥረኛ! እጅ እግሩን በካቴና በፌሮና በእግረሙቅ ቢጠፍሩት፣ “አንጐሌን አላሳስር!” ብሎ በር ተዘግቶበት፣ በስንት ጠባቂ አፈሙዝ ተደግኖበት እንኳ የውጪውን ዓለም ጨዋታ እንደልቡ ይጫወታል፡፡ ነገር የገባው እስረኛ እንዲህ ነው!
ተው ሲሉት በጄ አይል - በምናቡ እሩቅ አገር ይሄዳል!
ሌላው መዝናኛ መጽሐፍ ነው፡፡ በዛ ቢባል በዚያ ዋሻ ውስጥ በእኔ ጊዜ ሁለት ወይ ሶስት መጽሐፍ አለ፡፡ ለዛ ሁሉ ዜጋ መቼም ገጽ እየተበጨቀ ካልተሰጠ በቀር ለንባብ ማዳረስ አይቻልም፡፡ ስንት የተጠማ ዐይን፤ ስንት የተጠማ አዕምሮ እዚያ ታጅሎ ሁለት መፅሐፍ እንዴት ትብቃው? ያም ሆኖ ሰው መች ዘዴ ያጣል ወንድሜ! በስክ ያነበዋል፡፡
ስክ የዋሻው ውስጥ መዝገበ - ቃላት ያፈራው ቃል ነው፡፡ ያው የመከራ ምጥ የወለደው መግባቢያ! ልክ እንደተናጋሪዎቹ!  አመጣጡ እንደሚከተለው ነው፡- ያ እስር ቤት ክፍሉ ጠባብ ነው፡፡ ዜጋው ብዙ ነው፡፡ የቆዳ ስፋትና የህዝብ ብዛት አልተመጣጠኑም፡፡ ያለ ፕላን እያሠሩ ምርቱ በዝቶ መጋዘኑ ተጣቧል፡፡ ብቻ ምን ያረጋል፤ ሰውም ሠራ የሚባለውን ወንጀል በፕላን አይሠራ! እንዳመቸው ይሯሯጣል፤ ሳይዘጋጅ ይታሠራል፡፡ መች ተማረ! (ማንስ ከማን መች ልማር ይላል፡፡ ዝም ብሎ በየተራ ይታሠራል፤ ይቀፈደዳል) ታዲያ ያ የተትረፈረፈ ዜጋ ማታ ልተኛ ሲል ስንቱ ሊተኛ?! ቦታ የለም፡፡ እንግዲያው መላ ምቱ ተባለ፡፡ መላ ተመታ፡፡ ዘዴ ተገኘ፡፡ በፈረቃ መተኛት፡፡ ተፈራርቆስ መች ሆነ፡፡ ያለ ፕላን የሚታሠረው ታሣሪ ዜጋ በላይ በላዩ ሲመጣ በፕላን የሚተኛውን ፕላነ - ቢስ ያደርገዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በተቻለ ተጣቦ የመተኛት የመጨረሻው የቦታ ቁጠባ ፕላን ተነደፈ፡፡ ጐጆ እሚባል የቦታ ሽንሸና ተመሠረተ፡፡ አንዱ ክፍል አራት ጐጆ ይኖረዋል፡፡ አራቱ ጐጆዎች የክፍሉን ዜጋ ሁሉ በእኩል ተካፍለው ያስተናግዳሉ፡፡ የሚበላው ምግብ የጎጆው ነው፡፡ የሚነጠፈው አንሶላ የጐጆው ነው፡፡ የሚለበሰው ብርድልብስ የጐጆው ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም የጐጆው ነው፡፡ ጐጆው የክፍሉን አንድ አራተኛ ክልሉን ጠብቆ ለመተዳደር እጅግ ተጠጋግቶ መተኛት ነበረበት፡፡ ተኛ፡፡
 ታዲያ እራስ ለራስ ተገናኝቶ ሲተኙ ብዙ ቦታ መያዝ መጣ፡፡ ለዚህ ሌላ መፍትሔ ተገኘ፡፡ እራስጌና ግርጌ እየሆኑ መተኛት፡፡ አንደኛው ያንደኛውን እግር አቅፎ መተኛት፡፡ ስሙንም “ስክ” አሉት፡፡ ሰው እንደጨፈቃ ተጨፍቆ፣ እንደ አሹቅ ሾቆ፣ ሰው በሰው ማህል ተሰክቶ የሚያድርበት ዓለም “ስክ” ተባለ፡፡ ሆኖም ሙሉ ለሙሉ ጥበቱ አልተገወደም፡፡ እንደገና ሰብስቦ መላ ተመታ፡፡ በጀርባ ወይም በደረት መተኛት ዋና የቦታ ጠር ነው ተባለ፡፡ በተግባር ታየ፡፡ ዕውነት ሆነ፡፡
 ሁልህም በጐን በጐንህ ተኛ - ይዞታህ በጐንህ ስፋት ልክ ነው የሚል ህግ ወጣ፡፡ ይኸውም ከሰውነት ሁሉ ጠባቡ ስፋት ያለው በጐን በኩል ነውና በሰያፍ የሚተኛበት ዘዴ ሆኖ ፀደቀ፡፡ ስሙንም “ጩቤ ስክ” አሉት፡፡ የሰው ስለቱ ተገኘና “ጩቤ” የሚል ስም ወጣለት ማለት ነው፡፡ ይሄ ስክ የሚል ቃል አገልግሎቱ እንደ እሥር ዘመኑ ስፋትና እንደመጪው ዜጋ ብዛት ተስፋፋና መጽሐፍ ለማንበብም ዋና ዘዴ ሆኖ ተገኘ፡፡ የቀኑ ሃያ አራት ሰዓቶች በየአንድ አንድ ሰዓት ሃያ አራት ቦታ ይሸነሸኑና ሃያ አራት ሰው ይመደብባቸዋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው አንድ ሰዓት ይደርሰዋል፡፡ በዚሁ ጊዜ ሰዓቷን ሳያባክን ያነብባታል፡፡ እንግዲህ በቀኑና በማታው ጊዜ ውስጥ ሃያ አራት የመጽሐፍ ስክ አለ ማለት ነው፡፡
በዚህ ዓይነት የንባብ ስክ ሥርዓት ከፍተኛ የመነበብ ዕድል በማግኘት፣ ብትንትኑ እስኪወጣ ድረስ ህልውናው እፈተና ላይ የወደቀ ታላቅ መጽሐፍ፤ የማርጋሬት ሚሼል ጐን ዊዝ ዘ ዊንድ ነበር፡፡
ዘመነኛ ጓደኞቹ የሆኑት መጻሕፍት በሁለት በሦስት ዓመት ጡረታ ሲወጡ፤ እሱ በታተመ በሰላሳ ስድስት ዓመቱ፣ የወላጅ እናቱን የማርጋሬትን ዕድሜ ተሸክሞ፣ ጥቁር ከነጭ ፀጉር ካበቀለ በኋላ እንኳ፤ ጭራሽ ጉርምስና ተሰምቶት የቀኑ አልበቃው ብሎ ሌሊቱን ሙሉ ከእጅ ወደእጅ ሲዞር፤ ሲነበብ ያድራል፡፡ ሰዓት እላፊ - አያቅ፣ ዘመን - እላፊ አያቅ፣ ድንበር - እላፊ አያቅ እንዲሁ የጊዜና የቦታ ኬላ እንዳጣሰ ኖሮ፤ ይኸው ይባስ ብሎ እሥር ቤት ድረስ ገብቶ የዜጐቹን እንቅልፍ ይነሳል! በዚህ ሁኔታ እንቅልፍ ካጡት ዜጐች ማህል እኔ አንዱ ነኝ፡፡ ማንበብ ከጀመርኩበት እስከጨረስኩበት ሰዓት ድረስ አገሬን አገሬን እንደሸተተኝ ቆየ፡፡ ደግሜ ስክ ገባሁ፡፡ አነበብኩት፡፡ ከዜጐች ጋር ተወያየሁበት፡፡ በጣም ወደድነው፡፡ በደምብ ካነበብኩት፣ ከወደድኩት፣ የሥነጽሑፍ ችሎታው ካለኝና ከሁሉም በላይ ደግሞ ባገሬ የእስር ዋሻ ውስጥ እያለሁ አገሬን አገሬን ከሸተተኝ፤ የማልተረጉመው ሞቼ ነው ቆሜ? ደሞስ ከመቶ ሃያ ዓመታት በፊት ሌላ አገር ውስጥ የታየ ጦርነትና አስከፊ ውጤቱ፤ ዛሬ እኔ አገር ላይ ሲዘንብ እያየሁ፤ ይህን መጽሐፍ አንብቤ፣ ተርጉሜ ላላየ ወገኔ ዐይንና አዕምሮ ብሆነው፤ ብሞትስ ብቆምስ ግዴታዬም፣ አላማዬም አይደል እንዴ!!
መተርጐም አለብኝ ብዬ፣ ግጥምና ቴያትር ከመፃፍ አልፌ ወደ ትርጉም ተሸጋገርኩ!
ትርጉም ስራውን ለመጀመር ያነሳኋቸው አምስት ጥያቄዎች በጣም ጠጣር ነበሩ፡፡
እዋሻው ውስጥ ነኛ! የራስ ነፃነት ሳይኖር ለሌላው ነፃነትን ለማሳየት ሲፍጨረጨሩ አቤት ያለው ሳንካ! አቤት ያለው እንቅፋት! አቤት ያለው በወንጀል ላይ ወንጀል የማከል ስጋት!  የመጀመሪያው ጥያቄ በምን ሰበብ ልፃፍ? መፃፍ አይፈቀድማ! 2ኛው ጥያቄ በምን ላይ ልፃፍ? ወረቀት አይገባማ! ሦስተኛው ጥያቄ በምን ልፃፍ? እስክሪብቶ ከቤት ተጠሪ እጅ አይወጣማ - የተሾመልን ቤት- ተጠሮ ደሞ ፔናውን ለራሱና ለኢኮኖሚ ተጠሪው በቀር እንዳያውል ቃል የገባ ቤት - ተጠሪ! ደግሞም የመንግስት አደራ የማይበላና አፍቅሮተ - መንግስት እልቡ ውስጥ እንደጧፍ የሚነድ ጓድ ነው - ያውም” “ግለሰብ ነው እንጂ አብዮት አላሰረኝም” የሚል! አራተኛው ጥያቄ የት ልፃፍ? ቦታ የለማ! አምስተኛው ጥያቄ - ፅፌስ? ማውጫ የለማ! ፍቺም ሆነ ግመሽ ፍፊ (ከርቸሌ)፣ ቢገኝ ሲወጡ ከጥፍር እስከ ጠጉር ተፈትሾ ነው፡፡
አንድ ሺህ ሃያ አራት ገጽ ያለው መጽሐፍ፤ ተደክሞ ተተርጉሞ (ከኦርጅናሌው መብለጡ አይቀርምና) ምን ሊኮን ነው? የገረመኝ ነገር ከጥያቄዎቹ ሁሉ ከባዱንና የመጨረሻውን መጀመሪያ ለመመለስ መቻሌ! ጽፌስ? ብዬ ጠይቄ ጥቂት ካሰብኩ በኋላ መልሴን ሰጠሁ - ባወጣ ያውጣው! ነገም ሌላ ቀን ነው አልኳ! እንደ እስካርሌት!
ይቀጥላል    

Published in ጥበብ
Saturday, 29 November 2014 11:52

ቁራሽ ዳቦ

በ1970ዎቹ አካባቢ ነበር መስፍን ሀርዲመን በኮሎኔል የወታደሮች ቡድን ወደ ፈረንሳይ የተመለሰው፡፡
ወጣቱ መስፍን መሳሪያውን ትከሻው ላይ ጣል አድርጐ፣ ኮፍያውን አይኖቹ ድረስ ደፍቶ እጆቹን በግራ ቀኝ ኪሱ ከቶ ከአንድ መጠጥ ቤት በር ላይ አቀርቅሮ ቆመ፡፡ አይኖቹን መሬት ላይ ሰክቶ የገጠማቸውን እጅግ አሳፋሪ ሽንፈት በማስታወስ በትዝታ ወደኋላ ተጓዘ፡፡
የመጠጥ ቤቱን ግድግዳ ተጠግቶ በጀርባው ያዘለውን ሻንጣ አውርዶ ከከፈተ በኋላ ዳቦ አወጣ፡፡ ዳቦውን አንዴ ገመጥ አድርጐ ማኘክ ሲጀምር መበላሸቱን ጣዕሙ ነገረው፡፡ እስከ ነገ ሌላ ምግብ እንደማያገኝ ያውቃል፡፡ የገመጠውን ዳቦ በምላሱ እያላወሰ በእንግሊዝ ካፌዎች ውስጥ ይመገባቸው የነበሩ ጣፋጭ ኮተሌት፣ በቅቤ የተጠበሰ እንቁላልና ስጋ፣ እጅ የሚያስቆረጥሙ የአትክልት ምግቦችን በህሊናው አስታወሰ፡፡ ትውስታው ዳቦውን መብላት እንዳይችል ምክንያት የሆነበት ይመስል በእጁ የያዘውን ዳቦ ወደ ጭቃ ወርውሮ ያን ያለፈ ጣፋጭ ጊዜ እያስታወሰ ትንሽ እንደተራመደ አንድ ወታደር የወረወረውን ዳቦ በፍቅር አንስቶ ከጠራረገ በኋላ የመጠጥ ቤቱን ግድግዳ ተደግፎ በሚገርም የምግብ ፍላጐት ስሜት ሲበላ ተመለከተ፡፡
ሀርዲመን በሰውየው ድርጊት ሳይገረምና ሳይሸማቀቅ ብሎም ሳይደነግጥ አልቀረም፡፡ ምን አይነት የምግብ ፍላጐት ነው? እንዲህ አይነት አውሬ ተመጋቢም አለ ለካ? ሲል በውስጡ ተገረመ፡፡
ሰውየው ቀጭንና ረዘም ያለ ሲሆን ትከሻው ሰፊ ነው፡፡ ፊቱም በጺም ተወርሯል፡፡ የገረጣ ፊቱን ተመልክቶ አመድ የመሰለ ጺሙን ላስተዋለ ሰው፣ ሰውየው ለረጅም ጊዜ በድህነት የኖረ ስለመሆኑ መገመት አይገደውም፡፡
ሀርዲመን ወደ ወታደሩ ቀረብ አለና “በጣም ርቦህ ነበር?” ሲል ጠየቀው፡፡
“ያው እንደምታየው መሆኑ ነው ነገሩ” የመጨረሻ ጉርሻውን እየዋጠ መለሰ ወታደሩ፡፡
“እንግዲያውስ ይቅርታ አድርግልኝ! ምግቡን የምትፈልገው መሆኑን ባውቅ ኖሮ አልጥለውም ነበር”
“ኧረ ምንም ችግር የለውም፡፡ የሚበላ ተገኝቶ ደግሞ እንዲህ ሊባል ነው?” ሲል መለሰ ወታደሩ፡፡
“ድርጊቴ ፀፅቶኛል፡፡ ምግቡን መጣል አልነበረብኝም” አለ ሀርዲመን
“ኧረ ግድ የለዎትም፡፡ እርስዎ ይህን አላሰቡት ይሆናል” አለ ወታደሩ
“እንግዲያውስ አንዲት በትንሽዬ ጠርሙስ ያለች ግማሽ ብራንዲ አለችኝና አብረን ብንጐነጫት” አለ ሀርዲመን
ዳቦውን በልቶ የጨረሰው ወታደር በሀርዲመን ሃሳብ ተስማምቶ ብራንዲዋን አብረው ተጐነጩ፡፡
“ታዲያ እርስዎን ማን ልበል?” ወታደሩ መስፍን ሀርዲመንን ጠየቀው፡፡
ሀርዲመን ማዕረጉን ሳይጨምር ስሙን ብቻ ነገረውና፤
“ያንተስ?” አለው፡፡
“ዥን ቪክቶር እባላለሁ፡፡ በቻቲሎን አካባቢ ስለቆሰልኩኝ እዚህ ወታደራዊ ተቋም ውስጥ እርዳታ እየተደረገልኝ ነው፡፡ የጭረት ያክል ነበር የቆሰልኩት፡፡ በሆስፒታሉ የከባድ ቁስለኛ ልዩ ማቆያ ክፍል የፈረስ ሾርባ እየጠጣሁ ጥሩ ጊዜ ነበር የሳለፍኩት፡፡ ይሁንና ዋና አዛዡ የማሰናበቻ ደብዳቤ ጻፈልኝ፡፡ ያኔውኑ ነበር ወደነበርኩበት ረሀብ ዳግመኛ መመለሴን የተገነዘብኩት፡፡ ይገርምሃል ጓዴ እንደምታየኝ እድሜ ዘመኔን ሙሉ ስራብ ነው የኖርኩት፡፡ እመነኝ ጓዴ እድሜዬን ሙሉ ስራብ!”
የወታደሩ ስሜት የተቀላቀለበት አነጋገር የእንግሊዝ ካፌዎች ለናፈቁትና ምቾትን ለሚሻው ሀርዲመን አስገራሚ ነበር፡፡ ሀርዲመን ወታደሩን ድንጋጤ በሚነበብበትና በጥልቅ አግራሞት ሲመለከተውና ወታደሩም ሀዘንን በሚያንፀባርቅ ገጽታ ፈገግ ሲል የተራቡና የተኩላ የሚመስሉ ነጫጭ ጥርሶቹ ከገረጣውና ከሰልካካ ፊቱ ጋር ይታያሉ፡፡ ወታደሩ በራስ መተማመን በተሞላበት አንደበት እንዲህ አለ፡-
“ና ጓዴ እግራችንን ለማፍታታት ያህል ትንሽ ዞር ዞር እንበል እስኪ፡፡ እኔ ተጥሎ የተገኘሁ ልጅ ነኝ፡፡ ለዚያ ነው ዥን ቪክቶር ብቻ ተብዬ የምጠራው፡፡ ምንአልባትም ሰምተኸው የማታውቀውን ታሪኬን ላጫውትህ” አለ ወታደሩ - በቅንጦትና በደስታ ላደገው ሀርዲመን፡፡
“አሳዳጊዬ በሳንባ በሽታ ከመሞቷ በፊት በዚያ አዳሪ ት/ቤት ውስጥ ከህጻናቱ ጋር ከመጫወት ይልቅ ከእሷ ጋር መሆንን እመርጥ ነበር፡፡ አቅፋ ፀጉሬን እያሻሸች ታስተኛኝ ስለነበር ከልቤ ነበር የምወዳት፡፡ እሷም ከሁሉም ህጻናት አብልጣ ትወደኝ ነበር፡፡ በኋላ የአዳሪ ትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ በርካታ ማየት የተሳናቸው ልጆችን ወደ ት/ቤቱ ሲያመጣ የምንበላው ዳቦ እየቀጨጨ ሄዶ ጭራሽ ወረቀት የመሰለ ዳቦ መብላት ጀመርን፡፡ አስተዳዳሪውና ባለቤቱ ከሞቱ በኋላ ደግሞ ረሀብ መጣ፡፡ ከእኔ ጋር ይመገቡ የነበሩት ሁለቱ ዓይነ ስውራን ልጆችም በአመጋገባችን ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ያን እንደ ወረቀት የሳሳ ዳቦ አንዴ ከሰጡን በኋላ ቀሪውን ቆልፈውበት ይሄዳሉ፡፡ ያኔ በጣም ነበር የሚርበኝ፡፡ እና ይሄ ሁኔታ የኔ ስህተት ነው? አይመስለኝም፡፡ እንደዚያ እየራበኝ ለሶስት አመት ያህል በእንጨት ስራ አገልግያለሁ፡፡ ሶስት አመት ሙሉ አየህ! የእንጨት ስራ ስልጠናው ግን የአንድ ወር ብቻ ነው፡፡ ቅድም የጣልከውን ዳቦ አንስቼ ስበላ ተገርመህ ይሆናል፡፡ እኔ ግን ከዚያ አስር እጥፍ የባሰና የደረቀ ዳቦ ሳገኝ በውሃ ወይም በምራቄ እያራስኩኝ እንክት አድርጌ ነው የምበላው፡፡ ይኸውልህ ጓዴ፤ አንዳንዴ መልዕክት ለማድረስ በምላክበት ጊዜ እግረ መንገዴን ንፋስ የጣለውን የዛፍ ፍሬና ህጻናት ወደ ት/ቤት ሲሄዱ የጣሉትን የምግብ ትራፊ እየሰበሰብኩ ረሀቤን ለማስታገስ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ ከዚህ አስከፊ ረሀብ ለመላቀቅ ስል ድንጋይ ጠራቢነት፣ ሱቅ ጠባቂነት፣ ጽዳት ከዚያም ወዛደርነት ብሰራም ራሴን በበቂ ሁኔታ መመገብ አልቻልኩም ነበር፡፡ ዳቦ ጋጋሪነት መስራት ስጀምር ለትንሽ ጊዜ ቢሆንም ከረሀብ ርቄ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ እየኖርኩ ሳለ አቅፋ ፀጉሬን እያሻሸች፣ ትሁትና ታማኝ እንድሆን አሳዳጊዬ ትመክረኝ የነበረውን ሁሌም አልዘነጋውም፡፡”
ለአመጋገቡ እንደሚጠነቀቀው ሁሉ ለአለባበሱም የሚጨነቀው ሀርዲመን፣ የዚህን ተራ ወታደር አሳዛኝ ታሪክ በእርጋታ አዳምጦ ሲያበቃ በከባድ ሀዘን ተዋጠ፡፡ አይኖቹ በእንባ ተሞሉም፡፡ ሀርዲመን ወታደሩን በሀዘኔታ ካስተዋለው በኋላ፤
“ካለኝ የምግብ ፍላጐት አንጻር የእኔ የምግብ ድርሻ በእጥፍ የሚበልጥ ስለሆነ ከአሁን በኋላ ስለ ምግብ አታስብ፡፡ ልክ እንደ መልካም ጓደኞች ሆነን ከቁርስ እስከ እራት ድረስ ሁሌም ከድርሻዬ አካፍልሃለሁ” አለው፡፡
በዚህ ጊዜ ዥን ቪክቶር እጅግ ተደሰተ፡፡ ሌሊቱን ለማሳለፍ ከወጥ ቤት የወረደ ገጽታ ወዳላትና በሳር ወደተሰራችው የዥን ቪክቶር ማደሪያ አብረው ሄዱ፡፡ ዥን ቪክቶር ረሀብ እንቅልፍ ስለከለከለው እኩለ ሌሊት ላይ ተነሳ፡፡ ወርቃማና የሴት የመሰለ ፀጉሩ በጨረቃዋ ብርሃን የሚያበራው ሀርመዲን ግን እዚያው አልጋው ላይ ተኝቶ ይታያል፡፡ ዥን ቪክቶር የተኛውን ሀርዲመንን እየተመለከተ ስለ ሩህሩህነቱና ደግነቱ አሰበ፡፡
በዚያ ድቅድቅ እኩለ ሌሊት የወታደሮቹ አዛዥ አንድ በር እያንኳኳና የአንድን ተረኛ የጥበቃ ሰራተኛ ስም ሲጣራ ተሰማ፡፡ አዛዡ ከሚጠራቸው ስሞች መካከል የሀርዲመን ስም ይገኝበታል፡፡ በከባድ እንቅልፍ ውስጥ ያለው ሀርዲመን ግን ጥሪውን አልሰማም፡፡
“ይቅርታ አዛዥ! ሀርዲመን ከባድ እንቅልፍ ውስጥ ነው፡፡ ፈቃድዎ ከሆነ እሱን ተክቼ የጥበቃ ስራውን እንዳከናውን ቢፈቅዱልኝ” በማለት ዥን ቪክቶር ለአዛዡ ጥያቄ አቀረበ፡፡
“ትችላለህ” አለ አዛዡ
ዥን ቪክቶር የሀርዲመንን ቦታ ተክቶ ከአራት ተረኛ ወታደሮች ጋር በመሆን ወደ ጥበቃ ስራው ተሰማራ፡፡ ይህ ከሆነ ከግማሽ ሰዓት በኋላ በአካባቢው የተኩስ ድምጽ ተሰማ፡፡ በተኩሱ ድምጽ ከእንቅልፉ የነቃው ሀርዲመን፤
“ስንት ሰዓት ነው? ኧረ እባካችሁ ተረኞች ነን፡፡” በማለት ከሳር ቤቷ አጠገብ ባሉ ቤቶች ውስጥ የተኙትን ጠየቀ፡፡
“ዥን ቪክቶር አንተን ተክቶ ሊሰራ ሄዷል” በማለት አንድ ወታደር መለሰለት፡፡
ወዲያውም ለጥበቃ ከወጡት ወታደሮች መካከል አንዱ ወደ ሳር ቤቷ እየሮጠ በመምጣት ፐርሺያኖቹ ጥቃት እንዳደረሱ ገለፀ፡፡
“ጓዶቹስ?” ሀርዲመን ለወታደሩ ጥያቄ አቀረበ፡፡
“ከዚያ ምስኪን ዥን ቪክቶር በስተቀር ሁሉም አምልጠዋል” መለሰ ወታደሩ
“ዥን ቪክቶር!” አለ ሀርዲመን በከባድ ድንጋጤ ተውጦ
“አዎ! ምስኪኑ ዥን ቪክቶር ጭንቅላቱን በጥይት ተመቶ አንዲት ቃል እንኳ ሳይተነፍስ ነው የወደቀው” ሲል ወታደሩ ሀዘን በተሞላበት ቅላጼ መለሰ፡፡ ሀርዲመን በአንድ የክረምት ወቅት አመሻሽ ላይ ሳሉሰን ከሚባል መስፍን ጋር እየተዟዟረ ሳለ ቁራሽ ዳቦ ወድቆ አየ፡፡ ዳቦው ጭቃ የነካውም ነበር፡፡ ሀርመዲን ዳቦውን አንስቶ በትከሻው አንጠልጥሎ በያዘው ቦርሳ ውስጥ ከተተው፡፡ ይህን የሀርዲመንን ድርጊት የተመለከተው መስፍን ሳሉሰን፤
“አንተ አብደሃል! ጭቃ ላይ የወደቀ ዳቦ አንስተህ ልትበላ ነው እንዴ?” በማለት እየሳቀ ጠየቀው፡፡
“ይህ በጭቃ የተለወሰ ቁራሽ ዳቦ ቅንጣት ሳይሳሳ ህይወቱን አሳልፎ የሰጠልኝ የወታደሩ ዥን ቪክቶር ማስታወሻ ነው፡፡ በክብርም አኖረዋለሁ፡፡ አትሳቅ ከምሬ ነው” በማለት ለመስፍኑ የአግራሞት ጥያቄ ሀርዲመን መልስ ሰጠ፡፡

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 29 November 2014 11:48

“አዱኛ” ፊልም ሊመረቅ ነው

በስንታየሁ ካሣሁን ተደርሶ በምንተስኖት አስቻለው የተዘጋጀው “አዱኛ” ፊልም ነገ ይመረቃል፡፡
ወንጀልን፣ ፍቅርን፣ ክፋትና ደግነትን መሠረት አድርጐ የተሰራው ይኸው ፊልም አንድ ሰዓት ከሃያ ደቂቃ ጊዜን የሚወስድ ሲሆን ፊልሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ እንደወሰደባቸው የፊልሙ አዘጋጅ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ በፊልሙ ላይ ነብይ አንዋር፣ መሰረት ባጫ፣ ኖአሚን ሳሙኤል፣ ማሩ እንዳለና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ ፊልሙ ነገ በ8፣ በ10 እና በ12 ሰዓት በሁሉም የመንግሥት ሲኒማ ቤቶች ይመረቃል፡፡

በሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ የተዘጋጀና “አመሰግናለሁ” የሚል ርዕስ የተሰጠው የስዕል አውደርዕይ ትናንት በካፒታል ሆቴል ተከፈተ፡፡
ለአስራ አራት አመታት ሰውነቱን ማንቀሳቀስ ተስኖት በጀርባው ብቻ ተኝቶ የኖረው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኖ የሠራቸውን 40 የቀለም ቅብና ሪልፍ የባህል ሥራዎች በአውደርዕዩ ላይ አቅርቧል፡፡
ሰዓሊው በህመም ላይ በቆየባቸው አመታት ከጐኑ ባለመለየት ድጋፍና እንክብካቤ ያደረጉለትንና ባለፈው ሕዳር ወር በኪቶር ሆስፒታል የተካሄደውን የተሣካ የቀዶ ህክምና ለማድረግ እንዲችል የረዱትን ሁሉ ለማመስገንና ያደረጉለትን እንክብካቤ ለማሰብ አውደ ርዕዩን “አመሰግናለሁ” የሚል ስያሜ እንደሰጠውም ተናግሯል፡፡ ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ ለአስራ አራት አመታት ሰውነቱን ማዘዝ ተስኖት በጀርባው ተኝቶ ከቆየ በኋላ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር በኪዩር ሆስፒታል በተደረገለት ቀዶ ህክምና ለመቀመጥ መቻሉንና ይህም ታላቅ ደስታ እንደሰጠው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡  

Saturday, 29 November 2014 11:42

ፍቅርተና የፍቅር ዲዛይኗ

በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪና ስነ አእምሮ ያጠናችው ፍቅርተ አዲስ፣ በአልባሳት ጥበብ (ፋሽን ዲዛይን) የተዋጣላት ባለሙያ ናት፡፡ ከአራት ሺ ብር ገደማ አንስቶ እስከ 20 ሺ ብር የሚያወጡ የሰርግ ልብሶችን ለበርካታ ደንበኞች ማዘጋጀት፣ በተለይም በሰርግ ወራት ፋታ እንደሚያሳጣ የምትናገረው ፍቅርተ፤ የአልባሳት ጥበብን ኑሮና መተዳደሪያዋ አድርጋዋለች፡፡ ከሞሮኮ እስከ ጃማይካ፣ ከፓሪስ እስከ ኒውዮርክ በርካታ ትርኢቶችን አቅርባም እውቅናና ሽልማት አትርፋበታለች፡፡ ነገር ግን የስነ አእምሮ ትምህርቷ ባክኖ አልቀረም፡፡ የስራዋና የህይወቷ አካል ሆኗል፡፡ ቢቻል ሁሉም ሰው፣ በተወሰነ ደረጃ የስነ አእምሮና የፍልስፍና እውቀት ቢኖረው ይመረጣል ብላ ስትናገር ለወጉ ያህል አይደለም፡፡ ከአለባበስና ከአረማመድ ጀምሮ፣ የጨርቅ ቀለም ምርጫና የልብስ ዲዛይን ፈጠራ፤ የሰርግ ውድ ልብስና የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ሳይቀር ከስነ አእምሮ ጋር ይገናኛል፡፡ የስራ ባልደረቦች ግንኙነትና የቤተሰብ ሁኔታ፣ የደንበኞች ፍላጎትና መስተንግዶም እንዲሁ፡፡ የአገር ገፅታና የዓለም ገበያ፣ የፆታ ጥቃትና የልጆች አስተዳደግ ከስነ አእምሮና ከፍልስፍና ጋር የተያያዘ ነው ለፍቅርተ፡፡ ተወልዳ ባደገችበት አዲስ አበባ “የፍቅር ዲዛይን” የተሰኘ ቢዝነስ የከፈተችው ፍቅርተ፤ ስለ ልብስ ምርጫ እንዲህ ትላለች - ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት እቁባይ፡፡

ብዙ ሰው፤ ፋሽን ነው ተብሎ የሚመጣውን ነገር ሁሉ መልበስ ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ይስማማዋል ማለት አይደለም፤ የራስን የሰውነት ቅርፅና ቁመና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በዚያ ላይ ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ የግል ማንነት አለው፡፡ ፕሮፌሽናል ዲዛይነር እነዚህን ነገሮች ያገናዘበ ምክርና አገልግሎት ለደንበኞቹ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ሙያዬ ስለሆነ ደንበኞችን በደንብ አስተናግዳለሁ፡፡ ደንበኞች ሲመጡ፣ ለሰውነታቸው ቅርፅና ቁመት፣ ለሚፈልጉት ፕሮግራምና ዝግጅት፣ ለሚለብሱበት ሰአትና ለማንነታቸው  የሚስማማ ልብስ  እሰራለሁ፡፡ አንዳንድ ሰዎች በጣም ጎበዞች ናቸው፣ የሚያምርባቸውን ያውቃሉ፡፡ ከነሱ ጋር የማይሄድ ነገር የሚመርጡትንም ሰዎች ማስተናገድና በሙያዊ ምክር ማስተማር በጣም ደስ ይለኛል፡፡ ለምሳሌ ጋቢ ወይ ቡፍ የሚል ቀሚስ፣ ወፈር ላለ ሰው አይመከርም፡፡ ይህን የሚመርጡ ሲመጡ፣ ቁጭ ብዬ ጊዜ ሰጥቼ በተለያዩ ጨርቆች የተሰሩ ልብሶችን እየሞከሩ እንዲያዩ እና እንዲመርጡ እረዳቸዋለሁ፡፡  እኔ በጣም የሚያረካኝ አንድ ልብስ ጀምሬ ስጨርስና  የሰራሁላቸው ሰዎች በጣም ሲደሰቱ ሳይ ነው፡፡

የስነ አእምሮ ትምህርት - የአልባሳት ጥበብ
የመጀመሪያ ዲግሪዬን በኤዱኬሽናል ሳይኮሎጂ፣ የሁለተኛ ዲግሪዬን ደግሞ በዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ አግኝቻለሁ፡፡ የስነ አእምሮ ትምህርት በዚያው መስክ ላይ ለመቀጠር ሳይሆን በአጠቃላይ ለህይወቴ ጠቅሞኛል፡፡ እንዲያውም ገና ተምሬው አልጠገብኩም፤ ወደ ላይ እቀጥላለሁ፡፡ በእርግጥ ትምህርቱ ከስራ እና ከቤተሰብ ሀላፊነት ጋር በጣም ይከብዳል ግን በየእለቱ ሀያ አራት ሰአት አለሽ፡፡ የኛ የሰዎች ፋንታ፣ ቅድሚያ ለምትሰጪው ነገር ሰዓት መስጠት ነው፡፡  ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ አፕሪፍስ በተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ተቀጥሬ፤ ጥቃት ለደረሰባቸውና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለተጎዱ አማካሪ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ ህፃናቱ ከቤተሰቦቻቸው እና ከማህበረሰቡ ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት የስነልቦና ምክር በመስጠት እንዲዘጋጁ እረዳቸዋለሁ ማለት ነው፡፡ በዚህ ስራ ትልቁ የተማርኩት ነገር ምን መሰለሽ? ለነዚህ ልጆች የቱንም ያህል የስነልቦና እና ማህበራዊ ድጋፍ ብትሰጫቸው ኢኮኖሚው ላይ እሰካልተሰራ ድረስ ምንም ለውጥ አይመጣም፡፡

የዲዛይን ህይወትስ ከወዴት መጣ?
ዲዛይን ከልጅነቴ ጀምሮ ቀልቤን የምሰጠው ነገር ነው፡፡ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው የንድፍ ስዕል መስራት የጀመርኩት፡፡ እናቴና አክስቴ ልብስ ስፌት ይማሩ ነበር፡፡ ሁለቱም እየረዱኝ፣ ቤት ውስጥ በእናቴ የልብስ መስፊያ ማሽን በመቀስና በስፌት ማሽን ተለማመድኩ፡፡ የራሴን ልብሶች መለማመጃ አደረኳቸው፡፡ ልብሶቼን በተለያየ መንገድ እየቀያየርኩ፣ ገና የልብስ ስፌት ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊት ልብስ መስፋት እችል ነበር፡፡ ለራሴ ለጓደኞቼ እና ለቤተሰቦቼ ስሰራ፣ ከዚያ እነሱ የሚያውቋቸው ሰዎች ሲያዩ፣ በሰው በሰው ስራ እየመጣልኝ … ለካ ሳላውቀው ስራው ውስጥ ገብቼያለሁ፡፡ ሰዎች በአጋጣሚ አግኝተው ለሰርግ ልብስ ሰርተሽልን ነበር ሲሉኝ እደነግጥ ነበር፡፡ ከዛሬ አምስት አመት በፊት ነው ሙሉ ለሙሉ ወደዚህ ሙያ ጠቅልዬ የገባሁት፡፡ የስነ ልቦና ስራዬንና የዲዛይን ሙያዬን ደርቤ መስራት አልፈልግም፡፡ ከልጆቼ ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ ስላለብኝም ጊዜዬን በራሴ መንገድ ለመጠቀም ወስኜ፤ ይኸው እስከአሁን እየሰራሁ ነው፡፡

ትልቁ ፈተና - ፋታ የሚያሳጣ ሙያ
 ሌሎች ዲዛይነሮችም የሚጋሩት ይመስለኛል፡፡ በጣም ፈታኙ ነገር ስራን እና የቤተሰብ ህይወትን አንድ ላይ አጣጥሞ የማስኬድ ፈተና ነው፡፡ የዲዛይን ሙያ በጣም ጊዜ ይፈልጋል፡፡ በተለይ የሰርግ ወቅቶች ሲመጡ ትንፋሽ ያሳጣል፡፡ ከዚያ ውጭ ተስማምቶና  ተከባብሮ፣ ሙያውን ከልብ አፍቅሮ የመስራት ጉዳይ ነው፡፡
“የፍቅር ዲዛይን” የራሱ መርህ አለው፡፡ የአገር ውስጥ ምርቶችን እንጠቀማለን፡፡ አማራጭ ሲጠፋ ብቻ፣ የተወሰኑ የውጪ ጨርቆች ብንጠቀምም፤ ልብሶቻችን ከዘጠና በመቶ በላይ ከጥጥ የተሰሩ ናቸው፡፡ በዚያ ላይ የተማርኩት ሳይኮሎጂ ስለሆነ፣ በህፃናት የጉልበት ብዝበዛ ላይ ብዙ ነገር አውቃለሁ፡፡ በአለም ላይ የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ እጅግ ከተንሰራፋባቸው ዘርፎች ቀዳሚው የሽመና ዘርፍ ነው፡፡  የጨርቅ ምርት የሚያቀርቡልኝ ባለሙያዎች ከህፃናት ብዝበዛ የፀዱ ናቸው፡፡ ማህበራቸው “በህብረት እናምልጥ” ይባላል፡፡  ቦታ ተሰጥቷቸው ህጋዊ ሆነው የሚሰሩ በሙያው እጅግ የተካኑ ጎበዝ ሰራተኞች ናቸው፡፡ ከሁሉም ጋር ያለኝ ግንኙነት በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እነሱም ይፈልጉኛል፤ እኔም እፈልጋቸዋለሁ፡፡ ራሴን የራሴ አለቃ ሳደርግ ያገኘሁትን ነፃነት ሌሎችም እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፡፡ አንድ ሰው ከኔ ጋር አስር አመት ሰርቶ ጡረታ ይዞ ከሚወጣ፤ የራሱን ድርጅት ከፍቶ፣ እሱም በተራው ለሌሎች ሰዎች እድል ሲያመቻች ማየት ያስደስታል፡፡ የስራና የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ይፈጠራል፤ ሰዎችም ያድጋሉ፡፡ ይሄ የዘወትር ህልሜ ነው፡፡ ጥልፍ እና ኪሮሽ ከሚሰሩ ሴቶች ጋር እንሰራለን፡፡ ከሴቶች ጋር መስራት እንፈልጋለን፡፡ ግን ሴቶች ማለት እናቶች መሆናቸውንም መርሳት የለብንም፡፡ በስራ ራሳችንን ጠምደን ልጆቻችን እንዴት ሊጠፉ እንደሚችሉ ሳስበው ያስጨንቀኛል፡፡ የየቀኑ ፈተናዬ ነው፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት የተማሩትንና፣ የቤትስራ ይዘው የመጡትን፣ መከታተል የአባትና የእናት ሀላፊነት ነው፡፡  ያ ሳይሆን ሲቀር ነው፣ የተዛባ ባህርይ እየተስፋፋ አገር የሚያጠፋው፡፡ ስለዚህ እናቶች ከልጆቻቸው ሳይርቁ ቤታቸው ሰርተው በቀጠሮ ቀን እንዲያመጡ አደርጋለሁ፡፡ ለአንድ የጥልፍ ስራ እስከ 6 ሺ ብር ድረስ እከፍላለሁ፡፡

ሽልማቶች እና እድሎች
እንደጀመርኩኝ ብዙ ሾዎች ነበሩ፡፡ በዚያው አመት አሊያንስ በተዘጋጀ ውድድር ሁለተኛ ወጣሁ፡፡ ያን አጣጥሜ ሳልጨርስ፤ ሞሪሺየስ ላይ ከ12 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዲዛይነሮች የተሳተፉበት “ኦሪጅን አፍሪካ” በተባለ ውድድር ላይ አንደኛ ወጣሁ፡፡ በ2011 ኒውዮርክ የሚካሄደውን “አፍሪካ ፋሽን ዊክ” ተመርጬ አዘጋጀሁ፡፡ በ2012 እዚያው ኒውዮርክ  ውድድሩን ዲዛይነሯ ማፊ በማሸነፏ እኔ ደግሞ እንዳዘጋጅ እንደገና ተመርጬ አዘጋጀን፡፡ አሁንም ለማሳየት እየተዘጋጀን ነው፡፡ ሌላው የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም፣ አጎዋ ላይ ተሳትፈናል፡፡ ፕራግ፣ ፓሪስ፣ ጃማይካ እና ሌሎች ቦታዎችም አሳይቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ስም ሲነሳ በውጭው ዓለም የተቀረፀው መጥፎ ገፅታ ጎልቶ ይታያል፡፡ አንዳንዶቹ መጥፎ ገፅታዎች የእውነትም የሉም ማለት አይደለም፡፡ ለመለወጥ ብዙ መስራት አለብን፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ በጎ ገፅታዎችን ሳታጣ፣ መጥፎው ብቻ መጋነኑ ሚዛናዊ ስላልሆነ ያበሳጫል፡፡ በውጭ አገራት ትዕይንት ስናቀርብም የተጠቀምነውን የጨርቅ ምርትና ዲዛይኑን አይተው ሲደነቁ እጅግ ያስደስተኛል፡፡
ከሁሉም የሚበልጠው ሽልማት በስራው እውቅና ማግኘት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉንን ባህላዊ እሴቶች መማር ለኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ጨንቻ ሄጄ በተፈጥሮአዊ መንገድ ልብስ ሲያቀልሙ አይቻለሁ፡፡ ውጪ አገር ለተፈጥሮ ማቅለሚያ የሚከፈለው ገንዘብ ከአርቲፊሻሉ ይበልጣል፡፡ እነዚህን ጥበቦች መማሬ ያስደስተኛል፡፡
ገበያው ምን ይመስላል
የአገር ልብስ ተፈላጊነት እየጨመረ ነው፡፡ በፊት በጣም ጎበዝ ልጆች የነበሩ ቢሆንም ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም፡፡ በፊት ለመልስ ይፈለግ የነበረው የአበሻ  ልብስ፣ አሁን ለሰርግ የሚፈለግ ሆኗል፡፡ ዋጋው ከ3800 እስከ 20ሺህ ይደርሳል፡፡ አንድ ልብስ ስትሰሪ ለዛች ሴት ብቻ ነው የምትሰሪው፡፡ ለምሳሌ አስር ሴንቲ ሜትር ስፋት ያለው ጥልፍ፤ አንድ ጠላፊ ለወር ቁጭ ብሎ የሚሰራው ስራ ነው ለአንድ ወር ጊዜ ተሰጥቶ የተሰራው ስራ ዋጋው ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ ከሰርግ ውጪ የሚለበሱት ደግሞ 400፣ 500 ይሸጣሉ፡፡ ዋጋዬ ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ ግን የስራው እና የጨርቁ ጥራት ነው፡፡ ማሰብ ያለብን የአገር ውስተር ገበያ ብቻ አይደለም፡፡ የአልባሳት ስራ በደንብ ከሰራንበት በአለም ገበያ ተፈላጊነቱ እንደሚጨምር እርግጠኛ ነኝ፡፡

የትምህርት ቤት ዩኒፎርም  ለምን ግራጫ ይሆናል?
የመጀመሪያው ነገር ምቾት ነው፡፡ የሴት  ተማሪዎች ቀሚስ ከጉልበት በታች ሲረዝም ምቾት አይሰጣቸውም፡፡ ምቾት እና ውበትን፣ አላማንና ስብዕናን አንድ ላይ ማምጣት ይቻላል፡፡ ልጆቼን ሁልጊዜ “ቆንጆ ንፁህ ሰው ሁኑ” እላቸዋለሁ፡፡ ዝርዝሩን እድሜያቸው በጨመረ ቁጥር ያውቁታል፡፡ ነገር ግን በንፅህና ስብእና ይቃኛል፡፡ “የመታጠብ ንፅህና የልብ ንፅህና” እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ደማቅ ከለሮች ደስ ይላሉ፡፡
ልጆች ይወዳሉ፡፡ ታዲያ ለተማሪዎች ዩኒፎርም ለምን ደማቅ ቀለማት አይመረጡም ልትይ ትችያለሽ፡፡ ነገር ግን የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ምንን እንደሚወክል ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ዲሲፕሊን ወይም በስርዓት የመማር አላማን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህም ነው የትምህርት ቤት የደንብ ልብሶች በአብዛኛው በግራጫ ወይም በደብዛዛ ሰማያዊ ጨርቆች ተሰርተው የሚቀርቡት፡፡ አላማቸውን ያሳኩ ቀለሞች ናቸው፡፡ ደግሞም ያምራሉ፣ ከጥጥ የተሰሩ ቢሆኑ ግን  ደስ ይለኛል፡፡

ዲዛይን እና ሳይኮሎጂ  
ማንም ሰው ቢችል በተወሰነ ደረጃ ታሪክን፣ ፍልስፍናንና ሳይኮሎጂን ቢያውቅ ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሳይኮሎጂ የሰውን ባህርይ የሚያጠና ስለሆነ፣ የማይገባበት ነገር የለም፣ እሱን አወቅሽ ማለት፣ ህይወትን አንዴት እንደምትመሪ ቤተሰብ፣ ልጆች እንደምታሳድጊና በስራ ቦታ ባልደረቦችንና ደንበኞችን እንዴት እንደምታስተናግጂ አወቅሽ ማለት ነው፡፡ ከተፈጥሮዬም ጋር የሳይኮሎጂ ትምህርቴ ተጨምሮበት የደንበኞቼን አይን፣ የአካል እንቅስቃሴያቸውን አይቼ ስሜታቸውን ለመረዳት፣ እንዴት ልረዳቸው እንደምችል ለማሰብና መላ ለመፍጠር ትልቅ እድል ሰጥቶኛል፡፡
የኢትዮጵያውያን የልብስ ቀለም ምርጫ ከብዙ የአፍሪካ አገራት የደማቅ ቀለም ምርጫ የተለያየው ለምን ይሆን? ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶች የተለያየ የቀለም ዝንባሌ እንዳላቸው ፍቅርተ ትናገራለች፡፡
ባህላዊ ልብሶቻችን በቀለማት የተሞሉና የደመቁ ናቸው፡፡ ዘመናዊ ልብሶች ቀለም በአመዛኙ ነው ደብዘዝ ይላል፡፡ ያ ደግሞ ከውጪው ዓለም ተፅዕኖ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የዘመናዊ ልብሶች ብዙ ጊዜ ከሁለት ወይም ከሶስት ቀለሞች በላይ አይሄዱም፡፡ ጥቁር፣ ነጭ እና ዝም ያለ ቀለም ነው ይበዛባቸዋል፡፡ የባህል ልብሳችን፡፡ ደግሞ ተመልከቺ፡፡ ጥለት ውስጥ ስንት ቀለም እንዳለ አስቢ፡፡
በየዓመቱ ለማቀርባቸው አዳዲስ የአልባሳት ፈጠራዎች ለመዘጋጀት ወደ ሀረር ሄጄ ነበር፡፡ የሀረሪን፣ የሶማሌን እና የአፋርን የአለባበስ ዘይቤ ያካተተ ፈጠራ  ለመስራት ነው የፈለግኩት፡፡ ሃረር ስትደርሺ ቀለሞች ይቀበሉሻል፡፡ ግንቡ፣ ቀይ ፒንክ ነው፡፡
ጀጎል ስትገቢ ቀለሞቹ ሙቀት ይሰጡሻል፡፡ ዲዛይን እራስን የመግለጫ መንገድ ነው፡፡ አለባበስ ማንነትን አጉልቶ መናገር ይቻላል፡፡
የሀና ጉዳይ
የሚያስከፋ ነገር ነው፡፡ የማህበረሰብ ጤንነት ማጣትን ያሳያል፡፡ ኮሌክቲቭ ኮንፈርሚቲ የሚባል ነገር አለ፡፡ አንድ ላይ ስትሆኚ የምታመጪው ባህርይ ልክ ነው ብሎ ማሰቡ ራሱ በስራዬ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ያልተነካ በጣም ጥቂት ነው፡፡
 ወንዶች ይደፈራሉ፡፡ የስነልቦና ጤንነት እንደሌለ ያሳያል፡፡ ስለማይወራ ዝም የተባሉ ብዙ ተመሳሳይ ኬዞች አሉ፡፡ ልጆቻችንን ስንቶቻችን እናስተምራለን? ስንቶቻችን መረጃ እንሰጣለን? ጥቃት ምን እንደሆነ ምን ምን ነገሮች ሲያጋጥማቸው ለቤተሰብ ማሳወቅ እንደሚገባቸው እናደርጋቸዋለን? ጥፋት ፈፃሚዎቹ እኮ የሆኑ ሰዎች ልጆች ናቸው፡፡ እንዴት ነው ያሳደግናቸው? ምን ያህል ጥበቃ ያደርጋል? መንገድ ላይ ትንኮሳ ሲያጋጥም እንዴት ይታለፋል? የማህበረሰብ የጤንነት ደረጃን ያሳያል፡፡ ከቅጣት በፊት መከላከል ይቀድማል ሁሉም በየቤቱ ልጆቹን ጥሩ እሴት ይዘው እንዲያድጉ ማድረግ አለበት፡፡   እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ የሚለውን ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ጊዜ ላይ ነን፡፡  ሁላችንም ራሳችንን ሀና ቦታ ላይ እናስቀምጥ፡፡
ያለፈችባቸውን ስቃዮች እናስባቸው፡፡ ለቤተሰቦቿ መፅናናትን እመኛለሁ፡፡

Published in ጥበብ
  • ናይጄርያ ፤ ግብፅና ምስራቅ አፍሪካም የሉበትም
  • የዋልያዎቹ የውድቀት ሰበብ፤ ባሬቶ ወይስ ፌደሬሽኑ?

      30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከ62 ቀናት በኋላ በኢኳቶርያል ጊኒ አዘጋጅነት ይጀመራል፡፡ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር በአራት ዓመት ውስጥ ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎች ለማዘጋጀት በቅታለች፡፡ የመጀመርያው በ2012 እኤአ ከጋቦን ጋር በጣምራ ያዘጋጀችው 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ በኢቦላ ወረርሽኝ በመታመስ ሊስተጓጎል የነበረውን 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  ውድድሩ 5 ወር ሲቀረው መስተንግዶዋን በውዝግብ እና ቅጣቶች በተወችው ሞሮኮ  ምትክ ኢኳቶርያል ጊኒ አዘጋጅ ሆናለች፡፡ የአገሪቱ በበጀት አቅም፤ በአዳዲስ ስታድዬሞች እና በአስፈላጊ መሰረተ ልማቶቿ መሟላት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽንን ታድጓል፡፡ በኒሳን ኩባንያ ስፖንሰር ለተደረገው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  አዲስ ኳስ ‹‹መርሃባ›› በሚል ስያሜ በአዲዳስ እንደቀረበች ታውቋል፡፡
በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ ለሆኑት 16 ብሄራዊ ቡድኖች  የምድብ ድልድል በሚቀጥለው ሳምንት ይወጣል፡፡ በእጣ አወጣጡ ስነስርዓት አገራቱ በአራት ማሰሮዎች  ለእጣ ይቀመጣሉ፡፡ በማሰሮ 1 ኢኳቶርያል ጊኒ፣ ጋና፣ ዛምቢያና ቡርኪናፋሶ፤ በማሰሮ 2 አይቬሪኮስት፣ ማሊ፣ ቱኒዚያ እና አልጄርያ፤ በማሰሮ 3 ኬፕቬርዴ፣ ጋቦን፣ ዲ ሪፖብሊክ ኮንጎ እና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በማሰሮ 4 ካሜሮን፣ ሴኔጋል፣ ጊኒና ኮንጎ ይገኛሉ፡፡ በ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች የሚገኙት 399 ተጨዋቾች በዝውውር ገበያው አጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 713.10 ሚሊዮን ዩሮ ይገመታል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫው ወደ ምዕራብ  ማጋደል
ከ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ  አንስቶየአህጉራዊው ውድድር የሃይል ሚዛን ወደ ምዕራባዊው ዞን ማጋደሉ በግልፅ ይስተዋላል፡፡ ከምዕራባዊው የአፍሪካ ዋንጫ ዞን የተወከሉ ቡድኖች በምድብ ማጣርያ በስታትስቲክስ የነበራቸው ብልጫ የመጀመርያው ማስረጃ ነው፡፡  28 ብሄራዊ ቡድኖች በ7 ምድብ ተከፍለው ያከናወኑት የምድብ ማጣርያ ሶስት ወራትን የፈጀ ነበር፡፡ 84 ጨዋታዎች 193 ጎሎች ከመረብ ሲዋሃዱ የምዕራብአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ዋና ተዋናዮች ነበሩ፡፡ የቡርኪናፋሶው ጆናታን ፕሪቶፕያ በ6 ጎሎች ከፍተኛው ግብ አግቢ ሆኗል፡፡ በምድብ ማጣርያው ብዙ በማግባት 13 ጎሎች ያስመዘገበው ደግሞ የኮትዲቯር ቡድን  ነው፡፡ እያንዳንዳቸው አንድ ጎል ብቻ ተቆጥሮባቸው ከፍተኛ የመከላከል ብቃት ያሳዩት ደግሞ ካሜሮን እና ሴኔጋል ናቸው፡፡ በምድብ ማጣርያው ደቡብ አፍሪካ፤ ካሜሮን፤ ጋቦንና ቱኒዚያ ያለሽንፈት ማለፋቸውን ማረጋገጣቸው ብቻ የምእራቡን ብልጫ ያጠበበ ነው፡፡  በምድብ ማጣርያው የሰሜን አፍሪካ ቡድኖች አልሆናቸውም፡፡ ሁለት አገራት ሊቢያ እና ሞሮኮ አንዱ ባለመረጋጋት ሌላው በኢቦላ ስጋት የአፍሪካ ዋንጫንበአዘጋጅነት የመሳተፍ እድል ማጣታቸው የመጀመርያው ክስረት ነው፡፡  7 ጊዜ የአፍሪካ ሻምፒዮን በመሆን በከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘችው ግብፅ ሶስተኛ ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫ ሳታልፍ መቅረቷ ደግሞ ሁኔታውን አባብሶታል፡፡  ከምእራብ አፍሪካ ያልተሳካለት ያለፈው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን የሆነው የናይጄርያ ቡድን ነው፡፡ ለውድቀቱ ደግሞ በእግር ኳስ ፌደሬሽን አካባቢ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ትርምስ እና ዋና አሰልጣኙ ስቴፈን ኬሺ ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡ በ30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከሚሳተፉ አገራት  የአንበሳውን ድርሻ የያዘው በ9 አገራት የተወከለው ምዕራብ አፍሪካ ነው፡፡ ሴኔጋል ፤ ኬፕቬርዴ ፤ማሊ ፤አይቬሪኮስት ፤ጋና ፤ጋቦን ፤ቡርኪናፋሶ፤ ጊኒና አዘጋጇ ኢኳቶርያል ጊኒ ናቸው፡፡ በካሜሮን፤ ኮንጎ እና ዲሪ ኮንጎ የሚወከለው ማዕከላዊው አፍሪካ ይሆናል፡፡  ሰሜን አፍሪካ በቱኒዚያና  አልጄርያ  ሲወሰን ደቡባዊው አፍሪካ በመወከል  ደግሞ በደቡብ አፍሪካ እና በዛምቢያ ይገኛሉ፡፡ ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል ግን  ከ2 ተከታታይ የአፍሪካ ዋንጫዎች በኋላ ተወካይ አይኖረውም፡፡ የደቡብ እና የምስራቅ አፍሪካ አገራት በአፍሪካ ዋንጫ ለመግባት በማጣርያውእና ከዚያም በዋናው ውድድር ውጤታማ ለመሆን ቸግሯቸዋል፡፡ በደቡባዊው የአፍሪካ ዋንጫ ክፍል የሚወዳደሩ አገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ መክበድ አልነበረበትም፡፡ ደቡብአፍሪካ በዓለም ዋንጫ እና በአፍሪካዋንጫ አዘጋጅነት፤ በሊግ ውድድድሯ ጥንካሬ እና የክለቦቿ አህጉራዊ ውጤታማነት እንደምንም ለውድድሩ መብቃቷ አልቀረም፡፡ በአስተማማኝ ሁኔታ ያለፈችው የኛው የአፍሪካዋንጫ ዛምቢያ ናት፡፡ እነ አንጎላ፤ ማላዊ እና ዚምባቡዌ እና በተሳትፏቸውም ስኬት ለማግኘት ተቸግረዋል፡፡ በዋናነት ስፖርቱ በመሰረታዊ ደረጃ ስላልተሰራበት እንደሆነ የሚገልፀው የሱፕርስፖርት ትንታኔ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አገራት በበቂ በጀት አለመስራታቸው ደካማ አድርጓቸዋል፡፡ ፌደሬሽኖች የጉዞ ወጭን ለመሸፈን ተቸግረዋል፡፡ የውስጥ የሊግ ውድድሮች አለመጠናከርም ከምእራብ አፍሪካው እግር ኳስ እጅግ ወደኋላ እያስቀራቸው ነው፡፡  ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል በውድድሩ ክብደት መፎካከር ያቃተው ከደቡቡ በባሰ ነው፡፡ ባለፉት ሶስት አፍሪካ ዋንጫዎች ሱዳንና ኢትዮጵያ ዞኑን በመወከል እግር ኳሱን ሊያነቃቁ ሞክረዋል፡፡ አስተማማኝ ቡድን ያለው አገር ግን የለም በሚል የሚተነትነው የሱፕር ስፖርት ሀተታ ነው፤ የዞኑ እግር ኳስ በአፍሪካ ደረጃ ደካማ የሆነባቸው ምክንያቶች ብዙ ናቸው፡፡የፌደሬሽኖች ድክመት፤ የአሰልጣኞች የስራ ውጣውረድ፤ የበጀት አቅም መዳከም እና በአህጉራዊ ውድድሮች የክለቦችየፉክክር ደረጃ ማነሱን ዘርዝሯል፡፡ ለነገሩ የምስራቅ አፍሪካ አገራት እንኳንስ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ይቅርና የዞኑን ዋና ውድድር ሴካፋሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የሚያዘጋጅ ጠፍቶ በአሳሳቢ ውድቀት ውስጥ ይገኛል፡፡ በተያያዘ  የሚነሳው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ዞናዊ እና አህጉራዊ ውድድሮችን የማስተናገድ ምኞቱ በአቅም ማነስ እና በእቅድ ባለመስራት እንደተበላሸበት ነው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዛሬ ሳምንት ማዘጋጀት የነበረበትን የ2014 ሴካፋ ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ በበጀት እጥረት ላለማስተናገድ የወሰነው ከወር በፊት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡ ውሳኔው የዞኑን የእግር ኳስ ምክር ቤት አስቀይሟል፡፡ የሴካፋ ዋና ውድድር የሆነውን ሲኒዬርስ ቻሌንጅ ካፕ የሚያዘጋጅ አገር በ11ኛው ሰዓት ሲታቀብ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ውድድሩን ከማስተናገድ የተቆጠበችው ከስፖንሰርሺፕ እና ከብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ ዝግጅት በተያያዘ ውስብስብ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ እና የኤቦላ ወረረሽኝ ስጋት ሰበቦቿ እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ ኢትዮጵያን በመተካት የሴካፋው ፕሬዝዳንት መቀመጫ የሆነችው ታንዛኒያ እንድታዘጋጅ የዞኑ እግር ኳስ ምክር ቤት ደጅ እየጠና ነው፡፡ ሱዳንም ምላሽ ከመስጠት መቆጠቧ አዘጋጅ መገኘቱን አጠራጣሪ አድርጎታል፡፡ ምናልባት የምስራቅ አፍሪካ  ብሄራዊ ቡድኖች በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ እድል የሚኖራቸው ውድድሩን በማዘጋጀት ብቻ ይመስላል፡፡ አፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት እድል ግን አሁንም በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ምርጫ ወደ ምእራብ አተኩሮ ለሚቀጥሉት አራት የአፍሪካ ዋንጫዎች መቀጠሉ የእግር ኳስደረጃቸውን በይበልጥ እንዳያዳክመው ያሰጋል፡፡
የሰሜን አፍሪካ  ክፍል ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎችን ባለማስተናገዱ የአፍሪካ እግር ኳስ ፌደሬሽን ለአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ወደ ምእራቡ ክፍል አድልቷል፡፡  በምዕራብ አፍሪካ እግር ኳስ ባለው እድገት፤ ለስፖንሰሮች በሚገኝ ትኩረት እና ጥቅም በመሳብ  ካፍ የአፍሪካ ዋንጫውን ወደዚያው ዞን እንዲቀጥል ወስኗል፡፡ ከ30ኛው ጀምሮ ቀጣዮችን የአፍሪካ ዋንጫዎች 3 የምእራብ አፍሪካ አገራት እንዲያስተናግዱ መስጠቱ ማረጋገጫ ነው፡፡  በ2019 እኤአ ካሜሮን 32ኛውን፤ በ2021 እኤአ ኮትዲቯር 33ኛውን እንዲሁም በ2023 እኤአ   ጊኒ  34ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ እንዲያዘጋጁ መመረጣቸው ይታወቃል፡፡ አዘጋጁ ያልታወቀው በማሃል የሚገኘው የ2017 እኤአ 31ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ ለማዘጋጀት የሚፎካከሩት የምእራብ እና የሰሜን አፍሪካ አገራት አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ጋቦንና እና ጋና ናቸው፡፡  በአፍሪካ ዋንጫ የ29 ዓመታት ታሪክ ታሪክ 10 ዋንጫዎችን በመውሰድ የሚመራው ሰሜናዊው ዞን ነው፡፡ ግብፅ ለሰባት ጊዜያት እንዲሁም አልጄርያ፤ ሞሮኮ፤ ቱኒዚያ እኩል አንድ ግዜ ሻምፒዮን ሆነዋል፡፡ ምእራባዊው ዞን በስምንት ዋንጫዎች ይከተላል፡፡ ጋና አራት፤ ናይጄርያ 3 እንዲሁም ኮትዲቯር አንድ ዋንጫ አላቸው፡፡፤ ማዕከላዊ ዞን በሰባት ዋንጫዎች ሲመዘገብ፤ ካሜሮን አራት፤ ዲሪ ኮንጎ 2 እንዲሁም ኮንጎ ኪንሻሳ 1 ዋንጫ በማሸነፋቸው ነው፡፡ ምስራቃዊ ዞን በኢትዮጵያ እና በሱዳን እንዲሁም ደቡባዊው ዞን በደቡብ አፍሪካ እና ዛምቢያ እኩል ሁለት የአፍሪካ ዋንጫ ድሎች አግኝተዋል፡፡
ሰበበኞቹ  የማርያኖ ውጣ ውረዶች
በ2013 እኤአ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በታሪኩ ለ10ኛ ጊዜ ለመሳተፍ መብቃቱ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ ነበር፡፡ ከዓመት በኋላ ግን ይህን ስኬት መድገም አልቻለም፡፡ ቡድኑ ወደ 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በቀጥታ ምድብ ማጣርያ ውስጥ ከገቡ 24 ቡድኖች አንዱ ነበር፡፡ ቅድመ ማጣርያ ሳያደርግ ለምድብ ማርያ የተደለደለው በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመሳተፉ  ነበር፡፡ በምድብ ማጣርያው  ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎቹ አንዱን አሸንፎ፣ በአራቱ ተሸንፎ እና በአንዱ አቻ ተለያይቶ፣ ሊያገኛቸው ከሚችላቸው 18 ነጥቦች አራቱን ብቻ አግኝቶ ከምድቡ የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ አጠናቅቋል፡፡ በተለያዩ ሰበበኛ ውጣውረዶች እና በእግር ኳስ ደረጃው መዳከም ለ11ኛ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማልፍ ሳይችል ቀርቷል፡፡የተሸነፈባቸው ጨዋታዎች ከሜዳው ውጭ በማላዊ 3ለ2 እንዲሁም በአልጄርያ 2ለ0፤ እንዲሁም በሜዳው በአልጄርያ እና በማሊ በተመሳሳይ 2ለ0 ውጤት በመረታቱ ነበር፡፡ በምድብ 2 የአራተኛ ዙር ጨዋታ ከሜዳ ውጭ ማሊን 3ለ2 ሲያሸንፍ፤ ብቸኛውን የአቻ ውጤት ደግሞ ከማሊ ጋር 0ለ0 በመለያየት ሜዳው ላይ አስመዝግቧል፡፡ በዚህ መሰረት ዋልያዎቹ በምድብ 2  በ4 ነጥብ እና በ5 የግብ እዳ ጨርሰዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ማርያኖ ባሬቶ በብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ስምንት ወር ሊሆናቸው ነው፡፡ ባደረጓቸው የነጥብ ስድስት ጨዋታዎች  25 በመቶ ድል፤ 30.4 በመቶ አቻ እንዲሁም 44.6 በመቶ ሽንፈት ያስመዘገቡ ሲሆን በአንድ ጨዋታ መገኘት ከሚገባው ነጥብ 0.67 በማግኘት ብቃታቸው በትራንስፈርማርኬት ድረገፅ ተለክቶታል፡፡ እና ለብሄራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ማነው ሊጠየቅ የሚችለው ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ወይንስ የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ
በእርግጥ ዋልያዎቹ ለ30ኛው አፍሪካዋንጫ ለማለፍ በምድብ ማጣሪያ የነበራቸው ጉዞ በብዙ የአቅም ችግሮች ፤ በአወዛጋቢ አጀንዳዎች፤ በአንጋፋ ተጨዋቾች ስንብት፤ ጉዳት እና የትውልድ ሽግግር በውጣውረድ የተሞላ ነበር፡፡ ዋናው ተጠቂ ደግሞ ብሄራዊ ቡድኑን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲያደርጉ ከስምንት ወራት በፊት የተቀጠሩት ዋና አሰልጣኝ ማርያኖ ባሬቶ ናቸው፡፡ የምድብ ማጣርያው እንደተጠናቀቀ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በኮንትራታቸው ዙሪያ እና በፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ይለቁ እንደሆነ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡
በ2015 ለሚደረገው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን ማሳለፍ በኮንትራታቸው ላይ እንዳልሰፈረ እና እሳቸውም በፈቃዳቸው እንደማይለቁ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በአገልግሎት ዘመናቸው እንደ ግብ ያስቀመጧቸውዋና  ነገሮች ለአፍሪካዋንጫ ማለፍአይደለም በሚል ተሟግተዋል፡፡
በሃላፊነቱ በቆዩባቸው 8 ወራት ለወጣቶች እድል መስጠት እና የተጨዋቾችን ብቃት ማሳደግን ማሳካት እንደቻሉ በልበሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ውጤታማነት  ጊዜያዊ መፍትሄ ማሰብ አያወጣም ያሉት አሰልጣኙ፤ የረዥም ጊዜውን በማሰብ መስራት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ ስለ መጫወቻ ሜዳዎች እጥረት እና ስለ መንገድ ላይ እግር ኳስ አለመኖር እንዲሁም በወጣቶች እድገት እና በክለቦች ተጨዋች አያያዝ እና በተመሳሳይ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ማሪያኖ ባሬቶ ስራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በወዳጅነት ጨዋታዎች አለመኖር፤ በተጨዋቾች ምርጫ ሰፊ አማራጭ በማጣት እንዲሁም በልምምድ ሁኔታዎች አለመመቸት ቅሬታቸውን ሲገልፁ ነበር፡፡ በምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ለብሄራዊ ቡድኑ የልምምድ መስሪያ ትጥቆችና ሌሎች ቁሶች አቅርቦቶች ባለሟሟላቱ ደስተኛ አልነበሩም፡፡ ሊሟሉ የሚገባቸው ነገሮች በፌደሬሽኑ በኩል ባለመፈፀማቸው ፤  ወደ ሜዳ ከወጡ በኋላ ልምምዱን ሳያሰሩ ተጨዋቾቻቸውን ሰብስበው ወደ ሆቴል ተመልሰዋል፡፡
አሰልጣኙ ለነባሮቹም ሆነ አዲስ ለሚመረጡት ተጨዋቾች ፌዴሬሽኑ በግዜው የመጫወቻም ሆነ የመለማመጃ ትጥቆችን በስርዓቱ እንዲያቀርብ ጠይቀው ነበር፡፡ በተጨማሪ 30 የመለማመጃ ኳሶች እና ተንቀሳቃሽ ጎሎችም እንዲዘጋጁላቸውም አመልከተው ነበር፡፡
 እነዚህ አስፈላጊ አቅርቦቶች ስላልተሟሉላቸው ዝግጅታቸው ተስተጓጉሏል፡፡  
በትጥቅ ጉዳይ ግን ፌዴሬሽኑ   ከስፖርት ኮሚሽን ወይም ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና ሌሎች ድጋፎች ባሻገር ከስፖንሰርሺፕ ውሎች ማግኘት አለመቻሉ ችግሩን እንደፈጠረ መገንዘብ አያዳግትም፡፡፡ በዋልያዎቹ ዋና አሰልጣኝነት ላለፉት ስምንት ወራት የሰሩት የ57 ዓመቱ ማርያኖ ባሬቶ አምስት ቋንቋዎች እንደሚናገሩ ይገለፃል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመስራት በቂ በእንግሊዘኛ የመግባባት ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ራዕያቸውን በአስተማማኝ መሰረት ለመገንባት መቸገራቸው አልቀረም፡፡ በጋና፤ በሩስያ፤ በሳይፕረስ እና በሳውዲ አረቢያ የእግር ኳስ ባህሎች በቂ የስልጠና ልምዳቸውን በአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በመተግበር ስኬታማ ለመሆን ቢያንስ እስከ 4 ዓመታት ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡
 በአሰልጣኝነት ዘመናቸው እነ ሊውስ ፊጎ፤ ሪካርዶ ካልቫሆ፤ ማይክል ኤስዬንና እና ሌሎችን ያፈሩ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
 በኢትዮጵያ ታዳጊዎችን አውጥተው ለዚህ ደረጃ ለማብቃት የሚያቀርቧቸውን ስትራቴጂዎች በአግባቡ እየተረጎመ የሚሰራ ፌደሬሽን መኖሩ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ውጤታማ ብሄራዊ ቡድን ለመገንባት የሀ12 እና ሀ14 ታዳጊ ቡድኖች ውድድር መጀመር ወሳኝ እንደሚሆን በተደጋጋሚ መክረዋል፡፡  በሀ20 ይሰራ ብለው ሃሳብ አቅርበዋል፡፡ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በእነዚህ ደረጃዎች በስፋት የሚሰራበትን አቅጣጫ ሙሉ በሙሉ እየሰራ ግን አይደለም
በፌደሬሽኑ ካዝና መራቆት ውድቀቱ መባባሱ
 አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው የእግር ኳስፌደሬሽን ስራውን ከጀመረ 1 አመት ሊሆነው ነው፡፡ ከሳምንት በኋላ ጠቅላላ ጉባኤውን ያካሂዳል፡፡ ፌደሬሽኑ የውስጥ ውድድሮችን በተሳካ መንገድ እያከናወነ ቢቆይም በአስተዳደራዊ ድክመቶችና በበጀት እጥረት  ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን አልቻለም፡፡ እግር ኳሱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የማድረግ እቅድም አጀማመሩ እያማረአይደለም፡፡ ይህ ደግሞ የብሄራዊ ቡድኑን የአፍሪካ ዋንጫ ውድቀት አባብሶታል፡፡ ለዋልያዎቹ ሁለት ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ጨዋታዎች በቂ በጀት የለኝም በሚል እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከወር በፊት ያዘጋጀው ገቢ ማሰባሰቢያ ሁሉንም ችግር በገሃድ አሳይቷል፡፡ ትልልቆቹ የአፍሪካ ብሄራዊ ቡድኖች ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ እስከ 70 ሚሊዮን ብር በጀት ያወጣሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ቢያንስ ግማሹን ያህል በጀት አቅርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በበቂ በጀት ካልተሰራ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድል የተመናመነ እንደሚሆን ገምቶ መስራቱ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ነበር፡፡
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘው ፌደሬሽን ብሄራዊ ቡድኑን ዓለም አቀፍ ተፎካካሪ ለማድረግ ተነስቻለሁ ብሎ ስልጣኑን ቢረከብም በተግባር ስራውን አለመከወኑ ይስተዋላል፡፡ ከብሄራዊ ቡድኑ  አጠቃላይ የውድድር ሂደት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የፉክክር አቅም የሚያስገኙ የስፖንሰርሺፕ ድጋፎች አለመጠናከራቸውም ሌላው አሳሳቢና መሰረታዊው ችግር ነው፡፡
  ከ2 ሳምንት በፊት በሸራተን አዲስ በተደረገው የፌደሬሽኑ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ለ1100 ጥሪ ተደርጎ የተገኙት ግማሽ ያህሉ ነበሩ፡።
በገቢ ማሰባሰቢያው  20 ሚሊየን ብር  ለማግኘት ቢታቀድም በእለቱ  በቃል እና በተግባር የተገኘው ድጋፍ ከ4 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡ ይህም ገቢ ማሰባሰቢያው የተሳካ እንዳልነበር ያረጋግጣል፡፡

የሴቶች ስነ ተዋልዶ አከላት አፈጣጠር በምን መንገድ ነው?
ተጉዋደለ የሚባለው ምን ስለጎደለ ነው?
የአፈጣጠር ጉድለት ምን ጉዳት ያስከትላል?
ከላይ በተሰነዘሩት ጥያቄዎች ዙሪያ (Integrated family health program) በተቀናጀ የቤተሰብ ጤና ፕሮግራም ከፍተኛ የእናቶችና የጨቅላ ሕጻናት ጤና አማካሪ የሆኑት ዶ/ር ብርሃኑ ሰንደቅ የሰጡንን ማብራሪያ ነው በዚህ እትም ለንባብ ያቀረብነው፡፡
ጥ/    የተፈጥሮ ሂደት በምን ይገለጻል?
መ/    “...የሰው ልጅ ሲሰራ ከሁለት ሴሎች ድብልቅ ነው፡፡ እነዚያ ሁለት ሴሎች ሲባዙ ነው      የምናውቃቸውን የተሙዋላ ሰውነት ማለትም አይን እጅ እግር... እንዲሰራ ያደርጋል፡፡ በዚህ የሴሎች አሰራር ሂደት ውስጥም የሴት ልጅ ውጫዊና ውስጣዊ ስነ-ተዋልዶ አካላት ወይንም የመራቢያ አካላት የሚፈጠሩት
ጥ/    ሴሎቹ በደረጃ ይለያያሉ ወይንስ ተመሳሳይ ናቸው?
መ/    ሴሎቹ ሶስት ዋነኛ ክፍሎች (layers) አሉዋቸው፡፡ እነርሱም ኤክቶደርም ሜሶደርም እና ኢንዶደርም የሚባሉ ሶስት ላየሮች አሉ፡፡ የሴት የስነተዋልዶ አካል ማለትም ማህጸን፤     የማህጸን ቱቦዎች     እና ብልት የሚፈጠረው ፓራሜሶነፍሪንክ ወይም ሙለሪያን ዳክት     ከሚባለው ከሜሶደርመም የተገኘ ነው፡፡ በዚህ አፈጣጠር ሂደት ከኩላሊትና ከሽንት ቡዋንቡዋ ጋር ባላቸው ቅርበት የተነሳ አከላዊ ጉድለት ሲኖር ሁለቱም ጋ ሊከሰት ይችላል ስለዚህም በምርመራ ወቅት ይህን ግንዛቤ ወስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ጥ/    የሴቶች ስነ ተዋልዶ አከላት አፈጣጠር ጉድለት በምን ምክንያት ይከሰል?
መ/    ይህ ነገር በምን ምክንያት ይመጣል ለሚለው ጥያቄ አንድ መንስኤ ብቻ  መስጠት     አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ምክንያቶች ሊመጣ ስለሚችል ነው፡፡ ይህ የተፈጥሮ  ችግር     ከአካባቢ ተጽእኖ በዕርግዝና ወቅት ከሚወሰዱ ነገሮች ለአንዳንድ ነገሮች ከሚኖር     ተጋላጭነት... በመሳሰሉት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ችግር በአጠቃላይ “...ከብዙ ምክንያቶች የሚመጣ...” ተብሎ የሚገለጽ ነው፡፡
ጥ/     ጽንስ የወንድ ወይንም የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል እንዲሆን የሚያስችለው ተፈጥሮአዊ     ሂደት ምን ይመስላል?
 መ/    ጽንሱ የወንድ ወይም የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል እንዲኖረው የሚለየው ሙለሪያን     ኢነሂቢቲንግ ፋክተር የሚባል ንጥረ-ነገር ሲሆን ወንዶቹ ላይ ገና ከጅምሩ ይህ ነጥረ-ነገር     ስለሚኖራቸው የሴት ስነ-ተዋልዶ አካል አይፈጠርም፡፡ ስለዚህ ሙለሪያን     ኢነሂቢቲንግ ፋክተር መኖሩ ማህጸንና ሌሎች የሴት ብልት አከላት መሰራታቸው ይቀርና ይከስማሉ፡፡ ጽንሱ ሴት ከሆነ ግን ሙለሪያን ኢነሂቢቲንግ ፋክተር የሚባለው ስለማይኖር የማህጸን እድገት የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ እና ብልት የተባሉት ይሰራሉ፡፡  
ጥ/    አንዲት ሴት በማህጸንዋ ወይንም በብልትዋ የተፈጥሮ ችግር ያለባት መሆኑን እንዴት     ልታውቅ ትችላለች?
መ/    እነዚህ አካላዊ ጉድለቶች በአብዛኛው መከሰታቸው አይታወቅም ብዙዎች ምልክት ስለሌላቸው፡፡ ብዙውን ጊዜ በአጋጣሚ በኦፕራሲዮን ወቅት ወይም የላፓራስኮፒ ምርመራ     ሲደረግ እግረ መንገዱን የሚታይ ሊሆን ይችል፡፡ በብዛት የሚከሰቱት ምልክቶች የወር     አበባ አለማየት፤ በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወቅት ህመም፤ ማርገዝ አለመቻል፤     ተደጋጋሚ ጽንስ መቁዋረጥ፤ ያለጊዜ ልጅ መወለድ፤ የመሳሰሉትን ያከትታል፡፡
ጥ/    ምን ምን አይነት የአካል ጉድለቶች አሉ?
ጉድለቶች ብዙ አይነት ሲሆኑ ለመጠቆም ያክል ሁለት ማህጸን (uterine     didelphis)፤ አርኩዌት ማህጸን (arcuate uterus)፤ ሴፕቴትድ ማህጸን (septated     uterus)፤ ማህጸን አለመፈጠር (uterine agenesis)፤ የብልት መደፈን (imperforate     hymen/ vaginal septum) የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡
ጥ/    ማህጸን ወይንም የሴት ብልት ሁለት ሊሆን የሚችልበት ምክንያት ምንድነው?
መ/    ማህጸን ሲፈጠር በቀኝና በግራ ከሁለት ሙለርያን ዳክት ጥምርታ ሚፈጠር ሲሆን በዚህ ሂደት  በመሀል ሲለዩዋቸው የነበሩ ሴሎች/ቲሽዎች እሲከሰሙ አንድ ማህጸን ይሆናል፡፡     ይሄ     ውህደት ሊኖር ሲገባ ነገር ግን ሳይሳካ ከቀረ በግራና በቀኝ ሆነው የተፈጠሩት የማህጸን ክፍሎች ሁለቱም ለየብቻቸው ስለሚቀሩ ሁለት ማህጸን ሁለት የማህጸን     በር ሁለት ውጫዊ ብልት ሊኖር ይችላል፡፡  ብልት ሲባል ግን ከውጭ የምናየውን አካል ሳይሆን ወደማህጸን በር የሚያገናኘውን ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ተፈጥሮ     ሁለት ማህጸን ወይንም በከፊል የተከፈለ አለዚያም በመሀከሉ ስስ በሆነ ግድግዳ የተከፈለ ተብሎ ይገለጸል፡፡  
ጥ/     የስነ-ተዋልዶ አካላት አፈጣጠር ችግር ያለባቸው በህክምና ሊረዱ ይችላሉ ወይ?
መ/     አዎ፤ እንደ ጉድለቱ አይነት በህክምና ሊታገዙ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶቹ በቀላል ህክምና ሲድኑ  ሌሎቹ ግን ከፍተኛ ህክምና ያስፈልጋቸዋል፡፡
ማጠቃለያ፡-
“...በስተመጨረሻው ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ የምፈልገው... ሰዎች ካለምንም ምክንያትና     ምልክት ተፈጥሮአዊ ጉድለትን ለማወቅ ብቻ ሲሉ ወደ ህክምና ተቋም መሄድ አለባቸው ብዬ አልመክርም፡፡ ነገር ግን ችግሩን ለማወቅ ይረዳሉ የተባሉ ምክንያቶችን ሲያስተውሉ ግን ጊዜ ሳያጠፉ ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ አገልግሎቱን መግኘት ብልህነት ነው፡፡”

Published in ላንተና ላንቺ
Page 1 of 19