Saturday, 28 December 2013 12:28

ሴትና ኪነት

እንደውሀ ሀሳብ እየወረድልኝ ድርሰት መፃፍ ህልም ሆኖብኛል፤በቃ መፃፍ አቅቶኛል! አንድ አመት. . . ሁለት አመት. . . ሶስት አመት. . አምስት አመት. . .  ሙሉ ጠበቅሁ፤  ምንም ነገር ብቅ አላለም- አንድ ገፅ ቃለ ተውኔት መፃፍ እንኳ አልቻልኩም!
ድርሰት መፃፍ አቅቶኝ ማዘኔ ሳያንስ የምወዳት ሚስቴ ሜላት መካሻ ጥላኝ ሔደች!
መለየት እንደዱብዳ ወረደብኝ፡፡ የመፃፍ ችሎታዬ ተሟጦ ከእንግዲህ  መፃፍ እንደማልችል በትያትር ቤት ገምጋሚዎች በተነገረኝ በሁለተኛው ወር ምሽት ላይ ወደቤቴ ስገባ ባለቤቴ ጥላኝ እንደሔደች ተነገረኝ፡፡ ኪነትና ሴት ተመካክረው እስኪመስል ከህይወቴ ሰተት ብለው ወጡ። ኪነትና ሴትን አንድ ላይ ማጣት ልቋቋመው የምችለው አልነበረም። መኖር ራሱ ከዚህ በኋላ ምን ያደርግልኛል? ሰው መኖር ያለበት በምክንያት ነው፡፡ የመኖር ምክንያቶቹ በሙሉ የተወሰዱበት ሰው መኖር ምን ያደርግለታል? ለኔ የመኖር ምክንያቶቼ የነበሩት ሴት እና ኪነት ናቸው. . .  ሁለቱን ከተነጠቅሁኝ በኋላ መኖር ከመተንፈስ የዘለለ አይሆንልኝም፡፡  
ሀያ ስምንት ተውኔት ከፃፍኩ በኋላ በድንገት የመፃፍ ኃይሌን ተቀማሁ፡፡ የመፃፍ ችሎታዬን እንደተነጠቅሁ የተረዳሁት ከግማሽ በላይ ቴአትሮቼን ላሳየሁበት ቴአትር ቤት ያስገባሁት የተውኔት ፅሁፍ በተደጋጋሚ ውድቅ ሲደረግ ነበር።  ለመጨረሻ ጊዜ ግምገማ ሲደረግ፤ ገምጋሚዎቹ የተውኔቱን ፅሁፍ ቀሽምነት የሚያሳዩ ነጥቦችን እያነሱ አስተያየት ሲሰጡ ተሸማቅቄ መግቢያ ሳጣ- በቃ መፃፍ እንደማልችል በግልፅ  ገብቶኝ ነበር።  “መፃፍ አለመቻል ማለት የህይወት መጨረሻ አይደለም!” ብዬ ነበር ለራሴ ደጋግሜ የነገርኩት፡፡
ተሳስቼ ነበር፡፡ መፃፍ ለኔ ህይወት ነበር፡፡ ቃላትን መደርደር የህይወት ምልልሴ ነበር፡፡ ድርሰት ከመፃፍ ውጪ ጫማ ማሰር እንኳ አልችልም፡፡ የተወለድኩት እንድፅፍ ነበር የሚመስለኝ፡፡ በድንገት ግን ብዕሬ አልታዘዝ አለኝ፤ቃላት እንደሰማይ ራቁኝ። ለማን አቤት እንደምል አላውቅም. . . . . .
የመጨረሻውን ቴያትሬን ለግምገማ ሳቀርብ የመሞት ያህል ነበር የተሰማኝ፡፡ ከተውኔት ግምገማው ቢሮ ስወጣ ውስጤ ጭር ብሎ ነበር። በቁሜ የተገነዝኩ ያህል፣የራሴን የቀብር ንፍሮ የቀመስኩ ያህል . . . ድንጋጤ አቅሌን ሰውሮ ጭልም እንዳለብኝ ----ምን ነበር የቴያትር ገምገሚው ያለኝ? የቴያትር ገምጋሚው ንግግር በአእምሮዬ ደጋግሞ ያቃጭልብኛል፡፡ እስከ ህልፈተ ህይወቴ ድረስ በህሊናዬ የሚቀመጥ ንግግር ነበር የተናገረው፡፡
“ህሩይ እርግጠኛ ነህ ይህንን ጽሁፍ አንተ ለመፃፍህ?” ነበር ያለኝ ባለማመን፡፡ በአንገቴ ንቅናቄ ማረጋገጫዬን እንዳገኘ ወደኔ አፍጥጦ እያየ. . .
“ህሩይ ይህ ግምገማ በሁለት አመት ውስጥ ስድስተኛ  ሥራህ ላይ ያደረግነው ነው፡፡ አይገባህም እንዴ? በቃ! የጥበብ አድባር ርቃሀለች! መክሊትህን ጨርሰሀል! እስካሁን በሰራኸቸው እና ተመልካችን አጀብ ባሰኙ ሥራዎችህ እየታወስክ ትኖራለህ፡፡ ከእንግዲህ ግን ሙያ ቀይር! ለወጣቶቹ እድል ስጥ!” ሲል  የራሴን መርዶ ለራሴ ነገረኝ፡፡ ሀያ ስምንት ተውኔቶች ተለምኜ በፃፍኩበት መድረክ ላይ አንድ የሚበቃ ሥራ ማቅረብ አቃተኝ! ኪነት ጨርቄን ማቄን ሳትል ጣጥላኝ ሔዳለች. . . . .እብስ!
እውነቱን ስላላመንኩት ነው እንጂ በቃ መጻፍ አልችልም! አልችልም! አልችልም! ቃላት ያጎርፍልኝ የነበረው ምናቤ ሞቷል!
ለሀያ ምናምን ዓመት ያለማቋረጥ የሰራሁት ሥራ መፃፍ ነው! መፃፍ! መፃፍ! በቃላት ነፍስ መዝራት፤ በቃላት ህይወት መዝራት፤ ከህይወት ህይወትን ቀድቼ ህይወት ላላቸው ህይወትን ማጠጣት፡፡ አሁን ግን የህይወት ምንጬ ደረቀ፡፡ የፈጣሪነት ሚናዬን ተቀምቻለሁ!  ሥራዬ መፍጠር ነበር፡፡ ህይወቴ መፍጠር ነበር፡፡ ነበር፣ነበር፣ነበር. . . . . !!! አንድ የሚረባ ፅሁፍ መፃፍ አቅቶኝ አምስት አመት ተቆጠረ፡፡ መፃፍ እችላለሁ የሚለውን እምነት ይዤ ለአምስት አመት ታገልኩ. . .በቃ መፃፍ አቅቶኛል!
አእምሮዬ ድንገት እንደ ሻተር ዝግት አለ! በፊት በፊት ድርሰት እንዴት ነው የሚመጣልህ? ብለው ሲጠይቁኝ እስቅ ነበር- የአለቃ ገብረሀናን አሽሙር እንደሰማሁ፣የቻርልስ ቻፕሊንን ድምፅ አልባ ቧልት እንዳየሁ ሁሉ በሳቅ ፍርስ እል ነበር፡፡ በምድር ላይ ቀላሉ ሥራ በቃላት ሰዎችን መፍጠር፣እንዲናገሩ ፣እንዲያዝኑ ማድረግ ይመስለኝ ነበር፡፡ ሀያ ስምንቱም ተውኔቶቼ የተዋጣላቸው የሚባሉ ነበሩ፡፡ አምስት አመቴ! ቃላት ከአእምሮዬ መፍለቅ ካቆሙ፣ ቢፈልቁም ጣዕም አልባ ደረቅ ቃላት ናቸው፤ታሪክ በጣቴ በኩል አይመጣም፣ ታሪክ ብዬ የምፅፈው ከተራ ዝብዘባ ያነሰ ነው፡፡ በቃ መፃፍ አልችልም!!
አንድ የማላውቀው ኃይል የድርሰት አቅሜን ነጥቆኛል፡፡ የት ሔጄ አቤት እላለሁ? የትኛው ፍርድ ቤት ይግባኜን ይሰማኛል?
ስለማያስችለኝ ከቴያትር ቤቱ ደጃፍ ላይ ሔጄ ቁጭ እላለሁ፡፡ ከየት መጣ ያላልኩት እንባ አይኔን እየበረቀሰው ወደ ጉንጬ ይንፎለፎላል፡፡ ሰዓሊ ብሩሹ ሲደርቅ፣ቀራፂ መዶሻው ሲወልቅ. . . ምን ይላል? . . . ዘፋኝ ድምፁ ሲጎረንን፣ዳንኪረኛ እግሩ ሲሰበር. . . .  ምን ይሆን የሚሰሩት? እኔ ግን ግራ ገብቶኛል! ህይወት ትርጉም አጥታብኛለች፡፡ ስፅፍ እንዴት ደስተኛ ነበርኩ! ስፅፍ እንዴት ሀሴት አደርግ ነበር!. . . . ንስር የሆንኩ ይመስለኝ ነበር፤ሰማየ ሰማያት በርሬ ቁልቁል ዓለምን ሙሉ የምቃኝ ይመስለኛል፡፡ ሥነ-ፅሁፍ ነፃነቴ ነበር፣ ሥነ-ጽሁፍ ቁልፌ ነበር ከተዘጋ የአስተሳሰብ ሳጥን የምከፈትበት. . . . ሥነ-ፅሁፍ ማዕረጌ ነበር የምጠራበት. . .
የመጨረሻ የተውኔት ፅሁፌ በግምገማ እንዲያልፍልኝ ክፉኛ እንደተመኘሁ ትዝ ይለኛል፡፡ እናቴ በጠና በመታመሟ  ገንዘብ ማግኘት ነበረብኝ። የቤት ኪራይ አለ፣ፋሲካ እየደረሰ ነው. . . ገንዘብ ግን የለኝም ነበር፡፡ ገንዘብ እንዳገኝ የተውኔት ፅሁፍ አዘጋጅቼ ለቴያትር ቤቱ አስገባሁ፡፡ በግምገማ ቅስሜን እንደእንስራ ሰበሩት. . . .ይህ ሁሉ ጫና ኖሮብኝ ከኪነት እና ከሴት አንደኛቸው አብረውኝ ካሉ ጭንቅ አጠገቤ አይደርስም ነበር፡፡ ኪነት እና ሴት በአንድነት ሲርቁኝ ግን. . . .የጨለማ ግድግዳ የከበበኝ ይመስለኛል፡፡
በአንድ ተውኔቴ ውስጥ “ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” የሚል ገፀ ባህሪ አለ፡፡ የመፅሀፍ ቅዱሱ ኢዮብን አይነት መከራ የሚደርስበት ይኼ ገፀ ባህሪዬ፤ በመጨረሻ የዓለምን ስቃይ መቋቋም አቅቶት አቅሉን ይስታል-ያብዳል፡፡ ካበደ በኋላ ማበዱን የሚያሞካሽበት ቃለተውኔት አለ።  “ባላብድ ይገርመኝ ነበር! ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” ይላል ይህ ገፀ ባህሪዬ፡፡ “እንኳን አበድኩ! በጤነኛ አእምሮዬ ይህንን ሁሉ መከራ አልችለውም ነበር!” ይላል። የራሴን ህይወት እየተነበይኩ ነበር ማለት ነው። አንዴት አንድ የተሳካ ተውኔት መፃፍ ያቅተኛል? ማበድ ሲያንሰኝ ነው! ባብድ ይሻል ይሆን? እብደትን ተመኘሁ. . . .
ከድርሰት ውጪ ሰርቼ ገንዘብ ያገኘሁበት ሥራ ኖሮ አያውቅም! ስለዚህ ዓለም ያለጀንበር መኖር የጀመረች መሰለኝ. . . . .ጨለማ!
የመጨረሻ ተውኔቴ በግምገማ ከወደቀ በኋላ መጠጥ መቀማመስ አዘውትሬ ነበር፡፡ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ የተለመደውን አድርሼ ወደ ቤቴ አቅጣጫ ጉዞ የጀመርኩት. . . . .
11፡00 ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ተማሪዎች ከትምህርት ቤት የሚመለሱበት፣ ፀሀይዋ መስከን የምትጀምርበት፣ሠራተኞች ከሥራ ወደ ቤት የሚቻኮሉበት. . . ጓዳናው ላይ ሰው የሚፈስበት የምወደው ሰዓት ነበር፡፡ በዚህ ሰዓት ጎዳና ላይ መውጣት የድርሰት አምሮቴን ይቀሰቅሰው ነበር። ሰውን የማንበብ ሱስ ነበረብኝ፡፡ ብዙ አይነት ፊቶችን ማንበብ እወድ ነበር... የተከፋ፣ የደነገጠ፣ የተደሰተ፣ የተኮሳተረ፣ የፈገገ፣ የሚቸኩል፣ የተናደደ፣ ተስፋየቆረጠ፣ የተቆጣ፣ የተራበ፣ የተፀፀተ ፊት...፤ በፂም የተከበበ፣ በመነፅር የተጋረደ ፊት፤ ሾካካ፣ መልከቀና፣ የዋህ፣ ጅላጅል ፊት. . . .እነዚህን ፊቶች ማየት ነበር የቃላት ክምር፣ የዓረፍተ ነገር ቋጥኝ ወደ አእምሮዬ የሚያንደረድረው፡፡
ምን ሆኖ  ይሆን ያዘነው? ምን ሆና ይሆን የምትስቀው? ለምን ተፀፀተ?. . .እያልኩ የሰዎችን ፊት ካየሁ በኋላ. . . ወደ መመሰጤ እመጣለሁ --- የፈጠራ ሀሳቦች እየተንከባለሉ ወደ አእምሮዬ ዘው ይሉ ነበር፡፡ የሰው ፊት ነበር መጽሀፌ! የተገለጠ፣ያልተደበቀ፣በብራና ያልተለበጠ፣ነፍስ ያለው መፅሀፍ --- የሰው ልጅ ፊት! እነዚህ ሁሉ ትርጉም ከሰጡኝ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የሰው ፊት ሳይ አፍንጫ እና አይን፣ቅንድብና ጉንጭ፣ከንፈር እና ግንባር. . . ወዘተ ብቻ ናቸው የሚታዩኝ፡፡ ከዛ ውስጥ ያለው የሰው ልጅ ማንነት አይታየኝም. . .ምናቤን ተነጥቄያለሁና፡፡
መፃፍ አቅቶኛል! በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ ወደ ቤቴ እየሄድኩ ነበር፡፡ በመንገዴ ሙሉ የማስበው ስለተለየችኝ  ኪነት ነበር፡፡ ሚስቴ ያኔ አብራኝ ስለነበረች የኪነትን እጦት መፅናኛዬ እሷ ነበረች፡፡ እሷ ጋ እስክደርስ ግን ስለኪነት አስብ ነበር. . . .
መፍጠር መቻል የሚያስገኘው ደስታን ምናልባት የወለደ ብቻ ያውቀው ይሆናል፡፡ መፃፍ ደግሞ ከዚያ ይበልጣል፡፡ የተወለደ ልጅ ነፍስ ካወቀ በኋላ የራሱን የህይወት ትልም እራሱ ነው የሚኖረው። አማልክቱ ናቸው የተወለደ ልጅን እጣ ፈንታ የሚወስኑት፡፡ በድርሰት ግን ከዚያ በላይ መብት አለ፡፡ ገጸ ባህሪን መውለድ ብቻ ሳይሆን ጥሩና መጥፎ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል፡፡ ጥቁር አለያም ቀይ የፊት ቀለም መሥጠት ይቻላል፡፡ የፈጠሩትን ገጸባህሪ እንዲሳካለት ማድረግ ይቻላል፡፡ ደራሲነት የአማልክትን እጣ ፈንታ መጋራት ነው፡፡ እስካሁን ከነበሩ ወላድ እናቶች መካከል የልጁን አንድ ስንዝር አፍንጫ ቁመት የጨመረ የለም፡፡ በድርሰት ውስጥ ግን እነዚህ ሁሉ ይቻላሉ፡፡ የሳምሶን ኃይል ፀጉሩ ውስጥ ነበር፤ የጸሀፊ ደግሞ ምናቡ ውስጥ፡፡ ምናቤን ተቀምቻለሁ. . . በቃ ከእንግዲህ መጻፍ አልችልም!
ይኼን እያሰብኩ ቁልቁል ወደ አትክልት ተራ አቅጣጫ መጓዜን ቀጠልኩ፡፡ ከኋላዬ የሁለት ወጣት ልጃገረዶች ሹክሹክታ ይሰማኝ ነበር፡፡
“አየሽው! ህሩይ ማለት እኮ እሱ ነው፡፡ የዛሬ አምስት አመት በቴሌቪዥን ይታይ የነበረው የህልም ዓለም ሰዎች የሚለውን ድራማ አስታወስሽ? የሱ ደራሲ እኮ ነው፡፡” አለች ተለቅ የምትለው፡፡ የህልም ዓለም ሰዎች በሚል የፃፍኩት ድራማ በጣም ታዋቂ ነበር፡፡
“አረ እኔ አላውቀውም!” አለች አነስ የምትለው
“በተደጋጋሚ መፅሔት ላይ ይወጣ ነበር እኮ! ብዙ ቴያትር ፅፏል!. . .”ትልቅየው ልታስረዳት ሞከረች፡፡
ዞር ብዬ አየኋቸው፡፡ ትልቋ አስራ ስምንት፣ትንሷ ደግሞ አስራ ሁለት አመት ቢሆናቸው ነው፡፡ ትልቋ በአውቅሀለው ስሜት ፈገግ አለችልኝ. . . ትንሷ ደግሞ በእንግዳ ስሜት አየችኝ፡፡ ደነገጥኩ! ለአዲሱ ትውልድ የሚሆን ሥራ የለኝም! በቃ እኔ ታሪክ ነኝ!. .. መፃፍ አልችልም፡፡ ልጆቹን ትቼ ጉዞዬን ቀጠልኩ።
ከሸዋ ሱፐር ማርኬት በሶማሌ ተራ አድርጌ፣ ወደ ሰፈሬ ወደ አሜሪካን ግቢ እስክደርስ ድረስ የሚራመድ ግዑዝ አካል ሆኜ ነበር፡፡ ለወትሮው አሜሪካን ግቢ ስደርስ የሚሰማኝ ሰላም አብሮኝ አልነበረም። የአሜሪካን ግቢ ግርግር፣ልባሽ ጨርቅ የሚሸጡ ወጣቶች ውርውርታ፣በትንንሽ ፔርሙዝ ቡና የሚሸጡ ሴቶች፣የወደቀ የጫት ገረባ የሚበላ ፍየል፣ከመስጂድ የሚመለሱ አባት፣መኪና ላይ የሚጫን ካርቶን፣ ረጅም የብረት ቱቦ በትከሻው ተሸክሞ ”ዞር በሉ! ዞር በሉ!” እያለ የሚያስጠነቅቅ ወጣት፣የተደረደሩ የሊስትሮ ዕቃዎች፣የመስጅድ አዛን፣የራጉኤል ቅዳሴ. . . .አሜሪካን ግቢ የሰው እርሻ ነች፣ሰው ግጥግጥ ተደርጎ የተዘራባት የመርካቶ አዝመራ! አሜሪካን ግቢ የድርሰት ሀድራዬ ነበረች። ሰው ሰው የሚሸት ትንፋሽ የምታሸተኝ. . . ሰው ሰው የሚል ስሜት እንዲሰማኝ የምታደርግ. . . . ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን አሜሪካን ግቢ እነዚህን ሁሉ አትሰጠኝም! የማየው ተራ ግርግር ነው! የሰዎች ትርምስ - ምክንያቱም ምናቤን ተቀምቻለሁ!
እንዲህ እያሰብኩ ስሔድ. . . . ከኋላዬ ድምፅ ሰማሁ.. .
“ህሩይ!” ወደ መንደራችን መግቢያ መንገድ ጫፍ ላይ ካለው ሱቅ የተሰማ ድምፅ ነበር-የበድሩ ድምፅ። በተረቡ፣በቀልዱ፣በጨዋታው ቀኔን የሚባርክልኝ በድሩ። መከፋቴን ላጋባበት አልፈለግሁም- ዝም ብዬ ወደ ቤቴ አቅጣጫ መጓዜን ቀጠልኩ፡፡
“ህሩይ ፈልጌህ ነው!” በድሩ ተከትሎኝ ነበር፡፡ አጠገቤ ደርሶ ሁኔታዬን ሲያየው ደስ አላለውም፡፡
“ምን ሆነሀል ህሩይ?” በተጨነቀ ስሜት አስተዋለኝ። ምን ሆንኩ እለዋለሁ? ተዘረፍኩ ልበለው? የመፃፍ አቅሜ ተሟጠጠ፣ቃላት አውላላ ሜዳ ላይ ጥለውኝ እብስ አሉ!.. .ሊገባው አይችልም። እንኳን እሱ የገዛ ጓደኞቼ ችግሬን አውቀውት ምን ፈየዱልኝ?  “ you know what has happened to you? It is a writer’s block. ” እያሉ ለገጠመኝ ጉድ ገለፃ ለመስጠት ነው የሚሞክሩት፡፡ “አሜሪካዊው ደራሲ ፍራንሲስ ስኮት በዚህ በሽታ ይሰቃይ ነበር..   The love of the last tycoon የሚል ድርሰት ጀምሮ እስከህይወቱ ፍፃሜ ሳይጨርሰው ነው የሞተው...” ምናምን እያሉ ነገር ያራቅቃሉ።  እኔ የማውቀው ደስታዬን መነጠቄን ነው! የፀሀፊ መዘጋት የሚባል በሽታ እንደያዘኝ ማወቁ ሳይሆን መድሀኒቱን ነበር የምፈልገው፡፡ ከቃላት የማገኘውን ደስታ ድጋሚ ማግኘት የምችልበትን መንገድ! “ሶደሬ ለሁለት ሳምንት ተዝናና! ወደ ውጪ ሀገር ለምን ቫኬሽን አትወጣም?. . .” የአንዳንድ ሰዎች ምክር ነበር፤በሽታዬ እንዲለቀኝ፡፡ እኔ ግን ደራሲ ነኝ. . . ሶደሬ ለሁለት ሳምንት የሚያስኬድ ገንዘብ ብይዝ እናቴን ነበር የማሳክምበት፡፡
“ባክህ ተወኝ በድሩ! ጥሩ ስሜት ላይ አይደለሁም!” አልኩት፡፡
አንድ ነገር  ሊነግረኝ እንደፈለገ ሲያመነታ ቆየና በእሺታ አንገቱን ነቅንቆ ትቶኝ ሔደ፡፡
ወደ ቤቴ ገባሁ፡፡ ቤት ውስጥ ማንም የለም ነበር፡፡
“ሜላት?” የባለቤቴን ስም ደጋግሜ ጠራሁ፡፡ ምላሽ የለም!
የት ሔደች? ሜላት ከሌለች ቤቱ ሊበላኝ ይደርሳል፡፡ ሜላት ባትኖር በነዚህ አምስት አመታት ውስጥ ምን ልሆን እችል እንደነበር ማሰብ ይከብዳል፡፡ የብዙ ነገር መፅናኛዬ ሜላት ናት! እና እሷን ፈለግሁ. .  የት ሔዳ ነው? በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ተስፋ መቁረጤን መርሳት ሻትኩ፣በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ዓለምን መርሳት፣በእቅፏ ውስጥ ሆኜ ነገን መርሳት. . .ሜላት የመድሀኒት ያህል ናት ለኔ። በጡቶቿ መካከል አስገብታ፣ በጭኖቿ ደግፋ፣ በተስፋ መቁረጥ የደረሰብኝን ሀዘን የምታስረሳኝ መድሀኒቴ፡፡ . . .እና ክፉኛ ፈለግኋት. . . .
ወደ ሞባይሏ ስደውል ተዘግቷል የሚል ምላሽ አሰማኝ፡፡ በድሩ ትዝ አለኝ፡፡ እሱ ጋ መልዕክት አስቀምጣ ይሆናል፡፡ ወደ በድሩ ሱቅ ፈጠን ብዬ ሔድኩ፡፡
“ህሩይ እንኳን መጣህ! ቤት ልመጣ እያሰብኩ ነበር --- ሜላት መልዕክት ነግራኝ ነበር. . .እዚህ ቆመን ከሚሆን ሻይ ቤት ምናምን ሔደን. . . !” አለኝ። በድሩ ከበድ ያለ ጉዳይ ሲጋጥመው “ሻይ ቤት ሔደን እናውራ” የሚል ልማድ አለው፡፡
“በጣም እቸኩላለሁ! የምን መልዕክት ነው አንተ ጋ ያስቀመጠችው?”  አልኩት ነገሩን ለመስማት ጓጉቼ፡፡
“ትንሽ ጥሩ ነገር አይመስለኝም!. . . . . .” አለና በድሩ አቀርቅሮ ሲያስብ ቆየ፡፡ የፊቱን ጭንቀት ሳይ አንድ ጥሩ ያልሆነ ነገር እንዳለ ገመትኩ፡፡
“ግዴለም ንገረኝ ምንድነው? ሜላት ደህና አይደለችም እንዴ?” አልኩት
“ሜላት ሔዳለች ህሩይ!” አለኝ አንገቱን እንዳቀረቀረ
“የት ነው የሔደችው?”
“የት እንደሄደች ባላውቅም ምናልባት ወደ ክፍለ ሀገር እንደሔደች እገምታለሁ!”
“ለምንድነው የሄደችው? አልነገረችኝም እኮ!. . ” በቁጣ ጠየቅሁት
“አልገባህም ማለት ነው ህሩይ! ጥላህ ሔዳለች እያልኩህ ነው! . . . ላትመለስ ሔዳለች እያልኩህ ነው...” በድሩ እንደእድር ጥሩንባ ነፊ ሞቴን ያወጀ መሰለኝ፤ ከዛ በኋላ ያለውን ንግግሩን አልሰማሁትም። ውስጤ የነበረው ባዶነት እንደጥቁር አዘቅት blackhole/ ጥልቅ ሲሆን ይታወቀኛል- ወሰን አልባ ባዶነት!  
እንደቀፎ ባዶ የሆነ አካሌን እየጎተትኩ ወደ ቤቴ ነበር የተመለስኩት፡፡
ሜላት የወትሮ ፉከራዋ ጥዬህ እሔዳለው የሚል ነበር፡፡ ጨክና ታደርገዋለች የሚል እምነት ግን አልነበረኝም! ፈፅሞ!
ለብዙ ዘመን ፅሁፌ ላይ አተኩሬ ለሴት ልጅ የሚሆን ጊዜ አልነበረኝም፡፡ ሜላትን ካየኋት በኋላ ግን የሴትን ልጅ ውበት ችላ ማለቴን መቀጠል አልቻልኩም፡፡ ውድድ! አደረኳት፡፡ ጓደኞቼ እንኳን “ለረጅም ጊዜ አንድም ሴት ሳታፈቅር የቆየህበትን ጊዜ ለማካካስ ይመስላል” እያሉ ለእሷ ባለኝ ፍቅር ላይ ይቀልዱ ነበር፡፡ እንዲህ እንደምወዳት እያወቀች እንዴት ጥላኝ ትሔዳለች?
“ጠብ የሚል ነገር ለሌለው ለምን ጊዜህን እና ጉልበትህን ታጠፋለህ? ሌላ ሥራ ሞክር! መቀየር አለብን፣መሻሻል አለብን. . . ” ከተጋባን ጀምሮ እንዲህ ነበር የምትለኝ ሜላት፡፡  የእኔ ትልቁ መለያ ደግሞ ለሥጋ ማሰብ አለመቻሌ ነው፡፡ ካልሲ እንኳን ገዝቼ መቀየር የሚከብደኝ አይነት ሰው ነበርኩ፡፡ ሜላት ደግሞ የኔ ተቃራኒ ነበረች። የሚታይ የሚዳሰስ ነገር ትወዳለች፡፡ አዲስ የቤት ዕቃ፣መኪና፣የራሳችን ቤት. . .ቢኖረን የደስታዋ ምንጭ ነው፡፡ ለሷ ስል የቲያትር ቤቶችን መድረክ የሚነቀንቅ ተውኔት ለመፃፍ ደጋግሜ ሞከርኩ. . .ግን አልሆነም! በትዳር በቆየንባቸው አምስት አመታት አብዛኛው የቤት ወጪ የሚሸፈነው ሜላት ሰርታ በምታመጣው ገንዘብ ነበር፡፡ አሁን ግን ሔዳለች . . . .
በቃ ተሸነፍኩ! ሴትንም ኪነትንም በተከታታይ ማጣት ይከብዳል፡፡ የሁለቱም ፍቅር ገላንም ነፍስንም የሚያነድ፣የሚያንገበግብ አቅም ነበረው... “ማበድ ሲያንሰኝ ነው!” የሚለው ገፀ ባህሪዬ እያሽካካ የሚያየኝ ይመስለኛል፡፡ ኪነትንም ሴትንም በተከታታይ እንዳጡ ማወቅ ከባድ ነው. . . .ሴትና ኪነት ኪነትና ሴት. . . . .
ሜላት ጥላኝ እንደሄደች ካወቅሁ በኋላ ነገር ዓለሙ ዞረብኝ፡፡
ጥላኝ በሔደች በሶስተኛው ሳምንት አንድ ተአምር ተፈጠረ፡፡ እስከ ውድቅት ድረስ የቤቴን በር ሳልዘጋ በጨለማ ውስጥ በተቀመጥኩበት፤ ተስፋ መቁረጥ፣ብቸኝነት፣ባዶነት፣መሸነፍ. . . ዙሪያዬን እንደጥንብ አንሳ ይዞሩኝ በጀመሩበት አንድ ተአምር ተከሰተ፡፡ ሴት ብቸኝነትን ማርካ የምትገድል ብርቱ ጦረኛ ኖራለች? እያልኩ ሜላትን ክፉኛ በምፈልግበት ወቅት ተአምሩ መጣ፡፡ ሜላት መሸነፌን የምደበቅባት፣ተስፋ መቁረጤን የምከልልባት ስጦታዬ ነበረች፡፡ ሜላት!ሜላት!ሜላት! ብቸኝነት እንደ ውርጭ ነፍሴን አቆረፈዳት. .  ተስፋ መቁረጤን ማስተንፈሻ ፈለግሁ. . . ሜላት ስላልነበረች ሌላ አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ. . .
ለሰአታት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መብራቱን አበራሁ፡፡ ከአልጋው አጠገብ ካለች አነስተኛ ጠረጴዛ ላይ ልሙጥ ነጭ ወረቀት ተቀምጧል፡፡ መፃፊያ እርሳሴን አነሳሁ. . . .
“ባዶ ቤት! ” የሚል ርዕስ ከአእምሮዬ ተስፈንጥሮ ወጣ. . . . . . .
እስኪነጋ ድረስ ከተቀመጥኩበት አልተነሳሁም። ሀሳብ እንደ ጢስ አባይ ፏፏቴ እየተንዶሎዶለ ይጎርፍልኝ ጀመር፡፡ ሁሉን አጣሁ ባልኩበት ሰዓት ኪነት አለሁ ማለቷን ማመን አልቻልኩም፡፡ ለሊቱ ተገባዶ በንጋት ሲተካ በማያቋርጥ የምናብ ጉዞ ላይ ነበርኩ. . .እስከረፋዱ ድረስ ስፅፍ ቆየሁ፡፡ በሰው ተከቦ ብቸኝነት የሚሰማውን አንድ ገፀ ባህሪን መሰረት አድርጎ የሚሔድ የተውኔት ፅሁፍ ነበር፡፡  
እያንዳንዷ ቃል ውስጤን ጠርምሳ ስትወጣ ይታወቀኛል. . . . .በቃ! ከአምስት አመት በፊት እንደነበረው! . . . .የሚወጡት ቃላት እስኪገርሙኝ ድረስ፣የሚፈጠሩት ታሪኮች እስኪያስደምሙኝ ድረስ... .እየፃፍኩት የምጓጓለት ፍሰት ነበረው፡፡ የተሳካ ሥራ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ እራሴን በመጀመሪያ ያረካኝ ሥራ በግምገማ ፈፅሞ ወድቆ አያውቅም. . . አምስት አመት ሙሉ ያጣሁት ይኼንን ነበር፡፡ ሀያ ስምንት የመድረክ ጽሁፎቼን ስፅፍ የነበረኝ ስሜት እንደተመለሰ ገብቶኛል፡፡
“ተመልሻለሁ!” ብዬ መጮህ አማረኝ! ወይም እንደአርኬሜደስ “ዩሪካ! ተገኝቷል!” እያልኩ በአሜሪካን ግቢ ውስጣ ውስጥ ሰፈሮች፣በወለኔ ግቢ፣በወልደጋግሬ ግቢ፣በጎርዶሜ ወንዝ፣በጌሾ ጊቢ፣በአባኮራን ሰፈር... ብሮጥ በወደድኩ፡፡ መፃፍ፣መፃፍ. . በቃላት ዓለምን መበርበር. . .
ረፋዱ ላይ ትንሽ ድካም ተሰማኝ፡፡ ከድካሜ በላይ ግን የፃፍኩትን ሳይ ማመን አቃተኝ፡፡ ሀያ አምስት ገፅ ያለምንም ስርዝ ድልዝ ፅፌያለሁ፡፡ በዚሁ ፍጥነት ከሔድኩ በሁለት ቀን ውስጥ የተውኔቱን ፅሁፍ ልጨርስ እችላለሁ፡፡ የማይታመን ነገር ነው! ለእናቴ መታከሚያ ገንዘብ እንደማገኝ ሳስብ ደስታ ሰውነቴን ወረረው፡፡ ጽሁፉን አለፍ አለፍ እያልኩ አነበብኩት. . .አምስት አመት ሙሉ የቆየሁት እንዲህ አይነት ፅሁፍ ለመፃፍ ነበር!
አምስት አመት ሙሉ ግን የት ነበርኩ? እንደ ካዝና ቁልፍ የተዘጋብኝ የኪነት መንገድ እንዴት ሊከፈት ቻለ? እንቆቅልሹ ቅርፅ እየያዘልኝ ሲመጣ አንዳች አስደንጋጭ እውነት ውስጤ ዱብ አለ! ሜላትን ካገባሁ- አምስት አመቴ! የተውኔት ፅሁፍ መፃፍ ካቃተኝ አምስት አመት!
የመፃፍ አቅሜ ጥሎኝ የሔደው ሜላትን መከተል ስጀምር ነበር ማለት ነው! ከሜላት ጋር ከተጋባን ጀምሮ አንድ ተውኔትም ቢሆን መፃፍ አቅቶኛል! እውነቱ ይህ ነበር፡፡ ፈጽሞ ልረዳው ያልቻልኩት እውነት. . . ሜላትን ከማግባቴ በፊት ለረጅም አመት ብቻዬን ነበር የኖርኩት -በወንደላጤነት፡፡ ብሶቴን፣ንዴቴን፣ተስፋ መቁረጤን፣ጉጉቴን የምተነፍሰው በጽሁፍ ነበር፡፡ ኪነት መተንፈሻዬ ነበረች. . . ሜላትን ካገባሁ በኋላ ግን የኪነትን ቦታ ምህረት ወሰደች፡፡ ተስፋ ስቆርጥ በምህረት እቅፍ ውስጥ መግባትን እመርጣለሁ. . . . . ነፍሴ የምትተነፍሰው በሴት እና በኪነት በኩል ነው ማለት ነው. . . . አንደኛዋ ስትመጣ ሌላኛዋ ትሔዳለች. . .ሌላኛዋ ስትሔድ አንደኛዋ ትመጣለች. . . .እኩል መሔድ አይችሉም፡፡ ሁለቱም ሀሳብ ይፈልጋሉ፣ሁለቱም ውበት ይፈልጋሉ፣ሁለቱም ቀናተኞች ናቸው. . ሁለቱም ይናጠቃሉ!
ሜላት ስትሔድ ኪነት መጣች. . . . .
ሜላትን መቼም ማጣት የምፈልግ አይመስለኝም። እስከ ዓለም ዳርቻ ድረስ ሔጄም ቢሆን የምፈልጋት ይመስለኛል. . . ለጊዜው ግን ተውኔቱን መጨረስ አለብኝ። ለእናቴ መታከሚያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት ቅድሚያ የምሰጠው ተግባር ነበር፡፡ወደ ውጪ መውጣቴን ትቼ የተውኔት ጽሁፌን ቀጠልኩ፡፡ ለግማሽ ሰአት ያህል ሀሳቤ ሳይደናቀፍ ስጽፍ እንደቆየሁ የውጪው በር ሲከፈት ተሰማኝ፡፡ ማን እንደመጣ ለማየት ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ በሩ እየሄድኩ ሳለ አንድ ሰው ወደ ቤት ውስጥ ገባ- ሜላት መካሻ!
ክው ብዬ ቀረሁ! መፃፊያ ብዕሬ ከእጄ ወደቀ፡፡
ሜላት በቆመችበት እንባዋ በጉንጮቿ እየወረደ በሳግ በታፈነ ድምፅ “አልቻልኩም! ምንም ሳታደርገኝ ጨክኜ ጥዬህ ልሔድ አልቻልኩም!” አለችኝ፡፡ ሜላት ተመልሳ ነበር፡፡ ከሶስት ሳምንት በኋላ . . . .
ተሸክማው የነበረውን የልብስ ሻንጣ ተቀበልኳትና ወደ ጓዳ አስገባሁት፤በቆመችበት ጥምጥም አድርጌ አቀፍኳት፡፡ በከንፈሮቼ እንባዋን መጠጥኩት፤ በከንፈሮቿ ሳመችኝ፡፡ እጅግ አድርጋ ናፍቃኝ ነበር፡፡ ሰውነቴ እንደመንቀጥቀጥ እያደረገው ተንሰፈሰፈ፡፡ ወደ አልጋው ተሸክሚያት ሔድኩ. . . . ልብሷን እስክታወልቅ ትዕግስት አልነበረኝም፤በጭኖቿ ውስጥ ለመደበቅ ተቻኮልኩ፡፡
“እወድሀለው! እወድሀለው!” የሚል ለሆሳስ ቃል ሜላት ታሰማለች፡፡ከገላዋ ተጣብቄ “እኔም እወድሻለሁ!” እላለሁ. . . .የኔ ሴት ሆይ እወድሻለሁ! ላንቺ ያለኝ መውደድ በመስዋዕት የታጀበ ነው፡፡ እናቴን እና ኪነትን መስዋዕት የሚያደርግ መውደድ. . .
ከሴትና ከኪነት ሴትን መርጫለሁ! ሴትን ስመርጥ ደግሞ ሌላ ሴትን አጥቻለሁ. . . . . ሴትና ኪነት፣ ኪነትና ሴት. . . .

Published in ልብ-ወለድ
Saturday, 28 December 2013 12:21

“ሐቅ ሐቁን ለህፃናት”

በጥላቻና በእርግማን የተሞላ “መጽሐፍ”

ደራሲ - “አታኸልቲ ሓጐስ
ርዕስ -ሖቅ ሖቁን ለህፃናት
የገፅ ብዛት - 175
የታተመበት ዘመን - 1998 ዓ.ም
የሽፋን ዋጋ - ብር 15.00
መፅሃፉ፤ በአጤ ቴዎድሮስ፣ አጤ ዮሐንስና አጤ ምኒልክ ዘመነ ግዛት ላይ ተመስርቶ የሶስቱንም ነገሥታት ጥንካሬ ሳይሆን ድክመት ለማሳየት የሚሞክር ነው። በተለይ አጤ ኃይለሥላሴን ጨምሮ በዋናነት የሸዋንና የአጤ ምኒልክን “ከሃዲነት” ለማሳየት ያለ የሌለውን የስድብና የእርግማን ናዳውን ለማውረድ ይሞክራል፡፡ አጤ ዮሐንስን ለመናጆነት ቢጨምርም ጭካኔያዎቻቸውን ሌላው ቢቀር የእህታቸው ባል በነበሩት አጤ ተክለጊዮርጊስ ላይ የፈጸሙትን ዘግናኝ ጭካኔ እንኳ አይጠቅሰውም፡፡
ጥያቄ የሚያስነሳው ገና ከርዕሱ ነው፤ “ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” ይላል፡፡ በርዕሱ መሠረት መጽሐፉ የታለመው ለህፃናት ነው ማለት ነው፡፡ ግን ለህፃናት በሚመጥን መልኩ አልተዘጋጀም፡፡ ቋንቋው የተቃና አይደለም፤ ታሪኮቹ እዚያና እዚህ ይወራጫሉ፤ ከሐቅ ይልቅ ተራ ዘለፋና ስሜት ይበዛበታል፡፡ ቀድሞ ነገር ሐቅ የሚያስፈልገው ለህፃናት ብቻ ነው? ሐቅ ሐቁ ለህፃናት ከሆነ፣ ውሸት ውሸቱን ለማን እንዳሰቡለት ፀሐፊው አልገለጹም፡፡
በሶስቱ ነገሥታት ላይ ተመሥርቶ የተጻፈው “መጽሐፍ”፤ ከታሪክ ዘውግ ሊመደብ ቢችልም አንድም የታሪክ አጻጻፍ ባህርይ አይታይበትም፤ ፀሐፊው ራሳቸው እንደነገሩን የታሪክ ዕውቀት የላቸውም፡፡ ከታሪክ አዋቂነት ይልቅ ጨቋኞችን ለመጣል ወደ ትግል መግባታቸውን ነግረውናል (ገፅ 4)፡፡
“ንፁህ ህሊና ያለው ሰው ከእንግዲህ ታሪክ እየሠራን ወደፊት እንገሰግሳለን እንጂ ተመልሰን ቁስል እየነካካን እንኖራለን የሚል አልነበረም” የሚሉን ፀሐፊው፤ እዚሁ ገጽ ላይ (ገጽ 5) መልሰው የስድብ ናዳቸውን ያወርዱታል፡፡ ለጽሑፉ መነሻ የሆነው የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተፈጠረው ድንጋጤ መሆኑን ከመጀመሪያዎቹ የ“መጽሐፉ” ገጾች መገንዘበ ይቻላል፡፡
አንድ ታሪክ ጸሐፊ ከሁሉ አስቀድሞ ሊጽፍ በፈለገው ጉዳይ ላይ የተሟላ ዕውቀት፣ ትዕግስት፣ ሚዛናዊ አስተሳሰብና ክህሎት ሊኖሩት ይገባል፡፡ ታሪክ ልብወለድ አይደለም፤ ልብወለድ ስላልሆነም እንዳሻን እየፈጠርን ምናባዊ ታሪክ ልንተርክ አንችልም፡፡ በዚህ ስሌት ሲታሰብ “ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” በብዙ እንከኖች የተሞላ ነው፡፡
“መጽሐፉ” እጅግ ብዙ ገፅ የሰጠው ሸዋንና አጤ ምኒልክን በመዝለፍና በከሃዲነት በመወንጀል ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያን ታሪክ በመቶ ዓመት ብቻ ለመወሰን ይዳዳዋል፤ የዚህ ሰበቡም በአጤ ምኒልክ ላይ ያለውን መሪር ጥላቻ ለማሳየት ይመስላል፡፡
በመሠረቱ ይህ ታላቅ ስህተት ነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው’ኮ ከሉሲ ነው፡፡ እሱም ቢሆን የስነሰብእ እና የከርሰምድር ተመራማሪዎች አዲስ ግኝት እስከሚያወጡ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ የመንግስትነት ታሪክ ከሶስት ሺህ ዓመታት በላይ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እንደዚህ “መጽሐፍ” ጸሐፊ፤ ከሰሜኑ የአገራችን ክፍል የመጣ ሰው መቸም ይህን ይክደዋል ብዬ አላምንም፡፡ ትግራይ’ኮ የረጅም ጊዜ ታሪካችን መነሻ፣ የሥልጣኔዎቻችን እና የሃይማኖቶች ሁሉ በር፣ የኪነጥበባት ምንጭ ናት። የየሃን ምኩራብ፣ የአክሱምን ሀውልቶች፣ የኢዛናን የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ በቅርቡ የተገኘው የዓድአካውህ መካነ ቅርስና ሌሎችንም ለአፍሪካና ለዓለም ካበረከተ ታላቅ ህዝብ ውስጥ የወጣ ሰው፤ ታሪካችንን በመቶ ዓመት መጉመድ እጅግ አሳዛኝ ድፍረት ነው፤ ወይም አለአዋቂነት ይመስለኛል፡፡
እንደሚመስለኝ የመቶ ዓመቱ ተረት ሊፈጠር የቻለው አጤ ዮሐንስ በጐጃም ላይ በፈፀሙት ቅጣት ተበሳጭተው ታላቁን የትግራይን ህዝብ ጨምረው በአወገዙት ወይም በዘለፉት አፈወርቅ ገብረየሱስ ምክንያት ነው፡፡ አፈወርቅ አጤ ቴዎድሮስንና አጤ ዮሐንስን አውሬ አድርገው፣ አጤ ምኒልክን የመልአክነት ማዕረግ አቀዳጅተዋል፡፡ ለዚያ ደፋር ጽሑፋቸውም ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ በጊዜው ተመጣጣኝ ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ በዚያ ጽሑፍም ነጋድራስ ገብረ ህይወት የአገራችን የመጀመሪያው ሃያሲ መሆናቸውን የመስኩ ምሁራን አረጋግጠውላቸዋል፡፡
ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረየሱስ “አጤ ምኒሊክ” በሚል ርዕስ የጻፉት መጽሐፍ ከታተመ 105 ዓመት ሆኖታል፡፡ ዛሬም ያንኑ ስድብ እያነሱ መቃቃርንና ጥላቻን ለትውልዱ ማስተላለፍ ፋይዳው አይገባኝም። “ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ባሰ” እንደሚባለው፣ እያንዳንዱ መሪ በምስኪኑ ህዝብ ላይ የፈፀመውን የግፍ ዓይነት ብንዘረዝር፣ ሌላው ቀርቶ በሃይማኖት መጻሕፍት (በተለይ በገድሎች) ሰበብ ህዝብ ምን ያህል ሲንቋሸሽ እንደኖረ መግለጽ ይቻላል፡፡ ግን ፋይዳ የለውም፡፡
“በታሪክ የሚኮሩ ኋላ ቀሮች በአገራችን ብዙ ናቸው (ገጽ 8)” የሚሉን ጸሐፊው፤ ከታሪካችን ሌላ በምን እንደምንኮራ ሊነግሩን አልሞከሩም፡፡ “የዝንጀሮ ሰነፍ የአባቱን ዋሻ ይፀየፍ” እንዲሉ ካልሆነ በቀር ለምን በታሪካችን አንኮራበትም? ሰውን እንደ እንቁላል ቀቅለው የበሉት የሂትለርና ሙሶሎኒ ታሪክ እንኳ ከእነ እድፉ ከእነ ጉድፉ ተመዝግቦ እየተጠበቀ ነው፡፡ እንዲያውም በጀርመንማ “አዲሶቹ ናዚዎች ነን” የሚሉ ወጣቶች ፀጉራቸውን እየተላጩ በዋና ዋና ጐዳናዎች ሳይቀር መታየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡
“ጥቃቅን ነገሮችን ትተን በተግባር ላይ ህገ መንግሥት ለኢትዮጵያ ብቸኛና ሁነኛ መፍቻ ነው። ይህንን የሚቃወም ትግሬዎችን በመጥላት ብቻ በስሜት የሚነጉዱ ሸዋዊ የሚኒልክ አስተሳሰብ ጠፍቶባቸውና ጨልሞባቸው የሚባዝኑ ናቸው” (ገጽ 12) የሚለው አገላለጽ ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ታሪክንና ደፋር ዘለፋን ምን አገናኛቸው ያሰኛል፡፡ በአጤ ምኒልክ ዘመን አፈወርቅ ስለተሳደበ፣ በእኛም ዘመን የፈለግነውን ህዝብና ወገን ብንሰድብ ሃይ ባይ የለንም” ከሚል የጉራ መንፈስ በመነሳት ከሆነ ፍፁም የተሳሳተ መንገድ ነው፡፡
በመሠረቱ ህገመንግስቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ወዶና ፈቅዶ ያረቀቀውና ያፀደቀው እንጂ የትግራይ ክልል ብቻ የግል ሃብት አይደለም፡፡ በ1987 ዓ.ም በፀደቀ ህገመንግሥት ሰበብ ወደ ኋላ 100 ዓመት ተጉዞ ምኒልክንና ሸዋን መዝለፍ ከየት የመጣ ታሪክ ፀሐፊነት ነው? ህገመንግስት የእግዚአብሔር የእጅ ሥራ ውጤት አይደለም፡፡ በመሆኑም ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ እንዳፀደቀው ሁሉ እንኳን መቃወም ከነአካቴው ሊሰርዘውም ይችላል፡፡ ህገመንግስቱን መቃወም ማለት በምንም መንገድ የትግራይን ህዝብ መጥላት ሊሆን አይችልም፡፡
ሌላውና ያለ ቦታው የደነጐሩት ጉዳይ የክርስትናም ሆነ የእስልምና ሃይማኖቶች ሲመጡ በጦርነት መሆኑን የገለጹበት መንገድ ነው (ገጽ 16) ይህ ትልቅ ስህተት ነው፤ ክርስትናም ሆነ እስልምና ወደ አገራችን የገቡት ያለምንም ሁከት ነበር፡፡ ለዚህ ማስረጃ ፍለጋ ጸሐፊው ሩቅ መሄድ የለባቸውም፤ ውቅሮ የሚገኘውን የነጃሽ መስጅድ እና አክሱም ጽዮንን ጐብኝተው ሃይማኖቶቹ ያለ አንዳች እንከን ወደ አገራችን እንደገቡ መረዳት ይችላሉ፡፡
ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴንና አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያንም ፀሐፊው “ደቂቀ ምኒልክ” በማለት “ስሁል ሚካኤል” ለዘመነ መሳፍንት መከሰት አስተዋጽኦ አላቸው” በማለታቸው ወርፈዋቸዋል። ይህ አይነቱ ዞናዊ አስተሳሰብ በመሠረቱ ከአንድ “ታሪክ እጽፋለሁ” ብሎ ከተነሳ “ምሁር” የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ስሁል ሚካኤል አጤ ኢዮአስን ገድለው ወይም አስገድለው ከሆነ ታሪኩ መጻፍ ያለበት እንዳለ እንደነበረ ነው፡፡ ጸሐፊው “አላስገደሉም፤ አልገደሉም” ብለው የሚከራከሩ ከሆነ የቀደምት ጸሐፊያኑን ሃሳብ በማስረጃ ነው ውድቅ ማድረግ ያለባቸው እንጂ ተራ ዘለፋ የአዋቂነት መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡
“አጤ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ አደረጉ” የሚለው ሃሳብም ጸሐፊውን በእጅጉ አንገብግቧቸዋል፡፡ (ገፅ 20-21)፡፡ “እንደ ምኒልክ የሸዋ ንጉስ እንኳን የጐንደር ንጉስ ወይም የሌላ አካባቢ ንጉስ የሚባል ንጉስ ታይቶ አይታወቅም” ማን ነው ታዲያ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ያለና በአፄ ቴዎድሮስ ወደ አንድነት የመጣ?” ሲሉም ይጠይቃሉ፤ በስማቸው አደባባይና መንገድ መሰየሙንም ይቃወማሉ፡፡ (ገ. 26)  
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የጸሐፊው የታሪክ ሊቅነት ፈጥጦ የሚወጣው፡፡ ቀድሞ ነገር “ኢትዮጵያ” ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች ብቻ የምታጠቃልል አገር አልነበረችም፤ ሰፊ ግዛት የነበራት ገናና አገር ነበረች፡፡ በየአካባቢውና በየቋንቋው የተሰየሙ በርካታ ነገሥታትም ነበሩ፡፡ በርካታ የአካባቢ ነገስታት ስለነበሩም ነው ማዕከላዊውን ሥልጣን የሚይዘው ሰው “ንጉሠ ነገሥት” የሚል የማዕረግ መጠሪያ የሚሰጠው፡፡
ለምሳሌም በአፋር “ሱልጣን”፣ በሐረር “አሚር”፣ በወላይታ “ንጉሥ”፣ በከፋም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም መሰል የሥልጣን ማዕረጋት ነበሩ፡፡ ሆኖም በአጤ ቴዎድሮስ ተጀምሮ በአጤ ምኒልክ እስኪጠናቀቅ ድረስ የተማከለ መንግሥት አልነበረም፤ ከአጤ ቴዎድሮስ በፊት የነበሩት ነገሥታት በርካታ የመሆናቸውን ያህል የሚያስተሳስራቸው ፖለቲካዊም ሆነ ማህበረ ኢኮኖሚ ሥርዓት አልነበረም፡፡
“ንጉስ ሚካኤል በወሎ፣ ንጉስ ምኒልክ በሸዋና ከዛ በታች ያሉት ግዛቶች፣ ንጉስ ተክለ ሃይማኖት በጐጃም አድርገው ራሳቸው ንጉሰ ነገስት ተብለው በማዕከላዊነት እየመሩ ሥልጣን በየደረጃው ለማከፋፈል መሞከራቸው ያሳያል” (ገፅ 22) ይሉናል ጸሐፊው ሲያስተምሩን። ይህ “ታሪክም” ነው “ሐቅ” ሆኖ ለህፃናት ሊተላለፍ የተፈለገው። በመሠረቱ ይህ ታላቅ ውሸት ነው፡፡ ምኒልክ ከአጤ ቴዎድሮስ ጠፍተው ሸዋ እንደገቡ “ንጉሠ ሸዋ” የሚል ማዕረግ የሰጡት ለራሳቸው ነው፡፡ ራስ ሚካኤልም “ንጉስ” የሆኑት በልጃቸው በኢያሱ አባ ጤና ሲሆን የራስነት ማዕረግ የሰጧቸው ግን አጤ ዮሐንስ ናቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ የማይካደው ለጐጃሙ ራስ አዳል “ተክለ ሃይማኖት” የሚል ስምና የንጉሥነት ማዕረግ የሰጡ አጤ ዮሐንስ መሆናቸው ነው፡፡
ጸሐፊው የአጤ ቴዎድሮስንና የአጤ ዮሐንስን ጭካኔ ሲያነጻጽሩም በተንሻፈፈ ሚዛን ለማስቀመጥ ሞክረዋል፤ አጤ ቴዎድሮስን በተቻለ መጠን አውሬ ለማድረግ ይሞክሩና አጤ ዮሃንስ ላይ ሲደርሱ ብዕራቸው ይዶለዱምባቸዋል። “አፄ ዮሃንስ እንደ አፄ ቴዎድሮስ በሃይልና በማንጓጠጥ አያምኑም ነበር፡፡ ለሁሉም ተቀናቃኝ መሪዎች በሃይል ደምስሰው ስልጣን ብቻቸው እንዲይዙት አይፈልጉም ነበር። … ሳይቀበሏቸው ሲቀሩ ወደ ጦርነት ገብተው ከማረኳቸው በኋላም ወደ ማሰርና መግደል አይቻኮሉም ነበር፡፡ በጦርነቱ ካሸነፉ በኋላ ጦርነቱ የማያስፈልግ እንደነበረና ለተፈጠረው እልቂት አዝነው ሁለተኛ እንዳይደገም በመጽሐፍ ቅዱስ አስምለው መተማመኛ እንዲፈጠር ያደርጉ ነበር፡፡ እምብዛ መላላታቸው ግን ስህተት መሆኑ አይቀርም (ገፅ 31)” ሲሉም የዮሐንስ ጭካኔ መላላት እንዳስቆጫቸው ጽፈውልናል፡፡
ኧረ ለመሆኑ አድዋ ላይ ተዋግተው የማረኳቸውን የእህታቸውን ባል አጤ ተክለ ጊዮርጊስን እንደ አባ ገሪማ ላይ በምን አይነት መንገድ ነበር የገደሏቸው? እንኳንስ በጦር ሜዳ ተሰልፎ የወጋቸውን አንድም የመከላከል አቅም ያልነበረውን የወሎን ሙስሊም ሀይማኖቱን  በግድ ለማስለወጥ ምን አይነት እርምጃ ነበር የወሰዱት? በ1881 ዓ.ም በጐጃም ሰላማዊ ህዝብ ላይ ብቻ ሳይሆን በከብቱ፣ በቤቱና በደኑ ላይ ሳይቀር ምን ዓይነት የጭካኔ እርምጃ ነበር የወሰዱት? በዚህ ድርጊታቸው የተማረረው ጐጃሜስ ምን ብሎ ገጠመ? እያንዳንዱን የጭካኔ እርምጃ በማስረጃ በማስደገፍ መዘርዘር ይቻላል፤ ግን ዮሐንስም ሆኑ ምኒልክና ቴዎድሮስ መመዘን ያለባቸው በነበሩበት ዘመን በመሆኑ፤ በሌላም በኩል ጐጠኝነትንና ዘረኝነትን ለማራገብ ሌት ከቀን ለሚዋትቱ የዋሆች ደንጋይ ማቀበል ይሆናልና አልፈዋለሁ፡፡
“ሐቅ ሐቁን ለህፃናት” መጽሐፍ ላይ የወሎ ሙስሊሞችን አስመልክቶ የተገለፀው ሃሳብ ለብቻዬ እንድስቅ አድርጐኛል፡፡
“በወሎ የነበሩ አክራሪ ሸኾች ‘እስላም ሃይማኖትና ሃገር ነው፡፡ በቱርክ ሃይማኖትን የሚያስፋፋ እየመጣልን ነውና ግብፅን ለማገዝ ተነስ’ እያሉ ለግብፅ ወራሪ ሃይል በማገዛቸውና በሃገራቸው ነፃነት ላይ ስለተንቀሳቀሱ ነው ለውጡ የመጣው (ገፅ 32)” ሲሉ ጸሐፊው በወሎ ሙስሊሞች ላይ ዮሐንስ ለምን እንደ ጨከኑ ሊያስተምሩን ሞክረዋል፡፡ ለካ አክራሪነት የተጀመረው ያኔ ነው? ትልቅ “ግኝት” ነው፡፡
ደግነቱ ዮሐንስ ሞተዋል እንጂ ይህን ቢሰሙ “ለምን ትዋሻለህ? ሙስሊሞችን በጭካኔ የቀጣኋቸው ሃይማኖቴን ባለመቀበላቸው ነው” ሲሉ ጸሐፊውን ይወቅሷቸው ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አጤ ዮሐንስ “ሀቀኛ ክርስቲያን” ነበሯ!  
ገፅ 26 ላይ “የተበተነች ኢትዮጵያ አልነበረችም፤ ስለሆነም ቴዎድሮስ አንድ ያደረጉት ህዝብ የለም” ሲሉ ቆይተው፣ በገፅ 35 ላይ ደግሞ የመጀመሪያ ሃሳባቸውን በማፍረስ “አፄ ዮሐንስ ከሳቸው በፊት ተበታትኖ የነበረ የኢትዮጵያ ግዛት ወደ ነበረበት ለመመለስ ያደረጉት ጥረት አውሮፓ አገር ድረስ ታዋቂነት ያገኘ ነበር” ይሉናል፡፡
ለቴዎድሮስ ሲሆን አገር “አልተበተነም”፤ ለዮሐንስ ሲሆን ግን ይበተናል፡፡ ቀድሞ ነገር አጤ ዮሐንስ በግዛታቸው ላይ የጨመሩት እንኳንስ ጠቅላይ ግዛት አንድ ወረዳ መጥቀስ አይቻልም፡፡ እናም ወዳጄ! “የቄሳርን ለቄሳር!” እንዲሉ፤ የቴዎድሮስን ታሪክ ለቴዎድሮስ፤ የዮሐንስንም ለዮሐንስ መስጠት ይልመድብን፡፡ ሳምንት እቀጥላለሁ፡፡

Published in ጥበብ
Saturday, 28 December 2013 12:19

የእሾህዋ ወፍ!

“ብዙ ዜማ እንድትሰራ እሾኩ ዱልዱም ቢሆን ብዬ ተመኘሁ”

ከተራ ግለሰብነት ወደ ዝና ተራራ መውጣት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አንዳንዶች መውጣት የጀመሩት ተራራ እድሜ እና እድል አብሮአቸው ስላለ፣ በስኬት ሜዳልያ ተጥለቅልቀው ጉዞአቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ ሞታቸውም የድፍን ሀገር ሀዘን ይሆናል፡፡ እኔ ግን ስለእነዚህ አይደለም የማዝነው። እኔ የማዝነው ሰው አይን ገብተው “እንትፍ እደጉ!” እንኳን ለመባል ጊዜ ሳያገኙ ሞት የቀደማቸውን ነው፡፡
እኔ ሚካያ በኃይሉን የማውቃት አብሮ አደጌ ስለሆነች አይደለም፡፡ በእሷ ተወክለናል ከሚሉ የአስተማሪ ጐሳዎች አባልም አይደለሁም፡፡ እኔ ሚካያን የማውቃት በጆሮዬ ነው፡፡ በጆሮዬ አወቅኋት፡፡ በጆሮዬ ለመድኳት፡፡ ከትላንት ወዲያ ደግሞ በሬዲዮ በኩል በጆሮዬ በገባ ዜና መሞቷን ሰማሁ፡፡
እንዴት ተደርጐ መታዘን እንዳለበት የማይታወቅ ሀዘን ግን በልቤ ውስጥ ተሰማኝ፡፡ ጆሮዬ እሷን አስተዋወቀኝ፣ ጆሮዬ ድምፅዋን እንድለምድ እና እንድወድ አደረገኝ፣ ጆሮዬ እንደሞተች ነገረኝ…ጆሮ ግን የልብን ሀዘን ማድመጥ አይችልም፡፡
እስካሁን ከሰማሁት ዘፈኖቿ ውጭ አዲስ ዘፈን ከሚካያ ቅላፄ ወጥቶ ከእንግዲህ ወደኔ ነብስ አይደርስም፡፡ መኖር ብትቀጥል፤ የድምጿ እድገት የት ሊደርስ እንደሚችል መገመት አልችልም፡፡ ድምጿን የማነፃጽርበት መለኪያ የለኝም፡፡ ድምጿና እኔ ባንተዋወቅ ይሻለኝ ነበር እንዴ?
እኔ የመገናኛ ብዙሐን ተወካይ አይደለሁም፡፡ የመገናኛ ብዙሐን ሀዘን የምናውቀው ነው፡፡ ለአንድ ወይንም ለሁለት ሳምንት ብቻ የሚዘልቅ… እንጨት እንጨት የሚል፣ ሥራ ሥራ፣ እጅ እጅ የሚል ሀዘን ነው፡፡ የእውነት አይደለም፡፡ እውነተኛ ሀዘን ያለው እሷን በሰውነቷ ከሚያውቋት ዘመዶቿ፣ ጓደኞቿ … እና በምርጥ ዘፋኝነቷ ከሚወዷት የዘፈኗ አድናቂዎች ዘንድ ብቻ ነው፡፡ ሌላው የወሬ ፍጆታ ነው፡፡
እኔ በ1999 መጨረሻ አካባቢ የሷን ዘፈን ለመጀመሪያ ጊዜ ስሰማ የተሰማኝ ስሜት፣ በድርሰት ንባብ ላይ ምርጥ ታሪክ ሳነብ ከሚያቁነጠንጠኝ ስሜት ጋር አንድ አይነት ነበር፡፡ ስሜቱን ማንም ዝም ብሎ ሊፈጥርብኝ አይችልም፡፡ ስሜቱን የፈጠረችብኝ ዘፋኝ እና እኔ የአንድ የውበት ቀለም እና የሀሳብ ዘመን ሰዎች ነን፡፡
“ምን ሆና ነው የሞተችው?” ብዬ ስጠይቅ፤ አጥጋቢ መልስ እንደማይሰጡኝ አውቄአለሁ። እንደተለመደው “ታማ” ነበር አሉኝ፡፡ በመጠየቄ አላፈርኩም፡፡ ትርጉም የማይሰጥ ዘመን፣ ትርጉም የማይሰጥ ህይወት እና ሞት ትርጉም ከማይሰጥ መልስ እና ጥያቄ ጋር አንድ ናቸው፡፡
ታምማ ነበር!
ማን ያልታመመ አለ፡፡ መታመሙን ያላወቀ ነው እንጂ… ያልታመመ ማን አለ፡፡ ማን መሞት ያልጀመረ አለ፤ ሞቶ እስኪጨርስ ያለማወቅ ጉዳይ እንጂ!
ለነገሩ ሚካያ ዩኒቨርስቲ ገብታ ተምራ የተመረቀች ሴት መሆኗ ራሱ፣ መታመሟን የማወቋ ምልክት ነበር፡፡ መታመማቸውን ያላወቁትማ ዘፋኝ ለመሆን መማር አያስፈልጋቸውም፡፡ እነሱ፤ የድምጽ እድገት ከአስተሳሰብ እድገት ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ አይጠበቅባቸውም፡፡ የትኛዋ ዘፋኝ ናት መምህርት ሆና የምታውቅ?! ይህም ከህመም በማወቋ ለመዳን ብዙ የመሞከሯ ምልክት ነው፡፡
ሞክራለች፤ የሚሞከረውን ሁሉ፡፡
ለድንገተኛ ሞቷ ትርጉም ለማግኘት በማደርገው ሙከራ፣ የሷን ድምጽ ያሳጣንን ነገር ለመወንጀል ተመኘሁ፡፡ አንድ ነገር ከሆነ! እንክብካቤ የነፈጋት ማነው? ችላ ያላት ማነው? በጆሮው ድምጿን የበላው ህዝብ፤በዙሪያዋ እያለ ስትታመም ዝም ብሎአት ሲያበቃ… የሞቷን ወሬ ለመንገር ከመሮጥ ለምን ነው አብሮ የህመሟን ምክንያት ያልመረመረው?
ሀገርን ወክላ “ለኮራ” የሙዚቃ ሽልማት ስትታጭ፤ “ተባረኪ” ያላት ህዝብ፣ ሽልማቱን አሸንፋ መመለስ ሲያቅታት “ደባ ተሰርቶብኛል በውድድሩ ላይ” ስትል ምነው ጆሮውን ነፈጋት፡፡ ይህ ጆሮአችን “ድልን” እና “ብልጽግናን” ብቻ መስማት ወዶ “ድል” እና “ብልጽግና” የሚመጡት ለጥበበኛው ምን ሲሟላለት እንደሆነ መስማት እንዴት አቃተው?
“ደስተኛ አልነበረችም” አሉ…እኛን ግን በዜማዎቿ ደስተኛ አድርጋናለች፡፡ ድሮ፤ ጥበበኛን እንደ “እሾክ ወፍ” አድርጌ ስመስል፣ ተምሳሌቱ ሙሉ በሙሉ እውነት መሆኑን አምኜ አልነበረም፡፡ አሁን ግን እውነት መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ነገሩ እንደዛ ነው። ሚካያ በሀይሉም የእሾኳ ወፍ ናት፡፡ የእሾኳ ወፍ የምትዘምረው አንዴ ነው፡፡ ለመዘመር ዝግጁ ስትሆን ረጅም እና ሹል በሆነው እሾክ ላይ ደረቷን ታስደግፍና ማዜም ትጀምራለች፡፡ እሾኩ ደረቷን እየወጋ፣ እያስጨነቃት በሄደ ቁጥር የዜማዋ ድምጽ እያማረ፣ እየጠነከረ… አሳዛኝ እየሆነ ይሄድና…በስተመጨረሻ እሾኩ ደረቷን በስቷት ሲገባ…ዜማዋና ህይወቷ…አንድ ላይ ይጠናቀቃሉ፡፡
እሾኩ ደረቷን እየወጋት ስታዜም ያዳምጣት የነበረ ሕዝብ… የሚፈልገው ዜማውን ብቻ በመሆኑ ስለ ወፏም ሆነ ስለ እሾኩ አያገባውም፡፡ ህመሟ ምንድነው? ብሎ ማን ጠየቀ?...የሚፈልገው ዜማውን ብቻ ነው፡፡ ህዝብ መስዋዕት ይወዳል፡፡ ብዙ ዜማ እንድትሰራ እሾኩ ዱልዱም ቢሆን ምናለበት ብዬ ተመኘሁ፡፡ የምኞት ጊዜ ግን አልፏል ለሷ፡፡
የጥበብ ታዳሚ ወርቁን እንጂ ሰሙን አይፈልግም። ስለ ዜማው እንጂ ዜማው ከምን ውስጥ እንደመነጨ አይገደውም፡፡ የወፍን ድምጽ ቀርፆ መሸጥ፣ ለራሱ ስሜት ማሟያ መክፈት፣ ከወፏ  የሚገኘውን የድምጽ ደም ዋጋ በብር መልክ መቅዳት እንጂ…ስለ ወፏ ህመም አያገባውም፡፡ ምናልባት የሚካያ ህመም ምክንያት መታመሙን የማያውቀው ህዝብ ሊሆንም ይችላል። ወፏ ከሞተች በኋላ እሾኩ መኖሩን ይቀጥላል። ከዚህ በፊት ብዙ ምርጥ ቀለም ያላቸው የጥበብ ወፎችን እየወጋ ገድሏል፡፡ ወደፊትም የሚመጡ አዳዲስ ድምፆች መግደል እንዲችል ተዘጋጅቶ፣ ሾሎ እየተጠባበቀ ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የተሰማኝ ሀዘን የራሴ ነው፤ የመገናኛ ብዙሐንን ተዝካር የምወክል አይደለሁም፡፡ ያዘንኩት ለጥበበኞች የ40 ቀን እድል ነው፡፡ ለጥበበኞች አዲስ ዘመን አልመጣም፡፡ የድሮው ሰው አዲስ ጭምብል ለብሶ ነው የጥበብ ታዳሚ ነኝ የሚለው፡፡ ያሳዝናል፤ ያማል፡፡ “ምን ሆና ሞተች?” ስል “ታምማ ነበር” ነው ያሉኝ፡፡ እኔ አዝኛለሁ፤ ግን እጽናናለሁ፡፡ የእሷን ድምጽ ግን አባብሎም ሆነ አጽናንቶ የሚመልሰው ማንም ከእንግዲህ የለም፡፡     


Published in ጥበብ
Saturday, 28 December 2013 12:15

ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ

የቋንቋው ሊቅ፣ የቃላት መዝገቡ
ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “ጥሩ የአማርኛ ድርሰት እንደምን ያለ ነው?” ብለው ጠይቀው ነበር። በርሳቸው አጠያየቅ መንገድ “ጥሩ የቋንቋ ሊቅ እንደምን ያለ ነው?” ስንል የእኛ መልስ “እንደ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ያሉ” ይሆናል፡፡
መቸም የቋንቋን ነገር እጥግ ድረስ የተከታተሉ ሰዎች አሉ ከተባለ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ አንዱ መኾን አለባቸው፡፡ በተለይ በሥነ ልሳን ትምሕርት “ሴማዊ” የሚል ስም በተሰጣቸው ቋንቋዎች (አማርኛ ግእዝ፣ ዓረብኛና ዕብራይስጥ) ላይ የተራቀቁ ነበሩ፡፡
የዶክተር አምሳሉ አክሊሉ የቋንቋ ችሎታ በነዚህ አይወሰንም፡፡ ከአውሮፓውያኑ እንግሊዝኛን፣ ጀርመንንና ጣሊያንኛን ጥርት አድርገው የሚያውቁ ነበሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ባንዱ ቋንቋዊ ጉዳዮችን መጻፍና ማስረዳት የሚችሉ ልዩ ሰውም ነበሩ፡፡
“ቋንቋ እውቀት አይደለም፣” ይባላል፤ እውቀትን ማግኚያ እንጂ፡፡ ሁለቱንም የሚኾነው ለባለሞያው ነው። እንደዚያ ከኾነ፣ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከምር የቋንቋ ሊቅ ነበሩ፡፡ ይህንንም ሊገልጡ በሚችሉ መሠረታዊ ሥራዎቻቸው አስመስክረዋል።
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከአባታቸው ከቄስ አክሊሉ ወልደአብ እና ከእናታቸው ከእማሆይ ታንጉት በየነ፣ በ1922 ነሐሴ 27 ተወለዱ፡፡ የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ማብቂያ ላይ የተወለዱት አምሳሉ፤ እዚያው ደሴ አካባቢ የትውፊታዊውን ት/ቤትና የ፩ኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ፈጽመው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ት/ቤት የ፪ኛ ደረጃ ትምሕርታቸው ቀጥለዋል። ይኽንንም በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው የነፃ ከፍተኛ ትምሕርት ዕድል በማግኘት ወደ ግብፅ ሔዱ፡፡
በግብፅ ካይሮ ውስጥ በሚገኝ መንፈሳዊ ኮሌጅ የስነ መለኮት ትምሕርታቸውን እየተከታተሉ፣ እዚያው ካይሮ ውስጥ ባለው የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የሶሺዮሎጂ ትምሕርታቸውን ተምረዋል፡፡ በሁለቱም ትምሕርታቸው በ1949 ዓ.ም በአስደናቂ ውጤት ሁለት ዲግሪ አግኝተዋል።
ከዚያም ወደ ጀርመን በመሔድ በቲዩንቢንገን ዩኒቨርሲቲ በ1954 ዓ.ም የፒኤች.ዲ ዲግሪአቸውን አግኝተዋል፡፡ በጀርመን ቋንቋ ያቀረቡት ወረቀት በታዋቂው ኢትዮፒያኒስት በኦገስት ዲልማን ግእዝ-ጀርመን መዝገበ ቃላት ሥራ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተማሪያቸው ከነበሩትና አኹን በአ.አ.ዩ የቋንቋ ጥናት የፊሎሎጂ ዘርፍ ኃላፊ ከኾኑት ከዶክተር አምሳሉ ተፈራ ለመረዳት ችለናል፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፤ በ1958 በአ.አ.ዩ ረዳት ፕሮፌሰር፣ በ1969 ተባባሪ ፕሮፌሰር ማዕረግን ያገኙ ሲኾኑ፣ የዩኒቨርሲቲው የቋንቋ ጥናት ተቋም የፕሮፌሰርነት ማዕረግን እንዲያገኙ ለዩኒቨርሲቲው አቅርቦ እንደነበረም ታውቋል፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ከቲዩቢንገን የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ወደ ሀገራቸው በመመለስ፣ በብሔራዊ ቤተመዛግብት ወመዘክር የሳይንስ ቡድን ዳይሬክተር በመኾን ለሁለት ዓመት አገልግለዋል፡፡
ከ1956 ዓ.ም. ጀምረው በአ.አ.ዩ. የቋንቋ ትምሕርት ክፍል መምሕር በመኾን የግእዝ፣ የአማርኛ፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና መዝገበ ቃላት ማጠናቀርን ለሠላሳ ሁለት ዓመት ሲያስተምሩ ቆይተዋል፡፡ በ1988 ዓ.ም. ጡረታ እስኪወጡ ድረስ ባገለገሉበት የአ.አ. ዩኒቨርሲቲ በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም አከናውነዋል፡፡
በጀርመን ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጥናት ክፍል የአማርኛ እና ግእዝ መምሕር በመኾን እስከ 1996 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
ከ1996 ዓ.ም በኋላ ቀድሞ ሲያስተምሩ በቆዩበት አ.አ.ዩ፣ በነገረ ጽሕፈት ትምሕርት (ፊሎሎጂ) የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር አገልግሎታቸው የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አፍርተዋል፡፡
ከነዚህም ሌላ ከስምንት ያላነሱ ልዩና መሠረታዊያን የኾኑ መጻሕፍትን በማቅረብ፣ የቋንቋ እውቀታቸውን ከማስመስከራቸውም በላይ፣ እውቀታቸውን ለትውልድ በጽሑፍ ትተው ያለፉ ምሁር ናቸው፡፡
የአምሳሉ አክሊሉን እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት የማያውቃት ተማሪ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ውስጥ መምሕር ከነበሩት ከጂ.ፒ ሞስባክ ጋር ያዘጋጇት እንግሊዝኛ - አማርኛ መዝገበ ቃላት፤ በየትኛውም የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ንትብ ብላ እስክታልቅ ድረስ መገልገያ የኾነች ናት። ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ ስትታተም የቆየችው ይቺ መዝገበ ቃላት፤ በአማዞን ዶት ኮም እና በ“ጓዳ አታሚዎች” በሕገወጥ ከሚታተመው ውጭ፣ ከአንድ ቀጥተኛ ካልኾነ መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው፣ ከዘጠኝ ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ የታተመች መጽሐፍ ናት፡፡ ከአቀራረቡ ዓይነት ጀምሮ፣ ከቃላት ትርጉምም በላይ የኾነው ሌላው አስደናቂ ሥራቸው ደግሞ አማርኛ-እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ነው፡፡
እጅጉን የከበደ እና ጊዜ ፈጅ የኾነውን የመዝገበ ቃላት ማጠናቀር ሥራ ያስተምሩ የነበሩት ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፣ ጀርመን-አማርኛ መዝገበ ቃላትንም አሳትመው አቅርበዋል፡፡
ከነዚህም ሌላ ከአቶ ሙኒር አብራር ጋር በመኾን ዓረብኛ-አማርኛ መዝገበ ቃላትንም ሠርተዋል፡፡ ሙኒር አብራር እንደገለጹልን፤ “አቡጊዳ አማርኛ-እንግሊዝኛ” የተሰኘውን የመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸውን የአርትዖት ሥራም ያከናወኑት እኝኹ ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ ነበሩ፡፡
ሌላይቱ ምጥን ያለች አስደናቂ ሥራቸው በቡክ ወርልድ የታተመችላቸው የአማርኛ ሞክሼ ፊደላትን አጠቃቀም (አጻጻፍ) በሆሄያት ቅደም ተከተል ያቀረቡባት በኪስ መጠን የታተመችው መጽሐፋቸው ናት፡፡ እያንዳንዱ የአማርኛ ጸሐፊና ጋዜጠኛ ከኪሱ ሊለያት የማይገባው ምርጥ ሥራ ናት፡፡ በአ.አ.ዩ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ የታተመው “የአማርኛ ፈሊጦች” መጽሐፋቸው ደግሞ ሌላው የቋንቋ ሰውነታቸውንና ሙያቸውን ማሳያ ጠቃሚ ሥራ ነው፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ፤ የዩኒቨርሲቲው ህትመት ድርጅት ተጠባባቂ ዳይሬክተር በመኾንም በ1987 ተሾመው ነበር፡፡ ዶክተር አምሳሉ ለዩኒቨርሲቲው የስነ ጽሑፍ ትምሕርት ክፍል መማሪያ መጽሐፍ የሚኾን፣ “የኢትዮጵያ የስነ ጽሑፍ ቅኝት” የተባለ መጽሐፍም አቅርበዋል፡፡ ታትሞ በመማሪያነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በስነ ጽሑፍ በተለይም በአጫጭር ልብወለድ ታሪኮች ብቻዋን ጥሩ በመማሪያነት የምትኾነውና ልጨኛ የኾኑ፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የታወቁ ደራሲያን የጻፉዋቸውን አጫጭር ታሪኮች በአማርኛ ያቀረቡባት መጽሐፍም ሌላዋ ተወዳጅ ሥራቸው ናት፡፡
በትክክል በአማርኛ የቀረበች የትርጉም ሥራ ከመሆኗ በላይ፣ የታሪኮቹ ድንቅነት ተጨምሮ ዶክተር አምሳሉ በኢትዮጵያ የልብ ወለድ ሥነጽሑፍም ላይ የድርሻቸውን ጠብ ያደረጉ አባት መምሕር ነበሩ ያስብለናል፡፡
“ጥሩ የአማርኛ ልብወለድ ታሪክ እንደምን ያለ ነው?” የሚለውን ጥያቄ የመለሱ፣ “ለአንድ ሰው ምን ያህል መሬት ይበቃዋል?” ዓይነቶቹን ታሪኮች በትክክለኛ አማርኛ ያገኘንባት መጽሐፍ ናት፡፡
ዶክተር አምሳሉ፤ በአካዳሚክ ተቋማት እጅግ ያስከበሯቸውንና የተለያዩ ማዕረጐችን ያሰጧቸውን ብዙ የምርምርና የጥናት ሥራዎችን ያቀረቡም ነበሩ፡፡ ዓለም ዓቀፋዊ ዕውቅና ባላቸው በተለያዩ መጽሔቶች፣ መጻሕፍት፣ በመዛግብተ ስብእ፣ በዓውደ ጥበባት እና በመድብለ ጉባዔዎች የምርምር ሥራዎቻቸው የታተሙላቸው እንደነበሩ፣ በዜና ሞታቸው ላይ ከቀረበው ታሪካቸው ታውቋል፡፡ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብን በተመለከተ በጣሊያኖቹ ኢትዮ ፕያኒስቶች የቀረቡ ጽሑፎችንም ከሞገቱ ሁለት ሰዎች አንዱ ነበሩ። ምናልባት ከምርምርና ጥናታዊ ሥራዎቻቸው ውስጥ ከት/ቤት እና ዓውደ ምርምር ወጥቶ የተነበበ ጽሑፋቸው ይሄ ብቻ ሳይኾን አይቀርም፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በእርግጥም “የቋንቋ ሊቅ እንደምን ያለ ነው” ተብሎ ቢጠየቅ “እንደ ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ” ብለው ቢመልሱ፣ የማይበዛባቸው ታላቅ መምሕር፣ ታላቅ አባት ነበሩ።
እኝህ አባት መምሕር ናቸው ባለፈው ሳምንት በ84 አመታቸው ታኅሣሥ 11 ቀን 2006 ዓ.ም ዐርፈው በየካ ደብረ ሣህል ቅዱስ ሚካኤል ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሙያ ባልደረቦቻቸውና ተማሪዎቻቸው እንዲሁም በሥራዎቻቸው የሚያውቋቸውና አድናቂዎቻቸው በተገኙበት ቀብራቸው የተፈፀመው፡፡
ዶክተር አምሳሉ አክሊሉ በ1959 ዓ.ም ጥቅምት 13 ከወ/ሮ ቀለመወርቅ ጋር ሕጋዊ ጋብቻ በመፈፀም የሦስት ወንዶችና የሁለት ሴት ልጆች አባት ሲሆኑ የስድስት ልጆች አያትም ነበሩ፡፡  

Published in ጥበብ

በኢትዮጵያ እንደ አበባ ከፈኩት ጥበባት ውስጥ አንዱና በሌላው አገር የሌለው የግዕዝ ቅኔ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡  በኢትዮጵያ ጥንታዊ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ፣ በግዕዝ ተገጥሞ የሚቀርብ ሥራ ቅኔ መሰኘቱ የረቀቀና የመጠቀ ሐሳብ እጥፍ ድርብና መንታ ፍልስፍና ስለሚተላለፍበት ነው፡፡ ይህም ማለት ቅኔ የራሱ መነሻ ሰበብ፣ መድረሻ ምኩራብ አለው ማለት ነው፤ ትንሲቱ ብዙ ነው፡፡
ከጥንት ዘመን ጀምሮ ቅኔያት ከታላላቅ ሊቃውንት አእምሮ እንደግዮን ምንጭ እየፈለቁ ሲፈስሱ ኖረዋል። “ይበል እሰየው” እየተሰኙ በመደነቅም  ከትውልድ ወደ ትውልድ በቃል  ሲተላለፉ ኖረዋል። የተወሰኑትም እየተንባጠቡና እየነጠቡ ጠፍተዋል፡፡ ነገር ግን ለዚህ ታላቅ ቅርስና የአዕምሮ ፈጠራ የተቆረቆሩ ጥቂት ለባውያን ቅኔያትን ለማሳተም ጥረት አድርገዋል። ለቅኔ ፈጠራ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ከአሰባሰቡ የውጭ ሀገርና የአገር ውስጥ ምሁራንና ሊቃውንት መካከል ጣልያናዊው ኢኞሲዮ ጉይዲ (1901 ቅኔ ኦ .ኢኒ አቢሲኒ) በሚለው መጽሐፉ 44 ቅኔያትን፣ ፈረንሳዊው አንቶን ዲ አባዲዩ (1908 ልዳ ከልታ ዲ ቅኔ ኤም ኤስ) 86 ቅኔዎችን፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴር (1951 የዐባይ ውሃ ልማት መጀመሪያ መሠረት) 79 የቅኔ ፈጠራዎችን፣ አለቃ ይኹኖ አምላክ ገብረ ሥላሴ/1958 የጥንት ቅኔዎች/ 22 ቅኔዎችንና በትክክል የትርጉም ይትበሃሉን ጠብቀው ወደ አማርኛ የተረጐሙ/ ይሄይስ ወርቄ 1960 ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት አዕማደ ምሥጢራት/ 79 ቅኔዎችን በአግባቡና በጥልቀት የተረጐሙ፣ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተማርያም ወርቅነህ  (1963 ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት) 107 ቅኔዎችን፣ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ (1963 -1984 መጽሐፍ ቅኔ ዝክረ ሊቃውንት) 2829 ቅኔዎችን ያለ ትርጓሜ፣ አቅርበውልናል፡፡ ከፍያለው መራሂ (ቀሲስ) 2006 እ.ኤ.አ The meaning of quine; the river life) 31፣ ቋንቋዎች አካዳሚ (1980፣1984፣1955) በሦስት ክፍል 1143 ቅኔያትን የግዕዝ ቅኔያት፤ ከእነተርጉማቸውና ትንታኔያቸው፣ አለቃ ኤልያስ ነቢየ ልዑልና ቀሲስ ከፍያለው መራሒ (1992 ትርጓሜ ቅኔ ፈለገ ሕይወት) 120 የቅኔ ድርሰቶችን፣  ታደለ ገድሌ (1997 ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ) 47 ቅኔዎችን ወደ አማርኛ በመመለስ፣ ብርሃኑ ድንቄ /1997 አልቦዘመድ/ 10 ቅኔያትን፣ ያሬድ ሽፈራው ሊቀሊቃውንት (2002 መጽሐፈ ግስ ወሰዋሰው መርኖ መጻሕፍት) የራሳቸውን 213 ያለ ትርጉም፣ ዮሐንስ አፈወርቅ ኤስድሮስ (2002 የመምህር አካለወልድ የሕይወት ታሪክና ቅኔዎቻቸው) 184 ቅኔዎችን ወደ አማርኛ በመቀየር፣ ዕደ ማርያም ጸጋ ተሻለ/2003 የሊቀ ካህናት ጸጋ ተሻለ የሕይወት ታሪክ) 28 ቅኔያዊ ፈጠራዎችን ወደ አማርኛ በመቀየር አሰባስበው አቅርበውልናል፡፡
አቶ ተክለ ፃድቅ መኩሪያ (1951 የኢትዮጵያ ታሪክ ከዐፄ ዩኩኖ አምላክ እስከ ዓፄ ልብነ ድንግል) 25 የዓፄ ናዖድ የቅኔ ድርሰቶችን ከገድለ ፋሲለደስ ውስጥ አሰባስበው ሲያሳትሙ፣ አለቃ ዕንባቆም ቃለ ወልድ 33 የግዕዝ ቅኔያትን (ያልታተሙ) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናትና ምርምር ተቋም ሰንደውልናል፡፡
ዓለማየሁ ሞገስ (1961 ሁለት ወር በዋሸራ) 1976 የዋሸራ ቅኔዎችን አሰባስበውና ጽፈው አስቀምጠውልናል። ቅኔያቱ ገና አልተተረጎሙም፣ አልተተነተኑምም፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ሰዎች ከኢኛሲዮ ጉይዲና አንቶን ዲ.አባዲ በስተቀር እንዲሁም አቶ ተክለዳዊት መኩሪያ (መሠረታዊ የቅኔ ዕውቀት ግንዛቤ እንደነበራቸው ብቻ ተገንዝቤያለሁ) ሌሎች ቅኔ ቤት ገብተው ግስ የገሠሡ፤ በተለይም እንደነ መምህር አካለወልድ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አድማሱ ጀምበሬ፣ ይኄይስ ወርቄ፣ ይኩኖ አምላክ ገብረ ሥላሴ፣ ዓለማየሁ ሞገስ፣ ያሬድ ሺፈራው የመሳሰሉት በዕውቀት ሠገነት ላይ ወጥተው የሚቀመጡ ሊቃውንት መሆናቸው ጥርጥር የለውም፡፡
“ላይፈቱ አይተርቱ” እንዲሉ ይህንን ሁሉ የጠቀስኩት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሰሞኑን በታላቁ የቅኔ ፈላስፋ በተዋነይ ዘጎንጅ ስም አንድ መጽሐፈ-ቅኔ ታትሞ በማየቴ ነው፡፡ መጽሐፉን ማየት ብቻ ሳይሆን የገዛሁበት ትንሲቱም እንዲህ ነው፡፡
ሰሞኑን ከዋሸራ ማርያም ተነሥቼ ወደ ባሕር ዳር የምሔድበት ጉዳይ ገጥሞኝ ነበር፡፡ ባሕርዳር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ለጸሎት እንደቆምኩ አንድ መጽሐፍ አዝዋሪ የታላቁን የቅኔ ፈላስፋ የተዋነይን ስም የያዘ መጽሐፍ አሳየኝ፡፡ ወዲያው ከጸሎቴ ተናጠብኩና መጽሐፉን ተቀብዬ በዓይነ ገመድ አየት አየት አደረግሁት፡፡ የዋሸራ ሰው ደግሞ ከገንዘብ ይልቅ ለቅኔ ስሱ ስለሆነ ዋጋው ስንት ነው? ብዬ መጽሐፍ አዝዋሪውን ጠየቅሁት፡፡
“ዋጋው ከጀርባው ላይ አለ፤ 100 ብር” አለኝ። የመጽሐፉ ወረቀት ከግማሽ በላይ ባዶ ነው፡፡ ትናንሽ መስመር ያላቸው ቅኔዎች (ለምሳሌ አንዲት ባለ ሁለት ቤት ጉባዔ ቃና ቅኔ በአንድ ገጽ ላይ ሠፍራ ሌላው ወረቀት ባዶ ነው፡፡ በሚቀጥለው ገጽ ግን አቶ ኤፍሬም የቅኔያቱን ሰማዊ ፍች ወደ ግጥም ቀይሮ፣ ከባለ ቅኔው እሳቤ ውጭ ቃላት ደርድሮ ገጹን ለመሙላት ሞክሯል፡፡
የመጽሐፉ ርእስ “ተዋነይ ብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታትና ሊቃውንት” ይላል፡፡ አሳታሚው “ሻማ ቡክስ” ነው። የመጽሐፉ ገጽ 190 ሲሆን ቅኔያቱ ሁለት ሦስት እየሆኑ በየገጹ ቢስተናገዱ ኖሮ፣ መጽሐፉ ከ50 እና 60 ገጽ አይበልጥም ነበር፡፡ ስለዚህ አንባቢው ለዚህ መጽሐፍ 100 ብር የሚከፍለው ለባዶው ወረቀት ጭምር ነው፡፡
አቶ ኤፍሬም ሥዩም የተለመዱ ቅኔዎችን ከተለያዩ መጻሕፍት ቀንጭቦ 24 ጉባዔ ቃናዎችን፣ 6 ዘአምላኪየዎችን፣ 2 ሚበዝጐዎችን፣ 10ዋዜማዎችን፣ 10 ሥላሴዎችን፣ 1 ዘይዕዜ፣ 1 ሣህልከ፣ 1 ኩልክሙ፣ 13 መወድሶችን፣ 5 ክብር ይዕቲዎችን፣ 2 ዕጣነ ሞገሮችን፣ 2 አርኬዎችን፣ 1 ምስጋና /የያሬድ/፣ 1 ደረጃ ያልሰጠውና የሌለው (ግን የድሮ ባለ ሦስት ቤት ክብር ይዕቲ)፣ 2 ጥቅሶችን፣ በድምሩ የአቶ  በላይ መኮንንን ቅኔ ጨምሮ 83 ቅኔዎችን አሳትሟል፡፡ ማሳተም ብቻ ሳይሆን የቅኔዎችን ሰማዊ ትርጉም ወስዶ በራሱ መንገድ ወደ አማርኛ ግጥም ቀይሯቸዋል፡፡ ኤፍሬም አንዷን ባለ ሁለት ቤት ጉባዔ ቃና ዘተዋነይ (ገጽ 60) ከተዋነይ መንፈስና ዕሳቤ ውጭ በ3 ገጽ ግጥም ጽፎባታል፡፡ እዚህ ላይ የምናስተውለው የባለቅኔዎችን የመጠቀና የረቀቀ ምሥጢር ሳይሆን የኤፍሬምን ፈንታዚያ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በነጻና በውርስ ትርጉም ስም በቅኔ ጥበብ ላይ መቀለድ ነው፡፡ ቅኔ ደግሞ የወሸነኔ ስሜት መግለጫና መቀለጃ አይደለም፡፡ የቅኔ ይትበሀሉንና ሊቃውንቱንም መናቅ ነው፡፡ ለቅኔ ዋናው ተፈላጊ ነገርኮ ወርቁ ውስጠቱና ማሩ ነው፡፡ ሰሙ፣ ሰፈፉ፣ ገለባው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ገጽ 64 የቅኔ ቁጥር 21 “ሙሴ በታቦር እመ ትሬዒ ደመና፡፡ ኢይሞሰልከ እስኩ ዘይወርድ መና፡፡ ርዒተ መና ጥዑም አምጣና ተርፈ በሊና፡፡” የሚለውን ቅኔ፣ ኤፍሬም በመሰለው ግጥም ቢያደርገውም የራሱ ምሥጢር አለው፡፡ እና ምሥጢራትን፣ ወርቃዊ መልዕክቶችን ኤፍሬም ለምን አላነጠራቸውም? ግልጽ ነው፡፡ ራሱም እንዳለው ቅኔ ቤት ገብቶ ግስ አልገሰሰም፣ ተነሽና ወዳቂውን፣ ሩቅና ቅርቡን፣ ነጠላና ብዙውን፣ ረቂቁንና ግዑዙን፣ ጨለማና ብርሃኑን፣ ሰያፉን፣ አንቀጹን፣ ባለቤቱን፣ አቀባዩን፣ ዘርፍን አያያዙን፣ ዋዌውን፣ ገቢር ተገብሮውን፣ መዳቡን፣ ዕርባ ቅምሩን፣ ዕርባ ግሱን፣ ክረምትና በጋውን፣ ተባእቱንና አንስቱን፣ ዕፀዋቱን፣ አዝዕርቱን፣ ጠሉን እነ ራምኖንን፣ እነ ጳውቄናን … አልተማረም፡፡
ቅኔ ደግሞ በጨለማ የሚገቡበት፣ በነጻ ወይም በውርስ ትርጉም ስም የሚፏልሉበት ጥበብ አይደለም። ቅኔ ያልቆጠረ፣ ቅኔ ያልነገረ ሰው በድፍረት ዐደባባይ የወጣበት ዘመን ቢኖር ይህ ያለንበት ጊዜ ነው፡፡ የቅኔ ምሥጢሩ እንጂ መንፈሱ አይወረስም፡፡ ሰም በቅኔው ዙሪያ ለመሽከርከር የሚያጅብ ሚዜ እንጂ ዋናው ሙሽራው ወርቁ ነው፡፡ ሁለቱ አይለያዩም፡፡ አንዱ ከአንደኛው ተነጥሎ ቢቀርብ አይደምቅምም አያምርም። እሳት የሚጫረው ዐመዱ ተገልጦ ነው፡፡
ቅኔ በስማበለው አይታወቅም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ቤተልሔም አካባቢ የሚንገላወደው ሰሞነኛና አማርኛ ግጥም መግጠምና ቃላት መደርደር፣ መደረት የቻለ ሁሉ ባለቅኔ ይሆን ነበር፡፡ ለመሆኑ ነጻ ወይንም ውርስ ትርጉም ማለት ምን ማለት ነው? በእኔ ትሑት አረዳድ ነጻ ወይንም ውርስ ትርጉም የሚባለው በአንድ የውጭ አገር ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክና የአኗኗር ዘይቤ ላይ ተመሥርቶ የተሠራን የጥበብ ሥራ ወደ አገርኛ ቋንቋ ሲመለስ/ሲተረጐም/የአገራዊ ባህልን፣ አኗኗርን፣ ታሪክንና፣ ለዛን እንዲመስል ተደርጐ መተርጐም ይመስለኛል። ይኸውም አገሬውን እንዲመስል፣ የራሳችን መስሎ እንዲሰማንና እንዲገባን ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ነገር ግን ቅኔ የራሳችን ሀብትና ትውፊት እንደመሆኑ ይትበሃሉን ጠብቀን ሰም፣ ወርቅ፣ ምሥጢር ብለን መፍታት ሲገባን ውርስ ትርጉም እንጠቀም ዘንድ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ኤፍሬምም ቢሆን የውጭ አገር ዜጋ አይመስለኝም፡፡
በእርግጥ ለቅኔና ለሊቃውንቱ አክብሮትና ፍቅር ሰጥቶ፣ ይህንን ሥራ በድፍረትም ቢሆን መሞከሩ ያስመሰግነዋል፡፡ ቢሆንም እርሱ ያለው ስሜቱ እንጂ ዕውቀቱ ስላልሆነ ቅኔን ደፍሮ ይኸ ሰሙ፣ ይኸ ወርቁ፣ እያለ ባለመተንተኑ አልፈርድበትም፡፡ በእኔ አስተያየት የመጽሐፉ ትልቁ ጉድለት የሚመስለኝ የታላቁን ፈላስፋ የተዋነይን ስም ይዞ፣ ስለተዋነይ የሕይወት ታሪክና ሥራ በጥቂቱም ቢሆን አለማተቱ ነው፡፡ ብዙ ሰው ከቀደምት የኢትዮጵያ ነገሥታት የሚለውን ርእስ ሲመለከት የበርካታ ነገሥታት ቅኔዎች የተካተቱበት ሊመስለው ይችላል፡፡
ግን በመጽሐፉ ውጥ የምናገኘው ባለቅኔ ንጉሥ እስክንድር ብቻ ነው፡፡ ይኸውም ያው የተለመደው ከተዋነይ ጋር ገጥሞ የዘረፈው ሥላሴ ቅኔ ነው። ይልቅስ እውነቱ በተዋነይና በነገሥታት ስም ገበያ ፍለጋ ነው፡፡ ሥራው መክሊት እንጂ እውቀት ፍለጋ አይመስልም፡፡
በብሉይ የግዕዝ ቅኔያት ፍልስፍና ውስጥ የትላንቶቹ እነ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ አድማሱ ጀንበሬ፣ አራት ዓይና ጐሹና ሌሎች ተጠቅሰዋል፡፡ እና እነዚህ ሊቃውንት ለአቶ ኤፍሬም የብሉይ ዘመን ሰዎች መሆናቸው ነው? አቶ ኤፍሬም የብሉይ ዘመንን ቀመር ማስቀመጥ ነበረበት፡፡ ከዚህ እስከዚህ የብሉይ፣ ከዚህ እስከዚህ የአዲሱ ዘመን ቅኔ ነው ብሎ፡፡ በአቶ ኤፍሬም ሥዩም ሥራ ላይ በእጅጉ ያሳፈረኝ ደግሞ የአቶ በላይ መኮንን ምሥክርነት ነው፡፡ አቶ የምለው “ሊቀ ህሩያን” የተሰኘውን ማዕረግ የትኛው ሕጋዊ አካል እንደሰጠው ስለማላውቅ ነው፡፡ ለእኔ ራስን ከፍ አድርጐ ከማየት የመነጨ ሲመተ ርእስ ይመስለኛል፡፡
አቶ በላይ “ቅድመ መቅድም” በሚለው የመጽሐፉ ክፍል፣ ኤፍሬምን የጠቀመ መስሎት፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኛቸውን ዲግሪዎች ጨምሮ ስለራሱ ማንነት ነግሮናል፡፡ ኤፍሬም “የቅድመ መቅድም” ቦታ ሰጥቶት የመሠከረለት ይመስላል፡፡ ቅድመ መቅድም ደግሞ ሌላ መቅድም ሲኖር ነው የሚፃፈው፡፡ የኤፍሬም ግን “መግቢያ” ነው የሚለው፡፡
አቶ በላይ ለራሱ ያህል ቅኔ ቢዶገዱግ እንጂ ለሰው የሚተርፍ ዕውቀት ያለው አይመስለኝም። አቶ በላይ እውነተኛው ቅኔ አዋቂ ቢሆን ኖሮ፣ ቅኔ በወረቀት ላይ እንደ ግጥም እየጻፈ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ አያነብም ነበር፡፡ ቅኔ በቃል ይዘረፋል እንጂ ተጽፎ አይነበብም፤ ነውር ነው፡፡ ይህንን ምን ዓይነት የቅኔ መምህር እንዳስተማረው አላውቅም። አቶ በላይ አቶ ኤፍሬምን “ይበል የተባለለት ባለ ቅኔ ነው” (ተዋነይ ገጽ 2) እያለ ያዳነ መስሎ ከሚገድለው፣ ስሕተቱን አርሞና በበለጠ አውቆ እንዳይገኝ ከሚያደርገው፣ ቀድሞ ነገር ራሱ ወደ ቅኔ ቤት ሄዶ ቅኔውን ቢያለዝብና ቢቀጽል ይሻላል፡፡ ያኔ እግረ መንገዱን ኤፍሬምንም መቋሚያ አስይዞ ቢያስከትለው አይከፋም፡፡ ወደ ዋሸራ ከመጣም እንቀበለዋለን፡፡
ከንቱ ሙገሳ ሰውን አያሳድገውም፡፡ አንድ ጋትም ወደፊት አያራምደውም፡፡ አቶ በላይ በቅኔው ዘርፍ የበቃሁ ነኝ ካለ ትውልዱን ማስተማር፣ መንገድ ለጠፋው መንገድ ማሳየት ይገባል እንጂ “ስማ ምሥክሬ” ብሎ መፎከር የለበትም፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” እንዲሉ፡፡ ድፍረት ደግሞ ግብዝነት ይመስለኛል፡፡ መድፈር የደቦ ሥራ የሆነውን እንደዐባይ ዓይነቱን እንጂ በረቀቀና በመጠቀ የግለሰብ ፈጠራ ላይ የተመሠረተውን የግዕዝ ቅኔን አይደለም፡፡ “ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ጠፋ” እንደሚባለው፣ የኢትዮጵያ የቅኔ ሊቃውንት ሞተው ሳያልቁ በቁማቸው አራሙቻ ማልበስ አይገባም፡፡
ይህ ድርጊት ባለ ቅኔዎችን መናቅና ክብር ማሳጣት ነው፡፡ በቅኔ አዋቂነታቸው የመጠቁና የረቀቁ የቅኔ ፈላስፋዎችን ሥራ ማዋረድ ነው። የቆየውንና ነባሩን የቅኔ ቅርስ ማበላሸት ነው። የባለ ቅኔዎቹ ስምም በአግባቡ አልተጠቀሰም፡፡ ለምሳሌ በገፅ 164 ላይ የተጠቀሰው ጉባዔ ቃና የሊቁ መሪጌታ ስመኝ ሆኖ ሳለ፣ ተርጓሚው በአግባቡ አልጠቀሳቸውም፡፡ በአጠቃላይ የተደነቁት ሊቃውንት ቅኔ ግዕዙንም፣ የቅኔውን ምንነትም በማያውቅ ሰው ሊፈታ አይችልም፡፡ ይህ አንባቢንም ቲፎዞንም ማደናገር ነው። ምክንያቱም የአሁን ዘመን ሥራ የሚሠራው በቲፎዞ ስለሆነ ነው፡፡  መካሪውን፣ መሥካሪውን፣ ተመካሪውንም ያስነቅፋል፡፡
ለማንኛውም አስተያየቴን በጥበቡ አባአጋር መወድስ ቅኔ ላጠቃልለው፡፡
መወድስ
የመስከረም በሬ ዲያቆን ደርሶ የሚያገሳ፣
ሙጃ መክፈልት እስመ ለከርሱ ሰጠጦ፣
ወለድማሁ ዐቢይ ፀዊረ ጋዘና መለጦ፣
መሪር ልሳነዚአሁ እስመ ኮነ ግብጦ፡፡
ወቃለ መምህር ለእመ ሰምአ
ፈሪ ዲያቆን በረዊጽ ያመልጦ፡፡
ለዲያቆን ሂ ፀረ ተማሪ እንተ ያገንብጥ ቂጦ፤
ኤርትራ ቤተልሔም ከመፈርአን ትውህጦ፡፡
እመኒ ነጻረ ዓይነዚአሁ ገልብጦ፡፡
መክፈልት ጋለሞታ ለልበዚአሁ ትመስጦ፡፡


Published in ጥበብ

“ሰው ለማገልገል መፈጠር መታደል ነው”


ራስዎን ያስተዋውቁ …
ስሜ ጌታቸው ተድላ ይባላል፡፡ አሁን የምኖረው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ትምህርቴ በእርሻ ኢኮኖሚክስና በገጠር ልማት

ሲሆን የመጨረሻው ማዕረጌ PHD ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ ብዙ አገሮች ላይ ሰርቻለሁ፡፡ ጡረታ ስወጣ አገሬ ላይ መጥቼ

መፃፍ የጀመርኩ ሲሆን እስካሁን  ወደ ስድስት ያህል መፃህፍትን ጽፌያለሁ፡፡
የመጽሐፍቱን ስም ቢዘረዝሩልኝ?
የመጀመሪያው መጽሀፌ የአባቴ የእርሻ ሥራ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሁለተኛው መጽሐፍ እኔ ሳልጽፈው ክቡር ፀሐፊ ትዕዛዝ

አክሊሉ ሃብተወልድ (በኃይለስላሴ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ናቸው) እስር ቤት ሆነው የፃፉትን ህዝብ ማወቅ

አለበት በሚል በአማርኛም በእንግሊዝኛም ተረጐምኩት። በመጨረሻም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ “የአክሊሉ

ማስታወሻ” በሚል አውጥቶት በርካታ ቅጂዎች ተሸጠዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በራሴ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን “የህይወት

ጉዞዬና ትዝታዎቼ” የሚል መጽሐፍ ፃፍኩኝ። ይህን ከጨረስኩ በኋላ “ተስፋ የተወጠረች ህይወት” የሚል መጽሐፍ

ፃፍኩኝ። በደርግ ጊዜ ስድስት ልጆች ከዘመቻ ጠፍተው ወደ ጅቡቲ ሰባት ቀንና ሰባት ሌሊት የተጓዙበትን ታሪክ

ያሳያል፡፡ በመጨረሻም “ከትዝታ ጓዳ” እና “እንደወጡ የቀሩት ኢትዮጵያዊ” የሚል መጽሐፍ ለመፃፍ በቅቻለሁ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ውስጥ ለረጅም ጊዜ መስራትዎ ይታወቃል፡፡ እስኪ የት የት እንደሰሩ ይንገሩኝ…
ከ20 አመት በላይ በተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ነው የሰራሁት፡፡ በልዩ ልዩ አገሮች ለምሳሌ

በሌሴቶ፣ በታንዛኒያ እና በበርካታ አገሮች ሰርቻለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በአለም የስራ ድርጅት (ILO) ውስጥ ገባሁና

በናይጀሪያ ለአምስት አመት ሰራሁ፡፡ መጨረሻ ላይ በሰላም ማስከበር ሥራ በኢራቅ የሰሜኑ ክፍል (ኩርዶች በሚኖሩበት)

ሁለት አመት፣ ባግዳድ ደግሞ ሁለት አመት በአጠቃላይ ለአራት አመት አገልግያለሁ፡፡ ሳዳም ሁሴን በነበሩበት ዘመን

ማለት ነው።  
ጡረታ ከወጡ በኋላ ከመጽሐፍ ውጭ ምን እየሰሩ ነው?
ከመጽሐፍ ውጭ በአሁኑ ሰዓት በበጐ አድራጊ ድርጅቶች ውስጥ በበጐ ፈቃደኝነት ነው የምሰራው። በዋናነት ሜቄዶንያ

የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል ውስጥ ብዙም ባይሆን የአቅሜን ለማድረግ እየጣርኩኝ እገኛለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በወላጅ አልባ ህፃናት፣ በሴቶች ጥቃት፣ በትምህርትና የሴቶችን አቅም በመገንባት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ

የበጐ አድራጐት ድርጅቶች አሉ። እርስዎ ለምን ሜቄዶንያን መረጡ?
ሜቄዶንያን የመረጥኩበት ዋናው ምክንያት የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል በመሆኑ ነው። ብዙ በጐ አድራጐት

ድርጅቶች የሚሰሩት በህፃናት፣ በጉዲፈቻ እና በመሳሰሉት ላይ ነው። ሜቄዶንያ የሚሰራው ስራ በጣም ቅዱስና የተለየ

ነው፡፡ ይህን ስልሽ የሌላው መጥፎ ነው፤ ጥቅም የለውም ለማለት አይደለም። ሜቄዶንያ በትንሽ ብር ብዙ ስራ

የሚሰራበት፣ በጐ ፈቃደኞች ያለ ክፍያና ያለ ደሞዝ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፣ ሽንትና ሰገራ የማይቆጣጠሩትን ሳይጠየፉ

እያጠቡ እያገላበጡ የሚውሉ የሚያድሩበት ድርጅት ነው፡፡ ይህ በእውነት ልብ የሚነካ በመሆኑ የመረጥኩበት ዋነኛ

ምክንያቴ ነው፡፡ መስራቹ አቶ ቢኒያም በለጠን ውሰጅ… በጣም ወጣት ነው፤ ትልቅ ሰው ነው፤ የሚሰራውም ቅዱስ ስራ

ነው፡፡ ይህን የማይሞከር ስራ ሞክሮ ለዚህ የበቃ ፅኑ ልጅ ነው፤ ይህንን ልጅ ደግሞ ማገዝ አለብኝ በሚል ነው

የመረጥኩት፡፡
እንግዲህ በጐ ፈቃደኛ ሲኮን የግድ ገንዘብ ያለው መሆን አያስፈልግም፡፡ የሜቄዶንያ መስራች  የአቶ ቢኒያም መርህ

“ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው” የሚል ነው፡፡ እርስዎ በየትኛው ዘርፍ ነው እርዳታ የሚያደርጉት?   
እኔ እንግዲህ በተለያዩ ዘርፎች ነው የማገለግለው። በቻልኩት ሁሉ፡፡ ለምሳሌ በአስተዳደሩ በኩል እሰራለሁ። ከእኔ

መሰሎች ጋር ስድስት ሆነን “የአማካሪ ግሩፕ” በሚል ቡድን አቋቁመን የማማከር ስራ እንሰራለን። በገንዘብም በኩል

ቢሆን እውነት ለመናገር ያቅማችንን እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ ታህሳስ 13 ቀን 2006 ዓ.ም በተደረገው የግሎባል ሆቴል

የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ ለማሳተም 64ሺህ ብር ያወጣሁበትን “ከትዝታ ጓዳ” እና “እንደወጡ የቀሩት

ኢትዮጵያውያን” የተሰኙ ሁለት መፃህፍቶቼን 900 ያህል ቅጂዎች ለሽያጭ አቅርቤ ገቢ እንዲያገኙበት አድርጌያለሁ፡፡
እኔ ሁለቱን መፃህፍት በመቶ ብር እንዲሸጡ ነበር የተመንኩት፡፡ ነገር ግን እነሱ ሁለቱን በ150 ብር እንሸጣለን ብለው

በዚህ ዋጋ ሲሸጡ ነበር፡፡ ዘጠኝ መቶውም ካለቀ ወደ 135ሺህ ብር ገደማ ያገኙበታል ማለት ነው፡፡ ይህቺ የእኔ ትንሿ

አስተዋፅኦ ናት፡፡
በሜቄዶንያ ከሚገኙ 300 ያህል አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መካከል አይቼው በጣም ስሜቴን ነክቶታል የሚሏቸው

አሉ?
በአጠቃላይ እዛ ያሉት ሁሉ ልብ ይነካሉ፡፡ ነገር ግን እኔም ሆንኩ ባለቤቴ በጣም ልባችንን የነካው አልጋ ላይ ተኝቶ

የሚገኘው ጌዲዮን የተባለው ወጣት ነው፡፡ 24 ሰዓት እዛው እየተገላበጠ ነው የሚውል የሚያድረው። ሰውነቱ ከወገቡ

በታች ፓራላይዝድ ነው፡፡ (በነገራችን ላይ ጌዲዮን በጣም ወጣት፣ ቀይ፣ እጅግ መልከ መልካም ሲሆን መናገር ባይችልም

መስማት ግን ይችላል፡፡ አጠገቡ ያለች በጣም ወጣት አስታማሚና ተንከባካቢው ብቻ የአፉን እንቅስቃሴ አይታ

ትተረጉማለች፡፡ ከዚህ በፊት የሀብታም ቤተሰብ ልጅ ነበር ተብሏል) ይህ ወጣት በጣም ቆንጆና የሚያሳዝን ነው፡፡
አዲስ አድማስ ላይ የወጡት ኮሎኔል ታሪክም ያሳዝናል፤ ነገር ግን አሁን እርሳቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው የሚገኙት፡፡

ከሁሉም ከሁሉም ግን ማን ልቤን እንደሚነካው ታውቂያለሽ? የአዕምሮ ህሙማኑ አረጋዊያን እላያቸው ላይ ሲፀዳዱ

ተሯሩጠው የሚያፀዱትና ንፁህ የሚያደርጓቸው አስታማሚዎች ልቤን ይነኩታል። እውነቱን ልንገርሽ እኔ አላደርገውም፡፡

በዚህ መጠን ሰውን ለማገልገል መፈጠር መታደል ነው፡፡ እና እነዚህ በጐ ፈቃደኞች ዝም ብዬ ሳስባቸው ፅናታቸው

ልቤን ይነካዋል፡፡ እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡
ከመፃህፍቱ በተጨማሪ አንድ ስዕል ለጨረታ አቅርበው ነበር አይደል…?
አዎ! “የቴዎድሮስ የመጨረሻው የመቅደላ ጉዞ” የተሰኘ ስዕል ነበረኝ፡፡ ያወጣላቸውን ያህል ያውጣላቸው ብዬ

ሰጠኋቸው፡፡ ከ10ሺህ ተነስቶ መቶ ሺህ ብር ተሸጠ፡፡ በጣም የምወደው እና ሳሎኔ ውስጥ ሰቅዬው የነበረ ስዕል ነው፡፡

ቴዎድሮስ በፈረስ ላይ ሆነው ሰው ከቧቸው ሲጓዙ የሚያሳይ በጣም ማራኪ ስዕል ነው፡፡
ባለፈው እሁድ በግሎባል ሆቴል የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አጠቃላይ ድባብ ምን እንደሚመስል

ቢገልፁልኝ…
እውነት ለመናገር … የእሁዱ ፕሮግራም ከጠበቅነው በላይ ነበር፡፡ አንደኛ ከ3500 በላይ ሰው ተገኝቷል። በሁለተኛ ደረጃ

ሁሉም እጁን ዘርግቷል፤ በርካታ ብር ለግሷል፡፡ ለምሳሌ አንድ ስዕል ነበር፡፡ የአንዲት ሴት ስዕል ነው፡፡ ዝም ብሎ ስዕል

ነው፤ አንድ 20ሺህ ብር ቢያወጣልን ብለን ነበር የገመትነው፡፡ ነገር ግን 200ሺህ ብር ተሸጠ። ሌላ ስዕል ደግሞ 50ሺህ

ብር ቢያወጣልን ብለን አስበን 300ሺህ ተሸጠ፡፡ ብቻ ሰው የሜቄዶንያ ስራ ገብቶታል፤ መርዳት አለብን ብሎ አምኗል

ማለት ነው፡፡ ሌላው ስለሜቄዶንያ መታወቅ ያለበት በቀን አንድን ሰው ለመመገብ 20 ብር ያስፈልጋል፤ ለቁርስ፣ ምሳና

እራት ማለት ነው፡፡ አሁን ላሉት 300 ሰዎች በቀን 6ሺህ ብር እናወጣለን፡፡ በወር 180ሺህ ሲሆን በአመት 2 ሚሊዮን

አንድ መቶ ሰማኒያ ሺህ ብር ይወጣል፡፡ ይህ እንግዲህ ለምግብ ብቻ ነው። መድሀኒት፣ ልብስ፣ የንፅህና መጠበቂያ፣ እና

ሌሎችንም ሳይጨምር ነው፡፡ የዛሬ አመት ደግሞ ተረጂዎችን አንድ ሺህ የማድረግ እቅድ አለው፡፡ የሜቄዶንያ ተረጂዎቹ

አንድ ሺህ ሲደርሱ ለምግብ ብቻ ወጭው 20ሺህ ብር በቀን ይሆናል፡፡ በወር 600ሺህ ብር ይመጣል፣ በአመት ደግሞ

ወደ 5.5 ሚሊዮን ይሆናል፡፡ ይሄ ልጅ በእናትና አባቱ ቤት ነው 300ውን እየተንከባከበ ያለው፡፡
ታዲያ ተጨማሪ ቤት ሳይኖር እንዴት አንድ ሺህ ሰዎችን መርዳት ይቻላል?  
ያው መንግስት ሊሰጥ ያሰበውን 20ሺህ ሄክታር መሬት ቶሎ ቢሰጥና እዚያ ትልቅ ቤት ተሰርቶ አረጋዊያን ለብቻ፣

ሴቶችና ወንዶች ለብቻ፣ የአዕምሮ ህሙማን ለብቻ ሆነው፤ ክሊኒካቸዉ እዛው፣ ማረፊያቸውም እንዲሁ ሆኖ የተሻለ ስራ

መስራት ቢቻል ደስ ይለኛል፡፡ ቦታው ይገኝ እንጂ ግንባታው ጊዜ አይወስድም፤ ምክንያቱም ህዝብ ይገነባዋል የሚል

እምነት አለኝ፡፡
በእሁድ ዕለቱ ፕሮግራም በአጠቃላይ ምን ያህል ገቢ አገኛችሁ?
እኔ እስከማውቀው ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ዲኤክስ መኪናም አግኝተናል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ከጨረታውና ከመሰል ነገሮች እንኳን ከ600ሺህ ብር በላይ ነው የተገኘው። ነገር ግን ወጪው ብዙ ነው፡፡ ያውም

ተጠንቅቀው ነው ገንዘቡን የሚያስተዳድሩት፡፡ ይገርምሻል… ሰው ማኮሮኒ ይዞ ይመጣል፣ ዱቄት ይዞ ይመጣል። በረከቱ

ነው መሰለኝ ተረጂዎቹ ጦማቸውን አድረው አያውቁም፡፡ ቢሆንም አሁንም እርዳታዎቹ ተጠናክረው መቀጠል

አለባቸው፡፡
በመጨረሻ ስለሜቄዶንያና ስለ መስራቹ አቶ ቢኒያም ምን የሚሉት ነገር አለ?
ኦ…ህ ስለ ቢኒያም ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እሁድ ዕለት እንኳን ንግግር ሳደርግ ስሜታዊ ሆኜ ነው ያለቀስኩት፡፡
ቢኒያም የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ ለእነዚህ የአገር ባለውለታዎችና የአዕምሮ ህሙማን እግዚአብሔር የላከው ሰው ነው፡፡
በእንዲህ አይነት ጊዜ እንዲህ አይነት የተቀደሰ ስራ ለመስራት መመረጥና መታደል ያስፈልጋል። እኛ በእርሱ ዕድሜ

በነበርንበት ጊዜ ድግሪያችንን ይዘን፣ ፔኤች ዲ ይዘን፣ ንብረት አፍርተን፣ ቤት ትዳር ይዘን እያልን ነበር የምናስበው፡፡

እርሱ ግን  እንዴት ጉድጓድ ውስጥ የወደቁትን አንስቼ ያገግሙ እያለ ነው የሚጨነቀው፡፡ ይሄ በእውነት መታደል ነው።

ይህን ወጣት ማንኛውም ሰው ተሯሩጦ ማገዝ አለበት። አቶ ቢንያም እንዳለው “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ

ነው”፡፡
አመሰግናለሁ።  

Published in ህብረተሰብ

አያታችን የአፄ ምኒልክን፣ አባታችን የአፄ ኃይለስላሴን ዘውድ ሰርተዋል
ወንድሜን ሙያውን ጀርመን አገር ያስተማሩት ንጉሱ ናቸው
የአክሱምና ላሊበላ መስቀሎችን ዲዛይን አሻሽሎ የሰራው አባቴ ነው
ወላጆቻቸው የአንኮበር ተወላጆች ናቸው። አባታቸው ከአንኮበር ጀምሮ በአዲስ አበባ ቤተመንግሥትም የወርቅና ብር

ጌጣጌጦች ባለሙያ ነበሩ፡፡ ከታላቅ ወንድማቸው ጋር በመሆን የአባታቸውን ሙያ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ

የቀሰሙት አቶ ይሔይስ ደጀኔ፤ በጀርመን አገርም ተጨማሪ ዕውቀት ገብይተዋል፡፡ ደምበል ሕንፃ ላይ “ይሔይስ ደጀኔ

የወርቅና ብር ሠሪ” የሚል መደብር ያላቸው አቶ ይሔይስ፤ “አባታችን በሙያው የነበረውን ዕውቀት ዛሬ በ76ተኛ

ዓመቴም አልደረስኩበትም” ይላሉ፡፡ በወርቅና በብር ከሚሰሩ ጌጣ ጌጦች ጋር በተያያዘ የቤተሰባቸውን ታሪክና ተያያዥ

ጉዳዮችን አውግተውናል።
ከትውልድዎና አስተዳደግዎ ይጀምሩልኝ…
በአዲስ አበባ ከተማ ጐላ ሠፈር በ1930 ዓ.ም ነው የተወለድኩት፡፡ በልጅነቴ ያመኝ ስለነበር፤ ከጐንደር የመጡ መምሬ

ቅሩብ የሚባሉ ቄስ ተቀጥረውልኝ ቤት ውስጥ ነበር ትምህርቴን የተከታተልኩት፡፡ ሌሎችም የጐላ ሠፈር ልጆች እየመጡ

እንማርበት የነበረው ቤት የእናቴ ወንድም ነበር፡፡ የቤተመንግሥት ካባ ሰፊና ሙካሽ ጠላፊ ባለሙያ የነበሩት አጐቴ፤

አቶ አድማሱ ኃይለማርያም ይባላሉ፡፡ የቄስ ትምህርቴን ፊደል ከመቁጠር ጀምሬ፣ ዳዊት በመድገም፣ በወንጌል ንባብ

ካዳበርኩ በኋላ፤ በመርካቶው ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን እንድቀድስ ተጠይቄ ነበረ፡፡ እኔ ግን ዘመናዊ ትምህርት

የመማር ፍላጐት ስለነበረኝ፣ በ1944 ዓ.ም ኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡
የትምህርት ቤታችን ርዕሰ መምህር ካርል ማይክል የሚባሉ አሜሪካዊ ነበሩ፡፡ 12ተኛ ክፍልን ካጠናቀቅኩ በኋላ

ለተጨማሪ ትምህርት ወደ ጀርመን አገር እንድሄድ ነገሮችን ያመቻቸልኝ ታላቅ ወንድሜ አቶ ክበርዬ ደጀኔ ነበር፡፡
ይህንን ያደረገበት ምክንያት ደግሞ፤ ቤተሰባችን ለተሰማራበት የአንጥረኝነት ሙያ እኔ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳለኝ

በማስተዋሉ ነው፡፡ ታላቅ ወንድሜም ጀርመን አገር ድረስ ሄዶ ሙያውን ተምሮ ስለነበር፣ እኔም ወደዚያ እንድሄድ

ያመቻቸልኝ፤ በጀርመን አገር የሚያውቃቸውን ሰዎች በማነጋገር ነበር፡፡
እስቲ ወደኋላ መለስ ብለው የእናንተ ቤተሰብ ከአንጥረኝነት ሙያ ጋር በተያያዘ ያለው ታሪክ ምን እንደሚመስል

ይንገሩኝ…
የአባቴ አባት አቶ በላይነህ ዓለምነህ እና የእናቴ አባት አቶ ደገፉ ጋሼ፤ በአንኮበር ቤተመንግሥት በአንጥረኝነት ሙያ

ይሰሩ ነበር፡፡ በዚያ ወቅት መስቀልና የቤተክህነት ዕቃዎችን ሠርተዋል፡፡ አፄ ምኒልክ ሲነግሱ የተጠቀሙበትን ዘውድ

አርመናዊው ዲክራን አቢያን ሲሰራ፣ አያቴና ወንድሙ በሥራው ላይ ተሳትፈዋል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ሲነግሱ

የተገለገሉበትን ዘውድ በመስራትም አባቴ ሙያዊ ዕውቀቱን አዋጥቷል፡፡ ከዚያም በኋላ ብዙ ነገር ሠርቷል፡፡
ጥንታዊውን የአክሱምና የላሊበላ መስቀሎችን ዲዛይን አሻሽሎ የሰራው አባቴ ነው፡፡ አሁን በአራት ኪሎ ቤተመንግሥት

አጥር ላይ የሚታየውና የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ሥም ምህፃረ ቃል በድርብ ዲዛይን የቀረፀውም እሱ ነው፡፡ የጃንሆይ

የክብር አልባሳት ቁልፎችንም ሠርቷል፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ የልብስ ቁልፍ በመጀመሪያ ተሰርቶ የመጣው ከእንግሊዝ

ነበር፡፡ ንጉሡ ከለንደን የመጣውን ዲዛይን ስላልወደዱት አባቴ አሻሽሎ እንዲሰራላቸው ጠይቀውት፣ የልብስ

ቁልፎቻቸውን በ21 ካራት ወርቅ ሠርቶላቸዋል፡፡
የንጉሡ የልብስ ቁልፎች ላይ ምን ዲዛይን ነበረ?
የአፄ ኃይለሥላሴ ልብስ የወርቅ ቁልፎች በተለያየ ዲዛይን ነበር የተሰራው፡፡ መሐሉ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ አርማ ያለበት

አለ፡፡ ግራና ቀኝ የተጠላለፉ ሻምላዎችን አርማ የያዙም ቁልፎች ነበሩ፡፡ በክብ ቅርጽ የተሰሩት የልብስ ቁልፎች

በዙሪያቸው የዘንባባ ዲዛይን የተሰራላቸው ሲሆን ጫፋቸው ላይ ደግሞ የዘውድ አርማ አላቸው፡፡
አባትዎ በየትኛው ቤተመንግሥት ውስጥ ነበር እነዚህን ሥራዎች የሚሠሩት?
ከቤተመንግሥት ቅጥር ሠራተኞች አንዱ ሆኖ በአንጥረኝነት ሙያ ያገለገለው፤ በጃንሆይ ልዩ ግምጃ ቤት ውስጥ ነበር፡፡

ግምጃ ቤቱ በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የሚተዳደር ሲሆን፤ ቦታውም አሁን 6 ኪሎ ዩኒቨርስቲ በሆነው ገነተ ልዑል

ቤተመንግሥት ውስጥ፤ ከማርቆስ ቤተክርስቲያን በስተጀርባ ነበር። ከአባቴ ጋር የሚሰሩ በጅሮንድ ማንደፍሮ የሚባሉ

ሌላ ኢትዮጵያዊም ነበሩ፡፡
በሙያው ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ሰዎችስ አልነበሩም?
የአንጥረኝነት ሙያ በአገራችን በሁለት መንገድ ተስፋፍቶ ነው ለዛሬ የደረሰው፡፡ አንደኛው፤ ከጥንት አክሱማዊያን አንስቶ

ትውልዶች እየተቀባበሉ እዚህ ያደረሱት ሲሆን፤ ሁለተኛው ከአፄ ምኒልክ ጊዜ አንስቶ ልዩ ልዩ ዕውቀት ያላቸው የተለያዩ

አገራት ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ሲደረግ ከገቡት መሐል አርመኖችም ስለነበሩበት፣ እነሱ በአገራችን

የአንጥረኝነት ሙያ እንዲያድግና እንዲስፋፋ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
አባታችን በንጉሠ ነገሥቱ ግምጃ ቤት በሚሰሩበት ዘመን፣ ፒያሳ ላይ የወርቅና ብር መስሪያና መሸጫ ያለው ሳቫጂያን

የሚባል አርመናዊ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የንጉሡ ግምጃ ቤት “ብር መኪና ቤት”ም ተብሎ ይጠራ ነበር። አባታችን

እንደነገረን፣ በ”ብር መኪና ቤት” ገንዘብ የማተም ሥራ፣ የወርቅና ብር ሥራ ብቻ ሳይሆን ከረሜላ ሁሉ ይመረትበት

ነበር፡፡
አባትዎ የሰሯቸው ሌሎች ሥራዎች ካሉ ቢነግሩኝ…
ለአፄ ኃይለሥላሴና ለቤተመንግሥት ብዙ ነገር ሠርቷል፡፡ የጃንሆይን የልብስ ቁልፎች ከአባቴ ውጭ ማንም

አልሰማራም፡፡ የሲጃራ መያዣ ሣጥን፣ የሴት ቦርሳ ጌጦች፣ የተለያዩ አገራት እንግዶች ሲመጡ፤ ጃንሆይ በሽልማትነት

የሚሰጧቸው ኒሻንና ሜዳሊያዎች፣ የወታደራዊ የማዕረግ ምልክቶች፣ የሸሚዝ እጅጌ ማስያዣ ቁልፎች (ከፊሊንግ)፣ የአበባ

ማስቀመጫዎችና የተለያዩ የሳሎን ጌጣጌጦች፤ በወርቅ፣ በብር፣ በዝሆን ጥርስና በአልማዝ ጭምር ሠርቷል፡፡
አርመናዊው ሳቫጂያንም ለቤተ መንግሥት ብዙ ነገሮችን ሠርቷል፡፡ ማህተም ይቀርጽ ነበር። ለወታደራዊ አገልግሎት

የሚውሉ ጌጣ ጌጦች፣ የማዕረግ ምልክቶችና የልብስ ቁልፎችን ይሰራ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጥይት ፋብሪካም

በተመሳሳይ መልኩ በብዙ ሥራዎች ላይ ተሳትፏል፡፡
ከአፄ ኃይለሥላሴ ውጭ የልብስ ቁልፎችን በወርቅ ያሰራ ሌላ ማን አለ?
አንደኛ ሥራው በሚስጢር ነው የሚሰራው፡፡ ሁለተኛ የዲዛይን ሥራው የዳበረ ዕውቀትና ልምድ ስለሚጠይቅ፤ አሰራሩም

ጊዜ ስለሚወስድ ብዙ ሰው የልብስ ቁልፎችን ከወርቅ ሊያሰራ አይችልም። የማሰሪያ ዋጋውም ቢሆን ውድ ነው፡፡ ልዑል

ራስ አስራተ ካሳ ግን ከወርቅ የተሰራ የልብስ ቁልፎች ነበሯቸው፡፡
ታላቅ ወንድምዎ የወርቅና ብር ሥራን ለመማር ወደ ጀርመን መሄዳቸውን ገልፀውልኛል፡፡ እስቲ ስለ ወንድምዎ

ይንገሩኝ…
አቶ ክብርዬ ደጀኔ ታላቅ ወንድሜ ነው፡፡ አያታችን በአፄ ምኒልክ ዘውድ፣ አባታችን በአፄ ኃይለሥላሴ ዘውድ ሥራ ላይ

እንደመሳተፋቸው ሁሉ፤ አቶ ክብርዬም የሥላሴ ካቴድራልና የአክሱም ጽዮን ቤተክርስቲያናትን መንበር በብርና በወርቅ

በመሥራት ባለታሪክ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ አባታችን ወደሚሰራበት ቤተመንግሥት እየሄደ በመለማመድ ነበር ሙያውን

ያዳበረው፡፡ በየዓመቱ ለገና በዓል የአበባ ማስቀመጫ ከብር እየሰራ ለንጉሠ ነገሥቱ ያበረክትላቸው ነበር፡፡ ይህንን

ፍላጎቱን ያዩት አፄ ኃይለሥላሴ፤ ሙሉ ወጪውን ችለው ጀርመን አገር ሄዶ ሙያውን እንዲማር ረዱት፡፡ ከጀርመን

ሲመለስ ፒያሳ ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት በታች፣ ሱቅ ከፍቶ በወርቅና ብር ሥራ ላይ ተሰማራ፡፡
እርስዎስ ለትምህርት ጀርመን የሄዱት እንዴት ነበር?
ታላቅ ወንድሜ ጀርመን በሄደበት ወቅት፣ ትምህርት በማይኖረኝ ጊዜ፤ ቤተመንግሥት እየሄድኩ አባታችንን በሥራ እረዳ

ነበር፡፡ ወንድሜ የፒያሳውን ሱቅ በ1954 ዓ.ም. ከከፈተም በኋላ በተመሳሳይ መልኩ በሥራው ላይ እሳተፍ ስለነበር፣

ለሙያው ያለኝን ፍቅርና ችሎታ ያየው ወንድሜ፤ ጀርመን ሄጄ እንድማር ሁኔታዎችን አመቻችቶ ሲልከኝ፣ የትራንስፖርት

ወጪዬን የሸፈኑልኝ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ነበሩ፡፡
አባታችሁ በሙያቸው እያገለገሉ በቤተመንግሥት ሠራተኛነት የቆዩት ለምን ያህል ጊዜ ነው?
ጃንሆይ የጡረታ ዕድሜውን እያራዘሙለት ብዙ ቆይቷል፡፡ ንጉሡ ወርደው ደርግ የመንግሥት ስልጣን ሲይዝ፤ ኮሎኔል

መንግሥቱ ኃይለማርያም “እናውቃለን፤ ብዙ አገልግለዋል፤ ምንም የተሻለ ነገር ስላላገኙ ባለዎት ደሞዝ ጡረታ

እንዲወጡ ፈቅጃለሁ” ብሎት የቤተ መንግሥት ሠራተኛነት ሲያበቃ፤ ፒያሳ ወንድሜ በከፈተው ሱቅ ለብዙ ጊዜ

ሠርቷል፡፡ አሁን አባቴም ወንድሜም በሕይወት የሉም፡፡ እኔ ሙያውን ያስተማርኩት ታናሽ ወንድሜ ተመስገን ደጀኔ፤

በፒያሳ ወርቅ ቤት እየሰራ ነው፡፡ በውጭ አገር የሚኖሩ ወንድምና እህትም አሉን፡፡
እስቲ ስለ ጀርመን ትምህርትዎ ያጫውቱኝ…
የገባሁበት ትምህርት ቤት 26 ሠራተኞችና 150 ተማሪዎች ነበሩበት፡፡ 149ኙ ተማሪዎች ጀርመናዊያን ነበሩ፡፡ መጀመሪያ

ላይ ቋንቋቸው ቢያስቸግረኝም 6 ዓመት የሚፈጀውን ስልጠና በ3 ዓመት አጠናቅቄ ነው ዲፕሎማዬን ይዤ የመጣሁት፡፡

በብርና ወርቅ ሥራ ዲዛይን በማውጣትም ሆነ ያንን በትክክል ወደ ተግባር በመለወጥ ከልጅነቴ ጀምሮ የዳበረ ዕውቀት

ስለነበረኝ፤ ትምህርቱን በቶሎ ለማጠናቀቅ አስችሎኛል፡፡ ትምህርቱ የሙያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ታሪክና ጠቅላላ

ዕውቀትንም ያካተተ ነበር፡፡ በዚህም በኩል ቢሆን አጥጋቢ ውጤት ነበር ያመጣሁት፡፡ በአገር ውስጥ ተማሪ እያለሁ

በሒሳብ ትምህርት ጎበዝ ነበርኩ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ብዙ ነገር ባናውቅም የዓለምን ታሪክ በስፋት ነበር የምንማረው፡፡

ይሄ የጀርመኑን ትምህርት ቀላል አድርጐልኛል፡፡
ከጀርመን ከመጡ በኋላ ሥራ የት ጀመሩ?  
ወንድሜ አቶ ክብርዬ፤ ከፒያሳውም በተጨማሪ በጊዮንና በሒልተን ሆቴሎች ተጨማሪ ሱቆችን ከፍቶ ስለነበር፣

ከጀርመን እንደመጣሁ ሥራ የጀመርኩት እሱ ጋር ነበር፡፡ በወቅቱ አባታችንም በቤተመንግሥት ይሰራ ስለነበር፣ ሦስታችን

በመተባበር ብዙ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ የአፄ ኃይለሥላሴ 80ኛ ዓመት የልደት በዓል ሲከበር ምድር ጦር፣ ፖሊስ

ሠራዊት፣ ፓርላማ፣ የሐረር ሕዝብ፣ የባሌ ሕዝብ … ትዕዛዝ እየሰጡን ልዩ ልዩ የስጦታ ዕቃዎችን፤ ከወርቅ ከብር፣

ከአልማዝ፣ ከከርከሮ ጥርስ … ሠርተናል። በዲዛይን ሥራዎቹ ላይ ሎሬት አፈወርቅ ተክሌም የተሳተፉባቸው ነበሩ።
እራስዎን ችለው መሥራት የጀመሩት መቼ ነው?
በ1968 ዓ.ም ጥቁር አንበሳ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት “ይሔይስ ደጀኔ ወርቅና ብር ሠሪ” የሚል መደብር ከፈትኩ፡፡
ከዚያ በኋላ ለአገር ውስጥና ለውጭ ብዙ ታላላቅ ሰዎች በርካታ ጌጣጌጦችን ሠርቻለሁ፡፡ አልችልም ብዬ የምመልሰው

ሥራ የለም፡፡ እንዲህም ሆኖ በሙያው ላይ አባታችን የነበረውን ዕውቀት አሁን በ76ኛ ዓመቴም አልደረስኩበትም

እላለሁ፡፡
ለእኛ ዕውቀት መሠረት አባታችን እንደሆነው ሁሉ፣ እኔም ሙያውን ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን በማስተማሬ ደስተኛ ነኝ፡፡

የወንድሜና የእኔም ልጆች የቤተሰባችንን ሙያ ማስቀጠል የሚያስችል ዕውቀት አላቸው፤ ሥራውንም በደንብ እየሰሩት

ነው፡፡
በመጨረሻ በአገራችን የወርቅና ብር ሥራ ያለበትን ደረጃ ቢነግሩኝ…
በወርቅና ብር ሥራ የላቀ ችሎታ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በየቦታው አሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሉ የሚባሉት የከበሩ

ማዕድናትም ብዙዎቹ በአገራችን ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ለመፈለግና ለመስራት ግን አንተጋም። የመስራት ስንፍና አለብን፡፡

ድሆች ተብለን የምንጠራው ለዚህ ነው፡፡ መንግሥትና ሕዝብ ከተባበሩ ይህ ችግር ይቀረፋል ብዬ አምናለሁ። ተባብረንና

ተከባብረን እንስራ የሚል መልዕክት ባስተላልፍ ደስ ይለኛል፡፡   

Published in ህብረተሰብ
Saturday, 28 December 2013 11:53

የአውራምባ የጉዞ ማስታወሻ

ወደ አውራምባ የተጓዝነው በጠዋት ነው፡፡
ወረታን አልፈን ወደሰሜን ጐንደር የሚሄደውን መንገድ ትተን ወደ ቀኝ ወደ ደቡብ ጐንደር ኮረኮንቹን ይዘን ታጠፍን፡፡

ከወረታ ወደ አሥር ኪሎ ሜትር ገደማ ነው አውራምባ፡፡ ፊትለፊት ካለው ዛፍ ሥር የሚፈትሉ አባወራና ሴቶች እያየን

ነው ወደ አውራምባ ስዕላዊ መግለጫ/እግዚቢሽን ክፍል የገባነው፡፡ አንድ አስረጅ ለፈረንጆች ገለፃ ያደርጋል፡፡ እኔን

የምታስጐበኝ አንዲት ጠይም መልከ - መልካም፣ ንግግሯ ትንታግ የሆነች ልጅ ናት! ጥሩ ሰው ነው ስሟ፡፡
“ከንባቡ ጀምር” አለችኝ ወደተለጠፈው ጽሑፍ እያሳየችኝ፡፡
“ማንበብ ባልችልስ?” አልኳት፡፡
“እሱን ለእኛ ብትተውልን ይሻላል” ብላ ከት ብላ ሳቀች። ከአዲሳባ የመጣ ሰው ሁሉ ማንበብና መፃፍ ይችላል፤ የሚል

እሳቤ እንዳላት ገባኝ፡፡ ለፈረንጆቹ ገለፃ በእንግሊዝኛ የሚሰጠው ልጅ ይሰማኛል፡፡ “በዚያን ጊዜ የደርግ ጦርነት ነበር፡፡

ያካባቢው ህዝብና መንግሥት በደግ ዐይን አያየንም ነበር፡፡ ህዝቡ ለደርግ “ኢህአዴግ ናቸው” ብሎ ነገረ፡፡ ደርግ

ባህላችንን አጠፋ፡፡ አጠፋን፡፡ ማህበረተሰቡ ወደ ደቡብ መሰደድ ነበረበት፡፡ ከ5 ዓመት በኋላ ያ መንግሥት በኢህአዴግ

ሲተካ ተመልሰን መጣን - ሰላም ሆነ” አለ፡፡
እኔ ጽሑፌን ማንበብ ቀጠልኩ፣
“ሶስት ዓይነት ሰዎች አሉ፡፡ ታላቅ ሰው የሚያውቅም የሚጠይቅም ሰው ነው፡፡
ከዚያ መካከለኛ የሚባለው ሰው የማያውቅ ግን የሚጠይቅ ሰው ነው፡፡ ትንሽ ሰው የማያውቅም፣ የማይጠቅም ነው፡፡”
አለፍ አለፍ ብዬ ብዙ ጥቅሶች እያነበብኩ አለፍኩ፡፡ የመጀመሪያዎቹ በእንግሊዝኛ ናቸው፡፡ ሌሎቹ በአማርኛ ናቸው፡፡
“ሁለት መጥፎ ነገሮች” ይላል አንዱ ጥቅስ “መጥፎ ምግባርና መጥፎ ንግግር!”
“ከህብረተሰብ የተነጠሉ ሰዎች፤ ከባህር የወጣ አሳ ናቸው፡፡ አስጐብኝዬ ጥሩ ሰው ወደ አቶ ኑሩ እየጠቆመችኝ፤
“የአውራ አምባ የህብረት ሥራ ማህበር ሊቀ መንበር ነው፡፡ የዚሁ የአውራ አምባ ማህበረሰብ ልጅ ነው” አለች፡፡
የእየሩሣሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ተወካይ አብሮኝ ወደ አውራምባ መጥቷል፡፡ እሱ ብዙ ጊዜ ስለሚመላለስ ጥሩ

ሰውን ያውቃታል፡፡ ሞቅ ያለ ሰላምታ ተለዋወጡ፡፡ “የተለያዩ የህ/ሥ/ማኅበራት አሉ፡፡ የእኛ ማህበር አንዱ ነው” አለኝ፡፡

ገጠር ላይ ስላሉ ወደ ከተማም እየሄዱ ይሠራሉ…” አለና በሉ ከአቶ ኑሩ ጋር ቀጥሉ ብሎ የጄክዶው ተወካይ፤ ዞር ዞር

ሊል እኛን ትቶን ሄደ፡፡
“እስቲ ስለራስህ፣ ስለማዕረግህ፣ ምን ስትሰሩ ኖሯችሁ? ቀለል አርገህ እንደሰው፣ እንደሚገባኝ አርገህ ነገረኝ” አልኩት፡፡

ኑሩ ከት ብሎ ሳቀ፡፡ ዘለግ ያለ፣ ረጋ ብሎ የሚናገር እንደዕውነቱ ከሆነ የማይከብድ ልጅ ነው፡፡ ወደ 30-35 ሳይጠጋ

አይቀርም ዕድሜው፡፡ እንደሰማሁት የዙምራ (ማለትም የአውራምባ ማህበረሰብ መሪ) የወደፊት ወራሽ ነው፡፡
“ሰውና ሰው ሆነን እናውራ ማለቴ ነው፡፡ ደረቅ ሥራ እንዳናገረው… ብትፈልግ ስለራስህ፣ ብትፈልግ ስለሥራህ፣

የፈለከውን ንገረኝ፡፡ መጀመሪያ ግን ስምህን አስተዋውቀኝ” አልኩት፡፡
“ኑሩ በላይ እባላለሁ” አለኝ፡፡ “ማህበረሰቡ በሁለት ዓይነት አደረጃጀት የተደራጀ ማህበረሰብ ነው፡፡” አለ። አነጋገሩ

ገርሞኛል፡፡ (ኢህአዴግ አዲስ አበባ ከገባ በኋላ የሚዘወተሩ ዐረፍተ - ነገሮች ዓይነት መስሎ ነው የተሰማኝ)። ቀጠለ:-
“በአንድ በኩል በኮኦፕሬቲቭ የተደራጀ፣ በሌላ በኩል ደሞ ያው በአውራምባ ማህበረሰብ በሚል የተደራጀ ነው።  

“የአውራምባ ማህበረሰብ ግንባታ ህጋዊ ዕውቅና ያለው ማህበር ነው፡፡ በሁለት መልክ የተደረገው፤ ለአስተዳደርም

እንዲመች ነው፡፡ በኮኦፕሬቲቭ ውስጥ ለጊዜው የማህበሩ ሰብሳቢ ነኝ፡፡ እዚያ ላይ ነው የምሠራው…”
“ኮኦፕሬቲቩ እንዴት ተመሠረተ?”
“ማህበረሰቡ ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠረ ማህበረሰብ ነው፡፡ ከ64 ዓ.ም ጀምሮ፡፡ ማህበረሰቡ ለየት ያለ አኗኗር፣ ለየት

ያለ ባህል እንዳለው ብዙ ጊዜ በሚዲያ ተነግሯል፡፡ ለዚህ እንግዳ ትሆናለህ ብዬ አላስብም፡፡ በባህላችን አንተ እያሉ

መጥራት ይቀለናል፡፡ አንተ ልበልህ እ?...”
“ትክክል ነው ቀጥል” አልኩት፡፡
“በአደረጃጀት ባህሉ የእኛ ማህበረሰብ ለሰው ልጅ ትልቁ ሀብቱ ሰው ነው፤ ብሎ ነው እሚያምነው፡፡ ሰው ሳለ በህይወት

መተሳሰብ፡፡ መተጋገዝ፡፡ ሰው በሰውነቱ ሰው ነው ለማንም ሰው ሀብቱ ሰው ነው፡፡ ተፋቅረን መኖር አለብን። ይሄ

ለማንም ነው ሀብቱ ሰው ነው፡፡ ተፋቅረን መኖር አለብን፡፡
“አንተ እዚህ ተወላጅ ነህ ማለት ነው?”
“እዚሁ ተወልጄ ነው ያደግሁት”
“ሰው ነው የሰው ዋና ሀብቱ! ተሳስቦ እንዲኖር ነው ነው ያልከኝ?”
“ያው ዙሮ ዙሮ ቀጣዩ ሀብት ነው፡፡ ሀብት ለማግኘት መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የሥራ ፕላኖችን መንደፍ፣ ማንቀሳቀስ፣

ማገር፣ ይጠይቃል፡፡ ሠርተን በጋራ ነው የምንኖረው፡፡ ትርፍ ክፍፍላችን እኩል ነው፡፡ አንተ ደካማ ነህ፣ እኔ ጉልበት

አለኝ በሚል የተለያየ ክፍያ የለንም፡፡ የሥራ መስኩን ነው መደብ የምንሰጠው፡፡ ሥራ ክፍፍላችን ኃይል አሟጠን

እስከተጠቀምን ድረስ እኩል ሠርተናል፤ ብለን ነው እምናምነው፡፡ ምክንያቱም ጠንካራ ሥራ፤ በደካማ ሰውም ካልተደገፈ

ጠንካራ ሆኖ አይቀጥልም ብቻውን፡፡ ለምሳሌ ዕደ ጥበብ ላይ፣ አልባሳት ሥራ ላይ ብንሠራ፣ እሚሸምነውን ከሥር ከሥር

እሚሠራለት ሰው አለ፡፡ እሚሻም ነው ጠንካራ ጉልበት እሚጠይቅ ከሆነ፣ ያኛው ቀለል ባለ ጉልበት ካልመገበው ጠንካራ

ሥራ ሠርቶ አይውልም፡፡ ስለዚህ ያንና ያን አመጋግበን እኩል ነው የምንሰጣቸው፡፡ እያንዳንዱ የሥራ መስክ በንጽጽር

ብናየው መደጋገፍ የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ መሠረታችን ሥራ ነው - ማምረት፡፡ ትርፍ ክፍፍል ላይ እኩል

እንሰጣለን፡፡ በማህበራዊ ችግሮች ላይ ማህበራዊ መፍትሔ እንሰጣለን፡፡ የአንድ ግለሰብ ችግር ብቻ ሊሆን አይገባም፡፡

ሰው በሰውነቱ ወገን ሁኖ ዋስትና ማጣት የለበትም፡፡ የሰው ልጅ ለሰው ልጅ ዋስትና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ዋስትና ሊያገኝ

ይገባዋል፤ ብለን ነው እምናስበው፡፡ ባህላዊ አኗኗራችን ባጭሩ ይሄን ነው የሚመስለው፡፡ ታሪኩን ታቀዋለህ ብዬ ነው

ያልነገርኩህ…
“ግዴለም አጫውተኝ” አልኩት፡፡
“ይሄንን የመሠረተው ዶክተር ዙምራ ኑሩ፤ ያው በቅርብ አመታት ከጅማ የኒቨርሲቲ የዶክተሬት ማዕረግ የተሰጠው ነው፡፡

አጋጣሚ አዲሳባ ነበረ - ልታገኘው ትችል ነበር፡፡”
“ይህ ፍልስፍና እንዴት መጣ? ህብረተሰባችን ሌላ ዓይነት ያኗኗር ዘይቤ እየተከተለ ይሄኛው ለምን ብቻውን ያለ

ይመስላል?” አልኩት፡፡ “ነገስ ከሌላ ማህበረሰብ ጋር አይጋባም ወይ? ጋብቻ አይፈፃፀምም ወይ? እርስ በርስ አይተሳሰርም

ወይ? ባህሉ አይለወጥም ወይ? አንዱ አንዱ ውስጥ አይፈስስም ወይ? እንደዚህ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን አጫውተኝ”“እ…

ጋብቻ ላይ እኛ normally ግልጽ ነን፡፡ እኛ ከሌላ ማምጣት ችግር የለብንም፡፡ ሌሎችም ከእኛ መውሰድ ችግር

የለባቸውም፡፡ ግን በመሠረታዊ መንገድ ወደተግባር ሲለወጥ ባህላዊ ተጽእኖዎች አሉ፡፡ የብዙዎቹ ወደዚህ ማምጣት ለነሱ

ሊያስቸግር ይችላል፡፡ በተለይ ከፆታ አኳያ የሚደረገው ነገር ማለት ነው፡፡ ከእዚህ ወደዛ ግን በጭራሽ አያስቡትም፡፡

እዚያ ጋ ያለ አይመጣጠንላቸውም፤ አያስቡትም፤ ሴቶቹ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ወደዚያ መሄድ አያስቡም፡፡ ከዚያ ወዲህ

መምጣት ከቻለ ግን ችግር የለውም፡፡ ያ ሲመጣ ደግሞ ባህላዊ አስተሳሰቦቻችን እንዲከበሩ እንፈልጋለን፡፡ ሊያፈርስብን፣

ሊያበላሽብን መሆን የለበትም የሚመጣው። ራሱን አዘጋጅቶ ይሄን ባህል እጠብቃለሁ አስከብራለሁ ብሎ ነው መምጣት

ያለበት፡፡ በዚያ ዝግጁ ሆኖ ከመጣ መቀላቀል ይችላል በጋብቻ፡፡ በተለያየ መልኩ…”
“ግን ከዚህም ነፃ ናቸው፡፡ ሴቶቹ አያስቡትም እንጂ? አሁን ለምሳሌ አንዷ ልጅ አንዱን ወንድ ለማግኘት ብታስብ

መጀመሪያ ወይ በገበያ መገናኘት አለባት፡፡ ወይ በሆነ ዘመድ ወይም ምክንያት መሄድ አለባት እሱ ዕድል እንዴት

ይገኛል?” አልኩት፡፡
“ለምሣሌ ት/ቤት አለ፡፡ አሁን እዚህጋ ካንድ እስከ ስምንት አለ…ከ9-10 አለ…የህዝብ ት/ቤት ነው፡፡
ማንም እሚማርበት፡፡ ቢበዛ የእኛ ልጆች ከመቶ አምስት ፐርሰንት በላይ አይሆኑም፡፡ በዚህ ስሌት ይገናኛሉ፡፡ ሌላው

አብዛኛው ማህበረሰብ እዚህጋ ነው እሚውለው ለማለት ይቻላል፡፡ ወይ ገበያ ላይ፣ ወይ ወፍጮ አገልግሎት ያገኛል፣

የሱቅ አገልግሎት ያገኛል፣ እንዲሁ ባንዳንድ ሰላም በመሳሰሉ ነገሮች እንገናኛለን፡፡ ግንኙነቱ አሁን ሰፊ ነው።  ስለዚህ

በሰፊው የመገናኘቱ ዕድል አለ፡፡ ዙምራ እንዴት እንደጀመረው ሲናገር በአስተሳሰቡ በጣም የተለየ ሰው መሆኑን፤ ነው

የሚያሳየው፡፡ ሩህሩህ ነው በተፈጥሮው፡፡ በሰው ልጅ አንድነት ነው እሚያምነው፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በላይ ወገን ነው፤

ከዚህ በታች ወደባዕድነት እየተቀየር ይመጣል፤ ብለን በተለምዶ የምናስበው አስተሳሰብ፤ ከእሱ ዘንድ ምን ማለት ነው

የሚል ጥያቄ ነው እሚያስነሳው፡፡ የሰው ልጅ በሰውነቱ ወገን አደለም ወይ? ከየት መጥቶ ዘሩ ተቀየረ? ለምሣሌ ይሄንን

ዛፍ እዩት ሥሩን፡፡ ከላይ ግን ቀንዘሉ ሰፊ ነው፡፡ በቀንዘሉ ያፈራል ባዕድ ነወይ? ለሥሩ ቀንዝሉ ባዕድ ነወይ? እንደዚህ

ብሎ ነው እሚያስበው፡፡ እና ፍልስፍናው በጣም የረቀቀ ነው ከዛ አኳያ ማንም ሰው ውስጥ ሊወደዱ እማይገባቸው

ባህሪዎች አሉ፡፡ እነሱን ብቻ ነጥሎ በማስተማር፣ በመለወጥ፣ ሰውን መለወጥ ይቻላል፡፡ ሰው ተማሪ ነው ሰው፡፡

በተፈጥሮው ተማሪ ነው ይማራል፣ ስለዚህ እነዛን ባህሪዎቹን ነጥሎ፤ አይወደዱም፣ ሰላም ይነካሉ የሌላን ሰው መብት

ይነካሉ፣ ለራስም ሥነምግባርን ያጐድፋሉ፣ ለህሊናም እሚያረኩ አይሆኑም…የምንላቸውን በደንብ እስከሚወጡ ድረስ

እነዚህን መለወጥ እስከተቻለ ድረስ… ሁሉንም ባንድ ሚዛን መውሰድ ነው ተገቢ እሚሆነው፡፡ እናቱ፤ አሁን ቅርብ ጊዜ

እኛ ከደረስን ነው ያለፈችው፡(ይቀጥላል)

Published in ባህል

ከአዲስ አበባ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘውና በሀይቅ በተከበበችው ቢሾፍቱ ከተማ፣ በቢሾፍቱ ሃይቅ ዳርቻ ይገኛል - “አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት”፡፡ ሪዞርቱ የተገነባበት ቦታ ቀድሞ የከተማው ጠቅላላ ቆሻሻ መድፊያ ነበረ። በዚህም የተነሳ “አመድ ሰፈር” እየተባለ ይጠራ እንደነበር ይነገራል፡፡ ዛሬ ግን ቦታው ለአይን ማራኪ በሆነው “አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት” ተተክቷል፡፡ እንደ ሪዞርቱ ባለቤት አቶ ሳህሉ ሃይሉ ገለፃ፤ ይህን ቦታ አፅድቶ እዚህ ለማድረስ 815 መኪና ቆሻሻ ማንሳት ነበረባቸው፡፡ ለዚህም የወጣው ወጪ ሌላ ግንባታ ይሰራ ነበር ብለዋል፡፡ “እውነት ለመናገር ቦታው የቆሻሻ መጣያ መሆኑን ባውቅ ኖሮ አልረከብም ነበር” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ አሁን ያ ሁሉ ድካም አልፎ ለዚህ መድረሱ እንደሚያስደስታቸው ይናገራሉ፡፡
“አሻም አፍሪካ ሆቴልና ሪዞርት” በቢሾፍቱ ሀይቅ ዙሪያ ከተገነቡት አምሳያዎቹ በብዙ ነገሮች ይለያል። ለምሳሌ ኤርትራን ጨምሮ በ32 የአፍሪካ አገሮች የተሰየሙ የመኝታ ክፍሎች አሉት፡፡ በየአገራቱ ስም የተሰየሙት የመኝታ ክፍሎች የየአገራቱን ገፅታ የሚያንፀባርቁ ስዕሎች የተሰቀሉበት ሲሆን እስካሁንም 16ቱ የአፍሪካ አገራት በየመኝታ ክፍሎቹ የአገራቸውን መገለጫ ስዕል አስቀምጠዋል፡፡ ሌሎቹ 16ቱ አገራት ስማቸው ተፅፎ ያለቀ ሲሆን ቀስ በቀስም ስዕሎቻቸውን እንደሚያስገቡ ተገልጿል፡፡
40 ሚሊዮን ብር ገደማ እንደወጣበት የተነገረው ሆቴልና ሪዞርቱ፤ የመኝታ ክፍሎቹን በአፍሪካ አገራት ስም ለምን መሰየም እንዳስፈለገ የተጠየቁት ባለቤቱ፤ ላለፉት 35 አመታት በአለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በሰሩበት ወቅት ከባለቤታቸው ጋር በርካታ የአፍሪካ አገራትን የመጐብኘትና የመኖር እድል እንዳጋጠማቸው ገልፀው፤ በኋላም እነዚህን አገሮች አንድ የሚያደርግ እና የሚያስተናግድ ሪዞርት ለመክፈት መምከራቸውን ይገልፃሉ፡፡
“ከስያሜ ባለፈ አንድ ኬኒያዊ እንግዳ በናይጄሪያ ስም የተሰየመ መኝታ ቤት ሲገባ፣ ስለ ናይጄሪያ የተለያዩ መረጃዎችን ያገኛል” ያሉት የ65 አመቱ አቶ ሳህሉ፤ በየአገራቱ ስም መሰየሙና የየአገሩ ስዕል በየመኝታ ቤቱ መሰቀሉ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ያብራራሉ፡፡ የሆቴልና ሪዞርቱን ስያሜ አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም “አሻም” የሚለው ቃል በሀዲይኛና በኦሮምኛ “እንኳን ደህና መጣችሁ” (Welcome) ማለት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
“አሻም አፍሪካ”ን ለየት ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል ከመታጠቢያ ክፍሎች፣ ከወጥ ቤትና ከሌሎች ክፍሎች የሚወጡ ፍሳሾችን በማጣራትና ሪሳይክል በማድረግ በድጋሚ ጥቅም ላይ ማዋሉ ሲሆን ከዚህም ባሻገር ለባዮ ጋዝነት በማዋል፣ በባዮ ጋዝ ምግብ እንደሚያበስል ለማወቅ ችለናል።
“ሪዞርቱ ሲገነባ አንዳንድ ዛፎችን የቆረጥን ቢሆንም 1ሺህ 500 ያህል ዛፎችን ተክለናል” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ ለአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት መስጠታቸውን ይገልፃሉ፡፡
ሌላው አጃኢብ የሚያሰኘው እና አይንን የሚማርከው ከሆቴሉ የመኝታ ክፍሎች መካከል ለየት ባለ ሁኔታ የተገነቡ ክፍሎች መኖራቸው ነው። የውሀ ማሸጊያ ፕላስቲኮችን እንደ ብሎኬት እኩል በመደርደርና በሲሚንቶ በማያያዝ የተገነቡት የመኝታ ክፍሎች ውበት ግርምትን ይፈጥራል። “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ … ወዲህ ውበት ወዲህ ደግሞ አካባቢን መጠበቅ ድንቅ ነው፡፡ ሪዞርቱ የተገነባው በቢሾፍቱ ሀይቅ ዳርቻ ገደላማ ቦታ ላይ ነው፡፡  
አለታማውን ዳገት በረሃ ላይ የሚበቅሉ እና ስራቸው እምብዛም ወደ ውስጥ የማይዘልቅ የተለያዩ አበቦችን በመትከል፣ ግቢው ሙሉ በሙሉ አረንጓዴ እንዲለብስና ማራኪ እንዲሆን ተደርጓል። በአጠቃላይ ከአካባቢና ከተፈጥሮ ጋር ህብር የፈጠረ ሆቴልና ሪዞርት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ትልቅ ሬስቶራንት፣ 300 ሰው ማስተናገድ የሚችል የስብሰባ አዳራሽና ባሮችን ያካተተው አሻም አፍሪካ፤ ከ29 የአፍሪካ አገራት በተሰባሰቡ ስዕሎች የተሞላ ማራኪ አርት ጋለሪ ያካተተም ነው፡፡ ከመኪና ወርደው ገና ወደ እንግዳ መቀበያው ሲገቡ፣ እጅግ በርካታ የአፍሪካ አገራት የመገበያያ ብሮች ግድግዳው ላይ ተለጥፈው አይንን ይማርካሉ፡፡ የኢትዮጵያም ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋሉ የአስር፣ የሀምሳና የመቶ ብር ኖቶች ይገኙበታል፡፡
በአሜሪካ አገር ስሩ ሽቶና እጣን የሚሰራበት የሳር አይነት ከሪዞርቱ ግርጌ መጨረሻ ላይ ተተክሏል፡፡ ስሩ አምስት ሜትር ድረስ ወደ መሬት ይጠልቃል የተባለው ይሄው ሳር፤ አፈር በውሃና በንፋስ እንዳይሸረሸር በማድረግ ረገድ ወደር የለሽ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ከሆለታ ግብርና ምርምር አምጥተው እንደተከሉትም የ “አሻም አፍሪካ” ጠቅላላ አገልግሎት ኦፊሰርና የእለቱ አስጐብኚ አቶ ዳንኤል ግርማ ገልፀውልናል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ስራ ከጀመረ አንድ አመት ተኩል የሆነው “አሻም አፍሪካ”፤ ከ50 በላይ ለሆኑ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ ሲሆን  ከፈረንጆች አዲስ አመት በኋላ በይፋ ይመረቃልም ተብሏል፡፡
“እኔ ባለሀብት አይደለሁም፤ ሪዞርቱን የገነባሁት ከላይ እንደገለፅኩት አፍሪካን አንድ የሚያደርግና የሚያቀራርብ እንዲሆን ነው” ያሉት አቶ ሳህሉ፤ አብዛኛውን ወጪ ከባንክ በተገኘ ብድር መሸፈናቸውንና ብር ሲያገኙ ሲቀጥሉ፣ ብር ሲያጥራቸው ሲያቋርጡ ለግንባታው ወደ አምስት አመት ገደማ መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ የአፍሪካ ባህል፣ ገፅታ እና አጠቃላይ ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን በአንድ ቦታ የሚገኝበት አሻም አፍሪካን በመገንባቴ ደስተኛ ነኝ” ብለዋል፤ አቶ ሳህሉ ሀይሉ፡፡ 

Saturday, 28 December 2013 11:39

‘የንጉሥ ቃል…’

እንዴት ሰነበታቸሁሳ!
መቼም ነገር ሥራችን ሁሉ ጠያቂ የጠፋበት አገር መስሏል፡፡ “በምን ምክንያት?” “እንዴት እንዲሀ ይሆናል?”  ምናምን

መባባል … አለ አይደል….የሀጢአት ሁሉ መጨረሻ ሆኖ ሁሉንም ነገር “እሺ!” ብቻ ሆኗል፡፡
‘በዛኛው’ ባለፈው ዘመን አንደኛው ባለስልጣን አሉ አድራጊ ፈጣሪው ሲበዛባቸው… “አንድ ንጉሥ አውርደን ሁለት መቶ

ሰማንያ አምስት አነገሥን….” ምናምን ነገር ብለዋል ይባል ነበር፡፡ ‘ያልተቀቡ ነገሥታት’ በዙባቸዋ!
ታዲያላችሁ…ዘንድሮ በአንድ በኩል ‘ተቀብተንም’… “አልወርድምም አልፈርድምም!” ብለን ቅዝምዝም ‘ዝቅ ብሎ

በማሳለፍ’ የተካንን ባለወንበሮች አለን፡፡ “ውሳኔ አልወስንም፣ ፊርማ አልፈርምም ብለህ ህዝብ አጉላልተሀል…” በሚል

‘ሀጢአተኛ’ የመባል ዕድሉ ጠባብ ነዋ—ያውም የሚባል ከተገኘ!
ደግሞላችሁ…በሌላ በኩል ደግሞ ማን ‘ቀብቶ’ እንዳስቀመጠን የማንታወቅ ንጉሦች እየበዛን ነው፡፡ የታክሲ ረዳቱ

‘ንጉሥ’፤ “ከመገናኛ ፒያሳ ስድስት ብር ነው…” ሲል “በአንተ መጀን” ብሎ መቀበል እንጂ…  “መንግሥት ያወጣው ታሪፍ

እያለ አንተን ማን ወሳኝ አደረገህ?” ብሎ ነገር የለም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ! የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
ሌላው ታክሲ ረዳት ‘ንጉሥ’… “ሃያ ሁለት ብቻ ነው የምጭነው…” ሲል “በአንተ መጀን” ብሎ መቀበል እንጂ…አለ

አይደል… “ታፔላህ ላይ አራት ኪሎ፣ ካዛንቺስ ይል የለም ወይ…” ብሎ ሙግት አያዋጣም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ!

የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
እናላችሁ…‘ተቀብተው’… አለ አይደል… “ባልፈርም፣ ባልፈራርም አትገለብጠኝ!” ከሚሉት ይልቅ ‘ሳይቀቡ’ “ምንስ ባደርግ

ምን ታመጣለህ?” የሚሉ እየበዙ ነው፡፡ (ልጄ…ለነገሩ ‘ለመቀባትም’ ስንትና ስንት መስፈርት አለ!)
የመሥሪያ ቤቱ የምንና የምናምን የሥራ ሂደት ባለቤት ‘ንጉሥ’……“መሥሪያ ቤታችን በዘንድሮ የበጀት ዓመት የዕቅዱን

ዘጠና በመቶ አሳክቷል…”  ሲል “በእርሶ መጀን” ብሎ መቀበል እንጂ…አለ አይደል… “ከዘጠናው ውስጥ ሰባ አምስቱን

ከየት አምጥተህ ነው የዶልከው…” ምናምን ብሎ ሙግት የለም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ! የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
እናላችሁ…ዙፋን ችሎት ሳይሰየም፣ ‘ሬፈረንደም’ ሳይጠራ…የሚተላለፉ ‘ንጉሣዊ’ ትእዛዛትና ያልተጻፉ ህግጋት እያስቸገሩ

ነው፡፡
ለነገሩማ ምን መሰላችሁ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ ቦሶችን የሚያስቀይም ነገር እስካልተናገሩ ወይም

እስካላደረጉ ድረስ ‘ያልተቀባ ንጉሥ’ መሆን ይቻላል፡፡ ቀይ መስመር አልታለፈማ! ቀጪ፣ ተቆጪ የለማ!
እናላችሁ…የምግብ ቤት ባለቤት ‘ንጉሥ’ … ትናንትና በብር ከስሙኒ ይሸጠው የነበረውን ከቡና የጠቆረ ሻይ… “ከዛሬ

ጀምሮ የሻይ ዋጋ ሦስት ብር ከሽልንግ ነው…” ምናምን ሲል…አለ አይደል…“በአንተው መጀን” ብሎ መቀበል

እንጂ…“የስኳሩ ዋጋ ያው፣ የሻይ ቅጠሉ ዋጋ ያው…” ምናምን ብሎ ‘ጭቅጭቅ’ የለም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ!

የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
እናማ…ያልተቀባ ንጉሥ ሲበዛብን፣ የተቀባ ንጉሥ ሲዘባነንብን…አለ አይደል… ከዚህ በፊት እንዳወራነው “ይቺ አገር

ወዴት እየሄደች ነው…” ማለት ከጀርባው ‘ያለፈው ስርአት ናፋቂነት’ ምናምን ነገር ጉዳይ ሳይሆን… ግራ የመጋባት ጉዳይ

እንደሆነ ልብ ይባልልንማ፡፡
ስሙኝማ…ዘንድሮ እንደ ግል ትምህርት ቤት ባለቤቶች የተመቸው አለ! ልክ ነዋ ‘ተቀቡም አልተቀቡ’ እንደፈለጉ ዋጋ

መጫን ይችላሉዋ! በወር ክፍያ ላይ በአንድ ጊዜ አንድ ሺህና ሁለት ሺህ ብር ቢጨምሩ “በህግ አምላክ!” የሚላቸው ያለ

አይመስልም፡፡ እናላችሁ… የግል ትምህርት ቤት ባለቤት ‘ንጉሥ’… “ከዛሬ ጀምሮ በአንድ ተማሪ የወር ክፍያ ላይ አንድ

ሺህ ብር ጨምረናል…” ቢል…“በእርሶ መጀን” ብሎ መቀበል ነው እንጂ…“ምን ተጨማሪ ነገር አመጣችሁና ነው!” ምናምን

ብሎ ‘ጭቅጭቅ’ አያዋጣም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ! የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
ስሙኝማ…የግል ትምህርት ቤት ባለቤት አንድዬ ዘንድ ሲደርስ ምን የሚባል ይመስለኛል መሰላችሁ…
“ሥራህ ምን ነበር?”
“አንድዬ፣ የግል ትምህርት ቤት ባለቤት ነበርኩ።”
“እህ…አንተው ነህ? ስላንተ የሚነገረው አቤቱታ ከምድር አልፎ እኔንም እኮ ሲረብሸኝ ነው የከረመው። እንደው ለመሆኑ

እንዲህ ሰው ጤፉ የሆንከው ምን ተማምንህ ነው?”
“ጌታዬ ምን አደረግሁ…የህዝቡን ልጆች ባስተማርኩ፣ ድንጋይ እንዳይወረውሩና አማርኛ እንዳይናገሩ በህግ

ስለከለከልኩ…ደግሞ…”
“በቃህ፣ በቃህ!…ህጻናቱ በየጥጉ አደንዛዥ ዕፅ ሲያጨሱ የነበረው በአንተ ትምህርት ቤት አይደለም? እኔ ለአቅመ ዓዳምና

ሔዋን ስትበቁ ትደርሱበታላችሁ ያልኩትን ነገር ገና ጡጦ እንደጣሉ የሚለማመዱት በአንተ ትምህርት ቤት አይደለም!

በአሥራ ሦስት ዓመታቸው የሲጋራ ፓኮ በቦርሳቸው ይይዙ የነበሩት በአንተው ትምህርት ቤት አይደለም!”
“አንድዬ እኔ ምን ላድርግ፣ ወላጆቻቸው…”
“በቃህ፣ በቃሀ…የአንተ ጉዳይ አስቀድሞ የተወሰነ ስለሆነ ደብዳቤህን ሂድና ከመዝገብ ቤት ውሰድ…ደግሞ ስማኝ…”
“አቤት፣ አንድዬ…”
“ዲያብሎስን፣ ይኸው መልካም ወዳጅ ልኬልሀለሁ ብሎሀል በለው፡፡”
እናላችሁ…ያልተቀባን ነገሥታት በዝተናል። በሁሉም ነገር የእውቀት መጨረሻዎች እኛ እየሆንን ስትተነፍሱ

እያስፈቀዳችሁኝ ልንል ምንም የማይቀረን የቁጥራችን መብዛት ለጊነሱ መጽሐፍ ሊያደርስን ምንም አልቀረው፡፡ አይደለም

መልስ የሚሰጠን የትኛው እናቱ የወለደችው ነው ቀና ብሎ የሚያየን!
በዛ ሰሞን ኳሳችን ላይ “እህ…” ብሎ በጥልቀት ከመነጋጋር…አሼሼ ገዳሜው በቻ በዛና፣ “እንደው እዚች ቦታ አካባቢ

ቢታሰብበት…” ብሎ ነገር አስቸጋሪ ነበር፡፡ እናላችሁ…‘ያልተቀባ የኳስ ንጉሥ’…“የቡድናችንን ጨዋታ ድፍን ዓለም በጉጉት

እየጠበቀው ነው…” ሲል “በእርሶ መጀን” ብሎ መቀበል እንጂ…“ኧረ’ባካችሁ እንኳን የኳስ ቡድናችንን እኛ መኖራችንን

የማያውቅ ዓለም ብዙ ነው…” ብሎ ነገር የለም፡፡ ‘የንጉሥ ቃል’ ነዋ! የሚያስከትለው ጣጣ መአት ነዋ!
ስሙኝማ…‘ያልተቀባ ንጉሥ’ ሆኖ የከረመ የኳስ ሰው አንድዬ ዘንድ ሲደርስ ምን የሚባል ይመስለኛል መሰላችሁ…
“አንተ ደግሞ ሥራህ ምን ነበር?”
“አንድዬ ኳስ ተጫዋች ነበርኩ፡፡”
“ምን አልከኝ!”
“ቆይ..ቆይ እስቲ… ይሄን ያህል ችላ ብያችሁ ነበር እንዴ! ኳስ መጫወት ሥራ ሆኗል ነው የምትለኝ?”
“አዎ አንድዬ..”
“ማለት ኳስ ተጫውታችሁ የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ታገኛላችሁ?”
“አዎ አንድዬ፣ ያውም በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር፡፡ ምን ይገርማል?”
“ይገርማል እንጂ…እኔ ጥረህ ግረህ በግንባርህ ወዝ ብላ አልኩ እንጂ ኳስ ስታሳድድ ውለህ ብላ አልኩ…ተወው ብቻ

ይቅር፡፡ እና ለህዝቡ ምን አደረጋችሁ?”
“እንዴ አንድዬ አልሰማሁም እንዳትል…”
“ምኑን?”
“ከሠላሳ አንድ ዓመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈን ህዝቡን ፌሽታ በፌሽታ አድርገነው እንዴት አልሰማህም?”
“ተሞኝተሀል በለኛ፣ አምልጦሀል በለኛ…እኔ እኮ ከሠላሳ ምናምን ዓመት በኋላ የሚለውን ስትደጋገሙ ጎተራችን ሞላ፣

ወገናችን መራቡ ቆመ…ምናምን የምትሉ መስሎኝ ነበር፡፡ ኳስ ነበር እንዴ!”
“አንድዬ ድካማችንን ፉርሽ አታድርግብን እንጂ…”
“ይሁና… የአንተ ጉዳይ ሌላ ጊዜ ይታያል፡፡ እስከዛው እዛ ላሉና ገና ወደ እኔ ላልመጡ ዘመዶችህ ሠላሳ ምናምን ዓመት

እያላችሁ የምትደጋግሙት ነገር ሠላሳ የሚለውን ቁጥር ሊያስጠላኝ ስለሆነ ተዉኝ ብሏችኋል በልልኝ…”
እናላችሁ…የተቀቡም ያልተቀቡም ነገሥታት ኑሮን ከድጡ ወደማጡ እያደረጉብን ነው፡፡ ይኸው… በ‘ቦተሊካው’ እንኳን

እኛ ፍሬ ነገራችን ያልነውን የልብ፣ የልባችንን እንዳንተነፍስ ‘ነገሥታቱ’ ከወዲህና ከወዲያ  ቆቅ አየኝ በል እያሉን

ነው፡፡
ስሙኝማ…‘የተቀቡና፣ ያልተቀቡ ነገሥታት’ የሆኑት ‘ቦተሊከኞች’ አንድዬ ዘንድ ሲደርሱ ምን የሚባሉ ይመስለኛል

መሰላችሁ…
“አንተ ደግሞ ምን ነበርክ?”
“ፖለቲከኛ ነኛ!”
“ልታስቀኝ እየሞከርክ ነው፣ አይደል!”
“ኧረ በጭራሽ አንድዬ…በየመድረኩ ያንን ሁሉ ስለፈልፍ፣ በየጋዜጣው ላይ ፎቶዬን በትልቁ ገጭ አድርጌ ስወጣ፣

በየቴሌቪዥኑና በየሬድዮኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ስተነትን…ይሄን ጊዜ ሁሉ አይቼህ አላውቅም ነው የምትለኝ?”
“እኔን የገረመኝ ደግሞ ምን እንደሆነ ልንገርህ…በዛች አገር ፖለቲከኛ አለ ስትለኝ…”
“ሞልተናላ አንድዬ! በእርግጥ አንዳንዶቹ…”
“ቆይ ዝርዝሩን ተወውና ለህዝቤ ምን አደረጋችሁለት?”
“አንድዬ በእውነትም ረስተኸናል ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ እውቀቱ እንዲዳብር፣ ጠላቶቹን እንዲለይ፣ ከጎረቤቱ ጋር

በዓይነ ቁራኛ እንዲጠባበቅ…ምን ያላደረግነው አለ! ደግሞ ሰዉ የሚበጀውን ስለማያውቅ የሚበጀውን እንዲያውቅ…”
“በቃህ፣ በቃህ…አንተ ወደ ዳር ሁን…”
“ጌታዬ አሁን ወስንና ወደ መንግሥተ ሰማያት…”
“መንግሥተ ሰማያት መግባትም አምሮሀል? ስማኝ እናንተን ዲያበሎስ ዘንድ ብልካችሁም ከተገባራችሁ ጋር

ስለማይመጣጠን…ሌላ ከገሀነም ጓዳ የጨለመ ቦታ እስካገኝላችሁ ወደመጣችሁበት ትመለሳላችሁ፡፡”
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል….ጠፍተው ከርመው ብቅ የሚሉ ሰዎችን ሳይ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…አንድዬ

“ለእናንተ ቦታ እስኪያመቻች…” ብሎ የመለሳቸው! ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…‘የተቀቡም፣ ያልተቀቡም ነገሥታት’ ቁጥር በዝቶብናል ይቀነስልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Published in ባህል
Page 1 of 16