Saturday, 28 March 2015 10:17

የፍቅር ጥግ

አንዳንዴ ለዓይን የተሰወረውን ልብ ያየዋል፡፡
ኤች ጃክሰን ብራውን ጄአር.
ፍቅር ማለት ራስን ያለ ዋስትና መስጠት ነው፡፡
አኔ ካምቤል
አበባ ያለ ፀሐይ ብርሃን አያብብም፤ ሰው ያለ ፍቅር አይኖርም፡፡
ማክስ ሙለር
የፍቅር የመጀመሪያ ተግባሩ ማድመጥ ነው፡፡
ፓውል ቲሊች
ፍቅር፣ ዕድሜ፣ ገደብና ሞት አያውቅም፡፡
ጆን ግላስዎርዚ
የሌላው ሰው ደስታ የናንተ ደስታ ሲሆን ያኔ ፍቅር ይባላል፡፡
ላና ዴል ራይ
ማፍቀር ያለባችሁ ብቸኛ ስትሆኑ አይደለም፤ ዝግጁ ስትሆኑ ነው፡፡
ያልታወቀ ሰው
ለዘላለም እንዲዘልቅ የምትሹትን ነገር አታጣድፉት፡፡
ያልታወቀ ሰው
10 የማፍቀሪያ መንገዶች፡- ማድመጥ፣ መናገር፣ መስጠት፣ መፀለይ፣ መመለስ፣ መጋራት፣ መደሰት፣ ማመን፣ ይቅር ማለት፣ ቃል መግባት፡፡
ዊል ስሚዝ
በዓይኖቻችሁ ሳይሆን በልባችሁ አፍቅሩ፡፡
ያልታወቀ ሰው
ፍቅር አደገኛ የአዕምሮ በሽታ ነው፡፡
ፕሌቶ
ፍቅር ፍፁም እንዲሆን መጠበቅ የለብንም፤ እውነተኛ መሆን ብቻ ነው ያለበት፡፡
ያልታወቀ ሰው
በፍቅር መውደቅ፤ ደካማ አማልክት ያለው ሃይማኖት መፍጠር ነው፡፡
ጆርጅ ሉይስ ቦርግሰ
ለዓለም አንድ ሰው ብትሆኑም፣ ለአንድ ሰው ግን ዓለም ልትሆኑ ትችላላችሁ፡፡
ያልታወቀ ሰው

Published in ጥበብ
Saturday, 28 March 2015 10:15

የሥነ ጽሑፋዊ ሒስ ዳናዎች

መጽሐፍትን ማንበብ፣ የተፈተፈቱ አበቦችን ለነፍስ ማጉረስ ብቻ አይደለም፤ በነፍሳችን ጉሮሮ ላይ የሚሠነቀሩ እሾሆችንም መንቅሮ መጣል ነው። በጥበብ ምህዋር በደስታ የሚያንፈቀፍቁንና በሲቃ የሚያንሠቀስቁን ሁሉ የሚመዘኑበት ሚዛን፣ የሚጣሩበት ወንጠፍት አለ፡፡
በጥበብ ቤተዘመዶች ቅጥር ግቢ ውስጥ ሒስ የሚባለው አንዱ ድንኳን ውስጥ ያለው ሣይንስ ሥራው ይሄ ነው፡፡ ይህን ሳይንስ የሙጢኝ ብለው፣ ጥበቡን ከቆረቆንዳው ላይ እየፈለፈሉ፣ ከፊሉን ለወፍጮ፣ ከፊሉን ለቅርጫት የሚዳርጉት ለጥበቡ ካላቸው ፍቅር የተነሣ ነው ይላሉ፤ ጆርጅ ስቴይነር፡፡ በእሳቸው አባባል፤ ሃያሲ የሚረገዘውና የሚወለደው ጥበብና የሰውየው ልብ በፍቅር ሲወድቁ ነው፡፡ ምናልባትም የመጀመሪያው የሒስ አባት አርስቶትል፤ “ፖኤቲክስ” ብሎ የሥነጽሑፍ ውጤቶችን መበርበር የጀመረው ከዚሁ የፍቅር ቅብጠት የተነሣ ይመስለኛል፡፡ በትራጀዲ ውስጥ ያሉ ገፀባህርያትን፣ ኤፒክስ (የጀግንነት ግጥሞችን) ሥነ - ጽሑፋዊ ምነባን፤ ቅርፅንና ፍልስፍናን ሁሉ አገላብጦ ለማየት መፈልፈያ ያዘጋጃል ብሎ መዋቅር ያበጀለት ታላቁ ሰው ይህ ነው፡፡ ቀጣዩ ደግሞ አፍላጦን ነው፡፡ ይሁንና አንዱ ከአንዱ የሚለይበት የየራሱ ሀዲድ ነበረው፡፡
መነሻው እርሱ ይሁን እንጂ በየዘመኑ አንጓ ላይ የጥበቡ አሻራ አኗሪዎች በርካታ ናቸው፡፡ በሮማ ዘመን የላቲኑ ሆራስ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሃያሲ ነበር፡፡ ይህ ሰው በተለይ በእንግሊዝ፣ በ16ኛውና 17ኛው ክፍለ ዘመን ጆሮ ተከፍቶ የተሰጠው የዘርፉ ሊቅ ነበር፡፡
ይልቅስ የሒስ ጐጆ ቀዝቅዞ በረዶ የተጋገረበት በመካከለኛው ዘመን ነው፡፡ ለምን ቢሉ… የክርስቲያናዊው እምነት አለቆች፣ ወይም የነገረ መለኮት ሰዎች ትርጓሜና ትንታኔ መንገድ ነው፡፡ ከቅርፅና ከመዋቅር ወይም ከሥነ - ውበት ይልቅ፣ ወደ መንፈሳዊና ሞራላዊ ዝንባሌ ፈቅ በማለቱ፣ ጥበብ ከንፈሮችዋ ደርቀው፣ ነፍስ በውበት ጥም እንድትከሣ አደረጋት፡፡ ግና በዚህ መሀል እንደ ምድረበዳ ፅጌረዳ የታላቁ ጠቢብ ደራሲ የዳንቴ መዐዛ ነበር፡፡ በርግጥም ኢጣሊያዊው ዳንቴ ስለ ዐረፍተ ነገር አወቃቀር፣ ስለ አፃፃፍ ዘዬና መሠል ነገሮች መፃፉን አልተወም፡፡
ውሎ እያደር ግን በተሃድሶ ዘመን እንደ አዲስ ሙዚቃ፣ እንደ ትኩስ ጀንበር በጥበቡ ሠፈር ቄጠማ የጐዘጐዙ ምርጥ የጥበብ ሰዎች በኢጣሊያና በፈረንሳይ ብቅ ብቅ ብለው ነበር፡፡ በተለይ የነገረ መለኮታዊያኑን ባለ አንድ ክንፍ የሒስ መስመር በማቅናት፣ ሁለት ክንፍ ገጥመው እንዲበሩ ደመናውን ጠርገዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም ቪዳ፣ ሮበርቴሊ፣ ዳኒኤሎ፣ ሚንቱርኖ… ይጠቀሳሉ፡፡
በ1668 ገደማ ገጣሚውና ሃያሲው አሌክሳንደር ፖፕ፣ ጆን ድራይደን፤ በቀጣዩ ዘመን ደግሞ በርካታ የእንግሊዝ ገጣሚያን የሂሱን ሣይንስ መሬት እንዲረግጥ አግዘውታል፡፡ ሻማ ለኩሰው፣ ብርሃን ፈንጥቀውበታል፡፡
ስለ ሥነ- ጽሑፋዊ ሒስ ሥናነሳ፣ በየዘመኑ እያደገና እየተመነደገ መምጣቱ አሌ የማይባል ነው። ከትምህርት መስፋፋት ጋር፣ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ያደረጉ ኮርሶችንና ጥናቶችን የሚያሠሩ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት ይበልጥ አጎልብተውታል። ከዚያም የሚወጣው ብርሃን የፕሬስና ሌሎች መገናኛ ብዙሀን ዘርፍን ድጋፍ በማድረግ የተሻለ ሥራ ሰርተዋል፡፡
ሒስን አንዳንዶቹ ከልጅነት ጀምሮ የተዘረጋ ዘንግ ወይም ያነቦጠ ለጋ ኮክ አድርገው ያዩታል፡፡ ኢ.ኤ ግሪኒንግ ላምቦርን እንዲህ ይላሉ፡- “…Children are naturally good critics of poetry and they have an instinctive appreciation of its beauty…” ይሁን እንጂ እኒሁ ሰው፣ የሒስን ዝንባሌ ሰዎች በንባብና በትምህርት ደግፈው እንዲያሣድጉት ይመከራሉ፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን ሂስ በጥልቅ ምልከታ፣ በጠንካራ ንባብና ትምህርት አድጐ ትሩፋቱ ወደ ሕብረተሰቡ ሲደርስም ጣጣ አለበት፡፡ በተለይ ሥራው ላይ አስተያየት የተሰጠበት ደራሲ ቅጥር ግቢው እንደተደፈረበት ውሻ አገር ይያዝ ሊል ይችላል፡፡ የተለያዩ ምክንያቶችን በመፍጠርም ከክፋትና ከምቀኝነት ጋር ሊያገናኘው ይጥራል። የዚህ ዓይነቱ ገጠመኝ በኛ ሀገር ብቻ ሣይሆን በሌሎች ያደጉ ሀገሮች ቀደም ሲል ጐልቶ የታየ ችግር ነበር፡፡ ለምሳሌ በሥነፅሁፍ የኖቤል ተሸላሚው ዊልያም ፎክነር፤ “ስለ ሃያሲ የማስብበት ጊዜም የለኝ” ብሏል፡፡ ቻርል ዲከንስ፣ ማርክ ትዌይን፣ ሄነሪ ዎርድስ ወርዝ፣ ሎንግ ፌሎው፣ ኮልሪጅና ሌሎችም ሐያሲያን ላይ የስድብ ናዳ አውርደዋል። ይሁን እንጂ የሒሱ ሀዲድ ጉዞ አልተቋረጠም፡፡ በእኛ ሀገርም ለምሳሌ ደራሲ አቤ ጉበኛ፤ በሐያስያን ላይ መራራ ጥላቻ ነበረው፡፡ በየመጽሐፍቱ መግቢያ ላይም “ጠላቶቼ” እያለ እስከመሣደብ ይደርስ ነበር፡፡
ሒስ ለሥነ ጽሑፉ ዕድገት እጅግ ወሳኝ መሣሪያ ቢሆንም ዳግም እንዳያበቅል አድርጐ የሚሰብር መጥረቢያም ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ነው ሒስ ገንቢ መሆን አለበት የሚባለው፡፡ ዋነኛ ዓላማው ለማሣደግና ለማቅናት እንጂ ለመስበርና ለማዋረድ አይደለም፡፡ ይልቅስ ጥንካሬውን ነግሮ፣ ድክመቱን ጠቁሞ፣ ነገ የተሻለ የጥበብ ፅጌረዳ ለማሽተት መትጋት ነው ያለበት፡፡
ገጣሚና ሃያሲ ዮሐንስ አድማሱ፤ የሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ያለማደግ ምክንያት የሒስ አለመዳበር መሆኑን የፃፈው የዛሬ አርባ ዓመት ገደማ ነበር፡፡ በመረረ ቁጭትና ቁጣ የፃፈው ዮሐንስ፤ “እስከ 1959 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ የተሻለ የፈጠራ ድርሰት የፃፉት ሀዲስ አለማየሁ /ፍቅር እስከመቃብርን/ እና ነጋሽ ገብረማርያም ነበሩ” ይላል። ዮሐንስ ለሒሱ ያለመዳበር ምክንያት ያላቸውን ደራሲያንንም ወቅሷል፡፡ በ1983 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ በታተመው “የካቲት” መጽሔት ላይ ታየ አሰፋ የተባሉ ፀሐፊ፤ የሒስ አለመዳበር ለሀገራችን ሥነ ጽሑፍ ዕድገት እንቅፋት መሆኑን ሲገልፁ፤ “የሥነ ጽሑፍን እድገት የሚመጥንና የአማርኛ ልቦለድ የደረጃና የአቅጣጫ ለውጥ እንዲያሳይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽእኖ ሊያደርግበት የሚችል የሂስ ባህል አብሮት አልዳበረም፡፡” ብለዋል - ቶማስ ኬንና አልበርት ዤራርድን የመሳሰሉ የውጭ ባለሙያዎች፤ በኢትዮጵያ ሥነ -ጽሑፍ ላይ ጥናት ማካሄዳቸውን በመግለፅ፡፡ ፀሃፊው በጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ የሚታተሙ አስተያየቶችን “ስሜታዊና ተጨባጭ መረጃ የሌላቸው፣ የባለቤትነት ጠረን ያጠቃቸው ናቸው፡፡” ሲሉ ተችተዋል፡፡
አቶ ታዬ የጠቀሷቸውን ሃሳቦች ብዙዎቻችን የምንጋራቸውና እስካሁንም ድረስ የዘለቁ ችግሮች ናቸው፡፡ በእርግጥ እነዚህ ችግሮች በኛ ሀገር የተወለዱ ሳይሆኑ ከጥንት ጀምሮ በሌሎች ሀገሮችም የተለመዱ ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ከሥልጣኔና ከእውቀት ጋር እየተሻሻሉ የሚመጡ ችግሮች ናቸውና ልናስወግዳቸው ግድ ይላል፡፡ ምክንያቱም ሂሳዊ ግምገማ ለደራሲው ገበያ ከመፍጠርና ደራሲውን ከመጉዳት ያለፈ ዓላማ አለው፡፡ ያ ዓላማ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት፣ የሀገሪቱን ሥነ-ፅሁፍ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡ በዚህም ከፍታ፤ መጪው ትውልድ የተሻለ ኃላፊነት የሚሰማው፣ ኪነጥበባዊና ሳይንሳዊ ክህሎቱ የላቀ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
የስነ ጽሑፋዊ ሂስ ጉዞ የዘመኑን ሳይንስና አውድ በሚገባ ያጤነና ሀዲዱን ተከትሎ፣ ፍጥነቱን ጠብቆ የሚጓዝ እንዲሆን ማድረግ ጉዳዩ የሚመለከተን ሁሉ አብይ ተግባር ነው፡፡
ለምሳሌ በአባብዛኛው እንደተለመደው ቅርፃዊ ሂስን ብቻ ይዘን እሹሩሩ ብንል ዘመኑ አይቀበለንም። ቋንቋችንና ሀሳባችን ለየቅል ስለሚሆን ልንደማመጥ አንችልም፡፡ የድህረ ዘመናዊያኑን ሥራ በቅርፃዊ ሂስ ተንትነን መልክ ልናስይዘው አንችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ “አደፍርስ”ን ከ “stream of consciousness” ውጭ ልናጤነው አንችልም፡፡ ምክንያቱም የታሪኩ አወራረድ እንደ ሀዲድ አንድ መስመር ይዞልን አይሄድም፤ በተለያየ አቅጣጫ ይፈሳል፡፡ ሃሳቦቹ የቅደም ተከተል መሳበር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ስለዚህ ሐያሲው ዘመኑን ተከትሎ የሚፈጠሩትን የሥነ ፅሑፍ ስራዎች የሚከረክምበትን መቀስ ስሎ ሊጠብቅ ይገባዋል፡፡ “… ፍሬ የሚያፈሩትን አብዝተው እንዲያፈሩ፣ የማያፈሩትን ደግሞ ከግንዱ ላይ ቆርጦ ለመጣል!” እንዲል ወንጌሉ፡፡
ወደ ድህረ ዘመናይነት ስንመጣ ደግሞ “Deconstruction Criticism” አለ፡፡ ይህ ደግም ቋንቋ ሁሉንም እውነታ ለተደራሲው ያደርሳል ብሎ አያምንም፡፡ ስለዚህ ቋሚ መልእክት አስተላላፊ አይደለም ይላል፡፡ “Literary texts, which are made up of words, have no fixed, single meaning” አንባቢውን ያሳትፋልና ተደራሲው ሲያነብብ ደራሲው ሞቷል ይለናል፡፡ ዋናው ነገር ሮናልድ ባርትዝስና ማይክል ፎውካልት እንደሚሉት፤ “It  focuses on how language is used to  achieve power” ነው፡፡
ታዲያ ሥነ ልቡናዊ፣ ታሪካዊ፣ ፆታዊ፣ ባህላዊ… ሂሶችስ ቢሆኑ እዚህ ቦታ ምን ያህል አቅም ኖሯቸው ይቆማሉ፡፡ ስለዚህ ሀያሲ ዘመኑን የሚመጥን ሀሳብ፣ ነገን የሚደርስ ህልም ሊኖረው ይገባል፡፡ ያለበለዚያ የአዳም ረታን ስነ ፅሁፋዊ  ስራዎች በየትኛው ትልም አስቀምጠን  ውስጣቸውን መፈተሸ ይቻለናል? … መነፅራችንን መቀያየር የምንችልበት ዝግጅት ሊኖረን የግድ ነው፡፡
ለነገሩ የአፃፃፍ ዘዬ፤ ዘውግ፣ አወቃቀር፣ ድምፀት፣ ጭብጥና ቃላት አጠቃቀምን እንኳ መች በወጉ አጠናነው?… ከኛ የቀደሙት ምሁራንና ተመራማሪዎች ስራዎቻቸው በመጽሐፍት ባይጠረዙ እንኳ ቢያንስ በጋዜጦችና መጽሔቶች ጠቃሚና ብርቱ ስራዎችን ትተውልን አልፈዋል። በአሁኑ ዘመንም ዘርፉን ለማሳደግ የአቅማቸውን ለዳከሩ፣ ለታገሉና አንገታቸውን ቀብረው ለተጉ ሁሉ ምስጋናችን ብርቱ ሊሆን ይገባል፡፡

Published in ጥበብ

(ይህ ታሪክ የተፃፈው በ1940 እ.ኤ.አ ቢሆንም እስከ 1967 ዓ.ም ድረስ የመታተም እድል ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም የታተመው “ዘ ኦብጀክቲቪስት” በተባለው መጽሔት ላይ ነው፡፡ ታሪኩ የፈጠራ ምጥን ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡ አርቲስቱ በምን አይነት መንገድ የህይወቱን ጭብጥ ከአእምሮው ሃሳቦች እና ከተጨባጩ እውነታ ጋር አስተሳስሮ ለመግለፅ እንደሚቃትት ያስቃኛል፡፡)
   ሄንሪ ዶርን በዴስኩ ላይ ተቀምጦ ባዶው ወረቀት ላይ ያፈጥጣል፡፡ የደነዘዘ የድንጉጥነት ስሜት ወሮታል፡፡
ግን እኮ ይሄ እስከዛሬ ካከናወንከው አንፃር በጣም ቀላሉ ስራ ነው፤ ሲል ለራሱ ተናገረ፡፡
በቃ ደደብ መሆን ብቻ ነው ያለብህ፤ አለ ለራሱ። በቃ ይኼው ብቻ ነው፡፡ ዘና በልና በተቻለ መጠን ራስህን ደደብ አድርግ …ቀላል ነው አይደል? ምንድነው ያስፈራህ አንተ ሞኝ? ደደብ መሆን አልችልም ብለህ ነው የሰጋኸው…? ትዕቢት አለብህ፤ ብሎ ራሱን ገሰፀ፡፡
አዎ ይህ ነው ችግርህ፤ ትዕቢት አለብህ፤ ራስህን ጋራ አሳክለህ ነው የምታየው፤ ይኸው ነው ችግርህ፤ ስለዚህ ደደብ መሆን ይከብድሃል አይደል? አሁን ግን ይኼንን ስታስብ ደደብ እየሆንክ እንደሆነ ልብ በል፤ ለምን ግን ራስህን አዘህ ደደብ ማድረግ ያቅትሃል?
በቃ ከአንድ ደቂቃ በኋላ መፃፍ እጀምራለሁ፤ አለ። አንድ ደቂቃ ብቻ… ከዚያ እጀምረዋለሁ፡፡ አሁንስ አደርገዋለሁ፡፡ ለአንድ ደቂቃ ብቻ እረፍት ልውሰድ… ምን ችግር አለው? ለአንድ ደቂቃ ብቻ ባርፍበት? በጣም ደክሞኛል፡፡
ዛሬ ምንም አልሰራህም፤ አለ ራሱን በራሱ፡፡ ዛሬ አይደለም…ለወራት አንዳችም ነገር አላከናወንክም፡፡ ታዲያ ምንድን ነው ያደከመህ? አሀ ለዚህ ነው የደከመኝ፤ ምንም ስላልሰራሁ ነው የደከመኝ…
መፃፍ ብችል… መፃፍ እንደገና እንድችል ያስፈለገውን መስዋእትነት አደርጋለሁ… በቃ አቁም! እንደዚህ እያልክ ማሰብህን በቶሎ አቁም! ሌላውን ነገር ሁሉ ማሰብ መብትህ ነው፤ እንደዚህ  ብለህ ማሰብ ግን አይፈቀድም፡፡
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ጽሑፉን ለመጀመር ዝግጁ ነህ። አልችልም ብለህ ካሰብክማ… መቼም ዝግጁ አትሆንም። አትመልከተው! ወደዚያ ዞረህ እሱን ነገር አትመልከት…እያለ ራሱን ግን ዞሮ ተመለከተው፡፡ የተመለከተው አንድ ባለ ብዙ ገፅ ጠንካራ ሰማያዊ ሽፋን ያለው፣ በመደርደሪያ ላይ የተቀመጠውን መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ በመጽሔቶች ክምር ተደፍጥጧል፡፡ ከመጽሐፉ ጠርዝ ጋር የተነካኩት የፖስታ እሽጐች ነጭነታቸው የመጽሐፉን ሰማያዊ ቀለም አደብዝዞታል፡፡ የመጽሐፉ አርዕስት ጉልህ ሆኖ ይነበባል፡፡ “Triumph” (ድል አድራጊነት) በሄነሪ ዶርን ይላል፡፡
ከተቀመጠበት ተነስቶ መጽሔቶቹን ወደ ታች በመጐተት፣ የመጽሐፉ ገፅታ እንዳይታይ ሸፈነው፡፡ ለመፃፍ በምትሞክርበት ወቅት ከዚህ በፊት የፃፍከውን ባታስታውስ ይሻልሀል፤ አለ ለራሱ፡፡ ወይንም መጽሐፉ የአሁኑን ጽሑፍህን አይቶ እንዳይሸማቀቅ ብትደብቀው ይመረጣል፡፡ አይ አንተ ስሜታዊ ሞኝ ፍጡር! አለ ራሱን ደግሞ፡፡
ጥሩ መጽሐፍ አልነበረም የፃፍከው፡፡ ግን በምን አወቅህ ጥሩ መጽሐፍ ስለመሆኑ? አይ ይኼማ ራስን ማታለል ነው፤ እሺ በቃ ጥሩ መጽሐፍ ነበር፡፡ እንዲያውም እፁብ ድንቅ መጽሐፍ ነው! ምንም ማድረግ ባትችልም እውነቱ ግን ይኼ ነው፡፡ መጽሐፉ መጥፎ ስለመሆኑ ራስህን ማሳመን ብትችል ኖሮ ነገሮች በቀለሉልህ ነበር። ያኔ መጽሐፉ ተቀባይነት ማጣቱ … እውነትም ይገባዋል ትል ነበር፡፡
ያኔ አንገትህን ቀና አድርገህ የተሻለ ድርሰት ለመፃፍ መነሳት ትችል ነበር፡፡ ግን ችግርህ የመጽሐፍህን መጥፎነት አምነህ አልተቀበልክም፡፡ አምነህ ለመቀበል በጣም ደክመሃል ግን አልተሳካልህም፡፡
እሽ በቃ…አሁን ነገሩን ለቀቅ አድርገው፤ አለ ለራሱ፡፡ ይኼንኑ ሃሳብ ደግመህ ደጋግመህ ስታመነዥግ ቆይተሃል። ለሁለት አመታት ያህል፡፡ ስለዚህ አሁን ለቀቅ አድርገው። ቆይ አሁን ለቀቅ አላደርገውም… ትንሽ ላስበው፤ አለ ራሱን፡፡
ስለመጽሐፉ መጥፎነት የተለያዩ ሃያሲዎች የተናገሩት ነገር አይደለም ቅስሜን ለመስበር የሚፈታተነኝ… እንዲያውም ጥሩ የምላቸው ሃያሲዎች የሰጡት ሂስ ነው የእግር እሳት ሆኖ የሚፈጀኝ፡፡ በተለይ ፍሎሬት ሉም ያለችው፤ “እስከዛሬ ካነበብኳቸው ምርጥ መጽሐፍት አንዱ ነው…ምክንያቱም” አለች “በጣም ልብ የሚነካ የፍቅር ታሪክ በውስጡ ስለያዘ ነው…”
እሷ ይኼንን እስክትል ድረስ የፍቅር ታሪኩ ልብ የሚነካ ስለመሆኑ ይቅርና መጽሐፉ ውስጥ የፍቅር ታሪክ እንዳለ እንኳን አልተገነዘበም ነበር፡፡
ፍሎሬ ትሉም ስላልነበረው ነገር ስታወራ መጽሐፉ ውስጥ ስላለው ዋና ነገር ግን አልጠቀሰችም፡፡ ለአምስት አመት መጽሐፉ ውስጥ ለማስፈር ሌት ተቀን ሲያስብ ሲከትብ፣ በጥንቃቄና በቁጠባ ሲፅፋቸው የነበሩ ፍሬ ነገሮች አልታዩለትም፡፡
መጀመሪያ የሃያሲዎቹን አስተያየት ሲያነብ፤ በመጽሐፉ ውስጥ እሱ በልፋት ያኖራቸው ሃሳቦች ጭራሹን እንደሌሉ እርግጠኛ ሆነ፡፡ ያሉ መስሎት እንጂ ድሮውኑም አልነበሩም፤ ወይንም አታሚዎቹ መጽሐፉ ላይ ሳያሰፍሯቸው ቀርተዋል፡፡ ግን አታሚዎቹ የእሱን ሃሳብ ሳያካትቱ ከቀሩ፣ መጽሐፉ በምን ተአምር ተሞላ? ምን ሊሆን ይችላል እነዚያን ሁሉ ገፆች የሞላው ነገር?
መጽሐፉን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሳይፅፈው ቀርቶም ሊሆን አይችልም፡፡ ወይንም ብሩህ አዕምሮ አላቸው ብሎ የሚያስባቸው ሰዎች እንግሊዝኛ የማንበብ ችግር አለባቸው ማለትም አያስኬድም፡፡ ወይንም እሱ የጭንቅላት ጤና ጐድሎትም አይሆንም፡፡
ስለዚህ የራሱን መጽሐፍ ብዙ ጊዜ ደግሞ ደጋግሞ አነበበው፡፡ በጣም በጥንቃቄ፡፡ አንድ የተሳሳተ አረፍተ ነገር በንባቡ መሀል ሲገጥመው ወይንም ተዝረክርኮ የተፃፈ ምዕራፍ ሲያገኝ አሊያም ግልጽነት የጐደለው ሃሳብ ሲገጥመው ይደሰታል፡፡ ልክ ናቸው፤ ይላል፡፡ ልክ ናቸው፤ ችግር አለው… ግልፅነት ይጐድለዋል፡፡
ግን መጽሐፉን እስከ መጨረሻው አንብቦ ሲያጠናቅቅ ዋናው ነገር በደንብ እንዳለ ያረጋግጣል፡፡ ዋናው ጉዳይ መኖሩን ብቻ ሳይሆን… ግልፅነትም… ውበትም ተሟልተው እንደሚገኙበት መልሶ ያምናል፡፡ ይሄ ብቻም አይደለም። ከዚህ የተሻለ አድርጐ ሊፅፈው እንደማይችልም ይገለፅለታል፡፡
እናም መጽሐፉ እንዴት ተቀባይነት እንዳላገኘ መቼም ሊገባው የማይችል እንቆቅልሽ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፡፡ ደግሞም በህይወት መቆየት ካለበት መቼም ሳይገባው ቢቀር ነው የሚሻለው፡፡
እሺ…አለ፡፡ አሁን ይበቃል! ከአንድ ደቂቃ በላይ ስለ አለፈው ስታማርር ቆየህ አይደል? ከአንድ ደቂቃ በኋላ እጀምራለሁ ብለህ ነበር እኮ፡፡
የመፃፊያ ክፍሉ በር ክፍት ስለነበር ወደ መኝታ ቤቱ አሻግሮ ተመለከተ፡፡ ኪቲ ጠረጴዛው አጠገብ ተቀምጣ ካርታ (Solitaire) እየተጫወተች ነው፡፡ ሁሉም ነገር ጥሩ መሆኑን ለመመስከር የሚጥረው ገፅታዋ …ጥረቱ ተሳክቶለታል፡፡
ቆንጆ ከንፈሮች አሏት፡፡ የሰዎችን አፍ በመመልከት ማንነታቸውን ማወቅ ይቻላል፡፡ የእሷ አፍ በመላው አለም ላይ መሳቅ የፈለገ ይመስላል፡፡ ካልሳቀችበት ደግሞ ጥፋቱ የሷ ነው የሚሆነው፡፡ ደግሞም ከተወሰኑ ቅፅበቶች በኋላ፣ በአፏ አለም ላይ ትስቅበታለች፡፡ ምክንያቱም እሷም አለምም በመልካም ሁኔታ ላይ የሚገኙ ጤናማ ነገሮች በመሆናቸው ነው፡፡
በመብራቱ ወጋገን አንገቷ በጣም ነጭ እና ቀጭን ይመስላል፡፡ አንገቷ በተመስጦ በምትጫወተው ካርታ ላይ ተጐንብሷል፡፡ “ሶሊቴር” ወጪ የማይጠይቅ ጨዋታ ነው፡፡ ካርታዎቹ በዝግታ ሲወድቁ የሚፈጥሩት ድምጽ ይሰማዋል፡፡ በክፍሉ ጥግ እንፋሎት በቧንቧ ውስጥ ሲጓዝ የሚያወጣው አንዳች ድምጽ አለ፡፡
የበሩ ደወል አቃጨለ፡፡ ኪቲ በሩን ለመክፈት እሱን ቀና ብላ ሳታየው በክፍቱ በር አልፋ ቀደመች፡፡ ሰውነቷ ዓላማ በተላበሰ ቅልጥፍና ጠበቅ ማለቱን አስተውሏል። የህፃን ልጅ ልብስ የሚመስለው ሰፊ፣ በጣም ቆንጆ ቀሚሷ ከተገዛ ሁለት አመት አለፈው፡፡ ለበጋ ወቅት እንድትለብሰው ነበር የተገዛው፡፡
በእሷ ፋንታ እሱ በሩን ለመክፈት መነሳት ይችል ነበር፡፡ ግን ለምን ለመክፈት እንደፈለገች ስለገባው ነው የተወላት፡፡ ተነስቶ ቆመ፡፡ እግሮቹን ሰፋ አድርጐ ከፍቷል። ሆዱን ወደ ውስጥ ስቦ፣ ወደ በሩ አቅጣጫ (ሳይመለከት) ጆሮውን ግን በሩ ደጃፍ አነጣጥሮ ያደምጥ ጀመር፡፡ አንድ ድምጽ ከውጭ ሲናገር ሰማ፤ ከዚያ ኪቲ መለሰች፤ “በጣም ይቅርታ፤ እኛ ኤሌክትሮሉክስ ለመግዛት አንሻም”
የኬቲ ድምጽ ከእስር የተፈታ እፎይታ ይደመጥበታል፡፡ ግን እንዳያስታውቅባት እየጣረች ነው፡፡ ኤሌክትሮሉክስ አሻሻጩ ሰው መጥቶ በማንኳኳቱ ደስተኛ ከመሆኗ የተነሳ፣ ወደ ውስጥ እንዲገባ ብትጋብዘውም የምትፈልግ መሆኗ በቅላፄዋ እንዳያስታውቅባት እየጣረች ነው፡፡
የኬቲ ድምጽ ለምን እንደዚያ በደስታ እንደተሞላ አውቋል፡፡ የደስታው እፎይታ የወጣው ያንኳኳው ቤት ያከራያቸው ሰው ይሆናል ብላ ስለፈራች ነበር። ባለመሆኑ ቅልል አላት፡፡ ኬቲ በሩን ዘጋችና ወደ እሱ ዞራ ተመለከተችው፡፡ ክፍሉን እያቋረጠች “ይቅርታ” እንደማለት ፈገግ አለች፡፡ በህይወት ስለመገኘቷ የምትደሰት ሴት ናት፡፡ “የኔ ውድ፤ አልረበሽኩህም አይደል?” አለችውና ወደ ካርታ ጨዋታዋ ተመለሰች፡፡
ማድረግ ያለብህ ነገር ግልጽ ነው፤ አለ ለራሱ፡፡ ማድረግ ያለብህ ሃያሲዋን ፍሎሬት ሉምን ማሰብ ነው፡፡ ፍሎሬት ምንድን ነው የምትወደው? እሷ የምትወደውን ነገር በሃሳብህ መሳል ከቻልክ ያንን በፅሁፍ ማስፈር ብቻ ነው፡፡ ይኸው ነው ነገሩ፡፡ ከዚያ ገበያ ላይ ስኬታማ የሚሆን መጽሐፍ ደርሰህ ታሳትማለህ እናም ብዙ ገንዘብ ታገኛለህ፡፡ ይኼንን ማድረግ ላንተ በአለም ላይ የመጨረሻው ቀላል ነገር ነው የሚሆነው፡፡
መቼም አንተ ብቻህን ትክክል ሆነህ አለም ሁሉ ስህተተኛ ሊሆን አይችልም፤ አለ ለራሱ፡፡ ሁሉም ሰው ለገበያ የሚሆን መጽሐፍ እንድትፅፍ ሲወተውትህ ነበር። ስራ ለማፈላለግም ሞክረህ ስራ የሚሰጥህ አላገኘህም፡፡ ማንም ስራ እንድታገኝ ያገዘህም የለም፡፡ ማንም ከቁብ የጣፈህም አልነበረም፡፡
እንደ አንተ አይነት ጥይት ጭንቅላት ያለው ወጣት… እያሉ ይቆጩብሃል፡፡ ፖል ፓቲሰንን አትመለከተውም (ይሉሃል)፤ የአንተን ጭንቅላት ግማሽ ያህል አቅም ባይኖረውም… በአመት ሰማኒያ ሺ ዶላር ያገኛል፤ ፖል ህዝብ ማንበብ የሚፈልገውን ጠንቅቆ ያውቃል። የሚፈልጉትን ይሰጣቸዋል፤ አንተ ግትርነትህን ብታስወግድ ጥሩ ነበር፤ ይሉታል፡፡ ሁልጊዜ በጣም ምጡቅ ሃሳብ ማሰብን ብታቆም… ለምን በእውነታው አለም ላይ አትኖርም?... ለምን ሰው የሚገባውን አትጽፍም? ይሉታል፡፡ ሁሉም ሰው የሚገባውን ፅፈህ ሀምሳ ሺ ዶላርህን ከሰራህ በኋላ… ዘና ብለህ… ይሄ አንተ የምትፈልገውን አይነት “ጥልቅ” ስነጽሑፍ መፍጠር ትችላለህ፡፡ ከፈጠርከው በኋላ ባይሸጥም…
ለምን ሌላ ስራ ትይዛለህ? ይሉታል፡፡ ምን ክህሎት አለህ? በሌላ ዘርፍ ምን መስራት ትችላለህ… በሳምንት ሃያ አምስት ዶላር ብቻ ለማግኘት? ሞኝነት ነው… በጣም የተለየ ተሰጥኦ አለህ፡፡ በቃላት ላይ የመራቀቅ ተሰጥኦ እንዳለህ መቼም ታውቃለህ … ግን ብትጠቀምበት ምን አለ? … ለአንተ ደግሞ ይኼንን ማድረግ በጣም ቀላል ነው፡፡ ያንን አይነት ረቂቅ ነገር መፍጠር የቻልክ ሰው … አንድ ሁለት ተራ ታሪኮችን መፃፍማ ላንተ በጣም ቀላል ነው፤ ማንም “ፋራ” ያደርገው የለ? … ይሉታል…። ራስህን ማካበድ ተው … መስዋዕት መሆን ያስደስትሃል ወይ?… ይጠይቁታል፡፡ ሚስትህን ተመልከታት … ፡፡ ፖል  ፓቲሰን ማድረግ የቻለውን አንተ እንዴት ያቅትሃል? … ይሉታል …
ፍሎሬት ሉመንን ብቻ ዝም ብለህ አስብ፤ አለው ለራሱ፡፡
የፅሁፍ ጠረጴዛው አጠገብ ተቀምጧል፡፡ እሷ ምን እንደምትፈልግ መረዳት የሚያቅትህ ቢመስልህም … ቀላል ነው፡፡ ከፈለግህ ልትረዳት ትችላለህ፡፡ በጣም ለመራቀቅ አትሞክር፡፡ ተራ ሁን፡፡ እሷን ለመረዳት ተራ እና ቀላል ነገር ነው፡፡ ይኸው ነው፡፡ ስለ ሁሉም ነገር ቀለል አድርገህ አስብ … ቀለል ያለ ታሪክ ፃፍ፡፡ በጣም ቀላል እና ከንቱ ታሪክ፡፡ በፈጠረህ አምላክ! … ቀላል እና ትርኪ ምርኪ የሆነ አንዳች ታሪክ ማሰብ አትችልም?... ምንም ጥቅም የሌለው ታሪክ? አትችልም ወይ? … ይኼን ያህል ግዙፍ ነኝ ብለህ ትታበያለህ?... እንደው ይኼንን ያህል ምርጥ ነህ አንተ? … ምርጥ ከመሆንህ የተነሳ… ጥልቅ፣ ታላቅ እና በጣም መሰረታዊ ከሆኑት ጭብጦች ውጭ መፃፍ አይቻልህም ማለት ነው?... ዘወትር አለምን ከመከራዋ ለመታደግ ነው የተፈጠርኩት ብለህ ለምን ታምናለህ? … ዣን ደ አርክን የመሆን ግዴታ አለብህ?
እራስህን አታታልል፤ አለ አሁንም ለራሱ፡፡ ከፈለግህ ትችላለህ፡፡ አንተ ከማንም ሌላ ሰው የተሻልክ አይደለህም። ሳቁ አመለጠው፡፡ እንዲህ አይነቱ ከይሲ ነህ ለካ!... (አለ እራሱን በራሱ)
ሰዎች በራሳቸው ላይ የመተማመኛ አቅም ሲያንሳቸው ነው “እኔ ከማንም ያነስኩ አይደለሁም” የሚሉት፡፡ ስለዚህ አንተም “ከማንም የተሻልኩ አይደለሁም” ብለህ ራስህን ንገረው፡፡ … ለመሆኑ ይኼንን ትዕቢትህን ከየት እንዳገኘኸው እስቲ ንገረኝ  … ? ይኸው አይደል ችግርህ … ትዕቢት፡፡ ታላቅ ተሰጥኦ ወይንም የላቀ አዕምሮ ሳይሆን ያለህ ትዕቢት ነው የሞላብህ፡፡ ለጥበብ ራስህን መስዋዕት ለማድረግ ብቁ ያልሆንክ ባለሟል ነህ፡፡ በራስህ ምስል ስር የተንበረከክህ፣ ራስ ወዳድነት የሞላብህ ሰው ነህ … እናም ያጋጠመህ ውድቀት የሚገባህ ነው፡፡
ሀሪፍ ነኝ ነው የምትለው? ሀሪፍ ነኝ ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምኑ ነው? … አሁን ለመፃፍ ከራስህ ጋር እየተሟገትህ ያለኸውን የዘቀጠ የምትለውን ነገር ለመጥላት ማን መብት ሰጠህ? … ለወራት አንዳችም ፊደል አልፃፍክም፡፡ አትችልም፡፡ በቃ ፀሐፊነትህ አብቅቶለታል፡፡ ከዚህ በኋላም እስከ ወዲያኛው መቼም ቢሆን አትፅፍም፡፡…
እና አንተ መፃፍ የምትፈልጋቸውን ነገሮች መፃፍ የማትችል ከሆነ … ምን መብት አለህ ሌሎች መፃፍ የሚፈልጉትን ነገር ዝቅ አድርገህ ለማንኳሰስ? ለነገሩ ለማንኳሰስ ብቻ ነው የተፈጠርከው … ታላቅ ዘመን ተሻጋሪ ድርሳናት ለመፃፍ አይደለም፡፡ ስለዚህ፤ ይኼንን ተቀብለህ፣ አመስግነህ አርፈህ መፃፍ ብትጀምር ይሻልሃል … ሞት ተፈርዶበት ፊቱን ለጋዜጣ ገፅ ፎቶ ለማስነሳት እንደሚጠብቅ እስረኛ እዚህ ተጎልተህ ከምትፈዝ … ብትፅፍ ያዋጣሃል፡፡
አሁን ይሻላል፤ አሁን ወጣልኝ … መንፈሴም ተስተካከለ መሰለኝ… ስለዚህ መፃፍ መጀመር እችላለሁ … አለ ራሱን በራሱ፡፡
ግን እንዴት ነው ውዳቂ ነገሮችን መፃፍ የሚጀመረው? … እሺ እስቲ እናስብ … ቀላል የሰው ልጅ ታሪክ መሆን አለበት፡፡ … ሰውኛ ስለሆነ አንድ ተራ ነገር ላስብ፡፡ እንዴት ነው ግን ለተራ ነገር ጭንቅላትን ማሰራት የሚቻለው? …. እንዴት ታሪክ ከተራ ነገር ውስጥ ይፈጠራል? … እንዴት ፀሐፊ መሆንስ ይቻላል፤ ለተራ ነገር?
… በል እንጂ! … ከዚህ ቀደም ፅፈህ ታውቃለህ አይደል? … እንዴት ብለህ ነበር ታዲያ ፅሁፉን የጀመርከው? … ተው ተው … ወደ በፊቱ ፅሁፍህ ተመልሰህ ማሰብ ከጀመርክ ምሬቱ ተመልሶ ይመጣብሀል፡፡ ከመጣብህ ደግሞ ይጨልምብሃል፡፡ ወይንም ሌላ የባሰ ነገር ይከተላል፡፡
“ከዚህ በፊት ምንም ነገር ፅፌ አላውቅም” ብለህ አስብ፡፡ ገና ዛሬ መጀመሬ ነው … በል፡፡ … አዎ … ይኼ አስተሳሰብ የተሻለ ነው፡፡ እንደዚህ አዝረክርከህ ማሰብ ከቻልክ… ትፅፈዋለህ .. አዎ… አሁን እየመጣልህ ነው፡፡
(ይቀጥላል)

Published in ጥበብ
Saturday, 28 March 2015 10:05

የሲኒማ ጥግ

ሴት ተዋናዮች ስለሙያቸው)
በተዋናይነቴ እጅግ አስደሳቹ የትወና ክፍል ዳይሬክተሩን ማስደሰት ነው፡፡ ሁሌም ዳይሬክተሬን ማስደሰት እፈልጋለሁ፡፡
ጆን አን ቼን
ጠንክሬ መስራቴና ግሩም ሥልጠና ማግኘቴ ከአንዳንድ ተፎካካሪዎቼ የተሻልኩ ተዋናይት እንድሆን አስችሎኛል፡፡
ፓላ ኔግሪ
እንደሌላ ሰው የምዘፍን ከሆነ ጨርሶ መዝፈን አያስፈልገኝም፡፡
ቢሊ ሆሊዴይ
ሰዎች ሁለት ነገሮችን ፈጽሞ አይረሱም፡- የመጀመሪያ ፍቅራቸውንና ቀሽም ፊልም ለመመልከት የከፈሉትን ገንዘብ፡፡
አሚት ካላንትሪ
ተዋናይት መሆን አልፈልግም ነበር፡፡ የጥርስ ሃኪም መሆን ነበር ፍላጐቴ፤ ነገር ግን ህይወት የሚያመጣላችሁን አታውቁትም፡፡
ሶፍያ ቬርጋራ
ተዋናይት የምትተውነው ሴትን ብቻ ነው። እኔ ተዋናይ ነኝ፤ ምንም ነገር ልተውን እችላለሁ፡፡
ውፒ ጐልድበርግ (ሴት ተዋናይት)
በዘጠኝ ዓመት ዕድሜዬ ባልጀምር ኖሮ ተዋናይት እሆን ነበር ብዬ አላስብም፡፡
ክሪስቲን ስቴዋርት
ስጀምር ተዋናይት የመሆን ወይም ትወና የመማር ፍላጐት አልነበረኝም፡፡ ዝነኛ መሆን ብቻ ነበር የምፈልገው፡፡
ካታሪን ሄፕበርን
አምስት ዓመት ሲሆነኝ ይመስለኛል ተዋናይት ለመሆን መፈለግ የጀመርኩት፡፡
ማርሊን ሞንሮ
በተዋናይትነት ስኬታማ ለመሆን ሰብፅና በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡
ማ ዌስት
እስከ 45 ዓመቴ ድረስ ፍቅር የያዛት ሴት ሆኜ መጫወት እችላለሁ፡፡ ከ55 ዓመቴ በኋላ አያት ሆኜ እተውናለሁ፡፡ በሁለቱ መካከል ያሉት 10 ዓመታት ግን ለሴት ተዋናይ አስቸጋሪ ነው፡፡
ኢንግሪድ በርግማን
ዝነኛ ተዋናይት መሆን የትልቅነት ስሜት ሊፈጥርባችሁ ይችላል፡፡ ግን እመኑኝ…ቅዠት ነው፡፡
ጁሊቴ ቢኖቼ

Published in ጥበብ

አንድም - ሦስትም
 
(የመጽሐፍ ዳሰሳ)
   ሀብታሙ ስዩም በቀድሞው “አዲስ ጉዳይ” መጽሔት ላይ ሲተነፍሳቸው የነበሩትን ፖለቲካ ዘመም ግሩምሩምታዎች በ176 ገጽ ተምኖ፣ የድርሳን ግርማን አላብሶ፣ ለአንባቢ ካቀረበ ከረምረም አለ። የጥበብ ስራውን ገና በጠዋቱ ለተቀጨችው ለ“አዲስ ጉዳይ” መጽሔት እንደ ዝክር የሚወስዱለት ባይታጡም በጉያው የተሰበሰቡትን አፍላ ታሪኮች መልሶ ለመደባበስ ለፈቀደ አንባቢ ግን ግለታቸው አዲስነትን፣ የእስትንፋሳቸው ሙቀት ትኩስነትን እንደሚያውጁ አያጣውም፡፡ ደግሞም በመጽሔቱ ያልተካተቱ አዳዲስ ሥራዎች እንደ አጃቢ እዚያም እዚህም ስለተሰለፉ ታማኝ የመጽሔቷ አንባቢ ለነበረም ቢኾን ሌላ የንባብ ጉልበት እንደሚሆኑት ይታመናል፡፡ ፖለቲካን በረሃ ሳይወርድ በመጽሐፍ ገጾች ውስጥ ብቻ በስላቅ መልክ ማጣጣም ለመረጠ፣ የሀብታሙ ብዙዎቹ ትርክቶች የሚስማሙት ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉ ላይ የተካተቱት ብዙዎቹ ታሪኮች አንባቢን በስሜት ለማወበራየት የማይሰንፉ፣ ደመ-ግቡ የምናብ ፍሬዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡
ጥልቅ ዳሰሳ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለመልዕክት የሚጨነቁ የሽፋን ምስሎች አልፎ አልፎም ቢሆን ማየታችን ተስፋ ነው፡፡ የሀብታሙ “ማሳቅ፣ ማሳዘን ማሸበር” በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፉ አዲስ የተመረቀ የሰፈር ጥርጊያ መንገድ ይመስላል። በኮብል ስቶን በተዥጎረጎረ ገጽታው ላይ እንደ ኩል በኳሉት ሶስት አንጓ ምልክቶች እየተዘጋ የአንባቢን አምሮት ይለኩሳል፡፡ የቀድሞው ኢቴቪ “ሎጎ”፣ የዘመን ጋዜጣን የስያሜ ቁራጭ እንዲሁም አንድ የወታደር ጫማ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ጎልተው ይታያሉ፡፡ እንደ አንባቢ ሳንወድ በግድ የነዚህን ምልክቶች አንድነትና ልዩነት ለማሰላሰል እንገደዳለን። በርዕስነት የተቀመጡትን ሦስት አንኳር ቃላት (ማሳቅ፣ ማሳዘን፣ ማሸበር) ከነዚህ ሦስት ጉልህ ምልክቶች ጋር እያጋባን፣ ደግሞም እያፋታን እንብሰለሰላለን። የሦስትነትና አንድነቱን ቋጠሮ ለመፍታት በምናደርገው መውተርተር የመጽሐፍ ሽፋኑ ላይ ሳናስበው ጊዜ እናጠፋለን፡፡ የመጽሐፉን አንድ ቅጠል የምንገልጠውም ለዚህ አንኳር መጠይቅ ምላሽ ፍለጋ ነው፡፡
ከሃያዎቹ አጫጭር ታሪኮች ውስጥ “መጽሐፍ እና ሥጋ” የተሰኘው ቀዳሚ ተረክ የዋርካውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ሌሎች ታሪኮች ዋርካውን የተጠጉ ልምላሜዎች አድርገን ልንወስዳቸው እንችላለን። በእርግጥ ልምላሜው ሌጣውን አይደለም፡፡ አብሮት የሚፈካ አበባ፣ የሚጎመራ ፍሬ እዚህም እዚያም ይኖራል፡፡ ሆኖም ዋርካው ላይ በቁመናም፣ በቅርንጫፉም፣ በፍሬም፣ በልምላሜም የሚደርስ ተረክ አላገኘሁም፡፡
“መጽሐፍ እና ሥጋ” የሥጋ ጠኔ ከመንፈስ ጠኔ ጋር የሚሽቀዳደሙበት አውደ ርዕይ ተደርጎ ነው በደራሲው የተሳለልን፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ አንድ መጽሐፍ መደብር በተከፈተች ሌላ ሥጋ መደብር ጋር የሚደረግን ምናባዊ ሙግት እንቃኛለን፡፡ የአለማየሁ ሥጋ ቤትን የሚታደሙት ደንበኞች ኩታገጠም የሆነችውን መጻሕፍት ቤት ቀስ በቀስ ከእነመፈጠሯ  ሲዘነጓት እናያለን፡፡ ታሪኳ የአንባቢን ቁጥር መመናመን ብቻ ሳይሆን ዘመኑ ለስጋ እንጂ ለነፍስ ምግብ ብዙም የማይጨነቁበት እንደሆነ ታመለክታለች፡፡ ይህቺን ታሪክ የደራሲው የሀብታሙ ስዩም የፈጠራ ማማ አድርጌ እወስዳታለሁ፡፡ ገጽ 7 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
“… (ጎረቤቴ) አለማየሁ መጽሐፍ ለመግዛት የመጡ ደንበኞቹን መደብ ሥጋ ማስገዛት የሚያስችል መተት ሳያስቀብር አልቀረም፡፡ ሥጋ ቤቱ በተከፈተ በመጀመሪያው ቀን ወትሮ በሳምንት አራት ውድ መጻሕፍትን የሚገዙኝ ሰዎች ከሱ ሁለት መደብ ሽኮና ገዙና ከኔ ሁለት የተረት መጻሕፍትን ብቻ ገዝተው ሄዱ፡፡ በሁለተኛው ቀን እኒሁ ደንበኞቼ በሱ እልፍኝ ተሰገሰጉ፤ ለእኔ ግን የእግዜር ሰላምታ እንኳ ነፈጉኝ…፡፡”
የሥጋ ቤቱ እና የመጻሕፍት ቤቱ ተቃርኖ የሞት እና ሕይወት ነው፡፡ በላተኛው ስጋ ወይም ሞት ይላል፤ አንባቢው ተሽቀዳድሞ በሚያመነዥጋቸው መጻሕፍት የመብል ፍላጎቱን ይቆልፋል፡፡ አንዱ በአንዱ መቃብር ላይ  ነው የተቀለሰው፡፡ ኋላ ላይ ሥጋ አይሎ መንፈስን እንዴት አድርጎ አሟሙቶ እንደሚገድል በመጻሕፍት ቤቷ ውልደት እና ሞት እንመለከታለን፡፡ ነገሩ እየከፋ ሄዶ የመጽሐፍቱ ገጾች የሥጋ መጠቅለያ እየሆኑ ነፍስ እየተበደለ እንዴት እንደሚሄድ በዚህ ግሩም ታሪክ ጭብጥ ውስጥ ተካትቷል፡፡
ደራሲው “መጽሐፍና ሥጋ” የተሰኘችዋን ታሪክ ለመጽሐፍ መግቢያ መጠቀሙ እንደ ግሩም “አፕታይዘር” አገልግሎታል፡፡ ይቺን ታሪክ አንብበን ከደራሲው ብዙ ሳቅና ስላቅ መጠበቃችን ግድ ነው፡፡ በዚህ የስሜት ከፍታ ሆነን ነው “አባቴ ሲመረቅ፣ እኔ ስረገም” የሚል ታሪክ የምናገኘው፡፡
በርግጥ ከማንበብ የመናጠቡ ልማድም ሆነ የከሸፈ ጥቁር ቆብ ደፊነት በአንድ ማሕፀን የተኙ መንትያዎች ናቸው፡፡ ደራሲው ኮሌጅ መበጠሱን፣ ቆብ መድፋቱን ከሥራ አጥነት እና ከእንዝላልነት ጋር ማጎዳኘትን ቢመርጥም ክስረቱ ሁለንተናዊ ስለሆነ ይሄኛውም ውድቀት ሌላ መገለጫው ነው፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ድሮ ዲፕሎማ መድፋት ዛሬ ማስተርስ ከመድፋት የበለጠ ክብር እንደነበረው ደራሲው የአባቱን ዲፕሎማና የሱን ማስተርስ ተምሳሌት አድርጎ በቁጭት ይነግረናል፡፡
በሀብታሙ መፅሐፍ ውስጥ የታሪክ አደራደሩ ተስማምቶኛል፡፡ ሆን ተብሎ ይሁን በአጋጣሚ እንጃ እንጂ 20 ታሪኮች የተቀመጡበት ፍሰት ስሜት የሚሰጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ የፊተኞቹ ታሪኮቹ መጋቢ ናቸው፡፡ በአመዛኙ አንዱ ታሪክ የሌላው ውጤት ነው፡፡ ለምሳሌ በመጀመርያው ታሪክ ይህ ትውልድ ከመጽሐፉ ይልቅ ሙዳ ሥጋ አብዝቶ መውደዱን የሚናገር ሆኖ፣ በሁለተኛው ታሪክ ደግሞ የዲግሪና ማስተርስ ቆቦች በሥጋ በተለበጡ “ቀፎ” ጭንቅላቶች ላይ የተደፉ የሸክላ አክሊሎች እንደሆኑ የሚነግረን ታሪክ ይከተላል። ይህም “አባቴ ሲመረቅ፣ እኔ ስረገም” በሚል ርዕስ ስር የተቀመጠ ነው፡፡ ሁለቱ ታሪኮች  በርእስም በይዘትም የሚያገናኛቸው ነገር ባይኖርም በጭብጥ ደረጃ ግን መንስኤና ውጤት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ነገሩ በዚህ ብቻ አያበቃም። በሦስተኛው ታሪክ (“ኳስና ፖለቲካ” ይሰኛል) መጽሐፍ የማይሚገልጠው ትውልድ የልብ ልብ የሰጣቸው ፖለቲከኞች ቅሪላ ሊያለፉ ከኮምቦሎጆ ወርደው እናያለን፡፡ በርግጥም በሥጋ የሰባ ሰውነት ካምቦሎጆ መውረዱ የሚጠበቅ ነው፡፡
“ኳስ እና ፖለቲካ” ብሎ በሰየመው  በዚህ ግሩም ተረክ፣ ደራሲው ከንጉሡ ጀምሮ በነበሩ ሦስት መንግስታት የእግር ኳስ ቀጥታ ስርጭት ምን ይመስል እንደነበር የሚነግረን  ይምሰል እንጂ ማውጠንጠኛው አሁንም ጭልጥ ያለ ፖለቲካዊ ስላቅ ነው፡፡ የእግር ኳስ ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ የምንኮመኩም ቢመስለንም ተለውሶ ወደ ጆሯችን የሚንጠፈጠፈው ግን የፖለቲካ ጠብታ ነው፡፡ በርግጥ ጽሑፉ ያስቃልም፣ ያሸብራልም ያሳዝናልም፡፡ ይኸ ተረክ በፖለቲካዊ መልዕክቱም ሆነ ፈገግታን በማጫር የተሳካለት ነው ማለት ይቻላል። እዚህ ታሪክ ላይ ስንደርስ ነው ታዲያ በዐይናችን ማንበባችንን ገታ አድርገን ጆሯችንን የምናነቃው። የየዘመኑ የቅሪላ ለፋፊ (“ኮሜንታተር”) ድምጸት ለመለየት ጆሯችን አቅም ሲከዳው ደግሞ የምናባችንን ጉልበት ለመጠቀም እንታትራለን፡፡ ቁርበት ቁርበት ከሚለው ፖለቲካዊ ልፊያ የምንቃርመው ፈገግ ብሎ አፍታም ሳያቆዩ ፊትን ማደምን ነው፡፡ “ማሳቅ ማሳዘኑ” ስጋ ለብሶ ከፊት ለፊታችን ገጭ የሚለው ታዲያ ይሄኔ ነው፡፡ ገጽ 22 ላይ የሰፈረውን በምሳሌነት እናንሳ፡-
ጨዋታው የሚካሄድበት ዘመን - ዘመነ ጃንሆይ
ጨዋታው የተካሄደበት ቦታ - ጃንሜዳ
ጨወታውን የሚያንበለብለው ጋዜጠኛ - የጃንሆይ አሽከር
በመላው ጠቅላይ ግዛቶች የምትኖሩ በጃንሆይ መልካም ፈቃድ ራዲዮ የተሰኘውን ታምር ተጠግታችሁ የጃንሆይ ቡድን የሚያደርገውን ይህንን ጨዋታ ለማድመጥ ያቆበቆባችሁ የጃንሆይ አሽከሮችና ሌሎች … እንደምን አመሻችሁ፡፡ የጎዣም አድማጮች “እግዜር ይመስገን!” የማትሉ ጥጋብ ነው? ዋ! ጭስ እንጂ ጭሰኛ ማምለጫ ያለው መስሎሻል፡፡ በላይ ዘለቀ ለምን ተሰቀለ ብላችሁ ነው እንዲህ ምትጀበረሩ?
ለማንኛውም የሁለቱን ቡድኖች አሰላለፍ ከዚህ እንደሚከተለው እንገልጻለን፡፡
1ኛ. የግራዝማች ሞገሴ ልጅ ዳኛቸው ሞገሴ
2ኛ. የብላታ ዳርጌ የአጎት ልጅ አስታት ቢልልኝ
3ኛ. የነጋድራስ ባንት ይርጉ ውሽማ ዘበነ አስተስ
ከላይ የዘረዘርኳቸው ሀገር የመሰከረላቸው የጨዋና የመኳንንት ልጆች ሲኾኑ የሌሎችን ግን የመጫኛ ነካሽና የሸማኔ ልጆች እንደመሆናቸው ቢጠሩም ባይጠሩም ለውጥ ስለሌለው በቀጥታ ወደ ማላጋሲ ቡድን አሰላለፍ በንጉሡ ፈቃድ እሄዳለሁ፡
ደራሲው በድቡልቡሏ ኳስ አሻግሮ የሚለጋቸው ፖለቲካዊ ስላቆች ግሩም ፖለቲካዊ ጎሎችን የሚያስቆጥርባቸው ናቸው፡፡ የሦስቱ መንግስታት የካሞቡሎጆ ልፊያ ማሳደጊያ ባዶ ለባዶ ውጤት ነው፤ ምንምነት፡፡ በብዙዎቹ ተከታይ ታሪኮች የደራሲውን ለቀቅ ያለ አጻጻፍ እንታዘባለን፡፡ ምናብ እና አፍላ ፍቅር በሚፈጥሩት ሽኩቻ ውስጣችን አብዝቶ ይፈግጋል። በአጫጭር ዐረፍተነገሮች ውስጥ የሚፈነዳውን ጭብጥ እናደንቅለታለን፡፡ ለምሳሌ “83ን መጠበቅ” ብሎ በሰየመው ተረክ  የመጀመርያ አንቀጽ ደራሲው  በከተማ ድህነት ላይ እንዲህ ይቀኛል፡-
“ሀብታሞች አንበሳ አውቶብስን የድሃ መጋዘን ይሉታል፡፡ ድሆች “የጭቁኖች ባቡር” እያሉ ያቆላምጡታል፡፡ እኔ በበኩሌ “ክርስቶስ” እለዋለሁ፡፡ መምጫው አይታወቅም፡፡ ጠባቂዎቹ  ግን ብዙ ነን።” (ገጽ-32)
ብዙ አንቀጾች ላይ ደራሲው ቀልድ ሲመዠረጥ አይሰስትም፡፡ ምናባዊ ምልልሱ ሲናኝ አይጎረብጥም፡፡ ሁሉም ለስለስ ብሎ ከአንጀት ይደርሳል፡፡
እንደ ስንቅ የያዝነው ፈገግታ ሲሟጠጥብን ተዋከቦ ፊት ለፊታችን የሚደነቀረው “ባለቆቡ ወጣት” የተሰኘው ንኡስ ታሪክ ነው፡፡ “ባለቆቡ ወጣት” የቆመበት ፌርማታ ለአእምሮ ሰላም የሚሰጥ ስፍራ አይደለም፡፡ አጓጉል ትካዜን የሚያጭር፣ የድብርት ቆሌን የሚያስነሳ፣ የሐዘን ማቅን እንደ ጃኖ የሚያከናንብ ኬላ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማሸበር ከቃል ጨዋታ አልፎ የውስጥ ስሜትን ለመደቆስ ይሰናዳል፡፡ ከፍቅር ጭወውቱ አደባባይ ተስተጓጉለን ጫፉ ወደማይታይ ሸለቆ ውስጥ እንወረወራለን፡፡ ገጽ 130 ላይ ከሰፈረው በጥቂቱ፡-
“…አምባገነንነት ከመጠን በላይ ከመመለክ ፍላጎት የመጣ በሽታ ነው፡፡ ጨካኝነት ከመጠን በላይ ከመፍራት ፍላጎት የመነጨ ደዌ ነው፡፡ ውሸታምነት ከመጠን በላይ ከመሞገስ ፍላጎት የመነጨ ወረርሽኝ ነው፡፡ በተመሳሳይ መጨቆን ከመጠን በላይ ዝም የማለት ውጤት ነው፡፡ መረገጥ ከመጠን በላይ የመፍራት ዳርቻ ነው፡፡ መበደል ከመጠን በላይ የመለጎም መጨረሻ ነው፡፡ የሰው ልጆች ልካቸውን ቢያውቁ አሊያም ልካቸውን እንዲያውቁ ቢደረግ ዓለም ያየቻቸው እጅግ አስከፊ ምዕራፎች ቀድሞውኑ አይታሰቡም ነበር፡፡” (ገጽ 130)
የደራሲው “ኤርትራዊው” ገጸ ባህሪ ተስፋዚጊ ይባላል፡፡ ተስፋዚጊ የመወለድ ቋንቋነትን ከቃል ባለፈ በተግባር በተከፈለ የሕይወት መስዋዕትነት ያስተምረናል፡፡ ተስፋዚጊ እንደ ረመጥ የሚፋጅ የሃገር ፍቅርን ገዢዎች ሚዛን ሰፍረው፣ ደረጃ አውጥተው የሚያድሉት ራሽን አይደለም ይለናል፡፡ ለተስፋዚጊ ታላቅነት እማኝ ከሚሆኑ አንቀጾች መካከል በገጽ 138 ላይ የሚገኘውን እንመልከት፡-
“የአያቴ የቅድመ አያቴ ሀገር አሁንም የምኖርበት ነው፡፡ ወሰኑን የጠገቡ አንዴ ሲያሳጥሩት፣ አንዴ ሲለጥጡት፣ የሚለጠጥም ኾነ የሚጠብ ማንነት የለኝም፡፡ የጃንሆይ ሕፃን፣ የደርግ ጎልማሳ ነበርኩ፡፡ ኤርትራዊያን ስንት ግፍ እንደደረሰባቸው አውቃለሁ። ይሄ ግፍ የደረሰው ኤርትራዊ ስለኾኑ አልነበረም። በጨቋኝ መሪ ስር ከነበሩ የታሪክ ተጋሪዎች ውስጥ ስለነበሩ እንጂ፡፡ ኤርትራ ውስጥ ካለቀው ወጣት ያልተናነሰ ጐንደር ቀብራለች፡፡ ሰው በእግዜር ደንብ ማረኝ ተብሎ እስኪለመን ድረስ፡፡ አብዮት የበላው የአሰብን ወጣት ብቻ አልነበረም፡፡ አብዮት ሁሉን በልታለች፤ አብዮት ሆዳም ናት፡፡” የተስፋዝጊ ነፍስ ወሰን፣ አጥር ለመሻገር ትቃትታለች፡፡ በጣምራ ዜግነት መካከል እንድትጓጉጥ ወጀቡ፣ ውዥንብሩ ቢያጥበረብራትም የማኅተቧን ክር እንዳጠበቀች እስከ ወዲያኛው ታሸልባለች፡፡
መጽሐፉን ያሳሱት ገጾች
ሀብታሙ ስዩም “ተስፋ የሚጣልበት ቀልድ ፈጣሪ ነው” ብለን ለመደምደም አራት ነጥቦችን ስናፈላልግ ባልገመትነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ራሱ አውጥቶ ከሰቀለን የሳቅ ማማ ገፍትሮ የሚጥለን ደራሲ ነው። ፖለቲካዊ ስላቅ (Political satire) አሳክቶ መጻፍ፣ ጽፎም ማሳቅ፣ አስቆም መራር መልዕክት ማስተላለፍ ጥቂቶች ብቻ የሚታደሉት ትልቅ ጥበብ ነው፡፡ ሀብታሙ ስዩም በዚህ ጥበብ ደጅ ላይ ሆኖ የሚያንኳኳ ጀማሪ ፀሐፊ ይመስላል፡፡ ሆኖም በሩ እንዳይከፈትለት ያደረጉት ብረት መዝጊያዎችን መጠቋቆም በጐን ከሚመኝ ሀያሲ የሚጠበቅ ነው። አንዱ የደራሲው ማነቆ በጽሑፎቹ ውስጥ ጊዜና ሁኔታን ያላገናዘቡ መናኛ ቧልቶችን መርጨቱ ነው። ቧልቶቹ በግድ የተፈጠሩ ስለሆኑ አይወሃዱንም፡፡ እንዲያውም ይጐረብጡናል፡፡ የሳቅና የምቾት ጉዟችንን የፒስታ መንገድ ያደርጉብናል። ሄዶ ሄዶ መንገጫገጭ!
በርግጥም ደራሲው ውብ ታሪኮችን አጥምዶ በሳቅ ሊያፈነዳን ልባችንን ሰቅሎ ሲያበቃ በነዚህ መናኛ ቧልቶች ምክንያት ሳቅ አምካኝ ሆኖብን ያስቸግረናል። ለአብነት የሚሆኑ ጥቂት አረፍተ ነገሮችን ልጥቀስ፡-
“መጽሐፍና ሥጋ” በሚለው ታሪክ (ገጽ 9) ላይ የሥጋ ነጋዴውን አለማየሁን ሸንቋጭነትና የንግግር ግብረ መልስ በቀልድ መልክ ለመግለጽ ደራሲው እንዲህ ይላል፡-
“የአለማየሁ መልስ ከአለማየሁ ቴዎድሮስ አጽም አለመመለስ በላይ ያበሳጫል”
(ደራሲው አለማየሁ የሚለውን ስም በግድ ከአፄ ቴዎድሮስ ልጅ አለማየሁ ጋር አዛምዶ ሊያስቅን በከንቱ እንግሊዝ አገር መዳከሩ እኛ አንባቢዎቹን ያበሳጫል፡፡)
በገጽ 41 ላይ፡ “ታጋዩን በጥንቃቄ አስተዋልኩት፡፡ እንዴ…እንዴ! ይሄ የማየው ዋልተንጉስ አይደል እንዴ። አይ ዋልተ ንጉስ! ዋልተ ንጉስ ማለት በስልጠና ላይ እያለን ደንግጦ ሱዳን ከገባ በኋላ ለዓመታት ያላየነው ጓድ ነው፡፡ እሱን ብሎ ጓድ፤ ጉድ ብለው ይሻለኝ ነበር”
(“ጓድ” እና “ጉድ” የሚሉ ቃላትን በማገናኘት ሳቅ ለመፍጠር የተሞከረ፣ ነገር ግን ያልተሳካ ጥረት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ሁለት ተመሳሳይ ቃላትን አገናኝቶ ሳቅ መፍጠር ሁለት ባልጩት ድንጋዮችን አጋጭቶ እሳት የመፍጠር ያህል ቀላል እንዳልሆነ ደራሲው ብዙም የተረዳው አይመስልም፡፡)
ምናልባት ደራሲው ይህን ዘዬ እጅግ በተሳካ ሁኔታና በተገቢው ቦታ መጠቀም አለመጠቀሙ ለራሱ እምብዛምም ላይታወቀው ይችል ይሆናል። እንዲያ ከሆነም ተመሳሳይ ቃላት በማጋጨት ሳቅ የመፍጠር አቅሙን ምን ያህል እንደተሳካለት ለወዳጅ እያስነበበ ቢያስመሰክር ቀሪ አንባቢን ከሰቀቀን መታደግ ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ በርግጥ ሀብታሙ በዚህ ቃላትን አመሳስሎ በማጋጨት ሳቅን የመፍጠሪያ ዘዴ ተጠቅሞ ያሳካው ምንም አረፍተነገር የለም አይባልም፡፡ ሆኖም ከተሳኩለት ይልቅ ያልተሳኩለት ይበዛሉ፡፡ ደግሞም በኮሜዲ ዘውግ ከሺ ሳቅ ይልቅ አንድ የሳቅ ምክነት ጐልታ መታየቷ እሙን ነው፡፡
በነገራችሁ ላይ ቃላት እያጣመሙ ቀልድ የመፍጠር ስልት በምዕራቡ ዓለም malapropism እየተባለ ነው የሚጠራው፡፡ ይህ ዘዬ እንደ ቀልድ ዘውግ የተዋወቀው በ1775 በሪቻርድ ብሪንስሌይ የኮሜዲ ሥራ አማካኝነት ሲሆን ምዕራባዊያኑ ገና ድሮ ሳቃቸውን አንጠፍጥፈው የጨረሱበት የአቀላለድ ዘዴ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ወቅታዊነት ችግር
አንዳንድ ታሪኮች የወቅታዊነት ችግር ይስተዋልባቸዋል፡፡ ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከጋዜጣና ከመጽሔት ወደ መጽሐፍ በሚመለሱ ብዙ የጥበብ ሥራዎች ላይ የማስተውለው ድክመት ነው። በደራሲ ሀብታሙ ስዩም ሥራ ውስጥ ለዚህ እንደ አብነት የምወስደው “አሮጌ፣ አረቄ፣ አዲስ ዓመት” የሚለውን ታሪክ ነው፡፡ ታሪኩ ስለ አዲስ ዓመት ዋዜማ ነው የሚያወራው፡፡ ታሪኩ በተጻፈበት ወቅት የነበሩ አሁን ግን ስሜት የማይሰጡ ጉዳዮችን ደጋግሞ ያነሳል፡፡ “አፈር ስሆን ወደ ሳኡዲ እንዝመት” የሚለው ፅሁፍም እህቶቻችን ከሳኡዲ በ“ግፍ” በተባረሩበት ወቅት የተፃፈ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡  ተመሳሳይ ችግር ያስተዋልኩበት “ማንዴላ ሞቷልና እንደንስ” የሚለው ጽሑፍ ነው፤ ይህም የጊዜ ልኬት አፈር ድሜ ያስጋጠው ጽሑፍ ሆኗል፡፡ ሀብታሙ ሥራዎቹን ጥሩ አርታኢ ቢከረክማቸው ኖሮ ችምችም ያሉ ተክሎች በሆኑለት ነበር፡፡ እንዲህ ጊዜ ያጠወለጋቸው ከአረም ያልተናነሱ ታሪኮችም ተቆርጠው መውጣታቸው አይቀርም ነበር ስል ተመኘሁ፡፡
ፋታሊዝም /ጨለምተኝነት/
የሀብታሙ ስዩም “ማሳቅ፣ ማሳዘን፣ ማሸበር” የገዢውን ፓርቲ ጉድፍ በአጉሊ መነጽር የሚያሳይ ፖለቲካዊና ልቦለዳዊ የሥነ - ጽሑፍ ሥራ ነው ብዬ ማጠቃለል እችላለሁ፡፡ ይህ የጥበብ ሥራ መንግሥትን የማይተቸው “ማውጫ” በሚለው ክፍል ላይ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ደራሲው ወዳጆቹን እጅ በሚነሳበት የምስጋና ገጹ እንኳን የመንግሥትን ጨቋኝነት ጠቆም ለማድረግ የሚታትር ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከመግቢያው እስከ መውጪያው የናኘው ታሪክ ተስፋ የነጠፈበት ጭጋጋማ ከባቢ አድርጐታል። ብንስቅም ተስፋን አናይም፡፡ በእርግጥ ደራሲው ወደ ሌሎች ዘውጐች ዘው ብሎ ሌሎች ምልከታዎችን በማቀበል ጭጋጉን በተወሰነ ደረጃ እየገፈፈ፣ በስሜት ሽቅብ ወደ ላይ የመሰቀላችንን መጠን ማሳደግ ይቻለው ነበር፡፡ “መጽሐፍ እና ሥጋ” እንዲሁም “የዘገየው ዓላሚ”ን በከወነበት እጁ ሌሎች ተመሳሳይ ማኅበራዊ ጦሶችን በሳቅ ክዳን ቆርቆሮ ቢቀልስልን ምንኛ ባፍነከነከን ነበር፡፡
ክረት የተጠናወተውን ውጥንቁጥን የፖለቲካ ምህዳር በቀልድ ለመገዳደር መሞከር ትልቅ ወኔን ይጠይቃል፡፡ በእዚህ ረገድ ደራሲ ሃብታሙ ስዩም ብዙ ርቀት ተጉዞ ፈር ቀዶልናል፡፡ የማኅበረሰብን ህመም፣ የሕዝብን የተዳፈነ እሮሮ በቧልትና ስላቅ ውስጥ አሾልኮ ለዚያው ማኅበረሰብ ማቀበል መታደል ነው፡፡
በአጠቃላይ ደራሲው ይህ ሁለተኛ ሥራው እንደመሆኑ፣ ከዕድሜ ጋር ስክነትን፣ ከጊዜ ጋር ብስለትንና ጥበብን የመታደል እድል እንደሚኖረው በመገንዘብ፣ በርግጥም ተስፋ የሚጣልበት ወጣት እንደሆነ ለመመስከር ጉልበት እናገኛለን፡፡

Published in ጥበብ

የድምፃዊና ግጥምና ዜማ ደራሲ ጌትሽ ማሞ “ትወደኛለች” የተሰኘ ሁለተኛው የሙዚቃ አልበም የፊታችን ረቡዕ እንደሚለቀቅ ተገለፀ፡፡ የዛሬ 6 ዓመት ባወጣው “እያሴ” የተሰኘ የመጀመሪያ አልበሙና “መብቴ መብቴ ነው” በሚል ተወዳጅ ነጠላ ዜማው የሚታወቀው ድምፃዊው፣ በአዲሱ አልበሙ 16 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን ከአንዱ ዘፈኑ በስተቀር የቀሪዎቹን 15 ዘፈኖች ግጥምና ዜማ ራሱ እንደሰራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሙዚቃውን በማቀናበር ሰለሞን ሃ/ማሪያም፣ ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሚካኤል መለሰና ማሩ አለማየሁ እንደተሳተፉበትም ተገልጿል፡፡ ድምፃዊ ጌትሽ ማሞ ለተለያዩ አንጋፋና ወጣት ድምፃውያን ግጥምና ዜማ በመስጠት ይታወቃል፡፡

   ጋለሪያ ቶሞካ 14ኛውን የስዕል ትርዒት “ውስጣዊ ግለትና እንፋሎት” በሚል ርዕስ የፊታችን አርብ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሳር ቤት ካናዳ ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ቤተ ስዕል እንደሚከፍት ተገለፀ፡፡ በዚህ ትርኢት የወጣቱ ሰዓሊ አሸናፊ መስቲካ ከ35 በላይ ስራዎች ለዕይታ እንደሚቀርቡ የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ አስታውቋል። ሰዓሊው ዓለም በተቃርኖ የተሞላች መሆኗንና አንድ ሰው ከውጭ የሚያሳየው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በውስጡ ምን ሊመስል እንደሚችል የተረዳውን እሳቤ በስራዎቹ ለማንፀባረቅ ሞክሯል ተብሏል፡፡
የስዕል ትርኢቱ ለሁለት ወራት ለህዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ሚያዚያ 25 ከረፋዱ አራት ሰዓት ጀምሮ በሰዓሊው የአሳሳል ጥበብ፣ ፍልስፍና እና ለእይታ በቀረቡት ስዕሎቹ ዙሪያ ውይይት እንደሚካሄድ የጋለሪያ ቶሞካ አርት ዳይሬክተር ሰዓሊ እሸቱ ጥሩነህ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡

ውዝዋዜ ስልጠና ትሰጣለች
የኢትዮ ሲኒያ ፕሮሞሽን እና ኤቨንትስ መስራችና ዳይሬክተር ተወዛዋዥ ጌታነህ ፀሐዬ ከሶስት ወራት በኋላ በመላው ኢትዮጵያ የሚቀርበውንና በየዓመቱ የሚቀጥለውን “አንድነት የውዝዋዜ ፌስቲቫል” ለማዘጋጀት ሲያስብ ከአገሯ ከወጣች 22 ዓመት ያስቆጠረችው የውዝዋዜ ንግስት እንዬ ታከለ በህይወት እንዳለች አያውቅም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ዘንድሮ የሚቀርበው የውዝዋዜ ፌስቲቫል መታሰቢያነቱ ለእስክስታ እመቤቷ ደስታ ገብሬና ለውዝዋዜ ንግስቷ እንዬ ታከለ እንዲሆን የወሰነው፡፡
“እንዬ በህይወት መኖሯን ስሰማ በቀጥታ አድራሻዋን ወደማፈላለግ ነው የገባሁት” ያለው ጌታነህ፤ አድራሻዋን ካገኘ በኋላ ሊያዘጋጅ ባሰበው ፌስቲቫል ዙሪያ በጥልቀት ተወያይተው በመስማማቷ ከኢትዮጵያ ከወጣች ከረዥም ዓመታት በኋላ ሰሞኑን ወደ አገሯ ልትመጣ እንደቻለች ገልጿል፡፡
እንዬ ወደ አገር ቤት ከተመለሰች በኋላ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አራተኛው የግንባታ ዓመት በዓልን አስመልክቶ በሚሊኒየም አዳራሽ በሚዘጋጀው ኮንሰርት ላይ ስራዋን እንድታቀርብ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጥያቄ እንደቀረበላት ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮ ሲኒያ ፕሮሞሽንና ኤቨንትስ ባለቤት እና አርቲስት እንዬ ሰሞኑን በደብረዳሞ ሆቴል በሰጡት መግለጫ ላይ አርቲስቷ ለህዳሴው ግድብ 4ኛ የግንባታ ዓመት ስራዋን ለማቅረብ ፈቃደኛ እንደሆነች ጠቁማ “ድሮም አገራችን በረሃብ በተጠቃች ጊዜ ለረዱን የውጭ አገራት ምስጋና ለማቅረብ እስክስታ መትቻለሁ፤ የህዳሴው ግድብም የአገር ጉዳይ በመሆኑ እስክስታ እመታለሁ” ብላለች፡፡
በኢትዮጵያ በታዩት ለውጦች መገረሟን የጠቆመችው እንዬ ከረዥም ዓመታት በኋላ አገሯን ለማየት በመብቃቷ መደሰቷን ገልፃለች፡፡
የመጀመሪያው ዙር “አንድነት የውዝዋዜ ፌስቲቫል” ከሶስት ወር በኋላ በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ በጐንደር፣ በመቀሌ፣ በድሬደዋና በአዳማ እንደሚካሄድ የገለፀው አዘጋጁ ተወዛዋዥ ጌታነህ፤ በፌስቲቫሉ ላይ ለመታደም የሚፈልጉ የመግቢያ ትኬቱን ፌስቲቫሉ ከመካሄዱ አንድ ወር ከ15 ቀን ቀደም ብለው መግዛት እንዳለባቸው ጠቁሞ ከትኬቱ ጋርም በእንዬ አሰልጣኝነት የተሰራ የውዝዋዜ ሲዲ አብሮ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል፡፡
“ፌስቲቫሉ እስኪደርስ ባለው የአንድ ወር ተኩል ጊዜ ውስጥ ታዳሚዎቹ ውዝዋዜዎቹን እየተለማመዱ ቆይተው ፌስቲቫሉ ሲከፈት የውዝዋዜ ትርኢቱን ከእንዬ እኩል እየተወዛወዙ ዝግጅቱን ያደምቁታል” ብሏል ጌታነህ። ፌስቲቫሉ በቋሚነት በየአመቱ እንደሚካሄድ የገለፀው ጌታነህ፤ ፌስቲቫሉ አንድነታችንን በውዝዋዜና በብሔር ብሔረሰቦች መካከል በሚደረግ የባህል ልውውጥ ለማጠንከርና ለሙያውና ለሙያተኞቹ ክብር ለመስጠት ዋነኛ መሳሪያ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

Saturday, 28 March 2015 09:54

ወደ ምንጭ መመለስ

 መኝታ ከያዘበት ማንኩሽ ኢንተርናሽናል ሆቴል ወደ ሐይቁ ለመድረስ ምን ያህል ደቂቃ እንደሚያሽከረክር ለመገመት ሞከረ፡፡
“…ምን ነካኝ!? በፍጹም በዚህ ስሜት ውስጥ ሆኜ መኪና ማሽከርከር ጥሩ ስላልሆነ በሹፌር መሄድ አለብኝ!...” ስልኩን አንስቶ ደወለ፡-
ከ35 ዓመት በኋላ ነው ወደ ሐገር ቤት የተመለሰው፤ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ተሰምቶታል። እየተገነባ ባለው ፌዴራላዊ ከተማ ተገርሟል። በተደጋጋሚ “እኛ ኢትዮጵያውያኖች እዚህ እንደርሳለን ብዬ አላስብም ነበር!!” ይላል፡፡ ለውጣችን ያስገርመዋል፣ ያስደንቀዋል።
“ይህች የህዳሴውን ሐይቅ ተገን አድርጐ የተፈጠረችው ከተማ የነገዋ ኢትዮጵያ ተምሳሌት ናት! ማህበራዊ ስነልቦናችንን፣ ቀደምት ኪነ-ሕንፃዎቻችንና የምዕራባውያንንም መልካም ስልጣኔ ያካተተች ምርጥ ከተማ…” ይላል፡፡
“ብዙ ነገር ተቀይሯል!” ሲሉት፣ “እሰይ እንኳን የተቀየረ…ህይወት እንደዛ ነው!...ሐገር ወይ በበጐ አልያም በመጥፎ ትለወጣለች…የእኔም ሐገር ይኸው ተለውጣለች፡፡ ድንገተኛ ለውጥ ያስደነግጣል… ያስበረግጋል፡፡ አብዮት አልሰመረልንም፣ ዝግመተ ለውጥ አልተሳካልንም፡፡ ይህ ለውጥ ግን መንፈሳዊ ነው፤ መንፈሳዊ! ሳዖል ወደ ጳውሎስ የተቀየረበት ለውጥ፤ ሸንበቆን ወደ ዓለትነት የቀየረ መንፈሳዊነት። ሕብረት… እለዋለሁ…፡፡” ይህንን ሲናገር ገጽታው ማለዳንም፣ የጀንበር መጥለቅንም ይመስላል፡፡ ማለዳ ቀን ይዞ ይመጣል፤ የጀንበር መጥለቅም ከዋክብትን ጨረቃንና ነገን፣ አልፎ ተርፎም ያልተመረመረውን ጨለማ፡፡
የሐገሩ ፖለቲካ አይገባውም ነበር፡፡ አይገባውም አያውቅም አይደለም፡፡ ሐገርን፣ ብሔራዊ ተቋማትንና ብሔራዊ ስሜትን ግን ኑሮውና ደመነፍሱ አስተምሮታል፡፡ ቡድነኝነትን ይፀየፋል፣ ጐጠኝነትና ጠባብነት አይመጥነውም፡፡ እሱ የሰው ልጅነት፣ እሱ ኢትዮጵያዊነት፣ እሱ አባያዊነት፣ እሱ ውሃነት ነው። የሚሄድም፣ የቆመም፣ የሚከተርም ውሃ ነው፡፡ ጠረን የለውም፤ ቀለም የለውም…ድምፅ እንጂ ቋንቋም የለውም፡፡
ይህ ማለት እኔነቱ የለም ማለት አይደለም፡፡
የተወለደበት መንደር፣ ያደገበት ቀዬ፣ ከእናቱ ማኅፀን ሲወጣ የሸተተው አፈርና ምርጊቱን ዘልቆ የማገው የቀርከሃ፣ የሰንበሌጥ፣ የማንጐ፣ የሙጫና የቴምር ጠረን እሱነቱ አይደለም ያለው ማነው??
የመንደሯ አዛውንቶች እነ አባ አልናስር፣ እነ አባ አልጠይብ፣ እነ እማ ሀጀጀ..እማማ ከልቱም ከነፍሱ የተቋረቡ ናቸውና እንደምን ይተዋቸው??
“አሁን ጠይሟና መሀኗ የእናቴ ጓደኛ፣ እማማ ከልቱም አልወለዱኝምና እናቴ አይደሉም ልል ነው??...” ሲያስበው እንኳን ያንገሸግሸዋል፡፡ ይህ ተፈጥሯዊው ደሴትነቱ ነው፡፡ ይህ ደሴትነት ሁለንታ ነው፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊነቱ ነጠላ ሰደንቅ ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነት የተገነባባት ጡብ ነው፡፡
አይኖቹ ቦዘዙ፡፡ ላዕላይ አምሮቱ ከማንጐ ዛፍ ላይ ተሰንቅሮ ቀረ፡፡ የእጆቹ ጣቶች ግን አሁንም የሸበቱ የአገጭ ፂሞቹን ይፈልጋሉ! ረጅሙን የመሐል ጣት አንጓ በባህላዊ መንገድ የሚሰራው የበርታዎች የወርቅ ቀለበት ጋርዶታል፡፡ ነፀብራቁ ግን ለጣቶቹ ግርማን ሰጥቷል፡፡
አእምሮው ሸፈተበት፡፡
ለእናቱም ለአባቱም ብቸኛ የስጋ ልጃቸው፡፡ ነው ዘወትር ስለማይገባውና ስለተደጋገመው የአባቱ ምስል ያስባል፡፡ ለጋ፣ ልስልስ ያለና የወዛ ጥቁር ፊት አላቸው። ከእራሳቸው የማያወርዱት የሙስሊሞች ቆብ፣ ሰርስረው የሚያዩ፣ በትንንሽ አይኖች ላይ ሰፊና ጥቋቁር ብሌኖቻቸው ይመጡበታል፡፡
አምስት ሜትር በስምንት ሜትር በምትሆን የመንደሯ ጉሊት ላይ ከሱዳን የመጣ ስኳር፣ ኦሞ፣ ቡና፣ ጨው፣ ክብሪት፣ ዛላ ሚጥሚጣ፣ ቲማቲም፣ ሸንኮራ እና የተለያዩ ቀለማት ያሏቸው እንደ ኳስ የተድቦለቦሉ የሱፍ ክሮች ተዘርግተው ይሸጣሉ፡፡ አባቱና ሁለት አዛውንቶች ሶስት ማዕዘን ሰርተው፣ ከመሬት ስንዝር ከፍ በምትል ከቀርከሃና ከቆዳ በተሰራች በርጩማ ላይ እግራቸውን አጠላልፈው ይቀመጡ ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ኅብር በልጅ አእምሮው አይገለጥለትም ነበር፡፡
ከሁሉም ተለይቶ ይህ ምስል ለምን በአእምሮዬ ተነቅሶ እንደቀረ ሊባኝ አልቻለም?”
የተደወለለት ሹፌር መጣ፡፡ ሰላምታውን በፈገግታ መለሰ፡፡ የመኪናውን ፍጥነት እየሸሹ ወደ ኋላ የሚቀሩት አሁኖቹ፣ በልጅነቱ ትዝታ ተተኩ፡፡
የዱር ሙጫ የቀለመበትን፣ ቀርከሃ የሸፈነውን ምድር፣ የማንጎውን ደን፣ የአባይን ወንዝ፣ ከፀሐይ ይሁን ከሰው ዓይን ለመከለል በግራና በቀኝ የጋረዱትን የቴምር ዛፎች፣ የታጠበባቸውን የበለስ፣ የአይማ፣ የዳቡስ፣ የሸርቆሌና የጡነት ወንዞችን አሰበ።
ልጅነት ምንድነው? ልጅነት ማነው? ምንድነው ራሱ ማነው? ማነው ራሱ ምንድነው? ከትዝታህ ውስጥ እውቀትህ ምን ያህሉ ነው? ወይስ ትዝታህ ውስጥ እውቀትህ የለም?
“…ከሩቅ! ከሩቅ! አቧራ እያስነሱ የሚመጡትን መኪኖች ስናይ እንፈነድቃለን፡፡ አይኖቻችን ደካሞች ናቸው፤ የሚመጡትን መኪኖች እንዳናይ መሐላችን ገብቶ የሚያጥበረብረን ብርሃን ይከልለናል፤ እንበሳጫለን፡፡ የልጅነት ብስጭት፡፡ ትዕግስታችንን አጥተን እንጠብቃለን፤ የልጅነት መጠበቅ አሁንን ነው፡፡ መጓጓታችን ቅፅበትን ነው፡፡ ክፋታቸው ቶሎ አይደርሱም! ጥበቃችን ያይላል፡፡
“ይደርሳሉ”
“መድረሳቸውና መቆየታቸው አፍታ ነው። መጠበቃችን የትየለሌ፡፡ በአጠገባችን ውልብ ይላሉ። እንከተላቸዋለን፡፡ በማግኘታችንና በማጣታችን፣ በደስታችንና በቁጭታችን መሃል የስሜት ህዋሳታችን የሚለኩት ጊዜ የለም፡፡”
“አቧራቸውና ድምፃቸው እስኪቀር እየሮጥን እንከተላቸዋለን፡፡ እናቶቻችንም የሸፈነን አቧራ እስኪረጋ ልባቸው አይረጋም፤ ከማንም በላይ የእማማ ከልቱም መንሰፍሰፍ፡፡
“ሌላ ካሚዮን እስኪመጣ ስንት ለሊት ይነጋ ይሆን። የዕለት ተዕለት ጥያቄያችን ነበር፡፡ ለመኪኖች ልዩ ፍቅር ነበረን፣ በያኔው እውቀታችን፡፡  ከአባይ፣ ከበለስ፣ ከአይማ፣ ከዳቡስ፣ ከሸርቆሌና ከጡነት የምንጨልፈው ውሃ አንድ ይመስለን ነበር፡፡ ዛሬ ከቀዳነው ወራጅ ውሃ ላይ ነገም የምንቀዳ ይመስለን ነበር፡፡”
“ጉባ ዩኒቨርስቲ” የሚል አነበበ፡፡ አለፍ ብሎ ደግሞ “ዳቦስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል”
እኔነቱ ከአካባቢው ባህል፣ ወግ፣ ልማድ ጋር ተገምዷል፡፡ ያወዳድራል፣ ያነፅፅራል…ድሮና ዘንድሮን ባካተተ “ስልጣኔ” ይመሰጣል፡፡
“…ድሮ የምዕራባውያን “ስልጣኔ” የሰራው ትምህርት ቤት የለም፣ ትምህርት ግን አለ፤ የባህላዊ ህክምና እንጂ ክሊኒክ የለም፤ የወገኔ ሌጣ እግር የጠረገው ጐዳና እንጂ አስፓልት ወይም የባቡር ሃዲድ የለም፤ ብርሃን እንጂ የኤሌትሪክ መብራት የለም፤ ውሃ እንጂ ቧንቧ የለም፡፡ ያኔ ስሰደድ…”
“ያኔ! ሐገሬን ትቼ ስሄድ! ያኔ! የሰው ፍቅር እንጂ የሐገር ፍቅር የለኝም ነበር፤ ያኔ! ሐገር ማለት ጠባብ ግን ረጅምና ጥልቅ ወራጅ ውሃ ነበር…ያኔ! አባይ ለእኔ እንደ ሚሲሲፒ፣ እንደ ዛየር፣ እንደ ዛምቤዚ፣ እንደ ኒጀር፣ እንደ አማዞን፣ እንደ ቮልጋ ወንዝ ብቻ ነበር፡፡”
ያኔ እውነቱን ነው፡፡ በወንዙ ዳር ዳር በበቀሉት የዘንባባ ዛፎች ግርጌ ከተቀበሩት ዘመዶቹ መቃብር ላይ ጥርኝ አፈር ዘግኖ፣ በትንሽ የቆዳ ከረጢት ቋጥሮ ወደ ወንዙ ወረወረ፡፡ የወገኖቹን ቅሪት ቀድሞ አሰደደ፤ አስቀድሞ ወደ ተጓዥነት ቀየረ፡፡ ቀጥሎም ዕጣውን ለመተንበይ ተጣደፈ፡፡
የአባይን ወዛም ከንፈር ያለበሱትን አቧራማ መንገዶች ይዞ ተፈተለከ፡፡ እንዳቅሚቲ እያቦነነ ከነፈ። አይኖቹ ግን የሉል ቅንጣት በሚመስሉ እንባዎች ተሸፈኑ፡፡
ወንዙም ወንዝ ነውና፣ ሂያጅ ነውና እንደለመደው የእናት አባቱን፣ የአያት ቅድመ አያቱን ቅሪት ተሸክሞ ነጐደ፡፡ መነሻውን ያውቃል፣ መድረሻውን ግን ይመኛል፡፡ የስደት ነገር! ከረጢቷ በእልፍ አዕላፍ---------ትመሰላለች፡፡
አይኖቹ በዕንባ ቢጋረዱም ብዙ ሮጠ፡፡ አሁን ተረታ፡፡ በጉልበቱ ወደቀ፡፡ ጮኸ፡፡
“አንች ሐገር… አንቺ ምድር… ስለምን አባቶቻችን የጠረጉት ስልጣኔ ላይ እሾህና አሜኬላ የሚያፈራ ትውልድ አበቀልሽ…ስለምን እንደ ዳይኖሰር እርስ በእርሱ ተበላልቶ የሚያልቅ ትውልድ ፈጠርሽ? ስለምን “ጋራሽ ሸንተረሩ በአበቦች አጊጧል”…በተዘፈነልሽ ፋንታ ህፃን፣ የአስከሬን እናቱን ጡት ሲጠባ አየን? ስለምን? የሦስት ሺህ ዘመን ባለታሪክ ሆነሽ፣ የዳቦ ቅርጫት ነች እየተባልሽ ጨቅላ ከዓይነምድር ላይ ጥሬ ሲለቅም አየን?...” ጩኸቱን የገደል ማሚቶ አስተጋባች፡፡
ይህ ድምፅ ታላቅ ድምጽ ነውና በሞገድ ለሁለንታ ተዳረሰ፡፡ የደቀቀ አሸዋውንና አፈሩን ደምስሩ እስኪገታተር ድረስ ጨብጦ በተነው፤ ድምፁ እስኪታፈን የእጁ ጥፍሮች እስኪነቃቀሉ መሬቱን ጐደፈረው፡፡ ላቡ መላ አካሉን አጥለቀለቀው፤ የቆላው ሙቀት ላቡን ከገላው ላይ ሲያተነው ታየ። ይህ ማንነቱን ቆንጥሮ የወጣው ፈሳሽና እንፋሎት ሰውነቱ ላይ ነጭ መም ሰራ፡፡
ለሽራፊ ሰከንድ ብልጭ ያለች ፈገግታው ተገለጠች። ከዚህ በኋላ ተሰደደ ብቻም ሳይሆን፣ ተሳደደ፡፡ አሁን! ከዚህ ዘላለማዊ ከሚመስለው ትዝታ መንግሎ ያወጣው ህዳሴው ሐይቅ መድረሱ ነበር፡፡
አሽከርካሪው መኪናውን በትክክለኛው ቦታ እስኪያቆም ያለው ጊዜ የትየለሌ ሆነበት። ተቁነጠነጠ። አካባቢው ከተለያዩ አህጉራትና ሀገራት በመጡ ቱሪስቶች ተጥለቅልቋል፡፡ በውሃው ዳርቻ እና ተወዛዋዥ አልጋዎች ላይ ተሰጥተዋል፡፡ ይህ ሁሉ ወፈ ሰማይ ፈረንጅ ሊጥ የመሰለ ቆዳውን በፀሐዩዋ ግለት ሊያጠይም ነው! የእሱ ግን ይለያል። በሃሳቦቻቸው ያነጡትን ማንነት ሊያጠቁር ነው፡፡
ከውሃው በላይ በተዘረጋው ተንጠልጣይ ድልድይ ሄደ፡፡ በሐይቁ ዙሪያ ከተገነቡት ሆቴልና ሪዞርቶች መካከል አንዱ የባምዛ ሪዞርት ንብረት ወደ ሆነችዋ ጀልባ ተጣደፈ፡፡ ጉባ ወይም “ብርሃን” ትባላለች፡፡ ሳቂታው ካፒቴኗ በደስታ እየተፍለቀለቀ ተቀበለው። ፊቱን አይቶ በርታ እንደሆነ ገባው፡፡ በአይኖቻቸው ብቻ ተግባቡ፡፡
የካፒቴኑ ነጭ ጥርስ፣ ፀሐይ ከሀይቁ ውሃ ላይ ካስፈነጠረችው ፀዳል ተውሶ አንፀባረቀ፡፡ ጀልባዋ ተንቀሳቀሰች፡፡ የውሃው ቀለም የባለቤቶቹን የቆዳ ቀለም ይዟል፡፡ እጁን ወደ ውሃው መሰገ፣ ሰንጥቆ ገባ። ጉባም ተፈተለከች፡፡ እጁ ውሃውን እየቀረደደ ሄደ፡፡ በጣም ጮኸ፡፡ ሀይቁን በአይበሉባው ጠፈጠፈው፡፡ እመር ብሎ እጀልባዋ አፍንጮ ላይ ቂብ አለ፤ እጆቹን መስቀለኛ ዘረጋቸው፡፡
“…ከእኔና ከዘመዶቼ ውጪ እትብቱና አስክሬኑ በውሃ ውስጥ የተቀበረ ይኖር ይሆን??...የሸርቆሌ፣ የኩምሩክ፣ የጉባ…አባቶች እናቶች ሆይ፣ የልጆቻችሁ እትብት፣ የእናንተ አስክሬን ከፈርዖንም፣ ከነገስታቶችም፣ ከባለፀጐችም በላይ በሶስቱ የኦርዮን ኮከቦች መሃል በታላቁ ሕዳሴ ሐይቅ ውስጥ እንዳለ ለነፍሳችሁ አንሾካሹካለሁ፤…”
የፍርሃቱ መጠን ጨመረ፣ የጀልባዋ ፍጥነት በጣም ከቀነሰ በኋላ ሞተሯን አጠፋው፡፡ ስሜቱን ፈርቶታል። “ዋና…?”  “…እነሆ ለልጅ ልጆቻችሁ እላችኋለሁ ስሰደድ እትብቴ አዋይ፣ አፅማችሁ አድባር ነበር፡፡ ዛሬ ግን መንፈሳችሁ በሀይቁ ላይ ሰፎ አየሁ…!! ስሙኝ እናንተ፣ የያኔ አሳዳጆቼ፣ የአሁን የስደት ጓዶቼ፤ ዛሬ አልፈራም ዘመን ተቀይሯል፤  መንፈሳዊ እርቅ ታውጇል፡፡
የተጓዝንባቸው መንገዶች፣ ያስጠለሉን ሀገሮች፣ የተሳቀቅንበት ሐበሻነት፣ በስደት ሐገር ቀርቷል፡፡ ስማችን በረሃብና በስደት የሚነሳበት ቀን አልፏል…ኢትዮጵያዊነት ለዓለም ዜግነት የሚለመንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡
ከተሞቻችን በሮም፣ በአቴንስ፣ በፓሪስ፣ በኒው ዮርክ፣ በማድሪድ፣ በለንደን እና በጥንታዊው ስልጣኔያችን ተቀይጠዋል፡፡ የልቦቻችን ሃሳቦች፣ የመንፈሶቻችን ከፍታዎች ግን ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ በትግራይ፣ በሐረሪ፣ በሱማሌ፣ በአማራ ይገነባሉ፡፡
“እናንተ እንደ አድባር ንፍሮ በየቦታው የተበተናችሁ ወገኖች ሆይ! ኑ! ለልጅ ልጆቻችን የሚሆን የማንነታችን የአፈር እና የውሃ ቅይጥ እዚህ ሐይቅ ውስጥ አለ…፡፡ የእኔ በሌለበት፣ የእኛ በሆነበት ከሰንበሌጥ በተሰራው የአልካለዋ ዳስ ተሰብስበን እንጠብቃችኋለን፡፡ አልካለዋ የኢትዮጵያ ተምሳሌት ነው፡፡
ኑ! የነፍሶቻችሁን መክሊት፣ የልቦቻችሁን መስዋዕት እንጂ የቁሶቻችሁን ክምር የማትሻ እናት አለቻችሁ፡፡ ልባችሁ እንደ እጃችሁ ከምን ወደማትባሉበት ወደ ታላቁ አልካለዋ ግቡ፡፡ አልካለዋ ዘር፣ ብሔር፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉም የየፍላጐቱን ጥሪት የሚገበይበት ታላቅ ምኩራብ ነው።
ወደ ውሃው ተወረወረ፡፡ የጀልባው ካፒቴን ደነገጠ “አዞ…አዞ…” ጮኸ፡፡
መስመጥ ፈልጓል፤ ወደ ጥልቁ መግባት ሽቷል፤ ሐይቁ የተነጠፈ መስታወት ይመስላል፤ አላሰጥም አለው፡፡ ተፍጨረጨረ፤ የእሱነቱን ምንጭ፣ የኢትዮጵያዊነት ክምችትን ሊያገኝ ታተረ፡፡
ሌላ፣ ሌላ፣ ትልቅ የዝንተ ዓለም ድንጋይ ፍለጋ። ባይደክመውም እንደ ፈጣሪ ማረፍ ፈለገ፡፡ በጀርባው ተንጋሎ ውሃው ላይ ተኛ፡፡ በተራራው አናት እና ጥግ ጥጉን የከተመችው የአልካለዋ ከተማ ጥላ ህዳሴው ሀይቅ ላይ ወድቋል፡፡
አሰበ፣ አሰበ፡፡ ከትከት ብሎ ሳቀ፣ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ…
“…ከሚሊዮን ዓመታት በኋላ አርኪዎሎጂስቶች በባህር ውስጥ የእትብት ቅሪት ፈልገው ያገኙ ይሆናል!!”

Published in ልብ-ወለድ

በእርግዝና እንዲሁም በወሊድ ግዜ በእናቲቱ ላይ የሚከሰቱ የተለያዩ አካላዊ እንዲሁም ስነልቦናዊ ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ምንም እንኳን ይህ ለውጥ በተለያዩ ሴቶች ላይ የሚኖረው ሁኔታ  ቢለያይም እያንዳንዷ እናት ይህን አካላዊና ብሎም ስነልቦናዊ ለውጥ ማስተናገዷ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ አካላዊ ለውጥ ወይም በህክምናው አጠራር physiologic changes of pregnancy በእርግዝና ወቅት በእናቶች ሰውነት ውስጥ የሚመነጨው የሆርሞን መጠን በይዘትም ሆነ በአይነት ከመለወጡ ጋር ተያይዞ የሚከሰት እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡
በተመሳሳይ በእርግዝና ወይም በወሊድ ግዜ በእናቲቱ ላይ የሚስተዋሉ ስነልቦናዊ ለውጦችም ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህ ለውጦች መካከል ከወሊድ በኋላ ወይም በአራስነት ግዜ የሚከሰት የስሜት ለውጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን የስሜት ለውጥ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚቻል በድንበሯ የእናቶች እና ህፃማት ሆንፒታል የፅንስና ማህፀን እስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር አብዱ መንገሻ ያስረዳሉ፡፡
“በድህረ ወሊድ ወቅት የሚታዩ የስሜት ለውጦችን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንደኛው Baby blues  ወይም በአማርኛው የአራስነት መተከዝ ልንለው እንችላለን፡፡ ሌላኛው ደግሞ postpartum depression  ወይም የድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ነው፡፡ ሁለተኛው ከበድ ያለና የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው ሲሆን የአራስነት መተከዝ የምንለው ግን በብዙ አራሶች ላይ የሚከሰትና እንደ ጤና መጓደልም የማይታይ የስሜት ለውጥ ነው፡፡”
ይህ በአራስነት ወቅት የሚኖር የስሜት ለውጥ እናቲቱ ከወለደች በኋላ ለጥቂት ቀናት ብቻ የሚቆይ በመሆኑ በእርግዝና ወቅት ከሚታዩት ለውጦች እምብዛም የተለዩ አይደሉም ይላሉ ባለሙያው፡፡  
“ይህ የስሜት ለውጥ ከመቶ ምሳ የሚሆኑ እናቶች ላይ ሊከሰት የሚችልና በጣም ለአጭር ግዜ የሚቆይ ነው፡፡ ልክ በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ላይ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማቅለሽለሽ ወይም አልፎ አልፎ ጠዋት ጠዋት ማስመለስ እንደሚታየው ሁሉ  ከተገላገለች በኋላ ባሉት ሶስት ቢበዛ ደግሞ ስድስት ቀናት ውስጥም የሚከሰት የስሜት ለውጥ ይኖራል፡፡ እናም ከቤተሰብ ድጋፍና እንክብካቤ የዘለለ ህክምና አይስፈልገውም፡፡”
በእርግዝና ወቅት በሰውነት ውስጥ የሚመነጩት የሆርሞኖች መጠን በይዘትም በአይነት ይጨምራሉ። በአንፃሩ ከወሊድ በኋላ የእነዚህ ሆርሞኖች መጠን ይቀንሳል ይህም በአራስነት ወቅት ለሚከሰት የስሜት መለዋወጥ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡   
“ለዚህ የስሜት ለውጥ ዋና መንስኤ ተብሎ የሚታመነው በእርግዝና ወቅት በነብሰጡሯ ሰውነት በብዙ መጠን ይመረቱ የነበሩ ሆርሞኖች ከወሊድ በኋላ መቀነስ ነው፡፡ እናትየዋ ከወለደች በኋላ እነዚህ ሆርሞኖች መመረታቸውን ስለሚያቆሙ ወይም ከሰውነቷ ስለሚጠፉ የእነዚህ ሆርሞኖች ከሰውነቷ መጥፋት በአራስነት ግዜ ለሚኖር የስሜት መለዋወጥ እንደ አንድ ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ ምክንያት ነው ይህ የስሜት ለውጥ ግዜያዊ ወይም  ለአጭር ግዜ ብቻ የሚከሰት ችግር ነው የምንለው፡፡”
ለዚህም ተጠቃሽ የሚሆነው ፕሮጀስትሮን የተባለው ሆርሞን ነው፡፡ ይህ ሆርሞን በእርግዝና ወቅት ስሜትን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ላይ የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተፅእኖ ስለሚኖረው ነብሰጡሯ የተረጋጋ ስሜት ውስጥ እንድትሆን ያደርጋል፡፡ ነገር ግን አንዲት እናት ከወለደች በኋላ ይህ ሆርሞን ስለማይመረትና በሰውነቷ ውስጥ የዚህ ሆርሞን መጠን ስለሚቀንስ ስሜትን የሚቆጣጠረው የአንጎል ክፍል ከዚህ ሆርሞን ተፅእኖ ነፃ ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ የስሜት ሁኔታ ዝቅ እንዲል ያደርገዋል፡፡
ምንም እንኳን በወሊድ ግዜ የሚመረቱት ሆርሞኖች መጠን መቀነስ ለዚህ የስሜት መለዋወጥ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ ይወሰድ እንጂ ይህን ችግር ሊያባብሱ የሚችሉ ሌሎች ምክንያቶች አሉ ይላሉ ዶክተር አብዱ፡፡
“ዋናው ምክንያት የሆርሞን ለውጡ መከሰቱ ቢሆንም ይህ ችግር የተለያዩ ተጨማሪ ክስተቶች ድምር ውጤት ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለምሳሌ በእርግዝና እና በወሊድ ግዜ ነብሰጡሯ ሲሰማት የነበረው የመደሰት እንዲሁም የፍርሀት ስሜት መገላገሏን ተከትሎ ዝቅ ይላል ስለዚህ ይህ እንደ አንድ ተጨማሪ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ማለት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በመጀመሪያዎቹ የወሊድ ቀናት ላይ የጡት መወጠርም ወይም ሌሎች የእናቲቱን ምቾት ሊያጓድሉ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በአራስነት ግዜ ለሚኖር መተከዝ ወይም የስሜት መለዋወጥ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡”
ሁሉም እናቶች ላይ ባይሆንም ከወሊድ በኋላ የሰውነት ቅርፅ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም እናቲቱ የትዳር አጋሯን ጨምሮ በሌሎች ሰዎች ዘንድ የምስብ ወይም የምማርክ አይነት አይደለሁም የሚል ጭንቀት ሊፈጠርባት ይችላል። በተጨማሪም በምጥ ወቅት የሚኖር የእቅልፍ እጦትን ተከትሎ የሚከሰት የሰውነት መዛል ወይም መድከም፣ እናቲቱ ከወለደች በኋላ ጨቅላ ህፃኑን ለመንከባከብ ያላትን ችሎታ በመጠራጠሯ ምክንያት የሚፈጠር የጭንቀት ስሜት እነዚህ ነገሮች ሁሉ ቀደም ሲል ከተጠቀሰው መሰረታዊ የሆርሞን ለውጥ ጋር ተደማምረው የአራስነት መተከዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡    
ይህ ከወሊድ በኋላ የሚኖር የስሜት ለውጥ ሲከሰት በእናቲቱ ላይ ከሚታዩ የተለያዩ ምልክቶች መካከል፡-
እንቅልፍ ማጣት ወይም መደበት
ሆደባሻ መሆን “አለ ምንም ምክንያት በተደጋጋሚ ማልቀስ”
መጨነቅ
ትኩረት ማጣት “ሀሳብን ለመሰብሰብ መቸገር”
ነጭናጫ መሆን እንዲሁም
የስሜት መዋዠቅ
ዋናወናዎቹ ናቸው፡፡
እነዚህን ምልክቶች በተመለከተም ዶክተር አብዱ ይህን ብለዋል፡-
“ለምሳሌ አንዲት አራስ ሴት በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ሰአታት ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖራት እንዲሁ ዝም ብላ ስታለቅስ ቆይታ ተመልሳ ደግሞ ወደ ጤናማ ስሜቷ ልትመለስ ትችላለች፡፡ የተወሰኑ ደቂቃዎች ጤናማ የሆነ ስሜት ይኖራታል በሌላ ግዜ ደግሞ ያለ ምንም ምክንያት ልታለቅስ ወይም ልትነጫነጭ ትችላለች እንግዲህ ይህንን ነው የስሜት መዋዠቅ የምንለው፡፡”
ይህ ከወሊድ በኋላ የሚከሰት የስሜት መለዋወጥ ለአጭር ግዜ የሚቆይና ወደ ጤና ተቋም መሄድ ሳያስፈልግ ለእናቲቱ በሚደረግ እንክብካቤ ብቻ መከላከል በመቻሉ ከድህረ ወሊድ የድብርት ህመም ወይም postpartum depression  በእጅጉ ይለያል፡፡   
“ይህ የአራስነት መተከዝ በጣም ለአጭር ግዜ የሚቆይ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ይህ ነገር የሚከሰተው ከወሊድ በኋላ ባሉት ሶስት ወይም ስድስት እንደው ቢበዛ ለአስር ቀናት ያህል የሚቆይ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ከ postpartum depression ወይም ከድህረ ወሊድ የድብርት ህመም የሚለይበት ልዩ ባህሪው ነው፡፡”

Published in ላንተና ላንቺ
Page 1 of 21