በህንዳዊው መምህርና ፀሐፊ ሚ/ር ጆሴፍ ፍራንሲስ የተዘጋጀ “የድንቂቱ ኢትዮጵያ ድንቃድንቆች” (“This is Ethiopia – A Book of Fascinating Facts”) የተሰኘ ስለ ኢትዮጵያ የተለያዩ ድንቅ መረጃዎችን ያካተተ አዲስ መፅሐፍ የፊታችን ረቡዕ ከምሽቱ 12 ሰዓት ሚኒስትር ዴኤታ ሙሉጌታ ሰኢድ ዳምጠው በተገኙበት በካፒታል ሆቴል ይመረቃል፡፡
መፅሐፉ፤ ኢትዮጵያን ልዩ የሚያደርጋትን ከ245 በላይ መረጃዎች ያካተተ ሲሆን የተዘጋጀበትም ዓላማ፤ በተለይ የውጭ አገር አንባቢያንና ዳያስፖራዎች፣ ስለ ኢትዮጵያ መረጃዎችን በቀላሉና በአጭሩ እንዲቀስሙ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡ በመፅሐፉ ጀርባ ላይ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት የታሪክ ባለሙያው ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክረስት፤ “ስለ ኢትዮጵያ ብዙ የማናውቃቸው አስደናቂ ነገሮች መኖራቸውን… መፅሃፉ እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ መፅሃፉ ያካተታቸው መረጃዎች ብዙ አንባቢዎችን ሊያስደምሙ የሚችሉ ናቸው” ብለዋል፡፡
መፅሃፉ በእንግሊዝኛና በአማርኛ የተዘጋጀ ሲሆን ትርጉሙን የሰራው ደራሲ አማረ ማሞ ነው፡፡ የውስጥ ገፆቹ ሁሉ ባለቀለም ሆነው የተዘጋጀው “የድንቂቱ ኢትዮጵያ ድንቃድንቆች” መጽሐፍ መረጃዎች በተዋቡ ምስሎች ተደግፈው ቀርበውበታል፡፡ ላለፉት 30 ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በመምህርነት ያገለገለው ሚ/ር ጆሴፍ ፍራንሲስ፤ ከዚህ ቀደም “የአድዋ ጦርነት”፣ “ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ” እና “የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ፣ ልዑል ዓለማየሁ” የተሰኙ የልጆችና ወጣቶች መፃህፍትን አሳትሟል፡፡

“ቦሌ ፒኮክ ጋ ጠብቂኝ” በተሰኘው የሰለሞን ፍስሀ መጽሐፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አዳራሽ ውይይት እንደሚካሄድ ሚዩዚክ ሜይደይ አስታወቀ፡፡ ውይይቱን የሚመሩት ሃያሲ እና የወግ ጸሐፊ መስፍን ሀብተማርያም እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የጋዜጠኛና ገጣሚ ተስፋዬ ገብረማርያም “የማይሆን ዓለም” የተሰኘ ግጥሞች፣ አጫጭር ልቦለዶች እና ወግ የተካተቱበት መጽሐፍ ነገ በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ እንደሚመረቅ “ሀሳብ መልቲሚዲያ” አስታወቀ፡፡ በ62 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፣ በ20 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ጋዜጠኛና ገጣሚ ተስፋዬ በ“ኢትዮ ቻናል” ጋዜጣ ማህበራዊ ጉዳዮች አምድ ጸሐፊነቱና በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ በሚያቀርበው “ድርሻችን” የተሰኘ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ይታወቃል፡፡

“ዜማ ቃል” የተሰኘ ወርሃዊ የጥበብ ምሽት ሐሙስ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ  በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ለአንድ ዓመት በሚዘልቀው ዝግጅት፣ የገጣሚያን፣ ጸሐፍትና ኮሜዲያን  ሥራዎች የሚቀርብበት ሲሆን የመግቢያ ዋጋው በነፍስ ወከፍ 50 ብር እንደሆነ ዝግጅቱን የሚያስተባብረው ፈለቀ ካሳ ጥንድ ፕሮሞሽን  ጠቁሟል፡፡ 

በዶ/ር ሱዛን ጄፈርስ የተፃፈው “Feel the Fear and Do it Anyway” የተሰኘ መፅሃፍ፤“ፍርሃትን ማሸነፍ” በሚል ርእስ በቢኒያም አለማየሁ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ አሉታዊ አመለካከትን ስለማስወገድ፣ ውሳኔዎችን በሥራ ስለ መተግበር፣ ፍርሃትን ስለ ማጥፋት እና ሌሎች ተያያዥ ቁም ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ 192 ገፆች ያሉት መፅሃፉ፤ ዋጋው 40.50 ብር ነው፡፡
በሌላም በኩል “በአራጣ የተያዘ ጭን” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በዮፍታሔ ካሳ የተደረሰው መጽሐፍ፤ በ233 ገፆቹ አስራ ዘጠኝ አጫጭር ልቦለዶች ይዟል፡፡ በኤች ዋይ ኢንተርናሽናል ማተሚያ ቤት የታተመውን መጽሐፍ፤ ሊትማን ጀነራል ትሬዲንግ የሚያከፋፍለው ሲሆን ዋጋውም 46.99 ብር ነው፡፡
በተመሳሳይ “ከመለስ ሞት በስተጀርባ” የተሰኘ መጽሐፍ በዚህ ሳምንት ለንባብ በቃ፡፡ መፅሃፉ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ፣ በአባይ ግድብ፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ያጠነጥናል፡፡ በ70 ገጾች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ ለገበያ የቀረበው በ32 ብር ነው፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት ፎቶግራፎች መካከልም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የሃምሳ ብር ኖት ላይ የወጣው የአባይ ግድብን የሚያሳይ ምስል ይገኝበታል፡፡

ከሁለት ወር በፊት ራሷን ከጡት ካንሰር ለመታደግ ሁለት ጡቶቿን በቀዶ ጥገና ያስወገደችው አንጀሊና ጆሊ፤ለመላው ዓለም ስለ ጡት ካንሰር አስከፊነት ባስጨበጠችው ግንዛቤ ከፍተኛ አድናቆትን እንዳተረፈች ተገለፀ፡፡ ዝነኛዋ የሆሊውድ አርቲስት ህክምናውን ለማግኘት የወሰደችው ፈጣን እርምጃና ለመላው ዓለም ግልፅ መረጃ በማቀበል ባሳየችው ድፍረት የተመላበት ተግባር በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ተወድሶላታል። “ተግባሯ በሙያችን መነቃቃትና ግንዛቤ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል” ብለዋል - ባለሙያዎቹ፡፡ የስድስት ልጆች እናት የሆነችው የ37 ዓመቷ አንጀሊና ጆሊ፤ሁለት ጡቶቿን የሚያስወግድ ቀዶ ህክምና ባታደርግ ኖሮ 87 በመቶ ለጡት ካንሰር፣ 50 በመቶ ለማህፀን ካንሰር ትጋለጥ እንደነበር ታውቋል፡፡ አንጀሊና በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ባሰፈረችው ፅሁፍ፤ ህክምናውን ለመውሰድ የወሰደችው እናቷ በ56 ዓመታቸው በተመሳሳይ ችግር ለሞት በመዳረጋቸው እንደሆነ ገልፃለች። በመላው ዓለም በየዓመቱ ከ45ሺ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

“ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” በተሰኘው የኔልሰን ማንዴላ ግለታሪክ መፅሃፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራው አዲስ ፊልም ከወር በኋላ በመላው ዓለም መታየት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ ፊልሙ የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ትግል ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ታልሞ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
በጉበት ኢንፌክሽን በጠና ታመው በሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው የቆዩት ኔልሰን ማንዴላ፤ ከሳምንት በፊት 95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው የተከበረላቸው ሲሆን አሁን ከህመማቸው ማገገማቸው ታውቋል፡፡
“ማንዴላ፡ ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” በሚል ርእስ በተሰራው ፊልም ላይ የማንዴላን ገፀባህርይ የሚተውነው እንግሊዛዊው ተዋናይ ኤድሪስ ኤልባ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የ40 ዓመቱ ኤዲሪስ ኤልባ በፊልሙ ላይ ልዩ የትወና ብቃት እንደሚያሳይ ከወዲሁ የተነበየው ዘ ጋርድያን፤ ይሄም ለኦስካር ሽልማት ሊያሳጨው እንደሚችል ግምቱን አስፍሯል። “ማንዴላ፡ ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” የተሰኘው ፊልም በነፃነት ታጋዩ የልጅነት፤ የአስተዳደግና የትምህርት ሁኔታ እንዲሁም የ27 ዓመታት የእስር ቆይታ እና ደቡብ አፍሪካን በፕሬዝዳንትነት እስከመሩበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሂደት የሚተርክ መሆኑን “ዘ ስዌታን” ጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በማንዴላ ተፅፎ ለንባብ የበቃው ግለ ታሪክ መፅሃፍ በመላው ዓለም ከ15 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አጓጊው ዜና ምንድነው?
ዋርነር ብሮስ የተባለው የፊልም ኩባንያ እና ዲሲ ኮሚክስ እ.ኤ.አ በ2015 ባትማንና ሱፐርማንን በማጣመር ልዩ ፊልም እንሰራለን ማለታቸው ነው፡፡ ፊልሙ በሚቀጥለው ዓመት ቀረፃው የሚጀምር ሲሆን እውቆቹ የ“ሱፐርማን ሪተርንስ” ዳሬክተር ዛክ ስናይደር እና የ“ባትማን” ፊልም አካል የሆነው “ዘ ዳርክ ናይትስ” ዳሬክተር ክሪስቶፈር ኖላን በጥምረት ይሰሩበታል ተብሏል፡፡
ፊልሙን ለመሥራት እንዴት ታሰበ ?
የልዕለ ጀግና ጀብደኛ ገፀባህርያትን በመፅሃፍ እና በፊልም በመስራት ስኬታማ የሆነው ዲሲ ኮሚክስ፤ ባትማንና ሱፐርማንን በአንድነት በማጣመር ለመስራት የወሰነው አምና ማርቭል ኮሚክስ፤ የልዕለ ጀብደኛ ገፀባህርያትን ያሰባሰበውን “ዘ አቬንጀርስ” ለእይታ በማብቃት በመላው ዓለም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰቡን በማየት ነው፡፡
እነማን ይተውኑበታል?
ዘንድሮ ለእይታ በበቃው በ“ሱፐርማን ሪተርንስ” ፊልም ላይ በመስራት ባሳየው ብቃቱ የተደነቀው ሄነሪ ካቪል ሱፐርማንን ሲተውን ፤ ባትማንን ለመተወን ደግሞ በ“ዘ ዳርክ ናይትስ” ላይ የተወነው ክርስቲያን ቤል ታጭቷል - ማረጋገጫ ባይገኝም፡፡


ባትማንና ሱፐርማን በንፅፅር
*በካርቱን መፃህፍት ላይ ተመስርተው በመሰራት ትርፋማ ከሆኑት የሱፐርሂሮ ጀብደኛ ገፀባህርያት ባትማንና ሱፐርማን ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
የባትማን ገፀባህርይ በመፅሃፍ፤ በፊልም፤ በዲቪዲ ሽያጭ እና ሌሎች ንግዶች በመላው ዓለም 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገኝ የሱፐር ማን ገፀባህርይ ደግሞ በተመሳሳይ ዘርፍ 5 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡
ዘንድሮ ለእይታ የበቃው እና በዳሬክተር ዛክ ስናይደር የተሰራው “ማን ኦፍ ስቲል ሱፕርማን ሪተርንስ” 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቶበታል፡፡
ባትማን ሰብዓዊ ፍጡር ያለው ገፀባህርይ ሲሆን ሱፐርማን ግን ከሰብዓዊ ፍጡር የላቀ ተሰጥኦ ያለው ልዩ ፍጥረት ነው፡፡
ባትማን ልዩ ሃይልና ተሰጥኦ ባይኖረውም በሳይንስና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ጠቅላላ እውቀት የተገነባ የላቀ አዕምሮ ያለው ጀብደኛ የልዕለ ጀግና ገፀባህርይ ነው፡፡ ባትማን በምርመራ ችሎታው እና በሃብታምነቱም ይለያል፡፡ ሱፐር ማን ደግሞ መብረር የሚችል፤ከፍተኛ ጥንካሬ ያለውና በላቀ ተሰጥኦው የተለያዩ ጀብዶችን የሚያከናውን እንዲሁም ሰብዓዊ ፍጡር ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ተግባራት በቀላሉ የሚሰራ ገፀባህርይ ነው፡፡

ጥልቅና አንኳር አስተያየት ስለ
“የተረሳ ወራሽ”

“መጽሐፉ የእናቴ ስለሆነ የግድ አሪፍ
ነው ማለት አይደለም፡፡ እናንተ
ባለሙያዎቹ አስተያየት ስጡበት፡፡”
የመጽሐፉ ደራሲ ሴት ልጅ አዜብ መርሻ

የመጽሐፉ ምርቃት
ቅዳሜ ሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም
የተመረቀበት ቦታ
በቤተመጻሕፍት ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ
መጽሐፉ - የተረሳ ወራሽ
ደራሲ - መሰሉ መዝለቂያ
አርታዒ - አሊ መሀመድ አሊ
አስተያየት - ነቢይ መኮንን
እንደ መሽከንተሪያ (አንዳንዶች መስከንተሪያ ይሉታል) – (መሽከንተሪያን፤ ዘርጋው መዝገበ ቃላት ደግሞ “በመሬት ውስጥ የተሰራውን መመርመሪያ አርሶጦላብ” - ይለዋል)
መሽከንተሪያ ማለት፡- ዱሮ ልጅ ሆነን ስንጫወት፣ የባህር -ዛፍ ፍሬ እንለቅምና ሊሾ ሲሚንቶ ወለል ላይ ዙሪያ ተቀምጠን በሁለት ጣታችን ፍሬዋን ስናሾራት እዚያ ሲሚንቶ ላይ ፉርር እያለች ዙሪያውን ትሽከነተራለች፡፡ ቶሎ አትቆምም፡፡ ትዞራለች፡፡ መሽከንተሪያ እንግዲህ ማሾሪያ፣ ማሽከንተሪያ፣ ማዞሪያ፣ የመነሻ ጉልበት መስጫ (Starter እንደሚባለው በመካኒክ ቋንቋ - “ማስነሻ” መሆኑ ነው)
እንደገና፤ ዱሮ ልጅ ሆነን እናቶቻችን በእንዝርት ጥጥ ሲያጠነጥኑ እንዝርቷን በሁለት ጣታቸው መካከል አስገብተው ሲያሾሯት እንዝርቷ በጣም ትሽከረከራለች። ትሽከነተራለች፡፡ ከላይ በባህር - ዛፏ ፍሬ ስንጫወት ያደረግነውና የእናታችን የእንዝርት እሽክርክሪት ያው መሽከንተር ማለት ነው፡፡ እንግዲህ መሽከንተሪያን በጽሑፌ ውስጥ እንደመነሻ ኃይል፣ የጀርባ ታሪክ (Background) ወዘተ. ተጠቀምኩበት፡፡
በ“የተረሳ ውርስ” መጽሐፍ ላይ ይህን አስተያየት እንድሰጥ ያነሳሳኝ፣ መሽከንተሪያዬ ምንድን ነው? እነሆ፡-
ስልክ ይደወልልኛል፡፡
“ሃሎ?” አልኩ
“ሰላም ነቢይ፤ ታስታውሰኝ ይሆን?” አለች ከዚያኛው ጫፍ ያለችው ልጅ፡፡
“ማን ነሽ?” አልኩ በግርታ፡፡
“የመሰሉ መዝለቂያ ልጅ ነኝ…”
“መሰሉ? መሰሉ መዝለቂያ?...ትዝ ትዝ ይለኛል ስሟ…” አሁንም በግርታ፡፡
“ያኔ በእናንተ ጋዜጣ በነጋ - መዝለቂያ መጽሐፍ ላይ አስተያየት ትሰጥ የነበረችው እንኳን” በትሑት - አስረጂ መንፈስ መግለጽ ጀመረች፡፡
“ኣ! በደንብ አስታወስኩ!” አልኳት፡፡
“መሰሉ መዝለቂያ እናቴ ናት፡፡ ያኔ የሷን ጽሑፍ ይዤልህ የምመጣው እኔ ነበርኩ፡፡”
“ኦ! በትክክል ገብተሽኛል፡፡ ደህና ነሽ? ምን ላግዝሽ?”
“ደህና ነኝ ነቢይ…ለምን ደወልኩ መሰለህ? አሁን ደግሞ እናቴ መጽሐፍ ጽፋለች፡፡ እና እንድታይላት ከማተሚያ ቤት ሲወጣ ይዤልህ ልመጣ ፈልጌ ነበር። ጊዜ ካለህ…ከተመቸህ…”
ደስ አለኝ፡፡ “Great! መጽሐፍ መፃፏ በጣም ያስደስታል፡፡ ዱሮም ወደዚያው ነበር አዝማሚያዋ…ጊዜው ሲደርስ ደውይልኝ፡፡ ምንም ችግር የለም…አየዋለሁ” አልኳት፡፡
“በጣም አመሰግናለሁ ነቢይ”
ከአፏ ላይ “ነቢይ” የሚለው ቃል አይለይም። ያ ደግሞ ቀረቤታን፣ ዝምድናን ነው የሚያሳየው። አንድም፣ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “To a man, the sweetest word in any language is his own name” (ለሰው፤ በማንኛውም ቋንቋ ቢነገር እጅግ ጣፋጩ ቃል፤ የራሱ ስም ነው፤ እንደማለት ነው) ስለዚህ ሞቅ የማለት ስሜት አለው!
በኋላ ስታጫውተኝ “ለጓደኞቼ ዘመዳችን ነው” እላቸው ነበር ማለቷ ከአንደበቷ “ነቢይ” የሚለው ቃል ላለመለየቱ፣ ለቀረቤታው፣ ማፀህያ (verification) ወይም ማጠየቂያ (Justification) ይሆነናል፡፡
ለመሆኑ ደራሲዋ መሰሉ መዝለቂያ ማናት?
ነጋ መዝለቂያ ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኝ ሲሆን፤ የመሰሉ መዝለቂያ ወንድም ነው፡፡
የመሰሉ ወንድም ነጋ መዝለቂያ በ1994 ዓ.ም በእንግሊዝኛ “Notes from The Hyenas Belly” የሚል መጽሐፍ ይጽፋል፡፡ በዚሁም መጽሐፍ ዙሪያ “ዘ ፖኤትስ ኤንድ ራይተርስ” ለተባለ መጽሔት የሰጠው ቃለ - ምልልስ ጥር 18 ቀን 1994 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ተተርጉሞ ወጥቶ ነበር፡፡ እህቱ መሰሉ መዝለቂያ “ነጋ ከዕውነተኛ ታሪኩ አልተነሳም፡፡ አባይ ነው፡፡ ለዚህም እኔ እማኝ ነኝ” በሚል መንፈስ ትጽፍልናለች። የነጋ መጽሐፍ በደራሲው - በነጋ መዝለቂያ በደርግ ዘመን፣ የጅጅጋና የሐረር ግለ - ታሪክ ዙሪያ የተጠነጠነ ነው ይባል እንጂ የደራሲው እህት መሰሉ መዝለቂያ፤ “ዕውነተኛ ታሪክ” ነው ተብሎ የተፃፈው የወንድሟ መጽሐፍ አልተዋጠላትም፡፡
ስለዚህም ምርርና ክርር ያለ ሒሳዊ አስተያየት በሐተታ (article) መልክ ትጽፍና በሴት ልጇ በኩል፤ ለአዲስ አድማስ ትልካለች፡፡ እናነበዋለን፡፡ መሰሉ እጇ፣ ቀለም አጣጣሏ፣ የሃሳብ ውርዷ፣ አመክንዮዋ (reasoning)፣ አወዛጋቢነቷ (Controversy) እና ለታሪክ መቆርቆሩዋ ቁልጭ ብሎ ይታያል፡፡ “ግለሰቡ በግሌ ከጐዳኝ የበለጠ በወገን ታሪክ ላይ የፈፀመው ደባ የከበደ ስለመሰለኝ፣ ይህን የተጋነነና የገዘፈ ውሸት ቸል ብዬ ማለፍ አልሆነልኝም” ትላለች፡፡
ደሞ ሌላ ምሳሌ ለአብነት ጠቅሼ በምን ሁኔታ ልትጋተረው እንደሞከረች ላሳይ፤ (አዲስ አድማስ 1994 ግንቦት 10)
“ይህ ግለሰብ…(ከገጽ 134 የመጨረሻው አንቀጽ ጀምሮ) “አባቴ ቀብሪደሀር በሥራ ላይ እያለ በደርግ ካድሬዎች ተገደለብኝ፡፡ አንድ መኮንን መርዶውን ባያመጣልን እንደማንኛውም ወጥቶ የቀረ ዜጋ የደረሰበትን ሳናውቅ እንቀር ነበር” እያለ የቀብር ወግ ሳያገኙ ሜዳ ተጥለው ከቀሩት ዜጐች ጋር አብሮ መውደቁን ያረዳናል፡፡ በተጨማሪም የአባቱ የባንክ ተቀማጭና ሀብት ንብረት ውሃ በልቶት እንደቀረ ያዋየናል፡፡ ሃቁ ግን የሁለታችንም አባት የሆነው አቶ መዝለቂያ አልታዩ በ1966 ዓ.ም በጡረታ ተገልሎ ቀብሪደሀርን የለቀቀና ጅጅጋ ከሚገኘው ቤተሰብ ጋር ተቀላቅሎ በ95 ብር የጡረታ አበል መተዳደር የጀመረ ሲሆን፤ በ1967 ዓ.ም በጉበት በሽታ በመያዙ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በ1968 ዓ.ም ሚያዚያ 2 ቀን ማረፉ ነው፡፡ የቀብር ሥነስርዓቱም የተፈፀመው ጅጅጋ በቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ነው”
ነብሱን ይማረውና አሰፋ ጐሣዬ (የአዲስ አድማስ ሥራ አስኪያጅ) እንዲያነበው ሰጠሁት፡፡ አነበበው፡፡ ተደሰተ፡፡ “ልብ ያላት ፀሐፊ ናት!” አለ፡፡
እኔም፤ “አዎ፡፡ ወደፊት ጐበዝ ደራሲ ይወጣታል!” አልኩት፡፡
ተከታታይ ጽሑፍ አቀረበች፡፡
ይሄው ዛሬ መጽሐፍ ይዛ ብቅ አለች፡፡ እኔ እስከማውቃት ድረስ መሰሉ መዝለቂያ ይቺ ናት!
አንድም የጋዜጣችን ጽሑፍ አቅራቢ የነበረች በመሆኗ፣ አንድም የገባትና የሚገባት (“ገ”፣ “ባ” ይጠብቃል) ደራሲ በመሆኗ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ፤ ገና ታሪኩ ወደፊት የበለጠ፣ በጠለቀና በሰፋ መልኩ ይፃፋል ብዬ በማምነው በ1960ዎቹ ትውልድ ላይ በማተኮሯ፤ በያገባኛልና - በይገባኛል ባይነት፤ አስተያየት ልሰጥ አሰብኩ፡፡
የመሰሉ መዝለቂያ ልጅ ዛሬ መጽሐፉን ይዛልኝ ስትመጣ ያኔ ትንሽ ተላላኪ የነበረችው ትልቅ ሆና አገኘኋት፡፡ የጊዜው ሩጫ!- እኛን ለማስረጀት ያለው ችኰላ፤ ገረመኝ፡፡ “ጊዜ በረርክ በረርክ … ግና ምን ተጠቀምክ ምንም አላተረፍክ” የሚለው የደበበ ሰይፉ ግጥም ጥቂት መስመር ነው ትዝ ያለኝ፡፡
“መጽሐፉ የእናቴ ስለሆነ የግድ አሪፍ ነው ማለት አይደለም፡፡ እናንተ ባለሙያዎቹ አስተያየት ስጡበት” ብላ ነው የሰጠችኝ፡፡
ሌላ ቀን የመሰሉ ልጅ ስለራሷ ስታጫውተኝ፤
“በሲቪል ኢንጂነሪንግ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቅሁ፡፡ ቀጥዬ ኔዘርላንድስ ሄጄ ማስተርሴን ሰራሁ…ዩኒቨርሲቲ ሌክቸረር ሆኛለሁ አሁን፡፡ (እናቷ ግቧን መታለች!) ስለሥነጽሑፍ ግን ምንም አላውቅም” ትለኛለች፡፡
“ምንም ምንም?” ብዬ ጠየኳት
“ምንም!” አለች ፍርጥም ብላ፡፡
“ወይ ጉድ ‘ምንም!” ለማለት ድፍረት ያላት ልጅ ናት! እንዲህ ያለ ልጅ ብዙ አይገኝም በአሁኑ ዘመን!” አልኩኝ በሆዴ፡፡ ያሁኑ ትውልድ…የእኛ ትውልድ…እያልኩ ብዙ አውጠነጠንኩ፡፡
ዞሮ ዞሮ እናቷ ስለራሷ ትውልድ ነው የፃፈችው፡፡
በዚያ በደርግ ዘመን ባሏ ወደ ስደት፣ እሷ ወደ እሥር ቤት፣ የወንድሞች ስደት፣ ልጅ ይዞ ዩኒቨርሲቲ መግባት፣ የሌላ ልጇ ወደ ቤት ሥራ መሰማራት ወዘተ ተገፍታ፣ ተሰቃይታ፣ ልጅ አሳድጋ…ልጆቿን ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት ብዙ አበሳ አየች፡፡ የገዛ ታሪኳ ራሱ አስገራሚ ነው፡፡ “እያንዳንዱ ደራሲ በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ፣ የፃፈው ታሪክ ውስጥ እራሱ አለበት” (Each writer, this way or the other, is part of the story he wrote እንደተባለው ነው፡፡) አንዳንዴ ሳስባት፣ ለዋሸ፣ ለቀጠፈ፣ የትውልዷ አካል (ወንድሟን ጨምሮ) በመጽሐፍ መልክ መልስ መስጠቷ ይሆን እላለሁ፡፡
እንግዲህ ይቺን ደራሲ ከማድነቅ አልፌ ባበረታታት ሁሉ ፈቃዴ ሆነ!
መሽከንተሪያዬ እናቱም አባቱም ይሄው ነው! በሁለት ተከታታይ ክፍል ቢቀርብ ነው ክጃሎቴ፡፡ መጀመሪያ በዐይኑ በሰበከቱ በኩል እናያለን፡፡ ቀጥሎ በመልኩም በገበሩም፤ ብልት ብልቱን እናያለን፡፡
***
መጽሐፉ በተመረቀበት ወቅት በቦታው ተገኝቻለሁ፡፡ ትንሽ ንግግር አድርጌአለሁ፡፡ የዚያችንም ንግግሬን መንፈስ እዚህ አስተያየቴ ውስጥ ዶየዋለሁ፡፡ “ከአፍ ከወጣ አፋፍ” ነውና፤
መወራቱ ላይቀር በጽሑፍ ቢቀመጥ ምን ይገደዋል? ብዬ ነው፡፡
***
የተረሳ ወራሽ
የመጽሐፉ ርዕስ ደስ የሚል መስህብ አለው፡፡ የታመቀ ሃሳብ ያዘለ ይመስላል፡፡
የሽፋን ስዕሉ፣ በዕርበትም ሆነ በጀምበር ስርቂያ ስሜት፣ ደብዛዛ ከመሆኑና ህትመት ያጐሳቆለው ከመምሰሉ በስተቀር፤ ውስጡ ያለውን ይዘት ለመግለጥ አቅም አላነሰውም፡፡
የገፁ ብዛት - በንግግሬም ላይ እንደገለጥኩት፤ ለዛሬው የንባብ ውርጭ ለመታው አንባቢ 506 ገጽ ነውና ሳያስፈራው አይቀርም፡፡ ሆኖም እንቅልፍ ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም፡፡ በተለይ በረዥም ልብ ወለድ መልክ በሚፃፍ መፅሃፍ ፣ለአንባቢ ወይም ለገበያ ተብሎ ፤በጥቂት ገፆች ቀንብቦ ማቅረብ ፍትሃዊነት የጎደለው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ደራሲው ሀሳቡን ያቆረበትን ያህል ገጽ መቀበሉ መልካም ነው፤ እላለሁ፡፡
በእርግጥ “ግጥሜን ባሳጥረው” በሚለው ግጥሜ ውስጥ (ለግጥም ሆነ እንጂ) ተቃራኒ ሀሳብ ተንፀባርቆ ይሆናል፡፡
ግጥሜን ባሳጥረው
ጊዜ አጣሁኝ ብዬ ፣ ከቁመቱ በታች
ግጥሜን ባሳጥረው
“አይምሰልህ” አለኝ-
“ዕድሜ ሲያጥር እንጂ፣
ቁመት ሲያጥር አደለም፣ ግጥም የሚሞተው”
ብሎ መለሰልኝ፡፡
አንጀቴን አርሶ፣ ዕድሜ ጨመረልኝ!!
(የካቲት 1999ዓ.ም)
እርግጥ ነው፡፡ ሰንሰለቱ ሲረዝም እያንዳንዱ ቀለበት ይላላል፡፡ ይህም ዳተኛ አንባቢያንን የበለጠ ማሳነፉ አይቀሬ ነው፡፡ ሆኖም ትጉውን አንባቢ ማበረታታቱን ነው እኛ እምንመኘው፡፡ ዕይታችን ከአፍንጫችን ስር እንዳይሆን፣ሩቅ-አሳቢነቱን ረዥም-ተጓዥነትን እንለምድ ዘንድ ይረዳናልና ነው፡፡ ደግሞም ደራሲዋ ለምን ረዥሙን ሀሳቧን ትሸምልለው፣ ያፈተታትን ያህል እንድትፅፍ ነፃነቷን ማጎናፀፍ አንድም ለጋስነት ነው!!
የተረሳ ወራሽ- 506 ገፅ ነው ብያለሁ፡፡ ያውም ጥቅጥቅ ባለ ቀለም፡፡ ውስጡ ሲገቡ ግን የታሪኩ ፍሰት ገፁን ያሳጥረዋል ለማለት ይቻላል፡፡
የታሪኩ መቼት -በ1966 አካባቢ ጅጅጋን ፣ ድሬድዋን፣ ደሴን፣ አዲሳባንና አሰበ ተፈሪን ያካለለ ነው፡፡
ታሪኩ - እስከ ሶስተኛው ሚሊንየም መባቻ የሚዘልቅ ነው፡፡
ድርጊቱ- ዘመኑን ፊትና ኋላ የሚያስቃኝ ነው፡፡
በሴራውና በግጭት አፈጣጠር ረገድ፤
የትውልድን አለመተዋወቅ፣ በማንነት አለመረዳዳት (አባት-ልጅን፣ልጅ አባትን፣ዘመድ ዘመድን፣ ዘመነኛ ዘመነኛን ፣… ከሀገር ውስጥ እስከ ዳያስፖራ ወዘተ..) የሚያጠነጥን ነው፡፡ በጅጅጋና አሰበ ተፈሪ ወጣቶች እልቂት ውስጥ የተከሰተውን፤ ስደት፣ ያለ ወላጅ መቅረት፣ አድራሻ መጥፋት፣ ትዳርና ቤተሰብ መፍረስ፣ በትውልድ ላይ የደረሰ ድቀት፣ የሙያና የስራ ስሜት - ዕጦት (frustration) ወዘተ ያካተተ ነው፡፡ በአጠቃላይ ትውልዱ የከፈለውን መስዋዕትነት የሚነግረን ነው፡፡
ደራሲዋ ገፀ-ባህሪያቷን፤ከዚያ ምስቅልቅል ዘመን በተረፉ ባለታሪኮች መልክ ስላ፤ ከተሪፈ - ህይወታቸው ጋር አሰናስላ ነው ያቀረበቻቸው፡፡ ይሆናል የተባለው ሳይሆን፣ አይሆንም የተባለው ሆኖ ያለበት ዘመን የጣለባቸውን አሻራ የሚያሳዩ ገፀባህሪያት ናቸው፡፡ በዝርዝር ወደኋላ ላይ እናያቸዋለን፡፡
መፅሃፉ አንኳር ጭብጡ ፍለጋ ነው፡፡ የልጅ ፍለጋ፣የአባት ፍለጋ፣የስራ ፍለጋ፡፡ የትውልድ ፍለጋ፡፡ የማንነት ፍለጋ፡፡ በዋናነትም የትምህርት ፍለጋ፡፡
መፅሃፉ በአንኳር መፍትሄ - ጭብጡ ይቅርታ መደራረግን አበክሮ ያሳያል፡፡ ደራሲዋ በአፃፃፍ ስልቷ አልፎ አልፎ በምልሰት-ዘዴ ትጠቀም እንጂ አንፃራዊ አውታር (parallel dimension) ማለትም ባለታሪኮቹ በየምዕራፋቸው የየራሳቸውን መንገድ እየተጓዙ ልብ እንዲያንጠለጥሉ የማድረግን ዘዴ መርጣለች። ትስስሩ፣ ግጭቱም ሆነ ፍፃሜ - ክረቱ ወደ ኋላ ምዕራፎቹን ስታዋህዳቸው የምናይበት ዓይነት ነው፡፡
ቋንቋዋ ቀላልና ግልፅ ነው፡፡
የታሪኩ መሪ ገፀ-ባህሪ አንዲት በስርዓቱ አሰቃቂ የግድያ ተግባር ወላጆቿን ያጣች ልጅ ናት፡፡ አያሌ፤ ስቃይ እንደደረሰባትና በጥንካሬና በፅናቷ ሁሉን ተቋቁማ እንዴት ለአዎንታዊ ፍሬ እንደምትበቃ እንገነዘባለን፡፡ የመከራ ዘመን ምርት ነውና የሀዘን ተውኔቱ ይበዛል፡፡ አልፎ አልፎ የድርጊቶች መወሳሰብና የገፀ-ባህሪያት ብዛት ቢኖር፤ ለአወዛጋቢነቱ አስተዋፅኦ በአረገበት አቅጣጫ ካየነው ገንቢ ውስብስብነት ነው፡፡
“የተረሳ ወራሽ” ከአማርኛ ትውልድ ተኮር መፃህፍት አንፃር ሳየው የቆንጂት ብርሃነን “ምርኮኛ” የሚያስታውሰኝ ሲሆን፤ ከእንግሊዝኛ ክላሲክ መፃህፍት ደግሞ the miserables (les miserables) ያስታውሰኛል፡፡
ቀጥሎ የመፅሃፉን ብልት ብልት አካላት እናስተውላለን፡፡
ሁለት ጥቅሶችን እንውሰድ፡-
“ልመና ከረሃብ የበለጠ እንደሚጠብስ አታውቅም?!...
ረሃብ የሚጠብሰው ወደን ነው፡፡ ልመና ግን የለማኙን ፊት ፣ህሊና፣ሰብዓዊ ክብርና ዜግነቱን ጭምር ነውኮ የሚለበልበው፡፡ እስቲ ከልብ ሆናችሁ አስቡት ልጆቼ! በእርዳታና በልመና መኖር በጠላት ተሸንፎ ከመማረክና ከመሞት የበለጠ ውርደት አይደለም? ጠላት፤ ተይዞ የማያውቅ እጃችንን ለምፅዋት መዘርጋት፤ ከውርደትም በላይ ሞት አይደለም? ልመናው በሚያሳድርብን ሃፍረት የሚቀጨው አንገታችን የፈረንጆች መርገጫ መደላድል መሆኑ አያስቆጫችሁም?...”
* * * (ገፅ 416)
… ስላለፈው መጥፎ ድርጊት ይቅር ተባብሎና ያለፈው አልፏል ብሎ፣ብሄራዊ ስሜት በውስጡ ማስረፅ የቻለ ትውልድ ነው አገሩንም ትውልዱንና እራሱንም ከድህነት ነፃ ማውጣት የሚችለው” ገፅ 382)
ይቀጥላል

Published in ጥበብ
Saturday, 27 July 2013 14:26

የአፍታ ወግ ከአሚና ጋር

ባለፈው ሳምንት ጠዋት ሁለት ሰዓት አካባቢ ከቤቴ ስወጣ፣ አካባቢውን ሙዚቃዊ ለዛ ባለው ዜማቸው ካደመቁት ላሊበላዎች መካከል ከአንዷ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠምን፡፡ ድሮ ድሮ ላሊበላዎች በሌሊት በየሰፈሩ ተዘዋውረው የደንቡን አድርሰው ሳይታዩ ነበር ወደ መጡበት የሚመለሱት፡፡ ዛሬ ግን ከተማውን ለመዱ መሰለኝ እስከ እኩለ ቀን ድረስ በየሰፈሩ ሲዘዋወሩ ይታያሉ፡፡ አዋቂዎች፣ ህፃናት፣ ወንዶች፣ ሴቶች… እድሜዋ በአርባዎቹ መጀመሪያ ላይ እንደሆነ የነገረችኝ አበበች ጎበና፤ ሳቂታና ተጫዋች ናት፡፡ ለአፍታ እንዲህ አውግተናል -


የት ነው አገርሽ ?
ጎጃም ምድር፣ ደጀን ከምትባል ከተማ አካባቢ ታለ መንደር፣ ዓባይ ሸጥ ሸጡን ይዘን ነው የምንኖር.. ዋናው ስረ መሰረታችን ግን ወሎ ላሊበላ ነው፡፡
ምንድን ነው የምትባሉት ?
እዚህ በሽዋ “ላሊበላ” ነው የሚሉን፤ እኛ አካባቢ ያልሽ እንደሆነ ‹‹አሚና›› ነው የምንባል፡፡
/እጄን አየት አድርጋ/ልትፅፊኝ ነው----.በቴፕሽ የምትቀጂኝ ----
አዎ፡፡ በጋዜጣ ላይ አወጣሻለሁ፡፡ ፎቶም አነሳሻለሁ፡፡
የምጠቅምሽ ከሆነ ምን ችግር አለው፡፡ ልማድ የለኝም--- እንዳላሳስትሽ ---- ስትቀርጪው በወጉ እንድሆን አስረጅኝ፡፡ መቼም የከተማ ሰው ብልሃት አያጣውም ብዬ ነው፡፡
ላሊበላነት/አሚናነት ትምህርት ያስፈልገዋል?
ተማሪ ቤት ተገብቶ ማለትሽ ነው፡፡
ተማሪ ቤት ባይሆንም-----
ጉሮሮዋችንም ሆነ ግጥሙ የራሳችን ነው፡፡ ደሞ ምን ትምህርት የሚሻው ሆነና ማቀንቀን፣ መጫወት፣ መዝፈን---እንኳን እኔ አዋቂትዋ፣ ጉብላሊቱ ሁል እንዴት ያለ ድምፅ አለው መሰለሽ፡፡ ለእኛ ድምፃችን ከዘራችን ያመጣነው ነው፡፡ ይሄን ደሞ ሞያ ብለሽው----አሁን አንቺን አግኝሻለሁ ብዬ አላለምኩም ግን እንደዚህ ብዬ ብገጥምልሽ ምን ሞያ--- ትምህርት አለው፡፡
እመቤትዬ የእኔ መልከ መልካም
በእጅዋ ስራን እንጂ በአፏ ሰው አትነካም
አምላክ አንቺን ሰራ ተጨንቆ ተጠቦ
አንግትዋ የሚመስለው የእንግሊዝ ብርጪቆ
የእኔ ቆንጅትዬ እመቤትየዋ
ፃፍ ፃፍ አድርጊኝ እንደወረቀቱ
አንቺ አይደለሽም ወይ የመስራቤት ጌጡ
አንቺማ ተምረሽ ብዙ አገር አይተሸ
ደግሞ እንደማይሞች ታደርጊናለሽ
የእኔ ቆንጅትዬ እመቤትዬን
የእኔ ሴት ወይዘሮ የእኔ ስመ መልካም
በእጅዋ ስራን እንጂ በአፍዋ ሰው አትነካም
ሱሪዋን አጥልቃ ስትል ሞድ ሞድ
ሹጉጥ ያስታጠቅዋት ትመስላለች ወንድ
ለአንቺ ነበር እንጂ ሱሪ ማሰፋት
እንደ አዳል ጎረምሳ አትወድም ጥቃት---
ይቅርታ ላቋርጥሽ---
ምን አለ አቋርጪኝ እንጂ---ኋላ እቀጥላለሁ፡፡
ላሊበላ/አሚና ድሮ ቀረ ይባላል፡፡ ትስማሚያለሽ?
እንዴት---እነማን ናቸው የሚሉን---በደንብ ያውቁናል ብለሽ ነው…
ድሮ በማለዳ በየቤቱ ተዟዙረው ለምነው፣ ሳይነጋባቸው ለሰው ሳይታዩ ወደ መጡበት ይሄዳሉ፤ ወደሚለምኑበት ቤተሰብ ሲሄዱም የሰውየውን ስማና ማንነት አጥንተው ነው ይባላል---
እሱማ ዛሬስ መቼ ጠፋን ብለሽ ነው እነየዋ፡፡ ልክ ነው--- ፊት ፊት ሌባውም ቀማኛውም የለም ነበር፡፡ አሁን አሁን ግን የእኛን የአባቶቻችንን ታሪክና ስረ መሰረት ተከትለን እንሂድ ብንል--- ለምሳሌ እኔ እዚህ እናንተ ሰፈር መጥቼ አይደል የተገናኘን --- የምለምንበትን ቤት ባለቤት ስም አጥመ---ታሪክ ማጥናት አለብን፡፡ የሰውየውን ማንነት ብቻ ሳይሆን የልጆቹን ስም---
ስንት ልጆች እንዳሉትም ጭምር ?
እራ! ደግሞ ልጅማ እንዴት ይቆጠራል--- ነውር ነው በኛ አገር፡፡ ‹‹ስንት ልጅ አለው›› ብሎ መጠየቅ ግም ነው፡፡ ሴት፣ ወንድ፣ ልጆች፤ ከብት፣ ሃብት፣ ንብረት፣ ዝና፣ ጀግንነት፣ ብልሃቱን..እንደዚያ ነው የሚጠየቅ፡፡ ስሙን አጥንተን ወፉ ‹‹ጪጪጪጪ..›› ከማለቱ በፊት ከደጁ እንደርሳለን ---- ‹‹እንዲህ ነህ፣ እንዲያ ነህ----ጀግናው ጠንበለሉ---›› እያልን መለመን ነው፡፡ ደሞም አዳራችን እዚያው አካባቢ ካለ ጫካ ‹‹የመሸበት አዳሪ›› ብለን አጎራባቹን እንጠይቃለን---- እምቢ የሚለን የለ----እንደዛ ነበር፡፡
እዚህ አዲስ አበባ ነው ክፍለ ሃገር ?
አዲስ አበባ? እንኳን ሰው ሊያሳድሩ በቅጡም አይሸልሙ፡፡ ሁሉ ሱሪ ታጣቂ ሯጪ..ማን ዞርስ ብሎ ያይሻል አያ!!
በገጠር ሴትዋ እና ወንዱ እየተቀባበሉ ነበር የሚገጥሙት፡፡ አንቺ ግን ብቻሽን ነሽ---
እሱማ ነበር--- ዛሬ ዛሬ ኑሮም ከበደና ባለቤቴን ‹‹ምነ አንተም ብቻህን፤ እኔም ብቻዬን የማንለምን..›› ብለን ወጣነ ከአገራችን፡፡ እሱ ዘንድሮ ቢቸና ሂድዋል፡፡ እኔ ከልጄ ጋር እዚህ አዲስ አበባ መጣሁ።
ልጅሽም እንዳንቺ ላሊበላ/አሚና ናት?
ዋ!! ምን ታደርገዋለች የዘርዋ አይደል፡፡ ትልመደው እንጂ፡፡ አምና ጀምሮ አብራኝ ነው የምትወጣ፡፡ ያችውልሽ /በእጅዋ እየጠቆመችኝ/ ድምፅዋን መስማት ከፈለግሽ ሂጂ፡፡
እሰማታለሁ..እኔ የምልሽ በስንት ዓመትሽ ነው አሚናነት የጀመርሽው ?
እረ አልቆጠርኩትም፡፡ በጣም ልጅ እያለሁ ጀምሮ ነው፡፡ ደጀን፣ ማርቆስ፣ ባህርዳር፣ ፍኖተ ሠላም፣ አዲስ አበባ፣ ፍቼ፣ ቢቸና፣ ደብረወርቅ..ብዙ አገር ሂጃለሁ..በአመት ሁለት ጊዜ መሆኑ ነው…መለመን ግዳችን ነው፡፡ በዚህ ወቅት ቀየው ሙሉ ነቅሎ በየሃገሩ የደንቡን ያደርሳል፡፡
ቀዬው ባዶውን መክረሙ ነዋ --- ማን ያርሳል?-
ክረምት ነው ግን እርሻም ብዙ የለን--- ግን ደካሞች/አረጋዊያን፣ ህፃናት፣ ዘልቀው ሌላ አገር መሄድ እማይችሉት ባድማውን ይጠብቃሉ፡፡ ደሞ እሽም አይሉንም--- ሃምሌንና ጥቅምትን እንቀመጥ ብንል.. ምክንይቱም የዓመሉን ካላደረስን ወረርሽኙ----ህመሙ ስቃዩ ስለሚበረታብን ተያይዘን ከማለቃችን በፊት----በየአገሩ እንጓዛለን፡፡ ያልሽ እንደሆነ ደሞ ስረ መሰረቱ ዘራችን ሁላ ሃምሌ ከከተመ ጀምሮና ከዚያም ጥቅምት ሲጠባ ---- የእኛ አያቶች አባቶች የወጉን ያደርሳሉ፡፡ ከነሱ የወረስነው ነው፡፡
ባለቤትሽ፣ ልጅሽና አንቺ .ወደ ቤት ስትመለሱ በአንድ ላይ ስንት ብር ታጠራቅማላችሁ?
እዚሁ አይደል የሚያልቅ--- ከቁጥርም አይገባም---/ሳቅ/ ግን ከአምስት መቶ እስከ አምስት ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ ምን ዋጋ አለው---- ብክን ብሎ አይደል የሚያልቅ፡፡
ከመሃከላችሁ ይሄን ዜማችሁን በካሴት ያወጣ የለም እንዴ ?
/ሳቅ/ እረ የለም፡፡ ምኑን አመጣሽው!! እኛ ‹‹የደንቡን እንበል›› ብለን እንጂ ድምፃችን ጥሩ ነው ብለሽ ነው፡፡ እንደሱማ ከሆነ እኮ ሁሉም ሊያወጣ ይችላል፡፡
ከልጅ እስከ አዋቂ አሚና ነው፡፡ ከደጀን ከተማ ጀርባ አባይ ወንዝ ሸጡን ውስጥ ለውስጥ ይዘን እንወርድና ከሸለቆ ሸለቆ ድምፃችን ሲሰማ፣ ሲያቀነቅን፣ እንዴት ያስገመግማል መሰለሽ፡፡ ቅላፂያቸው ማማሩ ---ግን አንዳንድ ጊዜ በመኪና ተሰቅለን ከአንዱ አንዱ አገር ስንሄድ በመኪናው ውስጥ ቴፑ ሲዘፍን እሰማና፣ እየዘፈኑ ነው እያላገጡ---እላለሁ---ወትሮም ግጥሙ አይሰማ--- ከበሮው ብቻ ድም ድም---ይላል፡፡ በኛ ያልሽ እንደሆን---.ግን አሁን በሬድዮው ክተቱኝ ብል እሽ ሚለኝ አለ/ጠየቀችኝ/
ጥሩ ድምፅ አለኝ ብለሽ ታስቢያለሽ?
እውነት አይደል የጠየቅሽኝ…ድምፄን አስቤው አላውቅም ያውም ለመዝፈን እንጃ..!! ‹‹የደንቡን ላድርስ›› ብዬ ነው፡፡ ያልሽ እንደሆን ደሞ..ሰው እማትዘፍኝ..አሚናነትሽን/ላሊበላነትሽን ትተሽ ይሉኛል፡፡ ‹‹ወዲያ ሂዱ›› እላቸዋለሁ፡፡ እራ አንቺ እሱን ነገር ልሞክረው ብለሽ---.ግን ሳስበው ከዘመዶቼ አንዳቸው ቢሆን ይሄን አጥተውት አልመሰለኝም--- እንዴው ምናምን እርግማን አለው እንደሆን መዝፈን../ንግግርዋን አቋርጣ/
ተሎ ተሎ ብለሽ በቶሎ ሸኝኝ
ወደ ጎረቤትሽ ልመና አለብኝ
የነጪ ጤፍ ገንፎ ይላል ዋጡኝ ዋጡኝ
አንቺን ስመለከት ሌሎች አመለጡኝ
ለአስሩ ብር ነው ወይ እንዲህ ሽር ጉዱ
አባትሽ ይሰጣል በጉን ከነቀንዱ
የጎበዞች እህት አይባል አንድ ሰው
ስጥት ሰጥት ማድረግ አንጀት የሚያደርሰው
በራፉም ይከፈት ሞላው ይሰናዳ
ልክ የለውም አሉ ለዚህ ቤት እንግዳ
ቢያኖርሽ ነው እንጂ እኔስ መለመኔ
እንዳሻ ሁኝል እንዳይባክን አይኔ
/ከጎኔ ቆማ ንግግራችንን ስታዳምጥ የነበረችው እናቴ፣ ጠቀም ያለ ብር አውጥታ አስጨበጠቻት/
የጎበዞች እህት እመቤትየዋ
እግዚአብሄር ይስጥልን እግዚአብሄር ይስጥልን
ተባረኪልን ውለሽ ግቢልን
ውሎ ለመግባት ሰርቶ ለመብላት አይንፈግብን
የጌታን መንገድ የፅድቅን መንገድ ይስጥልን
አመት አመቱን ያድርስልን ውለሽ ግቢልን
ገበያውን ጥጋብ አገሩን አማን ያድርግልን
የልጆችሽን አበባ ያሳይሽ
መጠን አንጣሽ
ምቀኛሽን እንደባልቴት ጥርስ ያርግፍልሽ፡፡

Published in ጥበብ
Page 1 of 13