Administrator

Administrator

• ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን የተመዘገበ ሰርተፊኬት ተሰጥቷል
የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን፤ የ2016 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹን የ3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠናና ዓለማቀፍ የፕሮ ቴኳንዶ የመጀመሪያ ራስን መከላከል ስልጠና ተሳታፊዎች ትላንት መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም በወወክማ አዳራሽ አስመረቀ፡፡
ሥልጠናው ከአዲስ አበባና ከክልሎች ለተውጣጡ 28 ተሳታፊዎች ለ15 ቀናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፤ ተመራቂዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦንላይን የተመዘገበ ሰርተፊኬት ማግኘታቸው ታውቋል፡፡
 
ከሰልጣኞቹ መካከል 19 ያህሉ ሥልጠናውን በተሟላ መልኩ አልፈዋል የተባለ ሲሆን ሁለቱ አለማለፋቸው ነው የተነገረው፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንደተነገረው፤ ሳኦል ኹነቶች ለአራት ሰልጣኞች የስፖርት ማዘውተሪያ አዳራሽ ያመቻቸ ሲሆን፤ በቅርቡ ፒያሳ አካባቢ በኮሪደር ልማት ሳቢያ የስፖርት ማዘውተሪያ ለፈረሰበት አንድ ወጣት በቀጣይ ቦታ ለማመቻችት ቃል ተገብቶለታል።
የአዲስ አበባ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ማስተር ሃይለየሱስ ፍስሃ በመርሐግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ የተሰጠው 3ኛ ደረጃ የዳኝነት ሥልጠና፣ ሌጀንድ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ የሠጠው የመጀመሪያ ኮርስ ነው፡፡
የሌጀንድ ኢንተርናሽናል ፕሮ ቴኳንዶ አሶሴሽን የአፍሪካ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ የበላይ ጠባቂ ግራንድ ማስተር (ፒ ኤች ዲ በማርሻል አርት ሳይንስ) ሄኖክ ግርማ፣ለተመራቂዎቹ ሰልጣኞች ሽልማት ሰጥተዋል፡፡
 
ይህ በዚህ እንዳለ፣ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ከሳኦል ኩነቶች ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ 2016/2024 ኦፕን ቶርናመንት፣ ከግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄድ ሲሆን፤ ውድድሩን አስመልክቶ ነገ ቅዳሜ በአራት ኪሎ ስፖ/ትም/ሥልጠና ማዕከል በሚገኘው ትልቁ ጅምናዚየም ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡

ይህ ‹‹ሆኖ መገኘት፤ እኔም ኃይሌ ነኝ›› የተሰኘ መጽሐፍ በኢትዮጵያ የድርጅቶች አገልግሎት ልህቀትን ለማሳደግ በማሰብ የተደረገ የእውቀት ሽግግር ጥረት ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ልህቀት የሚደረግን ጉዞ የሚያግዝ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም መንገድንም የሚያመላክት እንጅ፡፡

‹‹ሆኖ መገኘት›› ማዕከል የሚያደርገው የአገልግሎት ልህቀት ከፍ እያለ በተግባር እየታየበት ያለውን ኃይሌ ሪሶርቶችና ሆቴሎች ሲሆን የሥረ ነገር ማጠንጠኛውም ራሱ ሆኖ መገኘትን ያሳዬን ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ነው፡፡ መጽሐፉ የሥራ ባህል ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን አጽኦት የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የስራ ባህል ምንነትን እና ተግባራትን ከመቅረጽ አንጻር ያለውን ሚና ያትታል፡፡

ሆን ተብሎ ቢሆንም እና ባይሆንም ባህል እያንዳንዱ ከባቢ ላይ ተጽዕኖውን ያሳርፋል፤ የግለሰቦች ይሁን የድርጅቶችንም ግብር እና ምግባር ይቀርጻል፡፡ ይህን ሀቅ ስንቅ አድርጎ በመያዝ ኃይሌ ሪሶርቶችና ሆቴሎች  ከቃል በላይ የሆነ በተግባርም የተገለጸ አዲስ ባህልን ለመፍጠር ችሏል፡፡

በዚህ መጽሐፍ የምንነግራችሁ ንድፈ ሐሳብ አይደለም፤ ይልቁንም እየተኖረ ያለ እና በተግባር የተገለጸን እውቀት እንጅ፡፡ ይህም እውቀት የጋራ የሆነ እንጅ ለጥቂቱ ተገልጦ ብዙኃኑ ያላገኙት ትንቢት አይደለም፡፡ ለውጡም ከተግባርዎ፣ ከምግባርዎ፣ ከሥነ ልቦናዎም ዘንዳ የሚታጨድ እሸት ነው፡፡ ስሊዚህም እንዲህ እንላለን ‹‹ማንም ቢሆን ልክ እንደ ኃይሌ ማሰብን መልመድን እና መሥራትን ይችላል›› ስለዚህም ‹‹እኔም ኃይሌ ነኝ›› ፍልስፍና የስኬት ቁልፍ ለእርስዎ እነሆ!

“አንዲት እናት ልጆቿን ብቻዋን ታሳድጋለች፡፡ የአስተዳደግ ዘይቤዋ ከሌሎች ወላጆች ለየት ይላል፡፡ ልጆቿ ከሰፈር ልጆች ጋር ተቀላቅለው ሲጫወቱ አይቼ አላውቅምና ሁሌም ጥያቄ ይፈጥርብኝ ነበር፡፡ ልጆችሽ ከእድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲጫወቱ አይቼ አላውቅም አልኳት፡፡
“በልጅነቴ ብቸኛ ወንድሜን ያጣሁት ሰፈር ውስጥ በተወረወረ ድንጋይ ነው” ወዲያውም ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡
“በጣም አዝናለሁ፤ መጠየቅ አልነበረብኝም” አልኳት፡፡
“እነዚህን ብርቅዬ ልጆች እንደ ወንድሜ ማጣት አልፈልግም፡፡ ውጭ እንደ ሌሎች ልጆች ቢጫወቱ ይሞቱብኛል ብዬ እፈራለሁ፡፡” አለችኝ::
ህክምና ያላገኘ የልጅነት ጠባሳ ጊዜ ጠብቆ በትዳር ህይወትም ይገለጣ:ል፡፡”
**
በደራሲ ብርሃኑ በላቸው አሰፋ የተዘጋጀው “ክቡር ልጆች፣ የልጆች ስነ ልቦና ለመገንባት እና የስሜት ስብራት ለመጠገን የሚረዱ ቁልፍ መንገዶች ” የተሰኘው መጽሐፍ፤ የፊታችን እሁድ መጋቢት 29 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ሳር ቤት በሚገኘው በኢንተርናሽናል ኢቫንጀሊካል ቤተ ክርስቲያን እንደሚመረቅ ደራሲው ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ (ለመግቢያ የተጠቀምንበት ጽሁፍም ከመጽሐፉ የተቀነጨበ ነው፡፡)
መጽሐፉ፤ በልጆች ስነ ልቦና ላይ ጥናትን መሰረት ያደረገና ሀገራዊ ለዛ ያለው እውነተኛ ታሪኮችን የሚያስቃኝ ሲሆን፤ በተለያየ ተግዳሮት ውስጥ ለሚገኙ ልጆች የመፍትሄ ሃሳብ ይዞ መቅረቡም ተጠቁሟል፡፡ በዋናነትም ልጆች የሚስተዋልባቸውን የስነ ልቦና ጫና እና የስሜት ስብራት የሚተነትን ሲሆን፤ በጥናት ላይ የተደገፈ የመፍትሄ ሃሳብን በተጨባጭ እንደሚያመላክትም ተነግሯል፡፡
“ክቡር ልጆች“ በአማርኛና አፋን ኦሮሞ ተዘጋጅቶ የተቀረበ ሲሆን፤ በዋናነትም ለትዳር ለሚዘጋጁ፣ ለወላጆች፣ ለመምህራን፣ እንዲሁም በልጆች ላይ ለሚሰሩ ባለሙያዎችና ለሌሎችም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ደራሲው በሆሊስቲክ ቻይልድ ዴቨሎፕመንት ሁለተኛ ዲግሪ ፣ በሶሽዮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪና በስነፅሑፍና ቋንቋ ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ሲሆን፤ ከልጆችና ወጣቶች እድገት ጋር በተያያዘ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ በተጋባዥ እንግድነት እየቀረበ ሙያዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ይታወቃል፡፡
 

ጠ/ሚኒስትሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ ጥሪ አቀረቡ

”60 ፓርቲዎች ሆናችሁ ልንደግፋችሁ ይቸግረናል“

ለሁለት ወር ግድም ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም በመቶዎች ከሚቆጠሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አመራሮች  ጋር በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የፓርቲ አመራሮቹ በውይይቱ ላይ ለጠ/ሚኒስትሩ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል የሰላምና ጸጥታ ችግር፣ የህግ የበላይነት አለመኖር፣ የፖለቲካ  ምህዳር መጥበብ፣ የሜጋ ፕሮጀክቶች ተጠያቂነትና  የዜጎች መፈናቀል ጉዳዮች ይጠቀሳሉ፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት ሃላፊን ጨምሮ አንዳንድ የፓርቲ አመራሮች የቢሮ፣ የአዳራሽና የፋይናንስ ችግር  እንዳለባቸው ጠቅሰው ላነሱት ጥያቄ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

እኛ እንደ ፓርቲ ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች እናያለን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ያንን ለማድረግ ግን ለፓርቲዎቹ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል - አሁን ያሉት 70 የሚደርሱ ፓርቲዎች 4 ወይም 5 ሆነው ሰብሰብ እንዲሉ፡፡

“አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ 66 ወይም 68 ገደማ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ለ68 ሊቀ መንበር ቦታ የለንም፤ ለ68 ሊቀ መንበር ቢሮ የለንም፤ 2-3-4-5 ሆናችሁ ብትሰባሰቡ --- ከብልጽግና ጋር 5 ወይም 6 ፓርቲ ብንሆን አንቸገርም ነበር፡፡”  ያሉት ዐቢይ፤ ”ለምሳሌ ዛሬ በውይይቱ ላይ ከእያንዳንዱ ፓርቲ አምስት አምስት ሰው ቢወከል፣ 25ቱም ሰዎች መናገር ይችሉ ነበር” በማለት አስረድተዋል፡፡

 “ስንበዛ መበተን ብቻ ሳይሆን በዚያው መጠን አቅማችንም ውስን ይሆናል፤” ሲሉም አክለዋል፡፡



ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ ውይይቱን የቋጩትም  የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ እንዲሉ በመማጸን ነበር፡፡

“እባካችሁ ወደ 4 ወይም 5 ፓርቲ ሰብሰብ በሉ፡፡ ግዴለም ይጠቅማችኋል፡፡ እንደዚያ ከሆናችሁ ፓርላማውም ይከፈታል፤ የምታስቡትም ሥልጣን ይመጣል፡፡ በዋና ዋና ጉዳይ ከተግባባችሁ በጋራ ሆናችሁ ብትታገሉ---አትጠራጠሩ ፓርላማውንም እንከፋፈለዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

“እናንተ ግን አሁን 60 ናችሁ፤ ይሄ ለህዝብም ያስቸግራል” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”እኔ እንኳን ስማችሁን አላውቀውም፤እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ--” ሲሉም ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ብለው እንዲታገሉ መክረዋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ከዚህ ቀደምም የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በጋራ እንዲታገሉ ጥሪ አቅርበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ ከጃፓን መንግስት የተበረከተላቸውን የወርቅ ጨረር ያለውን ኒሻን  ሽልማታቸውን ተረከቡ።
 
ይህ እውቅናና ሽልማት እኤአ ከ1875 ጀምሮ ለውጭ ሃገር ዜጎች በጃፓን መንግስት የሚሰጥ አንጋፋና ክብር ያለዉ ነው::  ከኢትዮጵያ የወርቅ ጨረር ያለው ኒሻን ሽልማት ከጃፓን መንግስት ሲሰጥ ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የመጀመሪያዋ ናቸው። በጃፓን እና በኢትዮጵያ መካከል በስፖርት ዲፕሎማሲ እና ልውውጥ ዘርፍ ላበረከቱት የላቀ አስተዋፅዖ ፣ በሌሎች ሀገራት እና አካባቢዎች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማሳደግ፣ ለአትሌቲክስ እድገት ፣ ለአገር ሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና በመስጠት በዓለም አቀፍ መስኮች የላቀ ስኬት ምክንያት ሽልማቱን አግኝተዋል። ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ሽልማታቸውን ዛሬ መጋቢት 24/2026 በኢትዮጵያ ከጃፓን አምባሳደር  ሚስተር ሺባታ ሂሮኖሪ እጅ ተረክበዋል ።

ጥበበ ተርፋ ማመጫ፤ በሐረር ከተማ በ1941 ዓ.ም ተወለዱ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሐረር መድኃኒዓለም ት/ቤት እንዳጠናቀቁ ወደ አዲስ አበባ ሥነ ጥበብ ት/ቤት (በአሁኑ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት) በመግባት ተመርቀዋል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሥነጥበብ ልምምድ ውስጥ ተዋጽዖአቸው ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ነበረ:: የሥዕል ሥራቸውን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ለዕይታ ያበቁ ሲሆን፣ በሙያው ስምና ዝና ያፈሩ አንጋፋ ሙያተኛ ነበሩ::

አቶ ጥበበ ተርፋ የሥራቸው አቅጣጫ ተወልደው ባደጉበት ሐረር ላይ በማተኮር የትላንቱንና የዛሬውን ገጿን በቀለማት እንቅስቃሴ ይገልጹ ነበረ። አቶ ታዬ ታደሰ ባዘጋጁት የሠዓልያን ታሪክ ውስጥ ጥበበ "የተለያዩ ቴክኒኮችን የሚጠቀሙ ሲሆኑ፤ የሚያደንቁት ግን ኤክስፕሬሽኒዝምን ነው" በማለት መጻፋቸው ይታወሳል::

ሠዓሊ ጥበበ ተርፋ ማመጫ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ሰምተናል:: ለመላው ቤተሰብ፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለአለ_የሥነጥበብ_ት/ቤት ማህበረሰብ፣ ለሙያ ጓዶቻቸውና አድናቂዎቻቸው መጽናናት እንዲሆንላቸው እንመኛለን።

ቀብራቸው ነገ ረቡዕ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በየካ ሚካኤል ቤተክርስትያን ከቀኑ 8:30 የሚፈጸም ይሆናል። ነፍስ ይማር።

(አገኘሁ_አዳነ_ድልነሣሁ)

በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው የ45ኛው ዓለም   አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአምስት ምድቦች ማለትም  8ኪ.ሜ. ከ20 ዓመት በታች  ወንዶች  ፣ 6 ኪ.ሜ. ከ20 ዓመት በታች  ሴቶች  ፣ 4x2 ኪ.ሜ የድብልቅ ሪሌ ሴት/ወንድ  ፣ የ10 ኪ.ሜ. የአዋቂ ሴቶች እና አዋቂ ወንዶች  በተካተቱበት ውድድር ከ51 አገራት  የመጡ 485 የሚሆኑ አትሌቶች ተፎካክረውበታል።  በዚህም ውድድር ኢትዮጵያ በ14 ሴት እና በ14 ወንድ በ28 አትሌቶች የተወከለች ሲሆን በ ሁለት ወርቅ ፣በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከአለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ ውድድሩርን ጨርሳለች ፡፡

ግሪን ዌቭ አሊያንስ ከኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት በዛሬው ዕለት  ረፋዱ ላይ ፈጸመ፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያና የግሪን ዌቭ አሊያንስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ረድኤት ያዘው በባለሥልጣኑ መ/ቤት አዳራሽ ተፈራርመዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ በፊርማ ሥነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በጠ/ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረውን አረንጓዴ ልማት ለማስቀጠል መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የዛሬው ስምምነት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣን መ/ቤቱ  ከመጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የአየር፣ የውሀ፣ የአፈርና የድምጽ  ብክለትን ለመቀነስ የሚያስችል የ6 ወራት ዘመቻ መጀመሩን የገለጹት ወ/ሮ ፍሬነሽ፤ በአጋርነት መሥራት ዘመቻውን ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የግሪን ዌቭ አሊያንስ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ሚኪያስ ነጋሳ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚያከናውናቸው ሥራዎች ሰፊ ከመሆናቸው አንጻር መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አጋርነት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ የተከናወነው ስምምነት የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴውን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚረዳ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት የዓባይ ግድብ 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ያዘጋጀዉን የመታሰቢያ ቴምብር በዓሉን በማስመልከት በተዘጋጀዉ የፓናል ዉይይት መድረክ ላይ ይፋ አደረገ።
የአባይ ግድብ የመታሰቢያ ቴምብሩን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣የዉሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እና የአባይ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በጋራ መርቀዋል።
የመታሰቢያ ቴምብሩ ከዛሬ ጀምሮ ለ192 የአለም አገራት እንደሚሠራጭ ተገልጿል።

የደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ "የዓለማችን ምስጢራት" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ከሰሞኑ ለአንባቢያን ቀርቧል።

ይህ አዲስ መጽሐፍ የፊታችን መጋቢት 28 2016 ዓ.ም በወመዘክር አዳራሽም ይመረቃል ተብሏል።

Page 3 of 700