Administrator

Administrator

   · የቤተ ክህነት የብዙኃን መገናኛ ድርጅት: “ፕሮግራሙን አላውቀውም፤” አለ
        · “የቤተ ክርስቲያኒቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ መጠቀም ስላልቻልን ወደ ሌላ ሔድን”
        · “እያስተማርን መጥተናል፤ እንቀጥላለን፤ልዩ ፈቃድ አይጠበቅብንም፤”
        · “ቅዱስነታቸው፥ የራሳቸውን ፕሮግራም ይጀምሩ፤ብለዋል፤”

      ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከነገ በስቲያ የዘመን መለወጫ ዕለት፣በአሌፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ መደበኛ ሥርጭቱን  እንደሚጀምር ያስታወቀ ሲሆን፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብዙኃን መገናኛ አገልግሎት ድርጅት በበኩሉ፣ “የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩን  አላውቀውም፤” አለ፡፡
ማኅበሩ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ አሜሪካን ሀገር በሚገኘው አሌፍ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የአየር ሰዓት በመግዛት በሳምንት ለ7 ሰዓታት፥ በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋዎች ትምህርተ ወንጌል  ለማስተላለፍ ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ከነገ በስቲያ የመክፈቻ መርሐ ግብሩን እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት፣ ለፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በጻፈው ደብዳቤ፥ ማኅበሩ በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ሥርጭት እንደሚጀምር በድረ ገጹ ቢያስተዋውቅም፣ ድርጅቱ ግን የሰጠው ፈቃድ እንደሌለ ገልጿል፡፡ ቀደም ሲል በተመሳሳይ ጉዳይ ለኢቢኤስ ቴሌቭዥን ጣቢያ በተጻፈው ደብዳቤ፣ በማኅበራትና ቡድኖች ላይ የተላለፈውን እገዳ የሚጥስ አካሔድ እንደሆነም ጠቅሷል፡፡
የድርጅቱ ቦርድ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት ከተወያየ በኋላ የተጻፈው ይኸው ደብዳቤ፤ ጉዳዩን ለፓትርያርኩ ከማሳወቅ ውጭ ሌላ የገለጸው ነገር እንደሌለ ምንጮቹ አስረድተዋል። “ክፈቱም ዝጉም ማለት አንችልም፤የላይኛው አካል ይወስንበት፤” ተብሎ በተደረሰው ስምምነት መሠረት እንደተጻፈ፣ ጉዳዩም በሒደት ላይ እንዳለና ውሳኔ አለማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡
የብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ፣ የጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተ አዲስ አድማስ የጠየቃቸው የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ፤ በመረጃ ደረጃ ከመስማት በቀር ከየትኛውም ወገን በይፋ ለማኅበሩ የደረሰ ክልከላ ወይም እግድ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡
“ቅዱስ ሲኖዶስ ለማኅበራችን አስቀድሞ በሰጠው እውቅና፣ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች ለትውልዱ የማስተላለፍ ሓላፊነት አለብን፤” ያሉት አቶ ተስፋዬ፣ “የቴሌቪዥን ሥርጭቱም ከመገናኛ ዘዴዎቹ አንዱ በመሆኑ በደንቡ የተፈቀደ ነው፤ እያስተማርን መጥተናል፤ አሁንም እንቀጥላለን፤ ልዩ ፈቃድ አይጠበቅብንም፤ በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ዕውቅና ያለን ማኅበር ነን፤” ብለዋል፡፡
ማኅበሩ ባለፉት 25 ዓመታት በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በራድዮና በመሳሰሉት የመገናኛ ዘዴዎች የሃይማኖቱን አስተምህሮ ሲያስተላለፍ እንደቆየና የዚሁ አካል ተደርጎ የሚታየው የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩም የተለየ ተግባር እንደማይሆን አስረድተዋል - አቶ ተስፋዬ፡፡
ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱን የቴሌቪዥን ጣቢያ ለመጠቀም እስካለፈው ግንቦት ድረስ የአየር ሰዓት በተደጋጋሚ ጠይቆ ምላሽ እንዳልተሰጠው የገለጹት ዋና ጸሐፊው፣ በርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ላይ በቀረበበት ወቅት፣ ፓትርያርኩ፤ “አቅም ስላላቸው የራሳቸውን ጣቢያ መክፈት ይችላሉ፤” ማለታቸውን ተናግረዋል።
በአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ መርሐ ግብሩን ለመጀመር የተነሳሳውም ከዚህ በኋላ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በዚህም መሠረት፣ በዘመን መለወጫ በሚጀምረው የማኅበሩን የቴሌቭዥን መርሐ ግብር ላይ የሚቀርቡ ተቃውሞዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም፤ ብለዋል።
መቀመጫውን በአሜሪካ ካደረገውና በባህላዊ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ከሚያተኩረው የአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋራ መዋዋሉን በተመለከተ፣ “ለምን ደግማችሁ ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ አላሳወቃችሁም?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “ተስፋችን የነበረው ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋራ አብረን እንሠራለን፤ ኃይል እንሆናለን ብለን ነበር፣ አልሆነም፤ ወትሮም መተዳደርያ ደንቡ ማኅበሩ እንዲሠራ ይፈቅድለታል፤ ቅዱስነታቸውም፣ የራሳቸውን መጀመር ይችላሉ፤ እያሉ ሌላ ፈቃድ መጠየቅ አይጠበቅብንም፤” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ይህም ሆኖ፣ ማኅበሩ፣ ከብዙኃን መገናኛ ድርጅቱ የጠየቀው የአየር ሰዓት ቢፈቀድለት፣አሁንም ተመልሶ ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ማኅበሩ፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የዘመኑን ትውልድ ለማስተማር የሚያስችል ሞያዊ አቅምና ዝግጅት እንዳለው አቶ ተስፋዬ ገልጸው፣ “የቤተ ክርስቲያን አቅም ነው፤ ልትጠቀምበት ይገባል፤” ሲሉ ሞግተዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከሚነሣው የተደራሽነት ጥያቄና ካለው ክፍተት አንጻርም፣ አንድ ብቻ ሳይሆን ብዙ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንደሚያስፈልጓትም አስገንዝበዋል፡፡  
የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የብዙኃን መገናኛ ድርጅት በተቋቋመበት ደንብ፣ በማንኛውም መልክ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የሚሠራጩ ሚዲያዎችን የማስተዳደርና ፈቃድ የመስጠት፤ የአየር ሰዓት ኪራይ ለሚጠይቁትም ውል የመዋዋል ሥልጣን እንዳለው የጠቀሱት የቦርዱ ምንጮች፤ ፓትርያርኩ በቅዱስ ሲኖዶሱ ላይ የሰጡት ምላሽ እንደ ውሳኔ አልያም ፈቃድ መስጫ ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል ይከራከራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም፣ ማኅበሩ በኢቢኤስ ያስተላልፍ የነበረው ፕሮግራም መታገዱን ያስታወሱት ምንጮች፤በተመሳሳይ ከነገ በስቲያ በአሌፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የማኅበሩ መርሐ ግብርም እንዳይሰራጭ ሊታገድ  እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

      ከኢህአዴግ ጋር በድርድር ላይ ከሚገኙ ተቃዋሚዎች መካከል መኢአድ እና ኢዴፓን ጨምሮ 12 ፓርቲዎች በጋራ ተወካዮች ለመደራደር
ተስማምተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ አንድ ዓይነት የመደራደሪያ አጀንዳዎችን በጋራ ቀርፀው ለአደራዳሪው አካል ማስገባታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ለድርድሩ በጋራ ለመቅረብ የተስማሙት ፓርቲዎች፡- የመላው ኢትዮጵያውያን አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ፣ አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ፣ የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (ኢትፓ)፣ የወለኔ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ (ኢድአን)፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን)፣ የመላ ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ)፣መሆናቸው ታውቋል፡፡ ፓርቲዎቹን በተደራዳሪነት እንዲወክሉም የመኢአድ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ፣ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ሊቀ መንበር አቶ ትዕግስቱ
አወሉ ተመርጠዋል፡፡ ድርድሩ ላይ የተበታተነ ሀሳብ ይዞ ከመቅረብ ይልቅ በአንድ አላማና አቋም ገዥውን ፓርቲ ለመገዳደር በማሰብ ፓርቲዎቹ በጋራ ለመቅረብ መወሠናቸውን አስታውቀዋል፡፡

  አንጋፋው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት፤ ከጀርመኑ ሙልባወር ኩባንያ ጋር በመተባበር የስማርት ካርድ ህትመት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡
ማተሚያ ቤቱ ከዚህ ቀደም ሚስጥራዊ ህትመቶችን በወረቀትና በቀለም ቴክኖሎጂ ያከናውን እንደነበር የጠቆሙት የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተካ አባዲ፤ በዓለማቀፍ ደረጃ በአብዛኛው ሚስጥራዊ ህትመቶች ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተሸጋገሩ በመሆኑ፣ ማተሚያ ድርጅቱ ራሱን ለማዘመን ቴክኖሎጂውን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት፣ የስማርት ካርድ ምርቶችን ለመጀመር ማቀዱን አስታውቀዋል፡፡
በዚህ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ በውጪ ሀገራት በስማርት ካርድ ቴክኖሎጂ የሚታተሙ የባንክ ገንዘብ ማውጫ ካርዶች፣ ሲም ካርዶች፣ የመታወቂያ ካርድ፣ ፓስፖርት የመሳሰሉትን በሀገር ቤት ለማተም ያስችላል ተብሏል፡፡
የማተሚያ ቤቱ አመታዊ ትርፍ ከነበረበት 8 ሚ. ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር ማደጉንና ትርፋማ መሆኑን ያወሱት ስራ አስኪያጁ፤ ቴክኖሎጂውን በስራ ላይ ለማዋል የገንዘብ አቅም ችግር የለብንም ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ከ125 እስከ 150 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመጠቆም፡፡ አገልግሎቱም ከ6-8 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር አቶ ተካ ተናግረዋል፡፡

እሳትና ውሃ ቀርቦላታል፤ እጇን ወዳሻት መስደድ የእሷ ምርጫ ነው- ዶናልድ ትራምፕ

       ባለፈው ማክሰኞ ባልተጠበቀ ሁኔታ ባለስቲክ ሚሳኤል ወደ ጃፓን በማስወንጨፍ አለምን በድንጋጤ ክው ያደረገቺው ሰሜን ኮርያ፣ “ይህ እኮ በፓሲፊክ አካባቢ የማደርገው ወታደራዊ ዘመቻ ጅማሬ ነው፤ ገና ብዙ ሚሳኤሎችን ወደ አካባቢው አስወነጭፋለሁ” ስትል በይፋ ተናግራለች፡፡
የሰሜን ኮርያው ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን፤ ሚሳኤሉን ያስወነጨፍነው አሜሪካና ደቡብ ኮርያ እያደረጉት ለሚገኘው ወታደራዊ ልምምድ ምላሽ ለመስጠት ነው፣ የአገሬ ጦር በፓሲፊክ አካባቢ የሚያካሂደውና የአሜሪካ ግዛት የሆነቺውን ጉኣም ለማጥቃት ያለመው ቀጣይ ወታደራዊ ዘመቻ ጅማሬ ነው ሲሉ በይፋ ማስታወቃቸውን ኬሲኤንኤ የተባለው የአገሪቱ መንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
“ያስወነጨፍነው ሚሳኤል አሪፍ መነቃቂያ ነው፤ ከፍተኛ እርካታ ተሰምቶኛል” ሲሉ በይፋ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ በቀጣይም ተመሳሳይ በርከት ያሉ ሚሳኤሎችን ወደ አካባቢው እንዲያስወነጭፍ ለአገሪቱ የጦር ሃይል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሰሜን ኮርያ ከሚሳኤል ሙከራዋ እንድትታቀብ በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና በአገራት መንግስታት ተደጋጋሚ ጫና ቢደረግባትም ባለፉት ወራት በተጠናከረ ሁኔታ የሚሳኤል ሙከራ ስታደርግ መቆየቷን ያስታወሰው ዘገባው፤ የማክሰኞው የሚሳኤል ማስወንጨፍ ድርጊት ግን ብዙዎችን ያስደነገጠ ነው ብሏል፡፡
ከፒንግያንግ አቅራቢያ ከሚገኝ ጣቢያ ወደ ጃፓን አቅጣጫ የተወነጨፈው ይህ ሚሳኤል፤ 2ሺህ 700 ኪሎ ሜትሮች ያህል በመጓዝ በሰሜናዊ ጃፓን በሚገኘው ሆካይዶ ደሴት ላይ ቢያርፍም በነዋሪዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አለማድረሱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ድርጊቱ የጃፓንን መንግስት በከፍተኛ ሁኔታ ማስደንገጡንና ይህን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ፤ ድርጊቱ ያልተጠበቀ፣ አጅግ አደገኛና አውዳሚ ስጋት ነው ሲሉ ሰሜን ኮርያን መኮነናቸውን አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የሰሜን ኮርያ ድርጊት ለጃፓንና ለአካባቢው አገራት ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተመድ አባል አገራት ከፍተኛ ስጋት ነው በሚል ድርጊቱን በይፋ ያወገዘው ሲሆን ሩስያና ቻይና ግን በአካባቢው ውጥረት እንዲነግስ ያደረገው የአሜሪካ ወታደራዊ ልምምድ ነው ሲሉ አሜሪካን ኮንነዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው፤ ድርጊቱ ሰሜን ኮርያ ለጎረቤት አገራት ያላትን ጥላቻ ያሳየችበት ነው፣ ከአሁን በኋላ እሳትና ውሃ ቀርቦላታል፤ እጇን ወዳሻት መስደድ የእሷ ምርጫ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 ጌም ኦፍ ትሮንስ በተመልካቾች ብዛት ክብረ ወሰን አስመዝግቧል

       የሃሪ ፖተር ተከታታይ መጽሃፍት ደራሲ የሆነቺው እንግሊዛዊቷ ጄኬ ሮውሊንግ፣ የ2017 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ደራሲ መሆኗን የዘገበው ኢኮኖሚክ ታይምስ፣ ደራሲዋ ከሰኔ ወር 2016 አንስቶ በነበሩት 12 ወራት ከመጽሃፍቷ ሽያጭ በድምሩ 95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷን አስታውቋል፡፡
የመጀመሪያውን የሃሪ ፖተር መጽሃፍ ለንባብ ያበቃችበትን 20ኛ አመት ክብረ በዓል በቅርቡ ያከበረቺው ደራሲዋ፣ መጽሃፍቶቿ ከፍተኛ ተወዳጅነትን በማግኘት በገፍ መቸብቸባቸውን ቢቀጥሉም፣ የአለማችን ቁጥር አንድ ከፍተኛ ተከፋይ ደራሲ ስትሆን ግን ይህ ከአስር ዓመታት በኋላ የመጀመሪያ ጊዜዋ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ጄምስ ፓተርሰን በ87 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ፣ ጄፍ ኬኒ በ21 ሚሊዮን ዶላር፣ ዳን ብራውን በ20 ሚሊዮን ዶላር፣ ስቴፈን ኪንግ በ15 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ መጽሃፍት ሽያጭ ገቢ፣ በቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ድንቅ ደራሲያን መሆናቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ተወዳጅ ሆኖ የዘለቀውና ሰባተኛው ሲዝን ላይ የደረሰው ጌም ኦፍ ትሮንስ ተከታታይ ፊልም ከሰሞኑ በታሪኩ ከፍተኛውን የተመልካች ቁጥር ማግኘቱ ተዘግቧል፡፡ የጌም ኦፍ ትሮንስ የሲዝን ሰባት ማጠናቀቂያ በ12.1 ሚሊዮን ተመልካቾች በቀጥታ፣ በ16.5 ሚሊዮን ተመልካቾች ደግሞ ከቀጥታ ስርጭት በኋላ መታየቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፤ከዚህ ቀደም በቀጥታ የተከታተሉት ተመልካቾች ከፍተኛው ቁጥር 10.1 ሚሊዮን እንደነበር አስታውሷል፡፡


   የዕውቁ የታሪክ ተመራማሪና የስነ-ፅሁፍ ባለሙያ ፕሬፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፣ “ስውሩና ያልተነገረው የአይሁዳውያንና ኢትዮጵያውያን ታሪክ” የተሰኘ መፅሀፍ፣ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡
መፅሀፉ በዋናነት፣ የሁለቱ አገራት ህዝቦች ከ4 ሺ ዓመታት በላይ ስላላቸው ትስስር፤ ስለ ዮዲት ጉዲት ያልተነገሩና ለኢትዮጵያ ስላደረገቻቸው መልካም ተግባራት፤ ስለ አፋር ህዝብና በስሙ ስለተሰየመው አፍሪቃና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ ይሰጣል፤ ተብሏል፡፡
ፕሮፌሰር ፍቅሬ ከዚህ ቀደም ይህንን መፅሀፍ “The hidden and untold history of the Jewish people and Ethiopian” በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ፅፈው አቅርበውት እንደነበር ተገልጿል። መፅሀፉ በ238 ገፅ ተቀንብቦ፣ በ101 ብር ከ20 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል። ፕሮፌሰር ፍቅሬ በቅርቡ ለንባብ ካበቁት፣‹‹የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” ከተሰኘው አነጋጋሪ መፅሀፋቸው በተጨማሪ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጀርመንኛና በአማርኛ በርካታ ግጥሞችን፣ ተውኔቶችንና ከ60 በላይ አጫጭር መጣጥፎችን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡


  እናት የማስታወቂያ ድርጅት፣ ከጀርመን የባህል ማዕከልና ከብሄራዊ ቤተ-መጻሕፍትና ቤተ- መዛግብት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር፤ ነገ ከቀኑ 8፡ 00 ጀምሮ፣ በሩስያዊው ጸሐፊ አንቷን ቼኮብ ተጽፎ በተርጓሚ ትዕግስት ኅሩይ “ቅብጥብጧ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተመለሰው መጽሐፍ ላይ፤ በመወዘክር አዳራሽ ውይይት ያካሂዳል፡፡ በዕለቱ፣ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት አቶ ዓለማየሁ አሊ እንደሆኑ የገለፀው እናት የማስታወቂያ ድርጅት፣ ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

Saturday, 02 September 2017 12:28

አዳራሹ ባዶ አይደለም!

 የ“እኔ” ስለምንላቸው ተመልካቾች መጻፍ ከፈለግሁ ቆየሁ፡፡ “እኔ” የሌለሁበት ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ “እኔ” ስል ግን እያንዳንዳችንን ማለቴ ነው፡፡ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ‹ጉዳይ› የምናደርጋቸው ሃሳቦች ብቻ ሳይሆኑ ሰዎች አሉ፡፡
የእያንዳንዳችን ኅሊና ደግሞ አዳራሽ ነው፤ አዳራሹ መድረክ አለው፤ አትሮኖሱ የተዘረጋውና መጽሐፉ የተገለጠው ለአንድ ሰው ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ መድረክ ላይ የሚቆመው ዲስኩር ሊያስደምጥ፤ ወይም ትርኢት ሊያሳይ ወይም ሊያሰማ ነው፡፡ ንግግርም ሆነ ትዕይንት ደግሞ ራስን ለማስደሰት ተብሎ ብቻ የሚደረግ አይደለም፡፡ ታዳሚ ይፈልጋል። ታዳሚውን ማስደመም ወይም ማበሳጨት ደግሞ መድረክ ላይ የወጣው ሰው ሚና ነው፡፡
እንደዚህ ዓይነት ነገር ወደ ጭንቅላቴ ሰርጎ መግባት ከጀመረ ዘጠኝ ዓመታት አልፎታል፡፡ ሰውን ሰው ያደረገው ሰው ነው፡፡ ስለ ሰው የማያስብ ሰው የለም፡፡ በዕለቱ እንተውናለን፤ ሲተወንም እናያለን፡፡ የቴአትር ጥበባት ተማሪ ሳለሁ፣ ስለ አዘጋጃጀት ጥበብ ያስተማረን መምሕር ተሻለ አሰፋ ‹Private audience› የሚለውን ቃል ያነሳሳልን ነበር፡፡ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” ማለት፣ አንድ ተዋናይ ወክሎት የሚጫወተውን ገፀ ባሕርይ በጥልቀት አጢኖ፣ ገጸ ባህርዩ ማንን አስቦ ነው፣ እያንዳንዱን ቃል የሚናገረው? ማንን አስቦ ነው፣ ድርጊቱን እየተገበረ፣ ሕይወቱን እየኖረ ያለው? ለሚሉ ጥያቄዎች ተዋናዩ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ፅንሰ-ሀሳብ ነው፡፡
ለምሳሌ ከሼክስፒር ተውኔቶች ውስጥ ኦቴሎን እንውሰድ፡፡ ኦቴሎ የእናቱ ነገር አይሆንለትም፡፡ የእናቱን ስጦታ፣ ያቺን መሀረብ፣ እንደ ማተብ ክር ይሞትላታል። የእናቱ ምስል እየተመላለሰበት ያንፀዋል፤ ያፅናናዋል። እናቱ ናት በውስጡ ያለችው፡፡ በኢያጎ ውስጥ ግን ጎልቶና ደምቆ የሚታየው ኦቴሎ ነው፡፡ ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት፣ የኢያጎ መንፈስ የሚናወፀው ኦቴሎ ከፍ ብሎ ሲታይ ነው፡፡ የአንድ ጥቁር ሰው ጄኔራል መሆንና በበላይ ሹማምንት ተወዳጅ መሆን ኢያጎን ረብሾታል፡፡ የሚገባኝ ቦታ በሌላ ሰው ተይዟል ብሎ ያምናል፡፡ ስለዚህ ኦቴሎ ከክብሩ ዝቅ እንዲል፣ ዝቅ ባለም ጊዜ ያልተገባ ነገር በራሱና አብረውት በሚኖሩት ታማኞቹ ላይ እንዲፈፅም ኢያጎ ነገር መጎንጎን ይጀምራል፡፡
ዴዝዴሞና ከቃስዮ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዳላት አስመስሎ፣ ኦቴሎ ለዴዝዴሞና የሰጣት ተወዳጁን መሀረብ ሚስቱ ሰርቃ እንድታመጣለትና ቃስዮ እጅ እንዲገባ አድርጎ፣ ቅናት አረሙን በትዳሩ ላይ ይዘራበታል፡፡ ከላይ በጠቀስነው “ኦቴሎ” ቴያትር ውስጥ፣ የኦቴሎ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” ማለት፣ እያንዳንዱ ገፀባህርይ በሕይወቱ ውስጥ ሰፊ ስፍራ የሚሰጠውን  ተመልካች የሚመለከት ይሆናል፡፡ ሰፊ ስፍራ የሚሰጠው ደግሞ ለሚወዱት ብቻ አይደለም፤ ለሚጠሉትም ጭምር እንጂ!
በእያንዳንዱ ድርጊቶች መሃል ይሄ ስሜት አለ። የተማርንም ያልተማርንም ያው ነን፤ ብቻችንን አይደለንም፤ ይዘናቸው ወይም በማይታይ አንቀልባ አዝለናቸው የምንዞራቸው ሰዎች አሉን፡፡ ያለ እነዚህ ሰዎች አንድ ስንዝር ፈቅ ማለት ይከብደናል፡፡ እነዚህ ሰዎች ወዳጆቻችን፣ ወይም ወላጆቻችን፣ ወይም የመሰረትነው የቤተሰብ አባላት ይሆኑ ይሆናል፡፡
ይህንን የተማርኩ ዕለት፣ “ፕራይቬት ኦዲየንስ” የሚባለውን ነገር፣ ‹ለገፀባህርይ አሳሽነት ብቻ› ሳይሆን ወደ የዕለት ተዕለት ሕይወት ማውረድ ፈለግሁ፡፡ አብረውኝ የሚማሩ ተማሪዎችን አሰብኩና፣ ራሴንም ጨመርኩና፣ እነዚህ ተማሪዎች በየኅሊናቸው ይዘዋቸው የሚዞሩ፤ ወደ  ዕድገት ተራራ ባቀኑ፣ ወይም ወደ ውድቀት ሸለቆ በወረዱ ቁጥር፣ ቶሎ ወደ ጭንቅላታቸው ብቅ የሚለው “ተመልካች” ማን ይሆን? ብዬ አሰብኩ፡፡ በየኅሊናቸው አዳራሽ እንዴት ያሉ ሰዎች ወንበሮቻቸውን ይዘው ተቀምጠዋል ብዬ የማይመለከተኝን አሰሳ አካሄድኩ፡፡ እነዚህ ተማሪዎች፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሞራላቸው ተሰብሮ ቢወድቅ “እኔን!” ብለው የሚደነግጡላቸው ሰዎች አሏቸው፡፡ በተቃራኒውም፣ “ይበላቸው!” ብለው ክፉውን ሁሉ የሚመኙላቸው ሰዎችም አሏቸው፡፡ ግና ተማሪዎቹ ማንን ደስ ለማሰኘት ወይም ማንን በንዴት ባህር ለማስዋኘት ብለው ነው፣ እየኖሩና እየተማሩ ያሉት? በእልልታና በእሪታቸው ጊዜ ቶሎ ወደ አእምሮአቸው ብቅ የሚለው አንዴት ያለ ሰው ነው? ሕይወት እንድትተውነው ባዘጋጀችላቸው ተውኔት ለመሳተፍ መድረክ ላይ ሲወጡ፣ ከእልፍ አእላፍ ተመልካቾች መሀል፣ ማንን ወይም እነማንን አስበው ነው፣ ትወናቸውን የሚያካሂዱት? ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡
አንድ ተማሪ ነበረ፡፡ እድሜው ገፋ ብሏል፡፡ የድርሰትም ሆነ የዝግጅት ዝንባሌ የለውም፡፡ የትወና ተሰጥኦም እንዳልታደለ ያውቃል፡፡ ግን ይማራል፤ ቴአትር ይማራል፤ ቴአትረኛ ለመሆንም ሆነ ለመባል ሳያጓጓውና የመንፈስ ግለት በውስጡ ሳይኖር ይማራል፤ የሚማረው ግን ንቃ የተወችውን ሴት፣ የት እንደደረሰ ለማሳየት ነው፤ አዎን፤ ንቃ የተወችውን ሴት ለማስቆጨት፣ “አመለጥኩሽ!” ለማለት!!
ይህቺን ሴት ይወዳት ነበር፡፡ ገጠር ገብቶ፣ የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎችን በሚያስተምርበት ጊዜ፣ ይህቺ ሴት ብዙ መደናበሮችን አስረስታው ነበረ። ደስታውና ፈገግታው ሞቅ፣ ፈካ እያለ እንዲሄድ አድርጋው ነበረ፡፡ ቆይቶ ግን አንድ ነገር ተፈጠረ። አንድ ቀን ጠረኖቻቸውን ተጠጋግበው ሲያበቁ፣ “ላገባሽ ወስኛለሁ!” አላት፤ ይህንን ስትሰማ ደነገጠች፤ መጀመሪያ አይደነግጡ አደነጋገጥ ደነገጠች፤ ቀጥሎ ሣቋ መጣ፤ ከትከት ብላ ሣቀች፤ ሣቀችበት፤ አሁን ድንጋጤዋን ተረከባት፡፡ በተራው ደነገጠ፡፡ “ሰርፕራይዝ አደርጋታለሁ!” ብሎ አስቦ በተናገረው ነገር፣ “ሰርፕራይዝ” ያደረገውን ምላሽ ሰጠችው፡፡ “ድፍረትህ! እኔ እኮ እዚህ ምንም መዝናናት በሌለበት ገጠር፣ ብቻ ከመሆን ይሻላል ብዬ የፍቅር ጥያቄህን ተቀበልኩህ እንጂ እኔና አንተ እኮ አንመጣጠንም! አንኳኋንም!” አለችው፡፡ ግራ ገብቶት፣ “ለምን?” አለ፡፡ መልስ ለመስጠት ደቂቃ አልፈጀባትም፣ “አንኳኋንም!! እኔ’ኮ ዲፕሎማ አለኝ!! አንተ ደግሞ ገና የቲ.ቲ.አይ. ምሩቅ ነህ! እንዴት ቁልቁል ወርጄ ካንተ ጋር ትዳር ልመስርት?!” አለችው፤ ጥያቄውን በማቅረቡም ታዘበችው፡፡
ምንጭ፡- (ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ፣ ”ያልተቀበልናቸው”
የወጎች መድበል የተቀነጨበ፤ ነሐሴ 2009 ዓ.ም)

  በረጅም ልብወለድ- አዳም ረታ (“የስንብት ቀለማት”)
በሥነ ግጥም- አበረ አያሌው (“ፍርድና እርድ”)
 በልጆች መፅሐፍ - አስረስ በቀለ (“የቤዛ ቡችላ”)
ኢስትዌስት ኢንተርቴይንመትና ኤቨንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጁት “ሆሄ” የሥነ ፅሑፍ ሽልማት፣ባለፈው ሰኞ ምሽት በብሔራዊ ትያትር ባካሄደው ሥነሥርዓት በየዘርፉ ተወዳድረው ያሸነፉትን  ሸልሟል፡፡ ዋናዎቹ የውድድር ዘርፎች ረጅም ልብወለድ፣ሥነግጥምና የልጆች መጻሃፍት ሲሆኑ ከሐምሌ 2008 እስከ ሐምሌ 2009 ዓ.ም ተፅፈው ለንባብ የበቁ መፅሐፍት በውድድሩ መካተታቸው  ታውቋል፡፡ ለእያንዳንዱ ዘርፍ ሶስት ሶስት ዳኞች ተመድበው ምርጫና ምዘናው መካሄዱም ተጠቁሟል፡፡ 80 በመቶ በዳኞች ምዘና ፣20 በመቶ ደግሞ በአንባቢያን ምርጫ መሰረት፣  አሸናፊዎቹ እንደተለዩ ተነግሯል፡፡
በረጅም ልቦለድ ዘርፍ ለውድድር ከቀረቡት ሥራዎች መካከል የዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ “ዝጎራ”፣ የአዳም ተረታ “የስንብት ቀለማት”፣ የሰብለ ወንጌል ፀጋ “መፅሀፉ”፣ የያለው አክሊሉ “ወሰብሳቤ” እና የብርሀኑ አለባቸው “የሱፍ አበባ” ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ሲሆን  የደራሲ አዳም ረታ “የስንብት ቀለማት፣ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ደራሲው በሃገር ውስጥ ስለሌለም፣ተወካዩ፣ ከደራሲ ሳህለ ስላሴ ብርሀነ ማሪያም እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡
በግጥም መፅሀፍ ዘርፍ ለውድድር ከቀረቡት ሥራዎች ውስጥ የኤፍሬም ስዩም “ኑ ግድግዳ እናፍርስ”፣ የትዕግስት ማሞ “የጎደሉ ገፆች”፣ የአበረ አያሌው “ፍርድና እርድ”፣ የዶክተር በድሉ “ተስፋ ክትባት” እና የበላይ በቀለ ወያ “እንቅልፍና ሴት” የግጥም መፅሀፍት ለመጨረሻው ዙር ያለፉ ሲሆን  የአበረ አያሌው “ፍርድና እርድ” አሸናፊ ሆኖ ከገጣሚ፣ ባለቅኔና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ እጅ ሽልማቱን  ወስዷል፡፡
በልጆች መፅሐፍ ዘርፍ ከቀረቡት ሶስት መፅሐፎች መካከል የኮሜዲያን አሥረስ በቀለ “የቤዛ ቡችላ” የተሰኘ መፅሐፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ ለመጨረሻው ዙር ካለፉት ሶስት የልጆች መፅሐፍት ሁለቱ የአሥረስ በቀለ ናቸው፡፡ ኮሚዲያን አሥረስ በቀለ ሽልማቱን ከተቀበለ በኋላ ባደረገው አጭር ንግግር፤ “እኔ ሁሌም ተስፋ ሳልቆርጥ ስለምሰራ ለዚህ በቅቻለሁ፤ ዛሬ ሆሄ የሽልማት ድርጅት ከሥነ-ፅሁፍ ጋር በይፋ ድሮኛል” ሲል ደስታውን ገልጧል፡፡ ኮሜዲያኑ አስከትሎም፤ “ዛሬ አበባ ተስፋዬ በህይወት ኖረው፣ ይህንን ክብር ቢያዩልኝ  ምን ያህል በታደልኩ” ሲል በቁጭት ስሜት ተናግሯል፡፡  
የ”ሆሄ” ሌሎች ተሸላሚዎች  
የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተ የሚዲያ ተቋም -
ሸገር ኤፍኤም 102.1 ሬዲዮ
በረጅም ዘመን የትምህርት ማስፋፋት የላቀ ባለውለታ- አቶ ማሞ ከበደ ሽንቁጥ
ለአይነ ስውራን መፅሀፍትን ተደራሽ በማድረግ የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከተ- “አዲስ ህይወት ለአይነ ስውራን ማዕከል”
በረጅም ዘመን ጋዜጠኝነትና ስነ-ፅሁፍን በትረካ ለህዝብ በማድረስ - ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን
በረጅም ዘመን የኃያሲነትና ስነ-ፅሁፍ ሥራ የላቀ አስተዋፅኦ በማበርከት- ኃያሲና ደራሲ አስፋው ዳምጤ
በህይወት ዘመን የስነ-ፅሁፍ ሽልማት- አለቃ አካለወልድ ክፍሌ (“መፅሀፈ ሰዋሰው ወግዕዝ”)

   ብክለትን ለመቀነስ የወጣው ህግ 176 ፋብሪካዎችን ያዘጋል፣ 60 ሺህ ሰራተኞችን ያፈናቅላል

        የኬንያ መንግስት፤ የፕላስቲክ ከረጢት ወይም ፌስታል ባመረተ ወይም በተጠቀመ ላይ እስከ 4 አመት እስር እና 40 ሺህ ዶላር የገንዘብ ቅጣት የሚጥልና በአለማችን በመስኩ እጅግ ጥብቅ የተባለ ህግ አውጥቷል፡፡
በኬንያ ከሰኞ ጀምሮ የፕላስቲክ ከረጢት ይዞ የተገኘ የአገሪቱ ዜጋ፣ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ ተገቢው ቅጣት እንደሚጣልበት የጠቆመው ዘገባው፤ የፕላስቲክ ከረጢቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችም ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው አመልክቷል፡፡
የፕላስቲክ ምርቶች በአካባቢ ብክለት ረገድ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለመቀነስ ታስቦ የወጣው ይህ እጅግ ጥብቅ ህግ፤ ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውል የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በአገሪቱ የፕላስቲክ ከረጢቶች በየቦታው እየተጣሉ ከፍተኛ ብክለት እየፈጠሩ እንዳሉም አመልክቷል፡፡
የፕላስቲክ ከረጢቶች ለመበስበስ እስከ 1000 አመታት የሚደርስ ጊዜ እንደሚፈጁ የገለጸው ዘገባው፤ እንስሳትም ያገለገሉ የፕላስቲክ ከረጢቶችን በመመገብ ለጤና ችግር እንደሚጋለጡና በመዲናዋ ናይሮቢ በሚገኙ የከብት ማረጃ ቄራዎች ከአንድ ከብት ሆድ ዕቃ ውስጥ እስከ 20 የሚደርሱ ያገለገሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
የፕላስቲክ ከረጢት ምርቶችን ወደ ውጭ አገራት በመላክ፣ከአካባቢው አገራት በቀዳሚነት የምትሰለፈው ኬንያ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ በሚል ያወጣቺው ይህ ህግ፣ በአገሪቱ የሚገኙ 176 ፋብሪካዎችን የሚያስዘጋና ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን ከስራ የሚያፈናቅል ነው በሚል የአገሪቱ የአምራች ኩባንያዎች ማህበር  ክፉኛ ተችቶታል፡፡
ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩዋንዳና ጣሊያንን ጨምሮ የተለያዩ 40 የአለማችን አገራት፣ የፕላስቲክ ከረጢቶችን ምርት በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ የሚከልክሉ ተመሳሳይ ህጎችን አውጥተው በስራ ላይ ማዋላቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡