Administrator

Administrator

የስራ አመራር መፅሐፍትን በመፃፍ የሚታወቁት በአቶ እሸቱ እንደሻው የተፃፈውና መልካም ባህሎችና ልምዶች ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ ማህበራዊ ስርዓት መገንባትን ዓላማው አድርጎ የተፃፈው “የሰለጠነ ማህበራዊ ሰው” መፅሐፍ የዛሬ ሳምንት ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ በራስ ሆቴል አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎችና በመፅሐፉ ላይ ዳሰሳ ይቀርባልም ተብሏል። መፅሐፉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እመርታን፣ ስኬትን፣ደስታን፣ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን፣ ፍቅርና ቤተሰብን የሚዳስሱ ሀሳቦችንና ተያያዥ ጉዳዮችን ይዟል፡፡ 112 ገፆች ያሉት ይኸው መፅሃፍ በ80 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  እ.ኤ.አ በ1972 ጥቅምት ወር መግቢያ ላይ የኡራጓይ የአየር ሀይል የመጓጓዣ አውሮፕላን የአንድ የራግቢ ክለብ ተጫዋቾችን እና ደጋፊዎቹን አሳፍሮ ከዋናው ከተማ ከሞንቲ ቪዲዮ ወደ ቺሊ ዋና ከተማ ሳንቲያጎ በመብረር ላይ እያለ በከፍተኛነቱ ከሚታወቀው አንድስ ተራራ ላይ ወድቆ የራግቢ ተጫዋቾቹና ደጋፊዎቻቸው ለ71 ቀናት በበረዶ ላይ ያሳለፉትን ስቃይ ከስቃዩ ተረፉትንና ህይወታቸው ያለፈውን ተጓዦች ጉዳይ የሚያወሳው የተራራው ምርኮኞች መፅሐፍ በድጋሚ ታትሞ ለንባብ በቃ፡፡ በደራሲ ፒየር ፖል ሪድ የተፃፈውና በሀዲስ እንግዳ አይቼህ የተተረጎመው ይህ መፅሐፍ እውነተኛ ታሪኩ አጃኢብ ያሰኘና አ ደጋውም የ ዓለም አቀፍ የ ዜና ሽፋን ያገኘ ሲሆን ታሪኩ ወደ መፅሐፍና ወደ ፊልም ተቀይሮ ብዙ አንባቢና ተመልካች ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡ መፅሐፉ በ321 ገፅ ተፅፎ በ150 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  እናት የማስታወቂያ ድርጅት ከጀርመን የባህል ማዕከል (ጎተ) ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መፃህፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ “አለመኖር” በተሰኘው የዶ/ር ዳዊት ወንድም አገኝ መፅሐፍ ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡ በእለቱ ለውይይት የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የስነ-ፅሁፍ ባለሙያው አቶ በአካል ንጉሴ እንደሆኑ የገለፀው እናት የማስታወቂያ ድርጅት ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡

  እስካሁን ለምን ዝም እንዳልኩኝ የምትረዱ ይመስለኛል፡፡ ድንጋጤና ሐዘን በጣም ጎድተውኛል፤ በትክክል ሁሉ ማሰብ አልቻልኩም ነበር፡፡ አሴ ቢሆን ስንት ፅፎ ነበር፡፡
በመጀመሪያ ለአባቴ የደረሰችለት ዳላስ ቴክሳስ የምትኖረው ወ/ሮ አብነት ከነቤተሰቧ፤ ተመላልሳ በመጠየቅ ከአጠገቡ የተገኘች መልካም ሴት ናት፡፡ መቼም ቢሆን አልረሳሽም፤ እግዚአብሔር ይስጥልኝ፡፡ መላው ቤተሰብ እንዲያውቅ አብነትንም ወደ አሴ እንድትሄድ ያደረጉ የአክስታችን የእትዬ ሽታ ልጆች ትዕግስትና ኤልሳ ምክሩ በጣም ኮርቼባችኋለሁ፣ የእትዬ ሽታ ምትክ ናችሁ።
አሴ አገሩ እንዲገባ ትልቁን ሚና የተጫወቱት በዳላስ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ኮሚኒቴ፤ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ገንዘብ አሰባስበው የሚያስፈልገውን ሁሉ በማድረግ፣ ከሆስፒታል ጀምሮ እስከ አሸኛኘቱ ድረስ ለፍተው ብዙ ጥረት በማድረጋቸው እንዲሁም በአሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች እንዲሁም በተለያዩ ውጭ አገራት ያላችሁ የአሴ ወዳጆች፣ ጓደኞች ሁሉ ያደረጋችሁትን መረባረብ ታሪክ አይረሳውም፡፡
በዳላስ ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል አስተዳዳሪና የቅዱስ ተቋም ዳይሬክተር፣ ቀሲስ አንዱዓለም ዳግማዊ፣ እግዚአብሔር ብድራቱን ይክፈላችሁ እላለሁ፡፡
በድጋሚ በዳላስ ቴክሳስ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲና በሌላውም ስቴት ያላችሁ፣ በመላው አለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ እሱ እንደወጣ እንዳይቀር ስላደረጋችሁ ደግሜ ደግሜ አመሰግናለሁኝ፡፡
ኢትዮጵያ ሲገባ ደግሞ ከመግባቱ ዜና ጀምሮ እስከ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ድረስ ህዝብ እንዲያውቀው በማድረግ ትልቁን ሚና የተጫወተው ሸገር 102.1 ሬዲዮ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ እኛ ለአንድም ሰው ደውለን አልተናገርንም፤ ሁሉንም ያሰባሰባችሁት እናንተ ናችሁ። አባቴን እንዳከበራችሁት እግዚአብሔር ያክብርልኝ። በተለይ አቶ ደምሰውንና ሌሎችንም የሸገር አዘጋጆች በሙሉ፣ ወ/ሮ መዓዛንም ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
ኢትዮጵያ ሲገባ ከቦሌ ጀምሮ አቀባበል በማድረግና በሁለተኛው ቀንም የቀብር ስነ ስርአቱን በደማቅ ሁኔታ ያስከበሩትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ፡፡›
በሌላ በኩል በአርባ ምንጭና በጨንቻ የቀብር ሥነ ሥርአቱ ይፈፀማል ብለው በጣም ሰፊ ዝግጅትና ድካም ሲያደርጉ የቆዩትን የአርባ ምንጭ ህዝብና የክልሉን መንግስት ይቅርታ እጠይቃለሁኝ፡፡ ያም ሳያንሳችሁ እዚህ ድረስ በመምጣት የቀብር ሥነ ሥርአቱ በባህሉ መሰረት፣ እዚህ ካለው ህዝብ ጋር በደማቅ ሁኔታ ስለአከበራችሁ አመሰግናለሁ፡፡
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የምትልኩልን የሐዘን መግለጫ ደርሶናል፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ ለምሁራን፣ ለባለሥልጣናት፣ ለአምባሳደሮች፣ ለሚኒስትሮች፣ ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች፣ ለአሴ የቅርብ ጓደኞችና ወዳጆች ከአጠገባችን ላልተለያችሁን ሁሉ እናመሰግናለን፡፡
የአባቴ የቅርብ ጓደኛና (ወንድም) አቶ ፍቅረ ማርያም ይፍሩ፤ አባቴ አገሩ ሲገባ ከአቀባበል ጀምሮ የህይወት ታሪኩን ባመረ ሁኔታ ፅፎ ያቀረበው የቤተክርስቲያኑ ፕሮግራም እንዲያ እስከ መጨረሻው ድረስ እንደ ሰርግ አምሮ ደምቆ እንዲደረግ የለፋ በመሆኑ እግዚአብሔር እድሜና ጤና ይስጠው እላለሁ፡፡
የአክስቴ ባለቤት አቶ ባልቻ ሙሊሣ፤ የአክስት ባለቤት ሊባል አይቻልም፤ አይገባውም፡፡ ለኛ አባታችን መሰብሰቢያችን ነው፡፡ አሁንም የአሴን ማረፍ ከሰማ ቀን ጀምሮ ቤተሰቡን ከየአለበት እንዲሰባሰብ በማድረግ፣ ደከመኝ ሳይል ያንን ሁሉ ቀን ቤተሰባችንን በመሰብሰብ የቀብሩ ሥነ ስርዓት በጥሩ ሁኔታ ተፈፅሞ፣ እንግዶች በስርአት እንዲሸኙ በማድረግ ትልቅ ነገር ነው ያደረገው፡፡ እግዚአብሔር እድሜና፣ ጤና ይሰጥልን፡፡
ለቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አስተዳዳሪ፣ ለካቴድራሉ ቀሳውስት፣ ካህናት ለአገልጋዮች በአጠቃላይ፣ ለቀሲስ ፀጋዬ በክብር ስለሸኛችሁት በልዑል እግዚያብሄር ስም አመሰግናለሁ፡፡
እንደ ሃሳቡና ፍላጎቱ እንደ ዶርዜ ወንድሞቼ፣ እንደ ጋሞ ዘመዶቹ በዋፈራና በሆታ ሸኙኝ ባለው መሠረት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳትሉ በድምቀት ከጥዋት ጀምራችሁ እስከ ቀብር ሥነሥርአቱ ድረስ ላሳመራችሁለት የልቡን ስለፈፀማችሁ፣ ለአቶ ሞላ ዘገየ እንደ ቤተሰብ መሀላችን ገብተህ የኢትዮጵያዊነትህን፣ የወንድምነትህን፣ የጓደኝነትህን ከሌሎች ከውጭም ከአገር ውስጥም ካሉ ጋር በመተባበር እስከመጨረሻው ከአጠገባችን ባለመለየት የሰማነውን የህይወት ታሪክ ባማረ ሁኔታ አሰማሀን፡፡
ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጆች (የአሴ ወዳጆች)፣ ለነብይ መኮንንና ለአለማየሁ አንበሴ እንዲሁም ለሌሎቹ ጋዜጠኞች በሙሉ ከመጀመሪያ ካረፈበት ግዜ አንስታችሁ ሰፊ ሽፋን ነው የሰጣችሁት፤ አስቀድሜ እንዲያውም በጣም ፈርቼ ማዘኔን ነግሬአችሁ ነበር፡፡ ብቻችንን ነን ብዬም ነበር፤ ኋላ ሁሉም ደረሰልን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡
ለነባዳን የሚዲያ ማማከር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (ለዳኒና ለነብይ) ለደራሲ እንዳለ ጌታና ለወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን፣ ለዘነበ ወላ … በአሜሪካን አገር ለሚኖሩ አባቴን እንደ አባት የሚጠብቁና የሚቆረቆሩለት ዳንኤል ካሣሁንና ዶክተር ግርማ አውግቸው ደመቀ እንዲሁም ለካሣሁን ሰቦቃ … ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
ለቤት አከራዮቼ (እንደ አባትና እናት) ለሚሆኑልኝ፣ በሐዘኔ በአጠገቤ ላልተለዩት ለአቶ ሲሳይ ወልተጂና ለወ/ሮ መለሰች ሁሪሳ ከነልጆቻቸው እንዲሁም ለጎረቤቶችና ለጓደኞቼ ለመላው ቤተሰብ ለሻምበል ሃ/ገብርኤል ጫቦና ቤተሰቡ፣ ለወ/ሮ ግንብነሽ ጫቦ ከነልጆቿ፣ ለወ/ሮ ቃልኪዳን መሸሻ፣  ለወ/ሮ ተቀባሽ አንጣልና ብርሃን አንጣል ከነልጆቻቸው፣ ለአቶ ሳምሶን አሰፋ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ አለማየሁ አሰፋ፣ ለአቶ ዋሴ አዛዥ ከነቤቴሰቡ ለአቶ የማነ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ ባንጃው ወዜ ከነቤተሰቡ፣ ለአቶ ፈለቀ በፀሎት ከነቤተሰቡ፣
ለውድ ባለቤቴ ለአቶ በላይ ይመርና ለልጆቼ እንዲሁም በስም ላልጠቀስኳቸው ብዙ ወዳጆቻችን … አመሰግናለሁ፡፡
ለድሬድዋ ነዋሪዎችና ለከተማዋ አስተዳደር ለወንድሜ የኤፍሬም አሰፋ ጫቦ ጓደኞችና ጎረቤቶች ሁሉንም… አመሰግናለሁ፡፡
ከኢትዮጵያ ውጭ ላሉ የሬዲዮና ቴሌቪዥን አዘጋጆችና ጋዜጠኞች በሙሉ …
በኢትዮጵያም ሆነ፣ በውጭ አገር ለምትኖሩ ሁሉ … ላደረጋችሁልን፣ ለአባቴ ለከፈላችሁት መስዋዕትነት ሁሉ እግዚአብሔር ይክፈላችሁ፤ አመሰግናለሁኝ፡፡
በመጨረሻ ለፍቶ እንዲያው እንዳይቀር በአገር ውስጥ አንድ የስሙ መጠሪያ እንዲደረግለትና “ቁጥር ሁለት የትዝታ ፈለግ” አባቴ ፅፎ ጨርሶ ነውና ያረፈው፤ ያንንም እቀጥላለሁኝ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአጠገቤ እንደማይለይ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እመቤት አሰፋ ጫቦና ቤተሰቦቿ

Sunday, 02 July 2017 00:00

‘የተሳሳተ ጥሪ’

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው፡፡ አንድ ወዳጄ አንድ ቀን ከምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ ስልክ ይደወልለታል። በዛ ሰዓት ይደውልልኛል ብሎ የሚያስበው ሰው ስላልነበር፣ የልብ ምቱ ትንሽ ፈጠን ይላል፡፡
“ሄሎ፣ ማን ልበል!” ይላል፡፡
በምላሹ “ሄሎ፣ እከሌ ነኝ፣” የለ፣ “ናፍቀኸኝ ነው” የለ፣ “ድንገት ትዝ ብለኸኝ ነው፣” የለ… “ፖለቲከኛው አለቃህ አሁንም ነክሶህ እንደያዘህ ነው ወይ!” ...ብቻ የሆነች ሴት ድምጽ በአንድ ሴከንድ ስድሳ ያህል ቃላት ታርከፈክፍበታለች፣ የስድብ ቃላት። በእሷ ዐይን ኤልሱን በጣም ጭምት፣ እንደ ኤሊ እየተንቀረፈፈች የምትናገር ነች፡፡ ቂ…ቂ...ቂ… ኧረ እሱ ላይ የደረሰው ነገር አያስቅም፡፡ ሊያስበው የሚችለውንና፣ የማይችለውን የስድብ አይነት ላይ በላይ ትዘረግፍበታለች፡፡ ስድቦቹ አይደለም በዚህ ዘመን በድሮው የ‘ሬድ ላይት’ ሰፈሮች እንኳን የተረሱ ናቸው፡፡ ከእሱ ጋር ቤተሰቦቹ አልቀሩ፣ ጓደኞቹ አልቀሩ፣ ሁሉም ‘የድርሻቸው’ ተሰጣቸው። ወላ ነጠላ ሰረዝ፣ ወላ አራት ነጥብ የሌለው አጥንት ሰባሪ ዘለፋ ታወርድበታለች፡፡ ቢቸግረው ስልኩን ይጠረቅመዋል፡፡ እንደገና ስትደውል አያነሳም፡፡ ደጋግማ  ስትደውል ለክፉም ለደጉም ብሎ ያነሳዋል።
“አንተ ማን አባክ ሆንክና ነው የምትዘጋብኝ!…” ብላ የአዲስ አበባን ቀለበት መንገድ ሦስት እጥፍ የሚረዝም የስድብ መአት ትደረድርለታለች። “ምን አለች በለኝ…” ብላ ታላላቅ ባለስልጣኖች እንደምታውቅ፡ ልቡ እስኪጠፋ እንደምታስጠበጥበው ፎከራ… “አንተን ልክ ካላስገባሁ ከምላሴ ጸጉር!” ምናምን ብላ ትዘጋበታለች፡፡
እኔ የምለው መጀመሪያ ስም አይቀድምም እንዴ!  “አንተን ማን ልበል፣” ምናምን አይነት ማረጋገጫ!
በማግስቱ በጊዜ ይደወላል ያው ቁጥር፡፡ አያነሳውም። ደጋግሞ ከተደወለ በኋላ “እባክህ ስልኩን አንሳልኝ፣” የሚል የጽሁፍ መልእክት ይደርሰዋል፡፡ ቀጥሎ ሲደወል ይነሳል፡ እያለቀሰች ይቅርታ ትጠይቀዋለች፡፡ ለካስ የገዛ ጓደኛዋን ይዞ የፈነገላት ‘ቦይፍሬንዷ’ መስሏት ነው፡፡ አሀ… ‘ቦይፍሬንድ’ስ ቢሆን ይሄን ያህል መሰደብ አለበት እንዴ! ማንኛውም ጨረታ ላይ እኮ “ድርጅቱ የተሻለ መንገድ ካገኘ ጨረታውን ማስተላለፍም ሆነ መሰረዝ ይችላል…” ምናምን የሚባል ነገር አለው (ሴትዮዋ ከሰማችን ሁለተኛው ዙር ለእኛ ነው፡፡)
በተለይ ደግሞ ከመሸ በኋላና በሌሊት የሚደውሉ የተሳሳቱ ጥሪዎች የምር አስቸጋሪ ናቸው፡፡
ይቺን ስሙኝማ፡፡ የቴሌፎን ኩባንያው ፕሬዝደንት ሌሊት እንቅልፉን ይለጥጣል፡  ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ገደማ ስልኩ ሲጮህ ይነቃል፡፡
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ የቴሌፎን ኩባንያው ፕሬዝደንት ነህ?”
“አዎ ነኝ፣  ምን ልርዳዎ?”
“እስቲ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት በተሳሳተ ጥሪ ከሚጣፍጥ እንቅልፍህ መቀስቀስ ምን እንደሚመስል አሁን ንገረኝ!” አለውና አረፈው፡፡
እናማ ‘የተሳሳተ ጥሪ’ ነገር አስቸጋሪ ነው፡፡
እናማ…ይሄ ‘የተሳሳተ ጥሪ’ ነገር የምር አስቸጋሪ ነው፡፡ የምር አሁን፣ አሁን የማትጠየቁት የሰው አይነት፣ የመሥሪያ ቤት አይነት የለም፡፡ አሁን እኔ ምኔ ‘እንትን ጋራዥ’ን ይመስላል! ቂ…ቂ…ቂ…  እናማ… ጥሪው ‘ከመሳሳቱ’ ሌላ የደዋዮቹ ባህሪይ ከአገር ሊያሰወጣን ምንም አልቀረው…  ከአገር የሚያስወጡ ነገሮች ያልበዙብን ይመስል!
ከአገር የመውጣት ነገር ካነሳን፣ ከዚህ በፊት አንስተናት ልትሆን የምትችል ነገር ላውራችሁማ። ‘በዛኛው ዘመን’ የሆነ ነው፡፡ ውጪ ተምሮ የመጣ ሰው ነው፡ ለምርምር ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ ይላካል። ታዲያላችሁ… “ይህ ሰውዬ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ሳይኖረው አይቀርም ተብሎ  እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በወታደር ይጠበቃል፡፡ ታዲያ ጧት፣ ጧት እየተነሳ ይሮጣል፣ ወታደሮችም ይከተሉታል። ይሀ ነገር ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥልና ከወታደሮቹ ይላመድና በራሱ እየሮጠ መመለስ ይጀምራል። ታዲያ አንድ ቀን በወጣበት ይቀራል፡፡ በሳምንቱ ገደማ… “ሩጫ ስለፈቀዳችሁልኝ አመሰግናለሁ፣” የሚል የስልክ ጥሪ ይደርሳል...ከኖርዌይ። (ሩጫ በሸታና እድሜን ማባረሪያ ብቻ ሳይሆን ‘መብረሪያ’ ሊሆን ይችላል ለማለት ያህል ነው።)
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ ማን ልበል?”
“ሄለንን አቅርብልኝ፡፡”  ጥያቄ ሳይሆን ትእዛዝ፡፡
“ጌታዬ ተሳስተዋል፡ ሄለን የሚባል ሰው የለም፡፡”
“አታቀርብልኝም፣ ማለት ነው?”
“ጌታዬ እንደዛ የሚባል ሰው የለም አልኩዎት እኮ!”
“በአንተ ቤት ማታለልህ ነው! ደግሞ ንገራት፣ እናትሽ ሆድ ብትገቢ አታመልጪኝም በላት፡፡ ይሄ የምትኩራሪበትን መልክሽን የህጻናት ማስፈራሪያ ባላደርገው እኔ አይደለሁም ብሏል በላት!”  ጥርቅም!
ሰውየው ይደውልና…
“ይሄ ቁጥር ስንት ነው?” ይላል፡፡ በወዲያኛው ጫፍ ያለው ምን ብሎ ቢመልስለት ጥሩ ነው… “አንተ ንገረኝ እንጂ፣ አንተ አይደለህ እንዴ የደወልከው?” አሪፍ መልስ አይደል!
እኔ እኮ ይሄ ሞባይል የሚሉት ነገር…ፎካሪው መብዛቱ! “ተሳስተዋል፣” “ሌላ ቁጥር ነው የደወሉት፣” እያላችሁት ያለ ጋሻና ጦር ቀረርቶውን ይለቅባችኋል። ሄለን የለችም ማለት፣ “ሄለን የለችም” ማለት አይደለም እንዴ!
ሀሳብ አለን…የተሳሳተ ቁጥር በደወሉ ጊዜ ምን ማለት እንደሚገባዎ የሁለት ወር ልዩ የክረምት ስልጠና ምናምን ይዘጋጅልን፡፡ አሀ..እነሱ በተጣሉት፣ እነሱ በተፈነጋገሉት፣ እነሱ በተካካዱት…እኛ ስድቡን የመሸከም ውል ተዋውለናል እንዴ!
“ሄሎ!”
“ሄሎ!”
“እስቲ ባንጃውን አቅርብልኝ…” ቁጣ፡፡
“ይቅርታ፣ ተሳስተዋል፡፡”
“ስማ፣ ሄደህ የምታሾፍበት ላይ አሹፍ፡፡ አሁን ባንጃውን ታቀርብልኛለህ፣ አታቀርብልኝም!”
ባንጃው ምንም ያድርግ ምን ጦሱ ወደ እናንተ ይመጣል፡፡ (ስሙ ግን ብዙ ነገር ማድረግ የሚችል ያስመስለዋል፣ ቂ…ቂ..ቂ…)
“ጌታዬ ምናልባት ሲደውሉ ቁጥር ተሳስተው ይሆናል፡፡”
ጆሯችሁ ላይ ጥርቅም!
ለነገሩ ዘንድሮ የባህሪይ ነገር፣ የስነ ምግባር ነገር ግራ እየገባን “ሰውረነ ከመአቱ…” አይነት የሚያስብል ሆኗል። ስልክ ደግሞ ሳይታዩ እንደልብ ለመሆን ስለሚያመች ይኸው እንግዲህ የተነጠቀውም፣ የተፈነገለውም፣ የተጭበረበረውም…እኛ ላይ ንዴቱን ይወጣል፡፡
ለመሳሳቱ እናንተ ምክንያት የሆናችሁ ይመስላል። ከተናደደ ቴሌ ጆሮ ላይ አይጠረቅመውም እንዴ!
እንግዲህ ባንጃው ማን ይሁን፣ ምን ይሁን የሚያውቅ ይወቀው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው በኦፕሬተር በኩል ይደውላል፡፡  
“ሄሎ!”
“ሄሎ፣ እንዴት ይዞሀል?”
“ደህና ነኝ፡፡ ስማ ትንሽ ብር ስለቸገረኝ መቶ ብር ያህል በባንክ ላክልኝ፡፡”
ድምጹ ይለወጣል፡፡ “ስልኩ ይንኮሻኮሻል…የምትለው አይሰማኝም፡፡”
“መቶ ብር በባንክ ላክልኝ ነው ያልኩህ…”
“ምን አይነት ስልክ ነው… የምትለው ምንም አይሰማኝም!”
ይሄኔ ኦፕሬተራ ጣልቃ ትገባና “እኔ የሚለው ይሰማኛል፣” ትላለች፡፡ ይሄኔ አጅሬው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እንግዲያው መቶ ብሩን አንቺ ላኪለት፡፡”
ደህና ሰንብቱልኝማ!  


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጐልማሣ ፈረስ መጋለብ በጣም ያምረውና ወደ ገበያ ፈረስ ሊገዛ ይሄዳል፡፡ ገበያ ውስጥ ብዙ ፈረስ የያዘና አንድ ፈረስ ብቻ የያዙ ሁለት ነጋዴዎች አሉ፡፡ ወደ ባለ ብዙው ፈረስ ይጠጋና፤
“ይሄ ስንት ነው?” ይለዋል፡፡
ባለብዙው ፈረስ - “ሁለት ሺ”
ፈረስ ገዢ - “ይሄስ?”
ባለብዙው ፈረስ - “ሁለት ሺ ሦስት”
ፈረስ ገዢ - “ይሄኛውስ?”
ባለብዙው ፈረስ  “ሁለት ሺ አራት”
ፈረስ ገዢ - “እንዴ-- አንዴ አንድ ዋጋ ከተናገርክ መቀጠል ነው ማለት ነው ሥራህ?”
ባለብዙው ፈረስ - “ጊዜው ነው ጌታዬ፡፡ የሚጨምር ነው እንጂ የሚቀንስ ነገር የለም”
ፈረስ ገዢው ይተወውና አንድ ፈረስ ወዳለው ነጋዴ ይሄዳል፡፡
ፈረስ ገዢ - “ይሄ ፈረስ ስንት ነው ዋጋው?”
ባለ አንድ ፈረስ “ስድስት ሺ”
ፈረስ ገዢ - “አሃ እዛኮ በሁለት ሺ አግኝቻለሁ”
ባለአንድ ፈረስ - “እኔ ሻጭ ነኝ፡፡ ይዤ እምወጣው አንድ ፈረስ ነው፤ እሱን ሸጬ መግባት ነው አላማዬ”
ፈረስ ገዢ - “ታዲያ በጣም አስወደድከዋ?”
ባለ አንድ ፈረስ - “የፈረሱ አይነት ነው፡፡ እንደምታየው ሠንጋ ፈረስ ነው፤ የዚህ ዓይነት ፈረስ የትም አታገኝ”
ፈረስ ገዢ - “ጥሩ፡፡ እገዛሃለሁ፡፡ ግን ልዩ ጥቅሙ ምንድነው?”
ባለአንድ ፈረስ - “እሱን ስትጋልበው ታየዋለህ”
ፈረስ ገዢ - “መልካም”
ፈረሱን ገዝቶ ይሄዳል፡፡
ቤቱ እንደደረሰ የግልቢያ ልብስ ይቀይርና ፈረሱ ላይ ወጥቶ ወደ ሠፈሩ ገና ብቅ ሲል፤ በሀብታምነቱ የሚያውቁት የሠፈሩ ሰዎች፤
“ፈረስ ማለት ይሄ ነው እንጂ!”
“ለእኛም ቢሆን ለአይናችን እንዲህ ያለ ፈረስ አይተን አናውቅምኮ፤ አለፈልን ዘንድሮ”
“የተጋጋጠ ፈረስ ለጋሪ እያሰለፉ ሲያሰቃዩን ከርመው ዛሬ ዕውነተኛ ፈረስ መጣ”
የማይሰጥ ዓይነት አስተያየት የለም፡፡ ጉድ ተባለ!
ባለፈረሱ መጋለብ ጀመረ፡፡ ለካ ፈረሱ አልተገራ ኖሮ አንዴ ሽቅብ ይዘላል፡፡ አንዴ ሳያስበው ሽምጥ ይሮጣል፡፡ በልጓም ቢለው፣ በእግሩ ቢለው፣ ከኮርቻው ቢነሳ፣ ወደፊት ቢያጐነብስ አልቆም አለ፡፡ ሩጫውን ቀጠለ፡፡
አንድ ጋላቢውን የሚያውቅ ወዳጁ ከቤቱ ሲወጣ አየውና፤
“አያ፤ ኧረ ወዴት ነው የምትሮጠው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ጋላቢውም፤
“እኔ ምን አውቃለሁ፤ ፈረሱን ጠይቀው” አለው፡፡
*   *   *
መልክና ቁመናውን ዓይተን ያልተገራ ፈረስ ከመግዛት ይሰውረን፡፡
“ስትጋልበው ታየዋለህ” እየተባልን የወጣንበት ፈረስ መጨረሻው አያምርም፡፡ በጊዜ ያልመከርንበት ገበያ ኪሣራው ብዙ ነው፡፡ ብቸኛ ሽያጫችንን ለማሳመር ብለን ያወዳደስነው ያልተጠና ነገር ጉዳቱ በርካታ ነው፡፡ የዛሬ ባለሀብትነታችንን አይቶ የሚያሞግሰን ሁሉ ዕውነተኛ ደጋፊ ነው ብለን ማሰብ አደገኛ ነው፡፡ ከሚጨምር ዋጋ ያድነን! ካልተገራ መመሪያ፣ ካልተገራ አዋጅና ካልተገራ ተከታይ ይሰውረን!
የሥልጣን ፖለቲካ ልሂቃን እንዲህ ይላሉ፡፡ መቀበል አለመቀበል እንደየመሪው ይለያያል፡፡
“ብቸኛ ተፈላጊ ለመሆን ህዝብ ባንተ እንዲተማመን እንዲመካ አድርግ፡፡ ህዝቦች ደስታና ብልጽግናን ካንተ ወዲያ ሊያገኙ እንደማይችሉ አድርገህ ቃኛቸው፡፡ ካንተ በላይ ሊያደርጋቸው የሚችል ዕውቀት አትስጣቸው”
ታዋቂው የፕሬዚዳንት ኒክሰን አማካሪ ሔንሪ ኪሲንጀር ራሱን ያቆየው፣ እዛም እዛም በሚነሱት ጉዳዮች ውስጥ ስለሚገባ፣ እሱን ማጣት ለፕሬዚዳንቱ በጣም ጐጂ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ አይተኬ በመሆኑ ነው፡፡ አይተኬነት የራሱ ችግር አለው፡፡ አጠቃላዩ ዕምነት ግን አይተኬ ነኝ የሚል ግለሰብ፤ ውሎ አድሮ አይነኬ ነኝ ማለቱ ነው፡፡ ከእኔ በላይ ላሣር ማለቱ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን!
ፀሐፍት፤ “የኮለምበስ ስትራቴጂ” የሚሉትን አንርሣ፡፡ “ሁሌ ጠንካራ ጥያቄ ይኑርህ፡፡ የራስህን ትልቅ ዋጋ አስቀምጥ፡፡ አታወላውል፡፡ በኩራት ከፍተኛው ደረጃ ካለው ሰው እኩል ቁም፡፡ አንድ ስጦታ ለበላይህ ስጥ” ይህን ስትራቴጂ የሚጠቀሙ አያሌ ናቸው፡፡ አንዱ የሙስና በርም ይሄ ነው፡፡ እኩያ ሙሰኞች፤ እኩያ የፖለቲካ አቅም እየፈጠሩ የሚከስቱት ነው፡፡ ህንፃዎቻችን፣ መኪናዎቻችን፣ መሬቶቻችን በምንና እንደምን ተገኙ ብሎ መጠየቅ የአባት ነው፡፡ መጠንቀቅ ያለብን፤ ማኪያቬሊ እንደሚለው፤ “ከመወደድ መፈራት ይሻላል፡፡ ምነው ቢሉ ፍርሃትን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ መውደድን ግን በፍፁም ለመቆጣጠር አይቻልም፤” ከሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች የሚመኩብን አብረውን ለመሆን ካላቸው ፍቅር ከሚሆን ይልቅ እኛን በማጣት ከሚፈጠርባቸው ፍርሃት የተነሳ ቢሆን ይሻላል - እንደማለት ነው፡፡ ይሄ በራሱ አደጋ እንደሚሆን ልብ እንበል፡፡
ሥልጣን ላይ ለመቆየት ከሚጠቀሱ ዘዴዎች መካከል አንድ ፈረንጆች የሚጠቅሱት አባባል አለ፤ “ኦርጅናሌ ሀሳብህን ለሚቻቻሉህ ጓደኞችና ልዩ ፍጡር መሆንህን ለሚያደንቁ ወዳጆችህ ብቻ አማክር” ይላሉ፡፡ ዕውነቱ ግን ህዝቡ ከልቡ ያልመከረበት ነገር ፍሬ - አልባ መሆኑ ነው፡፡ ህዝብን ማማከር ሲባል፤ ነገር ካለቀ ከደቀቀ በኋላ መሆን የለበትም፡፡ ፈረንጆቹ “የሞተ ፈረስ መጋለብ” የሚሉት ይሆናልና (Riding a dead horse) የተበላ ዕቁብ የሚለው ነው አበሻ፡፡ ባለቀ ጉዳይ ላይ መምከር አንድም “እንዳያማህ ጥራው” ነው፡፡ አንድም “ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ ነው፡፡
ሞንጐላውያን ቻይናን በወረሩ ጊዜ መሪያቸው ጄንጂስ ካን፤ ከሁለት ሺ ዓመት በላይ የቆየው የቻይና ባህል እሴት፤ አይታየውም ነበር፡፡ ይልቁንም ለፈረሶቹ ግጦሽ የሚሆን በቂ ሣር ያልበቀለባት አገር በመሆንዋ፤ “ቻይናውያንን ከምድረ ገጽ አጥፍቶ ሣር ማብቀል ይሻላል” የሚል አቋም ነበረው፤ ሆኖም ብልሁ አማካሪው ዬሎ ቹሳይ “አገሪቱን ከማጥፋት ይልቅ እዚያ የሚኖረውን እያንዳንዱን ነዋሪ ግብር ብታስከፍለው ያገር ሃብት ትሰበስባለህ” አለው፡፡ ካን አማካሪው ያለውን ፈፀመ፡፡ ቀጥሎ ኬይፌንግ ከተማን ወረረና ነዋሪውን ላጥፋው አለ፡፡ አማካሪው ቹሳይ “አይሆንም የቻይና ጥበበኞችና መሀንዲሶች ተሰብስበው የሚገኙት እዚህ ነውና ከምታጠፋቸው ተጠቀምባቸው” አለው፡፡ ጄንጂስ ካን አማካሪው የነገረውን አደረገ፡፡ ተጠቀመ። ወገናዊነት በሌለበትና ኢ-ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ግብር ማስገባት አግባብነት አለው፡፡ ምሁራንንም በአግባቡ መጠቀም ሥልጣኔ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን እንደ ዬሉ ቹሳይ ያለ አማካሪ ያሻል፡፡ መካር አሳስቶኝ ከሚባልበት ዘመን መውጣት ይጠበቅብናልና!
በሀገራችን ዴሞክራሲ ሙሉ በሙሉ እንደሰፈነ የሚያስመስሉ አያሌ አማካሪዎች ናቸው፡፡ ልማት ያጠጠባት፤ ፍትህ የበለፀገባት፤ መልካም አስተዳደር ቤት ደጁን ያጣበበባት አገር ናት እያሉ፤ ራሳቸው ግን ያልለሙ፣ ከኢ-ፍትሐዊነት ያልፀዱ፣ ያስተዳደር ጉድለት የሚፈጽሙ፣ ግን በአደባባይ ችሎት ስለ ንጽህናቸው የሚጮሁ አያሌ ናቸው፡፡ “ላም የሌለው ጉረኛ፤ አፉን በወተት ይጉመጠመጣል” ማለት እኒሁ ናቸው፡፡

Saturday, 24 June 2017 11:25

ቆቅ ሆነን

እየው ኖርን ሳንዋደድ፣ እድሜም ገፋ እንደ ዘበት፣
ለሰው ይምሰል ጥላችንም፣ እንደፍቅር ተወራለት፡፡
ባንድ ማድ፣ እየበላን እየጠጣን፣
ለሚያየን አስጎምጅተን፣ እያስቀናን፤
አለን ሳንተኛ፣ ሳናንቀላፋ፣
እኛው በኛ፣ ስንጋፋ፡፡
ቆቅ ሆነን፣ ስንጠባበቅ፣
ደግሞ- የዋህ መስለን ስንሳሳቅ፤
ብዙ…. ብዙ! ዘመን፣ ተቆጠረ፣
ቂም ሳይፈታ፣ እንደከረረ!፡፡
      ጋሻው ሙሉ

Saturday, 24 June 2017 11:23

እግዜር ግንበኛ ነው

የናንተን አላውቅም፣ እኔ ግን እላለሁ
እውነቱን ለእግዚአብሔር፣ እመሰክራለሁ፡፡
ጥሩ! አድርጎ እሚያንጽ፣ እግዜር ግንበኛ ነው
ያለ ጭስ ፋብሪካ፣ ሰውን ገጣጠመው፡፡

     በአምስት የስነ ልቦና ምሩቃን ከአንድ አመት በፊት የተቋቋመው ‹‹አብርሆት›› የስነ-ልቦና አገልግሎት ማዕከል በሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀመረ፡፡ ማዕከሉ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን እነዚህም የህፃናትና የወጣቶች የአዕምሮ ህመምና የጋብቻ፣ የሚዲያ የጥናትና ምርምር እንዲሁም የስልጠና እና በአደጋ ምክንያት ሰዎች የንግግር ክህሎታቸውን ሲያጡ የሚታከሙበት የንግግር ህክምና ዲፓርትመንቶች እንደሆኑ ታውቋል። በተለይ የህፃናትና የታዳጊዎች ዲፓርትመንት የአዕምሮ እድገትና የንግግር መዘግየትን ጨምሮ ሌሎች እክሎችን ምርመራና ምዘና በማድረግ ህክምና ይሰጣል ተብሏል፡፡ የስነ-ልቦና ጉዳይ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት፣ የስነ ልቦና መንስኤዎችና ወሳኝ መፍትሄዎች ደግሞ በጥናትና ምርምር ክፍሉ ይከናወናል ተብሏል፡፡
ስልጠናን በተመለከተ ማዕከሉ ለተቋማት፣ ለግለሰቦችና በተለይ የስነ-ልቦናና የአዕምሮ ችግር በቤተሰባቸው ውስጥ ላለ ወላጆችና አሳዳጊዎች በየደረጃው እንደሚሰጥም ከማዕከሉ መስራቾች አንዱ የሆኑት አቶ ሄኖክ ኃይሉ ገልፀዋል፡፡ ከሱስ፣ ከአዕምሮ ህመምና ከተያያዥ ችግሮች ጋር ያሉ ህሙማን ተኝተው መታከምና ማገገም የሚያስፈልጋቸው ከሆነም ለ“ቤዛ” እና “ስጦታ” ከተባሉ የስነ- አዕምሮ ህክምና ማዕከላት ጋር ማዕከሉ ባደረገው ስምምነት የሚታከሙበት ሁኔታ መመቻቸቱም ተገልጿል፡፡
ከሙያው ጋር ለ30 ዓመት እንደሚተዋወቁ የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር ፍሬው ከፍያለው፤ ወጣቶቹ ማዕከሉን ለማቋቋም ከፈቃድ ማውጣት ጀምሮ የገጠማቸው ውጣ ውረድ አልፈው ለዚህ መብቃታቸውን አድንቀው፤ በስራቸው ታማኝና ጠንካራ ሆነው ህዝብን በሀቅ እንደሚያገለግሉ እመተማመናለሁ ያሉ ሲሆን ወደፊትም በሚችሉት መጠን ማዕከሉንና ወጣቶቹን ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡ ‹‹አገራችን ላይ ሙያ ተሸጦ የሚተረፍበት ደረጃ ላይ አልተደረሰም›› ያሉት መስራቾቹ፤ “እኛም ሙያ ሸጠን ለማትረፍ ሳይሆን በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ክፍተት በአቅማችን ለመሙላት በጣም መጠነኛ በሆነ ክፍያ አገልግሎቱን ለመስጠት ማዕከሉን አቋቁመናል” ብለዋል፡፡

   በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማንሳት ስራ ላይ ተሰማርቶ የቆየው ሮዝ ቢዝነስ ግሩፕ በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን ባለ ሶስት እግር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የጃፓን ቴክኖሎጂን የታጠቁ፣ ባትሪያቸውን በኤሌክትሪክ በመሙላት ብቻ የሚጓጓዙ፣ ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎችን ደብረ ዘይት አካባቢ በገነባው ፋብሪካው ማምረቱን የኩባንያው ባለቤት አቶ ሮቤል እስጢፋኖስ አስታውቀዋል፡፡
ፋብሪካውን ከአንድ ዓመት በፊት መገንባት እንደጀመሩ የጠቆሙት አቶ ሮቤል፤በአሁኑ ወቅት በአንድ ሰዓት አንድ የኤሌክትሪክ ባለ ሶስት እግር መኪና ማምረት እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ለ4 ሰዓት በተሞላ ባትሪ መቶ ኪሎ ሜትር ድረስ መንዳት ያስችላል ያሉት ባለቤቱ፤ ኤሌክትሪክ ለመሙላትም 7 ብር ብቻ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል፡፡
ተሽከርካሪው በዋናነት ከከተማ ውጪ ላሉ አካባቢዎች የሚያገለግል ሲሆን ለሰፋፊ ግቢ የውስጥ ለውስጥ እንቅስቃሴ፣ ለሽርሽር እንዲሁም ለተለያየ ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል፡፡ ሹፌሩን ጨምሮም 7 ሰዎች የመያዝ አቅም አለው፡፡
ኩባንያው ተሽከርካሪውን ከኢትዮጵያ አልፎ ለምስራቅ አፍሪካ ገበያ ለማቅረብ ማቀዱንም ባለቤቱ ባለፈው ሰኞ፣ በተሽከርካሪው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
የኩባንያው መነሻ ካፒታል 24.9 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ለ105 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ሮቤል፤የተሽከርካሪውን ዋጋ በተመለከተ ገዥዎች ሲመጡ ብቻ ቢያውቁት ይሻላል በሚል ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡