Administrator

Administrator

ገጣሚ ሙሉጌታ ተስፋዬ በሙዚቃ ውስጥ የህብረተሰቡን ድርሻ ሲገልጽ ምን ብሏል መሰለዎ ?
“ሕብረተሰቡማ ምን ያድርግ ? ሙሾውንም ሰጠ፤ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ዓለማዊ ዘፈኑንም ሰጠ፤ ሲድር ደግሞ ‘ ጉሮ ወሸባ ‘ የሚባልበትንም ሰጠ። ሁሉንም ሰጠ። ከዚህ በላይ ምን አለውና ምኑን ይስጥ?
(“ፈርጥ” መጽሔት ሐምሌ /1992 በተፈራ መኮንን )
ይኸውልዎት እንግዲህ ሕብረተሰቡ ለእርስዎ ያለውን ሁሉ ሰጥቷል። አንድ ሕዝብ ለመሪው መስጠት የሚችለውን ሁሉ ሰጥቷል። ድጋፉን ሰጥቷል፤ ሕይወቱን ሰጥቷል፤ ድምጹን ሰጥቶ መርጧል፤ “ጦር ሜዳ ገብቶ ፈረስ አይለወጥም “ ብሎ መመረጥ ያለባቸውን የተፎካካሪዎችዎን እጩዎች ትቶ መመረጥ ያልነበረባቸውን የእርስዎን እጩዎች መርጧል። ሙሾውንም፣ የሰርግ ዘፈኑንም ሰጥቶዎታል። ሕዝቡ ያልሰጠዎት የለም። ከሕዝቡ የቀረ የለም። አሁን ያለው ከእርስዎ የሚጠበቀው ነው።
መስከረም 24 ቀን 2014 ከተመሰረተው አዲሱ መንግሥት ሕዝቡ ብዙ ይጠብቃል። ሕዝብ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ረሀቡንም ጥሙንም ችሎ ዝም ያለው፣ ሀገሪቷ እሷት ላይ መሆኗንና እርስዎም እሳት ማጥፋት ላይ መሆንዎን በማሰብ ነው። ሕዝብ በራሱ መሪዎች ሲበደልም ሲገደልም ዝም ያለው ይህን በመረዳት ነው። ስለዚህ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መስከረም 24 ቀን 2014 ለእርስዎ የደስታ ሳይሆን የፈተና መጀመሪያ ቀን ነው። ከዚያ በኋላ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ የተመረጠ የመጀመሪያው መንግሥት ምስረታ ቀን ይሆናል። ይህ መንግሥት ከሌሎቹ የበለጠ እዳ የተሸከመ መንግሥት ነው። ይህን ጦርነት በድል ይወጡታል። ኢትዮጵያ ስለምታሸንፍ። ማሸነፍ ስላለባት። ከዚያ ግን ፈተናዎ ይብሳል። የረጋ ሀገርን መምራት ይከብዳል። ሙሾውንም የሰርግ ዘፈኑንም የሰጠዎት ሕዝብ ከእርስዎ የሚጠብቀው እስካሁን የሰጡትን ያህል ብቻ አይደለም። እጅግ ብዙ ነው። ሕዝቡን እንዲያክሉ ፈጣሪ ይርዳዎ። አሜን።Wednesday, 13 October 2021 06:17

የፖለቲካ ጥግ

በአሜሪካ በሁለቱም ፓርቲዎች ውስጥ በርካታ የመርህ ሰዎች አሉ፤ የመርህ ፓርቲ ግን የለም።
አሌክሊስ ዲ ቶኩቪሌ
በጦርነት ልትገደል የምትችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በፖለቲካ ግን በተደጋጋሚ  ልትገደል ትችላለህ፡፡
ዊንስተን ቸርችል
በአብዛኛው ቋንቋ እውነትን መደበቂያ መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል።
ጆርጅ ካርሊን
ቃላት ሃቀኛና መልካም ሲሆኑ ዓለምን ሊለውጡ ይችላሉ።
ቡድሃ
መጥፎ ባለሥልጣናት የሚመረጡት ድምጽ በማይሰጡ ጨዋ ዜጎች ነው፡፡
ጆርጅ ዣን ናትሃን
እኛ መንግስትን ስንዋሽ ወንጀል ነው። መንግስት እኛን ሲዋሸን ፖለቲካ ነው።
ቢል ሙዴይ
ዲሞክራሲ ድምጽ የመስጠት መብት ብቻ አይደለም፤ በክብር የመኖር መብትም ነው።
ናኦሚ ክሌይን
ፖለቲካ ፍልስፍናን በተካበት ዓለም ውስጥ ነው ያለነው፡፡
        ማርቲን ኤል.ግሮስ
የፖለቲካ ሥልጣን ከጠብመንጃ አፈሙዝ ይወለዳል።
ማኦ ዚዶንግ
ዎልስትሪት የበዛ ሃብትና የፖለቲካ ሥልጣን አለው።
ቻርሊ ሙንገር
ፖለቲካ ከሞራል ጋር ዝምድና የለውም።
ኒኮሌ ማኪያቬሊ
መንግስት ሲሳሳት ትክክል መሆን አደገኛ ነው።
ቮልቴር

Wednesday, 13 October 2021 06:07

የጸሐፍት ጥግ

ፀሐፊ መሆን ከፈለግህ፣ ከምንም በላይ ሁለት ነገሮችን ማድረግ ይገባሃል፡፡ ይኸውም፡- ብዙ ማንበብና ብዙ መፃፍ።
ስቲፈን ኪንግ
* በውስጥህ ያሉትን ድምጾች ካልፈራህ፣ ካንተ ውጭ ያሉትን ሃያስያን አትፈራም።
ናታሊ ጎልድበርግ
* ፀሐፊ፤ ለዓለም ጉዳይ ትኩረት የሚሰጥ ሰው ይመስለኛል፡፡
ሱዛን ሶንታግ
* ትልቅ መፅሐፍ ለመፃፍ፣ ትልቅ ጭብጥ መምረጥ አለብህ።
ሔርማን ሜልቪሌ
* የማንበቢያ ጊዜ ከሌለህ፣ የመፃፊያ ጊዜ አይኖርህም።
ስቲፈን ኪንግ
* በጭንቅላትህ ውስጥ ላሉ ታሪኮች ታማኝ ሁን።
ፓውላ ሃውኪንስ
* መፃፍ ለእኔ፣ በጣቶቼ በኩል ማሰብ ነው።
አይሳክ አሲሞቭ
* መፅሐፍ በእጅህ ላይ የሚገኝ ህልም ነው።
ኔይል ጌይማን
* ያልተነበበ ታሪክ፣ ታሪክ አይባልም፡፡
ዩርሱላ ኬ.ሌ ጉይን
* ፀሐፊ መሆን ትመኛለህ? እንግዲያውስ ፃፍ።
ኢፒክቴተስ
* ህይወትህ ባዶ ገፅ ነው፤ ፃፍበት።
ዶናልድ ሚለር

Wednesday, 13 October 2021 06:09

የታሪክ ጥግ

ያለፈ ታሪኩን፣ አመጣጡንና ባህሉን
የማያውቅ ህዝብ፣ ሥር እንደሌለው
ዛፍ ነው።
ማርከስ ጋርቬይ
. የቀድሞው ህብረተሰብ ታሪክ በሙሉ
የመደብ ትግል ታሪክ ነው።
ካርል ማርክስ
. ታሪክን መለወጥ አልችልም፤
መለወጥም አልፈልግም። እኔ
የምችለው ነገን መለወጥ ብቻ ነው።
ያንንም እየሰራሁ ነው።
ቦሪስ ቤከር
. ስለ መጪው ጊዜ አትፍራ፤ ስላለፈው
ዘመን አታልቅስ።
ፔርሲ ቢሼ ሼሊ
. ታሪክ ከስምምነት ላይ የተደረሰበት
ውሸት ነው።
ናፖሊዮን ቦናፓርቴ
. ታሪካችን ዕጣ ፈንታችን አይደለም።
አላን ኮኸን
. ታሪክ መፃፍ ያለበት እንደ ፍልስፍና ነው።
ቮልቴር
. ሳይንስን ለመረዳት ታሪኩን ማወቅ
አስፈላጊ ነው።
አጉስቴ ኮምቴ
. ታሪክ የሚጻፈው በአሸናፊዎች ነው።
ዊንስተን ቸርችል
. በሁሉም ሰዎች ህይወት ውስጥ ታሪክ
አለ።
ማርክ ትዌይን
. ጊዜ ለእኔ ትልቁ ጠላቴ ነው።
ኢቪታ ፔሮን


Wednesday, 13 October 2021 06:06

የስኬት ጥግ

. ትችትን ለማስወገድ ብቸኛው
መንገድ፡- ምንም አለመስራት፣ ምንም
አለመናገርና ምንም አለመሆን ነው።
አሪስቶትል
. እስከዛሬ ስታደርግ የቆየኸውን
ካደረግህ፣ እስከዛሬ ስታገኝ የቆየኸውን
ታገኛለህ።
ቶኒ ሮቢንስ
. የራስህን ህልም እውን ካላደረግህ፣ ሌሎች
የራሳቸውን ህልም እውን ለማድረግ
እንድታግዛቸው ይቀጥሩሃል።
ዲሂሩቢሃይ አምባኒ
. እያንዳንዱን ቀን በምታጭደው
አዝመራ አትለካ፤ በምትተክለው ዘር
እንጂ።
ሮበርት ሉዊስ ስቲቨንሰን
. ጥያቄው ማነው የሚፈቅድልኝ
አይደለም፤ ማነው የሚከለክለኝ ነው።
አየን ራንድ
. ዛፍ ለመትከል ትክክለኛው ጊዜ ከ20
ዓመት በፊት ነበር፡፡ ሁለተኛው
ትክክለኛ ጊዜ ደግሞ አሁን ነው።
የቻይናውያን አባባል
. የህይወት ዘመንህ ውስን ነው፤
የሌሎችን ህይወት በመኖር
አታባክነው።
ስቲቭ ጆብስ
. በአስከፊ ሁኔታ ለመውደቅ የሚደፍሩ፣
በአስደናቂ ሁኔታ ስኬት ይቀዳጃሉ፡፡
ጆን ኤፍ. ኬኔዲ
. የትላንት ውሳኔህ የነገ ውጤትህን
እንዲወስን አትፍቀድ።
ማርክ ዱድሌይ
. አቋራጮች ረዥም መዘግየትን
ይፈጥራሉ፡፡
ጄ.አር.አር.ቶልኪን
. ዓላማ ቢስ ህይወት ትርጉም የለሽ ነው።
ኤሚ ቶሬስ
.ህይወት ባለበት ሁሉ ተስፋ አለ።
አሊሰን ኖዕል

 በቀድሞው የኢህአፓ መሥራችና ደራሲ ሃማ ቱማ (እያሱ አለማየሁ) የተጻፉ የእንግሊዝኛ ግጥሞች በቤተማርያም ተሾመ  ወደ አማርኛ ተተርጉመው፣ "የሃማ ቱማ ስብስብ ግጥሞች" በሚል ርዕስ ታትሞ ለሽያጭ ቀረበ፡፡ በመጽሐፉ የእንግሊዝኛ ግጥሞችና ትርጉማቸው ጎን ለጎን መታተማቸው ታውቋል፡፡  
ሀማ ቱማ በእንግሊዘኛ ግጥሞቹ አለም አቀፍ ዕውቅናን የተቀዳጀ  ደራሲ ሲሆን በበርካታ የፖለቲካ ስላቅ  መጣጥፎቹም  ይታወቃል። ብዙዎች “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ታሪክ” በሚለው ስራው ይበልጥ ያውቁታል።
በሙያው መካኒካል መሀንዲስ የሆነው ቤተማርያም፤ ከዚህ ቀደም  “ሦስተኛው ቤተመቅደስ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡ በቅርቡ ደግሞ “ጠያይም መላእክት" የተሰኘ አዲስ ስራውን ለንባብ እንደሚያበቃ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቤተማርያም በፌስ ቡክ ገፁ በሚያስነብባቸው ግጥሞቹም ይታወቃል።
የሃማ ቱማ ስብስብ ግጥሞች  በጃፋርና ሌሎች መጻህፍት መደብሮች እየተሸጠ ሲሆን መጽሐፉ  በቅርቡ በደማቅ ሥነስርዓት እንደሚመረቅም  ቤተማርያም ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ከዚህ በታች ከመጽሐፉ የተወሰደ አንድ የእንግሊዝኛ ግጥም ከእነ ትርጉሙ ቀርቧል፡፡
 ***
Just a Nobody
The dead man was no one,
just a man in tattered clothes,
no shoes,
just a coin in his pocket,
no id cards, no bus ticket.
He was a nobody,
dirty and skinny,
a no one, a nobody
who clenched his hand before he died?
When they pried open his fingers
this nobody,
they found a whole country.
***
ማንም ምንምነት
ቡትቶ የለበሰ አካሉ የገረጣ፣
ጫማ የማያውቀው እግሩ መጅ ያወጣ።
ምንም ‘ማይታወቅ “እከሌ” ‘ማይባል፣
ከስቶና ታርዞ አንድ ምስኪን ሞቷል።
አባከና ሊለው ማንም የማይደፍር፣
ኪሱ አንዳች የሌለው ከድንቡሎ በቀር።
ከቁብ የማይፃፍ ማንም ያልነበረ፣
ከመሞቱ በፊት ጣቶቹን ቆልፎ ጨብጦ ነበረ።
እጆቹን ፈልቅቀው ሲፈታ ጭብጡ።
ከጣቶቹ መሀል ሀገሩን አገኙ ፣ሀገሩን አወጡ።መቀመጫውን በአሜሪካ ዳላ ቴክሳስ ያደረገው አድዋ የባህልና የታሪክ ህብረት፤  የአርአያ ሰው ሽልማት መስራች ነው፡፡
ከኢትዮጵያ የባህል አልባሳት ውጭ መልበስ፣ እራስን ካለማክበር ይቆጠራል  ይላል። ለሀገር ለወገን ብዙ የሰሩን ባመሰገንን ቁጥር፣ ብዙ የሚሰሩ ዜጎችን እንፈጥራለን ብሎ ያምናል ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ፡፡  የአርአያ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ላለፉት አምስት ዓመታት በአሜሪካ ነበር የተካሄደው ስድስተኛው የአርአያ ሰው ሽልማት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ይካሄዳል።  አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከመስራቹ ዲያቆን ፍሬው ሰይፉ ጋር ተከታዩን ቃለመጠይቅ አድርጓል።                  ከምን ያህል ጊዜ በኋላ ነው ወደ አገርህ ከመጣህ?
በመሃል አንድ ሁለቴ ብመጣ  ስድስት ዓመት ያህል  ሳልመጣ ቆይቻለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ሁለት ሳምንትንት ሆኖኛል። እስካሁን ነገሮች ጥሩ እየሄዱ ነው።
ባህላዊ አልባሳትን ታዘወትራለህ፡፡ ሁሌም ነው?
ይሄ ልምድ አስራ አራት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ2000 ጀምሮ እነደዚህ ነው የምለብሰው፤ 365 ቀናት በአራት ዓመት አንዴም 366 ቀን ማለት ነው፡፡
ለስራና ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ?
አይከብድም! ምክንያቱም ለኔ በጣም ተመችቶኝ ነው የምለብሰው፡፡ መመቸት ወይንም ያለመመቸት ጭንቅላት ውስጥ ነው የሚያልቀው፡፡ በትክክል አሁን ትውልዱ የሚያደርገው ነገር የሚመች ነው ወይ ካልን ብዙ ምቾት የሚነሱ ነገሮች እናያለን፤ ግን ትውልዱ ደግሞ ተመችቶኛል ብሎ እየለበሰ ነው፤ ስለዚህ መመቸት ወይንም ያለመመቸት መጀመሪያ ጭንቅላት ላይ ነው የሚሰራው። ዓለም የሚያከብርሽ መጀመሪያ ራሽን ስታከብሪ ነው የራስነ ጥሎ ስልጣኔ የለም፡፡ ስልጣኔ ማለት የራስን እያከበሩ መኖር ማለት ነው፡፡ ምን አልባት እኛ ያለን የህይወት ዘይቤ እንዳይመች አደርጎት ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነው ሆኖ ግን ስራዬ ብለሽ ከያዝሽው ግን  ለዛ ነገር የሚያስፈልገውን እያበጀሽ ትሄጃለሽ፡፡ እርግጥ ቀላል አይደለም አብዛኞቹ ልብሶች ነጭ እንደመሆናቸው ጥንቃቄ በጣም ይፈልጋሉ ሲታጠቡ እነኳን ከሌላ ልብስ ጋር ተደባልቀው መታጠብ ላይኖርባቸው ይችላል። ደረቅ እጥበት ብቻ ሊፈልጉም ይችላሉ፡፡ እሱ ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ወጪ ነው፡፡ ስለዚህ በጣም በጉዳዩ ላይ ማመን ያስፈልጋል፡፡
ወደ አርአያ ሰው ሽልማት እንምጣ። መቼ ተመሰረተ አላማውስ?
የተመሰረተው እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ2006 ዓ.ም ነው አስካሁን ዘጠነኛው መሆን ነበረበት ግን በመሃል እኔ ወደ አሜሪካ ስሄድ እዛ ያለውን ማህበረሰብ እስካውቅና ማን አንዴት ነው የሚሸለመው የሚለው መልስ እስኪያገኝ ለሶሰት ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል፡፡ ዋና ዓላማም ምንድን ነው? እኛ እንዳለመታደል ሆኖ ከመመሰጋገን ከመከባበር ይልቅ መጠላለፍ ነው የሚቀናን። ብዙ ጊዜ ሰዎች ብዙ መልካም ነገሮችን ከማመስገን ይልቅ የተሳሳቷትን ጥቂት ነገር አጉልተን እያሳየን፣ ሰዎች ለተሻለ ነገር እራሳቸውን እንዳያዘጋጁ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ይህን ለመቅረፍ ምን እናድር አርአያ ሰዎች፤ ምሳሌ የሚሆኑ ሰዎች ያስፈልጉናል፤ ቢኖሩንም ግን ሳናመሰግናቸው ሃሳባቸው ተቀብሮ እንዳለነ ሲገባን የአርአያ ሰው ሽልማት በ2006 ዓ.ም አርአያዎቻችን ለማመስገን ተወለደ፡፡ ያኔ እኔ ካለሁበት ነው የተነሳው። ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያን ባህላዊ አልባሳት ዲዛይን በማድረግ፣ የቆዩት እማማ ፅዮን አምዶም (ኮሎኔል አማረ ኣምዶም እህት)  በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሞዴልና ዲዛይነር የነበሩት፣ የክብር ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወላጅ እናት እማማ ቅድስት የታወቁ ዲዛይነር ነበሩ። እሳቸው በህይወት ባይኖሩም፣ ይህንን መንገድ የክብርት ፕሬዚዳንቷ  እህት ወ/ሮ ራሔል አስቀጥለውት፣ አሁንም “ቅድስት ጥበብ” አለ፣ እማማ ደስታ (ዲዛይነር ደስታ) “የህዝብ ለህዝብን” ሙሉ ልብስ ያዘጋጁ እና ለ365 ቀናት የጥበብ ልብስ በመልበስ ከወንድ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅን ከሴት  ደግሞ የህሊና ገንቢ ምግቦች ፋብሪካ ባለቤት ወ/ሮ ገነት በለጠን በዛን ጊዜ ለ13 ዓመታት ጥበብ በመልበስ፣ ለ53 ዓመታት ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው፣ ብዕር ቀርፅው ታሪክን የዘገቡ መምህር ጌታ መክብብ የሚባሉ  ታዋቂ የብራና ፀሃፊ …. እነዚህ እነዚህን የመሳሰሉ የሙካሽ ሠራተኞች ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጀምሮ ለነገስታቱ ይሠሩ የነበሩ ትልልቅ የሀገር ባለሙያዎችን ፈልጎ፣ እነሱን በማግኘት ያመሰገንበት ሁኔታ ነው የመጀመሪያው ሽልማት፡፡
በቀጣይ ዓመት ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ መታሰቢያነቱን ለቱሪዝም አባት አቶ ሀብተስላሴ ታፈሰ እንዲሁም፣ ለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች፣ ለኢትዮጵያዊቷ ሆሜር ተብለው ለሚታወቁት ልበ ብርሃኗ እማሆይ ገላነሽ እና ለፊደል ገበታ አባት ተስፋ ወልደስላሴ እንዲሁም አወዘ ውስጥ እነ ጋሽ አበራ ሞላ፣ ጌታ መሳይ አበበ፣ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ እነ አለሙ አጋ እና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ የሆኑ ባለውለታዎች የተሸለሙበት ነበር፡፡
ከዛ ሶስተኛው ሽልማት ደግሞ በአሜሪካ ሀገር ተደረገ ኮሚኒቲውን በፍፁም ተህትና ሲያገለግሉ የነበሩ ከዛ እልፍ ሲል ደግሞ እንደ ማህበረሰብ እንደ ዜጋ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ለነበሩ እንደነ ታማኝ በየነ፣ የአምባሰሏ ንግስት ማሪቱ ለገሰ የመሳሰሉት ተሸልመዋል፡፡
ይኸው ዘንድሮ ስድስተኛው የአርአያ ሰው ላይ ደርሰናል፡፡ ዘንድሮስ ሽልማቱ በምን መስፈርት ነው የሚሰጠው?
እንደ ተቋም አድዋ የባህልና የታሪክ የሚባል አለ፤ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ያደረገ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ መሰረቱ ቴክሳስ የሆነ፣ በሃገሩ እውቅና ያለው፤ አርአያ ሰው የዛ ተቋም አንድ አካል ነው፡፡ በዋናነት ታሪክ ባህልና ቅርስን ነው የሚያስተዋውቀው ተቋሙ፡፡ ይልቁንም አሜሪካን አገር ተወልደው ለሚያድጉ ህፃናት እራሳቸውን ወደ ማወቅ እንዲመጡ፣ በራሳቸው እውቀት ላይ ተመስርተው ታሪካቸውን እንዲያውቁ በትምህርት ቤት ከሚማሯቸው ልጆች ጋር ስለ ማንነታቸው በደንብ እንዲናገሩ፣ ክህሎታቸውን ማሳደግ ነው፡፡ በዘርፉ ደግሞ በባህል በቱሪዝም በቅርስ አይተኬ የሚባል ትልልቅ ስራዎች ሰርተው ያለፉ እንዲሁም በህይወት ያሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዝግጅት ላይ የሚዘከሩበት የሚታሰቡበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ወደ መስፈርት  ስንመጣ  የኛ ሽልማት ውስጥ ምንም አይነት የተለየ ማወዳደሪያ የለም የሚወዳደርም የለም ሲጀምር፡፡ ዋናው ነገር አይተኬነት ነው። ለዘርፉ ዋጋ እየከፈሉ የሚያገለግሉ፣ እየተከፈላቸው ሳይሆን አስከ ህይወት መስዋትነት እየከፈሉ የሚያገለግሉ ናቸው። እርግጥ እንደዚህ አይነት ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት አሉ ወይ ቢባል የሉም ነው መልሱ፡፡ ለዛም ነው በብዛት የማናወዳድረው። በጣም ትንሽ ከመሆናቸው አንጻር እንሳሳላቸዋለን። ድንገት በሆነ ዘርፍ ላይ  ሁለት ሰዎችን ብቻ ልናገኝ እንችላለን፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በየተሰማሩበት የቱሪዝም መስክ በጣም የሚገርም አይነት አቅም ያላቸው እየተከፈላቸው ሳይሆን እየከፈሉ እንደዜጋ ኃፊነታቸውን እየተወጡ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ታዲያ እንደዚህ አይነት ዜጎችን ማወዳደር በራሱ የነሱን ድካም ዋጋ ማሳጣት ነው፡፡ የሚሰሩት ለገንዘብ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት ነው፡፡ ስለምንሳሳላቸው በአንደኛው አመት አንዱን ካመሰገንን በሚቀጥለው አመት አንደኛውን ከነሙሉ ክብራቸው እናመሰግናለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም ተሸላሚ ነበር በዘንድሮ ደግሞ የህይወት ዋጋ እስከመክፈል የደረሰው ታዋቂው የፎቶግራፍ ባለሙያ አዚዝ አህመድ በቱሪዝም ዘርፍ ተሸላሚ ነው፡፡ አዚዝን ከሄኖክ ጋር ማወዳደር አትችይም፡፡ ሁለቱንም በተሰማሩበት ዘርፍ  እንቁዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ እንሳሳላቸዋለን፤ ለማወዳደር፤ እራሱ አንደፍርም! ሀበሻ ልብስ ላይ ብትሄጂ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፤ ሶስት አራት አይሞሉም፤ ሶስት መቶ ስልሳ አምስት ቀን የሚለብሱ፡፡ ለምሳሌ ወ/ሮ ገነት በለጠን ከዘንድሮ ዓመት ተሸላሚ ጋር ብናወዳድራት፣ ሁለቱም የየራሳቸው ነገር ስላላቸው ለማወዳደር ይከብዳል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሰዎቸ እየቆጠብን ነው ወደ ሽልማት የምናመጣቸው፡፡
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ መቼና የት ነው የሚደረገው?
ጥቅምት 11 ቀን 2014  በዮድ አቢሲንያ የባህል አዳራሽ ይከናወናል፡፡
በዕለቱ የአለባበስ ህግም እንዳለ ሰምቻለሁ?
እውነት ነው፡፡ አንዱና ዋናው አላማችን፣ የራሳችን የሆነውን ነገር ማስተዋወቅ ስለሆነ፣ በዕለቱ ከባህላዊ ልብስ ውጪ መልበስ አይፈቀድም፡፡
ውድድሩ  የዳኞችና የህዝብ ድምጽስ አለው?
የህዝብ ድምፅም ዳኝነትም የለውም፤ ምክንያቱም ቅድም እንደገለፅኩት ተሸላሚዎቹ አይወዳደሩም፡፡ በስራቸው ይመረጣሩ፡፡
የዘንድሮ ሽልማት ለሶስት ሰዎች መታሰቢያነት እንደሚውል ገልፀሃል..
አንደኛው የተሰበረ ልብን የሚጠግኑት የመጀመሪያው የልብ ማዕከል መስራች ዶ/ር በላይ አበጋዝ፤ በርግጥ እኛ ከተነሳንበት የቱሪዝም ሃሳብ ጋር ምንም አያገናኛቸውም፤ ግን አይተኬ የሚባል ክስተት ናቸው፡፡ ብዙ የተሻለ ነገር ወደሚያገኙበት ቦታ መሄድ እየቻሉ ኢትዮጵያ ሀገሬን ብለው እያገለገሉ ያሉ ናቸው፡፡ እነሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳይሆን ኢትዮጵያ እነሱ ልብ ውስጥ ያለች እስኪመስል የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ አንድ ልቡ የተሰበረ ህፃን ልቡ እየተጠገነ ያለው እሳቸው በጣሉት መሰረት ነው፡፡ ድንገት ዶ/ር በላይ አበጋዝ ባይኖሩ ኖሩ፣ የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን መርጃ ህልም ሆኖ ይቀር ነበር፡፡  ሁለተኛው ብ/ጄኔራል ፍሬሰንበት አምዴንም ስንመለከት ትውልድና ትውልድን እንደ ድልድይ ያገናኙ ሰው ናቸው፤ ግን ያልተዘመረላቸው፡፡ ሌላው አለም ላይ ቢሆን አሁን የምናነሳቸው ሰዎች ሳስተው ሙዚየም ውስጥ  ያስቀምጧቸው ነበር፡፡ ግን ያልሆነ ቦታ ሆነና እነዚህን ሰዎች አጉልቶ ማውጣት አልቻልንም፡፡
ሌላ ሀገር ስትመለከቺ፤ መዝናኛ ፓርክ አበባና ዛፍ ብቻ ሳይሆን ለዛ ሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎች ሁሉ መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸው በየፓርኩ ቦታ አላቸው፡፡  ወደኛ ስንመጣ ለሀገር ውለታ የዋሉ ብዙ ሰዎች አሉን፤ ግን ለዛ የሚሆን እውቅና መስጠት ነው ያልቻልነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይም ያለፈው ዓመት ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የርዕሰ ብሔሯ መኖሪያ የሆነው ቤተ መንግስት ውስጥ ያለውን ቅርስ ሲያስጎበኙን ነበር፡፡ በቀጣይ ልክ እንደ ላይኛው ቤተ መንግስት የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን እየታደሰ ነው። እዛ ውስጥ ያየናቸው የጎበኘናቸው ቅርሶች ሁሉ  ለዚህ ትውልድ የደረሰው በብ/ጄ ፍሬሰንበት አምዴ ነው፡፡ እሳቸው 34 ዓመት ሙሉ አንድ ክፍል ቤት ተኝተው ነው ያንን ቅርስ ጠብቀው ያቆዩልን፡፡ ምን አልባት እሳቸው ያንን ስራ ባይሰሩ ኖሮ፣ ዛሬ ያሉት ቅርሰች ቦታቸው ላይ ላይገኙ ይችሉ ነበር። ግን አልተዘመረላቸውም! የኢትዮጵያን ነገር ማስቀደም አልቻልንም፤ ለዛም ነው እንዲህ ያሉ ሰዎችን በባትሪ ፈልገን ማግኘት ያልቻልነው፡፡ እሳቸው በሕይወት ባይኖሩም ልጆቻቸው ከአሜሪካ መጥተው ሽልማታቸውን ይቀበላሉ፡፡ ሶስተኛዋ የዘመን ክስተት፣ የእስክስታዋ ንግስት እንዬ ታከለ ናት፡፡ አሁን ላይ የባህል ውዝዋዜያችን የቱ ጋ ነው ያለው ብንል፤ ብዙ መወያያዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ምልክቶች ናቸው፡፡ የሆነ ጊዜ ይመጣሉ፤ ከዛ እንደ ቅርስ ነው የምታያቸው፡፡ ስለዚህ የዘንድሮ የአርአያ ሰው ሽልማት የእነዚህ ሶስት ሰዎች መታሰቢያ ይሆናል፡፡
የክብርና ልዩ ተሸላሚ ተብለው የየታሰቡ አሉ?
አዎ ከዚህ ዘርፍ ውጪ የሆነ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ስራ የሰሩ  አሉ፡፡ ለምሳሌ ወደ ኪነጥበቡ ብንመጣ ፣ ህዝቡ እውቅና ሰጥቷቸው ህዝቡን የማያገለግሉ አሉ፤ በዛው ልክ ደግሞ በተሰጣቸው እውቅና ልክ ለህዝቡ የሚያገለግሉ ክብር ዝና ህዝብ እንደሆነ የሚያውቁ አሉ፡፡ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ግንባር ቀደም የሆኑ ሰዎችን በማመስገን፣ እነሱን በሚመስሉ ሰዎች ዙሪያ ንቃተ ህሊናን መፍጠር ነው። ከኪሳቸው አውጥተው የሚጠቀሙት ምንም ነገር የለም፤ እነሱ የሚጠቀሙት ስማቸውነ በቻ ነው፡፡ ህዝቡ ደግሞ ስምሽን ተጠቅሞ ሊደግፍሽ የሆነ ነገር ሊያደርግልሽ ይቆማል፡፡ ለምሳሌ “ዛሬ ልደቴ ነው፣ ልደቴን በማስመልከት አንድ ብር በማዋጣት ይህን ተቋም ይደግፉ” የሚል አናገኝም ግን ቀላሉ መንገድ ይህ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የኢንስታግራም ተከታይ ኖሯቸው፣ ህዝብን የሚጠቅም ስራ ሳይሆን የሚሰሩት የራሳቸውን ፍላጎት የሚያሟሉ የኪነጥበብ ሰዎች በሞላባት ሀገር ውስጥ ጥቂት ብቅ ያሉትን አውጥተን ስናጎላቸው ስናመሰግናቸው፣ ሌሎችን ማንቂያ፡፡ ነው እነሱን ደግሞ በርቱ ከዚህ የተሻለም አንጠብቃለን ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ የክብር ተሸላሚያችን ሲስተር ዘቢደር ነች፡፡ በበጎ አድራጎት ስራ ይልቁንም ራሳችን ለራሳችነ መፍትሄ እንደምንሆን ያሳያችን፣ ለ27 ዓመት ምንም የውጭ ተቋም ሳታስገባ ራሷን ችላ  በአገር ውስጥ ደጋፍ ብቻ  መስራት እንደሚቻል አረጋግጣለች፡፡
ሌላኛዋ በኪነጥበብ ዓለም ተፅእኖ ፈጣሪና የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ማዕከል አምባሳደር የሆነቸው  አርቲስት መሰረት መብራቴም ተሸላሚ ናት። በዚህም ሌሎች የኪነጥበብ ሰዎችን የበለጠ ለማነቃቃት ይረዳናል ብለን እናምናለን። ስራዎችን እያየን እንደሆነና ያ ስራ ደግሞ እንደ ሀገር እየጠቀመን እንደሆነ ለማሳየትም ለማመስገንም ይረዳናል፡፡
በሀገራችን ሰባት ያህል የሽልማት ተቋማት አሉ ሰስለዚህ ማመስገንን ስላሳዩን ስላመሰገኑን ሰባቱን የሽልማት ተቋማት እናመሰግናቸዋለን፡፡ የሰሩ ሰዎችን ባመሰገንን ቁጥሩ ብዙ የሚሰሩ ሰዎችን እናፈራለን  እንፈጥራለን፡፡
ብዙ ጊዜ እንዲህ አይነት ስራዎች ስፖንሰር (ድጋፍ) ሲያገኙ አይታይም፡፡ ለምን ይመስልሃል?
ድጋፍ የሚሰጡ ተቋማት የንግድ ተቋም እንደመሆናቸው ምንድነው የማገኘው ትርፍ ብለው ያስባሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ የቢራ ፋብሪካ ስፖንሰር ቢያደርግ በዕለቱ ቢራውን ለታዳሚያን በነፃና በብዛት ማቅረብ ይፈልግ ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ አርአያ ሰው ሽልማት ላይ የማይታሰብ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሊያደርጉን አይፈልጉም፡፡ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት ሳይሆን ትርፍን ብቻ  ስለሚያስቀድሙ እንዲህ አይነት ነገሮች አይሳኩም፡፡ የሆነው ሆኖ ሌሎች  የዚህ አይነት እሳቤ የሌላቸው ተቋማት አሉ፡፡ ለምሳሌ ዮድ አቢሲንያ ያለምንም ክፍያ አዳራሹን ሲፈቅድልን፣ የኛን ስራ እየሰራህ ነው ብሎ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ሽልማቶች ድጋፍ ካላገኙ ቀጣይነታቸው እራሱ አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡ በኛ በኩል ግን ለቀጣይ 5 ዓመታት ስፖንሰር ቢኖርም ባይኖርም ይቀጥላል፡፡ የኛ ተቋም ሲመሰረት ባለቤቴ 1000 የአሜሪካን ዶላር ሰጥታ ነው የተቋቋመው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ የባሎቻቸውን ህልም የሚኖሩ ሚስቶችንና የሚስቶታቸውን ህልም የሚኖሩ ባሎችን ያብዛልን፡፡
ሰው ቤተሰቡ የሚሰራው ስራ ውስጥ እጁ ከሌለ በምትፈልጊው ልክ ሀሳብሽ አይሳካም። እና ሁሉን ነገር ፈቅዳና አምናበት “ያንተ ልፋት የኔ ልፋት ነው፤ ውጤትህ ውጤቴ ነው” ብላ የበኩሏን ስለምታደር ምስጋናዬ እጅግ ላቅ ያለ ነው፡፡


በሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት በየወሩ ሚካሄደው የኪነ- ጥበብ ምሽት ሰኞ ትቅምት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ከ11 ጀምሮ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል፡፡
“ታሪክ ምን ይለናል” በሚል መርህ በሚካሄደው የኪ-ጥበብ ምሽት ላይ ወግ ግጥም ዲስኩርና ሙዚቃ ለታዳሚ የሚቀርብ ሲሆን፣በዕለቱም ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)፣ የህግ ባለሙያው ወንድሙ ኢብሳ፣ገዛኸኝ ፀጋው(ዶ/ር)፣አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፣ ደራሲና ጋዜጠኛ ግሩም ተበጀ፣ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም፣ ጋዜጠኛ የኑስ መሃመድ፣ ገጣሚያኑ መንበረማሪያም ሀይሉ፣ መዝገበቃል አየለ ገላጋይ፣ ሀይማኖት አሰፋና ምንሊክ ብርሃኑ ከአድዋ ባንድ ጋር በመሆን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡ በዶ/ር ሙሉ የጥርስ ህክምና ስፖንሰር የተደረገው በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመታደም የመግቢያ ዋጋው 100 ብር ሲሆን የመግቢያ ቲኬቶቹ በጃዕፋር፣ በዮናስ በዘወዱ መፃህፍት መደብሮች እንደሚገኙም ታውቋል፡፡


በመላው አፍሪካ የሚገኙ የጥበብ፣ የባህል፣ የቅርስና የቢዝነስ ሰዎች የሚሳተፉበት “አፍሪካ ሰለብሪቲስ” ልዩ መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ለስምንት ቀናት ይካሄዳል፡፡የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን 2021 ዓ.ምህረትን የጥበብ፣የባህል፣ ቅርስና የቢዝነስ ዓመት አድርጎ በአጀንዳ 2063 ስር ማካተቱን ተከትሎ ይህ በርካታ ሁነቶች በአንድ ላይ የሚከወኑበት መርሃ ግብር መሰናዳቱን አዘጋጆቹ  ረቡዕ ረፋድ ላይ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ አፍረካ ሰለብሪቲ ሁነት በሁሉም አፍሪካ አገራት የሚገኙ የቢዝነስ የመዝናኛ የባህልና ቅርስ እንዲሁም የቢዝነስ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን “ክለብ አዲስ” እና ሌጀንደሪ ጎልድ ሊሚትድ ናይጀሪያና ፕሪስቲን ማርኬቲንግ በጋራ እንዳዘጋጁት ተገልጿል፡፡ በሁነቱ ላይ ከተለያየ የአፍሪካ ሀገራት የሚመጡ ተሳታፊዎች የየሀገራቸውን ባህል፣ቅርስ፣የቱሪስት መስህቦች፣የቢዝነስ ስራዎችና የፋሽን ስራዎችን ለእይታ  የሚቀርቡበት ነውም ተብሏል፡፡

 የታዋቂው የፊልም ባለሙያ  ዳንኤል ክሬግ ወይም ጀምስ ቦንድ የመጨረሻ ፊልም እንደሆነ የተነገረለት “No time to die” የተሰኘውን አዲስ ፊልም፣ ሃይኒከን ኢትዮጵያ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያ ፊልም አፍቃሪያን  ለእይታ አበቃ።
ፊልሙ ትናንት በሸራተን አዲስ በተከናወነ የቀይ ምንጣፍ ሥነሥርዓት ዝነኛ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት  ታይቷል፡፡
የአገራችንን የእግር ኳስ አፍቃሪያን ፍላጎት ለማርካት የሻምፒዮንስ ሊጉን ዋንጫና እነ ሮናልዲኒዮን የመሳሰሉ በዓለም ዝናቸው የናኘ ተጫዋቾች ወደ ኢትዮጵያ በማመጣት የሚታወቀው ሃይንከን ኢትዮጵያ፤ አሁን ደግሞ በመላው ዓለም እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘውን “No time to die” የተሰኘ የጀምስ ቦንድ አዲስ ፊልም ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለፊልም አፍቃሪያኑ አቅርቧል።
ሃይንከን ኢትዮጵያ፤ የፊልም አፍቃርያንን ፍላጎት ለማርካትና ከደንበኞቹ ጋር ያለውን ቤተሰባዊ ቅርርብ ይበልጥ ለማጠናከር በማሰብ፣ ፊልሙን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለእይታ ማብቃቱ ታውቋል።
በሸራተን አዲስ በተከናወነው የቀይ ምንጣፍ ስነ-ስርዓት ላይ ታዋቂ ግለሰቦችን ጨምሮ የሃይኒከን ኢትዮጵያ ቤተሰቦችና የምርቱ ተጠቃሚዎች ታድመው ነበር፡፡ በእንግሊዝ በመጀመሪያ ቀን እይታ ብቻ ከ5 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ገቢ ማስገኘቱ የተነገረለትና ባለፈው ሳምንት በእንግሊዝና አየርላንድ በሚገኙ 772 ሲኒማ ቤቶች ውስጥ ለእይታ የበቃው አዲሱ የጀምስ ቦንድ “No time to die” ፊልም፤ በኤድናሞል ሲኒማና በጋስት ሲኒማ ለተመልካቾች እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ሃይኒከን፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ከጀምስ ቦንድ ፊልም ጋር ባለው የአጋርነት ስምምነት መሰረት ነው ፊልሙን ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣው ተብሏል፡፡Page 5 of 556

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.