Administrator

Administrator

ሮተሪ ክለብ በአዲስ አበባ የተቋቋመበትን የ25ኛ ዓመት በዓል ዛሬ ያከብራል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ማዕከል በሚከበረው በዚሁ በዓል ላይ የክለቡ አባላት፣ በጐ ፈቃደኞችና ታዋቂ ሰዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
እ.ኤ.አ ፌቡራሪ 23 ቀን 1905 ዓ.ም በቺካጐ የተቋቋመው ሮተሪ ክለብ፤ በአሁኑ ወቅት በ200 አገራት ውስጥ የሚገኙ 33 ሺ ክለቦችንና ከ1.2 ሚሊዮን በላይ አባላትን ይዟል፡፡
ክለቡ በበጐ ፈቃደኛ አባላቱ አማካኝነት በመሠረታዊ ትምህርት አቅርቦት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በበሽታ መከላከል፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃና በንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም በማህበረሰብ ኢኮኖሚ ልማት ላይ እየሰራ ይገኛል፡፡

Saturday, 16 January 2016 10:39

የኪነት ጥግ

(ስለ ሥነጥበብ)
• ሁሉም ሰዓሊ መጀመሪያ አማተር ነበር፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
• ስዕል ቃላት አልባ ግጥም ነው፡፡
ሆራስ
• ስዕል ውብ መሆን የለበትም፡፡ ትርጉም
ያለው መሆን ነው ያለበት፡፡
ዱዋኔ ሃንስ
• ስዕል ለመሳል ዓይናችሁን ጨፍናችሁ
መዝፈን አለባችሁ፡፡
ፓብሎ ፒካሶ
• ጥበብ ድንቁርና የሚባል ጠላት አላት፡፡
ቤን ጆንሰን
• ጥበብ የሰው ተፈጥሮ ነው፡፡ ተፈጥሮ
የእግዚአብሔር ጥበብ ነው፡፡
ጄምስ ቤይሌይ
• የጥበብ ተልዕኮ ተፈጥሮን መወከል እንጂ
መኮረጅ አይደለም፡፡
ዊሊያም ሞሪስ ሃንት
• ጥበብ የነፃነት ልጅ ናት፡፡
ፍሬድሪክ ሺለር
• ጥበብ ቤትን ሳይለቁ የማምለጪያ ብቸኛ
መንገድ ነው፡፡
ትዊላ ዛርፕ
• ስዕል ሃሳቦቼን የማስርበት ምስማር ነው፡፡
ጆርጅስ ብራኪው
• ሰዓሊ የሚከፈለው ለጉልበቱ አይደለም፤
ለርዕዩ እንጂ፡፡
ጄምስ ዊስትለር
• የሰዓሊ ዋና ሥራው ወደ ሰው ልጅ ልቦና
ብርሃን መላክ ነው፡፡
ጆርጅ ሳንድ
• ዓይኖቼ የተፈጠሩት አስቀያሚውን ነገር
ሁሉ ለመሰረዝ ነበር፡፡
ራኦል ዱቲ
• ሰው በእርሳስ መሳል ሲያቅተው በዓይኑ
መሳል አለበት፡፡
ባልዙስ

    ታዋቂው ገጣሚና ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም “ከአሜን ባሻገር” የተሰኘ አዲስ መጽሃፍ ያሳተመ ሲሆን በመጪው ሳምንት ገበያ ላይ ይውላል ተብሏል፡፡ “በመጽሐፌ ከጉዞ፣ ከኑሮና ከምርምር የቀሰመኩትን እውነታ ለማካፈል ጥረት አድርጌያለሁ፡ ፡” ብሏል፤ በዕውቀቱ በፌስቡኩ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ፡፡በ2004 ዓ.ም በለንደን ኦሎምፒክ ከዓለም ዕውቅ ገጣሚያን ጋር የግጥም ሥራውን ያቀረበው በዕውቀቱ፤በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ በትምህርትና ምርምር ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም ደራሲው “ነዋሪ አልባ ጎጆዎች”፣ “በራሪ ቅጠሎች;፣ “እንቅልፍና ዕድሜ”፣ “መግባትና መውጣት” የተሰኙ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹን ለንባብ አብቅቷል፡፡

  ባለፈው ሐምሌ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ከወህኒ ያመለጠው፤ በ10 ሜትር ጥልቀት 1500 ሜትር መተላለፊያ ዋሻ                አስቆፍሮ ነው።
              ሰሞኑን፣ በልዩ ሃይል የተወረረው መኖሪያ ቤቱም፣ የማምለጫ ዋሻ ተሰርቶለታል - ጀርመን ልኮ                ባሰለጠናቸው መሃኒዲሶች።  
             በሜክሲኮ፣ የአደንዛዥ እፅ አስተላላፊዎች፣ በገንዘብና በትጥቅ የፈረጠሙ ቡድኖች ናቸው - 100                ከንቲባዎችን ገድለዋል።
    ከኮሎምቢያ ወደ አሜሪካ በሚያመራው፣ የአደንዛዥ እፅ ማስተላለፊያ መስመር መሃል ላይ ያለችው ሜክሲኮ፣ ከአሰቃቂ የግድያ ዜናዎች እፎይ ያለችበት ጊዜ የለም። የዘወትር ሕይወት ነው። ከሳምንት በፊት የተካሄደ የቀብር ስነስርዓትም፣ በሜክሲኮ ምድር፣ እንግዳ ነገር አልነበረም። ሟቿ፣ ጌሲላ ማዎቴ፣ አደንዛዥ እፅ በሚያስተላልፉ ታጣቂዎች ነው የተገደለችው። ለዚያውም፣ በከተማ የከንቲባ ምርጫ ያሸነፈቸው ጌሲላ፣ ደስታዋን የማጣጣም ጊዜ አልነበራትም። ስልጣን በተረከበችበት እለት ተገድላለች ይላል የታይም መፅሄት የሰሞኑ እትም። ካሁን በፊትም፣ 100 ከንቲባዎች በአደንዛዥ እፅ አስተላላፊ ቡድኖች እንደተገደሉ መፅሄቱ ገልጿል።
ታዲያ፣ ‘የአደንዛዥ እፅ አስተላላፊ’ ሲባል፣... ‘አይነት’ አለው። የየመንደሩ ዋና አለቆች፣ ታጣቂዎችን በቡድን አደራጅተው ያሰራሉ። የየከተማው አውራዎችም አሉ - የበላይነት ለማግኘትና ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር፣ ዘወትር ይገዳደላሉ፤ ይጨፋጨፋሉ። እነዚህን ሁሉ ጠቅልለው፣ በየክልሉ የገነኑ መሪዎች ግን፣ ሚሊዮነሮች ከመሆናቸውም በላይ፣ እልፍ ታጣቂዎች እንደሚያዘምት ሃያል ገዢ ነው የሚታዩት። ግን፣ የያዝኩትን ይዤ ልኑር ብሎ ነገር የለም። የገናናዎቹ ሁሉ ቁንጮ ለመሆንና ገዢነታቸውን ለማስፋፋት፣ ፋታ በማይሰጥ ጦርነት ይጠመዳሉ። መንግስት ያለበት አገር አይመስልም። እናም፣ አንደኛው ወገን በጦርነቱ ከቀናው፣ ገናና የአደንዛዥ እፅ ጌታ ወይም ንጉሥ ይሆናል።
ከ1995 ዓ.ም ወዲህ፣ ዙፋኑን ተቆጣጥሮ የቆየው፣ የሜክሲኮ የአደንዛዥ እፅ ንጉሥ፣ ጆአኪን ጉስማን ይባላል። በቅፅል ስሙ፣ ኢል ቻፖ ይሉታል (አጭሬው እንደማለት ነው)። ከኢል ቻፖ በፊት፣ ስመ ገናና የአደንዛዥ እፅ ንጉሦች አልነበሩም ማለት አይደለም። ፓብሎ ኢስኮባርን መጥቀስ ይቻላል። የኢል ቻፖ ንግሥና ግን ለየት እንደሚል የዘገበው ፎርብስ፣ እስከ አሜሪካ ከተሞች ድረስ መረቡን ዘርግቶ፣ የማከፋፈያና የችርቻሮ አውታሮችን በማደራጀት፣ በታሪክ አቻ ያልተገኘለት የአደንዛዥ እፅ ሽያጭ እንዳካሄደ ገልጿል።
በሜክሲኮ ምድር፣ ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመቀጠል፣ በሃያልነት የሚጠቀስ ‘ገዢ’ ኢል ቻፖ ነው። ገናናነቱ ግን፣ በሜክሲኮና በጎረቤት አገራት ብቻ አይደለም። በመላው አለም፣ ኢል ቻፖን የሚስተካከል የአደንዛዥ እፅ ወንጀለኛ የለም ብሏል ፎርብስ። ለዚህ የበቃውም፣ በአይምሬነቱና በጭካኔው ነው። ተቃናቃኞችን ማስገደል፣ መጨፍጨፍና ማጥፋት... ይሄ የተለመደ ነው። ሌላው ቀርቶ፣ ጥቂት ደቂቃ ያረፈደ የአደንዛዥ እፅ አመላላሽና አከፋፋይ እንኳ፣ በሕይወት እንደፈረደ ነው የሚቆጠረው - በኢል ቻፖ ግዛት።
እንዲህ፣ በጭካኔው፣ ከመንደርና ከከተማ አለቃነት፣ ወደ ላይ ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምር ነበር፣ በ1985 ዓም ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረው። እንደ ወንጀሉ ብዛት ባይሆንም፣ የሃያ ዓመት እስር ተፈረደበት። ግን የእስር ቅጣቱን ሳያጠናቅቅ፣ በ1993 ዓ.ም ከወህኒ አመለጠ። የቆሸሹ ልብሶችን ወደ እጥበት የሚወስድ መኪና ውስጥ ተደብቆ ያመለጠው ኢል ቻፖ፣ እቅዱን ለማሳካት ለበርካታ የወህኒ ቤቱ ፖሊሶች ደሞዝ በመክፈል እንዲተባበሩት ማድረጉን ዩኒቨርሳል የተሰኘው ጋዜጣ ዘግቧል። የሜክሲኮ ፖሊሶች፣ ኢል ቻፖን ለመያዝ የከፈቱት የምርመራና የአደን መዝገብ፣ በአጭር ጊዜ አልተቋጨም። አስተማማኝ መረጃ ያገኙት፣ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ነው - የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ። ከአራት በላይ ሚስቶች እንዳሉት የሚነገርለት ኢል ቻፖ፣ ወደ አንዲት የቀድሞ ሚስቱ መኖሪያ ቤት ጎራ ያለው፣ ደርሶ ለመመለስ ብቻ ሳይሆን፣ በዚያውም ከልጆቹ ጋር ለመሰንበት ነው።
መረጃው ትክክል ከሆነ፣ ኢል ቻፖን ለመያዝ አይከብደንም በሚል የተሰማሩት ፖሊሶች፣ እንደገመቱት አልሆነላቸውም። የቤቱን በር ገንጥለው ለመግባት ሞከሩ። በሩ፣ ግን ንቅንቅ አላለም። አያስታውቅም እንጂ፣ በጠንካራ ብረት ተደራርቦ ስለተሰራ፣ እንደ ካዝና በር፣ አይነኬ ሆነባቸው። በዚህም በዚያም ብለው፣ በስንት መከራ መግባታቸው ግን አልቀረም። አዩ፣ በረበሩ፣ ፈተሹ። ሰውዬው የለም። ለካ፤ መሬት ስር፣ አምስት ቤቶችን አቆራርጦ የሚያስወጣ፣ መተላለፊያ ዋሻ አሰርቶ ኖሯል። ፖሊሶቹ፣ ‘አመለጠ’ ብለው አልተቀመጡም። ሰውዬውም፣ ርቆ አልሄደም። ‘ሪዞርት’ ሆቴል ውስጥ፣ መሰንበቻውን ክፍሎች ተከራይቶ ተቀምጧል - ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር። 60 የባህር ሃይል ኮማንዶዎች፣ አካባቢውን በመቆጣጠር፣ ኢል ቻፖን አስረው ወደ ወህኒ መለሱት።
ኢል ቻፖ፣ እንደገና ከእስር ለማምለጥ፣ በርካታ አመታትን አልፈጀበትም። ከታሰረበት ክፍል ስር፣ በምድር ስር፣ ረዥም መተላለፊያ ዋሻ በማስቆፈር፣ አምና በ2007 ዓ.ም፣ አመለጠ። ከእስር ቤቱ ግቢ አልፎ፣ አንዲት አነስተኛ ቤት ድረስ፣ ከሰው እይታ ውጪ፣ በአስር ሜትር ጥልቀት የተቆፈረው መተላለፊያ ዋሻ፣ 1500 ሜትር ርዝመት አለው። የአየር ማስገቢ ቱቦና የመብራት መስመር ሁሉ ተዘርግቶለታል። በዚያ ላይ፤ አፈሩን በቁፋሮ ለማውጣትና በመጨረሻም ኢል ቻፖን ለማጓጓዝ፣ የሃዲድ መስመርና፣ በሃዲዱ ላይ የሚሄድ ሞተር ሳይክል... ምናለፋችሁ፤ ነገሩ ብዙ ተለፍቶበታል። ኢል ቻፖ፣ ከወህኒ ካመለጠ በኋላ፣ ለሆሊውድ አክተር ሾን ፔን በድብቅ ቃለምልልስ ሲሰጥ፣ ስለ ዋሻው አሰራር ተናግሯል። መተላለፊያ ዋሻውን የሰሩልኝ፣ የጀርመን ልኬ ያሰለጠንኳቸው መሃንዲሶች ናቸው ብሏል - አጅሬው።
አስገራሚው ነገር፣ ኢል ቻፖ፣ ለጋዜጠኛ ሳይሆን፣ ለሆሊውድ አክተር ለሾን ፔን፣ ቃለምልልስ የሰጠው፣ ከቃለምልልሱ ውጭ ሌላ ህልም ስለነበረው ነው። በሕይወቱ ዙሪያ፣ ፊልም የመስራት ህልም ነበረው ብሏል - የሳምንቱ አዲስ የኢኮኖሚስት መፅሄት እትም። ከፊልም ባለሙያዎችና ከተዋናዮች ጋር ለመነጋገር ሲሞክር ከርሟል። የሜክሲኮ ልዩ ሃይል፣ ኢል ቻፖን ለመያዝ አስተማማኝ መረጃ ያገኘውም በዚሁ አጋጣሚ ነው።
እንደተለመደው፣ ለአዳር የመረው መኖሪያ ቤት፣ ከመሬት ስር፣ ማምለጫ ዋሻዎች የተዘረጉለት ነው። ደግሞም፣ አምልጧል። ቱቦ ለቱቦ እየተሽለኮለከ፣ በጣም ርቆ ከሄደ በኋላ፣ ከዚያም ከቱቦው ወጥቶ የከተማ ዳርቻ ለመድረስ ሲቃረብ ነው የተያዘው።  

  አዲሱን “የአምስት ዓመት እቅድ” ለማስተዋወቅ የተለቀቀ ዘፈን! ግጥሙ እንዲህ ይላል፡
                 “If you want to know what China’s gonna do
                  Best pay attention to the shi san wu.”
            በግርድፉ አንተርጉመው ቻይና የምትሰራውን ልወቅ ካሉ የልማቱን እቅድ ልብ ይበሉ
   የቻይና መንግስት፣ አዲስ ዘፈን የለቀቀው ቢጨንቀው ይሆናል። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ እንደ ወትሮው አይደለም። ከ“ሁለት አሃዝ” እድገት ጋር እየተራራቀ ነው። በየዓመቱ ከ10% በላይ የኢኮኖሚ እድገት፣ ከእንግዲህ በቻይና እንደማይደገም፣ የአገሪቱ መንግስት ቁርጡን አውቆ ተናግሯል። በ7% ግን ያድጋል ተብሏል። ይህም ቀላል አይደለም።
ደግሞም፣ ለሰላሳ ዓመታት፣ አስደናቂ እድገት ስትገሰግስ የቆየች አገር ናት። ድንቅ ነው። 10 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ የሞቱባትና በከባድ ድህነት የምትሰቃ አገርኮ እንደነበረች። የያኔው የ‘ሶሻሊዝም’ አባዜ፣ በርካታ አገራትን፣ ቻይናንም ጨምሮ ለባሰ ድህነትና ረሃብ ዳርጓል።
አሃ፣ ሰው፣ በራሱ ጥረት፣ ህይወቱን እንዳያሻሽል የሚከለክል ሶሻሊስት ፓርቲ በገነነበት አገር፤... ሃብት ንብረት ማፍራት “ከሁሉም የከፋ ቁጥር 1 የወንጀል ተግባር ነው” ብሎ የሚያውጅ ሶሻሊስት መንግስት በነገሰበት አገር፣ እንዴት ከድህነት መውጣት ይቻላል? ቻይናም፣ ከዚሁ ታሪክ ቀማሽ ናት።
በ1967 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሶሻሊዝም አብዮት ሲታወጅና ንብረት ሲወረስ፤ ቻይና የሶሻሊዝምን መዘዝ ማለትም ድህነትንና ረሃብን እየተጎነጨች ነበረች። የአንድ ቻይናዊ አማካይ የአመት ገቢ፣ 200 ዶላር አይደርስም ነበር (ያው፣ ከኢትዮጵያና ከብዙዎቹ ድሃ የአፍሪካ አገራት የማይሻል)።
ደግነቱ፣ ብዙም ሳይቆይ ነው፣ አንዳንድ የአገሪቱ ባለስልጣናት የባነኑት። “ስራና ኑሮ - በማህበር ብቻ” ብሎ የግል ንብረት እየወረሰ አገርን ማተራመስ እንደማያዋጣ ሲያዩ፣ በዚያው የውድቀት ጎዳና ከመቀጠል ይልቅ፣ ቀስ በቀስ የግል ስራንና የግል ቢዝነስን ለመፍቀድ ለመፍቀድ ወሰኑ። “ሃብታም መሆን፣ ጀግንነት (ቅዱስ) ነው” የሚል መፈክር በየአደባባዩ ወደመዘርጋት ተሸጋገሩ (To be rich is glorious)።
ይህችኑን ‘ሚጢጢ የካፒታሊዝም ቡቃያ’ ትንሽ ትንሽ እያስፋፉ፣ በዚያችው መጠንም እየተሻሻሉ፣ ተዓምረኛውን የእድገት ግስጋሴ ‘ሀ’ ብለው ጀመሩት። ይሄውና ዛሬ፣ የአንድ ቻይናዊ አማካይ የአመት ገቢ፣ ከ7ሺ ዶላር በላይ ሆኗል።
አዎ፤ የተወሰነ ያህል የነፃ ገበያ አሰራርን በማስፋፋት፣ የተወሰነ ያህል አድገዋል። ከዚህ በላይ ለማደግ፣ የነፃ ገበያ አሰራርን ይበልጥ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግም አልጠፋቸውም። ግን፣ በፍጥነት ለመራመድ የቻሉ አይመስሉም። የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ቀስ በቀስ እየወረደ ነው።
ታዲያ፣ ጉዳቱ፣ ለቻይናዊያን ብቻ አይደለም። የአሜሪካና የአውሮፓ ኢኮኖሚ ሲዳከም፣ አብዛኞቹ አገራት ጉዳት ይደርስባቸው የለ? ምርቶቻቸውን፣ በብዛትና በጥሩ ዋጋ ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ በመሸጥ፣ የሚያገኙት ገቢ ይቀንስባቸዋል። ልክ እንደዚያው፣ የቻይና ኢኮኖሚ ከተዳከመም፣ እንደወትሮው በፍጥነት ማደግ ካቃተው፣ ጉዳቱ ለሌሎች አገራትም ጭምር ነው።
ምናልባት፣ እንደ በጎ ነገር ሊጠቀስ የሚችለው፤ የቻይና የነዳጅ ፍጆታ ከኢኮኖሚዋ ጋር አብሮ ሲረግብ፣ የአለም የነዳጅ ዋጋ ይቀንሳል። ብዙዎቹ አገራት፣ በዚህ ይፅናኑ ይሆናል። ቻይናዊያንስ? መንግስት በለቀቀው ነጠላ ዜማ።      

               ታላቁ እጣ ሐሙስ ማታ ወጥቷል።
                ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው።
                ግማሹን መንግስት በታክስ ቆርጦ ይወስዳል።
                በሎተሪው የማሸነፍ እድል በጣም ትንሽ ነው።
                    300 ጊዜ በመብረቅ የመመታት አደጋ ይበልጣል።
    ከሳምንት ሳምንት የሽልማቱ መጠን እየጨመረ፣ ብዙ ሲወራለት የሰነበተው ታላቁ የአሜሪካ ሎተሪ፣ የ1.6 ቢሊዮን እጣ በማውጣት ሐሙስ ማታ እልባት አግኝቷል።
የሎተሪው ሽልማት ከሦስት ሳምንት በፊት ከ$250 ሚሊዮን በታች ነበር። እጣው ወጣ። ያሸነፈ ሰው አልነበረም። የእጣው ቁጥር ሲታይ፣ ያልተሸጠ ቲኬት ነው። ግን፣ በዚያው ጭጭ ብሎ አይቀርም። በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ እጣው እንደገና እንዲወጣ ይደረጋል። እስከዚያው፣ የትኬት ሽያጩ ይቀጥላል - የእጣ ማውጫ ቀን (ሐሙስና ቅዳሜ) ድረስ።
ቀኑ ደርሶ፣ የሎተሪው አንደኛ እጣ ወጣ። ሽልማቱ ወደ 300 ሚሊዮን አድጓል።  ማን አሸንፎ ይሆን? እንደገና አሸናፊ የለም ተባለ። እንዲህ፣ ከሐሙስ ወደ ቅዳሜ፣ ከዚያም ወደ ሃሙስ እየተሸጋገረ፣ የትኬት ሽያጩ እየተስፋፋ፣ ሽልማቱም እያደገ ቀጠለ። ወደ 350 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ 450 ሚሊዮን ዶላር... ብዙም ሳይቆይ ግማሽ ቢሊዮን ደረሰ። ከዚያማ፣ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ነው፤ ከቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሄድ የደረሰው - ባለፈው ቅዳሜ።
ትኬት የቆረጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ በጉጉት ቢጠብቁም። በቅዳሜውም እጣ፣ አሸናፊ አልነበረም። ያው፣ ሐሙስን መጠበቅ ነው። ሳይሸጡ የቀሩ ትኬቶች፣ እንደ ጉድ ሲቸበቸቡ... ትናንት በእጣ ማውጫው እለት፣ ሽልማቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደረሰ። እጣው ሲወጣም፣ አሸናፊው ቁጥር ታወቀ።

ሎተሪ ማሸነፍና በመብረቅ መመታት
ቲኬት የገዛ ሰው፣ የአንደኛ እጣ አሸናፊ የመሆን እድሉ ምን ያህል ነው? እጅግ በጣም ቅንጣት እድል እንደሆነ ለማሳየት፣ በታላቁ ሎተሪ አሸናፊ የመሆን አጋጣሚን፣ በመብረቅ ከመመታት አጋጣሚ ጋር አነፃፅሮታል - ኤንቢሲ።
እጣው በየእለቱ ቢወጣ እንኳ፣... እርስዎም ሳያዛንፉ በየእለቱ ትኬት ቢገዙ እንኳ፣... በ800ሺ ዓመታት ውስጥ፣ አንዴ ብቻ አሸናፊ ይሆናሉ። በእነዚሁ አመታት ውስጥ ግን፣ 300 ጊዜ በመብረቅ የመመታት አደጋ ይደርስብዎታል።
ሽልማቱም ተቀናሽና ተቆራጭ ይበዛበታል
የ1.5 ቢሊዮን ዶላሩ እጣ ቢያሸንፉ፣ ገንዘቡ ሙሉ ለሙሉ ወደ ባንክ ሂሳብዎ ይተላለፋል ማለት አይደለም።
አንደኛ ነገር፤ ሽልማቱን የሚወስዱት፣ ደረጃ በደረጃ በሰላሳ ዓመታት ነው (በአማካይ፣ በየአመቱ 50 ሚሊዮን ዶላር)።
“ትዕግስት የለኝም፤ አንዴ ሽልማቴን አፈፍ አድርጌ ልውሰድ” የሚሉ ከሆነም ይችላሉ። ነገር ግን፤ 900 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ነው የሚደርስዎት።
በእርግጥ፣ ከዚሁም ውስጥ መንግስት የተለያዩ አይነቶ ታክሶችን ይቆርጣል። ቢያንስ ቢያንስ 400 ሚሊዮን ዶላር ያህል ይወስዳል።
ቢሆንም፣ 500 ሚሊዮን ያህሉ የእርስዎ ይሆናል። ‘ኢንቨስት’ ቢያደርጉትና ቢሰሩበት... ይህም ባይሆን፣ እንዲሁ ‘ያለ ሃሳብ’፣ ባንክ ቢያስቀምጡት እንኳ፣ በየአመቱ፣ 20 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ያስገኛል። ‘መታደል ነው!’ ያሰኛል።
ግን፣ በርካታ የሎተሪ ባለእድለኞች፣ ያን ያህል ‘እድለኞች’ አይደሉም ይላል ትናንት የወጣው የዩኤስ ቱዴ ዘገባ። አንዳንዶቹ፣ ድንገት እጃቸው የገባው ገንዘብ፣ መጥፊያቸው ይሆናል። እንደ ዘበት የተገኘን ገንዘብ፣ እንደ ዘበት እየበተኑ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ። በሶስት ሺ የሎተሪ እድለኞች ላይ የተደረገው ጥናትም፣ የሎተሪ ገንዘብ በሰዎች ኑሮ ላይ ብዙም ለውጥ እንደማያመጣ ያረጋግጣል ብሏል ዩኤስቱዴ። አስር የሎተሪ እድለኞችና ሌሎች አስር ሰዎች... ከጥቂት ዓመታት በኋላ የሚኖራቸውን ኑሮ ብታነፃፅሩ፤ ከሁለቱም ወገን፣ ስኬታማ የሚሆኑ ይኖራሉ፤ ከሁለቱም ወገን ችግረኛ የሚሆኑ ይኖራሉ።    

Saturday, 16 January 2016 10:09

የዘላለም ጥግ

(ስለ ደስታ)

- ደስታን በራስ ውስጥ ማግኘት ቀላል
አይደለም፤ ሌላ ቦታ ማግኘት ደግሞ
አይቻልም፡፡
አግኔስ ሪፕልየር
- ደስታ ልክ እንደ ደመና ነው፤ ለረዥም ሰዓት
ትክ ብለህ ካየኸው ይተናል፡፡
ሳራ ማክላችላን
- ደስታ የሚገኘው በመስጠትና ሌሎችን
በማገልገል ነው፡፡
ሔነሪ ድራሞንድ
- ደስታ በአካል አለመታመም ወይም በአዕምሮ
አለመረበሽ ነው፡፡
ቶማስ ጄፈርሰን
- የተካፈሉት ደስታ ይጨምራል፡፡
ጆስያህ ጊልበርት ሆላንድ
- ራስን መርሳት ደስተኛ መሆን ነው፡፡
ሮበርት ሉዊስ ስቲቨንሰን
- ደስታን መግዛት ነፍስን መሸጥ ነው፡፡
ዳግላስ ሆርቶን
- ፈገግታ አፍንጫህ ስር የምታገኘው ደስታ
ነው፡፡
ቶም ዊልሰን
- ነፃነት ደስታ ነው፡፡
ሱዛን ቢ.አንቶኒ
- ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልግህ ጥሩ
ጠብመንጃ፣ ጥሩ ፈረስና ጥሩ ሚስት ብቻ
ናቸው፡፡
ዳንኤል ቡኔ
- ደስታ ለሰውነት ጠቃሚ ነው፤ የአዕምሮን
ኃይል የሚያጐለብተው ግን ሀዘን ነው፡፡
ማርሴል ፕሮስት
- የደስታ ሁሉ መሰረቱ ጤና ነው፡፡
ሌይግ ሃንት
- በመከራ ወቅት የደስታ ጊዜን ከማስታወስ
በላይ ከፍተኛ ሃዘን የለም፡፡
ዳንቴ አሊግሂሪ

Saturday, 16 January 2016 10:07

የዝነኞች ጥግ

(ስለ ሞዴሊንግ)
- ሞዴል አይደለሁም፡፡ ሞዴል የእውነተኛው
ነገር ቅጂ ነው፡፡
ማ ዌስት
- በቀን ከ10 ሺ ዶላር በታች ለሆነ ክፍያ
ከእንቅልፌ አልነሳም፡፡
ሊንዳ ኢቫንጄሊስታ
- መቀመጫዬ ፎቶግራፍ ለማንሳት ትልቅ
ካልሆነባቸው፣ ለእኔ ትልቅ ሊሆንብኝ
የሚገባ አይመስለኝም፡፡
ክርስቲ ቱርሊንግተን
- ለ20 ዓመታት በየቀኑ መስተዋት
ተመልክቼአለሁ፡፡ ፊቴ ያው ነው፡፡
ክላውዲያ ሺፈር
- አንዳንዴ ብቸኝነት ይሰማኛል፤ ነገር ግን
ብቸኛ መሆን ግሩም ነው፡፡
ታትጃና ፓቲትዝ
- ሜክአፕ የሚያጐናፅፈኝን በራስ መተማመን
እወደዋለሁ፡፡
ቲራ ባንክስ
- ጋዜጣ ከማንበብ ይልቅ የአካል እንቅስቃሴ
ማድረግ እመርጣለሁ፡፡
ኪም አሌክሲስ
- መቀመጫዬ ወደ ጎን ባያዘነብል እመኛለሁ፤
ነገር ግን ያንን መጋፈጥ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡
ክሪስቲ ብሪንክሌይ
- የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ለማግኘት ሁሉም
ሰው በቂ ገንዘብ ሊኖረው ይገባል፡፡
ቢቨርሊ ጆንሰን
- ሽቶ የማትቀባ ሴት ወደፊት ተስፋ የላትም፡፡
ኮኮ ቻኔል
- ሰውነቴን እወደዋለሁ፡፡ እግዚአብሔር
የሰጠኝ ነው፡፡
ኬት አፕቶን
- ሞዴሎች ብዙ ጊዜ በእኔ ጥያቄዎች ይደነቃሉ፡
፡ ሃሳባቸውን፣ ተስፋቸውን፣ ህልማቸውን …
ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡
ሃርሌይ ብራውን
- ልዕለ ሞዴል ለመሆን ለራሴ የአንድ ዓመት
ጊዜ ሰጠሁት፤ እናም “ካልተሳካ ወደ ት/ቤት
እመለሳለሁ” አልኩኝ፡፡
ቲራ ባንክስ
- እውነተኛ ውበት፤ ለራስ ታማኝ መሆን ነው፡፡
ያ ነው ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ፡፡
ላቲቲያ ካስታ

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ቆንጂት ልትዳር ሽማግሌዎች መጥተው ልጅዎን ለልጃችን ብለው ይጠይቁና እሺ ተብለው፤ ቀን ተቆርጧል፡፡ የሠርጉ ዝግጅትም ተጠናቋል፡፡ ተደገሠ፡፡ ተበላ፡፡ ተጠጣ፡፡
“ሙሽሪት ልመጅ
ሙሽሪት ልመጅ
እሰው ሀገር ሄዶ የለም የእናት ልጅ
እንዝርቱን ልመጅ
ደጋኑን ልመጅ
ምጣዱን ልመጅ
ሰፌዱን ልመጅ
እሰው ሀገር ሄዶ የለም የእናት ልጅ!” ተባለላትና ተሸኘች፡፡
ለመደች ለመደችና እናት አባቷን ለመጠየቅ መጣች፡፡
እናቷ ከአባቷ ይልቅ በሴትነት ለመወያየት ይቀርባሉና፤
“እንዴት ከረምሽ ልጄ?” አሏት፡፡
ልጅ፤
“ደህና ከርሜያለሁ እማዬ”
እናት፤
“ሳይሽ ወፈርፈር ብለሻል፤ እንዲያው ለመሆኑ ፀንሰሽ ይሆን እንዴ? አርግዘሽ ከሆነ የገንፎ እህልም፣ ሌላም አስፈላጊ ነገር እንዳዘጋጅልሽ ቀኑን ንገሪኝ፡፡ ለመሆኑ ያረገዝሽበትን ጊዜ ታውቂዋለሽ?”
ልጅ፤
“አይ እማዬ፤ ቀኑን እንዴት አውቀዋለሁ፡፡ እሱ በላይ በላዩ ይጨምርበታል!!”
*          *         *
በላይ በላዩ የምንጨምርበት ነገር በበረከተ ቁጥር ችግራችን ቅጥ - እያጣ፣ ህይወታችን ቅጥ - እያጣ፣ በመጨረሻም አገራችን ዕቅድ - አልባ ወደመሆን እያመራች ትሄዳለች፡፡ ቅጥ - አልባ መሆን ለሀገር ትልቅ አደጋ ነው፡፡ ታቀደ የተባለው ሁሉ ዕልባት ሳያገኝ በላይ በላዩ ዕቅድ ካወጣንበት ሩጫችን ፍሬ-አልባ ነው የሚሆነው። ኑሯችንን እናጣጥም፡፡ ኢኮኖሚአችንን እናጣጥም፡፡ ፖለቲካችንን እናጣጥም፡፡ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ያልነውን እናጣጥም፡፡ “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል” የሚለውን ተረት እናጣጥም፡፡ ማንኛውም አዲስ መንግስት በመጣ ቁጥር ያለፈውን ሥርዓት መኮነኑ የተለመደና ምናልባትም ግድ ሊሆን ይችላል፡፡ የተለመደነቱ አዲሱ አሮጌውን መጣሉ አይቀሬ (Invincible) ስለሆነ ነው ይባላል፡፡ ግድነቱ ግን ከአሮጌው የተሻለ ነገር ሰርቶ ማሳየት ስላለበት ነው፡፡ ኩነና (condemnation) ብቻውን አቅም አይሆነንም፡፡ የኩነናችንን ምክን ከህልውናችን ምክን (raison d’être) ጋር ማያያዝ አለብን እንጂ ባዶ ኩነና (Vacant condemnation እንዲሉ) ምንም አይፈይደንም፡፡ ሁለተኛው ችግራችን ፍረጃ ነው (branding) ለየችግሩ ሁሉ እነእገሌ ናቸው ተጠያቂ ማለት፡፡ እነ እገሌ ደግሞ ይህን የሚያደርጉት እንትን ስለሆኑ ነው ብሎ ቦቃ ማበጀት፡፡ ፈርጅ መፍጠር፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ከዋናው ችግር ስለሚያራርቀን መፍትሄውም የዚያኑ ያህል ይርቅብናል፡፡ ችግሮቻችን የሚደራረቡት በቅጥ በቅጥ እየፈታናቸው ስለማንሄድ ነው፡፡ የፖለቲካውን ለፖለቲካ፣ የኢኮኖሚውን ለኢኮኖሚው ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ “የቄሣርን ለቄሣር” እንዲል መጽሐፍ፡፡ ሁሉን ችግር ፖለቲካዊ ፍረጃና መፍትሄ እንስጠው ካልን አገርን የፖለቲከኞች እንጂ የአገሬው አናደርጋትም፡፡ ዜጎቿን የማታከብር አገር ደግሞ አገር አትሆንም፡፡ ደካማ ትምህርት ያላት አገር ዕውቀት እንጂ ፖለቲካ አያሻትም፡፡ ደካማ ጤና ያላት አገር የጤና ባለሙያ እንጂ ፖለቲከኛ አያስፈልጋትም፡፡ ደካማ ኬላ ያላት አገር ሀቀኛ ተቆጣጣሪ እንጂ ፖለቲከኛ የግድ አያሻትም፡፡ መልካም ልማት የራባት አገር የልማት ባለሙያ እንጂ ፖለቲከኛ ገምጋሚ ባለውለታ አይሆናትም፡፡
አሁንም “የየሱስን ለየሱስ፤ የቄሣርን ለቄሣር እንስጥ!” ፍትህ የሚሻን ነገር ሌላ ሰበብ አንፈልግለት፡፡ ፍትሕ እንስጠው፡፡ ለምሳሌ በየኬላው የሚካሄዱ ፍተሻዎች ሚዛናዊ አይደሉም ከተባሉ ፈታሾቹን ፈትሾ ፍትሕ መስጠት ነው፡፡ ምሬቶችን አለማጠራቀም ለአገር ሰላም ይበጃል፡፡ ትናንሽ ጅረቶች ተጠራቅመው ወንዝ እንደሚሆኑ አለመርሳት ወሳኝ ብልሃት ነው፡፡ የቢሮክራሲው ቀይ ጥብጣብ (አሻጥር/bureaucratic red-tape እንቅፋት እንደማለት) አሁንም አልተበጠሰም፡፡ እንዲያወም ተተብትቧል ቢባል ይሻላል፡፡ ይህንንም መታገል ከልማት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነትና ተቀጣጣይነት ያለው ነው! በቅርብ እናስብብት!
እስከዛሬ አገራችን ተሰርቶላታል የምንለውን ነገር፤ ካልተሰራላት ጋር አነፃፅረን፤ የበላችውን ከተራበችው ጋር አወዳድረን፤ ከግብርናዋ ኢንዱስትሪዋን፣ ከኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዋ ያልተሰራውን ቤትና ያልገባላትን መንገድ አጢነን፤ ገና የሚቀረንን ጉዞ ማየት እንጂ በላይ በላይዋ ውዳሴ ብናበዛባት የአገራዊውን አባባል “የበላችው ያቅራታል፤ በላይ በላዩ ያጎርሷታል” የሚለውን መዘንጋት ይሆንብናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!

ለቤት ፈላጊዎች በአክሰስ ሪል ስቴት ስር ያሉ መሬቶች ይከፋፈላሉ

   የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፤ ከቤት ገዥዎች 1.4 ቢ. ብር ከሰበሰቡ በኋላ የገቡትን ውል ሳይፈጽሙ ባልታወቀ ምክንያት ከአገር መሰወራቸው ይታወሳል፡፡ መንግስት የቤት ፈላጊዎችን ተደጋጋሚ ክስና ቅሬታ መነሻ በማድረግም አቶ ኤርሚያስ ከአንድ ዓመት በፊት ያቀረቡት ዕቅድ ተቀባይነት አግኝቶ ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ይታወቃል፡፡ ባቀረቡት እቅድና በተሰጣቸው ጊዜ አንድም ነገር አላከናወኑም በሚል ሰሞኑን በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየካሄደባቸው ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በኋላ የቤት ፈላጊው ዕጣፈንታ ምን ይሆናል? የገባበት ያልታወቀው የ1.4 ቢ. ብር ጉዳይስ? አቶ ኤርሚያስ የታሰሩት ያቀዱት ባለመሳካቱ ነው ወይስ በሌላ? በሚሉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ችግሩን ለመፍታት በመንግስት የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ ከአቶ ኑረዲን አህመድ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡  
አቶ ኤርሚያስን በዋናነት ለእስር የዳረጋቸው ጉዳይ ምንድነው? የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ አልቆ ነው ወይስ…?
የጊዜ ገደብ አልቆ አይደለም የታሰሩት፡፡ ሆኖም በንግግራቸው መሰረት አልፈፀሙም፡፡ ከውጭም ሆነው የላኩትና እዚህም መጥተው ያቀረቡት የስድስት ወር እቅድ ነበረ፡፡ ይህ እቅድ በስድስት ወራት ውስጥ ሶስት ነገሮችን መፈፀምና አክሲዮን ማህበሩን ስራ ማስጀመር ነው፡፡
እነዚህ ሶስት ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
የመጀመሪያው ቅድሚያ የተሰጣቸውን ሳይቶች ማስነሳት፣ ሁለተኛው እቅድ የብድርና የእዳ ጉዳይ ያለባቸውንና የሶስተኛ ወገኖችን ጉዳይ መጨረስ፣ ሶስተኛው ደግሞ ሶስተኛ ወገን ጋ የሚገኘውን ብር መሰብሰብ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ይሄ ተከናወነ የምንለው አንድም ነገር አላገኘንም፡፡ ይሄ ማለት አንዳቸውም ሳይቶች አልተነሱም፣ ምክንያቱም ሳይት ለማስነሳት ገንዘብ መገኘት አለበት፡፡ ገንዘብ አመጣለሁ ያሉት ደግሞ አብሬያቸው የምሰራው የውጭ ኮንትራክተር ኩባንያዎች አግኝቻለሁ ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳቸውም መጥተው እንሰራለን ያሉ ወይም በተግባር ስራ የጀመሩ ኩባንያዎች የሉም፡፡ ሌላው ከሶስተኛ ወገኖች ጋር ያሉ ጉዳዮችን በድርድር እጨርሳለሁ አንድም በድርድር ያለቀ ጉዳይ የለም፡፡ ሶስተኛው 300 ሚሊዮን ብር አሰባስባለሁ ብለው ነበር፡፡ እንኳን ይሄን ገንዘብ አንድም ብር ወደ አክሲዮን ማህበሩ አካውንት አልገባም፡፡ ይህ የስድስት ወር እቅድ መጋቢት 14 ቀን 2007 ዓ.ም ነው የቀረበው፡፡ አብይ ኮሚቴውም ያፀደቀው ያን ጊዜ ነው፡፡ እስከ መስከረም 30 ቀን 2008 መከናወን ነበረበት፤ ምንም የተጀመረ ነገር ግን የለም፡፡ እንደገና ጥቅምት 18 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት የተዋቀረው ኮሚቴ ሌላ አቅጣጫ ዘረጋ።
ምን አይነት አቅጣጫ?
ሌላው ወዲያ ወዲህ ይቅርና ቢያንስ ከአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር ተስማምታችሁና ተግባብታችሁ መስራት መቻላችሁን እንድናረጋግጥ፣ በተለምዶ ኒያላ ሞተርስ የተባለውን ሳይት ለማስጀመር ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሳችሁ አምጡልን አልናቸው፡፡ ሆኖም እስከ ህዳር አጋማሽና ከዚያ በኋላም ምንም እንቅስቃሴ አልጀመሩም፡፡ ይህን ሁሉ እድል ሰጥተን ታግሰንም የእኛ ሪፖርት፤ ካቀረቡት እቅድ ውስጥ አንዱንም እንዳልሰሩ ያረጋግጣል፡፡
እሺ አቶ ኤርሚያስ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ቤት ለማግኘት ጓጉቶ የሚጠብቀው ቤት ፈላጊ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል ይላሉ?
የአቶ ኤርሚያስ መታሰር የህግ አግባብ ጥያቄ ነው፡፡ መጀመሪያም ከውጭ ሲመጡ የህግ ከለላ ተሰጥቷቸው ሳይሆን ያሉት በርካታ ክሶች ባሉበት ተቋርጠው የመፍትሔው አካል እንዲሆኑ ነው እንጂ ከህግ ተጠያቂነት ነፃ ሆነው አይደለም፡፡ ይህንን ስምምነት ማሳየት ይቻላል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ስነስርዓት አንቀጽ መሰረት፣ የተመሰረቱባቸው ክሶች ባሉበት ተቋርጠው የመፍትሔው አካል ይሆናሉ ተብሎ ነው የመጡት፡፡ ነገር ግን እርሳቸው ባቀረቡት እቅድና በተሰጣቸው እድል መሰረት መፍትሔ ማምጣት ስላልቻሉ ቀደም ብለው የተቋረጡት ክሶች እንደገና ተንቀሳቀሱት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የህግ ጥያቄ እንጂ ከቤት ፈላጊዎቹና ከአክሲዮን ማህበሩ ጉዳይ ጋር የተገናኘ አይደለም፡፡
የህዝቡን ጥያቄ በተመለከተስ?
ቤት ፈላጊ ህዝቡን በተመለከተ አክሲዮን ማህበሩ 1.4 ቢሊዮን ብሩን ከበላና ያ የተበላው ብር መሬት ላይ ነው የዋለው ከተባለ የአክሲዮን ማህበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ ያ ብር በምንና እንዴት ያሉ ጉዳዮች ላይ እንደዋለ እንዲያሳይ ነው የሚደረገው፡፡ ቤት ፈላጊዎቹ በኮሚቴ ተደራጅተዋል፡፡ ቤት የሚሰሩ ሰዎች የሚደራጁበት አካሄድና የህግ አግባብ አለ፡፡ በዚያ መልኩ ህጋዊ ቁመና ፈጥረው፣ አክሰስ ያለው መሬት ወደ እነሱ የሚዞርበትን መንገድ እያመቻቸን ነው ያለነው፡፡ የተባለውን ብር በተመለከተ ከአክሲዮን ማህበሩ ጋር እየተደራደሩ በህግ እየተከታተሉ ይቆያሉ፡፡ የመሬት ጉዳይ ግን በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙና በህጋዊ መንገድም የአክሰስ ሪል ስቴት የሆኑ መሬቶች አሉ፡፡ እነሱን ካሰባሰብን በኋላ ለቤት ፈላጊዎቹ እናደላድላለን፡፡
ቤት ፈላጊዎቹ መሬት ቢያገኙም የመስሪያውን ገንዘብ ከማውጣት አይድኑም ማለት ነው?
1.4 ቢሊዮን ብሩን በህግ ሂደት የሚያገኙበት መንገድ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን መንግስት የቤት ፈላጊዎቹን ችግር ለማቃለል ቢያንስ መሬቱን እንዲያገኙ ያመቻችላቸዋል፤ ስለዚህ በራሳቸው ገንዘብ ይሰራሉ ማለት ነው፡፡