Administrator

Administrator

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፣
ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ የፍትህ ሚኒስትር ተደርገው ተሾሙ

የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።  
ላለፉት ስምንት ወራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው፣ ዶ/ር ጌዲዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሾሙት።
በተጨማሪም፣ ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ  በዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ  ምትክ የፍትህ ሚኒስትር  በመሆን ሲሾሙ፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የቱሪዝም ሚኒስትር ተደርገው  ተሾመዋል። ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት በፋና ብሮድካስቲንግና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነት መሥራታቸው ይታወቃል፡፡
ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል፡፡


“ከህወሓት እጅ  የወጣው ስልጣን ወደ ህወሓት መመለስ አለበት”

በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል  የሚመራው የህወሓት ቡድን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ፣ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ ከባለሃብቶች ጋር ባካሄደው ስብሰባ፣ እርሳቸው የሚመሩት ቡድን ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይም፣ ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና ባልተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያልተሳተፉትንና በቡድናቸው የተባረሩትን የድርጅቱን አመራሮች ወቅሷል፡፡
“ጉባዔ እንዳናካሂድ ብዙ ሙከራ ተደርጎብናል፡፡ ጉባዔ አለማካሄድ ድርጅቱን ማፍረስ ነው። ይሁንና ወደ ጉባዔ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰን እያለ፣ እነርሱ ግን ‘አንገባም’ ብለው አንገራገሩ። ‘ጉባዔው ከተካሄደ ጦርነት ይከተላል’ ተባለ። የጉባዔው ተሳታፊዎች ጉባዔው ወደሚካሄድበት ቦታ እንዳይመጡ ጥረት ተደርጓል።” ሲሉ ዶ/ር ደብረጽዮን ተናግረዋል፡፡
 በጉባዔው ላይ እርሳቸው የሚመሩት የህወሓት ቡድን ያለፉትን ስድስት ዓመታት ፖለቲካዊ ስራዎች መገምገሙን የጠቆሙት ዶ/ር ደብረጽዮን፤  “በዚህ ጉባዔ ተበትኖ የሚገኘውን ሕዝባችንን ወደ ቀድሞ ቀዬው እንዲመለስ፣ መሬታችን ተመልሶ በእኛ አስተዳደር ስር እንዲሆን፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና በኢኮኖሚ ግንኙነቶችና በሌሎች ተጀምረው በነበሩ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማካሄድ እንቅስቃሴው ዳግም እንዲጀመር ውሳኔዎችን አስተላልፈናል” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የህወሓት፣ የትግራይ ሃይሎች፣ የምሁራንና ተቃዋሚ ድርጅቶች በመቀናጀት እንደመሰረቱት በማስረዳት፣ “ለአስተዳደሩ የጊዜ ገደብ አስቀምጠንለት ነበር። ይሁንና በክልላችን ሰላም ልናሰፍን አልቻልንም። ሕዝባችን ወደ ቀዬው አልተመለሰም። ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ትግራይን መልሶ ወደ መገንባቱ ሊገቡ አልቻሉም። እነዚህ ተግባራት በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ይህ ሁሉ የተፈጠረው ጊዜያዊ አስተዳደሩ መምራት ባለመቻሉ ነው” ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡
“የትግራይ ክልል ብሔራዊ ጥቅም”  አደጋ እየተጋረጠበት መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ “የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች የትግራይ ሕዝብን ለመበተን በአካባቢያዊነት ላይ አትኩረው እየሰሩ ናቸው” በማለት አብጠልጥለዋቸዋል። “ሃላፊነት ስላለብን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲፈርስ አንሻም። መንግሥትን የመጥላት ፍላጎት የለንም። በውስጣችንም ሆነ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ያሉንን ጉዳዮች በውይይት ‘እንፍታ’ ነው ያልነው፡፡ ግለሰብ ግን ተቋም እንዲሆን አንፈቅድም። ከሁሉም ወገን ጋር በመግባባት አሰራሮች መከናወን እንዳለባቸው እናምናለን። ለዚህም እየሰራን ነው” ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው የሚመሩት የህወሓት ቡድን ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርግ ያስታወቁት ሊቀ መንበሩ፤ “ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንሰራለን” ብለዋል። ወደፊት እንደሚደረግ የተገለጸው ሰላማዊ ትግል፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቃት ባላቸው አመራሮች  ስር ሆኖ የተሰጡትን ቁልፍ ሃላፊነቶች በተገቢው መንገድ እስኪተገብር ድረስ” እንደሆነም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡   
በዶ/ር ደብረጽዮን  የሚመራው የህወሓት ቡድን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ከቀናት በፊት ከመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ “ከህወሓት እጅ  የወጣው ስልጣን ወደ ህወሓት መመለስ አለበት። ይህን ለማድረግም ሕዝባችንን እናስረዳለን፤ እናነሳሳለን። በየደረጃው ዙሩን እያከረርን እንሄዳለን። በሕዝባዊ አመፅ ስልጣኑን እንዲለቅ እናደርገዋለን” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።


Saturday, 19 October 2024 12:13

ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም!..

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አንድ ልብስ ሰፊ ይሄዳል፡፡ ከዚያም፤
“ይሄውልህ ይሄን ምን የመሰለ ሙሉ ሱፍ እንደተሰፋ ገዝቼ እጅጌው ረዘመብኝ፡፡ ስለዚህ ይሄንን እጅጌ ትንሽ እንድታሳጥርልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ይመስልሃል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ልብስ ሰፊውም፤  “የለም ይሄ ማሳጠር ላያስፈልገው ይችላል፡፡ ዝም ብለህ ክንድህን እዚህ እክርንህ  ጋ አጠፍ ማድረግ ነው፡፡ አየኸው እጅጌህ ወደ ውስጥ እንደገባ?..” ይለዋል፡፡
ሰውዬው የተባለውን ካደረገ በኋላ በመስታወት ሲያየው ኮሌታው ደሞ ወደ ማጅራቱ ተሰቅሏል፡፡
ስለዚህ፤  “ኮሌታዬ ደግሞ አላግባብ ወደ ማጅራቴ ወጣብኝ፤ ይሄው ግማሽ ጭንቅላቴን ሸፈነውኮ! ምን ይሻላል?..” ሲል ጠየቀው፡፡
ልብስ ሰፊውም፤ የሰውዬውን ጭንቅላት ወደ ኋላ ቀና እያደረገ፣ “..በቃ ጭንቅላትህን ወደ ኋላ እንዲህ ቀና አድርገህ ስትለጥጠው ልክ ይገባል..” ይለዋል፡፡
ሰውዬው፤ “..አሁን ደግሞ ግራ ትከሻዬ በሦስት ኢንች ያህል ከቀኝ ትከሻዬ ወደ ታች ወረደ..”
ልብስ ሰፊው፤ “..ችግር የለም፡፡ ከወገብህ በኩል ወደ ግራ ጠመም በል፡፡ ልክ ይገባል፡፡..”
ሰውዬው እንደተባለው ወደ ግራ ከወገቡ ተጣመመ፡፡
ልብስ ሰፊውም፤ “..አሁን ትክክል ሆነሃል፡፡ ሱፉም ልክክ ብሏል፡፡ ገንዘብህን ከፍለህ መሄድ ትችላለህ..” አለው፡፡ ገንዘቡን ከፍሎ ሲወጣ የሰውዬው ቅርጽ እጅግ አስገራሚ ሆነ፡፡ የግራ ክርኑ ተንጋዶ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ጭንቅላቱ ወደ ኋላ ተገትሯል፡፡ ወገቡ ወደ ግራ ጥምም ብሏል፡፡ ለመራመድ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ ግራና ቀኝ እግሩን እያጠላለፈ እየተወለጋገደ ነው፡፡
እንዲህ እየተወለጋገደ በመሄድ ላይ ሳለ ሁለት መንገደኞች ያዩታል፡፡
አንደኛው፤ “ያን ምስኪን ሽባ ሰውዬ ተመልከተው፡፡ አንጀቴን ነው የበላው፡፡ አያሳዝንም?”
ሁለተኛው፤  “ያሳዝናል፡፡ ግን በጣም የሚደነቀው ልብስ ሰፊው ነው፡፡ ይሄ ሱፍ ልብስ ለዚህ ውልግድግድና ጥምም ላለ ሰው እንዲስማማ አድርጎ ሙሉ ሱፍ እንዲለብስ ማድረግ ትልቅ ጭንቅላት ይጠይቃል፡፡ ያ ልብስ ሰፊ ሊቅ መሆን አለበት!!” አለ፡፡
***
ምሁራን ሆኑም አልሆኑም፣ ፖለቲከኞች ሆኑም አልሆኑም፣ ቀራጮች ሆኑም አልሆኑም ባለሙያዎች ሆኑም አልሆኑም፤ እጅጌ ለማስተካከል ሰውዬውን አጣመው መልቀቃቸው ደግ ነገር አይደለም፡፡ ስህተት ለማረም ሌላ የተጣመመ ስህተት መሥራት የለብንም፡፡ ክርኑን ለማዳን አንገቱን መገተር፣ አንገቱን ለማዳን ወገቡን ማጣመም፤ በመጨረሻም ሰውዬው እንዳይራመድ አርጎ ማሽመድመድ ከቶም አያሳድገንም፡፡ አንድ የአገራችን ፀሃፊ እንዳለው፤ “..የአበሻንግድ የሌላውን ሥራ ማሽመድመድ፡፡ የአበሻ መኪና አነዳድ
በሌላው መንገድ መገድገድ፡፡..” እንዳይሆን ነገረ-ሥራችን፤ ቀና እንሁን፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚከተን፡፡ ሌሎች ካላለቀሱ እኔ አልስቅም ዓይነት አስተሳሰብ ቢያንስ ሳዲዝም ነው - በሌሎች ሥቃይ መደሰት፡፡
ሁሉን ጥቅም በሀሰት ሰነድ፣ በአየር - ባየር ገፈፋ ካላገኘሁ የሚል ስግብግብ እንዳለ ሁሉ ንፁህ ነጋዴ መኖሩን በቅጡ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡  ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ሂሳቡን የሚሠራ ቢሮና ሠራተኛ እንዳለ ሁሉ፣ ያለማምታታትና ያለግል ኪስ የማይንቀሳቀስ መኖሩንም ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የመንግሥት ላይሆን እንደሚችል ሁሉ፤ የግልም የግል ላይሆን ይችላል፡፡ በአገራችን የቤት ልጅ መበደልና ..”እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ማረጋገጥ”.. የተለመደ ነገር ነው፡፡
 “እያንዳንዱ ትውልድ የዱላ ቅብብል የሚጫወትበት እያልን”  የአንድ ትውልድ ብቻ መጫወቻ እንዳናደርገው መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለገቢ ፍትሐዊነት እየተናገርን፣ ገቢውንም ፍትሁንም እንዳናጣ እናስብ፡፡ The Holy Roman Empire was neither Holy nor Roman nor an Empire እንደተባለው እንዳይሆን (የተቀደሰችው የሮማ ግዛተ - ነገሥት፤ ቅድስትም፣ ሮማዊም፣ ግዛተ - ነገሥትም አልነበረችም፤ እንደማለት ነው)
ታዋቂው ፀሀፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በአንደኛው ተውኔቱ ውስጥ “አንዲት የዱር አውሬ፣ ልጅ በመውለጃዋ ሰሞን ልጇን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን..” የሚለን ለዚህ ነው፡፡
መልካም እንቅልፍ ለመተኛት መልካም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከግፍ መራቅ ያሻል፡፡ ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ ሸር መራቅ ይገባል፡፡ በፈረንጅ አገር አንድ ሰው ለአገሩ አገር ውስጥ ገቢ እንዲህ የሚል ማስታወሻ ጽፎ ነበር :- “የከፈልኩትን ታክስ አጭበርብሬ የከፈልኩ ስለሆነ እንቅልፍ መተኛት አቃተኝ፡፡ ገቢዬን ዝቅ አድርጌ አስገምቼ ነው፡፡ ስለዚህ የ150 ዶላር ቼክ ልኬላችኋለሁ፡፡ ይህም ሆኖ እንቅልፍ እምቢ እሚለኝ ከሆነ ግን ቀሪውን እልክላችኋለሁ፡፡”
ቼኩን በእጁ ያስገባው፤ የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኛውም “..እኔም ቀሪዋን እስክትልክ እንቅልፍ የሚወስደኝ አይመስለኝም..” ብሎ ፃፈለት፡፡ እንቅልፍ ከሚያሳጣ ዘመን ይሰውረን! አንድ የኢትዮጵያ አጎት ደግሞ የእህታቸው ልጅ ይሄንንም ግዛ ይሄንንም ግዛ እያለ ሲያስቸግራቸው፤  “አዬ፤ ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም” አሉ ይባላል፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን፡፡

ከሞቱ በኋላ ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑ ዝነኞች!
• ማይክል ጃክሰን ዓምና 115 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል
እኛ አገር ሰውየው ወይም ሴትየዋ በህይወት እያሉ የቱንም ያህል ተወዳጅና ዝነኛ ቢሆኑም እንኳን፣ ከሞቱ በኋላ ሁሉም ነገራቸው የሚያከትም ይመስላል - ሃብታቸውም ዝናቸውም ስማቸውም፡፡ በተለይ አርቲስቶቻችን ታመው አልጋ ከያዙ የችግር ቁራኛ ይሆናሉ፡፡ ለህክምና የገንዘብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በማይድን በሽታ ተይዘው እስከ ወዲያኛው ካሸለቡ ደግሞ ቤተሰቦቻቸው ክፉኛ ይቸገራሉ፡፡ የአሁኖቹ ትንሽ ሳይሻሉ አይቀሩም፡፡ የድሮዎቹ ግን ለሙዚቃ ፍቅር ህይታቸውን ጭምር ነው የሰዉት ማለት ይቻላል፡፡ ይሄ እንግዲህ አንድም የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ያለማደጉ ያመጣው ውጤት ነው፡፡
ዛሬስ የሃገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪው እንዴት ነው? የቱ ኢንዱስትሪ? እንዳትሉኝ ብቻ፡፡
የሰለጠኑት አገራት ሁኔታ በዚህ ረገድ ከእኛ በእጅጉ ይለያል፡፡ የውጭዎቹ ዝነኛ አርቲስቶች እንኳንስ በህይወት ሳሉ፣ ሞተውም እንኳን ገቢያቸውና ሃብታቸው አይሞትም፤ እንዲያውም ከዓመት ዓመት እያደገ ነው የሚመጣው፡፡
ፎርብስ እንደሚያመለክተው፣ በአሜሪካ በርካታ በሚሊዮኖች የሚሰላ ዓመታዊ ገቢ የሚያገኙ ሟች ዝነኛ ሰዎች አሉ፡፡ “ከፍተኛ ተከፋይ የሆኑ ስምንቱ የሞቱ ታዋቂ ሰዎች”፣ እ.ኤ.አ በ2022 ዓ.ም፣ በድምሩ 412 ሚ.ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የፎርብስ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡
የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ የነበረው ማይክል ጃክሰን፣ በ2023 ዓ.ም ከየትኛውም “ሟች ታዋቂ ሰው” የላቀ ከፍተኛ ገቢ አግኝቷል - 115 ሚሊዮን ዶላር፡፡ ጃክሰን እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም በሎስአንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ በ50 ዓመት ዕድሜው ነው የሞተው፡፡
ኤልቪስ ፕሬስሊ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ነው - ከሞተ በኋላ፡፡ ኤልቪስ እ.ኤ.አ በ1977 ዓ.ም በ42 ዓመቱ በድንገተኛ የልብ ህመም ነው የሞተው፡፡ በ2022 ዓ.ም ታዲያ 100 ሚሊዮን ዶላር አግኝቷል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የቀድሞው የኪቦርድ ተጫዋች ሬይ ማንዛሬክ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም በ74 ዓመቱ በካንሰር በሽታ ነው የሞተው፡፡ ይሁን እንጂ ይሄ ሙዚቀኛ በ2022 ዓ.ም 45 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የፎርብስ መረጃ ይጠቁማል፡፡
በዚህ ዝርዝር ውስጥ የምትካተተው ሌላዋ ባለ ትልቅ ስም ደግሞ ድምጻዊቷ ዊትኒ ሂዩስተን ናት፡፡ ሂዩስተን እ.ኤ.አ በ2012 ዓ.ም፣ በ48 ዓመቷ፣ በሆቴል መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በድንገት ሰጥማ ነው የሞተችው፡፡ እርሷም በ2022 ዓ.ም 30 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች ተብሏል፡፡
እኔ የምለው እኒህ የአሜሪካ ዝነኛ አቀንቃኞችና ሙዚቀኞች፣ እስከ ወዲያኛው አሸልበው ይሄን ሁሉ ሚሊዮን ዶላሮች ካገኙ፣ በህይወት ቢኖሩ ስንት ሊያገኙ ነበር?
ለነገሩ በህይወት እያሉ የለፉበትና የደከሙበት ነው ከሞት በኋላም ጭምር የሚከፍላቸው፡፡ በአብዛኛው የገቢዎቻቸው ምንጭ የሙዚቃ አልበሞቻቸው ሽያጭ፣ በደህና ጊዜ የገዟቸው መኖሪያ ቤቶችና የመሬት ይዞታዎች እንደሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ማሟሻ" ቅጽ ሁለት መጽሐፍ አርብ ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ለንባብ ይበቃል።

ይህም መጽሐፍ  ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ሰዓት ጀምሮ በመቅረዝ ሥነኪን ዝግጅት ላይ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አግልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ይመረቃል።

•  ከከፍተኛው የአክሲዮን መጠን በላይ መግዛት አይቻልም

ኢትዮ ቴሌኮም ራሱን ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማሕበርነት እንደቀየረ አስታውቋል። ተቋሙ አስር በመቶ ድርሻውን ለመሸጥ በማለም፣ 30 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን በዛሬው ዕለት ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሽያጭ አቅርቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የአክሲዮን ሽያጩን ያስጀመረው ተቋሙ፣ ለሽያጭ ያቀረባቸው አክሲዮኖች እያንዳንዳቸው 300 ብር እንደሚያወጡ ተገልጿል። እንዲሁም አንድ ሰው መግዛት የሚችለው ዝቅተኛው መጠን 33 ወይም 9 ሺሕ 990 ብር የሚያወጡ አክሲዮኖችን ስለመሆኑ ተነግሯል።

ሆኖም ግን አንድ አክሲዮን ገዢ ከ9 ሺሕ 990 ብር በላይ አክሲዮን መግዛት እንደማይችል የተብራራ ሲሆን፣ ኢትዮ ቴሌኮም በእያንዳንዱ አክሲዮን ላይ ታክስና አስፈላጊ የአገልግሎት ክፍያ አክሎ እንደሚያስከፍልም የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ አስታውቀዋል።

የተገዙ መደበኛ አክሲዮኖችን የመሸጥ፣ የመተላለፍ እና ባለቤትነትን ወደሌላ ማስተላለፍ የሚቻለው “ኩባንያው በኢትዮጵያ ሰነደ መዋዕለ ንዋይ የመካተቱ ሂደት ሲጠናቀቅ” መሆኑን ያመለከተው ኢትዮ ቴሌኮም፣ የአክሲዮን ግዢ ጥያቄዎችን የመደልደል ሃላፊነት የራሱ መሆኑንም ጨምሮ ጠቅሷል።

ኢትዮ ቴሌኮም  በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ መሰረት ከሰኔ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ራሱን ከልማት ድርጅትነት ወደ አክሲዮን ማሕበርነት በመቀየር መመዝገቡን ነው ያስረዳው።

የአክሲዮኖቹ ሽያጭ በቴሌብር አማካይነት እንደሚከናወን ሲነገር፣ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ሽያጩ እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል።

• ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ፉክክር ፈጥረዋል

ዳሽን ባንክ ባለፈው ዓመት የ6 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ተገልጿል። ባንኩ ዛሬ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ ባካሄደው የባለአክሲዮኖች 31ኛ መደበኛ እና 26ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት በሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ ከፍተኛ ፉክክር መፍጠራቸው ተነግሯል።

የዳሸን ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባለፈው በጀት ዓመት የባንኩ ተቀማጭ የገንዘብ መጠን የ30 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፣ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 145 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አውስተዋል፡፡

እንዲሁም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ለባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ያበረከተው ድርሻ 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር “ነበር” ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ የዳሽን ባንክ ሃብት ባለፈው በጀት ዓመት የ27 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ፣ 183 ነጥብ 7 ቢሊዮን መድረሱን አመልክተዋል፣ አቶ ዱላ።

ባለፈው በጀት ዓመት 1 ነጥብ 44 ሚሊዮን አዳዲስ ደንበኞችን ማፍራት መቻሉን ያስታወቁት አቶ ዱላ፣ ባንኩ በአሁኑ ወቅት ከ6 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉትም ነው ያብራሩት። ይሁንና ባንኩ ዓወንታዊና አሉታዊ ሁኔታዎችን የፈጠሩ ዓለም አቀፋዊ እና አገራዊ ክስተቶች “ነበሩ” በማለት በንግግራቸው ላይ አትተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በ"ቴሌ ብር" በኩል፣ እንዲሁም ሳፋሪኮም በ"ኤምፔሳ" አማካይነት በሞባይል ባንኪንግ አገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ፉክክር እንዲፈጠር “ያደረጉበት ዓመት ነው” ብለዋል፣ አቶ ዱላ።

• የካቲት 1 የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ይካሄዳል

ለመቄዶንያ የአረጋውያን እና አዕምሮ ሕሙማን በጎአድራጎት ድርጅት መስራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ የክብር ጥቁር ቀበቶ (ብላክ ቤልት) ተበረከተላቸው። ይህ የክብር ጥቁር ቀበቶ የተበረከተላቸው ከሃይሌ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ እንደሆነ ነው የተሰማው።

ትናንት ጥቅምት 3 ቀን 2017 ዓ.ም. አያት በሚገኘው የመቄዶንያ ማዕከል ሃይሌ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ እና ጂም ለ2 ሺሕ ሰዎች የምሳ ግብዣ ያካሄደ ሲሆን፣ በዚሁ ግብዣ ላይ የተገኙት የክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ግብዣውን ላዘጋጁት ሰዎች በሙሉ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። አክለውም፣ “ማዕከሉን መጎብኘት በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በዚህ ማዕከል ያሉ አረጋውያን እና አዕምሮ ሕሙማን በሙሉ በፊት ኑሯቸው ጎዳና ላይ ነበሩ። በዚህም ምክንያት የሰውን ፍቅር ይፈልጋሉ። እየመጣችሁ ጎብኙን!” ሲሉ ተናግረዋል።

የክቡር ዶክተር ቢኒያም በስፖርት ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ባለሞያዎች በሞያቸው ለመቄዶንያ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በማዕከሉ ለሚኖሩ አረጋውያን እና የአዕምሮ ሕሙማን በተዘጋጀው በዚህ የምሳ ግብዣ፣ ከሃይሌ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ ለክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ የክብር ጥቁር ቀበቶ (ብላክ ቤልት) ተበርክቷል። ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ከቴኳንዶ ማሰልጠኛ ተቋሙ መስራች ማስተር ሃይለኢየሱስ ፍስሐ የተበረከተላቸውን የክብር ጥቁር ቀበቶ ከተረከቡ በኋላ፣ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰይፉ ፋንታሁን ይፋዊ የዩቲዩብ ቻናል በቀጥታ ስርጭት ለሚከናወነው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሁሉም ዜጋ ተሳታፊ ለመሆን ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ከምሳ ግብዣው በተጨማሪ፣ ሃይሌ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ እና ጂም በ2016 ዓ.ም. በበጋ እና በክረምት ዓመቱን ሙሉ ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ሰልጣኞችን አስመርቋል። በኢትዮጵያ የቴኳንዶ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርቃቱን በመቄዶንያ “አድርጓል” የተባለለት ይህ የቴኳንዶ ማሰልጠኛ ተቋም፣ ከምሳ ግብዣው ባሻገር ማሕበራዊ ሀላፊነቱን ለመወጣት በማቀድ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቋል።


በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፅሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ዋሲሁን፣ ግራንድ ኪም ማስተር በፈቃዱ ታደሰ እንዲሁም ሌሎች አሰልጣኞች እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።


ሃይሌ ቤስት ወርልድ ቴኳንዶ እና ጂም በ2002 ዓ.ም. በማስተር ሃይለኢየሱስ ፍስሐ የተቋቋመ ሲሆን፣ አሁን ላይ በአራት ቅርንጫፎች የቴኳንዶ ስልጠናዎችን እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ17ኛ ጊዜ ‘’ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ’’ በሚል መሪ ቃል ይከበራል፡፡
በዓሉ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የምክር ቤቱ አባላትና የጽ/ቤቱ ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግቢ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
በበዓሉ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት፣ በክልሎች እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ በመከላከያ ሠራዊት ካምፖች እንዲሁም በኢትዮጵያ ኢምባሲዎች እና ሚሲዮኖች በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር 4፡30 ላይ ሰንደቅ ዓላማ በመስቀል እና በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቃለ-መሃላ በመፈፀም በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡

Page 7 of 735