Administrator

Administrator

ባለፉት አስር አመታት የህጻናትን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች ምንም አይነት ውጤት አለማስገኘታቸውን የገለጸው ተመድ፤ በማደግ ላይ በሚገኙ የአለማችን ድሃ አገራት ከሚኖሩ ህጻናት መካከል 67 በመቶ ያህሉ ለጤናማ የአካልና አእምሮ እድገት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ እንደማያገኙ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት እንዳለው፣ በበርካታ የአለማችን ድሃ አገራት ከ6 ወር እስከ 23 ወር ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ በየዕለቱ ማግኘት የሚገባቸውን ዝቅተኛ የምግብ መጠን እያገኙ አይደለም፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች በ91 የአለማችን አገራት ህጻናት የተመጣጠነ በቂ ምግብ እንዳያገኙና ለመቀንጨር እንዲዳረጉ ሰበብ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንዲሁም  በቀላሉ ለበሽታ እየተጋለጡና ለመቀንጨር እየተዳረጉ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

 ባለፈው ቅዳሜ በየመን የሁቲ ታጣቂዎች፣ ፍርድ ቤት በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ እሳቸው በወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ የወንድማቸውን ፍሬድ ትራምፕን ሴት ልጅና ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣን የከሰሱት ተንኮል በተሞላበት ሴራ የግል የፋይናንስ መረጃዎቼን ያለ አግባብ በመጎልጎል የታክስ ማጭበርበር እንደፈጸምኩ የሚያስመስልና በሃሰት የሚወነጅል ዘገባ ሰርተው ለንባብ አብቅተዋል፤ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊክሱኝ ይገባል በሚል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕ ባለፈው አመት ባሳተመቺው የግል ማስታወሻ መጽሃፍ ላይ የትራምፕ ቤተሰብ በምን መልኩ ሃብት እንዳፈራ የሚያጋልጡ መረጃዎችን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ የቤተሰቡን የግል የፋይናንስ መረጃዎች ለጋዜጣው አሳልፋ ሰጥታለች ተብላ በትራምፕ መከሰሷንና ይህም ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች ሰፊ የምርመራ ዘገባ ዋነኛ መነሻ መሆኑን ሮይተርስ አብራርቷል፡፡
የጋዜጣው ሪፖርተሮች ወራትን በፈጀ ምርመራ ያገኙትን ግላዊ መረጃ በማቀነባበር በሰሩት ሰፊ ዘገባ፣ ትራምፕ በተጭበረበረ መንገድ ከአባታቸው ግዙፍ የሪልስቴት ኩባንያ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በታክስ ተመላሽ መልኩ ተቀብለዋል ሲሉ ማጋለጣቸውን የጠቆመው ሮይተርስ፣ ዘገባውን የሰሩት የጋዜጣው ሶስት ሪፖርተሮች በዚህ ስራቸው በ2019 የታዋቂው ፑልቲዘር ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸውንም አስታውሷል፡፡
ትራምፕ ከ100 ሚሊዮን ዶላሩ በተጨማሪ የወንድማቸው ልጅ ካሳተመቺው መጽሃፍ የሚገኘው ገቢ በሙሉ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤት ባቀረቡት 27 ገጽ ክስ መጠየቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በ2018 በተፈጸመው የአየር ጥቃት ከተገደሉት የየመን ሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት ሃላፊ ሳልህ አል ሳማድ ግድያ ጋር በተያያዘ በሑቲ ታጣቂዎች ፍርድ ቤት በተመሰረተባቸው ክስ ባለፈው ቅዳሜ ከሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር  በሌሉበት ሞት እንደተፈረደባቸው ያስነበበው ቢቢሲ ሲሆን፣ ከእነ ትራምፕ ጋር የተከሰሱ 9 ሰዎች በአደባባይ የሞት ቅጣቱ እንደተፈጸመባቸውና ይህም ውሳኔ ተመድና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በበርካታ አገራት መንግስታት ክፉኛ መተቸቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የኢንተርኔት ነጻነትን የሚጻረሩ የተለያዩ አፈናዎችና ገደቦች ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በአለማቀፍ ደረጃ ተባብሶ መቀጠሉንና በአመቱ በ41 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሳቢያ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ነጻነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ መንግስታት በመብት ጥሰቶች መግፋታቸውንና ጥናት ከተደረገባቸው 70 የአለማችን አገራት መካከል በ56ቱ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዜጎች መታሰራቸውንና መከሰሳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የኢንተርኔት መብቶች ጥሰት ዘንድሮም በአለማቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ተከታታይ አመት ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ተጠቃሚዎችን በተለያዩ መንገዶች የሚያፍኑና ለእስር የሚዳርጉ መንግስታት ቁጥር መበራከታቸውንና በአንጻሩ ደግሞ በኢንተርኔት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች መበራከታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ 20 የተለያዩ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጣቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ 20 ያህል መንግስታት ደግሞ የማህበራዊ ድረገጾችን መዝጋታቸውን አስታውሷል፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ የከፋ የኢንተርኔት አፈና የታየባት ቀዳሚዋ አገር ተብላ በሪፖርቱ የተጠቀሰችው ቻይና ስትሆን፣ የኢንተርኔት አፈና በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰባቸው ተብለው የተጠቀሱት ቀዳሚዎቹ ሶስት የአለማችን አገራት ደግሞ ማይንማር፣ ቤላሩስና ኡጋንዳ ናቸው፡፡


 የአለማችን 2ኛው ግዙፍ የሞባይል አምራች ኩባንያ የሆነው የአሜሪካው አፕል ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ለገበያ ያቀረባቸው የአይፎን ስማርት ስልኮች ቁጥር ከ2 ቢሊዮን ማለፉን አንድ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በመላው አለም ስማርት ስልኮችን ከሚጠቀሙ 3.8 ቢሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 26 በመቶ ያህሉ የአይፎን ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የዘገበው ዳብሊውሲሲኤፍቴክ የተባለ ድረገጽ፣ በአሜሪካ 60 በመቶ ያህል የስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች አይፎን እንደሚጠቀሙም አመልክቷል፡፡
አፕል በተለይ በቅርቡ ያወጣው አዲሱ ምርቱ አይፎን 13፤ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሽያጩ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡


 ሶስት ጊዜ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በፈረንሳይ በእስር ላይ የሚገኘውና ከአለማችን ጨካኝ ወንጀለኞች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ቬንዙዌላዊው የ71 አመት ገዳይ ካርሎስ ቀበሮው፣ ከሰሞኑ በፈረንሳይ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ የእስራት ዘመኑ እንዲቀነስለት መማጸኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካርሎስ ቀበሮው በሚል ስሙ የሚታወቀውና እ.ኤ.አ በ1974 በፓሪስ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በፈጸመው ጥቃት ከ4 አመታት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ኢሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ፣ ባለፈው ረቡዕ ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ እስሩ እንዲቀንስለት መማጸኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከአራት አመታት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት በተፈረደበት ችሎት ላይ ሲቀርብ የሙያ መስክህ ምንድን ነው በሚል ከችሎቱ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ብቁ አብዮተኛ ሲል ምላሽ መስጠቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ዕድሜውን ሲጠየቅም 17 ነው፤ ደስ ካላችሁ 50 አመት ጨምሩበት ሲል ማላገጡን አስነብቧል፡፡
ከ27 አመታት በፊት በፈረንሳይ ልዩ ሃይል ክትትል በካርቱም በቁጥጥር ስር የዋለው ቬንዙዋላዊው አደገኛ ገዳይ ካርሎስ፤ በ1970 ዎቹ እና 80 ዎቹ በፈጸማቸውና ባስፈጸማቸው በርካታ የግድያ ወንጀሎች ለሶስት ጊዜያት የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበትና ከዚያ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ በእስር ላይ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡


 የእውቁ አፍሪካዊ አርቲስት ኮፍፊ አሊይድ ኮንሰርት ትላንት በክለብ አዲስ ተካሄደ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኮፍፊ ኦሊድ በተሰኘ የመድረክ ስሙ የሚታወቀው ተወዳጁ አርቲስት አንቶን ክሪስቶፍ አጌፓ ሙምባ ኦሎሚዴ ትላንት በክለብ አዲስ ስራዎቹን አቅርቧል፡፡
በክለብ አዲስ አዘጃጅነት በተካሄደው በዚህ ኮንሰርት ላይ አንጋፋው አርቲስት ስራዎቹን በማቅረብ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በአንድ ላይ አገናኝቶ ያዝናና ሲሆን፣ ዘ ክለብ አዲስ “የ2021 የአፍሪካ ህብረት የሆነውን በስነ-ጥበብ፣ባህልና ቅርስ ሀብቶቻችንን በመጠቀም የምንፈልጋትን አፍሪካ መገንባት” የተሰኘውን መሪ ቃል ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የአፍሪካዊያን ውብ ሀብቶቻችንን የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ማቅረቡም አስታውቋል፡፡
አንጋፋው አፍሪካዊ አርቲስት ከፍፊ ሶኩስ ዘፋኝ፣ ዳንሰኛ፣ፕሮዲዩሰርና አቀናባሪ ሲሆን በስራው በርካታ ወርቃማ ሽልማቶችን ከማግኘቱም በላይ ከነአ ፊሊ ኡፑፓ እና ፌሪ ጎ ከመሳሰሉ ዝነኛ አፍሪካዊያን አርቲስቶች ጋር በመሆን ታዋቂውን “ሩብ ላቲን ኢንተርናሽናል” ኦርኬስትራን መስርቷል፡፡ ይህን አንጋፋና ተወዳጅ አርቲስት ነው ዘክለብ አዲስ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ በማስመጣት ኮንሰርት እንዲያቀርቡ ያደረገው፡፡
በኮንሰርቱ ላይ አፍሪካን ሙዚቃና ጥበብ አፍቃሪያ፣የተለያዩ ሀገራት ኤምባሲዎች ተወካዮች፣አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች የኮንጎ ማህበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች መታደማቸውም ታውቋል፡፡


በ2011 ዓ.ም ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ በመጀመሪያ ዲግሪ እውቅና ባገኘባቸው በአካውንቲንግ ኤንድ ፋይናንስ እንዲሁም በማኔጅመንት የትምህርት አይነቶች በርቀት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 8 ቀን 2014 ዓ.ም ቃሊቲ በሚገኘው ካፍደም ሲኒማ አዳራሽ አስመረቀ፡፡
ኮሌጁ በ2011 በአዲስ አበባ ካምፓስ በነቀምቴ ጎንድር ግልገል በለስ ሰልጣኞችን በመመዝገብ ሲያስተምር የቆየ ሲሆን ለምርቃት ብቁ የሆኑ 186 ተማሪዎቹን ማስመረቁን የኮሌጁ ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ አቲቃ ገልፀዋል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ  የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ሀላፊዎች፣ የኮሌጁ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞችና እንዲሁም ተመራቂዎችና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ስራውን እየሰራ ጎን ለጎን ያለውን የመማርና የራስን ማሻሻል ፍላጎት አጥንተው ይህን ፍላጎት ለመሙላት ኮሌጅን መክፈታቸውን የገለፁት አቶ ክፍሌ፤ ከኮሌጁም በተለያዩ የሀገሪቱ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የማስተማር ልምድ ባካበቱ ምሁራን መቋቋሙንና ዘንድሮ የመጀመሪያዎቹን ተመራቂዎች ማስመረቃቸውን አቶ ክፍሌ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም ኮሌጁ አቅሙን እያሳደገ፣ተጨማሪ የትምህርት አይነቶችንን እያስፋፋና ከስራው ጎን ለጎን መማር የሚፈልገውን የማህበረሰብ ክፍል በስፋት የማገልገል እቅድ እንዳለው የኮሌጁ ስራ አስኪያጅ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

 የሶስቱ  ወንድማማች ደራያን አራት መፅሐፍት ዛሬ በብሔራዊ ቴአትር ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ ይመረቃሉ፡፡ ደራሲያኑ ወንድማማቾች እንድሪያስ ይዘንጋው፣ ዳዊት ይዘንጋውና ወሰንሰገድ ይዘንጋው የሚባሉ ሲሆን ከአራቱ ሁለቱ ማለትም “ይሁዳ መዳፎች” እና “ዕድወት” የተሰኙ ልቦለድ መፅሀፎች የደራሲ እንድሪያስ ይዘንጋው፣ “የተረሳች” እና ሌሎች የደራሲ ዳዊት ይዘንጋው (ዳይተም) እንዲሁም “የፍሬሹ ሰበዞች” ደግሞ የደራሲ ወሰን ሰገድ ይዘንጋው ስራዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ወንድማማቾቹ ደራሲያን፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በብሔራዊ ቴአትር በሚያስመርቋቸው መፅሐፎች ሥነ- ሥርዓት ላይ አንጋፋ ደራሲያን የሚታደሙ ሲሆን የመፅሐፍቱ ዳሰሳ፣የግጥም ሥራዎች ሙዚቃና ሌሎች ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች ለታዳሚያኑ እንደሚቀርቡ ለማወቅ የተቻለ ሲሆን ወደ ምረቃ ሥነ ሥርዓቱ የሚመጡ ታዳሚያን የኮቪድ ፕሮቶኮል ታሳቢ እንዲያደርጉ ደራሲያኑ አሳስበዋል፡፡


  አራተኛው “አግሮ ፉድ እና ፕላስት ፕሪንት ፓክ”  ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት ከጥቅምት 4-6 ቀን 2014 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል። የንግድ ትርኢቱ ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ  የሚደረግ የመጀመሪያው አለም አቀፍ የንግድ ትርኢት እንደሆነም ተገልጿል።
የንግድ ትርኢቱ በታዋቂው የጀርመኑ “ትሬድ ፌር” እና በኢትዮጵያ የኤግዚቢሽን ዘርፍ ከሚታወቁት አንዱ በሆነው  “ፕራና ኢቨንትስ” የጋራ ትብብር የሚዘጋጅ ሲሆን አዘጋጆቹ ባለፈው ረቡዕ በስካይ ላይት ሆቴል  መግለጫ፣ የንግድ ትርኢቱ በተለይም በኮቪድ 19 ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረውን የንግድ ልውውጥና ግንኙነት የማነቃቃት ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የፕራና ኢቨንትስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነብዩ ለማ፣ የትሬድ ፌር መስራችና ማኔጅንግ ፓርትነር ማርቲን ማርዝ፣ በጀርመን ኤምባሲ የባህልና የኢኮኖሚክስ ዘርፍ ሃላፊና ተቀዳሚ ፀሀፊ የሆኑት ዶ/ር ካሌብ ሆልዝፉስና በቱርክ ኤምባሲ የንግድ አማካሪ የሆኑት  ሰዓት ኤርዶጉ፣ የጣሊያን ንግድ ኤጀንሲ (ITA) ዳሬክተር ሪካርዶ ዙኮኒ፣ በፈረንሳይ ኤምባሲ የንግድ አማካሪና የአገር ውስጥ ተጠሪ ማክሲም ባይለፍና ሌሎችም ተገኝተዋል።
የፕራና ኢቨንትስ የስራ ባልደረቦች፤ ባለፉት ወራት ይህ አለምአቀፍ የንግድ ትርኢት በተሳካ መልኩ እንዲከናወን በትጋትና በቁርጠኝነት ሲሰሩ ቆይተው ለዚህ ውጤት መብቃታቸውን የፕራና ኢቨንትስ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ለማ ገልጸው፤ ይህ ዓለማቀፍ የንግድ ትርኢት በኢትዮጵያ መካሄዱ ያለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ከኢኮኖሚ መነቃቃት፣ ከአገር ተጠቃሚነት፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትና ከስራ እድል ፈጠራ አንጻር አብራርተዋል።
ባለፉት ሶስት ዓመታት ፕራና ኢቨንትስ፣ ይህንኑ አግሮፉድና ፕላስት ፕሪንፕ ፓክ የንግድ ትርኢት፣ ፕራና ኢቨንትስ ከጀርመኑ አጋሩ “ትሬድ  ፉርመሴ” ጋር በተሳካ ሁኔታ ማካሄዱን የገለጹት አቶ ነቢዩ፤ የዘንድሮው ከቦታ ጥበት አንጻር የንግድ ትርኢቱ በቁጥር የሚለካ ሳይሆን በራሱ  መካሄዱ ብቻ በሚፈጥረው መነቃቃት ለሌሎቹ ዓለምአቀፍ የንገድ ትርኢቶች መካሄድ በር ከፋች ነው ብለዋል።
በንገድ ትርኢቱ ላይ ከ11 አገራት ማለትም ከፈረንሳይ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከጀርመን፣ ከህንድ፣ ከጣሊያን፣ ከኩዌት፣ ከናይጀሪያ፣ ከሩሲያ፣ ከደቡብ አፍርካ፣ ከቱርክና ከአሜሪካ የተውጣጡ ተሳታፊ ድርጅቶች ከመላው ኢትዮጵያና ከጎረቤት ሀገራት ከሚመጡ የንግድ ትርኢቱ ጎብኚዎች ጋር ለመነጋገር፣ ፕሮጀክት ለመቅረጽና በጋራ ለመስራት ዝግጁ ሆነው የንገድ ትርኢቱን መከፈት እንደሚጠብቁ በመግለጫው ተብራርቷል። በንግድ ትርኢቱ ላይ ለኢትዮጵያ ፍላጎት የተዘጋጁ የግብርና፣ የምግብና የመጠጥ ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብአቶች የፕላስቲክ፣ የህትመትና ማሸጊያ ቴክኖሎጂዎችና ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው የንግድ ትርኢት ከ2ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።
አራተኛው አግሮ ፉድ ፕላስት ፕሪንትፓክ አለም አቀፍ የንገድ ትርኢት፣ በኢትዮጵያ በኩል ከግብርና ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ ምግብ መጠጥና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣  የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብአቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢኒስትትዩት፣ ከዓለም አቀፍ ደግሞ ከጀርመን ግብርና ማህበረሰብ፣ ከጀርመን መንግስት ምግብና  ግብርና ሚኒስቴር፣ ከጀርመን ዓለምአቀፍ ትብብር ማዕከል እንዲሁም፣ ከጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያና ቱርክ ኤምባሲዎች፣ ከሌሎችም በተጨማሪም ከዓለምአቀፍ ተቋማት እውቅና ድጋፍ ተችሮት የሚዘጋጅ የንግድ ትርኢት እንደሆነ ከዘጋጆቹ ለመረዳት ተችሏል።

  በ6 ወር ውስጥ ግማሽ ቢ. ብር አሰባስቧል


              ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመውና ባፋይናንስ እጥረት ከህልማቸው ያልተገናኙ ኢትዮጵያውያንን ለማገዝ ያለመው የ”ራሚስ” ባንክ ለምስረታ የሚያበቃውን ሀብት አሰባስቦ ማጠናቀቁን አስታወቀ። ባንኩ፤ በቅርቡ ብሔራዊ ባንክ ያወጣውን አዲስ መመሪያ ግማሽ ቢ. ብር በ6 ወር የማጠናቀቅ ሂደት ያሟላ መሆኑን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢው አቶ አብዱል ጀዋድ መሃመድና የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኢብሳ መሃመድ ሀሙስ ረፋድ ላይ በኢሊሌ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ባንኩ ከሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሞ አክሲዮን መሸጥ ጀምሮ  የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ መቆየቱን ያስታወሱት የባንኩ ሃላፊዎች ያን ሁሉ ጫና በመቋቋም ለምስረታ ከሚያበቃው የገንዘብ መጠን በላይ መሰብሰቡንና እስካሁን የተከፈለው የገንዘብ መጠንም 724 ሚሊዮን 612 ሺህ ብር መድረሱን ጠቁመው አስታውቀዋል። በቀጣዩ ሳምንት ቅዳሜ በኢሊሌ ሆቴል የመስራች ጉበኤውን እንደሚያካሁድ ጨምረው ገልጸዋል። ባንኩ ከ6 ሺህ በላይ ባለ አክስዮኖች በመላው አገሪቱ እንዳሉት ያስታወሱት አቶ ኢብሳ መሃመድ ተናግረዋል።
ባንኩ ለሽያጭ ካቀረባቸው 2 ሚሊዮን አክስዮኖች መካከል አብዛኞቹ ቃል የተገባላቸው እንደሆኑ የገለጹት ሃላፊዎቹ፤ የምስረታ ጉባኤው ከተከናወነ በኋላ ባንኮችን የመክፈትና ወደ ስራ የመግባት ፈቃድ ከብሔራዊ ባንክ እንደሚጠይቁ አመልክተዋል።
ራሚስ ባንክ ከወለድ ነጻ የባንክ ተጠቃሚውን ማህበረሰብ ለማገዝና በፋናንስ እጥረት እየተጉላሉ ያሉትን  ወገኖች ለማገልገል የተመሰረተ ሲሆን በግብርና፣ ሀሳብን ፋይናንስ በማድረግና በተለያዩ ፍላጎት ባለባቸው የስራ ዘርፎች ብድር በማቅረብ እንደሚሰራ ሃላፊዎቹ ተናግረዋል።
“ከነባሮቹና አሁን እየተመሰረቱ ካሉት አዳዲስ ባንኮች ጋር ያለውን ውድድር በምን መል ለማሸነፍ ዝግጅት አድርጋችኋል?” በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ፤ ሲመልሱ “እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ ህብረተሰቡ ያለው የፋናንስ አቅርቦት አገልግሎት 30 በመቶ ብቻ እንደሆነና ገና 70 በመቶው ያልተሳካ በመሆኑ ውድድሩ ተግዳሮት አይሆንብንም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
“ራሚስ” የሚለው ቃል የአዋሽ ወንዝ ዋና ገባር የሆነ ታዋቂ የወንዝ ስም መሆኑን የገለጹት ሃላፊዎቹ ባንካችንም በዘርፉ ያለውን የፋይናስ ክፍተት በመሙላት፣ በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።


Page 9 of 556

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.