Administrator

Administrator

Monday, 27 September 2021 13:04

የማህጸን ፍሬ ካንሰር፡፡

    በአለም አቀፍ ደረጃ ያለው የካንሰር ሁኔታ እ.ኤ.አ በ2020 ሲገመት 19.3 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በአዲስ በካንሰር ሕመም ይያዛሉ፡፡ ወደ 10.0 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በሕመሙ ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት የካንሰር ምርምር እንዳረጋገጠው ደግሞ የማህጸን ካንሰር በአለም ላይ በሴቶች ላይ በ8ኛ ደረጃ የሚከሰት ሕመም ሲሆን ከሌሎች ካንሰር ሕመሞችም የ18ኛ ደረጃ የሚሰጠው አስከፊ ሕመም ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2018 በተደረገው ጥናት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በአለም ላይ በአመቱ ወደ 300‚000 የሚደርሱ በህመሙ በአዲስ የሚያዙ ሴቶች ለህክምና ቀርበዋል፡፡  
በአለም ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ህመሞች መኖራቸው ሲታወቅ መፍትሔ የሚገኝላቸው ቢሆንም የካንሰር ሕመም ግን በአብዛኛው ሕመሙ ሲከሰት ጀምሮ ምልክት ላያሳይ ስለሚችል ሰዎችን ለህልፈት ይዳርጋል፡፡ ከጅምሩ ምንም ምልክት ከማያሳዩት የካንሰር ሕመሞች መካከል የማህጸን ካንሰር አንዱ ነው፡፡ ዶ/ር ዳዊት ደሳለኝ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ማእከል መምህርና ረዳት ፕሮፌሰር በአንድ ወቅት የሰጡትን ማብራሪያ ከወቅታዊ መረጃዎች ጋር አዛምደን እናስነብባችሁ፡፡
በዚህ እትም የምናስነብባችሁ የማህጸን ፍሬ ካንሰር ስለሚባለው ሕመም ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በማህጸን ፍሬ ላይ የሚወጡ እጢዎች በግምት ከ30-50 ኪሎ ግራም የሚደርስ ክብደት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የማህጸን ፍሬው እጢ በቀዶ ሕክምና ከተወገደ በሁዋላ ሕክምናው በዚያ አያበቃም፡፡ የካንሰር ሴሉ ወደአካባቢው ተሰራጭቶአል ወይንስ አልተሰራጨም የሚለው የሚለየው በቀጣይ በሚደረጉ ሕክምናዎች ነው፡፡ አንዲት ሴት በማህጸን እጢ ላይ የካ ንሰር ሕመም ቢገጥማት መዳን ያለመዳንዋ የሚለየው ባላት እድሜና የካንሰር ሕመሙ ባለው ደረጃ መሰረት ነው፡፡ እንደሚታወቀው የካንሰር ሕመም አራት ደረጃ ያለው ሲሆን በአንደኛ ደረጃ ያለው ካንሰር ሕክምና ካገኘ ቶሎ የሚድን ሲሆን በሁለተኛነት ደረጃም ያለው እንዲሁ ጥብቅ ክትትልና ሕክምናን ይፈልጋል እንጂ በአስተማማኝ ሊድን ይችላል የሚል የባለሙያዎች ምስክርነት አለው። በሶስተኛነት ደረጃ የሚገኘው የካንሰር ሕክምና ጠበቅ ያለና ጊዜ የሚፈጅ ሕክምና የሚፈልግ ሲሆን ለመዳን አስተማማኝ ተስፋ የማሰጥበት ነው። በአራተኛ ደረጃ የሚገኘው እጅግ አስቸጋሪው የካንሰር ሕመም ደረጃ ነው እንደባለሙያዎቹ ትንታኔ፡፡
የማህጸን ፍሬ ማለት ልክ እንደወንድ ልጅ የዘር ፍሬ መያዣ እንደሚባለው ሲሆን የወንድ ልጅ አካል ወደ ውጭ ወጥቶ ይታያል፡፡ የሴት ልጅ ግን በሆድ እቃ ውስጥ ከማህጸን ጋር ተያይዞ የሚገኝ ነው፡፡ የማህጸን ፍሬው ወይንም እንቁላሉ በግራና በቀኝ በኩል የሚገኙ ሲሆን ይህ አካል የሴት ልጅን ሴት የሚያሰኝ ባህርይ የሚሰጥ ነው፡፡ የማህጸን ፍሬዎች ሴትን ሴት ለማ ለት የሚያስችሉ ባህርያትን የሚፈጥር ሲሆን እነሱም እንደ ጡት፤የሰውነት ቅርጽን የመሳ ሰሉን እና በመቀመጫ አካባቢ ያለውን ውፍረት የመሳሰሉት ከእንቁላሉ ስራ ጋር የሚያያዙ ባህርያት ናቸው፡፡ የማህጸን ፍሬ ከዚህም ባለፈ ሴቶች በየወሩ የወር አበባ እንዲኖራቸው እና ማህጸን በትክክል ተፈጥሮአዊ ሂደቱን እንዲያከናውን የሚያደርጉ አካላት ናቸው፡፡
የማህጸን ፍሬ ያለበትን ማእቀፍ ልክ እንደከረጢት ያለ ሲሆን እንቁላሎቹ በከረጢቱ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከከረጢቱ፤ ከእንቁላሎቹ እንዲሁም በመካከል ካለው ቱቦ የሚነሳ እጢ ወይንም ካንሰር ሊኖር ይችላል፡፡ በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ እጢዎች ሲከሰቱ ገና ከጅምራቸው ምልክት ላይ ሰጡ እና ሳይታወቅ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉዳት የሚያደርሰው ከእንቁ ላል ከረጢቱ ላይ የሚነሳው ነው፡፡ ይህ የእንቁላል ከረጢት ካንሰር ይበልጥ ገዳይ ነው፡፡ የማህጸን ፍሬ ወይም የእንቁላል ከረጢት ላይ የሚነሳው ካንሰር በባህርይው ወደሌላ የሰውነት ክፍል የማይዛመት ሲሆን በዚያው አካባቢ እያደገ ሆድን ሊያሳብጥ፤ሽንትና ሰገራን መከልከል የመሳሰሉትን ሕመሞች ያስከትላል፡፡ ይህ የካንሰር ሕመም ምንም እንኩዋን ገዳይና አስከፊ ነው ቢባልም በጊዜው ከታከመ ግን ሊድን የሚችል መሆኑ እሙን ነው። ከዚህም ውጭ የማህጸን ፍሬዎች በካንሰር የመታመም ሁኔታ አልፎ አልፎ አንዱ ቢጠቃ አንዱ ሊተርፍ ስለሚችል ወደሌላ ደረጃ ከመድረሱ በፊት ሕክምና ከተደረገለት ተፈጥሮአዊ ሂደቱን በአንዱ መቀጠል ይችላል፡፡ ለምሳሌም ሁለት ሁለት እየሆኑ እንደተፈጠሩት እንደ እጅ ፤እግር ፤አይን እና ኩላሊት እነዚህም ፍሬዎች ሁለት ስለሆኑ አንዱ ቢጎዳ በአንደኛው መኖር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ጉዳቱ ኃያል ሆኖ ለሞት እንዳያደርስ አስቀድሞ ምርመራ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
አንዲት ሴት የማህጸን ፍሬ ካንሰር እንደሚይዛት አስቀድማ የምታውቅበት ምንም ምልክት ላታይ ትችላለች፡፡ የካንሰር ሕመሙ ሲጀምር ለጥርጣሬ የሚበቃ የህመም ስሜት ስለሌለው ብዙዎች የሚያውቁት ሕመሙ ከጠና በሁዋላ ነው፡፡ በገዳይነቱ ከፍ ያለ ደረጃ የሚሰጠውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የማህጸን የካንሰር ሕመም ለመከላከል ወይም አስቀድሞ ጥንቃቄ ለማ ድረግ አስቸጋሪ በመሆኑም የሚመከረው ቅድመ ምርመራ ማድረግ ነው፡፡ የማህጸን ፍሬ ካንሰር ሕክምና እንደታማሚዎቹ እድሜና የካንሰር አይነት ይወሰናል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው በእድ ሜያቸው እስከሀያ አመትና በዚያ አካባቢ ያሉት ሴቶች የሚያዙት ከእንቁላሉ በሚነሳው ካንሰር ነው፡፡  
የማህጸን ፍሬ ካንሰር ልጅ በመውለድ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶችን  ጭምር የሚይዝ በመሆኑ ህክምናው ከተደረገ በሁዋላ ልጅ የመውለድ እድሉ ሊኖርም ላይኖርም እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሕመሙ የተከሰተው በአንደኛው የማህጸን ፍሬ ላይ ከሆነ እና አንዱ ግን ከህመሙ ንጹህ ከሆነ የታመመው አካል በቀዶ ህክምና ተወግዶ በጤነኛው ፍሬ አማካኝነት ልጅ መው ለድ ይቻላል፡፡ ሁለቱም የማህጸን ፍሬዎች ከታመሙ እና በኦፕራሲዮን የሚወገዱ ከሆነ ግን ልጅ መውለድ አይታሰብም፡፡ የህክምናው ዘርፍ ምንጊዜም በቅድሚያ የሚያስበው ሴትየዋን ማዳን እንጂ ልጅ ስለመውለድ አይደለም፡፡ በእድሜአቸው ልጅ ከመውለድ የዘለሉ ሴቶች ግን ሁለ ቱም ይሁን አንዱ የዘር ፍሬአቸው በካንሰር ቢታመም ስለ ልጅ መውለድ መጨነቅ ሳይኖ ርባቸው በቀጥታ እንደህመሙ ሁኔታ ሕክምናውን ያገኛሉ፡፡ አንዲት ሴት እድሜዋ በወጣ ትነት ክልል ውስጥ እያለ በዚህ የካንሰር ሕመም ብትታመም እና ሁለቱም የዘር ፍሬዎቿ ወይንም ማህጸ ንዋ በቀዶ ህክምና እንዲወገድ የሚያሰገድድ ሁኔታ ቢያጋጥም ይህች ሴት በወ ደፊት ሕይወትዋ በሴትነትዋ ልታገኘው የሚገባትን ብዙ ነገሮች ሊያሳጣት ስለሚችል ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት ለዚህ ሕመም ሳትዳረግ በተወሰነ የጊዜ እርቀት ወደ ሐኪም እየቀረበች ስለመራቢያ አካላት የካንሰር ሕመም ሁኔታዋ ከሕክምና ባለሙያ ጋር መመካከር ይጠቅማታል፡፡ ሕክምናው ከተጀመረ በሁዋላም ብዙዎች በራሳቸው ውሳኔ ስለዳንኩኝ ሕክም ናው ይበቃኛል በማለት የህክምና ክትትላቸውን ማቋረጥና መድሀኒታቸውንም በትክክል ከመ ውሰድ የሚታቀቡበት ሁኔታ ስላለ ባልታሰበ ሁኔታ የካንሰር ሴሉ ለመሞት ከሚያበቃቸው ደረጃ ሊያደርሳቸው ይችላል፡፡
አንዲት ሴት በካንሰር ሕመሙ ትያዝ አትያዝ ለማወቅ አይቻልም ቢባልም ህመሙ ደረጃው ከፍ ሲል ግን አንዳንድ ስሜት መኖሩ አይቀርም። ሕመሙ የሚሰማቸው ግን የካንሰር ደረጃው ከፍ እያለ ሲሄድ ነው፡፡ የካንሰር ሕመም ከአንድ እስከ አራት ደረጃ ያለው ሲሆን ህመሙ መሰማት የሚጀመረው ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ ነው፡፡ የካንሰር ሕመሙ ደረጃውን ሲጨ ምር ሕክምናውንም ውስብስብ ሊያረገው ይችላል። የካንሰር ሕመሙ በአንደኛ ደረጃ ሲሆን ለህ ክምና ቢቀርቡ እስከ 80% የሚሆኑት ታካሚዎች ሙሉ በሙሉ ማዳን ይቻላል፡፡ የካንሰር ሕመሙ መኖሩ የሚሰማው ከእንቁላሉ ከረጢት ወጥቶ የማህጸን አካባቢን ነካክቶ ወደ ሆድ እቃ ውስጥ ሲገባ እና የተለያዩ ሕመሞችን ማሰማት ሲጀምር ነው። ለምሳሌም ምግብን ሲመገቡ ቶሎ መጥገብ፤ የምግብ አለመስማማት፤ የጨጉዋራ ሕመም፤ ቶሎ መጥገብ የመሳሰሉት እና ሰገራና ሽንት ላይ ችግር ማስከተል ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት በሆድዋ አካባቢ ሕመም ሲሰ ማት ለህክምና መሄድ ያለባት ወደ ውስጥ ደዌ ሕክምና ብቻ ሳይሆን ወደ ማህጸን ህክምናም ጭምር መሆን አለበት፡፡
ከማህጸን ፍሬ የሚነሳው ካንሰር ብዙ ጊዜ የሚያጠቃው ልጅ ያልወለዱ ሴቶችን ነው፡፡ ጡት ያላጠቡ እና የእርግዝና መከላከያ መድሀኒትን ያልወሰዱም ችግሩ ሊገጥማቸው እንደሚችል ይገ መታል፡፡ የእርግዝና መከላከያ እርግዝናን ከመከላከል ባሻገር የማህጸን ፍሬ ካንሰርንም ሊከላከል እንደሚችል የተረጋገጠ ነው፡፡ በቤተሰብ ደረጃም የማህጸን ካንሰር ሕመም ከነበረ በካንሰሩ የመ ያዝ እድል ይኖ ራል፡፡ ልጅ መውለድ በካንሰሩ ላለመያዝ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ነው ሲባል ግን በእቅድና በፕላን መሆን እን ዳለበት ሳይዘነጋ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡  ፖርቹጋላዊው የአለማችን የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በፎርብስ መጽሄት የአመቱ የአለማችን ባለ ከፍተኛ ገቢ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ የ1ኛ ደረጃን መያዙንና የዝውውር ክፍያን ሳይጨምር የተጫዋቹ አጠቃላይ ገቢ ከታክስ በፊት 125 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ተዘግቧል፡፡
ከሰሞኑ ከጁቬንቱስ ወደ ማንችስተር ያቀናው የ36 አመቱ ሮናልዶ፤ ለዝውውሩ በቦነስ መልክ የተከፈለውንና ደመወዙን ጨምሮ በአመቱ 70 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የዘገበው ፎርብስ መጽሄት፣ የተቀረው ገቢ ደግሞ ናይኪን ከመሳሰሉ ታላላቅ የንግድ ኩባንያዎቹ ጋር ባለው የማስታወቂያና የንግድ ስምምነቶች የሚያገኘው መሆኑንም አስታውሷል፡፡
የሁልጊዜ ተቀናቃኙና አምና በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው የ34 አመቱ አርጀንቲናዊ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ፣ ዘንድሮ በ110 ሚሊዮን አጠቃላይ ገቢ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቱንም መጽሄቱ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
የ29 አመቱ ብራዚላዊ ኔይማር በ95 ሚሊዮን ዶላር፣ የ22 አመቱ ኪሊያን ማፔ በ43 ሚሊዮን ዶላር፣ የሊቨርፑሉ ሞሃመድ ሳላ በ41 ሚሊዮን ዶላር እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ፎርብስ መጽሄት ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
የ2021 የፈረንጆች አመት 10 ባለ ከፍተኛ ገቢ የአለማችን የእግር ኳስ ተጫዋቾች እስከ አመቱ መጨረሻ በድምሩ ከታክስ በፊት 585 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ፎርብስ፤ በተጨዋቾች ገቢ ስሌት ውስጥ የዝውውር ክፍያ አለመካተቱንም አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ተጫዋቹ ባለፈው ረቡዕ ፖርቹጋል ከአየርላንድ ጋር ባደረገችው ጨዋታ ባስቆጠራቸው 2 ጎሎች በአለማቀፍ ጨዋታዎች ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን ያስቆጠራቸውን አጠቃላይ ጎሎች 111 በማድረስ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡ ተነግሯል፡፡
የአምስት ጊዜ የባሎንዶር የወርቅ ኳስ ተሸላሚውና በሻምፒዮንስ ሊግ የምንጊዜም ጎል አስቆጣሪ የሆነው የማንችስተር ዩናይትዱ አጥቂ ሮናልዶ በዕለቱ የሰበረው ክብረ ወሰን ከሌሎች ስኬቶች ሁሉ ልዩ ትርጉም የሚሰጠውና በእጅጉ ያስደሰተው እንደሆነ በኢንስታግራም ባሰራጨው መልዕክት ማስታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በአለማቀፍ ጨዋታዎች 109 ጎሎችን በማስቆጠር ክብረ ወሰኑን ይዞት የቆየው ኢራናዊው ተጫዋች አሊ ዳይ እንደነበርም የአልጀዚራ ዘገባ አስታውሷል፡፡


Tuesday, 28 September 2021 00:00

የእመጫት እናቶች ተስፋ

     የገንዘብ አቅም የሌላቸውና ተሯሩጠው ሰርተው ማደር የሚፈልጉ እመጫት እናቶች፣ ልጆቻቸውን ተቀብሎ በመንከባከብና መሰረታዊ ትምህርቶችን እንዲያገኙ በማድረግ የሚያቆይና ከክፍያ ነጻ የህጻናት ማቆያ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት መኖሩን ሰማንና ወደ ስፍራው አቀናን። ድርጅቱ ካሌብ ፋውንዴሽን ይባላል። ኮተቤ መሳለሚያ አካባቢ የሚገኘው ይኸው ድርጅት፤ ገና በጨቅላ ዕድሜያቸው ከእናቶቻቸው ጋር በየገበያ ስፍራውና በየመንደሩ ለህጻናት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የሚቆዩ ህጻናትን እየተቀበለ የምግብ የመጠጥና የንጽህና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በሞግዚቶች እየተንከባከበ ያቆያቸዋል። ህጻናቱ በማዕከሉ ውስጥ ከምግብና መጠጥ በተጨማሪ፣ ነጻ ህክምናና መሰረታዊ ትምህርቶችን እንዲያገኙ ያደርጋል። ለዚሁ በተመደቡ መምህራን ለየዕድሜያቸው የሚመጥን ትምህርት እንዲያገኙ ያደርጋል። የሕጻናቶቹ እናቶች ስራቸውን ሰርተው  ውለው እስከሚመለሱ ድረስ በማቆየት፣ ልጆቹን ለወላጆቻቸው ያስረክባል። በዚህ ሁኔታ ድርጅቱ በቀን ከ30 በላይ ህጻናትን እየተቀበለ አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ይገኛል።
በስፍራው ያገኘናቸው ወላጆች እንደነገሩኝን፤ ልጆቻቸውን ይዘው ስራ ለመስራት እጅግ ይቸገሩ  ነበር። አብዛኛዎቹ ሴቶች የሚሰሩት እንደ ልብስ አጠባና እንጀራ ጋገራ አይነት ስራዎች በመሆኑና እነዚህ ስራዎችም ልጅ ይዞ መስራት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ ሲቸገሩ መቆየታቸውን ይናገራሉ። ማእከሉ ከተከፈተ በኋላ ግን ልጆቻቸውን በማእከሉ ውስጥ እንዲቆዩላቸው ሰጥተው ያለ ሃሳብ ስራቸውን ሲሰሩ እንደሚውሉ ነግረዋል። ማዕከሉ ለዚህ አገልግሎቱ ምንም አይት ክፍያ የማይጠይቅ መሆኑንም እነዚሁ እናቶች ተናግረዋል።
በማቆያው ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ሲታመሙ የሚያክሟቸው በጎ ፈቃደኛ ሃኪሞች አሏቸው። የህጻና በሽታ ጠንከር ያለ ከሆነ ወደተለያዩ የግልና የመንግስት የህክምና ተቋማት ሄደው  የሚታከሙበት ሁኔታ ይመቻቻል።
ዓለማችን ለህጻናት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚቆዩና ለተለያዩ የጤና ችግሮች የሚዳረጉ ሕጻናትን መታደግ ነው የሚሉት የካሌብ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተወካዩ አቶ ዮሐንስ ግርማ፤ መስራት እየቻሉና እየፈለጉ በህጻናት ልጆቻቸው ሳቢያ ከስራ የታቀቡ እናቶችም ሰርተው ራሳቸውን ለመለወጥ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው ብለዋል።
ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት 450 ችግረኛ እናቶች ልጆችን ተቀብሎ በመንከባከብ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረግ ላይ ይገኛል። አቅማቸው እጅግ ደካማ የሆኑና የመስራት ፍላጎት ያላቸውን እናቶች ደግሞ ለተለያዩ የስራ ዘርፎች መነሻ የሚሆን የብድር ገንዘብ  በመስጠት ሥራ እንዲጀምሩ ያግዛቸዋል።
ማዕከሉ በየዕለቱ ከእናቶቻቸው የሚረከባቸውን ከ30 በላይ ህጻናት በእንክብካቤ በማቆየት እናቶቻቸው ያለ አንዳች ሃሳብና ጭንቀት ስራቸውን ተረጋግተው ሰርተው እንዲውሉ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ፍላጎታችን አገልግሎቱን ለማስፈትና ለበርካታ እናቶች እንዲደርስ ለማድረግ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ነገር ግን ሰርተው መለወጥ የሚፈልጉ እናቶችን ማገዝ ቢሆንም የቦታ ጥበት ማነቆ ሆኖብናል የሚሉት አቶ ዮሐንስ፤ ከግለሰብ ተከራይተው በያዙት አነስተኛ ግቢ ውስጥ አገልግሎቱ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ይህንን የአቅመ ደካማ እናቶችን ያሳረፈ ነፃ አገልግሎት በስፋት ተደራሽ በሚሆንበት ስፍራ ለመስጠት የሚያስችለንን ሁኔታ ቢያመቻችልን የበለጠ ለመስራት እንፈልጋለን ብለዋል።
የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት የህጻናት ባለሙያ የሆኑት ወ/ሪት ቃልኪዳን ተስፋዬ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የገንዘብ አቅም የሌላቸው እናቶች ስራ ለመስራት ቢፈልጉም ልጆቻቸውን ማቆየት የሚችሉበት ቦታ ስለማይኖራችሁ ከፍተኛ ችግር ያጋጥማቸዋል። ይህ ሁኔታ በዚህ ማዕከል ተቀርፎ እናቶች ልጆቻቸውን በማዕከሉ አስቀምጠው ያለ ሃሳብ ስራቸውን ሲሰሩ ውለው ይመለሳሉ። ህፃናቶቹም ለጤናቸው አደገኛ በሆኑ  ቦታዎች ከመዋል ይልቅ እንክብካቤ ማግኘት በሚችሉበት ስፍራ ትምህርታቸውን እየተማሩ እንዲቆዩ መደረጉ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ ህጸናቱ በቀላሉ በበሽታ እንዳይያዙና ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። ካሌብ ፋውንዴሽን ባለፉት 6 ዓመታት በህጻናትና ሴቶች ላይ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው።


  ጉዳዩ፡- ኪራይ ቤቶችን ይመለከታል

              ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ኢትዮጵያን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ ባሳዩን መጠነ ሰፊ ትዕግስትና አርቆ አስተዋይነት ያለኝን አድናቆት መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ በ2013 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት በነበሩት ሁለት አመታት በመላ ኢትዮጵያ ሞት፣ መፈናቀልና ውድመት በቀጠለበት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብ የአለም አቀፉ ህብረተሰብ የፖለቲካ ትኩሳት በሆነበት፣ ስድስተኛው ሀገራዊ መርጫ እንዲደናቀፍ የሻገቱ ፖለቲከኞች የሸረቡትን ሴራ ማክሸፍ፣ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የአራዊቶች ስብስብ የሆነው ሕወኃት ከቻለ  አራት ኪሎ ለመግባት ካልቻለ ኢትዮጵያን ለመበተን በከፈተው ጦርነት፣ በወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋና ያወደመው ንብረት፣ በገቡበት ሁሉ ሽንፈትና ውርደት እየተከናነቡ የሚወጡት አሜሪካኖችና አጋሮቻቸው ያደረሱብንን ጫና ተቋቁመው፣ ለድል መቃረብዎ የአድናቆቴ መነሻ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የዚያኑ ያህል ባይሆንም ስህተቶችን እየሰሩ እንደሆነ ስገልፅልዎ ከፍ ባለ ትህትና መሆኑን እወቁልኝ፡፡ ለምሳሌ ወያኔን በአሽከርነት ሲያገለግሉ የነበሩና ዜጎችን ከማሳሰርና ከማስገረፍ ጀምሮ በመዝረፍና በማዘረፍ የምናውቃቸውን ግለሰቦች በአማካሪነት፣ በቦርድ ሰብሳቢነትና በአምባሳደርነት መድበው ሲያሰሩ በማየታችን አዝነናል፡፡
በመሰረቱ አንድ ካድሬ ሁለት ጊዜ ሚኒስትር፣ እንድ ጊዜ አፈጉባኤ፣ አምስት ጊዜ አምባሳደር ሆኖ በሚሾምበት ጊዜ በየሙያው (Field of Study) የሰለጠኑ ምሁራን በአገራቸውን ጉዳይ ከመሳተፍ ይልቅ ገለልተኛ አቋም እንዲወስዱ ይገደዳሉ። በነገራችን ላይ ምሁራን ስንል ለወፍራም እንጀራ ደፋ ቀና የሚለውን አድር ባይና አስመሳይ ማለታችን አይደለም፡፡ ባጭሩ በሕይወት ካሉትና ከሌሉት እንደነ ሎሬንሶ ትዕዛዝ (ዶ/ር)፣ አክሊሉ ሀብተወልድ (ፀሀፊ ትዕዛዝ)፣  ተስፋዬ ዲንቃ (አቶ)፣ ጎሹ ወልዴ (ኮሎኔል)፣ ሀይሉ ይመኑ (አቶ)፣ ሀይሉ ሻወል (እንጅነር)፣ መርስኤ እጅጉ (አቶ)፣ ሚካኤል እምሩ (ልጅ)  እና የመሳሰሉት ልሂቃን  (intellect) ከነበራቸው መልካም ተሞክሮ ልምድ የተጋሩ አይመስለንም፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፡- ከላይ የጠቀስኳቸው ምስጋናዎችና ነቀፌታዎች እንዳሉ ሆነው፣ ለዛሬው በዋናነት የማነሳልዎ በቀድሞ ስሙ ኪራይ ቤቶች ስለሚባለው ተቋም  ይሆናል፡፡ ይህ ተቋም በደርግ መንግስት ከተቋቋመ አርባ አምስት አመት ያስቆጠረ ሲሆን አላማና ግቡም በአቅም ውስነት የመኖሪያ ቤት የሌላቸው ወገኖች ዝቅተኛ ኪራይ እየከፈሉ እንዲኖሩ ለማስቻል ነበር፡፡
ዛሬ ግን ተቋሙ ከሚያስተዳድራቸው 18,000  ስምንት ሺህ) ቤቶች  ሶስት አራተኛው ወይም 13,500 (አስራ ሶስት ሺህ አምስት መቶ) ከሚሆኑት ውስጥ 702 (ሰባት መቶ ሁለት) ቤቶች በቁልፍ ሰበራና በቁልፍ ግዢ የተያዙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ 12,798 (አስራ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ዘጠና ስምንት) ቤቶች በእከክኝና ልክክልህ ቲያትር ውስጥ በተወኑ ቤት ፈላጊዎችና በኪቤአድ የስራ ሀላፊዎች መካከል በተደረገ ድርድር የተከራዩ ናቸው፡፡
በተለይ ከ702 (ሰባት መቶ ሁለት) ተከራዮች ውስጥ ቁልፍ ሰባሪዎቹ በወንጀል መጠየቅ ሲገባቸው ውል እንዲዋዋሉ መደረጉ ኪራይ ቤቶች የቱን ያህል የነቀዘ ተቋም መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ ቀሪዎቹ አንድ አራተኛ ወይም 4,500 (አራት ሺህ አምስት መቶ) ቤቶች ከአስር አመት በላይ በወሰደ ደጅ ጥናት በህጋዊ መንገድ የተሰጡ ናቸው፡፡ ተቋሙ ከኋላ ታሪኩ ጀምሮ በሙስና የተጨማለቁ አመራሮች እየተፈራረቁ የድርሻቸውን የወሰዱበት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ተከስተ እና ተስፋሁን የተባሉትን ሙሰኞች፣ የፖሊስ መኮንን የነበረና በሙያው ዶ/ር የሆነ ሰው ቢሮአቸው ውስጥ ከገደላቸው በኋላ  እጁን ሰጥቷል፡፡
ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ የተደናገጡት የስራ ሀላፊዎች፣ ሽር ጉድ እያሉ ደንበኞችን ማስተናገድ ጀምረው የነበረ ቢሆንም፣ ወደነበሩበት ለመመለስ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ አሁንም ቢሆን በአከራይና ተከራይ መካከል ያለው ግንኙነት ግልፅነትንና ተጠያቂነትን መሠረት ያደረገ ባለመሆኑ አመራሮቹ የመንግስትን ቤት እንደፈለጉ ቆምረውበት፡፡
ኬቤአድ በአርባ አምስት አመት እድሜው አንድም ጊዜ  ከተከራዮች ጋር የሚያገናኘው መድረክ ባለመፍጠሩ እራሱን መፈተሽ ሳይችል ቀርቷል፡፡ ምንም እንኳ ሚኒስትሮች በሚገኙበት ቦርድ የሚመራ ተቋም ቢሆንም ቦርዱ በተሰበሰበ ቁጥር ቃለጉባኤዎችን ተፈራርሞ ይበተናል እንጂ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ አላመጣም፡፡ ለምሳሌ ቤት እንዴት እንደሚሰጥና እንደሚከለከል ግልፅ የሆነ መመሪያ የለውም፡፡ በዚህ ምክንያት የጀግና ሚስቶች ከእነ ልጆቻቸው፣ የጤና ባለሙያዎች፣ አስተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የግለሠብ ኩሽናዎችን እየተከራዩ ለመኖር ተገደዋል፡፡ ሕገወጦች ደግሞ የራሳቸውን ሁለትና ሶስት ቪላ ቤቶቻቸውን እያከራዩ በመንግስት ቤት ይኖራሉ፡፡ ወይም ለሶስተኛ ወገን ያከራያሉ፡፡ ወይም ውስጥ ለውስጥ ይሸጣሉ፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ኬቤአድ (ሻለቃ)፣ (ኮሎኔል)፣ (ወ/ሮ)፣ (አቶ)፣ እና ተጋዳላይ የነበሩ ሰዎች ስራ አስፈፃሚ፣ ዋና ዳይሬክተርና ሥራ አስኪያጅ እየተባሉ ተፈራርቀውበታል። ከአንዲት እንስት በስተቀር የሁሉም እጆች ረጃጅሞች ነበሩ። አሁንም ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት ያለ ሥራው ገብቶ ጥቃቅን ሳንቲሞች እሰበስባለሁ ካላለ በስተቀር ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት መስራት ያለበት ሲሆን ለዚህም ሂደት ይረዳ ዘንድ ሁለት አማራጮችን አቀርባለሁ፡፡
1ኛ. ቤቶቹ ለረጅም ጊዜ እድሳትና ጥገና ያለማግኘታቸው ብቻ ሳይሆን ድምፅ ስለሚያስተላልፉ የአንድ አባወራ ሬድዮ ወይም ቴሌቪዥን፣ ለስምንት አባወራ ከነቤተሰቡ ፀጥታ ይነሳል፡፡ የፍሳሽ ማስወገጃም ስለሌላቸው መጥፎ ሽታው ከተከራዮቹ አልፎ ለአካባቢውም ህብረተሰብ   ለስርዐቱ በነበራቸው ታማኝነት ያለ አግባብ ቤት የታደላቸውን ሳይጨምር፣ ተቋሙ ሲቋቋም በነበረው አላማና ግብ መሰረት ተከራይተው ለሚኖሩ ግለሰቦች ቢሸጡ የአገልግሎት እድሜያቸውን ማራዘም ከማስቻሉም በላይ መንግስት ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ ካለው ፍላጎት በተጨማሪ፣ እየተከተለ ላለው ፖሊሲና ለነደፈው ስትራቴጂ ተግባራዊነት አንዱን ምዕራፍ እንደጀመረ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የተወሳሰቡና  አሰልቺ አሰራሮችን ያመክናል። ኪራይ በመሰብሰብ የሚያጠፋውን ጊዜ ያስቀራል፡፡ በአ.አ መስተዳደር እና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለውን የአሰራር ክፍተት ይሸፍናል፡፡ ነገር ግን በውጭ ምንዛሬ የሚከራዩ ቤቶችን ያስቀጥላል፡፡
2ኛ. መንግስት ቤቶቹን የመሸጥ ፍላጎት ከሌለው ኬቤአድን በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች በመበተን ተከራዮች በአካባቢያቸው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ሲሆን ጉዳያቸውን ለማስፈፀም የሚያደርጉትን ረጅም ጉዞና ለትራንስፖርት የሚያባክኑትን ገንዘብ ያስቀራል፡፡ ይህ ያልተማከለ (Decentralized) አሰራር ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ያስቀራል ተብሎ ባይገመትም፣ ህዝቡ በቅርበት ስለሚከታተልና አዲስ በሚመሰረተውም መንግስት የተሻሉ አመራሮች ይመጣሉ ተብሎ   ስለሚጠበቅ መፍትሄ ይኖራል ብለን እንጠብቃለን፡፡     
ኢትዮጵያ ከወንበዴዎች፣ ዘራፊዎችና ሙሰኞች ተጠብቃ ለዘላለም ትኑር!
         ከውብሸት ተክሌ ፍትህአወቅ  (ገርጂ ቡናና ሻይ)

 ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ሎሌ፣ ጌታው ፊት ይቆምና ቃል ይገባል። የሎሌው ስም ብርቄ ነው።
ቃሉም፤
“ጌታዬ ሆይ”
ጌታው፤    
“እህ ብርቄ ምን ፈልገህ ነው?”
“ጌታዬ፣ ቃል እንድገባ ይፈቅዱልኛል?”
ጌታው፤
“አዎን እፈቅድልሃለሁ። የምን ቃል ልትገባ ነው የፈለከው?”
ብርቄ፤
“ጌታዬ አሁን አይበለውና የእርሶ ህይወት ቢያልፍ፣ ያለ እርስዎ መኖር ስለማልሻ ዓለም በቃኝ ብዬ እመንናለሁ።”
ጌታውም፤
“ተው አታረገውም ብርቄ። መመነን ቀላል ነገር አይምሰልህ!”
ብርቄ፤
“ጌታዬ፤ በጭራሽ ቃሌን አላጥፍም”
ጌታው ወደ ሌላው አገልጋያቸው ዞረው፣ “ንሣ አንተ አሽከር፣ ለብርቄ አንድ ኩታ ሸልምልኝ!” ሲሉ በትፍስህት ተሞልተው አዘዙ።
ያም ሌላኛ አገልጋይ ሮጦ ወደ ቤት ገብቶ አንድ ኩታ ይዞ መጥቶ ለብርቄ ሸለመ!!
ጌትዬው አርጅተው አፍጅተው ሞቱ። ብርቄ ሳይመንን ቀጣዩን ጌታውን ለጥ ሰጥ ብሎ ማገልገሉን ጀመረ።
 አዲስ የመጡት ጌታም ድንኳን አስጥለው፣ ጠጅ በጋን አስሹመው፣ ሰንጋ አርደው የሰፈር ሰዎችንና ሽማግሌዎችን እንዲሁም ዘመድ አዝማዱን ሁሉ ጠርተው ድል ያለ ግብዣ ደገሱ።
በድግሱ ላይ አንድ አዝማሪ ተገኝቷል። አዝማሪው ሟቹን ጌታም፣ አዲሱን ጌታም እያነሳ እንዲያወድስ አዲሱ ጌታ፤
“ንሳ አንተ አዝማሪ አጫውተና!” አሉት።
አዝማሪውም፣
“የኔማ ጌትዬ የሚበላው ጫማ
የኔማ ጌትዬ የሚጠጣው ጠጅ
እንዴት ዝም ይባላል ይሞገሳል እንጂ!” ብሎ ገና ሲጀምር፤
“ይበል! ይበል! ሠናይ! ሠናይ!” አሉ በደስታ እየተፍነከነኩ።
አዝማሪው ቀጠለና፤
“የኔማ ጌትዬ ዘረ መኳንንት
ሥጋ አልበላም አለ ትከሻው ከብዶት!” አለ።
አዲሱ ጌታም፤
“ንሣ አንተ አሽከር አንድ ኩታ ሸልምልኝ” አሉ።
አሽከር ፈጠን ብሎ ለአዝማሪው ኩታ ሸለመው።
ይሄኔ አዝማሪው ወዲያውኑ ቀልጠፍ ብሎ ቀጠለና፤
“ትላንትና ማታ…
የጥንቱን ጌታዬን መንገድ ላይ አግኝቼ፡-
ሚስቴ ደህና ናት ወይ?
ልጄስ አደገ ወይ?”
ብለው ቢጠይቁኝ፤
“ሚስትዎት ደህና ናቸው
ልጅዎትም አድጓል
ብርቄም አልመነነም!” ብዬ ብነግራቸው…
(ጣቱን እንደ ጌታው እያወናጨፈ ያሳያል)
“አዬ ጉድ!
 አዬ ጉድ!
አዬ ጉድ!...ያሉበት-
ረገፈ ጣታቸው!”
ሲል ገጠመ ይባላል።
*   *   *
ከነገር ሁሉ መጥፎ ቃልን አለመጠበቅ ወይም አለማክበር ነው።
 ጥንት፣ ገና በጠዋት፤
“ቆፒና ወረቀት፣ ቀሪ ነው ተቀዳጅ
መተማመን ካለ ይበቃል አንድ ወዳጅ!”
ተብሎ የተዘፈነው ለዚህ ነው።
በዘንድሮው አዲስ ዓመት አዲስ ራዕይ፣ አዲስ መንፈስ፣ አዲስ ተሐድሶ ይኖረን ዘንድ ልብና ልቡና ይስጠን! የተስፋችን ብርሃን የበለጠ ብሩህና ጋን የሚያጎናጽፈን ይሁን።
መልካም የ2014  አዲስ ዓመት ይሁንልን!
ከአዲስ አድማስ ጋር ወደፊት እንጓዝ!!

  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ባለው ጦርነት ምክንያት ከሃብት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች፣ የተለያዩ የቁስ ድጋፎችና እርዳታ እያደረገ መሆኑን  አስታውቋል።
ፓርቲው በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ያለውን የፖለቲካ ልዩነት ወደ ጎን አድርጎ፣  በህወሃት ጥቃት የተፈጸመባቸውን ዜጎች የመታደግ ተግባር ላይ መጠመዱን ያመለከተ ሲሆን በጎንደር፣ ደሴና አፋር ለሚገኙ ተፈናቃዮች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል። ከሰሞኑም የህወሃት ሃይል የከፋ ጭፍጨፋ በፈጸመበት በሰሜን ጎንደር ጭና ቀበሌ  በመገኘት በከፍተኛ አመራሮቹ በኩል፣ ከአራት መቶ ሃምሳ ሺህ ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አድርጓል ተብሏል።
በህውሃት ወራሪ ሃይል ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሴቶችና ህጻናት እንደመሆናቸው ፓርቲው የንጽህና መጠበቂያና አልባሳትን ነው ድጋፍ ያደረገው ብለዋል-የፓርቲው የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ቡድን ዋና ሃላፊ ማስተዋል አስራደ።
ኢዜማ ለወገኖቹ የሚያደርገው ድጋፍ በዚህ እንደማቆምና ቀጣይነት እንዳለውም ተናግሯል።
ኢዜማ ከሰሜን ጎንደር በተጨማሪ በደሴና በአፋር ክልል ለሚገኙ የጦርነቱ ተጎጂዎችም ወደ የአካባቢዎቹ ባሰማራቸው ልኡካን አማካኝነት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል።
በደሴ ከተማ ለሚገኙ የጦርነቱ ተፈናቃዮች፣ ከ1 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን መስከረም 13 ቀን 2014 ዓ.ም ያስረከበ ሲሆን በተመሳሳይ  ለአፋር ክልል ተፈናቃዮች የ7 መቶ ሺህ ብር ድጋፍ አበርክቷል።


Sunday, 26 September 2021 00:00

ሳምንታዊ ዜናዎች

    በቆቦ ከተማና ዙሪያው የሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ ተፈጽሟል ተባለ
                      
               ላለፉት ሁለት ወራት ተኩል ገደማ በህወሃት ቁጥጥር ስር በቆየው የራያ ቆቦ አካባቢ በተለይ በቆቦ ከተማና ዙሪያው ቁጥራቸውን በውል ለማወቅ አዳጋች የሆነ የሲቪል ሰዎች ጅምላ ግድያ መፈጸሙን በአካባቢው ላይ ጥናት ያደረገው የወሎ ህብረት ለአዲስ አድማስ የገለጸ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ፤ ስለ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ ተመሳሳይ መረጃዎች ማግኘቱን አመልክቷል። የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ ከ5 መቶ በላይ ሰዎች ስለመገደላቸው አስታውቋል።
የህወሃት ሃይሎች በተለይ ጳጉሜ 4 እና 5 ቀን 2013 ዓ.ም  በቆቦ ከተማ ህፃናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን በአጠቃላይ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ሲንቀሳቀስ ያገኙትን ሁሉ በመግደል፣  አስክሬኖችን ጭምር የመሰወር ዘግናኝ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈጸማቸውን የወሎ ህብረት በጎ አድራጎት ድርጅት ሊቀ መንበር አቶ ያሲን መሃመድ ለአዲስ አድማስ አመልክተዋል።
“አንዳንዶች የሟቾችን ቁጥር 800 ሲሉ ይገልጻሉ፤ ይህ ግን የሟቾችን ቁጥር ያሳነሰ ነው፤ ከዚህ በላይ የሆነ ህዝብ ነው የተጨፈጨፈው “ያሉት አቶ ያሲን፤ ገለልተኛ ተቋማት በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ማጣራት እድርገው ለህዝብ እውነታውን ሊያሳውቁ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በበኩሉ በቆቦ ከተማና ዙሪያው ባሉ የገጠር ከተሞች፣ በሲቪል ሰዎች ላይ በህወሃት ሃይል እየተፈጸመ ያለው ግድያ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል። የሲቪል ሰዎች መኖሪያ አካባቢዎችን፣ የቤት ለቤት ሃሰሳ ግድያ፣ ዝርፊያና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ጥቃት ጭምር መፈጸሙን ኮሚሽኑ ሪፖርቶች እንደደረሱት አስታውቋል።
ኢሰመኮ በጉዳዩ ላይም ተጨማሪ ምርመራ እንደሚደርግ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ) በበኩሉ በደረሰው መረጃ መሰረት ጳጉሜ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በህወኃት ሃይሎች በቆቦ ከተማ በተፈፀመ ጥቃት ከ5 መቶ በላይ ንፁሀን በአንድ ጀምበር ተጨፍጭፈዋል፣ የገበሬው የእርሻ ሠብሎች በሙሉ እንዲወድሙ ተደርገዋል፡፡ ነዋሪዎች በገፍ ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ተፈናቅለዋል፡፡

_______________________________________


                    “የሸቀጦች ዋጋ ንረት የዜጎችን በቂ ምግብ የማግኘት መብት እየተጻረረ ነው”
                      
            በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ ንረት በእጅጉ እንዳሳሰበው ያመለከተው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በቂ ምግብ የማግኘት መብታቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ነው ብሏል።
ኮሚሽኑ በሃገሪቱ የተከሰተውን የሸቀጦች ዋጋ ንረት አስመልክቶ ባወጣው አስቸኳይ መግለጫው የዋጋ ንረቱ  የሌሎችን በቂ ምግብ የማግኘት መብት የሚገድብ ከመሆኑም በላይ በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው ብሏል።
ችግሩን ለማቃለል መንግስት የወሰዳቸው አንዳንድ እርምጃዎች በተለይም የተወሰኑ ከሃገር ውጪ የሚሸመቱ የምግብ ሸቀጦች ከቁርጥና ከግብር ነጻ እንዲገቡና በሃገር ውስጥ በሚገበዩ ምርቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ግብር እንዲነሳ መደረጉ፣ አበረታች እርምጃ ነው ብሏል- ኮሚሽኑ በመግለጫው።
የዋጋ ንረትን ለማቃለል በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎች የተቀናጁ እንዲሆኑና በእርግጥም ለጉዳት የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እያደረጉ ስመሆኑ በየጊዜው ክትትል እንዲደረግ ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል።


________________________________________________


                     “ኢዜማ” እና “ነዕፓ” ከሶማሌ ክልል= ምርጫ ራሳቸውን አገለሉ
                              
            የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና ነፃነት እና እኩልነት ፓርቲ(ነእፓ) መስከረም 20 ቀን 2014 በሶማሌ ክልል ከሚካሄደው ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ከዚህ ቀደም በተካሄደው ሃገር አቀፍ ምርጫ የተስተዋሉ ስህተቶች በሶማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ እንዳይደገሙ በተደጋጋሚ ችግሮችን ያመለከቱ ቢሆንም፣ ምንም አይነት የማስተካከያ እርምጃ ባለመወሰዱ ራሳቸውን ከምርጫው እንዲያገሉ መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
በሶማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ የመራጮች አመዘጋገብ ህግን ያልተከተለ ለአንድ ወገን ያደላ፣ የምርጫ ቅስቀሳውም በተመሳሳይ ለሁሉም እኩል በተከፈተው ሜዳ ሳይሆን ለአንድ ወገን ያደላ በመሆኑ ፓርቲዎቹ በዚህ ምርጫ ውስጥ መቆየት ለሚፈለገው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋፅኦ አያበረክትም የሚል እምነት ስላደረባቸው ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ለአዲስ አድማስ ባደረሱት የጋራ መግለጫቸው ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ወደ ክልሉ የተጓጓዘው የምርጫ ቁሳቁስ ዘረፋ የተፈፀመበት መሆኑን በማስረጃ በማስደገፍ የምርጫ ቁሳቁሶች በሙሉ በአዲስ እንዲቀየሩ ለምርጫ ቦርድ  የቀረበው አቤቱታም ምላሽ አለማግኘቱን የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤ በዚሁ ሁኔታ የሚካሄድ ምርጫም ተአማኒነት የጎደለው ነው የሚሆነው ብለዋል። ተጨማሪ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ የቀረበው ጥያቄ ምላሽ አለማግኘቱን መግለጫው ያትታል፡፡
በየደረጃው መዋቀር የነበረበት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መዋቅር፣ ከመንግስት ጋር የተዋሃደ መሆኑን፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለሙያዎች ሳያውቁ የምርጫ ቁሳቁሶችና ሰነድ በወረዳና ቀበሌ የመንግስት መዋቅር ሠራተኞች እጅ እንዲቀመጥ ማድረጉ፤ እንዲሁም ስለ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ለተፎካካሪዎች ግልጽ መረጃ ያለመስጠቱ ምርጫውን ተአማኒ አያደርገውም ብለዋል-ፓርቲዎቹ፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ በቀሩት በሶማሌ ክልል፣ ሃረሪ ክልልና በደቡብ አጠቃላይ ምርጫ የሚደረግ ሲሆን በዚሁ ምርጫ በአጠቃላይ ከሰባት ሚሊዮን በላይ መራጮች ይሳተፋሉ፡፡

Monday, 20 September 2021 17:17

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

 የራሄል ጌቱ “ኢትዮጵያዬ” (የኔ 1ኛ)
                             ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ

                የፓብሎ ፒካሶን “ገርኒካ” ሥዕል የፈጠረው 2ኛው የዓለም ጦርነት ነው። ሕወሓት ባርኮ የጀመረው ጦርነትም እንዲሁ የብዙ የፈጠራ ስራዎች መነሻ መሆኑ እየታየ ነው። ኪነጥበብ ከምቾት ይልቅ መከራን የሚፈልግ ይመስለኛል። በቅርቡ ከ100 በላይ የጥበብ ሰዎች ተሰባስበው በ20 ቀናትና ሌሊቶች የሰሯቸው “ስለ ኢትዮጵያ” የተባሉ መንትያ አልበሞች የዘመናችን ሀገራዊ ሀውልቶች ሆነው ይጠቀሳሉ። ድምጻዊት ራሄል ጌቱ ሰሞኑን የለቀቀችው “እቴሜቴ” አልበሟ ውስጥ “ኢትዮጵያዬ” የተባለው ቁጥር 1 ወኔ ቀስቃሽ ዜማ በቅርብ ከተሰሩ ሀገራዊ ዜማዎች ሁሉ ለየት ያለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
በአሚናዎች እንጉርጉሮ የሚጀምረው ይህ ዜማ፣ ድምጻዊቷ ከፍ ያለ ስፍራ ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን ተክላ እስኪጠናቀቅ ሙሉ ሆኖ ዓይንንም ጆሮንም ሰቅዞ የመያዝ ኃይሉን አሳይቶናል። ስራው ሲያልቅ ማን ነው ይህን ምትሀት የፈጠረው? የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል። የግጥሙ ደራሲ ናትናኤል ግርማቸው ነው? የኢዮኤል መሀሪ ዜማና ቅንብር ነው? የቅድስት ይልማ ዳይሬክተር መሆን ነው ወይስ የሰዳኪያል አየለ ሲኒማቶግራፈርነት? አንድ ቦታ ላይ ቆሞ ለይቶ ማመስገን የሚቻል አይመስለኝም። የአማርኛ ዘፈኖች የጀርባ አጥንት የሆነው “እናናዬ . . . እህም እናኑ” እንኳ የክብር ቦታ አግኝቷል።
“እናና እናና እናና
ይጥለፈኝ ቀሚሷ ጉበኗ
ጠብ እርግፍ ያርገኝ ለክብሯ
ሆዴ እንዳታጣላኝ ካድባሯ
እናና እንዬ እናት ዓለም
የደም የአለላ ሰበዝ ቀለም “ ትላለች።
ቀጥላም፤ “ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኧረ ሰው ጌጥ ሀብቱ
ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኧረ ሰው ኩራቱ
እንደምን አይከፋው
አንገቱን አይደፋው
ሲከፋት እናቱ” እያለች የዛሬዋን ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በአጭር መስመሮች ስላ ታሳየናለች፡፡
ራሄል የምታዜማት ገጸ ባህሪ የኢሕአዴግ ዘመን ልጅ፣ ብሔሯ አማራ ናት።
“በልጅነት ፍቅርሽ የሰቀልኩት ሰንደቅ የታቀፍኩት በጄ
የዜግነት ክብር ስል የዘመርኩት ከሰልፍ ማልጄ
ያቆመሽ ካድባርሽ የነጻነት ደጄ
እሱ ነው እሱ ነው ወዳጄ” ብላ እያዜመች ነው ራሷን የምትገልጸው። በአሚናዎቹ እንጉርጉሮ የጀመረው ሀዘንና ልበሙሉነት የተቀላቀለበት ዜማ፣ ከቅድስት ይልማ ዝግጅትና ከራሄል ጌቱ እንደ አዚያዜሟ ሁሉ የቆፍጣና ፋኖ ምስለ ትወና የገፀባህሪዋን ማንነት እንደ ፎቶ ታሳየናለች።
“ኧረ ጎራው ኧረ ዱሩ
ጃል እንዴት ነው ዳር ድንበሩ
የእሷን ክፉ ቆሜ ከማይ
ያሳደገኝ አፈር ይብላኝ” ስትል ለዚያች የልጅነት ህልሟ ራሷን የመስጠት ቁርጠኝነቷን ቆርጣ ታሳየናለች፡፡
“ኧረ ጎራው ኧረ ዱሩ “ እያለች ዱር ታስገባናለች።
“ኧረገኝ ኧረገኝ ንቢቷን
ቀፎዋን የነኩባት ቤቷን
ኧረገኝ ኧረገኝ ፍም እሳት
ተባይ ሀገሬን ሲንቃት
ባይ ካንገት በላይ በላይ
ሁሉ ካንገት በላይ በላይ
ያለ ሀገር ኑሮ ስቃይ
ማን ኢትዮጵያን መሳይ ሲሳይ
ሲሳይ ነች እሷ ሲሳይ"
እያለች የፍቅሯን ጥግ፣ የቁጭቷን ጠርዝ “ያለ ሀገር" እያለች ሲርባት እሸት፣ ሲጠማት ቅራሪ ያቀመሷትን፣ የእናቷን ቀሚስ ተከትላ የሄደችባትን የሀገሯን ስቃይዋን ታጋራናለች። “ብሞትለት ሞት አነሰኝ” ስትል ነው አፈር ገፍቶ ለፍቶ የሚያጎርሳት ቀን የጎደለበትን፣ ቤቱ የፈረሰበትን፣ የአጋንንቶች ሰይጣናዊ በትር ያረፈበትን ወገኗን ነው “ ብሞትለት ሞት አነሰኝ የምትለው።
ይህ ቃሉ ነው። ምስሉ ከዚህ በላይ ጮኾ የሚናገር ነው።
“እናናዬ እናናይ" ስትል አንገቷ የሚሆነውንና የሚያስተላልፈውን መግነጢሲዊ ምስል በማሳየት ካልሆነ በቃላት መግለጽ አይቻልም። ቅድስት ይልማ እንደ ምንጊዜውም በ “ኢትዮጵያዬ” የሙዚቃ ቪዲዮ ላይ ተጠብባለች። የሙዚቃ ቪዲዮ በራሱ ጥበብ ከመሆኑም ባሻገር ስራውን ከፍ የማድረግ ኃይል አለው። ቅድስት ተክናበታለች። ጥላሁን ገሠሠ ንጉሠ ነገሥቱ ፊት በቀረበ ጊዜ ያሉት፤ “ድምጽህን ጠብቀው" ነበር ። ለራሄልም ይህንኑ ነው የምደግምላት።
“ኢትዮጵያዬ”ን በ2 ቀናት ውስጥ ከ30 ጊዜ በላይ ሰምቼዋለሁ። ገና ብዙ ጊዜ እደጋግመዋለሁ። ሙያተኞቹ ሁሉ ክበሩልኝ፡፡

________________________________________

                  
                   ‹‹ዋጋዬማ አትታረድም!››..
                          በድሉ ዋቅጅራ


              ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡፡
.ስነጥበብ በምጡቅ ምናብ (elivated imagintion) እና በውበት ስሱነት (sensitivity to beauty) ዳግም የሚፈጠር እውነት ነው፡፡ እቅጬ እውነት (fact) አይደለም፣ እውነት (truth) ነው፡፡ እውነት ከእቅጬ እውነት የሰፋ፣ የፋፋ፣ የተንሰራፋ ነው፡፡ ይህ መስፋት - መፋፋቱ ነው የምንኖርበትን ሁለንተናዊ መስተጋብር ውጤት (እቅጬ እውነታችንን) እንድናጠይቅ የሚጎነትለን፡፡ ስነጥበብ እቅጬ እውነታችንን እንድንቀበል ሳይሆን እንድንጠይቅ፣ እንድንመረምር ሲያደርግ ለግቡ በቅቷል፡፡
.የስነጥበብ ጉንተላ የማህበረሰብን ህሊናዊ ልእልና ይሞርዳል፤ የተሞረደ ህሊና ሳይቆርጥ - ሳያደማ በተወረወረለት ሀሳብ ላይ አይደላደልም፡፡
"ዋጋዬማ አትታረድም!" (እረኛዬ ተከታታይ ድራማ፣ ክፍል 4) ትላለች እናና፤ ከከብቶቿ ጋር ገደል የምትገባዋ እረኛ። ‹‹ሀገሬስ ለእኛ ለዜጎቿ እንዲህ አይነት እረኛ የምታቆመው መቼ ነው? በከተማ በገጠሩ፣ በየወንበሩ እንደ እናና ያሉ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያንስ አይሞቱም!›› የሚሉ፣ ከሚያስተዳድሯቸው ዜጎች ቀድመው ገደል የሚገቡ፣ በተተኮሰበት ጥይት ፊት የሚቆሙ እረኞች የምናገኘው መቼ ነው? . . . ይጎነትላል፡፡
የራሔል ጌቱ ‹‹ኢትዮጵያዬ›› የሚለው ዘፈን በዘነጋነው እቅጬ እውነት የገነነ ውበት ነው፡፡ ውበቱ ይቆጠቁጣል፤ እውነቱ ይሸነቁጣል፤ አይደለድልም፤ ይፈረፍራል።
እንደነዚህ ያሉ ስራዎች ዛሬያችንን አስጠይቀው ለነገ መልስ ያንደረድራሉ፣ የዛሬዬያችንን ጥቀርሻ ባንጠርገው መኖሩን አውቀን እንድንጸየፈው ያደርጋሉ፡፡ ... ‹የስነጥበብ ግብ ከማህበረሰብ ፊት ቀድሞ ለነገው ማዋጣት እንጂ፣ ከኋላው እየተከተሉ በጣለው ቆሻሻ መጫወት አይደለም› የምለው ለዚህ ነው፡፡


_________________________________________


                        Politicization of History... የአዲስነት ፀር!
                                ጌታሁን ሔራሞ                 ለዩጎዝላቪያ መፈራረስ የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ከብሔር ፖለቲሳይዜሽን ያልተናነሰ ሚና ተጫውቷል። የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ፅንሰ ሐሳብ ፖለቲከኞች ላለፈው ዘመን ታሪክም ሆነ በወቅቱ ንቃተ ህሊና መመዘን ላለባቸው ታሪክ-ተኮር ስህተቶች ዛሬ ፖለቲካዊ ቅርፅ ሰጥቶ በብሔሮች መካከል መቃቀርን ለመፍጠር የሚጠቀሙበትን ጥረት የሚያመላክት ነው። ያለፈ ታሪክ ስንል አፍቅሮተ ትናንት (Nostalgia) አሊያም የትናንት ጭቆና በሌለበትም ጭቆናው ዛሬም እንዳለ መቁጠርንም (Internalized oppression) እንደሚያካትት ይሰመር። ለምሣሌ ቀደም ሲል የዩጎዝላቪያ ሪፐብሊክ በነበረችው ክሮሺያ ከድህረ ኮሚኒዝምም በኋላ ፖለቲካዋን ይዘውር የነበረው ያለፈው ታሪኳ ነበር። በአጭሩ የትናንት ታሪክ የክሮሺያን የየዕለት ፖለቲካዋን ይቀርፃል። ኮሶቮ ውስጥም ቁርሾ ለመቀስቀስ ሲባል በጦርነት የተሰው አርበኞች አፅም ተቆፍሮ እየወጣ እንደገና ይቀበር ነበር፣ በብሔር ብሔረሰቦች መካከልም ጠብን ለመዝራት ሲሉ የብሔር ፖለቲከኞች ሐውልት ያቆሙ ነበር።
የብሔር ፖለቲከኞች የቅስቀሳ ዘዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይነቱ አንዱ ገራሚ ነገር ነው። ከእግዚአብሔር ምህረት ለጥቆ ዕድሜ ለሕዝባችን ንቃተ ሕሊናና ነባር ማህበረሰባዊ ትስስር እንጂ የኢትዮጵያ የብሔር ፖለቲካም መተንፈሻ ሳንባው፣ የትናንት ቁርሾና ታሪክ ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የትናንት ስህተቶች ለዛሬ ልምድና ትምህርት መቅሰሚያ አጋጣሚ ከመሆን ያለፈ ሚና ሊኖራቸው ዘንድ አይገባም። በቂም፣ በበቀልና በቁርሾ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ሀገርን አንድ ኢንች ወደ ፊት አያስኬድም። አዲስ ሐሳብን ለማፍለቅ አቅሙ የሌለው ፖለቲከኛ፣ በትናንት ትውስታ ዛሬን ለመኖር ይገደዳል። በአዲሱ ዓመት በአሉታዊ ትውስታ የተሰነገ አሮጌው ትናንቱ ይሰለጥንበታል።
መልካም አዲስ ዓመት!
በነገራችን ላይ ስለ ዩጎዝላቪያው የታሪክ ፖለቲሳይዜሽን ጠለቅ ያለ መረጃን ከሚቀጥለው መፅሐፍ ማግኘት ይቻላል፦
Nationalism and the Politicization of History in the Former Yugoslavia, Editors Gorana Ognjenovic and Jasna Jozelic, 1st ed. 2021.


_____________________________________                       “የአዲሱን ዓመት ለምድ ለብሰው ከሚመጡ 2012ቶችና 2013ቶች ተጠበቁ”
                                    ረድኤትአሰፋ


            ስልኬ የዛሬ ሳምንት አካባቢ መቀባዠር ጀመረች። ሁሉን ነገር በጸብ መፍታት አይገባኝም ብዬ ታገስኳት። በዚያ ላይ ደሞ ዓመቱ ነጃሳው 2013 ነው ብዬ፣ ያላበደ የለም ብዬ ታገስኩ። አዲስ ዓመት ይግባ ብዬ፣ መስከረም ይጥባ ብዬ ታገስኩ። <እንዳያልፉት የለ>ን ያለፖለቲካዊ ዘመኑ እያፏጨሁ፣ ዓዲሱን አመት ተቀበልኩ። ለካ መስከረም እንደ ክፉ ህጻን አባቱን ከልክሎ ለራሱ ብቻ ነው የሚጠባው! ትናንትና በ2014 ከእንቅልፌ ስነቃ ስልኬ ቴሌቭዥኔ ጋ ተመሳስላ አገኘኋት። የምትታይ ግን የማትነካ። ብትነካም እንዳኮረፈች ፍቅረኛ የማትሰማ የማትለማ። ጃንሆይ ወደ ቮልስ ዋገን በወረዱበት በመስከረም ሁለትስ አልዋረድም... ብዬ ባላየ አለፍኩት። ስልኬም ዶክተር አሸብርን በሚያስከነዳ ድርቅና ስታክ አድርጋ ዋለች።
ዛሬ በማለዳ ገላዬን ታጥቤ፣ የክት ልብሴን ለብሼ ካፌላቴ በአናቱ ከልሼ... ማህለኛውንና ሌባ ጣቴን በgoodluckኛ አቆላልፌ ... የቤትና የቢሮ ቁልፌን እያሽከረከርኩ ፉጨት አስቀድሜ... መገናኛ ካሉ ... ጉንዳን የወረራቸውን አጥንቶች... በሚያስቀና መልኩ በሰው ከተወረሩና የጾም ኬክ ከመሰሉ ህንጻዎች በአንደኛው ስር ከሚገኝ የስልክ ክሊኒክ ገባሁ።
እንደገባሁ አንድ ልጅ እግር አቀርቅሮ... እንደ ኢትዮ360 አናቷ ባጠረ ምላሷ በረዘመ መፍቻ የአንዲት ምስኪን ሞባይልን ሆድ እቃ ሲፈተፍት ደረስኩና < ደህና አደርክ?> አልኩት። በጎሪጥ ቀና ብሎ ፊቴን ሳያይ እጄ ላይ የያዝኳትን ስልክ አይቶ እና ለ “ደህና አደር”ኬ ሳይጨነቅ
“ምን ሆኖብህ ነው?” አለኝ
“ስነካት አልመልስ እያለች...” አላስጨረሰኝም
“ስክሪን ፌል አድርጎ ነው!... ሌላ ስልክ ግዛ...”
በሸቅኩ።
“እየመከርከኝ ነው? ምክር ፈልጌ ሳይሆን ሰሪ ፈልጌ ነው የመጣሁት ሰውዬ”
በንቀት የሽሙጥ ሳቅ ታጅቦ “የሱ ስልክ ስክሪን ውድ ነው” አለና ለመጀመሪያ ጊዜ ፊቴን አየው። የመግዛት አቅሜን እየመዘነ መሆኑ ታውቆኝ በብሽቀት፤
“ስለ ገንዘብ ማን አወራ? ስንትስ ቢሆን ...” ቁልፌን እያሽከረከርኩ ፎከርኩበት
ሳቅ ብሎ “አስር ሺህ ብር ነው” አለኝ። ከዛ በኋላ የሆነውን አላስታውስም። የስልክ ክሊኒክ ወድቄ ጤና ጣቢያ አልጋ ላይ ነቃሁ። ቀና ስል ስልክ ሰሪው ከአንዲት ነርስ ጋር በሀዘኔታ እያዩኝ ነው። ስልክ ሰሪው ፈጠን ብሎ አጠገቤ መጣና “አስጠንቅቄህ ነበርኮ... አልሰማ አልከኝ “ አለኝ በሀዘኔታ። ከኪሱ የገዛ ስልኩን ላጥ አድርጎ አወጣና ወደኔ ዘረጋልኝ። ምን አይነት ምስኪን ሰው ነው ብዬ ተገርሜ እጄን ስዘረጋ መልሶ ወደራሱ ወሰደውና፤
“እኔ ሙስሊም ነኝ.... ግን ይቺን መዝሙር ሊሰራ ከመጣ ስልክ ውስጥ ነው ያገኘኋት አድምጥበት “ ብሎ  ከፈተልኝ... በጉጉት የተዘረጋ እጄን አጥፌ መስማት ጀመርኩ
“ማን አለን ጌታ ሆይ ካንተ በቀር...”
ስልክ ላሰራ ሄጄ ዋጋው መንፈሳዊ ሰው ሊያደርገኝ ለጥቂት....
ወገን ከመቼ ጀምሮ ነው የስክሪን ዋጋ ከሙሉ ስልክ ዋጋ የበለጠው? ወይስ የድሮ ሼባዎች “በጉን አንድ ብር ገዝቼ ቆዳውን ብር ከሀምሳ ሸጥኩት” ያሉን ታሪክ በዲጅታልኛ ሊደገምብን ነው? ወይኔ 2014... አምኜህ?
{ይህንን ፖስት እጽፍ ዘንድ.... ለመታደስ ከመጡ ስልኮች አንዷን በማዋስ የተባበረኝን... ስልክ ጠጋኝ ቶፊቅ ኢብራሂምን አመሰግናለሁ። ካሁን በኋላ ምንም ፖስት በኔ አካውንት ብታዩ የቶፊቅ ወይም ስልክ ሊያሳድስ የሰጠው የባለቤቱ አቋም መሆኑን እወቁልኝ። ነጃሳ 2014 ? መች ነው 2015 ደሞ የሚጠባው?

Monday, 20 September 2021 16:38

የሶቅራጥስ ጅኒ (daemon) ምክር

 የአቴናው ሶቅራጥስ በፍልስፍና የታሪክ ሂደት ውስጥ ከዘመን ቅደም ተከተል አኳያ ከእርሱ ቀድመው (Pre-socratic) ከነበሩት ፍልሱፋን በተለየ ሁኔታ ያነሳቸው በነበሩት ጥልቅ የፍልስፍና እሳቤዎች፣  እንዲሁም ደግሞ ይኼንን ገቢራዊ ለማድረግ ይጠቀምበት በነበረውና የሶቅራጥስ መንገድ (Socratic Method) ተብሎ በሚታወቀው የመጠይቅ ስልቱም እጅግ ይታወቅ እንደነበር ይነገራል። ይኽ የሶቅራጥስ መንገድ ተብሎ የሚታወቀው በሌላ መጠርያው የማዋለድ ዘዴ (midwifery method) በመባልም ይታወቃል፤ ልክ አንዲት አዋላጅ የምትወልደውን እንስት ፅንሱን በሠላም እንድትገላገል ከመርዳት ውጭ ሌላ ነገር እንደማትፈይድላት ኹሉ፣ ሶቅራጥስም ልክ እንደ አዋላጅ እያንዳንዱን ሊቅ ነኝ ባይ ጥያቄ በመጠየቅ በልቡና ማኅፀን ውስጥ የተፀነሰውን ዕውቀት ከማዋለድ ውጭ ሌላ ሚና እንዳልነበረው ለማሳየት ይጥር ነበር። ቅድመ ታሪኩም እንደዚህ ነበር ይባላል፡- በአንድ ወቅት አንድ ኬይሪፎን (Chaerephon) የተባለ የሶቅራጠስ ባልንጀራ ደልፊ ወደተባለና በጊዜው ስመጥር ንግርት (Oracle)  የማወቂያ ሥፍራ  አንድ ነገር ለመጠየቅ  አቅንቶ እንደነበር ይነገራል፤ ጥያቄውም በዓለም ላይ ካሉት ሰዎች መካከል ጠቢብ ማነው? የሚል ነው። መልሱ ታድያ ሶቅራጥስ የሚል ነው የነበረው። ይኼን እንደተባለ የሰማው ሶቅራጥስ ግን ጠቢብ መባሉ እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥና ጥያቄዎችንም ከመጠየቅ አላገደውም፤ እንደውም ይኼ የተነገረለት ንግርት እውነት አለመኾኑን  ለማሳየት በሚመሥል መልኩ  አሉ የተባሉትን የአቴና “ጠበብት” የተለያዩ ፍልስፍናዊ ጥያቄዎችን መጠየቅ መቀጠሉን እስከ ሕይወቱ ኅልፈት ድረስ አላቆመም ነበር፤ ምክንያቱም እርሱ በእርግጠኝነት የሚያውቀው አንድ ነገር አለማወቁን ብቻ ነበርና። አፖሎጂ (Apology) በተባለውና የሶቅራጥስ ዋና ተማሪ እንደነበር በሚነገርለት አፍላጦን (Plato) እንደተጻፈ በሚታወቀው መጽሐፍ ላይ እንደተከተበው፤ ሶቅራጥስ ከእርሱ የሚልቁ ጠበብትን ፍለጋና አንድም ስለ እርሱ ጠቢብነት በደልፊ የተነገረው ንግርት እንደው የመላ የነሲብ አነጋገር እንደኾነ ለማረጋገጥ ከጠየቃቸው የዘመኑ “ጠበብት” መካከል የፖለቲካ ልሂቃን፣ ባለቅኔዎችና አደጓሪዎች (craftsmen)  ይገኙበት ነበር። በመጨረሻ ላይ ሶቅራጥስ የደረሰበት ድምዳሜ ግን  እነዚህ ኹሉ ምንም እንደማያውቁና ነገር ግን ራሳቸውን ልክ እንደ ዐዋቂ ይቆጥሩ እንደነበር ነው፤ በእነርሱና በእርሱ መካከል የነበረው ልዩነት ደግሞ ከላይ እንደተጠቀሰው እርሱ ከእነርሱ በተቃራኒ አለማወቁን በጥልቀት ማወቁ ብቻ ነበር።
በዚህ  አጭር ጽሑፍ ውስጥ የሃሳባችን የስኅበት ማዕከል እንዲኾን የፈለግነው ሶቅራጥስ፤ የዘመኑ የፖለቲካ ክበብ ላይ እንዳይሳተፍ ለመወሰን ምክንያት የኾነውን ነገር እንደ መንደርደርያ አስከትለን ጥቂት  እይታን ለማጋረት አልመን ነው።
ሶቅራጥስ በአፖሎጂ ላይ እንደሚከተለው ብሎ ነበር፡- ምናልባትም  አንዳንዶቻችሁ ለምንድነው ወደ አደባባይ በመምጣት ሃገረ መንግሥቱን ከማማከር ይልቅ ሰዎችን በግል በማማከርና ስለ እነርሱ በማሰብ ራሱን ፋታ የሚያሳጣው ብላችሁ ልትጠይቁ ትችሉ ይኾናል። የዚህን ምክንያት ልንገራችሁ።  ወደ እኔ ዘንድ ስለመጣው ንግርትና  ትእምርት (sign) ስናገር በተደጋጋሚ ሳትሰሙኝ አትቀሩም፤ ይኼንንም መለኮታዊነት ሜሊተስ (Meletus) በክሱ ሂደት ያጥላላው ጉዳይ ነበር። ይኽ ትእምርት ከልጅነቴ ጀምሮ ይከተለኝ የነበረ ነገር ነው፤ ይኽ ምልክት  ወደ እኔ የሚመጣ ድምፅ ሲኾን  ሁልጊዜ ላደርገው የምፈልገውን ነገር እንዳላደርግ የሚከለክለኝ ነበር፤ ነገር ግን የኾነ ነገር አደርግ ዘንድ ግን ትዕዛዝን አይሰጠኝም ነበር። እንግዲህ ይኽ ነበር ፖለቲከኛ እንዳልኾን አግዶኝ የነበረው።  የአቴና ሰዎች ሆይ! እኔም በእርግጥ እንደማስበው ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ ቢኖረኝ ኖሮ፣ ከብዙ ጊዜ በፊት ደብዛዬ ይጠፋ ነበርና፤ በዚህም የተነሳ ለናንተም ኾነ ለራሴ አንዳች ፋይዳ ያለው ነገርን መሥራት አይቻለኝም ነበር።
Plato: APOLOGY OF SOCRATES
ሶቅራጥስን ከልጅነቱ ጀምሮ ምልክትን በመስጠት ይከለክለው እንደነበር የነገረንን አካል ዓቃቤ መልአክ አልያም ደግሞ በዓረቢ ልሳን ‘ጅኒ’ ብለን ልንጠራው እንችላለን። ጅኒ የሚለውና ሴማዊ ጥንት (origin) እንዳለው የሚታመነው የዓረብኛ ሥም የሚያመለክተው  አንድ ከህዋሳተ አፍኣ (senses) የተደበቀን ህላዌ (being)  ለመግለጽ ነው። ለማንኛውም ይኼ የሶቅራጥስ አማካሪ ምልክትን በመስጠት ጭምር ከልጅነቱ ጀምሮ እንዳያደርገው ይከለክለው ከነበሩት ነገሮች መካከል በፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፍ የመምከሩ ጉዳይ ነው። በዚያ ላይ ይኼ አማካሪ ጅኒ ስልጡን ባሕርይ ቢጤ ያለው ሳይኾን አይቀርም፤ ምክንያቱ ደግሞ መከልከል እንጂ ማዘዝ ባለመፈለጉ ነው። ቢያንስ አለማድረግን እንጂ ማድረግን ካላስተማርኩህ ብሎ ችክ የማይል ዓይነት ነው።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፤ የሶቅራጥስን ልቡና ብሩህ እንዲኾን አድርጐት የነበረው ከፍተኛ የማሰብ አቅም (Personal faculty) በዘመኑ በነበሩት አቴናውያን ዘንድ ምናልባትም ራሱን የቻለ ጅኒ ወይም ከጅኒ ጋር እንደተያያዘ ተደርጎ ይታይ የነበረ ሳይኾን አይቀርም። በእርግጥ አሁን ሳይንስና ቁሳዊነት በተንሰራፋበት ሁኔታ ውስጥ ለምንኖር ሰዎች ስለ ዲበአካላዊ ህልዋን (metaphysical beings) አንስቶ መወያየቱ ብዙም ቀልብ የማይሰጠውና ተአማኒነት የሌለው ተደርጐም ሊወሰድ ይችላል፤ በፍልስፍና ግን አሁንም ድረስ ቁልፍ የምርምር ዘርፍ እንደኾነ የቀጠለ ጉዳይ ነው። በእርግጥ ከሶቅራጥስ ቀድሞ የነበረውና ሄራክሊተስ በመባል የሚታወቀው ፈላስፋ የሰው ጠባይዕ መንፈሱ ነው (“ethos anthropos daimon”) ማለቱን ስናስተውል፣ በቀድሞ የጽርዕ ፍልስፍና ውስጥ ለዲበኣከላዊ ህልዋን ይሰጥ የነበረው  ሥፍራ ራሱን የቻለና ትልቅ  እንደነበረ እንገነዘባለን።  በሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብዙዎች ፖለቲካን እንደ ትልቅ ሙያ ቆጥረውትና ከዚያ ውጭ ሙያ የሌለ እስኪመስል ድረስ  መድረኩን አጨናንቀውት ስንመለከት፣ ያ ሶቅራጥስን ፖለቲካ ላይ እንዳይገባ ይከለክለው የነበረው ስልጡን ጅኒ ምናልባትም በብዙ ምዕራፍ ርቋቸዋል  ለማለት የሚቻል ይመስላል፤ ስለዚህ ድምፁ እየተሰማቸው አይደለም፤ በመኾኑም አማካሪ አልባ ናቸው ማለት ይቻላል። በእርግጥ በዓለማችን አሠራር  በፖለቲካ እንዳትሳተፍ ለመከልከል የግድ እንደ ሶቅራጥስ የማይታይ ጅኒን ምክር መቀበል ላይጠበቅብህ ይችላል፤አምባገነን መንግሥታትም ለመንበራቸው ልታሰጋቸው ትችላለህና ራሳቸው በአካል ተገልጸው ይመክሩሃል ይዘክሩሃል፤ እምቢ ካልክ ደግሞ ወደ ወኅኒ ይወረውሩሃል። ልዩነቱ የሶቅራጥስ በፖለቲካ ውስጥ እንዳይሳተፍ መከልከሉ  አንድም ፖለቲካ፣ ያው የአላዋቂዎች ስብስብ በመኾኑ ቁምነገር አይገኝበትም ብሎ እና ሌላው ደግሞ ቀሪ  ጊዜውን ለፍልስፍናና ለጥበብ በማዋል ያለማወቅ ክፍተቱን ለመሙላት ፈልጐም ነው። በዚህ ተቋማዊ አስተሳሰብ በበዛበትና ሰዎች እንደ ግለሰብ ሳይኾን እንደ ቡድን በሚያስቡበት ጊዜ ላይ የሶቅራጥስን ዘመን አይሽሬ የትምህርት መንገድ መቅሰም አስፈላጊ ነገር ሳይኾን አይቀርም፤ ምክንያቱም ሶቅራጥስ ከፖለቲካ ሹመኝነት ይልቅ ራሱን ለፍልስፍና ጥያቄዎች አሳልፎ በመስጠቱ ማንም የማይቀማውን በጎ ዕድልን መርጧልና። እርሱ እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረስ መፈላሰፉን ቀጥሎ የነበረ ቢኾንም ታድያ የአቴና ፖለቲከኞች ግን በተለያየ ሰበብ ችሎት ፊት አቀረቡት፤ በፍልስፍና መስታወት አለማወቃቸውን በማሳየቱ እንደ ወንጀለኛ ለመቆጠር በቃ።
ከቢር (Kabir) በመባል የሚታወቀው የአስራአምስተኛው ክፍለዘመን ታዋቂ የህንድ ባለቅኔ እንደዚህ ብሎ ነበር፡- በዕውር ከተማ ውስጥ መስታውትን እሸጣለሁ (“I sell mirrors in the city of the blind”).
በመጨረሻም የሶቅራጥስ ኅልፈት  ጉዳይ በአቴናውያን ሸንጎ እጅ ለመውደቅ በቃ። ሶቅራጥስ በጊዜው  ተከስሶባቸው ከነበሩት ኹለት ነገሮች መካከል አንደኛው ወጣቶችን በፍልስፍናዊ የመጠይቅ መንገዱ (maieutics) እየተጠቀመ  ከስነምግባር እንዲያፈነግጡ ያደርጋል የሚል ሲኾን፤ ሌላኛው ደግሞ  በእኛ አማልክት አያምንም፤ እንደውም አዳዲስ አማልክትን አስተዋውቋል በሚል ነው። ሶቅራጥስ በእነርሱ የፍርድ ሚዛን ጥፋተኛ እንደኾነ ሲወሰንበት ኹለት አማራጮችን ሰጥተውት ነበር፤ ወይ ሃገራቸውን ለቅቆ እንዲሰደድ አልያም ደግሞ ሄምሎክ የተባለውን መርዝ ጠጥቶ እንዲሞት፤ ሶቅራጥስም መርዝ ጠጥቶ መሞትን መረጠ።
በቀላሉ ለመረዳት እንደሚቻለው የሶቅራጥስ ሞት መንስኤ ሌላ ነገር ሳይኾን ጥያቄ መጠየቁና መፈላሰፉ ብቻ ነበር፡፡ አሁን ላይም ብዙ ጠያቂና አሳቢ ምሁራንን እንጂ ፖለቲከኞች ብቻ የምንፈልግበት ጊዜ ላይ ያለን አይመስለኝም፤ በገሃድ የምናየው ሃቅ ግን በተቃራኒው ነው፡፡

              የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የባይደን አስተዳደር፣ የግብጽ መንግስት በዜጎቹ ላይ የሚፈጽማቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ለማስተካከል እርምጃ እስካልወሰደ ድረስ ሊሰጠው የታቀደው የ130 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ መሰረዙን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባለፈው ማክሰኞ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፣ የአሜሪካ መንግስት የተቃዋሚ አክቲቪስቶች እስራትን ጨምሮ በግብጽ መንግስት እየተፈጸሙ ያሉት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በእጅጉ ስላሳሰቡት ለአገሪቱ ሊሰጥ ካቀደው 300 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላሩን በጊዜያዊነት ለመሰረዝ ወስኗል፡፡
የመብት ተሟጋቾች የአሜሪካ መንግስት በአመቱ ለግብጽ ሊሰጥ ያቀደውን ወታደራዊ እርዳታ ሙሉ ለሙሉ እንዲያስቀር ቢጠይቁም፣ የባይደን አስተዳደር ግን 130 ሚሊዮን ዶላሩን ብቻ ማስቀረቱንና የግብጽ መንግስት የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ውጤታማ ስራዎችን መስራቱን ካረጋገጠ ብቻ ገንዘቡን እንደሚሰጥ ማስታወቁንም  ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ለግብጽ በየአመቱ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ሲሰጥ መቆየቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡


Page 10 of 556

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.