Administrator

Administrator

Saturday, 11 August 2018 10:56

ውሻው

 ሻምበል ባህሩ ገርበብ ብሎ በተከፈተው ፍሬንች ዶር አሻግረው ውጪውን እየተመለከቱ ቁዘማ ላይ ናቸው፡፡ ጥሪ መደበሪያቸው የነበረው ቴሌቪዥን ባይበላሽ ኖሮ፣ ይሄኔ እዚያ ላይ ነበር የሚጣዱት፡፡ ግን ከዚያ ከተረገመ መደበሪያ ማሽን ጋር ከተፋቱ ዓመት ሊሞላቸው ነው፡፡ ፊቱ ላይ ዳንቴሉን ጣል እንዳደረገ፣ እዚያው ኮመዲኖ ላይ ቦታውን እንደያዘ ነው፡፡ ቴሌቪዥኑም የተቀመጡበት ሶፋም የተገዙት ከስድስት ዓመት በፊት ነው፡፡ አንድያ ልጃቸው ብርቅነሽ አረብ አገር በሄደች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በላከችው ገንዘብ ነው እነዚህ ነገሮች የተገዙት፡፡ ወለላቸውን ሊሾ ያደረጉትና ፍሬንች ዶር የገጠሙትም ያኔ ነው፡፡ (በድሆች መንደር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ከታየ፣ ወደ አረብ አገር የሄደች ልጅ መኖሩን የሚያመለክት ነገር ነው)፡፡
ቤታቸውን ቤት፣ ቤት ያሸተተችው ይህች ብርቄ አሁን የለችም፡፡ በአሰሪዋ ተገድላ አፈር ከተጨናት አራት ዓመት ከሦስት ወር ሆኗታል፡፡ ትሩፋቶቿ ብቻ ናቸው አሁን የቀሩት፡፡
ፀሐይዋ አቅሟን አበርትታ ስትጠጋው በራቸው ስር ተኝቶ የነበረው ውሻ ተነስቶ ሱክ ሱል እያለ ሲሄድ ሻምበል ባህሩ በዓይናቸው ሲከተሉ ቆዩና፤ “እኔ እኮ የዚህ ውሻ ነገር አንዳንዴ ግራ ያጋባኛል” አሉ፡፡ የንግግሩ መዳረሻ እጠባቧ ጓዳ ውስጥ እየተንጎዳጎዱ የነበሩትን ባለቤታቸውን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ከወ/ሮ ባዩሽ ግን ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡
“የዚህ የቦቢ ነገር አንዳንዴ በጣም እኮ ነው የሚገርመኝ፤ ዝም ብዬ ሳየው ብዙ ነገሩ በግ እየመሰለኝ ነው፡፡” አሉና ቀጠሉ፡፡ ከአፍታ ዝምታ በኋላ፤ “ፀጉሩ ራሱ የበግ ለምድ እኮ ነው የሚመስለው፡፡” ከውስጥ በኩል ብቻ በጭቃ ወደተመረገው በር አልባ ኩሽና እያመራ ያለው ውሻ ላይ ነው አሁንም ዓይናቸው ያለው፡፡
“ጭራው ራሱ እኮ የቆላ በግ ላት ነው የሚመስለው፡፡” ሌላ ማመሳሰያ ተከተለ፡፡
“አሁንስ ይሄን ውሻ በግ አደረጉት እኮ!” አሉ ባላቸውን በአንቱታ የሚያወሩት ወ/ሮ ባዩሽ እዚያው ጓዳቸው ውስጥ እየተንጎዳጎዱ፡፡
“ምን! አይመስልም ልትይኝ ነው?” አሉ ባል ድምፃቸውን ዘለግ አድርገው፡፡ መልስ ግን አላገኙም፡፡ ውሻው ኩሽናው ውስጥ ገባና ተዘረጋ። እነ ሻምበል ባህሩ ከአራት ጎረቤቶቻቸው ጋር የሚጋሩት ኩሽና ነው፡፡ ለቦቢ ደግሞ ከከረረው የፀሐይ ቃጠሎ የሚሸሸግበት ሁነኛ ታዛው ነች፡፡
“ካልሽ እንደውም አጯጯሁ ራሱ ከሌሎቹ ውሾች የተለየ ነው፡፡ ምን! አይደለም ልትይኝ ነው!”
“አንድ ፊቱን እኮ በግ ነው ሊሉኝ ነው ምንም አልቀረዎት፡፡” አሉ ሚስት ረከቦትና ጀበና አንጠልጥለው ይዘው እየወጡ፡፡
“ቆይ ቢያንስ” አሉ ሻምበል ባህሩ፡፡ ሌላ ትንሽ ዝምታ ሆነ፡፡ “ኧረ’ዲያ!› አሉ ወደ ባለቤታቸው አዘምሞ የነበረውን አንገታቸውን ወደ ውሻው አቅጣጫ እየመለሱ፡፡
ረከቦትና ጀበናውን አስቀምጠው ወደ ጓዳ እየተመለሱ ነው ወ/ሮ ባዩሽ፡፡ የብረት ምጣድ የቆለሉበትን ከሰል ምድጃ ይዘው ተመለሱና፣ የተከበረ ቦታው ላይ አኑረው ተመልሰው ገቡ፡፡
“ባዩ! አንቺ ባዩሽ” እያሉ መጡ፤ የሆኑ ሴትዮ፡፡ ድምፃቸውንም ተከትለው በሩ ላይ ተከሰቱ፡፡
ከፊት ለፊት የተቀበሏቸው ሻምበል ባህሩ ናቸው፡፡
 “እንዴ ሻምበል--- እንዴት ዋልክ?”
“እንዴት ዋልሽ አስካለች? ግቢ፣ አረፍ በይ” እረፍት ጋበዙ፡፡
“ምኑን ተቀመጥኩት ብለህ ነው--”
“አስኩ መጣሽ! እንውጣ አይደል፣ ወይ የኔ ነገር! አቀራርቤው ብሔድ ይሻላል ብዬ እኮ ነው” እያሉ እጣን ማጨሻና የተቋጠረች ትንሽዬ ላስቲክ ይዘው ከጓዳ ወጡ፡፡
“በይ ነይ ውጪ፤ እነ ገነት ከመጡ ቆዩ” አሉ ወ/ሮ አስኩ፡፡
ወ/ሮ ባዩሽ በእጃቸው የያዙትን አስቀመጡና እዚያው ከቡናው ቦታ ጎን የግድግዳውን ጥግ ይዞ የተቀመጠው ኮመዲኖ ላይ የነበረውን ነጠላቸውን አንስተው አዘቀዘቁ፡፡
“ምግብ እንደሆነ ስትመጪ ብለዋል እንግዲህ፡፡ በይ ነይ እንውጣ”
“በል እንግዲህ ሻምበል” አሉና ወ/ሮ አስካለች በሩን ለቀቁ፡፡
“በሉ እሺ!” ሸኟቸው ሻምበል፡፡
ራቅ ብላ የምትታየው ኩሽና ውስጥ የተኛው ቦቢና ሻምበል ባህሩ ብቻ ቀሩ፡፡
“ውሻ ሰውን እየጮኸ ስለሚጠብቀውና በታማኝነት ስለሚያገለግለው ተወደደ እንጂ ከበግ ምንድን ነው የሚለየው? ሰው ደግሞ ስላገለገለው ብቻ ታማኝ ጓደኛ ምናምን እያለ ዝም ብሎ መካብ ይወዳል፡፡ ክቦ ክቦ ሲያበቃ እንደገና ያ አልበቃ ብሎ ውጉዝ በማድረግ ይጠብቀዋል፡፡ ከእነ በግ ለይቶ የሱን ስጋ እርም ማድረግ ምን የሚሉት ነገር ነው እስኪ አሁን፡፡ ፍጡር ፍጡር ነው፡፡ ስጋም ስጋ ነው፡፡ እንደውም ስጋው በጣም መድኃኒትነት አለው ነው የሚባለው፡፡” ይሄ ሁሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ነበር የሚመላለሰው፡፡ ወ/ሮ ባዩሽ ሲመጡ ፊት ለፊት የተቀበላቸው ትሪ ላይ የተከመረ ስጋ ነው፡፡ ከየት የመጣ ስጋ ነው ብሎ መጠየቅ አላስፈለጋቸውም፡፡
“ወዬው ጉድ …. ጉድ!” ሊጮሁ ሁሉ ከጅለው ከአፋቸው ላይ ነው የመለሱት፡፡
“ኤዲያ! ምን እዚህ እንትን ትላለች! ባክሽ ወታደር ቤት እያለን ስንቱን በልተናል፡፡ እነዚህ ቻይናዎቹ ውሾችን እየበሉ ጨረሷቸው ብለሽ የነገርሽኝ ራስሽ አይደለሽ? በቀኖና ታስረን እንጂ እኛስ ምን ለየን? ደሞም በዚህ መርከስ እንደዚያ የሚያደርግ ከሆነ መርከሱ ያዋጣል፡፡ መድኃኒት ነው ደግሞ--”
ወ/ሮ ባዩሽ ምራቃቸውን ቱ … ቱ … እያደረጉ እግዚኦታቸውን ያነበንቡታል፡፡ ከጓዳ ሳሎን፣ ከሳሎን ጓዳ እየተንቆራጠጡ ነው ቱ … ቱ…. ዋቸውን የሚያዘንቡት፡፡
“ይልቅ እምትሰሪልኝ ከሆነ ስሪልኝ፡፡ አለበለዚያ…” ብለው ሳይጨርሱ ባለቤታቸው ተቀበሏቸው፡፡
“ማ እኔ ባዩሽ!” አሉና መፀየፋቸውን በቁጣ እያቀጣጠሉ ተንቦገቦጉ፡፡ ከዚያም ጓዳ ገብተው ጠፉ፡፡
(ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው “ሌላ ዓለም” የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ)

በገጣሚ ሰላማዊት አድማሱ የተገጠሙና በማህበራዊ፣ በአገር፣ በተፈጥሮና በስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ55 በላይ ግጥሞችን ያካተተው “ያረፈደ ዳዴ” የተሰኘ የግጥም ስብስብ ለንባብ በቅቷል፡፡
ግጥሞቹ ከልጅነት ሀሳቦች ጀምሮ እያደጉ የመጡና በውስጧ የሚመላለሱ ጥያቄዎቿን ለመግለፅ የሞከረችበት መሆኑን ገጣሚዋ በመድበሉ መግቢያ ላይ ጠቁማለች፡፡ 86 ገፆች ያሉት መፅሐፉ፣ በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በቅርቡ ከአሜሪካ ለተጣለባት የቀረጥ ጭማሪ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት የወሰነቺው ቻይና፣ ወደ ግዛቷ በሚገቡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ በይፋ ያስታወቀች ሲሆን ሩስያም “ተጨማሪ ማዕቀብ የምትጥይብኝ ከሆነ፣ የአጸፋ እርምጃ እወስዳለሁ” ስትል አሜሪካን ማስጠንቀቋ ተዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ባለፈው ወር 34 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ በምርቶቿ ላይ የጣለባት ቻይና፤ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት በማሰብ ነዳጅ፣ የህክምና ቁሳቁሶችና ኬሚካሎችን ጨምሮ ከአሜሪካ በሚገቡ የተለያዩ ምርቶች ላይ ከነሃሴ ወር መጨረሻ አንስቶ 16 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ25 በመቶ የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ የአገሪቱ የንግድ ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ከቻይና በሚገቡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የቀረጥ ጭማሬ ለማድረግ ማሰቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ቻይናም በምላሹ በአሜሪካ ምርቶች ላይ 60 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የቀረጥ ጭማሪ እንደምታደርግ ማስጠንቀቋን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ ከወራት በፊት ተመርዘው በተገደሉት የቀድሞው ሩስያዊ ሰላይ ሰርጌ ስክራፓል ግድያ ላይ ቀንደኛ ተሳታፊ ነበረች በሚል በሩስያ ላይ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ተከትሎ፣ የሩስያ መንግስት በምላሹ ለአሜሪካ ሲሸጠው የቆየውን የሮኬት ሞተር ምርቱን ሊያቋርጥ እንደሚችል አስጠንቅቋል፡፡
አሜሪካ በሰላዩ ግድያ ላይ ተሳትፎ እንደሌላት በተደጋጋሚ ስታስታውቅ በቆየቺው ሩስያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል የያዘቺውን ዕቅድ የምትገፋበት ከሆነ፣ ሩስያ ስትሸጥላት የነበረውንና አርዲ-180 በመባል የሚታወቀውን የጠፈር መንኮራኩሮች ሞተር ምርቷን ለማቋረጥ እንደምትገደድ የአገሪቱ ፓርላማ የአለማቀፍ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ሊዮኒድ ስላትስኪ ማስታወቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ በትዊትር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ከኢራን ጋር የንግድ ግንኙነት ያላቸው አገራት በአፋጣኝ ግንኙነታቸውን ካላቋረጡ፣ ከአሜሪካ ጋር ያላቸው የንግድ ግንኙነት እንደሚቋረጥ ማስጠንቀቃቸውን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው፡፡

 በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ቫይረስ ወረርሺኝ ለመግታት የሚያስችል የኢቦላ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የአለም የጤና ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ክትባቱ በተለይ ደግሞ ለኢቦላ ቫይረስ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ለሆነ ዜጎች በመሰጠት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቀዳሚነትም በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘውና ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የኪቩ አውራጃ ውስጥ በስራ ላይ ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች መሰጠቱን ገልጧል፡፡
ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ወረርሽኝ ለመግታት የሚደረገው ጥረት አካል የሆነው የክትባት አገልግሎት በስፋት ለአገሪቱ ዜጎች ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የዘገበው ዥንዋ በበኩሉ፤ 3 ሺህ 220 ሰዎችን ለመከተብ የሚያስችል የኢቦላ ክትባት መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በኮንጎ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢ በምትገኘው የኪቩ አውራጃ የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ እስካለፈው ረቡዕ ድረስ 17 ሰዎችን ማጥቃቱ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሌሎች ተጨማሪ 74 የአገሪቱ ዜጎችም በቫይረሱ ተይዘዋል በሚል ተጠርጥረው በህክምና ማዕከላት ውስጥ እንደሚገኙ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ከአገሪቱ መንግስት የጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገሪቱ ታሪክ ለ10ኛ ጊዜ በወረርሽኝ መልክ የተቀሰቀሰውን የኢቦላ ቫይረስ ለመግታት፣ የህክምና ባለሙያዎች ግብረ ሃይል አቋቁሞ ሰፊ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

 5.5 ሚ ዶላር የሚያወጡ 77 የኮንትሮባንድ መኪኖችን አውድመዋል

     የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮዲሪጎ ዱቴሬ ሙስናን ጨምሮ የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽመዋል የተባሉ ከ100 በላይ የአገሪቱ ፖሊሶችን ከድርጊታቸው ካልተቆጠቡ ያለ ምህረት እንደሚገድሉ ከባድ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውና በድምሩ 5.5 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ መኪኖችን በአደባባይ ማውደማቸው ተዘግቧል፡፡
በስልጣን መባለግ፣ የአደንዛዥ ዕጾች ህገ ወጥ ዝውውር፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጠለፋና ዝርፊያን ጨምሮ በተለያዩ የወንጀልና የአስተዳደራዊ ድርጊቶች ክስ የተመሰረተባቸው ከ100 በላይ የሚሆኑ የአገሪቱ ፖሊሶች፣ በመንግስት ይቅርታ እንደተደረገላቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ማክሰኞ በቴሌቪዥን ባደረጉት ንግግር ፖሊሶቹ ለወደፊት በመሰል ተግባራት ላይ ተሰማርተው ከተገኙ ያለ አንዳች ማመንታት እንደሚገድሏቸው አስጠንቅቀዋል፡፡
“በእያንዳንዳችሁ ላይ ዕድሜ ዘመናችሁን በሙሉ እንደ ጥላችሁ እየተከተለ ምን እንደምትሰሩ የሚከታተል ስውር ሰላይ አሰማርቼባችኋለሁ፤ አንዲት ቅንጣት ስህተት ብትፈጽሙ ሰላዩ ከመቅጽበት መረጃ ይልክልኛል፤ ያን ጊዜ እናንተን አያድርገኝ” ሲሉም ጠበቅ ያለ ማስጠንቀቂያ ለፖሊሶቹ ሰጥተዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለፖሊሶቹ ቤተሰቦችም ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ “እነዚህ የውሻ ልጆች ከወንጀል እንዲታቀቡ ብትመክሯቸው ጥሩ ነው፡፡ በኋላ ቤተሰቦቻችን ተገደሉ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጸመ ምናምን እያላችሁ ብታላዝኑብኝ አልሰማችሁም!... ምክንያቱም እንደምገድላቸው አበክሬ አስጠንቅቄያቸዋለሁ!” ማለታቸውን አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የጸረ ሙስና ዘመቻ የጀመሩት ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱቴሬ፣ በኮንትሮባንድ ወደ አገሪቱ የገቡ 76 የቅንጦት መኪኖችንና ሞተር ብስክሌቶችን ባለፈው ሳምንት እሳቸው በተገኙበት በአደባባይ እንዲጨፈለቁ ማድረጋቸውን ሲኤንኤን ዘግቧል። በፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ በቡልዶዘር ተጨፍልቀው እንዲወገዱ የተደረጉት የቅንጦት መኪኖችና ሞተር ብስክሌቶች በድምሩ 5.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጡ የጠቆመው ዘገባው፤ ከተደመሰሱት እጅግ ዘመናዊ መኪኖች መካከል ላምቦርጊኒ፣ መርሴድስ ቤንዝ እና ፖሽ እንደሚገኙበትም አመልክቷል፡፡

 የአርጀንቲና ፓርላማ የአገሪቱ ሴቶች ባረገዙ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ጽንስ ማቋረጥ እንዲፈቀድላቸው የሚደነግገውን ረቂቅ ህግ ውድቅ ማድረጉ በበርካታ የአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ተቃውሞ ቢገጥመውም፣ድጋፋቸውን የገለጹ እንዳሉም ተዘግቧል፡፡
የፓርላማው አባላት በረቂቅ ህጉ ላይ ለ15 ሰዓታት ያህል ክርክር ካደረጉ በኋላ 38 ለ32 በሆነ አብላጫ ድምጽ ህጉ ውድቅ መደረጉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህም የሴቶች መብት ተሟጋች ተቋማትንና በርካታ የአገሪቱ ዜጎችን ማስቆጣቱን ጠቁሟል፡፡
የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን፣ የፓርላማ አባላቱ ህጉን እንዳያጸድቁት ግፊት አድርገዋል፣ ሴቶች ጽንስ የማቋረጥ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል በሚል የመብት ተሟጋቾቹ ተቃውሟቸውን መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፤በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በቦነሳይረስ ጎዳናዎች ላይ በእንባና በቁጣ የታጀበ ተቃውሞ ማድረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ህጉ ውድቅ መደረጉን የተቃወሙ አርጀንቲናውያን የመኖራቸውን ያህል፣ ውሳኔውን ደግፈው በአደባባይ ደስታቸውን የገለጹ የጽንስ ማስወረድ ተቃዋሚ ዜጎች በርካቶች እንደሆኑም ዘገባው ገልጧል፡፡ በቅርቡ የተደረገ ጥናት፤ አብዛኛው የአገሪቱ ዜጋ የጽንስ ማስወረዱን እንደሚደግፍ ለማረጋገጥ መቻሉንም አስታውሷል፡፡
በአርጀንቲና የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ማሬላ ቤልስኪ፤ ረቂቅ ህጉን በተመለከተ ዜጎች የያዙትን አቋም ለመፈተሽ በተደረገው ጥናት፣ 60 በመቶ ያህል ዜጎች ህጉ እንዲጸድቅ እንደሚፈልጉ መግለጻቸውን አስታውሰው፣ ፓርላማው ህጉን ውድቅ ማድረጉ አግባብነት የለውም ሲሉ ተችተዋል፡፡
በአርጀንቲና የጽንስ ማቋረጥ ማድረግ የሚቻለው ሴቶች በአስገድዶ መድፈር ሲያረግዙና እርግዝናው ለእናትየዋ ጤና አስጊ ሲሆን ብቻ እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡

•    ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ምደባ በሚል እየተተቸ ነው
•    በተደጋጋሚ በጥፋት የተነሡ ሓላፊ፣ ለሦስተኛ ጊዜ ተመደቡ
•    በተደጋጋሚ ሕጸጽና ምዝበራ የታገዱት አስተዳዳሪም ተመለሰ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፥ በሙስና፣ በአስተዳደር በደልና
በአሠራር ጥሰት የተካሔደውን ማጣራት ተከትሎ፣ 14 የዋና ክፍል ሓላፊዎች ከቦታቸው ቢነሡም፣ በምትካቸው የተደረገው ምደባ፣ ግልጽነትና አርኣያነት የጎደለው ነው፤ በሚል ቅሬታ አስነሣ፡፡ በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ በተቋቋመው ኮሚቴና የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር
በታዛቢነት በተገኙበት ለአንድ ወር በተካሔደው ማጣራት፣ የአድባራት ካህናትንና ሠራተኞችን አላግባብ ከሥራ በማገድና በማሰናበት የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደፈጸሙ ለቋሚ ሲኖዶስ ሪፖርት የቀረበባቸው የዋና ክፍል ሓላፊዎቹ እንዲነሡ መደረጉ ተገልጿል፡፡ ኾኖም፣ በቦታቸው ከተተኩት ሓላፊዎች መካከል የአንዳንዶቹ ምደባ፣ ከለውጡ ርምጃ ጋራ የማይጣጣም እንደኾነ ለአዲስ አድማስ አስተያየታቸውን የሰጡ አገልጋዮችና ሠራተኞች ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል፣ ሓላፊነታቸውን አላግባብ ተጠቅመው በመዘበሩት የቤተ ክርስቲያኒቱ ገንዘብ ከፍተኛ የግል ሀብት
በማፍራትና አስተዳደራዊ በደል በማድረስ የታወቁ ግለሰቦች በተተኪነት መመለሳቸው፣ለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ ነው፤ አገልጋዩንም ዋስትና የሚያሳጣ ነው፤ ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል - ሠራተኞቹ፡፡
“በሹም ሽረቱ የግብር ይውጣ ሥራ ተሠርቷል፤” የሚሉት ሠራተኞቹ፣ በ2007 ዓ.ም. በሀብት ብክነት፣
ሙስናና ሓላፊነትን በአግባቡ ካለመወጣት ጋራ ተያይዞ በቅዱስ ፓትርያርኩ መመሪያ ከሓላፊነታቸው ተነሥተውማጣራት እንዲካሔድባቸው የተወሰነባቸው የሒሳብና በጀት ዋና ክፍል ሓላፊ ሊቀ ጠበብት ኤልያስ ተጫነ፣ በአዲሱ ምደባ በዚያው ዋና ክፍል ለ3ኛ ጊዜ መሾማቸውን በመጥቀስ ምደባው ግልጽነትና አርኣያነት የሌለው ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ “በቂ ጥናት ሳይደረግና መመዘኛ መስፈርቱ ሳይታወቅ ወደ ሓላፊነት የመጡ ሰዎች ናቸው፤” የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ከተተኩት መካከል፣ ከቀድሞዎቹ ጋራ የጥቅም ግንኙነት እንደነበራቸው የሚወቀሱም
በመኖራቸው፣ የሀገረ ስብከቱን የለውጥ ርምጃ የሚመጥን አፋጣኝ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
በቅርቡ ተካሒዶ በነበረው የቅዱስ ሲኖዶስ አስቸኳይ ስብሰባ፣ በሀገረ ስብከቱ አስተዳደራዊ መዋቅር ውስጥ፣
ሙስናን፣ ጥቅመኝነትንና የመልካም አስተዳደር ችግርን ለዘለቄታው የሚፈታ የአደረጃጀት ለውጥ እንዲደረግ
መግባባት ላይ ቢደረስም፣ የአስተዳደር ሓላፊዎቹ ምደባ ሒደቱን የሚያራምድ እንዳልኾነ ጠቁመዋል፡፡
ጥቅመኝነትን፣ ደላላነትንና ኑፋቄን ለማስወገድ ቃል ለገቡት የሀገረ ስብከቱ የወቅቱ ሥራ አስኪያጅም ፈተና
እንደሚኾንባቸው ቅሬታ አቅራቢዎቹ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ ከቦታቸው በተነሡት የዋና ክፍል ሓላፊዎች፣ አላግባብ ከሥራቸው ታግደውና ተሰናብተው
በአቤቱታ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲጉላሉ የቆዩት ካህናትና ሠራተኞች፣ ደረጃቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ ወደ
ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን
በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ ታግደው በቆዩባቸው እስከ ሁለት ዓመታት ገደማ ያልተከፈላቸው
ወርኀዊ ደመወዝም ተሰልቶ እንዲከፈላቸው መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ኾኖም፣ ከታገዱት ሠራተኞች መካከል፥ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥሰት፣ በገንዘብ ምዝበራና በከፋ ምግባር
ተደጋጋሚ ጥፋት በመፈጸም ከሥራና ከደመወዝ እንዲታገዱ፣ ጉዳያቸውም በሊቃውንት ጉባኤ እንዲጣራ በቋሚ
ሲኖዶስ ውሳኔ የተላለፈባቸው ግለሰብ ወደ ደብር አስተዳዳሪነታቸው መመለሳቸው ተጨማሪ ቅሬታ ማስነሣቱ
ታውቋል፡፡ ከሃይማኖት ሕጸጽና ከሙስና ነጻ መኾናቸው እየታየ ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተሰጠውን አቅጣጫ
እንደሚፃረርም ጠቁመዋል፡፡ እንዲህ ያለው አሠራር፣ በውሳኔው አስተማሪነት ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ
በቀላሉ የሚታይ ባለመኾኑ በአፋጣኝ ሊጤን እንደሚገባም አሳስበዋል - ተቺዎቹ፡፡
 


 ከጎረቤት አገራት በህገወጥ መንገድ እየገቡ ዜግነት የሚያገኙ ስደተኞች ያማረሩት የህንድ መንግስት፣ ሰሞኑን በወሰደው እርምጃ አሳም በተባለው የአገሪቱ ግዛት የሚኖሩ 4 ሚሊዮን ሰዎችን ዜግነት መንጠቁን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ ነጻነቷን ካወጀችበት እ.ኤ.አ ከ1971 አንስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ባንግላዴሻውያን ወደ ግዛቱ በህገ ወጥ መንገድ እንደገቡ የጠቆመው የህንድ መንግስት፤ በቅርቡ ባደረገው ምርመራ ዜግነታቸውን የሚያረጋግጥ ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው 4 ሚሊዮን ሰዎች ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
እነዚሁ 4 ሚሊዮን ሰዎች ህንዳውያን መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የሰነድ ማስረጃ እስከ መስከረም ወር መጀመሪያ ድረስ ለሚመለከተው የመንግስት አካል በማቅረብ ዜግነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል ያለው ዘገባው፤ እስከዚያው ድረስ ግን ህገወጥ ስደተኛ ተብለው እንደማይመዘገቡ ቃል እንደተገባላቸው አመልክቷል፡፡

 ታዋቂው ፎርብስ የ2018 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ 100 ዝነኞች ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሜሪካዊው የከባድ ሚዛን ቦክስ ሻምፒዮናው ሜይዌዘር በ285 ሚሊዮን ዶላር ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
የኦስካር ተሸላሚው ታዋቂው የፊልም ተዋናይ ጆርጅ ክሉኒ ባለፉት 12 ወራት ከታክስ በፊት 239 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የሪያሊቲ ሾው አዘጋጇ ኬሊ ጄኔር በ166.6 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ፎርብስ ለ22ኛ ጊዜ ይፋ ባደረገው አመታዊው የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት የዘንድሮ 100 ከዋክብት በድምሩ 6.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ዝነኞቹ ከ17 የአለማችን አገራት የተውጣጡ ናቸው ተብሏል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ከፍተኛ ተከፋይ የአለማችን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ ከስፖርቱ ዘርፍ የተመረጡትን ክርስቲያኖ ሮናልዶና ሊዮኔል ሜሲን ጨምሮ፣ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በሚዲያና በሌሎች የተለያዩ መስኮች የሚታወቁ ከዋክብት መካተታቸውም ተነግሯል፡፡

 ሳምሰንግ በሽያጭ ሲመራ፣ አፕል ቦታውን ለሁዋዌ አስረክቧል

    ታዋቂው የቻይና ኩባንያ ሁዋዌ በአለማችን የስማርት ሞባይል ቀፎዎች ገበያ በርካታ ምርቶችን በመሸጥ በአፕል ተይዞ የቆየውን የ2ኛነት ደረጃ መረከቡን ሲኤንቢሲ ኒውስ ዘግቧል፡፡
የቻይናው ሁዋዌ እስካለፈው ሰኔ በነበሩት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ በአለማቀፍ ደረጃ 54.2 ሚሊዮን ሞባይሎችን መሸጡንና በአለማቀፍ ገበያ ውስጥ የ15.8 በመቶ ድርሻን መያዙን የጠቆመው ዘገባው፤ የታዋቂው አይፎን አምራች የሆነው አፕል ኩባንያ በአንጻሩ 41.3 ሚሊዮን ሞባይሎችን በመሸጥ የ12.1 በመቶ የገበያ ድርሻ መያዙን አመልክቷል፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ ኩባንያ በአለማቀፍ የሞባይል ሽያጭና የገበያ ድርሻ መሪነቱን ይዞ መቀጠሉን የጠቆመው ዘገባው፤ በተጠቀሱት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ 71.5 ሚሊዮን የተለያዩ አይነት የሞባይል ቀፎዎችን በመሸጥ በአለማቀፉ የሞባይል ገበያ ውስጥ የ20.9 በመቶ ድርሻውን መያዙን ገልጧል።