Administrator

Administrator

 በኢራቅ የአይሲስ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ብቻ ከምዕራባዊ ሞሱል ለማምለጥ የሞከሩ ከ231 በላይ ሰዎችን መግደሉ የተነገረ ሲሆን፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸመው ጥቃት 70 ያህል ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል፡፡
ታጣቂዎቹ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከአይሲስ ይዞታ በማምለጥ በኢራቅ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች ለማምለጥ ሞክረዋል የተባሉትን ከ231 በላይ ኢራቃውያንን መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ዛንጂሊ በተባለቺው የምዕራባዊ ሞሱል አካባቢ ሰሞኑን በተከፈተ የአየር ጥቃት እስከ 80 ያህል ኢራቃውያን መገደላቸውን የሚጠቁም መረጃ ማግኘቱን የገለጸው ተመድ፤ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በአሮጌዋ የሞሱል ከተማ ከ200 ሺህ በላይ ኢራቃውያን የስቃይ ኑሮ እየገፉ እንደሚገኙም ተመድ አመልክቷል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የአልሻባብ ወታደሮች ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶችን ማቁሰላቸውን የዘገበ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በቅርብ አመታት ታሪክ የተፈጸመው የከፋ ጥቃት ነው በተባለው በዚህ የአልሻባብ ጥቃት ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ አንገታቸው ተቀልቶ የተገደሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡  
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው፤ ቦኮሃራም በናይጀሪያዋ ሜዱጉሪ ከተማ ከትናንት በስቲያ በፈጸመው የተኩስና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 11 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡

ህንድ በጠፈር ምርምር ቴክኖሎጂ ታሪኳ ከሰራቻቸው ሮኬቶች ሁሉ በግዙፍነቱና በክብደቱ አቻ እንደማይገኝለት የተነገረውንና በክብደት ከአለማችን ሮኬቶች ሁለተኛውን ደረጃ የሚይዘውን ጂኤስኤልቪ ማርክ 3 የተሰኘ ሮኬት በተሳካ ሁኔታ ወደ ጠፈር ማምጠቋን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
640 ቶን ክብደት እንዳለው የተነገረለት ይህ ግዙፍ ሮኬት፣ በጠፈር ምርምር ዘርፍ ለምታመጥቃቸው እጅግ ከባድ ሳተላይቶች በብዛት የአውሮፓ አገራት ሮኬቶችን ስትጠቀም ለነበረቺው ህንድ ትልቅ እመርታ መሆኑንና ከጥገኝነት በመጠኑም ቢሆን እንደሚያላቅቃት ተነግሯል፡፡
ህንድ በአለማቀፉ የሳተላይት ማምጠቅ ገበያ ያላትን ድርሻ ለማሳደግ በስፋት እየሰራች እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ ለአውሮፓ አገራት ሮኬቶች ከፍተኛ ክፍያ ከመክፈል የሚያድናትን ይህን ግዙፍ ሮኬት ሰርታ ለማምጠቅ መቻሏም ጥረቷ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የሚያመለክት ነው ብሏል፡፡
የ43 ሜትር ቁመት ያለው ግዙፉ የህንድ ሮኬት ከአለማችን በክብደቱ ሁለተኛው እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤በክብደት ክብረወሰኑን የያዘው የናሳው ሳተርን 5 ሮኬት እንደሆነም አክሎ ገልጧል፡፡
አገሪቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ በጠፈር ምርምሩ መስክ ጉልህ የሚባሉ ውጤቶችን እያስመዘገበች ነው ያለው ዘገባው፣ ለውጤታማነቷ ማሳያ ይሆናሉ ብሎ ከጠቀሳቸው ስኬታማ ተግባራት መካከልም፣ ከወራት በፊት ወደ ማርስ ያደረገቺው የጠፈር ጉዞና በአንድ ተልዕኮ ከ100 በላይ ሳተላይቶችን ያመጠቀችበት አጋጣሚዎች እንደሚገኙበት አስታውሷል፡፡

    ሳኡዲ አረቢያንና ግብጽን ጨምሮ ስድስት የአረብ አገራት፣ አሸባሪ ቡድኖችን በመደገፍ ሽብርተኝነትና ጽንፈኝነት እንዲስፋፋ፣ አካባቢውም እንዳይረጋጋ አድርጋለች በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን በሳምንቱ መጀመሪያ በይፋ አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ ኳታር አይሲስና አልቃይዳን ጨምሮ ለተለያዩ አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድኖች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ቢወነጅሏትም፣ አገሪቱ ግን ውንጀላውም ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማቋረጣቸው መሰረተ ቢስና በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ ናቸው ስትል ምላሽ መስጠቷን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባህሬንና ሳኡዲ አረቢያ ብሄራዊ ደህንነታቸውን ከሽብርተኝነትና ከጽንፈኝነት ለመከላከል በሚል ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ባለፈው ሰኞ ማለዳ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን፣ በነጋታውም የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ፣ ግብጽ፣ የመንና ሊቢያ ተመሳሳይ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ አገራቱ የየብስና የባህር ድንበርን እንዲሁም የአየር ክልልን ከመዝጋት ባለፈ፣ አምባሳደሮቻቸውንም ከዶሃ አስወጥተዋል፡፡
የአረብ አገራቱ ተማክረው ፊት ለነሷት፣ ተባብረው ላገለሏት ኳታር መጪው ጊዜ እጅግ ፈታኝና ዘርፈ ብዙ ቀውስ የምታስተናግድበት የፈተና ወቅት እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡ ቀውሱ ከእለት ጉርስ እስከ ፖለቲካዊ ቀውስ ስር ሰድዶ አገሪቱን የከፋ አደጋ ውስጥ ሊከታት እንደሚችል እየተነገረ ሲሆን፣ የአገራቱ ውሳኔ ይፋ በተደረገ በሰዓታት ዕድሜ ውስጥ ነበር ይህንን እውነታ የሚያጠናክሩ አደገኛ ክስተቶች መታየት የጀመሩት፡፡
ከዕለት ጉርስ እስከ ስርዓት ለውጥ?…
2.7 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ኳታር ምንም እንኳን ቢዝቁት የማያልቅ የነዳጅ ባህር የታደለች ባለጸጋ አገር መሆኗ ባይታበልም፣ የምግብ ዋስትና ወሳኝ ክፍተቷ እንደሆነ ይነገራል፡፡ አገሪቱ 40 በመቶ ያህሉን የምግብ ፍጆታዋን ከሳኡዲ አረቢያ ጋር በሚያዋስናት የየብስ ድንበር በኩል ነበር በየዕለቱ በመቶዎች በሚቆጠሩ ከባድ ተሸከርካሪዎች እያስጫነች በገፍ  የምታስገባው፡፡
የሰሞኑ ድንገተኛ ውሳኔም ታዲያ፣ ይህ ወሳኝ የምግብ አቅርቦት የሚገባበትን የሳኡዲ አረቢያ ድንበር የሚዘጋ በመሆኑ፣ የምግብ እጥረት በመፍጠር አገሪቱንና ህዝቧን የከፋ ችግር ውስጥ ይጥላቸዋል እየተባለ ነው፡፡ የአገራቱን ውሳኔ ተከትሎ መጪው ጊዜ ያሰጋቸው በርካታ የኳታር ዜጎች፣ ለክፉ ቀን የሚሆን የምግብና የውሃ ስንቅ ለመያዝ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ ሱፐር ማርኬቶች በመጉረፍ ላይ እንደሚገኙም ዶሃ ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ ገልጧል፡፡
የምግብ አቅርቦቱ ወደ አገሪቱ የሚገባበት ይህ የየብስ ትራንስፖርት መስመር ከመዘጋቱ ጋር በተያያዘም፣ በኳታር የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ይከሰታል፤ የህዝቡ የዕለት ከዕለት ኑሮም ወደ ቀውስ ያመራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የአገሪቱ መንግስት ግን የምግብ እጥረት እንደማይከሰት በመግለጽ ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ኑሯቸውን እንዲገፉ ለዜጎቹ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ከኳታር ጎን የቆመቺው ኢራንም የተባለው የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለማድረግ አስቸኳይ የምግብ እህል ወደ ኳታር መላኳ ተነግሯል፡፡ የቱርክ ባለሃብቶችም ለኳታር የምግብና የውሃ አቅርቦት ለማድረስ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡
አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኞች ግን፣ ከምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊቀሰቀስ የሚችለው የህዝብ ምሬት ከዕለታዊ የፍጆታ ጥያቄነት አልፎ የስርዓት ወይም የመንግስት ለውጥን ወደ መሻት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴና ጫና ከፍ ሊልና አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ሊያስገባት እንደሚችል አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
አደጋ ላይ የወደቀ ንግድና ኢንቨስትመንት
እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ የአቡ ዳቢው ኢትሃድ ኤርዌይስ እና የዱባዩ ኤሜሬትስ አየር መንገድ ከማክሰኞ ማለዳ ጀምሮ ወደ አገሪቱ መዲና የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉ ማቆማቸውን አስታውቀዋል፡፡
አገራቱ በዚህም አላበቁም፡፡ የአየር ክልላቸውን ለታዋቂው የአገሪቱ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ ዝግ ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡ በየቀኑ ወደ እነዚህ አገራት በርካታ በረራዎችን ሲያደርግ የነበረውና በትርፋማነቱ የሚታወቀው ኳታር ኤርዌይስ፣ በአረብ አገራቱ ውሳኔ ሳቢያ በታሪኩ እጅግ የከፋውን ኪሳራ እንዳያስተናግድም ተሰግቷል፡፡ የአገራቱ ውሳኔ በኳታር ይሰሩ የነበሩ ታላላቅ ኩባንያዎች ስራቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ እየተነገረ ሲሆን፣ ታዋቂው የሳኡዲ የእግር ኳስ ቡድን አል አህሊ ከኳታር ኤርዌይስ ጋር የነበረውን የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ማፍረሱም ተዘግቧል፡፡
በኳታር እየተከናወኑ ከሚገኙ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የ2022 የአለም የእግር ኳስ ዋንጫን ሊያስተናግዱ የተወጠኑት ግዙፍ ስታዲየሞች፣ ወደብና የምድር ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት መስመር ግንባታ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ኮንክሪትና ብረትን ጨምሮ ለእነዚህ ታላላቅ የግንባታ ፕሮጀክቶች በግብዓትነት የሚውሉት ወሳኝ ጥሬ ዕቃዎች ከጎረቤት ሳኡዲ በየብስና በውሃ ትራንስፖርት የሚገቡ መሆናቸውን የጠቆመው ቢቢሲ፤ የየብስ ድንበሩ መዘጋቱ እንደ ምግቡ ሁሉ በግንባታ ግብዓቶች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ዕጥረትና የዋጋ ንረት እንዲከሰት እንዲሁም ግንባታዎቹ እንዲጓተቱ ምክንያት መሆኑ እንደማይቀር ዘግቧል፡፡
የሰው ሃብት ቀውስ
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ በግዛቷ ውስጥ የሚገኙ የኳታር ዲፕሎማቶች በ48 ሰዓታት ውስጥ እንዲለቅቁ አዝዛለች፡፡
ሳኡዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና ባህሬንም ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማቋረጥ መወሰናቸውን ከማስታወቃቸው ባለፈ፣ በኳታር የሚኖሩ ዜጎቻቸው በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ ማስቀመጣቸው ተነግሯል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ በአገራቱ ውስጥ የሚኖሩ ወይም ለጉብኝት የመጡ የኳታር ዜጎችም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ እንዲወጡ ቀነ ገደብ ተቀምጦላቸዋል፡፡  በኳታር 180 ሺህ ያህል ግብጻውያን እንደሚኖሩና አብዛኞቹም ምህንድስናና ህክምናን በመሳሰሉ ቁልፍ የሙያ መስኮች ላይ የተሰማሩ እንደሆኑ የዘገበው ቢቢሲ፤ ግብጽም የእነ ሳኡዲን ፈለግ ተከትላ ዜጎችን የማስወጣት እርምጃ ከወሰደች በኳታር የሚፈጠረው የባለሙያ እጥረት ቀውስ እጅግ የከፋ እንደሚሆን መነገሩን ገልጧል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ የፊሊፒንስ መንግስት የአገሪቱ ዜጎች ወደ ኳታር እንዳይሄዱ የሚከለክል ጊዚያዊ እግድ ባለፈው ረቡዕ ማውጣቱን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይሄም ሆኖ ግን የአገሪቱ መንግስት በኳታር በተለያዩ የስራ መስኮች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ከ200 ሺህ በላይ ዜጎቹን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የያዘው እቅድ እንደሌለም ጠቁሟል፡፡
 ኳታርን ማግለሉ ወደ አፍሪካም ተዛምቷል
በእነ ሳኡዲ የተጀመረውን የማግለል እርምጃ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆን ከኳታር ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጣቸውን የሚያስታውቁ አዳዲስ አገራት ብቅ እያሉ ነው፡፡ የአረብ ሊግ አባል የሆነቺዋ ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ሞሪታኒያ ኳታርን፣ እንዳንቺ ካለው የሽብር ደጋፊ ጋር ህብረት የለኝም፤ በቃሽኝ በማለት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ማቋረጧን በይፋ አስታውቃለች፡፡
ሴኔጋልም እነ ሳኡዲ በኳታር ላይ የወሰዱት እርምጃ አግባብ ነው፣ እኔም ከዛሬ ጀምሮ ከኳታር ጋር ያለኝን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጫለሁ በማለት ባለፈው ረቡዕ አቋሟን የገለጸች ሲሆን፣ በኳታር የሚገኘው አምባሳደሯ በአፋጣኝ ወደ አገሩ እንዲመለስ ጥሪ አስተላልፋለች፡፡
ቻድ በበኩሏ ከትናንት በስቲያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ባወጣቺው መግለጫ፤ የኳታርን ቀውስ ለመፍታት አገራቱ የውይይትን አማራጭ እንዲወስዱ ብትመክርም፣ አምባሳደሯን ከኳታር እንዲመለሱ ከማድረግ ወደ ኋላ አላለቺም፡፡
ሌላኛዋ አፍሪካዊት አገር ጋቦንም ከትናንት በስቲያ ባወጣቺው መግለጫ፤ ኳታርን “ለሽብርተኝነት ድጋፍ የምትሰጥ ያለመረጋጋት አጋር” ስትል ለመካከለኛው ምስራቅ ሰላም ማጣት ምክንያት በማድረግ አውግዛታለች፡፡
የመታረቅ ዕድል
ማግለል መፍትሄ አይደለም የሚል አቋም የያዙት ቱርክንና ኩዌትን የመሳሰሉ አገራት፤ እነ ሳኡዲ ከኳታር ጋር ያላቸውን ችግርና አለመግባባት በውይይት እንዲፈቱና ያቋረጡትን ግንኙነት እንዲቀጥሉ ጥሪ እያቀረቡ ሲሆን የኩዌቱ ኢምር ሼክ ሳባህ አል አህመድአል ሳባህም ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከርና መፍትሄ ለመሻት ባለፈው ማክሰኞ ወደዚያው ማቅናታቸው ተዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በአንጻሩ፣ ኳታርን ማግለል የሽብርተኝነት ሰቆቃ ፍጻሜ ጅማሬ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው በማለት እነ ሳኡዲ የወሰዱትን እርምጃ ማድነቃቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡ በነጋታው ግን፣ ትራምፕ ለኳታሩ ኢሚር ሼክ ታሚም ቢን ሃመድ አል ጣኒ ስልክ በመደወል፣ ከአገራቱ መካከል የተከሰተውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሜሪካ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸውላቸዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ኳታር በአካባቢው አገራት የደረሰባት መገለል እንዲያበቃ ከፈለገች፣ ከፍልስጤሙ “ሃማስ” እና ከግብጹ “ሙስሊም ብራዘርሁድ” ቡድኖች ጋር ያላትን ግንኙነት ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ማቋረጥ ይገባታል ብሏል፡፡
የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ሞሃመድ ጋርጋሽ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከኳታር ጋር ወደነበራት የቀድሞ መልካም ግንኙነት የመመለስ አማራጭን ማጤን የምትጀምረው የኳታር መንግስት ከሽብርተኛና ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ያለውን ግንኙነት በተጨባጭ እንደሚያቆም የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ፍኖተ ካርታ ሲያቀርብ ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የዘንድሮ ተመራቂ በሆኑት ዮሴፍ ከተማ የተፃፈው “እሬቶ” የተሰኘ መፅሐፍ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ይመረቃል፡፡ በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ደራሲያንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ደራሲው ገልፀዋል፡፡በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ታዋቂ ደራሲ በመፅሀፉ ላይ ዳሰሳ ያቀርባል የተባለ ሲሆን ደራሲያንና ገጣሚያን ስራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ የዝግጅቱ አስተባባሪ ይፍቱ ስራ ፕሮሞሽን ገልጿል፡፡ መፅሐፉ ታሪክ ቀመስ ልብ ወለድ ሲሆን ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመዳሰስ መረጃ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በ284 ገፆች የተመጠነው መፅሀፉ፣ በ65 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 እናት የማስታወቂያ ድርጅት ከወመዘክርና ከጀርመን የባህል ማዕከል ጋር በመተባበር “በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ›› በሚል ርዕስ በአርኖልድ ዲባዲ ተፅፎ በገነት አየለ ወደ አማርኛ በተመለሰው መፅሐፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የታሪክ ባለሙያው አበባው አያሌው እንደሆነ የገለፀው አዘጋጁ፤ ፍላጎት ያለው ሁሉ በውይይቱ ላይ እንዲካፈል ጋብዟል፡፡

  ታዋቂዋ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ እና በማደጎ የምታሳድጋት የ12 አመቷ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ታዳጊ ዘሃራ፣ የማደጎ ስምምነት የፈጸሙበትን 12ኛ አመት ለማክበር በመጪው ወር መጀመሪያ ላይ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ሆሊውድላይፍ ድረገጽ ዘግቧል፡፡
አንጀሊና ጆሊ እና የቀድሞው ፍቅረኛዋ ብራድ ፒት ከ12 አመታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በወቅቱ የስድስት ወር ጨቅላ የነበረቺውን ዘሃራን በማደጎ ወደ አሜሪካ ይዘዋት መሄዳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ አንጀሊና የማደጎውን 12ኛ አመት ምክንያት በማድረግ ዘሃራን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትውልድ አገሯ ይዛ ለመምጣት መዘጋጀቷን አመልክቷል፡፡
አንጀሊና ከዘሃራ በተጨማሪ ማዶክስ የተባለ የ15 አመት ካምቦዲያዊና ፓክስ የተባለ የ13 አመት ቬትናማዊ በማደጎ እንደምታሳድግ የጠቆመው ዘገባው፤ የማደጎ ልጆቿ የትውልድ አገራቸውን እንዳይረሱ፣ የወላጆቻቸውን ባህልና ማንነት ጠንቅቀው እንዲያውቁ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እንደምታደርግና በዚህም ብዙዎች እንደሚያደንቋት ገልጧል፡፡
ተዋናይቷ ከዚህ በፊትም ማዶክስንና ፖክስን ወደ ትውልድ አገራቸው በመውሰድ ከአገራቸው ባህልና ማንነት ጋር እንዲተዋወቁ ማድረጓንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ክንዱ ላይ ክርኑን በጣም ያመውና ለጓደኛው “.ምን ባደርግ ይሻለኛል?..” ይልና ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኛውም “..አንድ ዋሻ ውስጥ የሚኖር አዋቂ ሰው አለ፡፡ እሱ ጋ ሄደህ ችግርህን ብታስረዳው መፍትሔ ይፈልግልሃል..” አለው፡፡
“ስንት ያስከፍለኛል?”
“አስር ብር ብቻ፡፡”
“ምን ምን ዓይነት ምርመራ ያደርግልኛል?” ሲል ጠየቀ ታማሚው፡፡
“የሽንት ምርመራ ብቻ ነው የሚያደርግልህ፡፡ ዋሻው በራፍ ላይ በዕቃ ሽንትህን ታስቀምጣለህ፡፡ እሱ ይደግምበታል፡፡ ይመሰጥበታል፡፡ ከዚያ መድኃኒቱን ይነግርሃል፡፡ አለቀ፡፡”
ታማሚው ጓደኛው እንዳለው ዋሻው ደጃፍ ላይ ሽንቱን በዕቃ ያኖርና አብሮ አስር ብር ያስቀምጣል፡፡
በሚቀጥለው ቀን ወደ ዋሻው ደጃፍ ሲሄድ አንድ ማስታወሻ ተጽፎለት ያገኛል፡፡ እንዲህ
.. በሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ምክንያት ክንድህ ላይ ክርንህን ተጎድተሃል፡፡ ስለዚህ ክንድህን ለብ ያለ ውኃ ውስጥ ከተህ ታቆየዋለህ፡፡ ከባድ ዕቃ አታንሳ፡፡ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይሻልሃል ..
ታማሚው ማታ ቤቱ ገብቶ ነገሩን ሲያስበው፤ “የገዛ ጓደኛዬ ቢሆንስ ማስታወሻውን የጻፈው? ከዚያ አስር ብሬን ወስዶ አታሎኝ ቢሆንስ?” ደጋግሞ አሰበበትና በሚቀጥለው ቀን ወደ ዋሻው ደጃፍ ይሄዳል፡፡ አሁን ግን የራሱን የሽንት ዕቃ ሳይሆን የሚስቱንና የወንድ ልጁን የሽንት ምርመራ ናሙና፣ የውሻውን ፀጉርና የቧምቧ ውሃ ደባልቆ፤ በአንድ ዕቃ ዋሻው ደጃፍ ላይ ከአስር ብር ጋር ያስቀምጣል፡፡
ከዚያም ወደ ጓደኛው ይሄድና እንደገና ወደ ዋሻው ደጃፍ ሄዶ፣ የሽንት ናሙና በትልቅ ብልቃጥ እንዳስቀመጠ ይነግረዋል፡፡ ጓደኛውም፤ “አሁን ደግሞ ለምን አስቀመጥክ?”. ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
“ጤንነት አይሰማኝምና እንዳለፈው ጊዜ መፍትሔ እንዲሰጠኝ ፈልጌ ነው” ይለዋል፡፡ ጓደኝዬውም፤ “ጥሩ፡፡ እንግዲያው ነገ ሄደህ የምርመራውን መልስ ካወቅህ በኋላ እናወራለን..” ብሎት ይለያያሉ፡፡
በነጋታው ታማሚው ሰው ወደ ዋሻው ደጃፍ ሲሄድ እንደጠበቀው ሌላ ማስታወሻ ያገኛል፡፡ እንዲህ የሚል ጽሑፍ ፡- .. “የቧምቧህ ውሃ በጣም ወፍራምና ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያቀጥነውና የሚያሳሳው ኬሚካል ግዛ፡፡
ውሻህ የሚያሳክክ ቅንቅን አለበት፡፡ ስለዚህ ቪታሚን ገዝተህ ስጠው፡፡ ወንድ ልጅህ የአደንዛዥ ዕጽ ተጠቂ ሆኗል፡፡ ስለዚህ ከዚህ አባዜ እንዲላቀቅ ወደ ማገገሚያ ማዕከል ወስደህ ለተወሰነ ጊዜ እዚያ እንዲቆይ አድርገው፡፡ ሚስትህ አርግዛለች፡፡ ያውም መንታ ልጆች ነው ያረገዘችው፡፡ ልጆቹ ግን ያንተ አይደሉም፡፡ ስለዚህ ጠበቃ ግዛ፡፡ እንዲህ ስትጠራጠርና በራስህ ስትቀልድ የክርንህ ህመም እየባሰብህ ነው የሚሄደው፡”
*    *    *
በአጠራጣሪ ሁኔታ ውስጥ መኖርና ኮስተር ብሎ ጉዳይን አለመጨበጥ ሌላ ጉድ ያሰማል፡፡ ..አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል.. እንዲሉ፡፡
በአጠራጣሪ ዓለም እየኖርን ዕቅዶች ስናወጣ፣ ዕቅዶችም አጠራጣሪ ይሆናሉ፡፡ ለዚያውም ነገን በማናውቅበት ዓለም፡፡ ውዲ አለን የተባለው ኮሜዲያን “..ሰው ሲያቅድ እግዚሃር ይስቃል..” (when man plans God laughs እንዲል) ታዋቂው ሳይንቲስት አልበርት አነስታይን ደግሞ “በተጨባጭ ዓለም ውስጥ እየኖረ ..ዕውነትና ዕውቀት ላይ ፍርድ ሰጪ ዳኛ ነኝ የሚል ሰው፤ መርከቡ፤ አማልክቱ ሲስቁ ትንኮታኮታለች.”. ይለናል፡፡ ማንም ፍፁም ነኝ አይበል ነው ነገሩ፡፡ በገዢና በተገዢ መካከል ያለው ግንኙነት ፍፁምና ንፁህ ስምምነትና መተማመን መሆን አለበት ብሎ ግትር ማለት ቢያዳግትም፣ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባዋል፡፡ በተለይ ..እናቱ የሞተችበትም፣ እናቱ ወንዝ የወረደችበትም እኩል የሚያለቅስበት አገር.. ከሆነ አለመተማመንና መጠራጠር የታከለበት እንደሆነ በቡሃ ላይ ቆረቆር ይሆናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን፡፡
ቲ ኤስ ኢሊየት ያለንን አለመርሳት ነው ፡- Oh my soul…be prepared for him Who knows how to ask questions ..ነብሴ ሆይ  ተዘጋጂ አደራ አውጪኝ ከዛ ጣጣ  ጥያቄ መጠየቅ የሚችል ሲመጣ.. እንደማለት ነው፡፡)
ዛሬ በሀገራችን ስለተጠያቂነት ብዙ ይነገራል፡፡ ከዚህ ተነጣጥሎ የማይታይ ግን ቸል የተባለው ጉዳይ  ..ጠያቂውስ ማነው?.. የሚለው ነው፡፡ ታሪክ፣ ጊዜና ህዝብ ናቸው ቢባል መልሱን ይጠቀልለዋል፡፡ እንጠየቃለን ብለ አለመስጋት ማናለብኝን ያስከትላል፡፡ ማናለብኝ ደሞ ኢ - ዲሞክራሲያዊና ኢ- ፍትሐዊ ነው፡፡
ጥርጣሬ አገር ጐጂ እክል ነው፡፡ እርስ በርስ አለመተማመንና ኑሮን አለማመን ያስከትላልና፡፡ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም መረጋጋትን ያጫጫል፡፡ የሩሲያው መሪ ጆሴፍ ስታሊን፤ የጥርጣሬ መናኸሪያ ነበር ይባላል። ሁሉንም ሰው ሌባና አጭበርባሪ፤ ሁሉንም ሰው ክፉና መጥፎ አድርጐ የማየት ባህሪ ነበረው፡፡ ሁሉን በመጥፎ ስለሚፈርድም ራሱን ጥሩ አድርጐ ይደመድማል፡፡ መጥፎዎቹ ሁሉ በእኔ ላይ ይነሳሉ የሚል ጥርጣሬ ይወርረዋል፡፡ ስለዚህም ብዙ ሰው ላይ ግፍ እንዲፈጽም ይገደዳል፡፡ ፀረ - ዲሞክራሲ ተግባራቱ በይፋ ታይተዋል፡፡ ሩሲያ ለሆነችው ሁሉ ትልቅ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡
አንድ ፀሐፊ እንዳለው፤  ..ዕድገት ማለት ለውጥ ማለት ነው፡፡ ለውጥ ቢያዋጣም ባያዋጣም ደፍሮ መግባትን ይጠይቃል፡፡ ይህም ማለት ከሚታወቀው በመነሳት ወደማይታወቀው ዕመር ብሎ እንደመግባት ነው.. ለውጥ ለማምጣት አያሌ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስዋዕቶችን ይጠይቃል፡፡ ለዚህ ነው ለውጥ በተግባር እንጂ በአፍ አይገባም፤ የሚባለው፡፡ በተጨባጭ ከየት ተነስተን የት ደርሰናል? የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ የትምህርት ጉዳይ፣ የጤና ጉዳይ፣ የፍትህ ጉዳይ፣ የግንባታ ጉዳይ፣ የንግድና የግብር ጉዳይ፣ የዚህ ሁሉ ድምር የኑሮ ጉዳይ የት ደርሷል መባል አለበት፡፡
ጭቦ አትናገሩ ይላሉ አበው፡፡ ነገ በራሳችሁ ይደርስባችኋል ለማለት ነው፡፡
የሌለውን አለ፣ ያላደገውን አድጓል፣ የደረቀውን አልደረቀም በማለት ልንከላከለው ብንሞክር ..ሆድን በጐመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል.. ነው ውጤቱ፡፡ የዕውነቱ ለት ማነከሳችን ይታያልና። በሀገራችን በተደጋጋሚ የምናየው ሌላው አባዜ ተቻችሎ አለመኖር ነው፡፡ አለመቻቻልን ለመሸፈን የምናደርገው ጥረትም ሌላው ተጨማሪ አባዜ ነው፡፡ እኔ ፃድቅ ነኝ ለማለት ሌላውን መኮነን የሚመጣው እዚህ ላይ ነው፡፡ ተግባብቶ ሳይጠላለፉ መኖር የሚያቅተውም ለዚህ ነው፡፡
ሔንሪ ቫን ዳይክ እንዲህ ይለናል፤ ..ኤደን ገነት ዳግመኛ ብትሰጠን እንኳ በትክክል አንኖርም፣ ተስማምተን አንዝናናባትም ወይም ለዘለዓለም አንቆይባትም.. ይህ አባባል በእኛም ሳይሠራ አይቀርም፡፡ እንዲህ ኢኮኖሚያችን ቆርቁዞ፣ አስከፊ ድርቅ መትቶን፣ የኑሮ ውድነት ናጥጦብን ቀርቶ ..ለምለሟን..፣ ..የዳቦ ቅርጫቷን..፣ ..የአፍሪካ ኩራቷን.. ኢትዮጵያን ብናገኝ በትክክል አንኖርባትም፣ ተስማምተን አንዝናናባትም፤ አንቻቻልባትም እንደማለት ነው፡፡
በታሪክ እንደሚነገረው፤ ታሊያርድ የተባለው የፈረንሳይ ዲፕሎማት በየስብሰባው ላይ “..ቢዝነስ የምትሠሩ ሰዎች እጃችሁ ንፁህ መሆን አለበት..” ይል ነበር አሉ፡፡ ንፁህ ያልነበረው እጅ ግን የሱ የራሱ ነው። ያንን በመናገሩ ሌሎች ንፁህ እንዳልሆኑ ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ አለመተማመንን ያሰፍናል፡፡ መፈራራትንና ሥጋትን ያሰለጥናል፡፡ ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ እሱ ግን ከጥርጣሬው በላይ ተረጋግቶ ይቀመጣል፡፡ በጥርጣሬ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ለፍርሃት፣ ላለመረጋጋት፣ በዕቅድ ላለመኖር፣ ለሙስና፣ ምሬትን ለማመቅ፣ በኑሮ ተስፋ ለመቁረጥ እጅግ የተጋለጡ ናቸው፡፡ ይሄን ሁኔታ የሚፈጥሩ ወገኖች ደሞ በአጋጣሚው ለመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም፡፡ ወትሮም ሰበብ ይፈልጋሉና ባገኙት ቀዳዳ ይገለገላሉ፡፡ ሙስናቸውን ያስፋፋሉ፡፡ ያለገንዘብ ንቅንቅ የማይሉ ቢሮክራቶችን ይፈለፍላሉ፡፡ እየቦረበሩ ስለ ድል ያወራሉ፡፡ በአሸበረቁ ፖሊሲዎች ይምላሉ ይገዘታሉ፡፡ ብዙ ግብረ አበሮችን በመረብ ያደራጃሉ፡፡ የማይቀለበስ ደረጃ ደረስን ይላሉ፤ ከአጋጣሚ አጋጣሚን ይወልዳሉ፡፡ እንኳንስ ነጠላ አግኝታ ዱሮም ዘዋሪ እግር አላት ይሏል እኒህ ናቸው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶሱ ለአዊ ዞን ሀገረ ስብከት በከፍተኛ ድጋፍ መርጧቸው ነበር

      የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ እንዲሾሙ በቅርቡ ከመረጣቸው ቆሞሳት አንዱ፣ “የጀመርኩት ሥራ አለብኝ” በሚል ዕጩነቱን እንዳልተቀበሉት፣ የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች አስታወቁ፡፡
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ግንቦት 10 ቀን ባካሔደው ምርጫ ተወዳድረው ካለፉት ዕጩ ቆሞሳት አንዱ የሆኑት፣ አባ ገብረ ሥላሴ ተስፋ፣ በኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያኒቱ ገዳማት አገልጋይ እንደሆኑና ከቅዱስ ሲኖዶሱ በደብዳቤና በስልክ ለተላለፈላቸው ጥሪ፣ የጀመሩት ሥራ እንዳለ በመጥቀስ፣ ዕጩነቱን እንደማይቀበሉትና በሹመቱም ለመገኘት እንደማይችሉ ማስታወቃቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
በዕጩ ኤጲስ ቆጶሳት የምርጫ ሥርዓት ደንብ መሠረት፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ጋራ በምዕራብ ጎጃም - አዊ ዞን ሀገረ ስብከት ለውድድር የቀረቡት አባ ገብረ ሥላሴ፣ ድምፅ ከሰጡት 38 አጠቃላይ የምልአተ ጉባኤው አባላት 31ዱን በማግኘት በከፍተኛ ድጋፍ ተመርጠው እንደነበር ታውቋል፡፡
በቦታቸው ስለሚተኩት ዕጩ፣ ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት በተጨማሪነት ይካሔዳል ከተባለው ምደባ ጋራ ጉዳዩ እንደሚታይ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡  የአዊ ዞን ሀገረ ስብከትን በአሁኑ ወቅት ደርበው እየመሩ ያሉት፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡ ሊቃነ ጰጳሳት በሌሉባቸው አህጉረ ስብከት ምደባ ለማካሔድ፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ የተጠቆሙና በቅዱስ ሲኖዶሱ በተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ አማካይነት፥ ዕውቀታቸው፣ የቆየ ታሪካቸውና ሥነ ምግባራቸው ተገምግሞና ተመዝኖ ብልጫ ያገኙ 16 ዕጩ ቆሞሳት በቅዱስ ሲኖዶሱ እንደተመረጡ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባለፈው ግንቦት 14 ቀን መግለጫቸው አስታውቀዋል፡፡
የፊታችን ሐምሌ 9 ቀን ኤጲስ ቆጶስነት የሚሾሙት ዕጩ ቆሞሳት፣ ከመጪው ሁለት ሳምንት በኋላ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቀኖና፣ ትምህርተ ኖሎት፣ ሕግና ታሪክ፣ አስተዳደር፣ የቅርስ አያያዝ፣ ማኅበራዊ ኑሮና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሴሚናሮች እንደሚሰጣቸውና እስከ ሰኔ 15 ቀን ወደ መንበረ ፓትርያርኩ ተጠቃለው በመግባት ሪፖርት እንዲያደርጉ በቅ/ሲኖዶሱ ጽ/ቤት መታዘዛቸው ታውቋል፡፡

  በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ከ778 ሺህ ዩሮ በላይ በሆነ ወጪ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የአውሮፕላን ማቆሚያ ቴክኖሎጂ ተገጥሞ፣ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ለአዲስ አድማስ በላከው መረጃ፤ ከዚህ ቀደም አውሮፕላኖችን በቦታቸው ለማቆም አገልግሎቱ በሰው ኃይል ይሰጥ እንደነበረ ጠቅሶ፤ ይህ አሰራር ከአየር መንገዱ ዘመናዊ አሰራር ጋር የማይሄድ በመሆኑ በዲጂታል ቴክኖሎጂ መቀየር አስፈልጓል ብሏል፡፡
አንድ አውሮፕላን በማኮብኮቢያ ሜዳ ላይ ካረፈ በኋላ እስከ ማቆሚያው ወይም የመንገደኞች መሸጋገሪያ ድልድይ ድረስ ከፓይለቱ ጋር በመነጋገር አውሮፕላኑን የማቆም ስራ ይሰራ እንደነበር ጠቁሞ፤” ይህ አይነቱ አሰራር በፓይለቱና በመረጃ ሰጪው መካከል አለመግባባት ይፈጥር ነበር፤ ቴክኖሎጂው ይህን ችግር ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል” ሲል አብራርቷል፡፡  
ቴክኖሎጂውን ሴፍ ጌት የተባለ የስዊድን ኩባንያ ያቀረበ ሲሆን በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከሚገኙ 52 የአውሮፕላን ማቆሚያዎች መካከል ለጊዜው 14ቱ ላይ መሳሪያው ተተክሎ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ተጠቁሟል።
ቴክኖሎጂው የአውሮፕላን ማረፊያውን አገልግሎት በማዘመን፣ አለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ተብሏል።  

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዘንድሮ ለ2ኛ ጊዜ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ አየር መንገድ ተባለ፡፡
ሰሞኑን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው 26ኛው ዓመታዊ የአየር መንገዶች ጉባኤና ኤግዚቢሽን ላይ አየር መንገዱ “ከአፍሪካ ሀገራት አየር መንገዶች ምርጡ መስተንግዶ አቅራቢ” ተብሎ ከአፍሪካ አቪዬሽን የእውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡
አየር መንገዱ በተከታታይ ያስመዘገበውና እያስመዘገበ ያለው ፈጣን እድገት፣ ትርፋማነቱና ለአፍሪካ አቪዬሽን ኢንዱስትሪ ያበረከተው አስተዋፅኦ ተመራጭ እንዳደረገው ታውቋል፡፡ አየር መንገዱ፤ በርካታ ኩባንያዎችና አየር መንገዶች በከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ውስጥ በወደቁበት ወቅት አቅሙን ማጠናከሩና የበለጠ ትርፋማ መሆኑም ተመራጭ አድርጎታል ተብሏል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት የ70 በመቶ ትርፍ ማስመዘገቡን የጠቀሰው የሽልማት ተቋሙ፤ 265 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንና የተጓዦችን ቁጥር ቀድሞ ከነበረው በ18 በመቶ ማሳደጉን ጠቁሟል፡፡