Administrator

Administrator

Saturday, 05 March 2016 10:24

የዘላለም ጥግ

(ስለ ሥልጣኔ)
· መንግሥታት የስልጣኔ ነቀርሳ ይመስሉኛል፡፡
ቹክ ዲ.
· ቤተሰብ የስልጣኔ አስኳል ነው፡፡
ዊል ዱራንት
· ንግግር በራሱ ሥልጣኔ ነው፡፡
ቶማስ ማን
· አገርን ለመጠበቅ የጦር ሰራዊት ያስፈልግሃል፤
ሥልጣኔን ለመጠበቅ ግን የሚያስፈልግህ
ትምህርት ነው፡፡
ጆናታን ሳክስ
· ኪነ ህንፃ የሥልጣኔ ሳይሆን የባህል ውጤት ነው፡፡
አልቫር አልቶ
· ክርስትና የምዕራባውያን ሥልጣኔ ዋና ምንጩና
መሰረቱ ነው፡፡
ዲኔሽ ዲ’ሶውዛ
· ለሥልጣኔ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር ፍትህ
ነው፡፡
ሲግመንድ ፍሩድ
· ቀጣዩ ጦርነት የምዕራባውያንን ሥልጣኔ ለዝንተ
ዓለም ቀብሮ ሊያስቀረው ይችላል፡፡
አሌክሳንደር ሶልዝሄኒትሺን
· የፀሐፊ ዓላማ ስልጣኔ ራሱን እንዳያጠፋ መከላከል
ነው፡፡
አልበርት ካሙ
· ግብር መክፈል እወዳለሁ፤ በዚያም ሥልጣኔን
እገዛለሁ፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልምስ ጄአር.
· ሥልጣኔ ከንቱ ፍላጎቶችን የመፍጠር ጥበብ ነው።
ሊዮ ኢሬራ
· ሥልጣኔን የሚያመልከው ያልሰለጠነ ዓለም ብቻ
ነው፡፡
ሔነሪ ኤስ. ሃስኪንስ
· ሥልጣኔ የተጀመረው የተናደደ ሰው ለመጀመሪያ
ጊዜ በድንጋይ ፋንታ ቃላት ሲወረውር ነው፡፡
ሲግመንድ ፍሩድ

Saturday, 27 February 2016 12:17

የኪነት ጥግ

(ስለ ህንፃ)

- ጥሩ ህንጻዎች ከጥሩ ሰዎች ይመነጫሉ፡፡
ችግሮች ሁሉ በጥሩ ዲዛይን ይፈታሉ፡፡
ስቲፈን ጋርዲነር
- የሰዎች ሰብዕና እንደ ህንፃዎች ሁሉ የተለያዩ
ገፅታዎች አሉት፤ አንዳንዶቹ ለዕይታ
አስደሳች ሲሆኑ አንዳንዶቹ አይደሉም፡፡
ፍራንሶይስ ዲ ላ ሮቼፎካውልድ
- በዓለም ላይ በርካታ የተበላሹ ህንፃዎች አሉ፤
የተበላሹ ድንጋዮች ግን የሉም፡፡
ሁግ ማክዲያርሚድ
- ህንፃዎቼ ልጆቼ ማለት ናቸው፤ ስለዚህ ለይቼ
የምወዳቸው ህንፃዎች ሊኖሩኝ አይችሉም፡፡
ሴዛር ፔሊ
- ህንፃዎችም የምድርና የፀሃይ ልጆች ናቸው፡፡
ፍራንክ ሊሎይድ ራይት
- ህንፃዎቼ ከእኔ የበለጠ ዝነኞች ናቸው፡፡
ዣን ኖቬል
- ሎስ አንጀለስ ውስጥ 35 ዓመት ሲሞላህ፣
ከአብዛኞቹ ህንፃዎች ዕድሜ ትበልጣለህ፡፡
ዴልያ ኢፍሮን
- በጃፓን ጥንታዊ ህንፃዎችን ጠብቆ የማቆየት
ባህል ከአውሮፓ ያነሰ ነው፡፡
ታዳኦ አንዶ
- ለህንፃዎች ደስታ የሚሰጠው ብርሃን ነው፡፡
ጃኩሊን ቲ. ሮበርትሰን
- ሁልጊዜ በህንፃዎች ውጪያዊ ገፅታ በእጅጉ
እማረካለሁ፡፡ በመንገድ ላይ እየተጓዝኩ
የፊት ለፊት ገፅታቸውን በመመልከት
ብቻ እረካለሁ፡፡ ወደ ውስጥ መግባት
አያስፈልገኝም፡፡
ማርክ ብራድፎርድ

120ኛውን የአድዋ ድል በዓል በማስመልከት “ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን” የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶችንያካሂዳል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የአዝማሪ ሙዚቃ፣ዲስኩር፣ ወግ፣ ሽለላና ፉከራ እንዲሁም በባህላዊ ሙዚቃ የታጀበ ግጥም የሚቀርብ ሲሆን የመድረክ ላይ ቀጥታ ስዕልም ለታዳሚዎች እንደሚቀርብም አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ሞሰብ ባህላዊ የሙዚቃ ቡድን የተለያዩ ባህላዊና አገራዊ ዝግጅቶችን በማድመቅ እንደሚታወቅየቡድኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ጣሰው ወንድምተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በወንጀልነክ የፈጠራ ስራዎቻቸው የሚታወቁትን እና 17 መፅሀፍትን
ለንባብ ያበቁትን አንጋፋ ደራሲ ይልማ ኀብተየስን ዛሬ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ አዳራሽ እንደሚዘክር አስታወቀ፡፡ በዕለቱም በቅርቡ ለህትመት የበቃው “የቤቱ መዘዝ” የተሰኘው የደራሲው 17ኛ መፅሀፍ እንደሚመረቅም ታውቋል፡፡ የ78 ዓመቱ ደራሲ ይልማ ሃብተየስ በ1958 ዓ.ም “እሱን ተይው” የተሰኘ የመጀመሪያ የወንጀል ምርመራ የፈጠራ ፅሁፋቸው
ያሳተሙ ሲሆን ከዚያ በፊት “ያልታደለች በሰው ሰርግ ተዳረች” የተባለ ልብ ወለድ ማሳተማቸውም ታውቋል፡፡ ደራሲው “ሶስተኛ ሰው”፣ “ከቀብር መልስ”፣ “ያልተከፈለ ዕዳ”፣ “ሳይናገር ሞተ”፣ “ደስ ያለው ሀዘንተኛ”፣ “ያበቅ የለሽ ኑዛዜ” እና ሌሎችንም የወንጀል ምርመራ ፈጠራ
መፅሀፍትን ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በዝክር ፕሮግራሙ ላይ በደራሲው ስራዎች፣ በህይወታቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን የደራሲያን ማህበር ለአንጋፋው ደራሲ እውቅና እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል፡

Saturday, 27 February 2016 11:59

የዘላለም ጥግ

(ስለ አክብሮት)
- ሌሎች እንዲያከብሩህ ከፈለግህ ራስህን አክብር፡፡
ባልታሳር ግራሽያን
- እያንዳንዱ ሰው እንደ ግለሰብ መከበር አለበት፤
መመለክ ግን የለበትም፡፡
አልበርት አንስታይን
- የመውደድህና የመጥላትህ ነገር አያስጨንቀኝም
… እኔ የምጠይቅህ እንደ ሰው ልጅ እንድታከብረኝ
ብቻ ነው፡፡
ጃኪ ሮቢንሰን
- ለሃሳባቸው ክብር ከሌለኝ ሰዎች ጋር የመሟገት
ስህተት ፈፅሞ አልሰራም፡፡
ኢድዋርድ ጊቦን
- ነፃ ባንሆን ኖሮ ማንም ሰው አያከብረንም ነበር፡፡
ኤ.ፒ.ጄ. አብዱል ካላም
- ለሴት አያቴ ጤናማ አክብሮት እንደነበረኝ ሁሌም
አስታውሳለሁ፡፡
ልኡል ዊሊያም
- ሰዎች አክብሮት እንዲሰጡኝ አልጠብቅም፤እኔ
ነኝ ሁልጊዜ አክብሮት የምሰጣቸው፡፡
ማርያኖ ሪቨራል
- ያደግሁት ከእናቴና ከእህቴ ጋር ነው፤ ስለዚህ
ሴቶችን በጣም አከብራለሁ፡፡
ሃሪ ስታይልስ
- አንድ ሰው መልካም ምግባር ወይም አክብሮት
ከሌለው በእኔ ዓለም ውስጥ እንዲቆይ
አልፈቅድለትም፡፡
ጋብሪሌ ዩኒየን
- ጂምናስቲክ ሁሉንም ነገር አስተምሮኛል -
የህይወት ትምህርቶችን፣ ኃላፊነትን፣ ዲሲፕሊንና
አክብሮትን፡፡
ሻውን ጆንሰን
- ህይወት አጭር ናት፤ እናም እያንዳንዷን ቅፅበት
ማክበር አለብን፡፡
ኦርሃን ፓሙክ
- ነፃነት፣ የመምረጥ መብት፣ ድምፅ የመስጠት
መብት፣ ክብርና ፍትህ የሰዎች ሁሉ መሰረታዊ
መብት መሆኑን እናምናለን፡፡ ሁሉም ሰው
እነዚህን መብቶች መቀዳጀት አለበት፡፡
መሃመድ አህመዲንጃድ
- ውሱንነቶቼን አከብራለሁ፤ እንደ ሰበብ ግን
አልጠቀምባቸውም፡፡
ስቲፈን አር.ዶናልድሰን
- አዳዲስ ጓደኞችን መፍጠር እወዳለሁ፤ሰዎችን
በተለያዩ ምክንያቶች አከብራቸዋለሁ፡፡
ቴይለር ስዊፍት

    ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ታዋቂውን አሜሪካዊ ዘፋኝ ሬይ ቻርለስን ለመዘከር ባለፈው ረቡዕ
ምሽት በዋይት ሃውስ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይየድምጻዊውን ሙዚቃ ማቀንቀናቸውን ቢቢሲዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ቀደም ብለው በፕሮግራሙ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደማይዘፍኑ ቢያስታውቁም፣ወደ ኋላ ላይ ግን ነሸጥ እድርጓቸው ያቀነቀኑ ሲሆን “ሬይ ቻርለስ፤ ጃዝ፣ አር ኤንድ ቢ፣ ሮክ ኤንድ ሮል፣ ካንትሪና ሶልን በመሳሰሉ የሙዚቃ ስልቶች በግሩም ሁኔታ መዝፈን የሚችል ለሙዚቃ የተፈጠረ ሰው ነበር!” ሲሉ ድምጻዊውን ማሞካሸታቸውም ተነግሯል፡፡ “የሬይ የተለየ የሙዚቃ ብቃት በተለያዩ ትውልዶች ውስጥ ብቅ በሚሉ ሙዚቀኞች ላይተጽዕኖ ማሳረፉን ቀጥሏል” ሲሉም የድምጻዊውንዘመን ተሻጋሪነት መስክረዋል፤ኦባማ በንግግራቸው።እ.ኤ.አ በ1930 በወርሃ መስከረም ጂኦርጂያውስጥ የተወለደው ታዋቂው ድምጻዊ ሬይ ቻርለስ፤የተዋጣለት ድምጻዊ፣ የሙዚቃ ደራሲናኦባማ የሬይ ቻርለስን ሙዚቃ አቀነቀኑ አቀናባሪ እንደነበር ያወሳው ቢቢሲ፣ ብሉዝና ጃዝን በመቀላቀል አንቼን ማይ ኸርትን የመሳሰሉ ዘመንተሻጋሪ ተወዳጅ ሙዚቃዎችን ለአለም ማበርከቱንና በሰኔ 2004 ከዚህ አለም በሞት መለየቱን አስታውሷል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል በዘለቀው የድምጻዊው የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ አሸር፣ ዴሚ ሎቫቶ፣ ሊዮን ብሪጅስ፣ አንቶኒ ሃሚልተንና ሌሎችም ታዋቂ ድምጻውያን የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው ማቅረባቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሌባ በአንድ መለስተኛ ሆቴል አንድ ክፍል ለመኝታው ይከራያል፡፡ እዚህ መኝታ ክፍል ብዙ ቀናት በመቆየት የሚሰርቀው ነገር ሲፈልግ ቆየ፡፡ ዕድሉ አልተገኘለትም፡፡ አንድ ቀን ግን አንድ አጋጣሚ ተከሰተ፡፡ አንድ ድል ያለ ድግስ ተደግሷል፡፡ የሆቴሉ ባለቤት አንድ ምርጥ ውድ ኮት ለብሷል፡፡ እግሩን አንፈራጦ በሩ አካባቢ ተቀምጧል፡፡ ሌባው ያንን ኮት የመስረቅ ስሜቱ ወዲያውኑ ተነሳሳ፡፡ ሌላ የሚሠራው ነገር ስለሌለው ቀጥ ብሎ መጥቶ የሆቴሉ ጌታ ጐን ተቀመጠና በወሬ ጠመደው፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ሲያወጉ ቆዩ፡፡ በመካከል ሌባው ወሬውን ትቶ እንደ ተኩላ አዛጋና መጮህ ጀመረ፡፡
የሆቴሉ ጌታ ደንግጦ፤
“ምነው አመመህ እንዴ?”
ሌባውም፤
“ጌታዬ የዚህን ሚስጥር እነግርሃለሁ፡፡ ሆኖም ያንን ላንተ ከመንገሬ በፊት አንድ ነገር ቃል ግባልኝ፡፡ እኔ ስሄድ ልብሴን እንድትጠብቅልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ላንተ እተወዋለሁ ልብሴን፤ ምክንያቱም ራቅ ብዬ መሄዴ ስለሆነ ነው”
ጌታው፤
“የዚህ የማዛጋትህ ሚስጥር ግን ምንድነው?”
ሌባውም፤ “ጌታዬ፤ ምናልባት ከላይ እንደ እርግማን ተልኮብኝ ይሆን ይሆናል፡፡ ብቻ ዞሮ ዞሮ፤ ሰበቡ ምንም ይሁን ምን፣ ሦስት ጊዜ አዛግቼ ከጮህኩ ወደ ቁጡ ተኩላነት እለወጥና የሰው ጉሮሮ ማነቅ ነው ቀጥሎ፡፡”
ሌባው ንግግሩን እንዳበቃ ለሁለተኛ ጊዜ አዛጋ፣ አንፋሸከ፡፡ ይሄኔ የውቴሉ ጌታ ሌባው ያለውን እያንዳንዱን ቃል በማመንና በተኩላ የመበላት ነገር እየሰቀቀው፣ በጥድፊያ ተነስቶ ወደ ጓዳ መሮጥ ጀመረ፡፡ ሌባው ግን የጌታውን ኮት ከኋላ ጨምድዶ ያዘውና እየጮኸ፤
“ጌታዬ ጌታዬ፤ እባክዎ ልብሶቼን ይጠብቁልኝ፡፡ አለዚያ ይጠፉብኛል” አለና ለሶስተኛ ጊዜ ማዛጋቱን ቀጠለ፡፡ ጌትዬው ለሦስተኛ ጊዜ ሌባው ካዛጋ አይለቀኝም፣ መበላቴ ነው፤ ብሎ በፍርሃት ተጥለቅልቆ ኮቱን አውልቆ ለሌባው ትቶ መጭ አለ፡፡ ጓዳ ገብቶም በሩን ከርችሞ ቁጭ አለ፡፡
ሌባው እጁ ላይ ታላቁ ኮቱ ቀርቶለታል፡፡ አጅሬ ሌባ፤ ያን ውድ ኮት ተሸክሞ በኩራት እየሳቀ ከሆቴሉ ወጥቶ ሄደ!
*   *   *
ሌብነት የተሰራቂውን አስተሳሰብ ይፈልጋል፡፡ ተሰራቂው ሲፈራ፣ ሰራቂው ልብ ያገኛል፡፡ በቁማችን ኮታችንን ከሚገፍ ጃውሳ ይሰውረን፡፡ ሰው እንደ አውሬ ጮሆ ከሚያስፈራራን ጊዜ ያውጣን፡፡ የሰውን ማንነት እያወቅን ተኩላ ነኝ ሲለን ወደ ማመንና ወደ መፍራት ከተሸጋገርን ሁኔታው አደገኛ ነው ማለት ነው፡፡ በየራሳችን ንፅህና መተማመን፣ በየራሳችን ጥንካሬ መጽናት ያስፈልገናል፡፡ ራዕያችን መገደብ የለበትም፡፡ ይሄን ይሄን ግብ እንመታለን ብለን ስናበቃ፤ ቀጥሎስ ወዴት እንደርሳለን ማለት አለብን፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የማይቆም የማይገታ ራዕይ ምንጊዜም ወሳኝ መሆኑን አንዘንጋ፡፡
ዱሮ ከማንነት የሚመነጭ ክብር ነበረን፡፡ መልካም ስም ያኮራን ነበር፡፡ ስማችንን ከምንም ነገር በላይ እንጠብቀው፣ ቦታ እንሰጠው ነበር፡፡ ሼክስፒር በኦቴሎ ውስጥ በሎሬት ፀጋዬ አንደበት እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር
 ዋጋ አለው ግን ከንቱም ነው፣
የእኔም የእሱም የዛም ነበር
ግና ስሜን የሰረቀኝ
የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልጽ አደኸየኝ”
ይሄ ትላንትና ነበር፡፡ ዛሬ የስም ጉዳይ ሳይሆን ፈተናው የገንዘብ፣ የንብረት፣ የቤት፣ የመሬት ብቻ ሆኗል!! ከህዝብ ቆጠራ ወደ ቤት ቆጠራ መሸጋገራችን የዚህ ውጤት ነው፡፡ ቤት የሚቆጠረው ትርፍ ቤቶች ያሏቸውን ሰዎች ኢ-ህጋዊ መንገዶችን ለማጠር ነው፤ ይላሉ፡፡ ከዚያ የከፋ ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ ባለሥልጣኑ ለእገሌ ስጡ ያላቸው ቤቶች የቶቹ እንደሆኑ አይታወቁም፡፡ በር እየሰበረ፣ ቤት እየመዘበረ የገባው ጉልቤ ብዙ ነው፡፡ ደላላ “ባለቤት የለውም” እያለ የቸበቸበውም አይጠፋም፡፡ ይሄን ፈተና ለመወጣት መንግሥት አያሌ ቆጣሪዎችን መድቦ ማሰራቱ የሚያስመሰግን ቢሆንም፤ ቆጣሪዎቹም ሙስና ውስጥ ቢገቡ የሚደርሰውን ጥፋት ከወዲሁ ማጤን ተገቢ ይሆናል፡፡ ልክ “የትራፊክ አዲሱ ህግ ትራፊኩን ያበለፅገዋል” እያለ ህዝቡ እንደሚያማ ግንዛቤ ወስደን መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ሲጀመር የሚሰጥ አደራ ሲጨረስ ከሚሰጥ ትችት የተሻለ ነው በሚል ነው ከወዲሁ መናገራችን ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ ጧት ታቅደው ማታ ስለሚሞቱ ዕቅዶችና ሀሳቦች አንዳንድ ፍልስፍናዊ አባባሎችን አኑሯል፡፡ እነሆ
“አሁን እንደጥሬ ፍሬ፣ ሃሳብሽ ግንዱ ላይ ታዝሏል
ነገር ግን በስሎ ሲሟዥቅ፣ ማንም ሳይነካው ይወድቃል”
ራዕያችን በጥሬው ሲቀመጥና ሲበስል ልዩ ባህሪ አለው፡፡ በጥሬው እምንፈክርለት ሃሳብ፣ ሲበስል ምን እንደሚመስል ማስተዋል መሠረታዊ ሃላፊነታችን ነው፡፡ ያደገ የተመነደገ ሃሳብ የራሱ ምስል አለው፡፡ የራሱን አስተውሎት ይሻል፡፡
የአካባቢ ቀውስ፣ የተጠራቀመ ምሬት ውጤት መሆኑን አለማስተዋል ደካማነት ነው፡፡ የህዝብ እንቅስቃሴ፣ ወይም ሁከት እንደው በዘልማድ የረብሻ ሱስ ውጤት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ጉዳዮች፣ ብሶቶች ጥርቅም ውጤት ሊሆን እንደሚችል በማጤን “የመልካም አስተዳደር ጉድለት” ብቻ ምክንያት ብሎ ማሰብ የራሱ ችግር ሊኖረው የሚችለውን ያህል፤ የሌሎች እጅ አለበት ብሎ መደምደምም የራሱን ጥንቃቄ ይሻላል፡፡ ህዝቡን ከልብ የማሳተፍ ባህል እንጂ ዘመቻ አይደለም መፍትሔው፤ ዘመቻ ጊዜያዊ ነው፡፡ ባህል ዘላቂ ነው!  የሌሎች እጅ አለበት ስንል ህዝብ ያላሰባቸውን በርካታ ባዕድ እጆች በማሰብ እንዳይውዥበረበር መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ ሌላው ህዝብ የሚለውን ከመመሪያ ጋር ለማጣጣም በሚልም ሀቅ እንዳይጣመም ለማድረግ መጣር ሌላው ተገቢ አካሄድ ነው፡፡
ባንድ አንፃር ሁኔታዎች እየደፈረሱ መላ እንዳያጡ መታገል፤ ሥርወ አመጣጣቸውን መፈተሽ፣ መፍትሔአቸውን መሻት፣ አንዱ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አንፃር ወደ ታላቅ የአገር ፋይዳ የሚሸጋገሩ አገራዊ ዕቅዶችን ከሚያነቅፉ የኢ-ፍትሕ፣ የሙስና የኢ-ዲሞክራሲና የኢ-መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር መጋፈጥ የሀገራችን ነባራዊ- ዕውነታዎች ሆነዋል፡፡ ይህ ማለት አንዳች አጣብቂኝ ነው - በሁለት ጐሽ ማህል የተደበቀ በሬ መሆን! ከዚህ እንወጣ ዘንደ ቆፍጣና መላ ይስጠን! እንደጥርስ ህመም ማታ ማታ የሚያመንን በሽታ ቀን ማዳመጥ እንድንችል ልብ ይስጠን!”

የኦፌኮ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በኦሮሚያ በተከሰተው ግጭት፣መንግስት ሰሞኑን በሰጠው መግለጫና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን አጭር የስልክ ቃለ-ምልልስ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ
አለማየሁ አንበሴ ጋር አድርገዋል፡፡

ቢሮአችሁ ሰሞኑን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበር በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ተነግሯል -----
አዎ፡፡
ምን ነበር የተፈጠረው?
በቃ በእለቱ ሰው መግባትና መውጣት አይችልም ነበር ያሉን፡፡
ቢሮአችሁ ፍተሻ ተካሂዶበታል?
አልተካሄደም፡፡
የታሰረ ሰው አለ?
የለም፡፡
መቼ ነበር ይህ የሆነው?  
እሁድ፡፡
ከእሁድ በኋላስ ቢሮ መግባት ቻላችሁ ?
አዎ፡፡
በኦሮሚያ የተፈጠረውን ግጭትና የመንግስትን እርምጃ እንዴት ገመገማችሁት?
የህዝቡ እንቅስቃሴ አሁንም ቀጥሏል። መንግስትም እርምጃ መውሰዱን ቀጥሏል፡፡ እኛ ደግሞ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ እየጠየቅን ነው፡፡ ይሄ ነው ያለው ነገር፡፡
ፓርቲያችሁ ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥያቄ ያቀርባል?
አዎ! በፊትም ስናቀርብ ነበር፤አሁንም ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
መንግስት በኦሮሞ ህዝብ ስም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በተከሰተው ግጭት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት እየገለጸ ነው፡፡ ቀደም ሲል የእናንተ አባላትና አመራሮችም ታስረዋል፡፡ በተቃውሞው የኦፌኮ ሚና ምን ያህል ነው?
ህዝቡ ማንም ሳይቀሰቅሰው ከዳር እስከ ዳር ለመብቱ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ በአንድ ፓርቲ ቅስቀሳ ብቻ አይነሳም፡፡ የህዝቡን ብሶት ራሱ ኦህዴድም ያውቀዋል እኮ፤እኛ የተለየ ነገር የለንም፡፡
መንግስት ችግሮቹን እንዴት መፍታት አለበት ይላሉ?
ኢህአዴግ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር አለበት፡፡
እንዴት ነው ህዝቡን ማረጋጋት የሚቻለው፣ ምን አይነት የፖለቲካ ድርድር መደረግ አለበት --- በሚሉት ዙሪያ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ብሄራዊ መግባባት፣ ብሄራዊ እርቀ ሰላም መፈጠር አለበት፤ ነገር ግን ኢህአዴግ በዚህ መንገድ እየሄደ አይደለም፡፡
ከሰሞኑ ግጭት ጋር በተያያዘ የታሰሩባችሁ አባላት አሉ?
እስርማ ሁሌም አለ፡፡ እስሩ አሁንም ቀጥሏል፡፡

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል

   የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍሊፕ ሃሞንድ በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ጉብኝት ለማድረግ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ ከትናንት በስቲያ በድረ-ገጹ አስታወቀ፡፡ባለስልጣናቱ ኢትዮጵያን የመጎብኘት እቅድ እንዳላቸው ያስታወቁት፣ ባለፈው ረቡዕ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ የመከሩት የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ጉዳይ ቢሮ ሁለተኛ ቋሚ ጸሃፊ ኦሊቨር ሮቢንስ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ ጉብኝቱ የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ ግን ያለው ነገር የለም፡፡ ሁለቱ የእንግሊዝ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ በእስር ላይ የሚገኙትና እንግሊዛዊ ዜግነት ያላቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እንዲፈቱና በቆንስላ ተወካዮች የሚጎበኙበት ሁኔታ እንዲመቻች የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ቢልኩም መንግስት ግን ይህ ነው የሚባል ምላሽ አለመስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
ጉብኝቱ ዴቪድ ካሜሩን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ላይ ከወጡ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡበት የመጀመሪያው ጉብኝት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር እ.ኤ.አ በ2004 ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር ይታወሳል፡፡

    ሪንጊንግ ቤልስ የተባለው የህንድ የሞባይል ቀፎዎች አምራች ኩባንያ፣ በዓለማችን የስማርት ፎን ገበያ እጅግ ርካሽ ዋጋ የተተመነለትን ፍሪደም 251 የተባለ አዲስ የሞባይል ቀፎ ምርቱን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለገበያ እንደሚያቀርብ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡ከጥቂት ወራት በፊት የተቋቋመው ኩባንያው፣ለዚህ የሞባይል ቀፎ 7.3 ዶላር የመሸጫ ዋጋ የተመነለት ሲሆን የሞባይል ቀፎው 8 ጊጋ ባይት ሚሞሪ ያለውና በፊቱና በኋላው ሁለት ካሜራዎች የተገጠሙለት ነው ተብሏል፡፡ ኩባንያው በቅርቡም በአገሪቱ የ4ጂ የሞባይል ቀፎ ገበያ እጅግ እርካሹ ዋጋ የተተመነለትን ምርቱን ለገበያ ማብቃቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱን የሞባይል ቀፎውን የመገጣጠም ስራውን እንደጀመረና ምርቱን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ለአገር ውስጥ ገበያ ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡
ህንድ በአለማችን የሞባይል ቀፎ ገበያ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በአገሪቱ አንድ ቢሊዮን ያህል የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች እንዳሉም ገልጧል፡፡