Administrator
አንጋፋ ታጋዮች ስለ ህወኃት ይናገራሉ
“ታጋዮች የተሰውለት ዓላማ ተረግጧል”
ህወኀት የተመሰረተበት 39ኛ ዓመት በዓል ባለፈው ማክሰኞ በመቀሌ ከተማ በደማቅ ስነ-ስርአት አክብሯል፡፡ በዚህ በአል ላይ በትግሉ ወቅት የተሰው ቀደምት ታጋዮች የታወሱ ሲሆን የህወኀት ታሪክም በተለያዩ የፓርቲው አባላት ተነግሯል፡፡ ከህወኅት ምስረታ ጀምሮ በትግሉ ውስጥ የቆዩና በተለያዩ ጊዜያት ከፓርቲው የተለዩ አንጋፋ ታጋዮች ግን ህወኃት አላማውን ስቷል ሲሉ ይተቻሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኞች አበባየሁ ገበያው እና አለማየሁ አንበሴ ከእነዚህ አንጋፋ ታጋዮች መካከል አቶ ገብሩ አስራት እና አቶ አሰግደ ገ/ሥላሴን በህወኀት የትግል ዓላማ ዙርያ አነጋግረዋቸዋል፡፡
“ታጋዮች የተሰውለት ዓላማ ተረግጧል”
አቶ ገብሩ አስራት (የህወኀት አንጋፋ ታጋይ እና የአረና ፓርቲ መስራች)
መነሻው ላይ የህወኀት አላማ ምን ነበር?
በሃገሪቱ ላይ የሰፈነውን ጭቆና ማስወገድ ነበር፡፡ በወቅቱ የነበረው ስርዓት የግለሰብና የቡድን መብትን የማያከብር በመሆኑ የሃይማኖት መብትን ጨምሮ እነዚህን ሰብአዊ መብቶች ማረጋገጥ ነበር ዓላማው። መብቱ ብሄሮች እስከ መገንጠል የሚያደርሳቸው ጥያቄ ካለም መገንጠል ይችላሉ የሚል ሆኖ፣ ወሳኙ ግን ነፃነት የሚለው ነበር፡፡ የትግሉ ርዕዮተ ዓለም ማርክሲዝም ቢሆንም ማጠንጠኛው ነፃነትና የሰው ልጆች መብቶችን ማረጋገጥ ነበር፡፡
ትግሉ የትግራይ ሪፐብሊክን የመመስረት አላማ እንደነበረው ይነገራል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያሉ የህወሃት ታጋዮች ግን ይሄ ዓላማ አልነበረም ይላሉ። እውነቱ የትኛው ነው?
ህወኀት ለአንድ ዓመት ያህል የተፃፈ አላማና ፕሮግራም አልነበረውም፡፡ በኋላ ግን አንድ ማኒፌስቶ ተዘጋጀ፡፡ በዚህ ማኒፌስቶ የትግራይ ሪፐብሊክን የማቋቋም አላማ ተቀምጦ ነበር፤ ነገር ግን በጉባኤ አልፀደቀም፡፡ በወቅቱ የነበሩ አመራሮች አፅፈው ያሰራጩት ሲሆን በታጋዮች ዘንድ ግን ተቀባይነት አላገኘም፡፡ ተቃውሞ ስላጋጠመውም ለስድስት ወር ብቻ ነው በስራ ላይ የዋለው፡፡ “ይሄ ትክክል አይደለም፤ ከኢትዮጵያ መገንጠል እንደመብት እንጂ እንደ አላማ መቀመጥ የለበትም” የሚል ተቃውሞ ከቀረበበት በኋላ የሪፐብሊክ ምስረታ አላማ ውድቅ ተደረገ፡፡
እርስዎ ለየካቲት 11 የሚሰጡት ትርጉም ምንድነው? አላማውንስ አሳክቷል?
ትልቁ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በዘንድሮው አከባበር ላይ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሳይቀሩ ስለጠላቶች ነው የሚያወሩት፡፡ የትኞቹ ጠላቶች እንደሆኑ አልገባኝም፡፡ አካሄዳቸውን የሚቃወመውን፣ መብቴ ተነክቷል ወይም ሙስና ተንሰራፍቷል እያለ የመልካም አስተዳደር ችግሩን የሚተቸውን ሁሉ በጠላትነት እየፈረጁት ነው ማለት ነው? ይሄ የየካቲት 11 አላማ አይደለም፤ መስተካከል አለበት። አሁን ያሉት አመራሮች ከስልጣናቸው በላይ የሚያሳስባቸው ምንም ነገር የለም፡፡ ሃሳባቸው እሱ ብቻ ነው፡፡ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ህይወታቸውን የገበሩለት ዓላማ አሁን በቦታው አለ ብዬ አላምንም፡፡
የህወኀት ትግል ያመጣው ውጤት እንዴት ይገመገማል?
ደርግን ለመጣል በተደረገው ትግል ውስጥ ህወኀት ብቻ ሳይሆን በርካቶች ታግለዋል፡፡ ኢህአፓ አለ፤ ሌሎችም እንደዚያው፡፡ ስለዚህ ህወኀት ብቻ ውጤታማ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ ማንኛውም ፍትህና እኩልነትን አመጣለሁ ብሎ መስዋዕትነት የከፈለ ሁሉ የራሱ ቦታ አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ረገድ ደርግን መጣሉ አስፈላጊ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎች የተሰውለት አላማ ተረግጧል፡፡ በተለይ በትግራይ የተቃውሞ ፖለቲካ ነውር ሆኗል፡፡ መውጫና መግቢያ ታጥቷል፡፡ ስብሰባ ማካሄድ አልተቻለም። የካቲት 11 ደግሞ ስልጣን ላይ ለመቆየት ህዝቡን ማስፈራሪያ ነው የሆነው፡፡ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ እየዋለ ነው፡፡ በሰማዕታትና በተሰውት ታጋዮች ስም እየተነገደ ነው፡፡
የህወኀት የትግል ታሪክ በትክክል ለትውልድ የሚተላለፍበት መንገድ ተመቻችቷል ይላሉ?
በእርግጥ ብዙ የታሪክ መዛግብቶች አሉ። በትግሉ የነበሩና ዛሬ ወደ ጎን የተገፉ ወገኖችም ይህን ታሪክ የማረቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አሁን ታሪክ እየተቀለበሠ ነው፡፡ እንደውም ታሪኩ እየተነገረ ያለው ትግሉን በማያውቁ፣ ታሪኩን ባልተረዱ ግለሰቦች ነው፡፡ ሺዎች የተሰዉለትን መራር ትግል ተረት እያደረጉት ነው፡፡ እንደተረት ውሸት እየቀላቀሉ እያወሩት ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ይህን መሰል የታሪክ ቅልበሳ እየፈፀመ ያለው ጉልበት እና ገንዘብ ያለው ገዥው ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው ራሱን የዚህ ታሪክ ብቸኛ ባለቤት እያደረገ ነው፡፡ እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ መስዋዕትነት የከፈሉ ታጋዮች በትግሉ ወቅት ያበረከቱት አስተዋፅኦ እንኳ አይነገርም፡፡ ጭራሽ ሺዎች የተሰዉበት ታሪክ ወደ አንድ ሰው እየተጠቃለለ ነው፡፡ መለስ እና በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሰማዕታት እኩል እንኳ እየታዩ አይደለም፡፡ ይሄ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡
ከ1983 በኋላስ ህወኀትን እንዴት ይገመግሙታል?
ይሄ በአጭሩ መገለፅ የሚችል አይደለም፤ የራሱ ትንታኔ የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው፡፡
ከአቶ መለስ ህልፈት በኋላ በህወኀት ላይ የታዩ ለውጦች አሉ?
አይ የለም! ዋናው ጥንስሱ ያለው የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለው ነገር ዜጎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ማህበረሰቦችን ሁሉ ይፈርጃቸዋል፡፡ እሱን የሚያገለግሉትን ወዳጅ ሲላቸው፣ በተቃራኒው የተሰለፉትን ጠላት ሲል ይፈርጃቸዋል፡፡ ስለዚህ መሰረታዊ ችግሩ ርዕዮተ ዓለሙ ላይ ነው፡፡ በዚህ ርዕዮተ ዓለም የተዋቀረ መንግሥት ፀረ-ዲሞክራሲ ነው የሚሆነው፡፡ መጀመሪያ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ተቋማት፣ ፕሬሶች ነፃነት ተሰጥቷቸው ተቋቁመው ነበር፤ ከጊዜ በኋላ ግን ይሄን መፍቀዱ ለስልጣናቸው አስጊ ሆኖ ስላገኙት ይበልጥ አምባገነንና ጨቋኝ ስርአት መገንባትን አማራጭ አድርገዋል፡፡ “ቀይ መስመር”፣ “ፈንጂ ወረዳ” በሚል እነዚህ መብቶች ተሸራርፈው ቀዳሚው ትኩረት ስልጣንን ማስጠበቅ ሆኗል፡፡
የዘውድ ስርአቱ ካከተመ 40 ዓመት ተቆጥሯል። በእነዚህ ጊዜያት በተደረጉት የተለያዩ ትግሎች የተገኙት አንኳር ለውጦች ምንድን ናቸው?
የ1966 አብዮት ያመጣቸው መሰረታዊ ለውጦች አሉ፡፡ በአጠቃላይ ማህበረሰባዊ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ የፊውዳል ስርአት ተሰብሯል፡፡ የመሬት ስሪቱ አዲስ አቅጣጫ እንዲይዝ ተደርጓል፤ አዲስ ማህበራዊ ኃይል ተፈጥሯል፡፡ ገበሬዎች አዲስ ማህበራዊ ኃይል ነበሩ፤ ነገር ግን በደርግ ታንቀዋል። ይሄ ባይሆን ኖሮ በደርግ የ17 ዓመት የስልጣን ዘመን ብዙ ለውጥ ይመጣ ነበር ብዬ አምናለሁ። ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ በኢኮኖሚ ፖሊሲው ትንሽ የተሻለ ነገር ታይቶ ነበር፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ከጥቅም አንፃር ስለሚያየው እንደገና ኢኮኖሚውን ሁሉ የመቆጣጠር ፍላጎት እያሳየ ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የኢኮኖሚ ለውጦች መኖራቸው የማይካድ ነው፤ ይሁን እንጂ ለውጡ በጠንካራ ፖሊሲዎች የተደገፈ አይደለም። ፓርቲው ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር አባዜ ስለተጠናወተው በእድገቱ ላይ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያሳረፈ ነው፡፡
አሁን ስላለው የፖለቲካ ትግል የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ቻርተር፣ በአለማቀፍ ደረጃ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር ማንኛውንም አይነት መንገድ መጠቀም እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ጨቋኝ ስርአትን መታገል ተገቢ ነው፡፡ እኛ በደርግ ጭቆና ጊዜ የነበረን አማራጭ ትጥቅ ስለነበረ በዚያ መንገድ ሄደናል። አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር ስንመለከተው ግን ይሄ አካሄድ ወይም በጠመንጃ የመጣ ስልጣን ዲሞክራሲን ያሰፍናል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ መንግስት መቀየር ይችላል ነገር ግን ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ማምጣት የተለየ ነገር ይፈልጋል፡፡ ጠመንጃ ያነሳ ወገን፣ መብት ሁሉ ለሱ ብቻ እንደሚገባ ነው የሚያስበው፡፡ እኛ ከሌላው ይበልጥ ሞተንለታል የሚል ትምክህት ውስጥ ነው የሚከተው፡፡ አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የትጥቅ ትግልን የሚፈቅድ አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ የሰላማዊ ትግሉ መቀጠል አለበት፡፡ ድሮ “የፖለቲካ ስልጣን ከጠመንጃ አፈ ሙዝ ይመነጫል” ነበር የሚባለው፤ አሁን ግን የተገላቢጦሽ መሆን አለበት፡፡ የጠመንጃ አፈሙዝ በፖለቲካ ተገዢ መሆን ነው ያለበት፡፡
“የአብዮተኛው ትውልድ” ኪሳራ በስንት ይሰላል?
አብዮቱ ሲመነዘር፡ በሚሊዮኖች ረሃብና ሞት፣ በሚሊዮኖች ችጋርና ጉስቁልና የታጨቀ ነው።
መልኩ ሲታይ፡ በርካታ መቶ ሺ ዜጎች ያለቁበት ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብርና የጦርነት እሳት ነው።
“አብዮተኛው ትውልድ”፣ ስለ አብዮቱ 40ኛ አመት የሚናገርበት አንደት ማጣቱ አይገርምም።
ልክ የዛሬ አርባ አመት፣ የነዳጅ ዋጋ ላይ የአስር ሳንቲም ጭማሪ እንደተደረገ ነው አገሪቱ በቀውስ የተናጠችው - በየካቲት ወር አጋማሽ 1966 ዓ.ም። በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እየተዘወተረ ከመጣው ሰልፍ ጋር፤ የተማሪዎችና የአስተማሪዎች ረብሻ፣ የሰራተኞች አድማና የወታደሮች አመፅ ታክሎበት፣ አገር ምድሩ በተደበላለቀ ስሜት ተቀጣጠለ። ከከተሜነትና ከዘመናዊ ትምህርት፣ ከካቢኔና ከፓርላማ አሰራር፣ እንዲሁም ከመደበኛ የጦር ሃይል አደረጃጀት ጋር ገና መተዋወቅ የጀመረችው አገር፣ መላ ቅጡ ጠፋባት። ሁለት ወር አልቆየም። ጠቅላይ ሚኒስትሩና ካቢኔያቸው ስልጣን ለቀቀ። ለወታደሮች ደሞዝ ተጨመረ። ግን አገሬው አልተረጋጋም።
መንግስት መውጪያ መግቢያ ጠፋበት። ለአስተማሪዎችና ለሌሎች ሰራተኞች ሁሉ በአንዴ ደሞዝ የመጨመር አቅም የለም። የነዳጅ ዋጋ መደጎምም የማይሞከር ሆኗል። በመላው አለም ዋጋው አልቀመስ ብሏላ። በርካታ የአረብ አገራት በእስራኤል ላይ በከፈቱት ድንገተኛ ጦርነት ሳቢያ፣ ከጥቅምት እና ጥር 1966 ዓ.ም፣ በአለም ገበያ 3 ዶላር በበርሜል የነበረው የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከሶስት እጥፍ በላይ ንሯል - ከ10 ዶላር በላይ አልፏል። ኢትዮጵያ ውስጥ በቀድሞ ዋጋው መቀጠል አለበት ከተባለ፤ መንግስት ለሰራተኞችና ለወታደሮች የሚከፍለው ደሞዝ ያጣል። አጣብቂኝ ውስጥ ነው የገባው።
በዚያ ላይ፣ ከነዳጅ ዋጋ ንረት በተጨማሪ፣ በከፍተኛ ድርቅ ሳቢያ የእህል እጥረትና የዋጋ ንረት ተከስቷል። አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔ ቢሰየምም፣ ተደራርበው የመጡትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ምትሃት አልነበረውም። ለዚህም ይመስላል፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር “ትንሽ ፋታ” ለማግኘት የተጣጣሩት። በዚህ መሃል፤ በደሞዝና በጥቅማጥቅም ጥያቄ ዙሪያ ወታደሮችን ለማስተባበር ከየአካባቢው ግንኙነት የፈጠሩ የበታች መኮንኖች፣ ሳይታሰብ በአለቆቻቸውና በመንግስት ላይ ከፍተኛ ጉልበት እያገኙ መጥተዋል። ለዚህም አንዱ ምክንያት፤ እንደየእለቱ ስሜትና አዝማሚያ፣ “ያኛው ሚኒስትር ጉቦኛ ነው፤ ያኛው ባለስልጣን ዘራፊ ነው፤ ይያዝልን፤ ይታሰርልን” የሚሉ የተለያዩ ጩኸቶች መራገባቸው ነው። አንድ ጉበኛ ወይም አንድ አጭበርባሪ ባለስልጣን ቢታሰር፤ ቅንጣት መፍትሄ እንደማያስገኝ ግን ግልፅ ነው። እናም፤ የአገሪቱ ቀውስና ትርምስ ሳይረግብ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ካቢኔያቸው በአምስት ወር ውስጥ ከስልጣን ወረዱ።
የቀውሱ አቅጣጫና መጨረሻ፣ ወዴት ወዴት ይሆን ብሎ የሚጨነቅ ብዙ ነው። “አቅጣጫውን እኔ አውቃለሁ፤ እኔ ዘንድ ሁነኛ መፍትሄ ይገኛል” የሚል አንጋፋና አዋቂ ሰው ግን አልነበረም። በእርግጥ፤ በቡድን “እኛ እናቃለን፤ መፍትሄውም በእጃችን ነው” እያሉ ነጋ ጠባ መፈክር የሚያስተጋቡና የሚጮሁ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን፣ የአዋቂነት አልያም የአንጋፋነት ደረጃ ላይ የደረሱ አይደሉም። ብዙዎቹ ገና የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው፤ ጥቂቶቹ ደግሞ አዳዲስ ምሩቃንና ወጣት ምሁራን። እነዚህ ናቸው “አብዮተኞቹ”። ከሌላው ሕዝብ በቁጥር ሲነፃፀሩ፤ እጅግ በጣም ጥቂት ቢሆኑም፤ አንድ በመቶ ያህል እንኳ ባይሆኑም፤ ከሌላው ሁሉ የላቀ ሃይል አግንተዋል። ሌላው ሁሉ ግራ ተጋብቶ ሲደናበር፤ “የአገሪቱን ችግር ተንትነው የሚያውቁበት መመኪያ፤ መፍትሄ የሚያበጁበት መሳሪያና የወደፊቱን ጉዞ የሚመሩበት አቅጣጫ” መያዛቸውን እየተናገሩ ማን ይስተካከላቸዋል? መመኪያቸው የማርክስ የሌኒን መፅሃፍ ነው። መሳሪያቸው፤ “አብዮታዊ እርምጃ” ነው። ጉዟቸው ደግሞ ሶሻሊዝም።
በአብዮተኞቹ አስተሳሰብ፣ “ከሁሉም የከፋው ሃጥያት፣ የግል አእምሮውን መጠቀም፤ ለራስ ሕይወትና ለራስ ኑሮ ማሰብ ነው” ... ራስወዳድና ግለኝነት እጅግ ወራዳ ፀረሕዝብነት ነው በማለት ያወግዙታል። “ከሁሉም የከፋው ወንጀል ደግም፣ የራስን ሕይወት ማሻሻልና የንብረት ባለቤት መሆን ነው” ... ቡርዧ ወይም ንዑስ ቡርዧ እያሉ ያንቋሽሹታል። “ከሁሉም የከፋ በደል ደግሞ፤ የሥራ እድል መፍጠርና ሰራተኞችን መቅጠር ነው” ... በዝባዥ ወይም ጨቋኝ ተብሎ ይኮነናል። በማርክስና በሌኒን መፃህፍት ውስጥ ተደጋግመው የሰፈሩ እነዚህ ሃሳቦች ናቸው የአብዮተኛው ትውልድ መመኪያና አለኝታ። የግለሰብ ነፃነትን እያወገዙ፣ የንብረት ባለቤትን እያንቋሸሹ፤ የነፃ ገበያ ስርዓትንና ብልፅግናን እየኮነኑ ጥዋት ማታ አብዮተኞቹ መፈክር ሲያሰሙ፤ በአጠቃላይ የስልጣኔ አስተሳሰቦችን እያንኳሰሱ ሲጮሁ፤ በልበሙሉነት የሚሞግታቸውም ሆነ የሚመክታቸው አልተገኘም። ገና በጭላንጭል ይታዩ የነበሩ የስልጣኔ አስተሳሰቦች ከነአካቴው ተዳፍነው፤ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ሃሳቦች እንደ አዲስ ነገሱ። ከዚያማ መንገዱ ጨርቅ ሆነላቸው፤ መፈክሮቻቸው በቀላሉ ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ። ማውገዝ፣ ማንቋሸሽና መኮነን በቂ አይደለማ። “መርገጥ፣ መጨፍለቅ፣ መደምሰስ” የሚሉ የአብዮታዊ እርምጃዎች ተከትለው ይመጣሉ። ደግሞም አልዘገየም።
በየካቲት አጋማሽ “በግብታዊነት የፈነዳው አብዮት”፣ አመት ሳይሞላው ነው፤ ከሃሳብ ወደ ተግባር መሸጋገር የጀመረው። 120 የበታች መኮንኖች የተሰባሰቡበት ኮሚቴ፤ መስከረም ላይ ንጉሡን ከስልጣን ሲያስወግድ ባወጣው አዋጅ፤ መቃወም ወንጀል ነው ብሎ አወጀ። ሁሉም ሰው ከራሱ በፊት አገርን ማስቀደም እንዳለበት ሲያስረዳም፤ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን መርህ የሚቃወም፣ ለመቃወም የሚያስብ ወይም የሚያሳስብ... ወዬለት ሲል ዛተ። የራሴን ሃሳብ መግለፅ መብቴ ነው ብሎ መሟገት አይቻልም - ራስ ወዳድነትና ግለኝነት ተወግዟላ። ለማንኛውም የደርግ ዛቻ በባዶ አልነበረም። በእስር የቆዩ 59 የቀድሞ ባለስልጣናት፤ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡና ሳይከራከሩ እንዲገደሉ ህዳር ወር ላይ ተወሰነ - በአንድ የደርግ አባላት ስብሰባ። የየካቲቱ አብዮት አመት ሲሞላው፣ የደርግ የስልጣን ዘመን ገና መንፈቅ እንዘለቀ፤ ሌላ አዋጅ መጣ።
በአብዮታዊ እርምጃ፤ ባንኮች፣ ፋብሪካዎች፣ የቢዝነስ ድርጅቶች ተወረሱ። መሬት ሁሉ የመንግስት ነው ተባለ። ከ500 ካሬ ሜትር በላይ መሬት፣ ከአንድ መኖሪያ ቤት በላይ ግንባታና ሕንፃ ሁሉ ተወሰደ። ማከራየት ወንጀል ሆነ። ሰራተኛ መቅጠር ተከለከለ። አብዮተኛው ትውልድ መመኪያና አለኝታ አድርጎ የዘመረላቸውን መፈክሮች ሁሉ፤ በላይ በላዩ ተግባራዊ ለማድረግ ብዙ ጊዜ አልፈጁም። መቃወም ብቻ ሳይሆን ለመቃወም ማሰብ አይቻልም የሚል የአፈና አዋጅ፤ ፋብሪካ መፍከትም ሆነ ሰራተኛ መቅጠር አይቻልም ብሎ ንብረትን የሚወርስ የዝርፊያ አዋጅ፤ ያለ ፍርድ እንዳሻው ማሰርና መረሸን የሚችል የግድያ ስልጣን ... ምን ቀረ? የግል ሃሳብን፣ የግል ንብረትን፣ የግል ሕይወትን ... በአጠቃላይ የግል ነፃነትን ገና ሳይፈጠር በእንጭጩ ለማጥፋት የሚያስፈልጉ የአብዮተኞቹ ሃሳቦችና መፈክሮች በሙሉ ሳይውሉ ሳያድሩ በደርግ ተግባራዊ ሆነዋል። አብዮተኞቹ ተሳክቶላቸዋል።
ሶስተኛው ደረጃ በራሱ ጊዜ የሚመጣ ውጤት ነው - የሃሳብና የተግባር ውጤት። የማያቋርጥ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ስርዓት። ማለትም የሶሻሊዝም ጉዞ። እዚህ ላይም፣ አብዮተኞቹ ምንም የጎደላቸው ነገር የለም - የተመኙትን ውጤት አግኝተዋል። ከንጉሡ ዘመን ጋር እያነፃፀርን ልናየው እንችላለን።
“እንደተመኘኋት አገኘኋት” - የአብዮተኞቹ ጉዞ
እንደምታውቁት፣ የአፈና፣ የዝርፊያና የግድያ ስርዓት ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። ከአፈና ጋርም ነው መሃይምነትና ኋላቀርነት የሚንሰራፉት። ከዝርፊያ ጋር ደግሞ ድህነትና ረሃብ ይበረታሉ። ከግድያ ጋርም ሽብርና ጦርነት ይበራከታሉ። ኢትዮጵያ በእነዚህ ሁሉ ትታወቃለች። በንጉሡ ዘመንም እንዲሁ፣ አፈናው፣ ዝርፊያውና ግድያው ለአገሪቱ የሚያንስ አልነበረም። በእርግጥ፤ በዚያን ዘመን አንዳንድ የነፃነት ጭላንጭሎች እየተፈጠሩ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ከ1950ዎቹ ጀምሮ አፄ ኃይለስላሴ በተገኙበት ይዘጋጁ የነበሩ አመታዊ የግጥም ውድድሮችን መጥቀስ ይቻላል። ተማሪዎች በየአመቱ በሚያቀርቧቸው ግጥሞች፤ መንግስት ላይ ትችቶች ይሰነዝሩ እንደነበር አብዮተኞቹ አይክዱትም። የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የሚዘጋጁት ጋዜጣ ላይም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መረር ያሉ የተቃውሞ ፅሁፎች ታትመዋል። እንዲያም ሆኖ፣ የንጉሱ መንግስት፣ የሃሳብ ነፃነትን ያከብር ነበር ማለት አይደለም። ንጉሱ ከዩኒቨርስቲው አመታዊ የግጥም ውድድሮች ርቀው ጠፉ። የዩኒቨርስቲው ጋዜጣ ላይም እገዳ እንዲጣል አስደርገዋል። በአጭሩ፣ ንጉሡ የሃሳብ ነፃነትን በማስከበር የሚወደሱ አይደሉም።
አሳዛኙ ነገር፤ እጅግ የባሰ የአፈና ስርዓትን ጎትቶ የሚያመጣ አብዮት መፈጠሩ ነው። ስልጣን የያዘው ደርግ እና ከጎኑ የተሰለፉ አብዮተኞች፣ እንዲሁም ስልጣን ለመንጠቅ በተቃራኒ ጎራ የተሰለፉ አብዮተኛ ድርጅቶች ሁሉ፤ እንደየአቅማቸው የቻሉትን ያህል የአፈና ስርዓት ዘርግተዋል። ተቃውሞና ትችት መተንፈስ ጨርሶ ተከለከለ። ስልጣን የያዘ አብዮተኛ፣ “ተቃወምከኝ፣ ትችት ሰነዘርክ” ብሎ ካሰበ፤ “ፀረ አብዮት፣ ፀረ ሕዝብ” እያለ አፋፍሶ ያስራል፤ ይገድላል። ስልጣን ያልያዘ አብዮተኛም ቢሆን፣ አድፍጦ ይገድላል፤ ካልሆነለትም ስም የማጥፋት ዘመቻ ያፋፍማል። ይህም ብቻ አይደለም። በቃ፤ ለመቃወምና ለመተቸት ማሰብ ወይም ማሳሰብ፣ የአገር ክህደት ወንጀል ነው ተባለ። ምን ይሄ ብቻ?
በየመንደሩ የከተማና የገጠር ነዋሪዎች በቀበሌና በከፍተኛ፤ አልያም በፆታና በእድሜ፣ በስራ ቦታና በሙያ አይነት... የመሰባሰብ ግዴታ መሰባሰብ፣ የሴቶች ማህበር፣ የወጣቶች ማህበር፣ የወዛደሮችና የመምህራን ማህበር ... ወዘተ የማህበር አባል የመሆን ግዴታ፣ እናም ፓርቲንና መንግስትን የማወደስ የግዴታ ሸክም ተጫነባቸው። ቢያንስ ቢያንስ በንጉሱ ዘመን፣ ተቃውሞና ትችት የመሰንዘር ብዙ ነፃነት ባይኖር እንኳ፤ አፍን ይዞ ዝም ማለት ይቻል ነበር። ከአብዮቱ በኋላ ግን፣ ለፓርቲና ለመንግስት እየሰገዱ ውዳሴ የመዘመር ግዴታ መጣ። አይን ያወጣ ዘመናዊ አፈና ብለን ልንሰይመው እንችላለን።
ያው፤ አፈና በሚኖርበት ዘመንና ቦታ ሁሉ፣ በዚያው መጠን ወከባ፣ እስርና ግድያ ይኖራል። በእርግጥ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ በቀጥታ ንጉሡን መተቸትና መቃወም ከባድ ቢሆንም፣ በጥቅሉ ጥንታዊውን የፊውዳል ሥርዓት መተቸት እንደ ወንጀል አይቆጠርም ነበር። ሃዲስ አለማዬህን ድርሰቶች በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። እንዲያም ሆኖ፣ የመመረረ ተቃውሞ የሚሰነዝሩና የሚቀሰቅሱ ሰዎች በንጉሡ ዘመን መታሰራቸውና አንዳንዶችም መገደላቸው አልቀረም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዋናዎቹ የሶሻሊዝም አቀንቃኞች መካከል በገናናነት ስሙ የሚነሳው ጥላሁን ግዛው፣ በንጉሡ መንግስት ነው የተገደለው። ስም እየጠቀሱ፣ እገሌና እገሊት ብለው እየቆጠሩ፣ በንጉሡ ዘመን እነማን እንደተገደሉ የሚዘረዝሩልን የታሪክ ሰዎችን የምናጣ አይመስለኝም። ችግሩ ምን መሰላችሁ? የ66ቱ አብዮት ይህንን ሁሉ ታሪክ ገለባበጠው። ከአብዮቱ በኋላ፤ የሚታሰሩና የሚገደሉ ሰዎችን በስምና በቁጥር ለመዘርዘር መሞከር ከንቱ ሆነ። እንዲያውም ያልታሰሩትን መቁጠር ነበር የሚሻለው። እንደተራ ነገር፣ ከየቤቱና ከየጎዳናው በሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን እያፋፈሱ በየቀበሌ ማጎር፤ ከዚያም እንደዘበት በረድፍ መረሸን... የአገራችን የሶሻሊዝም አብዮተኞች ያስመዘገቡት ውጤት፣ ከሌሎች አገራት ሶሻሊዝም አብዮተኞች የተለየ አይደለም። የጅምላ እስርና የጅምላ ግድያ፣ ሽብርና ጦርነት ነው ውጤቱ።
የአብዮተኞቹ ውጤት ግን ከዚህም የላቀ ነው። ራስወዳድነትን በማውገዝ የሰዎችን የብልፅግና ፍላጎት ለመስበር ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ግለኝነትን በመኮነን የንብረት ባለቤትነትን ለማጥፋት ያለ እረፍት ዘምተዋል። ዘመቻቸው ያለ ውጤት አልቀረም። በእርግጥ ቀድሞውንም ያን ያህል ንብረትና ብልፅግና አልነበረም። ነገር ግን፤ በአብዮተኞቹ ዘመቻ የብልፅግና ተስፋ ተዳፍኖ፣ የንብረት ምልክት ጠፍቶ፤ የአገሬው ሕዝብ ከቀድሞ በባሰ ድህነትና ችጋር ለከፋ ስቃይ ተዳርጓል።
በቀይ ሽብርና በነጭ ሽብር፤ በስልጣን ሽሚያና በጦርነት ከተፈጠረው እልቂት ያልተናነሰ ጥፋት የተከሰተውም በድህነት ምክንያት ነው። በ77ቱ ድርቅ፣ ወደ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች በረሃብ እንደሞቱ በወቅቱ ተዘግቧል። የውጪ ለጋሾች ተሯርጠው ደራሽ እርዳታ ባያቀርቡ ኖሮ፤ በ81 እባ በ82 ዓ.ም እንዲሁም በ92 ዓ.ም ሚሊዮኖች በረሃብ ያልቁ ነበር። ታዲያ፤ የያኔዎቹ አብዮተኞች፣ አሁን በየካቲት ወር ወይም ዘንድሮ በ2006 ዓ.ም ስለ አብዮቱ አርባኛ አመት፣ አንዳች ቁምነገር ለመናገር የሚያስችል አንደበት ማጣታቸው ይገርማል?
የኢቴቪ ዋና ዳይሬክተር ታስረው እንዲቀርቡ ታዘዘ
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት እየታየ በሚገኘው 28 ተከሳሾች ላይ ለቀረበ የአቃቤ ህግ የቪዲዮ ማስረጃ አስተርጓሚ እንዲመድብ የታዘዘው የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ድርጅት፤ የፍ/ቤቱን ትዕዛዝ ተግባራዊ ባለማድረጉ ዋና ዳይሬክተሩ ፍ/ቤት ታስረው እንዲቀርቡ ታዘዘ፡፡
በእነ አማን አሠፋ መዝገብ በሚገኙ የሽብር ተጠርጣሪዎች ላይ አቃቤ ህግ የሰው ምስክሮችንና በሺዎች የሚቆጠሩ የሰነድ ማስረጃዎችን ለፍ/ቤቱ አቅርቦ ያጠናቀቀ ሲሆን በአረብኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች ለቀረቡት የቪድዮ ማስረጃዎች ኢሬቴድ አስተርጓሚ እንዲመድብ ከፍ/ቤቱ የተላለፈውን ትዕዛዝ ተግባራዊ አላደረገም ተብሏል፡፡ በዚህም ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ ኪዳነማርያም ታስረው ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ታዟል፡፡
ቀደም ሲል እነዚህን የሽብር ተጠርጣሪዎች አስመልክቶ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “ጅሃዳዊ ሃረካት” የሚል ዶክመንተሪ ፊልም ተዘጋጅቶ መሰራጨቱ የሚታወስ ሲሆን አቃቤ ህግም በክስ ማመልከቻው፣ ተጠርጣሪዎች የአልቃይዳ ህዋስ ሆነው በአለማቀፍ የሽብር መዋቅር ውስጥ ተሳታፊ እንደነበሩ ማመልከቱ ይታወሳል፡፡
የህክምና ተቋማትን አሠራር የሚወስን አዲስ መመሪያ ወጣ
- መሥፈርቱን የማያሟሉ ከሐምሌ 1 ጀምሮ እርምጃ ይወሰድባቸዋል
- በሥራ ላይ ካሉት ክሊኒኮች መስፈርቱን የሚያሟላ አይኖርም ተብሏል
- የግል ክሊኒኮች ማህበር በቂ የዝግጅት ጊዜ ሊሰጠን ይገባል አለ
የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችላቸውን መስፈርቶችና ደረጃዎች የሚወስን አዲስ መመሪያ ወጣ፡፡ የጤና ተቋማቱ በአዲሱ መስፈርት መሰረት ራሳቸውን እንዲያደራጁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን ከሐምሌ 1 ጀምሮ መሥፈርቱን ባላሟሉት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ቁጥጥር ባለስልጣን ያወጣውና በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት ይመለከታል የተባለው አዲስ መመሪያ፤ ተቋማቱ ማሟላት የሚገባቸውን ዝርዝር ጉዳዮች ይፋ አድርጓል፡፡ በዚሁ መመሪያ ላይ እንደተገለፀው፤ ሆስፒታሎች የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፣ አጠቃላይ ሆስፒታልና ስፔሻላይዝይድ ሆስፒታል ተብለው በ3 መደቦች የሚከፈሉ ሲሆን የጤና ማዕከላት፣ የጤና ጣቢያዎችና ልዩ ማዕከላትም በዘርፉ እንደሚጠቃለሉ ተጠቅሷል፡፡
መመሪያው ሆስፒታሎች እንደየደረጃቸው የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት እንደሚገባቸው በዝርዘር የገለፀ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ቢያንስ 35 አልጋዎች፣ አጠቃላይ ሆስፒታሎች 50 አልጋዎች እንዲሁም ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ከ300 የማያንሱ አልጋዎች እንዲኖራቸው ያስገድዳል። ሁሉም የጤና ተቋማት የማዋለድ አገልግሎት መስጠት እንደሚገባቸው የገለፀው መመሪያው፤ በክሊኒኮች ውስጥ አልጋ በማዘጋጀት ህሙማንን በመደበኛነት አስተኝቶ ማከም እንደማይቻልና መካከለኛ ክሊኒኮች ለድንገተኛ ህመምና ለማዋለድ አገልግሎት የሚሆኑ 10 አልጋዎች ብቻ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይደነግጋል፡፡ ክሊኒኮችን በስም መሰየም እንደማይፈቀድም በዚሁ መመሪያ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የህክምና መሣሪያዎች ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የቁጥጥር አስተባባሪ ሲስተር የሺአለም በቀለ መመሪያውን ማውጣት ያስፈለገበትን ምክንያት ሲናገሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በጤናው ዘርፍ ተሰማርተው ለህዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ የጤና ተቋማትን ለመቆጣጠርና ተቋማቱ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ባለመቻሉ፣ ይህንን ችግር በማስወገድ ተቋማቱ የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግና ህብረተሰቡን ለአደጋ የሚያጋልጡ አሰራሮችን ለማስወገድ ነው ብለዋል። በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ህገወጥ ተግባራትን በመቆጣጠር ለህብረተሰቡ ብቃት ያለው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እንደሆነም አክለው ገልፀዋል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ የጤና ተቋማቱ የሚተዳደሩበትን መመሪያና መስፈርት ህግ አድርጎ ከማፅደቁ በፊት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጉን የጠቆሙት ሲስተር የሺዓለም፤ በመመሪያው ላይ የተካተቱና ለአሰራር እንቅፋት ይሆናሉ የሚባሉ ጉዳዮች ካሉ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እንደሚቻል በተደጋጋሚ መገለፁን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ መመሪያው ሊያሰራን አይችልም የሚል ሃሳብ ከየትኛውም ወገን ባለመነሳቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህግ ሆኖ እንዲፀድቅ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ድርጅቶቻቸውን በመመሪያው መሰረት እንዲያደራጁ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2006 ዓ.ም ድረስ ጊዜ እንደተሰጣቸውና የጊዜ ገደቡ ሲጠናቀቅ ባለስልጣን መ/ቤቱ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ የግል ክሊኒኮች ባለቤቶችና አሰሪዎች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር አቶ አበበ ያለው በበኩላቸው፤ መመሪያው የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበና በዘርፉ የተሰማሩ በርካታ ባለሙያዎችን ከስራ ውጪ የሚያደርግ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ ህብረተሰቡ ጥራት ያለው የህክምና አገልገሎት እንዲያገኝና ዘርፉም ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል ታስቦ የወጣውን መመሪያ እንደማይቃወሙ ምክትል ሊቀመንበሩ ገልፀው፤ሆኖም በአገሪቱ የተሰማሩ የጤና ተቋማትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበና ምንም የመፍትሔ ሃሳብ ያላቀረበ በመሆኑ ብዙዎችን ከስራ የሚያፈናቅል ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከ500 በላይ አባላት ያሉት ማህበሩ፤ አዲሱን ህግና መመሪያ ተከትሎ በመስፈርቱ መሰረት በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ አገልግሎት መስጠት ይቻላል ብለው እንደማያስቡ ገልፀው መንግስት በቂ የዝግጅት ጊዜና የጤና ተቋም መገንቢያ ቦታ ሊሰጠንና የብድር አገልግሎት ሊያመቻችልን ይገባልም ብለዋል፡፡ “እንደዚያ ካልሆነ የምንሰራው ከግለሰቦች በተከራየናቸው ክሊኒኮች በመሆኑ መስፈርቱ የሚጠይቀውን ለማሟላት ስንል ማፍረስም ሆነ መቀየር አንችልም” ሲሉ ችግራቸውን ጠቁመዋል፡፡ መስፈርቱን ካላሟላችሁ መስራት አትችሉም ከተባለ ግን በርካታ ባለሙያዎች ከስራ እንደሚፈናቀሉና ህብረተሰቡም በቂ አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገር መታወቅ ይገባዋል ብለዋል።
ሲስተር የሺዓለም በቀለ በበኩላቸው፤“በአገሪቱ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው አገልግሎት ከሚሰጡ የጤና ተቋማት መካከል አዲሱን መስፈርት በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉ ተቋማት ስለመኖራቸው አፍን ሞልቶ መናገር አይቻልም” ይላሉ፡፡
ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ 180 የሳኡዲ ተመላሾችን በነፃ ሊያስተምር ነው
እስካሁን ለ3ሺ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጥቷል
ሴንትራል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በቅርቡ ከሳኡዲ ለተመለሱ 180 ያህል ኢትዮጵያዊያን ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታወቀ፡፡ የዩኒቨርሲቲው መስራችና ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብነት ግርማይ፣ በዩኒቨርሲቲው ሾላ ካምፓስ ከትላንት በስቲያ የትምህርት እድሉ የተሰጣቸው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተወካይ፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና ጋዜጠኞች በተገኙበት በሰጡት መግለጫ፤ ዩኒቨርስቲያቸው ከዚህ ቀደም ከተለያዩ የመንግስትና የግል ተቋማት ለተመለመሉና ከፍለው መማር ለማይችሉ 3ሺህ ተማሪዎች ነፃ የትምህርት እድል መስጠቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴርን መስፈርት ላሟሉ የሳኡዲ ተመላሾች ተመሳሳይ እድል መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በሀዋሳና በባህርዳር በአጠቃላይ ስድስት ካምፓሶች ያሉት ሲሆን በእያንዳንዱ ካምፓስ 30 ተማሪዎች ገብተው እንዲማሩ መወሰኑ ተገልጿል፡፡
ተማሪዎቹን አስተምሮ ለማስመረቅ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚፈጅ የጠቆሙት ዶ/ር አብነት፤ ከሌቭል አንድ እስከ ዲግሪ ድረስ እንዲማሩ እድሉ መመቻቸቱን ገልፀዋል፡፡ የትምህርት አሰጣጡንና አጠቃላይ የዩኒቨርስቲውን ድባብ በተመለከተ ተማሪዎቹ ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ የሚፈልጉትን የትምህርት አይነት፣ የት መማር እንደሚሹና የሚማሩበትን ሰዓት መምረጥ እንደሚችሉ ዶ/ር አብነት ተናግረዋል። “ትምህርታችሁን ጀምራችሁ እስክታጠናቅቁ ድረስ ራሳችሁን፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁንና የከተማ አስተዳደሩን የሚያስከብር ስርዓት እንድትከተሉ እጠይቃለሁ” ሲሉም ለተማሪዎቹ ምክርና ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ተወካይ በበኩላቸው፤ቢሯቸው ተማሪዎቹንና የትምህርት አቀባበል ሁኔታቸውን እንደሚከታተል ገልፀው፣ ለሁሉም መልካም እድል ተመኝተውላቸዋል፡፡ እድሉ የተሰጣቸው ተማሪዎችም ነፃ የትምህርት እድሉን በማግኘታቸው ከተማ አስተዳደሩንና ዩኒቨርሲቲውን አመስግነው ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል ቃል ገብተዋል፡፡
“የአባቴ ምክሮችና ሀሳቦቼ” ለንባብ በቃ
በዶክተር ብርሃኑ ደመላሽ የተፃፈውና በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተው የአባቴ ምክሮች ሀሳቦቼ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል።
95 ገፆች ያሉት መጽሐፍ፤ የደራሲው የመጀመሪያ ስራ ሲሆን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥንም ተገልጧል፡፡ መፅሐፉ መታሰቢያነቱ ለደራሲው ወላጅ አባት እና በፖለቲካ ምክንያት ለተሰዉ ዜጎች ሆኗል፡፡
መፅሐፉ በ30 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
“የፍቅረኞች ቀን” በአዲስ አበባ የተለያዩ ሥፍራዎች ተከበረ ይከበራል
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአገራችን በተለያዩ ሆቴሎችና የመዝናኛ ስፍራዎች መከበር የጀመረው የፍቅረኛሞች ቀን (Valentine’s Day)፤ በዛሬው ዕለት በከተማዋ የተለያዩ ሥፍራዎች ይከበራል፡፡
በዓሉ ከሚከበርባቸው ሥፍራዎች መካከል ኢስተምቡል ሬስቶራንት፣ ዲ ኤች ገዳ ታወር፣ ሐርመኒ ሆቴልና ቬልቪው ሆቴሎች የሚገኙበት ሲሆን በዓሉ በአበባና የተለያዩ ስጦታዎች፣ በሙዚቃ ድግስ፣ በጣፋጭ ምግቦች ዝግጅትና በትዊስት እንደሚደምቅ አዘጋጆች አስታውቀዋል።
የኔታ ኢንተርቴይመንትና ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን በትብብር ባዘጋጁት “የፍቅረኛሞች ቀን” በተለያዩ የኪነጥበብ ዘርፎች የላቀ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ባለሙያዎች እንደሚሸለሙ ታውቋል፡፡
ስለት
…ሰናይት ይሏታል፡፡ እኔ ሰኒ እላታለሁ፡፡ ከተዋወቅን ያለፈው ሰኔ ሚካኤል 3ኛ አመታችንን ደፈንን፡፡ ዝም ብሎ መተዋወቅ እንዳይመስላችሁ፡፡ ከመላመዳችን የተነሳ ፊቷን አይቼ ምን እንደምታስብ መገመት ሳይሆን ማወቅ ጀምሬያለሁ፡፡
እወዳታለሁ፡፡
እሷም “እወድሃለሁ” ትለኛለች፡፡
3ኛ አመታችንን ባከበርን ማግስት እድል እጇን ዘረጋችላት፡፡ ስትዘረጋላት “ልጨብጣት ወይ?” ብላ አማከረችኝ፡፡ “ምን ይጠየቃል ጨብጫት እንጂ” አልኳት፡፡ “እንዴት እንዲህ ትለኛለህ? ያንተ እጅ እያለ ባትወደኝ ነው እንጂ…” ብላ አኮረፈችኝ፡፡
ቶሎ ታኮርፋለች፡፡ ጥቃቅን ነገሮች ሁሉ ያስኮርፏታል፡፡ ብስክስክ ናት፡፡ እኔም አመሏን ለምጀዋለሁ፡፡ እሷም አልፎ አልፎ ቱግ የምለውን ነገር ታውቅልኛለች፡፡ መቻቻል ማለት ይሄ አይደል…ቢሆንም ይሄ አመሏ አንዳንዴ ትዕግስቴን ይፈታተነኛል፡፡
ከሰኒ ጋር የት ተገናኘን?
ቡና ቤት! (ለማንም ግን አይነገርም፤ ምስጢር ነው፤ በተለይ በተለይ ቤተሰብ እንዳይሰማ!)
ስንላመድ ከቡና ቤት አውጥቼ መጀመሪያ ወደ ልቧ፣ ኋላም ወደ ቤቴ አስገባኋት፡፡ ስትረጋጋ ቤተሰቤን ልጠይቅ አለችኝ ፈቀድኩላት፡፡ ያኔ እግረ መንገዷን ከእድል ጋር ተገናኘች፡፡
ታድያስ የእድሏ በር የተከፈተው በኔ ምክንያት አይደለምን? በሩን ባልከፍተው ቁልፉን ያቀበልሁ እኔ አይደለሁምን?
ውጭ ሀገር መሰደድ እንደ ሎተሪ በሚታይባት ሀገር ውስጥ ከዚህ የበለጠ ምን ጥሩ እድል አለ ጃል? አለ እንዴ? የለም እኮ!!
መሄድ የለብሽም ብላት በጄ እንደማትል ልቦናዬ እያወቀው፣ አፌን ለምን አበላሻለሁ ብዬ “ይቅናሽ” ብላት በአትወደኝም ተተረጐመብኝና በለመድኩት ኩርፊያ ገረፈችኝ፡፡
ውጭ ሀገር ለመሄድ 1…2 …ማለት ተጀመረ፡፡ ግን “ፕሮሰሱ” እንደታሰበው እንደጥንቸል ሊሮጥ አልቻለም፡፡
አንድ ቀን ይሄን “ውጭ” የሚለውን ልቧን ወደ ውስጥ ለመሳብ በማሰብ፣ ሻይ ቡና ልበልሽ ብዬ አንድ እኔ ነኝ ያለ ካፍቴሪያ ውስጥ ቋጠርኳት፡፡ አንድ ሁለት እያልን ጨዋታችንን አደራነው፡፡ ልክ እንደጥንቱ…ከወትሮው ልማዳችን በሹካ መጐራረሱን ብቻ ትተን…ልክ እንደ ጥንቱ በደንብ አወጋን፡፡
ምንጭ፡- (ባለ “ሚኒስከርቷ” የሥነግጥምና የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ)
“ትልቅ ስኬት የሚያስመዘግብ እንጂ የሚያጐድል አሰልጣኝ መመረጥ የለበትም”
ሚሉቲን ሴርዶጄቪች (ከኡጋንዳ፤ ካምፓላ)
ከሩብ ምዕተ ዓመት ውድቀት በኋላ የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ ባለፉት ጥቂት አመታት ማንሰራራቱና በአፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ቤተኛ እየሆነ መምጣቱ አንድ እርምጃ ነው፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ክለቦች፣ ስፖንሰሮች፣ ደጋፊዎች እና የፌዴሬሽን አመራሮች እንደየድርሻቸው ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን በዚሁ አህጉራዊ መድረክ ጠንካራ ተፎካካሪ የመሆን ምኞታችን ገና አልተሳካም፡፡ ፈተናውም ከእስካሁኖቹ ሁሉ የከበደ ነው፡፡ ለዚህም ነው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ምርጫ፤ የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ የማይገርመው፡፡
ለዚህ ትልቅ ሃላፊነት የሚመጥንና የሚስማማ አሰልጣኝ ለመምረጥ በተጀመረው እንቅስቃሴ፤ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሙያዎች በእጩነት ስማቸው እየተጠቀሰ ውይይት መሟሟቁም ተገቢ ነው፡፡ የተጀመረው ውይይትም፤ በቅንነት፣ በብስለት እና በእውቀት እየዳበረ መሄድ አለበት፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ ቀደም ሲል በኢትዮጵያና በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ አገራትና በደቡብ አፍሪካ የታወቁ ክለቦችን ያሰለጠኑ፤ እንዲሁም አስቀድሞ የሩዋንዳ አሁን ደግሞ የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑትን የ44 ዓመቱ ሰርቢያዊ ሚሉቲን “ሚቾ” ሴርዶጄቪች በአሰልጣኞች ምርጫ ዙሪያ አወያይተናቸዋል፡፡
እንደምታውቀው እኔ ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ነኝ። የትኛውም ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ደግሞ ስለደሞዙ በይፋ ለመናገር ፈቃደኛ አይሆንም፡፡ ስለዚህም ከመናገር እቆጠባለሁ፡፡ ምክንያቱም መቼም ቢሆን የኔ ሩጫ ገንዘብ ለማግኘት አይደለም፡፡ ይልቁንም የሁልጊዜ ፍላጎቴ፣ ራዕይ ላለው ፕሮጀክት መስራት ነው፡፡ እውነት ለመናገር፤ በአሰልጣኝነት በሰራሁባቸው አገራት ሁሉ ከማገኘው ንዋይ ይልቅ የምሰጠው አገልግሎት እና በትጋት ሰርቼ የማልፈው ይበልጣል፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፤ በአሁኑ ጊዜ ከውጭ አሰልጣኞች መካከል በምስራቅ አፍሪካ የእግር ኳስ መድረክ ለረጅም ጊዜ በመቆየት ቀዳሚውን ስፍራ ለመያዝ የበቃሁት፡፡ በምስራቅ አፍሪካ አገራት በ14 ዓመታት የስራ ጊዜ ከፍተኛ ልምድ አካብቻለሁ፡፡ ሁሉም የሚያውቀው ደግሞ ለ5 ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደታማኝ ወታደር አገልግያለሁ፡፡ እናም በአሰልጣኝነቴ ከገንዘብ ይልቅ በስራዬ ከፍ ያለ ስኬት እና የማይረሳ ታሪክ ትቼ ማለፉን በይበልጥ እፈልገዋለሁ፡፡
አሁን በስራ ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም፤ በስራዬ በኖርኩባቸው አገራት ውስጥ ከፌዴሬሽኖች እና ከእግር ኳስ ተቋማት ጋር ያለኝ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ስለዚህም በፌደሬሽን ስራዎች ላይ ጣልቃ ገብቼ ይህን አሰልጣኝ በዚህ ምክንያት ቅጠሩ በማለት ምክር በመስጠት ክብር ለመጋፋት አልፈልግም፡፡ ዋናው ነገር ኢትዮጵያ በአስደናቂ የባህል ትውፊቶቿ፤ ታሪኳ እና የአኗኗር ዘይቤ ልዩ አገር ናት፡፡ ይህን ክብር በመጠበቅ እና በማክበር፤ ከአገሬውና ከህዝቡ ጋር ተዋህዶ ሊሰራ የሚችል ሰው ያስፈልጋታል። ብሄራዊ ቡድኑ ከፊታችን ለሚጠብቁት ውድድሮች ረዥም የዝግጅት ጊዜ የለውም፡፡ ለ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር የሚደረገው ከ8 ወራት በኋላ ነው፡፡ ይህ የማጣርያ ውድድር በመስከረም አካባቢ ተጀምሮ በ3 ወራት ውስጥ 6 ጨዋታዎች የሚደረጉበት ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ይህን ከባድ ማጣርያ በከፍተኛ ዝግጅት በብቃት መወጣት እንዲችል በፍጥነት ውጤታማ አሰልጣኝ ያስፈልገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሰሩ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ጋር በታላቅ የስራ ፍቅር ተከባብሮ እና በጓደኝነት ተቀራርቦ የመስራት ልምድ አለኝ፡፡ ይህ ደግሞ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውንም ይጨምራል፡፡ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ለፈፀሟቸው ስኬታማ ተግባራት አድናቆት አለኝ፡፡ ሌሎችንም አደንቃለሁ ለጊዜው ግን፣ የአሰልጣኝ ምርጫ በሚካሄድበት ወቅት ከኢትዮጵያዊ አሰልጣኞች እገሌን ብዬ አድናቆቴን ብገልጽ ተገቢ አይሆንም፡፡ ግን እርግጠኛ ነኝ፤ በሙያችን የተዋወቅን አሰልጣኞች ሁሉ፤ ያለኝን ከበሬታ እና አድናቆት ያውቃሉ፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በከፍተኛ ትጋት የሚሰሩ እና የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንዲያንሰራራ ሁሉም በላቀ ደረጃ አስተዋፅኦ እንደነበራቸው አስባለሁ፡፡ በአሰልጣኝነት ሙያዬ ከኢትዮጵያውያን ጋር በመስራቴ ብዙ ትምህርት እና ልምድ ተጋርቻለሁ፤ አጋርቻለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ለሁሉም ያለኝን የከበረ ምስጋና እገልፃለሁ፡፡ ባለሙያዎችን በስም እየጠራሁ ያልዘረዘርኩት አሁን ጊዜው ስላልሆነ ነው፡፡ በቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ግን የማስበውን ነገር ሁሉ በዝርዝር ለመናገር ወደኋላ አልልም፡፡
የውጭ አገር አሰልጣኞችን በተመለከተ አሁን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላለበት አጣዳፊ ሁኔታ የሚሆን ባለሙያ በተፈለገው መስፈርት እና ብቃት በቀላሉ ማግኘት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ እኔም ለዚህ ሃላፊነት የሚመጥንና የሚስማማ የውጭ አሰልጣኝ ማን ነው ብባል፤ አንድም ሰው በአዕምሮዬ ሊመጣ አይችልም። ጥሩ አሰልጣኝ ለማግኘት በቂ ጊዜ ወስዶ መስራት ያስፈልጋል። ለአዲሱ አሰልጣኝ ቅጥር የሚሰሩትን ሁሉ በስራቸው እግዚአብሔር ይርዳቸው ነው የምለው። አሰልጣኝ ምርጫ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ አሁን እግር ኳሱ ባለበት የተነቃቃ መንፈስ ለተሻለ ለውጥና ለላቀ እድገት በብቃት ተስማምቶ የሚያገለግል ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ አፍቃሪዎች ካላቸው ትልቅ ስሜት ጋር የሚስተካከል ትልቅ ስኬት ለማስመዝገብ የሚሰራ አሰልጣኝ እንጂ የሚያጎድል ሰው መመረጥ የለበትም፡፡ ማንም ሰው ደጋፊዎችን የማስከፋት እና ተስፋ የማስቆረጥ መብት የለውም፡፡ ከዚህ ጥቅል አስተያየት ባሻገር፣ የአሰልጣኝ ምርጫን በተመለከተ ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የተነሳ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እገሌ ብዬ ለመጠቆም አሁን አልችልም፡፡
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝንት ከሚፈለጉ እጩዎች አንዱ ሆኜ ስሜ በመነሳቱ ብቻ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው፡፡ ለአሰልጣኝነቴ ዋጋ የሰጠ እውቅና በመሆኑ ከልብ ያስደስተኛል፡፡ አንድ ባለሙያ፣ ከምንም ነገር በላይ ለሙያው እውቅና ሲሰጠው ነው እርካታ የሚሰማው፡፡ ቢሳካ፤ ህልሜ እውን እንደሆነ እቆጥረዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ሁሉም አሰልጣኞች ትልልቅ ብሄራዊ ቡድኖችን በሃላፊነት ለመምራት ይፈልጋሉ፡፡ ሃቁን ልንገርህ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለእግር ኳስ ያላቸውን ፍቅር እና ስሜት እንዲሁም ልዩ ብሄራዊ ክብራቸውን ለሚያውቅ ሰው፤ ይህን ትልቅ ሃላፊነት ሲያገኝ፣ የዘወትር ህልሙ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ትልቁ ሃይል፤ በሃላፊነታቸው ለህዝብ ደስታን መፍጠር ነው፡፡ ለ90 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ደስታ መፍጠር የሚቻልበት ሃላፊነትን ማግኘት እጅግ ያጓጓል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ታላቅ ክብር ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ፣ አሁን መስቀለኛ መንገድ ላይ ያለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተፈጠሩ መነቃቃቶች እና ውጤቶች ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ ማንም አይፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የአጭር እና የረጅም ጊዜ ውጤታማ እቅዶችን የያዘ ብቁ አሰልጣኝ የሚያስፈልገው። የአጭርጊዜ እቅዱ በ2015 በሞሮኮ የሚስተናገደው 30ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነው፡፡ የረጅም ጊዜ እቅዱ ደግሞ በ2018 ራሽያ የምታስተናግደው 21ኛው የዓለም ዋንጫ ነው፡፡ አዲሱ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ እነዚህን አቅዶች ማሳካት የሚችል ፤ የተነቃቃውን ለውጥ በማስቀጠል ለላቀ እድገት የሚተጋ ሊሆን ይገባል፡፡ በምንኖርባት ፕላኔት ውስጥ፤ ለዚህ ሃላፊነት የሚስማማ፤ ይህን ከባድ ሃላፊነት በብቃት መወጣት እና መስራት የሚችል አንድ ባለሙያ አውቃለሁ፡፡ ግን እገሌ ብዬ ስሙንና ማንነቱን ለመንገር መብት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰው፤ በሌላ አገር የኮንትራት ስራ ላይ ስለሚገኝ ነው፡፡
እንደሁልጊዜው ልባዊ መልካም ምኞቴን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ለአንተም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም፡፡ በርቱ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ትክክለኛ ቦታው ከምርጦች ተርታ ነው፡፡ እዚያ ቦታ እንዲደርስ ሁላችሁም በህብረትና በትጋት ስሩ፡፡ ከስምንት አመት በፊት ከጋዜጣችሁ ባደረግነው ቃለምልልስ፣ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ብትሆን በማለት መልካም ምኞትህን ገለጽህልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የመሆን ልባዊ ምኞት እንዳለ ሆኖ፤ እኔ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆንኩ አልሆንኩ ምንግዜም የዋልያዎቹ ቁርጠኛ ደጋፊ ሆኜ እቀጥላለሁ፡፡
መከላከያ በሜዳው፤ ደደቢት ከሜዳ ውጭ ጥሎ ለማለፍ ይፋለማሉ
በ2014 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ ደደቢት እና መከላከያ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎቻቸው የምስራቅ አፍሪካ ክለቦችን ጥሎ ለማለፍ ትንቅንቅ ያደርጋሉ፡፡ ከሳምንት በፊት ደደቢት በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የዛንዚባሩን ኬኤምኬኤም በሜዳው 3ለ0 ሲያሸንፍ ጎሎቹን ዳዊት ፍቃዱ፤ ሺመክት ታደሰ እና ማይክል ጆርጅ ከመረብ አሳርፈዋል፡፡ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ መከላከያ ከሊዮፓርድስ ከሜዳ ውጭ በተገናኘበት ጨዋታ 2ለ0 ተሸንፏል፡፡
በኬንያው ብሄራዊ ስታድዬም ናያዮ በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለሊዮፓርድስ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠሩት አምበሉ ማርቲን ኢምባላምቦሊ እና ጃኮብ ኬሊ ናቸው፡፡ ደደቢት ከኬኤምኬኤም ጋር ከሜዳው ውጭ በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ከ2ለ0 በታች መሸነፍ፤ አቻ መውጣትና በማናቸውም ውጤት ማሸነፍ ጥሎ ለማለፍ ይበቃዋል፡፡
መከላከያ ደግሞ የኬንያውን ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ በሜዳው አስተናግዶ 3ለ0 ከዚያም በላይ በማሸንፍ የማለፍ እድሉን ይወስናል፡፡ በቅድመ ማጣርያው ከኢትዮጵያው ደደቢት እና ከዛንዚባሩ ኬኤምኬኤም ጥሎ ማለፍ የሚችለው ክለብ በአንደኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ የሚገናኘው ከቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ኤስፋክሲዬን ጋር ነው፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያው መከላከያ እና ከኬንያው ኤኤፍሲ ሊዮፓርድስ ጥሎ የሚያልፈው በአንደኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ የሚገናኘው ከደቡብ አፍሪካው ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ ወይም ከቦትስዋናው ጋብሮኒ ዩናይትስድ አሸናፊ ጋር ይሆናል፡፡ ሱፕር ስፖርት ዩናይትድ በቅድመ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ጋብሮኒ ዩናይትድስን 2ለ0 አሸንፎታል፡፡