Administrator

Administrator

የመንግስት ስልጣን ገደብ ቢኖረው ኖሮ ሚኒስትር ዲኤታው ፍ/ቤት ይቆሙ ነበር - ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ናፍቆት ዮሴፍ “ሰማያዊ ፓርቲ፣ ግንቦት ሰባት እና አክራሪዎች ጋብቻ ፈጽመዋል” በሚል የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ መናገራቸውን የተቃወሙት የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፤ “የፀረ ሽብር አዋጁ ካልተቀየረ ማንም አይምርም፣ የመንግስት ስልጣን ገደብ ቢኖረው ኖሮ ሚኒስትር ዴኤታው ፍ/ቤት መቆም ነበረባቸው” በማለት ምላሽ ሰጡ፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ በህዝብ ስም የተቋቋመ ስለሆነ የመንግስት ድክመቶችንና ክፍተቶችን እንዲያስተካክል መታገል ስራው ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ መንግስት የህዝብን ጥያቄ ከመመለስ ይልቅ መፈረጅ ይቀናዋል፤ ይህ ግን ከትግላችን አያግደንም” ብለዋል፡፡

“ከሁለት ወር በፊት የህዝብ ችግሮችና ጥያቄዎች ናቸው ብለን በሰላማዊ ሰልፍ ያሰማናቸው ጥያቄዎች አልተመለሱም” ያሉት ኢ/ር ይልቃል፤ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሁለተኛውን ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ “ኢትዮጵያ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ገና አልገባችም፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ገና የስልጣን ባለቤት አልሆነም” ያሉት ኢንጂነሩ፤ እነዚህ ነገሮች እውን እንዲሆኑ በምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ በሰላማዊ መንገድ የሚታገልን ፓርቲ ከአሸባሪዎች ጋር ጋብቻ ፈጽሟል በማለት መወንጀል የአገዛዝ ባህሪ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ አሸባሪ የሚለው ቃል ትርጉሙን ስቷል የሚሉት ኢ/ር ዘለቀ፤ የፀረ ሽብር አዋጁ እስካልተቀየረ ድረስም ማንንም ከመፈረጅ የሚያግድ ነገር የለውም ብለዋል።

ከደቡብ ኮሪያው ግዙፍ የኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ ሳምሰንግ የመጡ 100 አባላት ያሉት የበጐ ፈቃደኞች ቡድን፣ በቢሾፍቱ የህክምና ስልጠናዎችን በመስጠትና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በመለገስ ለአምስት ቀናት አገልግሎት እንደሰጡ ተገለፀ፡፡ ከሐምሌ 29 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 3 ቀን 2005 ዓ.ም በተካሄደው የበጐ ፈቃድ አገልግሎት፣ ለቢሾፍቱና አካባቢዋ ነዋሪዎች የተለያዩ ህክምናዎችና የመድሀኒት አቅርቦት ተሰጥቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሕሙማን ወደ ኮሪያውያኑ በጎፈቃደኞች በመምጣት፣ የህክምና አገልግሎት ያገኙ ሲሆን ህክምናው ሙሉ ምርመራንና የመድሀኒት አቅርቦትን ያጠቃልላል፡፡
የበጐ ፈቃደኞች ቡድኑ ከህክምና ባለሙያዎች በተጨማሪ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሙያ ላይ የተሰማሩ አባላትንም ያካተተ ሲሆን በቢሾፍቱ ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ግቢ ውስጥ ለአምስት ቀናት አገልግሎት ሲሰጡ መቆየታቸውም ታውቋል፡፡

Saturday, 03 August 2013 11:25

“የግጥም በጃዝ”

ሁለተኛ ሻማ ረቡዕ ይለኮሳል

በወጣት ከያንያን ተቋቁሞ ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን፣ ሙዚቀኞችና ሌሎች የጥበብ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት “ግጥምን በጃዝ” ኪነጥበባዊ ዝግጅት፤ ሁለተኛ ዓመት ክብረ በዓሉን በመጪው ረቡዕ 11፡30 በብሔራዊ ትያትር እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከቀረቡት ዝግጅቶች ላይ ተመርጠው የተሰናዱ ሥራዎች “ጦቢያ” በሚል ርዕስ በዲቪዲ የታተመ ሲሆን በ50 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል።
በረቡዕ ዝግጅት ላይ በአንደበተ ርቱዕነታቸው የሚታወቁት መምሕር እሸቱ አለማየሁ በተመረጠ ርእሰ ጉዳይ ላይ ዲስኩር የሚያሰሙ ሲሆን ገጣሚ ነቢይ መኮንን፣ ተፈሪ አለሙ፣ ጌትነት እንየው፣ አበባው መላኩ፣ ግሩም ዘነበ፣ ምስራቅ ተረፈ፣ ምህረት ከበደ፣ ሜሮን ጌትነት፣ ደምሰው መርሻ እና ምንተስኖት ማሞ የግጥም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በኤምቢዜድ ፊልም ፕሮዳክሽን የተዘጋጀው “ያልታሰበው” የተሰኘው ፊልም ነገ በአዲስ አበባ በሚገኙ የግል ሲኒማ ቤቶች ይመረቃል፡፡ የ103 ደቂቃ ርዝመት ያለው ፊልሙ ድራማቲክ ኮሜዲ ሲሆን፤ በማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ የሚገጥሙንን ልዩ ልዩ ጉዳኞች በአዝናኝና አስተማሪ ትእይንቶች እያዋዛ ቁም ነገር የሚያስጨብጥ ነው ተብሏል፡፡ በፊልሙ ላይ ከ90 በላይ አንጋፋና ወጣት ተዋንያን ተውነውበታል፡፡    

“ሞት ያልገታው ጉዞ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መጽሐፍ ዛሬ ከጠዋቱ 3፡00 ሰአት በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ይመረቃል፡፡ በደራሲ ሶስና ደምሴና በበየነ ሞገስ የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በክቡር ብላታ ደምሴ ወርቅ አገኘሁ የህይወት ታሪክ ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን በአምስቱ ዓመታት የጠላት ወረራ ወቅት ወገኖቻችን የደረሰባቸውን ሰቆቃና ጀግኖች አርበኞች ለነፃነታቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት ይተርካል፡፡ መጽሐፉ በቅርቡ በተለያዩ የመጽሐፍት መደብሮች ለሽያጭ ይቀርባል ተብሏል፡፡

ዘወትር ሐሙስ ከቀኑ 9-10 ሰዓት እና እሁድ ከ11-12 ሰዓት የሚቀርብ “እፎይታ” የተሰኘ የሬዲዮ ዝግጅት በኤፍኤም አዲስ 97.1 እንደሚጀምር ኪኖ ፕሮዳክሽን እና አርት ሶሉሽን አስታወቁ፡፡
ፕሮግራሙን “የወንዶች ጉዳይ” ቁጥር ፩፣ እና የ“ፔንዱለም” አዘጋጅ ሄኖክ አየለ፣ የ“ሚስኮል” ፊልም አዘጋጅ ደረጄ ምንዳዬ፣ አንጋፋዋ ድምጻዊት ነፃነት መለሰ እና ድምጻዊት አበባ ላቀው እንዲሁም የሙዚቃ ቪዲዮ ዳይሬክተሩ ፍፁም ይላቅ እንደሚያዘጋጁት ታውቋል፡፡

የሰዓሊ ሳሙኤል ሀብተአብ የፎቶግራፍ ሥራዎች የተሰባሰቡበት የፎቶግራፍ ትርዒት ትናንት ምሽት ሳር ቤት አካባቢ በሚገኘው ጋለሪአ ቶሞካ መቅረብ ጀመረ፡፡ ትርኢቱ እስከ ነሐሴ 23 ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ነሐሴ 19 ከጧቱ 4 ሰዓት በሰዓሊው ሥራዎች ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሏል፡፡

በፈለቀ ካሳ ጥንድ ፕሮሞሽን የሚዘጋጀው የጥበብ ምሽት፣ የመጀመሪያ ዝግጅቱን ከትናንት በስቲያ ማታ ቦሌ በሚገኘው ሻላ አዳራሽ ቀረበ፡፡ በየወሩ አንድ ደራሲና አንድ ሙዚቀኛ የሚቀርቡበት ኪነጥበባዊ ዝግጅት የመግቢያ ዋጋ በግለሰብ 50 ብር ሲሆን ከዚሁ ገቢ በየወሩ ለአንድ ሕጻን 200 ብር በመመደብ አምስት ሕጻናትን ለመንከባከብና ለማስተማር ይውላል፡፡ የጥበብ ምሽቱ በኮሜዲ ዝግጅቶችም እንደሚታጀብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

በጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ሽፈራው የተዘጋጁ ስድስት የተረት መፃህፍት ሰሞኑን ለንባብ በቁ፡፡ “ባለማሩ ገላ ሰውዬ”፣ “ደግ ለራሱ”፣ “ደጓ ዳክዬ ”፡ “ሆዳሙ ዘንዶ”፣ “ቀብራራዋ ድመት” እና “ትንሿ ሻሼ” የተሰኙት መፃህፍት ህፃናትን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ሲሆኑ የንባብ ልምድ በማዳበር ረገድም ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉ አዘጋጁ ተናግሯል፡፡ መፃህፍቱ እያንዳንዳቸው በ15.00 ለገበያ ቀርበዋል፡፡ ብር ጋዜጠኛና ደራሲ ቴዎድሮስ ሽፈራው፤ በኤፍ ኤም 96.3 የተለያዩ ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጅ ሲሆን በተለይ “ቀይ መብራት” በሚለው ፕሮግራሙ ይታወቃል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በደራሲ ሊዛ ተሾመ ተጽፎ የቀረበው “አሜኬላ ያደማው ፍቅር” ረዥም ልቦለድ መፅሃፍ ተሻሽሎ በድጋሚ ለንባብ በቃ፡፡ “በፍቅር ዓለም በራስ ላይ ማዘዝ ከባድ ነው” የሚለው ልቦለድ መጽሐፍ፤ ለደራሲዋ ሁለተኛዋ ሲሆን ካሁን በፊት “ፍትህን በራሴ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ አብቅታለች፡፡ 268 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ በኢንተርናሽናል ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ማተሚያ ቤት የታተመ ሲሆን ለሀገር ውስጥ ገበያ 45.60 ብር፣ ለውጭ ገበያ ደግሞ 10 ዶላር ይሸጣል፡፡