Administrator
ሁሉም ነገር ይለመዳል? እንደ ታክሲ ወረፋ
የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ቢሮ፣ ውጤት እያስመዘገብኩ ነው አለ እንዴት ቢባል፤ የታክሲ ስምሪት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማካሄድ ነዋ ሌላ አዲስ አበባ ካለ ይነገረን፤ ነባሯ ከተማ ግን ታክሲ ተቸግራለች ገና ምኑን አይታችሁ? የትራንስፖርት ሚኒስትርም ያሰበው ነገር አለ ከከተማ ውጭ፣ ማታ ማታ የመኪና ጉዞ ክልክል ይሆናል ተብሏል በዚህም ውጤት ይመዘገባል - የትራንስፖርት እጥረትን የሚያባብስ ሜክሲኮ አካባቢ፣ የስራ መውጫ ሰዓት ላይ፣ ወደ ጦር ሃይሎችና ወደ አውቶቡስ ተራ ለመሄድ አዳሜ ይጋፋል።
ከወዲያ ማዶ፣ ወደ ሳሪስና ወደ ጎፋ፣ መዓት ሰው ይተራመሳል። ወዲህ ዞር ስትሉም፣ ወደ መገናኛ ለመሄድ የሚጠብቅ እልፍ ሰው ታያላችሁ። የታክሲ ስምሪት ከታወጀ በኋላ፣ የትራንስፖርት እጥረት ተባብሶ፣ ግፊያውና ግርግሩ ጨምሯል። ለዚህም ነው፤ በርካታ ፌርማታዎች ላይ ወረፋ የተጀመረው። እዚያው ሜክሲኮ አካባቢ በገሃር መስመር፤ ወደ አራት ኪሎ ታክሲ ለመሳፈር የሚፈልግ ከ150 በላይ ሰው በሁለት አቅጣጫ ተሰልፏል። ታክሲ ጠፋ! ለነገሩ “ታክሲ ጠፍቷል አልጠፋም” ለማለት ያስቸግራል።
ወረፋ ከሚጠብቁ ሰዎች አጠገብ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው ቆመዋል። ግን ወደ ቦሌ መስመር የተመደቡ ናቸው፤ ከዚያ ውጭ ቢንቀሳቀሱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል። ምን የሚሉት ቅዠት ነው? ከመቶ በላይ ሰዎች ታክሲ አጥተው ለወረፋ ተገትረዋል፤ ከአስር በላይ ሚኒባስ ታክሲዎች ተሳፋሪ አጥተው በሰልፍ ቆመዋል። ወረፋ ጠብቀው አራት ኪሎ ሲደርሱም፣ ነገርዬው ተመሳሳይ ነው። ከአራት ኪሎ ወደ ፒያሳና ወደ መርካቶ ለመሄድ ብዙ ሰዎች ይሻማሉ - በታክሲ እጥረት። ዞር ብለው ሲያዩ ግን፣ ከአራት ኪሎ ወደ አምባሳደር መስመር የተመደቡ በርካታ ሚኒባሶች፣ ተሳፋሪ ጠፍቶ አፋቸውን ከፍተዋል።
ተሳፋሪ ወደሚበዛበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉማ። በደርግ ዘመን የነበረውን የታክሲ ስምሪት እንደገና ተግባራዊ ለማድረግ ውሳኔ ያስተላለፉ ባለስልጣናት፤ ገና ከጅምሩ መዘዙን ማሰብ አይችሉም ነበር? ይችሉ ነበር። ሰው ናቸው። ደግሞም፣ እነሱ ባይችሉ እንኳ፣ አስቦ የሚመክር አልጠፋም ነበር። ለምሳሌ፣ የስምሪት ቁጥጥር በግንቦት 2003 ዓ.ም ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በአዲስ አድማስ የወጡ ፅሁፎችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። የታክሲ ስምሪት የትራንስፖርት እጥረትን በማባባስ አሁን የምናየውን አይነት ቅዠት እንደሚፈጥር በግልፅ ተንትኖ የሚያቀርብ ፅሁፍ በአዲስ አድማስ መቅረቡን አስታውሳለሁ (የካቲት 26 ቀን 2003 ዓ.ም የአዲስ አድማስ እትም)። “በየአቅጣጫውና በየመስመሩ፤ የትራንስፖርት ፈላጊዎች ብዛት እንደእለቱና እንደሰአቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው ይለያያል።
... የሰኞ፤ የአርብ፣ የቅዳሜና የእሁድ ተሳፋሪዎች ቁጥር ተመሳሳይ አይሆንም። ማለዳ 11 ሰአት፤ ጥዋት ሁለት ሰአት፤ ረፋዱ ላይ፣ ከቀኑ 11 ሰአት፤ ከምሽቱ ሶስት ሰአት በኋላ በዚያው መስመር የሚኖረው የተሳፋሪ ቁጥር… ይለያያል። በክረምት፤ በበአል ቀናት፣ በልዩ ዝግጅቶች፣ በሰርግ ወራትም እንዲሁ ለየቅል ነው። “...ታክሲዎች የራሳቸውን ገቢ ለማሳደግ ብዙ ተሳፋሪ ማግኘት ስላለባቸው፤ በእያንዳንዱ መስመር ላይ እንደሰአቱና እንደእለቱ፣ እንደወቅቱና እንደሁኔታው የሚለዋወጠውን የተሳፋሪ ቁጥር በማስተዋል (መስመራቸውን እያስተካከሉ) ለመስራት ይጣጣራሉ። ... በስምሪት ቁጥጥር ከተመደቡበት መስመር ውጭ እንዳይሰሩ ከተከለከሉ ግን ገቢያቸው ይቀንሳል፣ ታክሲ ፈላጊውም ይጉላላል” “በሆነ ሰአት፤ …ተሳፋሪ ከመብዛቱ የተነሳ፤ በዚያ መስመር ከተመደቡት ታክሲዎች አቅም በላይ ይሆናል። ... ብዙ ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ለሰአታት ይቆማሉ፤ ሌሎች ታክሲዎች መጥተው መስራት አይችሉም። …በሌሎች ቦታዎች ደግሞ ተሳፋሪ ከማነሱ የተነሳ፤ በቦታው የተመደቡ ታክሲዎች ያለስራ ቆመው ጊዜ ያባክናሉ። በትራንስፖርት እጦት ብዙ ሰው ወደተጉላላበት ቦታ ሄደው መስራት አይችሉም። ከጥቂት ሰአታት በኋላ፤ ሁኔታው ይቀየራል። በመጀመሪያው ቦታ ተሳፋሪ ጠፍቶ ታክሲዎች ያለ ስራ ይቆማሉ። በሁለተኛው ቦታ ደግሞ፤ በታክሲ እጥረት፤ ተሳፋሪዎች ለረዥም ሰአት ይጉላላሉ።
” “…ተሳፋሪ አጥተው ያለ ስራ የሚቆሙ ታክሲዎችን እና ታክሲ አጥተው የሚንገላቱ ተሳፋሪዎችን ማበራከት ነው የቁጥጥሩ ውጤት። ቢሮክራቶቹ… የቁጥጥር ሱስ… የመጣው ይምጣ የሚያሰኝ እጅግ ሃይለኛ ሱስ ካልሆነባቸው በቀር፤ መዘዙን ያጡታል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል” እንዲህ እንደምታዩት፤ የስምሪት ቁጥጥሩ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጠቃሚ ምክር ቢቀርብም፣ የሚሰማ ባለስልጣን አልተገኘም። ለነገሩ፣ ከአንዳንድ የታክሲ ባለቤቶችና ሾፌሮች በስተቀር አብዛኛው ሰው፣ የታክሲ ስምሪት ጠቃሚ እንደሚሆን ገምቶ ነበር - የትራንስፖርት ችግር የሚቃለልለት መስሎት። ለምን መሰለው? ታስታውሱ እንደሆነ፤ አንዳንድ የታክሲ ሾፌሮችና ባለቤቶች ቅሬታቸውን ሲገልፁ፤ “ስምሪቱን የሚቃወሙት፣ ጥቅማቸው ስለሚቀርባቸው ነው” ተባለ። የዚህ ትርጉም ምን እንደሆነ አስቡት። አሃ… “ባለታክሲዎችና ሾፌሮች ከተጎዱ፣ ተሳፋሪ ይጠቀማል” ማለት ነዋ። እንዴት እንዴት? በንግድ እና በቢዝነስ ዙሪያ የብዙ ሰው አስተሳሰብ በጣም የተዛባ ከመሆኑ የተነሳ፤ ሻጮችና ሸማቾች፣ ባለታክሲዎችና ተሳፋሪዎች… ተቀናቃኝ ባላንጣ ሆነው ይታዩታል። ስለ ታክሲ ሲያስብ፣ 5 ሳንቲም አሳልፎ የማስከፈልና 5 ሳንቲም አጉድሎ የመክፈል ጉዳይ ብቻ ጎልቶ የሚታየው ሰው፤ “አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው በሌላኛው ጉዳትና መስዋእትነት ነው” ብሎ ያምናል።
እናም፣ “ስምሪቱ ባለታክሲዎችን የሚጎዳ ከሆነ፣ ተሳፋሪዎችን ይጠቅማል” ብሎ ይደመድማል። የሰዎች ኑሮ፣ ከአውሬዎች ሕይወት ብዙም የተለየ ሆኖ አይታየውም - እርስ በርስ እየተቦጫጨቁ መኖር። እውነታው ግን፣ የዚህ ተቃራኒ ነው። አንዱ የሚጠቀመው፣ ሌላኛው ሲጠቀም ነው። ባለታክሲው የሚጠቀመው መቼ ነው? በሆነ አቅጣጫ በክፍያ ለመጓዝ የሚፈልግ ተሳፋሪ ሲመጣለት። ተሳፋሪው የሚጠቀመውስ? ክፍያ ተቀብሎ ለማጓጓዝ የሚፈልግ ታክሲ ሲመጣለት። የባለታክሲው ጥቅም እየጨመረ የሚሄደው፣ ብዙ ተሳፋሪዎችን ፈልጎ ሲያገኝና ሲያስተናግድ ነው - ገቢው ያድግለታል። የተሳፋሪ ጥቅም የሚጨምረው ደግሞ፣ በርካታ ተሳፋሪዎችን የሚያስተናግዱ ታክሲዎች ሲመጡ ነው - በትራንስፖርት እጦት ተገትሮ አይውልም። አንደኛው ወገን ጥቅም የሚያገኘው፣ ሌላኛውም ወገን የሚጠቀም ከሆነ ነው። መሰረታዊው የቢዝነስ ቁምነገርም ይሄው ነው - አምስት ሳንቲም የማጉደልና የማሳለፍ ሳይሆን። የስምሪት ቁጥጥሩም፣ ይህንን መሰረታዊ ቁምነገር በማደናቀፍ ነው ባለታክሲዎችንና ተሳፋሪዎችን ለጉዳት የዳረጋቸው። ጉዳቱ ግን፣ ዛሬ የምናየው ቅዠት ብቻ አይደለም። የባለታክሲዎች ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመጣ ቁጥር፤ ወደ ቢዝነሱ የሚገቡ ሰዎችም ቁጥራቸው ይቀንሳል። በተቃራኒው፣ ከቢዝነሱ የሚወጡ ሰዎች ይበራከታሉ።
ለዚህም ነው፤ በአዲስ አበባ የታክሲ አገልግሎት የሚሰጡ መደበኛ ሚኒባስ ታክሲዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየቀነሰ የመጣው። ከጥቂት አመታት በፊት ቁጥራቸው 12ሺ ደርሶ እንደነበር መረጃዎች ቢገልፁም፣ አሁን ግን በስራ ላይ የሚገኙት 9ሺ አይሞሉም። አላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥር፣ ለጊዜው ካልሆነ በቀር፣ ውሎ አድሮ መዘዙ የከፋ እንደሚሆን ከዚህ ቀውስ መረዳት እንችላለን። የታክሲ ወረፋ ባልነበረበት ከተማ፣ በጥቂት ወራት ውስጥ… “የታክሲ ወረፋ” የኑሯችን አካል ሆኖ አረፈው። ተሳፋሪ ያጣ ታክሲ ተደርድሮ፣ ታክሲ ያጣ ተሳፋሪ ተሰልፎ የምናይበት የቅዠት ዓለም ውስጥ ገብተናል። ይህም አልበቃ ብሎ፣ ቅዠቱን የሚያጦዝ መግለጫ እንሰማለን። የአዲስ አበባ መስተዳድር የትራንስፖርት ቢሮ፣ ረቡዕ እለት በመንግስት ሚዲያዎች በኩል የሰጠውን መግለጫ አላዳመጣችሁም? በየጊዜው በምወስዳቸው እርምጃዎች መልካም ውጤቶችን እያስመዘገብኩ ነው ብሏል - የትራንስፖርት ቢሮው። ለምሳሌ ያህልም፤ የታክሲዎች ስምሪት ላይ ቁጥጥሩን ለማጥበቅ እርምጃ እንደወሰደ ቢሮው ሲገልፅ፤ አሁን አሁን ከተመደበበት መስመር ውጭ ውልፍት የሚል ታክሲ የለም ብሏል። ችግሩ ምን መሰላችሁ? አላስፈላጊው ቁጥጥር በተፈጥሮው መጥፎ ወይም ጎጂ ስለሆነ፣ ቁጥጥሩ በጥብቅ ተግባራዊ ሲደረግ ጎጂነቱ ይጨምራል እንጂ መልካም ውጤት ሊመዘገብ አይችልም። መልካም ውጤት የተመዘገበባትና ባለስልጣናት ብቻ የሚያውቋት ሌላ “አዲስ አበባ” ከሌለች በቀር፤ በነባሯ ከተማ ውስጥ የታክሲ ግርግርና ወረፋ ሲበራከት ነው የምንመለከተው።
የፌደራል ባለስልጣናት ደግሞ በበኩላቸው ሌላ ቁጥጥር ተግባራዊ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ገልፀዋል። ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ በማታ የሚደረጉ ጉዞዎች እንደሚታገዱ ለኢቴቪ የተናገሩ ባለስልጣናት፤ የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ የታሰበ እርምጃ ነው ብለዋል። ከከተማ ውጭ፣ በማታ በሚከናወን ጉዞ ላይ የትራፊክ አደጋ ይደርሳል ወይ? አዎ ይደርሳል። ነገር ግን፣ የከተማ ውስጥ እና የቀን ጉዞ ላይም የትራፊክ አደጋ ይደርሳል። ታዲያ፣ የትራፊክ አደጋ ለመከላከል አስበን፤ በከተማ ውስጥና ከከተማ ውጭ፤ በቀን እና በማታ የሚከናወኑ የመኪና ጉዞዎችን ለምን አናግድም? ለነገሩማ፤ አይነቱና መጠኑ ይለያያል እንጂ፤ በተፈጥሮው “አደጋ” የማያሰጋው አንዳችም የሰው እንቅስቃሴ የለም። ፎቅ መስራት፣ ጉድጓድ መቆፈር፣ መንገድ መጥረግ፣ መሬት ማረስ፣ ቤት ማፅዳት… ሁሉም አይነት ስራ፣ ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ መስራት ሳይቀር፣ ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበት አደጋ ይደርሳል።
ለምሳሌ፣ ከፍተኛ አደጋ ከሚያጋጥማቸው ነገሮች መካከል፣ እርግዝናና ወሊድ ሊጠቀሱ ይችላሉ። ምን ይሄ ብቻ? እንደአረማመዱና እንደአሯሯጡ፣ እንደአጎራረሱና እንደአጠጣጡ፣ እንደአስተኛኘቱና እንደአለባበሱ ሁኔታ ለአደጋ የሚጋለጥ ሰው ጥቂት አይደለም። እና፣ አደጋዎችን ለማስቀረት አርፎ መቀመጥና ሞቱን መጠባበቅ አለበት? በጭራሽ! ሰው፣ የስራውንና የእንቅስቃሴውን ምንነት ለማገናዘብ፣ በጥረቱ የሚያገኛቸው ጥቅሞችንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን ለማመዛዘን የሚያስችል አቅም አለው - የአእምሮ አቅም። ጥቅሞቹን የሚያሳድጉ ዘዴዎችና አደጋዎችን የሚያስቀሩ ጥንቃቄዎች የሚፈጠሩትም፣ በሰዎች የአእምሮ አቅም ነው። ያለ ድካም በፍጥነት ከቦታ ቦታ መጓዝ እጅጉን ጠቃሚ እንደሆነ ትጠራጠራላችሁ? መኪና የተፈጠረውና የሚመረተው፣ አስፋልት የሚቀየሰውና የሚገነባው፣ ለሌላ ምክንያት አይደለም - ያለ ድካም በፍጥነት ለመጓዝ ነው። በእርግጥ አደጋዎች ያጋጥማሉ።
ግን ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር፣ አደጋው በጣም ትንሽ ነው። መኪናና አስፋልት ባልነበረበት ዘመን፣ የሰዎች አማካይ የሕይወት ዘመን 30 አመት ገደማ ብቻ ነበር። አስፋልት ላይ ፈጣን የመኪና ጉዞ፤ የሰዎችን ሕይወት አሻሽሏል። ነገር ግን፤ ከጥቅሙ ጋር ሲነፃፀር አደጋው ትንሽ ነው በሚል፤ አደጋውን ቸል ማለት አለብን ማለት አይደለም። “አደጋ አለው” በሚል ሰበብ እርግዝናንና ወሊድን ለማስቀረት ማሰብ እብደት ቢሆንም፤ አደጋውን ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን ከመተግበር መቦዘንም “እብደት” ይሆናል። የመኪና ጉዞም ተመሳሳይ ነው። የትራፊክ አደጋ ተፈርቶ፤ የመኪና ጉዞን ማስቀረት የጤንነት አይደለም። አደጋውን በ“ፀጋ” መቀበልም እንዲሁ። ለዚህም ነው፤ የትራፊክ ደንቦችና ምልክቶች፤ የትራፊክ መብራቶችና የማሽከርከር ስልጠናዎች የተፈጠሩት። ይህም ብቻ አይደለም። አማራጮችን አመዛዝኖ፣ የመጓጓዣ አይነቱን፣ አቅጣጫውንና ጊዜውን መምረጥ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ፤ ዋጋውንና አቅርቦቱን፣ የመጓጓዣውንና የአሽከርካሪውን ብቃት ማነፃፀር አስፈላጊ የመሆኑን ያህል፤ በጥቅሉና በአመዛኙ ሲታይ፤ በብስክሌትና በሞተር ብስክሌት ከመጓዝ ይልቅ በመኪና መጓዝ የተሻለ መሆኑንም ማገናዘብ ይቻላል። በማታ ከመጓዝ ይልቅ በቀን፤ በመኪና ከመጓዝ ደግሞ በባቡር፤ በባቡር ከመጓዝ ደግሞ በአውሮፕላን ይሻላል። ለምን በጥቅሉ አማካይ የአደጋ መጠናቸው አነስተኛ ስለሆነ። እንዲህም ሆኖ፤ የአውሮፕላን ጉዞ የተሻለ ስለሆነ የመኪና ጉዞን ለማገድ፣ ወይም የመኪና ጉዞ ስለሚሻል የሞተር ብስክሌትን መከልከል፤ አልያም የቀን ጉዞ ስለሚሻል የማታ ጉዞን መከልከል… ከእብደት አይለይም። መከልከልና ማገድ ይቅርና፤ “ብስክሌት አትጠቀሙ፣ በማታ አትንቀሳቀሱ” ብሎ መምከርም ስህተት ነው።
ጥቅሙንና ጉዳቱን፣ ሰዓቱንና አቅጣጫውን፣ መጓጓዣውንና አሽከርካሪውን እያመዛዘናችሁ ተጠቀሙ ነው መባል ያለበት። “አትጠቀሙ፣ አትንቀሳቀሱ” ከሚለው የተሳሳተ ምክር አልፎ፤ ወደ ክልከላና እገዳ መግባት፤ ከመሳሳት አልፎ የሰውን ነፃነት መርገጥ ይሆናል። አለበለዚያማ፤ “የመንቀሳቀስ ነፃነት” ተብሎ በህገመንግስት የሰፈረው ፅሁፍ ምን ትርጉም አለው? ባለስልጣናት በፈቀዱት ሰዓት ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚቻለው? በደርግ ዘመን የ”ይለፍ” ወረቀት ያልያዘ ሰው ከከተማ ከተማ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር። ከድሮው የደርግ ዘመን የሰዓት እላፊ አዋጅ፤ በከፊል ተቀንጭቦ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ቢባል አይሻልም?
የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ህልም በውዝግቦች ታጅቧል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ ለሚያደርገው ሶስተኛ ጨዋታ ዝግጅቱን በውዝግቦች በመታጀብ ሊጀምር ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ከቦትስዋና ጋር ከ15 ቀናት በኋላ እዚህ አዲስ አበባ ላይ ይጫወታል፡፡ ይሄው የዋልያዎቹ ወሳኝ ጨዋታ ፌደሬሽኑ እና ክለቦችን ባነካኩ ውዝግቦች ገና ከዝግጅት ምእራፉ የመቃወስ አደጋ ውስጥ ወድቋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ለዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያው የሶስተኛ ዙር ጨዋታ የሚያደርገውን ዝግጅት ዛሬ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድድሮች የሚሳተፉት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለዋልያዎቹ ተጨዋቾቻውን ለመልቀቅ እንዳመነቱ ናቸው፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ስታድዬም በተደረገ የሊግ ጨዋታ ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ፈፅመዋል በተባለው የዲስፕሊን ግድፈት የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴ በክለቦቹ ላይ ያሳለፋቸው የቅጣት ውሳኔዎች በይግባኝ ክርክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ አወዛጋቢ ሁኔታዎች የዋልያዎቹን የተጨዋቾች ስብስብ በማቃወስ እና በክለብ ደጋፊዎች፤ በፌደሬሽኑና በብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በማካረር ለብሄራዊ ቡድኑ በሚፈልገው ትኩረት እና ሁለገብ ድጋፍ ላይ መቀዛቀዝ እንዳይፈጠር ስጋት ሆኗል፡፡ ለብሄራዊ ቡድን የተጠሩ 22 ተጨዋቾች ስም ዝርዝር ሰሞኑን በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ይፋ ተደርጓል፡፡ ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጠኝ እና ስምንት ተጨዋቾችን እንደቅደምተከተላቸው በማስመረጥ ከፍተኛ ውክልና አግኝተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ቡና ሁለት ተጨዋቾች ሲጠሩ ንግድ ባንክ ፤ መብራት ኃይልና ሰበታ ከነማ እያንዳንዳቸው 1 ተጨዋች አስመርጠዋል፡፡ የዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ህልም ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች በፈርቀዳጅነት በመሳተፍ ከሚጠቀሱ የአፍሪካ አገራት አንዷ ነበረች፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት የዓለም ዋንጫ ማጣርያ በ1962 እኤአ ላይ የነበረ ሲሆን ከዚያን ጊዜ ወዲህ በማጣርያው ውድድሮች በየአራት አመቱ በመደበኛነት ተሳታፊ ሆና ቆይታለች፡፡ በ2002 እኤአ ጃፓንና ኮርያ በጣምራ ላዘጋጁት የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሜዳው የቡርኪናፋሶ አቻውን 2ለ1 ቢያሸንፍም ከሜዳው ውጭ 3ለ0 ተሸንፎ ወደቀ፡፡
ከ4 ዓመታት በኋላ በ2006 እኤአ ላይ ጀርመን ለምታስተናግደው 18ኛው የዓለም ዋንጫ በተደረገው ቅድመ ማጣርያ ደግሞ ኢትዮጵያ በሜዳዋ 3ለ1 በማላዊ ተሸንፋ በመልሱ ጨዋታ 0ለ0 በመለያያት ቅድመ ማጣርያውን ማለፍ ተስኗታል፡፡ ከ3 ዓመት በደግሞ ደቡብ አፍሪካ ለምታስተናግደው 19ኛው የዓለም ዋንጫ በቅድመ ማጣርያው ሞውሪታንያን በደርሶ መልስ ጨዋታ ኢትዮጵያ 6ለ1 ብትረታም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከፊፋ ውድድሮች ተሳትፎ በመታደጉ ጉዞው በአጭሩ መቅረቱ ይታወሳል፡፡ በ2014 እኤአ ላይ ብራዚል በምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ በአስደናቂ ስኬት የተለየ ሆኗል፡፡ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደራቀበት የአፍሪካ ዋንጫ ተመልሶ መግባት የቻለው ብሄራዊ ቡድኑ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ ለብራዚሉ የዓለም ዋንጫ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ በምድብ 1 መሪነቱን እንደያዘ ነበር፡፡
በዓለም ዋንጫው የምድብ ማጣርያ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 1 ከደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ጋር ተደልድሏል፡፡ በምድብ ማጣርያው የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ዋልያዎቹ ከሜዳቸው ውጭ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተጫውተው 1 እኩል አቻ ተለያዩ፡፡ በሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ በሜዳቸው አዲስ አበባ ላይ መካከለኛው አፍሪካን 2ለ0 አሸንፈዋል፡፡ዋልያዎቹ ከእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች በሰበሰቡት አራት ነጥብ ሁለት የግብ ክፍያ የምድቡን መሪነት ጨብጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያው እዚህ አዲስ አበባ ላይ ከቦትስዋና አቻው ጋር የሚገናኝበት ግጥሚያ 3ኛው የምድብ ጨዋታ ነው፡፡ አራተኛው የምድቡን ጨዋታ ይህን ጨዋታ ካደረገ ከ10 ሳምንታት በኋላ ከሜዳው ውጭ በጋብሮኒ ቦትስዋናን መልሶ የሚገጥምበት ነው፡፡ ከዚሁ የቦትስዋና ጨዋታ በኋላ በሳምንቱ ደግሞ በምድቡ አምስተኛ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካን በሜዳው አስተናግዶ ይቀጥላል፡፡
በዚህ መሰረት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያው ሂደት የሚያበቃው ከ6 ወራት በኋላ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር በሚያደርገው ስድስተኛው የምድብ ጨዋታ ይሆናል፡፡ የጊዮርጊስ ፤ የደደቢት እና የዋልያዎቹ የጨዋታ ጭንቅንቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ለብሄራዊ ቡድን ያስመርጧቸውን ተጨዋቾች በመልቀቅ ዙርያ ከፌደሬሽኑ ጋር መወዛገብ የጀመሩት ከሳምንት በፊት ነው፡፡ ሁለቱ ክለቦች ባለፈው ሰሞን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ በቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎቻቸው የዛንዚባር እና የመካከለኛው አፍሪካ ክለቦችን ጥለው በማለፍ ወደ የመጀመርያው ዙር የማጣርያ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል፡፡
ለብሄራዊ ቡድኑ ዝግጅት ሲባል የመለስ ካፕ የሊግ ውድድር ለሶስት ሳምንት እንደሚቋረጥ ፌዴሬሽኑ እንዳሳወቀ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች ከየክለቡ አሰባስበው ዝግጅታቸውን በያዙት እቅድ ለመስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት በብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጥሪ የሚቀርብላቸውን ተጨዋቾቻቸውን ላለመልቀቅ ሲያመነቱ፤ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድደሮች ከሚያደርጉት የመጀመርያ ዙር የመጀመርያ ጨዋታዎች በኋላ ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ በመግለፅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ በበኩሉ ክለቦቹ በብሄራዊ ቡድኑ እጅግ ወሳኝ ሚና ያላቸውን የሁለቱን ክለብ ተጨዋቾች ለመልቀቅ እንዲችሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን የክለቦቹን የጨዋታ ፕሮግራም እንዲያሸገሽግላቸው እጠይቃለሁ እያለ ነው፡፡
በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ከሜዳው ውጭ በመጀመርያው ጨዋታ የዛንዚባሩን ጃምሁሪ በአጠቃላይ የደርሶ መልስ ውጤት 8ለ0 በማስመዝገብ ወደ የመጀመርያ ዙር ማጣርያው ገብቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ15 ቀናት በኋላ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ግጥሚያውን ከሜዳው ውጭ ከማሊው ክለብ ዲጆሊባ ጋር በማድረግ ይጀምራል፡፡ በአፍሪካ ክለቦች ኮንፌደሬሽን ካፕ የሚሳተፈው ደደቢት በበኩሉ የመካከለኛው አፍሪካውን ክለብ አንጌስ ዲፋቲማ ከሜዳው ውጭ 4ለ0 እንደረታ የሚታወስ ሲሆን ምንም እንኳን በመልስ ጨዋታው 2ለ1 ቢሸነፍም በደርሶ መልስ ውጤት 5ለ3 በማስመዝገቡ ሊያልፍ ችሏል፡፡
ደደቢት በኮንፌደሬሽን ካፑ የመጀመርያ ዙር ማጣርያ በሜዳው ከሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ኤልሻንዲ ጋር በመገናኘት ይቀጥላል፡፡ የፌደሬሽኑ ዲስፕሊን ኮሚቴና የቅጣት ውሳኔዎቹ ሰሞኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የደረሰን መረጃ ጉዳዩ የውድድር ፕሮግራምን ለማሳወቅ፤ በብሄራዊ ቡድኑ የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዝግጅት ዙርያ ወይንም በአጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ በጎ እንቅስቃሴን የተመለከተ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ ስለተከሰተ የስርዓት አልበኛነት ተግባር እና ይህንኑ ተከትሎ በፌደሬሽኑ የዲስፒሊን ኮሚቴ የቅጣት ውሳኔ ያትታል፡፡ መለስ ካፕ ተብሎ በተጠራው የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ 10ኛ ሳምንት በአዲስ አበባ ስታድዬም ላይ ቡና ከደደቢት ባደረጉት ጨዋታ ላይ ተፈፅሟል ባለው የዲስፕሊን ግድፈት ላይ የዲስፕሊን ኮሚቴው በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር እና በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ ያሳለፈውን ባለ ሁለት አባሪ ገፅ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ በሁለቱ ክለቦች ላይ የቅጣት ውሳኔውን ለማስተላለፍ የጨዋታ አመራሮችን ሪፖርት መመርመሩንና ማጣራቱን ገልጿል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው የመጀመርያ ውሳኔ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ላይ የተላለፈ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ስታድዬም ቡና ከደደቢት አድርገውት በነበረው ጨዋታ ላይ በቀኝ ጥላፎቅ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ አርማና ማልያ የለበሱ ደጋፊዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አባላት የሆኑትን እነ ደጉ ደበበ፤ አሉላ ግርማና አበባው ቡጣቆ የተባሉ ተጨዋቾችን ሞራል የሚነካ ቃላት በመወርወር እና አስፀያፊ ስድቦችን በመሳደብ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ዲስፕሊን ኮሚቴው ይገልፃል፡፡ የቡና ደጋፊዎች ተመሳሳይ የዲስፕሊን ግድፈት በፌደሬሽኑ ላይ መፈፀማቸውን ያሳወቀው ኮሚቴው፤ ይህ ሳይበቃቸው በእለቱ በሚያሟሙቁ የተቃራኒ ቡድን ተጨዋቾች ላይ የውሃ ላስቲክና ድንጋይ በመወርወር ስርዓት መጣሳቸውን ዘርዝሯል፡፡ በመሆኑም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 9 አንቀፅ አምስት ንዑስ አንቀፅ ሁለት በፊደል ኸ በተቀመጠው መሰረት የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በደጋፊዎች ለተፈጠረው የዲስፕሊን ግድፈት ተጠያቂ ተደርጓል፡፡
ስለሆነም የኢትዮጵያ ቡና የስፖርት ክለብ በዲስፕሊን መመርያው ክፍል 6 አንቀፅ 35 በንዑስ አንቀፅ አራት መሰረት 50ሺ ብር በቅጣት እንዲከፍል እና በፕሪሚዬር ሊጉ ባለሜዳ ሆኖ የሚያደርጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች ያለተመልካች በዝግ ስታድዬም እንዲጫወት በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡ የዲስፕሊን ኮሚቴው ሁለተኛ የቅጣት ውሳኔ ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስና የብሄራዊ ቡድን ተጨዋች በሆነው አበባው ቡጣቆ ላይ የተሰጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ደጋፊዎች ስድብና ዘለፋ የደረሰበት አበባው የኢትዮጵያ ባህል ባልሆነ መልኩ በሰውነት ምልክት ተሳድቦ ተመልካቹን እንዳስቆጣና ረብሻው እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል ብላል፡፡ ስለሆነም በዲስፕሊን መመርያው ክፍል ስድስት አንቀፅ 38 መሰረት አአባው ቡጣቆ ለክለቡ በ5 ጨዋታዎች እንዳይሰለፍ እና 5ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍል በዲስፕሊን ኮሚቴው ተወስኖበታል፡፡
የዲስፕሊን ኮሚቴው የቅጣት ውሳኔ ክፍል ሶስት የሚመለከተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበርን ነው፡፡ በቡና ደደቢት የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ በግራ ጥላ ፎቅ የጊዮርጊስን አርማና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች መሳደባቸውን የገለፀው ዲስፕሊን ኮሚቴው፤ በተጨማሪም የዚሁ ክለብ ደጋፊዎች የካቲት 15 ቀን በሴቶች የሊግ ውድድር የደደቢት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ሴት እግር ኳስ ቡድኖችን ባጫወቱ ዳኞች ላይ አስነዋሪ ተግባር መፈፀማቸውን ጨምሮ ለሁለቱም የደጋፊዎች የዲስፕሊን ግድፈቶች የስፖርት ማህበሩ ተጠያቂ ሆኖ እንዲቀጣ መወሰኑን አሳውቋል፡፡ ስለሆነም በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የዲስፕሊን መመርያ ክፍል 6 አንቀፅ 35 በቁጥር 4 በተቀመጠው ድንጋጌ መሰረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር 40ሺ ብር መቀጮ እንዲከፍልና በወንዶች ዋናው ቡድኑ በሜዳው የሚያደርገውን አንድ ጨዋታ በዝግ ስታድዬም እንዲያደርግ መወሰኑን ዲስፕሊን ኮሚቴው አመልክቷል፡፡
የጃኖ ባንድ ጠንሳሽ አዲስ ገሠሠ
“ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ” ከትውልድህ እንጀምር የተወለድኩት ጎሬ/ኢሊባቡር ነው፤በእኛ ጊዜ ጠቅላይ ግዛት ይባል ነበር፡፡ እዛ ትንሽ ተምሬአለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ እዛ ነበሩ፡፡ ከዛም በተረፈ አዲስ አበባ ተምሬ ነው በ17 ዓመቴ ከኢትዮጵያ የወጣሁት፡፡ በምን ምክንያት ወጣህ? ዕድል፡፡ እርግጥ ቤተሰቦቼ ገንዘብ ኖሯቸው አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ቺካጎ ገባሁ፡፡ ለብዙ ዓመት እዛው ኖሬያለሁ፡፡ በኋላ እናቴንም ወንድሞቼንም ወደዛው ለመውሰድ በቃሁ፡፡ አሜሪካ የኖርኩት ለ35 ዓመት ነው፡፡ እዚያ በመቆየቴ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ እንዴት? ተማርኩኝ - ቢዝነስ ማኔጅመንት፡፡ ሙዚቃ ውስጥ ያስገቡኝ ወንድሞቼ ናቸው፡፡ ከዛ በፊት ጎበዝ የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ሙዚቃ አለም ውስጥ ከገባሁ ጀምሮ በጣም የተሳካ ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡
እንዴት ነው ወንድሞችህ ወደሙዚቃው ያስገቡህ? ወንድሞቼ ከሃገር የወጡት ቀይ ሽብርን ሸሽተው ነበር፡፡ ጅቡቲ እስር ቤት ከነበረ ወንድሜ ደብዳቤ ሲደርሰኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ በዛን ጊዜ ነው ወንድሞቼን ከኢትዮጵያ ያወጣሁትና ቺካጎ የመጡት፡፡ እኔ ሙዚቃ እንደሚጫወቱ አላውቅም ነበር፡፡ ሙዚቃ መቻላቸውን ሲነግሩኝ...በጣም ተገረምኩ፡፡ የኢስተርን ኢሊኖ ዩኒቨርስቲን ዲን ‹‹እነዚህ ወንድሞቼ ሙዚቀኞች ናቸው›› ስለው በየዓመቱ ፌብሪዋሪ ብላክ ሂስትሪ መንዝ (February black history month) የሚባል አለ፡፡ ያኔ ለተማሪዎች በጀት አለ ብሎ ነገረኝ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ለዩኒቨርስቲው ሾው እንዲያቀርቡ መሳሪያ ተከራይቼላቸው ነበር - ያን ጊዜ ነበር የወንድሞቼን ችሎታ ያየሁት፡፡
በህይወቴ ውስጥ ለለውጥ የተነሳሁበት ቀን ይሄ ነው፡፡ ምን ዓይነት ሙዚቃ ነበር ያቀረቡት? በአማርኛ፣ በአፍሪካ፣ በሬጌ ...ሙዚቃውን አቀረቡ፡፡ እነሱ በጣም ልምድ አላቸው፡፡ ሌለው ቀርቶ ጅቡቲ ከእስር ቤት ወጥተው ለትንሽ ጊዜ ቆይተው ነበር፤በዚያን ጊዜ ባንድ አቋቁመው ይጫወቱ ነበር፡፡ በጣም ጎበዞች ነበሩ፡፡ ሁሉን ነገር ትተህ ወደ ሙዚቃው አደላህ ማለት ነው? አዎ! ሙሉ በሙሉ ወንድሞቼ ቀየሩኝ፡፡ ሙዚቃ ህይወት ነው፡፡ ሙዚቃ ይለውጥሻል፡፡ እንደ አዲስ መፈጠር ማለት ነው፡፡ ሁልጊዜ ልጅ ያደርጋል፡፡ ያን ደስ የሚል ስሜት ይዘን መከርን ከወንድሞቼ ጋር፡፡ የሙዚቃ መሳሪያ መግዛት አለብን አልኳቸው፡፡ አሜሪካ ከተሰራ፣ ከተማሩ፤ ጊዜን በአግባቡ ከተጠቀሙ በጣም ጥሩ አገር ስለሆነ፤ ሰው ይኮናል፡፡ እኔ ደግሞ ቺካጎ ስኖር ዘመድ የለኝም፣ ራሴን የማስተዳድር ነኝ፣ ትጉህ ሰራተኛና መልካም ባህሪ ያለኝ ሰው ነኝ፡፡ ወንድሞቼ የኔን ፈለግ ተከትለው በየሳምንቱ ከምንሰራው ደሞዛችን ላይ ገንዘብ አጠራቅመን መሳሪያ ገዛን፡፡ እኔ ደግሞ በክሬዲት ቫን አምጥቼ በራፋቸው ላይ አቆምኩላቸው፡፡ ሊያምኑ አልቻሉም፡፡
አሜሪካን አገር...ገና በስድስት ወራቸው አዲስ መኪና..፡፡ ህልም ነው፤እኔ ግን እውን እንደሚሆን አሳየኋቸው፡፡ ዋሽንግተን ሄድን ለአበሻው የመጀመሪያ አንድ ትልቅ ሾው ስናሳይ ህዝቡ ደነገጠ፡፡ ከየት መጡ፤ እነዚህ የቺካጎ ልጆች ተባልን፡፡ ከዛ ካሊፎርኒያ ሄደን ሰራን፤ብዙ ገንዘብ፡፡ ያንን ለዓመት የትምህርት ቤት ክፍያ አዋልነው፡፡ በዓመቱ የቦብ ማርሊ ልደት ይከበራል፡፡
በዛ ላይ ለመሳተፍ በቀጥታ ደብዳቤ ፃፍን፡፡ አክቲቭ መሆን ነው የእኔ እህት (ሳቅ) ከዚያ ሪታ ማርሊ የአውሮፕላን ትኬት ከፍላ፤ ሆቴላችንን አመቻችታ፤ ወንድሞቼ መጡ ብላ በአጀብ ተቀበለችን፡፡ የመጀመሪያውን ሾው የቦብ ማርሊ ሙት ዓመትን በማስመልከት በተወለደበት ጃማይካ ሄደን አከበርን፡፡ ያ የነገሮች ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ በስንት ዓመት ምህረት ማለት ነው? እ.ኤ..አ በ1991ዓ.ም. ማለት ነው፡፡ እኔም ወንድሞቼ ወደ አሜሪካ ከመጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እመጣለሁ የሚለውን ነገር ተውኩት፡፡ ለምን? ወንድሞቼ እንዲህ ተሰደው ከሃገር ከወጡ ትልቅ ችግር አለ የሚል እምነት አደረብኝ፡፡ በዚያ መንግስት ኢትዮጵያ ለመምጣት አልፈለግሁም፡፡ በጭራሽ፡፡ አንድ ወንድሜ ሞቷል፤ ሌሎች ወንድሞቼ ተሰደዋል፡፡ “ለምን ኢትዮጵያውያን ሆነን ተፈጠርን” የሚል አይነት አስተሳሰብ ይዘው ነው የመጡት፡፡ ከኢትዮጵያ መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን እስር ቤት በነበሩ ጊዜም ብዙ ተሰቃይተዋል፡፡ ይህንን ሳይ እዚሁ አሜሪካ መኖር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ዲግሪ አለኝ ተምሬያለሁ፤ሪታ ማርሊ ጥሩ ገንዘብ ሰጥታን ወደ ቺካጎ ተመለስን፡፡
እኔን ግን በጎን ታባብለኝ ነበር፡፡ እንዴት---ምን ብላ? ከእኔ ጋር ስራ፤ጥሩ ወንድማችን ትሆናለህ በማለት፡፡ መጀመሪያ ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም፤ በኋላ ግን ደስ አለኝ፡፡ አንድ እህት አገኘሁ፤ አፍሪካዊት ጃማይካዊት፣ ኢትዮጵያዊት..የሆነች እህት፡፡ እሷ ጋ ሄጄ መኖር ጀመርኩኝ፤ለአንድ ዓመት ያህል፡፡ አንድ ዓመት ስሰራ በጣም ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደረስኩኝ፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ እዛ መኖሩ አልታየኝም.. በጣም ከፍተኛ ደረጃ የደረስከው ሙዚቃ አብረሃቸው በመስራት ነው? የጃማይካ ባህል እንደኛው አገር ነው፡፡ የቦብ ማርሊ ልጆች ሃይስኩል እስኪጨርሱ ድረስ ነፃነት አልነበራቸውም፡፡
በአንዳንድ ካረቢያን ደሴቶች፤ትምህርት ቤት ሲዘጋ ደግሞ አሜሪካ አብረን ሄደን ሾው እንሰራለን፡፡ በኋላ ዚጊ ሃይስኩል ጨረሰ፤ሪታ ማርሊ ልጆቿዋን - ስቲቭን፣ ዚጊን፣ ሸረንና፣ ስዴላን ለእኔ ለቀቀቻቸው፡፡ ዚጊ ማርሊ “ዘ ሜሎዲ ሜከርስ” ተብሎ ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር ዳሎል ባንዱ ሆኖ ስራ ተጀመረ፡፡በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ግራሚ ከእሱ ጋ አገኙ፡፡ በከፍተኛ የአልበም ሽያጭ ጎልድና ፕላቲኒየም ሪኮርድም አገኙ፡፡ ለእኔ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ አንድ የድሃ ልጅ ...እኛ ምንም አልነበረንም፡፡ ቤተሰቦቼም እኔም ምንም አልነበረንም፡፡ ..ወጥተን በአለም ላይ፡፡ በጣም ትልቅ እድል ነው፡፡.
በሙዚቃ ሥራችሁ የት የት ዞራችሁ? የት አልዞራችሁም ብትይ ነው የሚቀለው የእኔ እህት...አሜሪካን ከዳር እስከዳር..አውሮፓ የቀረን አገር የለም..ወንድሞቼ ዘለቀ፣ ሙሉጌታ፣ ሩፋኤል፣ ደረጀ መኮንን (አሁን በቅርብ ጊዜ ያረፈው) በጣም ድንቅ ጊዜ ነበረን፡፡ በጣም ወጣት ነበርኩ፤እንደ አሁኑ ምርኩዝ አልያዝኩም (ረጅም ሳቅ) ህልም እውን ሲሆን ታውቂያለሽ...ትንሽ እንደሰራን ዚጊ ግፊት በዛበት.. ግፊት----ምን ዓይነት? ጃማይካ ውስጥ ሙዚቀኛ ጠፍቶ ነው ከኢትዮጵያውያን ሙዚቀኞች ጋር የሚጫወተው የሚል.. አለማቀፍ ግፊት ነው..የቦብ ማርሊ ልጅ እንዴት ከኢትዮጵያኖች ጋር ..የሚል ዓይነት ነበር፡፡ ግፊት ሲበዛ እኔን አማከረኝና የጃማይካውያን ሙዚቀኞች ባንድ መቋቋም አለበት ተባለ...ዳሎል ወደ ቺካጎ ተመለሰ፡፡
አሁን ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? አሁንም እንጠያየቃለን..አሁንም ሪታ ማርሊ እህቴ፣ እናቴ፣ ጓደኛዬ ናት፡፡ ማኔጀርዋ ነኝ.. በጣም እንገናኛለን፡፡ በቀደም እዚህ መጥታ ነበር፤ የቦብ ማርሊ ሃውልት የተሰራ አለ፤ለሱ ጉዳይ ነበር የመጣችው---.ባለፈው ፌብሪዋሪ 6 ለማስመረቅ አስበን ነበር፤ጤንነትዋ ጥሩ ስላልሆነ ተመለሰች፡፡ ከቦብ ማርሊ ቤተሰብ ምን አገኘህ? መውደድን የተማርኩት ከእነሱ ነው፡፡ በጣም ጥልቅ ፍቅር ነው ያሳዩኝ፡፡ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ጃማይካዎች፡፡ ጃማይካ ውስጥ ---- ጌቶ ውስጥ ብትይ፣ አፕታውን ብትይ፣ የፈለኩበት ቦታ ብሄድ ---- ንጉስ ነኝ፡፡ በቅርቡ ሎሳንጀለስ ሄጄ፤ ከዚጊ ማርሊ ጋር ትንሽ ጊዜ አጥፍቼ ነው የመጣሁት፡፡ በጣም ጠንካራ የሆነ ግንኙነት አለን፡፡ እማልቀይረው፡፡
ዳሎል ባንድ ከቦብ ማርሊ ልጅ ጋ ከተለያየ በኋላ እጣ ፈንታው ምን ሆነ? ይሰራል፡፡ ወንድሞቼ ዘለቀና ሙሉጌታ እየሰሩ ነው፤እንደውም እኮ እዚህ አገር ናቸው አሁን፡፡ ከዛ በኋላ ግን ኒውዮርክ መጥቼ ቢሮ ከፈትኩ፡፡ ለ19 ዓመት ኒውዮርክ ነበር ቢሮዬ፤ እመላለሳለሁ በሳምንት፣ በወር ... ጃማይካ፡፡ የማኔጅመንት ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ የኒውዮርክ እምብርት ላይ..ሆኜ ማኔጅ አደርግ ነበር - እነ ዚጊን፡፡ በዚህ መሃል የዛሬ 10 ዓመት ገደማ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ብቅ አለች፡፡ እስዋን ይዟት የመጣው ቶማስ ጎበና የተባለ ቤዝ ጊታር ተጫዋች ነበር፡፡ ከቤቴ ሁለት ብሎክ ላይ ሆኖ ስልክ ደወለልኝና- ‹‹አንድ ዘፋኝ ይዤልህ መጣሁ›› “የት ነው ይዘሃት የምትመጣው?” “ይህችን ልጁ አንተ ልታገኛት ይገባል..አለበለዚያ የትም አትደርስም...አንተ እንድታግዛት ነው” ብሎ ይዟት መጣ፡፡ ያኔ ጂጂን አላውቃትም ነበር፡፡ ጥሩ ድምፅ አላት፤ በጣም ጉጉ ናት፡፡ አወራኋት፡፡
ግቢዬ ውስጥ በጓሮ በኩል የሙዚቃ ቤት አለኝ..ገባንና ዝፈኝ አልኩዋት..ለቀቀችው፡፡ በጣም ተደነቅሁ፤ ደነገጥኩ፡፡ ማመን አልቻልኩም፤ ድፍረቷ፣ተሰጥዖዋ----በጣም ጎበዝ ልጅ! በዛን ወቅት የምትኖረው ሳንፍራንሲስኮ ነበር፡፡ ሳፍራንሲስኮ የሙዚቃ ከተማ አይደለም፤ ኒውዮርክ መምጣት አለብሽ አልኳት፡፡ ‹‹ብር የለኝም›› አለች፡፡ ‹‹ግዴለም እሱን ለእኔ ተይልኝ›› አልኳት፡፡ መጣች፤በጣም ጥሩ ቤት ተከራየንላት፡፡ ከትልቅ ኩባንያ ጋር አፈራረምኳት፡፡ አንዴም ድምጿን አልሰሙዋትም፤ በእኔ እምነት ነው የፈረሙት፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ አምጥቼ ሰጠኋት፤ አላመነችም፡፡ ጂጂን የማደንቃት ነገር ቢኖር ከዛ ገንዘብ ላይ ብዙውን ወደ ባህርዳር ቤተሰቦችዋ ጋ መላኳ ነው፡፡ በጣም ገረመችኝ፡፡ ገና ሳትደራጅ..ራስዋ በእግሯ ሳትቆም፡፡ በኋላ ቤላስዌልን አስተዋወቅኋት፡፡ ባለቤቷን ማለትህ ነው? ቤልን እንደ ጥላ ያመጣሁት እኔ ነኝ፡፡ አገባችው፡፡ በቃ አደገች፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ ቴዲ አፍሮ መጣ፡፡ እንደ ጂጂ ሁሉ የእርሱም በጣም የሚደንቅ ነበር፡፡ አላውቀውም፡፡ አንድ ዲጄ መንጌ የሚባል ልጅ አለ፡፡ “አንድ ጎበዝ ልጁ ተፈጥሯል አዲስ አበባ፤ እሱን ማኔጅ ማድረግ አለብህ” አለኝ.. “እኔ ጊዜ የለኝም” ብዬ አባረርኩት፡፡ የባለቤቴ ቅርብ ዘመድ ነው፡፡
እኔ ቱር ሄጄ ስመለስ ባለቤቴን በደንብ አድርጎ ሞልቷት፤እኔ ስመጣ የመጀመሪያ አጀንዳ ያደረገችው ቴዲ አፍሮ ነበር፡፡ በቃ እሽ አልኩ፡፡ እዚህ መጣሁና አገኘሁት፤ወደ ቺካጎ ይዤው ሄድኩኝ..ባንድ አዘጋጀሁለት..እኔ እዛ ክለብ ነበረኝ፤ ከዘለቀ ጋር ‹‹ዋንቴር›› የሚባል የታወቀ ክለብ ውስጥ ቀን ከሌት እንዲለማመዱ አደረግሁ --- ለአንድ ወር ተኩል፡፡ ሙዚቀኞች አያውቁትም ነበር፤እሱም አያውቃቸውም.. እኔም የዚህን ልጅ ስራ ብዙ አላውቅም፤ተገናኝተው ሲሰሩ ስሰማ በጣም ተደነቅሁ-----ሶስት ሙዚቃ ሰምቼ በአራተኛው ላይ ታክሲ ይዤ ለሌላ ስራ ወደ ኤርፖርት ሄድኩ፡፡ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ሾው አቀረብን፤ታሪክ ነው የተሰራው፡፡ ከሌሎች አለማቀፍ ዘፋኞችስ ጋር--- ከሎረን ሂል ጋር ትንሽ ጊዜ ሰርቻለሁ፤“አርዝ ዊንድ ኤንድ ፋየር” ከሚባሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች ጋር ለትንሽ ጊዜ ሰራሁ...፡፡ እነሱን የማውቃቸው ቺካጎ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹ተም ተም ዋሽንግተን›› የሚባል በጣም ከባድ አሬንጀር አለ፡፡ በአሜሪካ ምርጥና ድንቅ የሚባል፡፡ በሱ በኩል ነው የተዋወቅኋቸው፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥህን እናውራ--- ኢትዮጵያ ከመጣሁ አምስት አመቴ ነው፡፡ ላይንስ ዴይ ሆቴል የሚባል አለኝ፡፡ ባለቤቴ ነች የምታስተዳድረው፡፡
በጣም ጎበዙ ልጅ ናት፡፡ ሶስና ሽፈራው ትባላለች፡፡ ሁለት ልጆች አሉን፡፡ ሌሎችንም ስራዎች በአገሬ መስራት ጀመርኩ፡፡ የማዕድን ስራ፣ እርሻውን.. ከባለሞያዎች ጋር እየሰራን ነው፡፡ አዲስ የሙዚቃ ባንድም አቋቁመሃል ----- አዎ፡፡ ብዙ ልምድ አለኝ፡፡ ያለኝን ነገር ይዤ መሄድ አልፈልግም፡፡ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ በመጀመሪያ እንደመጣሁ በሙዚቃው ንፍቀክበብ ምን ማድረግ አለብኝ ብዬ አስብ ነበር፡፡ በየክለቡ፣ አንዳንድ ቦታዎች እየዞርኩ ሙዚቀኞችን አያለሁ፡፡ አንድ ጊዜ ምን ወሰንኩ---በቃ የሙዚቃ ባንድ መመስረት አለብኝ አልኩኝ፡፡ የራሳቸው ሳውንድ እንዲኖራቸው እፈልጋለሁ...ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ እንደ አትሌቶች..ደራርቱ፣ ጥሩነሽ፣ሃይሌ የአገራችንን ህዝቦች እንደሚወክሉ ሁሉ በሙዚቃው ደግሞ ይህን ሃላፊነት መውሰድ አለብኝ በሚል‹‹ጃኖ ባንድ›› ተጠነሰሰ፡፡ ይሄንን ሳደርግ ደግሞ ኤርምያስ አመልጋ (አክሰስ ሪል ስቴት) ባለቤት ጓደኛዬ ነው፤ ሄጄ አማከርኩት፡፡ ከመቶ መቶ ሃምሳ ከጎንህ ነኝ አለኝ፡፡ ‹‹አብረን እናድርገው›› አለ፤ከእርሱ ጋር አብረን ጀመርን፡፡ እኔ ነኝ ልጆቹን የሰበሰብኳቸው - ስምንት ሴቶች፣ አስራ አምስት ወንዶች መረጥኩኝ፡፡
ከኒውዮርክ እንዲረዳኝ ብዬ ቤላስዌልን ጠራሁት፡፡ ሴቶቹን በሙሉ አባረራቸው (ሳቅ)፡፡ ወንዶቹንም ስምንት ልጆች ብቻ ይበቃናል አለ፡፡ ፈትናችኋቸው ነው? አዎ እንዲዘፍኑ አደረግን.. ከዛ ሁለት ሴቶች ሃሌ ሎያና ሄዋንን እኔ ጨመርኩኝ፡፡ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተመሰረተ፡፡ ‹‹ተተካኩ›› ብላችሁ አይደል (ሳቅ) ጅምሬ ወዴት እንደሚሄድ አውቀዋለሁ...ትልቅ ነገር ነው የምንሰራው---- የኢትዮጵያን ስም የሚያስነሳ፡፡ ዲሲፕሊን ካላቸው ልጆች ጋር እየሰራሁ ነው፡፡ ቪዥነሪስ ናቸው፡፡ የምፈልገውን ራዕዬን (ቪዢኔን) የሚያሟላልኝ ቡድን ተፈጠረ፡፡ በጣም ጎበዞች ናቸው፡፡ ቢላስዌል እንደ ፕሮዲዩሰር ነው የመጣው፡፡ እሱ ደግሞ አራት ኢንጂነሮች ይዞ መጣ፡፡ ስራችን ሁሉ በዓለም የሙዚቃ ደረጃ የሚሰራ ነው፡፡ ‹‹ኤርታሌ›› የሚል ስያሜ የሠጠነውን የመጀመሪያ አልበማችንን እኔ ሪኮርድ አድርጌ ይዘን ሄድን፤ አሜሪካን አገር፡፡ እዚያ ተሰርቶ ተላከልን፡፡ እኛ ደግሞ ሲዲውን እዚህ ለቀናል፡፡
ሁለት ዓመታችን ነው፤ አንዳንድ ሾዎችን መስራት ጀምረናል፡፡ ዛሬ በ‹‹ላፍቶ ሞል›› ኮንሰርት አለን፡፡ ከዛ በኋላ አራት የኢትዮጵያ ዋና ከተማዎች ውስጥ ሰርተን ለፋሲካ ወደ አሜሪካ እንሄዳለን፡፡ ሮክ በእኛ አገር አልተለመደም---- እንደውም የሰው አቀባበል በጣም ነው ያስደነቀኝ፡፡ ከማምነው በላይ ነው የሆነብኝ..በየመኪናው፣ በየመገናኛ ብዙሃኑ፣ በየክለቡ ዘፈኑ ሲለቀቅ እሰማለሁ...ከክፍለ ሃገር መልክት ይደርሰኛል፡፡ በማህበራዊ ድረ ገፆች የሚመጣውን አስተያየት አያለሁ፡፡ በአጭር ጊዜ ነው ይህ የመጣው፡፡ የምሰራውን ነገር የሀገሬ ህዝብ ሲያደንቅልኝ አስቢ--- ምን ሊሰማኝ እንደሚችል፡፡ ትልቅ ደስታን የሚያጎናፅፍ ነገር ነው፡፡ ‹‹ጃኖ›› የሚለው የባንዱ ስያሜ እንዴት ወጣ?. በዲሞክራሲ አምናለሁ፡፡ የኖርኩበት የአሜሪካ ማህበረሰብ ያስተማረኝ ነው...በዚህ ሁኔታ ልጆቹ ስም ለማውጣት በጣም የተለያዩ አማራጮችን አቅርበው ነበር፡፡ ለሁለት ሳምንት ተከራክረንበታል፤ግን በተደጋጋሚ ይህ ስያሜ ስላሸነፈ በጃኖ ተሰየመ፡፡ ጃኖ ባንድ በዓለም ላይ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በማስተዋወቅ እንደ ቦብ ማርሊ.. ከሳውዝ አሜሪካ እንደወጡ የተለያዩ ሙዚቀኞች ይህችን የምንወዳትን ሃገራችንን በሰፊው ለማስተዋወቅ አልመናል፡፡ መድረሻችንን አውቀዋለሁ፡፡ ይህም በቅርብ ይሆናል፡፡
- “ጃኖ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው” ኪሩቤል ተስፋዬ የጃኖ ባንድ ኪቦርድ ተጫዎችና የቡድን መሪ ሲሆን ለ12 ዓመት በተለያዩ ባንዶች ውስጥ እንደሰራ ይናገራል፡፡ የ28 ዓመቱ ኪሩቤል በባንዱ ውስጥ ካሉ የሙዚቃ ባለሞያዎች በዕድሜ ትልቁ ነው፡፡ ስለጃኖ ባንድ ስያሜ ንገረኝ--- ከሙዚቃችን ተነስተን ነው፡፡ ሙዚቃችን ከግማሽ በላይ አማርኛ ነው፡፡ አገርኛ ነው፤ ባህላዊ፡፡ ያንን የሚያንፀባርቅ፣ሙዚቃችንን የሚገልፅ፣ ሰዎች ሲሰሙት ለጀሮ የሚቀል በሚል ነው--- ብዙ ስሞች መጥተው መጨረሻ ላይ ‹‹ጃኖ›› ላይ ፀናን፡፡ ጃኖ በራሱ የአገር ልብስ ጥለት ነው፤ ኢትዮጵያዊ መለያችን ነው፤ያምርብናል፤ ደመቅ ያለ ያማረ..በባህልና በስርዓት ለየት ላለ በዓል የሚደረግ ነው...የክብር ልብስ! ሁልጊዜ የሚደረግ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነታችንን በጣም ይገልፅልናል፡፡ እኛም እያደረግን ያለነው የአገራችንን ሙዚቃ ሌላው የዓለም ክፍል በሚረዳው መልኩ ለማቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ሙዚቃ እንዳላት ከዚህ በፊት ከተሰራው በተሻለ አቅም ለማስተዋወቅ ስለሆነ ጃኖ ባንድ ይገልፀዋል፡፡ የአልበማችሁን ስም ደግሞ “ኤርታሌ” ብላችሁታል---- ኤርታሌ በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ የሚገኝ ድንቅ ነገር ነው፡፡ እኛም የመጀመሪያ ኮንሰርታችንን ስንሰራ አዲስ የታመቀ ሃይል ፈንድቶ ሲወጣ፤ ሃይላችንን አቅማችንን አሳየን፡፡ ጊዜያችንን ሰጥተን የለፋንበት ስራ ነው፡፡ እሳተ ጎሞራም እንዲሁ ነው፤ ካልታሰበ ቦታ ገንፍሎ የሚወጣው አንፀባራቂ የሆነ ነገር----- እሳተ ጎሞራውም ወደ አለትነት ይቀየራል፡፡ ያ ደግሞ ያለን አቅምና ሃይል ነው የሚገልፀው፡፡ የመጀመሪያ አልበማችን ይህን ይገልፀዋል፡፡ አልበሙ ውስጥ ስለሃገር፣ ስለፍቅር፣ ስለማንነት፣ተዘፍኗል፡፡ አልበሙንና እኛን የሚገልፅ ስም ይሆናል በሚል ነው ‹‹ኤርታሌ›› ያልነው፡፡ ሙዚቃ እንጂ ድምፃዊያን የላቸውም፣ ለዜማና ለግጥም አይጨነቁም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል----- እንደዚህ ዓይነት አስተያየት አለ፤ ከብዙ አቅጣጫ፡፡ አዲስ ነገር እኛ አገር ይዘሽ ስትመጪ፤ ቶሎ ለመቀበል ይቸግራል፡፡ እኛም ፈርተነው ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ እያስለመድነው ወደ ምንፈልገው ደረጃ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ በዓለም ደረጃ እነሱ በሚያውቁት መልኩ ለማቅረብ፣አገር ውስጥ ላለው ደግሞ ከተለመደው ከሚሰማው የተለየ ብንሰጠው ይወደዋል ብለን ነው የሰራነው፡፡ ተቀባይነቱ ከጠበቅነው በላይ ነው፡፡ ከአልበሙ ውስጥ ሶስትና አራት ሙዚቃዎች ሃይል ኖሯቸው መደመጥ ችለዋል፡፡ በየዘመኑ የተለያየ ሳውንድና ሙዚቃ ይመጣል፡፡ ለውጥ ይኖራል፡፡ የመጀመሪያውን የእኛን አገር ብትወስጂ ኦርኬስትራ ባንድ ነበረ፣ ዘመናዊ ሙዚቃ መጣበት፣ ከዚያ ወደ ዲጂታል እያለ ወደዚህ መጣ፡፡ በመጀመሪያው አልበማችን ሰውን ሁሉ እንቆጣጠራለን ብለን አናስብም፡፡ ቀስ በቀስ ግን እንመጣለን፡፡ በዛሬው ኮንሰርት ምን የተለየ ነገር ታቀርባላችሁ? ብዙ አዲስ ነገሮች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት ወደ አምስት ኮንሰርቶች ሰርተናል፡፡ ትንንሽ ኮንሰርቶችን፡፡ በዛ ጊዜ ውስጥ የሰራናቸው ሙዚቃዎች አሉ፡፡ ብዙዎቹ አዳዲሶች ናቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ይኼ ላያዝናና ይችላል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰው የሚያውቀውን ሙዚቃ ስትጫወችለት ነው ደስ የሚለው፡፡ ሰው የማያውቃቸውን አዳዲስ ዘፈኖች አንጫወትም ብለናል፡፡ የድሮ ክላሲክ የሆኑ ሙዚቃዎችን እንጫወታለን፤የሃገራችንን ዘፈኖች፡፡ አሁን ወጣቱ የሚሰማቸውን አዳዲስ የውጪ ዘፈኖች፤ በየክለቡ የሚዝናናባቸውንም እናቀርባለን፡፡ አራት ድምፃዊያን አሉ፤ እየተፈራረቁ ያዝናናሉ፡፡ አልበሙ ላይ ያሉትንም እንጫወታለን፡፡ በአጠቃላይ ወደ ሰላሳ ዘፈኖች ይቀርባሉ፡፡ ከምሽቱ 2፡00 ሠዓት ሲሆን በዲጄ ሲያዝናኑ ይቆይና ከ4፡00 ጀምሮ ጃኖ ባንድ በድንቅ ስራዎቹ ብቅ ይላል፡፡ ልዩ ቀን ነው፡፡
- “ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት እንፈልጋለን” ሚካኤል ሃይሉ የጃኖ ባንድ ሚዩዚካል ዳይሬክተርና ሊዲ ጊታሪስት ነው፡፡ በጊታሪስትነት ከተለያዩ ባንዶች ጋር የተጫወተው ሚካኤል፤ በራሱ ስቱዲዮ ውስጥ ሙዚቃ ያቀናብራል፡፡ እስካሁን የሚካኤል በላይነህ፣የቴዲ አፍሮ፣የአቤል ሙሉጌታና የዘሪቱ ከበደን አልበም አቀናብሯል፡፡ አንድ ህልም ነበረኝ፡፡ ወደፊት ቢሆንልኝ ብዬ የማስበው፡፡ የዚህ ባንድ ባለቤት አዲስ ገሠሠ ትግል ላይ ነበር፡፡ ልጆች ሰባስቦ የኢትዮጵያ ሙዚቃ በውጭው ዓለም እንዲታወቅ እየተንቀሳቀሰ ባለበት ሰዓት እኔ ጋ ደውሎ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ፤ ምን ትላለህ?›› ሲለኝ ሃሳቡና ሃሳቤ ተገጣጠሙ፡፡ ህልሜን እውን ለማድረግ ጃኖን ተቀላቀልኩ፡፡ የዚህችን አሪፍ አገር ባህሏን፣ ህዝቦቿን የውጭው አለም እንዲያውቋት-----ስለዚህች አገር የተለያየ አመለካከት ነው ያለው፤ ..ብዙ ጊዜ በመጥፎ ነው የምትነሳው... ያለን ነገር ብዙም አይታወቅም፤ ለአለም በሚገባ በሙዚቃ ቋንቋ ያለንን ለማስተዋወቅ ነው ሃሳባችን፡፡ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ያላት ሀገር ናት፡፡ አለም ያላየውን ብዙ ጉድ የሚያሰኝ ሙዚቃ ለዓለም ለማሳየት ነው ዓላማችን፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከሮክ የሙዚቃ ሥልት ጋር ቀላቅለን ማስተዋወቅ ነው የምንፈልገው፡፡ በእኛ አገር ደረጃ ሙዚቃ በደንብ በሃላፊነት ደረጃ ተጠንቶ የተሰራበት ጊዜ የለም፡፡ ለህዝብ አዲስ ነገር ለማሳየት ነው የተነሳነው፡፡ ወጣት ሃሌሎያ ተክለፃዲቅ የባንዱ ድምፃዊት ናት፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ስራ ኮሌጅ አካውንቲንግ ምሩቅ ናት፡፡ በ
- ‹‹ኮንሰርታችንን ተጋበዙ፤ትደነቃላችሁ››‹‹ኤርታሌ አልበም›› ውስጥ አጃቢ ድምፃዊት ናት፡፡ ወደ ሙዚቃ የገባሁት ት/ቤት እያለሁ ነው - ካቴድራል ት/ቤት፡፡ ካርኒቫሎችና ፌስቲቫሎች ላይ እዘፍን ነበር፡፡ የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎችን ነበር የምዘፍነው፡፡ ከአኩስቲኮች ጋር እጫወት ነበር፡፡ ያን ጊዜ ነው ከአዲስ ጋር የተዋወቅሁት፡፡ አላመንኩትም ነበር፤ በጣም ትልቅ ነገር ስለሆነ፡፡ እኔንና ሄዋንን ቤላስዌል መጥቶ አየን፤ጥሩ ነው ብሎ ቀጠልን፡፡ ጥሩ ባንሆን ያስወጣን ነበር፡፡ ከጃኖ ባንድ ጋር ብዙ ኮንሰርቶችን እየሰራን ነው፤ በጣም ደስ የሚል ስብስብ ነው፡፡ አስራችንም እንደ አንድ ሰው ነው የምንጠራው፤ ‹‹ጃኖ ባንድ›› ተብለን፡፡ ለሃገራችን አልመን እየሰራን ስለሆነ ተመልካቾች የዛሬን የላፍቶ ሞል ኮንሰርታችንን ተጋበዙ እዩን፤ትደነቃላችሁ...
ለአቡነ ማትያስ አራት ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ መጽሐፍ ተበረከተላቸው
ባለፈው እሁድ በዓለ ሲመታቸውን አከናውነው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ የሆኑት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፤ አራት ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ተበረከተላቸው፡፡ ለፖርቱጋል መንግስት ይሰራ በነበረው ስፔናዊ ፔድሮ ፓያሽ በ1622 ዓ.ም በፖርቱጋልኛ ታትሞ በቅርቡ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውን የግእዝ አንቀፆች ያሉት መጽሐፍ፤ በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን ተገኝተው ለፓትርያርኩ በስጦታነት ያበረከቱት በኢትዮጵያ የፖርቱጋል አምባሳደር አንቶኒዮ ሉዊስ ኮትራም ናቸው፡፡
በሁለት ጥራዝ የተካተተውን የታሪክ መጽሐፍ ከፖርቱጋልኛ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም ስምንት አመታት የፈጀ ሲሆን በለንደን የታተመው መጽሐፍ ዋጋ 100 ፓውንድ ነው፡፡ መጽሐፉ ወደ እንግሊዝኛ ሲመለስ የፖርቱጋል ኤምባሲ የባህል አታሼና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖርቱጋሊኛ አስተማሪዎች ዶር. ኢዛቤል ቦቫዲያ፣ ማኑኤል ዣዎ ራሞስ እና ሄርቭ ፔናክ የአርትኦት ሥራውን ሠርተዋል፡፡ በሁለት ጥራዝ 900 ገፅ ያለው መጽሐፍ የወቅቱን የኢትዮጵያ አስተዳደር፣ ሃይማኖት፣ አለባበስ፣ እንስሳት … የያዘ ኢትዮግራፊክ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉ አዘጋጅ ፔድሮ ፓየዝ በአፄ ሱሱንዮስ እና አፄ ፋሲል ዘመነ መንግስት የመጣ የካቶሊክ ሐይማኖት ቄስ ነው፡፡
ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሕፃናት መጻሕፍት ያስመርቃል
ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዛሬ ሁለት የሕፃናት መፃሕፍት እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡ ዛሬ በጣይቱ ሆቴል የሚመረቁትን መፃሕፍት ነዋሪነቱን በሩስያ ይኖር የነበረው ኢትዮጵያዊ ደራሲ ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ነው፡፡ ሁለቱ መፃሕፍት ሲመረቁ የደራሲው ልደትም እንደሚታሰብ ዩኒቨርሲቲው ገልጿል፡፡ እያንዳንዳቸው አርባ ገጽ የሆኑት የሕፃናት የተረት መጻሕፍት “The Giant pineapple” እና “Muna’s Monkey” ሲሆኑ የመፃሕፍቱ ሥዕሎች በጃፓናዊት አርቲስት እንደተሰሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የሁለቱም መፃህፍት ዋጋ 33 ብር ነው፡፡ ደራሲው በሕፃናት ላይ ያተኮሩ አስራ አምስት መፃሕፍትን ጽፏል፡፡ በሌላም በኩል “የአህዛብ ጣዖታት” የተሰኘ የግጥም መጽሐፍ ነገ እንደሚመረቅ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር አስታወቀ፡፡ በአቶ ዳንኤል መንገሻ የተገጠሙ ግጥሞችን የያዘው መጽሐፍ የሚመረቀው በሀገር ፍቅር ትያትር ትንሿ አዳራሽ ነው፡፡
የግጥም በጃዝ 20ኛ ዝግጅት ረቡዕ ይቀርባል
.ወጣት እና አንጋፋ ገጣሚያን ሥራዎቻቸውን በሙዚቃ እያጀቡ የሚያቀርቡበት የግጥም በጃዝ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዚህ ዝግጅት ላይ ነቢይ መኮንን፣ ተፈሪ ዓለሙ፣ ጌትነት እንየው፣ ወሠንሰገድ ገብረኪዳን እና ምህረት ከበደ ግጥሞቻቸውን በአዲስ ጣእም ባንድ ሙዚቃዎች ታጅበው ያቀርባሉ፡፡ የዝግጅቱ መግቢያ በነፍስ ወከፍ 50 ብር ነው፡፡
“ባንቺ ጊዜ” ፊልም ይመረቃል
በባህሬን ከድር፣ ደረጄ ጋሻውና ኤልያስ አለሙ ተፅፎ የተዘጋጀው “ባንቺ ጊዜ” ፊልም ነገ እና ሰኞ እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በክልል እና በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች የሚመረቀው የ97 ደቂቃ ፊልምን ለመስራት ስድስት ወራት ያህል ፈጅቷል፡፡ በፊልሙ ላይ ሄለን በድሉ፣ ባህሬን ከድር፣ መልካም ይደግ፣ ኤልያስ አለሙ፣ ናትናኤል አማኑኤል፣ ብርሃኑ በነበሩ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡
ለንባብ የበቁ መፃሕፍት
የብራዚል ፊልም ፌስቲቫል ሰኞ ይከፈታል
በኢትዮጵያ የብራዚል ኤምባሲ ያዘጋጀው የፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሰኞ እንደሚጀምር ኤምባሲው አስታወቀ፡፡ ቦሌ በሚገኘው የብራዚል ኤምባሲ ለሕዝብ ከሚቀርቡት የብራዚል ፊልሞች መካከል ሶስቱ አስቂኝ ሦስቱ ድራማ ናቸው፡፡ ፊልሞቹ በየእለቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚታዩ ሲሆን ለአንድ ሳምንት እንደሚቆዩ ታውቋል፡፡ የመግቢያ ዋጋ በነፃ ነው፡፡
“Mandela’s Gun” በኢትዮጵያም ሊቀረጽ ነው
የደቡብ አፍሪካውን አንጋፋ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ሽጉጥ አስመልክቶ እየተሰራ ያለው ፊቸር ዶክመንተሪ ፊልም በኢትዮጵያም ሊቀረጽ ነው፡፡ የእንግሊዝ “ቢር ኸርት ሊሚትድ” እና የደቡብ አፍሪካ DV8 ኩባንያዎች በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በእንግሊዝ ቀረፃውን ያከናወኑ ሲሆን በኢትዮጵያ “ታይኩን ሪል ስቴት” በተባለ ኩባንያ አማካይነት የአሰሳ ጥናት ተጀምሮ ፊልሙ ሊቀረጽ እንደሆነ በኢትዮጵያ ለፊልሙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን የሚያስተባብረው ርእዮት ኪነጥበባት ፕሮሞሽን በተለይ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በትጥቅ ትግል ወቅት ኮለኔል ከነበሩት ኢትዮጵያዊ ጀነራል ታደሰ ብሩ ሽጉጥ ተበርክቶላቸው እንደጠፋና ቤት ቢፈርስም ሽጉጡ አለመገኘቱ ይታወቃል፡፡
ኢህአዴግ፣ የ“ዲሞክራሲ” እና የነፃ ገበያ ጭንብል ሰለቸው?
\ኢንቨስተርና ነጋዴ ሁላ! ተቃዋሚ ፓርቲ መስርት ተብለሃል። በማን? በኢህአዴግ ነፃ ገበያና “ዲሞክራሲ”፡ የህልውና ጥያቄ ሲሆኑበት ኢህአዴግ እስከ ዛሬ፤ ነፃ ገበያን እና የአሜሪካ ዲሞክራሲን ላለማጣጣል ይጠነቀቅ ነበር። በተለይ ከ1993 ዓ.ም ተሃድሶ ወዲህ፣ አውሮፓንና አሜሪካን በአርአያነት ይጠቅስ ነበር። ገናናነትና “ሶሻሊዝም”፡ የማይጥላቸው አባዜ ሲሆኑበት የኢህአዴግ መፅሄት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በግላጭ እያንቋሸሸ ፅፏል። የነአሜሪካን ዲሞክራሲ በማብጠልጠል፤ ኢህአዴግ በአለም ወደር እንደሌለው ገልጿል።
በአንድ በኩል፤ “ንብረት እየዘረፈ የሚያከፋፍል ቀማኛ”…. በሌላ በኩል ደግሞ “የንብረት መብትን የሚያስከብር ፖሊስ” መሆን ይቻላል? ሁለቱ ምርጫዎች ተቃራኒዎች ናቸው - የድህነትና የብልፅግና፣ የንጥቂያና የመብት፣ ወይም የሶሻሊዝምና የካፒታሊዝም ጎዳናዎች። በአንድ በኩል፣ “ያለ ፉክክር በአፈና ስልጣን የሚቆጣጠር ገናና ፓርቲ”… በሌላ በኩል ደግሞ “የአሜሪካና የአውሮፓ የዲሞክራሲ ስርዓቶችን የሚያደንቅ ባለራዕይ ፓርቲ” መሆንስ ይቻላል? እነዚህም ተቃራኒ ጎዳናዎች ናቸው - አንደኛው የውርደት፣ የመጠፋፋትና የውድቀት፣ ሌላኛው ደግሞ የመከባበር፣ የሰላምና የስኬት ጎዳና። ኢህአዴግ፤ ላለፉት አመታት መከራውን ሲያይ የቆየው እነዚህን ተቃራኒ ምርጫዎች ወይም ጎዳናዎች አቀላቅሎና አዳቅሎ ለመጓዝ ነው።
አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተፈጥሮው፤ “ነፃነትንና መብትን ከአፈናና ከዝርፊያ” ጋር ያደባለቀ ቅይጥ ፖለቲካ አይደል? ግን ምን ዋጋ አለው? “ሁለት ወዶ” አይሆን! እንደ ህዝቡ ስሜትና እንደ አለማቀፉ አዝማሚያ፣ አንዳንዴ ወደ ግራ እየሸመጠጠ፣ አንዳንዴ እየተመለሰ፤ አንዴ የነፃ ገበያና የዲሞክራሲ “ጭንብል” እያጠለቀ፣ ሲያገረሽበት ደግሞ የሶሻሊዝምና የገናናነት ጭምብል እየለበሰ ለመጓዝ ሲሞክር… በተቃራኒ አቅጣጫዎች ተወጥሮ በጭንቀት ይሰቃያል። የኢህአዴግ መፅሄት “አዲስ ራዕይ” የቅርብ ጊዜ እትም ሲነበብ ግን፣ ፓርቲው በነፃ ገበያና በዲሞክራሲ ጭንብል ተሰላችቶ፣ ወደ ድሮው የሶሻሊዝም ፍቅር ጭልጥ ብሎ መግባት ያማረው ይመስላል። ይሄ አዲስ እና አደገኛ ነገር ነው።
ሳይረፍድበት ሰከን ብሎ፣ “ነፃ ገበያና ዲሞክራሲ” የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን እንደገና ካልተገነዘበ፤ እያንቋሸሻቸው የሚቀጥል ከሆነ፣ ጦሱ ያስፈራል። ፓርቲውና አገሪቱ በቀላሉ ከማይወጡበት የትርምስ አዘቅት ውስጥ ይዘፈቃሉ። እርግጥ ነው፤ ኢህአዴግ እንደብዙዎቹ የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎች፣ መቼም ቢሆን ለነፃ ገበያ ፍቅር ኖሮት አያውቅም። በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና ፓርቲዎች በምርጫ የሚፎካከሩበት “የሊበራል ዲሞክራሲ” ስርዓት ለኢህአዴግ አይጥመውም። ኢህአዴግኮ፣ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ፤ “እኔን የሚስተካከል ኮሙኒስት (ሶሻሊስት) ይምጣ!” ሲል የነበረ ድርጅት ነው። ለነገሩ ሌሎቹ አንጋፋ ፓርቲዎችም ከዚህ የተለየ ባህርይ አልነበራቸውም። በደርግ (በኢሰፓ)፣ በኢህአፓ፣ በመኢሶን፣ በኢህአዴግና በሌሎች የአገሪቱ አንጋፋ ፓርቲዎች መካከል የነበረው ፀብ፤ “ሃቀኛ ኮሙኒስት እኔ ነኝ፤ እውነተኛው ሶሻሊስት እኔ ነኝ” የሚል ነበር። ደግነቱ፤ ፓርቲዎቹ ያኔ በጀመሩት የጥፋት አቅጣጫ እስከመጨረሻው ሊዘልቁበት አልቻሉም። ደርግ በአገሪቱ ውስጥ ያሰፈነውን የሶሻሊዝም ስርዓት ይዞ መቀጠል አቅቶት በ82 ዓ.ም ቅይጥ ኢኮኖሚን ሲያውጅ፤ ኢሰፓንም ለማፍረስ አቅዶ አልነበር? ልክ እንደዚያው፤ ኢህአዴግም የድሮ ሃሳቡን የሙጢኝ ብሎ “ሶሻሊዝም” እያለ ሊቀጥል አልቻለም።
ለምን ብለን ብንጠይቅ ሁለት ምክንያቶችን እናገኛለኝ። ደርግ የተዳከመበትና ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ የተቃረበበት ወቅት ላይ ሆናችሁ አስቡት። አንደኛው ምክንያት፤ ደርግ የተዳከመበትና ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ የተቃረበበት ወቅት፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሶሻሊዝም ተንኮታኩቶ፣ የዜጎች ድህነት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ መሆኑ ነው። መንግስት ኢኮኖሚውን በሙሉ እየተቆጣጠረና እየዘረፈ፤ ሰዎች ህይወታቸውን ለማሻሻልና ሃብት ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት እንደጥፋት እየተቆጠረ… እንዴት ኢኮኖሚው አይንኮታኮት? “እንኳን ዘንቦብሽ…” ሆነና፤ ኢትዮጵያ ማለት፣ በረሃብ መቶ ሺ ሰዎች የሚረግፉባት አገር ሆና አረፈችው።
ደህይቶ እርቃኑን በቀረ አገር ውስጥ፣ የዝርፊያ ስርዓት ይዞ ለመቀጠል መፎከርና መፍጨርጨር ከእብደት የማይተናነስ እንደሆነ በግልፅ መታየት ጀመረ። የሃብት ሽታ በጠፋበት ዘመን፣ “የሃብት ክፍፍል” እያሉ ሶሻሊዝምን ማነብነብ፤ ክፋት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ጭምር ይሆናል። ዝርፊያን እንደ ቅዱስ ተግባር ብንቀበለው እንኳ፣ ከአንድ ሰው ሃብት ዘርፎ ለሌላው መስጠት የሚቻለውኮ፤ በቅድሚያ ሃብት የሚፈጥሩ ሰዎች ሲኖሩ ነው። በያኔው ዘመን ግን፣ ሃብት ፈጣሪዎች ድራሻቸው ጠፍቷል። በአንድ ክረምት ድርቅ ሚሊዮን ሰዎች የሞቱባት ኢትዮጵያ፣ ከአመት አመት በሚባባስ ድህነት እየተዋጠች የነበረችበት ወቅት ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ በ60ዎቹ ዓ.ም የአገራችንን ተማሪዎች በስሜት እንዲጦዙ ያነሳሳቸው የኮሙኒዝም (የሶሻሊዝም) አስተሳሰብ፣ በ80ዎቹ ዓ.ም መባቻ ላይ በአለማቀፍ ደረጃ አከርካሪው መሰበሩ ነው። ዋነኛ አቀንቃኝ የነበሩ የሶቭየት ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ኮሙኒስት መንግስታት ፈራረሱ።
በእርግጥ “ለጭቁኖችና ለወዛደሩ ጥቅም!” በሚሉ ሰበቦች፣ ሰው እንደ መስዋእት በግ ለእርድ እንዲሰለፍ የሚያደርግ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ ተንኮታኮተ ማለት፣ ክፋት አበቃለት ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ለራሱ እንዳያስብ፣ የራሱን ጥቅም መስዋእት እንዲያደርግና የሌሎችን ጥቅም እንዲያስቀድም የሚሰብኩ… ሰውን እንደ መስዋእት በግ የሚነዱ ሌሎች ኋላቀር አስተሳሰቦች ሞልተዋል። የጥፋት ሰባኪዎቹ፤ በዝርፊያም ሆነ በአፈና እያንዳንዱን ሰው በአጭር ለማስቀረት ያለሙ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም፣ የግለሰብን ነፃነትና መብት ለመርገጥ የሚያቀርቡት ማመካኛ ሰበባቸው ግን ይለያያል። አንዱ “ህዝብ ይቅደም!” ብሎ ሲጮህ፣ ሌላኛው “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እያለ ፀብ ውስጥ ገብተው የዜጎችን ኑሮ ያምሳሉ - የሁሉም አውራ ለመሆን።
አንዱ “ሃይማኖት ትቅደም!” ሲል፣ ሌላኛው “ወግና ልማድ ይቅደም!” እያለ ሰውን ያሸብራሉ - በበላይነት ስልጣን ለመያዝ። አንዱ “አንድነት ይቅደም” ሲል፣ ሌላኛው “ብሄር ብሄረሰብ ይቅደም” እያለ አገሬውን በጦርነት ያተራምሳሉ - ገናና ሆኖ ለመውጣት። ከእነዚህ በርካታ ኋላቀር አስተሳሰቦችና ባህሎች መካከል አንዱ፤ ሌሎቹን ሁሉ ጠቅልሎ ወይም አሸንፎ በበላይነት ገናና ለመሆን ሲችል፤ ግርግሩና ውጥንቅጡ ቆሞ፣ አገሬው ሁሉ ፀጥ ረጭ ይላል። “ስርዓት ያለው አፈናና ዝርፊያ” ይሰፍናል። ገናና የሚሆን አስተሳሰብ ከሌለ ግን፣ “ስርዓት ያለው አምባገነንነት” ሊፈጠር አይችልም። ትርምስና ቀውስ ይነግሳል። እንግዲህ አስቡት! በርካታ የዝርፊያና የአፈና ኋላቀር ባህሎችን በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብና በበላይነት እየመራ በቀላሉ አምባገነንነትን ለማስፈን በቂ ጉልበት የነበረው የኮሙኒዝም አስተሳሰብ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ወደቀ። እናም በቀላሉ አምባገነንነትን ማስፈን የሚቻልበት ጊዜ አበቃለት። ለምን ቢባል፤ ኋላቀር ባህሎችን አጠቃልሎ በበላይነት የሚመራ ርዕዮተ ዓለም (አስተሳሰብ) የሌለውና በጠመንጃ ላይ ብቻ የሚተማመን አምባገነን ስርዓት ብዙ እድሜ አይኖረውም። የተለያዩ ኋላቀር ባህሎችን በየፊናቸው የሚያቀነቅኑ የተለያዩ ቡድኖች፣ በመላ አገሪቱ ብቸኛ ዘራፊና ቀማኛ ሆነው ለመግነን ሲፋጩ እርስ በርስ እየተጋጩ ይጨፋጨፋሉ። በአገር አንድነት ስም “አገርህን አስቀድም” እያለ፣ አልያም በሃብት ልዩነት “ድሆችን አስቀድም” እያለ፤ በሃይማኖት ተከታይነት “አምልኮን አስቀድም” እያለ፣ አልያም በአካባቢ ተወላጅነት “ብሄር/ብሄረሰብን አስቀድም” እያለ፣ … በጭፍን ስሜት ሰዎችን እያቧደነ ስልጣን ለመቀራመት የሚፈልግ የአፈና ጥመኛና የዝርፊያ ሱሰኛ ሁሉ፤ የጥላቻ መርዝና የሞት ጥይት ያርከፈክፋል። የዩጎዝላቪያ፣ የሶማሊያ፣ የሴራሊዮን፣ የሩዋንዳ አይነት ውጥንቅጥና እልቂት ይፈጠራል። ኢህአዴግ፤ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ በተንኮታኮተበት ዘመን፣ “ከድሮው የኮሙኒዝም አስተሳሰቤ ፍንክች አልልም፤ የመጣው ይምጣ” ቢል ኖሮ፤ ውጤቱ ከእንዲህ አይነት ውጥንቅጥ የተለየ አይሆንም ነበር። ከደርግ አምባገነንነት ወደ ትርምስ ነበር የምንሸጋገረው። በቅርቡ የታተመው የኢህአዴግ መፅሄት (አዲስ ራዕይ) እንደሚለውም፤ ኢህአዴግ የድሮ ሃሳቦቹንና አሰራሮቹን ለመለወጥ የተገደደው፤ ያኔ የኢትዮጵያ ድህነት በተባባሰበትና በአለማቀፍ ደረጃ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ በተፈረካከሰበት ጊዜ ነው። በአጭሩ፤ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎች በሙሉ አስተሳሰባቸውን ለመቀየር የተገፋፉት ከላይ በተጠቀሱት ከህልውና ጋር በተሳሰሩ ሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ ነገር፣ በሶሻሊዝም ምክንያት ድህነትና ረሃብ ተባብሶ ሚሊዮን ሰዎች አልቀው በርካታ ሚሊዮኖች የሞት አፋፍ ላይ ስለደረሱ፤ በአብዛኛው ሰው ላይ የህልውና ጥያቄ ጥርሱን አግጥጦ መጣ። የሚዘረፍ ሃብት ተሟጦ ገዢዎችም ከህልውና ጥያቄ ጋር የተፋጠጡበት ጊዜ ነው።
ሁለተኛ ነገር፣ በየፊናቸው ብዙ መልክ ይዘው የተቀመጡ የአፈናና የዝርፊያ ኋላቀር ባህሎችን በአንድነት ጠቅልሎ በበላይነት ለመምራት ያገለግል የነበረው የኮሙኒዝም አስተሳሰብ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ ተሸርሽሮ ተንኮታኮተ። እናም፤ እንደ ቀድሞው ዘመን አምባገነንነትን ለማስፈን መሞከር ወደ ትርምስ የሚያመራ በመሆኑ፤ በሁሉም ሰው ላይ የህልውና ጥያቄ ተጋረጠበት - ገዢ ለመሆን በሚመኙ ቡድኖች ላይም ጭምር። የለየለት የረሃብ እልቂትና የመጠፋፋት ትርምስ ወዲያውኑ ባይፈጠር እንኳ፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መከሰቱ አይቀርም። ለምን እንደሆነ ወደ በኋላ እናየዋለን። አሁንም ከአደጋው ብዙም አልራቅንምና። ደግነቱ የረሃብ እልቂትንና የመጠፋፋት ውጥንቅጥን በማስቀረት ህልውናን ለመጠበቅ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን ለስልጣኔና ለብልፅግና የሚያበቃ ትክክለኛ አስተሳሰብ አልጠፋም - በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና ነፃ የገበያ ስርዓትን የሚያሰፍን የካፒታሊዝም አስተሳሰብ። ካፒታሊዝም፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት የሰፈነበት ስርዓት ነው ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል ኋላቀር የአፈና ባህሎችንና ጅምላ ጥላቻን (ለምሳሌ በሃይማኖትና በብሄረሰብ ተቧድኖ የመጠፋፋት ጭፍንነትን) ለመከላከል የሚያስችል የፖለቲካ ነፃነት አለ። እያንዳንዱ ሰው በራሱ አእምሮ የመጠቀምና ሃሳብ የመያዝ ነፃነቱ ተከብሮ፣ በፈቃደኝነት ብቻ ሃሳብ የሚለዋወጥበት ስርዓት ነው - በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና የአፈና ትርምስን የሚያስቀር የፖለቲካ ስርዓት። በሌላ በኩል ኋላቀር የዝርፊያ ባህሎችንና የሽሚያ ግርግርን ለመከላከል የሚያስችል የኢኮኖሚ ነፃነት አለ። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት የማዘዝ ነፃነቱ ተከብሮ በፈቃደኝነት ብቻ የሚገበያይበት ስርዓት ነው - የዝርፊያ ግርግርን የሚያስቀር የነፃ ገበያ ስርዓት።
በጥቅሉ፤ የሃሳብ ነፃነትንና የንብረት መብትን የሚያስከብሩ፣ አፈናንና ዝርፊያን የሚከለክሉ ህጎች ተግባራዊ የሚሆኑበት (ማለትም የህግ የበላይነት የሰፈነበት)፣ ህግ የሚያስከብር መንግስት በዜጎች ፈቃድ ስልጣን የሚይዝበት (ማለትም ፓርቲዎች በምርጫ የሚፎካከሩበት) ስርዓት ነው - ካፒታሊዝም። የሊበራል ዲሞክራሲ ስርዓት ወይም የሊበራሊዝም አስተሳሰብ በሚሉ ስያሜዎችም ይታወቃል። ህዝቡ ከእልቂት፣ አገሬው ከውጥንቅጥ መዳን የሚችለው፤ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነትን ባካተተው የካፒታሊዝም ስርዓት ብቻ ነው። ኢህአዴግ ይህንን ስለተገነዘበ ይመስለኛል፤ “የዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ስርዓት መገንባት፤ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ብሎ በተደጋጋሚ የሚናገረው - በተለይ ከ1993 ዓ.ም “ተሃድሶ” በኋላ። የኢህአዴግ አጣብቂኝ ኢህአዴግ የገባበት አጣብቂኝ ቀላል አይደለም። በአንድ በኩል፤ ለአመታት የያዘውንና ያስተጋባውን የሶሻሊዝም አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ ለመጣል አልፈቀደም። ከድርጅቱ ባህልና ከመሪዎቹ ስሜት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ አስተሳሰብ ነውና። እናም፤ አንድ ፓርቲ የአገሪቱን ሃብት ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ እንዳሻው “እያከፋፈለ”፣ በብቸኝነትም ስልጣን ይዞ እንዳሰኘው አገሪቱን የሚገዛበት ስርዓት ቢፈጥር በወደደ! በእርግጥ ይሄኛው ጎዳና፣ የአገሪቱንና የራሱን ህልውና ለጥፋት የሚዳርግ አቅጣጫ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሃብት የሚፈጠረው፣ ስልጣን የሚሰነብተውና አገር ሳይታመስ ሊቀጥል የሚችለው፤ በነፃ ገበያና በ“ዲሞክራሲ” ስርዓት ብቻ ነው። ኢህአዴግ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን ፓርቲዎች፣ “ሶሻሊዝምን” ያመልካል።
በኋላ ቀር ባህሎች ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም ወደ ረሃብና ወደ ትርምስ የሚያደርስ የህልውና ፀር ቢሆንም፣ ለሶሻሊዝም “ሟች” ነው - እናም ከነጉዳቱም ቢሆን በከፊል ተግባራዊ ያደርገዋል። የስልጣኔና የብልፅግና መንገድ የሆነው ካፒታሊዝም ደግሞ፣ የህልውና ጉዳይ ነውና ኢህአዴግ በከፊል ተግባራዊ ያደርገዋል። በ“ግዴታ” እንደተጫነበት ሸክም ነው የሚቆጥረው። ቢሆንም፤ ነፃ ገበያን ወይም የምርጫ ዲሞክራሲን በግላጭ ለማብጠልጠልና አሽቀንጥሮ ለመጣል ከመቃጣት ተቆጥቧል - ቢያንስ ቢያንስ እስካሁን ድረስ ሳይሞክር ቆይቷል። አሁን ግን “የህልውና ሸክም” የሰለቸው ይመስል፣ አሽቀንጥሮ ለመጣል ሳይዳዳው አልቀረም - “ነፃ ገበያን”ና የምርጫ ዲሞክራሲን በግላጭ ማንቋሸሽና ማጣጣል ጀምሯል። ጭራሽ፣ ባለሃብቶችን በተቀናቃኝነት ፈርጆ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም እንደሚጠበቅባቸው በመፅሄቱ ፅፏል። በእርግጥ፣ አሁን በግላጭ ሆነ እንጂ፤ ካሁን በፊትም በዘወርዋራ መንገድ ሲያደርገው ነበር። እንዴት? በአንድ በኩል፤ “ነፃ ገበያንና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲን እገነባለሁ” እያለ ይናገራል፤ ይፅፋል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በዘወርዋራ መንገድ ሁለቱንም ያጣጥላቸዋል - በጥላቻ ስሜት “ኒዮሊበራሊዝም” ወይም “ሊበራል ዲሞክራሲ” እያለ። ምን ማለቱ እንደሆነ ጥርት አድርጎ አይናገርም።
“ኒዮሊበራል” ወይም “ሊበራል ዲሞክራሲ” እያለ ሲያወግዝ፣ ነፃ ገበያንና የነ አሜሪካ አይነቱን ዲሞክራሲ ማንቋሸሹ ነው። ግን በግልፅ እንዲታወቅ አይፈልግም። ወዲህና ወዲያ ሳይጠማዘዝ ፊት ለፊት፤ ነፃ ገበያንና የነአሜሪካ ዲሞክራሲን በግላጭ ላለማጣጣል ይጠነቀቅ ነበር። እንዲያውም፤ “የዳበረ የነፃ ገበያና ልማታዊ የሃብት ፈጠራ ስርዓት”፣ “የዳበረ የዲሞክራሲና የመከባበር ስርዓት” … በማለት አሜሪካን እና የአውሮፓ አገራትን በአርአያነት ያወድሳቸዋል - ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የዝርፊያ ስርዓትና ኋላቀር ባህል ጋር እያነፃፀረ። ማጣጣልንና በአርአያነት ማወደስን ምን አመጣው? አሃ! የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ስለሚያውቅ፤ ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን ያወድሳል። ለሶሻሊዝም “ፍቅር” ሲባል፣ ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን ያጥላላል - ግን በዘወርዋራ መንገድ። በግልፅ ማጥላላትማ ብዙ ጣጣ ያመጣበታል - ህልውናን ለአደጋ የሚዳርግ ብዙ ጣጣ።
በስድስት ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን ሲያውጅ ምን እንደተከሰተ ታስታውሳላችሁ? የዋጋ ቁጥጥሩ የገበያ ውጥንቅጥንና የሸቀጦች እጥረትን ቢያስከትልም፤ ቁጥጥሩ እንዲጠናከርና በሌሎች ሸቀጦች ላይም እንዲስፋፋ ነበር ከአብዛኛው ህዝብ የጥያቄ መዓት የጎረፈው። ቀውሱ ተባብሶ ቁልቁል ወደ አዘቅት ለመግባት? መንግስት ሞኝ ካልሆነ በቀር፣ እንዲህ አይኑ እያየ ህልውናውን ለአደጋ አያጋልጥም። እለት በእለት የሚዥጎደጎዱትን የቁጥጥር ጥያቄዎች መከላከልና ራሱን ከአደጋ ማትረፍ የሚችለው ደግሞ፤ “የነፃ ገበያ መርህ”ን በመከራከሪያነት ሲያቀርብ ብቻ ነው። ለነፃ ገበያ ፍቅር ባይኖረውም፤ ከጥፋት ለመዳን ሲል፣ የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ያቀርባል።
ለዚህም ነው፤ የዋጋ ቁጥጥር ማስታወቂያዎቹ ላይ ሳይቀር፤ “በምንገነባው የነፃ ገበያ ስርዓት መሰረት፤ በጥቂት ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን አውጥተናል” የሚል አስቂኝ ሃሳብ ሲያሰፍር የተመለከትነው። ለሶሻሊዝም ባለው ፍቅር የዋጋ ቁጥጥርን እያወጀ፤ ካፒታሊዝም የህልውና ጉዳይ እየሆነበት የነፃ ገበያ ስርዓትን እገነባለሁ ይላል። “ህልውና” ሲባል፤ የኢህአዴግ ወይም የስልጣን ህልውና ማለት ብቻ አይደለም፤ የአገሪቱ ህልውናም ጭምር እንጂ። የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ኢህአዴግ ነፃ ገበያን ሙሉ ለሙሉ በአደባባይ ሲያጣጥል፤ ፋታ በሚያሳጣ ናዳ ተቀብሮ ለመቅረት መዘጋጀት ይኖርበታል። ትንፋሽ አሳጥረው ህልውናውን በሚቀጩ፣ ቁጥር ስፍር በሌላቸው የሽሚያ ጥያቄዎች እድሜውን ለማሳጠር አምሮታል ማለት ነው…. “ድጎማ ስጠን፤ የስራ እድል ፍጠርልን፤ በብሄር ተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት እኩል የስራ ኮታ ይሰጠን፣ ማዳበሪያ በነፃ አከፋፍለን፤ ስኳርና ዘይት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር መንግስት ያቅርብልን፤ የሸቀጦችን ዋጋ ተቆጣጠርልን፤ ተወላጅ ያልሆኑ ከክልላችን ይውጡልን፤ መጤዎች በዘበዙን፤ ቅድሚያ ለነባር፣ ድጎማ ለተወላጅ! ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ይሟላልን፤ አስፋልቱ በኛ መንደር በኩል ማለፍ አለበት፤ የባቡር መስመሩ በኛ ወረዳ በኩል ማለፍ አለበት፤ ለነ እገሌ ባህል በጀት እየመደብክ ለኛስ? የኛ ሃይማኖትኮ የአገሪቱ ባህል አንድ አካል ነው!”… የሽሚያ ግርግሩ ማቆሚያ አይኖረውም። የሽሚያው ትርጉም ሌላ ሳይሆን፤ “ከሌሎች ነጥቀህ ለኛ ስጠን” የሚል ነው።
ስለዚህ ሁሉንም ማስተናገድ አይቻልም። የአንዱን ጥያቄ አስተናግዶ የሌሎችን በቸልታ መተውም ሆነ ውድቅ ማድረግም አያዋጣም። ቅሬታዎች ይበራከታሉ። ምንም መከራከሪያ አይኖረውም። ሁሉንም ቅሬታ በጉልበት ዝም ማሰኘት ደግሞ አይቻልም። የመንግስትም ሆነ የአገሪቱ ህልውና ለአደጋ ይጋለጣል። ነፃ ገበያን ከማብጠልጠል መቆጠብ የህልውና ጉዳይ ነው። “እኛ የህዳሴ ግንባር ቀደም መሪና የአገሪቱ ብቸኛ አለኝታ ነን፤ ስለዚህ ያሰኘንን እንሰራለን፤ አርፋችሁ ተገዙ” ብሎ ያለ ተፎካካሪ ስልጣን ይዞ በጉልበት ለመግዛት እየተመኘ፤ የነአሜሪካ አይነት የምርጫ ስርዓትን በግላጭ ሲያንቋሸሽስ? በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የምርጫ ዲሞክራሲን በአደባባይ ቢያጣጥልስ? ይሄም ጣጣው ብዙ ነው። በጉልበትና በጠመንጃ ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ ቡድኖችን የሚያወግዝበት ምክንያት ያጣል። ላውግዝ ቢልም፣ ሰሚ አያገኝም። እነሱምኮ እንደሱ “እኛ የእገሌ ብሄር ግንባር ቀደም መሪ ነን፤ የአንድነት ተቆርቋሪ የቁርጥ ቀን ልጅ ነን! የአምልኮ ጠበቃ የሃይማኖት ቀናኢ ተዋጊዎች ነን! ያሰኘንን እንሰራለን፤ አርፋችሁ ተገዙ” የሚሉ ናቸው። ስልጣን መያዝ የሚቻለው በጠመንጃ ሳይሆን በምርጫ ፉክክር ነው ብሎ ዜጎችን ማሳመን አይችልም - ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት የምርጫ ዲሞክራሲን ሲያጣጥል ቆይቷልና። “እኛ የምናምንባቸው የሃይማኖት ትእዛዛት የመንግስት ህግ መሆን አለባቸው፤ እያንዳንዱ አማኝ የሃይማኖቱን ትእዛዛት እንዲያከብር እናደርጋለን፤ እምቢተኞቹን ልክ እናስገባለን” የሚሉ የሃይማኖት አርበኞችን ምን ብሎ መከላከል ይቻላል? “የግለሰብ ነፃነትን አክብሩ” ብሎ ሊከራከር አይችልም - የግለሰብ ነፃነትን በማብጠልጠል፣ ያሰኘንን እንሰራለን የሚል ከሆነ።
በአጠቃላይ የራሱንና የአገሪቱን ህልውና ለአደጋ አጋለጠ ማለት ነው። ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትን የዲሞክራሲ ስርአት ከማንቋሸሽ መቆጠብ የህልውና ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ ለህልውናው ሲል፣ ነፃ ገበያንና የምርጫ ዲሞክራሲን በአደባባይ ላለማብጠልጠል ሲጠነቀቅ ቆይቷል። ነፃ ገበያን የማንቋሸሸ ዘመቻ ካካሄደ፣ ኢትዮጵያ እንደቀድሞው አንድ አገር ሆና የመቆየት እድል እንደማይኖራት ኢህአዴግ የሚገነዘብ ይመስለኛል - ቢያንስ ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይገነዘብ ነበር። ለምሳሌ “ድጎማና ድጋፍ ለአካባቢው ተወላጅ ብቻ! ኢንቨስትመንትና ስራ የሚፈቀደው ለነባር ብቻ! መጤው በዘበዘን፣ ስራ ተሻማን ይውጣልን” የሚሉ መፈክሮች አገሪቱን ወደ ቀውስ እንደሚገፉ ትጠራጠራላችሁ? ኢህአዴግም ይህንን አይክድም። ይህንን የህልውና አደጋ ለመከላከል የሚቻለው፣ የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት በማቅረብ ነው። የዲሞክራሲ ግንባታ ጥያቄ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ አቶ መለስ ያዘጋጁትና በ1994 ዓ.ም የታተመው መፅሃፍ ውስጥ የምናገኘው መከራከሪያም ይሄው ነው። ነፃ ገበያን የማይፈልጉ ሰዎች፣ የብሄር ብሄረሰብ ግጭት ለመፍጠር ይጥራሉ በማለት አደገኛነቱን ይገልፃል መፅሃፉ። ታዲያ ግጭትንና መበታተንን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው? በምን መከራከሪያ? በመፅሃፉ የሰፈረውን ሃሳብ ልጥቀስላችሁ።
“በገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ሸቀጥ ማምረት የማይችሉና የብሄር ታርጋቸውን ለጥፈው በህዝቡ ጫንቃ ላይ ለመክበር የሚፈልጉ ጥገኞች [በነፃ ገበያ ውስጥ በሂደት] እንደሚከስሙ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም… የብሄራቸውን ስም በመጠቀም አጥር አበጅተው በጥገኝነት ለመመዝበር መራወጣቸው አልቀረም፡፡ በህዝቦች መካከል አጥር ማበጀትና ቁርሾ እንዲፈጠር መጣር ከጥገኛ አመለካከታቸው የሚመነጭ ነው፡፡ … ዋናዎቹ የጠባብነትና የትምክህተኝነት አቀንቃኞች፣ በገበያ በነፃ ተወዳድረው መክበር የማይችሉ ጥገኞች… ናቸው” ታዲያ፤ የሶሻሊዝም ፍቅር የተጠናወተው ኢህአዴግ፤ የህልውና ጉዳይ ሆኖበት ነፃ ገበያን ላለማጣጣል መጠንቀቁ ይገርማል? የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ካልያዘ፤ “ሁሉህም በየብሄርህ፣ ሁሉሽም በየትውልድ ቦታሽ” ተብሎ አገር ስትታመስ ምንም መፍትሄ አይኖረውም። የህልውና ጉዳይ ሆኖበት የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ካቀረበ ደግሞ፣ የምዕራብ አገራትን በአርአያነት መጥቀሱ የግድ ነው። የአቶ መለስን መፅሃፍ በድጋሚ ልጥቀስላችሁ። “አንዳንድ ሰዎች፣ በአንድ አካባቢ አስር ወይም መቶ ልማታዊ ባለሀብቶች በሚሰማሩበት ጊዜ፣ ለሌሎች ባለሃብቶች ዕድሉ የተዘጋና ቦታው የተያዘ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ የነፃ ገበያን ባህሪ በሚገባ ባለመገንዘብ የሚመጣ ችግር ነው፡፡
በአለም ውስጥ፣ እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላት፣ ከሚልዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያላቸው በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ባለሃብቶች የተነባበሩባት አገር አሜሪካ ነች፡፡ ይህም ሆኖ ከመላው አለም የውጭ ባለሃብት ወደ አሜሪካ በሰፊው ይጎርፋል፡፡ …በአጋጣሚ የሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡ የግል ባለሃብቶች ልማታዊ እንቅስቃሴ በሚበራከትበትና.. በገበያ ውድድር በሚመራበት ወቅት፣ ለሌሎች ባለሃብቶች ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድል ይከፍታል፡፡ … አሜሪካኖች በላይ በላዩ የግል ባለሃብት ተከማችቶ፣ የስራ ዕድል መጣበብ ሳይሆን ቀጣይ የልማት ዕድልን ነው ያገኙት፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አንድ ተሰርቶ ያለቀለትን ዳቦ እንደመጋራት መወሰድ የለበትም፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በስራ ላይ በሚሰማራ ልማታዊ ባለሀብት የነበረውን ዳቦ የሚጋራ ሳይሆን አዲስ ሃብት የሚፈጥር ነው፡፡
ሊፈጠር የሚችለው ሃብት ገደብ ያለው አይደለም፡፡ …በአንድ አካባቢ ልማታዊ ባለሃብቶች በሰፊው ሲሰማሩ፣ ለአካባቢው ልማታዊ ባለሀብቶች መጠናከር ዕድል ከመፍጠር በስተቀር በባለ ሃብቶቹ ላይ የሚያስከትለው ምንም ጉዳት የለም፡፡ በየአካባቢው ልማታዊ የግል ባለሃብቶች ብሄራቸው ምንም ይሁን ምን በሰፊው እንዲሰማሩ… [የነፃ ገበያ መርህ] በጥብቅ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል” ኢህአዴግ የሶሻሊዝም ፍቅር ባይለቀውም፤ ነፃ ገበያንና የእነ አሜሪካን ዲሞክራሲ በግላጭ ከማጣጣል ተቆጥቦ የቆየው፤ ካፒታሊዝም የህልውና ጉዳይ እንደሆነ በተወሰነ ደረጃ በመገንዘቡ ነው ብዬ አምናለሁ። የአቶ መለስ ፅሁፎችም ይህንን ይመሰክራሉ።
ታዲያ፣ አሁን ለአቶ መለስ መታሰቢያ ተብሎ የተዘጋጀው የኢህአዴግ መፅሄት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ነፃ ገበያንና እነ አሜሪካን በተደጋጋሚ በግላጭ ማብጠልጠሉ ለምን ይሆን? ኢህአዴግ፤ ነፃ ገበያና “ዲሞክራሲ” የምር የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን ዘንግቶ ከሆነ፤ ተሞኝቷል። የተሟላ ትክክለኛ አስተሳሰብና ፅኑ አቋም ለመያዝ ባይበቃ እንኳ፣ በተግባር ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን በጥራትና በፍጥነት ለማስፋፋት ፍላጎቱ ባይኖረው እንኳ፤ ቢያንስ ቢያንስ የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን መርሳት የለበትም። ከተንሸራተቱ በኋላ ጣጣው ብዙ ነው።