Administrator

Administrator

“ግንባታው ህገ-ወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል” የወረዳ 11 ፍ/ፅ/ቤት

                    በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 11 ውስጥ ጥቁር ድንጋይ ለማምረት የ7 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተው በስራ ላይ የሚገኙት የደረጀ በለጠ የጥቁር ድንጋይና ገረጋንቲ ማምረቻ ድርጅት ባለቤት አቶ ደረጀ በለጠ ለድርጅታቸው እቃ ማከማቻ ፈቃድ ወስደው የገነቡት የሁለት ሚሊዮን ብር መጋዘን ያለአግባብ ፈርሶብኛል ሲሉ አማረሩ፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ፍትህ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ግንባታው ህገወጥ በመሆኑ ሊፈርስ ችሏል በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ በዓመት እስከ 1 ሚሊዮን ብር ግብር ከፋይ እንደሆኑ የተናገሩት የድርጅቱ ባለቤት፤ በ70ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታቸው ላይ ለሚያካሂዱት የጥቁር ድንጋይ ማምረት ሥራ ከስራው ጋር ተያያዥነት ያለውና እስከ ድርጅቱ የስራ ዘመን ማብቂያ የሚቆይ ጊዜያዊ ግንባታ አካሂደው እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በ29/06/2004 ዓ.ም የሰጣቸውን የፈቃድ ደብዳቤ አቶ ደረጀ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡

ድርጅታቸው ከ80 በላይ ሠራተኞችን ቀጥሮ እንደሚያስተዳድር የተናገሩት ባለሀብቱ፤ አንድም ከህግ ውጭ እንዳልተንቀሳቀሱ ገልፀው፣ አፍርስ ሲባሉ ወደ ህግ በማምራት ከፍ/ቤት የእግድ ትዕዛዝ ማውጣታቸውን ተናግረው፣ ከእግዱ በኋላ በፍ/ቤት ከወረዳው ጋር ክርክር መያዛቸውን ገልፀዋል፡፡ “በክርክሩ ወቅት ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ፍ/ቤት ቀርበን ለውሳኔ ግንቦት 21 ተቀጠርን” ያሉት አቶ ደረጀ፤ የፍ/ቤቱ ቀጠሮ ከመድረሱ አንድ ወር በፊት (ሚያዚያ 21 ቀን) ከሳሽና ተከሳሽ በሌሉበት ፍ/ቤቱ እግዱን አንስቷል፣ እንዲፈርስም አዟል በሚል ለውሳኔ በተቀጠረበት ግንቦት 21 ቀን መጥተው መጋዘኑን እና በውስጡ ያለውን ንብረት ያለማስጠንቀቂያ በግሬደር እንዳፈረሱባቸው በምሬት ገልፀዋል፡፡ በቦታው ተገኝተን ለመታዘብ እንደቻልነው መጋዘኑ ከነተሰራበት አይጋ ቆርቆሮ፣ ብሎኬትና ብረታ ብረት ፈርሷል፡፡ “ይግባኝ እንኳን እንዳልጠይቅ እኔ በማላውቀው መንገድ ፍ/ቤቱ ውሳኔ ሰጥቶ አንድ ወር ሙሉ የውሳኔ ቀጠሮውን እየጠበቅሁ እንድቆይ አድርጐኛል፡፡ በዚህም ሞራሌ ተነክቶና በዜግነቴ ላይ ጥርጣሬ አድሮብኛል” ብለዋል አቶ ደረጀ፡፡

የአቶ ደረጀ ጠበቃ አቶ ደሶ ጨመደ በበኩላቸው፤ ፍ/ቤቱ ግንቦት 21 ቀን ለውሳኔ ቀጠሮ ተሰጥቶ አጀንዳቸው ላይ መመዝገባቸውን ገልፀው፣ ፋይሉን ከቀጠሮው ወር በፊት ማን እንዳንቀሳቀሰው ሳናውቅ ሚያዚያ 21 ቀን ውሳኔ መስጠቱ ግራ አጋብቶናል” ብለዋል፡፡ በቦሌ ክ/ከተማ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ወ/ሮ ኤልሳቤት መንግስቱ፤ ባለሀብቱ በስራ ላይ እንዳሉ፣ በገነቡት መጋዘን ክርክር ላይ እንደነበሩ እና በፍ/ቤት እግድ ማውጣታቸውን እንደሚያውቁ ተናግረው፣ የፍርድ ሂደቱ በወረዳው ፍ/ጽ/ቤት የሚካሄድ በመሆኑ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀውልናል፡፡ “መጋዘኑን አውቀዋለሁ የፈረሰው ህገ-ወጥ ነው ተብሎ ነው” ያሉት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ በ2004 ዓ.ም ወረዳው ህገወጥ የሆኑ ግንባታዎችን ማፍረሱንና የአቶ ደረጀ መጋዘንም ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንዲፈርስ ታዞ እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በወረዳው የፍትህ ጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት ወይዘሪት አንቀፀ ዮሐንስ በበኩላቸው፤ አቶ ደረጀ ከአካባቢ ጥበቃ ባስልጣን የጥቁር ድንጋይ ማምረት ፈቃድ አውጥተው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀው፤ ወረዳ 11 ውስጥ ያለው ቦታ ሙሉ በሙሉ ሰነድ አልባ መሆኑንና ማንኛውም ግለሰብ ግንባታ ሲያካሂድ ወረዳው የግንባታ ፈቃድ መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ አቶ ደረጀ ከወረዳው ፈቃድ ሳይወስዱ በመገንባታቸው መጋዘኑ ሊፈርስ እንደቻለም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ከአካባቢ ጥበቃ ቀጥታ ለወረዳ 11 የተፃፈውን የፈቃድ ደብዳቤ አስመልክተን ላነሳነው ጥያቄ ሃላፊዋ ሲመልሱ፤ አካባቢ ጥበቃ ፈቃድ ሲሰጥ መነሻው ወረዳው ሊሆን እንደሚገባ የገለፁት ወ/ሪት አንቀፀ፤ አካባቢ ጥበቃ የፈቃድ ደብዳቤ ቢጽፍላቸውም የገነቡት ግን የወረዳውን ይሁንታ ሳያገኙ በመሆኑ፣ በፍ/ቤት ክርክሩም ሚያዚያ 21 ቀን ፍ/ቤቱ እግዱ እንዲነሳና መጋዘኑ እንዲፈርስ በመወሰኑ ሊፈርስ እንደቻለ አስረድተዋል፡፡ ለግንቦት 21 የውሳኔ ቀጠሮ ተይዞ እንዴት በአንድ ወር ቀድሞ ውሳኔ እንዳገኘ ተጠይቀው፤ ይሄ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ ነገረፈጆችን እንጂ እኔን አይመለከትም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የቦሌ ክ/ከተማ ፍትህ ቢሮ የፍ/ቤቱን ነገረ ፈጅ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ግን አልተሳካም፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ 1% የሚሆኑት እርግዝናዎች ከማህጸን ውጭ ሊፈጠሩ የሚችሉ እርግዝናዎች ናቸው፡፡ እርግዝናው ከዘር ማስተላለፊያ ቱቦ በተጨማሪ የሆድ እቃ ውስጥ ጭምር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን 1% ከሚሆኑት ከማህጸን ውጭ እርግዝናዎች 98% ያህሉ የሚቆዩት እዚያው የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ውስጥ ነው፡፡ ከማህጸን ውጭ የሚከሰት እርግዝና የሚያጋጥማቸው ሴቶች በእድሜ ከ35 -49 አመት“” ድረስ ያሉ ናቸው፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝናን አመላካች የሚሆኑ የህመም አይነቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌም ... የታችኛው የሆድ ክፍል ላይ ከበድ ያለ ህመም መሰማት፣ ሽንትን በመሽናት ጊዜ የህመም ስሜት፣ የማህጸን በር መድማትና ...ሌሎችም ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሰውን ርእሰ ጉዳይ በሚመለከት አንዲት ጉዳት የገጠማት ሴት እንዲህ ትላለች፡፡ “”...እኔ በእድሜዬ ወደ ሰላሳ ስድስት አመት እጠጋለሁ፡፡ እኔ በልጅነ ወለድ ወለድ አድርጌ የሶስት ልጆች እናት ነኝ፡፡

ከዚህም በሁዋላ ልጅ መውለድ አልችልም ...አልፈልግም ብዬ ባለቤንም አሳምኜ በመኖር ላይ ነበርኩ፡፡ ታድያ አንድ ቀን አመሻሹ ላይ እንዲያው ድካም ድካም ይሰማኝ ጀመር፡፡ ወደ ሶስት ሰአት ከምሽቱ ሲሆን ዝም ብዬ ወደ አልጋዬ ሄድኩኝ፡፡ ከተወሰነ መኝታ በሁዋላ ...የሆነ... ስሜት ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ፡፡ ወዲያው ቀና ስል ሰውነ በደም ተጨ ማልቆአል፡፡ በድንጋጤ ስጮህ ባለቤ ተነስቶ እፍስፍስ አድርጎ ወደሆስፒታል ወሰደኝ፡፡ እኔ ለጊዜው እራሴን አላውቅም ነበር፡፡ ድንጋጤውና የህመሙ ስሜት ተደማምሮ እራሴን እንደመሳት ብዬ ነበር፡፡ በሁዋላም አስፈላጊው ሕክምና ተደ ርጎልኝ ሲሻለኝ የሆንኩትን ነገር ጠየቅሁ፡፡ ለካንስ ከማህጸን ውጪ እርግዝና የሚባል ነገር ነው፡፡ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ሐኪሞቹም ከዚህ በላይም ለጉዳት ትጋለጪ ነበር የሚል ነበር መልሳቸው...” ስሜን አትግለጹ ከማህጸን ውጭ እርግዝና በሚለው ጉዳይ መልስ እንዲሰጡ ለዚህ እትም የተጋበዙት ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እና በብራስ የእናቶችና የህጻናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር መብራቱ ማብራሪያ ይህ የጤና እክል በተለምዶ ከማህጸን በላይ እርግዝና ቢባልም ትክክለኛ ስያሜው ግን ከማህጸን ውጭ እርግዝና በእንግሊዝኛው (Ectopic pregnancy) ይባላል፡፡ ከማህጸን ውጭ እርግዝና ቃሉም እንደሚያስረዳው እርግዝናው በትክክለኛው ተፈጥሮ አዊ ቦታው ማለትም በማህጸን ውስጥ ሳይሆን ከማህጸኑ ውጭ ባሉ አካላት ላይ እንዲሁም በሆድ እቃ ላይ የሚፈጠርበት አጋጣሚ ይከሰታል፡፡ ይህ እርግዝና ብዙ ጊዜ ዘለቄታ የለውም፡፡ እንደሚታወቀው እርግዝና የሚፈጠረው በወንዱ ዘርና በሴቷ ዘር ግንኙነት መንስኤነት ነው፡፡ ይህ በጤናማ መልኩ የተፈጠረ ከሆነ የሚገኘው በዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ላይ ነው፡፡ በዚያም የተወሰነ ቀን ካሳለፈ በሁዋላ የተወሰነ የሰውነት ገንቢ ሕዋሳቶች ደረጃ ላይ ሲደርስ ወደ ዋናው የማህጸን ክፍል ውስጥ ይገባል፡፡ በማህጸን ውስጥም እርግዝናው እስኪጨርስ እና አድ ጎም ለመወለድ እስኪደርስ ድረስ ይቆያል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ይህ ሂደት ሊዛባ ይችላል፡፡

በዚህም ሳቢያ ጽንሱ ወደ ማህጸን ከመሄዱ ይልቅ የተለያየ ቦታ በመቅረት ባለበት ቦታ እድገቱን ይጀምራል፡፡ በተለይም በዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ጫፍ ወይንም መሃል አለበለዚያም ወደ ማህጸን ተጠግቶ ሊያድግ ይችላል፡፡ ከዚህም ውጭ ጽንሱ እንደተፈጠረ ዝም ብሎ ሆድ እቃ ውስጥ በመውደቅ ሞራ ላይ ወይንም አንጀት ላይ እና በመሳሰሉት አካላት በመጠጋት በዚያው እድገቱን ሊጀምርም ይችላል፡፡ ዶ/ር መብራቱ በተጨማሪም እንዳብራሩት የወንድ እና የሴት የዘር ፍሬ ከተገናኙ በሁዋላ ወደትክክለኛው ማህጸን ከመግባት ይልቅ ወደተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ለማምራቱ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከዚህም ዋነኛው የዘር ማስተላለፊያው ቱቦ ክፍት መሆኑ ነው፡፡ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ከእንቁላሉ ተጠግቶ ያለ ሲሆን ወደ እንቁላሉ በመሄድ እንቁላሉን ይቀልባል፡፡ በመሀከላቸው ባለው ክፍተት አማካኝነትም እንቁላሉ ከቦታው በሚወጣ በት ጊዜ ተቀብሎም ወደ ዋናው ማህጸን ያመጣዋል፡፡ ይህንን በምሳሌ ለመረዳትም አሉ ዶ/ር መብራቱ ...የዘር ማሰተላለፊያው ቱቦ የሚሰራውን ስራ ከጉሮሮ ጋር ማነጻጸር ይቻላል፡፡

ጉሮሮ ምግብን ተቀብሎ ወደ ሆድ እቃ እንደሚያስተላልፈው ሁሉ የዘር ማስተላለፊያው ቱቦም ወደ ማህጸን በማምጣት ላይ ባለበት ጊዜ የወንድ የዘር ፈሳሽ ደግሞ ከብልት ወደ ውስጥ ሲፈስ መስመር ላይ የወንዱና የሴት የዘር ፍሬዎች እንዲገናኙ ምክንያት ይሆናል፡፡ ከተወሰነ ደረጃ በሁዋላም ወደዋናው ማህጸን በመግባት ፋንታ እዚያው ዘር ማስተላለፊያ ቱቦው ላይ ተጣብቆ የመቅረት ወይንም ወደ ሆድ እቃ የመግባት የመሳሰሉት ችግሮች ሲደርሱ ይስተዋላሉ፡፡ ይህንን ችግር ከሚያስከትሉት መካከል ፡- የማህጸን ቁስለት ኢንፌክሽን፣ የዘር ማስተላለፊያ ቱቦ ተፈጥሮአዊ እውክታ ..ወዘተ ይገኙበታል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉ አጋጣሚዎች ዘር ከተፈጠረ በሁዋላ ወደትክክለኛው ቦታ ለመም ጣት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን አያገኝም፡፡ በተለይም እያደገ በመጣ ቁጥር መጠ ኑም እየጨመረ ስለሚመጣ እንደልብ ለመንቀሳቀስ ስለሚቸገር እዚያው እነበረበት ቦታ ይቀጥ ላል፡፡ ጽንስ ሲፈጠር አብረው የሚፈጠሩ ነገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌም እንግዴ ልጅ ፣የሽርት ውሀ እና የመሳሰሉት ነገሮች በማህጸን ውስጥ የጽንሱ አካል በመሆን ጊዜው እስኪያበቃ ድረስ እድ ገቱን እየተቆጣጠሩ ምግብ እየመገቡ አየር እንዲኖረው አስችለው በስተመጨረሻው ልጁ ይወለ ዳል፡፡

ከማህጸን ውጪ እርግዝና በሚሆንበትም ጊዜ ጊዜው ወይንም እድገቱ እስከፈቀደ ድረስ ምንም ባልተጉዋደለ መልኩ ሁሉም ነገሮች በየደረጃቸው አብረው ይፈጠራሉ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ግን እንዳለበት ቦታ ይወሰናል፡፡ ዘር ከተፈጠረ በሁዋላ በዘር ቱቦው ውስጥ በመጀመሪያው በመሀ ሉና በስተመጨረሻው ባለው ቦታ እንደየጥበት እና ስፋታቸው የመለጠጥ አቅማቸው እንደፈቀደ እድገቱን ይዘው ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ጥበቱ እየተባባሰ በሚሄድበት ጊዜ ቱቦው ስለሚፈነዳ ደም በሴትየዋ ሆድእቃ ውስጥ ይፈሳል፡፡ ያን ጊዜ ሴትየዋ ችግር ላይ ትወድቃለች፡፡ በኢትዮጵያ በህብረተሰቡ ዘንድ አንድ ጥሩ ያልሆነ ልምድ አለ፡፡ አንዲት ሴት እርጉዝ ነኝ ብላ ቤተሰብዋን ወይንም ጉዋደኞቿን ስታማክር ሶስት ወር ሳይሞላት ወደሐኪም ቤት ሄዳ ምርመራ እንዳትጀምር የሚያደርጉ ምክሮች ይሰጡዋታል፡፡ ነገር ግን ይህ በፍጹም ትክክል እንዳልሆነ ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል፡፡

አንዲት ሴት እንዲያውም ወደሐኪም ቤት ሄዳ ምክር መጠየቅ እና ምርመራ ማድረግ ያለባት ከእርግዝና አስቀድሞ ሲሆን የወር አበባ ከቀረበት ጊዜ ጀምሮ ግን ወደሀኪም መቅረብ ግዴታ መሆን አለበት፡፡ አስቀድሞ ምርመራ ከተጀመረ እርግዝናው በትክክለ ኛው ሁኔታ ይሁን አይሁን በአልትራሳውንድ ጭምር በማየት ማወቅ የሚቻልበት የህክምና ዘዴ አለ፡፡ ስለዚህ ማንኛዋም ሴት ችግር ላይ ከመውደቅዋ አስቀድሞ እርምጃ ለመውሰድ ቀላል ይሆናል፡፡ ከማህጸን ውጪ እርግዝና ከሁለት እስከሶስት ወር ድረስ አደጋው ይከሰታል፡፡ አልፎ አልፎ ግን በሆድ እቃ ውስጥ የተረገዘው ጽንስ በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ እስኪወለድ ድረስ ማደግ መቻሉን መረጃዎች ይጠቁማሉ ብለዋል ዶ/ር መብራቱ ጀምበር ፡፡ ይቀጥላል

የኢትዮጵያው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአፍሪካ ስምንት ምርጥ ክለቦች ተርታ የገባበት ብቃት አስደነቀ። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሰው መልእክት የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ማጣሪያ ያለፈ የመጀመርያ ክለብ በመሆኑ ለሀገራችን እግር ኳስ እድገት ተምሳሌት መሆኑን አረጋግጧል በማለት ብሏል፡፡ ዘንድሮ በአፍሪካ ሁለት የክለብ ውድደሮች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌዴሬሽን ካፕ አስደናቂ ተሳትፎ ያደረገው ክለቡ ስምንት ጨዋታዎች አድርጎ አራቱን ሲያሸንፍ በ3 አቻ ተለያይቶ እና 1 ጨዋታ ብቻ የተሸነፈ ሲሆን 17 ግብ ተጋጣሚዎቹ ላይ ሲያስቆጠር፤ሰባት ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውበታል፡፡ የውድድር ዘመኑን በአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ በመሳተፍ የጀመረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውድድሩ ቅድመ ማጣርያ የተገናኘው ከዛንዚባሪ ጃምሁሪ ጋር የነበረ ሲሆን በሜዳው 3ለ0 ከዚያም ከሜዳው ውጭ 5ለ0 በማሸነፍ ብድምር ውጤት 8ለ0 አሸንፎ ወደ የመጀመርያው ዙር ማጣርያ ገብቷል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመርያ ዙር ያገኘው ክለብ የማሊው ዲጆሊባ ነበር፡፡

በሜዳው 2ለ0 አሸንፎ ከሜዳው ውጭ አንድ እኩል አቻ በመለያየት በድምር ውጤት ዲጆሊባን 3ለ1 በመርታት ወደ ሁለተኛው ዙር ገብቷል፡፡ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከግብፁ ክለብ ዛማሌክ ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ 1ለ1 አቻ ቢለያይም በሜዳው 2ለ2 አቻ በመለያየቱ በድምር ውጤት 3ለ3 ቢሆንም የግብፁ ክለብ ዛማሌክ ከሜዳው ውጭ ባገባቸው ጎሎች በልጦት ወደ ሻምፒዮንስ ሊጉ የምድብ ድልድል የሚገባበት እድል አምልጦት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሻምፒዮንስ ሊጉ ከተሰናበተ በኋላ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጥሎ ማለፍ የሚሳተፍበትን እድል አግኝቶ ከሌላው የግብፅ ክለብ ኤን.ፒ.ፒ.አይ ጋር ተገናኘ።

በሜዳው ኢኤንፒፒአይን 2ለ0 በማሸነፍ ለመልስ ጨዋታ ወደ ካይሮ በመጓዝ 3ለ1 ከተረታ በኋላ የደርሶ መልስ ውጤቱ 3ለ3 ቢሆንም ከሜዳው ውጭ ባስቆጠረ በሚለው ደንብ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኮንፌደሬሽን ካፕ የምድብ ድልድል በመግባት ታሪክ ሰርቷል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍ ፈርቀዳጅ የነበረ ክለብ ነው፡፡ የመድን እግር ኳስ ክለብ በኮንፌደሬሽን ካፕ ከኢትዮጵያ ክለቦች አምስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜ መድረስ የቻለበትን ክብረወሰን ዘንድሮ የተጋራው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለምድብ ድልድል የደረሰ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ክለብ በመሆን በፈርቀዳጅነት ቀጥሏል፡፡ የ2013 ኮንፌደሬሽን ካፕ በምድብ ጨዋታዎች ከ6 ሳምንት በኋላ ሲጀምር በምድብ 1 ከአንድ የሰሜን አፍሪካ እና ከሁለት የምዕራብ አፍሪካ ክለቦች ጋር የተገናኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ለዋንጫ ጨዋታ ሊደርስ እንደሚችል ግምት ወስዷል፡፡ በኮንፌደሬሽን ካፑ የምድብ ድልድል በምድብ 1 የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ፤ የማሊው ስታድ ደማሌይን፤ የናይጄርያው ኢኑጉ ሬንጀርስ እና የቱኒዚያ ኤትዋል ደሳህል ሲገኙ፤ በምድብ 2 የዲ ሪ ኮንጎው ቲፒ ማዜምቤ፤ የቱኒዚያው ሲኤ ቤዛርቲን፤ የአልጄርያው ኢኤስ ሴቲፍ እና የሞሮኮው ኢፍሲ ራባት ተደልድለዋል፡፡ በምድብ ድልድሉ በመግባት ለዋንጫው ጨዋታ መድረስ እና በየምድቡ በሚገኝ የደረጃ ውጤት መሰረት ለእግር ኳስ ክለቦቹ ብቻ ሳይሆን ለወከሉት አገር የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽንም የገንዘብ ሽልማት ይከፋፈላል፡፡

ከሁለቱ ምድቦች መሪ ሆነው የሚጨርሱት ለኮንፈደሬሽን ካፑ ዋንጫ ሲጫወቱ አሸናፊው ክለብ 625ሺ ዶላር ሲያገኝ የወከለው ፌደሬሽን 35ሺ ዶላር እንዲሁም 2ኛ ደረጃ ያገኘው ክለብ 432ሺ ዶላር ሲታሰብለት የወከለው ፈደሬሽን ደግሞ 30ሺ ዶላር ይሰጠዋል፡፡ በኮንፌደሬሽ ካፑ የምድብ ድልድል በየምድባቸው 2ኛ ደረጃ የሚያገኙት 239ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 25ሺ ዶላር፤3ኛ ደረጃ የሚያገኙት 239ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 20ሺ ዶላር እንዲሁም 4ኛ ደረጃ የሚያገኙት 150ሺ ዶላር ለወከሉት ፌዴሬሽን 15ሺ ዶላር እንደሚበረከትም ታውቋል፡፡

ለሩሲያዊው ባለቅኔ አሌክሳንደር ፔትሮቪች ፑሽኪን፣ ሦስት ቶን ክብደት ያለው ግዙፍ የነሐስ ሐውልት በአዲስ አበባ ሣር ቤት አካባቢ በሚገኘው “ፑሽኪን አደባባይ” ሊቆምለት እንደሆነ የሩሲያ የሳይንስ እና ባህል ማእከል አስታወቀ፡፡ ማእከሉ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፣ የነሐስ ሐውልቱ በአፍሪካ አህጉር በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ሲሆን በታዋቂው ሩስያዊ ቀራፂ ዲሚትሪ ኩኮለስ ተቀርፆ በሞስኮ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉልን ነው ያሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር፣ የፑሽኪንን ኢትዮጵያዊ ቅድመ አያት አብርሃም ጋኒባልን ያካተተው ሃውልት፣ በጣም ያጌጠና የውጭ ጐብኝዎችን ጭምር የሚስብ እንደሆነ ገልፀውልናል፡፡ የፑሽኪን ልደት በዚህ ሳምንት በሩስያ፣ በኢትዮጵያ እና በተቀረውም ዓለም እየተከበረ ነው፡፡

ከተመሠረተ 53ኛ ዓመቱን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ለመጀመሪያ ጊዜ “የጥበብ እልፍኝ” የተሰኘ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ባለፈው ማክሰኞ ጀመረ፡፡ በየሳምንቱ ማክሰኞ በኤፍኤም አዲስ 97.1 የሚቀርበው ዝግጅት፣የሁለት ሰዓት የአየር ቆይታ ይኖረዋል፡፡ የአየር ሰዓት በመስጠት የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ኢሬቴድ) ቀና ትብብር እንዳደረገላቸው የገለፁት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረክርስቶስ ኃይለሥላሴ፣ ዝግጅቱ መጀመሩ ድርሰትን ፀሐፍትንና መፃሕፍትን ይበልጥ ለሕዝብ በማስተዋወቅ የንባብ ባህልን ያደረጃል ብለዋል፡፡ በአባላት መዋጮ የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር፣ ወደፊት ከማስታወቂያ ተጠቃሚ በመሆን ራሱን በገቢ እንደሚደጉም ኃላፊው ገልፀዋል፡፡

Wednesday, 12 June 2013 14:09

ግጥም በጃዝ 23ኛ ያቀርባል

በወጣት ገጣሚያን እየተሰናዳ የሚቀርበው “ግጥም በጃዝ” 23ኛ ወርሃዊ ዝግጅቱን እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ በመጪው ረቡዕ ማምሻውን 11፡30 ጀምሮ በራስ ሆቴል በሚቀርበው ዝግጅት ላይ ግሩም ዘነበ፣ በረከት በላይነህ፣ ሜሮን ጌትነት፣ መንግስቱ ዘገየ፣ ዮሐንስ ሐብተማርያም በግጥም፤ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ብርሃነ ደሬሳ “የአፍሪካ የነፃነትና አንድነት ትግል” በሚል ርእስ ዲስኩር እንዲሁም ሀብታሙ ስዩም ወግ ያቀርባሉ፡፡

ፒያሳ አካባቢ የሚገኘው “ኤልቤት ሆቴል” ወርሃዊ የኪነጥበብ ዝግጅት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡ የዛሬ ሳምንት በሆቴሉ የሚጀመረው ዝግጅት ግጥም ላይ የሚያተኩር ነው ብሏል - ሆቴሉ፡፡ መድረክ ያላገኙ እና የራሳቸውን ግጥም የሚያቀርቡ ከሕፃናት እስከ አረጋውያን ሥራዎች ላይ እናተኩራለን ያሉት የሆቴሉ ሥራ አስኪያጅ፣ አንጋፋ ገጣሚያንም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በሀዲስ አለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” መጽሐፍ ውስጥ ያሉ ግጥሞች በመክፈቻው እለት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በዓለም ዙርያ በ60 አገራት መታየት የጀመረው የዊል ስሚዝ ፊልም‹አፍተር አርዝ› ገበያው እንዳልተሳካለት ተገለፀ፡፡ የፊልሙን አከፋፋይ ሶኒ ኩባንያ ለተፈጠረው የገበያ መዳከም ከዊል ስሚዝ ብቃት ይልቅ ዘንድሮ እየወጡ ያሉ ፊልሞች በገበያው የሚያሳዩት ከፍተኛ ፉክክር እንደሆነ ገልጿል፡፡‹ አፍተር አርዝ› በመጀመርያ ሳምንቱ ያስገባው 34.6 ሚሊዮን ዶላር በዊል ስሚዝ የሚሰሩ ፊልሞች አማካይ የመጀመርያ ሳምንት ገቢ በእጥፍ ያነሰ ነው፡፡ አምና ለእይታ የበቃው ‹ሜን ኢን ብላክ 3› እንዲሁም በ2008 እኤአ የታየው ‹ሃንኮክ› በመጀመርያ ሳምንታቸው 54.6 ሚሊዮን ዶላር እና 62.6 ሚሊዮን ዶላር እንደቅደምተከተላቸው አስገብተው ነበር፡፡

ከአዲሱ ፊልሙ የገበያ መቀዛቀዝ በኋላ ዊል ስሚዝ ለዲጂታል ስፓይ በሰጠው አስተያየት የደለበ ገቢ በሚያስገኙ ፊልሞች የመስራት ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል፡፡ ከዚሁ የዊል ስሚዝ አስተያየት በኋላ በከፍተኛ በጀት በመሰራት ጠቀም ያለ ገቢ የሚኖራቸው አይሮቦት 2፤ ሃንኮክ 2 እና ባድቦይስ 3 የተባሉት የቀድሞ ፊልሞቹ መሰራት አጠያያቂ ሆኗል፡፡ በ130 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራውን ‹ አፍተር አርዝ› የ44 ዓመቱ ዊል ስሚዝ ከ14 አመት የበኩር ልጁ ጄደን ስሚዝ ጋር የሰራው ሳይንሳዊ ልቦለድ ፊልም ሲሆን በመጀመርያ ሳምንቱ ያስገባው ገቢ ዘንድሮ ከወጡ ፊልሞች ደካማው ተብሏል፡፡

ዊል ስሚዝ በሚተውንባቸው ፊልሞች የቦክስ ኦፊስ የገበያ ደረጃዎችን በመቆጣጠር፤ ለተከታታይ ክፍል ስራዎች ምክንያት በመሆን የሚታወቀውና የ100 ሚሊዮን ዶላር ተዋናይ ይባል ነበር፡፡ ከአፍተር አርዝ በፊት ዊል ስሚዝ የተወነባቸው ያለፉት 10 ፊልሞች በአማካይ በመላው ዓለም እያንዳንዳቸው 150 ሚሊዮን ዶላር ያስገቡ ነበሩ፡፡ ዊል ስሚዝ በትወና ዘመኑ ከ20 በላይ ፊልሞች ሰርቶ ከ6.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመላው ዓለም በማስገባት የተሳካለት ነበር፡፡

ጄራርድ ዴፓርዲዮ በፈረንሳይ መንግስት በተጠየቀው የግብር እዳ በመማረር ፓስፖርቱን በመመለስ ዜግነቱን ለመፋቅ እንዳሰበ “ዘ ሆሊውድ ሪፖርተር” አስታወቀ፡፡ ‹ለስ ሚዝረብልስ› በተባለው ፊልም ዓለም አቀፍ ዝና ያተረፈው ተዋናዩ፤ 1.3 ሚሊዮን ዶላር የግብር እዳ አለበት በሚል የፈረንሳይ መንግስት ክስ መስርቶበታል፡፡ ክሱ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፍራንስዋ ሆላንዴ ድጋፍ ማግኘቱ ተዋናዩን እንዳበሳጨው ታውቋል፡፡ ከትወና ሙያው ባሻገር በፊልም ሰሪነት፤ በነጋዴነት እና በወይን እርሻ ባለቤትነት የሚታወቀው የ64 ዓመቱ ዴፓርዲዮ በሙያ ዘመኑ 17 ፊልሞች ላይ ሰርቷል፡፡

ከፈረንሳይ መንግስት ጋር የገባው እሰጥ አገባ ያማረረው ተዋናዩ፤ ኑሮውን በቤልጂዬም ለማድረግ ወስኗል ተብሏል፡፡ ከተመሰረተበት ክስ ጋር በተያያዘ በፓሪስ ከተማ ያለው 85 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ግዙፍ ቤቱ ሐራጅ ሊወጣበት እንደሚችል ተዘግቧል፡፡ ጄራርድ ጄፓርዲዬ ከሁለት ሳምንት በፊት የሩሲያ መንግስት በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አማካኝነት የራሽያ ዜግነት እንደሰጠው የገለፀው “ዘ ሆሊውድ”፤ በቺቺኒያ ታሪክ ዙርያ በሚሰሩ ሁለት የራሽያ ፊልሞች ላይ እየተወነ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ ተዋናዩ የራሽያ ዜግነቱን ካገኘ በኋላ ከሚያስገባው ገቢ እጅግ ያነሰ ግብር የሚከፍልበት እድል ማግኘቱን እንደገለፀ የዘገበው መፅሄቱ፤ በሞስኮ ከተማ ሬስቶራንት ለመክፈት ማቀዱን ይፋ እንዳደረገም አውስቷል፡፡

የፖፕ ሙዚቃው ንጉስ የነበረው ማይክል ጃክሰን ብቸኛ ሴት ልጅ ፓሪስ ጃክሰን ከሰሞኑ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ አድርጋ በከፍተኛ የህክምና እርዳታ ህይወቷ መትረፉን ሎስአንጀለስ ታይምስ ዘገበ፡፡ የጃክሰን ቤተሰብ ጠበቃ፤ የ14 ዓመቷ ፓሪስ ህክምና ከወሰደች በኋላ እያገገመች ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋታል ተብሎ ለሦስት ቀናት በሥነአዕምሮ ሆስፒታል እንድትቆይ መደረጉን ገልጿል፡፡ ወጣቷ ራሷን ለማጥፋት ሙከራ ያደረገችው ሞቶሪን የተባለ የህመም ማስታገሻ መድሃኒት አብዝታ በመውሰድ ሲሆን በአንድ ሮክ ሙዚቃ ኮንሰርት ላይ እንዳትሳተፍ በቤተሰብ መከልከሏ ራሷን የማጥፋት ሙከራ እንድታደርግ ሰበብ ሆኗታል ተብሏል፡፡ ራሷን የማጥፋት ሙከራ ከማድረጓ ከሰዓታት በፊት በትዊተር ማስታወሻዋ ላይ በህይወቷ ዙርያ ተስፋ መቁረጥ መንገሱን የሚጠቁም አሳዛኝ መልዕክቶችን ፅፋ ነበር፡፡ የ54 ዓመቷ እናቷ ዴቢ ሮው፤ ፓሪስ ራሷን ለማጥፋት ስትሞክር የመጀመርያዋ አለመሆኑን ለ“ኢንተርቴይመንት ቱናይት” ሲናገሩ፤ ባንድ ወቅት የእጇን ደምስሮች በመተልተል ለጥቂት ከሞት ተርፋለች ብለዋል፡፡
የዛሬ አራት ዓመት ማይክል ጃክሰን ከመሞቱ በፊት የመጨረሻዎቹን ትእይንቶች በአጠገቡ ሆና ያሳለፈችው ፓሪስ፤ አባቷን ካጣች በኋላ በከፍተኛ ሃዘን እና የመንፈስ ጭንቀት ስትረበሽ መቆየቷን ቤተሰቧ ይናገራሉ፡፡ ፓሪስ የማይክል ጃክሰን ብቸኛዋ ሴት ልጅ ስትሆን ሁለት ወንድሞች እንዳሏት ይታወቃል፡፡