Administrator

Administrator

 የታዋቂው አፕል ኩባንያ ምርት የሆነው አይፎን ለገበያ መቅረብ የጀመረበትን አስረኛ አመት እያከበረ ሲሆን፣ ባለፉት አስር አመታት ከ1 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ አይነት የአይፎን ስማርት ስልኮችን ለተጠቃሚዎች መሸጣቸው ተነግሯል፡፡ ከአለማችን ፈርቀዳጅ የስማርት ስልኮች አንዱ የሆነው አይፎን ላለፉት አመታት ከፍተኛ ተወዳጅነት ይዞ በስፋት ሲሸጥ መቆየቱን የዘገበው ቴክ ኒውስ፣ አምራቹ ኩባንያ አፕልም ከትርፋማ ኩባንያዎች አንዱ ሆኖ መዝለቁን ገልጧል፡፡
በየሳምንቱ 500 ሚሊዮን ያህል አለማቀፍ ደንበኞች የአፕልን የአፕሊኬሽን ስቶር እንደሚጎበኙ የተነገረ ሲሆን፣ ባለፉት 10 አመታት ከ180 ቢሊዮን በላይ የአፕል አፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ መደረጋቸው ተጠቅሷል፡፡
አፕል በመጪው መስከረም ወር አዲሱን አይፎን 8 ስማርት ስልኩን ለገበያ ያበቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የመሸጫ ዋጋው ከ1 ሺህ ዶላር በላይ ይሆናል መባሉንና ይህም ከአይፎን ስልኮች የመሸጫ ዋጋ ከፍተኛው እንደሚሆን አስረድቷል፡፡

    ታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ ቴስላ እስካሁን ከተሰሩት ሁሉ በዋጋ አነስተኛው የተባለውን የመጀመሪያውን ቴስላ ሞዴል 3 የኤሌክትሪክ መኪና በትናንትናው ዕለት አምርቶ ማውጣቱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ አስታውቀዋል፡፡ ቴስላ ሞዴል 3 ተባለቺው በኤሌክትሪክ ሃየል የምትንቀሳቀሰውና አንድ ጊዜ ቻርጅ በመደረግ እስከ 215 ማይል ርቀት መጓዝ ትችላለች የተባለቺው አምስት ተሳፋሪዎችን የመያዝ አቅም ያላት አዲሷ የኩባንያው መኪና በ35 ሺህ ዶላር ለገበያ እንደቀረበች ሚረር ድረገጽ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው የአሌክትሪክ መኪና ለማምረት የሚያስችለውን ህጋዊ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ከሚጠበቅበት ጊዜ በሁለት ሳምንታት ቀደም ብሎ ማግኘቱን የዘገበው ሚረር ድረገጽ፣ እስከ ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ 32 መኪኖችን፣ እስከ መስከረም ወር ደግሞ 1ሺህ 500 መኪኖችን አምርቶ ለደንበኞቹ ለማስረከብ ስራ መጀመሩን ገልጧል፡፡
ቴስላ ኩባንያ የማምረት አቅሙን በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ እስከሚቀጥለው አመት ታህሳስ ወር ድረስ በወር 20ሺህ መኪኖችን የማምረት አቅም ላይ እንደሚደርስም ተነግሯል፡፡
ኩባንያው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ ከ25 ሺህ በላይ ሞዴል ኤክስ እና 51 ሺህ ያህል ሞዴል ኤስ የተባሉ መኪኖቹን ለደምበኞቹ በመሸጥ 7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

  ቻይና በትልቅነቱ በአለማችን ቀዳሚነቱን ይይዛል የተባለውና በአመት 45 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለውን አዲሱ የቤጂንግ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በደቡባዊ ዳዢንግ አውራጃ እየገነባች ሮይተርስ ዘግቧል፡፡በ700 ሺህ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው ይህ ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ከሁለት አመታት በኋላ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ተጠናቅቆ በአራት የማኮብኮቢያ መንገዶች አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር የጠቆመው ዘገባው፣ በቀጣይም ሌሎች ሁለት ማኮብኮቢያዎች እንደሚጨመሩለትና የማስተናገድ አቅሙ ወደ 100 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል ገልጧል፡፡
በታዋቂው አርክቴክት ዛሃ ሃዲድ ዲዛይን የተደረገው አዲሱ የቤጂንግ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ፣ የመንገደኞችን መስተንግዶ የሚያቀላጥፍና በርካታ አውሮፕላኖችን ያለ አንዳች ችግር የሚያስተናግድ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

 በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰዋ የመን የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ ባለፉት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ1ሺህ 600 በላይ የመናውያንን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ ወረርሽኙ በስፋት በመሰራጨት ሁሉንም የአገሪቱ ግዛቶች ማዳረሱን ያስታወቀው ተመድ፣ ከ270 ሺህ ያህል ዜጎችም የኮሌራ ተጠቂ ሳይሆኑ እንዳልቀሩ መገመቱን ገልጧል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመግታትና
ታማሚዎችን በአግባቡ ለማከም ከአጋር ድርጅቶች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ ያስታወቁት የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋኒ ጃሪክ፣ ባለፈው ማክሰኞ 400 ቶን ያህል የህክምና ቁሳቁስና መድሃኒት ማግኘቱን ጠቁመዋል፡፡ በኮሌራ የተጠቁ የመናውያንን ለማከም በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 600 ያህል ጊዚያዊ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙም አመልክተዋል፡፡

  አሜሪካ ሰሜን ኮርያ በሳምንቱ መጀመሪያ ለፈጸመቺው የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ በሳምንታት ወይም በወራት ጊዜ ውስጥ የከፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ማስጠንቀቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ሙከራ ያደረገቺው ሰሜን ኮርያ እጅግ አደገኛ አካሄድ እየተከተለች ነው፤ ለዚህ ድርጊቷ ጠንከር ያለ ምላሽ ያስፈልጋታል ብለዋል ትራምፕ ከትናንት በስቲያ ዋርሶ ውስጥ በሰጡት መግለጫ፡፡ አለማቀፉ ማህበረሰብ ሰሜን ኮርያ ከዚህ አጥፊ ድርጊቷ እንድትታቀብ ማድረግ ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የሰሜን ኮርያ ሚሳኤል ረጅም ርቀት በመጓዝ የአሜሪካዋን የአላስካ ግዛት የመምታት አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የአሜሪካ አምባሳደር ኒኪ ሃሊ በበኩላቸው የሚሳኤል ሙከራውን ተከትሎ ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በሰጡት መግለጫ አሜሪካ በሰሜን ኮርያ ላይ መጠነኛ ወታደራዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል ማስታወቃቸውን አስታውሷል፡፡ ሰሜን ኮርያ የጸጥታው ምክር ቤት የተጣለባትን ማዕቀብ በሚጥስ መልኩ የሚሳኤል ሙከራውን ማድረጓን ተከትሎ፣ የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ አስቸኳይ ስብሰባ ያደረገ ሲሆን ድርጊቱን በጽኑ አውግዞታል፡፡ ደቡብ ኮርያን እና ፈረንሳይን ጨምሮ የተለያዩ አገራት መንግስታት ድርጊቱን ማውገዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተመድ የፈረንሳይ አምባሳደር በሰሜን ኮርያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል፡፡
ሩስያና ቻይና በበኩላቸው ድርጊቱን ቢኮንኑም፣ እነ አሜሪካ የያዙትን ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ አማራጭ ለሌላ የከፋ ቀውስ የሚዳርግ አደገኛ አካሄድ በሚል እንደማይደግፉት አስታውቀዋል፡፡

 በሀዋሳ፣ የእኛው ለእኛ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላት በበዓላት ወቅት ዶሮም ሆነ በሬ አርደው አረጋውያን አብረዋቸው በልተውና ጠጥተው ተደስተው ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ከእንብራ የማኅበር ሱቅ ዘይት፣ ዱቄት፣ ሳሙና፣… ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ገዝተው ለአረጋውን ይሰጣሉ፡፡ ቤታቸው በላያቸው ላይ የፈረሰባቸውና በዝናብ ወቅት የሚያፈስ ቤት ክፍለ ከተማውን አስፈቅደው፣ ለጥገና አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን የከተማው ባለፀጎች እንዲደግፏቸው ለምነው እነሱው አናጢ፣ እነሱው መራጊ፣ እነሱው ሁሉን ነገር ሆነው ቤታቸውን ይጠግኑላቸዋል፡፡
በየሳምንቱ እሁድ የአረጋውያን ቤት ይፀዳል፣ ልብሳቸው ይታጠባል፡፡ ሴት የማኅበሩ አባላት፤ እሁድ እሁድ ቡና አፍልተው በማጠጣት፣ ፀሐይ ሞቀውና ፈታ ብለው ወደ የቤታቸው እንዲመለሱ ያደርጋሉ፡፡ ልብስ ከከተማው ማኅበረሰብ ሰብስበው (ለምነው) አረጋውያኑን ያለብሷቸዋል፡፡ የተሰበሰበው ልብስ ልካቸው ካልሆነ ተሽጦ በገንዘቡ በልካቸው ልብስ ይገዛላቸዋል፡፡ አንሶላ፣ ትራስ፣ ፍራሽ፣ ብርድልብስ፣… እየገዙ ለአረጋውያኑ እንደሚሰጡ ወጣት አገኘሁ ወርቁ ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት ባለፈው ሳምንት የማኅበረሰብ ምሥርት ተቋማት የመልካም ተሞክሮ ቀን በቢሾፍቱ ከተማ ለ3ኛ ጊዜ ባከበረበት ወቅት ተናግሯል፡፡
በባህርዳርም ከተማም ተመሳሳይ ተሞክሮ እንዳለ፣ ለቀድሞ ባለውለታ አረጋውያን ክብር እየተሰጠ መሆኑን የባህርዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ተስፉ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳኛቸው ከጥምረቱ ውጭ ፋና የሕፃናትና ማኅበረሰብ ልማት ማኅበር አስተባባሪ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ሕፃናትንና አረጋውያንን ለመደገፍ በከተማዋ ብዙ ተግባራት እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እሳቸው የሚመሩት ፋና ማኅበር፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው፣ መሥራት ለማይችሉ፣ አልጋ ላይ ለወደቁ፣ ወጥተው መለመን እንኳ ለማይችሉና ለተረሱ 98 አረጋውያን ክብር በመስጠት ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው  ጠቅሰው፣ በራሳቸው መፀዳዳት የማይችሉትን የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር እንዲያፀዳዷቸውና ቤታቸውን በተራ እንዲያፀዱ፣ አረጋውያን ወደ ውጭ ወጥተው ፀሐይ የሚሞቁበት ተሸከርካሪ ወንበር የተለያዩ ድርጅቶችን በማስተባበር እንዲለግሱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ኢየሩሳሌም የሕፃናት ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት (ኢሕማልድ) የዛሬ 32 ዓመት በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ በነበረው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ለመታደግ የተቋቋመ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ናቸው፡፡
በድርቁ ወቅት ድርጅቱ 6 የሕፃናት ማሳደጊያ ከፍቶ፣ ከ1000 በላይ ሕፃናትን ከተለያዩ አካባቢዎች ሰብስቦ ሲያሳድግ እንደነበረ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ አንድ ሕፃን ኅብረተሰቡ ውስጥ አድጎ የኅብረተሰቡን እሴቶች ማወቅ፣ ፍቅር ሰጥቶ ፍቅር ማግኘት ስላለበት ኅብረተሰብ ተኮር የልማት ሥራ ውስጥ እንደገቡ ገልጸዋል፡፡
እነዚህን የልማት ሥራዎች ድርጅቱ ከዚያ ቢወጣ እንዴት ማስቀጠል ይቻላል? በማለት አንድ ማኅበር መስርተው 7 ዓመት አብረው ሰርተው ቢወጡም ምስርት ማኅበራትንና ዕድሮችን በማጎልበት ድርጅቱ ሲሰራ የነበረውን እነሱ እንዲሠሩ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ኢሕማልድ በአሁኑ ወቅት እያከናውናቸው ያሉት 3 ፕሮግራሞች 1ኛ፡- በማኅበራዊ አገልግሎት በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናትን ከቤተሰብ ጋር እያሉ መደገፍ፣ 2ኛው፡- የኑሮ ማሻሻያና የአካባቢ ጥበቃ፣ 3ኛው፡- የምስርት ተቋማትን አቅም ማጎልበትና ወደ ሥራ ማስገባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ የውጭ እጅ ከማየት ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አገር ውስጥ ያለን ሀብት በመጠቀም፣ ሀብቱ ውጤት እንዲያመጣ እየሠራን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤በዚህ ረገድ አንድ የስብሰባና የማሠልጠኛ ተቋም በቢሾፍቱ ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ማሠራታቸውንና ይህ አሠራር ወደ ምስርት ማኅበራትም እየወረደ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሕንፃናትን በተቋም ከማሳደግ ይልቅ ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ማድረግ ያለውን ሁለንተናዊ አስተዋጽኦ በመገንዘብ በ1996 ዓ.ም ከማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በሙከራ የተጀመረው የልማት ሥራ፤በአሁኑ ወቅት አድጎ በ22 የተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ከ142 ማኅበራትና  ዕድሮች ጋር ዘላቂ የልማት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት የኢሕማልድ የቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ መዓዛ ቅጣው፤ቀደም ሲል አባላትን በማስተዛዘን ሥራ ላይ ብቻ ተጠምደው የነበሩ ዕድሮች የአሰራር ስልታቸውን በመቀየር ሕዝቡ የራሱን ችግር በራሱ ለመፍታት ኅብረተሰብ አቀፍ ልማት ውስጥ መግባታቸው ምርጥ ተሞክሮና ትልቅ እመርታ ነው ብለዋል፡፡
በሐዋሳ ከተማ ከኢሕልማድ ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረተው የእንብራ ራስ አገዝ ማኅበር ወጣት ቡድን አባል የሆነው አገኘሁ ወርቁ፣ አባቱን በሞት የተነጠቀው በኤርትራ ጦርነት ነበር፡፡ ከእሱ ጋር የ3 ልጆች እናት የሆነችው እናቱ፤ምንም የሌላት የቤት እመቤት ነበረች። እቤት ውስጥ ከፍተኛ ችግር ስለነበረባቸው አገኘሁ ወደ ጎዳና ወጣ፡፡ እየለመነና ትንንሽ ዕቃዎች በመሸከም የሚያገኘው መጠነኛ ገቢ፣ ጎዳና ከወጣ በኋላ ለለመደው ሱስ አልበቃ አለው፡፡ ስለዚህ እሱና ጓደኞቹ ጨለማን ተገን አድርገው ሞባይል መቀማትና ኪስ መበርበር ጀመሩ፡፡ በወቅቱ እሱ ከሌሎች ጓደኞቹ ፈርጠም ያለ ስለነበር ሰዎችን አንቆ ሲይዝ፣ ሌሎቹ ኪስ ገብተው ይበረብሩ ነበር፡፡ አሁን የእሱና የጓደኞቹ ሕይወት ተለውጧል፡፡
እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር አቅርቧቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክርና ስልጠና ሰጣቸው፡፡ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶችን አሟልቶላቸው ያቋረጡትን ትምህርት እንዲቀጥሉ አደረገ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ተዘዋዋሪ ብድር በማመቻቸት ከቤት ወጥተው እንዲሰሩ አደረጋቸው፡፡ ፎቶ ኮፒ፣ መጠረዣና ማሸጊያ መሳሪያ ገዝቶ የሥራ ዕድል ፈጠረላቸው፡፡ ከአገኘሁ ጋር ሲቀሙ ከነበሩት ጓደኞቹ አንደኛው አሁን 5ኛ መንጃ ፍቃድ አውጥቶ፣ ወላይታ ሶዶ ውስጥ ሲኖትራክ እያሽከረከረ መሆኑን፣ አገኘሁ ደግሞ ሐዋሳ በሚገኝ አንድ ኮሌጅ የአካውንቲንግና ፋይናንስ 2ኛ ዓመት ተማሪ መሆኑን ገልጾ፣ ሕይወቱ እንዲለወጥ ያደረገውን ኢሕማልድን ከልቡ አመስግኗል፡፡
በማኅበረሰብ ምስርት ተቋማት ምርጥ ተሞክሮ ቀን የተገኙ በርካታ ማኅበራትና ዕድሮች ኢሕማልድ ቢወጣ የራሳቸው ገቢ ማግኛ ፕሮጀክት ስላላቸው ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን አገልግሎት እንደማያቋርጡ ተናግረዋል፡፡  
የባህር ዳር ከተማ ምስርት ማኅበራትና ዕድሮች ጥምረት ሰብሳቢ አቶ ዳኛቸው ሰይፉ ቤትና መጋዘን ሰርቶ በማከራየት፣ ሥጋ ቤት ከፍቶ በመነገድ፣ … በአጠቃላይ በተለያዩ የገቢ ማግኛ ፕሮጀክቶች በመሰማራት በዓመት ከ650 ሺህ ብር በላይ ስለሚያገኙ፣ ወላጅ አልባና የቤተሰባቸው የገቢ አቅም አነስተኛ የሆኑትን ሕፃናት አስፈላጊ ቁሳቁስ በማሟላት ወደ ት/ቤት ልከው እያስተማሩ መሆኑን፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ብድር በመስጠት የገቢ አቅም እንደፈጠሩላቸው፣ ለአረጋውያን የፈረሰባቸውን ቤት በመጠገን፣ በዓመት በዓል ጊዜ ከብት አርደው በማብላትና የተወሰነውን ወደ ቤታቸው ይዘው እንዲሄዱ ኅብረተሰቡን በማስተባበር የተለያየ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሐዋሳና አካባቢው (ሻሸመኔና አቼቡራን ያጠቃልላል) ምስርት ማኅበራት ጥምረት ዋና ጸሐፊ የሆኑት አቶ ተሾመ ከበደ የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ጥምረታቸው 41 ዕድሮችና ማኅበራትን የያዘ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኢሕማልድ የሚያደርግላቸውን ድጋፍ ቢያቋርጥ ለኅብረተሰቡ የሚሰጡትን ማህበራዊ አገልግሎት ላለማቋረጥና ራሳቸውን ለመቻል ማኅበራዊ ቢዝነስ በ3,170,200 ብር ካፒታል አቋቁመው፣ 1,869,621 ብር ትርፍ ማግኘታቸው ገልጸዋል፡፡
ባገኙት ትርፍ፣ በማኅበሩ ውስጥ ላሉና ለሌሎች ችግረኛ ሕፃናት ድጋፍ እንደሚያደርጉ፣ ወላጆቻቸውን በሞት የተነጠቁ ችግረኛ ቤተሰብ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት እያኮበኮቡ እያሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉላቸው፣ ለወጣቶች 2500 ብር ተዘዋዋሪ ብድር በመስጠት የተለያየ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን፣ ለችግረኛ ልጆች ቤተሰቦች 4000 ብር ብድር በመስጠት ነግደው የብድሩን 60 በመቶ ለራሳቸው ተጠቅመው፣ 40 በመቶውን እንዲመልሱ ይደረጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለገቢ ማግኛ በዕድሮችና ማኅበራት የሚተዳደሩ 15 ባጃጆች አሉ፡፡ እንብራ ራስ አገዝ ማኅበር 3፣ የዕድሮች ኅብረት 4፣ 03 ቀበሌ መረዳጃ ማኅበር ዕድር 2፣ ሐረር ሰፈር መረዳጃ ዕድር 4 ባጃጆች፣ እንዳሏቸው የገለጹት አቶ ተሾመ፤ ባጃጆቹ ከጧቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ሲሠሩ ቆይተው ሌሊት ለሕሙማን የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡   

   - 30 ተማሪዎችን ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል
                          - የዛሬ ሳምንት 100 እናቶችን በተለያየ ሙያ አስመርቋል
                          - በአሁኑ ወቅት ከ950 በላይ ሰዎች በቀን 3 ጊዜ ምግብ ያቀርባል
                       
     የአብስራ፣ እጆቿ ደረቷ ላይ ሆነው እግሮቿ ተጠላልፈው ነበር ከእናቷ ማህፀን የወጣችው፡፡ ስለዚህ እጅና እግሯን ማንቀሳቀስ አትችልም፡፡ ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች በኋላ ወ/ሮ ሙዳይ ተቀብላ እያሳከመች፣ ልዩ መቀመጫ ወንበር አሰርታላት፣ ዩኒፎርም አልብሳት፣ የትምህርት መሳሪያ አሟልታላትና እየመገበች እያስተማረቻት ትገኛለች፡፡ የአብስራ እጆቿ መንቀሳቀስ ስለማይችሉ የምትጽፈው በጥርሷ ነው፡፡ በጥርሷ የሚያምር ጽሑፍ እየጻፈች ዘንድሮ በ11 ዓመቷ ከመዋለ ህፃናት ትመረቃለች፡፡
“ድሃ ስለሆንኩ እሷን የግል ት/ቤት ከፍዬ ማስተማር አልችልም፡፡ ብችልም የሚቀበላት ት/ቤት የለም” ትላለች፤ እናትና ሞግዚቷ ወ/ሮ ገነት አዱኛ። “ያለኝ አማራጭ ልጅቷን ወደ መንግስት ት/ቤት መውሰድ ነበር፡፡ እዚያም ብወስዳት ለእሷ የሚሆን አስተማሪና ልዩ መቀመጫ የለንም፡፡ በአጠቃላይ ለእሷ የሚሆን የልዩ ፍላጎት ማስተማሪያ ስለሌለን አንቀበላትም” ብለው መለሷት፡፡ ስለዚህ እቤት መልሰናት በር ዘግተንባት ነበር ወደ ስራ የምንሄደው በማለት የልጇን ችግር ገልጻለች፡፡
ወ/ሮ ገነት አዱኛ አዲስ አበባ ውስጥ አንቆርጫ በሚባል አካባቢ ነዋሪ ነበረች፡፡ አብስራን የወለደችው የካቲት ሆስፒታል ነበር፡፡ ሐኪሞቹ ሲያዩዋት ሪፈራል ብለው ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጻፉልኝ፡፡ እዚያም ከአንድ ወር በኋላ አምጫት ብለው መለሷት። ጊዜው ሲደርስ ወሰድኳት፡፡ 15 ቀን አስተኝተው ኦፕራሲዮን አደረጓት፡፡ ከዚያም ጄሶ ታሰረላት፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ለ3 ወር 24 ሰዓት የሚደረግ ጫማ አሰሩላት፡፡ እሱም ምንም አላሻላትም፡፡ በመጨረሻ ሙከራችን ምንም ተስፋ የለውም” በማለት እንዳሰናበቷት በሀዘን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር፤ ጎዳና ላይ ወድቀው የነበሩ በልመና የተሰማሩና በሴተኛ አዳሪነት ሕይወታቸውን ሲገፉ የነበሩትን እናቶች፣ ከእነልጆቻቸው ከዚያ አረንቋ ውስጥ አውጥቶ አዲስ ሕይወት እንዲጀምሩ የሚያደርግ ደርጅት ነው። እናቶችን ከነበሩበት አስከፊ ህይወት አውጥቶ መጠለያ በመከራየት፣ ሙሉ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው፣ በተለያዩ ሙያዎች፣ በሽመና፣ በሸክላ ስራ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት፣ በዕደ ጥበብ ስራዎች አሰልጥኖ ከተመጽዋችነት ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
ልጆቻቸው ሙሉ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው፣ ዩኒፎርም ተሰፍቶላቸው፣ የትምህርት መሳሪያዎች እየተሰጣቸው፣ ቁርስ፣ ምሳና እራት እያበሉ እንደየትምህርት ደረጃቸው ሙሉ ወጪያቸው ችሎ፣ በነፃ ከመዋለ ህፃናት እስከ 8ኛ ክፍል ግቢው ውስጥ በሚገኘው “ፍሬሽ ኤንድ ግሪን አካዳሚ” እያስተማረ ነው፡፡ ከ9ኛ ክፍል እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም በአቅራቢያው ባሉ ት/ቤቶች እንዲሁም በተመደቡባቸው የትምህርት ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች ወጪያቸውን በመሸፈን እንዲማሩ ያደርጋል፡፡
ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት ለ430 እናቶች፣ ለ50 አካል ጉዳተኞች፣ ከ500 በላይ ለሚሆኑ ህፃናትና ተማሪዎች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን፣ በቀን ሶስት ጊዜ ቁርስ ምሳና ራት እንዲበሉም እያደረገ ነው፡፡ ማኅበሩ ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል በተለያዩ ሙያዎች፡- በሸክላ፣ በሽመና፣ በዕደ ጥበብ፣ በጥልፍ፣ በልብስ ስፌት ያሰለጠናቸውን 100 እናቶችን ያስመረቀ ሲሆን በድጋፍ ስራ ላይ በቆየባቸው 17 ዓመታት ከ1000 በላይ ለሆኑ እናቶች የተለያየ ሥልጠና ሰጥቶና ራሳቸውን ችለው ከማኅበሩ እንዲወጡ አድርጓል። 30 ተማሪዎችን ወጪያቸውን ችሎ በማስተማር፣ ከተለያዩ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች አስመርቋል። ለ1500 ሰዎች የትራስፖርትና ሌሎች አስፈላጊ ወጪዎችን ሸፍኖ፣ ወደመጡበት የመኖሪያ አካባቢ እንዲመለሱ ማድረጉም ታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በካፒታል ሆቴል 100 እናቶች በተመረቁበት ወቅት ጥቂቶቹን አነጋግረን ነበር። ዘሪቱ ራፍዬ በወሎ ክፍለ ሀገር የአማራ ሳይንት አካባቢ የቤት እመቤት ነበረች፡፡ አንድ ወንድ ልጅ እንደወለደች ባሏ ይሞትባታል፡፡ ቸግሯት አዲሳባ ወዳሉት ዘመዶቿ ዘንድ ከመጣች 16 ዓመት ሆኗታል፡፡ ገቢዋ በየሰው ቤቱ ልብስ እያጠበችና እንጀራ እየጋገረች የምታገኘው ትንሽ ገንዘብ ነበር። በዚህ መኸል ሌላ ወንድ ተዋውቃ ሴት ልጅ ወለደች። ሁለት ልጆች ማብላቱ ማጠጣቱ ማልበሱ፣ ማስተማሩ በአጠቃላይ ተንከባክቦ ማሳደጉ ትልቅ ፈተና ሆነባትና በጣም ተቸገረች፡፡
ወደ ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ከመጣች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ አመጣጧም ሰው ጠቁሟት እንደሆነ ተናግራለች፡፡ ሰዎች “ኮተቤ አካባቢ ሙዳይ በጎ አድራጎት የሚባል አለ፡፡ እንኳን አንቺን እንዲህ የተቸገርሽውን ቀርቶ ሌላውንም ይቀበላሉ፡፡ ሄደሽ ጠይቂ” አሏት፡፡ ሄዳ ጠየቀች፡፡ ወ/ሮ ሙዳይም ልታግዛት ፈቃደኛ ሆና ተቀበለቻት፡፡ እሷና ሁለቱ ልጆቿ በሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር መኖር ከጀመሩ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡
“እዚህ ከመጣሁ አንስቶ ድጋፍ የሚደረግ ነገር ሁሉ ምንም የቀረብኝ የለም፡፡ በጣም ታምሜ ነበር። አሳክማ ለልጆቼ እንድተርፍላቸው አድርጋኛለች። ልብስ በዓመት ሁለቴ ይሰጠናል። በቀን ሶስቴ እንበላለን፤ ቤት ተከራይታልኛለች፡፡ እዚሁ እሰራለሁ፣ በሽመና ሰልጥኜ ባለፈው ሳምንት በሻርፕ ስራ ተመርቄያለሁ፡፡ ሁለቱም ልጆቼ ጫማና ዩኒፎርም ተገዝቶላቸው፣ የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው፣ በቀን ሦስቴ እየተመገቡ፣ 6ኛና 4ኛ ክፍል እየተማሩ ነው፡፡ ተመስጌን ነው የምለው” በማለት ገልጻለች፡፡
የ27 ዓመቷ ራሄል ሽፈራው ትውልዷ ጅማ ነው። ወደ አዲስ አበባ የመጣችው አክስቷ ጋ ሆና ለመማር ነው። አክስቷም እያሳደገች አስተማረቻት። 10ኛ ክፍል ደርሳ ስትፈተን ውጤት ሳይመጣላት ቀረ፡፡ ይኼኔ ከአክስቷ ተጣልታ ከቤት ወጣች፡፡ ካፌ ውስጥ ተቀጥራ መስተንግዶ እየሰራች ስትኖር፣ ከአንድ ወንድ ጋር ተዋውቃ፣ በጓደኝነት አብረው መኖር ጀመሩ፡፡ አረገዘችና ልጅ ወለደች፡፡ ልጅ ተወልዶ ዓመት ሲሞላው ባል ጥሏት ጠፋ፡፡
ያለ አባት ለብቻልጅ ማሳደግ ከባድ ፈተና ነው ትላለች ራሄል፡ “ትልቅ ስቃይና ችግር ነው ያየሁት። ለልጁ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሁሉ ማድረግ አቅቶኝ ትልቅ ችግር ውስጥ ገባሁ፡፡ አሰሪዬ የቤት ኪራይ ትከፍልልኝ ነበር፡፡ እኔ ገንዘብ ለማግኘት ልብስ አጥብ ነበር፡፡ የማገኘው ገንዘብ ትንሽ ስለነበረ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝና ልጄን ማሳደግ አቃተኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዎች “የተቸገሩ የሚረዳ እንዲህ የሚባል ድርጅት አለ፡፡ እዚያ ሄደሽ ሞክሪ” አሉኝ፡፡
“ይኼ የሆነው በ2005 ነበር፡፡ ሙዳይ በጎ አድራጎት መጥቼ ችግሬን ነግሬ፣ እንድትረዳኝ ወ/ሮ ሙዳይን ጠየኳት፡፡ እሷም ቤቴን ሄዳ አይታ፣ ስለ አኗኗሬ ሰዎች ጠይቃ ተቀበለችኝ፡፡ ልጄ አሁን 4 ዓመቱ ነው፣ መዋለ ህፃናት ገብቷል። እኔን እያሰለጠነች ቤት ተከራየችልኝ፤ ቀለቤንና ወጪዬን የምትችለው እሷ ናት፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመረቅሁት በአበባ ማስቀመጫ ስራ ነው፡፡ ሌሎች ሙያዎችም ለማወቅ እጥራለሁ፡፡ ትልቁ ሙያዬ ግን የተመረቅሁበት ነው” በማለት ታሪኳን ገልጻለች፡፡
ሙዳይ በጎ አድራጎት ድርጅት ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ቋሚ ገቢ የለውም፡፡ የገቢው ምንጮች የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያደርጉለት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም ከመንግስትና ከግል ተቋማት የሚወሰድ ብድር ነው፡፡ እናቶች የሚሰሯቸው የተለያዩ የእጅ ስራዎች ተሸጠው አነስተኛ ገቢ ያስገኛሉ። ከምንም በላይ ከማኅበሩ ጎን በመሆን በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ታዋቂ ሰዎችና ግለሰቦች ሚና ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡ ስለዚህ “የግል ድርጅቶች፣ ግለሰቦች፣ ተቋማት፣ የመንግስት መ/ቤቶች፣ … አቅማችሁ በቻለው ሁሉ ድጋፍ እንድታደርጉልን በተረጂዎቹ ስም እጠይቃለሁ” በማለት ተማፅናለች፤ የማኅበሩ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ፣ ወ/ሮ ሙዳይ ምትኩ፡፡    

     የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለስልጣን ሰሞኑን  በአነስተኛ ነጋዴዎች ላይ እየጣለ ያለው አዲሱ የግምት የገቢ ግብር ተመን ከፍተኛ መደናገጥን የፈጠረ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ ከዚሁ የቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
የተጣለባቸውን የቀን ገቢ ግምት ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሮባቸው በድንገት ወድቀው ህይወታቸው ያለፈው አቶ አጎናፍር፤ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 በሰፈር ውስጥ በከፈቷት የሸቀጣሸቀጥ ሱቅ ነበር የሚተዳደሩት፡፡ ምንጮች እንደሚሉት፤ ሰሞኑን በተጀመረው የቀን ገቢ ግመታ፣ ሃምሳ ብር የማይሞላ የቀን ገቢ እንኳን በሌላት አነስተኛ ሱቃቸው ላይ የተጣለው የ5ሺ ብር የቀን ገቢ ግምት በፈጠረባቸው ድንጋጤ ራሳቸውን ስተው ይወድቃሉ፤ በወቅቱ በሥፍራው የነበሩ ሰዎችም አቶ አጎናፍርን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ወደ አዲስ ህይወት ሆስፒታል የወሰዷቸው ቢሆንም ህይወታቸውን ለማትረፍ አልቻሉም፡፡ የሟች ባለቤት ደግሞ ሸንኮራ ዮሐንስ ለንግስ በዓል ሄደው ነበር ተብሏል፡፡  
የከተማዋ ገቢዎች ባለስልጣን በቁርጥ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ላይ ሰሞኑን የጀመረው የቀን ገቢ ግምት ፍትሃዊ ያልሆነና ጥናት ያልተደረገበት መሆኑን የሚገልጹት  ነጋዴዎች፤ የንግዱን ማህበረሰብ ለምሬት የሚዳርግና ተስፋ የሚያስቆርጥ አሰራር ነው ይላሉ፡፡ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በሴራሚክ ሥራ ላይ የተሰማራ ረሻድ አወል የተባለ ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደገለጸው፤ በቀን ገቢ ግምቱ በቀን 10 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ በእጅጉ አስደንግጦታል። አምባሳደር አካባቢ የጀበና ቡና በመሸጥ ንግድ ላይ የተሰማራችው  ሌላዋ ወጣት ደግሞ የቀን ገቢሽ 3500 ብር ነው መባሏን ትናገራለች፡፡ “ከጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ በአንድ ቅፅበት ወደ መካከለኛ ግብር ከፋይ መዛወሬ አስደንጋጭም አስቂኝም ሆኖብኛል” ያለችው ወጣቷ፤” ለመሆኑ በቀን ገቢ ግምቱ ላይ ካፒታል የሚባለው ነገር አይታይም? የእኔ ካፒታል እኮ 100 ብር እንኳን የማያወጣ ጀበና እና ስኒ ነው፡፡ ሰዎቹ ግን እንዴት ነው የሚያስቡት? ይህን ያህል የቀን ገቢ ቢኖረኝ ፀሐይ ላይ ምን እሰራለሁ?” ስትል ደጋግማ ትጠይቃለች፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ሳሪስ አካባቢ በአነስተኛ የወንዶች ፀጉር ማስተካከል ሥራ ላይ የተሰማራው  ግብር ከፋይ፤የቀን ገቢ ግምቱ ሰሞኑን በደብዳቤ እንደደረሰው ጠቁሞ፤በቀን 5 ሺህ ብር ገቢ አለህ መባሉ ድንጋጤ እንደፈጠረበት ይናገራል፡፡ ቀደም ሲል በዓመት ከ8ሺህ ብር በላይ ከፍሎ የማያውቅ መሆኑንና በወር 2ሺ ብር የማይደርስ ገቢ እያገኘ የቀን ገቢህ 5 ሺህ ብር ነው መባሉ ፍትሃዊ አለመሆኑን ገልጿል።
በዚሁ ክፍለ ከተማ በፎቶ ኮፒና ፅህፈት ሥራ ላይ የተሰማራ ሌላ ወጣት የቀን ገቢህ ነው ተብሎ 6 ሺ ብር ግምት የመጣበት መሆኑን ገልፆ፤ ይህን ያህል ገቢ እንኳንስ በቀን በወር አግኝቶ ማወቁን እንደሚጠራጠር ተናግሯል። ሁኔታው ሰርቶ ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ በእጅጉ ያጨለመብኝ ነው ብሏል፡፡ የቀን ገቢ ግምቱን በሰማበት ወቅት የተሰማውን ሲገልፅም፤”ራሴን መቆጣጠር አቅቶኝ ነበር፤ ለሁለት ቀናት ያህል ምግብ መብላት እንኳን አልቻልኩም” ብሏል፡፡ ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር አቤቱታ ለማቅረብ ጥረት ማድረጉን የሚገልፀው ወጣቱ፤ ‹‹ከ500 በላይ ቅሬታ አቅራቢዎች ተሰባስበን ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ፅ/ቤት ሄደን ጥያቄ ብናቀርብም፣ የሚያናግረን የመንግስት አካል እንኳን አጥተን ተመልሰናል” ይላል፡፡
በማግስቱም ከ2 ሺ በላይ አቤቱታ አቅራቢዎች ተሰባስበው ወደ ክፍለ ከተማው ፅ/ቤት በማምራት አቤቱታቸውን ለማሰማት ጥረት ቢያደርጉም ምላሽ በማጣታቸው ጩኸታቸውን እያሰሙ በጎዳና ላይ መጓዛቸውንና ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መሞከራቸውን የተናገረው ወጣቱ፤ ”ድምፃችን  ይሰማ” ፣ ”መብታችን ይከበር” ለሚለው መፈክራችንና ጩኸታችን የተሰጠን ምላሽ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሳችኋል፤ ህገወጥ ተቃውሞ እያደረጋችሁ ነው፤ መብታችሁን መጠየቅና ቅሬታ ማቅረብ ከፈለጋችሁ ኮሚቴ ምረጡና በኮሚቴ ጠይቁ” የሚል ነው ብሏል፡፡ “ኮሚቴ አንመርጥም፤ ለጥቃት ይዳረጉብናል” ብለን ለመከላከል ብንሞክርም፣” ይህ ካልሆነ እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት ተበተኑ” ተብለን ተበትነናል፤ አቤቱታችን ሰሚ አጥቶ እንዲሁ የሚመጣውን ለማየት ቁጭ ብለናል ብሏል - ወጣቱ፡፡
ወ/ሮ ሂክመት በቦሌ ክ/ከተማ በተለምዶ 17/17 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የልብስ መሸጫ ሱቅ አላቸው፡፡ ሰሞኑን በተጣለባቸው “የግብር እዳ” ጤናቸው መቃወሱን ይናገራሉ፡፡ “ቡቲክ ውስጥ የምውለው እቤት ከመዋል ይሻላል በሚል እንጂ እንኳን በቀን 3700 ብር ልሸጥ አንድም ቲ-ሸርትና አንድም ሱሪ ሳልሸጥ የምውልበት ቀን’ኮ ብዙ ነው” ይላሉ፤ተገምቶ የተነገራቸውን የቀን ገቢ አስመልክተው ሲያስረዱ፡፡  “በቀን 3700 ብር ከሸጥኩ በዓመት 1.4 ሚ. ብር እሸጣለሁ እንደ ማለት ነው፤ ይሄን ሁሉ የምሸጥና ገቢ የማገኝ ከሆነ ላለፉት አራት ዓመታት ባገኘሁት ገቢ እንደ ባለ ሀብቶቹ ፎቅ እገነባ ነበር” ብለዋል፤ ወ/ሮ ሂክመት፡፡
“የሱቅ ኪራይ መክፈል እያቃተኝ አንዳንዴ ባለቤቴን አስጨንቄ እከፍላለሁ” ያሉት ወይዘሮዋ፤ “እንዲህ ዓይነት እዳ ከመሸከምና በሽታ ላይ ከመውደቅ ለምን ከርችሜው ቤቴ ቁጭ ብዬ ልጆቼን አላሳድግም?” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል፡፡ ሰሞኑን ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ከሌሎች ነጋዴዎች ጋር በመሆን ሲጨቃጨቁ መሰንበታቸውን ጠቁመው፤ በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ ለዛሬ ቀጥረውናል ብለዋል፡፡
የ32 ዓመቷ ፍቅርተ ገድሉ፤ የካ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ነዋሪ እንደሆነች ትናገራለች፡፡ ለ6 ዓመታት በኩዌት ስትሰራ ቆይታ ከተመለሰች አራት ዓመቷ ነው፡፡ የራሷን ስራ ለመስራት በማቀድ፣ ፀጉር ቤትና ሽሮ ቤት ከፍታ ስትሰራ እንደነበር ያወሳችው ፍቅርተ፤ ለኪሳራ በመዳረጓ የካፌ አስተናጋጅ ሆኗ መቀጠሯን ትናገራለች፡፡ ይህም የልቧን አላደርስ ስላላት፣ ቡና የምታፈላበትን በረንዳ በወር ሁለት ሺህ ብር ተከራይታ የጀበና ቡና እያፈላች መሸጥ መጀመሯን ትናገራለች፡፡ ምንም እንኳን የጀበና ቡና ሥራው ተስፋ ሰጪ ቢሆንም በቀን 2500 ብር ገቢ ታገኛለች መባሏ አገሯ ላይ የመስራት ተስፋዋን እንደ ጉም እንዳተነነው ፍቅርተ በምሬት ትናገራለች። “እውነት የጀበና ቡና ሸጣ በቀን 2500 ብር ታገኛለች ብለው ሳይሆን ለመለወጥ ያለኝን ተስፋ ለማሟጠጥ ነው” የምትለው ወጣቷ፤ ”እዚህ ያለው እንደዚህ የሚማረር ከሆነ የተሰደደውስ ምን ተስፋ ኖሮት ይመለሳል?” በማለት ትጠይቃለች፡፡
 የጀበና ቡና ገበያዋን በተመለከተ ስታስረዳም፤”በቀን  መቶና 150 ብር ብሸጥም ስኳር፣ ከሰል፣ ቡና፣ የራሴ ጉልበት አለበት፤ ለዚያውም 150 ብር የሸጥኩበት ቀን በጣም በቁጥር ነው፤ በተለይ ክረምቱ ከገባ በኋላ በረንዳው ስለሚያፈስ ገበያ ቀዝቅዟል፤በዚህ የተነሳ ክረምቱ እስኪያልፍ ስራውን ለማቆም እያሰብኩ ነበር” ብላለች፡፡ “እንዴት የጀበና ቡና እየሸጥኩ በቀን 2500 ብር ትሸጫለሽ ትላላችሁ? ከየትስ አምጥቼ እከፍላለሁ?” ብዬ ብጠይቃቸው፣ ‹‹በቀን ከምትሸጭው ላይ ለምን እቁብ እየጣልሽ አጠራቅመሽ አትከፍይም” ሲሉ ተሳለቁብኝ ያለችው ፍቅርተ፤አሁን እንደገና  ልቤ ለስደት ተነሳስቷል ብላለች፡፡  
ወጣት ባልና ሚስት ናቸው፤ እሱ ታዋቂ የፀጉር ስታይሊስት ነው፡፡ ባለቤቱም በሹሩባና በፀጉር ስፌት የተካነች ናት፡፡  ከመጋባታቸው በፊት ሁለቱም በተለያየ የውበት ሳሎን ተቀጥረው ይሰሩ  እንደነበር ይናገራሉ። “የራሳችንን የውበት ሳሎን የመክፈት ሀሳብ ስለነበረን እቁብ እንጥል ነበር፤ከረጅም ጊዜ ትግል በኋላ እቁብ አሰባስበን አራዳ ክ/ከተማ በተለምዶ ገዳም ሰፈር በሚባለው አካባቢ አንዲት ጠባብ ቤት በወር 5 ሺህ ብር ተከራይተን፣ ግማሹን የውበት መሳሪያ ገዝተን፣ ግማሹን በኪራይ አሟልተን፣ የውበት ሳሎን ከፈትን” ይላሉ፤ጥንዶቹ፡፡  ‹‹እርግጥ ነው የራሳችንን የውበት ሳሎን ከከፈትን በኋላ ተቀጥረን እንሰራባቸው ከነበሩ የውበት ሳሎኖች ደንበኞቻችን ተከትለውን መጥተዋል፤ የማደግና የመለወጥ ተስፋ ነበረን›› የሚሉት ባልና ሚስቱ፤ሰሞኑን በቀን 2800 ብር ታስገባላችሁ ሲባሉ በድንጋጤ ክው ማለታቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ግን እኮ እዚህ እኛው አካባቢ በቀን 10 እና 25 ሺህ ብር ያስገባል የሚባለው ሬስቶራንት የተገመተለትን ብትሰሙ  በሳቅ ትሞታላችሁ፤በቀን 1800 ብር ነው” ያለው ወጣቱ የውበት ሳሎን ባለቤት፤”አሁን ከተማዋ ላይ ትንሽ አብዶ የማሳበድ ስራ እየተሰራ ይመስላል” ብሏል፤የተሰማውን ሲገልጽ፡፡
 በቀን ትሰራለህ የተባልኩት በዓመት ሲባዛ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ነው ያለው ወጣቱ፤ ግብሩ የዚህ 20 በመቶ ሲሆን ስንት ሊመጣ እንደሚችል ማሰብ ራሱ ያሳብዳል ይላል፡፡ “ለመሆኑ የሚገምቱት አካላት በምን መስፈርት እንደሚገምቱ፣ መነሻቸው ምን እንደሆነ፣ መንግስት ለነጋዴው ግልፅ አድርጓል ወይስ ስራው በአቦ ሰጡኝ ነው የሚሰራው?” ሲል ይጠይቃል፤ወጣቱ፡፡ ቀጣይ ዕቅዳቸውን በተመለከተ ጥንዶቹ ሲናገሩ፤”ለጉዳዩ መንግስት መፍትሄ ካልሰጠና እልባት ካልተገኘ ወደተቀጣሪነታችን እንመለሳለን” ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በበኩሉ፤በግመታው ላይ የግንዛቤ ችግር መኖሩንና ህብረተሰቡን ስለ ጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጥ ተገቢ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዲስ አበባ የታክስ ፕሮግራምና ልማት ሥራዎች ዘርፍ ም/ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የዕለት ገቢ ግምት መነሻ ግብር ከፋዩ ራሱ ያቀረበው መረጃ ላይ ተመስርቶ የተሠራ መሆኑን ጠቁመው፤ቅሬታ አለኝ የሚል አካል ቅሬታውን ለሚመለከተው አካል በአግባቡ የማቅረብ መብት አለው ብለዋል፡፡ የንግድ ሥራው ባለበት አካባቢ ያለው የንግድ እንቅስቃሴና አማካይ የዕለት ገቢ ታሳቢ ተደርጎ ግምቱ መሰራቱንም ሃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ቅሬታዎች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን የጠቆሙት የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊዎች፤ ማንኛውም ግብር ከፋይ ቅሬታውን ከወረዳ ጀምሮ ላሉ ማዕከላት ማቅረብ እንደሚችልና ቅሬታውን ሲያቀርብ ግን በግል ብቻ መሆን እንዳለበት፣ በቡድን ተደራጅቶ  ቅሬታ ማቅረብ እንደማይቻልም አክለው ገልጸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሰጥና የሚያስረዳ ኮሚቴ መቋቋሙንም  ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል፡፡





     መንግስት በአጠቃላይ ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ በማድረግ ሰርቻቸዋለሁ ያላቸው 972 የ40/60 መኖሪያ ቤቶች  እጣ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የሚወጣ ሲሆን ዕድለኞች በወር ውስጥ ቤታቸውን ይረከባሉ ተብሏል፡፡  
ዛሬ ለእጣ ከተዘጋጁት 972 ቤቶች የሚጠበቅባቸውን የቤት ዋጋ ሙሉ ለሙሉ የከፈሉ 11 ሺህ 88 ቤት ፈላጊዎች የሚወዳደሩ ሲሆን ከነዚህ እድለኞች ውስጥ 20 በመቶ ለመንግስት ሰራተኞች፣ 3 በመቶ (29 ቤቶች) ለዳያስፖራዎች ቅድሚያ እድል የሚሰጥባቸው ይሆናሉ፡፡
የቤቶቹን እጣ አወጣጥ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የከተማ አስተዳደሩ፣ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ቤቶች ልማት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ለእነዚህ ግንባታቸው ከተጀመረ ከ4 ዓመት በኋላ ለተጠናቀቁ 972 ቤቶች አጠቃላይ ወጪ፣ ቤት ፈላጊዎች ከቆጠቡት በተጨማሪ መንግስት ከ725 ሚሊዮን ብር በላይ ድጎማ አድርጎባቸዋል ተብሏል፡፡
የ40/60 የቤት ፕሮግራም ከ4 ዓመት በፊት 44 ሲደረግ ባለ 1 መኝታ ቤት 55 ካሬ ሜትር፣ ባለ 2 መኝታ 75 ካ.ሜ እንዲሁም ባለ 3 መኝታ 100 ካ.ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ በተደረገ የዲዛይን ማሻሻያ ባለ 1 መኝታ ቤት እንዳይኖር ተደርጎ፣ ባለ 1 የነበረው ወደ ባለ 2 መኝታ ቤት 125 ካ.ሜትር ስፋት፣ ባለ 2 የነበረው ወደ ባለ 3 መኝታ ከፍ ተደርጎ፣ በ150 ካ.ሜትር ላይ እንዲሁም ባለ 3 የነበረው ወደ ባለ 4 መኝታ ቤት ከፍ ተደርጎ፣ 168 ካ.ሜትር ስፋት እንዲኖራቸው መደረጉ ተገልጿል፡፡  
የቤቶቹ ዋጋም ቀደም ሲል በካሬ ሜትር በ3200 ብር ታስቦ የነበረው ወደ 5680 ብር ከፍ ማለቱን፣ መንግስት በእያንዳንዱ ካሬ ሜትር ላይ የ720 ብር ድጎማ አድርጎ፣ እድለኞች ቤቱን በካሬ ሜትር 4918 ብር ሂሳብ እንዲረከቡ ማመቻቸቱን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡ በዚህም መሰረት፤ ዛሬ እጣ የሚወጣባቸው መኖሪያ ቤቶች ላይ እያንዳንዱ ባለ እድለኛ ቀድሞ ከነበረው ዋጋ ላይ በካሬ ሜትር 1718 ብር ጭማሪ እንደሚከፍል ታውቋል፡፡
በቤቶቹ ዋጋ ላይ በጠቅላላው 170 ሚሊዮን ብር ድጎማ መደረጉን እንዲሁም አስተዳደሩ ፓርኪንግ ለመሳሰሉ ወጪዎች 140 ሚሊዮን፣ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ 97 ሚሊዮን እና ለቫት 168 ሚሊዮን የከፈለውን ጨምሮ 725 ሚሊዮን ብር ድጎማ ማድረጉ ተመልክቷል፡፡
ለመኖሪያ ቤትነት እጣ ከሚወጣባቸው ቤቶች በተጨማሪ 320 የንግድ ቤቶችም በእለቱ በመነሻ ዋጋ በካሬ ሜትር 172 ሺህ ብር ለጨረታ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ከ40/60 ቤቶች የተወሰኑት ለመንግስት ቤቶች ኤጀንሲ እንዲሰጥ ጥያቄ መቅረቡን የጠቆሙት የአስተዳደሩ ም/ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው፤ዕድለኞች ክፍያ ፈፅሞ ቤቶቹን ለመውሰድ የሚከብዳቸው ከሆነ መንግስት ራሱ ቤቱን ይገዛዋል፤ዋጋው አሁን በዝቶብኛል ያሉ በቀጣይ በሚወጡ እጣዎች የመካተት እድል ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡  
የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ዛሬ እጣ የሚወጣባቸው የክራውንና የሠንጋ ተራ ሳይት ቤቶች መሠረተ ልማት እንደተሟላላቸውና በጥራት መሰራታቸውን ሙሉ ለሙ አረጋግጦ ባንኩ መረከቡን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም በ2005 ዓ.ም 164 ሺህ ያህል ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበው የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 140 ሺህ ቤት ፈላጊዎች ቁጠባቸውን ሳያቋርጡ አድላቸውን እየተጠባበቁ ነው ተብሏል፡፡ በቀጣይ ዓመትም 20 ሺህ ቤቶችን ለተመዝጋቢዎች ለማስተላለፍ እቅድ መያዙን የስራ ሃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎች በመተላለፍ ህገ መንግስታዊ ስርአቱን በኃይል ለማስወገድ ተንቀሳቅሰዋል በሚል የተከሰሱት አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ የምስክሮችን ዝርዝር የማወቅ መብትን” በተመለከተ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ላይ የፌዴሬሽን ም/ቤት የህግ ትርጉም እንዲሰጥበት ፍ/ቤቱ ብይን ሰጠ፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና ለፍ/ቤቱ ካቀረቧቸው የክስ መቃወሚያዎች መካከል ‹‹ክሱ የተሟላ አይደለም፤ ክሱ ፖለቲካዊ ነው፤ በሽብር ክስ ሳልከሰስ የሽብር ክስ ማስረጃ ሊጠቀስብኝ አይገባም›› የሚሉና ሌሎች የክስ መቃወሚያ በጠበቆቻቸው በኩል ያቀረቡ ቢሆንም ከአንዱ በስተቀር ቀሪዎቹን መቃወሚያዎች ፍ/ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት እንዳልተቀበላቸው አስታውቋል፡፡
ዶ/ር መረራ ጉዲና የተከሰሱት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማስፈፀሚያ ደንብና በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ ነው፡፡ የማስረጃ ዝርዝሩ የቀረበበባቸው ደግሞ በፀረ ሽብር አዋጁ መሰረት መሆኑን የዶ/ር መረራ የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሣ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡ በሽብር የተከሰሰ ሰው፤ የሰው ምስክሮች ላይገለጡለት እንደሚችል በህግ ተደንግጓል፡፡
ተከሳሹ በሽብር ወንጀል አለመከሰሳቸውን በመጥቀስ የሰው ማስረጃ ዝርዝሮች እንዲገለጥላቸው ጥያቄ በማቅረባቸው ፍ/ቤቱ የህግ ትርጉም ያስፈልገዋል ሲል ፌዴሬሽን ም/ቤት የህግ ትርጉም እንዲሰጥበት ብይን ሊሰጥ መቻሉን አቶ ወንድሙ አብራርተዋል፡፡
የፌዴሬሽን ም/ቤትን የህግ ትርጉም ለመጠባበቅ ጉዳዩ ለሐምሌ 25 ቀን 2009 ዓ.ም ተቀጥሯል፡፡
ዶ/ር መረራ ፍ/ቤት የመናገር እድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው ባደረጉት ንግግር፤ “የኔ ክስ የፖለቲካዊ ክስ ነው፣ ለኦሮሞ ህዝብ መብት በመታገሌ ነው የተከሰስኩት፣ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ነፃነት በመቆሜ ነው፤ ለሃቀኛ ፌደራል ስርአት መገንባትና ነፃ ፍ/ቤት፣ ነፃ የዳኝነትና የፍትህ ስርአት እንዲፈጠር ስለታገልኩ ነው የተከሰስኩት፡፡
ይሄን ትግል እኔ ብቻ አይደለሁም የታገልኩት፤ ቀደም ሲል አቤ ጉበኛ የሚባል ደራሲ “አልወለድም” የሚል መፅሃፍ ፅፎ ለንጉሡ ማስጠንቀቂያ ነግሮ፣ ንጉሡ ሳይሰማቸው መጨረሻው እንደዛ ሆነ፤ በደርግ ስርአት ደግሞ በአሉ ግርማ “ኦሮማይ” የሚል መፅሐፍ ፅፎ ለደርግ መንግስት ምክር ቢሰጥ ሳይሰማ ቀርቶ የሆነውን ታሪክም ፍ/ቤቱም ያውቃል፤ እኔ ደግሞ “የተራበ ህዝብ መሪዎቹን ይበላል” ብዬ መፅሓፍ ፅፌያለሁ፤ እባካችሁ ዳኞች ለታሪክ ስትሉ እነዚህን ሶስት መፅሃፎች አንብቡ …. የሰራሁት ወንጀል የለም፡፡ ለሁላችንም የምትሆን ህግና የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሰው ሁሉ በእኩል የሚኖርባትን ሀገር እንመስርት ብዬ አንድ ለሆዱ ከሚያስብ ምሁር በላይ ዋጋ በመክፈሌ ነው የተከሰስኩት” ማለታቸው ታውቋል፡፡