Administrator

Administrator

•  ዛሬ የተጀመረው የመጨረሻ ውድድር እሁድ ይጠናቀቃል

ባለፉት ወራት በአገሪቱ 10 ከተሞች ባሉ ከ400 በላይ ት/ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ከ120ሺ በላይ ተማሪዎች መካከል የሂሳብ ትምህርትና ስሌት ውድድር ሲያካሂድ የቆየው ማይ ሶሮባን ኢትዮጵያ፤ ለአሸናፊ ተማሪዎች የ1ሚ.ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

ውድድሩን በአስር ከተሞች በ5 ቋንቋዎችና በአምስት ዙሮች ሲያካሂድ የቆየው ተቋሙ፤ በውድድሩ እጅግ አስገራሚና ለሃገር ተስፋ የሚጣልባቸው የሂሳብ ዕውቀት ያላቸው ተማሪዎች የተከሰቱበት መሆኑን ገልፆ፤ በዚህ አገር አቀፍ ውድድር ወደ መጨረሻ ዙር ያለፉ 965 ታዳጊ ተማሪዎች በከፍተኛ ፉክክር ለአሸናፊነት መዘጋጀታቸውን አመልክቷል፡፡

የማይ ሶሮባን ኢትዮጵያ ሃላፊዎች ዛሬ አርብ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፍፃሜ ውድድሩ ከዛሬ ነሐሴ 19 እስከ እሁድ ነሐሴ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ታላላቅ የሂሳብ ልሂቃንና የመንግስት የትምህርት ዘርፍ ሃላፊዎች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት እየተካሄደ እንደሚቀጥል  ጠቁመዋል፡፡

ውድድሩ የፊታችን እሁድ  የሚጠናቀቅ ሲሆን.፤ለአሸናፊ ተማሪዎች የ1 ሚሊዮን ብር ሽልማት መዘጋጀቱ ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ዋንጫ፣ ሜዳሊያና ሰርተፍኬት ይበረከትላቸዋል ተብሏል፡፡

- "ስማርት ሶሉሽን ለስማርት ኢንቨስተሮች" የተሰኘ ፕሮጀክት አስተዋወቀ

አዋሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን አ.ማ፤ "ስማርት ሶሉሽን ለስማርት ኢንቨስተሮች" በሚል ከዛሬ ነሃሴ 20 ቀን 2015 እስከ ህዳር 16 ቀን 2016 ዓ.ም የሚዘልቅ ልዩ አክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን አስታወቀ።

የአሸዋ ቴክሎጂ ሶሉሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል በቀለ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጉዳዩን አስመልክቶ በሳፋየር አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

"ስማርት ሶሉሽን ለስማርት ኢንቨስተሮች" በሚል መርህ ለኢትዮጵያውያንና ለትውልደ ኢትዮጵያውያ ልዩ የኢንቨስትመንት ጥቅም የሚያስገኝ ዕድል ይዘን መጥተናል ብለዋል- ዋና ስራ አስኪያጁ በጋዜጣዊ መግለጫው።

ፕሮጀክቱን በአገር ውስጥ ለመተግበር ከ112,000,000 ብር በላይ ኢንቨስትመንት የሚፈጅ መሆኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ይኼ ኢንቨስትመንት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያስገኝ ነው ብለዋል።

"ድርጅታችን ሲቋቋም ከሚያስፈልገው የ200 ሚሊዮን ብር አክሲዮን ወደ 2 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ቦርዱ በወሰነው መሰረት ቀሪ አክሲዮኖቻችን በአጭር ጊዜ ሸጦ ለመጨረስ የተለያዩ ፓኬጆችን በማውጣት እየሰራ ነው።" ሲሉም አክለዋል- አቶ ዳንኤል።

በዚህም መሰረት፣ ድርጅቱ የአሸዋ ስማርት (ERP)፡- የሰው ሃብት አስተዳደር፣ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ፣ ኢንዱስትሪና የመሳሰሉትን የቢዝነስ ክንውኖችን የሚያቀላጥፍ፤ የተቋማትን ወጪ የሚቀንስ፣ ትርፋማነትን የሚጨምርና፣ ቀልጣፋ የአሰራር ሂደትን የሚፈጥር- ሁሉንም በአንድ ላይ የያዘ- ከ13 በላይ ኢንዱስትሪዎችን የሚሸፍን አስተማማኝ ሶፍትዌር በሳስ እና በሽያጭ መልክ ለገበያ አቅርቧል።

"Smart website Builder" የተሰኘው የድረ-ገጽ መገንቢያችን በደቂቃዎች ውስጥ ድንቅ ድረ-ገፃችን ለመፍጠር ያስችላል" ብሏል-ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ።

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በሰጡት ማብራሪያ፤ "እነዚህ የስማርት ፕሮጀክት አካል ላይ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ለማህበረሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በፕሮጀክቱ ውስጥ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ልዩ ጥቅም የሚያስገኘውን አክሲዮን የሚገዙ ኢንቨስተሮች ለተከታታይ አራት ዓመት ከሚገኘው ትርፍ በየዓመቱ የ50% ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል።

"አንድ ኢንቨስተር በ500ሺ ብር አክሲዮን ሲገዛ በአጠቃላይ በድምሩ 6,910,762.25 የሚያገኝ ሲሆን ከ4 ዓመት በኋላ መደበኛ ባለአክሲዮን በመሆን የጠቅላላ ትርፍ ተካፋይ ይሆናል።" ሲሉ አስረድተዋል- ዋና ሥራ አስኪያጁ።

አሸዋ ቴክኖሎጂ ሶሉሽን፤ ቴክኖሎጂን ዲሞክራሲያዊ በማድረግ ለማህበረሰቡ ዘመኑን የዋጁ ድንቅ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን በማቅረብ፣ በአገራችን ያለውን ዘልማዳዊ የቢዝነስ ሂደት በመቀየር፤ ቢዝነስን ቀላል፣ ዘመናዊና አስተማማኝ ለማድረግ አልሞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (Editors Guild of Ethiopia) በዛሬው ዕለት ሳምንታዊው የቁርስ ላይ ስብሰባውን ከጠዋቱ 2፡00 – 3፡30 በሂልተን አዲስ አድርጓል፡፡ የዕለቱም ርዕስ ጉዳይ 'Access to Information; why it matters in editorial decision making ...' የሚል ሲሆን፤ እንደ ወትሮው መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ በማህበሩ አባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በተለይም ኤዲተሮች ከመንግሥት ሃላፊዎች ወይም ተቋማት መረጃ ለማግኘት የሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች በስፋት ተነስተዋል፤ተዳስሰዋል፡፡
የመንግሥት ሃላፊዎች በየተቋሞቻቸው ያሉ መረጃዎች የራሳቸው ይመስላቸዋል ሲሉ ሃሳባቸውን የሰነዘሩ አንድ የማህበሩ አባል፤መረጃዎቹ በሙሉ ግን የግብር ከፋዩ ህዝብ ነው፤ ብለዋል - በጉዳዩ ላይ የግንዛቤ እጥረት በስፋት መኖሩን በመጠቆም፡፡ በመጨረሻም የመፍትሄ ሃሳቦች ተሰንዝረዋል - በማህበሩ አባላት፡፡
የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር በመላው አገሪቱ በህትመት፣ በብሮድካስትና በዲጅታል ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚሰሩ ኤዲተሮችን (አዘጋጆችን) በማቀፍ የዛሬ አራት ዓመት የተመሰረተ የሙያ ማኅበር ሲሆን፤ የማኅበሩ ተልእኮም በአገሪቱ የተሻለ የሚዲያ ነጻነትን መፍጠር ነው።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
• ካፒታሉን 5ቢ.ብር ለማድረስ፣ ለ3ዓመታት አክሲዮን እንዲሸጥ ተፈቅዶለታል
ከ10 ወር በፊት ዋና መስሪያ ቤቱን ደብረ ብርሃን ከተማ አድርጎ በይፋ ስራ የጀመረው አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ አክሲዮን ማህበር፤ አርቲስት ትዕግስት ግርማንና አርቲስት ይገረም ደጀኔን የብራንድ አምባሳደሮቹ አድርጎ መሾሙን በዛሬው ዕለት ረፋድ ላይ፣ በራስ አምባ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
የተቋሙ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሮቤል ንጉሴ በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት፤ አርቲስቶቹ ለብራንድ አምባሳደርነት የተመረጡባቸው መስፈርቶች በሙያቸው በስነምግባራቸውና በማህበራዊ አገልግሎታቸው የተመሰገኑና የተከበሩ በመሆናቸው ነው።
አርቲስቶቹ በብራንድ አምባሳደርነት ለአንድ ዓመት ለመስራት ነው የተፈራረሙት።
አርቲስት ይገረም በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር፤ ለዚህ ስራ መስፈርቱን አሟልቶ መመረጥ ቀላል እድል እንዳልሆነ ገልፆ፤ “ይህን ሥራ ለመስራት ከተከፈለኝ ገንዘብ በአብላጫው አክሲዮን ገዝቼ ተቋሙን የራሴ አድርጌዋለሁ፣ የምሰራውም ለራሴ ተቋም ነው“ ብሏል።
አርቲስት ትዕግስት ግርማም በበኩሏ፤ እኔ አክሲዮን ሳልገዛ ሌሎችን ግዙ ማለት አግባብ አለመሆኑን ገልፃ፣ አክሲዮን ገዝታ ተቋሙን መቀላቀሏንና በተሰጣት ሐላፊነት ተቋሙን ለማሳደግ ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች።
አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ፣ ካፒታሉን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ከብሄራዊ ባንክ ፈቃድ ማግኘቱን ጠቁሞ፤ በቀጣይ ከብራንድ አምባሳደሮቹ ጋር በመሆን ድርጅቱት በማስተዋወቅና ተጨማሪ አክሲዮኖችን በመሸጥ ከግቡ ለመድረስ ማቀዱን የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ሮቤል ንጉሴ ጨምረው ገልፀዋል።
አኩፋዳ ማይክሮ ፋይናንስ በተመሰረተ በ10 ወሩ የብድር አገልግሎቱን ተደራሽ በማድረግ የ1 ሺህ 600 ሰዎችን ህይወት የቀየረ መሆኑን የገለፁት የቦርድ ሰብሳቢው፤ የቅርንጫፎቹን ብዛት በአንድ ዓመት ውስጥ 50 ለማድረስ በገባው ቃል መሰረት ጥቅምት ላይ ቅርንጫፎቹ 50 እንደሚሞሉ ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ፣ በባህርዳር፣ ሐዋሳ፣ አርባ ምንጭና በሌሎችም ክልሎች ቅርንጫፎቹን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ተቋሙ፤ ስራ ሲጀምር 31 ሚሊዮን ብር የነበረው ካፒታሉ በአሁኑ ሰዓት ወደ 281 ሚሊዮን ብር መድረሱን አቶ ሮቤል ተናግረዋል።
ካፒታላቸውን ወደ 5 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ተቋሙ ለ3 ዓመታት አክሲዮን እንዲሸጥ የተፈቀደለት ሲሆን፤ የአክሲዮን ሽያጩ በ2018 ነሃሴ ወር ላይ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…

ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል፣ ዓመታዊ የጳጉሜን ለጤና ነጻ የህክምና ምርመራ ዘመቻውን ለ14ኛ ጊዜ ከጳጉሜ 1 እስከ ጳጉሜ 6 ቀን 2015 ዓ.ም ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በዘንድሮው ጳጉሜን ለጤና ነጻ የህክምና ምርመራ፣ ማዕከሉ፣ 14 ዓይነት በጎ አድራጎቶችን እንደሚያከናውን ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት 13 ዓመታት በሰጠው ነጻ የህክምና ምርመራ አገልግሎት፣ ከ52 ሺ በላይ ወገኖች ተጠቃሚ እንደሆኑ ያስታወሰው  ማዕከሉ፤ በዘንድሮው መርሃግብር ከ5ሺ በላይ ሰዎች  ነጻ የህክምና ምርመራ እንደሚያገኙ  አስታውቋል፡፡

የውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል አመራሮች፣ የጳጉሜን ለጤና የበጎ አድራጎት ሥራዎችና የነጻ ህክምና ምርመራ ዘመቻን አስመልክቶ፣ ዛሬ ጠዋት 4 ሰዓት ላይ በድርጅቱ ማዕከል  በሰጡት  ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ጳጉሜ ለእኛ በጣም በጉጉት የምንጠብቀው በዓላችን ነው” ብለዋል፡፡