Administrator

Administrator

እናት ባንክ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበትና ዳጎስ ያለ ሽልማት የሚያስገኝ “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ባንኩ ይህን ያስታወቀው ሀሙስ የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም ረፋድ ላይ በሀያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ስለ እናቱ የሚሰማውን ስሜት በA4 መጠን ወረቀት ከ3 ገፅ ባልበለጠና ባላነስ ፅፎ መወዳደር ይችላል ተብሏል፡፡
በፅሁፍ ሁሉም ሰው ለእናቱ ያለውን ፍቅር፣ ክብር፣ አክብሮትና ውለታ ግጥም ባልሆነ ነገር ግን በወግ፣ በደብዳቤ ቅርፅ የሚገልፅበትና ለእናቴ የሚልበት መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን የባንኩ የማርኬቲንግ ፕሮሞሽንን የደንበኛ አገልግሎት ዳይሬክተር ወ/ሮ አክሊል ግርማ ተናግረዋ፡፡የመወዳደሪያ መስፈርቱና የውድድሩ ዳኝነት በቋንቋና በፅሁፍ ተግባቦት ሰፊ ልምድ ባላቸው ከፍተኛ ባለሙያዎች የተዘጋጀና የሚከናወን እንደሆነም ሀላፊዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ የፎክሎር ባለሙያና መምህር ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር) እና ደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎሮስ ተ/አረጋይ በአማካሪነት የሚሳተፉበት ይሄው “ለእናቴ” የተሰኘ የፅሁፍ ውድድር፤ ለጊዜው በአገሪቱ የስራ ቋንቋ በአማርኛ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ተወዳዳሪዎች 50 በመቶ የቅርፅ ጉዳዮች፣ 50 በመቶ ደግሞ የይዘት ጉዮች በድምሩ 100 ነጥብ እንዲይዙ ተደርገው መዘጋጀታቸውም  ታውቋል፡፡
ተወዳዳሪዎች ለውድድር የሚያቀርቡት ፅሁፍ ከዚህ ቀደም በሌሎች የህትመት እና ኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙሃን ላይ ያልቀረቡ ወጥ እና አዲስ መሆን ያለበት ሲሆን ፅሁፍ ግልጽና ተነባቢ እንዲሆን በኮምፒዩር ተተይቦ በ12 ፎንት የፊደላት መጠንና በ1.5 የህዳግ መስመር መቅረብ እንዳለበትም ተብራርቷል፡፡ በተጨማሪም ተወዳዳሪዎች ስማቸውንና አድራሻቸውን ለውድድር በሚያቀርቡት ወረቀት ላይ መፃፍ እንደሌለባቸው የተገለጸ ሲሆን  ፅሁፉን አሸገው የሚያቀርቡበት ፓስታ ላይ ብቻ መፃፍ እንዳለባቸው ታውቋል የማስረከቢያ ጊዜው ከሚያዚያ 26 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተወዳዳሪዎች የመወዳደሪያ ጽሁፋቸውን በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የእናት ባንክ ቅርንጫፍ በአካል ሄደው ማስገባት ይጠበቅባቸዋል የተባለ ሲሆን በሁሉም አካባቢ እናት ባንክ ተደራሽ ባለመሆኑ Lenate @ enatbankssc.comየኢሜል አድራሻን በአማራጭነት መጠቀም ይቻላል ተብሏል፡፡ በውድድሩ ከ1-3 የወጡ አሸናፊዎች ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማትና የእውቅና የምስክር ወረቀት የሚበረከትላቸው ሲሆን አሸናፊዎች የሚሸለሙትን የገንዘብ መጠን የባንኩ ሃላፊዎች ከመግለፅ ተቆጥበዋል፡፡ አሸናፊ ፅሁፎችን ባንኩ ለተለያየ ጉዳይ ሊጠቀምባቸው ይችላል የተባለ ሲሆን ውድድሩ ማንኛውም እናቱን የሚወድ ሀሳቡን የሚገልፅበት እንጂ ፕሮፌሽናል የስነ ፅሁፍ ወድድር አለመሆኑን የፕሮጀክቱ አማካሪዎች በአፅንኦት ገልፀዋል፡፡
“ለእናቴ” የተሰኘው ይሄው ውድድር በየዓመቱ አይነቱን እየቀያየረ የባንኩ አንድ መለያ ሆኖ እንደሚቀጥልም ታውቋል፡፡ እናት ባንክ ማህበረሰቡ ከሚወዳደርበት በተጨማሪ የባንኩ ሰራተኞች ብቻ የሚወዳደሩበት መርሃ ግብርም እንደሚኖረው ተብራርቷል፡፡ እናት ባንክ በአሁኑ ወቅት ከብር ሁለት ቢሊዮን በላይ የተከፈለ ካፒታል ባለቤት ሲሆን ከ60 በመቶው በላይ ድርሻ የሴቶች መሆኑንና በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች 137 ቅርንጫፎችን ከፍቶ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ስለመሆኑ ያብራሩት የባንኩ ሃላፊዎች፤ ባንኩ በተለይም ለሀገራችን ባለውለታ እንቁ ሴቶች በስማቸው ቅርንጫፍ እየከፈተ ስራውን መቀጠሉ ልዩ ያደርገዋል ተብሏል፡፡


ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የዕድገት ማስፋፊያ  ዕቅዶችንም ይፋ አድርጓል

ጤና የምግብ ዘይት፣555 የጽዳት መጠበቂያ፣ ኦራ የግል ንጽህና መጠበቂያ ሳሙና፣ሼፍ ሉካ ፓስታና አኳሴፍ የተፈጥሮ ማዕድን ውሃ የመሳሰሉ በርካታ ታዋቂ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ደንበኞች በማቅረብ የሚታወቀው 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ. የቢዝነስ ግሩፕ፣ ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን አስታውቋል፡፡
የቢዝነስ ግሩፑ አዲሱን ስያሜውን ያበሰረው፣ ባለፈው ረቡዕ በሃያት ሬጀንሲ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ በዚህ መግለጫ፤ ግዙፍ የካፒታል ኢንቨስትመንትና የወደፊት የዕድገት ማስፋፊያ ዕቅዶችንምኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡ መግለጫውን  የሰጡት የ54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት፣ የኩባንያው  ማርኬቲንግ ማናጀር ወ/ሮ ዳርቻ መኮንንና  የኩባንያው ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተር አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በጋራ በመሆን ነው፡፡
ኩባንያችን  ጥራታቸውን የጠበቁ የደንበኞች ምርቶችን በማቅረብ ይታወቃል ያሉት ግሩፕ ማርኬቲንግ ማናጀሯ ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፤ “ከምርት እስከ ገበታ ከኢትዮጵያውያን ለኢትዮጵያውያን የሚል መርህ ነው የምንከተለው” ብለዋል፡፡
“ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ማቅረብ ዋና ዓላማችን ነው” ሲሉም አክለዋል፤ወ/ሮ ዳርቻ መኮንን፡፡ ባለፉት ዓመታት ኩባንያቸው በስኬትና በዕድገት ጎዳና ላይ ሲጓዝ መዝለቁን የገለጹት ግሩፕ ማኑፋክቸሪንግ ዳይሬክተሩ አቶ ኢዩኤል ሸዋንግዛው በበኩላቸው፤ በእነዚህ ዓመታት የተደረጉ የፋብሪካና ማምረቻ ማስፋፊያዎች፣ የተገነቡ አዲስ ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም ራሳቸው ማምረት የጀመሯቸው ለድርጅቱ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎችን በዝርዝር አብራርተዋል፡፡
54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ በቅርቡ ኖርፈንድ ከተባለው ታዳጊ አገሮች ላይ አተኩሮ የሚሰራ የኖርዌይ ኢንቨስትመንት ፈንድ የ21 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ኢንቨስትመንት አዲስ የኤክስፖርት ፋብሪካ ለመገንባትና ከገበሬዎች ጋር በቀጥታ አብሮ በመሥራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ አቅሙን ለማስፋት እንዲሁም  በኢትዮጵያ ለምግብነት የሚውል የዘይት ምርትን ለማሳደግ እንደሚውል ተጠቁሟል፡፡
 “በዚህ ኢንቨስትመንትና ተጨማሪ የንግድ ማስፋፊያ ዕቅዶች ምክንያት፣ 54 ኤፍ.ኤም.ሲ.ጂ  የኮርፖሬት ስያሜውን ወደ ሳማኑ መቀየሩን በደስታ ያበስራል” ብሏል፤ ኩባንያው  ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ፡፡ ‘ሳማኑ ፕራውድሊ ኢትዮጵያን - ሳማኑ በኩራት የኢትዮጵያውያን’ የሚል ነው አዲሱ ሙሉ ስያሜ፡፡ የሳማኑ አርማ መነሻ ተደርጎ የተወሰደው ከህይወት ምንጭ ‘አባይ ወንዝ’ እና ሣ ከሚለው የአማርኛ ፊደል መሆኑን የሚያብራራው መግለጫው፤ዲዛይኑ የሳማኑን ኢትዮጵያዊ መሰረት ለማጠናከር ያለመ ነው ይላል -ይህም ከፍተኛ ጥራት ያለው የፍጆታ እቃዎችን በማምረት ግንባር ቀደም ኢትዮጵያዊ በመሆን ለዕድገትና መስፋፋት ያለውን ጠኝካራ ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ በመግለጽ፡፡
የሳማኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚ/ር ጆአኪም ኢቡዌት በሰጡት መግለጫ፤ “ስለመጪው ጊዜ በጣም ደስተኞች ነን፤ ይህ አገሪቱ ያላትን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብትና ተሰጥኦ በመጠቀም የኢትዮጵያውያንን ህይወትና ኑሮ ለማሻሻል ራዕያችንን የምናጎለብትበት መንገድ ነው” ብለዋል፡፡
ከውጭ የተገኘውን ኢንቨስትመንትም በተመለከተ ሲናገሩ፤”አዲሱና ከፍተኛው የውጭ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለንን ቆይታ በማጠናከር ለሰፋፊው የልማት መንገድ አስተዋጽኦ እንድናደርግ ያግዘናል፡፡ ቀዳሚ ሂደቶችን ወደ ኋላ በማቀናጀት  የኢትዮጵያን ግብርና በሚያዳብርበት ወቅት የተዋቀረ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ለማምረት ያስችላል፡፡” በማለት አብራርተዋል፡፡“ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እያደረግንና የማምረት አቅማችንን እያሰፋን ባለንበት በዚህ ወቅት የኩባንያችንን ስያሜና ምልክት መቀየር ለድርጅታችን ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ “ግባችን በአገር ውስጥ የሚመረቱና የኢትዮጵያ ኩራት የሚሆኑ ከፍተኛ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ማቅረብ ነው” ብለዋል፡፡



የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕር ዳር፣ በጅግጅጋ እና በሃዋሳ ከተሞች ያካሄደውን ግልጽ የምርመራ መድረክ (National Inquiry/Public Inquiry) ተከትሎ፣ በአዳማ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አራተኛውን ግልጽ የምርመራ መድረክ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡
በመድረኩም በተለይ የዘፈቀደ እስርን፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስርና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎችና ምስክሮች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እንዲሁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾችን ማዳመጡ ተጠቁሟል፡፡
 ለአብነት ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል:- ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትእዛዝ አለማክበር ይገኙበታል ተብሏል።
በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበርና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል እንደሚገኙበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡
የግልጽ ምርመራ መድረክ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡
“አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፤ የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል፡፡” ብሏል፡፡
 ለግልጽ ምርመራው በኦሮሚያ ክልል ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር ወይም የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ፣ መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገ Oromo Legacy Leadership & Advocacy Association/OLLAA የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየበኩላቸውን መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ማስገባታቸው የታወቀ ሲሆን፤ በግልጽ ምርመራ መድረኩም ላይ በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዋና ዋና ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል ተብሏል፡፡
ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተን ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ አቅርበው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡
 “በኦሮሚያ ክልልና በተለያዩ ዞኖች በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽንና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ለቀረቡት አቤቱታዎችና ተፈጽመዋል ለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም የፍትሕና  የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ለመብት ጥሰቶቹ መነሻ ምክንያት የሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል::” ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው፡፡በአዳማ ከተማ የተካሄደውን ግልጽ ምርመራ መድረክ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እና የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ መርተውታል፡፡
የዝግጅቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ባደረጉት ንግግር፤ “በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መቻላቸው እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በሁሉም አካላት በኩል ለመደጋገፍ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚያበረታታ ነው፡፡” ብለዋል፡፡


ግሪን ቴክ ፤ላለፉት ሦስት ወራት በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት  ያሰለጠናቸውን 25 ተማሪዎች ባለፈው ማክሰኞ ፣ ቃሊቲ ቶታል በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መ/ቤት አስመረቀ፡፡
25ቱ ተመራቂዎች  በዘርፉ የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ሲሆኑ ፤ሥልጠናው የተሰጠው ከኤስኦኤስ የህጻናት መንደር ጋር በመተባበር  ነው  ተብሏል፡፡
ለተመራቂዎቹ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የግሪን ቴክ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ኢንጂነር ቅደም ተስፋዬ፤” በዘርፉ ተቀጣሪዎች ሳይሆን ሥራ ፈጣሪዎች እንድትሆኑ ነው የምንፈልገው” ብለዋል፡፡ሰልጣኞቹ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት የአምስት ቀናት የሥራ ፈጣሪነት (entrepreneurship) ሥልጠና እንደሚሰጣቸውም ተነግሯል፡፡
በአገራችን  በኤሌክትሪክ መኪኖች ቴክኒሽያንነት ሥልጠና የሚሰጥ ተቋም እንደሌለ የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ያሁኖቹ ተመራቂዎች የመጀመሪያዎቹ ሰልጣኞች ናቸው ብለዋል፡፡በዕለቱ የተመረቁት ተማሪዎች በኤሌክትሪካልና መካኒካል ኢንጂነሪንግ በድግሪና በማስተርስ ድግሪ ደረጃ ትምህርት የወሰዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ግሪን ቴክ በአጠቃላይ 300 ወጣቶችን በኤሌክትሪክ መኪና ቴክኒሽያንነት  ለማሰልጠን ያቀደ ሲሆን፤ 27 ወጣቶች በሥልጠና ሂደት ላይ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
ግሪን ቴክ ኢትዮጵያ፤ በአገራችን የመንገድ ትራንስፖርት ዘርፍ ፈር ቀዳጅ የሆኑና ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት የሚሰጡ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሪክና በሶላር ቻርጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለተጠቃሚው ህብረተሰብ እያቀረበ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ይህ መጽሐፍ አማርኛ ምን ያህል ባለጸጋ እንደሆነ ፣ በአንጻሩ ሥነ-አመክንዮ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ሥራ ነው :: በአማርኛ ቋንቋ ከተጻፉ ፣ ትውልድን ብዙ ከጠቀሙ አንጋፋ መጻሕፍት መካከል ይህ አንዱ ነው የሚል እምነት አለኝ :: "
ዓለሙ ፊጤ ( ዶክተር )
University Of Michigan America
ስለመጽሐፉ አስተያየት የሰጡ

 ሸበተ መሰለኝ!
               (በድሉ ዋቅጅራ)


        ሸበተ መሰለኝ፣ እውቀትም አረጀ፤
ጡት ተጣባውና፤
አበልጅ ሆኑና፤
ከድንቁርና ጋር፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
ብርሃኑ ጠፋ፣ አይኑ ደነገዘ፤
መቅኒው በረዶ ሆነ፣ በቁሙ ፈዘዘ፡፡
ይኽው እውቀት ጃጅቶ፤
ከድንቁርና ላይ፣ በሊዝ ቦታ ገዝቶ፤
ጎጆ ቀለሰና፣ መስሎ ጎረቤቱን፤
ፀሐዩን ይሞቃል፣ እያሻሸ ሪዙን፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
‹‹የት ይደርሳል›› ስንል በወጣትነቱ፤
እዚህ እቅርባችን፣ ይኽው ተመልከቱ፤
እውቀት ተመፃድቆ፤
ማወቁን አድምቆ፤
ህፀፁን ደብቆ፤
ከድንቁርና ጋር፣ ከጠላቱ ታርቆ፡፡
ደባልነት ገባ፣ አብሮ ቤት ቀለሰ፤
አንዱ ሲገነባ፣ አንዱ እያፈረሰ፡፡
ውሃ እያፈሱ፤
ጤፍ እየቆጠሩ፤
ውሃ እየወቀጡ፤
ባንድ ተቀመጡ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
የሀገር ጥሪት ነጥፎ፤
የሕዝብ ሀብት ባክኖ፤
የእድሜ ሻማ ነዶ፤
ስልጣኔ ብሎ፤ ፈረንጅ ሀገር ሄዶ፤
ሩቅ… ባህር ማዶ፤
የተገኘን እውቀት፤
ወይም
እዚሁ ሀገር ውስጥ፣ ኮሌጅ ተኮልጆ፤
የተገኘው እውቀት፤
ይኽው ተመልከቱ…
ከውጭ ሲመለስ፣ ከኮሌጅ ሲወጣ፤
ቦቃ በግ ሰውቶ፤
ዛፍ ቂቤ ቀብቶ፤
ንፍሮውን በትኖ፣ እጣኑን አጢሶ፤
ይኽው ተመልሶ፣
ተንበርክኮ ሽቅብ፣ ቱፍታ ይቀበላል፤
መርፌውን ሰክቶ፤
ከድንቁርና ጋር እውቀት ይማማላል፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር!
እውቀትም እንደ ሰው፣
ያለ እድሜው አረጀ፤
ከጠላቱ ጋራ፣ በወግ ተወዳጀ፡፡
አያት ድንቁርና፣ ለምለም አስጨብጠው፤
ለጋ የጊደር ቂቤ፣ ግንባሩን ቀብተው፤
በአምሳላቸው ቀርጸው፣
አውራ ጣት አጠቡት፡፡
ልጃቸውም ሆነ፣ አባት አያት ሆኑት፡፡
ከዚያማ ጋለቡት፣
ሉጋም አበጅተው፣ ለህሊናው መግቻ፤
ለራዕዩ መቀጨት፣ ለህልማቸው መፍቻ፡፡
ለእኩይ እጣ ብሎት፣
 እውቀትም አርጅቶ፤
ይኸው ተመልከቱ፤ ደጅ ተጎልቶ፤
ከድንቁርና ጋር፣ እሳት እየሞቀ፣
እውቀት ተጃጅሎ፡፡
ለአድባር ይሰዋል፤
ለአውልያ ይሰግዳል፤
ያማል፣ ያማል፣ ያማል፣
እውቀት ተጃጅሎ፤
የኦክስፎርድ ዲግሪ፤
ያለማያን ካባ፣ ግርግዳው ላይ ሰቅሎ፡፡
ይብላኝ ለዚች ሀገር!
ይብላኝ ለኢትዮጵያ!
እውቀት ድንቁርና ለተወዳጁባት፣
አንዱ ሲገነባ፣ ሌላው ለሚንዳት፡፡
መጥኔ ለዚች ሀገር፡፡
(1989- ፍካት ናፋቂዎች)




 ቢዝነስ አዋቂው ዊሊያም ሪግሊ

                  ለ8.5 ሚ. አሜሪካውያን መስቲካ በነጻ አስቀምሷል
                     ዋሲሁን ተስፋዬ


       ዊሊየም ሪግሊ፤ በአሜሪካን ፔንስልቫንያ የተወለደና ፡  እስካሁንም በአለም ላይ ቁጥር አንድ ተሻጭ ማስቲካዎች መሀከል አንዱ የሆነው የሪግሊ  ባለቤት ነው ።
በልጅነቱ በአባቱ የሳሙና ፋብሪካ ውስጥ በትርፍ ጊዜው ይሰራ ነበር ፡ እድሜው 13 አመት ሲሞላ ደግሞ ፡ በአባቱ ኩባንያ የሚመረተውን ሳሙና እየተረከበ መሸጥ ጀመረ ። በዚህ ሁኔታ የተወሰኑ አመታት እንደሰራ   በወቅቱ የነበሩትን የሳሙና ፋብሪካዎች በልጦ ለመገኘት አንድ ዘዴ ማሰብ ጀመረ ።
ይህ ዘዴ አነስ ያለ የቤኪንግ ፓውደር መስሪያ ማሽን በመግዛትና በማምረት ፡ የሱን ሳሙና ለሚገዙ ሰዎች ፡ አንድ ቤኪንግ ፓውደር በነጻ መስጠት ነው ።
 በዚህ መልኩ ሳሙናውን መሸጥ ሲጀምር፣ የሳሙናው ገበያ በሚገርም ሁኔታ ጨመረ ። ሆኖም  ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ፣ ሰዎች ሳሙናውን የሚገዙት በስጦታ መልክ፣ በነፃ ለሚያገኙት ቤኪንግ ፓውደር ሲሉ እንደሆነ አወቀ ።
ልክ ይህን እንደተረዳ፣ ወዲያውኑ ግዙፍ ማሽን ገዝቶ ፡ በሰው ዘንድ ተወዳጅ መሆን የጀመረውን የቤኪንግ ፓውደር ምርት በሰፊው ማቅረብ ጀመረ ።
በወቅቱ ቤኪንግ ፓውደር የሚያመርቱ ብዛት ያላቸው ካምፓኒዎች ስለነበሩም፣ የገበያ ፉክክሩን ለማሸነፍ ፡ ማስቲካ የሚያመርት ማሽን ገዝቶ፣ ቤኪንግ ፓውደር ለሚገዛ ሰው  አንድ ማስቲካ  መስጠት ሲጀምር. ..በነጻ ለሚሰጠው ሪግሊ ማስቲካ ሲባል፣ ቤኪንግ ፓውደሩ እንደ ጉድ መሸጥ ጀመረ ። ቢዝነስ አዋቂው ዊሊያም ሪግሊ ይህን እንደተረዳ። የቤኪንግ ፓውደር ማምረቱን በመተው፣ ሙሉ ለሙሉ ማስቲካ በማምረት ስራ ውስጥ ገባ። ምርቱ ተወዳጅ ሆኖ በመላው አሜሪካ ቆይቶም ፡ በመላው አለም ታዋቂ ብራንድ ሆነ።
እንግዲህ፤ ከላይ ባየነው አጋጣሚ ምክንያት የተፈጠረው ሪግሊ፣ ከአመታት በኋላ ዛሬ ላይ አመታዊ ሽያጩ ከሁለት ቢሊየን ዶላር በላይ አልፏል።
 ቢዝነስህን ወይም  ሥራህን አሻሽለህ ለመስራት ባሰብክ ቁጥር፣ ሥራህ  ወይም ቢዝነስህ  ያሻሽልሀል፡፡ .እዚህ ላይ ሳንጠቅስ የማናልፈው፣ ዊሊየም ሪግሊ፣ ይህን የማስቲካ ካምፓኒ ሲጀምር ፡ ማስቲካውን ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት ዘዴ እስካሁንም ይወራለታል ።
 ይህ ሰው ማስቲካ ማምረቱን በሰፊው እንደጀመረ ሰሞን  ....ለ8.5 ሚሊዮን አሜሪካውያን ሪግሊ ማስቲካን እንዲቀምሱ በነጻ ልኮላቸው ነበር ። ይህ የማስተዋወቅ ዘዴውም  ውጤታማ የሆነው ወዲያውኑ ነበር ።

____________________________________________

                      እያረሩ መሳቅ--?

 
         “… በነዳጅ ማደያ ዙሪያ ያለው የመኪና ሰልፍ ያስደነግጣል። ወደ አንዱ ባለ መኪና ጠጋ አልኩና ጠየቅኩት...
“ምነው ነዳጅ የለም እንዴ?”
“ኧረ አለ”
“ታዲያ ይኼ ሁሉ ሰልፍ ምንድነው?”
“የነዳጅ  ቀጂው ስልክ ዘጋበት”
“ምን ዘጋበት?”
“የስልኩ ቻርጅ አለቀበት” ሳቄ ደርሶ ድቅን አለ።
ይኸውልህ እንግዲህ፣ ያልተጠና አሰራር እንዲህ ያለ ችግር ይፈጥራል። የነዳጅ ቀጂ ስልክ ቻርጅ ማለቅም እንቅስቃሴ ይገድባል?
(Jony Zewde በገፃቸው ካሰፈሩት)




        ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነሕ በመደመር አፍሪካ የስነ ጥበብ ስፍራ ታላቅ አውደ ርዕይ “Reflections on the I Ching በሚል  ርዕስ አዘጋጅቷል። ከ70 በላይ ስዕሎች ለህዝብ እይታ ይቀርባሉ ። ለስነጥበብ ስራዎቹ  “The Complete I Ching : The Definitive Translation by Taoist Master Alfred Huang” የተባለው መፅሐፍ  መነሻ ሆኗል።
ሰዓሊ ዳዊት መፅሐፉን በመጥቀስ እንደገለፀዉ፤ ኤግዚብሽኑ “የገነት፤ የመሬትና የሰው ልጅ ትልቅነት...ገነት፤ መሬትና የሰው ልጅ የሚግባቡበት አስተሳሰብ “ ይንፀባረቅበታል። ብሏል፡የሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ Reflections on the I Ching ታላቅ  አውደርዕይ፣  በመደመር አፍሪካ የስነጥበብ ስፍራ ሰኞ ሚያዝያ 23 ላይ በይፋ ተመርቆ በመከፈት፣ በቋሚነት ጎብኝዎችን የሚያስተናግድ ይሆናል። በስነጥበብ ስፍራው በሚገኘው የከተማችን ግዙፍ የስዕል አዳራሽ Yellow hall እና በአስደናቂው የስነጥበብ ዱንካን ubntu dome ከ70 በላይ ስዕሎች ይቀርባሉ ።ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ በስነጥበብ ሙያው ከ28 ዓመታት በላይ ሰርቷል።  አፈርን ቀለም ባደረገ ምርምርና ጥናትም ተሳክቶለታል። ለስዕል ስራዎቹ ከኢትዮጵያ የተሰበሰቡ አፈርና ድንጋይ ተፈጭተው ቀለማት ሆነዋል። ሰዓሊ ዳዊት ሙሉነህ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ‹‹አለ የስነጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት›› በግራፊክ አርት በ1987 ዓ.ም በዲግሪ የክብር ተመራቂ ነው፡፡
 በአዲስ አበባ ከተማ  የስዕል ስቱድዮዎችን በግል እና በቡድን መስርቶ በመንቀሳቀስ ይታወቃል፡፡  ከ25 በላይ ኤግዚብሽኖችን  ለዕይታ አብቅቷል።



Saturday, 29 April 2023 18:23

የብልህነት መንገድ

  ምንም ነገር ጥሩም  ሁን መጥፎ እስከ ጽንፍ ድረስ አትውሰደው አንድ ብልህ ይሄን ጉዳይ በአንዲት አባባል ቀንብቦ አስቀምጧታል። ጽንፍ የወጣ ፍትህ ኢ-ፍትሐዊነት ይሆናል። ብርቱካንን አለአግባብ ብትጨምቀው ጭማቂው መራራ ይሆናል። ደስታም እንኳ ቢሆን መረኑን እስኪለቅ ድረስ መሆን የለበትም። ላምን አለቅጥ ማለብ ደም ያሳዣታል።
ለራስህ ትንሽ ስህተት ፍቀድለት እንደዚህ አይነት ግድየለሽነት በአብዛኛው ችሎታን ደግፎ ይገኛል። ቅናት የራሱ አይነት የተለየ ውግዘት አለው። መታወቅህ በጨመረ መጠን ወንጀልህ ይጨምራል። አንድ ነገር በሃጥያት አለመውደቅ መልሶ ራሱን በሀጥያተኛነት ይስከሰስዋል። ጽሩሕ በመሆኑ ብቻ ይወነጀላል። አርጎስ ይሆናል። ሂስ እንደ በረድ በነጻው ውስጥ ነቁጥን በመፈለግ፤ እንደ መብረቅ የተራራውን ጫፍ ትመታለች። የሆሜርን የጭንቅላት ውዝወዛ፣ ለጠላት መርዝ ማርከሻ እንዲሆን ፍቀድለት። ስለዚህ የማስተዋል ሳይሆን ያለማወቅ ትንሽ ዝንጉነትን ለጥላቻ ማብረጃ ፍቀድ።
ጠላቶችህን ተጠቀምባቸው ነገሮችን በሚቆርጠው  ስለታቸው አትያዝ፤ በአፎታቸው እንጂ። በተለይ ከጠላቶችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ይህ ህግ ከጉዳት ታደግሃል። አዋቂ ከጠላቶቹ ሚጠቀመውን ህል ነፍላላ ከወዳጆቹ አይጠቀምም። የጠላቶችህ  ክፋት የማትወጣውን የችግር ተራራን ወደ ሜዳ የመዳመጥ ሃይል አለው። ብዙዎች በገዛ ጠላቶቻቸው ታላቅነት እንደ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። ቁልምጫ ቆሻሻን ስለሚደብቅ ከጥላቻ የባሰ መጥፎ ነገር  ነው። ብልህ ክፋትን ወደ ጥሩ መስታወት ይቀይራል።
የረጅም ህይወት ምስጢር ጥሩ ህይወት መምራ ነው። ሁለት ነገሮች ህይወትን ወደ ፍጻሜዋ ያዳፏታል። ከንቱነት እና ሞራለ-ቢስነት።  አንዳንድ ብልሃቱ ስለሌላቸው ብቻ ህይወትን ያጧታል፤ሌሎች ደግሙ ፈቃዱ ስለሌላቸው። ሰናይነት ለህይወት ሽልማት እንደሆነ ሁሉ ሃኬትም ቅጣቷ ነው። ወደ ሃኬት ፊቱን ለማዞር የቸኮለ ሁሉ ሁለት ሞትን ይሞታል። የመንፈስ ሐቀኝነት ወደ ስጋ ይሰርጻል። ህይወት በቆይታዋ ድምቀት  ብቻም አይደል ጥሩ እምትባለው፤ በቆይታዋ ርዝመት ጭምር እንጂ።
እያመነታኽ አትስራ ጠርጣራ  ህሊና ለሁሉም ግልጽ ነው። በተለይ ለባላንጣ። በተጋጋለው ግርግር መሃል ብያኔኸ የሚመስለውን ፍርድ ካላቀበለህ፣ ኋላ ነገሮች ሲረጋጉ ይክስሃል። ጥንቃቄ የሚያሻው አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥም ምንም አለመስራቱ ይሻላል። ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ይሁንታን አይቀበልም። ሁሌም  በምክንያታዊነት የቀትር ብርሃን ነው የሚጓዘው። ጅማሮህ ላይ ችግር ካለ አፈጻጸሙ እንዴት ሊያምር ይችላል? በመጀመሪያ ጥሩ የመሰለህ ውሳኔ ውዳኤው ካላማረ፣ ተጠራጥረህበት የነበረውስ እንዴት ይከፋ ይሆን?
 እነሆ በሁሉም ዘርፍ የላቀ ጥበብ የባህርይ እና የንግግር ቀዳሚውና ዋነኛው ህግ ነው እላለሁ። በተለይ በስልጣን መሰላል ከፍ እያልህ በሄድህ ቁጥር ደግሞ አስፈላጊነቱ እየጨመረ ይመጣል። የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል ጥበብ ከጆንያ ሙሉ ብርታት ትልቃለች። ይሄ ብዙም ባይመሰገንም፣ በተፈጥሮ የተረጋገጠ ምንገድ ነው። የጥበበኛነት ክብር የዝናዎች ሁሉ የመጨረሻ ድል ነው። ብልሆችን ማርካት ከቻልክ በቂ ነው። ብያኔያቸው የስሜት ናሙና ስለሆነ።
ሁለገብ ሰው የፈርጀ ብዙ ብቃቶች ባለቤት  የሆነ ሰው፤ ብቻውን ከብዙ ሰዎች እኩል ነው። ይህን ፍስሃ ለባልንጀሮቹ በማጋራት ህይወታቸውን አበልጽጎ አስደሳች ያደርጋታል። ማለቂያ ባላቸው ጉዳዮች ያለ ልዩነት፣ የህይወት  ትፍስሕት ነው። ተፈጥሮ ሰውን በራሷ ረቂቅ አምሳያ እስካበጀችው ድረስ ጥበብ የሰው ልጅን ምርጫና ብልሃት በማሰልጠን፣ በውስጡ ደቂቅ ህዋን  እንድትፈጥር ፍቀድላት።
የችሎታህን መጠን አታሳይ ብልህ በሁሉ ዘንድ መከበርን ከመረጠ የእውቀቱንና  የችሎታውን ትግል አያሳይም። እንድታውቀው እንጂ እንድትረዳው አይፈቅድልህም።
ማንም የችሎታውን መጠን ማወቅ የለበትም። ካወቀ ይከፋል። ማንም ጥልቀቱን ለክቶት አያውቅም።
ምክንያቱም  ስለሱ ችሎታ የሚሰነዘሩ ግምቶችና ጥርጣሬዎች ካለው ከትክክለኛው ችሎታ በላይ ክብርን ያቀዳጁታልና።
ተስፋ አንብረው፤ እያነሳሳህ አቆየው። ቃል በመግባትና በድርጊት ተስጥኦህን አለምልም። ያለህን ሁሉ አንጠፍጥፈኽ በአንድ ጉዳይ ላይ ማዋል የለብህም። ትልቁ ታክቲክ የጥንካሬና የእውቀት አጠቃቀምህን እየመጠንክ ወደ ስኬት ማምራት ነው።
አስተውሎት የምክንያታዊነት አክሊል ነው። የጥንቃቄ መሰረት። በዚህች ዘዴ ብቻ ስኬት በትንሽ ወጪ ይገኛል። የመጀመሪያው እና ጥሩው ችሎታ እስከሆነ ድረስ በጸሎትም ቢሆን መገኘት አለበት። የሰማያት ስጦታ የሆነው አስተውሎት፤ እጅግ በጣም ጠቃሚው ጋሻ ሲሆን፤ ማመዛዘንህን ማጣት ትልቁ ሽንፈት ሊባል ይችላል። ጉድለቱ ከርቀት ይታያል። የህይወት ሁሉም ትግበራዎች በሱ ተጽዕኖ ስለ የወደቁ  የሱንም ይሁንታ የሚሹ እስከሆኑ ድረስ ሁሉም ነገር አስተውሎት ጋር  ተጓድኖ መሄድ አለበት። አስተውሎት በተፈጥሮው ምክንያታዊነት ጋር ተቀላቅሎ ለሚገኝ እርግጠኛ አቅጣጫ የማላት ባህርይ አለው። ዝናን አግኛት አኑራትም… ታዋቂነትን ማግኘት ውድ ነው። ከታላቅነት ስለሚገኝ።
 ተራ የሆኑ ነገሮች በብዛት የሚገኙትን ያህል ዝና ደግሞ ብርቅ ናት። አንዴ ከተገኘች ለመጠበቅ ትቀላለች።
ብዙ ግዴታዎችን  ትፈጥራለች። ውጤትንም ታገኛለች። ዝና በፍጽምነትዋ ዋና በተገኘችበት የስራ ዘርፍ የተነሳ ወደ ክብር ሰለምትቀየር ዘውዳዊነትን ትቀዳጃለች። ነገር ግን በጽኑ መሰረት ላይ የተገነባ ዝና ብቻ ነው ዘላቂ የሚሆነው።
ምኞትህን ደብቅ፤ ጥልቅ ስሜቶች የነፍስ መግቢያ በሮች ናቸው። ተግባራዊው እውቀት እነሱን መደበቅ ያጠቃልላል። የያዘውን ካርታ  ለእይታ አጋልጦ የሚጫወት የመበላት እድል አለው። ለተጠያቂዎች የማወቅ ፍላጎት ጥንቃቄ መደረግ አለበት። እንደ ዱር ድመት ካተኮሩ አይጦች፤ ከኩትል አሳ ቀለም ሁሉ መከለል አለበት። ፍላጎቶችህን በቅድሚያ በፍጥጫም ይሁን በቁልምጫ እንዳይገመቱ ደብቃቸው።
እውነታና ገጽታ ነገሮች በምንነታቸው ብቻ ተቀባይትን አያገኙም ፤በገጽታቸውም ጭምር  እንጂ። ጥቂቶች ናቸው ወደ ውስጥ የሚያጮልቁት። አብዛኞች በገጽታ ብቻ ይደሰታሉ። ገጽታህ የተሳሳተ ከመሰለ ትክክል መሆን ብቻውን በቂ አይደለም።  
***
(“ከየግሬሽያን ባልታሳር የብልህነት መንገድ” የተቀነጨበ)


  ‹‹ሁሉንም ሞክሩ፤የተሻለውን ያዙ›› የሚለውን አባባል፣ ቢያንስ እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርስቲ (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ገብቶ የተማረ ተማሪ ያውቀዋል፡፡ በየድግሪው ላይ የተፃፈ መሪ ቃል እና ጥቅስ ነው፡፡ በህይወታችን ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶች ይገጥሙናል፤ እና በየፈርጅ በየፈርጃቸው እየሞከርን፣ እየወደቅን እየተነሳን፤ በጎና ሰናይ የሆኑትን እየለየን እና እያጠናከርን፤ የሚበጀንን መያዝ አለብን፤ ለማለት ነው፡፡ በእርግጥም በየአንዳንዱ ሙከራ ወቅት፤ እንቅፋት፣ ችግርና መከራ መኖሩ አይቀሬ ነው ለማለት ነው፡፡ ለዚህ አብነት ይሆነን ዘንድ የሚከተለውን የአበው ወግ እንይ፡፡
ሁለት ደገኛ ገበሬዎች ኑሮ አልገፋ ብሎ ቁም ስቅላቸውን ያሳያቸዋል፡፡ አንዴ ዝናቡ እንቢ ይላል፡፡ አንዴ በሬዎቹ ይለግማሉ፡፡ አንዴ ደቦ ወጪዎች አይመቻቸውም፡፡ አንዴ ደግሞ ሰብሉን ተባይ ይፈጀዋል፡፡ በእጅጉ ይቸገራሉ፡፡ አዝመራውም አልሰምር ይላል፡፡
አንደኛው ገበሬ አንድ ቀን መላ ዘየደ፡፡ ንግድ መጀመር አለብኝ ብሎ ወሰነና፣ አዲስ ሙከራ ጀመረ፡፡ በሬዎቹን ሁሉ ሸጠ፡፡ የዘር እህሉንም ከሰቀለበት አውርዶ፣ ለቤት የሚፈልገውን ያህል አስቀረና አውጥቶ ሸጠ፡፡ ከዚያም ባገኘው ገንዘብ ወደ ቆላ ወርዶ ለማረሻ ለዶማና ለማጭድ ወዘተ--መስሪያ የሚሆን ብረታ ብረት ገዛ፡፡ የገዛውንም ብረታ ብረት ወስዶ ለቸገረው ደገኛ ህዝብ ቸበቸበው፡፡ ቀስ በቀስ ኑሮው ተለወጠ፡፡ አዱኛም አገኘ፡፡ ለውጡ በቀዬውም በአገሩም ተወራ፤ ተሰማ፡፡ ሃብቱ ጣራ ነካ፡፡ ይጭነው አጋስስ ይለጉመው ፈረስ በደጅ በግቢው ሞላለት፡፡
‹‹አያ፤ እንዲህ በአንዴ ዲታ የሆንከው ምን ዘዴ ከውነህ ነው ጃል?›› ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
ያም የድሮ ገበሬ፣ የዛሬ ነጋዴ፤ የተሰማራበትን ሙያ ያስረዳዋል፡፡ ወደህ ስራ ቢገባም በቀላሉ ካብታም እንደሚሆን ይገልፅለታል፡፡
ሁለተኛው ገበሬ፤ ሳይውል ሳያድር ምክሩን ተቀብሎ፣ በስራ ላይ አዋለና፣ ያለ የሌለ ንብረቱን ወደ ገንዘብ ለወጠ፡፡ ንግድ ጀመረ፡፡
ቆላ ወረደ፡፡ ያገሩን ብረታ ብረት ገዛ፡፡ ተሸከመና ሽቅብ ወደ ደጋ መንገድ ጀመረ፡፡ ሆኖም፤ ገና ዳገቱን አጋምሶ ሳያበቃ በተሸከመው ብረታ ብረት ክብደት ሳቢያ ወገቡም ጉልበቱም ከዳውና ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ አወዳደቁም አጉል ነበረና አረፋ አስደፈቀው ፡፡
አንድ መንገደኛ የሰፈር ሰው ድንገት ሲያልፍ አይቶት ኖሮ ወደሱ ቀርቦ፤
‹‹አያ እገሌ፤ምን ሆነህ ነው?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ገበሬውም፤ ‹‹አይ ወዳጄ፤ ያ ጎረቤቴ አያ እገሌ የሰራኝን ስራ ለጠላት አይስጥ!›› አለና መለሰለት፡፡
‹‹ምን አደረገህ? የልብ ወዳጁ እማይደለህ እንዴ? በሞቴ ንገረኝ፤ ምን አደረገህ?››
‹‹ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳነግረኝ፤ ይሄው ለዚህ ዳረገኝ!!›› አለው፡፡
***
ሁሉም ስራ ችግሩ የሚታወቀው ሲሞከር ብቻ ነው፡፡ ንግዱ፣ትምህርቱ፣ ልማቱ፣አስተዳደሩ፣ ፓርላማዊ ስነስርዓቱ፣ ምርጫው፣ ፍትሃዊ ባህሉ ወዘተ ሁሉም ተሞክሮ፣ ተሰርቶ ታይቶ ነው፡፡ ካላዋጣ ደግሞ ካፈርኩ አይመልሰኝ ሳይሉ፣ የማይሰራውን ፈጥኖ ጥሎ ሌላ መንገድ መፈለግ ግድ ነው፡፡ ስህተትንም በወቅቱ አርሞ፣ ሰናዩን አለምልሞ፣ ጠንካራውን አጎልብቶ፣ መያዝ ደግ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ከአምናው ምን ተምረናል? ለነገስ ምን ጨብጠናል? የማለት ድፍረትና ግልፅነት እንዲኖረን ያሻል፡፡
አዲስ ፈር ለመቅደድ መስዋዕትን መክፈል፣ ያልተሞከረውን መሞከር ያልታየውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ትላንት በሄድንበት መንገድ ዛሬም ብንመላለስበት ኮቴአችንን ከመጨረስ በቀር፣ ወደላቀ ግብ መድረስ እርም ነው፡፡ ትላንት በተሟገትንበት፣ በተዛለፍንበት፣ ላንደማመጥ በተጯጯህንበት ሸንጎ፣ ዛሬም ያንኑ እሪታና ጩኸት፣ ያንኑ ችኮላና ድንፋታ፣ ያንኑ እርግማንና ውግዘት ብናላዝን ብናስተጋባበት፤ ድምፃችን ከመዛሉ፤ ጉዟችን ከመሰናከሉ በቀር ብዙ አንራመድም፡፡ ከመበቃቀል መተራረም፣ ቂም ከማርገዝ የቂምን ሥነ-ነገር መርምሮ ለመንቀል መጣጣር ዋና ጉዳይ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡
ከቶውንም ትላንት እጅግ ጨለማ የመሰለንን ንፍቀ ክበብ፣ ዛሬ በመጠኑ እንኳን ደብዛዛ ውጋጋን ካየንበት ውጋጋኑን ለማስፋት እንጂ ‹‹ይሄውላችሁ፣ ዛሬም በደምብ አላነጉትም!›› እያልን ቡራ-ከረዩ ብንል አንድም የለውጥን አዝጋሚ ሂደት መካድ፣ አንድም ያ ውጋጋን ብሩህ ፀዳል እንዳያገኝ የእኛን አስተዋፅዖ መንፈግ ይሆናል፡፡ ባለፈው፣ ባልሞከርነው ነገር ሳቢያ ባጠፋነው ጊዜ ስንፀፀት አዲስ ሙከራ የምናደርግበትን ሌላ ውድ ጊዜአችንን እንዳናጨልም መጠንቀቅ ይበጃል፡፡ ሀገራችን አሁን ላለችበት ቦታ የበቃችውኮ በደጉም በክፉውም ሂደት ሳቢያ ነው፡፡ ማህበረሰባችንም እንደዚያው፡፡ ክፉውን አስወግዶ አንድ እርምጃ ለመራመድ ግን አዲስ ሙከራ እንደሚስፈልግ በመገንዘብ መንቀሳቀስ ይጠይቃል፡፡ የሌሎችን ድምፅ በትዕግስት መስማት፣ መንገዳቸውን በጥሞና ማየት፣ እኛ ያደረግንላቸውን ያህል እነሱም ያደርጉ ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትርፉን ብቻ አውቀን መከራውን ሳናውቅ ከተጓዝን ህልማችን ሁሉ ከላይ እንደተጠቀሰው ገበሬ ጉልበት አጥቶ ይወድቃል፡፡ የራእያችንም ክንፉ ከወዲሁ ይሰባበራል፡፡ ተስፋችን ሳይጫር ይከስማል፡፡ በዚህ መንገድ የሄዱ ቄሱም፣ ሼኪውም፣ ሹሙም ዜጋውም፣ የፖለቲካ ቡድኖቹም፣ መንግስታዊ የሆኑና ያልሆኑ ድርጅቶቹም አበክረው ማስተዋል ያለባቸው ቁምነገር ይሄ ይመስለናል፡፡
‹‹ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ፣ ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው እሚቆጨኝ››
ለማለት መቻል አለብን፤ እንደ ‹‹ቴዎድሮስ››፡፡ ያልሞከርነውን ለመሞከር ዝግጁነት ወሳኝ ነው!! የመንፈስም የአካልም፡፡
ከዚያ በኋላ፤ ‹‹ሁሉንም ሞክሩ፣ የተሻለውን ያዙ››! ለመባባል እንችላለን፡፡



Page 7 of 647