Administrator

Administrator

   - በሀገሪቱ ያሉ የግል ንግድ ተቋማት ዋንኛ ችግር የፀጥታና የደህንነት ስጋት ነው ተባለ
       - መንግስት የዜጎችን ደህንነት እንዲያስጠብቅ ጥሪ ቀርቧል


       በአገሪቱ ባሉ የግል የንግድ ተቋማት በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በዲጅታል ማርኬቲንግና በቱሪዝም ዘርፍ ላለው እንቅስቃሴ ዋንኛው ችግር የጸጥታና ደህንነት ስጋት  መሆኑንና ይህንንም ችግር ለመቅረፍ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባው ተገለጸ።
የኢትጵያ የንግድ ዘርፍ  ማህበራት ምክር ቤት፣ ከኢፌዲሪ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር፣ የፊታችን ማክሰኞ በስካይላይት ሆቴል የሚያካሂደውን የምክክር መድረክ አስመልክቶ የምክር ቤቱ ዋና ፀሃፊ አቶ ውቤ መንግስቱ ትላንት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ጸሃፊው በመግለጫቸው ላይ እንደተናገሩት፣ የምክክር መድረኩ በአመዛኙ በመንግስት ሊከናወኑ ይገባቸዋል በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ነው የተዘጋጀው ብለዋል።
ሚኒስትሮችና የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በሚሳተፉበት በዚህ የምክክር መድረክ፤ በሦስቱ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሚያጋጥሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች በስፋትና በጥልቀት እንደሚነሱ የገለጹት የም/ቤቱ ዋና ጸሃፊ፤ በተለይ የንግድ ዘርፉን እንቅስቃሴ እያወከና እያደናቀፈ የሚገኘው የጸጥታ ችግር ጉዳይ ዋና አጀንዳ ሆኖ ይነሳል ብለዋል።
በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በዋናነት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር፣ የግብይት ሰንሰለት መርዘም፣ ተቀናጅቶ የመሥራት ችግርና የመንገዶች ምቹ አለመሆን በመድረኩ ላይ እንደሚነሳ ነው የተገለጸው።
በኢ-ኮሜርስ ዘርፍ ከሁሉ አስቀድሞ መንግሥት ይህን ዘርፍ እንደ ዘርፍ ለአገር ይጠቅማል ብሎ ተቀብሎታል ወይ? የሚለውን ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ውቤ መንግስቱ፤ ኢኮሜርሱን ሊያስኬድ  የሚችል የተቀናጀ አሰራር (ስርዓት) ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
አንድ ነጋዴ በኢ-ኮሜርስ ፈቃድ ካገኘ በኋላ ለሁለት ዓመት የብቃት ማረጋገጫ ሳያገኝ የሚቆይበት ሁኔታ መኖሩንም በችግርነት አንስተዋል- ዋና ፀሃፊው። ካሉበት ችግሮች በዋነኝነት የሚጠቀሰው የኢንተርኔት መቆራረጥ መጥፋት ነው ያሉት ዋና ጸሃፊው፤ የግብይት ህግ ያልወጣለት መሆኑም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዲጂታል ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ነጋዴው ክፍያ ከፍሎ ደረሰኝ የሚያገኝበት አሰራር አለመኖሩም ሌላው መፍትሄ ሊፈለግለት የሚገባው ችግር መሆኑን አንስተዋል።
በቱሪዝም ዘርፉ ያሉት ጉልህ ችግሮች በምክክር መድረኩ ላይ እንደሚነሱ ያብራሩት የም/ቤቱ ዋና ጸሃፊ፤ በክልሎችና በፌደራሉ መንግስት መካከል የተቀናጀ አሰራር አለመኖሩ አንደኛው ችግር ነው ብለዋል።
ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ቱሪስቶችን ወደ አንዱ የአገሪቱ ክፍል አትሂዱ የሚለውን መግለጫ ወይም ማስጠንቀቂያ የሚሰጡት የውጭ አካላት መሆናቸውን ያነሱት ዋና ፀሃፊው፤ ከአገር ውስጥ መግለጫውን በተመለከተ ከአገር ውስጥ ማስተባበያ ወይም ማረምያ የሚሰጥ አካል አለመኖሩ ዘርፉን በእጅጉ እየጎዳው መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም ጠ/ሚኒስትሩ የሚመሩትና የቱሪዝምን እንቅስቃሴ የሚከታተል፣ ሚኒስትሮች በአባልነት የተካተቱበት የቱሪዝም ቦርድ ተቋቁሞ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ፀሃፊው፤ አሁን ግን ቦርዱ እንደሌለና ሥራውን እንዳቋረጠ ተናግረዋል።
አንድ ቱሪስት ወደ ክልል ሲገባ ከአስጎብኚ ድርጅቶች ክፍያ የሚቀበሉ በመንግሥት የተደራጁ ወጣቶች እንዳሉ የጠቆሙት የም/ቤቱ ዋና ጸሃፊ፤ ገንዘብ ይቀበላሉ ግን ደረሰኝ አይሰጡም፤ ይህም ዘርፉ እንዳያድግ እንቅፋት ይሆናል ብለዋል።
ማክሰኞ በስካይላይት ሆቴል እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የምክክር መድረክ ላይ በየዘርፉ ያሉ ችግሮች በጥልቀት ተነስተው የመፍትሄ ሃሳቦች የሚቀርቡበት ይሆናል ተብሏል።
በምክክር መድረኩ በፖለቲካና ስትራቴጂ የሚፈቱ ችግሮችን በመለየት ወደ መፍትሄ ለመግባትና በመንግስት ብቻ ሊፈቱ የሚችሉ እንደ ፀጥታ ችግር ያሉት ደግሞ መንግሥት ሃላፊነቱን በመወጣት እንዲፈታቸው እንደሚደረግ ነው፤ የኢትዮጵያ የንግድ ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ዋና ፀሃፊው ውቤ መንግስቱ ያብራሩት።

 - በመጀመሪያው ዙር 75ሺ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተኑና ከማህበረሰቡ ጋር የሚቀላቀል ስራ ከ150 ሚ.ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ተብሏል

   - በመጀመሪያው ዙር ከሚበተኑት ተዋጊዎች መካከል 50ሺ ያህሉ የሚገኙት በትግራይ ክልል ውስጥ ነው
               
        ትጥቃቸውን የሚፈቱ የቀድሞ ተዋጊዎችንና በመበተን ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ለማስቻል የተቋቋመው የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን፤ የመጀመሪያ ዙር ተዋጊዎችን የመበተን ስራውን ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ በመጪው መስከረም ወር ይጀመራል በተባለው የመጀመሪያው ዙር የብተና ስራ 75ሺ የሚሆኑ የቀድሞ ተዋጊዎች እንደሚካተቱ ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽንን የሚመሩት የቀድሞው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከትናንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ቀደም ሲል በተሃድሶ ፕሮግራሙ እንዲያልፉ ዕቅድ ተይዞላቸው የነበሩት 250ሺ የቀድሞ ተዋጊዎች ቢሆኑም፣ በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር ወደ 371ሺ 971 ማሻቀቡን ጠቁመዋል፡፡ ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ መከላከያ ሰራዊት እንደሚያከናውንም ተናግረዋል፡፡
ከተቋቋሙ ሳምንት ወራትን ያስቆጠረው የብሔራዊ፣ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ እንደሚናገሩት፤ እስከ አሁን በስምንት ክልሎች፡- ትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቢኒሻንጉል ጉምዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ውስጥ 371 ሺ 971 የቀድሞ ተዋጊዎች የተለዩ ሲሆን፤ መቀሌ ውስጥ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ተቋቁሞ በተሃድሶ ፕሮግራሙ ማለፍ የሚገባቸውን የቀድሞ ተዋጊዎች የመለየቱ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ከመጪው መስከረም ወር እስከ ህዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይከወናል በተባለው መጀመሪያው ዙር፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን የመበተኑ ስራ 75ሺ የሚሆኑ ታጣቂዎች የሚካተቱ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 50ሺ የሚሆኑት በትግራይ ክልል ውስጥ እንደሚገኙም ተጠቁሟል፡፡ ቀደም ሲል በተሃድሶ ፕሮግራሙ ተሳታፊ ይሆናል ተብሎ ለተያዙት 250ሺ የቀድሞ ተዋጊዎች የታቀደው 555 ሚሊዮን ዶላር የነበረ ቢሆንም ይህ በጀት በተሃድሶ ፕሮግራም የሚታቀፉ የቀድሞ ተዋጊዎች ቁጥር በማሻቀቡ ምክንያት በቂ እንደማይሆን አምባሳደር ተሾመ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለፕሮግራሙ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንን ግን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ይህ ተዋጊዎችን የመበተኑና ወደ ማህበረሰቡ የማቀላቀል ተግባር፣ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ከመንግስት ጎን ሆነው የተሰለፉትን የማያካትት መሆኑንና በመንግስት ላይ መሳሪያ አንስተው የተዋጉትን ብቻ የሚመለከት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
ለፕሮግራሙ አስፈላጊ ነው የተባለው ባጀት በአብዛኛው ከውጪ ለጋሾችዎች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

Saturday, 15 July 2023 20:50

ክፉ ፍርሃት

ክፉ ፍርሃት
ጨለማ እኮ…!
  በድቅድቁ - ምሽቱ ላይ ጥቁር
         ሌሊት መቀለሙ
ጽልመቱ ውስጥ - ተስፋ አርግዞ
         - ሊነጋ ነው መጨለሙ፡፡
ብርሃን ግን…
 ካድማሱ ጥግ ‘ብቅ‘ ብሎ - ፀሐይ
        ክንፉን ሚዘረጋው፣
የመከነ ተስፋ ይዞ - ሊጨልም
        ነው የሚነጋው፡፡
***
የሚሊኒየሙ አናፂ
አብዮት ፈንድቶ - ጥርስ ቀን ወጣለት፣
የተነቃነቀው - ድጋፍ ታሰረለት፡፡
      ሸራፋው ሊጠገን - መጠኑ ተለካ፣
     ያረጀው ተነቅሎ - በአዲሱ ተተካ፡፡
የተቦረቦረው - ተጠቅጥቆ ሞላ፣
ዱልዱሙ ክራንቻ - ተሞረደ ሰላ፡፡
    አዬ የኛ ነገር…
ማኘኪያችን ሾለ - ገንዘብ ጠላት ገዛ፣
የምንበላው የለን - ጥርስ አዳሹ በዛ፡፡
(ሲሳይ ዘ-ለገሃሬ)
***
የውዴ መዓዛ
አልሄድም ፍለጋ አሪቲና አደስ
ከርቤስ ምን ሊሆነኝ አልሻም ናርዶስ
ዕጣኑ፣ ብርጉዱ ሉባንጃው ወዲያልኝ
ዝባድና ሽቱ በጭራሽ ይቅሩብኝ
አልበልጥብህ አሉኝ ከውዴ መዓዛ
ልቤን ከሰወረው ከጠረንሽ ለዛ፡፡
(አበራ ኃ/ማርያም)

   ‹‹ . . .ወንድዬ ዓሊን በአማርኛ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ ልዩ ያደርጉታል ብዬ ከማምንባቸው ገጽታዎች አንዱ ምስሎቹን የሚጠልቅባቸው ባህሮች አያሌነት ነው። ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር በሌሎች ገጣሚዎቻችን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፣ እንዲሁም ዱሮና ዘንድሮን የማተረጓጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆኑ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው።--”



         በሥነ-ግጥም ስም እንጀምራለን።
በወሎ ክ/ሐገር በወረኢሉ አዉራጃ፣ ከየወል ተራራ ግርጌ ከከተመች ካቤ ከምትባል ከተማ የተወለደ፣ ራሱ ግጥምን የሆነ ሰው...!! ገጣሚ፣ አርታኢ፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊና ተመራማሪ፣ አዘጋጅ፣ ግለ-ታሪክ ፀሐፊ፣ የመዝሙር ግጥም ደራሲ ....
አብዛኛዉ የእድሜውን ክፍል በሚወደዉ ስራ ውስጥ የኖረ የሥነ-ፅሁፍ ወዛደር...!! ጋሽ ወንድዬን ሳዉቀዉ በሩቅ ነበር። በዝና... ‘በሆነዉ ልክ ማን አወጋለት!’ የሚል መብሰክሰክ ከነበረበት አንድ ገጣሚ ወዳጄ አንደበት...
መጀመሪያ ያነበብኳት ግጥሙም “ውጋት” የምትለዉን ነበር።
“ጣቶቼ:- ጥቅሻ ላይ፣
ሕሊናዬም:- የወግ ብካይ፤
ብራናውም:- ገና ለዛዛ፣
ቀለሙም:- ገና ፈዛዛ፣
መሆኑን ነግሬሽ ምነው!?
ውቃቢሽ የማይለመነው።”
[ወፌ ቆመች ገፅ 14 ]
በለመናትና በተለመነችዉ ዉቃቢ በኩል እንደ ቅዋ በሻትኩት በኩል ዘየረኝ። “እብዷን አብዶ”
ተብሎ በተደረሰበት ጎዳና ... ላይ ቆሜ ሳየዉ ወንድዬ ለራሱ ኖሮ አያዉቅም። በሰው ላይ ያያትን ትንሽ ተስፋ ለማብቀል ራሱን ሲሰጥ የኖረ ሰው መስሎ ታየኝ። መንገዱ ለገጠመለት ሁሉ እጅ ይዞ አድራሽ አይነት...
ያለ ቦታዉ ለተገኘ ደግሞ “ያንተን ነገር ማረቅ አዛባ እንደ መዛቅ ከባድ  ነዉ።” ብሎ ይሸኛል እንጂ ሰውን ያለ መንገዱ ጣት ጠቁሞ እንኳን አያሳይም።
[ወንድዬን በዚህ በኩል አየሁት። ... ወይም ታየልኝ።]
ማንም ባየው ልክ የሚለዉ አያጣም ብዬ ... በእድሜ ታላላቆቼ ከሆኑት ሥነ-ግጥሞች ውስጥ በመንፈሳቸዉ የገራልኝን ለማለት ስነሳ የራሱ ስንኞች አደፋፈሩኝ።
“ማን ይሰማኝ ብዬ!?
ማን አይሰማኝ ብዬ?!”
[ውበት እና ሕይወት _ ገፅ 68 ]
***
የመጀመሪያ የሥነ-ግጥም መድበሉ የሆነችዉ ‘ወፌ ቆመች’፣ በ1984 ዓ.ም በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ታትማ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ኮተቤ የመምህራን ኮሌጅ Modern poetry Curriculum ውስጥ ገብታ ለማስተማሪያነት እያገለገለች እንኳን ... እሱ ወረቀቱንና ራሱን አጥብቆ እንደያዘ ነበር።
አጥብቆ የያዛትም ነገር ‘ውበትና ሕይወት’ ሆና በ1998 ዓ.ም ተገለጠች።
(የወፌ ቆመች ቅፅ ፪...)
ወንድዬ ሊፅፍ ሲቀመጥ ዋርካዉን ይፈልጋታል። የፀጥታዉን...፣ የእርጋታዉን...! ሰማይ የተከፈተለት ዕለት መደዴዉ የረገበለት ዕለት ... ኹለንታዉ የእሱ የብቻዉ ሲመስለዉ እንዲህ ይሆንበታል።
“... በጥድፊያ ውሎዬ አክንባሎ ከድኜባቸዉ ያለፍኳቸዉ ዥንጉርጉር ትዝብቶች ... ደግሞ ሆን ብለዉ የሚከተሉኝና የሚጎትቱኝ እንደዚያ ባለዉ ወቅት ነዉ።-- ታዲያም ይህ ኹነት በመጣ - በሄደ ቁጥር በእርቃናቸዉ ያገኘኋቸዉን ትዝብቶች ለመሸፈን እኔዉ - ከ’ኔዉ ጉባኤ እቀመጣለሁ። እናም:- መለሎ ይሁን ጎልዳፋ፣ የቀና ይሁን ቆልማማ ወይም ሸካራ ቢሆን ለስላሳ ... ግን ሌጣ ሬትና ማር የሕይወት ገፅታዎችን ፈርቅጬ፣ ዳምጬ፣ ነድፌና አመልምዬ በፈተልኳቸዉና በሸመንኳቸዉ ማጎናፀፊያዎች ጥበባዊ ልቀት ላላብስ ሁለንታዬን አሰጣለሁ...።”
[ውበትና ሕይወት __ መግቢያ]
እንዲህ ነዉ ወንድዬ። ራሱን የሰጠላት ሥነ-ግጥም መልሳ ራሷን የሰጠችዉ። ወከክ ብላ የታየችለት ...።
ባሳየዉ በኩል ያዩትም እንዲህ ይሉታል፤ “የወንድዬ የገጣሚነት ምናብ ፤ እንደ ቅዱስ ያሬድ ማኅሌት ሥፍራና ጊዜን ከሚያጥፍ ኪናዊ ዘለዓለማዊ ሁለንተናዊነት ይወለዳል። በሌላ አባባል ፣ ገጣሚዉ ስለ ግጥምና ኪነት ሲዘምር፣ በቅኔ ሠረገላ ሰማያትን እያሰሰ፣ ከሰማያት ጉዞ ልምዱ ምስስልና ሕብር እያረቀቀ በመቅረፅ ነዉ።  [መድብለ ጉባኤ፤ ዘመናዊ የአማርኛ ሥነ-ግጥም]
ረዳት ፕሮፌሰር ብርሀኑ ገበየሁ ስለ ወንድዬ ሲገልፁ ...
‹‹...ወንድዬ ዓሊን በአማርኛ የሥነ ግጥም ባህል ውስጥ ልዩ ያደርጉታል ብዬ ከማምንባቸው ገጽታዎች አንዱ ምስሎቹን የሚጠልቅባቸው ባህሮች አያሌነት ነው። ከጸጋዬ ገብረ መድኅን፣ ከሰሎሞን ዴሬሳና ከዮሐንስ አድማሱ በስተቀር በሌሎች ገጣሚዎቻችን እምብዛም የማይታየውን ዛሬን ከነገ፣ እንዲሁም ዱሮና ዘንድሮን የማተረጓጎም ጥበብ የወንድዬ ሥራዎች ድርና ማግ እየሆኑ የሚመጣባቸው ሥራዎች እጅግ በርካታ ናቸው። ወንድዬ ለምናቡ ጥልቀት፣ ለግጥሙ ትርጓሜ ሁለንተናዊነት የሚያስገኘው ከቅዱሳን መጻህፍት በሚዘርፋቸው ዘመንና ቦታ የሚሻገሩ ምስሎችና ሰብእናዎች፣ እንዲሁም ከአደገበት ቃላት የባህል አውድማ ነው። የገጣሚውን ታላቅነት ለማድነቅ የሚያስገድደን አንድ እውነት የምንጮቹ ብዛት ሳይሆን፣ ከነባርና ዘመን አይሽሬ ውድማዎች የሚስባቸውን ሃሳቦችና ስሜቶች በተራቀቀ የትርጓሜ ስልት ለዘመኑ ሕይወትና እውነት ማሳያነት መገልገሉ፣ በሌላ አባባልም አዲስ ሚት(myth)፣ አዲስ እውነት ለማርቀቅና ለማበጀት መቻሉ ይመስለኛል።...››
ከሁሉም ስለ ወንድዬ ገጣሚነትና ስለ ግጥሞቹ አበክረን እናወጋለን።
ሥነ-ግጥምን የሚያዉቅ ያዉቃታል። ግጥምንም የሚያዉቅ ወንድዬን ያዉቀዋል። እሱ የሥነ-ግጥም አድባር ነዉ። በስራዎቹ ልክ ግን ራሱን ያልገለጠዉ ... ለምን ይሆን? የሚለዉ ጥያቄ ሁልጊዜ የምብከነከንበት ጉዳይ ነበር። እና አንድ ቀን ጠየኩት። “ለምን ግን የአደባባዩን ጉዳይ አልከጀልከዉም?”
“ጊዜ አልነበረኝም። በወቅቱ የነበረዉ የፖለቲካ ሁኔታ ... የሚገትት ነበር። እኔ ደግሞ እሱን አልፈለኩትም። በምንም አይነት ሁኔታ ተሸጉጬ ፍርፋሪ መብላት አልፈልግም። ተጠየፍኩት።”
መልሱ ይሄ ነበር። ይህችኑ ሐሳብ “ውበት እና ሕይወት” ላይ ባለች አንድ ሥነ -ግጥም ብንደግፋትስ ...!!
“ለማላውቃት
ከሕይወት ጥሪ ልስማማ
 ተጨምቄ ተበጥሬ ፤
በነፍሴ ተወራርጄ
የኑሮን ጥሻ መንጥሬ . . .
...
በትናንትና ሠረገላ
 ዘላለማት አምባ ወጥቼ ፣
ከፀሐይ ዙፋን .. ወዲያ .. ማዶ!
ነፍሴን ለንባብ አስጥቼ . . .   (አከራረሙ እነዚህን ስንኞች ይመስላል።... )
[ውበት እና ሕይወት __ ገፅ 3]
***
ግጥም ሥጋ የሚነሳዉ ገጣሚዉ ራሱ በማያዉቀዉ መነካት ውስጥ ሲገባ ፤ በማይረዳዉ ሐይል ሲገፋ፤ ከፍ ባለ አብርሆት ውስጥ ሲገኝ ... ወንድዬም እንደሚላት፤ “ቦግ እልሚቱ” ስትበራ ስትጠፋ ...
“መልካም አፈሳሰስ ... ወድቆ ‘ማይሰበር
ፈሶ ‘ማይደፋ ... ጮሆ ‘ማያሸብር ፤ ...” [ወፌ ቆመች ... ገፅ 1 __ ‘በስንኝ ሲሰክሩ ]
ሐሳብና ስሜትን ...ከጊዜ ስሌት ለማሳለፍ “ትንፋሽን በዋንጫ” እንደ መስፈር ያለን ኹነት ከላይ ከሰደርናቸዉ ስንኞች ተከትሎ ... ወንድዬ በስንኝ መስከርን እንዲህ ይገልፀዋል።
“... በዋርካ ጥላ ሥር፣
ተቀዛቅዞ ባ’የር፤
በዋርካው ጥላ ሥር ... ግራ ቀኝ አማትሮ፣
ውበትን በርብሮ ... ውበትን ቀምሮ፤
...
ከጎን ወደ ግድም ... አግድሙን ተልጎ፣
ከአናት ወደ ግርጌ ... ሸርተቴ ተንዶ፤
...
ከዚያ ጎን - እዚያ ጎን ... ድረሱን መሰበቅ
ውስጠ-ውጭ ፍልቀቃ ከሩሕ መተናነቅ፤
እንዲህ ነዉ ምስጢሩ፣
በስንኝ ሲሰክሩ።
[ወፌ ቆመች ... ገፅ 1 __ በስንኝ ሲሰክሩ]
ሥነ-ግጥም በመነካት ስካር ፣ በመከሰት ደስታ ዉስጥ እና ባለመከሰት ትግል (ማጥ) ዉስጥ የሚያቆይበትን የገጣሚዉንና የሁለንታን ትንቅንቅ “ከምኑ ምንጭ ዉበት ልቅዳ” [ወፌ ቆመች - ገፅ 128]  የሚያሰኝበትን መሆን፤ ከላይ ካነሳነዉ የስንኝ መስከር ኹናቴ ጋር ነገሩ ግዘፍ ሳይነሳ ሲቀር “ባላ ‘ደራም ነዉ ባለ እዳ!?” [ገፅ 128] ብሎ የግጥም ባላደራነቱን አሻግሮ የሚከሰትለትን ባለ እዳነት መሸሽ በሚመስል መንገድ የሰደረበት “ቀጠሮ” የምትል ርዕስ የሰጣትን ግጥሙ ዉስጥ ራሱንና ‘ቦግ እልሚት’ የሚላትን ይታዘባል።
“ቀጠሮ
ሰርፆብኝ አንዳች ኹነት ፣
ሕሊናዬ ውጥረት አዝሎ ፣
ይነዝረኛል - እናጣለሁ፤
አልወርድልህ ብሎኝ ቀለም ከብዕሬ ተንከባሎ።
ወደ ልቤ የሚፈሰው
መሆን-አለመሆን ግለቱ፣
ይጨምቀኛል፣
የሕይወት ነፀብራቅ ግዝፈቱ።...
....
ወዲያዉ ቃላት ተዥጎድጉደዉ፣
ብሂል ሆነዉ፣ ብዕሬን አልፈዉ፣
ጠብ ይሉ ብለህ?...
በምን ዕድሌ!
እንዲህ ቢሆን ሁሌ፣
እንዲህ ቢሆን ሁሌ።”
[ወፌ ቆመች - ገፅ 127]
ይህችን ቀጠሮ የምትል ሥነ-ግጥም፣ መስከረም 1978 ዓ.ም ይፃፋት እንጂ ... በገጣሚና በግጥም መካከልም ፤ (በእርሱና በፅሁፉም መሀል) ... መከሰትና አለመከሰት ፣ በፈለጉት ልክ መገለጥና አለመገለጥ ፤ ... ከራሚ ነገር መሆኑን ከ10 አመታት በኋላ የካቲት 1988 ዓ.ም በተፃፈችዉ ሁለተኛ የሥነ-ግጥም መድበሉ ጥራዝ ላይ በሰፈረችዉ “ምጤ የማይገባት” በምትል ግጥሙ ዉስጥ አበክሮ ይፈክራታል።
“ምጤ የማይገባት
..
የዚያ ቀን ብዕሬ፣
ቃላት ምንሽሬ፤
ወለምታ ተመ’ቶ፣
እርሳሱ ተደፍቶ፤
ቀለህ ብቻ ቀለህ - ቀለህ የቀረኝ ‘ለት
ለመፃፍ ስነሣ
አየር ለድልዶብኝ - ጨረሩ ዘንቦብኝ፣
መሬት አነሰችኝ - ሕይወት አፈነችኝ ...
እንዲያ ስንቆራጠጥ :-
ሀሳቤብ ‘ሚገዛ - ቀልቤን እሚሰርቀዉ፣
ለ’ኔ ሥጋ ነስቶ ላ’ንች የተሰወረዉ፤
ምን ብዬ ልንገርሽ ... ?
እቱ
የ’ኔ ገልቱ
የማምጠዉ ምጤ ... ገና የምወልደዉ
የሚገላገለኝ ... የምገላገለዉ ፤
ነበር።”
[ውበት እና ሕይወት - ገፅ 43]
***
ከ1970ዎቹ አጋማሽ እስከ 1980ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ተፅፈዉ ወፌ ቆመች ላይ የሰፈሩት ሥነ-ግጥሞች በአብዛኛዉ በሚባል ደረጃ የራስ በራስ ሙግት (ስለ ራስ ፣ ስለ ማንነት፣ ስለ ሞት፣ ስለ ሕይወት ...) የመሳሰሉትን አይነት የመኖር ግዙፍ ጥያቄዎች የሚያነሱ ... በመጠኑም ቢሆን ሐዘን ያረበበባቸዉ ስንኞች ያሉባቸዉ ይመስላሉ።
[ለምሳሌ ያህል :- የእንባ ስርዓቱ (ገፅ 10) ፣ ሽዉ እልም (ገፅ 25) ፣ ምስክር ፍለጋ (ገፅ 54) ፣ መላ (ገፅ 73) ... አይነቴ ግጥሞችን ልብ ይሏል።]
ራስን ስለማመን ባመኑትም ልክ በራስ ስለመተማመን .. ይህ የጎደለ ዕለት የሰው ልጅ የሚሆነዉን “ሽዉ እልም” ይለዋል ጋሽ ወንድዬ...
“ሽዉ እልም
ሽዉ - እልም ፣ ሽዉ እልም ፣
አሁን ወዲያ ቀና - አሁን ወዲያ ዘመም
ነፋስ ወደ ገፋዉ ...፤
...
በቃ:- ልክ እንደዚሁ ነዉ!
በራስ መተማመን ፣ ለሰው ከጎደለዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 25]
ደግሞ ስለማጣትም ፣ ስለ መነጠቅም ...
“መላ
የሚወዱትን እንዳጡ ÷ በልቅሶ ቢስረቀረቁ፣
ዐመድ - ነስንሰው
ማቅ - ለብሰው
ደረት ገልጠዉ - ቢደቁ ፣
...
ዋይታ ቢያንጎራጉሩ ፤
ዕድሜ እንደሁ - ትንሳኤ የለው፣
ከአለፈ - ያዉ አለፈ ነዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 73]
ከመኖር፣ ከሕላዌ ... የሚያረካ ምላሽ አጥተዉ የሚቅበዘበዙበትን ... በሀሳብ ፣ በቃልና በድርጊት ሀሰሳ ውስጥ መቆም አቅም  ያጣበትን ጉዳይ ... ሱባኤ ቢገቡ፣ ጥሬ ቢቆረጥሙ ...ራስን ቢያገሉ አልሆን ያለውን ነገር ወንድዬ አልፎት ምስክር ይፈልግለታል።
“ጭዉ - እብስ እንደ ቀልድ
ከሐሳብ ዉጣ ዉረድ፤
ሲጥ - እልፍ ለአንድ’ዜ
ከሕይወት ድንዛዜ፤
እንደሚሻል - የቱ ?
ባወጋልን ሙቱ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 54 __ ምስክር ፍለጋ...]
ጊዜን አልፎ የጠየቀበትን ፣ የተሻገረበትን የምናብ ከፍታ ፣ የሞገተበትን ፣ ያደረገዉን ሁሉ ... የሚያዉቀዉንም የማያዉቀዉንም መልሶ ለጊዜ ጉልበት ያስገዛዋል። (ይሄዉ ነዉ። የሰው ልጅ በመለኮትና በአፈር መካከል መሰቀሉ ... በሆነባት ቅፅበት ባደላበት በኩል መገለጡ...)
“የምናዉቀዉ ትዝታ እንኳን
ከእሳቢያችን ተቃቅሮ - ተገይዶ
ፈቃዳችን - የት የለሌ ÷ ከአድማስ ባዶ፤
ስኬታችን ሲሆንብን እዚህ ማዶ፤...
...
የስኬት የክንዉን አዙሪት ፤
የጊዜ ነውና ዳኝነቱ፣
ፍርዱን ለጊዜ ትቶ
ይሻላል መሰል መርሳቱ።”
[ወፌ ቆመች ገፅ 53 ]
***
እና ... የራስስ ነገር? ‘እኔ’ ብለዉ ባመኑትና ባላመኑት ‘ሌላ’ መካከል ... ብቻ ቀርተዉ...፤ በር ዘግተዉ __ ያለ ገላጋይ የተሟገቱበትን ጊዜ ወንድዬ “ወልይ” ይሆንበታል። ቀድሞ ይተነብየዋል። ወደ ፊት ጊዜን ያሰላዋል። ወደ ኋላም ያስታዉሰዋል። በሁለቱ ኹነቶች መገፋት አሁን ላይ ሲረጋ ግን ... የሆነዉም የሚሆነዉም እያደር ይገለጥለታል።
መገለጡን እንደዚህ ይለዋል። ከራሱ  እስከ ሌላዉ ‘ራሱ’ ድረስ...!!
“የእኔና - እኔ ነገር
እኔና ብቻዬ፣
ትንሿ ታዛዬ፣
ኮከብ ... ታዛቢያችን
ብለን:- ቁጭ አልን።
እኔ እና እኔ - እንደ ቀረን፣
ለብቻችን፣
ወደ ኋላም፣ ወደ ፊትም፣ ... ጊዜን አሰላነዉ
ዘመን:- ክፉም ...ደግም ... አለው
.....
የኔና - እኔ ነገር፣
ሁሌ - በክርክር ፣
እንዳለን :-
አለን።
....
እና:-
እኔና እኔም ... ባዳነታችን
እያደር - ተገለጠልን።”
[ወፌ ቆመች - ገፅ 11 ]
***
ወንድዬ ... የሚያዉቀዉን የሥነ-ፅሁፍ ቆሌና የፀሐፊ ነፃነት ጉዳይ እንደሚያብከነክነዉ “ላታዉቁበት” የምትለዉ ለጋሽ ስብሀት ገ/እግዚአብሄር እንደ ማስታወሻ የሰጣት፣ በ1982 ዓ.ም ሰኔ ወር ባ’ንዱ ቀን ፒያሳ ባለች በአንዷ ካፌ [ማኪያቶዉን እየጠጣ ይመስለኛል።] የከተባት ግልጡን ታሳያለች።
መፈለግም፣ መሻትም፣ መለመንም ያለባት ይች ግጥም፣ ጋሽ ስብሀት በልቡ ያለች መብሰክሰኩን ‘ቦግ እልሚቱ’ ለጋሽ ወንድዬ ሹክ ያለችዉ ይመስላል።
“ላታዉቁበት
... ቅጥሩ አይደል ... ከቅጥራችሁ ፣
ዉልዱ አይደል ... ከዉልዳችሁ ፤
ይጥፋ! - ተውት ... እባካችሁ ፣
ይፍዘዝ - ተውት - ባምላካችሁ።
... እሱ ሌላ! ... ብኩን ኬላ፣
ሥራዉ ሌላ! ... ጉም አዘላ፣...”
***
እንደገናም ለሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ማስታወሻ የፃፋት፣ “አስቸግርህ ባጣ” የምትለዉ ሥነ-ግጥሙ ... ለራሷ ለግጥም ፀሎት የማቅረብ ያህል ጉልበታም ነዉ። ራሷን ግጥምን የመካደም ያህል ይልቃል።
“አስቸግርህ ባጣ
በአዬር ... ደንገላሳ፣
በጨረር ... የሣንሳ፤
በነፋስ ትከሻ ... በገሞራ እስትንፋስ ፣
ልመንጠቅ - አንድ’ዜ! ... ስዉር ጥበብ ላስስ።
ትንሽ ... ልፋሰሰው! ... ዛቴን እዚህ ትቸዉ ፣
በሰማያት ጀርባ ... በማይጎረብጠዉ።”
[ወፌ ቆመች -- ገፅ 28]
በአጠቃላይ ግጥሞቹም በታዩልንና በማየታችን ልክ ... ጋሽ ወንድየም በገባን መጠን ይሄንን ብለናል።
“ደኅና እንሁን!!”



 አቈልቊዬ ፡ ባይ ፡ መሬቱን ፡
ቈስሎ ፡ አገኘሁት ፡ እግሬን ፡
ምን ፡ አሳዘነኝ ፡ ለእግሬ ፡ ቊስል ፡
ስሄድ ፡ እኖር ፡ ይመስል፡፡
(ከብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል)
ሞት በስሙ ኗሪ ነው፡፡ ሶምሶን ሹሩባው ላይ ሀይል እንዳለው ሁሉ ሞትም ስሙ ላይ ነው  ሀይሉ ያለው፡፡ ደህና ስም አጥፊ አጥቶ ይህ ሁሉ ዘመን ፋነነብን እንጂ፡፡ አንዳንድ ዘመን አለ፤ ሞት ስሙ የሚገንበት፡፡ ሞት ስሙ ሲገን ለሞት የብልፅግና ወቅት ነው፡፡ ይሄንንም የኛን ዘመን የሞት የልምላሜ ዘመን ነው እላለሁ። ከተፈጥሮ ግብሩ በዘለለ በሰዎችና በተፈጥሮ ክስተቶች እየታገዘ፣ ስሙን በየሜዳው የፃፈበት ለሰው የመከራ፣ ለሞት የተድላ ወቅት ነው። ሞትን መረሳት እንደሚገድለው እናምናለን። ምክንያቱም በስሙ ያለ ነዋ፡፡ ካልተጠራ ይሞታል፡፡
የዚህ ፅሑፍ አላማ፣ ሞት ቅጥራችንን እየዞረው ከሚኖር ከዚህ ዘመን ሰው ጋር፣ እንደው ሞታችን እርግጥ መሆኑን እያወቅን እንኳ፣ ሞትን እንዴት ባለ መንገድ ነው ማስተናገድ ያለብን የሚለው ላይ መምከር ነው፡፡ መቼም ከላይ የገባንባት መተከዣ መዲና ሳትገልጠን አትቀርም የሚል እምነት አለን፡፡ የመዲናዋ ጭብጥ እንዲህ ሊባልለት ከማይችል የባይተዋርነት ስምጥ እንደተጮኸ ልባችን ባይክድም፣ ለተነሳንበት ጭብጥ ስንል በታህታይ ትርጉሙ አባብለን እንዳመጣነው አንክድም፡፡ ለዚህም ነው አፉ በሉን የምንል፡፡
አንድ እየተባለለት ነው አጥርም የሚወድቅ፣ መንገድም፣… የሚያልቅ፡፡ እናም፣ እስኪ ሞትን ለመጣል ባንችል ለመነቅነቅ አንዳንድ እንምዘዝለት፡፡
ዋዛ ይመስላል ለሩቅ ሰው፣…
ፈራና አሁንስ፣ ፈራን አቦ! ፈረንጆቹ አስቦኩን፡፡ እንዴት ያሉ ውለታ ቢሶች ሆነዋል አንተ፣ A living dog is better than a dead lion. ከሞትክ አትረባም ማለታቸው ነው አይደል? ቁርጣችንን ንገሩን እንጂ ጎበዝ! ይሄ በአንበሳ የሰማነው ጉዳይ ሰውም ላይ ይሰራ ይሆን? ከሞተው ሰውስ ድመቱ ትሻላለች፣ ቢያንስ ከአዋኪ አይጥ ታሳርፋለች ማለት ይሆን? ጉርብትናውስ? ፍቅሩስ? ፅዋውስ በአንድ ሽክና አፍ ገጥመን የጠጣነው? ሞት ሲመጣ ሁሉ ገለባ ነው ማለት ነው? በቃ በቃ ሁሉ እንዲሁ ባክኖ ቀሪ ነው? ይህ ማለት አንበሶቹ የታሪክ ጀግኖቻችን ውኃ በላቸው ማለት ነው? ወይስ ለነሱ ሲሆን የትርጉም ማሻሻያ እናደርጋለን? 'ረ ፈራን ጎበዝ!' ረ የዚህን የሞት ነገር አንድ በለን ክንዴዋ!
አንድ!
ሞት የእግዜር እንግዳ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በስነ ፍጥረት ባህሪው እንግድነት ስላለበት በእንግዳ የሚጨክን አንጀት የለውም፡፡ (እንስሳት ምድር ላይ በመንፈላሰስ በአምስት ቀን ይቀድሙን የለም ወይ፣ ያ ማለትስ የእንስሳት ሀገር ሰው ነን ማለት አይደለም ወይ፣ ነው እንጂ ጎበዝ እየተማመንን፣ መቼም ሻል ያልን እንስሶች ብንሆንም፣ መልከጥፉን በስም ይደግፉ ብለን እንጂ እንስሳማ እንስሳ ነን፡፡ ሊያውም ፍጡር ከተበጃጀ ኋላ እጃችንን ኪሳችን አድርገን የገባን ኩሩ ቢስት፡፡ ቅዱስ መፅሐፍ አትግለጡብኝ የሚል ካለ ሌላ የራሱን የዳርዊን ወንጌል መግለጥ መብቱ በፍፁም ልብ የተረጋገጠ ነው፡፡ ምን ከመሰለ ለም መሬት ተጠፍጥፎ ከመሰራት፣ ተንፏቆ መምጣት ከበለጠበት መብቱ፡፡ ይንፏቀቅ)
አያ ሞት እንግዳ ነው ብለናል፡፡ በር ይቆምና፤ ” የመሸበት የእግዜር እንግዳ” ይላል፡፡ አቤት ድምፁ እንዴት ያስፈራል፡፡ ፍርሃት ደግሞ ሞት የሚገባበት ቀዳዳ ነው፡፡ ሰው ይሄን ሲሰማ፣ አንድም በፍርሃት ሁለትም በብድር መላሽነት በር ይከፍታል፡፡ ሞት ይገባል፡፡ ሲገባ ያኔ የሞት እንግድነት ያበቃል፡፡ ምክንያቱም ዐይን ያወጣ ባለጌ ነዋ፡፡ ሰዎች ሆይ፤ ሞትን ከደጅ መልሱት፡፡ በራፋችሁ ቆሞ ሲለምን እንዲህ በሉት፣
"…ቦታውን ሁሉ ሕይወት ሞልቶታል፣ ለሞት የሚሆን ስርፋ የለም!”
ፃድቁ ላዖ ሱም ረቡዕ በሚፀለይ ውዳሴው ይህንኑ ነው ያለው (መቼም ስሙ ሲነሳበት እንዴት ብሽቅ እንደሚል፣ አያ ሞት)
‹‹… He who knows how to live can walk abroad
Without fear of rhinoceroses or tiger.
He will not be wounded in battle.
For in him rhinoceroses can find no place to thrust their horn,
Tigers no place to use their claws,
And weapons no place to pierce.
Why is this so?
ምክንያቱም፣ He has no place for death to enter. ››
ከበር የመለስነው ሞት፣ በር ገንጥዬ እገባለሁ ካለስ አንልም? ካለማ አንድም ዘራፍ ብሎ መነሳት፣ አንድም ከነመኖሩ መርሳት፡፡ ዘራፉ (የአባቶቻችን እንጂ የኛ ስላልሆነ) ለጊዜው እሱ ይቆየንና ከነመኖሩ መርሳት ይቻላል ወይ? የሚለውን እንይ፡፡
the denial of death ስልታዊ ማፈግፈግ ነው፡፡ ልክ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ኢየሱስን እንዳስገደለው ያለ፡፡ ለሞት ጀርባ መስጠት፡፡ እኔ ጋ አይደለም የመጣው አልያም እኔ የለውበትም ብሎ ማለት፡፡
የሞትን ሕልውና አለማወቅ እና ሞትን መካድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እስኪ በተናጠል ለማየት እንሞክር፡፡ እውነት ሞት የለም ብሎ ማሰብ ለሰው ልጅ የሚቻለው ነውን? ሞት ቢረሱት የማይረሳበትን ደመኛነት ልቡ ስላለ የሚሆን ላይመስለን ይችላል፤ ነገር ግን እንደ ፍሩውድ ያሉ ሞትን ከመጤፍ የማይቆጥሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ግን እንዲህ ይላሉ፡፡ ፍሩውድ ያለው ይህን ነው፤
‹‹… እንዲያውም ልንገርህ፣ The conscious ጭርሱኑ does not know death or time, in man’s physiochemical, inner organic recesses he feels immortal.››
ይህ ማለት፣ ደጅ ቆሞ ‹‹ ቤቶች›› ሲል፡፡
‹‹ማን ነው?›› (ማለት፣ ተነስተህ ከመክፈትህ በፊት፡፡)
‹‹እኔ ነኝ›› (ስሙን አይናገርም? ሌባ)
‹‹ አንተ ማን ነህ? ስም የለህም? ›› (ጎበዝ! ደግ አደረግህ)
‹‹ሞት ነኝ››
‹‹ሞት ምንድን ነው? አውሬ ነው? ሰው ነው? ካለዛሬም ስምህን ሰምቼው አላውቅ›› ብሎ ማለትን ይመስላል፡፡ ታዲያ እንዲህ ባለ ሁኔታ የመለሱት ሞት፣ አንተ ባታውቀኝ እኔ አውቅሃለው ቢልስ አትሉም? ትላላችሁ እንጂ! ለምን አትሉም ሞት ጉዳዩ ያልሆነ ማን አለ። እንዲህ ያለ ፈጣጣነት ሲገጥመን ነው ወደ ሁለተኛው አማራጭ ፊት የምንመልሰው፡፡ ሞትን ማሻገር፡፡
ለዚህ ማሳያ ተመሳሳይ ምሳሌ እንጠቀም፡፡
ሞት ደጅ ይቆምና በር እየቀጠቀጠ ‹‹ቤቶች›› ሲል፡፡
‹‹እዚህ አይደለም የተንኳኳው፣ ጎረቤት ካለ ቤት ነው›› ብሎ በማሰብ፣ ምንም እንደሌለበት ሰው ፊትን ወደ ግድግዳ መልሶ ለጥ ማለት። ሞትን የምንክደው መኖሩን ካወቅን በኋላ ነው፡፡ እዚህ ጋ ነው ከፍሩውድ ጋር ልዩነት የሚፈጠረው፡፡ ይህን ዘዴ እንድንጠቀም የመከረን ኤርነስት ቤከር ነሆኑን ሳንጠቅስ ብናልፍ ወጭት ሰባሪ ነው የሚያደርገን፡፡
ሞት ባዳ ነው፡፡ ሞት ከሰው ወገን ስላልሆነ፣ ለሰው አይራራም፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀልስ ምን አሉ፣ የሞትን ነገር ታዝበው፤
‹‹… የሰው እንግዳ ሲመጣ፣
ግባ ይሉታል ብላ ጠጣ፣
ያንት መላክተኛ የመጣለት፤ ይዋል ይደር የለበት ››
ሞት ክፉ እንግዳ ስለሆነ ውለታውን በክፋት ነው የሚመልሰው፡፡ እርሱ ከፍቶ ባይሆን እንኳ፣ ውጤቱ ለእኛ ስለሚከፋ እጁ እስኪገነጠል ቢያንኳኳ እንኳ፣ የኛ በር እንዳልተንኳኳ ማመን እስከሚቻለን ድረስ መፅናትን መለማመድ። እውነት ማን ይሙት! የትኛዋ ልጃገረድ ናት የምጥ ስቃይን ከወላድ የምትጋራ? ስሜቱን። ምጥ እንዲያም ብታውቅ እንጂ ሕመሙ አይሰማትም፡፡ ሞትስ እንደ ውልደት አይደለም ወይ? ሕመሙን ሆነ ደስታውን እስካልቀመስነው መች ይሰማናል፡፡ አይሰማንም፡፡ ሰውም እንዲሁ ነው ስለ ሞት ያለው እውቀት፡፡ ከጎረቤቱ ጥል ባይሆን እንኳ ሞትን በማሻገር፣ አንዱ ቀሪና ቀባሪ እርሱ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡
ጋሽ ቤከርም ይህንኑ ነው ያሉት፣
‹‹… at heart one doesn’t feel that he will die, he only feels sorry for the man next to him.››
ሌላው ጥያቄ፣ እንዴት ነው ሞት ላይ ዘራፍ የሚሉት? እና፣ ዘራፍ ያሉት ጠላት፤ በዘራፍ አልበረግግ ቢልና ይልቁን ዘሎ ቢያንቅ ምን ያደርጋሉ? የሚለው ነው፡፡
ነገሩን ሁለት ቦታ ከፍለን ለማየት እንሞክር።
ታግሎ ማሸነፍና፣ ታግሎ መሸነፍ፡፡ ታግሎ መሸነፍን፣ በታሪክም በዓይናችን ብሌንም ዐይተን በተማርነው መሰረት የሁላችን ሊባል ቁጥሮች ለጎደለን ለ99ኞቹ ትተን ፣ ታግሎ ማሸነፍን ለአንዱ እንሰጣለን፡፡
ዘጠኝ ሞት መጣ ሲሉት፣ አንዱን ግባ በሉት አላ፡፡ ማ? አንዱ፡፡
አንዱ ማን ነው?
እዚህ ጋ ጋሽ ቤከርን በድጋሚ ወደ’ዚህ ለመጥራት እንገደዳለን (ለማይረባ ነገር አመላለስንዎት አይደል ጋሼ… ይቅርታ)
‹‹The hero was the man who could go into the spirit world, the world of dead, and return alive.››
ሆድህ ገብቼ ደም ሳይነካኝ እወጣለሁ እንደማለት ያለ ነው ነገሩ፡፡ ይሄ ከሞት ግብግብ በገጠሙበት እግረ መንገዱን ሽልማት የሚገኝበት ነው፡፡ ሽልማቱ ደግሞ ጀግንነት ነው። Hero’s journey ይሉሃል ይሄኔ ነው፡፡ ጀግና እንደካሮት ከመሬት አይበቅልም፣ ከአንተው ጋር ጭቃ አቡክቶ፣ ደንሶና አስደንሶ፣ አድጎ ነው ድንገት መድህን እንዲሆን የሚጠራው፡፡ ሞት ያልተፈራበት ዘመን አለ ቢሉ፣ ሰው አልነበረም ያኔ? ብለን ለመጠየቅ እንደፍራለን፡፡ ስፓርታ ልጆቿን ለክብር ሞት መውለዷስ? ብትሉ፣ ሰው ሕይወቱን በትፍስህት ለሞት አያጫትም፣ ቢሳካለት እንኳ ሞትን ተሻግሮ ማየት አልቻለም፤ እንላለን፡፡ ሁሉም ሕይወት ሞት ፊት ኢምንት ነው፡፡ ያንን ማወቅ ለፈለገ ለእገሌ እሞታለሁ ያለ ጀግና አንገት ላይ ሰይፍ ያስደግፍ፡፡ ያኔ ጉራውና ትምክህቱ ለነፍሱ ቦታ ስትለቅ ያያል፣ ነፍስ ደግሞ ፈሪ ናት፡፡ ነፍስ የታሰረችበት ግድግዳ ነው ስጋ ማለት፡፡ ነፍስ ስጋን መሽጋ የምትኖር የሌላ ዓለም ዜጋ ናት፡፡ ድንገት የዜግነት ማጣሪያ ሲደረግ ትበረግጋለች፣ በስጋው እንጂ በነፍሱ ጀግና የሰው ዘር የለም፡፡ እንዲያው ልቡ ጀግኖለት እንደ ስፓርታውያኑ ወጠጤዎች፣ ሞትን በድፍረት ቢጋፈጥ እንኳ ተመልሶ ገድሉን ለማፃፍ የሚሆን እድል አላገኘም፡፡ ካርል ዩንግ ይሄን የጀግንነት ጉዳይ ስነልቦናዊ ፍካሬ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሰው የራሱን ሞት ከማሸነፍ በዘለለ በሌሎች (የሞት አገልጋይ ተደርገው በተመሰሉ monsters and force of evil) ላይ በመዝመትና እነሱን በማሸነፍ ጭምር ነው ይለናል፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ አይደል ተረቱስ፣ እሱን ባይሆን መልዕክተኞቹን በመጠፍጠፍ የሰው ልጅ ንቀቱን አሳይቷል፡፡ ይሄን እምነት ለማሳየት በየጫካው እየዞሩ፣… እነማ አትሉም?
‹‹እነ ሄርኩለስ፣ እነ ዳዊት፣ እነ ጊዮርጊስ፣ ጊለጋሜሽ፣ ሲጉርድ፣ ዘንዶና አንበሳ በጥፊና በቴስታ ሲዘርሩ፣… ከላይ አንዱ ብለን የጠቀስንላችሁ ሰው መጣና እንዲህ ሲል ገሰፃቸው፣…
…አያይ እንደዚያ አይደለም፣… አንዱና ትልቁ (ጉልቤው) ሌላውን (ደካማውን) እየበላና እየገደለ መኖር ሥርዓተ ተፈጥሮ ነው። ማሸነፍ ያለብን ሞትን ነው፡፡ don’t kill the messenger፣… የቱ ሞኝ ነው ኮምፒውተሩን ቫይረስ ሲያጠቃው፣ ቫይረሱን ፀረ- ቫይረስ በማስረጨት ፈንታ አውጥቶ የሚወረውር? የቷስ ቂል ናት ስንት ፈዋሽ ፀበል (ቡሩክ ካህን) ባለበት ሀገር ቤቴ ሰይጣን ገባ ብላ ቤቷን ጥላ ብርር የምትል? ይሄ ሞኝነት ነው፡፡ ሞት ግድግዳ ነው። ግድግዳውን ማፍረስና መተላለፊያ ማበጀት ነው ያለብን፣ እኔ ያንን ነው ያደረግሁት፡፡››
ያለውን አደረገ፡፡ ይሄን ጀግንነት ያለተቀናቃኝ በምልዓት የተቆጣጠረው አንዱ ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰው ልጆች ጀግና ነው፡፡ ኢየሱስ ሞት ላይ ተረማምዶ ከማለፍ በላይ የጀግንነቱን ዜና በራሱ ጆሮ ለመስማት ችሏል፡፡
ከኢየሱስ ትንሳዔ ወዲህ ሞት እምብዛም ያልተፈራበት ዘመን ሆነ፡፡ ሰዎች እየሞቱ እያየ እንኳ ከሞት ባሻገር ስላለው ሕይወት ማወቁ ሰውን አፅናናው፡፡
ሞት ምን አለ ይሄን ጊዜ?
    ‹‹ ተበላሁ! ››
ሞት ይሄን ማለቱ በሀገር ተሰማ፡፡ ሀገሬው ሞት ይሄን ማለቱን ሲሰማ የድል ድግስ ደገሰ፡፡ (ረ ዘፈን ያወጡም አሉ አሉ፣… ሞትዬ ሞትነት፣ ሞት’ለም ሞቱካ፣… አሃሃሃ፣… እንዲህ ያለው ፈሪ፣ ልፍስፍስ ነህ ለካ፣… ሆሆይ ናና…) በየድግሱ ሞት ላይ ተቅራራ፡፡ የኢየሱስ ትንሳዔ ለሰዎች፣ ሞት ማለት ከገቡበት የማይወጡበት እንዳልሆነ መልመጃ ሆነ፡፡ ይሄን ጊዜ ጋሽ ቤከር ሰልፍ አሳብሮ ገባና እንዲህ አላ፣
‹‹when we see a man bravely facing his own extinction we rehearse the greatest victory we can imagine.››
ሰው በየመቅደሱ፣ በየእድሩ፣ በየዛፉ ጥላ፣ በየጨብሲ ቤቱ፣ ጠረጴዛ በጡጫ እየመታ ጥርሱን እያፋፋቀ ተማማለ፡፡ አንዱ ጎበዝ ብድግ ይልና መሃላውን ይመራል፣ ሌላው እየተከተለ እሱ ያለውን ይላል፡፡
‹‹ከእንግዲህ በኋላ፣… ሞት ሆይ እግር ብላ፣… If I am like my all powerful father, I will not die.››
ኦስትሪያዊው ዶክተር ዊልካልም ሪችም ይሄን መሃላ፤ Character armor ብሎ ጠራው።
እንበልና (በእንበልና ገብተው የእውነትን ቦታ ያገኙ ስንቶች እንዳሉ መረጃው ቢኖረንም) ቅድመ ክርስቶስ የነበረው የሰው ልጅ፣ ሞትን ሲፈራው የነበረው፣ ሞት የሙከራ ዕድል ስለማይሰጥ ነው እንበል፡፡
በምሳሌ እንየው፡- ከ’ለታት በአንዱ ቀን፣… እንዲያው አንዱ ጥጋብ ልቡን ንፍት ያደረገው ወጠጤ፣ በሰላም ኑሮውን እየኖረ ካለበት ድንገት ብድግ ብሎ የሞትን ነገር ቢያጣጥል፣ አጣጥሎም ባይቀርና ካልገጠምኩት ሞቼ ልገኝ ቢል፡፡
‹‹የታባቱንስና ደግሞ! አሁንስ ለማንም ጠቋራ (መቼም ፈረንጅ ይመስላል እንደማትሉኝ) መንቦቅቦቅ ሰለቸኝ››
ብሎ ቢገጥመውና ሞት በአንድ ቃሪያ ጥፊ ጥሎት ያንን የመሰለ መኳንንት ሙትት ብሎ ቢቀር፡፡ እሱኮ ሀሳቡ የነበረው፣ ሞት ቢያሸንፈው ከእንግዲህ ኋላ አንገቱን ሰብሮ ሊኖር፣ እንደሁ አድባር ቀንታው ሞትን ቢያሸንፈው ጊዮርጊስ እንደረገጠው ድራጎን ያለ ምስል፣ ሞትን ከእግሩ ስር ረግጦ የሚያሳይ ሀውልት አደባባይ አቁሞ ለመኖር ነበር፡፡ ሞት ግን አሰራሩ እንደዚያ አይደለም፣ ከተጣሉት ለእርቅና ለሽምግልና የሚሆን ጊዜ አይሰጥም፡፡ እንዲያው ዝግት ያለ ነገር ነው፡፡ ይህ እንዴት ማለት ነው? ለነገ የሚሆን እቅድ ይዘህ ከአልጋ ትወጣና ነገን ብትጠብቅ ብትጠብቅ ሳይመጣ ቢቀር፣ ይሄም በቀላል እንግልጣርኛ
‹‹any schoolboy can do experiments in the physics laboratory to test various scientific hypothesis. But man, because he has only one life to live, cannot conduct experiments to test whether to follow his passion [compassion] or not. ››
ኩንዴራ ከላይ ያለንን ሰምተን ‹‹ልክ ብለሃል›› ብለን ብዙም ሳንርቅ፣ ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ እንገባለን፡፡ አጣብቂኙ የመጣው ከታሪክ ነው፡፡
ቅድመ ክርስቶስ ያለው የሰው ልጅ ሞት የመጨረሻ አለመሆኑ ጠፍቶት ነው? የሚል። ‹‹እህሳ?›› ስንል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው ብሎ ይጀምራል አጣብቂኙ፣
‹‹ዛሬ አይምሰላችሁ፣ ጥንት የሄለናውያንን ፍልስፍና የሚያራምዱ የዜኖ ደቀመዛሙርት የሆኑት ስቶይክሶች፣ ቡድሂስቶች፣ ሂንዱሂስቶች ሁሉ ሳይቀር ሞት ለሰው ልጅ የመጨረሻው እንዳልሆነና Infinite (የሰው ልጅ የቁጥር እውቀቱ አገልግሎት እስከሚያጣበት) ጊዜ ተደጋግሞ ተወላጅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡››
የአጣብቂኙን ነገር ችላ ለማለት ‹‹የድሮ ሰው ምኑ ይታመናል›› ብለን ልናጣጥል ስንጀምር፣ የድሮ ሰዎች አምላክ ከድህረ ክርስቶስ ሰዎች ነብይ አስነሳብና፡፡ እንደ ኒቼ ባሉ ባለ ጎፈሬ ሙስታሾች ስል ምላስ ሊያስገርፈን፡፡ ኒቼ ተነሳ ያንን ዞማ ፅዕሙን እያስተኛ፣
‹‹የድሮ ሰው ምናምን እያልክ ነገር ከምታጣጥል ካሽ አውጣና መፅሐፌን ግዛኝ፣ እዛ ላይ ስለ Eternal recurrence የፃፍኩትን ታገኛለህ፣…››
ታዲያ እንዲህ ከሆነ ነገሩ የዛን ዘመን ሰው ሞትን ለምን ፈራ? ተብሎ ሲጠየቅ፣ እኛም መላምትን ለፈጠረ አምላክ ገለተ ጢሎሲ! እያልን መመልመት እንጀምራለን፡፡
መላምት1፡- በዚህኛው ዓለም ያስኮረፉት ሞት (የድሮው ሞት ደግሞ ተበቃይ ነው) በሌላኛው ሕይወት ሲያገኛቸው መከራቸውን እንዳያበዛው በመስጋት፡፡ ማን ያውቃል ሞትም የTalien principle ተከታይ እንደሆነ? የናቀውን በንቀት፣ የተሳፈጠውን በስፍጠት የሚመልስ እንደሆን? ሞት ሲሳፈጥ ደግሞ አሟሟት በማክበድ ነው ሲባል ሰምተናል፣ ሲያደርግ ባናይም፡፡
መላምት 2፡- ድግግሙ ቅልሽልሽ ስላለው። አልያም ምን የመሰለው ከበርቴ አሳማ ሆኜ ብመለስስ ከሚል ከንቱ ስጋት?
ደግሞ ሞትን መፍሪያ ምክንያት ጠፍቶ ነው? እንዲያው ስታደክሙን እንጂ፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ ሰው ምን በጀው? ብለን ከአፋችን ሳንጨርስ አጋፋሪሻ በቅሎአቸውን እየኮለኮሉ ከተፍ፡፡ በግራ ይሁን በቀኝ እጃቸው መፈክር ይዘዋል፡፡
‹‹ሞትን ሽሹት!›› የሚል የተፃፈበት፡፡
ጨዋታን ጨዋታ አይደል የሚያነሳው፣ ለመሆኑ አጋፋሪ ሞትን ሲሸሹ ነው ሲያባርሩ የሰነበቱት? ብሎ መጠየቅ አይከፋም። ምክንያቱም ሞት ሁሉ ሀገሩ ነዋ፡፡ ይልቅ አጋፋሪ በፍርሃትም ይሁን በግብታዊነት፣ ሞትን በንቃት ይከታተሉት ነበር፡፡ ንቃታቸው ሞትን ከጉያቸው አልለየውም፡፡ ባሰቡት ቁጥር ሞት ቅርባቸው እንዲገኝ ሆነ፡፡ ለመሸሽ ባሉት ልክ እየቀረቡት በአንፃሩ ሞት ያለቀጠሮ እንዳያስቱት (እንዳያስገድፉት) ብሎ ሲሸሽ እንደኖረ አድርገንም ማሰብ ይገባል፡፡ ይባስ ብለን፣ አጋፋሪ ሞትን ሳይሆን ሙታንን ነበር ሲሸሹ የነበሩት ብንልስ? ለምን አንልም ለምለም አንደበት እስካለን፡፡
እናም በስተመጨረሻ፣… ጋሽ ኩንዴራ The stupidity of people comes from having an answer for everything ብሎ እፍኝ ስላሳከለን መልስ ኪሳችን ቢኖርም፣ ታላቅ የመታዘዝ ባሕል እድሜው እንዲረዝም ሲባል ጠይቀን እንወጣለን፡፡
ከሚከተሉት ምርጫዎች መካከል እንደው ይሄ ለኔ ይበጀኛል ያላችሁት ላይ አክብቡ?
ሀ. ቤቴን በሕይወት ሞልቼ ለሞት የሚሆን ቦታ ማሳጣት
ለ. ሞትን ታግዬ ማሸነፍ
ሐ. ከነመኖሩ ርስት አድርጌው መኖር
መ. እንደ አጋፋሪ መሸሽ
ሠ. መልሱ እዚህ የለም
ረ. እዚህ ከሌለ የት ነው?





 ስኬት አመለካከት ነው፡፡ ስኬት ልማድ ነው። እንደሚቀዳጁት ለሚያምኑና መሻታቸውን ወደ ተግባር ለሚለውጡ ሁሉ፣ ስኬት በቀላሉ የሚገኝ ነው፡፡
ስኬት አንዳችም ምስጢር የለውም።  ስኬትን የተቀዳጁቱ አያሌዎች፤ ስኬታማ ከመሆናቸው በፊት ዓመታትን ለስራቸው፣ ከልባቸው ለሚወዱትና ለህልሞቻቸው መሰዋታቸውን በግልፅ  ይተርካሉ፡፡
በሁሉም ሁኔታ፣ ዋናው ጭብጥ ሁሌም ተመሳሳይ ነው፤ እነዚህ ስኬታሞች ሥራቸውን በፍቅር ይወዱታል፡፡ ስለዚህም ዞሮ ዞሮ፣ ይሄን ሥራቸውን መስራታቸው አይቀርም፡፡ ጥሩ አዱኛ… ወይም ቢያንስ የተወሰነ ደረጃ የገንዘብ ደህንነትና ስኬት… ብዙ ጊዜ የህልማቸው አካል ነው፤ ሃብትና ብልጽግና ግን በህይወታቸው የሚወዱትን በመከተላቸው የሚመጣ ተጓዳኝ ውጤት ነው፡፡ ታዋቂው አሜሪካዊ የፊልም ዳይሬክተር ስቲቨን ስፒልበርግ፣ በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር እየተከፈለው፣ ፊልሞችን የሚጠላ ቢሆን ብለህ አስበኸዋል? ኼነሪ ፎርድ በማሽነሪ ባይማረክስ ኖሮ?...ዶና ካራን አልባሳትን ብትጠላስ ኖሮ?...
የምንወደውን ስንሰራ፤ ሌሎች ላይ ጉዳት ሳናደርስ፣ ስጦታችንንና ተሰጥኦዋችንን ስናቀርብ፤ ለራሳችን፣ በዙሪያችን ላሉና ለፕላኔታችን የላቀ አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡
ስኬት የእጣ-ፈንታ ጉዳይ አይደለም፤ ይልቁንም እጅግ የተወሰኑ መርሆች ሥራዬ ብሎ በመተግበር የሚቀዳጁት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ እድል ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ ይኼም የሚሆነው፣ ዝግጁነት ከእድል ጋር ሲገጣጠም፣ በሚለው ብሂል መሰረት ብቻ ነው፡፡
እነዚህ መርሆዎች ባሉበት ሁኔታ፣ እድሜ፣ ትምህርት፣ ገንዘብ፣ የኋላ ታሪክና የልጅነት ተሞክሮ ምንም ቦታ የላቸውም - ለስኬት። የዓለማችን ባለፀጎች፣ ስኬታማ አርቲስቶችና ታዋቂ ተዋናዮች የልጅነት ተሞክሮ  እዚህ ግባ የማይባል ነው፤ ብዙ ጊዜ ደግሞ የድህነት፣ አንዳንዴም ጎስቋላ (አሳዛኝ)፡፡ በትምህርት ረገድም በርካታዎቹ ዘገምተኛ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን እያንዳንዳቸው፣ በህይወታቸው ወሳኝ ቅፅበት ላይ እድል ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው ለማስገባት በመወሰን፣ ራሳቸውን በመፃህፍት በማንቃትና በማበልፀግ፤ የሌሎችን አርአያነት በመከተል፣ እንዲሁም በተፈጥሯዊ እውቀትና ጥበባቸው ተጠቅመው  ስኬትን ገንዘባቸው ያደረጉ  ናቸው፡፡
በኛ “ፈጣን እርካታ- ወዳድ“ ህብረተሰብ ውስጥ ብዙ ጊዜ የመጨረሻ ውጤቱ ላይ ብቻ ነው የምናተኩረው፡፡ ለምሳሌ፤ የፊልም ኮከብ፣ ሚሊዬነር፣ ተደናቂ አርቲስት ወዘተ የሚለው የመጨረሻ ውጤት ላይ ብቻ፡፡ እናም ነገርየው የአንድ ጀምበር (አዳር) ስኬት ይመስላል፡፡ እነዚህ ስኬታሞች ያለፉበትን የዓመታት ልፋት፣ ቁርጠኝነት፣ ትጋት እንዲሁም ታጋሽነት ፈጽሞ አንመለከትም፡፡ አሜሪካዊው የፊልም ተዋናይ ደስቲን ሆፍማን፣ በአንድ ወቅት፣ “የአንድ ጀምበር(አዳር) ስኬታማ ለመሆን 10 ዓመታት ፈጅቶብኛል” ሲል ቀልዷል፡፡ የማክዶናልድ መስራች ሬይ ክሮክ ደግሞ በግለ-ታሪክ መፅሐፉ፤ “እሺ የአንድ ጀምበር (አዳር) ስኬት ነው እንበል፤ ነገር ግን 30 ዓመት ረጅም፣ በጣም ረጅም ሌሊት (አዳር) ነው” በማለት  ፅፏል፡፡
የስኬታማ ሰዎች የጋራ መገለጫ፣ ሁሉም ውድቀቶችን (ሽንፈቶችን) ማስተናገዳቸው ነው፤ አንዳንዴም ብዙ ውድቀቶችን ወይም ሽንፈቶችን! አብዛኞቹ ሰዎች  ስኬት ላይ ፈፅሞ አይደርሱም፤ ምክንያቱም ከአንድ ወይም ሁለት እንቅፋቶች በኋላ ተስፋ ቆርጠው የጀመሩትን ከእነ አካቴው ይተውታል - ከጉዟቸው ይገታሉ።
በአዲሱ ሚሊኒየም ስኬት አዲስ ትርጓሜ ተሰጥቶታል፡፡ የሚሊዮን ዶላሮች ህልምን ለማሳካት ሲሉ፤ ጤናቸውንና የቤተሰብ ህይወታቸውን መስዋዕት በማድረግ፣ በሥራ ሱስ ተጠምደው ለመቀጠል የሚሹ  እጅግ ጥቂት እየሆኑ መጥተዋል፡፡ አሁን ስኬትና ብልፅግና በእርግጠኝነት ሚዛናዊ ህይወትን የሚያካትት ሆኗል፡-በአንድ በኩል አጥጋቢ ሥራን መከወን፤ በሌላ በኩል ጤናንና የአካል ብቃትን እየጠበቁ፣ የፍቅር ግንኙነትና ደስተኛ ቤተሰብ ባለቤት ሆኖ፣ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እየተሳተፉ እንዲሁም፣ ውስጣዊ ሰላምንና እርካታን እየተቀዳጁ ህይወትን መምራት፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ  በሰራው ፖል፣ አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊዎች፣ ዋና ጉዳያችን ነው ያሉት፣  በዝግታ መጓዝንና ጥቂት መስራትን ነው፡፡ በተጨማሪም የበለጠ ክብርና ሃብትን ከማሳደድ ይልቅ የበለጠ ጊዜያቸውን ከወዳጆችና ቤተሰብ ጋር ማሳለፍን ትኩረት እንደሚሰጡትም ተናግረዋል፡፡
እውነተኛ ስኬት ይሄን ሁሉ ሊያካትት ይችላል፡፡ በፍቅር የምንወደውን ስራ ለዓለም ማቅረብ፣ በዙሪያችን ላሉ ሁሉ ድንቅ አገልግሎት ነው፡፡
ውብ ግንኙነቶችን መመስረትና እነሱንም ለማጣጣምና ለመጠቀም ጊዜ ማግኘት ሁላችንም ማሳካት የምንችለው ብርቱ ፍላጎት ነው፤ ከወደድን ማለት ነው፡፡ በቅጡ የታሰበበትና የታቀደ የስራ ልማድ፤… በተለይ የአዕምሮ ልማድ… የገንዘብ ደህንነትና ብልፅግና ሊያቀዳጅ ይችላል፡፡ በቂ ሃብት ሲኖረን፤ ከልባችን የምንወደውንና ደስታ የሚያጎናጽፈንን ያለ ጭንቀት ለመሥራት፣ እንዲሁም ለዓለም መልሰን ለመስጠትና ሌሎችንም ለመርዳት ትልቅ ነፃነት እንጎናፀፋለን፡፡
አንድ ጥንታዊ የቻይና ምሳሌያዊ አባባል፣ የአንድ ሺ ኪሎ.ሜትር ጉዞ፣ በአንድ እርምጃ ይጀመራል ይላል፡፡ ይህን መፅሐፍ ለማንበብ በመወሰንህ፣ ወደ ስኬትና ህልም ጉዞህ የሚያደርስህን የመጀመሪያ እርምጃ ወስደሃል። በህይወት ውስጥ ሁሉም ነገር የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ የዚህ መፅሐፍ አላማ፣ አንተ የምር የምትፈልጋቸውን (ህልሞችና ግቦችህን) ማወቅ እንድትችል የቀረቡልህን አማራጮች ግልፅ ማድረግ ብቻ አይደለም፤ እነዚያን ግቦች ታሳካም ዘንድ ማገዝም ጭምር እንጂ፡፡
- ሳምንት ይቀጥላል -
(ምንጭ፡- በሁለቱ ሚሊየነሮች ማርክ ፊሸርና ማርክ አለን አጋርነት ከተፃፈው “How to Think Like a Millionaire”  መፅሐፍ መግቢያ ላይ ስለ ስኬት ከቀረበው ሰፊ ሃተታ የተወሰደ)

በአይሁድ አፈ-ታሪክ አንድ ተረት አለ፡፡
እየተሳሰቡ አብረው የሚኖሩ አራት እንስሳት ነበሩ፡፡ እነሱም አንዲት ብልህ የጥንቸል ግልገል፤ ተኩላ፤ ዝንጀሮና የዱር ድመት ናቸው፡፡ ጥንቸሏ ገና ግልገል ትሁን እንጂ ብስል በመሆኗ ትክክለኛ አኗኗር ማለት ምን እንደሆነ ሁሌ ታስረዳቸው ነበር፡፡
አንድ ቀን ጥንቸሏ፤ “ነገ የፆም ቀን ነው፡፡ እኛ ምንም መመገብ የለብንም፡፡ በአንፃሩ ግን ለደሀ የሚበላ ነገር መመፅወት አለብን፡፡ ይህን ማድረግ ትችላላችሁ?” ስትል ጠየቀች።
ሌሎቹ ሦስቱ የሚበላ ነገር ሲፈልጉ ውለው አግኝተው መጡ፡፡ ጥንቸሏ ግን ከሳር በስተቀር ምንም ያገኘችው ምግብ አልነበረም፤ “ለማኝ ሳር አይበላም፡፡ እንግዲህ እኔ ምን ልመፀወት ነው?” ስትል አሰበች፤ ተጨነቀች፡፡ በመጨረሻ ግን፤ “በቃ ለማኝ ካጋጠመኝ ራሴን አሳልፌ እሰጠዋለሁ” ብላ ወሰነች፡፡
በድንገት የአማልክቱ ሁሉ ኃያል ነው የሚባለው የእንስሳት ፈጣሪ ወደ እሷ መጣ። ጥንቸሏ የገባችውን ቃል ሰምቷታል፡፡ ስለዚህ ሊፈትናት ፈለገ፡፡ የአማልክቶች አምላክ ነውና፣ ራሱን በፍጥነት ወደ አንድ ለማኝ ለወጠ፡፡ ከዚያም የሚበላ ነገር ይመፀውቱት ዘንድ ጠየቀ፡፡
ተኩላው፡- “ጥቂት ስጋ አግኝቻለሁ፤ እሱን ልመፅውትህ” አለው፡፡ ለማኙም አመሰግኖ፤ “ስመለስ እወስደዋለሁ” ብሎ ወደ ዝንጀሮው ሄደ፡፡ ዝንጀሮም ከዛፍ ያገኘውን ፍሬ እንደሚሰጠው ገለፀ፡፡ ለማኙም፤ “አመሰግናለሁ ቆይቼ እመለሳለሁ” ብሎ ወደ ዱር ድመት አመራ፡፡ የዱር ድመት ከጫካ ያገኘውን የአንድ የታረደ በሬ ትራፊ ሊሰጠው እንደሚችል ገለፀለት፡፡ ለማኙ ሦስቱንም አመሰገናቸው፡፡
“የሦስታችሁም ምፅዋት ይቀመጥልኝ፤ ተመልሼ መጥቼ እወስደዋለሁ” አለና ወደ ጥንቸሏ ሄደ፡፡ ጥንቸሊቱ ግን ምንም የምትመፀውተው አልነበራትም፡፡ ለድሀ እንዲመፀውቱ ስታስተምር የነበረችው ደግሞ እሷው ራሷ ናት፡፡ ስለዚህ እንዲህ አለችው፡
“ለማኝ ሆይ፣ እኔ ምንም የምመፀውተው ምግብ የለኝም፡፡ ያለኝ አማራጭ ራሴኑ አሳልፌ መስጠት ነው፡፡ እኔን ልትበላኝ ትችላለህ፡፡ እርግጥ ‘አትግደል‘ የሚል ህግ እንዳለ አውቃለሁ። ስለዚህ ልትገድለኝ አትችልምና አንድ ዘዴ ልንገርህ፡፡ እሳት አያይዝ፡፡ ከዚያ ለእኔ መመሪያ ስጠኝ። ዘልዬ እሳቱ ውስጥ እገባለሁ፡፡ በተቃጠልኩ ጊዜ የተጠበሰ ስጋዬ መልካም ምግብ ይሆንልሃል” አለችው፡፡
ለማኙም የተሸፈነ አምላክ ነውና ችሎታ ስላለው ወዲያውኑ እሳት ፈጠረ፡፡ ለጥንቸሏም “እሳቱ ተዘጋጅቷል” ሲል አስታወቃት፡፡ ጥንቸሊቱም ምናልባት ከቆዳዋ ውስጥ የተሸሸጉ ጥቃቅን ነብሳት ካሉ አብረዋት እንዳይቃጠሉ መጀመሪያ ቆዳዋን አራገፈች፡፡ ከዚያም ዘላ እሳቱ ውስጥ ጥልቅ አለች፡፡
የሚገርመው ግን እሳቱ አላቃጠላትም፡፡ ምክንያቱም ያ በለማኝ የተመሰለ አምላክ የሰራው የማያቃጥል አርቴፌሻል እሳት ስለነበረ ነው፡፡ እንዲህም አላት፤
“ጥንቸል ሆይ፤ እኔ እመገብ ዘንድ ያለሽን ሁሉ ሰጠሽኝ፡፡ ህይወትሽን ጭምር ለገስሽኝ። ከዚህ የበለጠ ምንም ስጦታ አይገኝም፡፡ ከሁሉም ያንቺ ስጦታ ትልቅ ነው፡፡ እኔ የአማልክቶች አምላክ ነኝ፡፡ ለደግነትሽ ውለታ ካሳ ይሆንሽ ዘንድ ጉልበተኛ አውሬዎችም ሆኑ ሰዎች እንዳያጠቁሽ ፈጣን-ሯጭ እንድትሆኚ አደርጋለሁ፡፡” ብሏት ተሰወረ፡፡ ጥንቸል ፈጣን-ሯጭ የሆነችው ከዚያን ጊዜ ወዲህ ነው ይባላል፡፡
*** ***
ቃሉን የሚያከብር ምንም ቢሆን የማታ ማታ ዋጋውን አያጣም፡፡ ቃሉን የሚያከብር መሪ፤ አለቃ፤ ኃላፊ ወይም ዜጋ ማግኘት መታደል ነው፡፡ እንደ እኛ ባለች የማህበራዊም ሆነ የፖለቲካዊ ሽግግር ውሽንፍርና ነፋስ ከአሰርት አሰርት በማይለያት አገር ውስጥ እጅግ የተለመደ ነገር ቢኖር ቃል-መግባት ነው፡፡ በየዘመኑ መሪዎች ቃል ይገባሉ፡፡ ቃሉ ካልተፈፀመ ህዝቦች ትዝብት ይፈፅማሉ፡፡ በአብዛኞቹ ቃል - የሚገቡት በመፈክር መልክ ነው፡፡ “ከምንወድደውና ከሚወደን ህዝባችን የምናስቀድመው ምንም ነገር አይኖርም።”…”የሀገር ልማትና የህዝብ እድገት ተቀዳሚ አደራችን ነው…” “እስከ መጨረሻው አንድ ሰው ድረስ እንታገላለን፡፡”… “ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናለብሳታለን!”… “ተፈጥሮን በቁጥጥር ሥር እናውላለን!”…”ከእንግዲህ ርሀብ፣ ድንቁርና ድህነት የምናይባት ሀገር አትኖረንም”…
…“አንድ ጥይት የማይተኮስባትና ሰላም የሰፈነባት አገር ነው ከእንግዲህ የሚኖረን…” …“በቀን ሦስቴ የምንመገብበትን ሁኔታ እንፈጥራለን”… “የአገርን ጉዳይ ለድርድር አናቀርብም…”…”ከልማት የምናስቀድመው ነገር አይኖርም…” “ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ ሰላም፣ መልካም አስተዳደር ይሰፍናል…”።
 “ከእንግዲህ ሳናጣራ አናስርም!”፤ “ኢትዮጵያ አትፈርስም”፤ “ለልጆቻችን የበለጸገች አገር ነው የምናስረክበው” “ለሁሉም የምትመች ኢትዮጵያን እንፈጥራለን“ ወዘተ… ቃል-መግባት፣ ቃል-መግባት፣ አሁንም ቃል መግባት፡፡ ተግባሩ የት ድረስ ነው? በተጨባጭ ምን ያህል አራመደን? ከገባነው ቃል አንፃር ወዴት እያመራን ነው? የማይጠየቁ፣ የማይመረመሩ፤ ሌላው ቀርቶ በወጉ በታሪክ መልክ እንኳ የማይፃፉ ጥያቄዎች፡፡ ተገብተው ያልተፈፀሙ ቃል-ኪዳኖች፣ የትላንቱን እንድናወግዝ እንደሚያደርጉን ሁሉ፣ እኛንም ለውግዘት ሊዳርጉን ለመጪው ዘመን እንደሚያመቻቹን ማስተዋል ይኖርብናል። አዲስ ዕቅድ ስናወጣ፣ አዳዲስ ሹማምንት ስንመርጥ፣ “የኔን ዘፈን ያዜመ የኔ አጋር ነው” ብለን መሆን የለበትም፡፡ ሰው ለውጥ ካላመጣ፤ አላማው፣ ፕሮግራሙ፤ የግምገማ ስርዓቱ አይለወጥም፡፡ ያ ለውጥ ከሌለ ደግሞ አገር ካለችበት ፈቀቅ አትልም፡፡ ግዙፍ ተስፋዎችን ተክለናል ብለን፤ ሰፋፊ ህልሞችን በሰፋፊ ማሳ ላይ ዘርተናል ብለን፤ አንዳችንም የተግባር እመርታ ካላሳየን፣ “የተማመኑበት ቢላዋ ይሰበራል” ይሆናል መጨረሻችን፡፡
ነቢብ ወገቢር እንዲሉ ቃል ከተግባር ካልተዋሃደ ወይ ማታለል፤ ወይ መደለል አሊያም የእለት ጭንቅን በጮሌነት ለማለፍ መሞከር ነው፡፡ በየስብሰባው የሚታየው የአንድ ሰሞን ውጣ ውረድና ሹም ሽር፣ የለውጥ ምልክት ሳይሆን “የፕወዛ” ፈሊጥ (reshuffling style) እንዳይሆን ከተፈለገ፣ በምወስደው እርምጃና በማደርገው ግምገማ አገር ምን ያህል ትራመዳለች፤ ምን ያህል የሰው ኃይል አጣለሁ? ምን ያህል ሀቀኛ አስተያየት ሰብስቤያለሁ… ማለት ያሻል፡፡ አለበለዚያ ስልጣንም እንደሽርክና ኩባንያ “የካዚኖ ቁማር ነው” እንዳይባል ያሰጋል። እንደ ፈረንጆቹ አባባል “who guards the guards” (ጠባቂዎቹን ራሳቸውንስ ማን ይጠብቃቸዋል?) ማለት ያባት ነው። የትላንት ገምጋሚ የዛሬ ተገምጋሚ የሚሆንበት፣ “አሳሪው ሲታሰር ታሳሪው ሲፈታ” አይነት አካሄድ ተፈጥሮአዊ  ሂደት እስኪመስል ድረስ መደጋገሙ የጤና አይደለም ብሎ ማሰብ አግባብ ነው፡፡
ከአለቆችና ከፖለቲካ መሪዎች ሙገሣን ለማግኘት ብቻ ላላመኑበት ፅላት መስገድ፣ በማያውቁት ዘፈን መደነስ፣ በማይረዱት ፅንስ-ሀሳብ ግነን በሉኝ ማለት፣ ከጊዜያዊ ጭብጨባ ባሻገር ረብ-ያለው ፍሬ እንደማይኖር ለማየት፤ ደግሞ ሌላ የዓመት መዝጊያ ሪፖርት መጠበቅ አያስፈልግም። በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ገና ከዐይነ-ውሃው ለመለየት ይቻላልና፡፡
ከቶውንም “ያሞገሷት ምራት አማቷ ፊት ራቁቷን ትጨፍራለች” የሚለውን ተረት ልብ ማለት ለአሞጋሽም ለተሞጋሽም ትልቅ ቁም ነገር አለው፡፡ ለታዛቢ ደግሞ የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ከቶውንም “ማንም በዚህ መንገድ ከመጣ ጠብ የለንም፤ ችግር የለብንም” የምንልባቸው ብዙዎች ጉዳዮች ጠብም ችግርም የሚሆኑት ውለው አድረው መሆኑን አለመርሳት ይኖርብናል። ወዲህ በቢሮክራሲው ቀይ ሽረሪት-ድር (red-tape) ሲተበተቡ፤ ወዲህም በሙስና ሲገዘገዙ ያኔ ነው ጉዱ! አንድም፣ ከምናቀልላቸው በላይ ሊወሳሰቡ እንደሚችሉ፣ አንድም ደሞ፣ ‘እኔ ፈቃጅና ሰጪ፣ አንተ ለማኝና ተቀባይ ነህ፣ የሚል ትርጓሜ ይኖረው ይሆን?’ ወደሚል መደምደሚያ እንዳያመሩ መጠንቀቅ፣ አካሄድን ማወቅ ነው፡፡
“አንዴ ካፍ የወጣን ነገር፣ ለምን አልኩት ብሎ ማለት
ለማለት ብቻ ማለት!”
የተባለውን አስታውሶ ከመናገር በፊት ልብንም ሀሳብንም ማጥራት ደግ ነው። መንግስት ከህዝብ ብዙ መጠበቁን የመናገሩን ያህል፤ ህዝብም ከዚያ ጋር ታሳቢ የሚሆነውን መብቱን፣ ነፃነቱን፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙን፣ የምግብ ዋስትናውን፣ ማህበራዊ ጥበቃውን፣ የትምህርትና የስራ እድሉን፣ ከረሃብ መላቀቁን፣ የልማት መሬት ካለአድልዎ ማግኘቱን፣ በልማትና በ“ህገወጥነት“ ሰበብ ከመኖሪያው አለመፈናቀሉን፣ ወዘተ ይጠብቃል፡፡
የፓርቲ ሹማምንት በተቀያየሩ፣ የቢሮ ኃላፊዎች በተበወዙ፣ መመሪያ በተዥጎደጎደና እቅድ-ነዳፊው እንቅልፍ ባጣ ቁጥር፤ ህዝብ አዲስ መና ሊወርድልኝ ነው ማለቱ አይቀሬ ነው። እንደ ጥንቸሏ ራሱን አሳልፎ የመስጠትን ያህል ቁርጠኝነትና ተግባራዊ ልባምነት ሳይኖር፣ አዳዲስ ቃል-ኪዳንና አዳዲስ መፈክር፤ በአዳዲስ ማህደር ብናኖር፤ የህዝብን ተሳትፎና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በጠየቅን ጊዜ “እንካን የማያውቅ አምጣን ማን አስተማረው” መባል አይቀርልንም። አምጡ እንጂ እንኩ አላልንምና! በቅጡና በጊዜ መረዳት የሚገባን  አንድ ቡጥ ቁም-ነገር፣ ፈተናችን ጥንቸሏ እንደገባችበት አርቴፊሻል እሳት ዓይነት ብቻ ሳይሆን የእውነት ወላፈንም እንዳለበት ነው፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት


በኦሮሚያ  ክልል የሚፈጸሙ  ጥቃቶች በመንግስት የጸጥታ ኃይሎችና    በክልሉ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች   የሚፈጸሙ ናቸው  
የአስገድዶ መሰወር ወንጀል የሚፈጸምባቸው ሰዎች  የሚያዙት  የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግስት ጸጥታና ደህንነት ሰራተኞች  መሆኑ ተጠቁሟል
መደበኛ ባልሆኑ ማቆያዎች የታሰሩ፤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ “ድብደባ እና ግርፋትን ጨምሮ ሌሎች ኢ-ሰብዓዊና አዋራጅ ተግባራት  ይፈፀምባቸዋል

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ባለፉት 12 ወራት  በአገሪቱ ከዚህ በፊት የማይታወቁ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  መጠናቸው እየሰፋ መምጣታቸውንና በዜጎች  ላይ አስገድዶ የመሰወር፣ ተጠርጣሪዎችን በጭካኔ፣ በአዋራጅና ኢ-ሰብአዊ በሆነ መንገድ የመያዝ ድርጊት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጿል።  ኮሚሽኑ  በተጨማሪም በአገሪቷ ውስጥ ያሉ የኢመደበኛ ማቆያ ቦታዎች መበራከታቸውንና   ከሕግ ውጪ የሆኑ የዘፈቀደ እስሮችና በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መሰወር ወንጀሎች  እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም   አመልክቷል።
የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የደረሱትን አቤቱታዎችና ጥቆማዎች መሠረት ባደረገው ክትትሎች ፣ በአገሪቱ የአስገድዶ መሰወር  ወንጀል በስፋት እየተፈጸሙ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎችን አግኝቼአለሁ ብሏል ።
አብዛኞቹ የአስገዳጅ ስወራ ሰለባ የሆኑ ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤታቸው፣ ከሥራ ቦታ ወይም ከመንገድ ላይ የሲቪልና የደንብ ልብስ በለበሱ የመንግሥት ፀጥታና ደኅንነት ሠራተኞች መወሰዳቸውንም  ኮሚሽኑ ገልጿል ።  ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ የተያዙት ሰዎች  ወዳልታወቀ ስፍራ እንዲሰወሩ እንደሚደረጉም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ  ገልጿል። የተወሰኑት ከቀናት፣ ከሳምንታት ወይም ከወራት መሰወር በኋላ የተገኙ ቢሆንም፣ እስከ አሁንም  በግዳጅ እንደተሰወሩ  የቀሩ  በርካቶች መኖራቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል።
በተለይም በመከላከያ ሠራዊት አባላት ተይዘዋል የተባሉ ሰዎች ከመደበኛ ማቆያ ቦታዎች ውጪ በወታደራዊ ካምፕ ውስጥ እንደሚታሰሩ፣ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡና የመጎብኘት መብታቸውን እንደተነፈጉ የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሣያል ።
 መንግስታዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ ( ኢሰመኮ ) 106 ገጾች ያሉትና  በአገሪቱ ያለውን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታን  ሰፋ ባለ ሁኔታ የሚቃኝ   ዓመታዊ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገ ሲሆን በሪፖርቱም  በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶች ያስከተሏቸው የሰብአዊ መብት  ጥሰቶች መበራከታቸውን ፣ በፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ ህገወጥ እስሮችና ወከባዎች እየጨመሩ መሄዳቸውን  ፣ ዜጎች  ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸው  መገደቡንና እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን  ይፋ አድርጓል ።
  ከሰኔ 2014 እስከ ሰኔ 2015 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል የተባለውና  ለሁለተኛ ጊዜ የወጣው የኮሚሽኑ ዓመታዊ የሰብዓዊ መብቶች ሪፖርት ፤ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል እንዲሁም የአካል ጉዳት ደርሷል ብሏል። ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ባለፉት አስራ ሁለት ወራት በህይወት ከመኖር መብት ጋር በተያያዘ ተፈጸሙ ላላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣   ምክንያት ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጧል።
በኦሮሚያ ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑት ጥቃቶች በክልሉ ውስጥ  በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እና   በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፤ በኦሮሚያ ክልል አስራ ሁለት ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች የሚደርሱ ግጭቶችና ጥቃቶች አሳሳቢና ከፍተኛ ትኩረት የሚሹ  መሆናቸውንም አመላክቷል። በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ  በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ላይ በተፈጸመ ጥቃት፣ ከ60 በላይ  ሰዎች መገደላቸውን የጠቀሰው የኮሚሽኑ ሪፖርት  በተመሳሳይ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጎቡ ሰዮ ወረዳ ከስድስት ወራት በፊት የከተማ ፖሊስና የቀበሌ ሚሊሺያ አባላትን ጨምሮ 50 ሰዎች መገደላቸውን  አመልክቷል ። ጥቃቱን ያደረሱት የወታደር ልብስ የለበሱ የኦነግ ሸኔ  ታጣቂዎች መሆናቸውን ነዋሪዎች ነግረውኛል ብሏል ።
በተመሣሣይ ሁኔታ፤ በአማራ ክልልም ለሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ክስተቶች መፈጸማቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቁሟል። በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኝ ገዳም፤  የመንግስት የጸጥታ አካላት  ወስደውታል በተባለ የኃይል እርምጃ  ከ15 ሰዎች በላይ መገደላቸው በሪፖርቱ ተካትቷል። በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች  ሰፋ ያለ የመብት ጥሰቶች መከሰታቸውንም ኮሚሽኑ በሪፖርቱ አመልክቷል ።  ከሁለቱ ክልሎች በተጨማሪ   በአዲስ አበባ ከተማ ፣   በሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝና ደቡብ ክልሎች  ለሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት የሆኑ ጥቃቶች መድረሳቸውን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤   ታጣቂዎችና የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች “ይፈጽሟቸዋል” ባላቸው  ጥቃቶች   የሰው ህይወት መጥፋቱን  ጠቁሟል።
ሪፖርቱ እንዳመለከተው፤ ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው  ወራት፤ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላትና አመራሮች ላይ የሚፈጸሙ እስሮች፣ ወከባዎችና ሌሎች እንግልቶች መጨመራቸውን ማረጋገጡን  የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ አስታውቋል።  
 ኮሚሽኑ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች፤ የተጠረጠሩበትን ወንጀል እንዲያምኑ ድብደባና ግርፋትን ጨምሮ ሌሎች ኢ-ሰብዓዊና አዋራጅ ተግባራት እንደተፈጸሙባቸው በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ኢሰመኮ እነዚህ ተግባራት ይፈጸማሉ ያለው በእስር ቤቶች እና መደበኛ ባልሆኑ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች ውስጥ መሆኑንም አመልክቷል ።
ኮሚሽኑ አሣሣቢነቱ መቀጠሉን በሪፖርቱ ይፋ ካደረጋቸው ጉዳዮች መካከል ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ላይ የሚጣል ገደብ አንዱ ነው። የሰዓት እላፊ ገደብ በመጣልና መስፈርቶችን በማስቀመጥ፤ በመንቀሳቀስ መብት ላይ የተደረጉ በርካታ ገደቦች በዘንድሮ በጀት ዓመት  በስፋት ተመዝግበዋል ብሏል-በሪፖርቱ። ኮሚሽኑ ለዚህ በማሳያነት ካነሳቸው ውስጥ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተደርጓል  የተባለው ገደብ ይገኝበታል።
 በሸኖ ከተማ  ውስጥ ተፈጸመ የተባለውን  ከአማራ ክልል የሚመጡ ሰዎችን አስሮ ማቆየት እንዲሁም ወደመጡበት ስፍራ ያለ ፍላጎታቸው እንዲመለሱ በማድረግ የመዘዋወር ነጻነታቸውን  የመገደብ ተግባር ኮሚሽኑ አሣሣቢ ብሎታል ።
የአስገድዶ መሰወር፣ የጭካኔ፣ አዋራጅና ኢሰብአዊ አያያዝ መጨመር፣ የኢ-መደበኛ ማቆያ ቦታዎች መበራከት እንዲሁም ከሕግ ውጪ የሆኑ የዘፈቀደ እስሮችም ሆኑ በመብቶች ላይ የሚጣሉ ገደቦች እጅግ አሳሳቢና በሌሎች ነጻነቶችና መብቶች ላይ እጅግ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚኖራቸውና  አጠቃላይ አገራዊውን የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ከማሻሻል ይልቅ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው ያለው ኮሚሽኑ ፤ ግጭቶችን በሰላም ለመቋጨት ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪም በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሱትንና እየደረሱ ያሉትን የመብቶች ጥሰት ተጠያቂነትና ፍትሕ የማስገኘት ጥረት በፌዴራልና በክልል መንግሥታት  በኩል ተገቢው ጥረት መደረግ እንዳለበት አመልክቷል ።



ሰሞኑን  በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢጋድ ሰላም አፈላላጊ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የሰጡት አስተያየት በእጅጉ እንዳስደነገጣቸውና ቅር እንዳሰኛቸው  የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ ። 
የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በሱዳን ላይ ” የአየር በረራ እገዳ” እንዲጣልና ተፋላሚዎች “የከባድ ጦር መሳሪያ ትጥቅ እንዲፈቱ” እንዲደረግ ጥሪ አድርገዋል በማለት አገሪቱ  ጥሪው “ሉዓላዊነቴን የጣሰ ነው”  ብላለች ።
ሰሞኑን  በሱዳን “የአመራር ክፍተት ተፈጥሯል” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ  የሰጡት አስተያየት  ከዚህ ቀደም ለሱዳን ሉዐላዊ ምክር ቤት ሰብሳቢና ለሀገሪቱ ጦር አዛዥ አብዱልፈታ አልቡርሃን በግል ከነገሯቸው አቋም ጋር የሚቃረን መሆኑን የገለፀው የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር  መግለጫ በዚህም አስተያየት ሱዳን መደናገጧን  ገልጿል ።።
በአዲስ አበባው የሰላም አፈላላጊ የአራት ሀገራት መሪዎች ምክክር ላይ ሱዳን ለመሳተፍ ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም በጉባዔው ላይ ሳትገኝ ቀርታለች። የሰላም አፈላላጊ አባል ሀገራቱ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ናቸው።  ሱዳን የኢጋድ የሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ሊቀመንበር የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ “ገለልተኛ አይደሉም” በሚል የኢጋድን ሽምግልና  አሻፈረኝ ስትል ቆይታለች።  ሱዳን በግብፅ በተጠራውና በካይሮ ነገ በሚደረገው ለሱዳን ሰላም የማፈላለግ ጉባዔ ላይ  ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኗንም አስታወቃለች።
የኢጋድ ሀገራት የሱዳንን ሉዐላዊነት ጥያቄ ውስጥ በሚከት አቋማቸው ከቀጠሉ “ሱዳን የኢጋድ አባልነቷን ዳግም ለማጤን ትገደዳለች” ብሏል የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መግለጫ።


ለግዥ ከወጣው የተጋነነ ገንዘብ በተጨማሪ ምትክ ቦታ ተሠጥቷል ተብሏል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ከፍተኛ ባለአክሲዮን ለሆነበት የአዲስ አፍሪካ የስብሰባና ኤግዚቢሽን ማእከል ማስፋፊያ በሚል በግንባታ ላይ ለሚገኝ ህንጻ፣ 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ከፍሎ እንደገዛው ምንጮች ጠቁመዋል። ጉዳዩን ይበልጥ አስገራሚ ያደረገው ለግዥ የወጣው የተጋነነ የህዝብ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ምትክ በሚል የተሰጠው ቦታ እንደሆነም እነዚሁ ምንጮች አመልክተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ  በሲኤምሲ አደባባይ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘውን የስብሰባና ኤግዚቢሽን ማእከል ለማስፋፋት በሚል በአቅራቢያው የሚገኝና በግንባታ ላይ የነበረ ባለ 22 ፎቅ ህንጻን ግዥ ፈጽሟል ተብሏል ።
ይህ ከመሃል ከተማ ራቅ ባለ አካባቢ  የሚገኝ ህንጻ፣ የተጋነነ  ዋጋ ቢያወጣ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ሊያወጣ እንደማይችል የሚገልጹት ምንጮች፤   የከተማ አስተዳደሩ ከመሃል ከተማ ወጣ ብሎ ለሚገኝና እጅግ አነስተኛ ቦታ ላይ ላረፈው ለዚህ  ህንጻ ይሄን ያክል ዋጋ መክፈሉ ፍፁም ለማመን የሚቸግርና አጠራጣሪ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ ሰፊ ፕሮጀክት አቅዶም ከሆነ መስቀል አደባባይ የሚገኘው ኤግዚቢሽን ማአከልን  ለማስፋፋት ከአመታት በፊት ሰፊ ፕላን አውጥቶ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ማእከል ለመገንባት እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበር የሚያስታውሱት ምንጮች፤  የከተማ አስተዳደሩ አሁን ለህንጻ ግዥ ያወጣው 9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ለዚህ ማእከል ግንባታ ሊያውለው ይገባ ነበር ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
ከ9 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የግዥ ክፍያ በተጨማሪ የከተማ አስተዳደሩ በህወሃት ቀስቃሽነት ከተለኮሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከአገር ሸሽተው የቆዩትንና በቅርቡ ወደ አገር የተመለሱት ታዋቂው የአልኮል መጠጥ አስመጪ ለአቶ ቢኒያም ብርሃኔ፣ በወንዝ ዳር ልማት ሰበብ በቅርቡ ከፈረሱት አካባቢዎች መካከል በመሃል አዲስ አበባ አምባሳደር ትያትር  ቤት ፊት ለፊት የሚገኝ 10 ሺ ካሬ ሜትር ቦታ ለማካካሻ በሚል ሰበብ እንደሰጣቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ  ገልፀዋል፡፡
የሰሞኑን የከተማ አስተዳደሩን የግዥና ምትክ ቦታ አሰጣጥ የተመለከቱ የከተማው ባለሃብቶች፤ “ከተማ አስተዳደሩ በሲኤምሲ አካባቢ የሚገኝ ቦታችንን ይግዛን” በማለት ማዘጋጃ ቤቱን  ማጨናነቃቸውን ጠቁመዋል፡፡


Page 11 of 665