Administrator

Administrator

Saturday, 01 July 2023 00:00

ሁሌም መማር አታቋርጡ!!

እውነቱ ምን መሰላችሁ? ከምትገምቱት በላይ  አዕምሮ፣ ችሎታና አስተዋይነት ተችሯችኋል - በቀሪው ዕድሜያችሁ  ልትጠቀሙበት ከምትችሉት በእጅጉ የላቀ፡፡ እናንተ ከምታስቡት በላይ  በእጅጉ ብልህ ናችሁ፡፡ የማታሸንፉት መከራ፣ የማታልፉት መሰናክል፣ የማትሻገሩት እንቅፋት የለም፡፡
የማትፈቱትም ችግር እንዲሁ፡፡ አዕምሮአችሁን ተጠቅማችሁ የማታሳኩት አንዳችም ግብ የለም፡፡
አዕምሮአችን ከጡንቻችን ጋር ይመሳሰላል፡፡ የሚገነባውና  የሚዳብረው ስንጠቀምበት ብቻ ነው፡፡ የሰውነት ጡንቻዎቻችሁን ለማዳበር ማንቀሳቀስ እንዳለባችሁ ሁሉ፣ አዕምሮአችሁንም ለመገንባት የአዕምሮ ጡንቻዎቻችሁን ማሰራት አለባችሁ፡፡
ብዙ በተማራችሁ ቁጥር የበለጠ የመማር አቅም ታዳብራላችሁ፡፡ ብዙ ስፖርት ስትሰሩ የተሻለ የአካል ብቃት እንደምትጎናጸፉት ሁሉ፣ ራሳችሁን የበለጠ ለህይወት ዘመን ትምህርት በሰጣችሁ ቁጥር፣ በቀላሉና በፍጥነት ብዙ የመማር ክህሎት ታዳብራላችሁ፡፡
በ21ኛው ክ/ዘመን ወሳኙ ነገር የማያቋርጥ ትምህርት ነው፡፡ በያዛችሁትም ሙያ ሆነ በሌላው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ከእናንተ የሚጠበቀው ትንሹ ነገር፣ ራሳችሁን ለህይወት ዘመን ትምህርት ማዘጋጀት ነው፡፡ የሙያችሁ ተማሪ ለመሆንና በትምህርት ለመግፋት እንዲሁም በቀሪው ህይወታችሁ የተሻለ ብቃት ለማዳበር ዛሬውኑ ወስኑ፡፡
በህይወት ዘመናችሁ ሁሌም ከመማር እንዳትነጠሉ የሚረዱ ወሳኝ ተግባራትን እንመልከት፡፡ የመጀመሪያው ወሳኝ ጉዳይ፣ በእያንዳንዱ ቀን ከመኝታችሁ ስትነሱ ከ30 – 60 ደቂቃ ማንበብ ነው፡፡ የሰውነት እንቅስቃሴ ለአካል ብቃት እንደሚያስፈልገው ሁሉ፣ ንባብም ለአዕምሮ ብቃት እንዲሁ ነው፡፡
 በቀን ለአንድ ሰዓት ስታነቡ፣ በሳምንት አንድ መጽሐፍ አነበባችሁ ማለት ነው፡፡ በዓመት 50 መጻሕፍት ይሆናል፡፡ በአሥር ዓመታትስ?  500 መጻሕፍትን ጠጥታችኋል፡፡ አንድ አማካይ አዋቂ ሰው በዓመት ከአንድ መጽሐፍ በታች ስለሚያነብ፣ እናንተ በቀን ለአንድ ሰዓት ማንበብ ስትጀምሩ በሙያ ዘርፋችሁ የማይታመን ለውጥ ታመጣላችሁ፡፡
በቀን ለአንድ ሰዓት በማንበብ ብቻም በሙያችሁ እጅግ የተካናችሁ፣ ብቁና ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ ትሆናላችሁ፡፡ የህይወት ዘመን ትምህርት ሁለተኛው ወሳኝ ጉዳይ፣ በድምጽ የተሰናዱ (Audio) ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ማዳመጥ ነው - በተለይ ከቦታ ወደ ቦታ በመኪና ስትዘዋወሩ፡፡
 አንድ አማካይ ሰው በዓመት ከ500 – 1ሺ ለሚሆኑ ሰዓታት በመኪናው ውስጥ ይቀመጣል፡፡ በሳምንት ከ12 – 40 ለሚሆኑ ሰዓታት ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት የሚሆን የሥራ ጊዜ በመኪና ውስጥ ያጠፋል እንደ ማለትም ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ከአንድ ወይም ከሁለት የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሴሚስተር ጋር እኩል ነው፡፡
እናም መኪናችሁን ተንቀሳቃሽ ዩኒቨርሲቲ ልታደርጉት ትችላላችሁ፡፡ ምንጊዜም በኦዲዮ የተሰናዱ ትምህርታዊ ፕሮግራሞችን ሳትከፍቱ መኪናችሁን ፈጽሞ አታንቀሳቅሱ፡፡ የህዝብ ትራንስፖርት ተጠቃሚ ከሆናችሁም፣ ስፖርትና ሙዚቃ በሞባይል ስልካችሁ  እንደምታዳምጡት ሁሉ፣ትምህርታዊ ፕሮግራሞችንም እንዲሁ ማድመጥ ትችላላችሁ፡፡
ለህይወት ዘመን ትምህርት ሦስተኛው ወሳኝ ጉዳይ፣ በሙያ መስካችሁ የተሻላችሁ ለመሆን የሚረዷችሁን ማናቸውንም ኮርሶች፣ ሴሚናሮች፣ ዎርክሾፖች መውሰድ ነው፡፡ መጻሕፍት፣ ኦዲዮ ፕሮግራሞችና ሴሚናሮች በመቶዎች የሚሰሉ ሰዓታትንና በሺዎች የሚገመቱ ብሮችን ያድናሉ፡፡ ተመሣሣይ የስኬት ደረጃን ለመጎናጸፍ ያስፈልግ ከነበረው የብዙ ዓመታት ልፋትና ድካምም ያተርፋሉ፡፡
የዕድሜ ልክ  ተማሪ ለመሆን ዛሬውኑ ቆርጣችሁ ተነሱ፡፡ በሙያ ዘርፋችሁ ላይ በሚያመጣው የላቀ ለውጥ በእጅጉ ትደነቃላችሁ፡፡

ሰባት ወንድ ልጆች የነበሯቸው አንድ ባለፀጋ ነበሩ፡፡ ከሰባቱ ልጆች ትልቅዬው ነበር ብልህ፡፡ ለሰባቱም መሬት ገዝተው ሰጥተዋቸዋል፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የጨመሩላቸው ነገር የለም፡፡ ይልቁንም በየጊዜው ግብር እያስገበሩ የሩቅም የቅርብም ዘመድ- አዝማድና ጎረቤቱን ሁሉ እየጠሩ ፈንጠዝያ ያደርጉ ነበር፡፡ የቅርብ ወዳጆቻቸው፤ “ተው አይሆንም፤ ገንዘብህን የትም ለማንም አትዝራ፤ ለልጆችህ አቆይላቸው” ሲሏቸው፤
“የለም ለልጆቼ መሬት ገዝቼ ሰጥቻቸዋለሁ፡፡ ቢያውቁ ይወቁበት፡፡ እኔ የራሴን ሀብትና ንብረት ነው ለድግስ ያዋልኩት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የነበረኝን ወርቅ ከአንዳቸው መሬት ውስጥ ቀብሬዋለሁና አንዱ ያገኘዋል፡፡” አሉ፡፡
ሰነባብቶ አባትየው ሞቱ፡፡ ልጆቹ ለኑዛዜው ተጣደፉ፡፡ እንደ ጠበቁት ኑዛዜው ተነበበ፡፡ ኑዛዜው፡-
“ከሰባቱ ልጆቼ በአንደኛው መሬት ውስጥ ወርቅ አኑሬያለሁ፤ ከሳጥኔ ውስጥም በብራና ተፅፎ የተቀመጠ ገንዘብ አስቀምጫለሁ” ይላል፡፡
ልጆቹ ኑዛዜው ከፈሰሰ በኋላ በኑዛዜው መሰረት ሳጥኑን ከፍተው ቢያዩ አንድ የተጠቀለለ የብራና ቁራጭ አገኙ፡፡ በብራናው ላይ የሚከተለው ፅህፈት አለበት፡፡
“ራስህን ይብረደው
እግርህን ይሙቀው
ለልጆቼ ይህን አውርሻለሁ” የሚል ነው፡፡ የዚህን ፅሁፍ ፍቺ የሚያውቅ ሰው በድፍን አገር አልተገኘም፡፡ በኋላ ግን አንድ እዚህ ግባ የማይሉት ተማሪ ፍቺውን ተናገረ፡፡ በተማሪው ፍቺም መሰረት፡-
“እራስህን ይብረደው ማለት፤ በራስ የገባ ህመም ይገላል ማለት ነው፡፡
“እግርህን ይሙቀው ማለት በእግር የገባ ህመም ስንኩል ያደርጋል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ እንዳያጋጥምህ አድርግ ማለት ነው” ሲል ፈታው፡፡ አገሬውም አደነቀው፡፡  ልጆቹ ግን ሳጥን ውስጥ ምንም ወርቅ ባለመገኘቱ በጣም ከፋቸው፡፡
አንጋፋው ልጅ የአባቱ ብልሃት ገብቶታል፡፡
“እንግዲህ በአባታችን ቃል መሰረት መሬት እንቆፍርና አንዳችን ዘንድ የተቀበረው ገንዘብ ይገኝ ይሆናል” ተባባሉ፡፡ የሰባቱም ተቆፈረ፡፡ አንዲት እንክብል ወርቅ አልተገኘችም፡፡ ተናደዱ፡፡ ከማጣታቸው ይልቅ ድካማቸው አሳዘናቸው፡፡
“እንግዲህ እዚህ ምድር ላይ ምን ተረፈን፤ ምንስ አለን? ለቀን ወደ ሌላ ቦታ እንሂድ” ተባባሉ፡፡
 አንጋፋው ወንድማቸው ግን የአባቱ ብልሃት ስለገባው እዚያው ቀረ፡፡ ሲቆፍሩ የተባበራቸው ልምሰላቸው ብሎ እንጂ ነገሩ በቁፋሮ እንደማይሆን ገብቶታል፡፡ የነገ ህይወቱ በምን እንደሚመራ በልቡ ሲያወጣ ሲያወርድ ቆይቷል፡፡
ወንድሞቹ ሁሉ ወደ ሌላ አገር ተሰደው በየጌታው ቤት ሎሌነት አደሩ፡፡ የአባቱ ብልሃት የዘለቀው ልባሙ አንጋፋው ልጅ ግን ወንድሞቹ ቆፍረውት የሄዱት መሬት ላይ ወቅቱን ጠብቆ እህል ዘራበት፡፡ አዝመራው አማረ፡፡ በቀጠለውም አመት እንዲሁ አደረገ፡፡ ሃብት በሃብት ሆነ፡፡ አባትየው “ከምድራችሁ ወርቅ ቀብሬአለሁ” ማለታቸው ይሄ ነበር ትርጉሙ፡፡ ጉዳዩ ገብቶት ስራውን ስለሰራ የገበሬ ሁሉ ንጉስ ሆነ፡፡ ከሱ ገንዘብ የማይበደር ሰው የለምና ወሬው በየአገሩ ተስፋፋ፡፡
ወንድሞቹ በቅምጥል ስላደጉ በሄዱበት ሎሌነት መስራቱ አልሆንላቸው አለ፡፡ መከራ በመከራ ላይ ተደራረበባቸው፡፡ ስለዚህ መከሩ፡፡ “እዚህ ተቀምጠን የምንፈይደው ነገር የለም፡፡ ወደ ወንድማችን ዘንድ ሄደን እናዋየው“ ተባባሉ፡፡ ተጎሰቋቁለው፣ ከሰውነት ጎዳና ወጥተው ወደ ወንድማቸው ተመልሰው መጡ፡፡ ጨርሶ ሊለያቸው አልቻለም፡፡ ማንነታቸውን ሲነግሩት አለቀሰ፡፡ ምግብ እንዲበሉ መጠጥም እንዲጠጡ አደረገ፡፡ ወደየ መሬታቸው መልሶ እልቅናቸውን ዳግም አፀናላቸው፡፡ እድሜ ለብልሁ ወንድማቸው፣ ኮርተው ደስ ብሎአቸው ኖሩ፡፡ መከራ ቀጥቅጧቸዋልና ያለ አንዳች ዋልጌነት፣ ያለ አንዳች ዋዛ ፈዛዛ ስራ ይሰሩ ጀመር፡፡ ሰው አከበራቸው፡፡ ጎረቤት ፈራቸው፡፡ የአባታቸውም ምክር ለመላው አገሪቱ ተባዛ፡፡
***
እውነትም በራስ የገባ ብርድ ይገላል፡፡ ራስ ያጣ ህብረተሰብ መንግስት፣ ፓርቲ፣ ድርጅት ወዘተ … እንደሙት እንደበድን የሚቆጠር ነው፡፡ ከሌላው የሰውነት ክፍላችን ይልቅ ራሳችን የተራቆተ ለታ፣ ራሳችንን የበረደን ለታ፣ አለቀልን ማለት ነው፡፡ አመራር አጣን ማለት ነው፡፡ መሪ የለንም ማለት ነው፡፡ አቅጣጫ ጠቋሚ የለንም ማለት ነው፡፡ በዚሁ አይነት እግራችንን ካልሞቀንም ጅማታችን ይኮማተራል፡፡ ሰንካላና መራመድ የማንችል መሆናችን ነውና ጉዞአችን በአጭር የተቀጨ እንሆናለን፡፡ ሁሌም በራስ ከሚገባ ብርድና ሙቀት ከተለየው እግር ይሰውረን ዘንድ ሳናሰልስ ለራሳችን ቃል ልንገባ፣ መልካም ምኞት ልንመኝ ይገባል፡፡
ከአባትም መልካም አባት ቁራጭ ብራና ያወርሳል፡፡ ብራናም ቢሉ የእውነት ሰብል ሊመረትበት  የሚችል ሁነኛው አዱኛ፣ ሰፊ አዝመራ ነው፡፡ ከሀብት ይልቅ የሃብት ማግኛውን ሰረገላ ቁልፍ የሚያወርስ አባት ያሻናል፣ ይሻለናል፡፡ ምድራችን ውስጥ ወርቅ የሚቀብር፣ ለነገ እድገታችን የሚያስብ አንጋፋ ሰው ያስፈልገናል፡፡
ሁሌም ሎሌነት ከማደር፣ የሰው ፊት ከማየት፤ ያልተቀጣ ያልተቆነጠጠ ከመሆን፣ ለስደት ከመዳረግ፣ ይሰውረን፡፡ … ሁሌም ቅርስና ውርሱን የሚመረምር በራሱ የሚተማመን ትውልድ እንድናፈራ በፅናት የምንጣጣር ዜጎች መሆን አለብን፡፡
ተሳስተን ለመከራ ተዳርገን ከሆነም መክረን፣ ዘክረን፣ ተወያይተን አቅጣጫችንን የሳትንበትን ነጥብ እናይ ዘንድ፤ ቆም መለስ ብለን ታሪካችንን፣ ጉዞአችንን፣ ዱካችንን እንድናይ ልብና ልቡና ይስጠን፡፡ ወደ ኢትዮጵያዊነታችን፣ ወደ ህብረታችን መልሶ እራሳችንን እንድንመራ የሚያደርግ መሪ፣ አለቃ፣ አጋር፣ ወንድም እንዲኖረን የምንመርጠውን ሁሉ እንደ ንስር በነቃ አይን ለማየት የምንችልበት ሁኔታ ለማምጣት መጣጣር ይኖርብናል፡፡
ልብ ለልብ፣ አዕምሮ ለአዕምሮ፣ ቋንቋ ለቋንቋ የማንጠፋፋበት፤ የምንደማመጥበት፣ አዲስ  ሃሳብ የምንቀበልበት የሰለጠነ መድረክ ይፈጠር ዘንድ ጠባቡ እንዲሰፋ፣ አምባገነኑ እንዲገራ፣ ጥጋበኛው እንዲበርድለት፣ አመፀኛው እንዲገታ፣ ለእኔ ብቻ ባዩ እንዲያጋራ፣ እምቢተኛው እንዲጨምት፣ ጥፋተኛው እንዲተጋ፣ ሃሞት - የለሹ እንዲጀግን፣ ሞራለ-ቢሱ እንዲፀና መሃይሙ እንዲማር  ዘመኑን በቀና ልቦና ማየትና ዝግጁ መሆን ይገባናል፡፡
እንደ መስቀል ወፍ በአመት አንዴ የምናቅደውን እቅድ የምንመራበትን ፖሊሲ፣ የምንቀይሰውን ርእዮት ደግመን ደጋግመን የምናስተውልበት ሁኔታ መፍጠር አለብን፡፡
ሁሌም አምስቱን ህዋሶቻችንን በሚገባ እናንቃቸው፡፡ አይናችን በቅጡ ይይ፤ ጆሯችን በተገቢው መጠን ይከፈት ምላሳችን ሀቅ ይልመድ፡፡ አፍንጫችን መአዛ ይለይ፤ እጃችን መጨበጥ ይወቅ፡፡ ከአምስቱ ህዋሶቻችን የሚያመልጥ አንዳችም የሃገር ጉዳይ የለም፡፡ አለበለዚያ “ደሃ እስኪለብስ ሸንጎ ይበተናል” (እንዲል ወላይታ)፤ የምንይዝ የምንለቀው እንደጠፋን ዘመን እንደ ዋዛ ይነጉዳል፡፡ በራሳችን ብርድ የሚገባው ያኔ ነው፡፡

(ዕዝራ እንዳይረሳ - በሰባት ዓመቱ)
አብደላ ዕዝራ ከ1980ዎቹ መጀመሪያ አንሥቶ እስካረፈበት ግንቦት 2008 ዓ.ም. ድረስ፣ በተለያዩ የሥነ ጽሑፍ መድረኮች (በአብዛኛው መጽሔቶች እና ጋዜጦች) ላይ በሚያቀርባቸው ሂሳዊ ንባቦቹ የምናውቀው እና ሃያሲ የሚልን “ማዕረግ” ባልተጻፈ ስምምነት ከሰጠናቸው አንድ ኹለት ሰዎች መሐል የምናገኘው ሃያሲ ነበር፡፡
ባለቅኔ እና ሐያሲው ዮሐንስ አድማሱ ከ1933 -1960 በተጻፉ የአማርኛ የፈጠራ መጻሕፍት ላይ በብስጭት በጻፈው ትችት መግቢያ ላይ፣ “ኂስ ለሥነ ጽሑፍ ሕይወት መጠበቂያ ዓይነተኛውና ፍቱን መድኃኒቱ ነው፣” ይላል፡፡ ዕዝራ ይህንን ሥነ ጽሑፉን በሕይወት የማቆየት ሚና በገዛ ፈቃዱ መውሰዱን ከሂሳዊ ንባቦቹም ኾነ ከመጻሕፍት ዳሰሳዎቹ  እንገነዘባለን፡፡ ዕዝራ በርቅቀታቸው፣ በቋንቋ ውበታቸው፣ በምሰላቸው አንብቦ ያደነቃቸው ድርሰቶች ለምን ሂሳዊ ንባብ ተነፈጉ የሚለው ቁጭት ከሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ጋር ተደምሮ በየሳምንቱ በቸርነት ሂሳዊ ንባቦችን ለመጻፍ ያተጋው ይመስለኛል፡፡
በእዝራ የሂስ መርህ አንድን ሥነ ጽሑፍ በሕይወት የሚያቆየውም ይኹን ከተሳካለትም የሚያሳድገው፣ ደራሲው አብዝቶ ስላፈራው አረም ሲሸማቀቅ እና ሲጸጸት እንዲኖር መውቀስ ሳይኾን፣ በኩንታል አረም መሐል ያፈራትን ስንዴ ለከርሞ እንዲያበዛት ማበረታታት ይመስላል፡፡ ምንም እንኳን “ኂስ ጉድለትንም ጥራትንም መግለጫ ጥበብ” ቢኾንም ዕዝራ ግን የድርሰቶቻችንን ድክመት እያደበዘዘ፣ በቀጣይ ሥራዎቻችን ልናጎለብታቸው የሚገቡትን ጥቂት ብቃቶቻችንን አድምቆ ማሳየትን መርጧል፡፡
ዕዝራ የድርሰቶቻችን ብርታቶች ላይ ማተኮሩ በህትመት ያገኘናቸው የፈጠራ ድርሰቶች በቁጥር እንጂ በኪነታዊ ብቃታቸው የሚደነቁ አለመኾናቸውን አጥቶት አይደለም፡፡ ያም ኾኖ ዘጋቢዎቹ፣ የማይናደፉቱ (በፍዝ ቋንቋ የተጻፉቱ)፣ ወይም እሳቦቶቻቸው እንደ ተን ፈጥነው የሚጠፉብን ግጥሞች ላይ ጊዜውን፣ ስሜቱን ምናቡንም ሲያባክን አናገኘውም፡፡
ዕዝራ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ከመመዘን ይልቅ መፈከርን በመምረጡ አመጸ ብንልም፤ ለግጥምም ኾነ ለዝርው ድርሰቶች የሚቀበላቸውን የሥነ ጽሑፍ ደንቦች ሲያጸናም እናገኘዋለን፡፡ ያም ኾኖ ግን ከጥራዝ ነጠቅ ንባብ ተነሥተን ግጥም እንዲህ መኾን አለበት፣ ልቦለድ እንዲያ መኾን የለበትም እንደምንለው እንዳብዛኞቻችን ድምዳሜ አይሰጥም፤ የሚጽፈው ደንቦቹ በየጊዜው፣ በየአውዱ ስለሚቀያየሩለት/በት የፈጠራ ሥራ እንደኾነ አይዘነጋም፤ ይልቅ በተዘዋዋሪ እንዲህ ቢኾን ይሻላል በሚል ትሕትና እና በድግግሞሹ ሥር በሥር ደንብ ሲያስተዋውቅ እና ሲያስለምድ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ፣ የግጥምን የትርጉም አሻሚነት (ambiguity) አንዱ ገጣሚ ጋ በማድነቂያነት፣ ሌላው ጋ በጉድለት መጠቆሚያነት በተደጋጋሚ ከማንሣቱ እና ከማስረዳቱ የተነሣ አሻሚነትን ገጣሚያን ሊያስቡበት የሚገባ የግጥም አላባ መኾን አለበት የሚል ደንብ ማበጀቱን እናያለን፤ እንዲያውም የግጥም የትርጉም አሻሚነት ግጥሙን አንባቢው ልብ ውስጥ ያከርመዋል የሚል አቋሙን ጽሑፎቹ ውስጥ ደጋግመን እናነባለን፡፡የእዝራ የሂስ ስልት የደራሲውን ተቋማዊ ህልውና ክዶ፣ የግጥሙንም ይኹን የልቦለዱን ትርጉም ከድርሰቱ ላይ ብቻ መፈለግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ደራሲው ምን ለማለት ፈልጎ ነው ብሎ የድርሰቱን አቅም ከመገደብ ይልቅ ድርሰቱ ምን ይነግረኛል ብሎ ሥራውን የመመርመሩን አካሔድ እንደሚከተል ለመረዳት በተለይ ጥልቅ ሂሳዊ ንባቦቹን ማንበብ ብቻ በቂ ነው፡፡
ዕዝራ በዚህ ሂሳዊ አተናተን እንደተመሰጠ ከሚያሳዩን የሂሱ ጠባያት አንዱ አንድን ድርሰት ብቻውን ሲፈክረው አለማግኘታችን ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የሚያተኩረው ግጥሞች ላይ እንደመኾኑ፣ አንድን ግጥም ሲተነትን ግጥሙን መድብሉ ውስጥ ካሉ ግጥሞች ጋር ያናብባል፤ ግጥሙን በዚያ መድብል ውስጥ ካልተካተቱ የገጣሚው ሌሎች ግጥሞች ወይም ዝርው ድርሰቶች ጋር እና ከሌሎች ድርሰቶች ጋር ያናብባል፡፡ የዕዝራ ሀያሲነት ከጥልቅ ንባብ የተገኘ መኾኑን ከምናይባቸው የሂሱ ጠባያት ይሄ አናባቢነቱ አንዱ ነው፡፡
በዕዝራ ሂሳዊ ንባቦች ላይ አልፎ አልፎ አንዱን ግጥም ከሌሎች የተሻሉ ግጥሞች ጋር በማናበብ ያንንን ግጥም በተሻሉት ግጥሞች ትከሻ ላይ አቁሞ ለማሳየት የመሞከር አዝማሚያ አይቻለኹ፡፡ ይህንን ማድረግ ደከም ያለውን ገጣሚ የተሻለ ነገር ይዞ እንዲቀርብ ያበረታታው ይኾናል፤ የዕዝራም ምክንያት ይሄ ይመስለኛል፤ ነገር ግን በተቃራኒው እንዲህ ያለው ሂስ ደካማው ደራሲ ደረጃውን አውቆ፣ ድክመቶቹን ለይቶ ለመሻሻል እንዲሞክር ከመገፋፋት ይልቅ ልቡን አሳብጦ እዚያው ድክመቱ ላይ እንዲከርም ሊያደርገውም ይችላል፡፡
ሌላው የዕዝራ ንባቦች ጠባይ፣ ሂሱ ከሥነ ጽሑፍ ሥራው ተነጥሎ እንዳይታይ ያሰበበት ይመስል፣ ለሂሳዊ ድርሰቶቹ ውበት መጠንቀቁ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የእሱ ሂሳዊ ንባቦች ከሚተነትናቸው ድርሰቶች በላይ በዘይቤ በታሸ፣ ከሰርክ መግባቢያ ከፍ ባለ ቋንቋ እና በአመስጣሪው የላቀ ምናባዊነት ተጽፈው ይገኙና ከሂስነታቸው ይልቅ ወደ ፈጠራ ድርሰትነት ያዘነብላሉ፡፡ ለወትሮው ሐያሲን ፈራጅ፣ ደራሲን ተከሳሽ አስመስሎ የሚያሳየውን አካሄድ ትቶ፣
ራሱን የፈጠራ ሂደቱ አካል ማድረጉን ከጽሑፎቹ እንረዳለን፡፡በርግጥ ይሄ በፈጠራ  ሒደቱ የመሳተፍ ነገር መልካም ቢኾንም ሐያሲው ሚዛኑን ካልጠበቀ የሚያሔሳቸውን ሥራዎች ውበት ከማሳየት ይልቅ በራሱ ምናብ የመመሰጥ፣ ወይም ድርሰቶቹን አላቅማቸው የማንጠራራት አደጋ ሊኖረው ይችላል፡፡ ኹለቱንም ዓይነት ችግሮች አልፎ አልፎ በዕዝራ ሂሶች ውስጥ አላየኹም አልልም፡፡ (በአንባቢ ልቤ “ይሄ ዕዝራ አኹንስ አበዛው!” ብዬ የተበሳጨኹባቸው ሂሶች አሉ፡፡)
በአጠቃላይ፣ ዕዝራ ሂስ ጎድሎብን ሳለ፣ ተከታታይ የግጥም ሂስ ደግሞ ጠፍቶብን ሳለ ግጥምን ያክል አመጸኛ የድርሰት ዘውግ ለማጥናት እና ለመተንተን መነሳቱን አይተን፣ ለሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ሲል “”አዲስ ስርዓት” የመትከልን፣ ግጥሙን መልሶ የመፍጠርን ያህል ፈታኝ” ኃላፊነትን እንደወሰደልን ልንረዳ ይገባል፡፡ እዝራ ይህን የባህል እና ሥነ ጽሑፍ ተቋማት የሸሹትን ኃላፊነት በግሉ ወስዶ፣ ከማንም ሽልማትም ይኹን ክፍያ ሳይጠብቅ፣ በትጋት ይወጣልን ጀምሮ ነበር፡፡
ዕዝራን መዘከር፣ የዕዝራን የሂስ ትጋት፣ ለሥነ ጽሑፋችን ያለውን ምኞት፣ በሃያሲነቱ እና በሥነ ጽሑፍ ፍቅሩ ይዟቸው የነበሩትንም ዕቅዶች በከፊልም ቢኾን በማሳካት ቢገለጥ የሚሻል ይመስለኛል፡፡
በመጨረሻም፣ ዘመኑ የሂስ ባህል ያልዳበረበት እንደመኾኑ፣ እንዲህ እንደ ዕዝራ ያሉ ብርቅ ሐያስያን ሲገኙ፣ ሥራዎቻቸው የሂስ እና የምርምር ዕድል ሊነፈጉ ስለማይገባ፤ የሥነ ጽሑፍ ተማሪዎች እና ተመራማሪዎች ሂሱን ለመተንተንም ይኹን ለመሔስ (በሂስም ላይ ሂስ አለበትና) ሥራዎቹን አጥንተው የዕዝራን አስተዋፅዖዎች በጥልቀት ቢያሳዩን ደግ ነው ብዬ አምናለኹ፡፡ ለእዝራ ኅልፈቱ ዕረፍቱ እንዲኾንለት እመኛለኹ፡፡
(ቴዎድሮስ አጥላው)

ነባሩን አገር፣ ትናንት የተገነባውን ባሕልና ስርዓት ለማፍረስ መሽቀዳደም ክፋት ሳይሆን ሙያ  መስሏል።
ነባሩን ለማጽናትና ለማሻሻል፣ አዳዲስም ለመገንባትና ለማሳደግ የሚተጋ ሰው ከየት እንዲመጣልን ፈልገን ይሆን?
ነባሩን ክፉኛ ለማጥላላት፣ የትናንት ታሪክን በጭፍን ለማንቋሸሽ የሚጣደፉት የት ላይ ቆመው ነው? ትናንት የተወለዱ፣ ከነባር ወላጆች ጠብተው ጎርሰው ያደጉ ናቸው።

ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት ክፉና ደጉን እያየች እስከዛሬ የዘለቀች ታሪከኛ “የተስፋ አገር” ብትሆንም፣ ስንቱን አደጋ መሻገርና እስከ መቼ መቆየት እንደምትችል አያሳስባችሁም?
“አሁንስ አለቀላት” በተባለችበት ዘመን ሁሉ መጎሳቆሏ መቁሰሏ ባይቀርም ህልውናዋ አልተቀበረም፤ ታሪኳ አልተቋረጠም። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በዓለም ዙሪያ ሁሉ፣ እንደ ኢትዮጵያ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ታሪካቸው ሳይቋረጥ እስከዛሬ የደረሱ አገራት፣ ሦስት ወይም አራት ቢሆኑ ነው።
ክፉኛ እየወደቀች አፈር ለመልበስ የተቃረበችበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ግን ወድቃ አልቀረችም። አፈር ልሳም ቢሆን በተደጋጋሚ ከወደቀችበት እየተነሳች አንሰራርታለች። ከሩቅም ከቅርብም፣ ከባህር ማዶ ከየአህጉሩ በርካታ አዋቂዎች፣ ኢትዮጵያ ላይ ተስፋ ሳይቆርጡ በየዘመናቸው በክብር መጻፋቸው ለዚህ ነው።
እውነት ነው፤ የተስፋ ምድር ናት። ነገር ግን፣ ምንም ብናድርግ፣ ምንም ብትሆን፣ ቢንጧት፣ ማእበል ቢመታት፣ አንገጫግጨን ብናላትማት፣ እየተቃወስን ብናናውጣትና ተረባርበን ብንጥላት እንኳ፣ ወድቃ አትቀርም ማለት ነው? አክርረን ብናሳምማት እንኳ አትሞትም? ጠፍታ አትጠፋም?
ፍርሃታችንን ለማለሳለስ፣ የተስፋ ጭላንጭል እንዳናጣና ራሳችንን ለማፅናናት፣… “ወድቃ አትወድቅም” እንላለን።
አገርን የሚሸረሸር፣ የሚሰረስርና የሚቦረቡር፣ የሚሰነጣጥቅና የሚያፍረከርክ እልፍ የጥፋት ዓይቶችን በዘፈቀደ እለት በእለት እየፈጸሙ፣ ከህሊና ወቀሳ ለማምለጥ የሚፈልጉ ሰዎችንም፣ “ጠፍታ አትጠፋም” ብለው ራሳቸውን ያታልላሉ።
ሌላው ሰው ሁሉ እንዳሻው እያፈረሰ፣ ተቀናቃኞቻችን ሁሉ እንዳሰኛቸው እየፈመነጩባት፣ “እኛ ለብቻችን ጨዋ የአገር ተቆርቋሪ ብንሆን ዋጋ የለውም” ብለው የጥፋት እሽቅድምድም ውስጥ የሚገቡም ሞልተዋል።
“ሌላው ሁሉ በብሔር በብሔረሰብ ሲደራጅ አገርን እንደሚበታትን ብናውቅም፣ በዘር መቧደን መጥፎ ነው ብለን መቃወማችን ውጤት አያመጣም። በየዋህነት ከጨዋታ እንወጣለን። ወይ ወገን የለሽ የጥቃት ሰለባ እንሆናለን። ተቀናቃኞቻችን እንዳደረጉት፣ በብሔር ብሔረሰብ ከመቧደን ውጭ አማራጭ የለንም” የሚሉ ሰዎችንም እናያለን።
ከዚህ የባሱም አሉ።
የአገር ሰላምና የአገር ህልውና… የሌሎች ሰዎች ሃላፊነት ነው ብለው ያስባሉ። ለጊዜው አንዳች ጥቅም የሚያስገኝላቸው ከሆነ ወይም ከመሰላቸው፣ ተከታይና ቲፎዞ የሚመጣላቸው፣ ተቀናቃኞችን ለማበሳጨት የሚያገለግል፣ ሰፈር ምድሩን የሚያነቃንቅ፣ ሕዝቡን የሚያስጨንቅ፣ ኃይል ሆኖ ለመታየትና ለመግነን የሚጠቅም ከመሰላቸው፣ የአገር ምሰሶና ማገሮችን ለመከርከርና ለመስበር አመነቱም።
በማፍረስና በመገንደስ ነው ኃይልና ዝና የምናገኘው ብለው ያስብሉ። የመሰረትና የማዕዘን ድንጋይ ለመፈንቀል ለመናድ ይሽቀዳደማሉ። አገርን ያስተሳሰረ የጨዋነት ድርና ማግ እየበጣጠሱ ለመጣል ይወዳደራሉ።
ኧረ አገር እያፈረሳችሁ እየበተናችሁ ነው የሚላቸው ቢመጣ ግድ የላቸውም።
ለምን ይፈርሳል? ለምን ይበተናል? ስንበጥስ እናንተ መጠገን ያቅታችኋል? እኛ እንዳሻን እናደርጋለን። ተቆርቋሪዎች ይጭነቃቸው…
እንዲህ ዓይነት ፖለቲከኞች ዛሬ ዛሬ እጅግ ብዙ ናቸው። ንግግራቸውና ተግባራቸው አንዳች ነገር ለመስበርና ለመበጠስ የተነጣጠረ ነው።
እና እኛ ምን እዳ አለብን፣ የበጠሱትን ለማያያዝ የሰበሩትን ለማቃናት የመጨነቅና የመጠበብ እዳ አለብን? እንደዚህ ማሰብ ከጀመርን በኋላ፣ እንደ አፍራሾቹና እንደ በጣሾቹ ለመሆን ብዙም አይቀረንም። ማመካኛና ማሳበቢያ እያዘጋጀን ነዋ። እነሱ እንዳሻቸው እያፈረሱ እኛ ምን እዳ አለብን በሚል ሰበብ፣ የማፍረስ ጨዋታው ውስጥ እንገባለን።
ምናለፋችሁ፣ ለክፋትና ለጥፋት ሰበብ አናጣም። ሞልቶ ተርፎ።
የመፍትሔ ሃሳቦችን ለማጣጣልና ተስፋ ለመቁረጥም አልፍ ሰበቦች እናመጣለን።
ትክክለኛውና ተገቢው የአገር ሥርዓት ምን ዓይነት እንደሆነ በቅጡ ለመገንዘብና ለማወቅ መነጋገራችን ለከንቱ አይደለም። ሌላ መልካም አማራጭም የለም።  ነገር ግን፣ “ምን ዋጋ አለው?” የሚል ጥያቄ ሊፈጠርብን እንደሚችል አያጠራጥርም።
“ትክክለኛው ሃሳብ” እና “ተጨባጭ ተግባር” እንደ ሰማይና ምድር ከተለያዩ፣… “ተገቢው ሥርዓት” እና “የየእለቱ አኗኗር” ወዲህና ወዲያ ማዶ በተቀራኒ አቅጣጫ ከተራራቁ፣ ማወቅና መነጋገር ምን ጥቅም አለው?
ትክክለኛ ሃሳቦችንና መፍትሔዎችን ለማጣጣል፤ በዚሁም ሰበብ የክፋትና የጥፋት ፖለቲካ ውስጥ እየተለወሱና እየተራገጡ፣ እልቂትና ስደትን እያዛመቱ ለመቀጠል ማመካኛ ዘዴ የሚፈልጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
በሌላ በኩል ግን በቅን ልቦና እያሳሰባቸው፣ ትክክለኛ ሃሳብ በተግባር ለኑሮ ይጠቅማል ወይ ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ሞልተዋል። አዎ፣ ዛሬውኑ ለፍሬ አይደርሱም። ነገር ግን ለነገ ዛሬ መትከል የለብንም? በትክክል ካላሰብን የተግባር ስህተቶችን መለየት አንችልም። ተገቢውን ስርዓት ካላወቅን፣ ወቅታዊ ሁኔታዎችን መመርመርና የቱን ያህል እንደተበላሹ መገንዘብም ሆነ ጉድለታቸውን መለካት አንችልም።
በዚያ ላይ፣ ከቀን ወደ ቀን ስህተት እየበዛና እየሰፋ፣ ብልሽት እየባሰና እየከፋ ቢሆን እንዴት ማወቅ እንችላለን? በየእለቱ ስህተቶች እየታረሙ፣ ብልሽቶች እየተቀረፉ፣ ተግባሮቻችን እየተስተካከሉ፣ አኗኗራችን እየተሻሻለ መሆኑንስ እንዴት ማገናዘብና ማመዛዘን እንችላለን?
ወደ ትክክለኛው ሃሳብና ወደ ተገቢው ስርዓት ምን ያህል እንደተራመድን ወይም የቱን ያህል የኋሊት እንደተንሸራተትን፣ ምንኛ ቁልቁል እንደወረድን በማየት ነው- መሻሻል ወይም መበላሸትን የምንለካው።
የመሻሻል መንገዶችን ለመክፈትና ጉዞ ለማቃናት እድል የሚኖረንም፣ “ትክክለኛ ሃሳብና ተገቢ ሥርዓት” ምን ዓይነት እንደሆነ የምናውቅ ከሆነ ነው። ያው ባወቅነው መጠንና ማወቅ በምንችልበት ልክ ማለት ነው።
እንዲህ ሲባል ግን፣ “ትክክለኛውና ተገቢው ሥርዓት” ወደ ተግባር ተተረጎመ ማለት… ነባር ነገሮችን ሁሉ መቀየር፣ እስከዛሬ ያልነበሩ ነገሮችን ከባዶ መፍጠር ማለት አይደለም።
በመርህ ደረጃ በግልፅ ባይቀረፁም፣ በስርዓት ደረጃ በጽኑ መሰረት ባይታነጹም፣… በተናጠልና እንደመሰንበቻ የምናከናውናቸው በርካታ የዘወትር ተግባራት፣ እንዲሁም በልማድ የምንከተላቸው በርካታ የአኗኗር ዘይቤዎች፣… እነሰም በዛ የትክክለኛ ሃሳብ፣ የተገቢ ስርዓት ገጽታዎችን በውስጣቸው ያቀፉ ናቸው።
ቅንነትንና መከባበርን እንደ መርህ  እንኖርባቸው ይሆናል። ነገር ግን፣ በቅንነትና በመከባበር ለመኖር ሞክረን አናውቅም ማለት አይደለም። በየሰፈራችንና በየከተማው፣ በስራ ቦታና በየጎዳናው፣… ሁሌም ባይሆን እንኳ በአብዛኛው በሰላም ለመንቀሳቀስና በሰላም ለማደር የምንችለው አለምክንያት አይደለም። በነባሩ ባሕል ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን የመከባበርና የጨዋነት መንፈሶች በመኖራቸው ነው በጥቂቱም ቢሆን በሰላም የምንኖረው።
እነዚህን ነባር የጨዋነትና የመከባበር ገጽታዎች ወደ መርህ የማሳደግ ጉዳይ ነው- ስልጣኔ። የሰውን ሕይወት ማክበር ማለት፣ የሰውን አእምሮ፣ ሃሳብ፣ እውቀትና ንግግር፣ የሰውን አካል፣ ስራ፣ ምርትና ግብይት፣… ቤትና ንብረት፣ የእያንዳንዱን ሰው ህልውናና ሰብዕና ማክበር ማለት ነው- ስልጣኔ-ሌላ አይደለም።
ትክክለኛና ተገቢ ሥራዓት፣… ነባር ነገሮችን ሁሉ የማፍረስ፣ ታይተው የማያውቁ ነገሮችን የመፍጠር ጉዳይ አይደለም።
“ትክክለኛና ተገቢ ሥርዓት” ምን ማለት እንደሆነ ይበልጥ ባወቅን ቁጠር፣… ከታሪክ የተማርናቸው ከህይወት ዘመንም የታዘብናቸው ትክክለኛ ተግባራትን፣ ቀና መንገዶችን አጥርተን እያገናዘብን፣ በተናጠልና በዘልማድ ብቻ ሳይሆን በመርህ ደረጃ አዋህደን ቅጥ ልናስይዛቸው፣ ቅርፅ ልናበጅላቸው እንችላለን።
በሌላ አነጋገር፣ ስህተትንና ጥፋትን ላለመድገም ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል- መርህ። ትክክለኛና ተገቢ ተግባራትን ላለመዘንጋት ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ነገሮችን አጥርተን የምናይበት ብርሃን፣ እነዚህን የሚያበራክት የተቃና መንገድ ይሆንልናል-መርህ።
ያተሞከሩና ያልነበሩ አዳዲስ የመፍጠር ጉዳይ አይደለም-ሥልጣኔ።
ነባር ስህተቶችንና ትክክለኛ ተግባራትን፣ አጥፊና አልሚ ነባር የአኗኗር ልማዶችን በማገናዘብ፣ ጠማማና መጥፎ ገደላገደሎችን ከወዲሁ ባህርያቸውን ማወቅና መጠንቀቅ፣ የሕይወት መስመሮችንና የተቃኑ የበረከት መንገዶችንም ባሕርያቸውን እያወቁ በዚያው ልክ የማጽናትና የማስፋፋት ጉዳይ ነው- ሥልጣኔ።
ነባር ክፋቶችን እየገቱ አዳዲስ የክፋት መርዞችን እንዳንፈጥር መከላከል ስልጣኔ ነው።
ነባር ፀጋዎችን እያከበሩ፣ እያሳደጉና እያሻሻሉ፣ አዳዲስ ፍሬዎችን መጨመርም ሥልጣኔ ነው።
ሁለቱንም ነጥቦች አያይዘን መጨበጥ ይኖርብናል።
ሥልጣኔ፣ ነባር ነገሮችን የማጥፋት ጉዳይ አይደለም። ነባር ነገሮችን በዘልማድ የመደጋገም ጉዳይም አይደለም።
እንደማንኛውም አስደናቂ ፈጠራ፣… ነባር ፈጠራዎችን እንደመንደርደሪያ በመጠቀም፣ ነባር ነገሮችን በአዲስ ቅንብር ከቀድሞው የላቀ ውጤታማ ሥርዓት (System) የማበጀት ጉዳይ ነው።
ከቀድሞ አዋቂዎች ምንም አልማርም፣ ከነባሩ ተፈጥሮ አንዳችም አልነካም ብሎ፣… ቅንጣት ቁም ነገር መስራት የሚችል ሰው የለም። የተሻለ ነገር ለመፍጠር ይቅርና፣ በወጉ መቆምና መራመድም ይሳነዋል እንጂ። ነባር ጥበበኞችንና ነባር እውቀቶች ያላከበረ ሰው፣ ይባስ ብሎም ማንኛውንም ነባር ሃሳብና ቅርስ፣ ታሪክና ባሕል ለማፍረስ የመዝመት ሱስ የተፀናወተው ሰው፣ ቅንጣት  አዲስ ነገር መገንባት አይችልም። ማጥፋትና ማጨለም አዲስ ብርሃን መለኮስ አይደለምና።
በሌላ በኩል፣ ነባር ነገሮችን በዘፈቀደ በዘልማድ መደጋገምም፣ ቀደምት ጠቢባንንና ታሪክን ማክበር ሳይሆን ማዋረድ ነው፡፡
ነባር ነገሮችን ማጥላላትና በጭፍን መቃረን፣ ከዚያም አልፎ ለማፍረስ መዝመት፣ የቀድሞ ልማዶችን ብቻ ሳይሆን፣ ራስን የመጥላትና የማዋረድ በሽታ ነው፡፡
መቼም፣ በነባሩ ውስጥ እንጂ ከመጪው ዘመን ተወልዶ ወደ ዛሬ የመጣ ሰው የለም፡፡
ማንም ሰው ቢሆን በነባር ወላጆች፣ በነባር አሳዳጊዎች፣ በነባር አስተማሪዎች ነው የሚችለውን ያህል የሚያድገው፣ የሚማረው፡፡
አነሰም በዛ፣ በነባር አቅም ነው የነገን ህንፃ ዛሬ መገንባት የሚችለው፡፡ የቅርብም ይሁን የሩቅ፣ የትናንት ጥረቶችንና ነባር ግንባታዎችን፣…እንማርባቸዋለን፤ እንሰራባቸዋለን፤ አርአያነት እናገኝባቸዋለን። የእውቀት መማሪያ፣ የኑሮ መገልገያ፣ የተግባር መሳሪያ፣… የመንፈስ ሃይል ከነባሩ ውስጥ ለማግኘት ያልፈለገና ያልቻለ ሰው እንዴት ውሎ ማደር ይችላል?
ነባሮችን ዘወትር እያጥላላን ለጊዜው ግን እየተጠቀምንባቸው፣ ተጠልለንም እየኖርንበት፣ ግን ደግሞ እለት በእለት ማፍረስ፣ የት ያደርሰናል? የቀድሞ ፍሬያማ ጥረቶችን፣ የተገነቡ ቅርሶችን፣ የተዋቀሩ ሥርዓቶችን ያላከበረ፣… አዳዲስ ግንባታዎችን የማክበርም ሆነ የመስራት መንፋሳዊ ሃይል ያጣል፡፡ ውስጡ ይንጠፈጠፋል፡፡
 ማፍረስን እንደ ስራ ይቆጥረዋል፡፡ የእውቀትና የሃሳብ፣ የኑሮና የተግባር፣ የማንነትና የራዕይ፣ የስልጣኔና የብልፅግና መነሻችን፣… አነሰም በዛ፣ ሌላ ሳይሆን ነባሮቹ የትናንት ውጤቶች ናቸው፡፡ ሁለት ነጥቦችን አይተናል። የወደፊት ራዕይ እና የቀድሞ ነባር ቅርስ፡፡
የወደፊት ራዕያችን፣ ማለትም መርህ ትክክለኛውና ተገቢው ሥርዓት ምን ዓይነት ነው?
በአንዳች ተዓምር፣ በአንድ ጀምበር እውን አይሆንም፡፡ ነገር ግን፣ አቅጣጫችን ወደ ተሻለ ኑሮ ወደ ከፍታ መሆኑን ወይም ወደ ባሰ መቀመቅ የሚያሽቆለቁል መሆኑን ለይተን ለማወቅ፣ ትክክለኛ ሃሳብና ትክክለኛ ራዕይ ሊኖረን ይገባል። ያኔም ለማስተካከል እንችላለን። “እያንዳንዱ እርምጃችን የመገንባት እርምጃ መሆኑን ወይም የማፍረስ  እርግጫ መሆኑን በውል ማወቅና መለካት የምችለው፣ በመልካም የወደፊት ራዕይ አማካኝነት ነው፡፡ ከነባሩ የሚሻል ነገር ለመፍጠር መፈለጋችን ተገቢ ነው፡፡ የነባሩ ጉድለቶች ላይ ቅሬታ ቢኖረን አይገርምም፡፡ ነገር ግን፣ በቅሬታ ሰበብ በጥላቻ ስሜት ወደ ባሰ ገደል ለማሽቆልቆል ሳይሆን ለመሻሻልና ለማደግ መሆን አለበት ዋና ሃሳባችን፡፡
ሁለተኛ ነገር፣ የህልውናችን ምንጭ ሁሌም የቀድሞው ታሪክና ነባር ቅርስ ውስጥ ነው፡፡ የተሻለ የነገ ራዕይ ለመያዝና ለመጓዝም፣ መነሻችንና አቅማችን ከትናንት ውጤቶችና ከነባር ታሪኮች የሚመነጭ ነው ይብዛም ይነስ፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የተወለዳችሁበት ዘመን፣ የጥጋብ ጊዜ፣ ወይም የድርቅ ዓመት ሊሆን ይችላል። የተማራችሁበት ቦታ፣ ያደጋችሁበት የኑሮ ደረጃ፣… ለሕይወት አመቺ ወይም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡
ነገር ግን፣ በችግርም ይሁን በምቾት፣ ከዚያው ከነባሩ ሁኔታ ነው የእርምጃ መነሻና መንደርደሪያ የምናገኘው። ከነባሩ ነው ትንፋሽ የምንወስደው።
 የህልውናችን ምንጭም ሆነ የነገ መነሻችን ሌላ ሊሆን አይችልም፡፡ ከመወለድ ውጭ ሌላ መነሻ፣ ከእስከዛሬው ነባር ባሕልና ከእስከዛሬው ታሪካችን ውጭ፣ ለነገ ጉዟችን የሚጠቅም ሌላ መነሻ አቅም የለንም፡፡ ሊኖረንም አይችልም፡፡ ከነባሩ ውስጥ እንጂ፡፡
የትናንት ነባር አቅሞችን ማክበር፣ ለነገ መልካም ራዕይን መያዝ፣ ዛሬ በቅጡ ለማሰብና ለመነጋገር፣ የዛሬ ተግባራችንን ለማስተካከልና ለመምረጥ ይጠቅመናል፡፡ የጉዞ መስመራችን ይቃናል፣ የእለት ተእለት እርምጃችንም ብርታት ያገኛል። የመሻሻል ግስጋሴን ይሰጠናል፡፡
እንደ ማዕቀፍ ሰብሰብ አድርገን፣ እንደ መነፅር የቅርብና የሩቁን አጥርተን አዛምደን የአገራችንን ሁኔታ ለማገናዘብ ይረዱናል የትናንት ነባር አቅሞችና የነገ ትክክለኛ ራዕዮች፡፡
እነዚህ ማዕቀፎችና መነፅሮች፣ እልፍ አእላፍ አላስፈላጊ ውዝግቦችን ለማስወገድ፣ በዚያው ልክ የመግባቢያ መንገዶችን ለመክፈት ይጠቅማሉ፡፡
ለእነዚህ ማዕቀፎችና መነፅሮች ቀዳሚ ትኩረት ካልሰጠን፣ ውይይቶች ሁሉ ከንቱ ወገኛ ወሬዎች ወይም መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ውዝግቦችና የፀብ ማቀጣጠያ ሰበቦች ይሆናሉ፡፡ ምክክሮች ሁሉ፣የእልፍ መከራዎች ክምር፣ የቅንጥብጣቢ ሃሳቦች ግርግር፣ ወይም የጉም ሃሳቦች አሰልቺ ስብሰባ፣ ወይም በትንሽ በትልቁ የመከራከር፣ በብሽሽቅ ነጥብ የማስቆጠር ንትርክ ይሆናሉ፡፡

ጉዳዩ የማስታረቅና የማቃረን ጉዳይ ብቻ ባይሆንስ?


ሳይንስንና ኃይማኖትን፣ እውቀትንና እምነትን ለማስታረቅ፣ ብዙ ፈላስፎችና ጥበበኞች ለዘመናት ተመራምረዋል፤ ላይ ታች ወርደዋል። በዚያው ልክ፣ እርስ በርስ እንደሚቃረኑ ለማሳየት፣ ቅራኔያቸውም እንደማይታረቅ ለማስረዳት የደከሙ አዋቂዎች ብዙ ናቸው። ኃይማኖትና ሳይንስ፣ አንዱ በሌላኛው መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር፣ አብረው ሊዘልቁ እንደማይችሉ ለማሳመን እልፍ ትንታኔዎችን ያቀርባሉ- በየጎራው ተሰልፈው ይወራወራሉ።
ለሺ ዓመታት የጎረፉ ፍልስፍናዎችና ሐተታዎች ወደ እልባት ካላደረሱት፣… በጣም ከባድ ጉዳይ ቢሆን ነው። ግን ደግሞ፣ ነገርዬው “የማስታረቅና የማቃረን ጉዳይ” ብቻ ባይሆንስ? ድራማና ዜና፣ ግጥምና ንግግር፣… በሆነ ነገራቸው ተቃራኒ ወይም ተጣማሪ ናቸው ብሎ መከራከር ይቻላል።
ከግጥም ውስጥ መረጃና እውቀትነፍ፣ ከዜና ውስጥም ጥበብና የመንፈስ መዝናኛን ለማጥለል ሁለቱንም ለማስታረቅ መሞከር አያቅትም። ነገር ግን፣ በሰው ሕይወት ውስጥ የየራሳቸው ቦታ ያላቸው የተለያዩ ገጽታዎች መሆናቸው ላይ ማተኮርስ አያስፈልግም ወይ?
ዓለማዊና መንፈሳዊ፣ ኃይማኖትና ኑሮ፣ እምነትና እውቀት፣… ከሰው ሕይወት ገጽታዎች ጋር አዛምደን ብናያቸውስ? “የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት” በሚለው ሃሳብ ዙሪያ፣ የተለያዩ ዓለማዊና መንፈሳዊ ገጽታዎችን ለመመልከት ብንሞክርስ? መቼም፣ “የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት” ሲባል፣… ብዙ ገፅታዎችን፣ ብዙ ትርጉሞችን ያቀፈ ነው። “አሜን” እና “ፅድቅ” የሚሉ ቃላትም፣ እያንዳንዳቸው በርካታ ገፅታዎችን የሚያዛምዱ በርካታ ትርጉሞችን እንደሚዋህዱ እናያለን።
የተፈጥሮና የሰው የዘወትር ግንኙነት - በእግዚሄርና በሰዎች ግንኙነት ይመሰላል።
“አሜን” የሚለው ቃል፣ “አዎን እውነት ነው” የሚል ትርጉም አለው፡፡
የሰው አእምሮ ከተፈጥሯዊ እውነታ ጋር ምን ዓይነት ግንኑነት ሊኖረው ይገባል? ለዚህ ጥያቄ  “አሜን” የሚለው ቃል ነው አጭሩ መልስ፡፡
የሰዎች ድርሻ፣ ተፈጥሯዊውን እውነታ አስተውለው፣ በአዎንታ አሜን ብለው መቀበልና እያገናዘቡ እውቀት መገንባት ነው። ማንገራገርና ማማረር፣… ምን ትርጉም አለው? ከተፈጥሮ ሕግ መሸሽ፣ ከእውነታ ጋር መጣላት፣ የትም አያደርስም።
አየር መንፈሱ፣ አሸዋ መንሸራተቱ፣ አለት መጠጠሩ፣… የተራራው ከፍታ፣ የሸለቆው ዝቅታ አልወደድንላቸውም ብንል ለውጥ የለውም፡፡ የምርጫ ጉዳይ አይደሉም፡፡ ውሃ መፍሰሱ፣ የባህር ጥልቀቱ ባይዋጥልን፣ በቅሬታ ብዛት እንቀይረዋለን? ከንቱ ልፋት ነው። ከአለት ጋር ለመላተም፣ ገደል መቀመቅ ለመግባት፣ በጎርፍ ተጠራርጎ ከጥልቅ ባሕህ ውስጥ ለመስመጥ፤ በበረሃ አሸዋ ለመቀበር ካልሆነ በቀር፣ ሌላ ውጤት የለውም።
ይልቁንስ በተፈጥሯዊው እውነታ ውስጥ ነው የሕይወት ቦታ፤ የመልካም አማራጮች መገኛ።
የተፈጥሮ ሕግ ዘላለማዊ ነውና፣ እውነታውን ማስተዋልና በአዎንታ አምኖ መቀበል፣ ዝንፍ ሳይሉ የእውነትን መንገድ መከተል፣ የሰዎች የመጀመሪያው የመልካም ምርጫዎች ሁሉ መሠረት ነው። ለዘላለማዊ እውነታ ለተፈጥሮ ህግ የኛ ምላሽ የአዎንታ መሆን አለበት። አሜን እንበል።
አሜን ማለት “አዎን፣ እውነት ነው” ማለት ነውና። እሙን ነው ነገሩ። ፅድቅ ማለትም እውነት ማለት ነው፡፡ እውነታውን መመስከር፣ እውነት መናገር ነው ጽደቅ ማለት። የአማን እና የፅድቅ ሌሎች ተዛማጅ ትርጉሞችንም አንተዋቸውም። እናመጣቸዋለን።
የሁሉም መነሻ ግን፣ እውኑን ተፈጥሮ በአዎንታ በአመኔታ መቀበል ነው። ከተፈጥሮና ከእውነታ ውጭ ሕይወትም መልካምነትም የለም - ጥፋት እንጂ። እግዚሄርን በአዎንታ፣ በሙሉ ልብ፣ በሙሉ ሃሳብና በሙሉ መንፈስ አምኖ መቀበል፣ መውደድና ማክበር እንደሚያስፈልግ መፅሐፍ ያስተምራል። ለምን?
አንዱ ምክንያት፣ የእግዚሄርና የሰዎች ግንኙነት፣… እውነት ላይ መመስረት እንዳለበት ለመግለጽ ይሆን? የእግዚሄር ስም “ያለና የሚኖር” በሚሉ ቃላት ተገልጾ ያለ! እውን የሆነውን ደግሞ “አዎ፤ እውነት ነው” ብሎ መቀበል ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ሕግና የሰዎች ግንኙነት በዚህ ይመሰላል- ግን ይህ ብቻ አይደለም።
የወላጅና የልጆች፣ የአስተማሪና የተማሪዎች ግንኙነትንም ይመስላል - የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት።
ሃይማኖታዊ ትረካዎችን ተመልከቱ፡፡ እግዚሄር ይመክራል፣ ይገስፃል። ይቆጣል፣ ይቅር ይላል። ያደንቃል፣ ይወቅሳል - እንደ ወላጅና እንደ አስተማሪ። ያለ ወላጅ ፍቅር ወይም ያለ አሳዳጊ እንክብካቤ፣ ሕፃናት በጤናና በደህና ማደግ አይችሉም።
 ያለ አዋቂና ያለ አስተማሪ፣ ያለ ፍቅርና ያለ እንክብካቤ፣ የሕጻናት ሕይወት ምን ሊሆን እንደሚችል አስቡት። ሕፃናትን በፍቅርና በተግሳጽ፣ በእንክብካቤና በክትትል ማሳደግ፣ “ለአቅመ ሰው” ማብቃት፣ አንድ የህይወት መሰረት ነው። ይህን ፀጋ ከማክበር ጋር ይመሳሰላል- የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት። ይህም ብቻ አይደለም።
የሰው ልጅ ከሌሎች ፍጡራን የተለየና እጅግ ድንቅ የመንፈስ ፀጋ ተሰጥቶታል። ሕይወቱ ከባዶ አይጀምርም። በእርግጥ አዋቂ ጀግና ሆኖ አይወለድም፡፡ እናም በባዶ እጅ ሕይወትን ይጀምራል ብንል አልተሳሳትንም፡፡ ነገር ግን፣ እንደሌሎች እንስሳትም አይደለም፡፡
በቀድሞ ጥበበኞች የተዘጋጁ ነባር ፀጋዎች እንደ መነሻና መንደርደሪያ ይሆኑለታል፡፡
አለበለዚያ ሕይወቱ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የዘመናት ድግግሞሽ ይሆናል፡፡
 ከቀድሞ ጥበበኞች ዘንድ፣ ነባር እውቀቶችን ካልተማረና ነባር ሙያዎችን ካልተላመደ፣… ወደ ላቀ እውቀትና ወደ ተሻለ ኑሮ የመራመድ አቅም አያገኝም። እንደ ሌሎች እንስሳት ዘላለሙን ከባዶ የሚጀምር ቢሆን፣ የሰው ልጅ… የታሪክ ቅርስ ሽራፊ ወይም ቅንጣት የተስፋ ጭላንጭል አይኖረውም ነበር። ከትውልድ ትውልድ፣ የሰው ኑሮ ተመሳሳይ በሆነ ነበር - እንደ ሌሎች እንስሳት።
ካለፈው ዘመን ተምሮ ወደ ፊት ተሻሽሎ የመራመድና ወደ ላቀ ከፍታ የመጓዝ እድል ከሌለ፣… ታሪክና ቅርስ፣ ራዕይና ተስፋ አይኖርም። ደግነቱ ከባዶ አይጀምርም፡፡ ከቀድሞ ትውልዶች መልካም መልካሙን መማር ጅምሮችን ማሳደግ ይችላል፡፡ ትክክለኛ ሃሰሳብ ተቀብሎ ችግኞችን ኮትኩቶ እንደ ማፅደቅ ቁጠሩት፡፡
ነባር እውቀትንና ሙያን፣ ባሕልና ልማድን፣ ወላጅ አሳዳጊዎችንና ጥበበኛ አስተማሪዎችን ማክበር ያስፈልጋል። አሜን (ተገቢ ነው ትክክል ነው የሚል ትርጉም አለው፡፡)
በእርግጥ፣ የቀድሞ ጥበበኞችና ነባር ትምህርቶች፣ እንደ ተፈጥሮ ሕግና እንደ እውነታ አይደሉም።
ጥበበኞች ሊሳሳቱ፣ አስተማሪዎች ሊያዛቡ፣ ወላጆች ሊያጣምሙ፣ አሳዳጊዎች ሊያበላሹ ይችላሉ። ይህም ጉዳት አለው። ነገር ግን፣ ስህተታቸውና ጥፋታቸው እጅግ ጎጂ የሚሆነው ለምን እንደሆነ አስቡት? ለሕይወትና ለእድገት፣ ለሰው ልጅ ታሪክና ለስልጣኔ ጉዞ በጣም እጅግ ውድ አለኝታ መሆን ስለሚችሉ፣ ከጎደሉብን ከተበላሹብን እጅግ ክፉ ጉዳት ይሆኑብናል። ባይጎድሉብንና ባይበላሹብን ምንኛ መታደል ነው! ውድ ጸጋ ስለሆኑም ነው ክብር የሚገባቸው። የወላጅና የልጅ፣ የአስተማሪና የተማሪ፣ የታሪክና የትውልድ ግንኙነት፣… መልካምና የተቃና፣ የፍቅርና የተግሳፅ ግንኙነት መሆን አለበት። በምሳሌያዊ ዘይቤም፣ የሰዎችና የእግዚሄር ግንኙነትን ይመስላል ልንል እንችላለን። ይህም ብቻ አይለም።
ሰውና ህሊና
ሰዎች፣ ሁሉንም ነገር በስውር ከሚያውቅ ህሊናቸው ጋር የሚኖራቸው የሁልጊዜ ግንኙነት ይመስላል - የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት። ለክፉም ለደጉም፣ ሌላ ሰው ቢያይም ባያይም፣ አመስጋኝና ወቃሽ ታዛቢዎች ባይኖሩም፣… ጥሩ ወይም መጥፎ ነገር በስውር ብንሰራ፣ ሕሊናችን በስውር ያያል፤ ይፈርዳል።
ውስጣዊው የሕሊናችን ተፈጥሮ ተገልጦ ባይታይም እንኳ፣ በስውር እየተመለከተ ይዳኛል። መልካምነትህን አይክድብህም፤ ክፋትህንም አይሸፍንልህም።
ጥሎ አይተውህም፣ ሸሽተህ አታመልጠውም።
እግዚሄር በስውር ያያል፤ በስውር ይከፍላል እንደሚባለው ነው።
ሰዎች ቢያምኑንም ባያምኑንም፣ የሚያውቅልህ ወይም የሚያውቅብህ ሰው ባይኖርም፣ እውነት ወይም ውሸት የተናገርክ ጊዜ፣ አእምሮህ ወይም ሕሊናህ በስውር ያውቃል። ከሕሊና የተሰወረ ነገር የለም።
ታዲያ፣ የሰውና የሕሊናው የሁልጊዜ ግንኙነት፣… የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት ይመስላል ብንል ምን ስህተት አለው? ይህም ብቻ አይደለም።
ሰዎችና ዳኝነታቸው - የፍቅርና የፍትሕ ግንኙነት
የሰዎች የእርስበርስ ግንኙነት፣ የመንግስትና የዜጎች፣ የከተማ ዳኛና የከተማ ነዋሪዎች… ከእነዚህ ግንኙነቶች ጋር ይመሳሰላል - የእግዚሄርና የሰው ግንኙነት። የፍትሕና የፍቅር አስፈላጊነት ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታልና ግንኙነታቸው።
የሰዎች ግንኙነት፣ መረጃና ሃሳብ የመለዋወጥ (የመማማር)፣ በስራና በኑሮ የመተባበር (የመረዳዳትና የመገበያየት)፣ በሕይወትም የራስ ሃላፊነትን የመወጣትና ራስን አክብሮ፣ የሌሎችንም ብቃት የማድነቅ፣ አርአያነትንም የማክበር የፍቅር ግንኙነት መሆን አለበት - በአንድ በኩል።
በሌላ በኩል፣ ራስን ጭምር፣ ሁሉንም ሰው፣ እንደየስራውና እንደየባሕርይው እንዳኛለን ማለት፣… የፍትሕ ግንኙነት ነው። በዚህ ይመሰላል- የሰውና የእግዚሄር ግንኙነት።
“የሕይወት መዝገብ” - ሁሉንም ነገር ይመዘግብልናል፤ ይመዘግብብናል!
የሰው እና የእግዚሄር ግንኙነት፣… በሰው እና “በሕይወት መዝገብ” መካከል ባለው ግንኙነት ጋር ይመሰላል።
በተፈጥሮ፣ የሰው አእምሮ፣… የእለት ተእለት ሃሳቡንና ተግባሩን ይመዘግባል። የግል አእምሯችን፣ እንደየ ምርጫችን የሕይወት ውሏችንን የምንዘውርበት፣ መንገዳችንን የምንነድፍበትና የምንጓዝበት መሣሪያ ነው። ግን ደግሞ፣ የሕይወት መዝገባችንም ነው - አእምሯችን። እንዳይመዘግብ ማድረግ አይቻልም። አእምሯችን መዝጋቢ ነው። መዝገብም ነው። መዝገብ ማጥፋት፣ በፎርጅድ መተካት፣ ባሰኘን ጊዜ መሰረዝ መደለዝ፣ ቆርጦ መቀጠል አይቻለንም ብለናል´ኮ።
copy - paste,… cut - replace,… undo - redo,… post - delete፣… የእለት ተእለት ሃሳብና ተግባር ላይ፣… እነዚህን አማራጮች መሞከር እንችላለን። ማሰብ አለማሰብ፣ ማድረግ አለማድረግ፣… የእያንዳንዷ የሕይወት ደቂቃና ቅፅበት ምርጫዎች ናቸው። መዝገብ ውስጥ መስፈራቸው ግን አይቀሬ ነው ተባብለናል።
ይመዘግብልናል። ሳይመዘገብልን የሚቀር መልካም ነገር አይኖርም።
ይመዘግብብናል። ሳይመዘገብብን የሚያመልጥ መጥፎ ነገር የለም።
ማሰብ አለማሳባችን፣ ማድረግ አለማድረጋችን፣ ከነምንነታቸው አእምሯችን መመዝገቡ፣ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። ይመዘግባል።
በዚህም ማንነት ያንጻል ወይም ያፈራርሳል።
ባሕርይን ያጎድፋል ወይም ያነጻል፤ ያጣምማል ወይም ያቃናል።
የተጣመመውን ያደነድናል ወይም የተቃናውን ያጸናል።
ታዲያ፣ ይህ ድንቅ የሰው ተፈጥሮ፣ ግሩም የፍትሕ ፀጋ አይደለምን? የፈላስፋውን አባባል ጠቅሰን እንደነበር አስታውሱ። ቸመልካም ስራ፣… አንተ ብትረሳው እንኳ የሚመዘግብ አለ… ይላል ፈላስፋው ወልደሕይወት። “Sense of life” ትለዋለች ፈላስፋዋ፡፡ የሰራነውን ሁሉ ማስታወስ አንችልም ማለት ከመዝገብ ያመልጣል ማለት አይደለም፡፡ በከንቱ የሚባክንም የለም።
የሕይወት መዝገብ፣ ሁሉንም እየመዘገበ እንደየስራችን ማንነታችንን ያበለፅግልናል። እንዲህ አይነት ሰው ፃድቅ ይባላል፡፡ አሜን፣ ተገቢ ነው እንደ ማለት ነው፡፡
ክፋት ከሰራንም ከብዛቱ የተነሳ ብንረሳው እንኳ፣ ከመዝገብ ውስጥ አይጠፋም፡፡ በጥቁር ነጥቦች ብዛት የሕይወት ገፃችን ይጠቁራል፡፡
የሕይወት መዝገብ፣ ማምለጫ የሌለው የፍትሕ ዳኛ ነው - “የእጃችሁን ታገኟታላችሁ” የሚለን። አንድም ሳያመልጠው ይመዘግብብናል።
እንደየጥፋታችን ልክም የግል ማንነታችን ይረክሳል፤ የእኔነት መንፈሳችን ይሟሽሻል።
“ፈሪሀ እግዚሄር” የምንለው ሃሳብ ከዚህ ጋር የተዛመደ ገጽታ አለው። ፈሪሃ እግዚሄር  “የጥበብ መጀመሪያ ነው” ተብሎ የለ! የዛሬ ሃሳባችንና ድርጊታችን፣… ውሎ አድሮ፣ በነገ ማንነታችንና በነገ የአገራችን ባሕል ላይ፣ ለክፉም ለደጉም፣ ውጤትና መዘዝ እንደሚኖረው ካልተገነዘብን፣ ወደ ጥበብ ደጃፍ አልደረስንም።
ለእውነታ በመታመን፣ ሕይወትንም በማክበር፣ በየቀኑ በሃሳብና በተግባር የምናከናውናቸው ፍሬያማ ጥረቶችን የሚመዘግብ፣ በዚህም ላይ የየእለቱን እየጨመረ የሚገነባ የተፈጥሮ ፀጋ ባይኖረን ኖሮ፣… አስቡት።
አስቡት? አእምሯችን “መዝጋቢም፣ መዝገብም” ባይሆን ኖሮ፣ እንዴት ተደርጎ ይታሰባል? “መማርና ማገናዘብ”፣ “መለማመድና መፍጠር” የምንላቸው ነገሮች ትርጉም ያጣሉ። በየእለቱ ከባዶ የሚጀምር ደንዛዛ ወይም ቀበዝባዛ አዙሪት ይሆን ነበር - የሰው ሃሳብና ኑሮ። እውቀት፣ አስተዋይነትና ቋንቋ፣… የሙያ ልምድ፣ ብልኀትና ጥበብ የሚባል ነገር አይኖረንም - አእምሯችን የሕይወት መዝገብ ባይሆን ኖሮ።
የግል ማንነትና የእኔነት መንፈስ፣ የአገር ባሕልና ሥርዓት፣ ቀና አድናቆትና የወዳጅነት ፍቅር፣ የወደፊት ራዕይና ተስፋ፣ የሕይወት ትርጉምና ጣዕም የምንላቸው ነገሮች አይኖሩንም - አእምሯችን የየእለቱን ሃሳብና ተግባር የማይመዘግብ ቢሆን።
ደግነቱ፣ ይመዘግባል። መዝገብም ነው።
“የተፈጥሮ ፀጋ፣ የተፈጥሮ ፍትሕ” ብንለው አይበዛበትም - “የእግዚሄር በረከት፣ የእግዚሄር ፍትህ” እንደማለት።በዚያው ልክ፣ እያንዳንዷ ውሸትና ሽንገላ፣ የምንሰራት ሸፍጥና በደል፣ የምንፈፅማት ጥቃትና ጥፋትም ከመዝገብ አታመልጥም። አንዲትም ሳትሰወር፣ አንድም ተሸሽጎ ሳይደበቅ ሁሉም ይጻፋሉ። በዚሁም ላይ የየእለቱ እየተጨመረና እየተመዘገበ፣… አእምሮ ይደፈርሳል፣ ይወሳሰባል፣ ይጨልማል። ሕሊና ይዶለዱማል፤ ይጎድፋል። ማንነት ይበላሻል፤ ከጊዜ ወደ ጊዜም ጠማማው ይባስኑ እየተጠማዘዘ ይደነድናል። ማምለጫ የሌለው “የተፈጥሮ ዳኝነት፣ አይቀሬ ፍትሕ”፣… ልንለው እንችላለን። “የእግዚሄር ፍትሕና ዳኝነት” እንደማለት ነው።


ትናንት 250 አባላትና አመራሮቹ ፓርቲውን መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል

  ለገዥው ብልፅግና ፓርቲ ወግኗል ያሉ  የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)  አባላትና አመራሮች  በግልና በቡድን  ፓርቲውን መልቀቃቸውን ቀጥለዋል። በትናንትናው ዕለት ከ250 በላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች እንዲሁም የፓርቲው  አባላት ኢዜማን ለቀው መውጣታቸውን ይፋ አድርገዋል።
አመራሮቹና አባላቱ ፓርቲውን ለመልቀቃቸው ከጠቀሷቸው ምክንያቶች መካከል፡-  ፓርቲው በጥቂት የስልጣን ችሮታ በክህደት መንገድ ተጉዞ  ከአላማው መስመር ስለወጣና ወደ መስመሩ እንዲመለስ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም አሁን ባሉት ከፍተኛ አመራሮች ምንም አይነት ለውጥ ሊመጣ እንደማይችል በመረዳታችንና ፓርቲው ለገዥው ብልጽግና  እያሣየ ባለው ገደብ ያለፈ ውግንና ሣቢያ፣ ብልጽግናን ታግሎ አገር አፍራሽነቱን የማስቆም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌለው በመረዳታችን እንዲሁም  ብልፅግና የብሔር ፓርቲ መሆኑን  ፓርቲው ስለ ራሱ የሰጠውን ምስክርነት በመካድ፣ የዜግነት ፖለቲካ አራማጅ አድርጎ በሰነዱ ማሳየቱ ፖርቲው ለመሻሻል ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው መሆኑን  ስላረጋገጠልን ለውሣኔ ተገደናል ብለዋል። አያይዘውም፤ ፓርቲው አስጠናሁት ባለው አንድ  ጥናት ላይ እንደተመለከተው፣ የአባላቱን ጥያቄ ተቀብሎ ወደ ትክክለኛ መስመር  ከመግባት ይልቅ የአንባገነኖች መሳሪያ ሆኖ መቀጠል እንደፈለገ በግልጽ ያሳየ በመሆኑ ከዚህ በኋላ ከፓርቲው ጋር አብሮ መቀጠሉ ተገቢ ባለመሆኑ  ሌሎች  አማራጮችን  በመከተል ኢትዮጵያን ከመፍረስ፣ ህዝባችንን ከስቃይ ለመታደግ መታገላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።  በትናንትናው ዕለት ከፓርቲው መነጠላቸውን ይፋ ያደረጉት 250 አመራሮችና  አባላት በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልልና በደቡብ ክልል የኢዜማ መዋቅር ውስጥ የነበሩ አመራሮችና ተራ አባላት ናቸው። ቀደም ሲል ኢዜማ የአባላቱን ቅሬታ መነሻ አድርጎ በተለይም ገዥው ፓርቲ ከሚመራው መንግስት ጋር ያለውን ትብብር በተመለከት ጥናት አድርጎ ውይይት ማድረጉን አስታወቆ ነበር። በዚህ ጥናት ብዙ ችግሮች ይፈታሉ ብለው ተስፋ አድርገው እንደነበር የሚገልፁት ተሰናባቾቹ፤ ውጤቱ  እንደተጠበቀው ባለመሆኑ ፓርቲውን ለመልቀቅ ተገደናል ብለዋል። የኢዜማ አመራሮች በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ሳይሆን ከመንግስት ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ተባብሮ እንደሚሰራ በአፅንኦት ያስረዳሉ። ከፓርቲው የሚለቁ አባላትን በተመለከተ ኢዜማ በጥቂት አባላት መልቀቅ የሚፈርስ ፓርቲ አይደለም ሲሉም ይከራከራሉ።ከአንድ ወር በፊት አርባ አንድ የፓርቲው የቀድሞ አመራሮችና አባላት ድርጅቱን ለቀው መውጣታቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በመላው ሀገሪቱ ለህፃናት ጥራት ያለው ትምህርት የመስጠት ራዕይ የሰነቀው ዲቤክ አለም አቀፍ የእውቀት ማዕከል፣ “መልካም ዕውቀት በክረምት” በሚል መርህ ለሁለት ወር የሚቆይ የልጆች ስልጠና ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ማእከሉ ይህን ያስታወቀው ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 21 ቀን 2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በሳፋየር አዲስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡ ማዕከሉ የክረምቱን ሥልጠና ያዘጋጀው ዕድሜያቸው ከ9-18 ዓመት ለሆኑ ታዳጊና ወጣቶች ሲሆን፤ ልጆች የሥነ ልቦና፣ የተግባቦትና አጠቃላይ ሁለገብ የሆነ ስልጠናና እውቀት የሚያስጨብጣቸውን መልካም አጋጣሚ ለመፍጠር እውቅ ምሁራንንና ባለሙያዎችን ማዘጋጀቱን የዲቤክ ዓለም አቀፍ የእውቀት ማእከል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቤዛዊት አበራ በጋዜጣዊ መግለጫው አብራርተዋል፡፡ለነዚህ ሀገር ተረካቢ ታዳጊና ወጣት ልጆች ለሁለት ወራት የተዘጋጁት የስልጠና አይነቶች፣ የፈጠራና ቴክኖሎጂ፣ ሜታፊዚክስ፣ ሥነ-ፈለክ፣ የሂሳብ፣  የሥነልቦና የእውቀትና እድገት፣ ፕሮግራሚንግና ሌሎችም በርካታ ስልጠናዎች ለሁለት ወራት የሚያገኙ ሲሆን ስልጠናው በቨርቹዋልና በአካል እንደሚካሄድ ዶ/ር ቤዛዊት ገልጸው፣ በቨርቹዋልም ሆነ በአካል መጥተው ለሚሰለጥኑ ልጆች ማእከሉ የመቀበል አቅሙ ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡ የስልጠና ክፍያውም ቢሆን የወቅቱን የኑሮ ውድነትና አጠቃላይ ሁኔታዎችን ያገናዘበም ነው ብለዋል ዋና ስራ አስኪያጇ፡፡በአካል ተገኝተው ሥልጠናውን ለሚወስዱ ቦሌ፣ ብስራተ ገብርኤልና ፒያሳ የተዘጋጁ ማእከላት መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፣ በቨርቹዋል ስልጠናውን ለሚወስዱ ከየትኛውም አካባቢ ሆነው ተሳታፊ እንዲሆኑ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ተጠቁሟል፡፡ዲቤክ ዓለም አቀፍ የእውቀት ማእከል በ2012 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን በራሱ ማእከል ከሚሰጣቸው ሁለገብ የልጆች እውቀት ስነልቦናና ሁለንተናዊ እድገት ስልጠናዎች በተጨማሪ በየተጋበዘባቸው ተቋማት እየተገኘ ስልጠና በመስጠት የተቋቋመበትን አላማ እያሳካ መሆኑም ተብራርቷል፡፡ “ይህ መልካም እውቀት በክረምት” የተሰኘ የክረምት የልጆች ስልጠና፣ ማእከሉ ከተቋቋመባቸው አላማዎች አንዱ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፣ ልጆች በክረምት ጊዜያቸውን በአልባሌ ሁኔታ ከሚያሳልፉ ይልቅ ስልጠናውን እየወሰዱ ቢቆዩ ለመደበኛ ትምህርታቸውም በእጅጉ እንደሚያግዛቸው  ተገልጿል፡፡ ስልጠናው ከሀምሌ 1ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ወራት በተጠናከረ ሁኔታ እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡

  የጋዜጠኛ ታምሩ ከፈለኝ የመጀመሪያ ሥራ የሆነው “የሊስትሮው ማስታዎሻ” ልብ ወለድ መፅሐፍ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 19 ቀን 2015 ከቀኑ 10፡00 ጀምሮ አራት ኪሎ ኢክላስ ህንፃ ላይ በሚገኘው ዋልያ መፃህፍት ቤት ይመረቃል። መፅሐፉ በዋናነት አንድ ጫማ በማስዋብ ስራ ላይ የሚተዳደር ሊስትሮን ህይወት የሚዳስስና የሚያስቃኝ ልብ-ወለድ ታሪክ ስለመሆኑ የመፅሐፉ ደራሲ ጋዜጠኛ ታምሩ ከፈለኝ ገልጿል። በ135 ገፅ ተቀንብቦ በ300 ብር ለገበያ በቀረበው በዚህ መፅሐፍ ምረቃ ላይ የመፅሀፍ ዳሰሳ፣ ከመፅሐፉ የተመረጡ ታሪኮች ንባብና የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ መሰናዶዎች ለታዳሚ ይቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ወጣትና አንጋፋ ደራሲያን፣ የስነ-ፅሁፍ አፍቃሪያን፣ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በምረቃው ላይ ይታደማሉም ተብሏል።

 በዳንኤል ተፈራ ማሞ የተጻፈው “ከአቧሬ ካዛንቺስ እስከ ኮለምበስ ኦሃዮ“ የተሰኘ መጽሐፍ፣ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 19፣ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በሃገር ፍቅር ትንሹ አዳራሽ እንደሚመረቅ ተገለጸ፡፡
ጸሃፊው፤ በስደት ህይወቱ ያሳለፋቸውን ውጣውረዶች፣ አስተማሪና አዝናኝ ገጠመኞች  እንዲሁም በጀብዱ የተሞላ እውነተኛ ታሪኩን ነው ለአንባብያን ያበረከተው ተብሏል፡፡
የሥነጽሁፍ ባለሙያው ደሳለኝ ሥዩም በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው አስተያየት፤ “በዳንኤል ተፈራ ማሞ ህይወት ውስጥ ዕውቂያ ያልነበራቸው ወይም የሌላቸው የኪነጥበብ ሰዎች፣ የፖለቲካ ሰዎች፣ ወይም ባለሃብቶች የሉም ማለት ይቻላል፤ ከብርሃኑ ነጋ እስከ ዲማ ነገዎ፣ ከጎሹ ወልዴ እስከ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከአዲሱ ለገሰ እስከ መለስ ዜናዊ፣ ከአሃዱ ሳቡሬ እስከ ማናህሎሽ ጎላ (የአዜብ መስፍን እናት)፣ ከሰጠኝ መርቆ እስከ አስቴር አወቀ፣ ከሙለር ሪል እስቴት እስከ ቀበሪቾ ሬስቶራንት ዳንኤል የማያውቃቸው ምስጢሮች ወይም መረጃዎች የሉም፤ ስለሁሉም ተሰምተው የማያውቁ መረጃዎች ይነግረናል፡፡ በሌላ ጥበብ ውስጥ ላሉ ሰዎች አንድ ብቻ ጥያቄ ጣል ላድርግ፤ ይሄ ታሪክ ፊልም ካልሆነ የትኛው ታሪክ ፊልም መሆን ይችላል?” ሲል ጠይቋል፡፡
በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍና ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ የተጠቆመ ሲሆን፤ በመርሃግብሩ ላይ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሥነጽሁፍ ባለሙያዎችና የክብር እንግዶች እንደሚታደሙም ታውቋል፡፡   


 ከማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጨረፍታ

 

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ የቻይና አቻቸውን፣ “አምባገነን” መሪ ናቸው ማለታቸው ውዝግብ ፈጠረ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው አንቶኒ ብሊንከን፣ በቤጂንግ ከፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ምክክር ባደረጉ ማግስት የተሰማው አስተያየት ከምን የመነጨ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ፕሬዚዳንት ሺ እና ብሊንከን የሀገራቱን የተካረረ ግንኙነት የሚያለዝቡ ውይይቶች እንዲደረጉ መስማማታቸውን ማሳወቃቸው ይታወሳል።
ራሳቸው ባይደንም ሰኞ እለት የአሜሪካና ቻይና ግንኙነት ወደ ትክክለኛው መስመር እየተመለሰ መሆኑን ተናግረው ነበር። ፕሬዚዳንቱ ማክሰኞ  ምሽት በካሊፎርኒያ በተደረገ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ላይ ግን ብሊንከን ሰኞ እለት “ቢዘጋ” ይሻላል ያሉትን አጀንዳ አንስተዋል።
“ፕሬዚዳንት ሺ የቻይና እንደሆኑ የተጠረጠሩት ተንሳፋፊ የስለላ ፊኛዎች፣ በአሜሪካ የአየር ክልል ተመተው በመውደቃቸው ሀፍረት ተሰምቶታል“  ነው ያሉት ባይደን።
 “ሺ ጂንፒንግ በወቅቱ የተረበሸው በስለላ ቁሳቁሶች የተሞላው ተንሳፋፊ ፊኛን መትቼ ስጥለው የት እንዳለ እንኳን ስለማያውቅ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ይህ ለአምባገነኖች እጅግ አሳፋሪ ነገር ነው፤ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ሳያውቁ ሲቀሩና ባልጠበቁት መንገድ ስንመታው (ፊኛውን) ተበሳጭተዋል” በማለትም አክለዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማኦ ኒንግ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት አስተያየት ”በእጅጉ አሳዛኝና ሃላፊነት የጎደለው” ነው ብለውታል፡፡
 ከመሰረታዊ እውነታ የሚጻረርና የዲፕሎማሲ ፕሮቶኮል በእጅጉ የሚጥስ  ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ፤ ”ግልጽ የፖለቲካ ትንኮሳ ነው” ሲሉም  ተችተዋል፡፡
ቃል አቀባይዋ አክለውም፤ ”ቻይና ከፍተኛ ቅሬታዋንና ተቃውሞዋን ትገልጻለች” ብለዋል፡፡ ከአምስት አመት በኋላ ሰሞኑን ከፍተኛ ባለሥልጣኗን ወደ ቻይና የላከችው አሜሪካ፥ ውጥረቱ ረገበ ሲባል ዳግም ቁርሾ የሚቀሰቅስ ንግግር በፕሬዚዳንቷ በኩል መሰማቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። ዋሽንግተንና ቤጂንግ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ ከስምምነት ላይ ይድረሱ እንጂ፣ አሁንም የልዩነት ምንጭ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች አሏቸው።  የንግድ፣ የሰብአዊ መብትና የታይዋን ጉዳይ ሃያላኑን ሀገራት እንዳፋጠጡ ቀጥለዋል፡፡(አል-ዐይን)