Administrator

Administrator

  በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማካይነት በአፍሪካ ዘላቂ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ እድገት የማምጣት ተልዕኮ አንግቦ  የተቋቋመው ስማርት አፍሪካ አሊያንስ የተባለ አህጉራዊ ጥምረት አባል የሆኑ 30 የአፍሪካ አገራት መሪዎች በኢንተርኔት አገልግሎት ዋጋ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ ለማድረግ መስማማታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ጋቦን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ደቡብ ሱዳንና ማሊን ጨምሮ በአባልነት የተካተቱበት የጥምረቱ አባል አገራት መሪዎች፤ ከመጪው የፈረንጆች አመት ጀምሮ በየአገራቸው የኢንተርኔት አገልግሎት ታሪፍ ላይ የ50 በመቶ ቅናሽ ለማድረግ መወሰናቸውን ባለፈው ሰኞ ባወጡት የጋራ መግለጫ ማስታወቃቸውን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
በአፍሪካ አገራት የኢንተርኔት ክፍያ እጅግ ከፍተኛ ወይም እጅግ ውድ በመሆኑ ዜጎች የሚፈልጉትንና የሚገባቸውን ያህል የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ መግባባት ላይ የደረሱት የጥምረቱ አባል ፤ የኢንተርኔት አገልግሎትን ለዜጎች በተመጣጣኝ ክፍያ ለማዳረስ ሲሉ የዋጋ ቅናሹን ለማድረግ መስማማታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በመላው አለም እጅግ ውድ የሞባይል ኢንተርኔት ክፍያ የሚጠየቀው በአፍሪካ እንደሆነ ኢኮ ባንክ በ2018 ያወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከአፍሪካ ከፍተኛ ክፍያ በሚጠየቅባቸው ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ዚምቧቡዌና ስዋዚላንድ ለአንድ ጊጋ ባይት ኢንተርኔት ከ20 ዶላር በላይ እንደሚከፈልም አክሎ ገልጧል፡፡

  አንጌላ መርኬል ለ10ኛ ጊዜ 1ኛ ደረጃን ይዘዋል


            በተለያዩ የሙያ መስኮች ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉና ተሰሚነት ያተረፉ የአለማችን ሴቶችን በየአመቱ እየመረጠ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሔት ከሰሞኑ የ2020 የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶችን ዝርዝር ያወጣ ሲሆን፣ ላለፉት 9 አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበሩት የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል ዘንድሮም ክብራቸውን የሚነጥቃቸው አላገኙም፡፡
የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ፋላፊ ክርስቲያን ላጋርድ እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፤ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት፣ ጥቁር አሜሪካዊትና እስያ አሜሪካዊት ምክትል ፕሬዚዳንት ሊሆኑ የሳምንታት ጊዜ ብቻ የቀራቸው ካማላ ሃሪስ፤ የአመቱ ሶስተኛዋ የአለማችን ሃያል ሴት ተብለዋል፡፡
ኡርሱላ ቫን ደር ላይን አራተኛዋ፣ የቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ተባባሪ ሊቀ መንበር ሚሊንዳ ጌትስ አምስተኛዋ፣ ሜሪካ ባራ ስድስተኛዋ፣ የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ሰባተኛዋ፣ አና ፓትሪሺያ ቦቲን ስምንተኛዋ፣ አቤጊየል ጆንሰን ዘጠነኛዋ፣ ጌል ቦድሬክስ አስረኛዋ የአመቱ የአለማችን ሃያል ሴት ተብለው በፎርብስ መጽሔት ተመርጠዋል፡፡
ፎርብስ ለ17 ጊዜ ያወጣው የአለማችን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የ30 አገራት ሴቶች የተካተቱ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አስሩ የአገራት መሪዎች፣ ሰላሳ ስምንቱ የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎችና አመራሮች፣ አምስቱ ደግሞ በመዝናኛው መስክ የተሰማሩ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡


 የልብ ህመም ባለፉት 20 አመታት በገዳይነት አቻ አልተገኘለትም


           እስካለፈው ሰኔ ወር ድረስ በመላው አለም ግጭት፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ውንጀላን ጨምሮ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ80 ሚሊዮን በላይ ማለፉን ተመድ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን በማስጠለል ቀዳሚዋ አገር ቱርክ ስትሆን በአገሪቱ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 3.6 ሚሊዮን ያህል ስደተኞች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በመላው አለም በአስገዳጅ ሁኔታ ከተፈናቀሉት ሰዎች መካከል 45.7 ሚሊዮን ያህሉ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ አገራቸውን ጥለው የተሰደዱት 29.6 ሚሊዮን፣ ጥገኝነት የጠየቁ ደግሞ 4.2 ሚሊዮን እንደሚደርሱ አመልክቷል፡፡
በአንድ አገር ዜግነት ያልተመዘገቡ ወይም የአገር አልባ ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ባይታወቅም፣ በመላው አለም የሚገኙ 79 ያህል አገራት በግዛታቸው ውስጥ በድምሩ 4.2 ሚሊዮን ያህል አገር አልባ ሰዎች እንደሚገኙ ማስታወቃቸውንም ሪፖርቱ አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም ባለፉት 2 አስርት አመታት በርካታ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት በመዳረግ ረገድ የልብ ህመም ቀዳሚነቱን ይዞ መዝለቁንና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ በአለማችን 9 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በልብ ህመም ለሞት መዳረጋቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በርካታ ሰዎችን ለሞት በመዳረግ ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ከያዙት የሞት ምክንያቶች መካከል 7ቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መሆናቸውን የጠቆመው መግለጫው፣ 10 ምክንያቶች በ2019 ብቻ በመላው አለም 55.4 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች በገዳይነት የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ ከወሊድ ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮች ደግሞ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡


 በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ክትባቱን ለማግኘት አመታት ሊፈጅባቸው ይችላል

            ሃብታም አገራት አጠቃላይ ህዝባቸውን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ከ3 ጊዜ በላይ ሊከትቡበት የሚችል እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው የኮሮና ቫይረስ ክትባት ገዝተው ቢያጠናቅቁም፣ በመላው አለም ከሚገኙ 10 የድሃ አገራት ዜጎች ውስጥ 9ኙ ወይም 90 በመቶ ያህሉ እስከ መጪው የፈረንጆች አመት 2021 ድረስ ክትባቱን ላያገኙ እንደሚችሉ ኦክስፋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የኮሮና ክትባትን በፍትሃዊነት ለማዳረስ ታስቦ የተቋቋመውና አገራትንና አለማቀፍ ተቋማትን በአባልነት ያካተተው አለማቀፉ የክትባት ጥምረት አባል የሆነው ግብረ ሰናይ ድርጅት ኦክስፋም ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ አነስተኛና ዝቅ ያለ መካከለኛ ገቢ ያላቸው 67 የአለማችን አገራት በመጪው የፈረንጆች አመት የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ማዳረስ የሚችሉት ለ10 በመቶ ዜጎቻቸው ብቻ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
አገራት የኮሮና ክትባትን ፈጥነው ለማግኘት እሽቅድምድም ሲያደርጉ እንደቆዩ የጠቆመው ዘገባው፣ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አገራትና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠና እጅግ ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ ከተመሰከረላቸው የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች መካከል 53 በመቶ የሚሆኑትን ቀደም ብለው የገዟቸው ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 14 በመቶ ያህሉ ብቻ የሚገኝባቸው ጥቂት አገራት መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
ሃብታም አገራት የጀመሩት የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽሚያ አንዳች ሁነኛ መላ በፍጥነት ካልተበጀለት በአለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአመታት ያህል ክትባት ላያገኙ እንደሚችሉ ስጋቱን የጠቆመው ኦክስፋም፣ ለአብነትም ከውጤታማዎቹ የኮሮና ክትባቶች አንዱ የሆነው ፋይዘር ክትባት 96 በመቶ ያህሉ በሃብታም አገራት ቀደም ብሎ መገዛቱን ጠቅሷል፡፡
ያደጉ አገራት ክትባቱን በፍትሃዊነት ለማዳረስ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የገቡትን ቃል በመጣስ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በመግዛት ላይ እንደሚገኙና እስካሁንም 7.3 ቢሊዮን ያህል ክትባቶች መሸጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ክትባቱን በብዛት ከገዙ አገራት መካከል በምሳሌነት ያቀረባት ካናዳ አጠቃላይ ህዝቧን ከአምስት ዙር በላይ ደጋግማ ለመከተብ የሚያስችላትን ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በገፍ መግዛቷን አብራርቷል፡፡
ስትሬት ታይምስ በበኩሉ፣ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ መጠን ያለው የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በመግዛት ህንድ በአንደኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና አገሪቱ እስካሁን አስትራዜንካ፣ ኖቫቫክስና ስፑትኒክ 5ን ጨምሮ በድምሩ 1.6 ቢሊዮን ክትባቶችን መግዛቷን ዘግቧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ዜና ደግሞ፣ ፋይዘር የተሰኘውን የኮሮና ቫይረስ ክትባት በመግዛት ከአለማችን አገራት ቀዳሚዋ በሆነችው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱ ለተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎች ባለፈው ማክሰኞ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን፣ በሰሜን አየርላንድ የሚኖሩት የ90 አመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ማርግሬት ኪናን ክትባቱን ከምርምር ውጭ በመደበኛነት የተከተቡ የመጀመሪያዋ የአለማችን ሰው ሆነው ተመዝግበዋል፡፡
ሩስያ በበኩሏ፤ አስተማማኝነቱ አነጋጋሪ ሆኖ የቆየውንና 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ አረጋግጫለሁ ያለችውን ስፑትኒክ 5 የተሰኘ የራሷ ምርምር ውጤት የሆነ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ በመዲናዋ ሞስኮ ለዜጎች መስጠት መጀመሯንም ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ከሳምንታት በኋላ ቃለ መሃላ ፈጽመው ወደ ነጩ ቤተ መንግስት እንደሚገቡ የሚጠበቁት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በመጀመሪያዎቹ 100 የስልጣን ቀናት ውስጥ በመላ አገሪቱ የሚገኙ 100 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ክትባት እንዲያገኙ ለማስቻል ማቀዳቸውን ከሰሞኑ ማስታወቃቸውን ያስነበበው ደግሞ ቢቢሲ ነው፡፡ የኮሮና ክትባትን በአገልግሎት ላይ ለማዋል ዝግጅቷን እያጠናቀቀች በምትገኘው አሜሪካ፤ ህዝቡ ለክትባቱ በጎ አመለካከት እንዲኖረውና ለመከተብ እንዲነሳሳ ለማበረታታት በማሰብ የቀድሞዎቹ የአገሪቱ ፕሬዚዳንቶች ቡሽ፣ ክሊንተንና ኦባማ በቴሌቪዥን እየታዩ ክትባቱን ለመውሰድ ቃል መግባታቸውም ተነግሯል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና፣ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከ2.29 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮሮና በተጠቁባትና 55 ሺህ የሚሆኑም ለሞት በተዳረጉባት አፍሪካ በድምሩ 54 ሺህ ያህል የጤና ሰራተኞች በቫይረሱ መያዛቸውንና አብዛኞቹም ነርሶች መሆናቸውን የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡


 አንዳንድ ታሪክ ጊዜው እጅግ ሲርቅ ተረት ይሆናል፡፡ በጥንት ዘመን አንድ ሮማዊ ጀግና ወታደር ነበር ይባላል፡፡ አያሌ ጦርነቶችን በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ አብዛኛውን ህይወቱን በጦር ሜዳ ስላሳለፈ በአካል የሚያውቀው ሰው የለም፡፡ ዝናው ግን በሰፊው ይወራል፡፡ አንድ ጊዜ ታዲያ አጠቃላይ ምርጫ በሀገሪቱ ሲካሄድ፣ ያ ጀግና፣ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አለብኝ ብሎ ወሰነ፡፡ ስለዚህም በምርጫው ለከፍተኛው የፓርላማ ቦታ ይወዳደር ጀመር፡፡ በዚያን ጊዜው የሮማውያን የምርጫ ባህል፣ ጥሩ ዲስኩር (ንግግር) ማድረግ ግድ ነበር፡፡ ጀግናው ንግግሩን የጀመረው ለዓመታት ለሮማ ሲዋጋ፣ በጥይት ብዙ ቦታ ቆስሎ ነበርና፣ ገላው ላይ ጠባሳዎቹን በማሳየት ነበር፡፡ ህዝቡ ከንግግሩ ይልቅ ጠባሳዎቹን እያየ ዕንባ በዕንባ ተራጨ፡፡ የዚያ ጀግና በምርጫው አሸናፊነት ከሞላ ጐደል የተረጋገጠ መሰለ፡፡ ታዲያ የዋናው ምርጫ ቀን፣ ያ ጀግና፣ በመላው የፓርላማ አባላትና በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ታጅቦ ወደ መድረኩ ብቅ አለ፡፡ ህዝቡ ግራ ተጋባ፡፡ “በእንዲህ ያለ የምርጫ ቀን፣ ይሄ ሁሉ ጉራ ለምን አስፈለገ?” ይባባል ጀመር፡፡ ያ ጀግና ንግግር ሲያደርግ፣ አጃቢዎችንና ሀብታሞችን የሚያወድስ፣ በትዕቢትና በጉራ የተሞላ፣ የጦር ሜዳ ድሎቹን እያሳቀለ፣ "ከኔ ወዲያ ጀግና ላሳር ነው" ይል ጀመር፡፡ ተፎካካሪዎቹንም "አንተና አንቺ" እያለ ያዋርድ ገባ። ቀልድ አወራሁ ብሎ የሚናገራቸው ወጐች ራሳቸው፣ የሰው ሞራል የሚነኩና ህዝቡን የሚያበሳጩ ሆኑ፡፡ “ለሮማም እስከ ዛሬ ታይቶ የማይታወቅ ልማትና ሀብት አመጣላታለሁ!” እያለ በከፍተኛ መወጣጠር መድረኩ ላይ ተንጐራደደ፡፡ ህዝቡም፤ “ያ እንደዚያ ዝናው የተወራ የጦር ሜዳ ጀግና፣ እንዲህ ያለ ቱሪናፋ ነው እንዴ?” አለ፡፡ ወሬው በአገሪቱ ሙሉ ወዲያው ተሰማ፡፡ “ይሄንንማ ፈፅሞ አንመርጥም፡፡ እንዳይመረጥም ላልሰማው ህዝብ መናገር አለብን”፤ አለ ህዝቡ፡፡ ጀግናው ድምፅ አጣ! ሳይመረጥ ቀረ፡፡ ወደ ጦር ሜዳው ተመለሰ፡፡ “ያልመረጠኝን ህዝብ አሳየዋለሁ። እበቀለዋለሁ!” ይል ጀመር። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ሮማ የእርዳታ እህል በመርከብ መጣ፡፡ ምክር ቤቱ በነፃ ይታደል አለ፡፡ ያ ጀግና፤ “ይሄ እህል በነፃ መታደል የለበትም፡፡ እምቢ ካላችሁ ጦር ሜዳውን ትቼላችሁ እመለሳለሁ” እያለ ያስፈራራ ጀመር፡፡ ይሄን ወሬ፣ ምክር ቤቱ ለህዝቡ ነገረ፡፡ ህዝቡ ተቆጣ፡፡ “ያ ጀግና እፊታችን ቀርቦ ያስረዳ” አለ፡፡ ጀግናው ደግሞ “ህዝብ ብሎ ነገር አላቅም፡፡ ዲሞክራሲም አልቀበልም፡፡ አልመጣም” አለ፡፡ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ጮኸ፡፡ ምክር ቤቱ ያን ጀግና የግዱን እንዲመጣ አደረገውና፣ ሸንጐ መድረክ ላይ ቆሞ እንዲናገር ታዘዘ፡፡ ጀግናውም አሁንም በእልህና በትእቢት ሁሉንም መሳደቡን ቀጠለ፡፡ ህዝቡ በሆታ አስቆመው፡፡ ለፍርድ ይቅረብልን አለ። ምክር ቤቱ ምንም ምርጫ አልነበረውም። ለፍርድ አቀረበው፡፡ በዚያን ዘመን ወንጀለኛ ይቀጣበት በነበረው፤ ከከፍተኛ ተራራ ወደ መሬት ይወርወር፤ የሚል ሀሳብ ቀረበ፡፡ ሆኖም አስተያየት ተደርጐ ቅጣቱ እድሜ ልክ ይሁንለት ተባለና፣ ዘብጥያ ተወረወረ! ህዝቡ በሆታና በዕልልታ መንገዱን ሞላው፡፡
 *   *   *
 ሰዎችን በንግግር እንማርካለን ብለን ብዙ በለፈለፍን ቁጥር ብዙ ከቁጥጥራችን የሚወጡ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ጠንካራና ልባም ሰዎች ጥቂት ምርጥ ነገሮችን ብቻ በመናገር የሰውን ልብ ይነካሉ፡፡ ስለዚህ ከአንደበታችን በመቆጠብ፣ ትሁት በመሆን፣ ህዝብን ባለመናቅ፣ ለምንናገረው ነገር የቤት- ሥራችንን ጠንቅቀን በመስራትና ጉዳያችንን በማወቅ ነው ለውጥ ለማምጣት የምንችለው፡፡ ከሁሉም በላይ ተአብዮ፣ አገርንና ህዝብን ይጐዳል፡፡ "ከማንም በላይ ነኝ" እና አምባገነንነት የእብሪት ልጆች ናቸው፡፡ ንቀት፣ ሰው-ጤፉነት፣ ሁሉን አውቃለሁ ባይነት፣ ቆይ - አሳይሃለሁ - ባይነት፤ ብቆጣም እመታሻለሁ፤ ብትቆጪም እመታሻለሁ ማለት፤ የማታ ማታ ከላይ የተጠቀሰውን የጦር-ሜዳ ጀግና ዕጣ-ፈንታ የሚያሰጠን መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ከበደ ሚካኤል፤
“ኩራትና ትእቢት፣ የሞሉት አናት
ሰይፍና ጐራዴ፣ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ” የሚሉን ለዚህ ነው፡፡
ከልክ ያለፈ ውዳሴና ማሞካሸትም ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ተወዳሹ እስኪታዘበን ድረስ ብናሳቅለው ለማንም የማይበጅ ንግግር እንዳቀረብን ነው የሚቆጠረው፡፡ ፀጋዬ ገብረመድህን፤ “ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት ማሞካሸት የማይደክማት” የሚለን ለዚህ ነው፡፡ እናስተውል፡፡ ብዙ "እዩኝ እዩኝ ደብቁኝ ደብቁኝ"ን እንደሚያስከትል አንርሳ፡፡ ብዙ በተናገርን ቁጥር አልባሌና ዝቅ የሚያደርጉንን ጥፋቶች ለመስራት በር እንከፍታለን፡፡ ባልዳበረ አእምሮና ባልበሰለ አንደበት ስንቶችን ልናስቀይም እንደምንችል እናጢን፡፡ “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚለውን ተረት ከልቦናችን አንለይ፡፡ ከቶውንም "እኔ አውቃለሁ"ን ስንፈክር፣ ሌላውም ያውቃልን አንርሳ፡፡ ባደባንበት ሊደባብን እንደሚችል፣ ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን መሆኑን፣ ሥራ ለሰሪው እሾክ ላጣሪው እንደሚሆን አንዘንጋ፡፡ የወላይታው ተረት - “የኛ ቤት ጠማማነት እኛን ይጨርሳል፤ አለ እንጨት” የሚለን ይሄንኑ ነው!  በብዕር ስሙ “ገሞራው” በመባል የሚታወቀው ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ፣ ሐምሌ 1935 ዓ.ም በደብረ ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ፣ አዲስ አበባ ተወለደ። አባቱ መሪ ጌታ ገብረ ዮሐንስ ተሰማ፣ እናቱ ወ/ሮ አመለወርቅ ሀብተወልድ ይባላሉ።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና በሰዋሰው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሏል። ከዚያም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ የቋንቋ ጥናትና የስነ ልሳን ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቀ። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቀ በኋላ በመጀመሪያ ተግባረዕድ ትምህርት ቤት፣ ቀጥሎም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መምህራን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት (ኮተቤ) በመምህርነት አገልግሏል።
በ1968 ዓ.ም ባገኘው የነፃ ትምህርት ዕድል ወደ ቻይና ሄዶ በቋንቋና በፊሎዞፊ መስክ ሁለተኛ ዲግሪውን የተቀበለ ሲሆን፤ ወደዚያ የተጓዘበትን ትምህርት ከአጠናቀቀ በኋላ በቻይና ቋንቋና ስነ-ጽሑፍ ላይ ምርምር አደረገ። የቻይና ስነ-ጽሑፍ ነፃነት የሌለው ሆኖ ስለታየው በመንግሥቱና በሥርዓቱ ላይ የፅሑፍ ትችትና ነቀፋ ሰነዘረ። በዚህ ምክንያት ከቻይና ወደ ስዊድን ሄደ። ከዚህ በኋላ ስደተኛ ሆኖ ቀረ።
ኃይሉ፣ እ.ኤ.አ ከ1980 እስከ 2010 በኖርዌይና ስዊድን ሀገሮች በስደት ሲኖር በትርፍ ጊዜው በልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ከ30 በላይ ጽሑፎችን አስር መጻሕፍትን ለኅትመት አብቅቷል። ከእነዚህም ውስጥ ጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. በረከተ መርገም፡- የግጥም መጽሐፍ ነው። የጻፈውና በንባብ ያስደመጠው ቀ.ኃ.ሥ. ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበረበት በ1959 ዓ.ም ሲሆን፣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ግን በ1966 (ብርናንና ሰላም ማተሚያ ቤት)ነው። በድጋሚ እ.ኤ.አ. የካቲት 1980 ስዊድን አገር ታትሟል።
2. ፍንደቃ፡- በ1968 ዓ.ም ፣ አዲስ አበባ፣ ትንሣኤ ዘጉባዔ ማሚያ ቤት ታተመ።
3. ዜሮ ፊት አውራሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥር 1980፣
4. ዛር ነው በሽታዋ:- እ.ኤ.አ. መጋቢት 1981፣
5. በናቴኮ ሴት ነኝ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1982፣
6. ወይዘሪት ወይዘሮ፡- እ.ኤ.አ ግንቦት 1983.
7. እናትክን በሉልኝ፡- እ.ኤ.አ  ሕዳር 1984.
8. ቆርጠሃት ጣልልኝ፡- እ.ኤ.አ ሰኔ 1985፣
9. የመንጎሌ ጥሪ፡- እ.ኤ.አ. ጥቅምት 1985፣
10. የሽግግር ደባ፡- እ.ኤ.አ. የካቲት 1986፣
(ከተራ ቁጥር 2-10 የተጠቀሱት መጻሕፍት የታተሙት፣ በNina Printing press, Kungsangsvagen  25፣ S-753 23 Uppsala Sweden ማተሚያ ቤት ነው።)
ኃይሉ (ገሞራው)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎችን እንቅስቃሴ በብዕሩ በማጋጋል የታወቀ ነበር። በዚህም የተነሳ በተደጋጋሚ የእስር ቤት ሰለባ ከመሆኑም በላይ ከዩኒቨርሲቲው እስከ መባረር ደርሶ ነበር። በሕዝቡ፣ በተለይም በዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ አድናቆት፣ እውቅናና ሽልማት ያገኘበት “በረከተ መርገም” የተባለው ግጥም ነው። በ1960ዎቹ ውስጥ የነበሩት የመንግስት ፀጥታ ሠራተኞችና ፖሊሶች “ባለ መርዛሙ ብዕር” ብለው ይጠሩት እንደነበር ይታወቃል። ከ“መርዛሙ ብዕር” የቀለም ጠብታ ለአብነት እነሆ፡-
“በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መካከል፤
ሕይወት የምንለው እንደ ጥሬ እህል፤
በኑሮ ምጣድ ላይ ቢቆላ ቢማሰል፣
የበሰለው ያራል ጥሬው እስኪበስል።
በሰበብ አስባቡ ራስን ለመጥቀም፤
ንብረት ለማደርጀት እያጋነኑ ስም፤
በህግ አመካኝቶ እየተወጡ ቂም፤
ደግሞም ለመፈንጠዝ በማዕዘን ዓለም፤
ጭቆና ባርነት፣ አድልዖና አመጽ፣ እንዲስፋፋ በጣም።
እንዲሆን ከሆነ አስበው መርምረው፣ ስልጣንን የሰሩት፣
ደግሞም አስተዳደር፣ ሕግም ሆነ መንግሥት፤
እነዚያ ጀጁዎች የዋሆቹ ፍጥረት፣
ፕሌቶ አርስቶትል ሁላቸው ሊቃውንት፣
ይህን ግብዝ ሐሳብ፣ ከግብ ሳያደርሱት
በሥራ ላይ ሳይውል ገና ሲወጥኑት፣
ይሻላቸው ነበር፣ አፎቿን ከፋፍታ ብትውጣቸው መሬት”
ኃይሉ፣ ከሚወዳት ሀገሩ ርቆ፣ ብሶቱን ሲሰማለት ከነበረው ወገኑ ተለይቶ፣ ለ35 ዓመታት በቻይና፣ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት፣ በኖርዌይና በስዊድን እየተዘዋወረ ሲኖር፣ በርከት ያሉ ጽሑፎችን በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በኖርዊጂያንና በስዊድንኛ ቋንቋዎች አበርክቷል።
ይህ ታዋቂ ገጣሚ በሀገራችን የተፈራረቁ የመንግስት ስርዓቶችን አንዱንም ደግፎ አያውቅም። ይልቁንም ባለበት ሀገር ሆኖ በተባ ብዕሩ ሲሄሳቸውና ሲነቅፋቸው ኖሯል።
ኃይሉ (ገሞራው) ባደረበት ፅኑ ሕመም ምክንያት በተወለደ 72 ዓመቱ ጥቅምት 30 ቀን 2007 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በኑዛዜው መሰረት አስክሬኑ ከኖረበት ስዊድን፣ ወደሚወዳት ሀገሩ መጥቶ፣ በደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ዐረፈ።
(በኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከታተመው “ማህደረ ደራስያን" አዲስ መፅሐፍ የተወሰደ) መላው አለም ውጤታማነታቸው ከተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ጋር ተመሳስለው የተሰሩና ለጤና ጎጂ የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በህገወጥ መንገድ በድብቅ ለመሸጥና ትክክለኛ ክትባቶችን መዝረፍን ጨምሮ በርካታ “ኮሮና ነክ ወንጀሎችን” ለመፈጸም ያቆበቆቡ የተደራጁ ወንጀለኞችን ነቅቶ እንዲጠብቅ አለማቀፉ የፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል አስጠንቅቋል፡፡
የተለያዩ አገራት ኩባንያዎችና የምርምር ተቋማት ውጤታማነታቸው የተረጋገጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ጥቅም ላይ ለማዋል የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ በደረሱበትና አገራት ክትባቶችን ቀድመው ለማግኘት በሚሯሯጡበት እንዲሁም የግዢ ስምምነት በመፈጸም ላይ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት፣ የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ሃሰተኛ ክትባቶችን ለመቸብቸብ እንዲሁም ትክክለኛ ክትባቶችን ለመዝረፍ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ መረጃ ደርሶኛል ብሏል ኢንተርፖል ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ።
ተቀማጭነቱ በፈረንሳይ የሆነው አለማቀፉ የፖሊስ ትብብር ተቋም ኢንተርፖል፣ በአባልነት ላቀፋቸው 194 የአለማችን አገራት በላከው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፣ የተደራጁና ረጅም የወንጀል ሰንሰለት የፈጠሩ ወንጀለኞች ከኮሮና ክትባቶች ጋር በተያያዘ አካላዊም ሆነ በኢንተርኔት በኩል የሚካሄድ የወንጀል ድርጊት ሊፈጽሙ ስለሚችሉ የህግ አስከባሪ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተለያዩ የአለማችን አገራት ባልተጠበቀ ሁኔታ ለስግብግብ ወንጀለኞች መጠቀሚያ መልካም እድል ከሆነ መሰነባበቱን ያስታወሰው ተቋሙ፣ በቀጣይም ከጥራት በታች የሆኑ ሃሰተኛ ክትባቶችን በድብቅ አምርቶ መሸጥ፣ የክትባቶች ዝርፊያና ህገወጥ የክትባት ማስታወቂያዎችን ጨምሮ ኮሮና ተኮር የወንጀል ወረርሽኝ በስፋት ሊሰራጭ እንደሚችል ያለውን ስጋትም ገልጧል፡፡
ወንጀለኛ ቡድኖቹ ከዚህ ባለፈም ሃሰተኛ የኮሮና መመርመሪያ መሳሪያዎችን በህገወጥ መንገድ አምርተው ለገበያ የማቅረብ ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፣ የአለም አገራት መንግስታት፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ ህግ አስፈጻሚና የደህንነት ተቋማት እነዚህን ወንጀለኞች ለመከላከልና በቁጥጥር ስር ለማዋል በንቃት እንዲሰሩና ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መድሃኒቶችን በመሸጥ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 ሺህ ያህል ድረገጾች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ ከ1 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑት ለወንጀል የተቋቋሙ ወይም በቫይረስ አማካይነት የኢንተርኔት ጥቃት የሚያደርሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉን የሚናገረው ተቋሙ፣ ህብረተሰቡ በድረገጾች አማካይነት ከሚከናወኑና ሰዎችን ለሞት አደጋ ብሎም ለከፋ የጤና ችግሮች ከሚያጋልጡ የሃሰተኛ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ሽያጮች ራሱን እንዲያርቅም ምክሩን ለግሷል፡፡
የአሜሪካው የአገር ውስጥ ደህንነት ምርመራ ቢሮ በበኩሉ፣ ከሰሞኑ በአገሪቱ ሁለት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች እውቅና አግኝተው በስራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ከመጠበቁ ጋር በተያያዘ አጭበርባሪዎች ይበራከታሉ ተብሎ በመገመቱ አዲስ ዘመቻ እንደሚጀምር ማስታወቁን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ከዚህ በፊት ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገው ዘመቻ ከጥራት በታች የሆኑ የፊት መከላከያ ጭንብሎችንና ለኮሮና ፈዋሽነቱ ያልተረጋገጠውን ክሎሮኪን የተባለ የወባ መድሃኒት አስመስለው ማምረትና ማከፋፈልን ጨምሮ ከ700 በላይ ኮሮና ነክ ወንጀሎችን መመርመሩን ያስታወሰው ቢሮው፣ ከመሰል ህገወጥ ንግድ የተገኘ 27 ሚሊዮን ዶላር መያዙንና በመሰል ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው የተገኙ ከ70 ሺህ በላይ ህገወጥ ድረገጾችን መዝጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዜናዎች ደግሞ፣ ብሪታኒያ ፋይዘርና ባዮንቴክ የተባሉት ኩባንያዎች ያመረቱትና ከኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ 95 በመቶ አስተማማኝ እንደሆነ የተረጋገጠው የኮሮና ቫይረስ ክትባት በግዛቷ ውስጥ በጥቅም ላይ እንዲውል በመፍቀድ ከአለማችን አገራት ቀዳሚ መሆኗን የዘገበው ቢቢሲ፣ አገሪቱ ከኩባንያዎቹ 40 ሚሊዮን ክትባቶችን ማዘዟንና የአገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ተቋም ክትባቱ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል ሲል ፈቃድ መስጠቱንም ገልጧል፡፡ የጃፓን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መንግስት በበኩሉ፤ ባለፈው ረቡዕ ባሳለፈው ውሳኔ፣ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ ለሚኖሩት 126 ሚሊዮን ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን በነጻ እንዲያዳርስ መወሰኑን ያሁ ኒውስ የዘገበ  ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስት ሞዴርና ከተባለው የክትባት አምራች ኩባንያ ለ85 ሚሊዮን ሰዎች፣ አስትራዜንካ ከተባለው ክትባት ደግሞ ለ120 ሚሊዮን ሰዎች የሚሆን ክትባት ማዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ቢዝነስ ኢንሳይደር በበኩሉ፤ የሰሜን ኮርያው መሪ ኪም ጁንግ ኡን በቻይና የተመረተና ውጤታማነቱ ያልተረጋገጠ የኮሮና ቫይረስ ክትባት መከተባቸውን የዘገበ ሲሆን፣ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ቤተሰቦቻቸውም ክትባቱን ወስደዋል መባሉን አክሎ ገልጧል፡፡  ኢንተርናሽናል ኤስኦኤስ የተባለው ተቋም በ2021 የፈረንጆች አመት ለጎብኝዎችና መንገደኞች እጅግ አደገኛ የሆኑና ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ይኖርባቸዋል ያላቸውን የአለማችን አገራት ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ሊቢያ፣ ሶርያና አፍጋኒስታን ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የፖለቲካ ነውጥ፣ ማህበራዊ አለመረጋጋት፣ የደህንነት ሁኔታ፣ የአደጋ ጊዜ ምላሽ አገልግሎቶች ሁኔታ እና የወንጀል ድርጊቶችን ጨምሮ በተለያዩ የደህንነት ስጋት መመዘኛዎች ተጠቅሞ በመገምገም፣ የአለማችን አገራትን የአመቱ የስጋት ደረጃ ይፋ ያደረገው ተቋሙ፣ ኢራቅና ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የአራተኛና አምስተኛ ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡
በአመቱ እጅግ አነስተኛ የስጋት ደረጃ ይኖራቸዋል ተብለው በሪፖርቱ የተጠቀሱት ሰባት የአለማችን አገራት በሙሉ የአውሮፓ አገራት ሲሆኑ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስሎቫኒያና ሉግዘምበርግ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተጓዦች መይም መንገደኞች ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ሶስቱ የአለማችን አገራት ብሎ ተቋሙ የጠቀሳቸው አገራት ሩስያ፣ ዩክሬንና ኦስትሪያ ሲሆኑ፤ በአንጻሩ አነስተኛ ተጽዕኖ ያደረሰባቸው ያላቸው አገራት ደግሞ ኒውዚላንድ፣ ታንዛኒያና ኒካራጓ ናቸው፡፡


በአለም ዙሪያ በየ100 ሰከንዱ 1 ህጻን በኤችአይቪ ቫይረስ እንደሚጠቃ እና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 በመላው አለም 110 ሺህ ያህል ህጻናት በኤድስ ምክንያት ለሞት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በመላው አለም 320 ሺህ ያህል ህጻናትና ወጣቶች በቫይረሱ መያዛቸውን ያስታወቀው ድርጅቱ፤ በቫይረሱ የሚያዙና ለሞት የሚዳረጉ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ሲሆን የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እያገኙ እንዳልሆነም ገልጧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ለህጻናት፣ ወጣቶችና ነፍሰጡር እናቶች የሚሰጡ የጸረ ኤች አይቪ ህክምና አገልግሎቶች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎሉ እንደሆነ የጠቆመው የድርጅቱ ሪፖርት፤ መንግስታት አገልግሎቶቹን ለማሟላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክቷል፡፡
በ2019 የፈረንጆች አመት በመላው አለም 1.7 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ መጠቃታቸውን ያስታወሰው የተመድ የዜና ድረገጽ በበኩሉ፣ በአመቱ በድምሩ 690 ሺህ ያህል ሰዎች ከኤችአይቪ ጋር በተያያዘ ለሞት መዳረጋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

 የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በቅርቡ ለንባብ ያበቁት “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” የተሰኘው መጽሐፍ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ በ1.7 ሚሊዮን ቅጂዎች መሸጡንና በዚህም አዲስ የሽያጭ ክብረወሰን ማስመዝገብ መቻሉን ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
መጽሐፉ በአሜሪካና ካናዳ ታትሞ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ቀን ብቻ ከ887 ሺህ በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡ ያስታወሰው ዘገባው፣ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በ1 ሚሊዮን 710 ሺህ 443 ቅጂዎች በመሸጥ አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቡን ፔንጉዊን ራንደም ሃውስ የተባለው የመጽሐፉ አሳታሚ ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሽያጩ የወረቀት፣ የድምጽና የዲጂታል ቅጂዎችን እንደሚያጠቃልል የጠቆመው ዘገባው፣ በመጀመሪያ ዙር በ3.4 ሚሊዮን ቅጂዎች የታተመው “ኤ ፕሮሚስድ ላንድ” ከሰሞኑ በተጨማሪ ቅጂዎች እንደታተመና እስካሁን ድረስ ለህትመት የበቃው አጠቃላይ ቅጂ 4.3 ሚሊዮን መድረሱንም አክሎ ገልጧል፡፡