Administrator
የፖለቲካ ሹመኞች በሙያተኞች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የመንግስት ሥራ እየተደናቀፈ ነው ተባለ
የፖለቲካ ሹመኞች በሙያተኞች ላይ በሚያሳድሩት ጫና የመንግሥት ሥራ እየተደናቀፈ ነው ሲሉ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎቹ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ። በብዙዎቹ የመንግስት መ/ቤቶች ሃላፊዎች ሥልጣን ላይ የሚቀመጡት በፖለቲካ ታማኝነት እንጂ በዕውቀትና በብቃት ባለመሆኑ በሙያተኞች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ሥራውንም ባለሙያውንም እየጎዳው መሆኑንም ያስረዳሉ። እየጎዳው ነው ተብሏል፡፡
በአንድ የመንግስት መ/ቤት ውስጥ በከፍተኛ ኤክስፐርትነት የሚሰሩት ግሩም ኤሊያስ (ዶ/ር) የተባሉ ግለሰብ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ በመ/ቤቱ ውስጥ በከፍተኛ ኤክስፐርትነት ቢቀጠሩም፣ በሃላፊነት የተመደበው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የፖለቲካ ሹመኛ በመሆኑ ሙያተኞች ሥራቸውን በቅጡ መስራት አልቻሉም ብለዋል።
እንደ ኤክስፐርቱ ገለፃ፣ ለሀገር ይጠቅማል ብለን የምናጠናው ጥናት፣ የምናቅደው ስትራቴጂክ ዕቅድ በሙሉ በዋና ስራ አስፈጻሚው ውድቅ ይደረጋል። የተሻለ ሀሳብ አይቀርብም፣ የተለፋበት ጥናትና እቅድ መና ይቀራል፡፡ እኛ ግን ከፍተኛ ደሞዝ እየተከፈለን ቀጥለናል። ይህ ደግሞ ህሊና ላለው ሰው ከባድ ነው ብለዋል፤ ግሩም ኤልያስ (ዶ/ር)።
ለደህንነታቸው ሲሉ የመስሪያ ቤታቸው ስም እንዳይጠቀስ የፈለጉት እኚህ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ በሥራ ባልደረቦቻቸው ዘንድ በማያምኑበት ጉዳይ ሁሉ ከአለቃቸው በመቃወም የሚታወቁ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ከአንዴም ሶስት ጊዜ በዲሲፕሊን ጥሰት የደሞዝ ቅጣት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ የመደረግ ዕጣ ፈንታ እንደገጠማቸው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
ግሩም ኤርምያስ ላለፉት ዓመታት ሲሰሩ በቆዩበት መስሪያ ቤት፣ ሥራቸውን በብቃትና በትጋት ከሚሰሩ ኤክስፐርቶች ይልቅ ለበላይ አካል ወሬ የሚያቀብሉና የሚላላኩ፣ የመስሪያ ቤቱ “ቁንጮ ሰራተኞች” ተብለው ይሸለማሉ፣ ደሞዛቸው ያድጋል ይመነደጋል፤ የደረጃ እድገትም ያገኛሉ መንግስት ይህን፤ አገርንም ህዝብንም የሚጎዳና እድገትን የሚጎትት የፖለቲካ ሹመኞች ፈላጭ ቆራጭነት በጊዜ ማስተካከል ካልቻለ፣ አገር ወደፊት መራመድ አትችልም ብለዋል። እርሳቸው በሙያቸው አገር ማገልገል ስላለባቸው ወደ ግል ተቋማት እያማተሩ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ሌላው በኢትዮ ቴሌኮም በከፍተኛ ባለሙያነት የሚሰራው ዘሪሁን አማን (ስሙ ተቀይሯል) የተባለ ወጣት ኤክስፐርት በበኩሉ፤ ከደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪውን ይዞ ወደ ሀገሩ መመለሱን ይናገራል። በለውጡ ሰሞን በኢትዮ ቴሌኮም የተቀጠረው ይሄው ወጣት ባለሙያ፤ ለውጡ የመጣ ሰሞን የነበረውን ተስፋና የለውጡ መንግስት ሥልጣን በያዘ ሰሞን በአገሪቱ የተስተዋለውን መነቃቃት በመተማመን ሀገሩን ለማገልገል ወጣትነቱን፣ ትኩስ ጉልበቱንና እውቀቱን ይዞ ወደዚህ መስሪያ ቤት መግባቱን ገልጿል።
በተለይ የመሥሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ከተሾመች በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ፈጣን ለውጦችን እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቁን የሚናገረው ወጣቱ፤ ከሃላፊዋ ስር ያሉ የፖለቲካ ሹመኞች ግን ተቋሙ የበለጠ እድገት እንዳያስመዘግብ ሙያተኞች ላይ የሚያሳድሩት ጫና ከፍተኛ ነው ይላል በምሬት። “ለሙያውና ለቴክኖሎጂው ያለኝን ቅርበትና የውጪ ተሞክሮዎችን በመጠቀም ተቋሙ የሌላው አገር ቴሌኮሙኒኬሽን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ ሌት ተቀን የማደርገው ጥረት ለአለቃዬ ምቾት አይሰጠውም፣ ያለው ወጣቱ፤ ከፍተኛ ኤክስፐርት፤ ይህም በሀገሬ በሙያዬና በአጠቃላይ ባለው በሁኔታ መሰላቸትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እያስገባኝ ነው ብሏል።
ወጣቱ አክሎም፤ ቢያንስ የፖለቲካ ሹመኞች የፖለቲካ ታማኝነታቸው እንዳለ ሆኖ ለሚመሩት መስሪያ ቤትና የስራ ጠባይ ቢቻል ሙያውን የተማሩና በዘርፉ እውቀት ያላቸው፣ ካልተቻለ ተቀራራቢ ሙያ ውስጥ ያሉ ቢሆኑ አገርን ከዘርፈ ብዙ ችግር መታደግ ስለሚችል መንግስት ጉዳዩን ያስብበት ጥሪ አቅርቧል።
ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም ዛሬ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ይካሄዳል
• ገዳሙን ለመታደግ 100 ሚ.ብር ያስፈልጋል
ለአቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም፣ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ፣ በካፒታል ሆቴል ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር የሚካሄድ ሲሆን፤ገቢው በገዳሙ ይዞታ ላይ ለሰፈሩ ነዋሪዎች ካሣ በመክፈል ይዞታውን ለገዳሙ ለማስመለስ ነው ተብሏል፡፡ የገዳሙ ገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ እንደገለጸው፤ ገዳሙን ለመታደግና ለማስፋፋት በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡
ገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል የአንድነት ገዳም፣ በ1574 የተመሰረተና የጻዲቁ አባት አቡነ ሐራ ድንግል ገድልና ገቢረ ተዓምራት የሚካሄድበት ገዳም ነው - ይላሉ የገዳሙ መነኮሳት፡፡
ከ400 ዓመት በላይ ታሪክ ያለው ይህ ትልቅ ገዳም በሰሜን ጎጃም፣ ባህርዳር ዙሪያ የሚገኝ ሲሆን፣ ጻዲቁ አቡነ ሐራ ድንግል፣ ከፈጣሪያቸው በተገባላቸው ቃልኪዳን መሠረት፣ ደዌን ሲፈውሱና ተዓምራትን ሲሰሩ የቆዩበትና አሁንም የሚሰሩበት ጥንታዊ ገዳም መሆኑን፣ የገዳሙ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ገቢረ ተዓምር የሚሰራበት ታሪካዊ ገዳም፣ ትልቅ ችግር እንደተጋረጠበት መነኮሳቱ ተናግረዋል፡፡
“ለፈውስና ለድህነት ከመላው አገሪቱ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ምዕመናን ድህነትና ፈውስ ካገኙ በኋላ፣ ገዳሙን ተጠግተው ቤት በመሥራት እዚያው እየኖሩ፣ ገዳሙ ይዞታውን እየተነጠቀ ከመጣበቡም በላይ፣ የገዳሙን ቅድስና የሚያረክሱ ተግባራት እየተፈጸመበት ይገኛል፡፡” ይላል፤ የኮሚቴው መግለጫ፡፡
የገዳሙ መነኮሳት የታሪክ ዶሴና ማስረጃ ላይ ተንተርሰው እንደሚናገሩት፤ ዓጼ ዮሐንስ በነቀርሳ ተይዘው በአቡነ ሐራ ድንግል ጸበል በመዳናቸው ነበር ለገዳሙ የአንድ ሰዓት የእግር መንገድ ያህል ስፋት ያለው ቦታ ለገዳሙ የሰጡት፡፡ ደርግ ሥልጣን ሲይዝ በገዳሙ 800 የሚደርሱ መናንያን እንደነበሩ የሚያስታውሱት መነኮሳቱ፤ በወቅቱ “መሬት ላራሹ” የሚል አዋጅ በመታወጁ የገዳሙን ይዞታ አርሶ አደሮች እየተቆጣጠሩት እንደመጡና መናንያኑ ገዳሙን ጥለው መኮብለላቸውን ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ይዞታ ላይ ከ250 በላይ አባወራዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የሚገልጹት መነኮሳቱ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ለመንግሥት በተደጋጋሚ አቤቱታ ካቀረቡ በኋላ፣ መንግሥት ነዋሪዎቹን አንስቶ ሌላ ቦታ ለማስፈር ፈቃደኛ ቢሆንም፣ ለነዋሪዎች ካሣ ለመክፈል በጀት እንደሌለው በመግለጽ፣ ገዳሙ ካሣውን እንዲከፍል መወሰኑን ይናገራሉ፡፡
ሆኖም የሚከፈለው ካሣ ከገዳሙ አቅም በላይ በመሆኑ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል የሚለው የገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም የገቢ ማሰባሰቢያ ኮሚቴ፤ ባለፈው ሐሙስ በጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ፣ ስለ ገዳሙ አሁናዊ ሁኔታና ስለ ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተነገረው፣ የአማራ ክልል ካቢኔ ለገዳሙ ሁሉንም ይዞታውን ባይሆንም 60 ሄክታር የሚደርስ ቦታ እንዲመለስለት የወሰነ ሲሆን፤ ገዳሙ በበኩሉ ለአርሶ አደሮቹ የሚገባቸውን የመሬት ካሣ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ ይህን የመሬት ካሣ ለመክፈልና ለገዳሙ የማስፋፊያ ልማት ለማከናወን፣ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም በካፒታል ሆቴል፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት፣ ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ 6 ሰዓት የሚቆይ ዓለማቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እንደሚያካሂድ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡ ለአርሶ አደሮቹ የመሬት ካሣውን ለመክፈልና የገዳሙ ይዞታ ከተለቀቀ በኋላ በሥፍራው ለሚከናወኑ ልማቶች በአጠቃላይ 100 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው የገለጸው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተክርስትያን ልጆችና የጻድቁ አቡነ ሐራ ወዳጆች በዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ በንቃትና በትጋት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ የሚገኙ መናንያን ቁጥር 5ሺ እንደሚደርሱና በጾም ወቅት የጸበልተኛው ቁጥር ከ50 ሺ በላይ መሆኑን የጠቆመው የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴው፤ እኒህን ሁሉ በአግባቡ የሚያስተናግድ በቂ መጠለያና የልማት ሥራዎች ማከናወን አስፈላጊ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግሯል፡፡
"ስብሐቲዝም የሀሳብ ውይይት" እሁድ ይካሄዳል
ስብሐቲዝም የሀሳብ ውይይት የፊታችን እሁድ ሚያዝያ 20 2016 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቤተመዛግብት እና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት(ወመዘክር) አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።
የሕላዌ እንቆቅልሽ " የተሰኘ መጽሐፍ ነገ ይመረቃል
"የሕላዌ እንቆቅልሽ " የተሰኘ መጽሐፍ ነገ ይመረቃል
የደራሲ ማንደፍሮ ማሩ "የሕላዌ እንቆቅልሽ" የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ቅዳሜ ሚያዝያ 19 2016 ዓ.ም ከቀኑ 10:00 ጀምሮ በወመዘክር አዳራሽ ይመረቃል።
"ፋሽን" መጽሐፍ ቅዳሜ ይመረቃል
በደራሲ ባየህ ንጉሴ የተዘጋጀው “ፋሽን” የተሰኘ በፋሽን እና ሞዴሊንግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ መጽሐፍ ቅዳሜ ሚያዝያ 19/2016 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር) አዳራሽ ጥሪ የተደረገላቸው
የጥበብ ቤተሰቦች እና እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል ይመረቃል።በስድስት ምዕራፍ የተከፈለው መጽሐፉ ስለ ሞዴሊንግ አይነቶች፣ ሞዴል የመሆን ትሩፋቶች እና ተግዳሮቶች፣ የቁንጅና ውድድር፣ ሻምፖ እና ኮድሽነር አመራረጥ፣ ፖርትፎሊዮና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል።
ዘመን ባንክ የሠራተኞቹን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ከሊንክድኢን ለርኒንግ ጋር የአጋርነት ስምምነት ፈጸመ
ዘመን ባንክ የሠራተኞቹን ዕውቀትና ክህሎት ለማሳደግ፣ በዓለም ትልቁ የኢንተርኔት የመማሪያ መድረክ ከሆነው ሊንክድኢን ሊርኒንግ ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
የዘመን ባንክ የሰው ሀብት ምክትል ዋና ኦፊሰር አቶ ታከለ ዲበኩሉ ስለ ስምምነቱ ሲገልጹ፤ “ዘመን ባንክ ለሰራተኞቹ ቀጣይነት ያለው የመማርና የሙያ እድገት ባህልን ለማሳደግ ቁርጠኛ ነው። ከሊንክድኢን ለርኒንግ ጋር ያደረግነው ስምምነት፣ ይህንን ቁርጠኝነት የሚያጎላ ከመሆኑም በላይ ሠራተኞቻችን በፋይናንስ ዘርፉ የሚጠይቀውን ችሎታ፣ እውቀትና ክህሎት እንዲያሳድጉ የሚረዳ ነው፡፡" ብለዋል፡፡
የሊንክድኢን ታለንት ሶሉዩሽን ዋና ኃላፊ ማቲው ግሬይ በበኩላቸው፤ ”ከዘመን ባንክ ጋር ያደረግነው ስምምነት የሰራተኞቹን የክህሎትና የእውቀት ክፍተቶችን ለማሟላት እድሉን የሚሰጠን ከመሆኑም በላይ ሊንክድኢን ለርኒንግ በአፍሪካ ተመራጭ የክህሎት ልማት መድረክ ሆኖ መቀጠሉን ስለሚያሳይ እጅግ ተደስተናል። የዘመን ባንክ የሰው ሃብት ስትራቴጂ በቀጣይ አመታት ይበልጥ እንዲጎለብትና ውጤታማ እንዲሆን አብረን እንሰራለን።" ብለዋል፡፡
የእነዚህ ኮርሶች ወጪ ሙሉ በሙሉ በዘመን ባንክ የተሸፈነ ሲሆን፤ የባንኩ ሠራተኞች ሥልጠናውን በነፃ እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡