
Administrator
በአልባኒያ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ጋናዊው አጥቂ በጨዋታ መሐል ሕይወቱ አለፈ
ኢትዮጵያን ያመለጣት ዕድል!
ኮሎኔል መንገሻ ወልደ ሚካኤል (8) ከአባቴ ጋር አንድ ኮርስ ሲሆኑ ያገኘኋቸውም አዲስ አበባ ነበር። አባቴ የልዩ ኃይሉ አዛዥ ሆኖ ድሬደዋ የሚሠራበት ወቅት እሳቸው እዚያው ከተማ የመድፈኛ ጦር የትምህርት መኮንን ሆነው ለአንድ ዓመት ቆይተዋል። በወቅቱም ከአባቴ ጋር ብዙ ተቀራርበው እንደነበር ቃለ-ምልልስ ስናደርግ አጫውተውኛል። ከዚያ ወዲያም በደብዳቤ ያስታወሱትን ሁሉ ጽፈው ልከውልኛል። ድሬደዋ በእረፍታቸው ወቅት በአባቴ ላንድሮቨር ሆነው አብረው ይዝናኑ እንደነበር ነግረውኛል።
“በዚያ ወቅት አባትሽ ጂቡቲ ገና ነፃ ሳትሆን ሀረር፣ ጅጅጋና ኦጋዴን በመሯሯጥ እጅግ ይባክን ነበር። አንዳንዴ በጣም በጠዋት ቀድሞ ይነሳና ከተባሉት ሥፍራዎች ሲዞር ውሎ ማታ ይገባል። የተሰጠውን ግዳጅ ለመፈጸም ሁሌ እንደተሯሯጠ ነበር።” ኮሎኔል መንገሻ ወልደሚካኤል።
ኮሎኔል መንገሻ ወልደሚካኤል አባቴን ሲያነሱ “ውድ ወንድሜ ጀግናው ዳግማዊ ቴዎድሮስ” በማለት ነው በደብዳቤአቸውም ሆነ በቃላቸው የሚጠቅሱት። በተለምዶ አብሮ ትምህርት የጨረሰ ሰው ይናናቃል-ይባላል። እሳቸው ግን በጣም የጠራ ቅንነት ቢኖራቸው ነው እንዲህ ማለታቸው። ክፋቱ ግን ከአባቴ ጋር ምንም አብረው አልሠሩምና ስለ አባቴ የሚያቁት ነገር በጣም የተወሰነ መሆኑ ላይ ነበር።
አባቴን ከጂቡቲ ጉዳይ ጋር በማያያዝ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሱልኝ ሰው ግን እሳቸው ነበሩ። አባቴ ጂቡቲን በተመለከተ “በመሯሯጥ እጅግ ይባክን” የነበረው ምን እያደረገ እንደሆነ ግን ፈጽሞ አያውቁም። ምን ዓይነት ተግባር እንደፈጸመ ማወቅ አልቻሉም። በጠዋት ተነስቶ ማታ መግባቱን ግን አስተውለዋል። አብረው እየዞሩ እየጠጡና እየተዝናኑም አላጫወታቸውም። ከባድ ሚስጥር እንደነበር ግልጽ ነው። እናም አልተወው ነገር አክብደው ነው የገለጹት። እናኔም ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ለመቀላቀል እንድትችል ይደረግ ከነበረው የፖለቲካ፣ የፕሮፓጋንዳ እና የውጭ ጉዳይ የዲፕሎማሲ ጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ጽሁፎችንም በሄሊኮፕተሮች ይበትኑ እንደነበር ሰምቻለሁ። ለዚሁ ተግባር ይሆናል አባቴ ሲሯሯጥ የነበረው ብዬ ገመትኩ።
ይህንን እንደዚህ ደምድሜ ካለፍኩ ወዲያ ብዙ ቆይቶ በሌላ ቃለ-ምልልስ ካልጠበኩትና ከጉዳዬም ጋር ግንኙነት ይኖረዋል ብዬ ካልገመትኩት ሰው ፍንጩን የሚያብራራ አቢይ ነጥብ አገኘሁ። የመደምደሚያ ግምቴም ብዙም ከእውነቱ አለመራቁን አረጋገጥኩ። አንዳንዴ ሰዎች የሚሰጡት ትንሽ ፍንጭ ከሌላ ሰዎች መረጃ ጋር ሲዋሃድና ሲጣመር ይጎላና ይገዝፋል።
አቶ እጅጉ ደሴ (40) በኢትዮጵያ የአየር መንገድ አስተዳደር ውስጥ አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ሆነው ያገለገሉ ናቸው። ስለበረራ ድህንነቱ የአባቴ አገልግሎት- ስናደርግ በአጋጣሚ የጅቡቲውን ነገር አነሱብኝ። አባቴ አየር መንገዱን ከለቀቀ ወዲህ አንዴ እራት ጋብዘውት እቤታቸው ይወስዱታል። በእራቱ ግብዣ ላይ ሲጨዋወቱ በአጋጣሚ የጅቡቲው ነገር ተነሳ። ጅቡቲ ከላይ እንዳሰፈርኩት ተጠቃላ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት የሆነችው እ.ኤ.አ በ1888 ዓ.ም ላይ ነበር። ፈረንሳይ በጀነራል ቻርለስ ደጎል እየተመራች በነበረበት ወቅት፤ እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም ላይ፤ የጅቡቲ ህዝብ አንድ የብያኔ ህዝብ እድል አገኘ። ቀደም ሲልም ሌላ እድል ተሰጥቶት ከፈረንሳይ ጋር ለመቆየት መርጦ ነበር። ይህን ጊዜ ግን ጄኔራል ደጎል ከጃንሆይ ጋር ጥሩ ቅርበትና መልካም ግንኙነት ነበራቸውና ከብያኔ ህዝቡ ወደ ፈረንሳይ ጅቡቲን በምትለቅበት እለት ኢትዮጵያ በምትኩ ብትገባ ምንም እንደማይቃወሙና እርምጃም እንደማይወስዱ አረጋግጠውላቸው ነበር።
ጂቡቲ የአፋርና የኢሳ ብሔር ህዝቦች ይኖሩባታል። ኢትዮጵያ በአፋሮቹ ከኢትዮጵያ መቀላቀል መፈለግ ስታምን፣ ሱማሊያ ደግሞ በኢሳዎቹ ከሶማሊያ መቀላቀል ታምናለች። ለጅቡቲ ህዝብ ድምጽ አሰጣጥም ኢትዮጵያና ሶማሊያ የራሳቸውን ቅድመ ቅስቀሳና ጥረት አድርገዋል። ሱማሊያ ከቅስቀሳው ባሻገር የእራሷን ሰው ለምርጫ ወደ ጁቡቱ ሱማሌያ ስታግዝ፣ ኢትዮጵያ ከፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ውጭ አልዘለቀችም ነበር። ውጤቱ ደግሞ ለሁለቱም አልሆነም፤ የጅቡቲ ህዝብ በፈረንሳይ እጅ ሆኖ ወደ ነጻነት ለማምራት በድምጹ ወሰነ።በወቅቱ ጃንሆይ የደጎልን የይግቡ አረንጓዴ መብራት እንዳገኙ የ3ኛ ክፍለ ጦርና የክብር ዘበና ጦርን ከጅቡቲ ድንበር በተጠንቀቅ አሰፈሩ። አባቴ በድንበሩ ተጠንቀቅ ላይም ከ3ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ከጄ/ል አበበ ገመዳ ጋር አብሮ ነበር። ይህንን ነበር አይቶ እጅጉ ደምሴን ያጫወታቸው።
በቦታው ሆነው የጃንሆይን “የወደፊት ቀጥሎ” ትዕዛዝ ሲጠባበቁ ከሌሊቱ 6፡00 ሰዓት ገደማ ላይ እራሳቸው ጃንሆይ በስልክ/ሬዲዮ ጄኔራሉን አስቀርበው፣ “አበበ አትግባ!” አሏቸው። ጄነራሉ ስልኩን ሰምተው ስቅስቅ እንዳሉ ገልጾ፤ “ሁለተኛ ኢትዮጵያ እንደዚህ አይነት እድል አያጋጥምሽም! ደጎል እኮ እኛ ስንወጣ እናንተ ግቡ ብሏል!” ብሎ በምሬትና ቁጭት አባቴ እንዳጫወታቸው አቶ እጅጉ ደምሴ ገለጹልኝ።
ጃንሆይ ለምን አትግባ አሉ? ለሚለው ጥያቄም አቶ እጅጉ ደምሴም መልሱን በደንብ ደርሰውበታል። ቀደም ሲል አልጀሪያና ሞሮኮ ተጋጭተው ሊዋጉ ጦራቸውን በየድንበራቸው በማዘጋጀት ላይ እያሉ በአጋጣሚ ጃንሆይ በወቅቱ በይይቤሪያ በጉብኝት ላይ ሆነው ሁኔታውን አወቁ። ከዚያ አልጀርስና ካዛብላንካ ተመላልሰው መሪዎችን አነጋግረው፣ የሁለቱንም ጦር ከድንበራቸው እንዲያፈገፍጉ በማድረግ ጦርነቱን አስቀሩት። ሱዳንንም ከተቃዋሚ ቡድን ጋር አስታርቀው ነበር።
ስለዚህም ጃንሆይ “የሰላም የኖቤል ሽልማት” ያገኛሉ ተብሎ በተስፋ ላይ ነበሩ። በዚያ ወቅት ጅቡቲን ከወረሩ ያ የኖቤል ሽልማት እድል መቅረቱም ሆነ ለዚህ ነው ጦሩን እንዲመለስ ያደረጉት። ሻምበል ጌታቸው ወ/ማርያም የክብር ዘበኛ ጦር፣ ያኔ ድንበሩ ድረስ መሄዱንና የጃንሆይን የኖቤል ሽልማት ጉዳይ ትክክለኝነት ማወቃቸውን በደንብ አረጋግጠውልኛል። ዶ/ር ሰለሞን አበበ (41) ደግሞ የኖቬል ሽልማትን ጉዳይ እንደ አንድ ምክንያት ተቀብለው በተጨማሪም ጃንሆይን ከጅቡቲ ህዝብ መሃል በፈረንሳይ ደሞዝተኝነት የሚተዳደረው ብዙ ነበርና ያንን ማስተዳደሩና ደመወዝ መክፈሉን ፈርተው የውሃና የመብራት ችግሩን ብቻ እንኳን ምን ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ አውቀውና መክረው ያደረጉት ነው ብለው ያምናሉ። ጦሩ ድንበር ላይ በተጠንቀቅ መቆሙን በተመለከተም እሳቸው በወቅቱ ሀረር ክፍለ ሀገር የልማት አስተዳዳሪ ሆነው ይሰሩ ስለነበር በደንብ ማወቃቸውን አረጋግጠውልኛል።
ዶ/ር ሰለሞን የተወለዱትና ያደጉት ሀገር ሲሆን በተለያዩ ክፍለ ሀገራት በአስተዳደርና ልማት ስራ አገልግለው ከዚያም በተመድ የስደተኛ አስተዳዳሪነት በየሀገሩ ተዘዋውረው አሁን ዳላስ ቴክሳስ ውስጥ በጡረታ ይኖራሉ። በዚህ በዳለስ ከተማ ባለው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ በአባትነት መካሪ፣ አስተባሪና አስታራቂ በማገልገል ተወዳጅነት አላቸው።
በሌላ ምዕራፍ ላይ የጠቀስኳቸው ኮሎኔል ዘሩ እጅጉ (921) ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በስራ አባቴን የተገናኙት ድሬዳዋ ሆኖ ነበር። እሳቸው በዚህም ወቅት በመረጃ ሥራው ላይ ነበሩ። ድሬዳዋ አየር ኃይል ማሠልጠኛ ሲቋቋም እሳቸውም በሙያቸው መምጣታቸውን ያስታውሳሉ። የፕሮፓጋንዳ ሥራውን በተመለከተ በጣም የቀረበና የበለጠ ትዝታ አላቸው። በዚህ ወቅት አባቴ የሚመራው ልዩ ኃይል የሱማሌን መንግስት ለማናወጥ ብዙ የፕሮፓጋንዳና ቅስቀሳ ሥራን መስራቱን በደንብ ያስታውሳሉ። ጽሁፎችን በአየር ላይ ሆነው ለመበተን አባቴና አባባሎቹ እስከ በረራ ድረስ ጠልቀው ይገቡ እንደነበር ገልጸው፤ አባቴ ጦሩን ይዞ ሲንቀሳቀስ እሳቸው መረጃ በመስጠት የጠበቀ የስራ ግንኙነት ትብብር እንደነበራቸውና እሳቸው እራሳቸውም በሙያቸው የተካፈሉበት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ አረጋግጠውልኛል።
ሙዙን ስታይ፤ መዘዙንም እይ!
ከእለታት አንድ ቀን፣ አያ ዝንጀሮ፣ የአንበሳን ሚስት ሊያሽኮረምም አስቦ አንበሳ በሌለበት ወደ ሚስትየው ይሄዳል፡፡ የአንበሳ ሚስት የዝንጀሮን መላ ሰውነት ቃኝታ ስታበቃ፣
“አያ ዝንጀሮ፤ አይንህ ለምን ቀላ?” ብላ ትጠይቃለች፣ አይኑን አተኩራ እያየች፡፡
ዝንጀሮም፤
“የዐይኔ መቅላትማ የጀግንነት ምልክት ነው” ይላታል፡፡
ቀጥላ ወደ እጁና ወደ እግር ጥፍሩ እያስተዋለች፤
“ጥፍርህስ እንዲህ ረዝሞ ለምን አደገ?” ትለዋለች፡፡
“ፍሬ ለመፈልፈል እንዲረዳኝ ብዬ ያሳደግሁት ነው፡፡ እኔ‘ኮ ምንም ነገር ያለ አንዳች ብልሃት አልሰራም!”
የአንበሳ ሚስት ከፊቷ የሚጎማለለውን ዝንጀሮ ዘወር ዘወር ብላ ተመለከተችና፤
“መቀመጫህስ በምን ምክንያት ተመለጠ?” ብላ ጠየቀችው፡፡
“እሱ ዓለም የሚያውቀው ነገር እኮ ነው፡፡ መቀመጫዬ የተመለጠው ህይወቴ በጦር ሜዳ ውሎና በጀብድ የተሞላ እንደመሆኑ፤ ከፈረስ ፈረስ ስዘል ነው” አለና መለሰላት፡፡
በመጨረሻም፤
“ይገርማል አያ ዝንጀሮ፤ ዛሬ ከቁመትህ ሁሉ በጣም የገረመኝ ደግሞ የጎፈርህ መንዠርገግ ነው፡፡ የአንበሳን ጎፈር መሰለኮ”
“ይሄማ ጠላትን መከላከያ ነው፡፡ ከሩቅ ግርማ - ሞገሴን እያየ የዱር አውሬው ሁሉ የሚሸሸኝ እኮ በዚህ በጎፈሬዬ ምክንያት ነው!”
አያ ዝንጀሮ እንዲህ እየፎከረ የአንበሳን ሚስት ሲያማልል ሲጎማለል፤ ድንገት አያ አንበሶ ከተፍ አለ፡፡ ከዚያም ጥያቄ ይጠይቀው ጀመር፤
“አያ ዝንጀሮ፤ ምነው ዐይንህ ቀላ?”
ዝንጀሮ ድምፁ ሁሉ ኮሰመነና ልቡ ከዳው፡፡
“ዐይኔ የቀላው በድህነት ምክንያት ነው” አለ፡፡
አንበሳ ቀጠለና፤
“ጥፍርህስ ለምን አደገ?”
“መሬት የምቧጥጥበት ነው ጌታዬ!”
“መቀመጫህን ደሞ ምን መለጠው?”
“ከተራራ ተራራ የምንፏቀቅበት ነው!”
“ፀጉርህንስ ምን እንዲህ አንጨፈረረው?”
“ለብርድ፤ ለብርድ ነው ያሳደግሁት ጌታ አንበሶ!”
አንበሳም ክፉኛ እየተኩራራ፤
“ሂድ ጥፋ ከዚህ! አስኮናኝ!” አለው፡፡
ዝንጀሮ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡
አንበሳም ወደ አንበሲት ዞሮ፤
“አንቺም ሁለተኛ ከእንደዚህ ያለ ተልካሻ ቡክን ጋር እየዋልሽ አታዋርጂኝ!” አላት፡፡
***
“እዩኝ እዩኝ ያለች ደብቁኝ ደብቁኝ ትላለች” ነው ነገሩ፡፡ ያልሆነውን ነን ማለትን የመሰለ ክፉ በሽታ የለም፡፡ ለአንዴና ለዛሬ ብቻ ያልሆነውን ነን በማለት ለማጭበርበር እንችል ይሆናል፡፡ ነገ ግን ማንነታችን ይጋለጣል፡፡
“ጓሣና ድንግል አላንድ ጊዜ አይበቅል” የሚለውን ተረት አለመርሳት ነው፡፡ ለታይታ የምናደርገው ሁሉ የአፍታ ስም ብቻ ነው የሚተርፈን፡፡ በሆይሆይታና በግርግር የምንፈጥረው ማናቸውም ትልቅነት በቀላሉ እንደሚናድ ካብ ነው፡፡ በትህትናና በሥርዓት የተሰራ ነገር ሁሉ ግን ፍሬያማ ይሆናል፡፡
ልባምነት ጽናትና ጥንካሬ ያለው፣ እርጋታ ውስጥ እንጂ ችኩልነት ውስጥ አይደለም፡፡ ችኩል ጅብ ቀንድ ይነክሳል ይሏልና፡፡
“አደባባይ ሲበዛ የክት ልብስ ይጠፋል” የሚለውን አነጋገር መቼም ቢሆን አለመዘንጋት ነው፡፡ ብዙ ጉራ በመንዛትና አደባባይ በመታየት ውስጥ ብዙ ስህተቶችን እናፈራለን እንጂ ደርዛችን እፍኝ ታህል አትሆንም፡፡
“የማትሰግር በቅሎ ጌጧ ይበዛ” ነውና መመሪያ ብናበዛ፣ ገለፃ ብናዘወትር፣ ያላንዳች አማራጭ አዲስ ሀሳብ፤ ያንኑ ያንኑ ዲስኩር ደጋግመን ብንደሰኩር፣ ራሳችንን ከማድመጥ በቀር ወደፊት አንራመድም፡፡የሀገር ጉዳይ ሁሌም ረዥም መንገድ ነው፡፡ ብዙዎች የሀገር ችግሮች አቋራጭ የላቸውም፡፡ መሳለጫ መንገድም የላቸውም።
አጫጭር አቋራጮችን ስንፈልግ መቸኮል ይመጣል፡፡ ሥረ-ነገሩን ትተን ላይ ላዩን ብቻ መነካካት ይበዛል፡፡ ሥር የሰደደ፣ “ለዘር ለቀለብ ይበቃል” የሚል ነገር ይጠፋል፡፡ በጭብጥ እህል ጠብ መጫር ይበዛል፡፡ “ስንቃችሁ ግማሽ ቁና፤ ነገራችሁ አህያ እማይችለው” የሚባልበት ወቅት ይሆናል፡፡
“የአዕምሮህ ዛጎሉ ውጪ ፀሐይ የሚሞቅ ከሆነ፣ ከውስጥም ዕንቁው አለመኖሩ ይታወቃል” እንዲሉ፤ ውዱንና ትልቅ ዋጋ ያለውን ቅርስ አለማርከስ ተገቢ ነው፡፡ በምናደርገው ነገር ውስጥ ሁሉ መላ፤ ጥበብና ስልት ካልታከለበት ፍሬያማ አይሆንም፡፡
ስለ ፖለቲካ ሸንጎ የሚያውቁ ፀሐፍት እንዲህ ይመክራሉ፡-
“ስለ ማሸነፍህና ድልህም ቢሆን ብዙ ጥሩምባ ከመንፋት ተቆጠብ፡፡ ስለ ራስህ በምትናገረው ሁሉ ቁጥብና ትህትናን የተላበሰ ሁን፡፡ ብዙ የምትሰራና እድገቱ ሁሉ የኔ ነው የምትል አትሁን፡፡ ማር ሲበዛ ይመራልን አትርሳ፡፡ ለተገቢው ነገር ብቻ ትኩረትን ሳብ፡፡
በተለመደና በአሰልቺ ልሳንና ዲስኩር አትናገር፡፡ ልሳንህ ሁኔታዎችን የሚገዛ መሆን አለበት፡፡ የመጥፎ ዜና ተሸካሚ ላለመሆን መጣር አለብህ፡፡ ከመናገርህ በፊት ሁለት ሶስቴ አስብ ይሏል፡፡
ህዝብን አለመናቅ የጥበብ መጀመሪያ ነው፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎች የነገ ቂም እርሾ ናቸው፡፡ ለሚሰሩ ሰዎች ምስጋናና ሽልማትን አትንሳ፡፡ የሰዎችን ሽልማትም በግፍ አትውሰድ፡፡ የበታቾችን ማንጓጠጥ የመሪዎች ታላቅ ህፀጽ ነው፡፡ የፈጠራዎች ሁሉ እናት መስተዋት ነው፡፡
ሌሎች እንደሚያዩን አድርጎ ራሳችንን ያሳየናልና፡፡ ራሳችንን የምናይበት መስታወት ከእጃችን መለየት የለብትም፡፡ ስሜቱን የማይቆጣጠር መሪ ለአደጋ የተጋለጠ ነው፡፡ መንፈሱን ከጊዜው ጋር ካላጣጣመም የመምራት መላው ሰንካላ ይሆናል፡፡ ማንኛውም መሪ ነገን የሚያስብ ጭንቅላት ሊኖረው ይገባል፡፡
ራሳችንን ለሌሎች የደስታ ምንጭ ለማድረግ መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ወዝና ለዛ ያለው መሆን አለብን፡፡
ዣን ዴ ላብሩዩር የተባለ ፀሀፊ፤ “የፖለቲካ ሸንጎን የሚያውቅ ገጽና መልኩን (gesture) ለመቆጣጠር የሚችል፤ አይኑን መግራት የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ብቁና የማይደፈር፤ ከቶም የማይገሰስ ነው፡፡
መጥፎ ምግባራትን ማሟሸሽ፣ ለጠላቶቹ ፈገግ ማለት፤ ቁጣውን ማለዘብ፣ ስሜቱን መሸፈን፣ የልቡን በልቡ መያዝና አንዳንዴ የማይፈልገውን ከስሜቴም ውጪ ለመናገር መገደድን የሚችል ሰው ነው” ይለናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ሳይገነዘብ የሚጓዝ፣ “ሙዙን ስታይ፣ መዘዙንም እይ!” የሚለውን ምሳሌያዊ አነጋገር የዘነጋ ነው!
አይቲ ፓርክ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ
ቋሙ በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑ ተጠቁሟል
በአፍሪካ የአይቲ ማዕከል ለመሆን ራዕይ ሰንቆ በአዲስ መልክ እየተዋቀረና እየተደራጀ መሆኑ የተነገረለት የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡ በአይቲ ፓርኩ፣ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የግል የዳታ ማዕከል አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ተጠቁሟል፡፡
ይህ ይፋ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ጠዋት በሸራተን አዲስ ሆቴል፣ “የዳታ ማዕከል አገልግሎት ሥነምህዳር ዕድሎችን ለፋይናንስ ዘርፉና ለቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው ማመቻቸት” በሚል ርዕስ፣ ለግማሽ ቀን በተካሄደ ጉባኤ ላይ ሲሆን፤ ጉባኤውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽንና የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል በትብብር እንዳዘጋጁት ታውቋል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽኑን የሚያስተዳድረው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር እውን በማድረግ ረገድ አይቲ ፓርኩ ጉልህ ሚና የሚጫወት ይሆናል፡፡ ከዚህ አንጻር ጉባኤው ወቅታዊና ተገቢ መሆኑን ሚኒስትሩ አስምረውበታል፡፡
የአይቲ ፓርክ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ አህመድ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፣ የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ዓላማው ቢዝነስ መሥራት የሚያስችል ሥነምህዳር መፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ሁሉም በጋራ የሚጠቀምበት ሪሶርስ በአንድ ቦታ ያቀርባል ብለዋል፡፡
ራዕያችን የአፍሪካ የአይቲ ማዕከል መሆን ነው ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህን ለማሳካትም የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማምጣትና አቅምን በማሳደግ ዓለማቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ጉባኤ ላይ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የግል የዳታ ማዕከል፣ በአይቲ ፓርክ ገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የጠቆመው ዊንጉ አፍሪካ የዳታ ማዕከል ኩባንያ፤ በምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊላንድና ታንዛንያን ጨምሮ በአራት አገራት በዘርፉ አስተማማኝ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ስመ-ጥር ኩባንያ ነው ተብሏል፡፡
ኩባንያቸው በቀጣናው ተጠቃሽ የዳታ ማዕከል አገልግሎት አቅራቢ መሆኑን የገለጹት የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ተሾመ፤ በኢትዮጵያም ዓለማቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አስተማማኝ የዳታ ማዕከል መገንባቱን ጠቁመው፤ በዋናነት የፋይናንስ ዘርፉና የቴክኖሎጂ ተቋማት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡ዊንጉ አፍሪካ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ሥራ ከጀመረ 18 ወራት ማስቆጠሩን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ የዚህ ጉባኤ አንዱ ዓላማ እነዚህ የፋይናንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ከፍተኛ ወጪ አውጥተው፣ የየራሳቸውን የዳታ ማዕከል ከመገንባት ይልቅ በኛ ማዕከል ቢጠቀሙ፣ የበለጠ እንደሚያዋጣቸው መረጃና ግንዛቤ ለመስጠት ነው ብለዋል፡፡ ጉባኤው አጋርነትና ትብብር የመፍጠሪያ መድረክ እንደሚሆንም ጨምረው አመልክተዋል፡፡
የዳታ ማዕከሉን ከሚመሩት ውስጥ 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን መሆናቸው የገለጹት የኩባንያው አመራሮች፤ ማዕከሉ ለወጣት ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ኢንጂነሮች ትልቅ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አውስተዋል፡፡የዘርፉ ዓለማቀፍ ተዋናዮች በአጋርነት አብረውን እንዲሰሩ መሳብ ችለናል ያሉት አመራሮቹ፤ የመንግሥት ደንብና መመሪያዎች ወጥተው እንደተጠናቀቁ እኒህ ተዋናዮች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ ማይክሮሶፍት፣ ቲክቶክና ሜታ (የቀድሞው ፌስቡክ) የመሳሰሉ ግዙፍ ዓለማቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ወደዚህ አገር እንዲመጡም እየሰራን ነው ብለዋል - የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል ኩባንያ አመራሮች፡፡ የዊንጉ አፍሪካ ዳታ ማዕከል፣ በ50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ መገንባቱ ይታወቃል፡፡በዚህ ለግማሽ ቀን በሸራተን አዲስ በተካሄደው ጉባኤ ላይ፣ የአይቲ ኢንዱስትሪው መሪዎች፣ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የፋይናንስ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡
በህጋዊ ሽፋን የሚገባው የኮንትሮባንድ ምርት በህጋዊ አምራችና ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ የህልውና አደጋ መፍጠሩ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኩል በህጋዊ ሽፋን ያለ በቂ ቀረጥ እየገባ ያለ ኮንትሮባንድ ምርት መበራከቱ በአገር ውስጥ አምራቾች እና ህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው ተባለ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የድሬዳዋ ቅርንጫፍ በኩል ያለበቂ ቀረጥ ከፍተኛ የሆነ ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ ነው የሚሉት አምራቾች እና ነጋዴዎች ይህ ሁኔታ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረና ከስራቸው እያፈናቀለን ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ተደጋጋሚ አቤቱታ አሰምተናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች ችግሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲባባስ እንጂ ምንም የመርገብ ምልክት አልታየበትም ብለዋል፡፡
እንደመረጃ ምንጮች በተለይ ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ የግንባታ እቃዎች እና መሰል ሌሎች ሸቀጦች መዳረሻቸውን መሃል አገር አድርገው በድሬዳዋ ጉምሩክ በሚወጣ ዲክላራሲዎን ምንም በሚባል ቀረጥ እየገቡ በገበያ ውስጥም ከፍተኛ ጫና ፈጥረዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
ይህ ሁኔታ የአገር ውስጥ አምራች እና ህጋዊ ምርት አስገቢዎችን ብቻ ሳይሆን አገሪቷ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን በቢሊዎን ብሮች የሚቆጠር የመንግስት የቀረጥ ገቢም እንድታጣ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ነው ያከሉት፡፡
በማሳያነት የቆርቆሮ እና አርማታ ብረት ህገወጥ እንቅስቃሴን የሚጠቅሱት ቅሬታ አቅራቢዎች የጉምሩክ ኮሚሽን ከሰሞኑ ከኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎች ማህበር አመራሮች ጋር ስለችግሩ መምከሩን መግለጹ የችግሩን መኖር አመላካች ነው ብለዋል፡፡
ምንም እንኳን ኮሚሽኑ ስለጉዳዩ መወያየቱን ቢገልፅ የችግሩን መኖር በይፋ አላመነም ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎች በጥቅሉ ያሉ ችግሮችን እፈታለው ብሎ መግለጹ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በማህበራዊ ገጹ ስለውይይቱ ባጋራው መረጃ የኢትዮጵያ መሰረታዊ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎች ማህበር ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ፣ ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና ለዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ እያበረከተ የሚገኘው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ማለታቸውን ጠቅሶ ከጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የተደረገው ውይይትም እየገጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል ሲል አክሏል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙሌ አብዲሳ በበኩላቸው የሐገር ውስጥ የብረት አምራቾች የሚያነሱትን ጥያቄ ለመመለስ ኮሚሽኑ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡
እንደ ቅሬታ አቅራቢዎች ገለፃ ከፍተኛ የሆነ የብረት ምርት በፍራንኮ ቫሉታ እየገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህ እጅግ አነስተኛ ቀረጥ እየተከፈለበት የሚገባ ምርት ገበያውንም በማጥለቅለቅ የአገር ውስጥ አምራቾችን በእጅጉ እየጎዳና አንዳንዶቹም ስራ ለማቆም እንዲገደዱ እያደረገ ነው ተብሏል፡፡
አዲስ አድማስም የተለያዩ የጉምሩክ ሰነዶችን ማየት የቻለ ሲሆን፡፡ ሰነዶቹ የተለያዩ ግለሰቦች የተለያየ መጠን ያለው ብረት ከመደበኛው ማስቀረጫ መጠን እጅጉ ያነሰ ቀረጥ ተከፍሎባቸው የብረት ምርቱ እንደገባ ያሳያል፡፡
እስከ 300 ሺ ቶን ብረት በአንድ የጉምሩክ ሰነድ በአንድ ግለሰብ እንዲገባ መፈቀዱን የጠቀሱት የመረጃ ምንጮች፡፡ በተመሳሳይ 120 ሺ ቶን፣ 150 ቶን በሌላ ግለሰብ እንዱም ሌሎች በርካታ የብረት ጭነቶች በተለያዩ ግለሰቦች ስም በድሬዳዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ በኩል እንዲገቡ ይሁንታ ያገኙበት ሰነዶችምን በመረጃነት ቀርበዋል ።
ባለፉት ጥቂት ወራት የወጡት የጉምሩክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ግለሰቦቹ የከፈሉት የጉምሩክ ቀረጥ መጠንም በኪሎ ግራም ከ92 ሳንቲም፣ 74 ሳንቲም እና 50 ሳንቲም ብቻ መሆኑን የተረዳን ሲሆን፡፡በአንጻሩ በተመሳሳይ ወቅት በህጋዊ መልኩ የገባ ብረት በኪሎ ግራም 35 ብር አካባቢ እንደተከፈለባቸው ያገኘናቸው የጉምሩክ ሰነዶች ያሳያሉ፡፡ በመሆኑም በህጋዊ የጉምሩክ ሰነድ እጅግ ባነሰ የቀረጥ መጠን እየገቡ የሚገኙት ብረቶች የሁለት አስገቢዎች ብቻ ተሰልቶ እንኳን ለአገሪቱ መግባት የነበረበትን ከ 14 ቢሊየን ብር በላይ ያሳጣ ነው ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎች ያብራራሉ፡፡በጉዳዩ ከትናንት በስቲያ መግለጫ የሰጠው የመሰረታዊ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኢንዱ ስትሪዎች ማህበር ልዩ ልዩ የማጭበርበሪያ ዘዴ እና ህጋዊ ሽፋን በመጠቀም እየገባ የሚገኝ የተለያየ የብረት ምርት በአምራች ኢንደስትሪው ህልውና ላይ አደጋ ጋርጧል ሲል አስታውቋል፡፡
የማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ሙሉጌታ በመግለጫው እንደተናገሩት 76 የሚሆኑ የማህበሩ አባላት አርማት ብረት (Reienforcment bar)፥ ጋልቫናይዝድ ቆርቆሮ (Galvanized sheet)፥ ቱቦላሬና የበርና የመስኮት ዘንጎች( Tubular sections)፥ እንዲሁም ልዩ ልዩ የብረታብረት ኢንጂነሪንግ ምርት ውጤቶች ለመሰረተልማት የጀርባ አጥንት የሆኑ የኮንስትራክሽን ግብአቶችን እንደሚያስመጡ ገልጸዋል። አያይዘውም በአገራችን የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የብረት ማምረት አቅም 10 ሚሊዮን ቶን በአመት መድረሱንና በአንጻሩ ፍላጎት ደግሞ እስከ 2 ሚሊዮን ቶን በአመት እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።
ይህም ሆኖ ያለቀላቸው ምርቶች ከውጭ አገር በህጋዊ መንገድና ስርአትን ባልተከተል መንገድ የሚገቡ በመሆኑ በገበያው ላይ ኢ-ፍትሃዊ የንግድ ውድድር በመፍጠር ኢንዱስትሪዎች ላይ የህልውና አደጋ እንዲጋረጥባቸው እያደረጉ ይገኛል ሲሉ ነው ያከሉት።
እነዚህን ምርቶች የሚያመርቱ የአገር ውስጥ አምራቾችን ከገበያ ውጭ ሊያደርጉ የሚችሉ የኮንትሮባንድና ሌሎች ህግን ሽፋን አድርገው የሚፈፀሙ ህገ ወጥና ምንጫቸው ያልታወቁ ምርቶች ከማምረቻ ዋጋ በታች በሆነ ዋጋ የሚሸጡና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ገበያውን እየተቆጣጠሩት በመምጣታቸው በተለያዩ መድረኮች ድምፃችንን በማሰማትና ለሚመለከታቸው ሁሉ አቤቱታችንን በደብዳቤ ጭምር እያሳወቅን ቆይተናል ያሉት የማህበሩ ዋና ስራ አሰስኪያጅ።
በአሁኑ ወቅት ለቆርቆሮ ለቱቦላሬ ምርት የሚያገለግሉ የጥቅል ጥቁር ብረቶችና የአርማታ ብረት ምርቶች በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በስፋት እየታየ እንደሚገኝ መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ ሲሉ ነው ያከሉት።
ማህበራቸው የዘርፉን አጠቃላይ ሁኔታ የመቃኘትና የመከታተል ኃላፊነቱን በመወጣት ሂደት ላይ ሳለ በቀርቡ ለማመን የሚያስቸግሩ መረጃዎች እየደረሱት መሆኑን አቶ ሰለሞን ጠቅሰው፤ እነዚህ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በቢሊዮኖች የመንግስትን ገቢ ሊያስቀሩ የሚችሉና የአገር ውስጥ አምራቾችን ሙሉ ለሙሉ ሊያዘጉ የሚችሉ ችግሮች ሆነው አግኝተናቸዋል ብለዋል። በመሆኑም በዚህ መንገድ ፈፅሞ ሊታመን በማይችልና በየትኛውም ዓለም ሊኖር በማይችል ዋጋ የብረታ ብረት ምርቶች እንደተገዙ ተደርጎ የጉምሩክ ቀረጥ ለማስፈፀም ማቅረብ ምን ያህል የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚጎዳ የሚታወቅ ሲሆን በተለይ ደግሞ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሰው በማምረት ተግባር ላይ የተሰማሩትን የአገረ ውስጥ አንዱስትሪዎች አሽመድምዶ ከገበያ ውጭ ሊያደርጋቸው የሚችል ድርጊት እንደሚሆን ለማንም ግልፅ ነው ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ማሊን 2ለ0 አሸነፈች
ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ማሊን 2ለ0 አሸነፈች
የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ከሜዳዋ ውጪ ማሊን 2ለ0 አሸንፋለች።
የማሸነፊያ ጎሎቹንም ንግስት በቀለ በ57ኛው፣ እሙሽ ዳንኤል በ68ኛው ደቂቃ ለኢትዮጵያ አስቆጥረዋል።
የመልሱ ጨዋታ እሁድ ህዳር 9 በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ይደረጋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas
"የነገዋ ኢትዮጵያ በእናንተ ትልቅ ተስፋ አላት" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
በዛሬዉ እለት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንሰቲትዩት በመገኘት ለሁለት ወራት ስለሰዉሰራሽ አስተዉሎት ቴክኖሎጅ ምንነት እና ጠቀሜታ ስልጠና ተከታትለዉ የተመረቁ የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን ተመልክቻለሁ፡፡
ልጆቻችን የኢትዮጵያን ችግሮች በሰዉ ሰራሽ አስተዉሎት በመታገዝ ለመፍታት ቁልፍ የሆነዉን እዉቀት መገብየታቸዉ ተስፋ ሰጭ ነዉ፡፡
በልጆቹ አቅም በመገረም የሃገራችንን እድገት ለማረጋገጥ እንደሚችሉ ሙሉ እምነት አለኝ፡፡
ሉላ ገዙ፣ የሮያል ፎምና ፈርኒቸር ብራንድ አምባሳደር ሆነች
ሉላ ገዙ፣ የሮያል ፎምና ፈርኒቸር ብራንድ አምባሳደር ሆነች
የኢቢኤስ ፕሮግራም አቅራቢዋና የማስታወቂያ ባለሙያዋ ሉላ ገዙ፤ የሮያል ፎምና ፈርኒቸር ብራንድ አምባሳደር ሆና ተመረጠች፡፡
ሉላ ገዙ፤ ለቀጣዮቹ 4 ዓመታት የሮያል ፎምና ፈርኒቸር ብራንድ አምባሳደር ሆና ለመሥራት በዛሬው ዕለት ከሮያል ግሩፕ አመራሮች ጋር በይፋ ተፈራርማለች።
እስራኤል በሰሜናዊ ጋዛ በየቀኑ የአራት ሰዓታት የተኩስ አቁም ለማድረግ መስማማቷን አሜሪካ አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ ትክክለኛ እና በቀጣናው የሚፈለገውን መሻሻል ለማምጣት ሚናው ከፍተኛ ነው ሲሉ አወድሰዋል፡፡
የተሰኩስ አቁሙ በዋናነት በሥፍራው የሚገኙ ንጹሃን ዜጎችን ከአካባቢው እንዲሸሱ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ከዚህ ባለፈም በቦታው ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረሰ እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡
የእስራኤል ጦር ከዚህ በፊት በጋዛ ለሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ “ታክቲካል የተኩስ አቁም” እንደሚያደርግ ማስታወቁን ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል፡፡
የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎበኙ።
የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎበኙ።
መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ላደረጉ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች በጉባ ጉብኝታቸው፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።
ውሃው ተርባይኑን መትቶ ወደ ተፈጥሮአዊ ፍሰቱ የሚመለስና በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት የሚያመጣው ችግር እንደሌለ መመልከታቸውንም ወታደራዊ አታሼዎቹ በአስተያየታቸው ገልጸዋል።
ከዘጠና ሰባት መቶኛ በላይ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ባለፈ በከፍተኛ የሀይል እጥረት የምትታወቀውን አፍሪካ ልማት የሚያፋጥንና ለቀጠናዊም ሆነ አህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስር የራሱን በጎ ሚና የሚጫወት አቅም እንደሆነም ነው በጉብኝቱ የተገለጸው።
ኢትዮጵያ ገና በጥቅም ላይ ያልዋሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት እንዳላት የተናገሩት አስተያየት ሰጪ ወታደራዊ አታሼዎቹ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆና ግዙፉን የህዳሴ ግድብ እውን ማድረግ መቻሏ ሙሉ ለሙሉ የተሟላ ሰላም ካሰፈነች በፍጥነት ማደግ የምትችል ስለመሆኗም ነው የተናገሩት።
ጉብኝቱን ያመቻቸው የመከላከያ ውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ሲሆን ወደ ስልሳ የሚጠጉ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ግድቡን ጉብኝተዋል።
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas