Administrator

Administrator

   ተቀማጭነቱ በእስራኤል የሆነው ሹራት ሃዲን የተባለ የመብቶች ተሟጋች ቡድን በቅርቡ በፍልስጤም ከተከሰቱ የሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ በታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ ላይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ካሳ የሚጠይቅ ክስ መመስረቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
በሽብር ጥቃቶች የተገደሉ አሜሪካውያን ግለሰቦችን ቤተሰቦች በመወከል ክሱን የመሰረተው ቡድኑ፣ የማህበራዊ ድረገጹ የአሜሪካን የጸረ ሽብር አዋጅ በመጣስ ለሽብርተኞች የጥፋት መልዕክቶችን ማሰራጫ መንገድ ሆኖ አገልግሏል በሚል ፌስቡክን ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ማድረጉን ዘገባው ገልጧል፡፡
የመብት ተሟጋች ቡድኑ ሃማስን የመሳሰሉ ቡድኖች አዳዲስ አባላትን እንዲመለምሉ፣ ጽንፈኛ አመለካከቶቻቸውን እንዲያራምዱና ለሽብር ለሚያሰማሯቸው ታጣቂዎች መመሪያ እንዲያስተላልፉ ምቹ ዕድል ፈጥሯል በሚል ባለፈው ሰኞ በኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት በፌስቡክ ላይ ክሱን እንደመሰረተ ተነግሯል፡፡
ቡድኑ በመሰረተው ክስ ላይ የተጠቀሱት የሽብር ጥቃት ሰለቦች የሆኑ አምስት ቤተሰቦች ሁሉም አሜሪካውያን እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህም መካከል ባለፈው መጋቢት ወር ላይ እስራኤልን ሲጎበኝ በፍልስጤማውያን ጥቃት የተገደለው ቴለር ፎርስ የተባለው የ28 አመት አሜሪካዊ ቤተሰቦች እንደሚገኙበት አክሎ ገልጧል።

     አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር ማጥፋት ወንጀል የከሰስኳቸውንና የእስር ትዕዛዝ ያወጣሁባቸውን የሱዳኑ ፕሬዚዳንት አልበሽርን በቁጥጥር ስር አላዋሉም በሚል በጅቡቲና በኡጋንዳ መንግስታት ላይ ወቀሳ ማሰማቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት አልበሽር ባለፈው ግንቦት ወር ወደ ሁለቱ አገራት አምርተው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ፍርድ ቤቱም የአገራቱ መንግስታት ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ፕሬዚዳንቱን በቁጥጥር ስር አላዋሉም ሲል ባለፈው ማክሰኞ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት መውቀሱን ገልጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ የጦር ወንጀልና ኢ-ሰብዓዊ የወንጀል ተግባራትን መፈጸም የሚሉ ሁለት ክሶችን በ2009 አልበሽር ላይ መመስረቱንና ከአንድ አመት በኋላም የዘር ማጥፋት የሚል ተጨማሪ ክስ መመስረቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፍርድ ቤቱ በፕሬዚዳንቱ ላይ የእስር ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም አንድም አገር ተፈጻሚ እንዳላደረገው ጠቁሟል፡፡ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አልበሽርን ለማሰር ፈቃደኞች አልሆኑም በሚል ተመሳሳይ ወቀሳዎችን ሲያሰማ መቆየቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፈው ሰኔ ወር ላይም የፍርድ ቤቱ ዋና አቃቤ ህግ አልበሽርን አናስርም ባሉ አገራት ላይ እርምጃ አልወሰደም በሚል በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ላይ ትችት መሰንዘራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡


ቴለር ስዊፍት በ12 ወራት 170 ሚ. ዶላር በማግኘት ትመራለች
    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በ2016 ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የዓለማችን 100 ዝነኞችን ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረገ ሲሆን አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው ድምጻዊቷ ቴለር ስዊፍት ባለፉት 12 ወራት 170 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በዝርዝሩ የመጀመሪያውን ደረጃ ይዛለች፡፡
ድምጻዊቷ በአመቱ ያከናወነቺው 1989 የተባለ አለማቀፍ የሙዚቃ ጉዞ ከፍተኛ ገቢን እንዳስገኘላት የጠቆመው ፎርብስ፤በማስታወቂያና በሌሎች መንገዶች ያገኘቺው ገቢ ተደምሮ በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኘች ቁጥር አንድ የዓለማችን ዝነኛ እንዳደረጋት ገልጧል፡፡ዋን ዳይሬክሽን የተባለው የሙዚቃ ቡድን በ110 ሚሊዮን ዶላር ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ታዋቂው ደራሲ ጄምስ ፓተርሰን በ93 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የገለጸው ፎርብስ፤ ዶክተር ፊል ማክግሮው በ88 ሚሊዮን ዶላር፣ ፖርቹጋላዊው የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ88 ሚሊዮን ዶላር የአራተኛና የአምስተኛ ደረጃ መያዛቸውን አስታውቋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ድምጻውያን፣ የፊልም ተዋንያን፣ ኮሜዲያን፣ አትሌቶች፣ የእግር ኳስ ተጫዋቾችና በሌሎች ዘርፎች ታዋቂ የሆኑ የአለማችን ዝነኞች የተካተቱ ሲሆን እነዚህ 100 ዝነኞች ከሰኔ ወር 2015 እስከ ሰኔ ወር 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በድምሩ 5.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡
በፈረንጆች አመት 2015 በዝርዝሩ ውስጥ ተካተው የነበሩ 34 የዓለማችን ታዋቂ ግለሰቦች፣ በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ለመካተት በለስ እንዳልቀናቸው የጠቆመው ፎርብስ፤ ከእነዚህም መካከል ታዋቂዎቹ ድምጻውያን ሌዲ ጋጋ እና ጀስቲን ቲምበርሌክ እንደሚገኙበት አስታውቋል፡፡
እስከ 20ኛ ባለው ደረጃ ከተቀመጡት የአለማችን ታዋቂ ድምጻውያን መካከል በ80 ሚሊዮን ዶላር 9ኛ ስፍራን ያያዘቺው አዴል፣ በ76.5 ሚሊዮን ዶላር 12 ደረጃን የያዘቺው ማዶና እና በ75 ሚሊዮን ዶላር 13ኛ ደረጃን የያዘቺው ማዶና ይገኙበታል፡፡

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በጠና ታመመና አልጋ ላይ ዋለ፡፡ በየጊዜው እየሄደ ዶክተሮች ያነጋግራል፡፡
1ኛው ሐኪም - “አይዞህ ቀላል ነው፡፡ ለክፉ አይሰጥህም” አለው፡፡
ህመምተኛው - “ዕውን ሐኪም በዚህ ተፅናንቼ ልቀመጥ?”
1ኛው ሐኪም - “እርግጡን ነው የነገርኩህ”
ህመምተኛው - “እንዳፍዎ ያድርግልኝ!”
ግን አያርፍም ህመምተኛው - ወደ ሁለተኛው ዶክተር ይሄዳል፡፡  
ሁለተኛው ሐኪም - “ምንም ችግር የለብህም፤ አሁን የያዘህ በሽታ በረዥም ጊዜ የሚድን ስለሆነ ብቻ ነው አልጋ መያዝ ያስፈለገህ”
ህመምተኛው - “ቃልዎትን አምኜ ዝም ብዬ ልተኛ ሐኪም?”
ሁለተኛው ሀኪም - “እቺን ታክል አትጠራጠር!”
ህመምተኛው - “እንዳፍዎ ያድርግልኝ!”
ወደ ሶስተኛው ሀኪም በሚቀጥለው ቀን ይሄዳል፡፡
ሶስተኛው ሐኪም - ከሁሉም የተለየ ነገር ነው የነገረው፡፡
“ወዳጄ የያዘህ በሽታ ፈፅሞ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሀያ አራት ሰዓት ለመቆየት መቻልህን እጠራጠራለሁ፡፡ ስለዚህ ምንም አላደርግልህም”
ህመምተኛው አመስግኖ ሄደ፡፡
ሁኔታው ሶስተኛው ሐኪም እንዳለው ሳይሆን ቀረ፡፡ ሰውየው ከቀን ቀን እየተሻለው መጣና በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ካልጋው ተላቆ ቆሞ መሄድ ቻለ፡፡ በእርግጥ ግን ህመሙ ብዙ ስጋውን ስለበላው በአፅሙ የሚሄድ ይመስላል፡፡
አንድ ቀን መንገድ ላይ ሶስተኛውን ሐኪም አገኘው፡፡ ሐኪሙ በጭራሽ ያየውን ማመን አልቻለምና፤
“የወዲያኛውን ዓለም አይተህ ተመልሰህ መጥተህ መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ጥርጥር የለኝም፡፡ ከዚህ ቀደም ተለይተውን ወደ ሰማይ ቤት የሄዱት ወዳጆቻችን እንዴት ናቸው ባክህ?”
ህመምተኛውም - “እጅግ በጣም ተመችቷቸው፣ ደልቷቸው ነው የሚኖሩት፡፡ ዘለዓለማዊውን ውሃ ጠጥተውና የዓለም ችግር ሁሉ ረስተው፤ በጣም ተመችቷቸው ይኖራሉ፡፡ በነገራችን ላይ እኔ ከዛ ለቅቄ እየመጣሁ ሳለሁ ምድር ላይ ባሉ ዶክተሮች ላይ ፍርድ ለመስጠት እየተዘጋጁ ነበር፡፡ ያስቀመጡት ምክንያት ህመምተኛ ሰዎች በተፈጥሮአዊ መንገድ እንዳይሞቱ ጥበብ እየተጠቀሙ በህይወት እንዲቆዩ በማድረጋቸው ነው፡፡ አንተንም ከሌሎቹ ጋር እንደሚቀጡህ ሲያስቡ ነበር፡፡ እኔ ግን እሱን ተዉት፤ ምክንያቱም እሱ አባይ ጠንቋይ እንጂ ዶክተር አይደለም አልኳቸው!”
*              *           *
ውሸተኛ ዐባይ ጠንቋዮች እየበዙ፣ ዕውነተኛ ዶክተሮች እየሳሱ ከመጡ አገራችን አደጋ ላይ ናት! ዐባይ መምህራን እየበዙ ዕውነተኛ መምህራን ከተመናመኑ የትምህርት ነገር አዲዮስ! የሚባል ይሆናል! ዐባይ ጠበቆችና ዐባይ ዳኞች ከተበራከቱና ዕውነተኛ ዳኞችና ሀቀኛ ጠበቆች ከጠፉ “O! Justice thy has flown to beasts!!” (ፍትሕ ሆይ! ወደ አራዊት በረርሽን!) እንዳለው ሼክስፒር ይሆናል፡፡ ግልፅነትና ተጠያቂነት ለአፍ አመል ብቻ እየተስፋፉ በተግባር ግን ሁሉ ድብቅ፣ ሁሉ የአዋቂ አጥፊ እየሆነ የሚገኝ ከሆነ፤ የለበጣ ዲሞክራሲ እንጂ ሌላ የለም፤ ሃሳዊ መብት እንጂ ለዕድገት የቆመ ሀቀኛ ሥርዓት አይኖርም፡፡ የካብነው እየተናደ፣ አደግን ያልነው ቁልቁል እየሔደ፤ በየቀኑ በችግር ማጥ ውስጥ መላሸቃችን አሳዛኝ ነው! የግል ት/ቤቶች ዕውቅናና ፈቃድ አስቂኝ  ደረጃ ላይ ደርሷል! የት/ቤቶች ተቋማት ዕድሳት ዘወትር በማስጠንቀቂያና በማስፈራሪያ የሚታለፍ የመስፈራሪቾ (Scare-crow) ሂደት ሆኗል፡፡ ሥርአተ- ትምህርት አደረጃጀቱን ማጥራት እንዳቃተው ከረመ! የግብዓት አቅርቦትና አገልግሎት እንከን አልባ ለመሆን አልታደለም! የዝውውር ፖሊሲ እንደተሽመደመደ ነው፡፡ የመረጃ አያያዝ የተቆጣጣሪ ያለህ! እያሰኘ ነው፡፡ በት/ቤት ተቋማት ውስጥ ‹‹በአጋዥ መፃሕፍት› ሰበብ ያለንግድ ፈቃድ የችብቸባ ሥርዓት መፈጠር ዘግናኝ ዕውነት ነው፡፡ የወላጆች አቤቱታ የምድረ ባዳ ጩኸት ሆኗል (Crying in the Wilderness)፡፡ የዚህ ሁሉ ውጤት የሆነው የፈተና ብቃት አለ ወይ? ብለን ገና መልስ ሳናገኝ፤ የፈተና ስርቆሽ አደጋ አናታችን ላይ ያንዥብባል? ያውም ኢንተርኔት እስከማዘጋት የደረሰ የሌብነት መንግሥታዊ ሥጋት … ይህ ሁሉ ሲታይ እንዴት ሚሥጥራችን በሀገር ደረጃ ይጠበቃል? ብለን ዕምነት እንጣል፡፡ ዕምነት ማጣት ያለመረጋጋት እናት መሆኑን እንርሳ!
ችግሮችን የመፍታት መንገዳችን ወይ መንገድ አደለም፤ ወይ ወልጋዳ መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ችግርን ለመፍታት ሌላ ችግር መንገድ ነው፡፡ ይህ ማለት ችግርን ለመፍታት ሌላ ችግር መቀፍቀፍ ነው፡፡ ችግር በችግር አይፈታም፡፡ ዘላቂ መፍትሔ በማይሆን መልኩ ጥገናዊ ማስታመሚያዎች ብንደረድር ቁስላችን ማመርቀዙ አይቀሬ ነው፡፡ ውስጣችን መፈተሽ አለበት፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ በማላከክ ሳይሆን ዕውነተኛውን በሽታ ፈልቅቆ በማውጣት ነው ህክምናችን የተሳካ የሚሆነው፡፡ አለበለዚያ፤ አንደኛው ሀኪም ቀላል ነው፤ ሁለተኛው ሀኪም በረዥም ጊዜ የሚድን በሽታ ነው፤ ሦስተኛ ሀኪም- ሀያ አራት ሰዓት አትቆይም! አይነት መፍትሔ ይዘን እንደ አፍዎ ያርግልኝ እያልን በጥንቆላ የምንተዳደር ሊመስለን አይገባም፡፡ በሽታችን የሚወሳሰበው ጊዜ ወስደን በጥሞና ስለማንከታተለው ነው፡፡ የበሽታችንን መንስዔ ከስር መሰረቱ ለማወቅ፣ አካሚውም ታካሚውም ግልፅነት ስለሌለን ነው፡፡ በሽታውን የደበቀ መድሀኒት አይገኝለትም የሚለው ዕውነት እንዳለ ሆኖ፤ መድህን አያገኝም የሚለው ታክሎብናል፡፡ የመጨረሻው አሳሳቢ ነገር ደግሞ ትክክለኛውን መረጃ አለማግኘት ነው፡፡ ይህ እክል አንድም ከመረጃ ሰጪ ንፉግነት የሚመነጭ ነው፡፡ አንድም የመረጃ ሥርዓቱ ብቃት ማጣትና ይሆነኝ ተብሎ እንዲጥመለመል ማድረጉ ነው፡፡ አሊያም ጨርሶ ለመረጃ ፋይዳ ጥረት አለመስጠት ነው! ከሁሉም ይሠውረን፡፡ እጅግ አስከፊው ገፅታችን ግን፤ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› እንዲሆን ካደረግን ነው፡፡ ሆን ብለን መረጃ ካጣመምን ማለትም መረጃ ተቀባይ ትክክለኛውን መረጃ ሳይሆን የተሳሳተውን ወስዶ ሌሎችን እንሳስት አድርገን፤ እኛም መልሰን እሱን ከሳሽ ከሆንን የመርገምት ሁሉ መርገምት ይሆንብናል! እንዲህ ያለውን ሂደት መዋጋት የግድ ነው፡፡ መረጃ፤ መረጃ የሚሆነው ለሚመለከተው ጉዳይ በአግባቡ ሲውል ነው፡፡ አለበለዚያ፤ ‹‹ከአንበሳና ከዝሆን ማን ያሸንፋል?›› ቢለው፤ ‹‹ከሁሉም ከሁሉም አሳ ሙልጭልጭ ነው!›› የሚለውን ተረት ስናደምቅ መኖራችን ነው!

“መንግስት እንደፈለገ ያድርገን ብለን ቁጭ ብለናል”

   በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ስሙ ‹ማንጎ› የተባለው አካባቢ፣በቤት ፍርስራሾች ተሞልቷል፡፡ ቦታው በጦርነት ወይም በተፈጥሮ አደጋ የወደመ ነው የሚመስለው፡፡  የወዳደቁ የቤት ፍራሽ እንጨቶች፣የተጨረማመቱ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎች ለዓይን ይታክታሉ፡፡ በፍርስራሾቹ ጥጋጥጎች ላይ በተጨረማመተቱ ቆርቆሮዎችና በፕላስቲክ የተሰሩ ዳሶች በብዛት ይታያሉ፡፡ በቤቶቹ ፍርስራሾች ላይ ተፈናቃዮች ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አረብ ሀገር ሰርታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ከአርሶ አደር ላይ ቦታ ገዝታ ባለ 3 ክፍል ቤት በመሥራት፣ ላለፉት 10 ዓመታት በቦታው ላይ መኖሯን የምትናገረው ወጣት ትገኝበታለች፡፡  
  ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት ስትሆን፤ ቤቷ ከፈረሰ በኋላ ከእነቤተሰቦቿ እዚያው ፍርስራሹ ላይ በፕላስቲክና በቀዳዳ ቆርቆሮ ከለላ ሰርታ መጠለሏን ገልጻልናለች፡፡   
በህይወቴ እንዲህ ያለ ምስቅልቅሎሽ አጋጥሞኝ ቀኑ ይጨልምብኛል፣ መግቢያ አጣለሁ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር የምትለው ወጣቷ፤መሄጃ አጥቼ ከእነልጄ ጭቃ ላይ እየተንከባለልኩ ነው የማድረው ብላለች-ግራ በመጋባት ስሜት ተውጣ፡፡ በዳስዋ ውስጥ ለአፍታ በነበረን ቆይታ ጥቂት ጥያቄዎችን አቅርበንላት መልስ ሰጥታናለች፡-
 ይሄ ሁሉ ቤት በስንት ቀን ነው የፈረሰው?
በአንድ ቀን ነው ያፈረሱት፡፡
አስቀድሞ ይፈርሳል ተብሎ ተነግሯችሁ ነበር?
እኛ አካባቢ ይፈርሳል የሚል ወሬ ፈፅሞ አልሰማሁም፡፡ የሰማሁት ኤራኤልና፣ ጨሬ ቀርሳ ነው፡፡ ግን ሳናስበው ያንን አጋጣሚ ተጠቅመው የኛንም አፈረሱብን፤መግቢያ አሳጡን፡፡
ቤታችሁ ከፈረሰ በኋላ ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል አለ?
ማንም ያነጋገረን አካል የለም፡፡ እናንተ ናችሁ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥታችሁ የጠየቃችሁን፤ሌላ ዞር ብሎ ያየን የለም፡፡ ሀገር እንደሌለን ሜዳ ላይ ስንወድቅ የጠየቀን ማንም የለም፡፡
እናንተስ ---- ለመንግስት አቤቱታ ለማቅረብ አልሞከራችሁም?
እኛማ ማጣፊያው አጥሮናል’ኮ! የት ብለን ማንን እንጠይቅ፡፡ በቃ የሆነውን እንሁን ብለን እዚችው የቤቷ ፍራሽ ላይ ቀርተናል፡፡ ለራሴም ቤት ሰርቼ፣ አንድ ሁለት ክፍል ሰርቪስ ቤቶች ከጎን ቀጥዬ እያከራየሁ ገቢ አገኝ የነበረው ቀርቶ፣ዛሬ ይኸውና ለራሴም መጠለያ የሌለኝ ሆኛለሁ፡፡ ሀብት ንብረቴ ሁሉ ወድሟል፡፡
አሁን በምንድን ነው የምትተዳደሪው?
ቤቱ ከፈረሰ በኋላ ምንም ገንዘብ የማገኝበት ነገር የለም፤ሰው እየረዳኝ ነው የምኖረው፡፡
የሚከራይ ቤት ለማግኘት አልሞከራችሁም?
እኔ እዚህ ምንም ዘመድ የሌለኝ ሰው ነኝ፡፡ ማን ጋ ልጠጋ? ቤት ተከራይቼ እንዳልኖር ትንሹ የቤት ኪራይ 1500 ብር ነው፤ ከየት አመጣለሁ? ምንም ገቢ የማገኝበት ነገር የለኝምኮ! አቅሜ አይፈቅድም፡፡ በቃ ባዶዬን ቀርቻለሁ፡፡
መንግስት ምን እንዲያደርግ ነው የምትፈልጉት?
 ቦታውን እፈልገዋለሁ ብሎ እንዲህ ካደረገን በኋላ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ እኛም የዚህች ሀገር ዜጎች ነንና ያስብልን፡፡ ለዚህች ሀገር ልማት እናዋጣ የነበርን ዜጎች ነን፡፡ መንግስትን ምን በደልነው? ልጆቻችንስ በልጅነት አይምሮአቸው ለምን ይጎዱ፡፡
 ልጆቼ እየተሳቀቁ የሚበሉት አጥተው እየተቸገርን ነው፡፡ ወንድሜ እስቲ ንገረኝ ---- የገቢ ምንጭ ከወደመ በኋላ ይህችን ልጅ ምን ላብላት? … ዘንድሮ በኔ የመጣ ቁጣ እንዲህ ነው ተብሎ አይነገርም፡፡
“ከጅብ ጋር እየተፋጠጥን ነው የምናድረው”
አንዱ በአንዱ ላይ የተደረማመሱትን ቤቶች እየተመለከትን፣ከአንደኛው የቤት ፍራሽ ጥግ ላይ ወደተቀለሰች ዳስ አመራን፡፡ በዳሱ ውስጥና በራፉ ላይ አራት ሰዎች ቁጭ ብለው ቡና እየጠጡ ነበር፡፡ ጎራ ብለን ማነጋገር ጀመርን፡፡
ቤታችሁ ከፈረሰ በኋላ በእንዲህ ያለ ሁኔታ እዚህ ለመኖር ለምን መረጣችሁ? ቤት ተከራይታችሁ አትኖሩም?
(ከመካከላቸው አንደኛው በፍጥነት ምላሽ መስጠት ጀመረ …)
እየውላችሁ ወንድሞቼ---እኛ የቀን ሰራተኞች ነን፤ ከተማ ገብተን በ4ሺ እና 5ሺህ ብር ቤት ለመከራየት ይቅርና ለእለት ጉርሳችንም ስንቸገር የኖርን ነን፡፡ በምን አቅማችን ነው ቤት የምንከራየው?
በፊት በምን ነበር የምትተዳደሩት?
አንድና ሁለት ክፍል ቤት ከመኖሪያ ቤታችን ጎን ቀጥለን እየሰራን፣እያከራየንም ገቢ እናገኛለን፡፡ አብዛኞቻችን የቀን ሰራተኞች ነን፡፡ እኔ የምሰራው ድንጋይ ፈላጭነት ነው፡፡ ኮብልስቶንም እንሰራለን … በዚህ ነው የምንተዳደረው፡፡
ቦታውን ከአርሶ አደር ላይ ስትገዙ ህገወጥ መሆኑን አታውቁም ነበር?
በወቅቱማ ማንም አልተቃወመንም፡፡ አንድም ቀን ህገ-ወጥ ናችሁ ተብለን አናውቅም፡፡ ቤት ስንሰራ ደንቦች ይመጣሉ፤ግን አፍርሱ አይሉንም ነበር፡፡ አሁን እንኳ ሊፈርስብን ሰሞን መንገድ ለመስራት ባዋጣነው ገንዘብ፣የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ተገዝቶ ሊቀበር በዝግጅት ላይ ነበር፡፡ ገንዘብ አዋጡ ተብለን እያዋጣን መብራት፣ መንገድ፣ ውሃ አስገብተናል፡፡
ውሃ በየግቢያችን እንዲገባ የተላከ ከወረዳው በማህተም የተደገፈ ወረቀት አይተናል፡፡ ለልማት 9 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብለን ስናዋጣ ነበር፡፡
 ይሄን ሁሉ ስናለማ ዝም ብለውን፣ ዛሬ አንገታችንን ቀና አደረግን ስንል፣እንዲህ መልሶ ቅስማችንን የሚሰብረን መንግስት ምን አድርገነው ነው? ምን በድለነው ነው? ለአንድ ቀን እንኳ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠን ምን አለበት?
ከመፍረሱ በፊት እቃችሁን አውጥታችሁ ነበር?
ድንገት እኮ ነው ማፍረስ የጀመሩት፡፡ የቻልነውን አትርፈናል፡፡ ብፌ፣ ሶፋ ግን እንዳለ ወድሞብናል፡፡
ለምን እቃችሁን ለማውጣት አልቻላችሁም?
ማን ያውጣው!? ወንዶቹን እየለቀሙ ነው ያሰሩት፤ግማሹ ሸሽቶ ከአካባቢው ራቀ፡፡ ሴቶች ብቻ ነበሩ የቀሩት፡፡ በዚያ ላይ 8 ማሽን ነበር ቤቱን ሲያፈርስ የነበረው፡፡ አካባቢው በአቧራ ታጥኖ … ሁኔታው ሁሉ አስፈሪ ነበር፡፡ እንዲህ እንደሚወራው ቀላል እደለም፡፡
አሁን እንዴት ነው የምትኖሩት?
ይኸው እንደምታዩት ጭቃ ላይ ፍራሽ አንጥፈን ነው የምንተኛው፡፡ አሁን የምንጠጣውን … ቡና ዘመድ ነው ያመጣልን፡፡ ልጆቻችን ተበታትነዋል፡፡
 ሁላችንም ዘመድ ከምናስቸግር ብለን በየቦታው በትነናቸው ነው እኛ እዚሁ የቀረነው፡፡ ት/ቤት ሄደው እስኪመጡ የማናምናቸው ሰዎች ዛሬ ምን ይሁኑ አናውቅም፡፡
ያነጋገራችሁ የመንግስት አካል የለም?
ማንም ዞር ብሎ ያየን የለም … ወገን እንደሌለን ሜዳ ላይ ቀርተናል፡፡
(አባወራዎቹ ቦታውን አንዱን ካሬ ሜትር በ100 ብር ሂሳብ እንደገዙት ይናገራሉ፡፡)
ለወደፊት ተስፋ የምታደርጉት ምንድን ነው?
ምን ተስፋ አለን?! ምንም ተስፋ የለንም፤መሄጃ የለንም፡፡ እንደሚባለው ትርፍ ቤት ቢኖረን እዚህ ቦታ ውሃና ጭቃ ላይ አንተኛም ነበር፡፡ መንግስት እንደፈለገ ያድርገን ብለን ቁጭ ብለናል፡፡




    ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት፤ የማህበረሰብ ምስረታ ተቋማት የመልካም ተሞክሮ ቀን በዓል አከበረ፡፡ ድርጅቱ ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ በሚገኘውና የጄክዶ አፖርቹኒቲ ፎር ቼንጅ እየተባለ በሚጠራው የስልጠና ማዕከሉ ውስጥ ባከበረው በዚሁ የመልካም ተሞክሮ ቀን ክብረ በዓል ላይ የማህበረሰብ ምስርት ተቋማቱ ተወካዮች ተገኝተው ከድርጅቱ ጋር በማከናወን ላይ ስለሚገኙት የልማት ስራዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡ “የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት አጋርነት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪ ቃል በተከናወነው በዚህ የመልካም ተሞክሮ ቀን በዓል ላይ ተሞክሮአቸውን ለማካፈል ከተገኙት የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት መካከል ዕድሮች፣ ማህበራትና የልማት ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡ የእየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሙሉጌታ ገብሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ከ140 በላይ የማህበረሰብ ምስርት ተቋማት ጋር በአጋርነት የሚሰራ ሲሆን በተለያዩ የልማት መስኮች በሺዎች የሚቆጠሩ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬታማ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡

     የአርጀንቲናው አሊሚኔተር ግሩፕ የቬንዳኖቫ ምርት የሆነውና ላለፉት አራት ዓመታት በአርጀንቲና ጥቅም ላይ የዋለውን ጥርስን ያለ መቦርቦሪያ ድሪልና ያለ ማደንዘዣ አፅድቶ የሚሞላው መሳሪያ ሰሞኑን አገራችን ገባ፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት እውቅና የተሰጠውና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አገር ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ የተሰጠው ይሄው መሳሪያ ከተፈጥሮአዊ እፅዋት በሚሰራ ጄል ያለ ማደንዘዣና ያለ ድሪል ጥርስን በማፅዳት የሚሞላ ሲሆን አንድ ሰው በ10 ደቂቃ ውስጥ ጥርሱ ፀድቶና ተሞልቶ ወደቤቱ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ የአምራች ድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ሚስተር ጆርጅ ሌይንና የኢትዮጵያ ወኪሉ ሚረር ‹ትሬዲንግና ሰርቪስ› ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋየየ ወንድሙ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ በሂልተን ሆቴል  በሰጡት መግለጫ፤ መጀመሪያ ምርቱ በጥርስ ህመም የሚሰቃዩ ህፃናትን ታሳቢ አድርጎ የተሰራ እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት አዋቂዎችም በስፋት እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል በዕለቱ የ50 ሚ. ዶላር ስምምነት የተደረገ ሲሆን መሳሪያውን በዋና በወኪልነት ሚረር ትሬዲንግና ሰርቪስ እንደሚያከፋፍልና ከአርጀንቲና የሀኪሞች ቡድን እንደሚመጣና ለኢትዮጵያዊያን የጥርስ ሀኪሞች ስለመሳሪያው አጠቃቀም ስልጠና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ አንዱ መሳሪያ ጫፉ እየተቀየረ ለ10 ሰዎች ያገለግላል የተባለ ሲሆን አንድ ሰው በመሳሪያው ታክሞ ለመዳን አምስት ዶላር ብቻ እንደሚያስፈልገው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል፡፡ የመሳሪያው ተፈላጊነት ከጨመረ ፋብሪካው ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚከፈትና ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም እንደሚከፋፈል የገለፁት ሚስተር ጆርጅ፣ እስካሁን ከአርጀንቲናና ከሌሎች የላቲን አሜሪካ አገሮች በተጨማሪ ደቡብ አፍሪካም መሳሪያውን በስፋት እየተጠቀመችበት  እንደምትገኝ በዕለቱ ተገልጿል፡፡


     እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት ለመውጣት ህዝበ ውሳኔ ማድረጓን ተከትሎ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን፣ ባለፈው ረቡዕ ስልጣናቸውን ለአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ያስረከቡ ሲሆን ሜይ በአገሪቱ ታሪክ ከማርጋሬት ታቸር ቀጥለው ሁለተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡
ላለፉት ስድስት አመታት የእንግሊዝ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ዋና ጸሃፊ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት የ59 አመቷ ቴሬሳ ሜይ በአፋጣኝ የካቢኔ አባላትን የማዋቀርና መንግስት የመመስረት ስራ ይሰራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ አዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር አገሪቱንና የፋይናንስ ገበያዋን የማረጋጋትና ሌሎች ወሳኝ ስራዎችን የመስራት ተልዕኳቸው እጅግ ፈታኝ እንደሚሆን መነገሩን ገልጧል፡፡
እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ ለመውጣት ያሳለፈቺውን ህዝበ ውሳኔ ተፈጻሚ የማድረጉን ሃላፊነት የሚወጣውን ሚኒስትር የመምረጡ ሃላፊነትም፣ አገራቸው በህብረቱ አባልነት እንድትቀጥል ይፈልጉ የነበሩት የአዲሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጣይ ተልዕኮ ይሆናል ብሏል ዘገባው፡፡
ቴሬሳ ሜይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን መያዛቸው፣ ወሳኝ በሆኑ የስልጣን ቦታዎች ላይ የሚቀመጡ የአገሪቱ ሴቶችን ቁጥር ያሳድገዋል ተብሎ እንደተገመተም ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የ49 አመት እድሜ ያላቸውና ላለፉት 6 አመታት  አገሪቱን የመሩት ተሰናባቹ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን ከ1895 ወዲህ በዚህ በአነስተኛ እድሜያቸው ስልጣን የለቀቁ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ የ59 አመቷ ቴሪሳ ሜይ በበኩላቸው፤ ከ1976 ወዲህ እድሚያቸው ከገፋ በኋላ ስልጣን ላይ የወጡ የመጀመሪያዋ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆኑ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

እስከ ፊታችን ማክሰኞ ይዘልቃል

የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በየዓመቱ ሰኔ 30ን ምክንያት በማድረግ የሚያዘጋጀው አገር አቀፍ የንባብ ቀን ባለፈው ሐሙስ በተለያዩ የኪነ ጥበባት ዝግጅቶችና የመፃህፍት አውደ ርዕይ የተከፈተ ሲሆን ክንውኑ የፊታችን ማክሰኞ ድረስ ይዘልቃል ተብሏል፡፡“ንባብ አስተማማኝ ድህነትን መመከቻ ጋሻ ነው” በሚል መርህ እየተካሄደ ባለው በዚህ የኪነ ጥበብ ዝግጅት ላይ በየቀኑ የመፅሀፍት
አውደ ርዕይ፣ ዲስኩር፣ ወግ፣ ጥናታዊ ፅሁፍና፣ ግጥሞችና እንደሚቀርቡ ደራሲያን ማህበር
ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡ ዛሬ ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በተዋናይ ፍቃዱ ከበደ፣ በደራሲ እንዳለጌታ ከበደና በኢየሩሳሌም ነጋ ወጎች የሚቀርቡ ሲሆን ነገ ጠዋት ደግሞ “የመፃህፍት ስርጭት በገጠር ኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የፎክሎር እጩ ዶክትሬት (Phd) የሆነው ገዛኸኝ ፀጋው፣ ጥናታዊ ፅሁፍ የሚያቀርቡ ሲሆን ይታገሱ ጌትነት እንዲሁ “የህፃናት
መፅሀፍት በኢትዮጵያ” የሚል ጥናት ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ ገጣሚ ስዩም ተፈራ፣ ተዋናይ
አልአዛር ሳሙኤል፣ አርቲስት ተፈሪ አለሙና ገጣሚ ሰለሞን ሞገስ ደግሞ የግጥም ስራቸውን
ያቀርባሉ፡፡ በዕለተ ሰኞ ጋዜጠኛና ደራሲ አበረ አዳሙ፣ደራሲና ጋዜጠኛ ታደለ ገድሌ፣ መዝገበ
ቃል አየለና መምህርት ኑአሚን ቅኔያቸውን በማቅረብ ታዳሚውን ያስደንቃሉ ተብሏል፡፡
ማክሰኞ ጠዋትም የህፃናት መፅሀፍት ንባብና የሽልማት ስነ-ስርዓት ተካሂዶ የፕሮግራሙ መዝጊያ እንደሚሆን ታውቋል፡፡

የሥዕል ትርዒት ዳሰሳ
(Exhibition Review)
የትርዒቱ ርዕስ፡
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል
የትርዒቱ አይነት፡
ፌስቲቫል
የሚታይበት ጊዜ፡
ሰኔ 18 - 27: 2008 ዓ.ም
ቦታ፡
በኦሮሞ ባሕል ማዕከል
ዳሰሳ አቅራቢ፡
ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)


የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል
ወሳኝነት ያላቸው የግል ትርዒቶች ያውም በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ሁለት ሰዓልያን ስራቸውን በመዲናችን በሚያሳዩበት ሳምንት ዳሰሳውን ቢያንስ ከሁለት አንዳቸው ላይ መስራት ሲኖርብኝ፣ ወደ ፌስቲቫል ዳሰሳ ማተኮሬ፣ ይህ የተጠቀሰው ፌስቲቫል ዓመታዊ በመሆኑና አመቱን ጠብቆ ሲመጣ (በዚህ ሁኔታው ጭራሽ ባይመጣ እላለሁ) ከነ ህፀፁና ግሳንገሱ ተመልሶ እንዳይመጣ ትምህርትና ተግሳጽ ቢወስድ ከሚልና አዘጋጁ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራጽያን ማህበር ባለፉት ዓመታት ውስጥ ካለው እንቅስቃሴ አንፃር እየተጫወተ ወይም እያልተጫወተና እየቀለደባቸው ካሉ የማህበሩ ማንነትንና ህልውና ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ ሁነቶች አኳያ ሊነሱ የሚችሉ ነጥቦችን በመተንተን የዛሬውን ዳሰሳ እነሆ፡፡
(ለሚቀጥሉት ሳምንታት ዳሰሳዎች የተሻለ አትኩሮት እንዲኖራችሁ ትርዒቶቹን ብትመለከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በአዲስ ፍይን አርት - ሠዓሊ መሪኮከብ ብርሃኑ የግል ትርዒት፣ በሞደርን አርት ሙዚየም ገብረክርስቶስ ደስታ ሴንተር - ሠዓሊ ጁሊ ምሕረቱ ስራዎቻቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአቅጣጫ +251 911 702 953)
“የኢትዮጵያ”
“ልጅሽ ነኝ፤ አንቺም እናቴ ነሽ” በሚል የፍቅር አይሉት የድፈረት ወይ የንቀት ካባ የተጀቦነች ብሔርተኝነት (Nationalism) የምታመጣው ጣጣና እንክርፍፍነት ቀላል እንዳይመስላችሁ፡፡ ”የጋን ውስጥ መብራት” ከሆነና ውጪው አረፋ ከሞላው ውሃ ተነክሮ ከሚወጣና እፍ ሲሉት የሚያምር ቀለማትን አየር ላይ ለሽራፊ ሰከንዳት በተንሳፋፊ ክቦች አሳይቶ ከሚጠፋው (bubble) እንኳ የማይተካከል ሃሳብ ይዞ፣ስያሜውን ግን ጠጣር በሆነ ውህዷ ከምትታወቀው /ቢያንስ ውስጣችን እንዲህ ዓይነት ግዝፈት ካላት/ ሀገራችን ስም በመነሳት “የኢትዮጵያ …” እያሉ ስያሜ መስጠት አይሉት ማላዘን የተለመደና ብዙ ተቋማት ለሚወጥኑት የእንቶ-ፈንቶ ድግስ ማድመቂያ ተቀጽላ ከማድረግ አልፎ ነቀርሳ እየሆነ መጥቷል፡፡ ምናለ በሆነ ባልሆነው ጨርቋን ባይጎትቷት፣ምናለ ባይጎነትሏትና ባይተነኩሷት? “ምነው?” የማትል ድንዙዝ ከሆነች ሰነባብታለች፡፡ ለነገሩ እሷም አውቃ የተኛች ይመስላል፤እንኳን ሲጠሯት ጆሮዋን ሲቆርጧትም ማነው የማትል ድንዙዝ ከሆነች ሰነባብታለች፡፡
ለነገሩ ለምን “የኢትዮጵያ” አልክ ብሎ የሚጠይቅ እስከሌለ ድረስ ‘ሃገር የጋራ ናት’ በሚለው አባባል፣ በመደፋፈር ጨርቅ ጉተታና ጉንተላ አይደለም ‘የአስገድዶ መድፈር’ ቢደርስባት እንኳን የሚገርም አይሆንም (ሀገር ፆታ የለውም፣ የአንድ ሀገር ስያሜም ወንዴና ሴቴ የለውም፡፡ እዚህ ፅሁፍ ላይ ሀገሬን አንቺ ብላትና በሴት ፆታ ብጠራት የቀለለኝና የተመቸኝ በመሆኑ እንጂ ፆታ እሱ ወይም ‘እሷ ኢትዮጵያችን’ እያልኩ ብጠራው ፆታዊ ከሆነ ከተግባራዊ ጉንተላ፣ ከሱሪ ጉተታና መደፈር ላያመልጥ የሚችል ሀገራዊ ማንነት ላይ የቆምን ባለመሆኑ ኢትዮጵያን እሱ አንተ ብንለው ወይ እንደለመድነው አንቺ- እሷ ብንላት ምንም ለውጥ እንደሌለው ለፆታዊ (gender) ጉዳዮች ስሱ የሆነ/ነች አንባቢ እንደሚረዳኝ /ትረዳኝ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ )
እና … ‘የኢትዮጵያ’ በሚል ስያሜዎችን ከሚጠቀሙት ዝግጅቶችና ተቋማት መሀከል የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር፣ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ይህ ስሙ ብቻ የከበደውና የተካበደው ዓመታዊ ፌስቲቫል አንዱ ነው፡፡ እስቲ ውስጡ ይፈተሽ፡-
የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል ማንን ነው የሚወክለው? ‘የኢትዮጵያ ሠዓልያንን’፤ ‘የኢትዮጵያ ዘመንኛ ሥነ-ጥበብን?’ ‘የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሥነ-ጥበባዊ ተዋፅኦን’… የቱ ጋ ነው የፌስቲቫሉ “የኢትዮጵያዊ”ነት?፡፡“የኢትዮጵያ” የምትባለው ኢትዮጵያ በሌለችበት ምነው ስሟን ማንቆለጳጰስ ብቻ ተወደደ? ነው ወይስ የኢትዮጵያ ስለተባለች ብቻ ሆ…! ብሎ የሚነሳ ሥነ-ጥበብ አለ …? “የኢትዮጵያ” ስለተባለች ብቻ ደስ የምናሰኛት ኢትዮጵያ አለች?…. ካለችም ምናለ ኢትዮጵያነቷን የሚወክል ሥራ ሰርተንላት ስያሜዋን ጥቅም ላይ ብናውለውና ደስ ብናሰኛት… አለዚያ አርፈን ብንቀመጥና እሷም ባለችበት አርፋ ብትቀመጥ- ባንነነዘንዛት ነው የሚሻላት፡፡ ስሟ በተጠራ ቁጥር ስቅ እያላት ተቸገርች እኮ!
… ፌስቲቫሉ “የኢትዮጵያዊ”ነት ራዕይ ከሌለው፣ለማይወክላት ስራ የማይወክላትን ስያሜ እየሰጠ ችክ አይበልባት … የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል አንዱና ዋንኛው ችኮ በመሆኑ እተቸዋለሁ! (ማለት የተቻለበት በምክንያት ከቀረበልኝም ሂሴን ለመዋጥ ዝግጁ ነኝ!)
የማዝነው - ይልቅስ የማዝነው በስራዎቻቸው “ኢትዮጵያን” በብቃት የመወከል ሥነ-ጥበባዊ አቅምና ህልውና ያላቸው ጉምቱ የሥነ-ጥበብ ሰዎቻችን ኢትዮጵያችንን ለማይወክላት የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል “የኢትዮጵያን” ታላቅነት (glory) ለማጉላትና ለማድመቅ (ሊሆን ይችላል) ወይም በቅን ልቦና ጊዜአቸውንና ስማቸውን መጠቀሚያ ማድረጋቸው ወይም መጠቀሚያ እንዲሆን መፍቀዳቸው፡፡ ጊዜአቸውና ስማቸው ብክነት ላይ መዋሉን ልብ ባለማለታቸው ግን አዝናለሁ፡፡ ፌስቲቫሉ ከዓመት ወደ ዓመት እያሽቆለቆለ ሲመጣ እያዩ፣“የኢትዮጵያ” የሚለውን ስያሜ መጠቀሙን ባይጠይቁና፣ ተው ብለው ባይገስፁ እንኳ ፌስቲቫሉ እንዲሻሻል ያደረጉት አስተዋፅዖ መኖር አለበት እላለሁ፡፡ (ካለም … ይኸው ባደባባይ ነው የምናገረው … ባደባባይ እማራለሁ እታረማለሁ፡፡) ሆድ ያባውን በጋዜጣ ያወጣዋል እንዲሉ የእኔን ነጥቦች እንካችሁ፡-
የፌስቲቫሉ አጀማመርና ከፍታ (ከፍታ ከተባለ)፡ የ2006 ዓ.ም የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት አካባቢ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር፣ ለሠዓሊያንና ለሥነ-ጥበብ ተቋማት ጥሪ አደረገ፡፡ በጥሪው መሰረት ተከታታይነት ያላቸው ረዘም ያለ ጊዜ የፈጁ ውይይቶች  ተካሄዱ፡፡ የውይይቱ ጭማቂ ይህን ፌስቲቫል ወለደ፡፡ “በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ክብር፣ ለሠዓሊያንና ለሥነ-ጥበብ ሲሰጥ ያየሁት በዚህ ነው .. መቼስ ምን እላለሁ አንግሳችሁናል!”  የሚል ለሙያው ጥልቅ ፍቅር ያለው ሠዓሊ ከሰጠው አስተያየት ጀምሮ፣ ከጥሪው በኋላ ባሉ ስብሰባዎችና በፌስቲቫሉ አካሄድና አሰራር  ዙሪያ ጥርጣሬዎቻቸውና ጥያቄዎቻቸው በማህበሩም ሆነ በሚኒስቴሩ ሊፈታ ባለመቻሉ አንዳንዳቸው እቅጩን ተናግረው ፣ ሌሎች አጉረምርመው፣ሌሎች በዝምታ ተለጉመው ቀስ በቀስ ድምፃቸውን አጠፉ፡፡ ከጥሪውም ከፌስቲቫሉም ቀሩ፡፡ ሃሳቡ ቀጠለ፡፡ “ጥበብ ለሁሉም!” በሚል መሪ ቃልም ዝግጅቱ ተጀመረ፡፡
ሚኒስቴሩ በፌስቲቫሉ እንዲተገበሩ በቀረቡ ሃሳቦች ምንነት ላይ ትኩረት ከመስጠት ይልቅ “በጀቱን ቀንሱ” እያለ የሥራ ዕቅዱን ሲያመላልስ በበጎ ፈቃደኝነት ሥነ -ጥበባዊ ፋይዳ ለመከሰት፣ ሃገራዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣትና ለመሳተፍ የመጡ ባለሙያዎችን ሲያጉላላ ቆይቶ፣ በሶስተኛው ሩብ የበጀት ዓመት መባቻ ላይ በሰኔ 2006 ዓ.ም የመጀመሪያው ፌስቲቫል ተከወነ፡፡
እንደ መጀመሪያነቱ እንዲሁም ቀጥለው ከመጡት ሁለቱ ፌስቲቫሎች አንፃር የዚህ ፌስቲቫል ከፍታ ልንል የምንችላቸውን ሥነ-ጥበባዊ ክዋኔዎችና ፕሮራሞችን እንጥቀስ፡፡ ከፍ ያለው በጣይቱ ኢንተርናሽናል አርት ሴንቴር በዋናነትም በወቅቱ የሴንተሩ አጋፋሪ ዘላለም ግዛው (ሠዓሊ) የተዘጋጀውና የተከወነው የሕፃናትና የጎዳና ላይ ታዳጊዎች የሥዕል ሰርቶ ማሳያ (workshop) እና የሰርቶ ማሳያው የሥዕል ትርዒት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሴት ሠዓልያን ማኅበር በብሔራዊ ቴአትር ጋለሪ ያዘጋጀውና በጋለሪው በር የሚያልፍ ማንኛውንም ሰው ሥዕል እንዲስል የሚጋብዝ አሳታፊ መሰናዶ የመጀመሪያው ፌስቲቫል ከፍታ ሊባል ይችላል፡፡  ሌላኛው በጉራምዓይኔ የሥነ-ጥበብ ማዕከል የተዘጋጀውና አስር ሰዓልያንን አሳትፎ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመልሶ ማልማት ፍርስርሷ እየወጣና ማንነቷን እየተነጠቀች ከመጣቸው አዲስ አበባችን ውስጥ ካሉ አካባቢዎች በንፅፅር ሲታይ በዚያን ጊዜ (2006 ዓ.ም) እና አሁንም በጥቂቱ( ታሪካዊው ውቤ በርሃ መንኮታኮት ውጪ) የታሪካዊነት ቅሪታቸው ሊታይ በሚችሉት በአራት ኪሎና የፒያሳ አዋሳኝ መሃል ያሉ ታሪካዊ ቤቶችና መንገዶች፣ ምልክት የሆኑ ቦታዎች (landmarks)፣ መነጋገሪያ የሆኑ ቦታዎችን እንዲሁም እየተገነቡና እየፈረሱ ያሉ የፒያሳና የአራት ኪሎ ቦታዎችን የሚቃኙ ሥዕሎች ተሰርተዋል፡፡
ይህም ቦታዎቹን በሥነ- ጥበብ ከመሰነዱም በላይ ሰዓልያኑ በቦታዎቹ ላይ ቆመው ሲስሉ በተለያዩ የሬዲዮን ጣቢያዎች በቀጥታ ይተላለፉ ስለነበር ክዋኔውን በሬዲዮን የሰሙና ቦታው ሲመላለሱ የነበሩ መንገደኞች፣ቆም ብለው ሠዓሊያኑ የሚሠሩትን የማየትና የመጠየቅ፣በዚያውም (አባይን በጭልፋ አይነት ቢሆንም) ስለ ሥነ-ጥበብ ያላቸውን ግንዛቤ የማዳበር እድል የከፈተ ክዋኔ ነበር፡፡ በሐበሻ ስቱዲዮው ሠዓሊ ወርቅነህ በዙ የቀረበውና በከተማዋ ዋና ዋና ቦታዎች እየተዘዋወረ የታየው የፓፔት ትርዒት፣የሥነ-ጥበብን ሰፊ ተደራሽነትና ተግባራዊ ፋይዳ ያመላከተ ነበር፡፡ የትርዒቱ አካል የነበረውና በሁለት ዓመት ውስጥ ካቀረባቸው ሠዓሊያንና ትርዒቶች መሀከል ስራዎችን መርጦ ካሳየው ጋለሪያ ቶሞካና የታላላቅ ሠዓልያንን ስራዎች ከወጣት ሠዓልያን ስራዎች ጋር አጣምሮ በትርዒት መልክ ካሳየው የላፍቶ አርት ጋለሪ በተጨማሪም ያልተሳካ የፓናል ውይይትም ተወጥኖ ነበር፡፡ በዚህ በመጀመሪያው ፌስቲቫል ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የአንዱ ዳይሬክቶሬት ቢሮ ሃላፊ ከሆኑ ተወካይ፣ በአንድ የትርዒት መክፈቻ ላይ ብቅ ከማለት ውጪ የሚ/ር መ/ቤቱ ባለስልጣናት ዝር አለማለታቸው፣ ለፌስቲቫሉ የሰጡትን ዝቅተኛ ትኩረት ያሳየ ነበር፡፡
ሁለተኛው ፌስቲቫል ከሞላ ጉደል በቀደሙት ፌስቲቫሎች የነበረውን ችግር ለመቅረፍና አዲስ አካሄድ ለመቀየስ ያለመ ነበር፡፡ ይበልጥ አልተሳካለትም እንጂ፡፡ የተሻለ በጀት መድቦ ነበር፤ወደ ሰባ በመቶ ተመላሽ ሆነ እንጂ፡፡ ተሳታፊ ሰዓሊያንና ተቋማት ብቁ ሀሳብ ይዘው አልመጡም እንጂ፡፡ የሚ/ር መ/ቤቱ ባለስልጣናት ሲገኙ፣ትርዒቱ የተመልካች ድርቅ መታው እንጂ (በኢትዮጵያ ባህል ማዕከል (ስብሰባ ማዕከል) ነበር የተዘጋጀው፡፡)
የዘንድሮውና ሶስተኛው የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል ደግሞ ይበልጥ ግራ የገባው፣የተደናበረ አቅጣጫውን የሳተ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ ፌስቲቫል ያስተናገደውንና በሶስቱ ፌስቲቫሎች የተስተዋሉ ቁልቁለቶችን በመዘርዘር ትችቴን አጠናቅቃለሁ፡፡
የፌስቲቫሉ ቁልቁለቶች
የወጥነት ጉድለት፡- የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሥነ-ጥበብ ፌስቲቫል ሶስቱንም ጊዜ መልክ የሌለው፣ የተዘባረቀ፣መያዣ የጠፋውና ቅርጽ አልባነቱን ያሳየ ፌስቲቫል ሲሆን በዚሁ ለአራተኛና ከዚያም ለዘለለ ጊዜ ከቀጠለ ይህ አሜባዊ ቅርፅ-አልባነቱ ወደ ሙሉ ጥፋትነት ይቀየራል ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህ ወጥ ቅርፅ (FORMAT) ይዞ መምጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ስኬታማ ፌስቲቫሎች ይህን ነው ሚያደርጉት፡፡
ቅንድብ እንኳ መሆን አለመቻል፡- ለሶስተኛ ጊዜ የተደገሰ፣ “የኢትዮጵያ” የሚል ትልቅ መጠሪያ ያነገበ፣ በማህበር ኃላፊነትም ሆነ በማህበሩ የበላይ ጠባቂነት በሙያቸው ከበቂ በላይ ልምድ ኖሯቸው እየሰሩ ያሉና እየጠበቁ ያሉ ሠዓሊያንና ሙያተኞችን በስሩ ካቀፈ፣ በሚኒስቴር መ/ቤት ድጋፍ ካለውና… ሌሎች አቅሞችን ማዳበር ከሚችል ፌስቲቫልነቱ አንፃር ሲታይ እንኳን ዓይን ይቅርና ቅንድብ መሆነ አለመቻሉ የፌስቲቫሉ ሌላኛው ቁልቁለት ነው፡፡
3- የተመልካች ትኩረት፡-ፌስቲቫሉ እንደ አብዛኛዎቹ የሃገራችን የሥነ-ጥበብ ተቋማት ሁሉ በእርግጠኝነት ሊገነባ የሚሻው የተመልካች አይነት ላይ ትኩረት አላደረገም፡፡ “የኢትዮጵያ” ይላል፡፡ ትኩረቱ የኢትዮጵያ ህዘብ ላይ ነው? የአዲስ አበባ? የሥነ-ጥበብ ማህበረሰቡ? ተማሪው? ወጣቱ? ነጋዴው? የትኛውም ላይ ትኩረት ያለው አይመስልም፡፡ ለህዝቡ ማድረስም ጉዳዩ አይመስልም፡፡ “ጥበብ ለሁሉም!” በሚል መሪ ቃል ነው ሶስቱም ጊዜ የተከወነው፡፡ ጥበብ ለሁሉም ምን ይሁን? ብለን ስንጠይቅ ግን “አይድረስ! ፤ ለሁሉም ቢደርስም ባይደርስም መከወኑ አይቀርም … ዘንድሮ 3ኛው ነው እሺ!” የሚሉና ወዘተ ምላሾችን የሚሰጥ የሚመስል የተመልካች ትኩረቱን ያልወሰነ ቁልቁለትም እየወረደ ነው፡፡
ተሳታፊያንና የስራዎቻቸው ውክልና፡- የትኛው የኢትዮጵያ ሠዓሊያንን ትውልድ ወይም የአሰራር ዘዬ ወይ የኪነ-ቁስ አይነት መሰረት በማድረግ ነው ፌስቲቫሉ ተሳታፊያንና ስራዎቻቸውን የሚመርጠው? ወጥ ወይም ግልፅ  የሆነ ቅርፅ የለውም፡፡ ወሰኑን የማበጀት ግዴታ ባይኖርበትም መግለፅና መተንተን ቢችል ግን የተሻለ ስራ ይሰራል፡፡ “የኢትዮጵያ” … እየተባለ በተሳታፊያንና በስራዎቻቸው የምትወከል ኢትዮጵያ አለመኖሯ .. ይህች ኢትዮጵያ በፌስቲቫሉ የመንፈስነት (ghost’ነት) ቦታ እንኳ እንደሌላት ያሳየናል፡፡
 ቸልታዎች፡- ሚንስትር መ/ቤቱ የፌስቲቫሉን አቋምም ሆነ አካሄድ ልብ ያለው አይመስለኝም፡፡ ወይም ረክቶበታል፡፡ አሊያም ምንም ይሁን ምን  … ዝም ብሎ መኖሩና መካሄዱ ብቻ ይበቃል የሚል ይመስላል፡፡ ከዘንድሮ መጪው ዓመት ይሻላል እያለ ሊሆን ይችላል፡፡ ከኢትዮጵያ ግብር ከፋይ ዜጎች ከሚሰበሰብ ገንዘብ ተቀንሶ እንዲሁም መንግስት ተበድሮና ተለቅቶ ከሚያመጣው ዓመታዊ በጀት ተቆንጥሮ በሚለቀቅ ፈሰስ የሚከወነው ፌስቲቫል፤ በመንግስት ሊቸረው ከሚገባው ትኩረት አንፃር ገና አፍላ ለሆነው የሥነ-ጥበብ ዘርፍ ፌስቲቫሉ ሊፈጥር የሚችለውን አቅም ሚኒስቴር መ/ቤቱ (እንደ ዋና የሥራ ሂደቱነት ማህበሩ)፣ ተሳታፊ ሰዓልያንና የሥነ- ጥበብ ተቋማት፣ ኢ-ተሳታፊ ሠዓሊያንና ተቋማት፣ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎችና አድናቂዎች እንዲሁም ሌሎች
ታዛቢያን (መቼም ታዛቢ አይጠፋም) ያሳዩት፣ እያሳዩ ያሉትና ወደ ፊት ሊያሳዩ የሚችሉት ቸልታዎች ፌስቲቫሉን ከቁልቁለት ወደ አዘቅት ሊጨምሩት ይችላሉ፡፡
ፌስቲቫሉ በአግባቡ ከተሰራበት ሊፈጥር የሚችለውን አቅም የሚጠረጠር ያለ አይመስለኝም፡፡ ለአብነት አንድ  ምሳሌ ልጥቀስ፡፡
ከ2000- አሁን -አዲስ ፎቶ ፌስት፡- ደስታ ፎር አፍሪካ (DFA Plc) በዋነኝነትም በፌስቲቫሉ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ፣በፎቶግራፈር አይዳ ሙሉነህ አማካኝነት የሚካሄደው አዲስ ፎቶ ፌስት መመለስ የሚገባው ጥያቄዎች ቢኖሩትም በስኬት እየተጓዘና በአንድ ግለሰብ ማለትም በአይዳ ሙሉነህ ጉንዳናዊ ትጋትና እልህ አስጨራሽ ጥረቶች እየተካሄደ ይገኛል፡፡ ዘመንኛ የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብም በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ብቅ እንዲል ምክንያት የሆነ ፌስቲቫልም ነው፡፡ ዋቢ ባይሆንም መማሪያ ይሆናል፡፡
በ1987 ዓ.ም አዲስ አበባን የነቀነቀ፣ ሥነ-ጥበባችንን ያነቃቃ አንድ ፌስቲቫል ተካሄዷል፡፡ ለጊዜው ዝርዝር መረጃው የለኝም፡፡ ጥናት ቢደረግበት ግን አብነት መሆን የሚችል ፌስቲቫል ነበር፡፡
ጥቂት ስለ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር፡
በ25 አባላት በበጎ አድራጎትና ማህበራት ማደራጃ ኤጀንሲ አዋጅ መሰረት፤ ግንቦት 2003 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ አባላት አሉት፡፡ ሲያደርጋቸው ከቆዩ አንቅስቃሴዎች መሃል የተለያዩ የፓናል ውይይቶችን ማዘጋጀት፤ በአዳማ፣በመቀሌና በሐዋሳ መሰል ማህበራትን ማቋቋም፤ ለአባል ሠዓልያን ድጋፍ መስጠት  ለስራዎችቸው የመሸጫ መድረኮች ማመቻቸት፣የድጋፍ ደብዳቤ መፃፍ፤ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጥበባዊ ደጀን እንዲኖረው፣በተለያዩ ጊዜያት ሠዓሊያንን ወደ ቦታው መውሰድ፤ ከጉብኝታቸው መልስ የተሰማቸውን እንዲስሉና የሣሉትን ሥዕል ለዕይታ ማቅረብ-----ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ማህበሩ ህፀፅ በሞላው መልኩ ከፈፀማቸው ወይም ከሚፈፅማቸው እንቅስቃሴዎች መሃል ይህ ዓመታዊ ፌስቲቫል እንዲሁም በቦሌ መንገድ አፍሪካ ጎዳና ላይ ባሉ የመንገድ አካፋይ የሲሚንቶ ግድግዳዎች ላይ አንድ ሥነ-ጥበብን በሀገር ደረጃ ለማንቀሳቀስ ከተመሰረተ ማህበር በማይጠበቅ፣ ሃላፊነት በጎደለው መልኩ ገና ካሁኑ በወራት ውስጥ ቀለሙ እየተፈገፈገ የመጣው፣የዕይታ ብክለት ያስከተለ፤ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንን ሙያዊ ብቃት ጥላሸት የሚቀባ፣ የህዝብ ቦታንና በቦታው የሚተላለፈውን መንገደኛ እይታ የሚበክል----ቀለም መቀባት አይሉት ሥዕል መስራት ሊገለፅ የማይችል ተግባር ማከናወኑ ሌላኛው ህጸጹ ነው፡፡ በእርግጠኝነት ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ!
ቸር እንሰንብት !