Administrator

Administrator

አብደላ እዝራ ከአባቱ ከአቶ መሐመድ ሳልህ አልአረግስኢ እና ከእናቱ ወ/ሮ መሪሃም በ1950 ዓ.ም በአዲስ አበባ፣መርካቶ አንዋር መስጊድ አካባቢ ተወለደ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከ1ኛ-6ኛ ክፍል በአፍሪካ አንድነት ትምህርት ቤት የተከታተለ ሲሆን 7ኛ እና 8ኛን በልዑል ወሰን ሰገድ ትምህርት ቤት፣የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ተምሯል፡፡ ወደ የመን፣ ሰንዓ በመጓዝም  የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርቱን አጠናቋል፡፡ እዚያው የመን ውስጥ በየመኒ ኤርዌይስ ተቀጥሮም ጡረታ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ሠርቷል፡፡
አብደላ አብላጫውን የሕይወት ዘመኑን በሥነጽሑፍ ሥራዎች ላይ ጥናትና ምርምር በማድረግ ያሳለፈ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላም የበርካታ ገጣምያንና ደራስያን ሥራዎችን በሂሳዊ ብዕሩ ጎብኝቷል፡፡ ሃያሲው ቀደም ባሉት ዓመታት በ“አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦች እንዲሁም የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) በሚያዘጋጀው “ብሌን” መጽሔት ላይ ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየበት ጊዜ ድረስ ደግሞ በ“አዲስ አድማስ” ጋዜጣ ላይ ጥልቅ የሥነጽሁፍ ትንታኔዎቹን አቅርቧል፡፡ አንጋፋው ሃያሲ ሥራዎቻቸውን በጥበባዊ ሂስ ከተነተነላቸው ዕውቅና ድንቅ ደራሲያን መካከል በዓሉ ግርማ፣ ደበበ ሰይፉ፣ ሲሳይ ንጉሡ፣ አዳም ረታ፣ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ነቢይ መኰንን፣ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ አበራ ለማ፣ ኤፍሬም ሥዩም፣ ደምሰው መርሻና በድሉ ዋቅጅራ ይጠቀሳሉ፡፡  
 አብደላ እዝራ ድንገት ባደረበት ሕመም፣ለአጭር ጊዜ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 27 ቀን 2008 ዓ.ም ከቀኑ10፡30፣ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ በነጋታው እሁድ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቂት ሰዎች በተገኙበት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡  

    ለዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሱትና ወደ ዋይት ሃውስ የሚያቀናውን የፍጻሜ ጉዞ የጀመሩት ሁለቱ ዕጩ ተፋላሚዎች ታውቀዋል - ሄላሪ ክሊንተንና አወዛጋቢው ዶናልድ ትራምፕ፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ሪፐብሊካኑን ወክለው እንደሚወዳደሩ ካረጋገጡ ሰንበትበት ቢሉም፣ ዲሞክራቷ ሄላሪ ግን ገና ባለፈው ማክሰኞ ነበር ፓርቲያቸውን ወክለው የሚወዳደሩ የመጀመሪያዋ ሴት ዕጩ መሆናቸውን ያረጋገጡት፡፡
ይሄን ተከትሎ የአሜሪካ ዝነኞች ከሁለቱ ዕጩዎች ለማን ድምጻቸውን እንደሚሰጡ አበክረው ማስታወቅ ጀምረዋል፡፡
የእንግሊዙ “ሚረር” ጋዜጣ የአሜሪካ ዝነኞች በየማህበራዊ ድረገጹና በየአጋጣሚው ማንን እንደሚደግፉ ያስተላለፉትን መልዕክት አሰባስቦ፣ ከትናንት በስቲያ ለንባብ አብቅቶ ነበር፡፡
ታዋቂዋ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ ባለፈው ማክሰኞ በማህበራዊ ድረገጽ በኩል ባስተላለፈቺው መልዕክት፤ በመጪው ምርጫ ለሄላሪ ክሊንተን ድምጽ እንደምትሰጥ የገለጸች ሲሆን፣ 17 ሚሊዮን ለሚደርሱ የማህበራዊ ድረገጽ ተከታዮቿም፣ ለውጥ ከፈለጋችሁ ሄላሪን ምረጡ ስትል ጥሪ አቅርባለች፡፡ ዝነኛው የሆሊውድ አክተር ጆርጅ ክሉኒም፣ ሰሞኑን በድረገጹ ላይ ባተመው ይፋ ደብዳቤ ለሄላሪ ክሊንተን ያለውን ድጋፍ ገልጾ፣ “ይሄ ትራምፕ የሚባል ሰው አገራችንን መቀመቅ ሊከት ያኮበኮበ ሰው ነውና ድምጻችሁን በመንፈግ ክንፉን ስበሩት” ሲል ለአድናቂዎቹ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ ጆርጅ ክሉኒ ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይም፣ ከባለቤቱ ጋር በመተባበር ለሄላሪ ክሊንተን የምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ሲያሰባስብ መክረሙ ተገልጿል፡፡
ሄላሪን እንደሚደግፉ በይፋ ካስታወቁ ዝነኞች ሌላኛዋ፣ ታዋቂዋ ክርስቲና አጉሌራ ናት፡፡ ይህቺው ዝነኛ አርቲስት በትዊተር ገጽ ላይ ባስተላለፈቺው መልዕክት፣ ሄላሪን በመደገፏ ታላቅ ክብር እንደሚሰማት ገልጻለች፡፡ “ሄላሪ ክሊንተን ታሪክ የሰራቸው ለራሷ ብቻ አይደለም፤ በመላ አለም ለሚገኙ ሴቶች እንጂ!...” ስትልም፣ ለዲሞክራቷ ዕጩ ለሄላሪ ያላትን ክብር ገልጻለች፡፡ ለሄላሪ የገቢ ማሰባሰቢያ ታስቦ ባለፈው ሰኞ ምሽት፣ በካሊፎርኒያ በተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ላይም፣ ሪኪ ማርቲን፣ ክርስቲና አጉሌራ፣ ጆን ሌጀንድና ስቲቪ ዎንደርን የመሳሰሉ ድንቅ ድምጻውያን ስራዎቻቸውን በማቅረብ ለሴትዮዋ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል፡፡ ሄላሪ በዝነኞች ስትከበብ፣ አነጋጋሪው ትራምፕ ግን፣ እምብዛም የዝነኞችን ቀልብ አልሳቡም፡፡
ከትራምፕ ጎን ቀድሞ የቆመው ታይሰን ነው፡፡ የዓለም የከባድ ሚዛን ሻምፒዮኑ ማይክ ታይሰን፣ ለአገሬ የሚበጃት ሁነኛ መሪ ዶናልድ ትራምፕ ነው ባይ ነው፡፡
“ዶናልድ ትራምፕን እወደዋለሁ!... ዶናልድ በስደተኞች ላይ የያዘው አቋም ዘረኛ ነው ያስብለዋል ብዬ አላምንም” ያለው ታይሰን፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆን ያለበት ትክክለኛው ሰው እሱ ነው!...” ሲል አቋሙን በግልጽ አንጸባርቋል፣ ሰሞኑን ከሃፊንግተን ፖስት ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፡፡
ቫንዳምም የትራምፕ ደጋፊ ነው፡፡ ዝነኛው የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ ዣን ክላውድ ቫንዳም፣ “ሌ ግራንድ” ለተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ፤ ዶናልድ ትራምፕን እንደሚደግፍ ተናግሯል፡፡
“ትራምፕ ቢመረጥ የአሜሪካን ኢኮኖሚ የሚያሻሽል ስርዓት ይፈጥራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ጎበዝ የቢዝነስ ሰው ነው...” ያለው ቫንዳም፣ ትራምፕን እንደሚደግፍ ቢገልጽም፣ በምርጫው አያሸንፍም ብሎ እንደሚያምን አልሸሸገም፡፡ ዝነኛው የካንትሪ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኬኒ ሮጀርስም ለትራምፕ ያለውን አድናቆት ገልጿል፡፡
“ሰውዬውን በጣም ነው የምወደው!... የሚናገራቸውን ነገሮች እወድለታለሁ፡፡ ሌሎች ሰዎች ለመናገር የማይደፍሯቸውን ነገሮች፣ እሱ ያለምንም ይሉኝታ ፍርጥርጥ አድርጎ ያወራቸዋል፡፡ እርግጥ ይህን ማድረጉ ትክክል ይሁን አይሁን አላውቅም!...” ብሏል የ77 አመቱ አቀንቃኝ ኬኒ ሮጀርስ፡፡ ታዋቂዋ የሆሊውድ ተዋናይት ክርስቲ አሊም፣ እንደ ኬኒ ሮጀርስ ሁሉ፣ ለትራምፕ ያላትን ድጋፍ ገልፃለች፡፡


አሜሪካ በርካታ ሃያላን ሴቶችን በማስመዝገብ ከአለማችን ቀዳሚ ሆናለች


በየተሰማሩበት መስክ የላቀ ተሰሚነትን ያገኙ የአለማችንን 100 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ ሰሞኑን ባወጣው የ2016 ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የጀርመን መራሄ መንግስት አንጌላ መርኬልን ለስድስተኛ ጊዜ በቀዳሚነት አስቀምጧል፡፡
በፎርብስ አመታዊ ዝርዝር ውስጥ ላለፉት አምስት አመታት የዓለማችን ሃያል ሴት ሆነው የዘለቁትን አንጌላ መርኬልን በመከተል እንደ አምናው ሁሉ ዘንድሮም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት፣ በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፉክክር ላይ የሚገኙት ሂላሪ ክሊንተን ናቸው፡፡
የአሜሪካ የፌደራል ሪዘርቭ ሊቀመንበር ጃኔት ያለን ሶስተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ በጎ አድራጊዋ ሚሊንዳ ጌትስና የጄነራል ሞተርስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሜሪ ባራ በአራተኛና አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲያን ላጋርድ፣ የፌስቡኳ ሼሪል ሳንበርግ፣ የዩቲዩቧ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱዛን ዎጅኪኪ፣ የኤህፒ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሜግ ዊትማንና ባንኮን ሳንታንደር የተባለው ድርጅት ሊቀመንበር አና ፓትሪሺያ ቦቲን እንደ ቅደም ተከተላቸው እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ 100 የአመቱ የዓለማችን ሀያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሴቶች መካከል 26 ያህሉ የፖለቲካ መሪዎች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከአፍሪካ ፖለቲከኛ ሴቶች መካከልም የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍና የሞሪሽየስ ፕሬዚደንት አሚና ጉሪብ ፋኪም በዝርዝሩ ተካትተዋል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱት ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሴት ናይጀሪያዊቷ ባለሃብት ፎሎሩንሽኮ ኣላኪጃ ናቸው፡፡
አሜሪካ በርካታ ሴቶችን በሃያላኑ ዝርዝር ውስጥ በማስገባት ከአለማችን አገራት ቀዳሚቱን እንደያዘች የታወቀ ሲሆን 100 የተለያዩ አገራት ፖለቲከኞችን፣ የኩባንያ ስራ አመራሮችን፣ በጎ አድራጊዎችን፣ ስራ ፈጣሪዎችንና ሳይንቲስቶችን ባካተተው በዘንድሮው የፎርብስ ሃያላን ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት አሜሪካውያን ሴቶች 51 መሆናቸው ተነግሯል፡፡

የኤርትራ መንግስት የተመድን ሪፖርት አጣጥሎታል

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ኮሚሽን፣ የኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት በዜጎቻቸው ላይ ለሩብ ክፍለ ዘመን በፈጸሙት የማሰር፣ የማሰቃየት፣ የመግደል፣ የአስገድዶ መድፈርና የመሳሰሉ ኢ-ሰብዓዊ የወንጀል ድርጊቶች በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርበው ሊጠየቁ ይገባል ማለቱንና፤ የጸጥታው ምክር ቤትም በአገሪቱ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል መጠየቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የኤርትራ መንግስት በበኩሉ፤ የተመድን ሪፖርት ፖለቲካዊና መሰረት የለሽ ነው ሲል በመተቸት፣ መሰል ውንጀላዎች በኤርትራ ላይ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍሪካ ላይ የሚቃጡ ጥቃቶች ናቸው ብሏል።
አገሪቱ ነጻነቷን ከተጎናጸፈችበት ጊዜ አንስቶ መሪዎቿ በዜጎች ላይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን ባለፈው ረቡዕ የገለጸው ኮሚሽኑ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው ጠቁሞ፣ በምርመራው ያገኘውን ውጤት ለአለማቀፉ ፍርድ ቤት ማስተላለፉንም አስታውቋል፡፡ ባለፉት 25 አመታት 400 ሺህ ያህል የአገሪቱ ዜጎች በወታደራዊ ግዳጅና በመሳሰሉት የግዳጅ ተልዕኮዎች የባርነት ህይወትን ሲገፉ ቆይተዋል ያለው መርማሪ ቡድኑ፣ በአገዛዙ ተማርረው ከአገሪቱ ለመውጣት የሚሞክሩ በርካታ ዜጎችም በአገሪቱ መንግስት የድንበር ጠባቂዎች እንደሚገደሉ አስታውቋል፡፡
በየወሩ በአማካይ 5 ሺህ ኤርትራውያን በአገዛዙ ተማርረው አገራቸውን ጥለው ይሰደዳሉ ያለው ኮሚሽኑ፤ዜጎችን በኢ-ሰብዓዊ መንገድ የሚያሰቃዩት እነዚህ ከፍተኛ ባለስልጣናት አለማቀፍ ህጎችን በመጣስ በሰሩት ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው ጠቁሞ፣ በአገሪቱ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቋል፡፡
የኤርትራ ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምርመራ ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት መሰረተ ቢስና ምንም አይነት ማስረጃ የሌለው መሆኑን በመጥቀስ፣ መንግስታቸው ሪፖርቱን እንደሚያወግዘው አስታውቀዋል፡፡
ኮሚሽኑ በኤርትራ ላይ አደረግሁት የሚለው የጥናት ሪፖርት፣  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጥናት መርሆችን ያላከበረና ሙያዊነት የጎደለው ነው ያሉት አቶ የማነ፤አገሪቱ ነጻነቷን ከተጎናጸፈችበት ጊዜ አንስቶ የተመዘገቡ መልካም ለውጦችን ለማካተት ያልደፈረና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡

   ለዘንድሮ “የበጎ ሰው” ሽልማት በ10 ዘርፎች ህብረተሰቡ እጩዎች እንዲጠቁም ተጠየቀ፡፡ በመምህርነት፣ በሳይንስ፣ በድርሰት፣ በማህበራዊ ጥናት፣ መንግስታዊ የስራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት፣ በቅርስና ባህል፣ በስፖርት፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት፣ በበጎ አድራጎትና በንግድና ፈጠራ ዘርፎች ለሀገራቸው ጠቃሚ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ የህዝቡን ህይወት የሚለውጥ የተሻለ ውጤት አምጥተዋል የሚላቸውን ሰዎች ህዝቡ እንዲጠቁም የሽልማቱ አዘጋጆች ጠይቀዋል፡፡
እስከ ሰኔ 24 ድረስ በስልክ ቁጥር 0915 44 55 55 ወይም በኢሜል This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. አሊያም በአካል አዲስ አበባ ለም ሆቴል አካባቢ ማቲያስ ህንፃ ቢሮ ቁጥር 408 ድረስ በመቅረብ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻል አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የሽልማት ስነ ስርአቱ ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በደማቅ ስነ ስርዓት ይከናወናል ተብሏል፡፡

ለ3 ሺህ 100 ዲያስፖራዎች የሸጠው ቦንድ ህገ-ወጥ ነው ተብሏል
መንግስት ጥፋቱን አምኖ ገንዘቡን ለመክፈል ተስማምቷል

የኢትዮጵያ መንግስት ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ በማቀድ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያደረገው የቦንድ ሽያጭ የአሜሪካ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ በመሆኑና ህገወጥ መሆኑ በመረጋገጡ፣ ከሽያጩ ያሰባሰበውን 5.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጨምሮ በድምሩ 6.5 ቢሊዮን ዶላር መልሶ እንዲከፍል ተወሰነበት፡፡
የአሜሪካ የቦንድ ሽያጭና ግዢ የሚቆጣጠረው ሴኪዩሪቲስ ኤንድ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን የተባለ ተቋም ከትናንት በስቲያ እንዳስታወቀው፣ የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2014 ባሉት አመታት የአሜሪካ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ፣ በአገሪቱ ለሚኖሩ ከ3 ሺህ 100 በላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባከናወነው ያልተመዘገበ የቦንድ ሽያጭ፣ የሰበሰበውን 5.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እና 601 ሺህ የአሜሪካ ዶላር የወለድ ገንዘብ መልሶ እንዲከፍል ውሳኔ ተላልፎበታል፡፡
ተገቢውን ምዝገባ ሳያሟላ በአሜሪካ ዋና ዋና ከተሞች የባለሃብቶች ስብሰባዎችን በማካሄድ፣ የቦንድ ሽያጭ ማስታወቂያዎችን በኢምባሲው ድረ ገጽ፣ በሬዲዮና በቴሌቪዥን በማስተላለፍና ሽያጩን በማከናወን ህገወጥ ተግባር ፈጽሟል የተባለው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት በበኩሉ የፈጠመውን ጥፋት በማመን፣ የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲመልስ የተላለፈበትን ውሳኔ ተቀብሎ ለመክፈል መስማማቱንም ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ መንግስት ቦንድ የገዙ የዲያስፖራ ባለሃብቶች ያወጡትን ገንዘብ ከነወለዱና ከነካሳው እንደሚያገኙም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ከ8 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ በወይን ጠመቃ የተሰማራው ካስትል የወይን ጠጅ ፋብሪካ፣ ከነጭና ቀይ ወይን በተጨማሪ “ሮዜ” የተሰኘ አዲስ የወይን ጠጅ ለገበያ አቀረበ፡፡  
በወይን ጠመቃ አለማቀፍ እውቅና ያለው የፈረንሳውያኑ ካስትል ቤተሰቦች ወይን አምራች ኩባንያ በኢትዮጵያ ያለውን የወይን ጠጅ ገበያ ድርሻ እያሰፋ መሆኑን የገለጸ ሲሆን በዓመት ከ1.4 ሚ. ጠርሙስ በላይ ወይን ለገበያ እያቀረበ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ አዲሱ “ሮዜ” የተሰኘው ምርቱ በኢትዮጵያ የወይን ወዳጆች በስፋት ከሚታወቁት “ነጭ” እና “ቀይ” ወይን የተለየ አዲስ የፈጠራ ምርት ነው ተብሏል፡፡ ይሄም ፈጠራ ካስትልን ብቸኛ ያደርገዋል፡፡
በተጨማሪም ኩባንያው በቀላል ዋጋ ተጠቃሚዎች ሊያገኟቸው የሚችሉ የካርቶን ወይኖችን  ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆኑን የኩባንያው የማርኬቲንግና ሽያጭ ማናጀር ወ/ት አለም ፀሐይ በቀለ ገልፀዋል፡፡ የወይን ፋብሪካው አሁን ካለው 162 ሄክታር የወይን እርሻ በተጨማሪ 85 ሄክታር የማስፋፊያ ስራ እየሰራ መሆኑን ወ/ት አለምፀሐይ አስረድተዋል፡፡
የካስትል ወይኖች ለምን ዋጋቸው ተወደደ ተብለው የተጠየቁት ሃላፊዋ ሲመልሱ፤ነጋዴዎች ፋብሪካው ከተመነው ዋጋ በላይ ከ100--200 ፐርሰንት ጭማሪ እያደረጉ ስለሚሸጡ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያው ስለ ወይን ጠጅ አይነቶች ለመስተንግዶ ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡  

የትርዒቱ ርዕስ፡ የአዲሳባ ልጅ
    ሠዓሊ፡ መዝገቡ ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር)
      የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡ ሃያ ስራዎች
      የቀረበበት ቦታ፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ፡ አዲስ አበባ
     ጊዜ፡ ግንቦት 05-ሰኔ 03: 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)
እንደ መሻገሪያ
ይህ ዳሰሳና ትችት ‘ወቅቱን ያልጠበቀ’ ወይም ‘ያለፈበት’ ሊባል ይችላል፡፡ ምክንያት? ትርዒቱ የዕይታ ጊዜው አልፎበታል፡፡ ሆኖም፡ ’የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘው የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የሥዕል ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ በተለይም በያዝነው ዓመት ከቀረቡ የሥዕል ትርዒቶች መሃከል በይዘትም ሆነ በቅርጽ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ የዕይታ ጊዜው ቢያልፍበትም ባያልፍበትም ለመዳሰስና ሂስ ለመስጠት አይነተኛ ነው፡፡ እንቀጥል?
1. ‘ቢስ!’ ፡ ‘ይደገም!’  
ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ፤ የዛሬ ሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ ‘ንግስ’ በሚል ስያሜ በብሔራዊ ሙዝየም፡ ጊዜያዊ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ ለዕይታ ያቀረበው ትርዒት በዘመንኛው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ታሪክ የሠዓሊውንም ሆነ የትርዒቱን ልዩ አሻራ ትቶ ያለፈ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እውነታን ከምጡቅ ምናብ አሰናኝቶ በተለይም ሠዓሊው ከልጅነት እስከ እውቀት፣ በእዝነ-ልቦናው ግዘፍ ነስተው የተቀመጡ የተፈጥሮና የመልክዓ ምድር ቅርጾችን፣ ለዕይታችን እጅግ ገዝፈውና እጅግ ደቅቀው የሚገኙ አካላት ከሰው ልጅና እንስሳት አንጻር፣ የሶስት አውታረ መጠንነትን  በሁለት አውታረ መጠን ሥዕል መተግበር መቻሉን በስራዎቹ አሳይቶ ነበር። ታዲያ ይህ ትርዒት  ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ የሚል ጥያቄ ከተመልካች እንደቀረበለት ይነገራል፡፡ ‘ንግስ’ ታላቅ ነበረና ጥያቄው መቅረቡ የሚያስገርም አይመስለኝም! የአቅም ጉዳይ ሆኖ እንጂ በሙዝየሙ ብቻ ሳይሆን ‘ንግስ’ በመላው ሃገሪቱም ተዟዙሮ መታየት ነበረበት፡፡ አሊያም አሁንም የአቅም ጉዳይ ሆኖ ይመስለኛል እንጂ የ’ንግስ’ ትርዒት ሙሉ በሙሉ በሙዝየሙ ቋሚ ስብስብ መካተት ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ምናልባት ወደፊት ይሆናል፡፡ የ’ንግስ’ የ’ይደገም!’ ጥያቄ እውነት ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆንም ረዳት ፕሮፌሰር መዝገቡ ተሰማ  ባሳለፍነው ወር ‘የአዲሳባ ልጅ’ የተሰኘ ሰፊ የተመልካች ዓይነት፡ እጅግ በርካታ ምናልባትም በጎብኚዎች ቁጥር ከፍተኛ የሆነ፡ የተመልካቹን ቀልብና ተመስጦ የገዛ ትርዒት ለሕዝብ ዕይታ አቅርቦ ነበር፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’፤ የ’ንግስ’ ‘ቢስ!’ ወይም ‘ይደገም!’ ከሆነ ምክንያታዊ መሰረቱ በ’የአዲሳባ ልጅ’ ትርዒት ከቀረቡት ስራዎች ጋር ይጣረሳል፡፡ ‘ቢስ!’ ካልሆነና ራሱን ችሎ የቀረበ ከሆነም ቀጥሎ የማቀርበው ነጥብ ይጎድለዋል፡፡
2. ‘የአዲሳባ ልጅ’ ፡ የትርዒቱ ማንነት(The Identity of the Exhibition)
የትርዒት ማንነትና ምንነት የሚገለጸው ባካተታቸው የስራዎች የአሳሳል ዘዬ(style)፣ ይዘት (content)፣ ቅርጽ (form)፣ ዓይነ-ግብ (subject matter)፣ አቀራረብ (presentation)  እንዲሁም እኒህ ሁሉ ሲጣመሩ የሚሰጡት የትርዒቱ አንድምታዎች ነው። ከነዚህ አኳያም ‘የአዲሳባ ልጅ’ የራሱ የሆነ የትርዒት ማንነቱን የተሟላ ለማድረግ እምብዛም የተጨነቀ አይመስልም። እያንዳንዱን የትርዒቱ አናስራት(elements) ነጥለን ስንመለከት የጎደለው ነገር እንዳለ አይሰማንም፡፡ በዚህ ረገድ ከሠዓሊው የዳበረ ልምድ፡ ከገነባው ሥነ-ጥበባዊ ግለሰባዊነትና ከዘለቀበት ከፍታ አንጻር እንዲያው በደፈናው (by default) የሚጠበቅ ነው፡፡ በርግጥም ምሉዕ ሥነ-ጥበባዊ ሰብዕናውን በእያንዳንዱ ስራው ላይ እናያለን፡፡ ሆኖም፡ አንድ ትርዒት የመታያ ጊዜው ካበቃ በኋላ በተመልካቹም ሆነ በሠዓሊው እዝነ-ልቦና የሚቀረው ትርዒቱ ትቶለት ያለፈው ወጥ ምስልና እሳቤ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግን ‘የአዲሳባ ልጅ’ ጠንካራና ሁለንተናዊ ምስል እንዲሁም የተገራ የትኩረት አቅጣጫ ትቶልን ያለፈ ትርዒት እንዳልነበረ ምክንያቶቼን በመደርደር እተቸዋለሁ። ጠንከር ያለ ትችት ማቅረብ ከማይቻልበት አንደኛው ነጥብ ብጀምር፣ ‘ከብርሃን ተቃራኒ’ የተሰኘው ስራው በዘዬ፣ በይዘትና በዓይነ-ግብ ከሌሎች ተነጥሎ ለብቻው የሚታይ እንጂ በአንድ ትርዒት ለመቅረብ አጥጋቢ ምክንያት የለውም። በእርግጥ ይህ የብርሃንን አቅጣጫ ለማጥናትና ሌሎች ስራዎቹ ላይ የሚጠቀምበትን ቴክኒክ ማሳያ ሊሆነው ይችላል። ነገር ግን፡ ይህ ከስያሜም የሚልቅ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በሚል ርዕስ በቀረበ ትርዒት ውስጥ (እንደ ሟሟያ) መካተቱ ለትርዒቱ አውራ ትኩረት መነፈጉን ያሳያል፡፡
ለትርዒቱ ተብሎ በተዘጋጀው ካታሎግ ውስጥ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ስራዎቹን የሰራበትን መነሾዎችና መደንግጉን (artist statement) ከማቅረብ ይልቅ ትምህርታዊ ጽሁፍ ነው ያቀረበው፡፡ ሙሉ መብቱ የሠዓሊው ነው፡፡ ይህ አይነቱ አቀራረብ በራሱ ጥልቅ ምሁራዊ እይታና ምርምር ይጠይቃል፡፡ በመምህርነት የአንድ ትውልድ እድሜ የሚሆን ጊዜ በአዲስ አበባ  ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት ላሳለፈው ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ይህ የሚቻለው በመሆኑም ነው ያደረገው።  የመደንግጉ (artist statement) አለመኖር የሚያመላክተው ክፍተት ግን ለትርዒቱ ማንነትና ምንነት የሰጠው ቦታ አለመኖሩን ነው፡፡ በተለይ በይዘት ከሌሎቹ ስራዎች ጋር ለማይደጋገፉትና የትርዒቱን ስያሜ ለተሸከሙት ከቁጥር 1-3 ላሉት፣ ‘የአዲሳባ ልጅ’ ለተሰኙት ስራዎች ማብራሪያ እንኳን ባይሆን የዓይነ-ግብና የይዘት ለውጥ ያሳየበትን አመክንዮ ጠቆም አለማድረጉ፣ ትርዒቱን እንደ ትርዒት ማንነት የሚያሳጣው ነጥብ ነው፡፡ እነዚህ ስራዎች ከሌሎቹ ጋር ያላቸውን የሃሳብ ዝምድና ለማየት የሞከርን እንደሆነም ትርዒቱን አንድምታ ያሳጣዋል፡፡
ተመልካች ስለ ትርዒቱ ወጥ እሳቤ እንዳይኖረው ተደናቅፏል ባይ ነኝ፡ ይልቅስ በተለይ ዓይኑና የዕይታ ባሕሉ ያልሰለጠነው ተመልካች፤ እንደ ሠዓሊው ፍላጎት፣ ቅርጽና እይታዊ መስህብ እንዲሁም ‘የቀለም ቅብ ምትሃታዊ እንቅስቃሴ’ ላይ እንዲደመም ሆኗል፡፡ ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ፤ ስለ ስራዎቹ ከሥነ-ጥበብ ማኅበረሰቡና ከአድናቂዎቹ ጋር ባደረገው ውይይትም፤ ’የሥነ-ጥበብ እድገት ሊረጋገጥ የሚቻለው ለቅርጽ በሚሰጥ ትኩረት’ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ ሥነ-ጥበብን ከነባራዊው የሃገራችን ዓውድ አንጻር ስንመለከተው፣ ሰዓሊው የሚሞግተው ነጥብ አግባብነት ያለው ይሆናል።  ሠዓሊው የሚጠቀማቸው ዓይነ-ግቦች ቀጥተኛ መረዳት፡ ግንኙነትና እይታዊ መስህብ ሊፈጥርላቸው ለሚችልላቸው ተመልካቾች ወይም የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ ለስራዎቼ ይስማማልኛል ለሚላቸው የቅርጽ አትኩሮቶች አጽንኦት መስጠቱ ብልህነት ነው፡፡
ለይዘት ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለመስጠት አሁንም በሠዓሊው ፈቃድና ነጻነት ስር የሚያልፍ መሆኑን ሳልዘነጋ፤ ሥነ-ጥበብ ለምንኖረው ሕይወት የሰላ እይታ እንዲኖረን እሴት ከመጨመር አንጻር የሚኖረውን ፋይዳ እንደ ‘የአዲሳባ ልጅ’ የትርዒት አርዕስትነትና እንደ ሰዓሊ  መዝገቡ ተሰማ ባለ ታላቅ ሠዓሊነት ከመዳሰስም አልፎ፣ ረገጥ ተደርጎ መወያያ መሆን ነበረበት የሚል ነው አቋሜ፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ከትርዒት ማንነት ባሻገር የሥነ-ጥበብን ህላዌ እንድንፈትሽ ያስችለናል፡ ስለ ትርዒት ማንነትና ምንነት ማንሳት የፈለግኩትም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡
3. ‘የአዲሳባ ልጅ’ - ውይይት
በሃገራችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ በሥዕል ትርዒት ዙሪያ ውይይት ሲደረግ በጣት ከሚቆጠሩ ሰዎች ያውም ከከያንያኑ የዘለለ ተሳታፊዎችን ማየት ብርቅ ነገር ነው፡፡ ‘የአዲሳባ ልጅ’ በርካታ የሥነ-ጥበብ ቤተሰቦችን ያፈራ እንደነበር ውይይቱ ላይ የተገኙት ከሶስት መቶ በላይ ተሳታፊዎች የትርዒቱን ስኬታማነት ያመላክታሉ፡፡ ይሄ ያስደስታልም፡ ያኮራልም፡፡ የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ የግል ጥንካሬ በመሆኑም መመስገን ይገባዋል፡፡
በሥነ-ጥበብ ዙሪያ ትንታኔዎችን በማቅረብና የሥዕል መሳያ ቀለሞችን በሃገራችን በማምረት የሚታወቀው ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ፤ ስለ ትርዒቱ፡ ስለቀረቡት ስራዎች በተለይም ረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ  አሜሪካ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ስራዎቹ ስለመቀየራቸው ባቀረበው ጽሁፍ ነበር ውይይቱ የተጀመረው፡፡ ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ  ስለዚህ ጉዳይ አስተያየትም ሆነ ማብራሪያ አለመስጠቱ፣ተሳታፊው ራሱ ውሳኔ ላይ እንዲደርስ የፈቀደ ይመስላል፡፡ ሆኖም ይህ አይነቱ ገለጻ፤ ከሠዓሊው የአሰራር ልምድ፡ ሂደትና ለውጥ ጋር በቀጥታ የሚያያዝ በመሆኑ፣ የሠዓሊው አተያይ ይጠቅም ነበር ባይ ነኝ፡፡ ቀጥሎ ከመድረክ የቀረበው ጽሁፍ የጋዜጠኛ ይትባረክ ዋለልኝ ሲሆን የአቶ ሰለሞን ተሰማን ጥናታዊ ጽሁፍ መሰረት ያደረገና የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ  መዝገቡ ተሰማ’ን ስራዎች፣ሃገረሰባዊ ማንነት በማላበስ የሚያትት ነበር፡፡ ከታዳሚው ወደ ቀረቡ አስተያየቶች ስንመጣ፡  ሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ፤ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ባዳበረው አሳሳል ተከታዮች እያፈራ በመሆኑ ‘መዝገብኛ’ ተብሎ ሊሰየም የሚችል አሳሳል መምጣቱን በመጠቆም አስተያየት የሰጡ ሲሆን ከረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ የተሰጠ ምላሽ  አልነበረም፡፡
በሥነ-ጥበብ ታሪክ ግለሰቦችና ቡድኖች ያዳበሩትንና የሚከተሉትን ዘዬም ሆነ ፍልስፍና በManifesto አስደግፈው ያውጃሉ፡፡ የሥነ-ጥበብ ታሪክ አጥኚዎችና ተመራማሪዎችም ስለ ሠዓሊዎች ስራ፡ አሰራርና ፍልስፍናም ጥናትና ምርምር በማድረግ ስም ያወጡላቸዋል፡፡ የሠዓሊና መምህር እሸቱ ጥሩነህ ግላዊ አስተያየት፣ ምን ያህል በጥናት የተደገፈ እንደሆነ ባላውቅም ‘መዝገብኛ’ የሚለው ስያሜ አሁንም የረዳት ፕሮፌሰር ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ’ን ሥነ-ጥበባዊ ጉዞ መሰረት ያደረገ በመሆኑ፣ የሠዓሊው ይሁንታ ወይም አሉታ አሊያም ማብራሪያ ያስፈልግ ነበር ባይ ነኝ፡፡ ውይይቱ ካስተናገዳቸው አዝናኝ አስተያየቶች መሃከል ፤’ጥበብ በፍቅር ቃላት ብቻ ነው የምትዳብረው’ በሚል ከዚህ ውጪ ትችት አስፈላጊ እንዳልሆነ የሚሰብከው አስተያየት አንዱ ነበር፡፡ የፍቅር ቃላት ብቻ ሳይሆን ጥበብና ፍቅር የሚነጣጠሉ አይደሉም፡፡ ሆኖም፡ ያለ ትችትና ያለ ሂስ የሥነ-ጥበብ አካሄድ ሊቃና አይችልም፡፡ ቸር ይግጠመን!





Saturday, 11 June 2016 13:27

የውለታ ቀስተደመና

(ከአለማየሁ ገላጋይ “ኩርቢት” የተወሰደ)
አጣሁት፣ አጣሁት፣ እንጂ እንደ ችግሬስ ፈጣሪዬን ለሰላሳ ብር እሸጠው ነበር፡፡ ይሄን አድርጌው ቢሆን ይሄን ጊዜ እንደ ከንቱው ገበሬ “እንዲህ ልጠግብ በሬዬን አረድኩት” እል ነበር፡፡ ምክንያቱም ትናንት ሎተሪ እንደደረሰኝ አረጋግጫለሁና ነው፡፡
ግን ይሁዳ እግዚሃርን ለሰላሳ ብር ሲሸጥ የነበረበት ችግር ለምን አልተፃፈም? እንደኔ እርቦት የነበረ ቢሆንስ? እንደኔ ወይም ሚስቱ  ወልዳበት ቢሆንስ? እንደ እኔ እናቱ ታመውበት ቢሆንስ? እንደኔ ከሥራ ተባሮ ቢሆንስ? እሺ ያኔ ሥራ የለም ነበር እንበል፤ የሚያርስበት በሬ ገደል ገብቶበት እንደሆንስ? ይህን ሁሉ አራቱም ወንጌሎች አሟልተው አልገለጡም። እንዳውም ይሁዳን ያስመሰሉት ለመክዳት ሲል ብቻ መድኃኒዓለምን እንደሸጠው ነው፡፡ ከሐዲነት እኮ ያለ ገንዘብ አሳልፎ በመስጠትም ብቻ ይረካል፡፡ ታዲያ ሠላሳ ብሩ…
ኤዲያ! የኔ ነገር፡፡ የፈለኩትን ትቼ ሌላ ስዘበዝብ እገኛለሁ፡፡ ትናንት ሎተሪ ደረሰኝ፡፡
እስከ ዛሬ ከቤቴ አልወጣሁም፡፡
ኧረ እንዳውም ካልጋዬ አልወረድኩም፡፡
እንደ ሚስቴ የደስታ አራስ ሆኛለሁ፡፡ እንደ ሚስቴ ጨቅላውን ደስታ ታቅፌ፣ ያጋተ የምኞቴን ጡት አጠባዋለሁ፡፡ እንደ ሚስቴ ሁሉ ከዘመድ አዝማድ ለአራስ ጥሪ የመጣውን እየቀማመስኩ መጋደም፤ ጐጇችን የሁለት አራስ ቤት ሆኗል፡፡ ሚስቴ የታቀፈችው ጨቅላ የጋራችን ነው፡፡ የኔ ደስታ ግን የግሌ፤ አልነገርኳትማ!
ምነው አለመንገሬ? እኔን የመታኝ የደስታ ፍላፃ፣ እርሷ ላይ ቢያርፍ አትተረተርም፡፡ እርግጠኛ ነኝ እሁለት ትከፈላለች፡፡ ሎተሪ ሻጩን ጠርቼ፣ በሻካራ እጄ ሳሻሻት የምትመስጠኝን የሳምንት ወዳጄን ያቺን ሎተሪ ከማውጫው ጋር አመሳከርኩ፡፡ መጀመሪያ እግዚሃር ሲያላግጥብኝ መሰለኝ፡፡ መቼም መተከዣው አድርጐኛል…
ግን እውነት ነበር፡፡ ይሄን ላረጋግጥ አንድ ስል፣ ስሜት ከደመና በላይ ተወርውሮ የአናቴን እኩሌታ ከፍሎ፣ ወደ ልቤ በማድላት እየተረተረኝ ወረደና ሙሐሊቴን አቋርጦ አለፈ፡፡ አልፎም እንደ መብረቅ ክንድ መሬት ሰንጥቆ ገባ፡፡ ግራ አካሌና ቀኝ አካሌ ተፋትተው ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ በየፊናቸው የወደቁ መሰለኝ፡፡
ሎተሪውን ዳግም ያመሳከርኩት ማውጫውን ከሎተሪ ሻጩ ላይ በሃያ ሳንቲም ገዝቼ አልጋዬ ላይ ጋደም ብዬ ነበር፡፡ ጉደኛው ደስታ በተረጋጋ ስለት በለመደው አኳኋን ዳግም አካሌን ጐበኘው፡፡
እነሆ እስካሁን አልተነሣሁም፡፡
ደስታ ስለት ብቻ አይደለም፡፡ እንደ ማር ያለ ጣፋጭ ነው፡፡
ከመጠኑ ሲያልፍ ለሃጭ ያዝረበርባል፡፡
ተዝረበረብኩ፡፡
እንደ አራሷ ሚስቴ ወገብ ያልጠናው በራችን እየተልመጠመጠ ተከፍቶ እማማ አስላኩን አስተናገደ፡፡ ከገቡም በኋላ በራችን ልምጥምጡን ለሰላሳ ሴኮንድ ያህል መቀጠሉ አበሳጨኝ። እርግጥ ያበሳጨኝ በሩ ብቻ አልነበረም፡፡ የእማማ አስላኩ በትርና ጐድጓዳ ሰሃን ግራና ቀኝ እጆቻቸው ላይ ውለው፣ እኔ እቀድም እኔ እቀድም እየተፎካከሩ ሲመጡ አበሳጩኝ፡፡ ለወትሮው በትሩንም ባይሆን ጐድጓዳ ሰሃኑን እናፍቅ ነበር፡፡ ዛሬ ግን በውለታ ሥም እንጀራ ተሸክሞ የሚመጣው የእማማ አስላኩ ጐድጓዳ ሰሐን ከሎተሪው ብር ካልተሞላ እንደማይወጣ ሆኖ ተሰማኝ፡፡
“ጐድጓዳ ሰሐን ምግብ፣ በጐድጓዳ ሰሐን ብር!” መጮህ ከጀለኝ፡፡
“እንኪ እስቲ ይቺን ቅመሺ… የማሪያም አራስ” አሉ እማማ አስላኩ፡፡
ገብቶኛል፡፡ እኚህ ቀበኛ አሮጊት ውለታቸውን ለማሪያም ያስተላለፉት ቤተሰቡ ምንም እንደሌለው ስላወቁ ነው፡፡ ሎተሪ እንደደረሰኝ ሲሰሙ ግን ባለውለታ ጐድጓዳ ሰሐናቸውን በብር የመሙላት ዕዳ ይጭኑብኛል፡፡
ዘለግ አድርጌ ተነፈስኩ፡፡
ብዙዎቹ ጐረቤቶቼ የአራስ ጥሪ ያመጡበትን ዕቃ ይዘው ከእማማ አስላኩ ኋላ ይሰለፋሉ። ፔርሙስ፣ ብረት ድስት፣ ሰፌድ፣ እንቅብ፣ ደንበጃን…ውሃ የቀዱልን ሁሉ ባሊያቸውን ይዘው ሰልፉን ከአድማስ ያሻግሩታል፡፡
እንግዲህ ምን ተረፈኝ? ስም፣ ስም ብቻ!! የውለታ ቀስተ ደመና የህይወቴን ሰማይ ከቦታል።
“እዳዬን እንድከፍል ኑሯል ሎተሪ ያወጣህልኝ?” ስል እግዚሃርን ተደናቆልኩት፡፡
እንደውም በደንብ ሳሰላው ስራ የፈታው ህይወቴ፣ በጐረቤቶቼ ዳቦ የቆየበት ሦስት ዓመት በደረሰን ሎተሪ አይሸፈንም፡፡ ገንዘቡን ማከፋፈል ሳያንስ ያልተወራረደ ውለታ ያላቸው ጐረቤቶቹ፤ የውለታ ዕቃቸውን እንደያዙ የወቀሳ ኮረት እየለቀሙ ቤቴን፣ እኔ፣ ቤተሰቤን፣ ነፍሴን…ይደበድባሉ፡፡
ምን ፈረድብኝ?
ሆዴ ከጐረቤቶቼ ጋር አድሞ እሱም የውለታ ዕቃውን ይዞ አጉረመረመ፡፡
ምን አልኩህ፤ ፈጣሪዬ? ስለምን በስምህ የተዳፈነውን የውለታ ሰደድ በሎተሪ ስም ቆሰቆስከው? ስለምንስ በፅድቅ ስም ያሸለበውን የሶስት ዓመት ውለታ እንደ አላአዛር ከጥልቅ ሞት አስነሳኸው?
ዕዳዬ ውለታ ብቻ እንዳልሆነ አውቀዋለሁ፡፡
“መድፉ ሎተሪ ደረሰው” ሲባል የሰማ የስራ - ፈት ጅጊ ተውረግራጊ ቤቴን ይከባታል፡፡ ከቦም ያስጨንቃታል፡፡ ያኔ ደሜ በራሴ ላይ ነው፡፡
ምን ፈረደብኝ?
የሚወተውተኝን ሆዴን ለማስታገስ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄድኩ፡፡ ለእኔ ከማበሻነት በላይ ጥቅም የሌላት ዕድሌን በቀኝ እጄ እንደጨመደድሁ፡፡  

ባለፈው ቅዳሜ ድንገት ባደረበት ህመም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን አንጋፋውን የሥነ ፅሁፍ ሃያሲ አብደላ እዝራን የሚዘክር የኪነ ጥበብ ምሽት ከነገ ወዲያ ሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ በ“ዝክረ አብደላ” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ ሃያሲ አብደላ
እዝራ ለአማርኛ ስነ ፅሁፍ ያበረከተው አስተዋፅኦ የሚዳስስ ሲሆን “አብደላና ሂስ”፣ “አብደላና ህይወቱ” በመሳሰሉት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሥነ ፅሁፍ ባለሙያዎች አስተያየት ይሰጣሉ፡፡
የቅርብ ወዳጆቹም ስለ አብደላ የሚያወቁትን ይመሰክራሉ፤ አብደላን የሚያወድሱ፣ ስራውንና
ሰብዕናውን የሚያወሱ ግጥሞችና ወጎችም ለታዳሚያን ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
ይህን የ“ዝክረ - አብደላ” የኪነ ጥበብ ምሽት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ያዘጋጀው ሲሆን፣ በምሽቱ አንጋፋና ወጣት ፀሐፍትና ገጣሚያን ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ። ከእነዚህም መካከል ነቢይ መኮንን፣ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ ደረጀ በላይነህ፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ደምሰው መርሻ፣ ምስራቅ ተረፈ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡