Administrator

Administrator

የጋዜጠኛና ደራሲ ተሾመ ገብረሥላሴ “ባልታሰሩ ክንፎች” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡
መጽሐፉ፤ ወጐችን ተረኮችን፣ የታሪክ ማስታወሻዎችን፣ ዝርው ግጥሞችንና አጭር ልብወለዶችን ያካተተ ሆኖ በ184 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
“ጋዜጠኝነትን ሙያዬ ብዬ የጀመርኩት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው” ያለው ተሾመ፤ ከዚያም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በሸገር ሬዲዮና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞችና አምዶችን ከአዘጋጅነት እስከ አርታኢነት እንደሰራ ይናገራል፡፡
ደራሲው “የባህር ጠብታ” የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፉን ከ10 ዓመት በፊት ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡ 

  በገጣሚና ጋዜጠኛ አንዱአለም ጌታቸው የተፃፈው “ዮሪካ” የተሰኘ የግጥም መድበል ዛሬ ከ3 ሰአት ጀምሮ በሀገር ፍቅር ቴያትር ቤት ይመረቃል፡፡ የጋዜጠኛው የበኩር ስራ የሆነው የግጥም ስብስቡ በማህበራዊ፣ በፍቅርና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጥናል ተብሏል። የግጥም መጽሐፉ መጠሪያ የሆነውን “ዮሪኮ”ን ጨምሮ 50 ግጥሞችን በ64 ገፆች ያካተተው መድበሉ፤ በ30 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በሪፖርተርነት ያገለገለው ገጣሚው፤ በአሁኑ ወቅት በዛሚ ኤፍ ኤም የሚቀርበው “ጥበብ ለሁሉም” የተሰኘው ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነው፡፡

የወራት እድሜ የቀሩት የአሜሪካ ምርጫ ከወዲሁ አለማቀፍ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ አሁን ፍጥጫው
በሪፐብሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕና በዲሞክራቷ ተወካይ ሂላሪ ክሊንተን መካከል የሆነ ይመስላል። የዛሬ 8 ዓመት ባራክ ኦባማ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲወዳደሩ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች በአብዛኛው የኦባማ ደጋፊዎች ነበሩ፡፡
በዘንድሮስ ምርጫ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣
ፖለቲከኞችና ምሁራን በአሜካ ምርጫ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት ጠይቋቸዋል፡፡
ለመሆኑ የምርጫው ውጤት በኢትዮጵያ ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል? ፖለቲከኞቻችን ከዲሞክራትና
ከሪፖብሊካን ማን ቢያሸንፍ ይመርጣሉ? አስተያየታቸው እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

“እንደ ትራምፕ ያለ ሰው ቢመረጥ ምን እንደሚወስን አናውቅም”
(አቶ ሞሼ ሰሙ፤
የኢዴፓ መስራችና የቀድሞ ሊ/መንበር)

(አቶ ሞሼ ሰሙ፤
የኢዴፓ መስራችና የቀድሞ ሊ/መንበር)
በአሜሪካ ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ በአለማቀፍ ደረጃ ትኩረት የሚያገኘው አገሪቱ በኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አቅም ሃያል ስለሆነች ነው፡፡ በኢኮኖሚ ችግር ላይ ላሉ ሀገራትም በተለይ ማህበራዊ እርዳታ ላይ በርካታ አስተዋፅኦ ታበረክታለች፡፡ ከዚህ አንፃር በሀገሪቱ የሚደረጉ ምርጫዎችና ውጤቶቻቸው በሀገራችን ተፅዕኖ ሊኖራቸው ይችላል፡፡
የአሜሪካ ሁለቱ ፓርቲዎች - ሪፐብሊካንና ዲሞክራት፣ በአብዛኛው ልዩነታቸው የውጭ ፖሊሲያቸው ነው፡፡ ዲሞክራቶቹ ያላደጉ ሀገራትን በመርዳት የሚያምኑና ፀብ አጫሪነትን የማይሹ፣ በማስታረቅና በማረጋጋት ስራ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ሪፐብሊካኖቹ ደግሞ ጣልቃ ገብነታቸው ጠንካራ ነው፡፡ ራሳቸውን የዓለም ሰላም አስከባሪ አድርገው ያያሉ፡፡ ጣልቃ ገብተው መንግስት እስከ ማስወገድ ይደርሳሉ፡፡ ለዚህ ነው  እንደ ኢትዮጵያ ያለ መንግስት በጥንቃቄ የሚያያቸው፡፡ ልክ እንደ መስቀል ደመራ፣ ወዴት ነው የምርጫው ውጤት የሚወድቀው ብለን ሁሌ የምንጠብቀው ለዚህ ነው፡፡ እዚያ ሀገር ስልጣን የሚይዝ ፓርቲ የሚኖረው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ የእኛን ሀገር ጨምሮ በሌሎች ሀገሮች ላይ ተፅዕኖ አለው፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ የመሰረተ ልማት እርዳታ አታደርግም፤ትኩረቷ ማህበራዊ እርዳታ ላይ ነው፡፡ አሁን ያለውን ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የበለጠ እየተዳከመ እየመጣ ቢሆንም አሜሪካውያን አይናቸውን ጨፍነው እየረዱ ነው። ከዚህ አንፃር ከአሁን በኋላም የሚመጣው አመራር፣ ለሀገራችን የተለየ አመለካከት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ማዕከሉ ሽብርተኝነትን መከላከል ነው፡፡ እንደ ትራምፕ ያለ ሰው ቢመረጥ ምን እንደሚወስን አናውቅም፤ አስቸጋሪ ነው፡፡
እንደሚታወቀው ሀገሪቱ የራሷን ብሄራዊ ጥቅም ነው የምትመለከተው፡፡ ከዚህ አንፃር በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ ጉዳይ፣ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ የትኛውም የአሜሪካ ፓርቲ ቢመረጥ፣የሚያስቀድመው የራሱን ጥቅም ስለሆነ ተመሳሳይ ፖሊሲ ነው የሚያራምደው፡፡

==================================

“ዶናልድ ትራምፕ ለእኔ እብድ ነው”

(ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤ የመድረክ ሊቀ መንበር)

(ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፤
የመድረክ ሊቀ መንበር)
ኢትዮጵያውያኖች የአሜሪካን ምርጫ በትኩረት ይከታተሉታል፡፡ ኦባማ ወደ ምርጫ ሲመጣ ሰፊ ድጋፍ ያደርጉለት ከነበሩት መካከል ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡ ግን ሰውየው ከተመረጠ በኋላ ተስፋ የተጣለበትን ያህል በሀገራችን ጉዳይ ለውጥ አላመጣም፡፡ እንደውም ከፍተኛ ጉዳት ነው ያደረሰብን፡፡ እዚህ መጥቶ የተናገረው ንግግር፣ አሁን ላለው መንግስት የልብ ልብ ሰጥቶ፣ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ እስከ መገደልና አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊፈጸም ችሏል፡፡ “ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ደጅ ታሳድራለች” እንደሚባለው፣ አሜሪካንን ከያዙ እንደማይጠየቄ ስለሚያስቡ ያሻቸውን እያደረጉ ነው፡፡
እንደኔ ዲሞክራቶች የተሻሉ ናቸው፡፡ የሪፐብሊካኖቹ ዶናልድ ትራምፕ፣ለእኔ እብድ ነው፤ አካሄዱ ደስ አይልም፡፡ የዲሞክራቶቹ ሂላሪም ብትሆን እናውቃታለን፤እዚህ መጥታ ይሄን መንግስት ደግፋ ነው የሄደችው፡፡ ስለዚህ ሁሉም የራሱን ጥቅም ነው የሚያስጠብቀው፡፡ እኔ በነሱ ላይ ምንም አይነት እምነት የለኝም፤ኢህአዴግን የሚወዱት ስለሚያገለግላቸው ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ደግሞ ጥሩ አጋራቸው ሆኖላቸዋል፤ ስለዚህ ምንም ተፅዕኖ ያሳርፋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ዲሞክራቶቹ ግን በመጠኑ የተሻሉ ናቸው፡፡

====================================

“ከዝንጀሮ ቆንጆ ምረጥ ከተባልኩ ዲሞክራቶቹ ይሻሉኛል”
(ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)
(ኢ/ር ይልቃል ጌትነት፤
የሠማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)
የአሜሪካና የቻይና ፉክክር ባለበት ሁኔታ ሁሉም የራሱን ጥቅም ከማስከበር የዘለለ በሌሎች ጉዳዮች የተፅዕኖ አድራጊነት ሚናው እምብዛም ነወ፡፡
ሪፐብሊካንና ዲሞክራቶች እምብዛም የፖሊሲ ልዩነት የላቸውም፡፡ ለእነሱ ዋናው ሀገራቸው ነው፤ የሚያስቀድሙት ሃገራቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ቢመረጡ የራሳቸው ጥቅም እስካልተነካ ድረስ በአምባገነን መንግስት ላይ የሚያሳርፉት ተፅዕኖ አይኖራቸውም፡፡
ኦባማም ቢሆን መጀመሪያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርግ ይናገራቸው የነበሩ ነገሮችን ተግባራዊ ሲያደርግ አላየነውም፡፡ ኦባማ በውጭ ፖሊሲው ከስሯል - በኔ እይታ፡፡ ምናልባት የሀገሩን ኢኮኖሚና ፖለቲካ አሻሽሎ ሊሆን ይችላል፤ለኢትዮጵያና ለተቀረው አፍሪካዊ ግን ምንም የሠራው ነገር የለም፡፡ የመሪዎቹ መለዋወጥ በፖሊሲያቸው ላይ ለውጥ እንደማያመጣ ከዚህ ማየት ይቻላል። በተለምዶ ዲሞክራቶች የተሻሉ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ሪፐብሊካኖች ደግሞ አሁን በጣም እያከረሩ መጥተዋል፡፡ የዶናልድ ትራምፕ አካሄድ ለዚህ አስረጅ ነው፡፡ በኢምግሬሽን፣ በፀረ ሽብር፣ በእስላማዊ አክራሪነት ላይ ያላቸው አቋም፣ ፖለቲካዊ መፍትሔ በነሱ ዘንድ ዋጋ እያጣ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ለኔ ከዝንጀሮ ቆንጆ ምረጥ ከተባልኩ ዲሞክራቶቹ ይሻሉኛል፡፡

==================================

“ዲሞክራቶችም ሆነ ሪፐብሊካኖች ለኔ አንድ ናቸው”
                       (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ፖለቲከኛ

(ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ ፖለቲከኛ)
የቀድሞዎቹ የሪፐብሊካንና የዲሞክራት ተወካዮች አሜሪካን ተፈራርቀው ሲመሩ እንደታዘብነው፣የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ነው የሚያስጠብቁት፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚከተሉት ፖሊሲም በዚሁ አንጻር የተቃኘ ነው፡፡ ለኔ ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሪፐብሊካንም ይመረጥ ዲሞክራት ምንም ለውጥ የለውም፡፡ በሀገራችን ያለው መንግስትም የነሱን ፍላጎት የሚያስጠብቅ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ፓርቲዎች ይፈልጉታል፡፡ የዲሞክራቶቹና የሪፐብሊካኖቹ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተለያየ ይምሰል እንጂ የመጨረሻ ማጠንጠኛው፤ “የራስ ጥቅምን ማስቀደም” የሚለው ነው፡፡
አሜሪካኖቹ በኢትዮጵያ ያለውን ስርአት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የኛም ሀገር ስርአት በ25 ዓመት ልምዱ የአሜሪካ መንግስታት በቀጠናው ምን ፍላጎት እንዳላቸው ጠንቅቆ ስለሚያውቅ እነሱ እንደሚፈልጉት ይሆንላቸዋል፡፡ ዲሞክራቶችም ሆኑ ሪፐብሊካኖች ለኔ አንድ ናቸው፡፡ የትኛውን ትመርጣለህ ብባልም፣ ሁለቱም ያው ናቸው ይሆናል ምላሼ፡፡


======================================
“የዲሞክራቶቹ አገዛዝ ቢቀጥል ይሻላል”

(ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤ የኢዴፓ ሊቀመንበር)

(ዶ/ር ጫኔ ከበደ፤
የኢዴፓ ሊቀመንበር)
ሁሉም አገር እንደሚያደርገው አሜሪካውያንም ከምንም በላይ ለራሳቸው ጥቅም ነው የቆሙት፡፡ በየሀገሩ ካሉ መንግስታት ጋር ያላቸው ወዳጅነትም ጥቅማቸውን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ከባሰ አምባገነን መንግስትና የሰብአዊ መብቶችን ከሚደፈጥጡ ሃገራትና መንግስታት ጋር የተሻለ ወዳጅነት ሲፈጥሩም እንመለከታለን፡፡ ይሄ የሚያሳየን ቅድሚያ ለራሳቸው እንደሚሰጡ ነው፡፡
አስታውሳለሁ፤ኦባማ ሲመረጥ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ የተሻለ ነገር ይሰራል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ ያ ሲሆን ግን አልተመለከትንም፡፡ እንደውም እዚህ መጥቶ፤ “በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት ነው” የሚል ምስክርነት ሰጥቶ ነው የሄደው፡፡ በእርግጥ አሁን አሜሪካ ብቻዋን እንደ ቀድሞው በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ  አይደለችም፡፡ ብዙ አይነት ተፅዕኖዎችና ፖለቲካዊ ባህሪዎች እየገነኑ ነው፡፡ አሁን በዚህ ምርጫ ሪፐብሊካኖች የያዙት አቋም አስደንጋጭ ነው፡፡ ለሀገራቸውም ስጋት የደቀኑ ይመስለኛል፡፡ በዚህ አቋማቸው ከቀጠሉ ሃገራቸውን ሊከፋፍሉ ይችላሉ፡፡ በጥቁሮችና በሃይማኖት ጉዳይ የያዙት አቋም አስፈሪ ነው፡፡ እንደኔ ለአለምም ሆነ ለአገሪቱ ሰላም የዲሞክራቶቹ አገዛዝ ቢቀጥል ይሻላል የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡ እነሱ ለዘብተኛ አካሄድ ነው ያላቸው፡፡


===============================

“ትራምፕ የዲፕሎማሲ ሰው አይመስለኝም”

(ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ የአ.አ.ዩ.የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዲን)

(ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፤ የአ.አ.ዩ.የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ዲን)
አሜሪካ አሁንም በዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆና የቀጠለች ሃገር ነች፡፡ እነሱ ራሳቸውን የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የዓለም መሪ አድርገው ነው የሚመለከቱት፡፡ “አሜሪካ ስታስነጥስ ሌላው አለም ጉንፋን ይይዘዋል፡፡” የሚል አባባል አለ፡፡ ይሄ ምን ያህል ተፅዕኖ አሳራፊ ሀገር መሆኗን ያመላክታል። ኢትዮጵያ የዚሁ ተፅዕኖ አካል ነች፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያውያንም ጉዳዩን በንቃት ነው የሚከታተሉት፡፡
አሁን ፉክክሩ ያለው በዶናልድ ትራምፕና በሂላሪ ክሊንተን መካከል ይመስላል፡፡ ስለዚህ አንዳቸው ቢመረጡ በኢትዮጵያ ላይ የራሳቸውን ተፅዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሃገራት ቀዳሚ የአሜሪካ ድጋፎች ተጠቃሚ ነች። ድጋፎቹም በሚቀያየሩት መንግስታት ላይ የተመሰረተ ሲሆኑ እንመለከታለን፡፡
ሂላሪ የኦባማ ፓርቲ አባል በመሆኗም ከያዘችው አቋምም አንጻር ብትመረጥ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም የተሻለ ነው፡፡ ትራምፕ በአንፃሩ ለየት ያለ ባህሪ ማንፀባረቁ፣ በሀገራት መካከል ድንበር አበጃለሁ ማለቱ ተደማምሮ የዲፕሎማሲ ሰው አይመስለኝም። እሱ ቢመረጥ ሀገሩ የተሻለ ትርፍ የምታገኝበትን አማራጭ ብቻ የሚያይ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ለኢትዮጵያ ጥቅም አለው ብዬ አልገምትም፡፡ ሌላው መቀመጫቸውን አሜሪካ ያደረጉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን ሊሰማ ይችላል የሚል ግምት አለኝ፡፡ እነዚህ ሃይሎች ተፅዕኖ ለመፍጠር ከሞከሩ፣ ሰውየው ሃገራችን ላይ ማዕቀብ እስከ መጣል የሚደርስ ውሳኔ የሚያሳልፍ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ደግሞ በብዙ መልኩ አሁን ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል፡፡ እርዳታ ላይም የራሱን ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ዲሞክራቶቹ የተሻሉ ናቸው።  




የተጨዋቾችስነልቦና ጠንካራእንዲሆን ስራዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ዋና አምበል ሽመልስ በቀለ
        ከአልጄርያ ጋር በተደረጉት ሁለት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ዋልያዎቹ ያሳዩትአቋም የተለያየ ለምን ሆነ?
የመጀመርያው ጨዋታ ላይ ያው ተደጋግሞ እንደተገለፀው እኛ በተለያዩ ውጫዊ ምክንያቶች ድካም ነበረብን፡፡ እነሱም በሜዳቸው እንደመጫወታቸው ጫና ፈጥረው ብልጫ ወስደውብናል፡፡ እንደምታውቀው በዋልያዎቹ ስብስብ ብዙ አዳዲስ ተጨዋቾች አሉ፡፡ እነሱ በወጡበት ጊዜ የተፈጠሩ የተለያዩ ችግሮች አዲስ እንደመሆናቸው ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል፡፡  የተፈጠሩ ውጫዊ ተፅእኖዎች በአካል ብቃትም በስነልቦናም ለመቋቋም ባለመቻላቸው በመጀመርያው ጨዋታ ያ ከባዱ ሽንፈት መጋፈጥ ግድ ሆኖብናል፡፡
ዋናው ችግር በትራንስፖርት የተፈጠረውን አድካሚ ጉዞ እና መጉላላት ነው፡፡ ከሁለት ቀን በኋላ ለሚደረግ ጨዋታ 38 ሰዓታት በትራንዚት መጓጓዝ በጣም ይከብዳል፡፡ ረቁቅ ጉዞ ስታደርግ በፌደሬሽኑ በኩል ቀደም ብሎ መዘጋጀት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከነበረው ድካም አንፃር በጨዋታ መልካም ብቃት ማሳየት አይቻልም፡፡ ስፖርተኛ በቂ እረፍት እና ሙሉ አቅም ግንባታ ያስፈልገዋል፡፡
የአልጄርያው አሰልጣኝ ዮሃን ጉርኩፍ በመልሱ ጨዋታ የአንተን ብቃት ተመልከተው ምርጡ ተጨዋች እንደሆንክ እና ረጅም ጊዜ ሲከታተሉህ እንደነበር ተናግረዋል የሰሜን አፍሪካልምድ እንዳለህ ይታወቃል በፊት በሊቢያ ክለብ ትጫወት ነበር፤ አሁን ደግሞ ግብፅ ነው ያለሀው፡፡ የአልጄርያ ክለቦች ፍላጎት ያላቸው ይመስለኛል?
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ የአልጄርያ ክለብ በጥሩ የዝውውር ሂሳብ እያነጋገረኝ ነበር፡፡ በአጋጣሚ አልተሳካም ፤ አሁን ደግሞ የአልጄርያ ፌደሬሽን ክለቦች ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች የሚገዙበትን ሁኔታ በመዝጋቱ እድል ያለ አይመስለኝም፡፡ የግብፅ ሊግን ጉርኩፍ የሚከታተል ይመስለኛል፡፡ አስተያየቱም በዚያ ላይ የተንተራሰ ነው፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ በቀጣይ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች የማለፍ ዕድል ይኖረዋል?
በእኔበኩል እድል አለን ብዬ ነው የማስበው፤፤ ቀሪዎቹን ሁለት ጨዋታዎች ካሸነፍን 11ነጥብ ይኖረናል፡፡ ይሄ 11 ነጥብ ደግሞ በጥሩ ሁለተኛ ለማለፍ ያስችለናል ብዬ ነው የማስበው። በየምድቡ ያሉት መሪዎቹ እንኳን 7 ነጥብ ነው ያላቸው በዚህ ስሌት መሰረት የኢትዮጵያ ዕድል የሚወሰን ይሆናል፡፡
በወዳጅነት ጨዋታ የተጠናከረ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል፤ ተጨዋቾችን በደህና ሆቴል ማሳረፍ ብቻ አይደለም፤ በስነልቦና በቂ ዝግጅት እንዲኖራቸው ማድረግና መንከባከብ ያስፈልጋል፡፡ ሞራል የሚጠብቁ ተግባራት በፌደሬሽኑ መከናወን አለባቸው፡፡ የቡድኑ ተጨዋቾች ጭንቅላታቸው ጠንካራ እንዲሆን የሚያግዙ አሰራሮች ያስፈልጋሉ
የብሄራዊ ቡድኑ አምበል ስትሆን ለመጀመርያ ጊዜ ነው የምታስተላልፈው መልዕክት ምንድነው?
እውነቱን ለመናገር በመልሱ ጨዋየታ ያሉብንን ችግሮች ተቋቁመን ህዝብ ለማስደሰት መስዕዋትነት ከፍለናል፡፡ ህዝቡ ይሄን እንዲረዳው እፈልጋለሁ፣፣ በሌላ በኩል 7ለ1 በመሸነፋችን እኛም አዝነናል፤ በቡድኑ ስምም ይቅርታም መጠየቅ እፈልጋለሁ፡፡ የብሄራዊ ቡድን ዋና አምበልነት የሚያስደስት ግን ከባድ ሃላፊነት ነው፡፡ ቡድንህ ጥሩ ውጤት እንዲያመጣ ማነሳሳቱ፤ ከተጨዋቾች ጋር ተመካክሮ መስራቱ፤ ሃላፊነቱ መውሰዱ የሚያስደስት ነው፡፡ እናም ባለኝ አቅም አገሬን እያገዝኩ ውጤታማ እያደረግኩ መቀጠል እፈልጋለሁ፡፡

ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይላል፡-
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ትልቅ በረት ውስጥ አንድ አውራ ዶሮና አህያ ይኖሩ ነበረ። አህያው ለአውራ ዶሮው፤
“ስማ አያ አውራዶሮ፤ መቼም እኔና አንተ የረዥም ጊዜ ወዳጆች ነን፡፡ ምንም ዓይነት ችግር ቢገጥመን እንዳንከዳዳ”
አውራ ዶሮም፤
“ይሄንን ነገር ማንሳትህ ራሱ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ ስንት ዓመት ሙሉ ለጌታችን እየታዘዝን በአንድ ጣራ ስር ኖረናል፡፡ አንተም ሸክምህን ተሸክመህ፤ አንዴ በቀርበታ ውሃ ተሞልቶ ከወንዝ እዚህ ድረስ ስታመላልስ፣ አንዴ እህል ተጭነህ ወፍጮ ቤት ድረስ ስታመላልስ፣ አንዴ እንጨት ሲጭኑብህ ብዙ ስትንገላታ በዐይኔ በብረቱ አይቻለሁ፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ችግርና መከራ ቢደርስብህ ባለኝ አቅም ሁሉ እረዳሃለሁ፡፡ ሸክሙንም ቢሆን ቢቻለኝ አግዝህ ነበር” አለው፡፡
አህያም በጣም ተደሰተና፤
    “እንግዲያው ሆዴን ቀብትቶኛል፤ አንድ ጊዜ ላናፋ” አለው፡፡
አውራ ዶሮም፤
    “ማናፋት አውሬ ይጠራብናል፡፡ ጌታችንንም ያስቆጣል ይቅርብህ” አለው፡፡
አህያ ፤ “እባክህ አንዴ ብቻ” አለና ለመነው፡፡
ፈቀደለትና አንዴ ጮክ ብሎ “ሃ! ሃ! ሃ!” አለ፡፡ ከዚያ ተኙ፡፡
ጥቂት ቆይቶ አሁንም አህያ፤
    “ሆዴን ነፋኝ ቀበተተኝ፤ አንድ ጊዜ ላናፋ” ሲል ጠየቀው፡፡
አውራ ዶሮ፤
“ተው አያ አህያ፤ የቅድሙ የት እንዳለን ማሳያ፣ የአሁኑ ማቅረቢያ እንዳይሆን” ሲል አስጠነቀቀው።
አህያ፤
“ማንም የት እንዳለን ደኑ ውስጥ ሆኖ አያውቅም፡፡ ግዴለህም አንዴ ላናፋና ይውጣልኝ፡፡ በዚያ ላይ በረታችን የተከበረ በረት ነው፡፡ ማንም እዚህ ለመግባት አይደፍርም፡፡” አለና ማናፋቱን ቀጠለ፡፡
ለጥቂት ጊዜ እፎይ ብለው ተኙ፡፡ ሆኖም ከተወሰነ ሰዓት በኋላ አህያ፤
    “ስማ አያ አውራ ዶሮ፤ አንተ’ኮ በየሌሊቱ ትጮሃለህ ታድለሃል፤ እኔ ግን አይፈቀድልኝም”
አውራ ዶሮም፤
“የእኔ ጩኸት የዜማ ስልት ያለውና የሰው ልጆችን ለሥራ ስቀሰቅስ እንድኖር በተፈጥሮ የተሰጠኝ ግዴታ ነው፡፡ ያንተ ግን ስትጠግብና ሆድህ ከልኩ በላይ ሲሞላ ብቻ የምታናፋው ጩኸት ነው። ወዳጅንም ጠላትንም የሚጣራና የሚረብሽ ነው” አለና አስረዳው፡፡
አህያ ግን በጄ አላለም፡፡ አንዴ ለሶስተኛ ጊዜ “ሃ! ሃ! ሃ!” ሲል አናፋ፡፡
አውራ ዶሮም፤
“የመጀመሪያው መጥሪያ፣ ሁለተኛው ማቅረቢያ፣ ይሄ ሦስተኛው መበያ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ” አለው፡፡
አውራ ዶሮ ተናግሮ ሳይጨርስ አንበሳ መጣ፡፡ አህያ የሚገባበት ቦታ ጠፋው፡፡
አውራ ዶሮው ብልህ ነውና ዘሎ ቆጡ ላይ ወጣና ክንፎቹን ደፍደፍደፍ አርጎ መትቶ አንዴ ኩኩሉ ብሎ ጮኸ፡፡ አንበሳ በዓለም ላይ የሚፈራው ነገር ቢኖር የአውራ ዶሮ ጩኸት ነው፡፡ ስለዚህ እግሬ አውጪኝ አለ፡፡ ወጥቶ ወደ ዱሩ መንገድ ቀጠለ፡፡
ይሄንን ያየው አህያም “አንበሳ እንደዚህ ፈሪ ነው ለካ! ተከትዬ እደቁሰዋለሁ!” ብሎ ከበረት ወጥቶ እየሮጠ ሊይዘው ሞከረ፡፡ አንበሳ ግን ፊቱን አዙሮ አህያን በክርኑ ደቁሶ ደቁሶ ከጥቅም ውጪ አደረገው፡፡
                                                            *   *   *
አቅምን አለማወቅ ለውድቀት መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡ የጥጋብና የቁንጣን ጩኸት የማታ ማታ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ምክር የማይሰማ፣ እያደር የሚደነቁር ፍፃሜው የሮማ አወዳደቅ ነው፡፡ ችግር ሲኖር መጮህ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ስልት ያለው ጩኸት መሆን አለበት፡፡ ደግሞ ጊዜውን መጠበቅ አለበት፡፡ “ጊዜ የስልጣን እጅ ነው” ይለናል ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡ በሀገራችን በርካታ ስህተቶች በየጊዜው ሲሰሩ እንመለከታለን፡፡ የሚሰራ ይሳሳታልና አስገራሚ ላይሆን ይችላል፡፡ “የመላዕክት ስብስብ አይደለንም” ብለዋል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (ነፍሳቸውን ይማረውና!) ዋናው ስህተትን ማረም ነው፡፡ ስህተት ካልታረመ ወደ ክፉ ጥፋት ያድጋል፡፡ ውሎ አድሮም ወደ ካንሰር ይለወጣል፡፡ ለብዙ ዓይነት ውድቀቶች መንስኤም ይሆናል፡፡
በዕውቀትና በመግባባት ላይ ያልቆመ ብልፅግናና ኃጢያት (ጥፋት) በዛበት አገር የችግር መናኸሪያ ነው፡፡ አንጋራ ፈላስፋ (የፈላስፎች አነጋገር) የሚባለው፣ ሊቀ መዘምራን ሞገስ እቁበ ጊዮርጊስ ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት መጽሀፍ ይሄን ይለናል፡- “በሀገር ላይ ኃጢያት የተደረገ፣ ክፋት የተገለጠ እንደሆነ፣ ጥበብ ከሀገር ወጥታ ትሸሻለች፡፡ ጥበብ ከሀገር ወጥታ የተለየችና የሸሸች እንደሆነ፣ ሕግ ትዋረዳለች፣ ትናቃለች፡፡ ሕግም የተዋረደችና የተናቀች እንደሆነ፣ የንጉሡ ግርማ (መታፈር፣ መፈራት) ይጠፋል፡፡ ልብሰ መንግሥቱ ይገፈፋል፡፡ ጠላቶቹ ይሰለጥኑበታል (ይደፍሩታል)”
በተደጋጋሚ ያየናቸውና ያነሳናቸው ችግሮች እየተዋለዱ ለያዥ ለገራዥ አልመች ያሉ ሆነዋል፡፡ የችግሩን ሥር አግኝቶ ሥር ነቀል እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደሞ ንፁህ እጅ ያስፈልጋል፡፡ ንፁሃን መክረው ለመጓዝ መተማመንና ፍቅር ሊኖራቸው ያሻል፡፡ “ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይባላልና ባለ ጮማና ባለ ፎቆቹን በዓይነ - ቁራኛ እያዩ፣ ባለ ጎመኖቹን አቅፎ መጓዝ የአባት ነው፡፡ “የበላን አብላላው፣ የለበሰን በረደውን”ም አለመዘንጋት ደግ ነው፡፡
የመሬት ነገር አንገብጋቢ መሆኑ መቼም ተወርቶ አልቋል፡፡ ጥያቄው የተረፈ ቦታ አለ ወይ? የአዲሳባ ደር ዳሩ ተነክቷል፡፡ አንዳንዶች እንደሚሉት፤ የተበላ ዕቁብ ነው፡፡ “ዳሩ ሲነካ መካከሉ ዳር ይሆናል” የሚለው አባባል እዚህ ጋ ትርጉም ያገኛል፡፡ አስገራሚው ነገር በዳሩም በማህሉም መጠየቅ ያለባቸው አካላት፣ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑና ብዙ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም ብዝበዛው አለመስከኑና ዛሬም የመሬት መዋዋሉ እንደቀጠለ አለመነገሩ ነው፡፡ ተራው ያልደረሰው ሙስናው ደጃፍ ላይ ተሰልፏል፡፡ የሚነገርለት መረብ አለመበጣጠሱና ድለላው ይብስ መጧጧፉ የመንግስት ድክመት፣ የባለስልጣናት ረጅም እጅ አሁንም መዘርጋቱ የሁለት ቢላዋ (የሁለት ቤት) ሰራተኞች መበርከት፣ በጊዜ ያልተቆጡትና ያልቀጡት የቤት ልጅ መብዛት፣ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” የማይባሉ ባለጊዜዎች መኖር፣ “ባለቤቱን ካልናዉ አጥሩን አይነቀንቁ” የሚለው ተረት የማይመለከታቸው ባለሀብቶች ከቤት ደጅ መትረፍረፋቸው፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል ሰበቡ፡፡ ይሄ ሁሉ በወገንተኝነት ሲጠረነፍ እንግዲህ መጠንጠኛ ምህዋሩ፤ ባለጊዜው፣ ባለሥልጣኑና ባለእጁ ያሉበት ጨዋታ በመሆኑ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ጮክ ብለው ለመናገር እያቃታቸው፣ ጥቅሙም እንዳይቀር እያሳሳቸው ማጨብጨባቸውን መቀጠላቸው ነው፡፡ “እንዳንዘፍነው ዘፈንህ ሆነብን፤ እንዳንተወው ጣመን” ማለት ይሄ ነው!

Monday, 04 April 2016 07:48

የዘላለም ጥግ

(ስለ ውበት)
· ውብ ነገሮች ባይፈቀሩ እንኳን ሊደነቁ ግድ
ይላል።
ኤል.ፍራንክ ባዩም
· ውበት ሁል ጊዜ የሚወለደው ከጨለማ ሃሳች
ጋር ነው፡፡
ናይትዊሽ
· በውት ላይ እንከን ያለመኖሩ በራሱ እንከን ነው።
ሃቬሎክ ኤሊስ
· ውበት የሚታየው በፊት ገፅታ ላይ አይደለም፤
ውበት በልብ ውስጥ ያለ ብርሃን ነው፡፡
ካህሊል ጂብራን
· ውብ ያልሆነ ሳቂታ ፊት አይቼ አላውቅም፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
· ውበትን የሚያጣጥም ነፍስ አንዳንዴ ብቻውን
ሊጓዝ ይችላል፡፡
ጆሃን ቮንገተ
· አስቀያሚ መሆን የማትችል ሴት ውብ
አይደለችም፡፡
ካርል ክራውስ
· አካላዊ ውበት ዓለምን መግዛቱን ይቀጥላል፡፡
ፍሎሬንዝ ዚግፌልድ
· ውብ ነን ብላችሁ ካሰባችሁ ባትሆኑም ውብ
ናችሁ፡፡
ቴሪ ጉይሌሜትስ
· ደረጃ የተበጀለት ውበት አልወድም - ባዕድነት
የሌለው ውበት የለም፡፡
ካርል ላገርፊልድ
· የሰው ልጅ ገላ ምርጥ የጥበብ ሥራ ነው፡፡
ጄስ ሲ. ስኮት
· ያልሆንከውን ለመሆን አትሞክር፡፡ ከደነገጥክ
ደንግጥ፡፡ ካፈርክ እፈር፡፡ ያንን ማድረግ ውብ
ነው፡፡
አድሪያና ሊማ

      መድረክ፤ ባለፉት 3 ሳምንታት ከአዲስ አበባ ከተማ የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተደረጉ ተቃውሞዎች የተሳተፉ 2ሺህ 627 ሰዎች በመንግስት ሃይሎች ታስረዋል ማለቱን ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ፤ መንግስት ተቃዋሚዎችን ያሰረው በቀጣይ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች እንዳይደረጉ ለመከላከል በማሰብ ነው ሲሉ መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ 12 የተለያዩ አካባቢዎች 2 ሺህ 627 ሰዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ውለዋል ማለታቸውንም ገልጿል፡፡
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ከማስተር ፕላኑ ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ክልል በተደረጉ ተቃውሞዎች ከ200 ያህል፤ ሰዎች ሳይገደሉ አልቀሩም ማለታቸውንም ዘገባው አስታውሷል። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግሥት ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካ ሮይተርስ ጠቁሟል፡፡

ሊቀመንበሩን ጨምሮ አምስት የሠማያዊ ፓርቲ አመራሮች እንዲባረሩና እንዲታገዱ በስነስርአት ኮሚቴ የተላለፈውን ውሣኔ የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን ውድቅ አድርጐታል፡፡
የስነስርአት ኮሚቴው በምርጫ 2007 አምስት አመራሮች ያለአግባብ የፓርቲውን ገንዘብ አባክነዋል በሚል የቀረበለትን ክስ ሲመረምር ቆይቶ ባሳለፍነው ሣምንት ውሣኔ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በውሣኔውም የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነትና የሂሣብ ክፍል ሃላፊው አቶ ወረታው ዋሴ ከፓርቲው ሙሉ ለሙሉ እንዲባረሩ፤ የፓርቲው ም/ሊ/መንበር የነበሩት አቶ ስለሺ ፈይሳና የምክር ቤት አባልዋ ወ/ት ወይንሸት ሞላ፣ ለሁለት አመት እንዲታገዱ እንዲሁም አቶ ጌታነህ ባልቻ ለሶስት ወር እንዲታገዱ ያሳለፈውን ውሣኔ፣ የፓርቲው ኦዲትና ኢንስፔክሽን “አግባብ አይደለም” በማለት ሽሮታል፡፡
ለተከሳሾቹ ከመገለፁ በፊት በማህበረሰባዊ ሚዲያዎች ውሳኔው ይፋ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን የጠቀሰው የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው፤ ውሳኔውም የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ ያልተከተለና የስነ ስርዓት ቅጣት አላማን ያላገናዘበ ነው ብሏል፡፡
መባረራቸውና መታገዳቸው ተገልፆ የነበረው የፓርቲው አመራሮች፤ መደበኛ ስራቸውን እንዲቀጥሉ የወሰነው  የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው፤ በማህበራዊ ድረ ገፆች ይሄን አስመልክቶ የሚካሄዱ ዘመቻዎች መቆም እንዳለባቸውም አሳስቧል፡፡

የወልቃይት ወረዳ በአማራ ክልል ውስጥ መሆን አለበት የሚል ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያስገቡ አቤቱታ አቅራቢዎች፤ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው የተናገሩ ሲሆን ፌዴሬሽን ም/ቤት በበኩሉ፤ በመጀመሪያ ጥያቄው መታየት ያለበት በክልል ምክር ቤት ነው የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ አለ፡፡
ጥያቄ በማንሳታችን በደል እየተፈፀምብን ነው በማለት አቤቱታ አቅራቢዎቹ ገልፀዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር ግን አስተባብሏል - የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም በማለት፡፡
ጥያቄያችንን ለፌዴሬሽን ምክር ቤትና ለተለያዩ የመንግስት አካላት በተደጋጋሚ አሰምተናል ያሉት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ የወረዳው ባለስልጣናት እንግልትና በደል እየፈፀሙብን ነው ብለዋል፡፡
ህግን ተከትለን የወልቃይት ጠገዴ ወረዳ በአማራ ክልል ስር እንዲሆን ጥያቄ ማንሳት የጀመርነው በ1983 ዓ.ም ነው በማለት የተናገሩት አቤቱታ አቅራቢዎች፤ “ጥያቄያችን ምንም የፖለቲካ ፍላጎት ባይኖረውም አላግባብ ተፈርጀን እንግልት እየደረሰብን ነው ብለዋል፡፡
የወልቃይት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀጃው ደሞዝ በበኩላቸው፤ “ጥያቄ ማንሳት ያለበት የወረዳው ህዝብ እንጂ በሌላ አካባቢ የሚኖር ግለሰብ አይደለም፤ ህዝቡ እንዲህ አይነት ጥያቄ አላነሳም” ብለዋል፡፡
ጥያቄ አቅርበዋል የሚባሉት ሰዎች የወረዳው ነዋሪዎች አይደሉም ያሉት አቶ ጀጃው፣ የወረዳው ማህበረሰብ በመልካም አስተዳደርና በልማት ስራዎች ላይ እየተረባረበ ነው ብለዋል፡፡

    የሴባስቶፖል ሲኒማና ኢንተርቴይመንት ባለቤት፣ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሩ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በ“ሶስት ማዕዘን” ፊልም ምክንያት ከቀረበበት የ10 ሚሊዮን ብር የፍትሃ ብሄር ክስ በነፃ ተሰናብቷል፡፡
አርቲስቱ “ሶስት ማዕዘን” የተሰኘውን ፊልም ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ በ2000 ዓ.ም ካሳተመው “ፍቅር ሲበቀል” መፅሃፍ ወስዶ ነው የሰራው የሚል ክስ የቀረበበት ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ከሳሽ ደራሲ አትንኩት፣ለደረሰባቸው የሞራል ጉዳት የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር፡፡
አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 18ኛ ፍ/ብሔር ችሎት፣ በከሳሽ የቀረቡ የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም በተከሳሽ የቀረቡ ተመሳሳይ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ የከሳሽ ማስረጃ ክሱን በአግባቡ የሚያስረዳ ሆኖ እንዳላገኘውና ክሱ ያለ አግባብ የቀረበ መሆኑን በመግለፅ ከትናንት በስቲያ ውድቅ አድርጎታል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በክሱ ሂደት የደረሰበትን ጉዳትም በዝርዝር መጠየቅ እንደሚችል ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
 የክሱን መመስረት ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ዘገባዎች፣ በስራውና በሞራሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት የገለጸው አርቲስቱ፤በእቅድ የያዛቸው ስራዎችም እንደተሰናከሉበት ተናግሯል፡፡