Administrator

Administrator

   የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ሆሳም ሞጋዚ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችውን አወዛጋቢውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ በተመለከተ  አለማቀፍ ሽምግልናን እንደአማራጭ ለመውሰድ ጊዜው ገና ነው ማለታቸውን አሃራም ኦንላይን የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘገበ፡፡
ግብጽ የግድቡ መሰራት ወደተፋሰሱ አገራት የሚደርሰውን የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሰዋል በሚል ስጋቷን ስትገልጽ እንደቆየች ያስታወሰው ዘገባው፣ በግድቡ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በአለማቀፍ ሸምጋዮች መፍታትን እንደአማራጭ እንደማትወስድና አፍሪካውያን አደራዳሪዎች በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገቡ እንደማትፈልግ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ገልጧል፡፡
ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኡመር አልበሽር ታላቁ ህዳሴ እውን መሆኑ ተረጋግጧል፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተባብረው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ በተናገሩ ማግስት እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ሚኒስትሩ በቅርቡም ግድቡ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያደርሰውን ተፅዕኖ በተመለከተ የሚደረጉ የቴክኒክ ጥናቶች ሳይጠናቀቁ የግድቡ ግንባታ መፋጠኑ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን አስታውሷል፡፡
ሚድል ኢስት ሞኒተር በበኩሉ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ፣ ግብጽ የተባበሩት አረብ ኢሜሬትስን በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት በግድቡ ዙሪያ የሚታዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ድጋፍ እንድታደርግ መጠየቋን አስነብቧል፡፡
የኢትዮጵያ፣ የግብጽና የሱዳን የውጭ ጉዳይና የመስኖ ሚኒስትሮች በግድቡ ዙሪያ በሚመክረው አስረኛው ዙር የጋራ ስብሰባ በሱዳን መዲና ካርቱም ከትናንት ጀምሮ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

• “መብራት ተቋርጦ ሶስት ህሙማን ሞተዋል” - የሆስፒታሉ ባለሙያ
• “መብራት የተቋረጠው ከሆስፒታሉ አቅም በላይ በሆነ ችግር ነው” - የሆስፒታሉ አስተዳደር


        በሀዋሣ ሪፈራል ሆስፒታል፤ መብራት በመቋረጡ ምክንያት፤ በፅኑ ህክምና ክፍል 3 ታማሚዎች እንደሞቱ፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮችን በመጥቀስ አዲስ አድማስ  ያወጣውን ዘገባ፣ ሆስፒታሉ ተቃወመ፡፡ ህሙማኑ መሞታቸውንና መብራት መቋረጡን ሆስፒታሉ ቢያምንም፤ ህሙማኑ የሞቱት በመብራት መቋረጥ ሳቢያ እንደሆነ የሚያረጋግጡ በቂ መረጃዎች በዘገባው አልቀረቡም፤ ሚዛናዊነትንም አያሟላም በማለት ቅሬታ አቅርቧል፡፡ ቅሬታዎቹ ብዙ ናቸው፡፡
የመብራት መቋረጥ ከሆስፒታሉ አቅም ውጪ የሆነ ክስተት እንደሆነ የሆስፒታሉ አስተዳደሩ ሲያስረዳ፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መስመር በመጥፋቱ ምክንያት የተፈጠረ ክስተት መሆኑን የመብራት ኃይል ተቋም አረጋግጦልኛል ብሏል ለአዲስ አድማስ በፃፈው ማስተባበያ ደብዳቤ፡፡ በኤሌክትሪክ መቋረጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን በጀኔሬተር ለማቃለል ከፍተኛ ርብርብ አድርጌአለሁ በማለት የሆስፒታሉ አስተዳደር ጽፏል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በዘገባው አለመካተታቸውን ተችቷል፡፡
3 ህሙማን ሞተዋል የሚለው ዘገባ ስህተት ነው ሲል ሆስፒታሉ አስተባብሏል፡፡ ስህተቱንም ሲያስረዳ፤ ሁለቱ ህመምተኞች የሞቱት ህዳር 20 ቢሆንም አንድ ወላድ ህመምተኛ የሞተችው ህዳር 18 ቀን ነው ብሏል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሆስፒታሉ ባለሙያ ለአዲስ አድማስ በሰጡት መረጃ፤ በሁለቱም ቀናት መብራት ተቋርጦ ችግር እንደተፈጠረ አረጋግጠው፤ ከዚህም ጋር ተያይዞ ሦስት ህሙማን መሞታቸው እውነት ነው ብለዋል፡፡ በሁለቱም ቀናት መብራት መቋረጡንና በጀነሬተር ችግሩን ማቃለል አለመቻሉን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው የሆስፒታሉ የህግ ክፍል ተወካይ፤ በደብዳቤ ከተፃፈው ምላሽ ውጭ ጥያቄዎችን ማንሳት አስፈላጊ አይደለም ብለዋል፡፡
የሆስፒታሉ አስተዳደር የፃፈው ደብዳቤ ግን ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ አልሆነም፡፡
ችግሩን ለማቃለል ርብርብ ማድረጉን፤ ታካሚዎቹ ህመም ፀንቶባቸው እንደነበር፣ ወላዷ እናት የሞተችው “በዋነኛነት” በመብራት መቋረጥ ሳይሆን በህመሟ መባባስ ምክንያት እንደሆነ ነው ደብዳቤው በደፈናው የሚገልፀው፡፡ በመብራት መቋረጡ ሳቢያ በህሙማን ላይ ጉዳት መድረስ አለመድረሱን በሚመለከት የተጠየቁት የህግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ በቀለ በኩካ “በዘገባው ላይ በተገለፀው ዕለት መብራት መጥፋቱ የማይካድ ሃቅ ነው፤  በዚሁ ምክንያት የሰው ህይወት አልፏል ወይንስ አላለፈም በሚለው ጉዳይ ላይ ግን በማስተባበያ ደብዳቤው ላይ በተገለፀው መሠረት ብቻ ማረሚያ አውጡ” በማለት ለጥያቄያችን ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት የሆስፒታሉ ተጠባባቂ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብይ ሚካኤል፤ መረጃ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው፤ “ምላሻችንን በኢሜይል እልካለሁ” ካሉን በኋላ፤ “ከሆስፒታሉ ሃኪሞች ጋር መነጋገር አለብኝ” በማለት ምላሽ ሳይሰጡን መቅረታቸው ይታወሳል፡፡    
ሆስፒታሉ፤ ሁሉም የጤና ባለሙያዎች ተጋግዘው የሚሰሩበትና ነርሶችም በኃላፊነት ከሃኪሞች ጋር የህክምና አገልግሎት በመስጠት የሚሳተፉበት አሰራር እንዳለ ደብዳቤው አክሎ ገልጿል፡፡  

    ኢትዮ ቴሌኮም፤ በ“አፍሪካ ቴሌኮም ሊደርሺፕ አዋርድ” በአራት ዘርፎች የአመቱ ምርጥ ተብሎ መሸለሙን አስታወቀ፡፡
የዓመቱ ምርጥ ቴሌኮም ኦፕሬተር፣ የአመቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ ለሰው ሀይል አስተዳደር ትኩረት የሰጠ ምርጥ ዋና ስራ አስፈፃሚና አለም አቀፍ ቀጣይነት ያለው ስራ አመራር  የተገበረ ተቋም በሚሉ ዘርፎች ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የቴሌኮም ተቋማት ጋር ተወዳድሮ በማሸነፍ፣ በ5ኛው የአፍሪካ የስራ አመራር ሽልማት ተሸላሚ መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል፡፡
በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ አንዷለም አድማሴ፤ ኩባንያው የሀገሪቱን ህዝቦች የቴክኖሎጂ ተቋዳሽ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ፕሮጀክት ነድፎ ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጠዋል፡፡ ሽልማቱም አነሳሽና ለበለጠ ሰራ የሚያተጋ እንደሆነ ተናግረዋል፤ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡ ውድድሩን የመሩት ዳኞች አለማቀፍ እውቅና ካላቸው ኩባንያዎች የተውጣጡ ኤክስፐርቶች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ 

•    ፖሊስ አደጋውን እያጣራሁ ነው ብሏል
በትላንትናው ዕለት በታላቁ አንዋር መስጊድ በደረሰ የቦንብ ፍንዳታ በ5 ሰዎች ላይ ከባድ የመቁሰል አደጋ ሲደርስ በ19 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት መድረሱ ታውቋል፡፡ ፖሊስ ቦንቡን የወረወረውን ግለሰብ ለመያዝ ክትትል እያደረገመሆኑን አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስቴር አቶ ጌታቸው ረዳ አደጋውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ፤ፍንዳታው የአካል ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው የሞተ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ጉዳቱ የደረሰባቸው ዜጎችም ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ በሚገኙ የህክምና ማዕከላት ተወስደው እርዳታ እንዲያገኙ ተደርጓል ተብሏል፡፡
ትላንት ምሽት የብሔራዊ  የመረጃና የደህንነት አገልግሎትና የፖሊስ ግብረ ሃይል በሰጡት መግለጫ፤በመርካቶ ታላቁ መስጊድ የጁምአ ጸሎት አድርሰው ሲወጡ በነበሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ ማንነቱ ባልታወቀ ግለሰብ የተወረወረው ቦንብ በ5 ሰዎች ላይ ከባድና በ19 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ማድረሱን የገለጸ ሲሆን ፖሊስ ቦንቡን የወረወረውን ግለሰብ ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 05 December 2015 15:57

ማስተካከያ

     ቅዳሜ ህዳር 18 ቀን 2008 ዓ.ም በቅፅ 16 ቁጥር 828 የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ “አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያም ከሳሽም ምስክርም ሆኖ ፍ/ቤት ቀረበ” በሚል ርዕስ በወጣው ዘገባ፤ “ፍ/ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮችን በሙሉ ካዳመጠ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከሉ በማለት ምስክሮችን ለመስማት ለጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል” የሚለው፣ “ምስክሮችን ካደመጠ በኋላ ፍ/ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጥሯል” በሚል ተስተካክሎ እንዲነበብ እየገለፅን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

         ህንድ ባለፉት ከ100 በላይ አመታት ከተመዘገቡት የዝናብ መጠኖች ከፍተኛው የተባለውን ሃይለኛ ዝናብ ባለፈው ረቡዕ በደቡባዊ ክፍሏ ያስተናገደች ሲሆን ዝናቡ ባስከተለው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ክፉኛ መመታቷን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ታሚል ናዱ በተባለው የአገሪቱ ግዛት የዘነበው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀሉን የጠቆመው ዘገባው፤ የግዛቱ መዲና በሆነችው ቼናይ፣ ፋብሪካዎች መዘጋታቸውንና አውሮፕላን ማረፊያውም ስራ ማቋረጡን ገልጧል። በአካባቢው ወሩን ሙሉ ይዘንባል ተብሎ ከሚጠበቀው አማካይ የዝናብ መጠን በሁለት እጥፍ የሚበልጥ ዝናብ በ24 ሰዓታት ውስጥ መዝነቡንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
በህንድ አራተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችው ቼናይ፣ ከአገሪቱ ዋነኛ የመኪና አምራችና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከላት አንዷ እንደሆነች ዘገባው ጠቁሞ ከተማዋ ጎርፉ ባስከተለው የመብራት መቋረጥ እንቅስቃሴዋ ሙሉ ለሙሉ መገታቱን አስረድቷል። የጎርፍ አደጋው ያስከተለውን ጥፋት ለማከምና ተረጂዎችን ለማቋቋም አስቸኳይ የአደጋ ጊዜ ግብረ ሃይል ተቋሙሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጧል፡፡

 ፖሊሶችና የመንግስት ባለስልጣናት ይከተላሉ
                     - በአመቱ ከ75 ሚ በላይ የ28 አገራት ዜጎች በሙስና ገንዘብ ከፍለዋል
    በአፍሪካ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በ2015 በሙስና ከፍተኛውን ደረጃ የሚይዙት፣ በተለያዩ የንግድ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለጸጎችና የኩባንያ ስራ አስፈጻሚዎች መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ያወጣው አመታዊ የጥናት ውጤት እንደሚለው፣ በአህጉሪቱ ከባለጸጎች በመቀጠል በሙስና ሁለተኛውንና ሶስተኛውን ደረጃ የሚይዙት የፖሊስ መኮንኖችና የመንግስት ባለስልጣናት ናቸው፡፡
በ28 የአፍሪካ አገራት ላይ በተሰራው በዚህ ጥናት፣ ከ43 ሺህ በላይ አፍሪካውያን ቃለመጠይቅ እንደተደረገላቸው የጠቆመው ዘገባው፤በዚህም ሙስና በአህጉሪቱ ክፉኛ መስፋፋቱንና በአመቱ ከ75 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን ከፖሊስ ወይም ከፍርድ ቤት ቅጣት ለመዳንና መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸው እንዲሟሉላቸው ለማስቻል፣ በሙስና መልክ ገንዘብ እንደከፈሉ ተደርሶበታል ብሏል፡፡
ጥናቱ ከተሰራባቸው የአፍሪካ አገራት በአመቱ የከፋው ሙስና የተመዘገበው በላይቤሪያ ሲሆን፣ ካሜሩን፣ ናይጀሪያና ሴራሊዮን ይከተላሉ ተብሏል። ከምስራቅ አፍሪካ አገራትም ኡጋንዳና ኬንያ ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ተነግሯል፡፡
በላይቤሪያ ቃለመጠይቅ ከተደረገላቸው የአገሪቱ ዜጎች መካከል 69 በመቶ የሚሆኑት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት ሲሉ ለስራ ሃላፊዎች ገንዘብ በሙስና መልክ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ በቦስትዋና እና በሞሪሺየስ 1 በመቶ ያህሉ ሰዎች ብቻ ሙስና እንደሰጡ የገለጸው ዘገባው፤በጥናቱ ከተዳሰሱ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አነስተኛውን ሙስና ሰርተው የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች መሆናቸውን ገልጧል፡፡ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ድህነትን ከማባባስ በተጨማሪ የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዳይሟሉ ያግዳል ያለው ተቋሙ፤በመገባደድ ላይ ባለው የፈረንጆች አመት ስልጣናቸውን ያለአግባብ በሚጠቀሙ አካላት ሳቢያ ክፉኛ የተጎዱት ሙስና መስጠት አቅም የሌላቸው አፍሪካውያን ድሆች መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

        የቀድሞው የጊኒ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ፤ ከሁለት አመታት በፊት በኢትዮጵያ በኩል ወደ አሜሪካ ጉዞ ባደረጉበት ወቅት ከ64ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ ደብቀው ማሸሻቸውን ባለፈው ማክሰኞ በኖርዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት ቀርበው እንዳመኑ አሶሼትድ ፕሬስ ዘገበ፡፡
ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ በወቅቱ ዋሽንግተን በሚገኘው ዱሌስ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ፣ ከ10 ሺህ ዶላር በታች እንደያዙ በመናገር ቀሪውን ገንዘብ በሻንጣቸው ውስጥ ደብቀው ለማሳለፍ መሞከራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ይህ ድርጊታቸው በጥበቃ ሃይሎች ተደርሶበት ክስ እንደተመሰረተባቸው ገልጧል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ ለፍርድ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ቃላቸውን በሰጡበት ወቅትም፣ በቋንቋ ችግር ምክንያት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ያለውን የጉምሩክ አሰራር በአግባቡ መረዳት አልቻልኩም ብለው ሊያመልጡ መሞከራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአሜሪካ የፍትህ ሚኒስቴር እንዳለው፤ የ51 አመቱ ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴን ጉዳይ ሲመረምር የቆየው ፍርድ ቤት በመጪው የካቲት በሚሰየም ችሎት በግለሰቡ ላይ እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት ቅጣት ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሴኩባ ኮናቴ በጊኒ የ50 አመታት ታሪክ የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በተባለውና እ.ኤ.አ በ2010 በተከናወነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ መሸነፋቸውን ተከትሎ ስልጣን እንደለቀቁ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም የአፍሪካ ህብረት የጸጥታ ሃይል ጄኔራል ኮማንደር ሆነው ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠቁሟል፡፡

 - በዱባይ በበኩሏ ጤናማ
             አኗኗር የሚከተሉትን ልትሸልም ነው
    የጂያንግሱ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውና በምስራቃዊ ቻይና የምትገኘው የናንጂንግ ከተማ የቆሸሹ መኪኖችን ሲያሽከረክሩ የተገኙ ሾፌሮችን በገንዘብ የምትቀጣበትን አዲስ አሰራር ተግባራዊ ልታደርግ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከተማዋ ገጽታዋን ለመገንባት የጀመረችው እንቅስቃሴ አካል የሆነው ይህ የቅጣት መመሪያ እንደሚለው፣ አካላቸውና ጎማቸው የቆሸሸ መኪኖች 16 ዶላር፣ የታርጋ ቁጥራቸው በቆሻሻ የደበዘዘ ወይም ህጋዊ ፍቃድ የሌለው ማስታወቂያ የተለጠፈባቸው መኪኖች እስከ 320 ዶላር የሚደርስ ቅጣት ይጣልባቸዋል ይላል፡፡
ኒጃንግ ዴይሊ የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ አዲሱን መመሪያ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፣ ቻይናውያን የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎች “የእኛ መኪና ለቆሸሸ፣ መንግስትን ምን ጥልቅ አደረገው” ሲሉ የከተማዋ አስተዳደር ያቀደውን የቅጣት አሰራር ክፉኛ እየተቹት እንደሚገኙ ዘገባው ገልጧል፡፡
አንዳንዶቹ የማህበራዊ ድረገጽ ተጠቃሚዎችም የቅጣት አሰራሩን መንግስት ገንዘብ ለመሰብሰብ ሲል የቀየሰው ተገቢ ያልሆነ ስልት ነው ሲሉ መተቸታቸው ተነግሯል፡፡ዱባይ በበኩሏ! ነዋሪዎቿን ንቁና ጤናማ እንዲሆኑ ለማበረታታት በማሰብ የሲኒማ መግቢያ ትኬትና ነጻ የጂምናዚየም አባልነት መታወቂያ ልትሰጥ ማቀዷን ገልፍ ኒውስ ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ የዱባይ የጤና ባለስልጣን መስሪያ ቤት ያወጣው አዲስ የማበረታቻ ዕቅድ እንደሚለው፣ አዘውትረው ጤናማ ምግብ የሚመገቡና የሰውነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ በሁሉም የዕድሜ ክልሎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች በየጊዜው በድረገጽ አማካይነት የሚሰጡት ሳምንታዊ ውጤት ተመዝግቦ የማበረታቻ ሽልማቱን ያገኛሉ፡፡
69 በመቶ የዱባይ ነዋሪ የሆኑ አዋቂዎች ከመጠን ያለፈ የውፍረት ችግር ተጠቂ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ከተማዋ ከዚህ በፊትም ክብደታቸውን ለመቀነስ የቻሉ ነዋሪዎቿን ወርቅ የምትሸልምበት አሰራር ተግባራዊ አድርጋ እንደነበር አስታውሷል፡፡

    አይሲስ ትዊተር በተባለው ታዋቂ የማህበራዊ ድረ ገጽ አማካይነት የሽብር እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት የሚያግዝ የፕሮፓጋንዳ ስራ የሚሰሩና ለሽብር ቡድኑ አዳዲስ አባላትን የሚመለምሉ ከ300 በላይ አሜሪካውያን አምባሳደሮች እንዳሉትና አብዛኞቹም ሴቶች እንደሆኑ ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የጽንፈኝነት ጥናት ፕሮግራም ተመራማሪዎች፣ በአሜሪካ የሚኖሩ የአይሲስን አላማ የሚያቀነቅኑ ግለሰቦች በተለይም ትዊተር በተባለው ማህበራዊ ድረገጽ አማካይነት የፕሮፓጋንዳና የምልመላ ስራቸውን እንደሚያከናውኑ የገለጹ ሲሆን ምንም እንኳን ትዊተር፣መሰል አካውንቶችን በተደጋጋሚ ቢዘጋም የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ግን አልቀነሰም ብለዋል፡፡ ትዊተር ከአይሲስ ጋር ንክኪ አላቸው ብሎ የሚገምታቸውን አካውንቶች እየተከታተለ ቢዘጋም፣ ተጠቃሚዎቹ በሰዓታት እድሜ ውስጥ አዲስ አካውንቶችን በመክፈት፣ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ያህል የተከታይ ቁጥር እያገኙ ነው ብለዋል አጥኚዎቹ፡፡
ተጠቃሚዎቹ በዋናነት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ከሽብር ጋር በተያያዙ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚወያዩና የሽብር ቡድኖች በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጽሟቸውን የሽብር ጥቃቶችም ሲደግፉና ሲያደንቁ እንደተገኙ ዘገባው ገልጧል፡፡