Administrator

Administrator

- አወዛጋቢው የአገሪቱ ምርጫ ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል
- ክልላዊው ፍርድ ቤት ግጭቱን ማጣራት ጀምሯል
       በመጪው ማክሰኞ ይከናወናል ተብሎ ከሚጠበቀው የብሩንዲ ምርጫ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተቀሰቀሰውን ግጭት መፍታት የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒ አደራዳሪነት ውይይት ሊያደርጉ ነው ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለወራት የዘለቀውን የብሩንዲ ግጭት ለማስቆምና በፖለቲካ ሃይሎች መካከል የተፈጠረውን ችግር በድርድር ለመፍታት ሙከራ ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል ያለው ዘገባው፤ ዩሪ ሙሴቬኒ የአገሪቱን መንግስትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራሮችን ለማደራደር ባለፈው ማክሰኞ ቡጁምቡራ መግባታቸውን ገልጿል፡፡
አምስት የምስራቅ አፍሪካ አገራትን በአባልነት በያዘው የኢስት አፍሪካ ኮሚዩኒቲ ድርድሩን እንዲመሩ ባለፈው ሳምንት የተመረጡት ሙሴቬኒ፣ በመጪው ማክሰኞ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀውን አወዛጋቢ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሰላማዊ ለማድረግና ተልዕኳቸውን ለማሳካት የቻሉትን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡ ሙሴቬኒ ባለፈው ማክሰኞ ከብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ መወያየታቸውንም ዘገባው ገልጿል። ክልላዊው የምስራቅ አፍሪካ የፍትህ ፍርድ ቤት በበኩሉ፤ በብሩንዲ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ ከሳምንታት በፊት የቀረበለትን ክስ በታንዛኒያ መዲና አሩሻ ባለፈው ማክሰኞ የምርመራ ሂደት መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ፓን አፍሪካን ሎየርስ አሶሴሽንና ኢስት አፍሪካን ሲቪል ሶሳይቲ ፎረም የመሰረቱት ክስ፣ የብሩንዲ የህገመንግስት ፍርድ ቤት ለግጭቱ መንስኤ የሆኑት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ በምርጫው መሳተፍ ይችላሉ በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔ እንዲሻር የሚጠይቅ ነው ተብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ ባለፈው ሚያዚያ ወር ላይ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ማስታወቃቸውን ተከትሎ በአገሪቱ በተቀሰቀሰውና ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ77 ሰዎች በላይ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ100ሺህ በላይ ዜጎችም ወደ ጎረቤት አገራት መሰደዳቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

     ከ10 አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ተከታትለዋል
   ደቡብ አፍሪካዊው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ ሊቃነ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ ባለፈው ማክሰኞ ባጋጠማቸው ህመም ኬፕታውን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ምንነቱ በውል ባልተገለጸ በሽታ ተጠቅተው ሆስፒታል የገቡት የ83 አመቱ ዴዝሞን ቱቱ፤ ከአስር አመታት በላይ የፕሮስቴት ካንሰር ህክምና ሲደረግላቸው እንደቆየ ያስታወሰው ዘገባው፣ ወደ ሆስፒታል ያስገባቸው የሰሞኑ ህመም ግን፣ ከዚህ ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑ አለመታወቁን ገልጿል፡፡ የዴዝሞን ቱቱ ልጅ ሞህ ቱቱ አባቷ ተገቢውን ህክምና በማግኘት ላይ እንደሆኑና በጥቂት ቀናት ውስጥ አገግመው ከሆስፒታል ይወጣሉ የሚል ተስፋ እንዳላት መናገሯን ዘገባው ጠቁሞ፣ ኢንፌክሽን ከመሆኑ ውጪ የህመማቸውን ምንነት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱን ጠቁሟል፡፡
ከአስር አመታት በላይ በፕሮስቴት ካንሰር ህክምናቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ዴዝሞን ቱቱ፣ ባለፈው ታህሳስ ወር ላይም ወደ ሮም ለመጓዝ ይዘውት ነበረውን እቅድ ህክምናቸውን ለመከታተል ሲሉ መሰረዛቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአፓርታይድ አገዛዝን በጽናት በመቃወም የሚታወቁት ዴዝሞን ቱቱ፤ እ.ኤ.አ በ1984 የኖቤል የሰላም ሽልማትን እንደተቀበሉና ከቀናት በፊትም ከባለቤታቸው ሊያ ጋር የጋብቻቸውን 60ኛ አመት በዓል ማክበራቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ባለፈው ግንቦት በምርጫ አሸንፈው ስልጣን የያዙት አዲሱ የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ፣ አሸባሪውን ቡድን ቦኮ ሃራም ለመደምሰስ የያዙትን ቀዳሚ እቅዳቸውን በአግባቡ ለማሳካት በሚል የቀድሞ የአገሪቱ የምድር ጦር፣ የባህር ሃይል፣ የአየር ሃይልና የመከላከያ መሪዎችን ከስልጣናቸው ማባረራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን ባለፉት ስድስት አመታት በአገሪቱ ሰሜን ምስራቃዊ አካባቢዎች 13ሺህ ያህል ዜጎችን ለህልፈተ ህይወት በዳረገውና 1.5 ሚሊዮን ዜጎችን ባፈናቀለው ቦኮ ሃራም ላይ ተገቢ እርምጃ አልወሰዱም በሚል በስፋት ሲወቀሱ እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ቡሃሪ የሽብር ቡድኑን ሙሉ ለሙሉ ለመደምሰስ እንደሚሰሩ ቃል መግባታቸውንና የጦር መሪዎችን ማባረራቸውም የዕቅዳቸው አንዱ አካል መሆኑን ገልጿል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ከስልጣናቸው ያባረሯቸው የጦር መሪዎች፡- ማርሻል አሌክስ ባዴህ፣ ሜጀር ጄኔራል ኬንዝ ሚናማህ፣ ሪር አድሚራል ኡስማን ጂብሪንና ምክትል ማርሻል አዴሶላ አሞሱ ናቸው ተብሏል፡፡
በምርጫው አሸንፈው ስልጣን ከያዙ፣ የመጀመሪያ ተልዕኳቸው የሚያደርጉት ቦኮ ሃራምን መደምሰስ እንደሆነ ሲገልጹ የነበሩት ቡሃሪ፣ ግንቦት ወር ላይ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ፣ የአገሪቱን የመከላከያ ዕዝ መቀመጫ የአሸባሪ ቡድኑ መፈጠሪያ ናት ወደምትባለው ሜዱጉሪ ማዛወራቸውንና፣ ቡኮሃራምን ለመደምሰስ ያለመውን የአገራት ጥምር ሃይል ማዘዣ ጣቢያም በቻድ መዲና ጃሜና ማቋቋማቸውንም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

ጥርስ ድህነት አይታየውም፡፡
የማሳዮች አባባል
ትዕግስት ከሌለህ ቢራ መጥመቅ አትችልም።
የአቫምቦ አባባል
የእንቁላል ቅርጫት ተሸክመህ አትደንስ፡፡
የአምቤዴ አባባል
የአይጥ ልጅ አይጥ ናት፡፡
የማላጋሲ አባባል
ላልተወለደ ልጅ ስም ማውጣት አትችልም።
የአፍሪካውያን አባባባል
በሽምግልናህ የተቀመጥክበት ቦታ በወጣትነትህ የቆምክበትን ቦታ ያሳያል፡፡
የዩሩባ አባባል
የሚሸሽን ሰው አትከተለው፡፡
የኬንያውያን አባባል
ቤት ስታንፅ ምስማሩ ቢሰበርብህ፣ ማነፁን ትተወዋለህ ወይስ ምስማር ትቀይራለህ?
የሩዋንዳውያን አባባል
እናቱ የሞተችበት ጥጃ የራሱን ጀርባ ይልሳል።
የኬንያውያን አባባል
ንዴትና እብደት ወንድማማች ናቸው፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
አንዲት ደስታ መቶ ሃዘኖችን ታዳብራለች፡፡
የቻይናውያን አባባል
 ፍቅር ለአሉባልታ ጆሮ የለውም፡፡
የጋናውያን አባባል
ሙሉ ጨረቃ ከወደደችህ፤ የክዋክብቶቹ ለምን ያስጨንቅሃል?
የቱኒዚያውያን አባባል

 ለቤጂንግ 44 አትሌቶች ያሉበት የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ቡድን ታውቋል
                               
           9ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮሎምቢያዋ ከተማ ካሊ ባለፈው ሐሙስ ሲጀመር ኢትዮጵያ የመጀመርያ የወርቅ ሜዳልያዋን በ3ሺ ሜትር በማስመዝገብ ጥሩ አጀማመር አሳይታለች። የወርቅ ሜዳልያውን ያገኘችው አትሌት ሹሩ ቡሎ ስትሆን በ3ሺ ሜትር ሴቶች ያሸነፈችው የሻምፒዮናውን ፈጣን ሰዓት በ9 ደቂቃዎች  ከ01.12 ሰከንዶች አስመዝግባ ነው፡፡ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ 10 ሴትና 10 ወንዶች ባካተተ ቡድኗ የምትሳተፍ  ሲሆን ሻምፒዮናው ነገ ሲጠናቀቅ ቢያንስ  9 ሜዳልያዎች ሶስት ወርቅ፤ 3 የብርና 3 የነሐስ እንደምትሰበስብ ግምት አለ፡፡ በዓለም የታዳጊዎች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን በሁለቱም ፆታዎች የወከሉት 20 አትሌቶች አሰላ ላይ ለሶስተኛ ጊዜ በተደረገው የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመሳተፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ መሆናቸውን ያስታወቀው ፌደሬሽኑ የወደፊት የአገሪቱን ኮከብ አትሌቶች ለማግኘት ዓለም አቀፍ ውድድሩ ወሳኝ እንደሆነ አምኖበታል። በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የሚዘጋጀው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ በ16 እና 17 ዓመት የእድሜ ክልል የሚገኙ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በ40 የውድድር መደቦች ይሳተፉበታል።  ከ800 እስከ ሁለት ሺህ ሜትር  የሩጫና እርምጃ  ውድድሮች የሻምፒዮናው አካል ናቸው፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት በዩክሬኗ ከተማ ዶኔትስክ ላይ ተደርጎ በነበረው 8ኛው የዓለም ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የኢትዮጵያ ቡድን  ሶስት የወርቅ፣ ሶስት የብር እና ሁለት የነሐስ ሜዳሊያ በመሰብሰብ ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
በተያያዘ ከወር በኋላ በቻይናዋ ከተማ ቤጂንግ ለሚደረገው 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ለሚወክለው ቡድን የተመለመሉ አትሌቶች  ጊዜያዊ ስም ዝርዝርን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል አስታወቀ።  በነሐሴ ወር አጋማሽ  በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ኢትዮጵያ በ800 እና 1500 ሜትር መካከለኛ ርቀት፤ በ3ሺ ሜትር መሰናክል፤ በረጅም ርቀት 5ሺ እና 10ሺ ሜትር እንዲሁም በማራቶን ውድድሮች በምትሳተፍበት ቡድን 44 አትሌቶች በጊዜያዊ ስም ዝርዝሩ ገብተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኮሙኒኬሽን ክፍል ሐምሌ 9/2007 ዓ. ም. ይፋ ያደረገው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ ቡድን ጊዜያዊ ቡድን የአትሌቶች  ስም ዝርዝር ከዚህ በታች የቀረበው ነው፡፡
በ800 ሜትር በወንዶች መሃመድ አማንና ጀና ኡመር እንዲሁም በሴቶች ሃብታም አለሙ፣ ባይህ ጫልቱ ሹሜ ረጋሳና ኮሬ ቶላ ነገሆ
በ1500  ሜትር በሴቶች ዳዊት ስዩም ፣ ሰንበሬ ተፈሪ ፣አክሱማዊት እምባዬና ጉዳፍ ፀጋዬ እንዲሁም በወንዶች ሱር አማን ወጤ እና መኮንን ገ/መድህን
በ5 ሺ ሜትር ዘጠኝ እንዲሁም በ10ሺ ሜትር ስምንት አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በጊዜያዊ ዝርዝሩ ተካትተዋል፡፡ በ5ሺ ሜትር ወንዶች ዮሚፍ ቀጀልቻ፣ ሐጐስ ገ/ህይወት ደጀን ገ/መስቀልና የኔው አላምረው ሲሆኑ በሴቶች ደግሞ  አልማዝ አያና፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ አለሚቱ ሃዊ  አዝመራ ገብሩ
በ10 ሺ ሜትር ወንዶች ሙክታር አድሪስ፣ ኢማነ መርጊያ፣ ሞስነት ገረመውና  አዱኛ ታከለ፤ በሴቶች ደግሞ ገለቴ ቡርቃ፣ አለሚቱ ሃሮዬ ፣በላይነሽ ኦልጅራ እና  ማሚቱ ዳስካ
በ3000 ሜትር መሠናክል በሁለቱም ፆታዎች ስምንት አትሌቶች ሲያዙ በሴቶች ሕይወት አያሌው፣ ሶፊያ አሰፋ፣ ብርቱካን ፋንቴና ትዕግስት ጌትነት  እንዲሁም በወንዶች ጂክሳ ቶሎሳ፣ ኃ/ማርያም አማረ፣   ታፈሰ ሰቦቃና  ጫላ በዩ
በማራቶን በሴቶች   ትርፌ ፀጋዬ፣ ማሬ ዲባባ፣ ትዕግስት ቱፋ፣ ብርሃኔ ዲባባ  ተይዘው፤ በወንዶች ደግሞ ሌሊሳ ዲሳሳ ፣ የማነ ፀጋዬ፣ ለሚ ብርሃኑ እና እንደሻዉ ካሳ

   በአብያታና ሻላ ሃይቆች በሚገኙት ፓርኮች እና ተራራማ ስፍራዎች የሚካሄደው የኢትዮትሬል የተራራ ላይ ሩጫ ውድድር እድገት በማሳየት ከወር በኋላ እንደሚካሄድ ታወቀ፡፡ ለሯጮች፤ ለተራራ ወጪዎች እና ተጓዦች እንዲሁም ሙሉ ቤተሰብ  አሳታፊ ለሆኑት የኢትዮትሬል  ውድድሮች የዓለም አቀፍ ተሳታፊዎች ጉጉት አስደናቂ ሆኗል፡፡  ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ በሚካሄደው  የኢትዮ ትሬል የተራራ ላይ ሩጫ በሶስት ርቀቶች በ42፤ በ21 እና 12 ኪሎሜትሮች ተካፋፍሎ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ለስፖርት አአድማስ በላኩት መግለጫ አመልክተዋል፡፡ የተራራ ላይ ሩጫው በኢትዮጵያ የስፖርት ቱሪዝምን ለማስፋፋት እና ጤናማ አኗኗርን ለማበረታታት የሚዘጋጅ ነው፡፡ ዘንድሮ በዓለም አቀፉ የትራያል ሩጫ ማህበር አባልነት የተመዘገበው ኢትዮትሬል ከዓለም 50 መሰል ሩጫዎች አንዱ ሆኖም ተጠቅሷል፡፡ ባለፈው ዓመት ውድድሩ ሲካሄድ ከአገር ውስጥ እና ከባህርማዶ እስከ 300 ተሳታፊ ስፖርተኞች እና 2000 ተመልካቾች የነበሩት ሲሆን ዘንድሮ የተሳታፊዎቹን ቁጥር ወደ 800 እንደሚያሳድግና ታዳሚዎቹም ከ3ሺ በላይ እንደሚሆኑ ተጠብቋል፡፡

Saturday, 18 July 2015 11:33

ፀጉርዎ እየሳሳ ነው….?

   የፀጉር መሳሳት የበሽታ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ የታይፎይድ እጢና የስኳር በሽታዎች የፀጉር መሳሳትን የሚያስከትሉ በሽታዎች ናቸው፡፡ ችግሩ ከመባባሱና አስከፊ ሁኔታ ላይ ከመድረስዎ በፊት ሃኪምዎን ያማክሩ፡፡
አመጋገብዎን ያስተካክሉ፡፡ የተስተካከለ አመጋገብ ጤናዎንና አካልዎን ብቻ ሳይሆን በፀጉርዎ ላይም የራሱን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖዎች ማሳረፍ ይችላል፡፡ ስለዚህም ስለሚመገቡት ምግብ ምንነትና ጠቀሜታ አብዝተው ይጨነቁ፡፡
አዕምሮዎንም ሆነ ሰውነትዎን ያሳርፉ፡፡ ድካምና እረፍት ማጣት የፀጉር መመለጥን (መሳሳትን) ከሚያስከትሉ ምክንያቶች ዋንኞቹ ናቸው። ህይወትዎ ምንም ያህል በውጥረት የተሞላ እንኳን ቢሆን ለራስዎ ጊዜና እረፍት መስጠት ይኖርብዎታል፡፡  እንደ ዮጋና ሜዲቴሽን፣ ያሉ ነገሮች ጭንቀትና ውጥረትን ለማስወገድ እጅጉን ይረዳሉ፡፡ ለፀጉርዎ የሚጠቀሟቸውን ሻምፖና ኮንድሽነሮች እንዲሁም የሚቀቧቸውን ቀለማት ምንነትና አጠቃቀም በደንብ ይረዱ፡፡ በአግባቡ ያልተረዷቸውን ምርቶች ከመጠቀም ይቆጠቡ፡፡
በሻምፖ፣ በኮንድሽነሮችና በፀጉር ማቅለሚያዎች ውስጥ ያሉት ኬሚካሎች የፀጉር መሳሳትና መመለጥን ከሚያፋጥኑ ነገሮች መካከል በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ ይልቅ ተፈጥሮአዊ ይዘታቸውን ያልለቀቁ ንጥረነገሮችን አዘውትረው ይጠቀሙ።

  ወቅቱ ክረምት ነው፡፡ ልጆች የዓመቱ ትምህርታቸውን አጠናቀው እረፍት የሚያደርጉበት ጊዜ፡፡  በዚህ የክረምት ወቅት ልጆች እንደየአካባቢያቸው፣ እንደየቤታቸውና እንደየልማዳቸው የእረፍቱን ጊዜ የሚያሳልፉባቸው መዝናኛዎች አሏቸው፡፡
በአሁኑ ጊዜ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች በስፋት እየተለመዱ ከመጡ የልጆች መዝናኛዎች መካከል ፊልሞች፣ ጌሞችና ፕሌይ ስቴሽኖች ይጠቀሳሉ፡፡
በተለይ የተለያዩ ጌሞችን ከኢንተርኔት በቀጥታ በመውሰድ ልጆች በስልኮች፣ በላፕቶፖችና በቲቪ ስክሪኖች ጭምር እንዲጫወቱበት ማድረግ እየተለመደ መጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ እነዚህ ጌሞች ከመዝናኛነት ባለፈ ልጆችም ትምህርት የሚያገኙባቸው እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለልጆችዎ የሚመርጧቸው ጌሞች ቀለል ባለ መልኩ ህፃናት እየተዝናኑ እንዲማሩባቸው ሆነው የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል። ለህፃናት በሚመች መልኩ የተሰሩና ህጸናትን እያዝናኑ ለመማር ያስችላሉ የሚባሉ ጌሞችን ከያዙ ድረ-ገፆች መካከል ጥቂቶቹን እነሆ፡-
Learning games for kids
በዚህ ዌብሳይት ላይ ያሉት ጌሞች በተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮች የተከፋፈሉ ናቸው
Educational songs and videos
የህፃናት መዝሙሮችንና ሳይንስና ምርምር ነክ የሆኑ ነገሮችን ቀለል ባለ ሁኔታ የሚያስረዱና ዝግ ባለ እንቅስቃሴ የተዘጋጁ ቪዲዮዎች የሚገኙበት ክፍል ነው፡፡    
Health games
ልጆች ስለ አለርጂክ፣ ስለ ጥርስ ጤና አጠባበቅ፣ ስለ ጤናማ ሰውነት አቋም እንዲያውቁ የሚያግዙ መረጃዎችን በአዝናኝ መንገድ ያቀርባል፡፡  
Maths games
ልጆች በጨዋታ መልክ ስለ ሂሳብ ጠቃሚ ዕውቀቶችን የሚገበዩበትና የሂሳብ ችሎታቸውን የሚያሻሽሉበት ጌሞችን የያዘ ክፍል ነው፡፡
Geography games
ልጆች የተለያዩ የዓለም ክፍሎችን እንዲያውቁ የሚረዱ ጌሞች የተካተቱበት ነው፡፡
Science games
በእንስሳት፣ በተፈጥሮና፣ በህዋ ላይ ባሉ ሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ ተመስርተው የተሰሩና ለልጆች መሠረታዊ ዕውቀትን የሚያስጨብጡ ጌሞች ያሉበት ነው፡፡
Keyboarding games
ልጆች በኮምፒዩተር የመፃፍ ችሎታቸውን እንዲሁም የቋንቋ ዕውቀታቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውና ጥሩ ክህሎትን የሚጨብጡበት ጌሞች የሚገኙበት ክፍል ነው፡፡
Miscellaneous games  
እኒህ ልጆችን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ልዩ ልዩ ጨዋታዎችን ያካተቱ ጌሞች ናቸው፡፡
Pre-school games  
በአፀደ ህፃናት ደረጃ ላይ ያሉ ህፃናትን እያዝናኑ የሚያስተምሩ ጌሞች ይገኙባቸዋል፡፡
ወላጆች፡- ልጆቻችሁ አልባሌ ፊልሞችን እያዩ ጊዜያቸውን ከሚያጠፉ እንዲህ ዓይነት ጌሞችን በመጫን፣ የእረፍት ጊዜያቸውን የትምህርትና የመዝናናት ብታደርጉላቸው አይሻልም?! 

      በእስልምና ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበሩ ሁለት ኢዶች (በአሎች) አሉ፡፡ የመጀመሪያው የረመዳን ፆምን ማብቃት የሚያበስረው ኢድ - አልፈጥር ሲሆን፣ ሁለተኛው ደሞ ከሁለት ወራት በኋላ የሐጂ ስነ - ስርዓትን ተከትሎ የሚመጣው ኢድ - አልአድሓ (የእርድ በዓል ነው፡፡ ረመዳን ተጠናቆ የምናከብረው በዓል ኢድ አልፈጥር) ስለሆነ እኔም የማወራችሁ ስለዚሁ ክብረበዓል አጠቃላይ ገፅታ ነው፡፡
ረመዳን፤ ሙስሊም ምእመናን ራሳቸውን የሚያንፁበት፣ ወደ አምላክ የሚቀርቡበት የኢማን እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ የፆም ወር ነው። የረመዳን ወር ከሌሎቹ ወራቶች የተለየና  ትልቅ የሚያደርገው፣ ምእመናን ፀሐይ ከመውጣቷ በፊት አንስቶ እስከ ጠለቀችበት  ድረስ ከምግብ፣ ከውሐ፣ ከወሲብ ግንኙነት (ህጋዊ ትዳርን ጨምሮ)፣ ከመጥፎ ንግግር እና ባህሪ የተቆጠቡ መሆን ስላለባቸው ነው፡፡ በእርግጥ ህጋዊ ያልሆነ ወሲብን ጨምሮ ሌሎቹ መጥፎ ባህሪያት በሌላው ወር ይፈቀዳል ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የወሩን ታላቅነት አፅንኦት ለመስጠት አላህ የደነገጋቸው ህጎቹ ናቸው። በተጨማሪም 30 ጁዝ (ምዕራፍ) የያዘውን ቅዱስ ቁርአንን ምዕመናን በረመዳን አንብበው የሚያጠናቅቁበት ወር ነው፡፡
የረመዳንን ወር ከአንድ አነስተኛ የማሰልጠኛ ተቋም ጋር ማመሳሰል እንችላለን፡፡ በአንድ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሆነ ዘርፍ አጥንተን እውቀትና ስነ - ምግባሮች እንደምንጨብጠው ሁሉ፤ በረመዳን ወቅትም በቁርአን እውቀት አዕምሯችንን አበልፅገን፣ በመንፈሳዊ እሴቶች ተሐድሶ ወስደን የምንወጣበት ወር ነው፡፡ ወይም ደግሞ በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ሰልጣኞች አካላቸውን ለማፈርጠም እና የሰውነታቸውን ጥንካሬ ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልጠናዎችን እንደሚወስዱት ሁሉ፤ በረመዳንም ምእመናን መንፈሳዊ ጥንካሬን ለማግኘት እምነቱ የሚያዘውን አመጋገብ ዘይቤ ይለውጣሉ፡፡ እንዲሁም በረመዳን ወር ብቻ የሚገኙ ሃይማኖታዊ ስልጠናዎችን ተግብረው ቀሪውን ህይወታቸውን ከፈጣሪ ጋር ለማቀራረብ ይሞክራሉ፡፡ በጎ ስራዎችን ማሳደግ እና የአምልኮ ስርአቶችን በብዙ መፈፀም ሌሎቹ የስልጠና ግብአቶች ናቸው፡፡
ራሳችንን ከምግብና ከውሃ ማቀብ፣ በድህነት ለሚኖሩ ሚስኪኖች እንድናስብ ያደርገናል፡፡ ምግብና ውሃ አጥቶ መኖር ምን እንደሚመስል የምናውቀው በረመዳን ወር ነው፡፡ ምግብና ውሃ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የቅንጦት ነገሮችን ማጣት ያለውን ስሜት በረመዳን ወር ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ራስን ዝቅ አደርጎ ለፈጣሪ መስገድ ያለውን እርካታ ረመዳን ይነግረናል፡፡ ማፍጠሪያ ሰዓት ደርሶ ከቤተሰብ እና ከወዳጆች ጋር ተሰብስቦ አብሮ መብላት ራሱን የቻለ የማህበራዊ በጎ እሴት ነው፡፡ ከነዚህ ስልጠናዎች በኋላ የሚቀረን ተመርቆ ከስልጠናው መሰናበት ነው፡፡ የረመዳን ምረቃ ደግሞ ኢድ - አልፈጥር ነው። ምእመናን ኢድ - አልፈጥርን በማክበር ከረመዳን ስልጠናዎች ተመርቀው ይወጣሉ፡፡
ኢድ - አልፈጥር ትርጉሙ ራሱ የፆም ማጠናቀቂያ ክብረ - በአል እንደማለት ነው፡፡ በአብዛኛው “የአለም ሀገሮች ውስጥ ለ3 ቀናት በድምቀት ይከበራል፡፡
ኢድ አልፈጥር በብዙ ሀገሮች በተለያዩ መንገዶች ቢከበርም የጋራ የሆነ አንድ ነገርን ይዟል፡፡ ይሄውም በበአሉ ቀን ሁሉም አማኞች በጧት ተነስተው ልዩ የሶላት ስግደት ወደሚደረግበት ቦታ ይተማሉ። በኛ ሀገር ምእመናን በለሊት 11 ሰዓት ተነስተው ወደ ስግደት ከመሄዳቸው  በፊት ተሰብስበው ገንፎ በቅቤ ወይም በተልባ ይበላሉ፡፡ አሁን አሁን ብዙም ባይስተዋልም እንጀራ በፌጦ የመጉረስ ልማድ ነበር። (በሀገራችን ለዘመን መለወጫ መስከረም ላይ እንደሚደረገው አይነት)
የኢድ-አልፈጥር ስግደት የሚደረገው በመስጂድ ውስጥ ወይም ሁሉንም አማኝ ሊያሰባስብ በሚችል አንድ ገላጣ ቦታ ላይ ነው፡፡ የእምነቱ ተከታዮች በቡድን እየሆኑ ተክቢራ በማድረግ (የበአሉ የውዳሴ ዜማዎች) ወደ ስግደቱ ቦታ ይተማሉ፡፡ በሀገራችን ውስጥ ሙስሊሞች ከተለያዩ አቅጣጫዎች በቡድን እየሆኑ፣ ተክቢራ እያደረጉ ወደ ስታዲየም እንደሚሄዱት ማለት ነው፡፡
ከስግደት መልስ ምእመናን የበአል ድግስ አድርገው ከቤተሰብ፣ ከዘመድ - አዝማድ እንዲሁም ከጐረቤት ጋር በአሉን በደስታ ያሳልፋሉ፡፡ ቤተ ዘመዶችን እየዞሩ መጠየቅና እንኳን አደረሳችሁ ማለት የኢድ አልፈጥር ልዩ ባህሪው ነው፡፡ የምግቡ አይነት እንደየባህሉ ከሀገር ሐገር ቢለያይም፣ ልዩ ምግቦችን ማዘጋጀት ግን የማይቀር ጉዳይ ነው። በተለይ ህፃናቶች በኢድ አልፈጥር ጊዜ በአዲስ ልብሶች አጊጠው በዘመድ አዝማድ ቤቶች እየዞሩ “የሚናኢድ” በማለት ሳንቲሞችን ይቀበላሉ፡፡ ይህ በአል በህፃናቶች ዘንድ ልዩ በመሆኑ ከቤተሰብና ከዘመድ አዝማድ የሚሰበሰቡት ሳንቲሞች በጣም ብዙ ናቸው፡፡
አንድ ሙስሊም በረመዳን ማፍጠሪያ ወቅት ምጽዋት ያልሰጠ ከሆነ የኢድ አልፈጥርን በአል ተጠቅሞ ለሚስኪኖች ዞካ መስጠት አለበት፡፡ የምግብ አልያም የገንዘብ ስጦታ ሊሆን ይችላል፡፡ ብዙ ሙስሊሞች የበአል ድግስ አድርገው ደሐዎችን ያበላሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የታረዙትን ያለብሳሉ፡፡ ምንም ይሁን ነገር ግን በኢድ አልፈጥር በአል ወቅት ለድሐዎች የምጽዋት እጆችን መዘርጋት ሐይማኖቱ የሚመክረው በጐ ተግባር ነው፡፡ መልካም የኢድ አልፈጥር በአል ለመላው የእስልምና ተከታዮች በሙሉ እንዲሆን እየተመኘሁ እሰናበታለሁ፡፡  

Saturday, 18 July 2015 11:23

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ንባብ)
- ግሩም መፅሐፍ መጨረሻ የለውም፡፡
አር.ዲ. ከሚንግ
- ባህልን ለማጥፋት መፃህፍትን ማቃጠል
አያስፈልግም፡፡ ሰዎች ማንበብ እንዲያቆሙ ብቻ
ማድረግ በቂ ነው፡፡
ሬይ ብራድበሪ
- መፅሃፍ በእጅህ የምትይዘው ህልም ነው፡፡
ኔይል ጌይማን
- ሁሉም ሰው የሚያነባቸውን መፃህፍት ብቻ
የምታነብ ከሆነ፣ ሁሉም ሰው ከሚያስበው
ውጭ አታስብም፡፡
ሃሩኪ ሙራካሚ
- ራስህ የማታነበውን መፅሃፍ ለልጅ አለመስጠትን
መመሪያህ አድርገው፡፡
ጆርጅ በርናርድ ሾው
- በመፃህፍት ካልተከበብኩ በቀር እንቅልፍ
መተኛት አልችልም፡፡
ጆርጅ ሉዊስ ቦርጅስ
- መፅሃፍ ምናብን የሚያቀጣጥል መሳሪያ ነው፡፡
አላን ቤኔት
- የሰው ማንነት በሚያነባቸው መፃህፍት
ይታወቃል፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰን
- መፅሃፍ ስታነቡ ፈፅሞ ብቻችሁን አይደላችሁም።
ሱሳን ዊግስ
- ጥቂት ገንዘብ ሳገኝ መፃህፍት እገዛበታለሁ፡፡
ከዚያ ከተረፈኝ ምግብና አልባሳት እሸምታለሁ፡፡
ኢራስመስ
- እንደ መፅሃፍ ያለ ታማኝ ጓደኛ የለም፡፡
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
- የምናነበው ብቻችንን አለመሆናችንን ለማወቅ
ነው፡፡
ሲ.ኤስ.ሌዊስ
- አሮጌውን ኮት ልበስና አዲሱን መፅሃፍ ግዛ፡፡
ኦዩስቲን ፉልፕስ
- ብዙ አንብቦ ትንሽ ከማሰብ፣ ትንሽ አንብቦ ብዙ
ማሰብ ይሻላል፡፡
ዴኒስ ፓርስንስ ቡርኪት
- ህፃናት አንባቢያን የሚሆኑት በወላጆቻቸው
ጭን ላይ ነው፡፡
ኢሚሊ ቡችዋልድ
- ንባብ ዘላቂ ደስታ ያጎናጽፋችኋል፡፡
የአሜሪካ ቀዳሚ እመቤት ላውራ ቡሽ
- ሁሉም አንባቢያን መሪዎች አ ይደሉም፤ ሁ ሉም
መሪዎች ግን አንባቢያን ናቸው፡፡
ሐሪ ኤስ. ትሩማን
- ንባብን ማስተማር ሮኬት ሳይንስ ነው፡፡
ሉዊስ ሞትስ
- የዛሬ አንባቢ፣ የነገ መሪ ነው፡፡
ማርጋሬት ፉለር
- በልጅ ህይወት ውስጥ መፃህፍትን የሚተካ
የለም፡፡
ሜይ ኤለን ቼስ