Administrator

Administrator

የሸራተን አዲስ ሆቴል ሰራተኞች፤ የውጭ አገር ዜጋ በሆኑት የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ የሚደርስብን ችግር ከአቅም በላይ በመሆኑ ሰላማዊ ሰልፍ ልንወጣ ነው አሉ፡፡ ከዚህ በፊት  የመብት ጥሰት እንደደረሰብን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በደብዳቤ ብንገልፅም ምላሽ ባለማግኘታችን በድጋሚ ደብዳቤውን አስገብተናል ብለዋል - ሰራተኞቹ፡፡
በትምህርት ደረጃና በእውቀት ከሀበሾቹ የማይበልጡ የውጭ ዜጐች አሰሪዎቻችን ያንቋሽሹናል፤ ዛሬ ፆም ነው ይህን አንበላም ስንል “ድሮ ረሀብተኞች ስለነበራችሁ ረሀባችሁን ለማስታወስ የምታደርጉት ነው” ይሉናል፤ ጥቅማጥቅሞቻችን አይከበሩም፣ እድገት እንከላከላለን ያሉት ሠራተኞቹ፤ “ፈረንሳዊው ስራ አስኪያጅ ዲፓርትመንቶችን በመበታተን፣ ሰራተኞችን ወዳልፈለጉትና ወደማይመለከታቸው ቦታ ይመድባሉ፤ ይህን ስንቃወም እስከመደብደብ እንደርሳለን” ብለዋል፡፡
“የዜጐች ደህንነት ጥበቃ ከአገር ውስጥ ይጀምራል፤ በአገራችን ነጮች እያንቋሸሹን እና ሞራላችን እየተነካ ነው” የሚሉት ሰራተኞቹ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግራችንን በዝምታ ማለፋቸው አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
“ችግራችን ሲብስ ፒቲሽን ተፈራርመን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያስገባነው ደብዳቤ፤ ለሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ለሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ከደረሰ በኋላ፣ ስቃያችን በዝቷል ያሉት ሰራተኞቹ፤ አንድ ነገር ለማስፈቀድ፣ አቤቱታ ለማሰማትና ለእድገት ለመወዳደር ስንጠይቅ ስራ አስኪያጁ  ፒቲሽን የፈረሙትን ሰራተኞች ስም ያወጡና “በእኔ ላይ ፈርመሀል፤ እድሜ ልክህን እድገት አታገኝም፣ ይህ አይፈቀድም” እያሉ እንደሚያንገላቷቸው ተናግረዋል፡፡ ሸራተን አዲስ ሆቴል ከ800 በላይ ቋሚ ሰራተኞች እንዳሉት የገለፁት ሰራተኞቹ፤ ይህ ሁሉ ሰራተኛ ባለበት ስራ አስኪያጁን ጨምሮ አንዳንድ የውጭ አሰሪዎቻችን እያንጓጠጡንና ጫና እየፈጠሩብን ስለሆነና የሚመለከተው የመንግስት አካል ምላሽ ስላልሰጠን በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት አስበናል ብለዋል፡፡
የሆቴሉ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበሩ አቶ ዳንኤል አለሙ ታሪኩ በበኩላቸው፤ “ሰራተኞቹ ከማህበሩ ወጥተው በራሳቸው ተደራጅተዋል፤ ነገር ግን ማኔጅመንቱና ሰራተኛው ተቀራርበው እንዲሰሩና በውይይት ችግራቸውን እንዲፈቱ ብዙ ርቀት ብንሄድም የሆቴሉ ስራ አስኪያጅ ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍ ፈቃደኛ አልሆኑም” ብለዋል፡፡
የሆቴሉን ስራ አስኪያጅ  ሚስተር ዦን ፒይር ማኒንጐፍን ለማነጋገር ብንሞክርም እረፍት ላይ በመሆናቸው ሳይሳካልን ቀርቷል፡፡ ሌላ ሃላፊ ለማነጋገር ፀሃፊዋን ጠይቀን፤ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሚሰጡት ስራ አስኪያጁ ብቻ እንደሆኑ ገልፃልናለች፡፡    

“የጐበዝ አለቃ” እሽ ያለውን በፈቃዱ፣ እምቢ ያለውን በግድ የሚገዛ ወንዝ አፍራሽ ገዥ ነው። የጐበዝ አለቃ የመሰለውን ይፈርዳል እንጂ ሕግ የሚባል ነገር አይገባውም፤ ወይም ለሕግና ሥርዓት ደንታ የለውም፡፡
የጐበዝ አለቆች ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱት የመንግሥት አቅም ሲላላ ወይም “መንግሥት የለም” ብለው ሲያምኑ ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ማይጨው ላይ ሠራዊታቸውን ለነጭ አሞራ በትነው ወደ እስራኤል ቀጥሎም ወደ እንግሊዝ የሄዱ ጊዜ የተከሰተውን ማንሳት ለርዕሰ ጉዳያችን ጥሩ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ንጉሡ በመሸሻቸው አገሪቱ ያለ መሪ ቀረች፤ በአንጻሩ ጣሊያኖች ፋሽስታዊ ቅጣታቸውን በወታደሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በህፃናትና ሴቶች፣ በመነኮሳትና እንስሳት ላይ ሳይቀር እየፈፀሙ በማስቸገራቸው ህዝቡ ተቃውሞውን ለመግለጽ መደራጀት ነበረበት፡፡ ግን የሚያደራጀውም ሆነ የተደራጀ አካል በማጣቱ የሚያስተባብሩትን የጐበዝ አለቆች መፈለግ ነበረበት፡፡ ስለሆነም በጊዜው ጉልበት ያለው ሁሉ የጐበዝ አለቃ ሆነ፡፡ በላይ ዘለቀ፣ አበበ አረጋይ፣ ገርሱ ዱኪ፣ ወዘተ የጐበዝ አለቆች ነበሩ። እንዲያውም አበበ አረጋይንማ “ራስ” የሚል ማዕረግ ያስገኘላቸው የጐበዝ አለቅነታቸው ነው፡፡
በጣሊያን ጊዜ የነበሩ የጐበዝ አለቆች ዓላማቸው ኢትዮጵያን ከፋሽስት መንጋጋ ማላቀቅ ነበር። የተሳካ እንቅስቃሴ በማድረጋቸውም ከአምስት ዓመት የሞት ሽረት ትግል በኋላ ንጉሡን ለዘውድ አብቅተዋል። በ1960 ዓ.ም ጐጃም ላይ ተከስቶ የነበረውን ህዝባዊ አመጽ የመራውም “ባምላኩ አየለ” ወይም በፈረስ ስሙ “ባምላኩ አባ ግዮን” የሚባል የጐበዝ አለቃ ነበር፡፡
ባምላኩ አባ ግዮን የሚመራው የገበሬ ጦር፣ መላ ጐጃምን ለጊዜውም ቢሆን ከንጉሡ አገዛዝ ነፃ ማውጣት ችሎ ነበር፤ ለአመጽ ምክንያት የነበረውን የብር ከሃምሳ ተጨማሪ ግብርም በጉልበቱ አስነስቷል፡፡ በትግራይም “የቀደማይ ወያኔ” አመጽ የተመራው በጐበዝ አለቆች ነው። የኃይለ ሥላሴን ሥርዓት ያንኮታከቱትም ከየወታደሩ ክፍል በጉልበት የተሰባሰቡ የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡ ዙሩ ሲደርስ ደርግን ራሱን የጣሉትም የኢህአዴግ የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡
ወያላዎች የጐበዝ አለቆች ሆነዋል
የከተማዋን የታክሲ ስምሪት ሥርዓት ለማስያዝ ሲባል የትራንስፖርት ባለስልጣኑ መሥመር አመልካች ጽሑፎች (ታፔላ) በየታክሲው አናት ላይ እንዲለጠፍ ወስኖ ነበር፤ እሱን ተግባራዊ ለማድረግም ብዙ ጊዜ አምጦበታል፡፡ ግን እርምጃው የመጓጓዣ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ አወሳሰበውና ህዝቡን ቁምስቅሉን ያሳየው ጀመር፡፡
በከተማዋ ትራንስፖርት ባለሥልጣን እርምጃ የተበሳጩት ወያላዎች፤ ከህዝቡ ትከሻ ላይ ፊጥ አሉና ሲፈልጉ ለሁለት ሰው በተዘጋጀ ወንበር ላይ “ጠጋ በል” እያሉ ሶስትና አራት ተሳፋሪ እንደ ቂጣ እየደራረቡ ያሰቃዩታል፤ ሲያሻቸውም ትራንስፖርት ባለሥልጣኑ ካወጣው ታሪፍ በላይ ይወስኑበታል። የጐበዝ አለቆችን ውሳኔ የሚጥስ ካለ፣ ክብሩንም ገንዘቡንም አጥቶ ተዋርዶና ተደብድቦ መግባት ግድ ሆኖበታል፡፡
ሰሞኑን ያጋጠመኝን ልጥቀስ፤ ከታህሳስ አንድ ጀምሮ መንግሥት “መጠነኛ ማስተካከያ አድርጌያለሁ” ያለውን ዋጋ፣ ህዳር 30 ምሽት በቴሌቪዥን ቁጭ ብዬ አስተውያለሁ፡፡ በ “መጠነኛ” ማስተካከያው መሠረት 1.40 የነበረው ወደ 1.45፤ 2፡70 የነበረው ወደ 2፡80 ማደጉ ገርሞኝ፣ ጥዋት ከመገናኛ ወደ ካዛንችስ ታክሲ ከተሳፈርን በኋላ (ያውም በሰልፍ መከራ አይተን) የጐበዝ አለቃው “ዋጋው አራት ብር ነው” የሚል አዋጅ በኩራት አሰማን፡፡ “እንዴ! ማታኮ በቴሌቪዥን 2.80 ተብሏል፤ እንዴት? ከየት የመጣ አራት ብር ነው?” ብለን ሁላችንም ስንጮህ “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታክሲ ይግዛላችሁ” አለን የጐበዝ አለቃው፡፡
የወያላው ሳይንስ ሹፌሩም ዳር ይዞ ቆመና “ከፈለጋችሁ ክሰሱ፤ መውረድ ትችላላችሁ፤ ጥሩንባ ሁሉ” አለና ታክሲ ሙሉ ሰው ዳቦ በቀደደ አፉ መዘርጠጥ ጀመረ፡፡ ሌላ የጐበዝ አለቃ ተጨማረ ማለት ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ምሬትና ሃዘን እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከሁሉ ትዝ የሚለኝና የገረመኝ አንዲት ወይዘሮ የተናገሩት ነው፡፡ “መክሰስ አለብን ትራፊክ ፖሊስ? እንሂድ፤ የለም ትራንስፖርት ባለሥልጣን ይሻላል ወደዚያ እንሂድ” የሚሉ ሰዎች ስለነበሩ ወይዘሮዋ ምን አሉ መሰላችሁ? “ሚስት አረገዘች? ብሎ ጓደኛውን ቢጠይቀው “ማንን ወንድ ብላ?” አለው ይባላል፡፡ ለመሆኑ መንግሥት ቢኖር ቂጡን ያልጠረገ ውርጋጥ መቀለጃ እንሆን ነበር?” ሲሉ እንባቸውን በነጠላቸው ጫፍ ጠራረጉ፡፡ እውነት ለመናገር የሴትዮዋ አባባል ልክ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ትንሹን ወያላ መቆጣጠር ካልቻለ እንዴት ነው ሌሎች ከባድ ወንጀሎችን በመቋቋም ህዝቡን ከስጋትና ከዝርፊያ መታደግ የሚችለው?
አሁን እየባሰበት የመጣው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የእነዚህ የጐበዝ አለቆች የሥምሪት መስመር ነው “ከካዛንችስ በአራት ኪሎ ፒያሳ” የሚል ጽሑፍ ለጥፎ “ፒያሳ በአቋራጭ!” ይላል፡፡ በአራት ኪሎ ሂድ ሲባልም በፍጹም በእጅ አይልም፡፡ ይህ የአቋራጭ መንገድ በአቋራጭ ለመክበር እንጂ በአቋራጭ ህዝብን ለማገልገል እንዳልሆነ ግን ግልጽ ነው፡፡ ይህንንም የትራንስፖርት ባለሥልጣኑ መቆጣጠር አልቻለም፤ የትራፊክ ፖሊሶችም እያዩ ትንፍሽ አይሉም፡፡ የህዝብን ችግር የማይፈቱ ከሆነ ትራንስፖርት ባለሥልጣንና ሰራተኞቹ ለምን ያስፈልጋሉ? የትራንስፖርት ዘርፉ የሚመራውኮ በእነሱ ሳይሆን በጐበዝ አለቆች ነው፡፡
“ተራ አስከባሪ” የሚባሉትም ሌሎች የጐበዝ አለቆች ናቸው፡፡ ከታክሲ ሹፌሮች ጋር በመሞዳሞድ ሕዝቡን ቁም ስቅል ያሳያሉ እንጂ ለህዝቡ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ ቀድሞ ነገር የሰውን ነው የመኪናውን ተራ የሚያስጠብቁት? የቱ መኪና ገዝቶ ነው ተራ የሚያስጠብቁት? መላ የጠፋው ተቋም!
መንገድ ጠራጊዎች የጐበዝ አለቆች ናቸው
መንገዱም ሆነ ሌላው ነገር የሚፀዳው ለህዝቡ ጤንነት ሲባል ነው፡፡ ባህርዳር፣ አዋሳም ሆነ ሌሎች የአገራችንና የውጭ አገር ከተሞች መንገዶች የሚፀዱት ህዝቡ እንቅስቃሴ ሳይጀምር ንጋት ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ግን “ጽዳቱ” የሚጀመረው ነዋሪው ሥራ ለመግባት ሲጣደፍ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ህዝቡ የታክሲ ወረፋ ለመያዝ ረጅም ሰልፍ ይዞ ካዩት፣ ወይም ንፁህ የለበሰ ካዩ ቅናት ያለባቸው ይመስል አስፋልት ላይ የነበረውን አቧራ አንስተው ይከምሩበታል፡፡
“ለምን እንዲህ አረጋችሁ?” የሚላቸው አካልም የለም፤ በድርጊታቸው የተበሳጨ ሰው አቧራውን ከልብሱና ከሰውነቱ ላይ እያራገፈ “ለምን እንዲህ ታረጋላችሁ?” የሚል ጥያቄ ሲያቀርብላቸውም መልሳቸው የሰሌን መጥረጊያ ሊሆን ይችላል፡፡
ለመሆኑ መንገዱ የሚጠረገው ለማን ጤንነት ታስቦ ነው? ለነዋሪው ነው? ወይስ ለአስፋልቱ ታስቦለት መንገድ ጠራጊ የጐበዝ አለቆችና ኃላፊዎቻቸው (ምን አልባት ካላችሁ) እባካችሁ የጽዳት ዓላማ ይግባችሁ፡፡ መንገድ የምትጠርጉት ለነዋሪው ጤና እንጂ ለአስፋልቱ ታስቦ አይደለም፡፡
መብራት ኃይልና ቴሌም ሌሎች የጐበዝ አለቆች ናቸው
መብራት ኃይልና ቴሌ በህግ የተቋቋሙ የመንግሥት አካላት ቢሆኑም ከመንግሥት አፈንግጠው የራሳቸውን ደሴት ፈጥረዋል።  በህጋዊነት ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የጐበዝ አለቅነትን የመረጡ መስለዋል፤ ያለምንም ማስጠንቀቂያ አገልግሎት ያቋርጣሉ፤ ለምን ተብለው ሲጠየቁም ሠራተኞቻቸው ደንበኛቸውን ይገላምጣሉ፤ አገልግሎቱንም ይበልጥ ያሽመደምዳሉ፡፡
የሁለቱም ተቋሞች አገልግሎት ይሻሻል ዘንድ መንግሥት በየጊዜው የመዋቅር ማሻሻያና የመሣሪያ ግዥ እንደሚያደርግና እያደረገም እንደሆነ በየጊዜው በኢቴቪ እናያለን፤ እንሰማለን፡፡ ግን አቅመ ደካማነታቸውን ሊያሻሽሉ አልቻሉም፡፡
ለምሳሌ መንግሥት ቴሌን ከኮርፖሬሽን ወደሚኒስቴር መ/ቤት አሳድጐታል፤ አገልግሎቱ ግን እየባሰ፣ እየዘቀጠ ሄደ እንጂ አንዳችም መሻሻል ሊያሳይ አልቻለም፡፡ ትላንት የተቋቋመችው ደቡብ ሱዳንና የተረጋጋ መንግሥት የሌላት ሶማሊያ፤ ከእኛ በአያሌው የተሻለ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ እኛ ግን ገና እንድሃለን፡፡ ለመሆኑ ልናገኘው የፈለግነውን ሰው ያለምንም ድምጽ መቆራረጥና ጥሪ መሰናከል መቸ ይሆን ማናገር የምንችለው? የጐበዝ አለቆች ሆይ፤ እባካችሁ ወደነበረው ባለገመድ ስልክ መልሱን፡፡
የመብራት ኃይል ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች በመቅበጥ (ኪራይ ሰብሳቢነት) ተጠርጥረው ከርቸሌ መግባታቸውን ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነግሮናል፡፡ የተከሰሱበት ወንጀል እውነት ሆኖ ከተፈረደባቸው “እሰየው” ያሰኛል፡፡ መብራቱን እያጠፉ የእኛን አንጀት ነበራ ሲያቃጥሉ የኖሩት፡፡ መንግሥት ቢቸግረው የመብራት ኃይል ባለሥልጣኑን ሰሞኑን በሌላ ቀይሯል። ግንኮ ስርዓቱን (ሲስተሙን) ማስተካከል ነው እንጂ ሰው ቢቀያየር ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ በአጠቃላይ በከተማችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎችና በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የጐበዝ አለቆች ተበራክተው ነዋሪውን ቁምስቅሉን እያሳዩት ነው፡፡ መንግሥት መንቃት አለበት። ክቡር ከንቲባውም በየቦታው ምን እየተሰራ እንደሆነ ተዘዋውረው ሊያዩና አፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል። አለዚያ ከተማቸውን የጐበዝ አለቆች እየተቀራመቷት ነውና የመረረው ሕዝብ…

አንድ ዝነኛ ዕዳና ነጋዴን የሚያሳይ ወግ አለ፡፡  ሲቆይ ተረት ይመስላል እንጂ ዕውነተኛ መሰረት አለው፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ ከተማ፣ አንድ ባለፀጋ ቱሪስት፣ ወደ አንድ ሆቴል ይመጣል፡፡ በዚህ ወቅት በዚያ ከተማ ዝናብ በጣም ይዘንባል፡፡ከተማው የተወረረ ይመስላል፡፡ ሰው በመንገድ አይታይም።  ጊዜው ክፉ ጊዜ ነው፡፡ ሰው ገንዘብ ስለሌለው አንዱ ከአንዱ እየተበደረ ነው የሚኖረው፡፡ ብድር የሌለበት ሰው የለም፡፡ ዕዳ በዕዳ ሆኗል ከተማው፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት እንግዲህ የመጣው ይሄን ሰዓት ነው፡፡ ጥሩ መኝታ ያለው ትልቅ ሆቴል ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ብዙ ሆቴሎች አይቶ የተመቸ አይነት ክፍል አላገኘም፡፡ ይሄኛውን ሆቴል በዐይኑ ወዶታል፡፡
“ጤና ይስጥልኝ” አለ ወደ ሆቴሉ ባለቤት ቀርቦ፡፡
“እንኳን ደህና መጡ ጌታዬ”
“ጥሩ ክፍል አላችሁ - ለመኝታ?”
“አዎ ጌታዬ፤በጣም በርካታ ክፍሎች አሉን፡፡ ቢፈልጉ ምድር ቤት፣ቢፈልጉ ፎቅ ላይ፡፡ ብዙ ዓይነት ክፍሎች አሉን”
“መልካም፤ የሚያሳየኝ ልጅ መድብና ክፍሎቹን ልያቸው፤ከተስማማኝ ልጁን እልከዋለሁ - ትመዘግበኛለህ፡፡ ካልተስማማኝ ራሴ እመጣለሁ፡፡ ይኸው ይሄንን መቶ ዶላር ያዝ” ብሎ ባንኮኒው ላይ ብሩን አስቀምጦ ወደ ፎቁ ወደ ሚያወጣው ደረጃ ሄደ፡፡
የሆቴሉ ባለቤት ፈጠን ብሎ መቶ ዶላሩን ወስዶ አጠገቡ ለሚገኘው ባለልኳንዳ ዕዳውን ከፈለ፡፡
ባለልኳንዳው ደግሞ ወዲያው፤ በሬ ለሚያመጣለት በሬ - አድላቢ - ነጋዴ ዕዳውን ሊከፍል በረረ፡፡ በሬ አድላቢው - ነጋዴ በበኩሉ፤ መኖና አትክልት ወደሚያቀርብለት ነጋዴ በፍጥነት ሄደና “እንካ ዕዳዬን አወራርድ” አለው፡፡
መኖና አትክልት አቅራቢው ነጋዴ ደግሞ እየበረረ በከተማው ወደታወቀችው ሴተኛ አዳሪ ሄዶ፤ በክፉ ጊዜ በዱቤ ስላሳደረችው አመስግኖ 100 ዶላሩን ሰጥቶ ከዕዳ ነፃ ሆነ፡፡
ሴተኛ አዳሪዋ በጣም ፈጥና ወደዚያ ሆቴል ሄደች፡፡ ከዚያም፤ ደምበኞቿን እያመጣች በተከታታይ በዱቤ የተኛችበትን የክፍል ሂሳብ ለባለ ሆቴሉ ዕዳዋን ከፈለች፡፡
ባለሆቴሉ ያንን መቶ ዶላር ባንኮኒው ላይ አስቀመጠው፡፡ ቱሪስቱ እንዳይጠረጥርም፤ በትክክል ባስቀመጠበት ቦታ ነው ያኖረለት፡፡ ባለፀጋው ቱሪስት የፎቁን የመኝታ ክፍሎች ሁሉ ሲያይ ቆይቶ፣ አንዱም ሳይስማማው ስለቀረ፤ ከፎቁ ወርዶ፣ወደ ባለቤቱ መጣ፡፡ ከዚያም “የሆቴሉን መኝታ ክፍሎች፣ በሙሉ ለማለት እችላለሁ፤አየሁዋቸው፡፡አንድም ክፍል እኔ የምወደው ዓይነት አልሆነልኝም፡፡ ስለዚህ 100 ዶላሩን ስጠኝና  ሌላ ቦታ ልፈልግ” አለ፡፡
“በጣም እናመሰግናለን ጌታዬ” አለ ባለሆቴሉ፤ በትህትና ገንዘቡን እየሰጠ፡፡
ባለፀጋው ቱሪስት ገንዘቡን ተቀብሎ ሄደ፡፡
በዚህ የመቶ ዶላር ታሪክ ውስጥ፤ ማንም ምንም ገንዘብ አላገኘም፡፡ ያም ሆኖ የከተማው ነጋዴዎች አሁን ዕዳቸውን አቃለዋል፡፡ ወደፊት ያልፍልናል ብለው በተስፋ ተሞልተው ተቀምጠዋል፡፡
*     *     *
የትኛውም ባንክና ኢንሹራንስ በዚህ ህግ እንደሚሰሩ ልብ እንበል!
ዕዳ ስንፈራረም የነገ እጣችንን እናስብ፡፡ ማ እየተጠቀመብን እንደሆነ እናስብ፡፡ ስልጣኔ ብዙው እጁ ከቀናን መበዝበዝ ካልቀናን መበዝበዝ ነው፡፡ “ዕዳ ይሻግታል እንጂ አይበሰብስም (a debt may get moldy but it never decays) ይላል፤ ናይጄሪያዊው ደራሲ ቺኑዋ አቼቤ፡፡
“ሰርቼ እከፍላለሁ” ብሎ መበደር የያያዋጣበት ጊዜ አለ፡፡ ግን ሁል ጊዜ አያዋጣም፡፡ በተለይ ደሀ አገሮች የሚያስይዙት ንብረት ወይም ቅድመ - ሁኔታ (conditionality) ስለሚኖር መቼ እጃቸውን ተጠምዝዘው አንዳች ግዳጅ ውስጥ እንደሚገቡ ማስተዋል ይገባቸዋል፡፡ “አሁን እየተበደርን ባለንበት ፍጥነት በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ጀምረን የገነባናቸው ህንፃዎች በሙሉ የኛ አይደሉም ማለት ነው” ይላል አሜሪካዊው ኢኮኖሚስት ፖል ቮልከር፡፡ ይህን አጥብቆ ልብ - ማለት ይገባል! ብድር እንዲህ ከሆነ እግዚሃር ያውጣን፡፡ ነገን ሳናጤን የምንጓዝበት መንገድ ትውልድን የማይችለው ጣጣ ውስጥ መክተት ነው፡፡ “ያባት ዕዳ ለልጅ” የሚለውን ስሜት በአግባቡ መመርመር ግዴታ ነው! “የኑሮ ደረጃችን እየተጠገነ ያለው በምርታማነት! ወይም በደሞዛችን አይደለም፡፡ በውጪ አገር ካፒታል እንጂ”  የሚለውን የጄፍሬይ ሳችስ (ታይም) አስተሳሰብ ጠለቅ ብሎ ማየት ያባት ነው! የሀገር ዕዳ ከነእንድምታው መጤን ይኖርበታል፡፡ ብድር የኢኮኖሚ ጉዳይ ብቻ ነው ብለን ካሰብን ቢያንስ የዋህነት አጥቅቶናል፡፡
“በሃገር ደረጃ ያለ ዕዳ ጥሩ ነገር ነው፡፡ አደገኛው ነገር ግን መልሰን እንዳንከፍል የፖለቲካል ኢኮኖሚ ጣጣ መኖሩ ነው” ይላል የብሪታኒያው ስላቅ ፀሃፊ ደብሊው ሴላር፡፡
ዕዳ አባዜው ብዙ ነው፡፡ የዕዳ ማስወገድን ችሎታና ጥበብ ከላይ የጠቀስነው፤ ተረት - መሰል ዕውቀት ይነግረናል! “ለኗሪዎች አክብሮትን፣ ለሟቾች ዕውቀትን የመስጠት ዕዳ አለብን”
የሚለው የፈላስፋው ቮልቴር አባባል ደግሞ፤ የራሳችንን ሰዎች እንዴት እንደምናከብር ይጠቁመናል።
የአገራችን ትላልቅ አበዳሪ ነጋዴዎች ስናይ ተበዳሪዎች ጤና መሆናቸውን ለማረጋገጥ በየሆቴል ጅምናስቲክ መስሪያ ቦታ ማለዳ እየሄዱ ያረጋግጣሉ፤ይባላል፡፡
“ዕመነኝ አበዳሪዎችህ፤ በቆራጥነት አምላክ ዕድሜህን እንዲያረዝምላቸው ይፀልያሉ፡፡ ከአንተ ሞት የበለጠ የሚያስፈራቸው ነገር የለምና!” ይለናል ፈረንሳዊው ምፅታዊ ደራሲ ፍራንሷ ራቤሌ፡፡ እናስብበት!
አገር በዱቤ መተዳደሯ፤መጨረሻው አሰቃቂ ነው!
“በመበደርና በእዳ ላይ የተመሰረተ ቤተሰብ አንድም ነፃነትን፣ አንድም ውበትን ያጣ ይሆናል” የሚሉትን ፈረንጆች፤ “በሽታ የሌለበት ክሳትና እዳ የሌለበት ድህነት አያሳስብም” በማለት ያጠናክረዋል፤ የወላይታ ተረት፡፡ አገርን በብድር ማስተዳደር አዳጋች የመሆኑን ያህል፤ ብድርን ለመክፈል፤ በጥድፊያ አገር እናለማለን ብሎ ማለምም አደጋ አለው፡፡ ሆነ ራሳችንን የምናይበት የሀብት ማፍራት መንገድ፤ በቅጡ የተፈተሸና በተግባር የተፈተነ መሆን ይኖርበታል፡፡ ምርታማነታችንና አልሚነታችን መፈክርና ዲስኩር ላይ የተንጠለጠለ ሳይሆን፤ በእርግጥ የኢኮኖሚ መስፈርቶችን ቁቤ ያለ ቢሆን አግባብነትና አስተማማኝነት ይኖረዋል፡፡ አለበለዚያ “ጦጣ፤ ጠዋት ነጭ ሽንኩርት ተክላ፣ ማታ ወደቤት ስትመለስ ነቅላ፤ “አይ የመሬት ነገር፤ ይገርማል!” ትላለች፤ የተባለው የወላይታ ተረት ይመጣል፡፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነባሩን የሥራ አስፈፃሚ አባላት ባለፈው ሐሙስ በወይን ኢትዮጵያ የባህል ምግብ አዳራሽ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ሸኘ፡፡
አንጋፋና ወጣት ደራስያን እንዲሁም የልዩ ልዩ ሙያ ማህበራት መሪዎች በተገኙበት  የተሰናባቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ገጠመኞቻቸውን እያቀረቡ ታዳሚውን ከማዝናናታቸውም በላይ ለስምንት ዓመታት ማህበሩን ሲመሩ፣ የነበራቸው የእርስ በርስ መናበብ ሐላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ብርታት እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት የሚመሩት ዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ የግል ሥራቸውንና ማህበራዊ ጉዳዮቻቸውን በመተው ለማህበሩ ዕድገት ሲጥሩ ለነበሩት የቀድሞ መሪዎች ክብርና ሞገስ ሊቸራቸው ይገባል፣ አዲሱ አመራርም አርአያነታቸውን ተከትሎ በትጋትና በፍቅር በመሥራት ማህበሩን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ይጥራል ብለዋል፡፡
ክቡር አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በበኩላቸው፤ ለተሰናባቾቹ ሥራ አስፈጻሚ አባላት ማህበሩ ያዘጋጀላቸውን የዋንጫና የአድናቆት ምስክር ወረቀት ከሰጡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሌሎች የሙያ ማህበራት መሪዎችም ከኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሊማሩ ይገባል፤ ሚኒስቴር መ/ቤታችንም ከኪነ ጥበብ ማህበራት ጋር ለመሥራት ከመቸውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ማህበሩን በፕሬዚዳንትነት ይመሩ የነበሩት አቶ ጌታቸው በለጠ ከመስከረም 25 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ ከሃላፊነታቸው ወርደው በዶ/ር ሙሴ ያዕቆብ ፕሬዚዳንትነት የሚመራ አዲስ ሥራ አስፈፃሚ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

Saturday, 14 December 2013 13:06

ማንዴላንአትመልስም!

“የታሪክህ አፅም
ተቆፍሮ ቢወጣ፤
ቀን የጣላት፣ ዘውድ ናት
የደፋሃት ባርኔጣ
የማንነትህ ዙፋን ነው
በርጩማህንም ነፃ አውጣ፣
ሥርወ - ቤትህን አውጅ
ጐጆህ ሀገር ትውጣ
ሳትነግሥ እንዳትሞት
አንጋለህ ሳትቀጣ
ብድርህን ሳትመልስ
ወግረህ ሳትቆጣ”
…እያለ ከሚያዝህ
ከዚያ ውዥንብር መንፈስ፣
ቀልብያህ ሳትድን
ነፍስህ ሳትፈወስ፣
ማንዴላን አታንሳ
ትርጉም ለማልፈስፈስ፡፡
ከተጠናወተህ፤ ስም አይጠሬ ህመም
የትውልድ በሽታ፣
ከሚያስደረድርህ፤ ጠመንጃና መውዜር
በበገና ፈንታ፣
አረር ከሚያስጤስህ
ከከርቤ እያፋታ፣
ጐጆ ከሚያስመልክ
ሀገር እያስረታ፤
ታሞ ካሳመመህ
ከይሄ ርኩስ መንፈስ፣
ቀልብያለህ ሳትድን
ነፍስህ ሳትፈወስ
ሕዋ ያህል ቃልን
በጐጆ አፍ ማወደስ
የጀግናውን ገድል
ትቢያ ላይ መለወስ፡፡

ሳምሶን ጌታቸው ተ.ሥ  

Saturday, 14 December 2013 12:39

ስለ ይቅር ባይነት

አባቴ ሆይ፤ የሚሰሩትን ያውቃሉና ይቅር በላቸው፡፡
ካርል ክራዩስ (የኦስትሪያ ፀሐፊ)
ጠላቶችህን ምንጊዜም ይቅር በላቸው፤ ስማቸውን ግን ፈጽሞ እንዳትረሳ፡፡
ሮበርት ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፖለቲከኛ)
እኔ ጠላቶቼን ይቅር ማለት አይጠበቅብኝም፤ ሁሉንም ገድዬ ጨርሻቸዋለሁ፡፡
ራሞ ማርያ ናርቫዝ (ስፔናዊ ጄነራልና ፖለቲከኛ)
ታላቅ ሰው የትላንት ጉዳቶቹን እያሰበ አይብከነከንም፡፡
(ዩሪፒደስ (ግሪካዊ ፀሐፌ ተውኔት)
ለቡጢህ ምላሽ የማይሰጠህን ሰው ተጠንቀቀው! እርሱም ይቅር አይልህ፤ ለራስህ ይቅርታ እንድታደርግም አይፈቅድልህ፡፡
ጆርጅ በርናንድ ሾው (አየርላንዳዊ ፀሐፌ ውኔት)
ሌሎችን ተጠያቂ እንደምታደርግ ራስህን ተጠያቂ አድርግ፤ ለራስህ ይቅርታ እንደምታደርግ ሌሎችንም ይቅር በል፡፡  
የቻይናውያን አባባል
ሰው አንዴ ከተፀፀተ በኋላ ጥፋቱን ፈጽሞ አስታስታውሰው፡፡
የሂብሩ አባባል
የፈለገ ቢሆን ከአምስት ዓመት በላይ ሰው ላይ ቂም አልይዝም፡፡  
ዊሊያም ኬኔዲ (አሜሪካዊ ፊልም ፀሐፊናደራሲ)
እግዚአብሔር ይቅር ይበልሽ፤ እኔ ግን ፈጽሞ ይቅር ልልሽ አልችልም፡፡
ቀዳማዊት ኤልዛቤት (እንግሊዛዊት ንግስት)
እውነትን ውደድ፤ ለስህተት ግን ይቅርታ አድርግ፡፡
ቮልቴር (ፈረንሳዊ ፀሐፊና ፈላስፋ)

Saturday, 14 December 2013 12:32

ለቡጊ

በግሬ ጣራ መርገጥ
ሙዚቃ ሲጋልብ መውጣት መውረድ መፍረጥ
ዓይኔን ማገላበጥ
መርበትበት መንቀጥቀጥ
መላጋት መንገድገድ እንደሰከረ ሰው
የናፈቀኝ ይህ ነው፡፡
ተነስቼ ልዝለል
ቡጊ ቡጊ ልበል…
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
    ከበሮ ሲያጋፍት ሙዚቃ ሲያናፋ
ልብሴን ጥዬ ልጥፋ
ልራቆት አብጄ
ልብረር ካለም ሄጄ
ሙዚቃ በጥላው ይምጣ ይሸፍነኝ
ሁሉንም ያስረሳኝ፡፡
እንደ እሳት ቦግ ቦግ
መውለብለብ መንተግተግ
መቃጠል መሞት ነው
ይህ ነው፣ ዳንሴ ይህ ነው፡፡
ልቤን ይነሳኛል
ዛር ይሰፍርብኛል
ልወርውር እጆቼን
    ሙዚቃን እንደ ኳስ ልለጋው በግሮቼ
ልዝለል ተነስቼ፤
ቡጊ ቡጊ ልበል
መሬት ልንከባለል
ልዝለል ጮቤ ልምታ
ያቃዠኝ አንዳፍታ፤
ቡጊ ቡጊ ቡጊ
ገብረክርስቶስ ደስታ

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገነባው ሁለገብ የስፖርት አካዳሚ እና የመወዳደርያ ስፍራ 42 በመቶ መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡ ከ530 ማሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚሆንበትን አካዳሚው የሚገነባው አፍሮፅዮን ኮንስትራክሽን ሲሆን አማካሪው ሺጌዝ ኮንሰልታንሲ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የዘንድሮውን የከፍተኛ ትምህርት የስፖርት ፌስቲቫል በዚሁ ሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እንደሚያስተናግድም ታውቋል፡፡ የስፖርት ፌስቲቫሉ ከመጀመሩ 10 ቀናት ቀናት ቀደም ብሎ የአካዳሚው የመጀመርያው የግንባታ ደረጃ ይጠናቀቃል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዓመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ከየካቲት 1 እስከ 16 ሲከናወን ድረስ 34 ዩኒቨርስቲዎች እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ12 የስፖርት ዓይነቶች የሚካፈሉ ከ6 ሺ በላይ ስፖርተኞች በማሳተፍ ይወዳደሩበታል፡፡

የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ በሁለገቡ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ እያስገነባቸው ካሉት የስፖርት መወዳደርያዎች መካከል ሶስትና ሁለት ውድድሮችን ማስተናገድ የሚችሉ አምስት የእጅና ቅርጫት ኳስ ሜዳዎችን ጨምሮ ሁለት የሜዳ ቴኒስ፣የዋና እና የእግር ኳስ ሜዳ ይገኙባቸዋል። ከእነዚህ 5 የስፖርት መወዳደርያ ሜዳዎች የሁለቱ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቀሪዎቹ ደግሞ 85 በመቶ የግንባታ ስራው መጠናቀቁ ተገልጿል። በግንባታ ላይ ከሚገኙት የስፖርት መወዳዳርያዎች 25 ሺ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችለው የእግር ኳስ ሜዳ እንዲሁም የሜዳ ቴኒስና የዋና መወዳደርያዎች የግንባታ ስራ 50 በመቶ የተከናወነ ሲሆን እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል፡፡ የሁለገብ የስፖርት አካዳሚና የመወዳደርያ ስፍራ ግንባታው በዩኒቨርሲቲው ለሚሰጠው የመጀመርያና ሁለተኛ ድግሪ የሰውነትና ጤና ማጎልመሻ ትምህርት አገልግሎት የሚውሉ 10 የመማርያ ህንጻዎችም ግንባታን ያካትታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በአዲስ አበባ ከተማ ሊደርሱ የሚችሉትን እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ነዋሪውንና ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ፣ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከልና ከተከሰተም ፈጥኖ በመቆጣጠርና በማረጋጋት የነዋሪውን ደህንነት (Safety) እንዲጠበቅ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ተልዕኮው መሰረት ህዳር 25 ቀን 2006፣ ከቀኑ 9፡15 ገደማ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ጆንያ ተራ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የገበያ ማዕከል የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ፣ የእሳት አደጋው ከተከሰተው በላይ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር መቻሉ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የእለቱን አደጋ አስመልክቶ ጋዜጣችሁ ባለፈው ቅዳሜ ህዳር 28 ቀን 2006 እትሙ ላይ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርዕስ፣ የተቋማችንን ተልዕኮ በሚያሳንስና ገጽታችንን በሚያበላሽ እንደዚሁም ተቋማችንን ከህዝብ ጋር በሚያጋጭ መልኩ፣ መልካም እይታና ሚዛናዊነት የጐደለው ስሜትን ብቻ ያስተናገደ ዘገባ ማቅረባችሁ መስሪያ ቤታችንን አሳዝኗል፡፡ በዘገባችሁ ላይ አንዳንድ ነጋዴዎች፤ “የእሳት አደጋ ሰራተኞች ከበላይ አካል መመሪያ አልተላለፈልንም በሚል ሰበብ ቆመው ሲያዩ ነበር” ለተባለውኧ በማናቸውም እሳትና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎችን ምክንያት መተኪያ የሌለውን የሰውን ህይወትና ንብረት ማዳን ሰብአዊ አገልግሎት ጭምር ከመሆኑም ባሻገር፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበት ዋናው አላማ ነው፡፡

ማናቸውንም አደጋ ፈጥኖ ለመቆጣጠር ባለሙያዎችም ሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የመስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎች፤ በአደጋው ስፍራ የሚገኙ በመሆኑና ስራው ላይም በቀጥታ የሚሳተፉበት አሰራር እንጂ የሰው ህይወትና ንብረት ለማዳን የማንም አካል ትዕዛዝ ወይም ፈቃድ ተጠይቆ አያውቅም፤ ወደፊትም አይጠየቅም፡፡ አንዳንድ የመስሪያ ቤታችን ሰራተኞች ጉቦ ጠይቀዋል ለተባለውም፣ እንደዚህ አይነት አሉባልታ ቀደም ሲልም ሆነ አሁን በግለሰቦች የሚነገር ሲሆን ይህንኑ ለማጣራት በሚደረገው ሂደትም የጋዜጣ ዝግጅት ክፍላችሁን ጨምሮ “ሲሉ ሰማን” ከማለት ውጪ ተጨባጭ መረጃ አልቀረበም፡፡ ይሁን እንጂ ስራችን በህዝብ ፊት የሚሰራ በመሆኑ፣ ተጨባጭ መረጃዎች ካሉ ከህግ አካላት ጋር ተባብረን የምንሰራ መሆኑን ማረጋገጥም እንወዳለን፡፡ ሌላው አደጋዎች ሰፋ ሲሉ ሌሎች ተባባሪ ተቋማትንና የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያጋብዙ በሆነ ጊዜ ሁሉ በትብብር ስንሰራ ቆይተናል፡፡ በዚህ የእሳት አደጋም የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ፤ ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችና የአካባቢውን ህብረተሰብ በማሳተፍ፣ በሁሉም ቅርንጫፍ ጣቢያዎቻችን የሚገኙ የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎችንና አምቡላንሶችን ከበቂ ባለሙያዎች ጋር በማሰማራትና ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ተችሏል፡፡

ጋዜጣችሁ ባቀረበው ዘገባ ግን የአደጋ መቆጣጠር ሰራተኞቻችንም ጭምር የአደጋው ሰለባ በመሆን አደጋውን ለመቆጣጠር ያደረጉትን ጥረት ለማየት አልፈለገም፡፡ ስለዚህም የላክነውን ይሄን ጽሑፍ በጋዜጣችሁ ላይ በማስተናገድ ላቀረባችሁት ዘገባ ማስተካከያ እርምጃ እንድትወስዱ እያሳሰብን፣ ይህ ሳይሆን ቢቀር የህግ አግባቦችን ለመጠቀም የምንገደድ መሆኑን እንገልፃለን፡፡ አማኑኤል ረዳ ኃይሉ (ኮ/ር) ም/ዋና ዳይሬክተር ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ቅዳሜ የጋዜጣችን ዕትም፤ “ከንቲባ ድሪባ የእሳት ቃጠሎ ተጐጂዎችን አቤቱታ አጣራዋለሁ አሉ” በሚል ርእስ የወጣው ዘገባ፣ ጋዜጠኞቻችን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ተገኝተው ተጐጂዎች ለከንቲባው ያቀረቡትን አቤቱታ በመስማት፣ ተጐጂዎችን በማነጋገርና ፎቶግራፍ በማንሳት የተጠናቀረ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን ደውለን የሚመለከተውን ኃላፊ በማነጋገር፣ በጉዳዩ ላይ የሰጡትን ምላሽ አካተን ማውጣታችንን ይታወሳል፡፡

  • የፓርቲው አመራሮች በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ሀዘናቸውን ገልፀዋል

የታላቁን የነፃነት ታጋይ የኔልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ከትላንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የሀዘን መግለጫ ፕሮግራም በጽ/ቤቱ ያካሄደ ሲሆን በፕሮግራሙ ላይም ስለኔልሰን ማንዴላ የነፃነት ትግል፣ ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ቁርኝትና ከማንዴላ ምን ትምህርት ይወሰድ በሚሉት ዙርያ ንግግር ተደርጓል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ከፕሮግራሙ ቀደም ባሉት ቀናት ደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ በመሄድ፣ በኔልሰን ማንዴላ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን መግለፃቸውን የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲው ወር በገባ በሶስተኛው ቀን በሽብርተኝነት ወንጀል ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የሚገኙትን እነ አንዷለም አራጌን እንደሚያስብ የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ አስራት ጣሴ፤ የኔልሰን ማንዴላን የሀዘን መግለጫ ታህሳስ ሶስት ቀን ያደረገው ማንዴላ በነፃነት ትግል፣ በእነ አንዷለም ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ያሳረፉ መሆናቸውን ለመጠቆም እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

“ማንዴላን ደቡብ አፍሪካ ወልዳ ብታሳድገውም ኢትዮጵያ ደግሞ አስተምራና ከሞት አትርፋ ለደቡብ አፍሪካ አበርክታዋለች” ብለዋል-ፀሃፊው፡፡ ማንዴላ ኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ላይ እያሉ የደቡብ አፍሪካ ነጭ መሪዎች ለግል ጠባቂው ጉታ ዲንቃ፣ ጉቦ ከፍለው ሊያስገድሏቸው እንደነበር ያስታወሱት አቶ አስራት፤ ሆኖም ጉታ ዲንቃ ምስጢሩን ለማንዴላ አስተማሪ በመንገራቸው ከሞት መትረፋቸውን ጠቅሰው፣ ይህ ምስጢር ወጥቶ ከሞት ባይተርፉ ኖሮ ኢትዮጵያም፣ አፍሪካም ሆነ ዓለም ማንዴላ ስለሚባል ሰው አያውቅም ነበር ብለዋል፡፡ በ25 አመታቸው አፍሪካ ናሽናል ኮንግረስን (ANC)ን ተቀላቅለው፣ በ46 ዓመታቸው ለእስር የተዳረጉ የነፃነት ታጋይና የመቻቻል ተምሳሌት ኔልሰን ማንዴላ፤ በሮቢን ደሴት ለ27 ዓመት በእስር ተሰቃይተው ከወጡና አፓርታይድ ከወደቀ በኋላ እ.ኤ.አ በ1994 የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

ማንዴላ፤ “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግርን እንዳስተማሩና ያሰሯቸው ሰዎች ላይ የቂም በቀል እርምጃ ከመውሰድ እርቅና መግባባትን በመምረጣቸው አለም በአንድ ድምፅ ተስማምቶ “ተምሳሌት” ብሏቸዋል ያሉት አቶ አስራት፤ ከ1ሺ በላይ ሽልማቶችና የማዕረግ ስሞች፣ 85 የክብር ድግሪዎች፣ የ45 የአለም ከተሞች የክብር ነዋሪነት፣ እንዲሁም ማንዴላ የተወለዱበት የልደት ቀናቸው ጁላይ 18 በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ “የማንዴላ ቀን” ተብሎ ተሰይሞላቸዋል፤ ይህ ሁሉ የተገኘው ለነፃነት በተከፈለ መስዋዕትነት ነው ብለዋል አቶ አስራት ጣሴ፡፡

“እነአንዷለም ሽብርተኞች ተብለው ታስረዋል፤ ግን ሽብርተኞች አይደሉም፤ የነፃነት ትግል ቄስና ደብተራ ናቸው” ያሉት አቶ አስራት፤ ኔልሰን ማንዴላም በእንግሊዞች “አሸባሪ” ተብለው እንደነበር አስታውሰው፤ እነ አንዷለምም በቅርቡ የነፃነት ታጋይነታቸውን አለም እንደሚያውቀው ተናግረዋል፡፡ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ሊቀመንበር አቶ አበባው መሀሪ ያደረጉት ንግግር ደግሞ በኔልሰን ማንዴላና በአፄ ሚኒልክ ላይ ያተኮረ ሲሆን ልክ እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሁሉ አፄ ምኒልክም በኢትዮጵያ ውስጥ የመቻቻልና የአንድነት መንፈስ እንዲኖር ያበረከቱትን አስተዋፅኦ አስታውሰው፤ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የጥላቻና የጐሪጥ መተያየት ፖለቲካ አውግዘዋል። አቶ አበባው አክለውም፤ በምኒልክ ዘመን መቻቻልና አንድነት በመኖሩ የውጭ ጠላትን ማሸነፍ መቻሉን የገለፁ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ማንዴላ ይቅር ባይነትና መቻቻል ካልመጣ፣ ለአገሪቱም ሆነ ለህዝቧ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡