Administrator

Administrator

ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ለሕዝብ ተጠቃሚነት እና ለሰላም ላበረከቱት ታላቅ አስተዋፅዖ ፣ ያሳዩት በሳል እና ምሳሌያዊ አመራር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚገኙ መሪዎች ምሳሌ የሚሆንና መነሳሳት የሚፈጥር በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ይህንን Doctorate of Philosophy እንዳበረከተላቸው የትሪኒቲ ኢንተርናሽናል አምባሳደሪስ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ዶ/ር ዣክሊን ሞሀየር ገልፀዋል::
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር እና የነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ላሳዩት ቁርጠኝነት እና ለሌሎች ሃገራት መሪዎች አርአያ የሚሆን ስራ በመስራታቸው የጆርጂያ ግዛት የክብር ዜግነት ሽልማት እንደተበረከተላቸው የግዛቱ ሴናተር ጋይል ዴቨንፓርት በመድረኩ ላይ ተናግረዋል::
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ ዶ/ር አዳነች አቤቤ ለዚህ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ላበረከቱ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
AAU Confers full professorships on seven faculty members.
1. ፕሮፌሰር ዮናስ ጨቡዴ
በኢንኦርጋኒከ ኮሚስተሪ
2. ፕሮፌሰር አህመድ ሙስጠፋ
በኮምፒቲሽናል ኬሚስተሪ
3. ፐሮፈሰር ኑርልኝ ተፈራ
በኬሚካል ኢነጂነሪንግ
4. ፐሮፌሰር አምቢሳ ቀነዓ
በጄነራል ኢዱኬሽን
5. ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጋሻው
በፊዚክስ
6. ፐሮፌሰር አበባው ይረጋ
በሀየር ኢዱኬሽን
7. ፕሮፈሰር ታደሰ በሪሶ
በአንትሮፖሎጂ
Tuesday, 24 October 2023 19:53

https://online.fliphtml5.com/etocz/wusy/

* ወላጆችን በተደጋጋሚ ሀኪምን እንዲጎበኙ ምክኒያት ከሆኑ  ህመሞች አንዱ በተለምዶ ቁርጠት (Infantile colic) የሚባለው ነው። ቁርጠት በተወለዱ በመጀመሪው ወር በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚከሰት ሲሆን በቀን ለሶስት ሰአትና ከዛ በላይ ፣ በሳምንት ለሶስት ቀናትና ከዛ በላይ እንዲሁም  ለሶስት ሳምንታትና ከዛ በላይ የሚቆይ የለቅሶና መነጫነጭ ስሜት ነው።  ስለዚሁ ህመም ወላጆች ማወቅ ያሉባቸው 10 ነጥቦችን በዛሬው ጽሁፍ ይዤ ቀርቤያለሁ እስከመጨረሻው አንብቡት።

1. የህፃናት ቁርጠት (infantile colic)  መንስኤው ምንድን ነው?

* በመንስኤው ላይ በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ወጥ የሆነ መግባባት ባይኖርም የአንጀትና ባጠቃላይ የስርአተ ልመት ኢንዛይሞች ከአለመጎልመስ ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ ይታሰባል።

2. ህመሙ እስከ መቼ ይቀጥላል ?

* በአብዛኛው ህጻናት ዘንድ ህመሙ እስከ ሶስት ወር የሚቆይ ሲሆን  አልፎ አልፎ ግን በጣም ጥቂት ህጻናት ላይ እስከ ዘጠኝ ወር ሊዘልቅ ይችላል።

3. የምታጠባ እናት ከምትበላው ምግብ ጋር የቁርጠት ህመም ምን ግንኙነት አለው?

* የምታጠባ እናት  ቡና፣ ቅመም የበዛባቸው ምግቦች ወይም የላም ወተት ብትቀንስ ቁርጠት ላለባቸው ህፃናትን ቁርጠቱ እንዲቀንስላቸው ሊያግዝ ይችላል።

4. የጣሳ ወተትን በመቀየር ቁርጠትን መከላከል ይቻላል?

* ህጻኑ የጣሳ ወተት ሲወስድ የመነጫነጭና ማልቀስ ምልክት ካለው የጣሳ ወተቱን ቢቀየር ይመከራል ።

5. ቁርጠት ላለበት ልጅ መድሀኒት ቢሰጠው ለህመሙ ይረዳዋል?

* የቁርጠት መንስኤ የተለያዩ ምክኒያቶች በመሆናቸው እንዲሁም የህመሙ ባህሪ ከልጅ ልጅ ስለሚለያይ ለቁርጠት ወጥ የሆነ ህክምና የለውም። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት መድሀኒት መስጠት ለቁርጠት ብዙ ጠቀሜታ አይሰጥም።

6. በወላጆች በኩል ቁርጠቱን ለማስታገስ ምን ቢደረግ ይመከራል?

* ህጻኑን ዘና እንዲልና እንዲረጋጋ የሚያደርጉ ለምሳሌ ገላን በሙቅ ውሀ ማጠብ፣ ለስለስ ባለ ብርድ ልብስ መጠቅለና፣ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ህጻኑን መወዝወዝ( rocking motion)፣ ለስላሳ ሙዚቃ መክፈትና እሹሹ እያሉ ማረጋጋት ህጻኑ ህመሙ ቀለል እንዲልለት ይረዳል።

7.  ለረጅም ሰአት ህጻኑ በማልቀሱ ምን ጉዳት ያመጣበታል?
* ህፃኑ ለረጅም ሰአት በማልቀሱ የሚመጣ ጉዳት የለም። ህጻኑ የአካል ጥንካሬው ጥሩ ከሆነ፣ በደምብ የሚጠባ እንዲሁም በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ ካለና ቆዳ ከለሩም ካልተለወጠ፣ የ ትኩሳት ምልክት ካልታየበት ከሰላሳ ደቂቃ በላይ ቢያለቅስም ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም። ስለዚህ ወላጆች ህፃናትን ለማረጋጋት ከሚጠቀሙበት መንገዶች ውጪ ከ አምስት እስከ አስር ደቂቃ ህፃኑ እንዲያለቅሱ በመተው ራሱን በራሱ እንዲያረጋጋ ማድረግ ይቻላል ።

8. ቁርጠቱ ከሌላ ህመመ ጋር አለመያያዙን በምን ምርመራ ማወቅ ይቻላል?

* ለቁርጠት የሚደረግ ምርመራ የለም። ነገር ግን ቁርጠቱ ሲከሰት ህፃኑ በ ህፃናት ህክምና ባለሙያ እንዲታይ በማድረግ የችግሩ መንስኤ ቁርጠት ወይም ሌላ ህመም መሆኑን ማወቅ ይቻላል። ህጻኑ በህጻናት ህክምና ስፔሻሊስት   ከታየ በኋላ ከአንጀት ጋር የሚያያዝ ችግርን ከተጠረጠረ ራጅ ወይም አልትራሳውንድ ምርመራ እንደሁኔታው ሊታዘዝ ይችላል።

9. ቁርጠት የያዘውን ህፃን በሀኪም እንዲታይ ማድረግ ያለብን መቼ ነው?

* አብዛኞቹ የቁርጠት ህመሞች በተደጋጋሚ ጊዜ ሰአት ለይተው የሚከሰቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁርጠቱ ማታ ማታ በተደጋጋሚ ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን ለቅሶው ከተለመደው በጣም ከረዘመና ከህፃኑ ባህሪ ጋር ባልተለመደ መልኩ የሚከሰት ከሆነ ለሀኪም ማሳየቱ ይመከራል። ከዚህ በተጨማሪ የንቃት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ ጡት አለመጥባት ወይም ምግብ ፍላጎት መቀነስ ፣ ተደጋጋሚ ትውከት፣ ያልተለመደ የሆድ ድርቀት ወይም ተቅማጥ፣ እና በፊንጢጣ የሚወጣ ደም ካለ ቶሎ ለሀኪም ማሳየት ያስፈልጋል።

10. ልጁ ቁርጠት እንዳለበት ከታወቀ ለክትትል መቼ መምጣት አለበት?

* አንድ ህፃን ቁርጠቱ ከሶስት ወይም ከአራት ወር በኋላ ከቀጠለ በሀኪም መታየት ይኖርበታል። 
በዶ/ር ኤርሚያስ አበባው ሲኒየር የህፃናት ህክምና ስፔሻሊስትና የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ)

ዓለም አቀፍ የስታርትአፕ ሽልማት በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ዓለም አቀፍ የስታርትአፕ ሽልማት ጉባዔ በአዲስ አበባ በሳይንስ ሙዚየም ከጥቅምት 14-16/2016 ይካሄዳል።
በጉባዔው ከ300 በላይ አህጉርና አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች ይወዳደራሉ።
ጉባዔውን አስመልክተው የስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው ጉባዔው ከጥቅምት 14-16/ 2016 በሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል ብለዋል።
ከእነዚህ ውስጥ የተሻለ ስራ ይዘው ለቀረቡ 15 ተወዳዳሪዎች ሽልማት እንደሚበረከትም ተናግረዋል።
ጉባዔው የልምድ ልውውጥ የሚደረግበትና አለም አቀፍ ትስስር የሚፈጠርበት እንደሚሆንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ለሌላው አለም በማስተዋወቅ ወደ አህጉርና አለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ገበያ ለመግባት ይረዳልም ብለዋል።
ሚኒስትሯ አክለውም "ኔክስት ኢትዮጵያን ስታርትአፕ ኢኒሼቲቭ" ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተናግረዋል።
ይህም ለቴክኖሎጂ ልማት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል።
መድረኩ በስራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ትብብር እንደሚዘጋጅ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ነጻ የትራኮማ እና የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል!!
ኤችሲፒ የተባለ  መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ከእዩ ክሊኒክ ጋር በመተባበር በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከጥቅምት 22/2016 ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት የትራኮማ እና የአይን ሞራ ግርዶሽ ቀዶ ህክምና በነጻ ይሰጣል።
በመሆኑም ማንኛውም ችግሩ ያለበት ዜጋ በወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተገኝቶ የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን!
Worabe Comprehensive Specialized Hospital!!!!!

Friday, 20 October 2023 00:00

ዲፕረሽን ወንዶች ላይ

ዲፕረሽን ወንዶች ላይ
=============
የዲፕረሽን ምልክቶች በሴቶችም በወንዶችም ላይ ተመሳሳይ ይሁኑ እንጂ መገለጫዎቹ ይለያያሉ፡፡ የልዩነቱ መንስኤ አስዳደግ ላይ "ወንድ አይደለህ ቆፍጠን በል!" የመሳሰሉት አባባሎች ስነ ልቦና ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ ወይም ተፈጥሯዊ ልዩነት ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ምክኒያት ዲፕረሽን ወንዶች ላይ ሲከሰት በቀላሉ ለመለየት ከማስቸገሩም በላይ የሀፍረት ስሜት ተከትሎት ከመጣ ጥሩ ያልሆኑ ውጤቶች ያስከትላል፡፡
በዲፕረሽን ላይ ሀፍረት ተጨምሮ ሲመጣ ከሰዎች መገለል፣ ስሜትን አውጥቶ ለመናገር አለመቻል (ለቅርብ ሰዎች እንኳ) እንዲሁም የህክምና እርዳታ አለማግኘትን ያስከትላል፡፡ እንዲሁም በዲፕረሽን ምክኒያት የሚመጣውን መከፋት ለመሸፋፈን ወይም ለመቋቋም አልኮልና እና ሌሎች ሱስ አምጪ ነገሮችን አብዝቶ መጠቀም፣ ቁማር አብዝቶ መጫወት፣ ህይወትን ለአደጋ በሚያጋልጥ መልኩ ማሽከርከር፣ ብስጩ መሆንና በቀላል ነገሮች መናደድ ያስከትላል፡፡ በተለይ ብስጩ መሆን ለቤተሰብ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
የሚወዱትን ሰው ያጡ አንዳንድ ወንዶች 'ጠንከር እንዲሉ' እና ሀዘናቸውን እንዳይገልፁ የሚደረገው ክልከላ እርማቸውን እንዳያወጡና የተወሳሰበ ሀዘን (Complicated grief) ውስጥ እንዲገቡ ሲያደርጋቸው ያጋጥማል፡፡
አብዛኛው ዲፕረሽን ውጤታማ በሆነ መልኩ የሚታከም በመሆኑ ጥሩ ስሜት ካልተሰማ ወይም የፀባይ ለውጦች ካሉ ከአእምሮ ሀኪም ወይም ከስነ ልቦና ባለሞያ ጋር በመነጋገር መፍትሄ ማግኘት ይቻላል፡፡ የአእምሮ ህመም ፆታ፣ ብሄር፣ የትምህርት ደረጃ ሳይለይ ሁላችንም ላይ ሊከሰት የሚችል፤ ውጤታማ ህክምና ያለው ህመም ነው፡፡
ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም!!!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው
 

 *ከሊባኖስ እስከ ዌስተርን ባንክ እና ዋሺንግተን የተቀጣጠለው ተቃውሞ
       *ለጋዛ የሆስፒታል ፍንዳታ እስራኤል ተጠያቂ አይደለችም - ዋይት ሃውስ
       *አሜሪካ በመላው ዓለም ለሚገኙ ዜጎቿ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች
       *3500 ፍልስጤማውያን፤ ከ1400 በላይ እስራኤላውያን ተገድለዋል

          የእስራኤል ሃማስ ጦርነት በተጀመረ በ12ኛው ቀን ላይ፣ መላውን ዓለም ያስቆጣና ያሳዘነ የሮኬት ጥቃት በጋዛ ተፈፀመ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በጋዛ የሚገኘው የአል-አህሊ ሆስፒታል ላይ በደረሰ ፍንዳታ 500 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ታጣቂው ቡድን  ሃማስ ያስታወቀ ሲሆን፤ ትክክለኛውን ቁጥር በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም ተብሏል፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች በሆስፒታሉ ተጠልለው የነበሩና ህክምና የሚጠባበቁ ፍልስጤማውያን ነበሩ ተብሏል፡፡
 ሃማስ ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ እስራኤል በበኩሏ ፍንዳታውን ያደረሰው የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ ነው ስትል ወንጅላለች፡፡ ለዚህም የተለያዩ ማስረጃዎችን አቅርባለች፤ የተጠለፈ የሃማስ ታጣቂዎች ንግግር ኦዲዮን ጨምሮ፡፡  
የጋዛው ፍንዳታ በተሰማ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከሊባኖስ እስከ ዌስት ባንክ እንዲሁም  ዋሺንግተን ዲሲ ድረስ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣና ተቃውሞ ተቀጣጥሏል፡፡ የዓለም አገራትና መንግስታትም ጥቃቱን ክፉኛ አውግዘዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ኳታር፣ ፈረንሳይ፣ዮርዳኖስ፣ ግብጽና ሌሎች በርካታ አገራት አሰቃቂውን የጋዛ ፍንዳታ በማውገዝ፣ የጥቃቱ ፈጻሚ ናት ያሏትን፣  እስራኤልም አጥብቀው ኮንነዋል፡፡
በቤሩት መዲና ሊባኖስ፣በጋዛ በደረሰው ፍንዳታ የተቆጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች፤  በአሜሪካና ፈረንሳይ ኤምባሲዎች አቅራቢያ ተሰባስበው እስራኤልን ያወገዙ ሲሆን ለፍልስጤምም አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች፣ ረብሻና ግጭት ለመፍጠር በሞከሩ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል፡፡
በዮርዳኖስ አማን ደግሞ ከ1ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ ላይ በመሰባሰብ ለፍልስጤምና ሃማስ ድጋፋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ እስራኤልን ክፉኛ አውግዘዋል - “ሞት ለእስራኤል!” በማለት፡፡ የእስራኤልንና የአሜሪካንን ሰንደቅ አላማ ሲያቃጥሉም ተስተውለዋል። ተቃዋሚዎች በእስራኤል ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክሩም፣ የፀጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ተቃውሞውን ለመበተን ችለዋል፡፡
በቱርክ ኢስታንቡል በሺዎች  ተቃዋሚዎች በእስራኤል ቆንስላ አካባቢ ተሰባስበው በጋዛ  ለደረሰው ፍንዳታ እስራኤልን ያወገዙ ሲሆን፤ ለፍልስጤም ድጋፋቸውን አሰምተዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ወደ ቆንስላው ህንፃ ድንጋይ፣ ዱላና ተቀጣጣይ ነገሮችን ሲወረውሩም ታይተዋል፡፡ በተመሳሳይ በፈረንሳይ ኤምባሲ አቅራቢያ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች፤ እስራኤል በጋዛ ላይ ፈጽማዋለች ያሉትን ጥቃት በህብረት አውግዘዋል፡፡ አንድ ተቃዋሚ ለጋዜጠኛ በሰጠው አስተያየት፤ የቱርኩ ፕሬዚዳንት፣ እስራኤልን ከማውገዝ ባለፈ ከድርጊቷ እንድትታቀብ የሚያደርጋት ተጨባጭ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም ሲል ወቅሷቸዋል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ በዋሺንግተን ዲሲ፣ አፍቃሬ - ፍልስጤም የሆኑ በርካታ የአሜሪካ- አይሁድ ተቃዋሚዎች፣ ካፒቶል  ህንጻ ውስጥ ተሰባስበው በመግባት፣ አስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ እንድታቆም ጠይቀዋል - በጭብጨባና በመዝሙር ታጅበው፡፡ “አሁኑኑ የተኩስ አቁም፤ ነፃነት ለፍልስጤማውያን፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቁም” የሚሉ መፈክሮችንም  አሰምተዋል፡፡ በመጨረሻ ግን ፖሊስ ለመበተን አሻፈረኝ ብለዋል ያላቸውን 300 የሚደርሱ ተቃዋሚዎች፣ በቁጥጥር ሥር  ማዋሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ደግሞ የፖሊስ መኮንንኖች ላይ ጥቃት በመፈጸም መከሰሳቸውን የካፒቶል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 በተቃውሞ ትዕይንቱ ከተሳተፉት አንዱ የሆነው  ማቲው ሆህ፤ ከኖርዝ ካሮሊና ድረስ የመጣው በተቃውሞው ላይ ለመናገራል፡፡ በኢራቅና አፍጋኒስታን ጦርነቶች ውስጥ  መሳተፉን የገለጸው ማቲው፤ አሁን ግን ይጸጽተኛል ብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በጋዛ ሆስፒታል ላይ ለደረሰው ፍንዳታ፣ ሃማስ እስራኤልን ተጠያቂ ለማድረግ ያለ ወትሮው ተጣድፏል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የሟቾችን ቁጥርም በዚያ ፍጥነት ይፋ ማድረጉ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ፡፡ ከሁሉም ደግሞ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ከሃማስ የተሰጠውን መግለጫ ተቀብለው እንደ ተዓማኒና ገለልተኛ መረጃ በእርግጠኝነት ማሰራጨታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ “እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ላይ ባደረሰቸው ፍንዳታ 500 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን ተገደሉ” የሚለው መረጃ በጥድፊያ መሰራጨቱ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ቀስቅሷል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ የሃማስም ዓላማ በትክክል ይኸው ነበር ይላሉ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የአረቡ ዓለም በእስራኤል ላይ በጋራ እንዲነሳ ማድረግ፡፡
ሃማስ የጋዛው ሆስፒታል ፍንዳታ የደረሰው እስራኤል በተኮሰችው የሮኬት ጥቃት ነው ሲል ቢከስም፤ እስራኤል ግን ክሱን በማጣጣል፣ ፍንዳታውን ያደረሰው የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ መሆኑን በማስረጃ አስደግፋ አቅርባለች፡፡ የእስራኤል ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ሮኬቱ ከእስራኤል የተተኮሰ ሳይሆን ከጋዛ የተተኮሰ ነው ብለዋል። የድምፅ፤ የምስልና የኢንተለጀንስ ማስረጃዎችንም ይፋ አድርገዋል፡፡
የጋዛ ሆስፒታል ፍንዳታን ተከትሎ፣ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ፣ የምዕራብ አገራት ለዜጎቻቸው የጉዞ ጥንቃቄ አለርት እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ሊባኖስ ከመጓዝ እንዲታቀቡ እያሳሰቡ ነው፡፡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሰሞኑን ባወጣው የማስጠንቀቂያ አለርት፤ በሊባኖስ የሚገኙ አሜሪካውያን አስቸጋሪ ነገር ተፈጥሮ በረራ ከመታገዱ በፊት በፍጥነት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ረቡዕ ለ7 ሰዓት ያህል በእስራኤል ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ፕሮዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትንያሁና ከሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ሃማስ በእስራኤል ህጻናት እናቶችና አረጋውያን ላይ በጅምላ የፈጸመውን  አስከፊ ጥቃት አጥብቀው ያወገዙት ባይደን፤ “ሽብርተኛነት አያሰንፍም፤ አሸናፊው  ነጻነት ነው” ብለዋል፡፡
ጆ ባይደን ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የጋዛው ፍንዳታ የተፈፀመው ሃማስ እንደሚለው በእስራኤል ሳይሆን፣ በሌላ ታጣቂ ቡድን መሆኑን ተገንዝቤአለሁ ብለዋል፡፡ “ማክሰኞ በጋዛ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ የብዙዎች ህይወት በመጥፋቱ ተቆጥቻለሁ፤ አዝኛለሁም። ያሉት ማስረጃዎች ግን የሚያመለክቱት፣ ፍንዳታው የደረሰው በጋዛ በሚገኝ የሽብርተኛ ቡድን በተተኮሰ ሮኬት መሆኑን ነው፡” በማለት እስራኤልን ከተጠያቂነት ነፃ አድርገዋታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ፤ ከእስራኤሉ ጉብኝታቸው በኋላ በዮርዳኖስ አማን ከተማ፤ ከግብጽ፣ ፍልስጤምና ዮርዳኖስ መሪዎች ጋር ተገናኝተው፣ በጋዛ ጉዳይ ለመምከር ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ይታወቃል፡፡ የጋዛውን አስከፊ ፍንዳታ ተከትሎ ግን የአረብ መሪዎቹ ከባይደን ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ መሰረዛቸውን  አስታወቁ፡፡ ይህም የሃማስ ሃሰተኛ መግለጫና የሚዲያዎች ሙያዊ ሥነምግባር የጎደለው  ዘገባ ውጤት ነው ይላሉ - የፖለቲካ  ተንታኞች፡፡
በሌላ በኩል፤ 20 የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ግብፅ መስማማቷን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት  ባለፈው ረቡዕ  አስታውቀዋል፡፡ ከእስራኤል ወደ ዋሺንግተን ሲመለሱ በፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን “ኤር ፎርስ ዋን” ውስጥ ሆነው ለሪፖርተሮች  ማብራሪያ የሰጡት ጆ ባይደን፣ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲስ ጋር፣ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ በስልክ መወያየታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የግብፁ ፕሬዚዳንት የተወሰኑ ሰብአዊ እርዳታዎች በራፋህ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገባ በመፍቀዳቸው፣ “ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ እርዳታውን የተባበሩት መንግስታት ሠራተኞች ጋዛ ላይ ተቀብለው ለፍልስጤማውያኑ ያከፋፍሉታል ተብሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ልክ በዛሬው ዕለት፣ ኦክቶበር 17 ቀን 2023 ዓ.ም ታጣቂው የሃማስ ቡድን በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ፣ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት እየደረሰ ሲሆን፤ እስካሁን 3ሺ 500 ገደማ ፍልስጤማውያን መገደላቸውንና ከ1ሺ 400 በላይ እስራኤላውያን መሞታቸው ተዘግቧል። ከሁለቱም ወገን ወደ 15ሺ ሰዎች ገደማ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
***

 እጅግ የሚፋቀሩ ባልና ሚስት በአንድ የገጠር መንደር ይኖራሉ። ባል ገበሬ ነው። ቀኑን ሙሉ ሲታትር ውሎ፣ ያረሰውን አርሶ ቤቱ ሲደርስ፣ ሚስት ለእግሩ ውሃ አሙቃ እግሩን አጥባ ራቱን አብልታ፣ አሳስቃ-አጫውታ ታስተኛዋለች። እሱም፣ የፍቅሯን ብዛት ለመግለፅ፣
“እንዲያው አንቺዬ አንቺ ባትኖሪ ምን ይውጠኝ ኖሯል?” ይላል።
“እንዴት? ለምኑ?” ትላለች፤ ጥያቄውን በጥያቄ መልሳ።
“ዘንድሮ እንደሰማዩ ባዶነትና እንደመሬቱ አልታረስ ማለት’ኮ የምንልሰው የምንቀምሰው አይገኝም ነበር። አንቺ ግን ያለውን አብቃቅተሽ፣ ስቀሽ አሳስቀሽ ጠግበን እንድናድር ታደርጊያለሽ”
“ያ የእኔ ሳይሆን የአምላክ ፀጋ ነው። ሁለተኛ ደግሞ የአንተ ድካም ፍሬ ነው። ይልቅ ተመስገን በልና ተኛ! ጎረቤታችንን አያ እገሌን አታየውም? ይጭነው አጋሰስ፣ ይለጉመው ፈረስ፣ ይልከው አሽከር ሞልቶ ተርፎት ሲያበቃ፣ ጧት ማታ አምላክን ሲያማርር እንዲህ ደህይቶ ቁጭ ብሎ ቀረ”
“እሱስ እጅግ ያበዛዋል”
“ዛሬ ጠዋት በተስኪያን ቄሱን ሲጨቀጭቃቸው ነበር። እሳቸው ግን የልብ- አውቃ አደሉ አንጀቴን አራሱኝ።”
“ምን ብለው?”
“ምን ይሆንልሃል፤አጅሬ እንደተለመደው ከስብከት በኋላ ይጠብቃቸዋል። እኔም ቤት መጥተው ጠበል እንዲረጩ ልነግራቸው እዚያው ቆሜያለሁ። ጨርሰው ሲመጡ እንዲህ ይላቸዋል። - “አባ ሰሞኑን ክፉ ክፉ ህልም እያየሁ ተቸግሬአለሁና እስቲ ይፍቱልኝ?”
“ምን ችግር ገጠመህ፣ ምን ህልም አየህ አያ?” አሉት ቄሱ።
“ይሄውሎት አባ፤ በህልሜ በየማታው አንድ በሬ ይመጣብኛል። ቀንዱ በጣም የሾለና አስፈሪ ነው። እየመጣ ሊወጋኝ ሲያባርረኝ አያለሁ። አሁን አሁንማ ጭራሽ ሩጫውና ፍጥነቱ አያድርስብዎት! ይኸው ሣምንቴ ስሮጥ ስባረር! ከእንቅልፌ  እየባነንኩ ስጨነቅ አድራለሁ!! እንደው ምን ባደርግ ይሻለኛል አባ?
“አንተ መኝታህ ምን ላይ ነው?”
“ኧረ የረባም መኝታ የለኝ አባ። እንዲያው የሣር ፍራሽ ላይ ነው የምተኛው።”
“ታዲያ ዋና ቀለቡ ላይ እየተኛህ ዱሮስ ላያባርርህ ኖሯል እንዴ?”
***
በሰው ቀለብ ላይ መተኛት በሰው ህይወት ሂደት ላይ ጋሬጣ መሆን ነው። በሰው እንጀራ መግባትም የዚያኑ ያህል የሌላውን ህይወት መቀማት ነው። ሠራተኛ የሚጠበቅበትን ያህል ሥራ ሰርቶ፣ የሚገባውን መብትና ጥቅም ማስከበር ይፈልጋል። ይህ መብትና ጥቅም ከሚሰራው ስራ ጋር ሁነኛ ትስስር ያለው እንደመሆኑ፣ አንዱ ሲጎድል ሌላኛው መነካቱ፣ ያንዱ ፍሰት ሲቋረጥ የሌላኛው ቧንቧ እንደሚዘጋ አያጠያይቅም።
በሀገራችን ሥራና ሠራተኛ በትክክልና በውል ተገናኝተዋል ለማለት አይቻልም። ሥራና ሠራተኛ የሚገናኙበት ቦታ ደግሞ የሥራ-ብቃት ያለው ሠራተኛ ሞልቶ ተትረፍርፏል ለማለትም ከቶ አያስደፍርም። በዚያ ላይ ሁለቱም በወግ ሰምረው የተገናኙበት ቦታ ደግሞ ጥሩ የሥራ ከባቤ- አየር (Atmosphere) አይኖርም። የግሰብ አለቆች ማንነት፣ የፖለቲካው ንፋስ፣ የሥራ ባህል ድክመት፣ የቢሮ ሥርዓት ማጣት ወዘተ… ብርቱ እንቅፋት ሆነውበት ይገኛል። በዚህ ምክንያት ብዙ ስፍራ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ሲሆን ይታያል። የታሰበው ግብ አይመታም። እድገት የለም። የሠራተኛ መማረርና ብሶት የዕለት- የሠርክ እሮሮ ይሆናል። ሁሉም በወጉና በሥርዓቱ በቅርበት መመርመር አለባቸው።
ዋናው ባለጉዳይ እያለ አጃቢው የሚያስቸግርበት ሁኔታ ሞልቷል። የሚመለከተው ሹም እያለ ምንዝሩ አለሁ አለሁ የሚልበት ሁኔታ ጎልቶ ይታያል። ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ የሚለው መርህ፣ አንዱ መሰናከያው ይሄ ነው። “የምትወልደው ገበያ ሄዳ የምታዋልደው ቤት አልጋ ላይ ትተኛለች” የሚባለውም ይሄ ነው። አጃቢና አጫፋሪ በበዛ ቁጥር ዋንኛው ሰው ኃላፊነቱን በአግባቡ የሚወጣበትን እድል ያጣብቡበታል። አንድም ደግሞ ከጳጳሱ በላይ ካቶሊክ የሆኑ ሰዎች ጣልቃ እየገቡ ሥራውን ያበላሹበታል ማለት ነው። እንዲህ ያለው ጉዳይ በተለይ በፖለቲካው መስክ ሲታይ ደግሞ የበለጠ ጎጂ ይሆናል። በሀገራችን በታዩት ለውጦች ውስጥ ሁሉ፣ ዋናው የፖለቲካ ሃላፊ ወይም መሪ በእርጋታ በሚወያይበት ቦታ፣ ካድሬው ከልክ ያለፈ ልፈፋና መፈክር ሲያበዛ፣ ዋናው ባለሥልጣን በመግባባትና በመቻቻል ይፈታል የሚለውን ጉዳይ ካድሬው ጦር ሲሰብቅለት ይገኛል።
ይህም  በወጉ ካልተያዘ ለማናቸውም ሥራ እንቅፋት መሆኑ አሌ አይባልም።
ባልተጋበዙበት ድግስ የሚመጡ፣ የማይመለከታቸው ጉዳይ ላይ ንግግር የሚያደርጉ፣ ባልሰለጠኑበት ሙያ ከባለሙያው በላይ ዘራፍ የሚሉ አያሌ ናቸው። እነዚህም ሥራን በማበላሸት ረገድ ጉልህ ድርሻ አላቸው። እንደዚህ ያሉት “ወይ ትንሽ የምትበላ አይደለህ”፣ ወይም ከበላን በኋላ አልመጣህ” የሚባሉት ዓይነት ሲሆኑ፤ በራሳቸውና በተመደቡበት ስራ ላይ ሳይሆን በቅልውጥ ሥራ የተካኑ ናቸው። ለዚያውም ድግስ ያበላሻሉ። ገበታ ያዘበራርቃሉ። ሥራና ሠራተኛን ያለያያሉ።
በማናቸውም የሥራ መስክ ላይ፣ በቢሮ አካባቢም ሆነ በፖለቲካው የሥልጣን መዋቅር ዙሪያ እጅግ አስቸጋሪና ጎጂ የሆነው ባህል፣ ጥፋትን በሌሎች ላይ የመላከክ (Blame-Shifting) ተግባር ነው።  ይህ አሉታዊ ተግባር ከልሂቅ እስከ ደቂቅ፣ ከትላልቅ የፖለቲካ መሪዎች እስከ አማካዩ ሟች ፍጡር (Average mortal) ድረስ ሥር-የሰደደ አባዜ ነው።
ቀበሌው በወረዳ፣ ወረዳው በቀጠና፣ ቀጠው በመስተዳድሩ ያላክካል። ሚኒስትሩ በምክትሉ፣ ምክትሉ በሥራ አስኪያጂ፣ ሥራ-አስኪያጁ በመምሪያው እያለ እስከ ዜጋው እርከን ድረስ ይወርዳል። ሁሉም “እሱ ነው!” እንጂ “እኔ ነኝ” ለማለት ዝግጁ አይደለም። አንዱ አንደኛውን “ባጋለጠ” ቁጥር የራሱን ንፅህናና ትክክለኝነት ያረጋገጠ እየመሰለው በግብዝነት መደገጉ የተለመደ ክስተት ሆኗል። የሌሎችን ጉድለት በማጉላት የራስን ትልቅነት ማሳየት የሚቻል የሚመስላቸው አያሌ ናቸው። ይህ ደግሞ የአሉታዊነት ባህሪን እያደበረ አገርን እያኮሰሰ ወደ ውድቀት፣ ህዝብ እያጎሳቆለ ወደ ድቀት የሚያመራ፣ ከቶም በቀላሉ የማንሽረው ባህል ነው።
 ዛሬ እኛ በሌላው ላይ ክፉ ስናደርግ ባህሉን ማጠንከራችን ነውና፣ ነገ በእኛ ላይ ላለመድረሱ ምንም ዋስትና እንደማይኖር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ለጊዜው እንደ ህልውና የምንቆጥራቸው ትናንሽ ድሎች፣ ከቶም ለጠዋት ድምቀትና መታያነት ያገለግሉ እንደሆነ እንጂ ማምሻው ላይ በዋናው ሰዓት ከተጠያቂነት አያድኑም። “ቀርክህ ጠዋት ለብሶ ማታ ይራቆታል” እንደሚባለው መሆኑ ነው። መንግሥታዊው ፓርቲ በተቃዋሚ፣ ተቃዋሚው በመንግሥታዊ ፓርቲ ላይ ድክመቱን አያሻገረና እያጋባ ይኖራል። የራስን ሥራ የሌላው ሥራ አድርጎ ከወቀሳ ማምለጥ እንደ ዋና ኑሮ ተይዟል። የራስን ጥፋትና ወንጀል የሌላው አድርጎ፣ ሌላውን ማስገምገም ከቀን ቀን እየከፋ የመጣ የአገር በሽታ ሆኗል- እንደቆላ ቁስል አልድን ያለ እክል ነው! በወደቀው መንግሥት በተሸነፈው ፓርቲ፣ በተባረረው ሠራተኛና በተጣሉት ወገን ላይ ጥፋትን እያላከኩ መኖር  እጅግ ክፉ እርግማን ነው። ወላይታ ሲተርት “ወተት የጠጣ ውሻ ሰርዶ በበላ አህያ አፍ ይጠርጋል” የሚለውም ይሄንኑ ነው።

“ጥያቄው አገሪቱ ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል”
                            
           ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ  ሰሞኑን ለጎረቤት ሀገራት  ያቀረቡትን  የወደብ ባለቤትነት ድርድር ጉዳዪ የሚመለከታቸው ሁሉም አገራት ውድቅ አደረጉት ። ኤርትራ  ጅቡቲና  ሱማሊያ  የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ እንደማይቀበሉ ይፋ አድርገዋል ።   የወደብ ባለቤትነት  ጥያቄው  አገሪቱ  ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል ተብሏል ።


ሱማሊያ  ከጠ/ሚኒስትር የቀረበውን የወደብ ባለቤትነት ውይይት እንደማትቀበለውና የወደብ ጉዳይ ልክ እንደ ሌሎች የሉኣላዊነት ጉዳዮች የሚታይ ነው ማለቷን ብሉንበርግ ዘግቧል ።የሶማሊያ ፕሬዝዳንት አማካሪ አብዲራህማን አብዲሻኩር  በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በኩል በተደጋጋሚ የወደብ ባለቤትነትን አስመልክተው የሚሰጡትን አስተያየት እንዲሁ ችላ  የሚባል አለመሆኑንና   መንግስታቸው ሁኔታውን በትኩረት እንደሚከታተለው መግለፃቸውን ሶማሊ ጋርድያን በድረገጹ አስነብቧል።

የሶማሊያ ብሔራዊ የደህንነት መስሪያ ቤት (NISA) ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ኢስማኤል ኦስማን በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በቀይባህር ዙሪያ የወደብ ባለቤት ለመሆን እየሄደችበት ያለው መንገድ አለም አቀፍ አካሄድን የጣሰ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።ኢስማኤል ኦስማን በሰጡት ትንታኔ፤ የአለም ሀገራት የራሳቸው የሆነ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት እንዳላቸው ጠቁመው፤ ሀገራት ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ማለትም ነዳጅም ሆነ ወደብ በአለም አቀፍ የትብብርና በሰላማዊ መንገድ በሽያጭና በተለያየ መንገዶች በጋራ እንደሚጠቀሙ አስታውቀዋል።


ከዚህ ውጭ ግን በጉልበት ለማግኘት መጣር አለም አቀፍ አካሄድን የጣሰ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ጠ/ሚኒስትር በቀይባህር ዙሪያ የወደብ ባለቤት ለመሆን ያቀረቡት ሀሳብና ለማግኛነት ያቀረቡት አካሄድ የተባበሩት መንግስታት ቻርተርንና አለም አቀፍ ህግን የጣሰ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የቀድሞ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ባላል ሞሃመድ ኩስማን በበኩላቸው፤ የጠ/ሚኒስትሩ የወደብ ባለቤትነት ሀሳብ፣ ኢትዮጵያ ከአጎራባቾቿ ጋር ያለትን የቆየ ቁርሾ እንደመቀስቀስ ይቆጠራል ሲሉ ተችተዋል።
ባላል ሞሃመድ፤ ሂራን ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍም ጠ/ሚኒስትር አብይ ዛይላ ወደብን አስመልክቶ የሰጡት አስተያየት፣ በብዙ ጥረት ወደ መልካም ግንኙነት የተመለሰውን የሶማሊያና ኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያበላሽ ነው ሲሉ አሳስበዋል።


ጉዳዩ ቀጠናውን ወደ ቀውስ የሚወስድ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ  ሰሞኑን ለጎረቤት ሀገራት  ያቀረቡትን  የወደብ ባለቤትነት ድርድር ጉዳይ የተቃወመችው ሌላኛዋ አገር ጅቡቲ ነች ። የጅቡቲ ፕሬዝዳንት እስማኤል ኡመር ጊሌ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሌክሴስ ሞሃመድ፤ ጅቡቲና ኢትዮጵያ ጠንካራ የሆነውን ግንኙነታቸውን አስጠብቀው የሚኖሩ ሀገራት  መሆናቸውን ጠቅሰው፤ “ ነገር ግን ጅቡቲ ሉአላዊ ሀገር ናት፤ የግዛት አንድነታችን ዛሬም ሆነ ወደፊት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም” በማለት ጥያቄው በሀገራቸው በኩል ተቀባይነት እንደሌለው መግለጻቸውን ብሉምንበርግ ዘግቧል ። ኤርትራ በማስታወቂያ ሚኒስትሯ በኩል በሰጠችው ምላሽ፤ ኤርትራ የኢትዮጵያን የወደብ ባለቤትነት ጥያቄ እንደማትቀበለውና ቦታ እንደማትሰጠው ገልፃለች፡፡ ኤርትራ አክላም፤ በባሕር በር ዙሪያ የተነሳው ትርክት “ከመጠን ያለፈ” እና “ግራ የሚያጋባ ነው” ስትል ጉዳዩን ውድቅ አድርጋዋለች ።

Page 10 of 677