Administrator

Administrator

     አሜሪካ፣ አለምባንክ፣ ሱዳን እና ግብጽ ጫና እያሳደሩ ነው
                    በህዳሴው ግድብ ጉዳይ እየተደረገ ባለው ድርድር አሜሪካ፣ አለም ባንክ፣ ግብጽ እና ሱዳን በጋራ ተሰልፈው በኢትዮጵያ ላይ ጫና እየሳረፉ ነው፤ የድርድሩ አቅጣጫም ወደ ውሃ ድርሻ ክፍፍል እንዲዞር ተደርጓል ተብሏል፡፡
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና በድርድር ሂደቱ ኢትዮጵያን ከወከሉ ኃላፊዎች አንዱ የሆኑ ባለስልጣን ለውጭ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መረጃ ድርድሩ ፈሩን ለቆ ወደ የውሃ ድርሻ ድርድር ዞሯል ብለዋል፡፡
“ቀደም ሲል በግድቡ የውሃ አሞላል ጉዳይ የነበረው ድርድር ወደ ውሃ ድርሻ ድርድር ዞሯል” ያሉት ኃላፊው በግድቡ ጉዳይ ብዙውን ጊዜ ከኢትዮጵያ ጐን ትሠለፍ የነበረችው ሱዳንም ከግብጽ ጋር ወግናለች ብለዋል፡፡
ድርድሩ እየተካሄድ ያለው ኢትዮጵያ በአሜሪካ፣ አለም ባንክ፣ ሱዳን እና ግብጽ ጫና ስር ወድቃ 4 ለ1 በሆነ ሁኔታ ነው ሲሉ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በአሜሪካ ሲካሄድ በቆየው ድርድር ጉዳዩ ለመገናኛ ብዙሃን ቀደም ባለው ሣምንት ማብራሪያ የሰጡት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ድርድሩ ከተቋጨ በኋላ ለፊርማ የተዘጋጀው ሰነድ የተሟላ ሆኖ ባለመገኘቱ በኢትዮጵያ በኩል ውድቅ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡
ድርድሩ የውሃ ድርሻ ክፍፍል መልክ እንደነበረው ያረጋገጡት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በኩል ተገቢ ያልሆነ ስምምነት እንዳይፈርም ጥንቃቄ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በበኩላቸው ቀደም ባለው ሣምንት ፓርላማው ባቀረቡት ማብራሪያ ስምምነቱ እንዲዘገይ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡  


 ዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ በርካታ መንገደኞችን በማስተናገድ ቀዳሚ ሆኗል

             ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 የተለያዩ የአለማችን አገራትን የጎበኙ አለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር በ4 በመቶ በማደግ፣ 1.5 ቢሊዮን መድረሱንና በአመቱ ከ90 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች የጎበኙዋት ፈረንሳይ፤ በበርካታ ቱሪስቶች የተጎበኘች ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗ ተነገረ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የቱሪዝም ድርጅት ያወጣውን አመታዊ ሪፖርት ጠቅሶ ፎርብስ መጽሄት እንደዘገበው፤ በአመቱ በ83.8 ሚሊዮን ቱሪስቶች የተጎበኘችው ስፔን የሁለተኛነት ደረጃን ይዛለች፡፡ በቱሪስቶች እድገት ከአለማችን አገራት ቀዳሚነቱን የያዘችው ማይንማር ስትሆን አገሪቱን የጎበኙ የቱሪስቶች ቁጥር በአመቱ የ40.2 በመቶ እድገት ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ የ31.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበችዋ ፖርቶ ሪኮ በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው አለማቀፍ መንገደኞችን በማስተናገድ በአለማችን ቀዳሚው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ሆኖ የዘለቀው የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቆ መዝለቁን የዘገበው ገልፍ ኒውስ፤ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ 86.4 ሚሊዮን መንገደኞችን ማስተናገዱን አመልክቷል፡፡ የእንግሊዙ ሄትሮው አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ 80.4 ሚሊዮን መንገደኞችን በማስተናገድ፣ የአለማችን ሁለተኛው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ መሆኑንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


የሌሴቶ ቀዳማዊት እመቤት ጣውንታቸውን ገድለዋል በሚል በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ዘ ጋርዲያን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ የቀድሞ የትዳር አጋር የነበሩት ሊፖሊዮ ታባኔ በ2017 መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በግድያው ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉት የወቅቱ የአገሪቱ ቀዳማዊት እመቤት ሜሳህ ታባኔ ባለፈው ማክሰኞ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንና በነፍስ ማጥፋት ሊከሰሱ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ፖሊስ ከግድያው ጋር በተያያዘ ምርመራ መጀመሩን ተከትሎ ከእስር ለማምለጥ አገር ጥለው ወደ ደቡብ አፍሪካ ጠፍተው የነበሩት ቀዳማዊት እመቤት ሜሳህ ታባኔ፣ ባለፈው ማክሰኞ ወደ አገራቸው እንደተመለሱ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቶማስ ታባኔ የቀድሞ የትዳር አጋራቸው ሊፖሊዮ ታባኔ ከመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ተገድለው ከተገኙ ከሁለት ወራት በኋላ ከአሁኗ ቀዳማዊት እመቤት ሜሳህ ታባኔ ጋር ትዳር መመስረታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በግድያው የተጠረጠሩት ቀዳማዊ እመቤቷ በቅርቡ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

Saturday, 08 February 2020 16:21

የልጆች ጥግ

 
           ውድ ልጆች፡- መኝታ ክፍል የግል ሥፍራ መሆኑን ታውቃላችሁ አይደል!? ሰው መኝታ ክፍል ውስጥ ዘው ብሎ አይገባም፡፡ በመኝታ ክፍላችሁ ውስጥ የራሳችሁን ነገሮች ታስቀምጣላችሁ፡፡ አንዳንድ ነገሮቻችሁን ሰዎች እንዲያዩባችሁ አትፈልጉ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የዕለት ማስታወሻ ማስፈሪያችሁን (ዲያሪያችሁን) ማንም እንዲነካባችሁ ላትፈልጉ ትችላላችሁ:: ትክክል ናችሁ፡፡ እናንተም የሌሎችን የግል ንብረት ያለ ፈቃድ መንካት የለባችሁም፡፡
የቤተሰብ አባላትን የመኝታ ክፍሎች አክብሩ፡፡ በሌሉበት መሳቢያቸውን ወይም ኮመዲናቸውን ከፍታችሁ መመልከት ወይም መበርበር የለባችሁም፡፡ ቦርሳቸውን ወይም ሞባይላቸውን መክፈት ወይም መውሰድ ትክክል አይደለም፡፡ የሰው ዕቃ የወንድም ይሁን የአባት ወይም የእናት ሳታስፈቅዱ መውሰድ የለባችሁም፡፡
የመኝታ ክፍሉ በሩ ዝግ ከሆነ፣ ከመግባታችሁ በፊት ማንኳኳት አለባችሁ፡፡ ከዚያም ‹‹እገሌ ነኝ፤ መግባት እችላለሁ?›› ብላችሁ ጠይቁ፡፡ “መግባት ትችላለህ” ወይም “ትችያለሽ” እስክትባሉ ድረስ በትዕግስት ጠብቁ፡፡ መታጠቢያ ክፍል ከሆነ ደግሞ በሩን ከመክፈታችሁ በፊት ባዶ መሆኑን ወይም ሰው አለመኖሩን አረጋግጡ፡፡
ውድ ልጆች፡- ሁሌም አባትና እናታችሁን፣ ታላላቅ ወንድምና እህቶቻችሁን ማክበርና የሚነግሯችሁን መስማት አለባችሁ፡፡ መምህራኖቻችሁንም አክብሩ፡፡ በመምህራን መሳቅና ማሾፍ ተገቢ አይደለም፡፡ ታናናሾቻችሁን ደግሞ በምትችሉት ሁሉ እርዷቸው፡፡  
እደጉ! እደጉ! እደጉ!

      የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀምና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ ከስልጣን እንዲነሱ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በሴኔቱ ውሳኔ ነጻ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ሪፐብሊካኑ አብላጫ ወንበር የያዙበት ሴኔት ባለፈው ረቡዕ በትራምፕ ላይ በተመሰረቱት ሁለት ክሶች ላይ ድምጽ የሰጠ ሲሆን፣ ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የቀረበባቸውን ክስ 52 ለ48፤  የአገሪቱን የምክር ቤት ስራ አደናቅፈዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ደግሞ 53 ለ47 - ሁለቱንም ክሶች በአብላጫ ድምጽ ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡
ምንም አይነት ጥፋት አልፈጸምኩም በማለት ሲከራከሩ የቆዩት ዶናልድ ትራምፕ፤ በአገሪቱ ታሪክ ሴኔት ፊት ቀርበው ክሳቸውን እንዲከላከሉ የተወሰነባቸው ሶስተኛው ፕሬዚዳንት ቢሆኑም፣ ሴኔቱ በሰጠው ድምጽ ስልጣናቸውን ከመልቀቅ እንደታደጋቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ትራምፕ የዩክሬን አቻቸው ቭላድሚር ዘለንስኪን በቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትና በምርጫ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደን እና በልጃቸው ላይ የሙስና ምርመራ እንዲያደርጉ በመደለልና ጫና በማድረግ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም፤ እንዲሁም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለሚደረግባቸው ምርመራ መረጃዎችን ባለመስጠትና የምክር ቤቱን ስራ በማደናቀፍ እንዲከሰሱ በቀረበባቸው የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ የአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወር በፊት ለአስር ሰዓታት ያህል ክርክር ካደረገ በኋላ እንዲከሰሱና ሴኔት ፊት ቀርበው የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው ረቡዕ ሴኔቱ በሰጠው ድምጽ ከሁለቱም ክሶች ነጻ ሊወጡ መቻላቸውንም አመልክቷል፡፡
የቀረበባቸውን ክስ የአክራሪ ግራ ዘመሞች ነጭ ቅጥፈትና በሪፐብሊካን ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ሲሉ በአደባባይ ያጣጣሉት ዶናልድ ትራምፕ፤ ከስልጣን እንዲለቁ በዲሞክራቶች የተጎነጎነባቸውን ሴራ በመበጣጠስና ራሳቸውን ነጻ በማውጣት ያስመዘገቡትን ድል ለሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመን በሚወዳደሩበት ቀጣዩ የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመድገም መዘጋጀታቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በኮንግረስ ውሳኔ ሴኔት ፊት ቀርበው ክስ እንዲመሰረትባቸው የተወሰነባቸው ሁለት የአገሪቱ መሪዎች አንድሪው ጆንሰንና ቢል ክሊንተን እንደነበሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ያም ሆኖ ግን ሁለቱም ከስልጣን እንዲለቅቁ እንዳልተወሰነባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡


Saturday, 08 February 2020 16:03

የግጥም ጥግ

  ሞልትዋል ብላቴና

ደመረ ብርሃኑ
(በአዲስ አድማስ 15ኛ ዓመት የግጥም
ውድድር 2ኛ የወጣው ግጥም)
ነበር ፍጹም ጨቅላ በጥቁር አፈር ላይ በጥቁር
ተፀንሶ
ጥቁር የወለደው ጥቁር ስጋ አልብሶ፣
ነበር ብላቴና
ከጥቁር ገላ ውስጥ ነጭ ወተት ግቶ
አጥንቱ የጸና የቆመ በርትቶ፣ ነበር ደቀ መዝሙር
ጥቁር ብላቴና
በነጭ ጠመኔ በጥቁር ሰሌዳ
ሀ ሲሉት ሃ ብሎ A ሲሉት A ብሎ
ጥቁሩን ከነጩ ጋር አዋዶ ያጠና፡፡
ታሪክ የጻፈውን ሳይንስ እያጠፋ
ሳይንስ የፃፈውን ሂሳብ እያጠፋ
ሂሳብ የፃፈውን ሲቪኩ እያጠፋ፤
በተዥጎረጎረች ባንዲት ሰሌዳ ላይ
ሁሉም የእየራሱን ሲያስተምር ሲለፋ
አንዲትዋ ሰሌዳ ጥቁር ወዝዋ ወድሞ
ወጭው የጫረውን ገቢው እያጠፋ
ነበር ብላቴና
ካንድ ወንበር ተቀምጦ ትዝብቱ ያልሰፋ
በሰሌዳው ማድያት በስሎ ያልተከፋ፡፡
***

Saturday, 08 February 2020 16:02

የፖለቲካ ጥግ

 • በርግጥም ፖለቲከኞችን ተዋንያን ብለን ልንጠራቸው ይገባል፡፡
 ማርሎን ብራንዶ
• ፕሬዝዳንቶች ለሚስቶቻቸው ያላደረጉት ነገር ካለ ለአገራቸው ያደርጉታል፡፡
 ሜል ብሩክስ
• እኔ ፖለቲከኞች የሚባሉትን በሙሉ ስጠላ እንደ ጉድ ነው፡፡ የመጨረሻ የደደቦች ስብስብ ማለት እነሱ ናቸው፡፡
 ማይክል ኬን
• ሬጋን ሲናገር አዳምጬ ሳበቃ፣ ድንጋይ ወርውር ወርውር አሰኝቶኛል፡፡
 ሔንሪ ፎንዳ
• እኛ ሁላችንም ድምፅ በመስጠት አንድ ሰው እንመርጣለን፡፡ ስለሆነም ‹‹ከእኛ ጋር አግባብ ያለው፣ ፍፁም ተግባቢ ሰው እናስመስለዋለን›› እንደ እውነቱ ከሆነ
ግን ተዋናይ ማለት እራሱን መግባባትን ለመሸወድ ለዓመታት ሲሰለጥን የከረመ ሰው ነው፡፡
 ዴስቲን ሆፍማን
• ከፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ጋር በኋዋይት ሀውስ ለ15 ደቂቃ ያህል አብሬ ቆይቻለሁ:: እግዚአብሄር በሚያውቀው ምንም ምቾት አልተሰማኝም፡፡ ለነገሩ ይሄ የእኔ እንጂ የእሱ ችግር አይደለም፡፡
 ሮበርት ሬድፎርድ
• እኔ ከልቤ ኮሙኒስት ነኝ ፡፡
 ሪቻርድ በርተን
• በሕይወቴ አንድ ቀን እንኳ ድምጽ ሰጥቼ አላውቅም፤ ወገናዊ ለሆነ ፖለቲካም ሆነ ሃይማኖት ፍላጎት የለኝም፡፡ ምናልባት በ16 ዓመቴ ኮሙኒስት ሆኜ ይሆናል፡፡ በ22 ዓመቴ ሶሻሊስት ነበርኩ፡፡ አሁን ያለ ጥርጥር ካፒታሊስት ነኝ፡፡
 ማይክል ኬን
• ፖለቲካ ወይ የሀብታሞች ወይ የሸርሙጦች ስፖርት ነው፡፡
 ሪቻርድ ድሬይፉዝ
• በበኩሌ የግራ ክንፍም ሆነ የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኛ ልሆን አልችልም፡፡ ምክንያቱም ራሴን በጣም ግለኛ አድርጌ ስለምቆጥር ነው፡፡
 ክሊንት ኢስት ውድ
• የብሪታኒያ ሰዎች በአዕምሯቸው፣ ሶሻሊስቶች በልባቸው ወግ አጥባቂዎች (Conservative) ናቸው፡፡
 አልበርት ፊኔ
• ካፒታሊስት ነኝ፡፡ ፕሮዲዩሰር ነኝ፡፡
 ዣን ሉክ ጎዳርድ
• ለእኔ ኤክስትራ ቴሬስትሪያል የዘመናት ሁሉ ታላቅ የፖለቲካ ፊልም ነው፡፡ እንደሚመስለኝ ለዛ ፊልም ስፒልበርግ የሰላም የኖቤል ሽልማት ሊሰጠው ይገባል፡፡
 ክላውድ ሌሉ
• ልክ እንደ ሲኒማ ንግድ፣ ፖለቲካም እንደነበረው አይኖርም፡፡ አሁን ያለውም መሆን እንደሚገባው አይደለም፡፡
 ሮበርት ሬድፎርድ
• ፖለቲካ አጠገብ ድርሽ አልልም፡፡ የዞረበት አልዞርም፡፡
 ሊይን ሬድፎርድ
• በበኩሌ የግራ ክንፍ መሆን የሚችለውን ያህል የግራ ክንፍ ነኝ፡፡
 ቫኔሳ ሬድ ግሩቭ
• ኮሙኒስት ሆኜ ባውቅ ኖሮ የራስህ ጉዳይ እልህ ነበር፡፡ እኔና ባሌ ኮሙኒስት እንዳለመሆናችን ወደፊትም የራስህ ጉዳይ ለማለት ዝግጁ ነን፡፡
 ሲሞን ሲግኔት
• እኔ ሪፐብካዊ ገበር ያለኝ ዲሞክራት ነኝ፡፡ ስለ ብዙ ነገሮች ነፃ አስተሳሰብ ነው ያለኝ:: እንደ አሜሪካ ግን ምንም የምጠምደው አገር የለም፡፡
 ስቲቨን ሰፒልበርግ

Saturday, 08 February 2020 15:10

ኮሮና ቫይረስ በሳምንቱ

ቻይናን ጨምሮ በመላው አለም በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስከ ትናንት ድረስ ከ28 ሺህ ማለፉንና በቫይረሱ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም 565  መድረሱን የተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ባወጧቸው ዘገባዎች ገልጸዋል፡፡
ከቻይና ውጭ በተለያዩ 31 የአለማችን አገራት በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር እስከ ትናንት ድረስ 262 ያህል መድረሱን የዘገበው ሮይተርስ፣ በሆንግ ኮንግ አንድ፣ በፊሊፒንስ አንድ ሰው ለሞት መዳረጋቸውንም አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ በቻይናዋ ውሃን ግዛት የተወለደ ጨቅላ ከተወለደ ከ30 ሰዓታት በኋላ በኮሮናቫይረስ መጠቃቱ በምርመራ መረጋገጡን የዘገበው ሮይተርስ፣ የህጻኑ እናት ከወሊዱ በፊት በተደረገላት ምርመራ በቫይረሱ መጠቃቷ መረጋገጡንና ይህም ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድል እንዳለው ፍንጭ የሚሰጥ በመሆኑ ተመራማሪዎች ትኩረት እንዲሰጡት ማድረጉን አመልክቷል፡፡
በጃፓኑ ዩኮሃማ ወደብ ዳርቻ ስትንቀሳቀስ በነበረች አንዲት ግዙፍ መርከብ ውስጥ ከነበሩ መንገደኞች መካከል 20ዎቹ በኮሮናቫይረስ እንደተጠቁ መረጋገጡን ተከትሎ፣ መርከቧ እንዳትንቀሳቀስ መደረጓንና መንገደኞች ለ14 ቀናት ያህል መርከቧ ውስጥ ይቆያሉ መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በሆንግ ኮንግም በተመሳሳይ ሁኔታ፣ 3 ሺህ 600 መንገደኞችን ይዛ ስትጓዝ ከነበረች መርከብ ውስጥ 3 መንገደኞች በቫይረሱ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ፣ ተጓዦች ከመርከቧ እንዳይወጡ ተደርገው ምርመራው መቀጠሉንና የአገሪቱ መንግስት ከቻይና የሚገቡ መንገደኞችን በሙሉ በልዩ የተገለለ ስፍራ እንደሚያቆይ ማስታወቁም ተነግሯል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስን ስርጭት ለመግታት ለሚደረገው ጥረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት 675 ሚሊዮን ዶላር እንዲለግሱ ጥሪ ማቅረቡ የተነገረ ሲሆን፣ ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ከትናንት በስቲያ ለኮሮና ቫይረስ ክትባት ምርምርና ህክምና የሚውል የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉንም ፎርብስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ሳምንት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿን ከቻይናዋ ውሃን ግዛት ያስወጣችው አሜሪካ፤ ባለፉት ቀናትም ተጨማሪ 350 ዜጎቿን ማስወጣቷንና ሰዎቹ ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኙ ወታደራዊ ማዕከላት ከሰው ተገልለው እንዲቀመጡ መደረጋቸው ተነግሯል:: የታይዋን መንግስት ከሃሙስ ጀምሮ ከቻይና ለሚመጡ ሰዎች ድንበሯን ዝግ ማድረጉን በይፋ ያስታወቀ ሲሆን፣ አውስትራሊያና ኒውዚላንድን ጨምሮ በርካታ የአለማችን አገራት ዜጎቻቸውን ማውጣት መቀጠላቸውም ተዘግቧል፡፡
ከአውሮፓ አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በቫይረሱ የተጠቁባት አገር ጀርመን መሆኗን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ እስከ ትናንት ድረስ 12 ጀርመናውያን በቫይረሱ መጠቃታቸውንም አመልክቷል፡፡ በአሜሪካም በተመሳሳይ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር 12 መድረሱን ዘገባው አስታውቋል፡፡
በቻይናዋ የፋይናንስ ከተማ ሻንጋይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በሙሉ ለአንድ ወር ያህል እንዲዘጉ መወሰኑን የዘገበው ሮይተርስ፣ ኤር ካናዳ፣ ኤር ፍራንስ፣ ኤር ኢንዲያ፣ ኤር ታንዛኒያና ኳታር ኤርዌይስን ጨምሮ ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ሙሉ ለሙሉና በከፊል ለማቋረጥ የወሰኑ አየር መንገዶች መበራከታቸውን ጠቁሟል፡፡ ኮሮና ቫይረስ በአለማቀፍ ደረጃ እያሳደረ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ተባብሶ መቀጠሉን የዘገበው ዘ ጋርዲያን በበኩሉ፣ በታላላቅ አየር መንገዶች፣ በመኪና አምራችና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች፣ በቱሪዝም ተቋማት፣ በአክሲዮን ገበያዎች ወዘተ ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረሱን አመልክቷል፡፡
ከ170 ቀናት በኋላ የሚጀመረው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊስተጓጎል እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መፈጠሩን የአዘጋጅ ኮሚቴው ሃላፊ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ከቻይና የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መባባስ ጋር ተያይዞ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እጥረት ገጥሟት በሰነበተችው ሆንግ ኮንግ ከሰሞኑ ደግሞ የመጸዳጃ ቤት ወረቀትና የኮንዶም እጥረት መከሰቱን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ማህበራዊ ድረገጾች ባለፉት ቀናት ያሰራጩት የምርቶች እጥረት ማስጠንቀቂያ መልዕክት በርካታ ዜጎችን እንዳስጨነቃቸውና ምርቶችን በብዛት መግዛት እንዳስጀመራቸው የጠቆመው ዘገባው፤ ካለፈው ረቡዕ አንስቶ በአገሪቱ በሚገኙት መደብሮች የመጸዳጃ ቤት ወረቀትና ኮንዶምን ጨምሮ በርካታ ሸቀጦች መጥፋታቸውን አስታውቋል፡፡


             ከዕለታት አንድ ቀን በርካታ የተራቡ ጅቦች በአንድ ገደል አፋፍ እየሄዱ ሳሉ፤ አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን እገደሉ አዘቅት ውስጥ ወድቆ ሞቶ አዩ፡፡
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ጎበዝ አዘቅቱ ውስጥ የወደቀው ዝሆን ይታያችኋል?›› አለና ጠየቀ፡፡
ሁለተኛው ዝሆን፤
‹‹ፍንትው ብሎ ተጋድሞ ይታየኛል››አለና መለሰ፡፡
ሦስተኛው ዝሆን፤
‹‹እኔ አንድ ሀሳብ አለኝ››
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ምንድን ነው ንገረና?››
ሦስተኛው ዝሆን፤
‹‹ለምን ገብተን አንበላውም? በጣም የሰባ ምርጥ ጮማ ያለው ዝሆን እኮ ነው፡፡››
ሁለተኛው ዝሆን፤
‹‹ይሄ ምርጥ ሀሳብ ነው፡፡ ቶሎ እንግባ እባካችሁ?››
አንደኛው ዝሆን፤
‹‹ዕውነት ነው እንግባ ጎበዝ!››
ሁሉም ‹‹ይሁን፣ ይሁን›› አሉ፡፡
ሁሉም የገደሉን ቁልቁለት ወረዱት፡፡
ያንን ጮማ ዝሆን እያሽካኩ ተቀራመቱት፡፡
ሁሉም ሆዳቸው ሞላ፡፡ ግን አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡
በሞላ ሆድና በዝሆን ግዝፈት ማን ገደሉን ወደ ላይ ይውጣው?
ዋሉ፡፡
አደሩ፡፡
ረሀብ መጣ፡፡
ጥቂት ቀናት ቆይተው አንድ ሌሊት ላይ አንዱ ዝሆን ጭልጥ አድርጎ እንቅልፍ እንደወሰደው ሌሎቹ ዝሆኖች ተሰበሰቡና መከሩ፡፡ በመጨረሻም፤ በሚያንቀላፋው ዝሆን ፈረዱበት - ሊበሉት፡፡
በሉትና ጥግብ አሉ፡፡ በአካባቢው ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ወደ ገደሉ አፋፍ ለመውጣት ግን አልቻሉም፡፡ ስለዚህ አንዱ አንዱን እንኮኮ እያለ፣ ወደ ጫፍ ዘለቁ፡፡ በመጨረሻ ግን አንዱ ተሸካሚ ዝሆን ከታች ቀረ፡፡ ማንም ሊያወጣው የሚችል አልኖረም፡፡
ብቻውን ቀረ፡፡
ቀን እየገፋ መጣ፡፡ አካሉ ሁሉ እየከሳ መጣ፡፡ ረሀቡን መቋቋም አቃተው፡፡ በዚያው ሕይወቱ አለፈ፡፡
*   *   *
ነገ የሚከተለውን ችግር ሳያስቡ መጓዝ መጨረሻው አያምርም፡፡ በተራ ሰው ግምት እንኳ ቢጠናና ቢመረመር ነገን ሳያስቡ መጓዝ፣ የዛሬን አላስተማማኝ መንገድ ማረጋገጥ ነው፡፡ የማያስተማምኑ መንገዶች መድረሻን ወደ አለማወቅ የሚያመሩ በመሆናቸው ለውድቀት ይዳርጋሉ፡፡ ቢያንስ አይቀሬ ወደሆነው የዕለት - ሰርክ የሥጋት ዓለም ውስጥ በሽብልቅ የሚደነጎሩ ይሆናሉ፡፡ የተሸበለቀ ሕይወት፤ የተውገረገረ አመለካከትና እሳቤ ውስጥ ስለሚከት፣ የነገ ብሩህና የጠራ አስተሳሰብ እንዳይኖረን የሚያደርግ ጎልዳፋ ህልውና ላይ ይጥለናል፡፡
የአገራችን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሕልውና ቅጥ አምባር በቀና አመራር ሥር ከተቀነበበ፣ የተስፋና በእቅድ የተያዘ ምንነት ይኖረዋል፡፡ የሕግን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የፍትህ ርትዕ ጥራትና ግዝፈት ይጎላ ዘንድ ይሆን ተብሎ ሊታሰብበት የሚገባ ነው፡፡ ያልጠና ዳኝነት ከናካቴው ካልታየው አንድ ነው፡፡ በሙስና ውስጥ የተዘፈቀ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ማንነት ወደ ማህበራዊ ማንነት ማምራቱ አይቀሬ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓት ሲዛባና የጤና ሥርዓት ጤና ሲያጣ፣ ባህል ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ ላይ ይወድቃል፡፡ የባህል ወግ ማዕረግ አባ-ከና የሚለውና ባለቤት ያጣ ቤት ሲሆን የሕዝብ ሥነ ልቦና ሳይቀር የሚያዝ የሚጨብጠውን ደርዝ ያጣል፡፡
በመሠረቱ ኃላፊነት የሚሰማው ሕብረተሰብን ለመፍጠር፣ በኃላፊነት የሚቀመጥበትን ቦታ አጥብቆ የተገነዘበ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ ትክክለኛውን ሹም በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ ምንጊዜም ቢሆን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ (The right man at the right place እንዲል መጽሐፍ) በጥኑና በጥንቃቄ የተቀመረ መዋቅራዊ ሥርዓት ያሻል፡፡ ነገሮች እንደ ሰንሰለት የተሳሰሩ ናቸው፡፡ ይህ ሥርዓት በቀናና በሰለጠነ መሰረት ላይ ካልተቀነበበ፣ የላላና ውሽልሹል የሆነ አጥር እንደማለት ይሆናልና በቀላሉ ይደረመሳል፡፡
በተለይ የነቃና የተባ ወጣት ትውልድ፣ ፍሬ ያለው ይሆን ዘንድ ብርቱ ጥረት ይጠበቅበታል፡፡ ከመዋሸት፣ ከመስረቅ፣ የራስን ዕምነት ከማጣት መገላገል ተገቢ ነው:: ምንጊዜም ወደፊትና ወደ ተሻለ ሕይወት ለመጓዝ ዝግጅት ያስፈልገዋል። ወጣቱ በተለያየ ምክንያት እየፈዘዘና እየደነዘዘ ከሄደ እንቅስቃሴው የተዳከመ ይሆናል:: የጥንቱ የስፖርት ባለሙያ ታላቅና መሪ፣ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሱዳን በኳስ እንዴት ከኛ የተሻለ ሁኔታ ላይ ተገኘ? ሲባሉ፡- ‹‹ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ›› ያሉት ይሄንን ዓይነቱን ሁኔታ አስተውለው ነው!!    


   ከእስያ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ መካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ መላውን አለም በስጋት ማራዱን፣ ብዙዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን፣ ከጤና ችግርነት አልፎ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቀውስ ማስከተሉን ተያይዞታል - በቻይና ተቀስቅሶ በፍጥነት በርካታ አገራትን ማዳረሱን የቀጠለው አደገኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፡፡
ባለፈው ወር በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ለመጀመሪያ የታየውና እያደር እየተስፋፋና በወረርሽኝ መልክ በመከሰት አህጉር ተሻግሮ ወደተለያዩ የአለማችን አገራትን በመዛመት ብዙዎችን ማጥቃቱን የቀጠለው ኮሮና ቫይረስ የአለማችን መገናኛ ብዙሃን የሳምንቱ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ጉዳዩን በተመለከተ በሳምንቱ ካወጧቸው ዘገባዎች የቀነጫጨብናቸውንና የኮሮና ቫይረስን ወቅታዊ ሁኔታ ያስቃኛሉ ያልናቸውን መረጃዎች እንዲህ ይዘን ቀርበናል፡፡

እያሻቀበ የመጣው የተጠቂዎችና የሟቾች ቁጥር
የቫይረሱ ወረርሽኝ በተቀሰቀሰባት ቻይና እስካ ትናንት ተሲያት ድረስ ከ213 በላይ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውንና በድምሩ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን የአገሪቱ መንግስት ይፋ ባደረገው መረጃ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከቻይና ውጭ በቫይረሱ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩ ተነግሯል፡፡
ዘጋርዲያን እንደዘገበው እስከትናንት ረቡዕ ድረስ ታይላንድ 14፣ ሆንግ ኮንግ 8፣ ጃፓን 7፣ አሜሪካ፣ ታይዋንና አውስትራሊያ እያንዳንዳቸው 5፣ ሲንጋፖር፣ ደቡብ ኮርያ፣ ፈረንሳይና ማሌዢያ እያንዳንዳቸው አራት፣ ካናዳ 3፣ ቬትናም እና እንግሊዝ 2፣ ኔፓል፣ ካምቦዲያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመንና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እያንዳንዳቸው 1 ዜጎቻቸው በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸውን በይፋ አስታውቀዋል፡፡

አገራት ዜጎቻቸውን እያወጡና ድንበር እየዘጉ፣ አየር መንገዶች በረራ እያቋረጡ ነው
አሜሪካ እና ጃፓን ባለፈው ረቡዕ ብቻ በቻይናዋ ውሃን ግዛት ውስጥ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ያስወጡ ሲሆን፣ እንግሊዝም በርካታ ዜጎቿን ወደ ግዛቷ መልሳለች ተብሏል፡፡
የእንግሊዙ ብሪቲሽ ኤርዌይስ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች በሙሉ መሰረዙን ባለፈው ረቡዕ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካው ዩናይትድ ኤርላይንስም ወደ ቻይና ያደርጋቸው የነበሩ 24 በረራዎችን መሰረዙን ገልጧል፡፡
ወደ ቻይና ያደርጉት የነበረውን በረራ በእጅጉ ከቀነሱ ሌሎች የአለማችን አየር መንገዶች መካከልም ኤር ካናዳ፣ ካቲ ፓሲፊክ፣ ኤር ሴኡልና ላዮን ኤር አንደሚገኙበትም ዴይሊ ሜይል ዘግቧል፡፡
የፊት ጭምብል እጥረት ተከስቷል
ቫይረሱ በትንፋሽ የሚተላለፍ እንደመሆኑ ቻይናውያን አፍንጫ እና አፋቸውን በጭምብል ሸፍነው እንዲንቀሳቀሱ በመንግስት አካላት መመሪያ እንደተሰጣቸው የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ ይህን ተከትሎም በአገሪቱ የጭምብል እጥረት መከሰቱን አመልክቷል፡፡
ይህን የአቅርቦት ችግር እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በመዲናዋ ቤጂንግ ጭምብሎችን ከመደበኛው ዋጋቸው በ6 እጥፍ ያህል ጨምሮ ሲሸጥ የተገኘ አንድ መድሃኒት ቤት 400 ሺህ ዶላር እንደተቀጣም ዘገባው ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኔሴፍ የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን እጥረት ለመቅረፍ በማሰብ ጭንብልን ጨምሮ 6 ሜትሪክ ቶን የሚመዝኑ ቁሳቁሶችን ባለፈው ረቡዕ ወደ ቻይና መላኩን አስታውቋል፡፡
 
ክትባት ፍለጋ ደፋ ቀና
የኮሮና ቫይረስ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ከ17 አመታት በፊት በአገሪቱ ተከስቶ የነበው ሳርስ የተሰኘ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ካጠቃቸው ሰዎች መብለጡን የዘገበው ዘጋርዲያን፣ ይህን ተከትሎም አገሪቱ ከአለም የጤና ድርጅትና ከሌሎች አገራት መንግስታት ጋር በመተባበር ወረርሽኙን ለመግታት ጠንክራ መስራት መጀመሯን አመልክቷል፡፡
ኮሮና እያደር ወደ በርካታ አገራት መስፋፋቱንና አለማቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ፣ ቻይናውያንን ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት ስመጥር የህክምና ሊቃውንትና የዘርፉ ተመራማሪዎች ለዚህ አደገኛ ቫይረስ ክትባት ለማግኘት ሌት ተቀን ደፋ ቀና በማለት ላይ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
ከቻይና ተመራማሪዎች በተጨማሪ የአሜሪካ እና የአውስትራሊያ የምርምር ተቋማትና ሳይንቲስቶች ወረርሽኙን ለመግታት የሚያስችል አንዳች መላ ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ሮይተርስ፣ የሚልቦርን ተመራማሪዎች ከአንድ ታማሚ ደም በመውሰድ ለምርምር የሚውል ቫይረስ እየፈጠሩ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ጉዳዩ አለማቀፍ ስጋት መሆኑን ተከትሎ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ባለፈው ረቡዕ ወደ ቻይና አቅንተው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በቤጂንግ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ድርጅታቸው የቫይረሱን ስርጭት ከቻይና ጋር በትብብር እንደሚሰራ እና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡
 
ኮሮና እና የአለም ኢኮኖሚ
በቻይና የሚንቀሳቀሱ የአሜሪካ ኩባንያዎች የኮሮና ቫይረስ መስፋፋቱን ተከትሎ ስራቸውን በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ እያቋረጡ መውጣት መጀመራቸውን የተለያዩ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመዘገብ ላይ ይገኛሉ፡፡
ስታርባክስ በቻይና ከሚገኙት መደብሮቹ ግማሹን ወይም ከ2ሺህ በላይ የሚሆኑትን መዝጋቱን ባለፈው ማክሰኞ ያስታወቀ ሲሆን፣ የአሜሪካው ማክዶናልድ፣ የጃፓኑ ኒፖንና የደቡብ ኮርያው ኤልጂ ኤሌክትሮኒክስም በቻይና የነበራቸውን ቢሮ በመዝጋት ስራ ማቋረጣቸውን አመልክቷል፡፡
ፌስቡክ፣ ማይክሮሶፍትና አፕል ሰራተኞቻቸው ወደ ቻይና እንዳይጓዙ እገዳ መጣላቸውን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፣ በቻይና የሚገኙትም ለጊዜው ከቤት እንዳይወጡ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን አስረድቷል፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ አራት ሰራተኞቹ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁበት የጀርመኑ መኪና አምራች ኩባንያ ዌባስቶ በቻይና የሚገኘውን ፋብሪካውን ላልተወሰነ ጊዜ መዝጋቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ የጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያም እስከ መጪው የካቲት ወር አጋማሽ በቻይና ያለውን ፋብሪካውን እንደሚዘጋ አስታውቋል፡፡
የጃፓኑ ሆንዳ ሞተርስ ሰራተኞቹ ወደ ቻይና እንዳይሄዱ ማገዱንና ስታንዳርድ ቻርተርድ ባንክና የአውስትራሊያ ኮመንዌልዝ ባንክን ጨምሮ ታላላቅ አለማቀፍ ባንኮች ሰራተኞቻቸውን ወደ ቻይና እንዳይሄዱ ማገዳቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በቻይና እየተዘጉ ያሉ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች እየተበራከቱ መምጣታቸው፣ አየር መንገዶችና አገራት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ ማቋረጣቸውና በአውሮፕላን ጣቢያዎች የሚደረገው ምርመራ ጉዞን በማስተጓጎል ቢዝነስን መጉዳቱ አይቀሬ ነው እየተባለ ነው፡፡
በቻይና ሂልተንና ማሪዮትን የመሳሰሉ ሆቴሎች ስራቸውን ማቆማቸውን፣ ታላላቅ ሆቴሎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች ኦና ውለው ማደር መጀመራቸውን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፣ የንግድ እንቅስቃሴ መገታቱንና ወረርሽኙ የቻይናን የአዲሱ አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት ዕድገት ከ5 በመቶ በታች ሊያደርገው እንደሚችልም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በመናገር ላይ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡

አፍሪካ
ባለፈው ረቡዕ ወደ መካከለኛው ምስራቅ መሻገሩና በተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች አንድን ሰው ማጥቃቱ የተነገረለት ኮሮና፣ በዚህ አያያዙ በፍጥነት ወደ አፍሪካ መግባቱ እንደማይቀር የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡
ደቡብ አፍሪካ፣ ኢትዮጵና ግብጽን የመሳሰሉ በርካታ የአፍሪካ አገራት በአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎቻቸው የምርመራ ማዕከላትን በመክፈት ቫይረሱ ወደ ግዛታቸው እንዳይገባ በተጠንቀቅ ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የአፍሪካ ህብረት የጤናው ዘርፍ ሃላፊ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ በተለያዩ አገራት በወሬ ደረጃ የታመሙ ሰዎች ስለመኖራቸው ቢነገርም እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በየትኛውም የአፍሪካ አገር በህክምና ምርመራ የተረጋገጠ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው አልተገኘም፡፡

48 ሰዓት የፈጀው ሆስፒታል
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሌት ተቀን ታጥቃ የምትሰራው ቻይና 1 ሺህ አልጋዎች ያሉትን የኮሮና ቫይረስ ህክምና ሆስፒታል በ48 ሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በማደራጀት ለአገልግሎት ክፍት ማድረጓ ተዘግቧል፡፡
5000 ያህል የቻይና የግንባታ ሰራተኞች፣ ኤሌክትሪሻኖችና ሌሎች ባልደረቦቻቸው በውሃን ግዛት አቅራቢያ የሚገኝን አንድ ባዶ ህንጻ በ40 ሰዓታት ውስጥ ተረባርበው ለሆስፒታልነት እንዲበቃ ማድረጋቸው ነው የተነገረው፡፡
ቻይና ሌሎች ሁለት አዳዲስ ሆስፒታሎችን በቀናት እድሜ ውስጥ ገንብታ ለማጠናቀቅ ተፍ ተፍ እያለች እንደምትገኝም ተዘግቧል፡፡
ቻይና ውሃንን ጨምሮ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸውና 20 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ከሚኖርባቸው ሶስት ግዛቶች መንገደኞች እንዳይወጡና ቫይረሱን እንዳያሰራጩ ለማድረግ ሲባል ሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባለፈው ሳምንት ሃሙስ ዝግ ያደረገች ሲሆን፣ በሌሎች ግዛቶች የሚንቀሳቀሱ ዜጎችም ጥብቅ የጤና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝና የአዲስ አመት በዓልን ጨምሮ ሌሎች ዝግጅቶች እንዲሰረዙ መወሰኑም ይታወሳል፡፡
የቻይና መንግስት ባለፈው የፈረንጆች አመት የመጨረሻ ዕለት ከአለም የጤና ድርጅት ጋር በጋራ በሰጠው የማስጠንቀቂያ መግለጫ ቫይረሱ መቀስቀሱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ከአስር ቀናት በኋላ በቫይረሱ የተያዘው የመጀመሪያው ሰው መሞቱንና በቀጣይ ሳምንታትም በስፋት በመሰራጨት በርካቶችን ማጥቃቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ኮሮና ምንድን ነው?
ከቻይና ተነስቶ አለምን በፍጥነት በማዳረስ ላይ የሚገኘው አዲስ በሽታ ኮሮና በተባለ ቫይረስ ምክንያት የሚመጣ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሰዎችን የሚያጠቁ ከዚህ ቫይረስ ጋር ዝምድና ያላቸው ስድስት አይነት የቫይረሱ እንደነበሩ ተነግሯል፡፡
የሰሞኑ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን ግዛት ውስጥ ከሚገኝ የደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ የአሳ መሸጫ ገበያ መነሳቱን የሚጠቁሙ መረጃዎች የተገኙ ሲሆን፣ በበሽታው የተያዘ ሰው ቫይረሱን እስከ ሦስት ለሚደርሱ ሰዎች ሊያስተላልፍ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ካደረጉት ጉዳዮች አንዱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች የበሽታው ምልክቶችን ከማሳየታቸው በፊት ቫይረሱን ወደ ሌሎች ሰዎች ማስተላለፍ መቻላቸው እንደሚገኝበት የቻይና የህክምና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Page 2 of 464