Administrator

Administrator

     ኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ምንድን ነው?
ኖቭል ኮሮና ቫይረስ (COVID-19) ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ህመም ሚያስከትል ቫይረስ ነው፡፡ እንደ ጉንፋን አይነት ቀላል ምልክቶችን አሳይቶ በራሱ ሊድን ይችላል፤ ወይም ሊባባስና እንደ ሳንባምች፣ ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ብ ሎም የ ኩላሊት ስ ራ ማ ቆምና ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡

    ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

• ትኩሳት
• ማሳል
• የትንፋሽ ማጠር
• ለመተንፈስ መቸገር
በሽታው እየተባባሰ ሲሄድም፡-
• የሳምባ ምች
• የኩላሊት ስራ ማቆምና ሞት ያስከትላል፡፡

     እንዴት ይተላለፋል?

COVID-19 በሽታ ከሰው ወደሰው የሚታላለፈው አብዛኛውን ጊዜ በሳልና በማስነጠስ ጊዜ ከአፍና አፍንጫ በሚወጡ ረቂቅ የፈሳሽ ጠብታዎች ወይም ብናኞች፣ በንክኪና እጅ ለእጅ በመጨባበጥ ነው፡፡ እንዴት መከላከል ይቻላል?
• ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱና ትኩሳት ካላቸው ሰዎች መራቅ፡፡
• እጅን በአልኮል የተዘጋጀ መታሻ ወይም በሳሙና አዘዉትረዉ መታጠብ፡፡
• ከሰዎች ጋር አለመጨባበጥ፡፡
• እጆችን ሳይታጠቡ አይንን፣ አፍንና አፍንጫን አለመንካት፡፡
• በሚያስልም ሆነ በሚያስነጥስ ጊዜ አፍንና አፍንጫን በመሀረብ ወይም በሶፍት ወይም በክንድን በአፍና አፍንጫን መሸፈን፡፡
• የተጠቀሙበትን ሶፍት ወረቀትና ተመሳሳይ ነገር ወዲያውኑ በሚከደን ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ዉስጥ መጣል፡፡
• በየጊዜው ከጤና ጥበቃ/የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ስለበሽታው ሁኔታ የሚወጡ መረጃዎችን መከታተልና ተግባራዊ ማድረግ፡፡

   ከዕለታት አንድ ቀን ብዙ አህዮች በጠፍ ጨረቃ መንገድ ይጀምራሉ፡፡ አንዲት ቀበጥ አህያ ከመካከላቸው አለች፡፡ ግጦሽ አግኝተው እንደ ልባቸው ከጋጡ በኋላ ይቺ ቀበጥ አህያ፤
‹‹የዚህ አካባቢ ሳር እምብዛም አይጣፍጥም፡፡ ወደሚቀጥለው መንደር እንሂድና የተሻለ ሣር እንፈልግ›› ትላለች
አባወራው አህያ፤
‹‹ሣር ሣር ነው፡፡ ዝም ብለሽ ጋጪ! በዚህ ጠፍ ጨረቃ ጅቦች ያገኙንና ኋላ ደግ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ጥሩው ዘዴ እንቅስቃሴ ሳናበዛ፣ ድምፃችንን አጥፍተን፣ እስከምንጠግብ መጋጥ ነው›› አለ፡፡
ያቺ ጥጋበኛ አህያም፤
‹‹ግዴላችሁም ‹እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል
ደሀ ሞኝ ነው ሞቱን ይመኛል› ተብሏል፡፡ የተሻለ ሣር ወደምናገኝበት መንደር ሄደን እንደ ልብ የምንግጠው ሣር እናገኝ ይሆናል፡፡››
‹‹እሺ። በየት አቅጣጫ እንሂድ?›› አንደኛው አህያ
‹‹ወደ ምሥራቅ ጥሩ ጨፌ እንዳለ አውቃለሁ›› ሁለተኛው
‹‹ከሆነስ አይቀር ወደ ደቡብ ከሄድን በጣም ለምለም ሣር በገፍ ይገኛል፡፡›› ሦስተኛው
‹‹እኔም ፈጥነን ሳይመሽብን ወደ ደቡብ እንገሥግሥ ነው የምለው!›› አንደኛው
‹‹ደቡብ አቋራጭ ስለሌለው ይመሽብናል፡፡ የሚሻለው እኔ ያልኩት ምሥራቁ ነው፡፡ ለም ነው፤ ቅርብም ነው፡፡ ከዚያ በላይ ምን ትፈልጋላችሁ?››
ቀበጧ አህያ፤
‹‹ምርጫ  እያለን ለምን አንድ ነገር ላይ ሙጭጭ ትላላችሁ፡፡ በግድ ይሄ ቦታ ካልሆነ ካላችሁ ግን በቃ ዕጣ እናውጣ!››
አንደኛው፤
‹‹እሺ እናውጣ››
ሁለተኛው፤
‹‹እሺ ዕጣ ይለየን››
ሦስተኛው፤
‹‹እኔም በዕጣው እስማማለሁ››
በዕጣ እንዲለይ ተወሰነና ዕጣ ወጣ፡፡ ቀበጧ አህያ ያለችው ምርጫ ላይ አረፈ ዕጣው፡፡
‹‹ዕጣው እንደዛ ከሆነ ምን ማድረግ ይቻላል? ዘወር ዘወር ብለን ቦታ እንምረጥ በቃ››
መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
አንድ ለም ቦታ ደርሰው መጋጡን ተያያዙት፡፡ ጠገቡ፡፡
ያቺ ቀበጥ አህያ፤
‹‹ነፋኝ ቀበተተኝ… አንድ ጊዜ ልጩህ›› አለች፡፡
አባወራው አህያ፤
‹‹ተይ አይሆንም፡፡ ድምፅሽን ተከትሎ ጅብ ሊመጣብን ይችላል፡፡ አደጋ አለው!›› አለና አስጠነቀቀ፡፡ አሁን ቀበጧ አህያ ትንሽ ታገሰች፡፡ ትንሽ ቆይታ ግን፤
‹‹ኧረ እኔ አልቻልኩም፤ ነፋኝ ቀበተተኝ፡፡ እባካችሁ አንድ ጊዜ ልጩህ!››
አባወራው ተይ እመት አህያ… ጦስሽ ለሁላችንም ይተርፋል!”
አህያይቱ አንዴ አናፋች፡፡
ትንሽ ቆይታ ‹‹አሁንም አንዴ ልጩህ” አለች፡፡
ጮኸችና፤
‹‹ይሄዋ ምንም አልመጣም›› አለችና፡፡ ለሁለተኛ ጊዜም ጮኸች፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ ልትጮህ ተነሳች፡፡
አባወራው አህያም፤
‹‹እመት አህያ አስተውይ፡-
የመጀመሪያው ጩኸትሽ - መጥሪያ፡፡
ሁለተኛው ጩኸትሽ - ማቅረቢያ ነው፡፡
ሦስተኛው መበያሽ ነው!
አህይቱ ነገሩ ስሜትም ሳይሰጣት
ሦስቴ ጮኸች - ውጤቷ መበላት ሆነ!››
***
ሳያስቡ መጮህ ውጤቱ አያምርም፡፡ የራስን ማናፋት ለማስተንፈስ ስንቃጣ ምን እንደምናስከትል አናውቅም፡፡ ደርግ በዱሮ ዘመን መግለጫው፡-
‹‹በጫጫታና በጩኸት የፈረሰች አገር ብትኖር የመጽሐፍ ቅዱሷ እያሪኮ ብቻ ናት፡፡ እኛ ደግሞ የምትገነባ አብዮታዊት አገር እንጂ የምትፈርስ እያሪኮ የለንም›› ይል ነበር፡፡
ዕውነት ነው፡፡ በጫጫታ ላለመፍረስ የሰከነ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ ሕይወትን እንዴት መምራት እንደምንችል ማጤን ተገቢ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሁኔታ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ሞላ ሲሉት የሚጐድል፤ ጐደለ ሲሉት የሚሞላ፣ ሁሌም ትኩሳቱ የሚፈላና የሚቀዘቅዝ ነው፡፡ ሰው ሁሉን ችሎ በሁሉ ረክቶ መንቀሳቀስን ልማድ አድርጐታል፡፡ ‹‹ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል›› ይለናል፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤ እንዲህ እያለ፡-
‹‹ዛሬ ለወግ ያደረግሺው ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው
ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የተሰለጠነ እንደሁ፣
ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል!››
…እያለ ዛላውን ያስጨብጠናል፡፡
ሁሉም የዘመናችን ገጣሚያን የየራሳቸውን
ረቂቅ ቅኔ ይቀኛሉ፡፡ ገጣሚ መንግሥቱ ለማ በ “ባለ ካባና ባለ ዳባ” ቴአትራቸው አፄ ቴዎድሮስን እንዲህ ያናግሯቸዋል፡-
‹‹ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ጽድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው፣ ኪኖር በምጽዋት”
የገጣሚ ነፃነት ህይወት - አከል ነው፡፡ ባሻው ሰዓት ነፃነትን ያሰርፃል፤ ራሱ ረክቶ ሌሎችን ያረካበታል፡፡ ዓለም፤ ሰጥቶ መቀበል መሆኑን አሳምሮ ያውቃል፡፡ የሚሰጠውን አይሰስትም፡፡ የሚሰጡትን በምሥጋና ይቀበላል፡፡ መንግሥቱ ለማ እንዲህ ያሳምሩታል፡-
‹‹ደሞም ያ ገጣሚ፣ ልዩ ሥልጣን አለው
ሲያማ ሰው ቀርቶ፣ እዝጌሩም አይተርፈው!››
የሚባለው ደርዝ ባለው ገፁ ነው፡፡
በየጊዜው በአገራችን ላይ የሚከሰቱ አያሌ ጉዳዮች እንደመኖራቸው፣ የየጉዳዮቹ ባለቤት የሆኑ አያሌ ሰዎችም ከክስተቶቹ በየጀርባ ይኖራሉ፡፡ ከነዚህም መካከል የነቁና ያልነቁ አሉባቸው፡፡ የነቁትን ቁጥር ማብዛት የእኛ ፋንታና ሐላፊነት ነው! ሐሳዊ መሲህን ከመካከል ብቅ ማለታቸው አይቀሬ ነው፡፡ በሁሉም መስክ አለን አለን ሲሉ ይገኛሉ፡፡ እንደ ንሥር የነቃ ዐይን ከሌለን ለጮሌና ጨላጣ ብልጠት እንጋለጣለን፡፡ እንዲህ ላሉቱ ሁሉ አንድ ጠንካራ ተረት ያሻቸዋል፡-
‹‹እቺ ጐንበስ ጐንበስ ሣር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነው!››


Monday, 02 March 2020 00:00

የመዝገበ ቃላት ሽያጭ

በክስታኔ ጉራጌ ሕዝብ የልማት ማህበርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባሕሎች አካዴሚ በጋራ የተዘጋጀው የክስታንኛ፣
አማርኛና እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት በሽያጭ ላይ ይገኛል፡፡
ይህ የዛሬውም ሆነ መጪው ትውልድ ከታሪኩና ከባሕሉ ጋር አዛምዶ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ እንዲጠቀምበት ለማስቻልና ቋንቋው
ዘላቂ ሕይወት እንዲኖረው በማሰብ የተዘጋጀው ክስታንኛ-አማርኛ- እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት በርካታ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን መሸጫ
ዋጋው ብር 300.00 ነው፡፡
ልደታ ክ/ከ ከከፍተኛው ፍ/ቤት ፊት ለፊት ኑር
ህንፃ 4ኛ ፎቅ ቢሮ ቁጥር 6 ቢመጡ ያገኙታል፡፡
ስልክ፡- 0118 29 95 36
09 10 29 91 98
09 20 01 82 08
የማህበሩ ጽ/ቤት

Sunday, 08 March 2020 00:00

የፀሐፍት ጥግ

 • ‹‹…የብሔር ፖለቲካ የተፈጠረውና እንደ ጎላ ድስት ከስሎ የወጣው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ በተነሳ ቁጥር ዋለልኝ መኮንን ይጠቀሳል:: የዋለልኝ ሀሳብ ጥሩ ቢሆንም አገሪቷ መከፋፈል የጀመረችው እሱ ባመጣው ሀሳብ ነው፡፡…››
• ‹‹…ገዳም የገባ መነኩሴ የሚፈተነውም በዝምታ ወቅት ነው፡፡ ገዳም የገባ መናኝ መሆኑ የሚረጋገጠው አርምሞ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁሉን
አውቆ ንቆ ሲተው ነው፡፡ አርምሞ ላይ ለመድረስም ፈታኝ ነው፡፡ ለዚህም ድንጋይ እስከ መንከስ የደረሱ መናኞች አሉ፡፡…››
• ‹‹…የዕውቀት መሰረት በመማር ብቻ አይመጣም፡፡ ብዙ ያልተማሩ ምሁሮች አሏት - አገራችን፡፡ አድዋ የዘመቱትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዛ በፊትም ለሙሴ
አመራር ያስተማረውን የምድያሙን ካህን ዮቶርን መጥቀስ ይቻላል፡፡…››
• ‹‹…ወንጀልን ስትፈፅመው አትፀፀትም:: ከዛ በኋላ ግን ወንጀሉን እንዴት ልደብቀው ትላለህ… ነፃ ሆነህ መኖር ትፈልጋለህ! ወንጀሉን የሚያጣራ አካል እንዳይመጣ ትፀልያለህ! ሆኖም ለማን እንደምትፀልይ አይገባህም፡፡ ፈጣሪን ትረግመዋለህ፡፡…››
• ‹‹…በተሰበክነው ስብከት መሰረት እኛ በህብረት መሥራት አንችልም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ግን እንችላለን፡፡ ሩጫ እንችላለን:: እግር ኳስ ግን አንችልም፡፡ ሜዳ
ታጥቶ አይደለም፡፡ በህብረት መስራት ስለማንችል ነው፡፡ ብሔር ሆነን የሰራነው አንድም ቅርስ የለም፡፡ ብሔር ሆነን ለእኛ የማይታገሉ መሪዎች እንመርጣለን እንጂ ምን እንደሰሩ አንጠይቅም፡፡ ብንጠይቅም አገሪቷ ደሃ ናት ይሉናል፡፡…››
(ከደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ‹‹ደህንነቱ›› መጽሐፍ የተወሰደ

    የቀጠሮን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም፡፡
ማለቅ ያለበት ከሆነ ሥራህን በዕለቱ ጨርስ፡፡
ጊዜን ያከበረ አሉ፤ ራሱ የተከበረ ይሆናል፡፡ ያላከበሩት ጊዜ በጭንቅ ወቅት እንዲደርስልህ መጣራት አግባብ አይደለም:: ያላከበርከው ጊዜ፣ የውርደት ጉድጓድዎችን ይቆፍርልሃል እንጂ ከማጥ አያወጣህም፡፡
ማደር የሌለበት ሥራህን ለሚቀጥለው ቀን አለማስተላለፍ ቀንህን ብሩህ ያደርገዋል:: የተደላደለ ሕይወት እንድትመራ ጥርጊያ መንገድ ያመቻችልሃል፡፡
አንዳንዶች “MISTER TODAY!” ይሉኛል፡፡ “MISTER TODAY”/ሚስተር ቱዴይ መባል መባረክ ነው፡፡ ሣሙኤል የዛሬ ሰው ነው እንደማለት ነው፡፡ መጠርያው በትክክልም እኔን ይገልጸኛል ብዬ አምናለሁ:: ሰው የሚሳካለት የጊዜ ባርያ ሲሆን ነው፡፡
ጠዋ፣ ጐኅ ሲቀድ እነሳለሁ፡፡ “ጂም” እሠራለሁ፡፡ ሰውነቴን ሳላፍታታ፣ አዕምሮዬን ሳላዝናና ወደ ሥራ ገበታዬ አልሰማራም፡፡ ከጥዋቱ ሁለት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ቢሮዬ ነኝ፡፡ ምሳ ለመብላት ቤት እሄዳለሁ:: እመለሳለሁ፡፡ ባለ ጉዳይ እቀጥራለሁ:: የቀደመ ቀጠሮ ካለኝ አስተናግዳለሁ:: አመሻሹን ማርዮት ሆቴል ነኝ፡፡ ለየት ያሉ ጉዳዮችን የምጨርሰው እዚህ ሆቴል፣ የቀጠርኳቸውን ሰዎች እራት እየጋበዝኩ ነው፡፡
የምንቀሳቀሰው በአጀንዳ ነው፡፡ ቀጠሮ ካለኝ አምስት ደቂቃ ባላረፍድ ደስ ይለኛል:: የዛሬ ሰው ነኝ፡፡ መሥራት እየቻልኩ ለነገ የማሳድረው ነገር የለኝም፡፡ የዛሬን ዛሬ፡፡ ከዛሬ ትናንት ይሻላል፡፡
ትናንት የሠሩት ሥራ ከብዙ ነገር ይጠብቅዎታል፡፡ ዛሬ ነገ ሲሉ፣ ሊሠሩት ካሰቡት ጋር የተያያዘ ሌላ አዋጅ ወጥቶ ዕቅድዎ ሊሰናከል ይችላል፡፡
የሰን ሻይን ኮንስትራክሽን ሠራተኛ ሁሉ ጉዳይ ይዞ እፊቴ ሲቀርብ ወይም ፈልጌው ሲመጣ አጀንዳ ይዞ ነው፡፡ በየአመቱ፣ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር 1ሺ500 ቅጂ አጀንዳ በሰንሻይን ድርጅት ስም ይታተማል:: አጀንዳ እወዳለሁ፡፡ መቼ ከሀገር ውጭ እንደምሄድ ቀድሜ አውቃለሁ፡፡ አንድ ሰው ጊዜዬን ከሚያበላሽብኝ ገንዘቤን ወስዶ ሳይመልስልኝ ቢቀር ይሻለኛል፡፡
ስለ ጊዜ በቂ ግንዛቤ ሲኖርህ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለህ፣ ነገ ሥራህ ምን ሊገጥመው እንደሚችል መረዳት ትችላለህ፡፡
ማለቅ ያለበት ከሆነ ሥራዎትን በዕለቱ መጨረስ፡፡
ማደር የሌለበት ሥራዎትን ለሚቀጥለው ቀንም አለማስተላለፍዎ ቀንዎን ብሩህ ያደርገዋል፡፡ የተደላደለ ሕይወት እንዲመሩ ጥርጊያ መንገድ ያመቻችልዎታል፡፡ “MISTER TODAY!” (ሚስተር ቱዴይ) መባልዎ መባረክ ነው፡፡
በተቻለ መጠን በደንብ የምታውቀውን ብቻ ሥራ፡፡
ሁላችንም ያለን የተመጠነ ዕድሜና የተመረጠ የሥራ ዓይነት ነው፡፡ ያየነው ሁሉ ሊያምረን አይገባም፡፡ የማናውቀውን ስንሞክር ሕይወታችን ግራ በመጋባት የተሞላ ይሆናል፡፡ በአጭሩ ይህን በማድረግህ ከብት ባልዋለበት ኩበት እንዳትለቅም ያደርግሃል፡፡
እኔ በበኩሌ የማውቀው ነገር ላይ ነው፣ ልቤን ማሳረፍ፣ ጊዜዬን ማሳለፍ የምፈልገው:: እርሻ ላይ ቢጥሉኝ የትኛው ስንዴ፣ የትኛው የገብስ አዝመራ እንደሆነ ስለማላውቅ፣ ሌላው ገብቶ አተረፈበት፣ ወይም ስም አገኘበት ብዬ ዘልዬ ለመግባት አልፈልግም፡፡
በማውቀው ስራ ላይ ካተኮርኩ ሌላው ቢቀር ራሴን አልጐዳም፡፡ ሆስፒታል ብከፍት የዶክተሮቹ ታዛዥ ነው የምሆነው:: ቋንቋውን ሙያውን አላውቀውም፡፡ የእኔ ቁርኝት ከመሀንዲሶች ጋር ነው፡፡ የሚሉት ይገባኛል፡፡ የምለው ይገባቸዋል፡፡ ስለዚህ እንተጋገዛለን፡፡ ተልዕኮአችንን እናውቀዋለን:: አዲሱን ነገር እስክለምደው ድረስ ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ያን ለመልመድ የሚፈጅብኝን ጊዜ ደግሞ እኔ አጥብቄ እፈልገዋለሁ፡፡
ያ ማለት ደግሞ አዲስ የቢዝነስ አማራጮችን ለመሞከር እፈራለሁ ማለቴ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ወደ ሆቴል ሙያ ስገባ ተፈትኜ ነበር፡፡ እየዋልኩ እያደርኩ ግን የሥራውን ሂደት ተረዳሁት፡፡ የሆነ ጊዜ፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ዘንድ ተጋብዘን ቀርበን ነበር:: የቀረብንበት ምክንያት በሪል ስቴት ሥራ ላይ ተሰማርተን የነበርን ኢትዮጵያውያን ክስና ወቀሳ ቀርቦብን ነው፡፡ አቶ መለስ፣ በንግግራቸው እኛን ሸንቆጥ አደረጉን፡፡ እኛም፤ “ምንድነው ያጠፋነው?” አልናቸው::
እሳቸውም፤ “ያጠፋችሁት ነገር የለም፤ የእናንተ ሥራ ማለትም የሪል ስቴት ሥራ “ፋስት መኒ” ነው፡፡ አሁን ተዘርቶ፣ አሁን በቅሎ፣ አሁኑኑ ውጤቱ የሚገኝ፡፡” አሉን፡፡
“ታዲያ ሰርቶ ማደር ወንጀል ነው ወይ?”
“እኛ የምንፈልገው ብዙ ሠራተኞችን የሚያሳትፍና የሥራ አጡን ቁጥር የሚቀንስልን ነው፤ ለምን ግብርና፣ ወይም ኢንዱስትሪ ላይ አትገቡም? ወደዚህ ሙያ እንድትገቡ ደግመን ደጋግመን ነገርናችሁ፤ ዕድሉን አመቻቸንላችሁ፤ በቁጣም በማባበልም ሞከርናችሁ፤ እናንተ ግን ልትሰሙን አልቻላችሁም” አሉን፡፡
እኔም ነገርኳቸው፤ “ክቡርነትዎ! እኔን ወደ ሆነ ማሳ ወስደው የትኛው ስንዴ፣ የትኛው ጤፍ ነው? ብለው ቢጠይቁኝ ለመመለስ የምቸገር ሰው ነኝ:: እድገቴም ብቃቴም ኮንስትራክሽን ላይ የተመሰረተ ነው እንጂ ለግብርና ባዶ ነኝ፡፡ ወድጄው ፈቅጄው ካልተሰማራሁበት ደግሞ አትራፊ አልሆንም፡፡ ለዜጋው የረባ ለውጥ አላመጣም፡፡ አስተዳደጌ ነው፡፡ ከየት አመጣዋለሁ? ለአንዳንዱ በግብርና ላይ መሰማራት እጅግ በጣም ቀላል ነው:: እኔ ግን አይሆንልኝም፡፡ ኢንዱስትሪው የሕይወቴ መሰረት ነው፡፡ ሀገሬን መለወጥ፣ ሙያዬን ማሳደግ የተሰማራሁበትን መስክ ማዘመን በምፈልግበት ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ሞራል የሚነካ ነገር መሰማት ቅር ያሰኘኛል:: እንዴት አርባ ሃምሳ ባለሐብት በአንድ ጊዜ ወደዚህ ሙያ እንዲገባ ግዴታ ይጣልበታል? ለሚፈልጉት ግን መንገድ ይከፈትላቸው፤ መንገድ ይዘርግላቸው” አልኳቸው፡፡
ከዚያ በኋላ በዚህ ጉዳይ ዳግም አልተሰባሰብንም፡፡
በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የሚደውልልዎት ሰው ስለሚኖር በተቻለ መጠን ሁሉንም ስልክ ለማንሳት መሞከር፡፡
አንዷ ስልክ ምን ይዛ እንደመጣች ወይም ልትመጣ እንዳሰበች የምታውቀው ነገር ስለሌለ፣ ስልክ ለመመለስ መሞከር ተገቢ ነው፡፡
5- የሚሰሩትን ሥራ በተቻለ መጠን ጥዋት
    በመግባት ይፈጽሙ፡፡
ይህን በማድረግዎ፣ ቀኑ አለአግባብ እንዳይባክን ያግዝዎታል፡፡ በነቃና በተደራጀ አመለካከት ሥራዎትን እንዲሰሩ ያበረታታዎታል፡፡
የሚሰሩት ሥራ ከአቅም በላይ እንዳይሆን ይሞክሩ፡፡
በሚችሉት አቅም ብቻ በመሥራት በወቅቱ ለመጨረስ መሞከር ተገቢ ነው፡፡
የሚያደርጉት የኢንቨስትመንት ሥራ በአቅም የተደገፈ ይሁን፡፡
በቶሎ የሚመለስ ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ አቅምዎትን ከደገፉ በኋላ ለረጅም ጊዜ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ለቤተሰብና ለሀገር ስለሚጠቅም፣ ለመስራት ይሞክሩ፡፡
8- እየኖሩ ለመሞት ይሞክሩ!
“ለወደፊት ማለትም አቅሜ ከጠነከረ በኋላ ነው የምደሰተው፣ ወይም የምዝናናው” ብለው ለራስዎ ደስታ የቀጠሮ ጊዜ አያስረዝሙ፡፡ ራስን በመጉዳትና ስሜትን አለቅጥ በመጨቆን ነገን ማፍካት አይቻልም:: እናም ለራስዎ ጊዜ ሰጥተው፣ ለእናቴ ልጅ ነኝ ለማለት ሞክሩ፡፡
በተቻለ መጠን ለሚሠሩ የድርጅቱ ባልደረቦች ሃላፊነት እየሰጡ እንዲሠሩ ይምረጡ፡፡
ሁሉም ሥራ በራሴ ብቻ ነው የሚከናወነው ብለው አይመኑ፡፡ በአንድ እጅ አይጨበጨብም፡፡ እርስዎ የድርጅቱ አንድ እጅ ነዎት፤ ሠራተኞቹ ደግሞ ሌላኛው እጅ፡፡ ቤተሰብዎም በሥራዎና በውጥንዎ እንዲካተት ያድርጉ፡፡
10- እንደገና ሞክር፣ አሁንም እንድገና ሞክር!
በአንድ ወቅት የግል ሄሊኮፕተር ለመግዛት እንቅስቃሴ ውስጥ ገባሁ:: ይህን የሰሙ ብዙዎች ተደናገጡ፡፡ የድንጋጤያቸው ምንጭ ይገባኛል፡፡ እኛ አገር የግል ሄሊኮፕተር መግዛት የተለመደ አይደለም፡፡ እኛ አገር ባይለመድም በውጭ አገር ግን አንድ ባለሐብት ጊዜውንና ምቾቱን ለመጠበቅ ሲል የግል ሄሊኮፕተርና ጄት ይኖረዋል፡፡ ይህን የምለው ስለ አውሮፓና አሜሪካ ባለሐብቶች አይደለም፡፡ ደቡብ ሱዳን ብትሄድ ባለሐብቱ ሠፋፊ እርሻዎቹን የሚያስጐበኝህ በግል ሄሊኮፕተር እያዟዟረ ነው፡፡
እናም፣ እኔም እንደሚያስፈልገኝ አሰብኩ:: ቢኖረኝ ጊዜዬን እጅጉን ይቆጥብልኛል፡፡ ጠዋት ተነስቼ መኪና ይዤ ሰሜን ወሎ የሚገኘውን የመንገድ ፕሮጀክት ለመከታተል ብነሳ፣ መንገዱ ብቻ ሦስት ቀን ይፈጅብኛል፡፡ በአንድ ቀን አጠናቅቄ መመለስ የምችለውን ነገር ሦስት ቀን ከወሰደብኝ፣ ይህን ለማቅለል የግል ሄሊኮፕተር ብገዛ ምንም ማለት አይደለም:: ዛሬ የአንድ የግል ሄሊኮፕተር ዋጋ ዘመናዊ ከሚባል መኪና ጋር ተቀራራቢ ነው፡፡
ሆኖም፣ ለመግዛት ወሰንን፡፡ ሄሊኮፕተር ማሳረፊያ ዱከም ቦታ ከወሰድን በኋላ፣ ደብረዘይት ሌላ ማሳረፊያ ስላለ ተቀራራቢ ቦታ መሆን የለበትም አሉን፡፡ አሁንም ግን አማራጭ መንገዶችን እየፈለግን ነው:: እንሞክራለን፤ እንደሚሳካልንም ጥርጣሬ የለንም፡፡   
(ከሣሙኤል ታፈሰ “ተግባር፤ እኔና ሰንሻይን ከትናንት እስከ ዛሬ” መጽሐፍ፤ የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለቤትና ፕሬዚዳንት)

    የማስታወቂያ ሥራ ፈር ቀዳጁና የአንበሳ ማስታወቂያ መሥራችና ባለቤት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ባደረባቸው ህመም  በቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው፣ ባለፈው የካቲት-2012 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ሥነሥርዓታቸውም፣ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና የቱሪዝምና ባህል ሚኒስትሯ ዶ/ር ሂሩት ካሣሁን እንዲሁም አንጋፋና ዝነኛ አርቲስቶች፣ የማስታወቂያ ባለሙያዎችና ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት በቅዱስ ሥላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በክብር ተፈጽሟል፡፡  
ጋሽ ውብሸት በጥቁር ካባቸው ተውበው፣ በአገራዊ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባልነት፣ በቻምበር ኦፍ ኮሜርስ ሃላፊነት እንዲሁም፣ በቀይ መስቀልና ደም ባንክ አምባሳደርነት አገልግለዋል።
ነፍስ ይማር!
ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጆቻቸው መጽናናትን እንመኛለን፡፡
***
“ከመንዝ እስከ አዲስ አበባ”
የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ፈር ቀዳጅ መሆናቸው የሚነገርላቸው ጋሽ ውብሸት ወርቃለማሁ፤ ለእንግድነት ከተጠሩ በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት የተዋበ ነጭ ልብስ ያዘወትራሉ፤ ከዚያም አጠር ካለው ቁመናቸው ጋር የሚሄድ ካባ በላዩ ላይ ይደርቡበታል።
በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የማስታወቂያ ስራዎች የእርሳቸው አሻራ አርፎባቸዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ማስታወቂያዎችን ሰርተዋል። ለዛ ባለውና በሚያስገመግመው ድምጻቸው ይታወቃሉ። ለወጣት የማስታወቂያ ባለሙያዎች አርአያ በመሆናቸው ብዙዎችም ያከብሯቸዋል። በቀብር ሥነሥርዓታቸው ላይ የተገኙ የአገሪቱ ታዋቂ የማስታወቂያ ባለሙያዎችም ይህንኑ ነው በአንደበታቸው የመሰከሩት፡፡
“ከመንዝ እስከ አዲስ አበባ”
አቶ ውብሸት ወርቅአለማሁ የተወለዱት መንዝ በቀድሞው ይፋት አውራጃ፣ ማፉድ ገበያ፣ አንቃውሃ በተባለ አካባቢ ነው። የትውልድ ዘመኑን የሚያስታውሱት ከታሪክ ግጥጥሞሽ ጋር በማያያዝ እንጂ በስንት ዓመተ ምህረት እንደሆነ በውል አያስታውሱትም።  በወርሃ መስከረም ጃንሆይ ድል አድርገው ከገቡ በኋላ እንደተወለዱ ከእናታቸው መስማታቸውን ይገልጻሉ፡፡ የግለ ታሪክ መፅሐፋቸው ደግሞ በ1934 ዓ.ም እንደተወለዱ ይናገራል።
አባታቸው አለቃ ወርቃለማሁ ወልደየሱስ፣ ወንድ ከወለዱ እረኛ ሆኖ ያገለግለኛል ቢሉም፤ ሳይጠቀሙባቸው ለስራ ወደ አርሲ ይሄዳሉ። ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ወይም ሰባተኛ ልጅ የሆኑት አቶ ውብሸት በተወለዱ በዓመታቸው አባታቸውን በሞት ይነጠቃሉ። በዚህም በእናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ አበሩና በአያታቸው ወይዘሮ ዘነበች እጅ አደጉ፡፡ እናታቸው ወይዘሮ ተናኜወርቅ፣ ልጃቸውን በቤት ውስጥ መምህር ቀጥረው ፊደል እንዲቆጥሩ አደረጓቸው። መምህር ሸዋለማ የተባሉት የቤተክህነት መምህር ደግሞ ቅስና፣ ዳዊት መድገም እንዲሁም ዜማን አስተማሯቸው።
የትምህርት አቀባበላቸው ጥሩ ነበርና እድሜያቸው አስር ሳይደርስ ማፉድ ደብረኃይል ቅዱስ ሚካኤል ደብር በዲቁና ማገልገል ጀመሩ። ዲያቆን እያሉ ግን አንድ ቀን በተወለዱበት አካባቢ ማፉድ ገበያ ያለው ክንውን ቀልባቸውን ይስበዋል። የገበያው ትርምስ፣ የሸማችና ሻጭ አለመገናኘት በአጠቃላይ የቀያቸው ንግድ ቀልባቸውን ቢስበው አንድ መላ ይዘይዳሉ። ረጅም ሰው በረዳትነት በማቆም ገዢና ሻጩን እያገናኙ ገንዘብ እንደሚያገኙ በማሰብ ስራውን ጀመሩት። አብሯቸው የሚሰራው ደግሞ ሁለት ሜትር ከአስር ሳንቲ ሜትር ርዝመት ያለው ቁመተ መለሎ ሰው ነበር። በማፉድ ገበያ አንድ ጠዋት፣ ረጅሙ ሰው ትከሻ ላይ ወጥተው «ይህን ያህል ሰንጋ፣ ይህን ያህል ጤፍ፣ ሁሉም በየአይነቱ ገብቷል» በማለት የመጀመሪያውን ማስታወቂያ በአየር ላይ አዋሉ። በማስታወቂያው የተሳበው ሸማች፣ የትነው ያለው እያለ፣ ከሻጭ ጋር እየተገናኘ ግብይቱ ሲጧጧፍ ዋለ። መጠነኛ ገቢም ከሻጮች በመቀበል፣ የዕለት የማስተዋወቅ ውሏቸውን አጠናከሩት።
አያታቸውና አንዳንድ የቤተሰብ አባላት ግን «እንዴት የጨዋ ልጅ በገበያ መሃል ይጮሃል» እያሉ የማስታወቂያ ስራቸውን እንዲተዉ መገሰፃቸው አልቀረም። እርሳቸው ግን ስራውን ከማቆም ይልቅ ይበልጥ ገፉበት። በድቁና ስራቸው በዓመት አምስት ማርትሬዛ የሚያገኙት አቶ ውብሸት፤ በማፉድ ገበያ የሆሳዕና ዕለት በሰሩት የማስታወቂያ ስራ ብቻ ከአጋራቸው ጋር አስር ማርትሬዛ ማግኘታቸውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ሲሸከሟቸው ለሚውሉት ቁመተ መለሎ የተወሰነውን ማርትሬዛ በመስጠታቸውና እርሳቸውም እኩል መካፈል አለብኝ በማለታቸው ትብብራቸው መፍረሱን ያስታውሳሉ።
ግን ለበጎ ነበር፡፡ ሰው ትክሻ ላይ ወጥተው ማስታወቂያ ከመስራት ይልቅ ወደ ጽሁፍ ማስታወቂያ እንዲሸጋገሩ አድርጓቸዋል። አጤፋሪስ እና የከሰል ድቃቂ አቀላቅለው ለሶስት ቀን በማቡካት ያገኙትን ቀለም የፍየል ቆዳ አስወጥረው መፃፍ ጀመሩ። በገበያው በሚገኝ ትልቅ ዛፍ ላይ ቆዳውን በአጋም እሾህ ይወጥሩትና የገባውን እህልና ሰንጋ ብዛት እየጻፉ ማስተዋወቁንም ተያያዙት።
ቆዳው በየሳምቱ ቅዳሜ ዕለት ይታጠብና ሌላ ማስታወቂያ ይጻፍበታል። እንዲህ እንዲህ እያሉ የማስታወቂያ ስራ ታዋቂነታቸውን በመንዝና ይፋት አካባቢዎች አሰፉት። ከዚያ ከገበያ በኋላ ለእንጨት መጫኛ ከባድ መኪና አስተዋዋቂ ሆነው መስራት ጀመሩ። መኪናው እንጨት ከጫነ በኋላ ወደ አዲስ አበባና ወደተለያዩ ቦታዎች የሚሄዱ ተሳፋሪዎችን ይጭናል። አቶ ውብሸት ደግሞ «መኪናው ለአደጋ የማያጋልጥ ጠንካራ ነው፤ አይገለበጥም ተሳፈሩበት» እያሉ ያስተዋውቃሉ። ይህ ስራቸውም ጋቢና ተቀምጠው በነጻ የፈለጉበት ቦታ ደርሰው እንዲመለሱ ረድቷቸዋል። አንድ ቀን ግን ገበያው የደራለት ሾፌር፣ አቶ ውብሸትን ከላይ ከህዝቡ ጋር ለመጫን ይወስናል። በድርጊቱ የተበሳጩት አቶ ውብሸትም ያኮርፉና የባለመኪናውን ስም እየጠሩ «የክብረት መኪና አይረባም፣ ይገለበጣል» በማለት አሉታዊ ማስታወቂያ በመስራት ተጠቃሚ እንዲያጣ እንዳደረጉት አይረሱትም። ከዚያ የመማር ፍላጎት ያደረባቸው አቶ ውበሸት፤ የማስታወቂያ ስራቸውን ትተው አዲስ አበባ ታላቅ ወንድማቸው ዘንድ ለትምህርት መጡ።
አዲስ አበባ ከተማ ተስፋ ኮከብ የተባለ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን የጀመሩት አቶ ውብሸት፤ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን፣ ሙዚቃና ቴአትር መማር ጀመሩ። በወቅቱ ፈረንሳይ አገር ተምረው የመጡት የቴአትር ባለሙያው አቶ ማቴዎስ በቀለ ነበሩ የሚያስተምሯቸው። እናም አንድ ተውኔት ተዘጋጅቶ የሀብታም ልጅ ገጸባህሪን ተላብሰው እንዲጫወቱ ተመረጡ። በወቅቱ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሃረርጌ የሀገር ፍቅር ቴአትር ስላቋቋመ አቶ ውብሸት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ሳይጨርሱ ወደ ድሬዳዋ እንዲሄዱ ተደረገ።
በሁለት ዓመት የሃረርጌ ሀገር ፍቅር ቆይታቸው ጭሮ፣ ገለምሶ፣ ኦጋዴንና ቀብሪደሃር የመሳሰሉ አካባቢዎችን በመዘዋወር በርካታ ቴአትሮች ላይ ሰሩ። ከቴአትር ስራቸው በተጓዳኝ መድረክ መሪም ነበሩ። በመድረክ ላይ ቀልድና እያዋዙ በሚያቀርቡት መልዕክት ታዳሚዎቹን ያስደምሙ ነበር። በዚህም ብዙዎች መድረክ በመምራት ሙያ እንዲገፉበት ያበረታቷቸዋል። የሃረርጌው ሀገር ፍቅር ከሁለት ዓመት በኋላ ሲፈርስ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ዳግም ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተቀላቀሉ።
በዚህ ቴአትር ቤት በተለያዩ ቴአትሮች ላይ በመሳተፍ ከወጋየሁ ንጋቱና አንጋፋ ተዋናዮች ጋር የመስራት እድልን አግኝተዋል። በቴአትር ክፍሉም በተዋናይነት፣ በደራሲነትና በመድረክ አስተዋዋቂነት ሰርተዋል። በወቅቱ ግን አጎታቸው “አዝማሪ ቤት ስራ ገብተሃል” ብለው አቶ ውብሸትን እስከ ማሳሰር ደርሰው እንደነበር ያስታውሳሉ። በሀገር ፍቅር መድረኮች የአፄ ኃይለስላሴን ገጸባህሪ ወክለው በመተወን ከንጉሱ ጭምር አድናቆትን ያተረፉት አቶ ውብሸት፤ ቴአትሩን በሚሰሩበት ወቅት መልካቸውም ሆነ ሁለመናቸው ንጉሱን ስለሚመስል ታዳሚዎች ልክ እንደ ንጉሱ እጅ እየነሱ ሰላምታ ይሰጧቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ከሀገር ውጭም ቢሆን መድረክ የሚመሩበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር። የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ቴአትር ቤትና በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤቶች በሁለት ቡድኖች ሆኖ ቻይና እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ሲሄዱ እርሳቸውም ተጓዥ ነበሩ። በዚህም ለሁለት ወራት ያክል በየመድረኮቹ በመምራት ብቃታቸውን አስመስክረዋል። በዚያም ችሎታቸውን ይበልጥ ለማዳበር ሞስኮና ቻይና የቴአትር ትምህርት ለመከታተል ፍላጎት አደረባቸው። ሀገራቱ ኮሚኒስት በመሆናቸው ግን ውጣ ውረዱ ይበዛብኛል በሚል ስጋት ዕቅዳቸውን ሰርዘው ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ከስራቸው በኋላ ማታ ማታ መደበኛ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት አቶ ውብሸት፤ በስራ ቦታቸው ላይ ደረጃቸውን እያሳደጉ በቴአትር ቤቱ እስከ ምክትል ዳይሬክተር ደረጃ ደርሰው እንደነበር ይናገራሉ። ቴአትር ቤቱን ለቀው ሲወጡም በብሔራዊ ሎተሪ ድርጅት የማስታወቂያ ባለሙያነት ተቀጠሩ። ከቴአትር ሙያቸው ጋር በተያያዘ «እኔና ሰባት ገረዶቼ፣ ማን መክቶት፣ 3 ለ1፣ የጥንቆላው መዘዝ፣ ውለታ በጥፊ፣ ሁለተኛ ምዕራፍ እና ባሻህ ዘመኑ» የተባሉ ድርሰቶችን አዘጋጅተዋል። ሰባት የቴሌቪዥንና ሁለት የመድረክ ስራዎችንም አቅርበዋል። «የክትነሽ» የሚል ፊልም ደግሞ በአሜሪካን ስቱዲዮ አቀናብረው ለእይታ አብቅተዋል።
የሙሉ ጊዜ ማስታወቂያ ሥራ
ብሔራዊ ሎተሪ ትኬቶቹን የሚያሻሽጥለትና ወደተሻለ ትርፍ የሚያመራው ሁነኛ የማስታወቂያ ሰው ይፈልግ ነበርና በመድረክ ስራቸው የሚታወቁትን አቶ ውብሸት ወርቃለማሁን ያገኛል። የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅትን ኢ ቦኑሜር የተባሉ ስራ አስኪያጅ፣ አቶ ውብሸትን የማስታወቂያ ክፍል ሹም አድርገው ይሾሟቸዋል። በወቅቱ ዜጎች በሬዲዮ የሚነገረውን የሎተሪ ዕድል አላምን ብለው ነበርና፣ አቶ ውብሸት ሎተሪ የደረሳቸውን ሰዎች በእማኝነት ያቀርቡ ነበር። «ትከብራለህ ሎተሪ ግዛ!» እያሉም በራዲዮንና በድምጽ ማጉያ በከተሞች እየተዘዋወሩ ቅስቀሳ ያሰሙ ነበር።
በከተማዋ ለማስታወቂያ ስራ ሲዞሩ ግን አንድ ዘዴ ይመጣላቸዋል። ወዲያው ሰበታ ሄደው በ25 ብር አህያ ከገዙ በኋላ የብሄራዊ ሎተሪ ድርጅት ቀለብና ማረፊያዋን እንዲያዘጋጅ ያደርጋሉ። ከዚያም አህያዋ ላይ ብር በማዳበሪያ አድርገው ጠመንጃ በያዙ ጠባቂዎች እንድትታጀብ ያዛሉ። ማዳበሪያው ለይምሰል ከላይ የተወሰኑ የብር ኖቶች ጣል ይደረግበት እንጂ አብዛኛው በጭድ የተሞላ ነበር። አህያዋንም በከተማ እያዞሩ «ብሩ መጥቶልሃል ትኬትህን ቁረጥ» እያሉ የሎተሪ ማስታወቂያቸውን አጧጧፉት። አህያዋ በባቡር እስከ ድሬዳዋ፤ ጅማ ድረስ በመኪና ተጉዛ ማስታወቂያውን እንድትሰራ ያደርጉ ነበር።
በሌላ በኩል፤ በማስታወቂያ ስራቸው በእነ ምኒልክ ወስናቸውና ታዋቂ ሙዚቀኞች ጭምር የሚታጀብ ስለነበር በርካታ የሙዚቃና የንግግር እንዲሁም የማስታወቂያ ሥራዎችን በሬዲዮ እንዲያዘጋጁ እድል ተፈጥሮላቸው ነበር። በጊዜው ደመወዛቸው 400 ብር ሲሆን፤ ሎተሪ ድርጅቱም በእርሳቸው ዘመን ትርፋማነቱ ጨምሮ እንደነበር ያስታውሳሉ። ከሶስት ዓመት የሎተሪ አስተዋዋቂነት ሙያ በኋላ ደግሞ በተሻለ ደመወዝ ወደ ፊሊፕስ ኩባንያ ማስታወቂያ ባለሙያነት ተሸጋግረዋል።
ፊሊፕስ ኩባንያ ውስጥ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን አስተዋውቀዋል፡፡ ሥራቸው የተቃና እንዲሆን ኩባንያው መኪና ሰጥቷቸዋል። ለማስተዋወቅ ስራቸው ለየት ያሉ ስራዎችን ይጠቀሙ የነበሩት አቶ ውብሸት፤ ለአብነት ፊሊፕስ ኩባንያ ቸርቸል ጎዳና የመንገድ መብራቶችን ግራና ቀኝ ተክሎ ስለነበር እርሳቸው ሌሊት ጭምር መብራቱ ስር ቆመው ጋዜጣ ያነባሉ። ይህም የመብራቱን ኃይል ለማስተዋወቅ አስበው ያደረጉት ነበር። ኩባንያው ገበያው እየደራለት ሲመጣ፣ አቶ ውብሸትን ለተጨማሪ ማስታወቂያ ትምህርት ሆላንድ አገር ላካቸው።
በሆላንድ የሶስት ወራት ቆይታ ስለማስ ታወቂያ ቴክኒኮች፣ ድምጽ ቀረጻና አርት ኦት ተማሩ። ስድስት ዓመታትንም በፊሊፕስ ኩባንያ የራዲዮንና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ማስታወቂያ ሰሩ። ከበርካታ ድርጅቶች ጋር ለመተዋወቅ ቻሉ። ከዚህ በኋላ የራሳቸውን ማስታወቂያ ድርጅት በማቋቋም ከሚወዷቸው እንስሶች መካከል አንዱ የሆነውን አንበሳን መጠሪያ በማድረግ፣ በ1656 ዓ.ም አንበሳ የማስታወቂያ ስራዎች ድርጀትን ከፈቱ። ከአንድ አርመናዊ ወዳጃቸው ያገኙትን ሁለት ሺ ብር እና ከሌላ ሰው አምስት ሺ ብር በመበደር መቅረፀ ድምፅና የተለያዩ መሳሪያዎች ገዝተው፣ ቢሮ ተከራይተው ስራ ጀመሩ።
ፊሊፕስ ኩባንያን ጨምሮ አምስት ድርጅቶችን ይዘው በአንድ ወር ውስጥ 10 ሺ ብር በመስራታቸው ብድራቸውን መለሱ። የማስታወቂያ ድርጅቱ አሁንም ድረስ በስራ ላይ ያለ ሲሆን፤ በስሩም 12 ቋሚ ሰራተኞች ይዟል። 10 በትርፍ ጊዜ የሚሳተፉ ሙያተኞች አሉት። አቶ ውብሸት በማስታወቂያ ድርጅታቸው በአቢሲኒያ ባንክና በመድን ድርጅት ማስታወቂያዎች በይበልጥ ይታወቃሉ፤ ለበርካታ ድርጀቶች ለዘመናት ማስታወቂያዎችን አዘጋጅተዋል። ይሁንና በደርግ ዘመን ይህ ሙያቸው ሊያስገድላቸው እንደነበር አይረሳቸውም። ለዚህ መንስኤውም የሰሩት የበረሮ ማስታወቂያ ነበር።
በራዲዮ «ቢንቢ የት ልትገቢ፣ በረሮ መጥፊያሽ ነው ዘንድሮ» የሚል የነፍሳት ማጥፊያ ማስታወቂያ ሰርተው ነበር። በአየር ላይ ከዋለ በኋላ በመኪናቸው ሜክሲኮ ላይ ሲዘዋወሩ አንድ የደርግ አባል ያስቆማቸዋል። ከዚያም ለጥያቄ እንደሚፈለጉ ይነግራቸዋል፤ ፖሊስ መኮንኖች አካባቢ በሚገኘው የደህንነቶች ቢሮ እንዲሄዱ ያዛቸዋል። ይሁንና ቤቱ በወቅቱ ሰዎች ይገረፉበት የነበረና ጭካኔ የሚፈጸምበት መሆኑን በወሬ ሰምተዋልና መንገድ አሳብረው ወደ ሌላ ቢሮ ይሄዳሉ።
ከብሔራዊ ቤተመንግስት አካባቢ ሲደርሱ ቀድሞ የሚያውቋቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰብሳቢ በኋላም ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፍሰሃ ደስታ ቢሮ ዘው ብለው ገቡ። በማያውቁት ሁኔታ ሰዎች እንደሚያሳድዷቸው አስረዷቸው። የደርግ አባሉ ተከትሏቸው ኖሮ፣ ለአቶ ፍስሃ ደርግን የሚሳደብ ማስታወቂያ ሰርተዋል «ትጠፊያለሽ በረሮ ያለው ደርግን ነው» ብሎ ወነጀላቸው። ክሱ ተቀባይነት ባያገኝም አቶ ፍሰሃ «የማስታወቂያ ጽሁፉ ሳንሱር እየተደረገ ይለፍ» የሚል ትዕዛዝ ሰጥተው ያሰናብቷቸዋል። የተባለው ቢሮ ቢሄዱ ኖሮ ሊፈጠር የሚችለውን መከራ ሲያስቡ ሁሌም ይዘገንናቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ --
(ከጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን ገጽ የተወሰደ)

Saturday, 07 March 2020 12:59

የስኬት ጥግ

 • ሕይወትህ በዕድል የተሻለ አይሆንም፤ የተሻለ የሚሆነው በለውጥ ነው፡፡
   ጂም ሮህን
 • ስኬታማ ሰው ባየህ ቁጥር የምታየው የአደባባይ ሞገሶቹን ነው፤ እዚያ ለመድረስ የተከፈለውን የግል መስዋዕትነት አይደለም፡፡
  ቫይባህቭ ሻህ
• ሁልጊዜ አስታውስ፤ ትኩረትህ እውነታውን ይወስነዋል፡፡
  ጆርጅ ሉካስ
• ከአሉታዊ ሰዎች ራቅ፤ ለእያንዳንዱ መፍትሄ ችግር አያጡም፡፡
  አልበርት አንስታይን
• አመለካከት ምርጫ ነው፡፡ ደስተኝነት ምርጫ ነው፡፡ ተስፈኝነት ምርጫ ነው፡፡ ደግነት ምርጫ ነው፡፡ ልግስና ምርጫ ነው፡፡ አክብሮት ምርጫ ነው፡፡
ምንም አይነት ምርጫ ብታደርግ አንተን ይፈጥርሃል፡፡ ስለዚህ ምርጫህን በብልህነት አድርግ፡፡
  ዋልት ዊትማን
• በሕይወት ውስጥ ለማሸነፍ፡-
• 1. ተግተህ ሥራ
• 2. ምሬትን ቀንስ
• 3. ብዙ አድምጥ
• 4. ሞክር፣ ተማር፣ እደግ
• 5. ሰዎች እንደማይቻል እንዲነግሩህ አትፍቀድላቸው
• 6. ሰበብ አትደርድር
• አዎንታዊ አመለካከት መገንባት፣ በራስህ ከመተማመን ይጀምራል፡፡
  ሮጀር ፍሪትዝ
• አዎንታዊ ተግባር ለማከናወን፣ አዎንታዊ ራዕይ መቅረፅ አለብን፡፡
  ዳላይ ላማ
• በእያንዳንዱ ቀን 1 ሺ 440 ደቂቃዎች አሉ፡፡ ይሄ ማለት በየዕለቱ አዎንታዊ ተፅዕኖ የምናሳድርበት 1 ሺ 440 ዕድሎች አሉን ማለት ነው፡፡
  ሌስ ብራውን
• አመለካከት ትልቅ ልዩነት የሚፈጥር ትንሽ ነገር ነው፡፡
  ዊንስተን ቸርቺል

Saturday, 07 March 2020 12:59

የልጆች ጥግ

   እጃችሁን በሳሙናና በውሃ ታጠቡ!

          ውድ ልጆች፡- ሁልጊዜም ሰውነታችሁን መታጠባችሁንና ንፁህ ልብስ መልበሳችሁን አረጋግጡ፡፡ ጥፍራችሁ ውስጥ የተሰገሰጉ ቆሻሻዎችንም አስወግዱ፡፡ ጥፍራችሁን መቁረጥም አትዘንጉ፡፡ ወደ ውጭ ከመውጣታችሁ በፊት ደግሞ የለበሳችሁትን በጥንቃቄ ተመልከቱ፡፡ ፍፁም ንፁህ መሆኑን እርግጠኛ ሁኑ፡፡ ንፁህ ካልሲም አድርጉ፡፡ ካልሲያችሁ መጥፎ ጠረን ሊኖረው አይገባም፡፡ የለባችሁም፡፡ ከቤታችሁ ወጥታችሁ ስትሄዱ ከተለያዩ ሰዎች ጋር ትገናኛላችሁ፡፡ በታክሲ ላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ቲያትር ቤትም ከሰው ጋር ልትቀመጡ ትችላላችሁ፡፡ ስለዚህ ጽድት ጥንቅቅ ማለት አለባችሁ፡፡ ለነገሩ ንፅህና የሚያስፈልገው ሁልጊዜ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እጃችሁን በሁሌም በሳሙናና ውሃ ሙልጭ አድርጋችሁ መታጠብ ይገባችኋል ከበሽታ መከላከያ ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ እደጉ! እደጉ! እደጉ!

Saturday, 07 March 2020 12:57

የግጥም ጥግ

የድል በር
ተፅፎ ባይታይም
አቅጣጫ ሚጠቁም ጉልህ ማሳሰቢያ
ለጀግና መውጪያው ነው የፈሪዎች መግቢያ
***
የላጤ ሐገር
ከአቅመ አዳም ልንገባ ደጁ ተሰልፈን
ሃያ አመት ከሞላን ሃያ አመት አለፈን
***
ለፓርቲዎቻችን
ከአምስት አመት እንቅልፍ ድንገት ስትነሱ
ህዝቡ ቀድሞ ነቅቷል እንዳትቀሰቅሱ
***
ታራሚ
የኔና ያንቺ ነገር ግራ ነው ለዳኛ
አብረን መቆም ሳንችል አብረን የምንተኛ
***
ጊዜ የሰጠው
ጊዜን ጊዜ ሲወልድ ቀን እየበረረ
ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ከሰበረ
ይሄ ሁሉ አለት ለም አፈር ሆኖ እንዳይ
ቅል አርገኝ አምላኬ ለሀገሬ ድንጋይ
ከሙሉቀን ሰ.
፪ሺህ፲፪


      --የታሪክ ሰነዶች እንደሚያስረዱት፣ የመጀመሪያው የግብጽ መሪ ኸዲቭ እስማኤል፣ የዓባይ ተፋሰስ አገራትን ‹‹ውሃ›› ለማስገበር ወረራ አድርጓል፡፡ የግብጽ ጦር ሠራዊት አስቀድሞ ሱዳንን ያዘ፡፡ በ1868 ዓ.ም. ከከረን ወደ ደጋማው የኢትዮጵያ ክፍል ተመመ:: የኢትዮጵያው ንጉሥ አፄ ዮሐንስ አራተኛ፤ ጦርነቱን መግጠም አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የተቻለውን ሁሉ ጥረት አደረጉ፡፡ ጥረታቸው ግን አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም፡፡ አፄ ዮሐንስ ኅዳር 8 ቀን 1868 ዓ.ም. ማለዳ፣ ጉንዳጉንዲ ወይም ጉንደት ላይ ግብፅን ጦርነት ገጠሙ፡፡ የግብጽ ሠራዊት በኢትዮጵያ ወታደሮች ድባቅ ተመታ፡፡
ለግብጻውያን ሽንፈቱ አልተዋጠላቸውም:: ከአራት ወራት በኋላ ለኢትዮጵያ የመልስ ምት ለመስጠት 25 ሺህ ሠራዊት አስታጠቁና ዳግም ለጦርነት ተሰለፉ፡፡ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለሦስት ቀናት እልህ አስጨራሽ ውጊያ ተደረገ:: አሁንም ጦርነቱ በኢትዮጵያ አቸናፊነት ተጠናቀቀ፡፡ ይሁንና በሐምሌ ወር ከተካሄደው ጦርነት በኋላ፣ በ1876 ዓ.ም. ወደ ካይሮ የተላኩትን የአፄ ዮሐንስ መልዕክተኛን፣ ብላታ ገብረእግዚአብሔርን ግብፅ አሰረች፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም ያለ ምንም ይቅርታ መልሳ ፈታች፡፡
የጥንቶቹ የግብጽ መሪዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የዝናብ መጠኑ ሲያንስና የዓባይ ወንዝ የውሃ ሙላት ሲቀንስ፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ገድበውት ወይም ጠልፈውት ነው›› እያሉ ክፉኛ በስጋት ይናጡ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ ኢትዮጵያ የወቅቱ ነገስታት አማላጅ እየላኩ፣ የዓባይ ወንዝ እንዳይገደብባቸው ወይም እንዳይጠለፍባቸው ሲማፀኑ፤ ደጅ ሲጠኑ ኖረዋል፡፡
አፄ ይምርሐነ ክርስቶስ (1077-1117)፤ የግብፅ ክርስቲያኖች በእስላም ገዥዎቻቸው ትዕዛዝ የከፋ ስደትና መከራ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ሰማ፡፡ በዚህን ጊዜ ለግብፁ ገዥ ክርስቲያኖችን ለማጥፋት የጀመረውን እኩይ ተግባሩን እንዲያቆም፤ ካላቆመም ዓባይ ወንዝን ከእነ ገባሮቹ ወደ ሌላ በረሃማ አቅጣጫ በመመለስ፣ ግብፃውያንን በውሃ ጥም ለመበቀል የቆረጠ መሆኑን የሚገልፅ መልዕክት ሰደደለት፡፡
የግብፅ ሕዝብ ይህንን በሰሙ ጊዜ በ‹‹ድርቅ ማለቃችን ነው›› ብለው በእጅጉ ተጨነቁ፡፡ የግብፅ ገዢም ዛሬ ነገ ሳይል እጅ መንሻ አሲይዞ፣ የግብፅ ፓትርያርክን አቡነ ሚካኤልን ወደ ኢትዮጵያ ላከ፡፡ እርሳቸውም አፄ ይምርሐነን  ያሰበው የዓባይ ውሃ ወደ ሌላ አቅጣጫ ቢቀለበስ በሚከሰተው ድርቅ የሚጐዱት ክርስቲያኖችም ጭምር እንደሆኑ አስረዱ:: አፄ ይምርሐነ ክርስቶስ፤ ለግብፅ ሕዝብና ለፓትርያርኩ ክብር ሲል እቅዱን መተውን ነገራቸው፡፡ ፓትርያርኩም የተላኩበትን ተግባር አከናውነውና ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው፤ ለተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ምዕመናን ቡራኬ ሰጥተው በደስታ ወደ ግብፅ ተመለሱ፡፡
በአፄ ዐምደ ጽዮን (1297-1327) እንዲሁም በአፄ ሰይፈ አርእድ (1327-1355) የንግስና ዘመንም፣ ግብጾች “የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ በመቀየር ጉድ እንሰራችኋለን” ተብለዋል፡፡ ግብጾች በ19ኛው ክፍለ ዘመን በዘላቂነት በዓባይ ወንዝ ላይ ያላቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁበትን መላ ከመዘየድ አልቦዘኑም፡፡ በመካከለኛ ዘመን ከ1789-1879 እ.ኤ.አ. የግብፅ መሪ የነበረው መሐመድ ዓሊ፤ ‹‹የግብፅ ደህንነትና ብልፅግና የሚረጋገጠው፣ ግብፅ ከፍተኛ ውሃ በምታገኝበት የኢትዮጵያ ግዛት ላይ አሸናፊነቷን ስታስከብር ነው!›› የሚል አቋም ነበረው፡፡ ቀጥሎ የመጣው የግብፅ መሪ ከዲቭ እስማኤል አማካሪ የነበረው የስዊዝ ዜጋ ዋርነር ሙዚንገር ዓባይን በተመለከተ‹‹ኢትዮጵያ ለግብፅ አስጊ ሀገር ናት!›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር መለገሱ ይነገራል፡፡
*    *   *
ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በ1927 እ.ኤ.አ በጣና ሐይቅ መውጫ ላይ ግድብ ለመሥራት ማቀዳቸው ተሰማ፡፡ ይሄን ተከትሎ ግብጾች ሥም የማጥፋት ዘመቻቸውን ተያያዙት፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ›› የሚለውን ስያሜ የሚጠቀሙት ‹‹ኢትዮጵያውያን የንጉሥ ሰለሞን የእሥራኤል ዘር ስላላቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የእሥራኤል ወዳጅ ናቸው፡፡ ጽዮናዊ የመንግሥት ሥርዓትንም ያራምዳሉ›› በማለት ኢትዮጵያን ከአረብ አገራት ጋር ለማራራቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡
ንጉሡ ግድቡን በእውን ለመተግበርም በአሜሪካን አገር በሚገኘው ‹‹ዋይት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን›› አማካኝነት ማስጠናት ጀመሩ፡፡ የካርታ ሥራው ከተከናወነ በኋላ ግን በግብፅና በእንግሊዝ መንግሥታት ክፉኛ ተቃውሞ በመነሳቱ ሥራው ሳይተገበር ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የግብጽ ዜጐች በዓለም ባንክ እስከ ምክትል ዳይሬክተርነትና በተባበሩት መንግሥታት እስከ ዋና ፀሐፊነት በያዙት ኃላፊነት በመጠቀም፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ለምትሰራው ግድብ፣ እርዳታና ብድር እንዳታገኝ ሳያሰልሱ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ በግብፅ እጅ ጥምዘዛ፣ እ.ኤ.አ በ1929 የግብፅና የሱዳን ስምምነት መሰረት፣ የዓባይ ወንዝ ይኖረዋል ከተባለው አጠቃላይ የውሃ መጠን ግብፅ 92 በመቶ፣ ሱዳን 8 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጋለች፡፡ በዚህ ወቅት በቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀችው ብቸኛ አገር ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራት፣ ከዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ድርሻ እንዳይኖራቸው ተደርጐ ከድልድሉ ውጭ ሆነዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የላይኛው ተፋሰስ አገራት በግልፅ የውሃ ድርሻ የተነፈጋቸውና እንደ ባለድርሻ ያልታዩበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡
እ.ኤ.አ በ1947 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአገራትን የኢኮኖሚ መብቶችና ግዴታዎች ለመደንገግ ያፀደቀው ቻርተር፤ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቶቿን የመጠቀም መብቷን አይከለክልም፡፡ ይህንን እያወቁ ግብጦች ከላይ ታች፤ ከታች ላይ መማሰን ጀመሩ፡፡ ይሁንና ግብጾች በጦርነት፣ እንግሊዝ በውልና በስምምነት ስም፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ምኞታቸውን ማሳካት አልተቻላቸውም፡፡ በ1941 እ.ኤ.አ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በጣልያን ጦርነት ምክንያት በስደት ሱዳን ካርቱም በነበሩበት ወቅት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንን የነበረው ጋማል አብድል ናስር፣ የዓባይ ወንዝ ከመነሻው እስከ መድረሻው ለመቆጣጠር ‹‹የዓባይ ተፋሰስ አንድነት›› በሚል ሽፋን፣ ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን እንዲዋሃዱ ሀሳብ አቅርቦላቸው ነበር፡፡ ይሁንና በወቅቱ በሱዳን ካርቱም፣ የኢትዮጵያ ቆንስላ የነበሩት መለስ አንዶም ወደ ካይሮ አመሩ፡፡ በዓባይ ተፋሰስ አንድነት ስም የተጠነሰሰውን ሴራ በማጋለጥም መልዕክታቸውን አድርሰው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ፡፡---
(በቅርቡ ለኅትመት ከሚበቃው የጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን መጽሐፍ ላይ የተቀነጨበ)

Page 11 of 476