Administrator

Administrator

Saturday, 16 November 2019 13:11

የዕይታ ጥግ

            
(ስለ አመለካከት)
• አንድን ነገር ካልወደድከው ለውጠው:: ልትለውጠው ካልቻልክ ደግሞ አመለካከትህን ለውጥ፡፡
    ማያ አንጄሎ
• አዕምሮ እንደ ፓራሹት ነው - የሚሰራው ሲከፈት ብቻ ነው፡፡
   ቶማስ ዴዋር
• በጥሩና በመጥፎ ቀን መካከል ያለው ብቸኛው ልዩነት አመለካከትህ ነው፡፡
   ዚግ ዚግላር
• ቀና አመለካከት ያለው ሰው፣ በየትኛውም ወቅት እንደሚያፈራ ተክል ነው፡፡
   ሺቭ ክሄራ
• ሰው በዓለም ላይ የሚያየው በልቡ ውስጥ ያለውን ነው፡፡
   ጆሃን ዎልፍ ጋንግ ቮን ጎተ
• እኔ፣ በጎ በጎው ላይ ማተኮርን እመርጣለሁ፡፡
   ሃሊማ አደን
• በጎና ጠቃሚ መልዕክቶችን ለማሰራጨት የአቅምን ሁሉ አድርግ፡፡
   ስቲፋን ማክ ማሆን
• እጣ ፈንታህን መለወጥ የማትችል ከሆነ፣ አመለካከትህን ለውጥ፡፡
   ቻርልስ ሬቭሶን
• ፈጠራ ተሰጥኦ ሳይሆን አመለካከት ነው::
   ጄኖቫ ቼን
• ክዋክብትን ማየት የምትችለው በጨለማ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
  ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄ.አር.
• ቀና አስተሳሰብ በቀና ተግባር መደገፍ አለበት፡፡
   ጆን ሲ.ማክዌል
• አዎንታዊ አስተሳሰብ ስኬትን ይፈጥራል::
   ዩሪጃህ ፋበር

Saturday, 16 November 2019 13:01

አዲስ ጐጆ

   እንደ ወትሮው የቢሮ ሥራ ጨርሶ፣ ታክሲ ተራ ረዥም ሠልፉን ታግሶ፣ ሠፈር ሲደርስ ወደ አትክልትና ፍራፍሬ ቤት ጐራ ብሎ፣ ፌቨን የምትወደውን ጠቃጠቆ ሙዝ ፍለጋ፣ አንድ ሁለት ቤት ረገጠና አገኘ፡፡ ሙዙን አስመዝኖ ወደ ቤቱ በእግሩ ሲያቀጥን፣ አንድ ሁለቴ ስልኳን ሞክሮ እምቢ አለው፡፡ ያቺን በቅመም ያበደች ሻይዋን መጠጣት ፈልጐ ነበር፡፡
በርግጠኝነት በዚያ ሰዓት ፌቨን እቤት መድረስ አለባት፡፡ እሱ ከሲኤምሲ ተነስቶ አየር ጤና እስኪደርስ፣ እሷ ካራቆሬ ቤቷ መድረሷ የተለመደ ነው፡፡ ምናልባት ብሎ ቴክስት አደረገላት፡፡
“አንቺ ቅመም፣ ያንን የቅመም ሻይሽን አጠጪኝ፤ እየመጣሁ ነው፡፡”
መልስ አልሰጠቺውም፡፡
ቤት ሲደርስ ቁልፍ ነው፡፡ ቁልፉን ሰደደና ከፈተው፡፡ ቤቷ ዝብርቅርቅ ብሏል፡፡ የፌቨን ሻይ የለም፡፡ ምሥልቅልቅ ያለ ነገር ተፈጥሯል፡፡ እጁ እግሩ፣ ወገቡ… መላው ሰውነቱ የተቆራረጠ፣ ወይም እንደ ባቢሎን ግንብ የፈራረሰ መሰለው፡፡
ሶፋዎቹ መካከል ያለችው ጠረጴዛ ላይ በነጭ ወረቀት የተፃፈ ደብዳቤ ላይ፣ ንፋስ እንዳይወስደው የቴሌቪዥኑ ሪሞት ተቀምጧል፡፡ ብድግ አድርጐ አነበበው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ወለሉ ላይ ባፍጢሙ ተደፋ፡፡ እንደ ሕፃን ልጅ ተንሰቀሰቀ፡፡
“እኔ ምን በደልኩሽ ታዲያ?”
አሁን ያንን ሁሉ ድካሙን ረስቶ፣ አክስቱ ጐረቤት ወዳለው ፍፁም ቤት ለመሄድ ተነሳ፡፡
ፌቨንን ያገኛት እዚያ ሠፈር፣ አክስቱ ቤት በሚሄድበት ጊዜ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ ሳንቲም ሲያስፈልገው፣ ወይም ጥሩ ምግብ ሲያምረው፣ የእናቱ እህት ቤት ይሄዳል፡፡ አንዳንዴ ጓደኞቹንም ይዞ ይሄድ ነበር፡፡ አክስቱ በኑሮ ከእናቱ በጣም ትሻላለች፡፡ እናቱ ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ልጆቻቸውን ማሳደግ መከራ ሆኖባቸው ነበር፡፡
የአክስቱን ቤት ይወደዋል፡፡ ለሚበላው ምግብና አንዳንዴ ለሚሰጠው ብር ብቻ ሳይሆን ፌቨንንም ያገኛት እዚያው ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲሄድ እርሷም ብቅ ስትል ተገናኙና ጐጆ ለመቀለስ በቁ፡፡
የእርሷ የልጅነት ጓደኛ፣ እንጀራ ፍለጋ ወጥቶ ዲላ የምትባል ከተማ ከሰመጠ በኋላ ፌቨን የራሷን ሕይወት ጀመረች፡፡ ይህንንም በስልክና በፌስቡክ ተነጋገሩ፡፡ ትዳር ከያዘች በኋላ ሁሉም ነገር አበቃ፡፡
ታክሲ ውስጥ ሲገባ፣ ሂሣብ ሲከፍልም ነፍሱን አያውቅም፡፡ ታክሲው ሲሄድ እንደ መጀመሪያ ተሣፋሪ ፎቁ፣ ዛፉ… ምናምኑ ሁሉ አብሮት የሚሄድ እስኪመስለው ግር አለው፡፡ እንባውን ውጦት እንጂ ቢዘረግፈው ደስ ባለው፡፡
የቀድሞ ፍቅረኛዋን እስኪያገኘው ድረስ ቸኩሏል፡፡ ከሥራ ተመልሶ ቤት እንደሚሆን ገምቷል፡፡ የቤቱን በር ቆልፎት እንደሆነ እንኳ አላወቀም፡፡ ምናልባት ቁልፉን በሩ ላይ ለክቶት መጥቶ ይሆናል፡፡ “የራሱ ጉዳይ” አለ፡፡ ከዚህ ስቃይ መሞት ባንድ ጣዕሙ ይሻላል፡፡
ታክሲው ገሰገሰ፣ ሙዚቃው ነደደ፤ ልቡ ልትፈነዳ ነው፡፡
ሲያገኘው ምን ሊፈጠር እንደሚችል፣ ምን ማድረግና እንዴት እንደሚያደርግ ገና የሰከነ ዕቅድ የለውም፡፡ የሚንቀሳቀሰው በደመ ነፍስ ነበር፡፡
ቀድሞ አክስቱ ቤት እንደማይገባ ወስኗል፡፡ እርሷም ግን መስማቷ እንደማይቀር ያውቀዋል፡፡
ባላንጣው በር ላይ ሲደርስ በሩን አንኳኳ፡፡ አልተከፈተም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ሠራተኛዋ መጣችና ተመለሰች፡፡
አሁንም አንኳኳ፡፡
መጥታ ከፈተችለት፡፡
“ሰለሞን የለም?” አላት፡፡
“አለ” ስትለው፣ ሳያስፈቅዳት ገባ፡፡
ምናልባት አብሯት ሄዷል የሚል ፍርሀት ነበረው፡፡ ትንሽ ቀለል አለው፡፡
ሲገባ ሶፋ ላይ ተቀምጦ ቴሌቪዥን እያየ ነው፡፡
ተወርውሮ ወደቀበት፡፡
ሠራተኛዋ እየሮጠች የፍስሃ አክስት ቤት ሄደች፡፡
ሳሎኑ ላይ እንደወደቀ የአክስቱ ድምጽ ይሰማዋል፡፡ በሩን በርግደው ገብተው፤ “ምንድነው?...ምንድነው?” አሉ፤ እየጮኹ፡፡
ፍሰሃ ያለቅሳል፡፡
“ያለ ፌቨን መኖር አልችልም፤ እባክህ፣ እባክህ መልሳት… እባክህ መልሳት” ይላል፡፡
አክስቱ ግራ በመጋባት “እግር ላይ መውደቅ ምን አመጣው? የገዛ ሚስትህን ከየት ነው የሚመልስልህ?”
ፍሰሃ ከወደቀበት ተነስቶ፣ “አክስቴ… ጥላኝ ሄዳለች”
“ታዲያ እርሱ ምናገባው?”
“በእርሱ ምክንያት ነው፤ ከርሱ ጋር ይገናኛሉ፡፡ ከኔ ጋር በዚህ ሁኔታ መኖሩ ህሊናዋን ስላሰቃየው ጥላኝ ሄደች፡፡ ፌቪ ስስ ናት… ፌቪ ንፁህ ናት፡፡››
“ሂድ! የምን ንጽህና ነው? ንፁህ ከሆነች ሁለት አልጋ ምንድነው?”
ደግሞስ ለምን ጥርግ አትልም!”
“አክስቴ… ተዪኝ!”
“ለካ እንዲህ አልጫ ነህና!...ድንቄም የኛ ኢንጂነር!”
“…ዕውቀትና ሥልጣን፣ በፍቅር ፊት የሚያለቅስ ሻማ ነው፡፡”
“የራስህ ጉዳይ ነው! አሁን ይልቅ ተነስና ውጣ!”
“እባክህ ወንድሜ… ካለችበት አሥመጣልኝ!”
“እርሱ አስመጥቶልህ ሚስቴ ናት ብለህ አቅፈሃት ልተኛ?!”
“አዎ፤ እሾኋን እረስቼ አበባዋን አሸታለሁ፤ አክስቴ ተዪኝ!”
በሩን በሀይል ዘግታው ወጣች፡፡
“ለዚያች ለናትህ እነግርልሃለሁ፡፡ አሁን እርሷ አንተን ወለደች!? አንበሳ ድመት ይወልዳል?”
መልስ አልሰጣትም፡፡
እናቱ ነጠላቸውን አንጠልጥለው ታክሲ ሲሳፈሩ፣ ትንሹ ልጃቸው በድንጋጤ ተከትሏቸው ወጣ፡፡ እንደዚህ ሲበሽቁ አይቷቸው አያውቅም፡፡ ፊታቸው የጭራቅ ፊት መስሏል፡፡
“እውነት አንቺ ልደትዬ ካለሽ.. እውነት ከልጅነቴ ጀምሮ አንቺን የሙጢኝ ብዬ እንደሆነ”…
“እማዬ…እማ!”
“ዞር በልልኝ አልጫ! የአልጫ ዘር!”
መለስ አለና ቀስ ብሎ ተከተላቸው፡፡ ታክሲ ውስጥ ሲገቡ፣ እርሱም ተከትሎ ገባ፡፡
ልደታ ቤተ ክርስቲያን ደጅ ‹‹ወራጅ›› አለ ብለው ሲወርዱ አብሯቸው ወረደ፡፡
ከዚየም ቀስ እያለ ተከተላቸው፡፡ እየፈጠኑ ሄደው አንድ ጥግ ተንበረከኩ፡፡ ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ይሰማል፡፡
“ያን ጀግና - አብዮትን በወለድኩበት ማህፀን… ይህንን አልጫ ወለድኩ! ላገሩ ጦር ሜዳ የሞተውን አንበሳ በወለድኩበት፣ ለሴት ብሎ የባላንጣውን ጫማ የሚስም አልጫ ሰጠሽኝ! ምነው ይሄ ድፍት ብሎ… ያኛው እንደ ጌታ ከሞት ቢነሳልኝ? ምን ብዬ ልኑር?...አሁን እንዴት ልኑር?›› ስቅስቅ እያሉ አለቀሱ፡፡
…“እባክህ አንተ መድሃኔዓለም… ገላግለኝ!..እባክህ “በቃሽ” በለኝ፡፡ አሁን በዕድሬ ሰዎች መካከል… በተከበርኩበት ሠፈር… በዚህ ውርደት እንዴት እኖራለሁ? ሀገር ለቅቄ እንዳልሄድ… ይሄ ራሱን ያልቻለ ልጅ አለ…››
ፀሎታቸውን ጨርሰው ቀና ሲሉ፣ ስልካቸው አቃጨለ፡፡
“ሄሎ?”
“እመት”
“ነገሩ ተበላሸ”…
“ምንድን ነው?”
“ልጅቷ ራሷን አጥፍታለች!”
“ተገላገልና! ስሙን አጨቅይታ ሞተች?...ባለጌ!”
“ተዪ እንርሱ አይባልም!”
“አዋርዳኝ ሞተቻ! ምናለ ዝም ብላ ብትሞት?”
“ጨዋ ስለሆነች አይደል ራሷን የገደለች!”
“ጨዋማ መጀመሪያ ሁለት ከንፈር አያምረውም!”
“ተዪ በቃ!”
ስልኩን ዘጉትና ከደጀ ሠላሙ ቀጥ ብለው ወጡ፡፡
ትንሽ እንደቆዩ አሁንም ስልካቸው ጮኸ፡፡
“ልጅቷ ተርፋለች፣ ልጅሽ ሆስፒታል ገብቷል!”
“ይደፋ! ድብን ይበል!...አሰዳቢ!”

   ሁዋዌ ለሰራተኞቹ የ285 ሚሊዮን ዶላር ጉርሻ ሰጠ

            የአለማችን ቁጥር አንድ ማህበራዊ ድረገጽ፣ ፌስቡክ እስካለፈው መስከረም በነበሩት የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ3.2 ቢሊዮን በላይ የፌስቡክና የኢንስታግራም ሃሰተኛ አካውንቶችን መዝጋቱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፤ ፌስቡክ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በመላው አለም የሚገኙ ተጠቃሚዎች ያሰራጯቸውን 11.4 ሚሊዮን ያህል የጥላቻ ንግግሮችና መልዕክቶች ከድረገጹ ላይ ማጥፋቱን ጠቁሟል፡፡ በዚሁ የስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ኢንስታግራም በተሰኘውና ተጠቃሚዎች ፎቶግራፎችን በሚያሰራጩበት አፕሊኬሽኑ የተለቀቁ 1.2 ሚሊዮን የሚደርሱ የህጻናት ርቃንና የወሲብ ምስሎችን ማጥፋቱን የገለጸው ፌስቡክ፤ የተለያዩ አሸባሪ ቡድኖችና ደጋፊዎቻቸው ካሰራጯቸው የሽብር ፕሮፖጋንዳ መልዕክቶች መካከል 98 በመቶ ያህሉን ማስወገዱንም አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ የአለማችን ሁለተኛው ግዙፍ የሞባይል አምራችን ኩባንያ የሆነው የቻይናው ሁዋዌ፣ ሰራተኞቹ ከአሜሪካ መንግስት የተጣለበትን ማዕቀብ ተቋቁመው፣ ለተሻለ ስኬት እንዲነቃቁ ለማትጋት በድምሩ 285 ሚሊዮን ዶላር በጉርሻ መልክ መስጠቱ ተነግሯል፡፡
ኩባንያው የማትጊያ ጉርሻውን የሰጣቸው በማይክሮ ቺፕስ ምርት፣ በምርምርና ልማት እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ ለሚሰሩ 90 ሺህ ያህል ሰራተኞቹ መሆኑን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ እያንዳንዱ ሰራተኛ በአማካይ 3 ሺህ 100 ዶላር ገደማ  እንደሚደርሰው አመልክቷል፡፡
ሁዋዌ፤ ከዚህ በተጨማሪም 180 ሺህ ለሚደርሱት ሁሉም ሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ እንደሚያደርግ ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ሰራተኞቹ ለስኬቱ ቁልፍ ሚና በመጫወታቸው ምስጋና ለመስጠትና ለወደፊቱም ተግተው እንዲሰሩ ለማበረታታት በማሰብ ውሳኔውን ማሳለፉን እንደገለጸ አመልክቷል፡፡

   በብዙ መከራ የተሰባሰቡ አራዊት፡፡ ጉዳያቸውን ባለማወቅ ለመግባባት ብዙ ሰዓት ፈጀባቸው፡፡
ጦጢት ነገሩ ገብቷታል፡፡ አላግባባ ያላቸው “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ” ነው፡፡
አንበሳ፤
“እስከዛሬ እኔን ተቀብላችሁ ስትኖሩ የነበራችሁ የዱር አራዊት፣ ዛሬ ምን ተፈጠረና ነው አዲስ መሪ ካልመረጥን የምትሉት?” አለ፡፡
ነብር፤
“አያ አንበሶ፣ መቼም እርጅናን የመሰለ የዱር አራዊት ጠላት የለም፡፡ እርስዎ ራስዎ ሲተርቱ እንደሰማነው፣ “እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደለም ወይ?” ብለዋል፡፡
ስለዚህ እንደ እርጅና አሳሳቢ ጠላት የለንም ማለት ነው”፡፡
ዝሆን፤
“እኔም አያ ነብሮ ያለውን ነው የምደግፈው”፡፡
ጦጢት ዛፍ ላይ ሆና፣ የሚባለውን ሁሉ እያዳመጠች ናት፡፡
“እኔ ሞት ይሻላል ነው የምለው፡፡
“ያው ሞቱ ይሻላል ቁርጡ የታወቀው” ይል የለ አበሻ” አለች፡፡
“እንዲህ ሞትን ስትመኚ መበላትም እንዳለ አትርሺ!” አላት አያ አንበሶ፡፡
*    *    *
አበሻ መሟረት ይወዳል - ከምኞት ላያልፍ፡፡
ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፤ ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሾተላይ አለባት፡፡ መርገምት አለባት፡፡ እያደር ቁልቁል እንጂ ሽቅብ አትሄድም፡፡ አንዱ መርገምቷ ይሄ ነው፡፡
ሁለተኛው መርገምቷ መሪ እንዲዋጣላት አለመሆኑ ነው፡፡ ከትናንሽ ከንቱ ሰዎች አንስቶ እስከ ትላልቅ ሹማምንት ድረስ፣ በየጊዜው በሚገርም ፍጥነት ይቀያየራሉ፡፡ አንዱ የጀመረውን ሌላው ለመጨረስ ፋታ የለውም፡፡ እንደተዋከበ ጀምሮ እንደተዋከበ ያበቃል፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤
“ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ሰሎሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት ራሱ ሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን”
የተለመዱት አባባሎች ላይ ሃሳብ ጨምረን ማዳበር ትልቅ ክህሎት ነው፡፡
አገራችን እንደዚህ ዓይነት ርቀትና ልቀት ያሻታል፡፡ መንገዱ ረዥም ይሁን እንጂ ፍፃሜው ጣፋጭ እንደሚሆን ማመን ትልቅ ችሎታ ነው፡፡
ያለ ድካም ፍሬ አይገኝምና!
አለ በውስጣችን ደግ ደግ ፈለግ
ደሞም ዕውቀት ማለት
ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ
ዕድሜህ እየጨመረ ሲመጣ ሱስህ እየበረታ ከመጣ፣ የነገ መንገድህን በቅጡ መርምረው! ይላሉ ፈላስፎች፡፡

Saturday, 09 November 2019 13:40

የህይወት ጥግ

- የሻማዎቹ ዋጋ ከኬኩ ዋጋ ከበለጠ፣ ዕድሜህ መግፋቱን ትገነዘባለህ፡፡
   ቦብ ሆፕ
- አዛውንቶች ሁሉን ነገር ያምናሉ፤ መካከለኛ ዕድሜ ላይ ያሉቱ ሁሉን ነገር ይጠረጥራሉ፤ ወጣቶች ሁሉን ነገር ያውቃሉ፡፡
   ኦስካር ዋይልድ
- ሰው ለመተኛት አልጋ ላይ ከመውጣቱ በፊት ቁጣውን ወይም ንዴቱን መርሳት አለበት፡፡
   ሞሃንዳስ ጋንዲ
- አንዳንድ ሰዎች የቱንም ያህል ቢያረጁ፣ ውበታቸው አ ይነጥፍም - ከ ፊታቸው ወ ደ ልባቸው ይሻገራል እንጂ፡፡
   ማርቲን ቡክስባዩም
- ለህፃናት ሁሌም መልካም ሁን፤ የመጨረሻ ማረፊያ ቤትህን የሚመርጡልህ እነሱ ናቸውና፡፡
   ፊሊስ ዲለር
- የሞት ፍራቻ የሚመነጨው ህይወትን ከመፍራት ነው፡፡ ህይወቱን በተሟላ መልኩ የሚመራ ሰው በማንኛውም ጊዜ ለመሞት  ዝግጁ ነው፡፡
   ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
- ከትላንት ተማር፤ ዛሬን ኑርበት፤ ነገን ተስፋ አድርግበት፡፡ ዋናው ነገር መጠየቅን አለማቆም ነው፡፡
   አልበርት አንስታይን
- አንድን ሃሳብ ሳይቀበሉት ማስተናገድ የተማረ አዕምሮ መገለጫ ነው፡፡
   አሪስቶትል
- ሌሎች የተናገሩትን መድገም ትምህርትን ይጠይቃል፡፡ ሌሎች የተናገሩትን መገዳደር አዕምሮን ይጠይቃል፡፡
   ሜሪ ፒቲቦን ፑሌ
- የህይወት እንቆቅልሾች በሙሉ የሚፈቱት በፊልሞች ላይ ነው፡፡
   ስቲቨን ማርቲን
- ጥሩ ጦርነትና መጥፎ ሰላም፣ ኖሮ አያውቅም::
   ቤንጃሚን ፍራንክሊን
- ሰው የተፈጠረው ለውድቀት ሳይሆን ለስኬት ነው፡፡
   ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዮ

     ሁዋዌ በ5ጂ ኢንተርኔት ፍጥነት አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገበ

              የኢንተርኔት አገልግሎትን በማቋረጥና ስለላን ጨምሮ ሌሎች ነጻነትን የሚጋፉ እርምጃዎችን በመውሰድ የዜጎችን የኢንተርኔት ነጻነት በማፈን ላለፉት ሶስት ተከታታይ አመታት ከአለም አገራት ቀዳሚነቱን ይዛ የዘለቀችው ቻይና፣ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧ ተዘግቧል፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም በ56 የአለም አገራት ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ጠቅሶ ዴይሊ ሜይል እንደዘገበው፣ ቻይና በአመቱ እጅግ የከፋውን የኢንተርኔት ነጻነት አፈና በመፈጸም ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ ኢራንና ሶርያ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ይከተላሉ፡፡
በሪፖርቱ የዜጎችን የኢንተርኔት አገልግሎት ነጻነት በማክበር ከአለማችን ቀዳሚዋ አገር ተብላ የተጠቀሰችው አይስላንድ ስትሆን፣ ኢስቶኒያና ካናዳ በሁለተኛና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ሁዋዌ፣ በ5ጂ የሞባይል ኢንተርኔት ፍጥነት አዲስ ክብረ ወሰን ያስመዘገበበትንና በሰከንድ ከ2.92 ጊጋ ባይት በላይ ፍጥነት ያለውን አዲስ ኔትወርክ በስራ ላይ ማዋሉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ሁዋዌ ከቱርክ ቴሎኮም ኩባንያ ጋር በመተባበር በኢስታምቡል ይፋ ያደረገው ይህ እጅግ ፈጣን የሞባይል ኔትወርክ፣ በሁዋዌ ሜት ኤክስ ስማርት ፎን አማካይነት ተሞክሮ በፍጥነት አዲስ የአለም ክብረወሰን ማስመዝገቡ ታውቋል፡፡
ኩባንያው ይህንን እጅግ ፈጣን ኔትወርክ በስራ ላይ ለማዋል የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙን ማስታወቁን የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ይህ አዲስ እምርታ ኩባንያው ከአሜሪካ መንግስት እየተደረገበት ያለውን ጫና ተቋቁሞ በአለማቀፉ የሞባይል ስልኮች ገበያ ያለውን ድርሻ ለማሳደግ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

   ከከፋ የእርስ በእርስ ግጭት ለጥቂት ተርፋ ፊቷን ወደ ሰላም ያዞረችውና በተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የምትገኘው ሱዳን፣ የመጀመሪያዋን ሳተላይት ባለፈው እሁድ በተሳካ ሁኔታ ማምጠቋ ተዘግቧል፡፡
የሱዳን ጊዜያዊ መንግስት ምክር ቤት ሃላፊ ጄኔራል አብደል ፈታህ አልቡህራን አገራቸው በቻይና መንግስት በተደረገላት ድጋፍ ወደ ጠፈር ያመጠቀችው ሳተላይት በወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የጠፈር ቴክኖሎጂ ዘርፎች ምርምር ለማድረግ የታለመ መሆኑን መናገራቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
“ሱዳን ሪሞት ሴንሲንግ ሳተላይት - ዋን” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሳተላይት፣ ባለፈው እሁድ ማለዳ ከሰሜናዊቷ የቻይና ግዛት ሻንዚ በተሳካ ሁኔታ ወደ ጠፈር መምጠቁን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሳተላይቱ እጅግ ጠቃሚ መረጃዎችን በመሰብሰብ ለአገሪቱ ምርምር እድገት ወሳኝ ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚጠበቅ መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

  በደቡብ ኮርያ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች በህይወት እያሉ የቀብር ስነስርዓት በተሳካ ሁኔታ የመፈጸም አገልግሎት የሚሰጥ በአይነቱ ለየት ያለ ድርጅት መቋቋሙንና ከ25 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎች በዚህ ድርጅት አማካይነት ሳይሞቱ ቀብራቸው መፈጸሙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሆዮዎን ሂሊንግ ሴንተር የሚል ስያሜ ያለውና ከሰባት አመታት በፊት የተቋቋመው ድርጅቱ፤ ሰዎች በቁም እያሉ የቀብር ስነስርኣታቸውን በመፈጸም፣ ሞትን እንዲያስታውሱና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያስችል አገልግሎት የመስጠት ዓላማ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ እስካሁን ድረስም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎቱን መስጠቱን አመልክቷል፡፡
“እንደምትሞት በቅጡ ከተረዳህና ሞትን በህይወት እያለህ ከተለማመድከው፣ ህይወትህን የምትመራበትን መንገድና አኗኗርህን ትለውጣለህ” ያሉት የ75 አመቱ የዕድሜ ባለጸጋ ቾ ጃሂ፤ “በጥሩ ሁኔታ መሞት” በተሰኘውና በድርጅቱ በሚሰጠው የጅምላ የቀርብ ስነስርዓት ላይ ቀብራቸውን ማስፈጸማቸውን ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በቅርቡ ባከናወነው የጋራ የቀብር ስነስርኣት ላይ ህጻናትና አረጋውያንን እንዲሁም ቀሳውስትንና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው ደቡብ ኮርያውያን መሳተፋቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰዎቹ በሬሳ ሳጥን ውስጥ ተጋድመው ለ10 ደቂቃ ያህል በመቆየት ቀብራቸው መፈጸሙንም አመልክቷል፡፡
ድርጅቱ በህይወት እያሉ የቀርብ ስነስርዓታቸውን እንዲያከብሩ በማድረግ ዜጎች ለህይወታቸው ዋጋ እንዲሰጡ፣ የበደሏቸውን ይቅር እንዲሉና ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲመሩ የማገዝ ራዕይ ሰንቆ ስራ መጀመሩንና የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ዘገባው አስታውቋል፡፡

   እማሆይ ወለተማርያም ገላው መነኩሲት - የማህበረሰብ መሪ - ገበሬ

                      እዚህ ገዳም ውስጥ እየሰራሁ መኖር የጀመርኩት፣ ፈጣሪ ለመንፈሳዊ ሕይወት ስለጠራኝ ነው፡፡ ብዙ ሴቶችና ወንዶች መንፈሳዊ ፈውስንና እፎይታን ለማግኘት ወደዚህ ስፍራ ይመጣሉ፡፡ ወደ አራት መቶ ሀምሳ ከምንሆነው የገዳሙ መነኩሲቶችና መነኩሴዎች በተጨማሪ የኛን እርዳታና እንክብካቤ የሚሹ በርካታ ወላጅ አልባ ሕጻናት፣ የአካል ጉዳተኞች፣ በእድሜ የገፉ አዛውንቶችና አቅመ ደካማ እናቶች አብረውን ይኖራሉ፡፡ በፀሎትና በአገልግሎት ከመትጋት ጎን ለጎን፣ በፈጣሪ የተመረጠችውን ይህቺን መሬት ለመንከባከብና ለማልማት እንታትራለን:: ራሳችንን ለመደገፍና ለሌሎች ለማካፈል በጋራ እንሰራለን፡፡ የፈጣሪ ቸርነት የተመሰገነ ይሁንና በአካባቢ ጥበቃና በዘላቂ የግብርና አሰራር፣ በዙሪያችን ላሉ መንደርተኞች አርአያ ለመሆን በቅተናል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ማቻከል ወረዳ፣ ኪሻካ ቂርቆስ በሚባል አካባቢ፣ በ1954 ዓ.ም ግድም ከገበሬ ቤተሰብ ነው የተወለድኩት:: ወላጆቼ በእርሻ ሥራ የተዋጣላቸው ትጉህ ገበሬዎች ነበሩ:: እኔም ከልጅነት እድሜዬ አንስቶ በታታሪነት መሥራት ያስደስተኝ ነበር:: ለወላጆቼ አምስተኛ ልጅ ብሆንም፤ እህት ወንድሞቼ በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ በለጋ እድሜያቸው ነበር የሞቱት፡፡ ነፍስ ሳላውቅ በአስር አመቴ ከተዳርኩ በኋላ፣ በጠና እስከታመምኩበት ጊዜ ድረስ ሁለት ልጆችን ወልጃለሁ፡፡ በበሽታ የተያዝኩት 22 ዓመት ሲሆነኝ አካባቢ ነበር፡፡ ክፉኛ በመታመሜ እኔም እንደ እህት ወንድሞቼ በወጣነት እድሜዬ እሞታለሁ ብዬ ብፈራም ተረፍኩ፡፡ ጤናዬ ሲመለስልኝ ‹‹ከቤተሰቤ ጋር ዓለማዊ ሕይወትን እመራ ዘንድ የፈጣሪ ፈቃድ አይደለም፤ እሱን እንዳገለግለው ይፈልጋል›› የሚል አዲስ ሀሳብ በውስጤ ይመላለስብኝ ጀመር፡፡
መጀመሪያ በአካባቢያችን ወደሚገኘው ደብረ መድሃኒት ኪሻካ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል ገባሁና፤ አዲስ ቤተ ክርስቲያን ለማሳነፅ እያገዝኩ ሰባት ዓመታትን አሳለፍኩ። ከዚያ ግን ከሚያውቁኝ ሰዎች ርቄ ወደ ግሸን ማሪያም ወይም ወደ ላሊበላ ገዳማት መሄድ አሰኘኝ፡፡ ፈጣሪ ያሰበኝ ግን ለሌላ ነበር:: የት ሄጄ ፈጣሪዬን እንደማገለግል ሳስብና ስፀልይ፣ በሕልሜ አንድ ዋሻ ታየኝ፡። ይሄው ዋሻ እየደጋገመ መላልሶ በህልሜ መጣ፡፡ አንድ ክረምት ካለፈ በኋላ፣ እዚህ አሁን ያለሁበት አካባቢ የጊራም ማሪያም ቤተ ክርስቲያን ለማሰራት እንዳግዛቸው ጠሩኝ፡። በአቅራቢያው ለፀሎት የምቀመጥበት ገዳም ይኖር እንደሆነ ስጠይቃቸው፣ ከአንዲት ወራጅ የምንጭ ውሃ ከፍ ብሎ ወደሚገኘው ዋሻ ይዘውኝ መጡ:: ልክ በህልሜ ሲመላለስ ያየሁት አይነት ዋሻ ነበር፡፡ በዚያ የዋሻ ገዳም ውስጥ በዱር እንስሳት መሀል ለሁለት ዓመታት ኖርኩ፡፡ እዚህ መጥቼ የምኖረው በፈጣሪ ፈቃድ ስለሆነ እሱ ይጠብቀኛል ብዬ ስለማምን በጅብ፣ በነብርና በሌላ የአራዊት መንጋ ዙሪያዬ ቢከበብም አልፈራሁም፡፡
በ1986 ዓ.ም የፋሲካ በዓል እንዳለፈ፣ አንድ ሌሊት ላይ ከወዲያ ጫካ ውስጥ ነብር ብቻ ሲቀር፣ ሌላው የአራዊት መንጋ ሁሉ ተጠራርጎ ሄደ፡፡ ያኔ ይህ ስፍራ በፈጣሪ መመረጡ ተገለጠልኝ:: ስሙ እንዲቀደስበትና እንዲወደስበት፣ የሰው ልጆችም ምህረትንና በረከትን እንዲያገኙበት፣ ፈጣሪ ይህን ቦታ እንደመረጠው ገባኝ፡፡ የአገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ ፈቅደውም፣ በአቡነ ተክለሃይማኖትና በቅዱስ ሩፋኤል ላይ ገደም እንዲቆምበት ቦታው ተባርኮ ተቀደሰ። አቡነ ዘካርያስ ባረኩንና ገዳሙንም “ዋሻ አምባ ተክለሃይማኖት አንድነት” ገዳም ብለው ሰየሙት:: እኛም መቀመጫውን አዲስ አበባ ባደረገው የዋሻ አምባ ተክለሃይማኖት ተቋራጭ ኮሚቴ እገዛ፣ ቤተ ክርስቲያኑን ገነባነው፡፡ የኮሚቴው አባላት ላሰባሰቡልን የገንዘብ ድጋፍ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡
በፈጣሪ ፈቃድ፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ጠበል ለመጠበቅና ምህረት ለመቀበል ሰዎች መምጣት ጀመሩ፡፡ ብዙ ሰዎች ከህመማቸው ተፈውሰዋል፤ ከመከራ ተገላግለዋል። ተዓምራት ያሳያቸውን ፈጣሪ ለማመስገንና የፈጣሪ በረከት ከኛ ጋር እንዲሆን በጉልበታቸውና በገንዘባቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ እርዳታ ሰጥተዋል፡፡
መሬቱንና ዙሪያ ገባውን ለማልማት ደፋ ቀና ማለት የጀመርኩት እግሬ ይህን አካባቢ በረገጠበት በ1984 ዓ.ም ነው፡፡ ከሞላ ጎደል አፈሩ ሁሉ ተራቁቶ፣ ለአይን ማረፊያ አንድም አጽዋት አልነበረውም፡፡ የድሮው ደን ተመንጥሮና ጠፍቶ፣ የወጥ ማማሰያ እንጨት ተፈልጎ የማይገኝበት በረሃ ሆኖ ነበር። የተራቆተው 52 ሄክታር መሬት እንደገና ነፍስ እንዲዘራና ደን ለምቶበት አረንጓዴ እንዲለብስ በማሰብ፣ ለመንግሥት አስተዳደር አመለከትኩ፡፡ ቀንና ሌሊት ዛፍ ለመቁረጥ ተደብቀው የሚመጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ ዛፍ ሲቆርጡ እንዳንሰማቸውና እንዳንይዛቸው በመጋዝ ቢጠቀሙም፣ ዛፎች ተገንድሰው ሲወድቁ መስማታችን አይቀርምና ተከታትለን እንይዛቸዋለን፡፡ ሕግን የሚጥስና አካባቢን የሚያጠፋ ተግባር እየፈፀሙ መሆናቸውን እንነግራቸዋለን፡፡ ሁሌም ስለ አካባቢ ጥበቃ እናስተምራለን፡፡ በመጨረሻ ግን በፈጣሪ ቸርነት ሁሉም ሰው ጫካው መነካት እንደሌለበት ስለተገነዘበ፣ ዛሬ የአካባቢው ነዋሪ ራሱ ደኑን ከጭፍጨፋ ይጠብቃል፡፡ የዱር እንስሳትን መንከባከብ የጀመርኩት ግን ከጊዜ በኋላ ከዋሻው አቅራቢያ ድኩላ ሲገደል አይቼ ነው፡፡ ለድኩላና ለሚዳቋ እንዲሁም ለሌሎች አራዊቶችና ለአእዋፍ ዘሮች መጠለያ እንዲሆናቸው የተለያዩ የዛፍ ችግኞችን ተክያለሁ፡፡ ዛፎቹ እያደጉ ሲመጡ ጉሬዛ፣ ከርከሮ፣ አቦ ሸማኔዎችና ሌሎች የዱር እስሳት እንዲሁም ሌሎች በርካታ አዕዋፋት በአካባቢው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡ ይህንን ደን የምንቆጥረው እንደ ሰውነታችን አካል፣ እንደ ሕይወታችን ክፋይ ነው፡፡
መሬቱን ለማልማት በምናደርገው ጥረት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈናል፡፡ የ5 ሺ ብር መነሻ ገንዘብ ከልማት ኮሚሽን ከማግኘታችን በተጨማሪ የተለያዩ አካላትም ድጋፍ አድርገውናል፡፡ ሁሉንም ሥራ ያከናወንነው በራሳችን አቅም ነው፡፡ ወዲህ የሚመጡ መነኩሲቶች፣ መነኩሴዎችና ቤተሰቦች ሲበራከቱ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ማብቀል እንዲሁም እንስሳትን ማርባት ጀመርን፡፡ ባለ አራት ቋት የወፍጮ ማሽን ተክለናል፡፡ ለችግር ሳንገበር እንደምንተጋ ያዩ በጎ ሰዎችም አግዘውናል፡፡ በአቅራቢያችን በሚገኘው አማኑኤል የተባለ ቦታም ባለ አራት ማሽን የዳቦ መጋሪያ አቋቁመናል፡፡ አሁን ደግሞ መንግሥት የማህበራችንን እድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ መንደራችንን ከዋናው ጎዳና ጋር የሚያገናኝ የበጋ የክረምት መንገድ በመሥራት ለጥያቄያችን ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ ኤሌክትሪክም አስገብቶልናል፡፡ እኛም ሥራችንን ቀጥለናል፡፡ እንደ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ቀይ ስር፣ ቃሪያና ካሮት የመሳሰሉ አትክልቶችን እናመርታለን:: ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ሎሚ፣ ትርንጎ፣ ዘይቱን ብርቱካንና ሌሎች ፍራፍሬዎችንም እናለማለን፡፡ ወቅቱን ተከትለን የሸንኮራ አገዳና ሌሎች ተክሎችን እንተክላለን፡፡ ለምግብ ፍጆታ ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ለመደገፍና ችግረኞችንም ለመርዳት የገቢ ምንጭ እንዲሆነን ነው የምናመርተው፡፡ ከጀርመን የልማት ተራድኦ ተቋም ጂቲዜድ ባገኘነው ድጋፍም፣ ማገዶ የሚቆጥብና የምግብ ማብሰያ ክፍላችንን በጭስ የማያፍን የኮንክሪት ምድጃ አሰራር አውቀንበታል፡፡ ምድጃ እየሰራን ለአካባቢው ነዋሪዎች እንሸጣለን፡፡ በአንድ ወገንም ለነዋሪዎቹ ጤንነት የሚጠቅም ምድጃ ነው፡፡ አላማችን አብረን እየተደጋገፍን መኖር ነው፡፡ ለወደፊት ትልልቅ እቅዶችም አሉኝ፡፡
ለመነኩሴዎች መኖሪያ ቤት መሥራት፣ የብሉይና የሃዲስ ቅዱሳን መጻሕፍትን አሰባስቦ የሚይዝ ቤተ መጻሕፍትን መገንባት፣ በዜማና በቅኔ የምናደርሳቸውን የአምልኮና የውዳሴ ስርዓቶቻችንን የሚያስጠና የሃይማኖት ትምህርት ቤት መክፈት፣ ሕጻናት እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩበት ዘመናዊ ትምህርት ቤትና የጤና ማዕከል መክፈት፣ የግብርና ምርቶቻችንን ወደ ሰፋፊ ገበያዎች ለማድረስና በጥሩ ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችሉንን መኪኖች መግዛት፣ ከፍጆታ እየተረፈ በማጓጓዣ እጦት እየተበላሸ የሚባክንብንን የወተት ምርታችንንም ለገበያ ማቅረብና ለአካባቢያችን ሙሉ አገልግሎት ከሚሰጥ የእንግዳ ማረፊያ ጋር ለኢኮ ቱሪዝም መዳረሻነና ማልማት በመሳሰሉት እቅዶቻችን አማካኝነት ወደፊት ይበልጥ ጠንካራ እንሆናለን::  
በእስካሁኖቹ ጥረቶች ያገኘነው መንገዱ ቀላል ሆኖልን አይደለም፡፡ ስኬታማ የሆንነው እንቅፋቶችን እየተሻገርን ነው:: በየጊዜው የሚያጋጥሙን ችግሮች የሰውን ልጅ እንደሚያጠነክሩትና ወደ በጎ ነገሮች እንደሚመሩት አምናለሁ፡፡ መጀመሪያ ላይ የአካባቢው ሰዎች ደናችንን እየጨፈጨፉ፣ ለመተዳደርያቸው ሊያውሉት ይፈልጉ ነበር:: በዚህ ሳቢያ ከብዙ ሰዎች ጋር ተቃቅሬ ዛቻና ማስፈራሪያ ሳይቀር ደርሶብኝ ነበር፡፡ ያኔ ሲዝቱብኝ የነበሩ ሰዎች ዛሬ አብረውን ይሰራሉ:: የኛን ፈለግ ተከትለው ዛፎችን ይተክላሉ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያለማሉ፡፡ ብዙዎቹ በሕይወታቸው ላይ በጎ ለውጥ ለማየትና ኑሯቸውን ለማሻሻል በቅተዋል፡፡
በአካባቢያችን የሚገኝ ሶስት ሄክታር የተራቆተ መሬት በመጨመር፣ ደኑን ያስፋፋነው ሲሆን አሁንም እየተንከባከብነውና መልሰን እያለማነው እንገኛለን፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የምርጥ ዘር ማባዣ ማዕከል በመፍጠር ለአካባቢው ገበሬዎች ለማከፋፈል እንፈልጋለን፡፡ ወደፊት ሥራችንን አስፍተንና አሻሽለን እንድንሰራ እውቀቱ ያላቸው ሰዎች ቢረዱን ደስ ይለናል፡፡ ዛሬ በእግዚአብሔር እርዳታና በራሳችን ጥረት፣ ሥራችንን በክልልና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ማግኘትና መከበር ጀምሯል፡፡ ከኢትዮጵያም ሆነ ከባህር ማዶ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ማህበር አማካኝነትም ሆነ በራሳቸው ሃይማኖት በኩል የደገፉንን ሁሉ ከልቤ አመሰግናለሁ፡፡
ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክት እንዲህ የሚል ነው- አንድ ነገር ስትጀምሩ ጥሩና መጥፎ ነገሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ፡፡ ትርፍና ኪሳራ ሁሌም ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ የምታገኙት ትርፍ ትንሽ ሆኖ ቢታያችሁም እንኳ ተስፋ አትቁረጡ፡፡ የበለጠ ትርፋማ የሚያደርግ መንገድ ለማግኘት መርምሩ፡፡ ቅጠላ ቅጠልን ሰብስቦና አድርቆ መሸጥ አልያም ትንሽ የሚመስሉ ሌሎች ሥራዎችም እንኳ ቢሆኑን፣ ከልባችሁ አስባችሁ ከገባችሁበት የሰራችሁት ነገር ትርፋማ ይሆናል፡፡
ወጣቶች፣ ዶሮ ቢያረቡ፣ ከብቶችን ቢያደልቡ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ቢያመርቱ፣ ወይም በሌሎች  መስኮች ተግተው ቢሰሩ፣ ራሳቸውንና አገራቸውን ይጠቅማሉ፡፡
ሴቶች ጠንካራ ለመሆንና ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚያስፈልጋቸው መማር፣ ራሳቸውን መቻልና ከወሲባዊ ግንኙነት በመታቀብ ጤናቸውን መጠበቅ ነው፡፡ ሁልጊዜ ወጣቶችን የምመክራቸው፣ በትምህርታቸው እንዲገፉ፣ በፈጣሪ እንዲያምኑና በሃይማኖታቸው እንዲፀኑ ነው፡፡ ሁላችንም አገራችንን መውደድና ማገልገል አለብን፡፡  

   ሰኔ 15 በአማራ ክልል ከፍተኛ ኃላፊዎችና በመከላከያ አዛዦች ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ ተጠርጥረው ታስረው የነበሩና ከአራት ወራት በኋላ የተለቀቁት ግለሰቦች፤ “የታሠርነው በማንነታችንና በምናቀርበው የተለየ ሃሳብ ነው” ሲሉ ትናንት በባለ አደራው ም/ቤት ቢሮ ተገኝተው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
አቶ ማስተዋል አረጋ የገቢዎች ሚኒስቴር ሠራተኛ እንደነበረ ጠቅሶ፣ በሚሠራበት መስሪያ ቤት በሚያነሳቸው ሃሳቦች እና በብሔር ማንነቱ ምክንያት መታሰሩን ገልጿል፡፡ ይሄንንም በምርመራ ወቅት ከቀረበለት ጥያቄ መረዳቱን ተናግሯል፡፡
ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለ በኋላ ሰኔ 17 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹በዚሁ ሰበብ አስራችሁ እሹት›› የሚል መመሪያ ከገቢዎች ተሰጥቶ መታሠሩንም በመግለጫው ላይ አስረድቷል፡፡
‹‹ለ33 ቀናት ጨለማ ቤት ነበርኩ›› ያለው አቶ ማስተዋል፤ በምርመራ ወቅት አንድም ጊዜ ከግድያው ጋር የተያያዘ ጥያቄ እንዳልቀረበለትም ገልጿል፡፡
የፌደራል አቃቤ ህግ እንደሆነ የገለፀው አቶ ህሩይ ባዩ በበኩሉ፤ ‹‹ጠ/ሚኒስትሩ ከፍትህ አካላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ባነሳሁት ጥያቄ ነው የታሰርኩት እንጂ ከሰኔ 15ቱ ክስተት ጋር በተያያዘ አይደለም” ብሏል፡፡
በወቅቱ ጠ/ሚኒስትሩ “አንተ ፖለቲከኛ ፖለቲከኛ ትሸተኛለህ” ብለውኝ ነበር ያለው የህግ ባለሙያው ህሩይ፤ በታሰርኩበት ወቅት ከግድያው ጋር በተያያዘ ምንም ምርመራ አልተደረገልኝም ብሏል፡፡
የአብን የፋይናንስ ሃላፊ መሆኑን የገለፀው አቶ ሲያምር ጌቴ፤ የአብን አባልና የፓርቲው  የድጋፍ ገቢ አሰባሳቢ በመሆኑ ድርጅቱን ለመጉዳት ሆን ተብሎ እንደታሠረ ገልጿል፡፡ በምርመራ ወቅትም “የባላደራው ም/ቤት አባል ናችሁ ወይ? ዐቢይን ትደግፋላችሁ? አብን ድጎማውን ከየት ነው የሚያገኘው?” የሚሉና ሌሎች ከግድያው ጋር ተያያዥነት የሌላቸው ጥያቄዎች እንደቀረቡለት ነው ያስረዳው - የአብን አባል የሆነው አቶ ሲያምር ጌቴ፡፡
ከእስር የተፈቱት ተጠርጣሪዎች ከጐናቸው የቆሙትን ወገኖች ያመሰገኑ ሲሆን በዋናነትም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡