Administrator

Administrator

የጀርመን የባህል ማዕከል (ጎተ) አዲስና ደረጃውን የጠበቀ ቤተ መፃህፍት ከትላንት በስቲያ ምሽት ላይ አስረመቀ፡፡ ቤተ መፅሐፍቱ ሶስት የተለያዩ ክፍሎችን የያዘ ሲሆን አንደኛው መፅሐፍትን ለማንበብና በጥሞና ሀሳቦችን ለማውጠንጠን የተዘጋጀ ሲሆን ከ20 ሰዎች በላይ በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል ተብሏል፡፡
2ኛው ክፍል ሲዲ፣ ኦዲዮ መፅሐፍት፣ ፊልም ማየት ለሚፈልጉና ኢንተርኔት መጠቀም ለሚፈልጉ ተጠቃሚዎች የተሰናዳ ክፍል ሲሆን አምስት አይፖዶችና ላፕቶፖችም የሚገኙበት እንደሆነና በአንዴ 18 ያህል ሰዎች የማስተናገድ አቅም ያለው ስለመሆኑ የቤተ - መፅሐፍትና የኢንፎርሜሽን ኃላፊው አቶ ዮናስ ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡ ሶስተኛው ክፍል ደግሞ አነስተኛ ስቱዲዮና አረንጓዴ ስክሪን የተገጠመለት ክፍል ሲሆን ይህ ክፍል ስለፊልም በቡድን ለሚወያዩ፣ ፊልም ኤዲት ለሚያደርጉ፣ ስቱዲዮ ውስጥ ኢንተርቪው ለሚቀርፁና ለመሰል ተግባራት የሚያገለግል እንደሆነ የገለፁት አቶ ዮናስ በአጠቃላይ ቤተ - መፅሐፍቱ “መልቲ ፊንክሽናልና መልቲ ሚዲያ” ሆኖ ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
በፊት የነበረውን የተለመደውን ቤተ - መፅሀፍት ለመቀየር ጥናት መስራቱንና ከውጭ የመጣች ባለሙያ የተለያዩ ተጠቃሚዎች የቋንቋ ተማሪችንና ሌሎችንም ከጎተ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተጠቃሚዎችን፣ ቃለ መጠይቅ ካደረገችና ፍላጎታቸው ከታወቀ በኋላ የቤተ መፅሐፍቱ ዲዛይን መስራቱን የገለፁት ኃላፊው ግንባታው አራት ወር እንደፈጀና ከ200 ሺህ ዩሮ በላይ እንደወጣበት ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በምርቃት ስነ - ስርዓቱ ላይ ከንባብ ጋር የሚሰሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የባህል ማዕከሉ ኃላፊች ታድመው ነበር፡፡

በቅርቡ በመንግስት ውሳኔ ከእስር ከተለቀቁ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት የኮሚቴው ህዝብ ግንኙነት የነበሩት ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ እንቅስቃሴዎች፣ ከመንግስት ጋር ስለተደረጉ ውይይቶች፣ ስለ እስር
ጊዜያቸው፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ እንዲሁም ስለ ወደፊት ዕቅዳቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡

ለእስር የተዳረጉበት አጋጣሚ ምን ይመስላል?
እኔ የተያዝኩት ሐምሌ 13 ቀን 2004 ነው። ዕለቱም የረመዳን የመጀመሪያ ቀን፣ እለተ አርብ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ባሉት ወራት፣ በተለይ ከየካቲት 26 ቀን 2004 በኋላ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች ዙሪያ ስድስት ሰዓት የፈጀ ውይይት አድርገን፣ በዚያ ላይ አለመግባባትና አለመስማማት ተፈጥሮ ነበር። ከዚያ በኋላ በመንግስት በኩል ኮሚቴውንም ጥያቄውንም በአሉታዊነት የመመልከትና “ህብረተሰቡን አይወክሉም፤ እስላማዊ መንግስት ሊመሰረቱ ነው” የሚሉ ቅስቀሳዎች በስፋት ይካሄዱ ነበሩ። በተለይ ከመጋቢት 7 ምሽት የኢቴቪ ፕሮግራም በኋላ ይሄ ቅስቀሳ ተጠናክሮ ነው የቀጠለው፡፡ የደህንነት ሃይሉም ከዚያ በኋላ፣ 24 ሰዓት ሙሉ እንቅስቃሴያችንን መከታተልና ስጋት መፍጠር ጀምሮ ነበር፡፡
ሚያዚያ 25 ደግሞ በሚዲያም 15 ደቂቃ የፈጀ ውንጀላ ያዘለ መግለጫ ተነቧል፡፡ እነዚህ ነገሮች ሲካሄዱ ቆይተው፣ የኮሚቴውን አባላት መያዝ የተጀመረው ሐምሌ 12 ቀን 2004 ነበር፡፡ እኔ የተያዝኩት ሐምሌ 13 ነው፡፡ ካራ ቆሬ አካባቢ በሚገኘው የጓደኛዬ ቤት እንዳለሁ ነው መጥተው የያዙኝ፡፡ ከያዙኝ በኋላ ፊቴን በጨርቅ ሸፍነው፣ በመኪና አድርገው ወደ ማላውቀው ቦታ ወሰዱኝ። በኋላ ላይ ነው ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው የደህንነት ቢሮ መሆኔን ያወቅሁት፡፡ ሌሎች ጓደኞቼ ያሉበትን እንድጠቁም ሲደበድቡኝና ሲያስፈራሩኝ ቆይተው፣ ሌሊት 6 ሰዓት ላይ ወደ ቢሮ አስገብተውኝ፣ ሽንት ቤት ገብቼ ፊቴን ሲፈቱኝ ነው ቸርችል ቪው ሆቴል የሚለውን አንፀባራቂ ማስታወቂያ አይቼ፣ ያለሁበትን ያወቅሁት፡፡ በማግስቱ ሐምሌ 14 ማዕከላዊ ወስደው አስረከቡኝ፤ ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ፡፡ ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ አራዳ ፍ/ቤት አቀረቡኝና የ28 ቀን ቀነ ቀጠሮ ጠየቁ። በወቅቱ ለፍ/ቤቱ የተናገሩት፤ ”ውጭ ሃገር ቆይቶ የአልቃይዳ አባል ሆኖ ሠልጥኖ መጥቷል፣ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ትራንዛክሽን በአካውንቱ ገብቷል፡፡ ህዝቡንም ለማሠልጠን እያደራጀ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ስለምንጠረጥረው የ28 ቀን ቀጠሮ ይሰጠን” በማለት ነበር፡፡ በእውነቱ ስለ እኔ ሳይሆን ስለ ሌላ ሰው የሚናገሩ ነበር የመሰለኝ፡፡ በዚህ መልኩ የ28 ቀን ቀጠሮ ተፈቅዶ ወደ ማዕከላዊ ተመለስኩ፡፡
የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጋር በወቅቱ ሲያደርጋቸው የነበሩ የውይይት ጭብጦች ምን ነበሩ?
17 አባላት ያሉት ኮሚቴ ነበር፡፡ ይሄ ኮሚቴ የሙስሊሙን ጥያቄዎች ያነገበ ነው፡፡ ከጥያቄዎቹ አንዱ፤ መጅሊስ የህዝበ ሙስሊሙ መሪ ድርጅት ቢሆንም በተግባር ደረጃ እንደ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ፍቃዱን በየ3 አመቱ የሚያድስ፣ የስራውን ሪፖርት የሚቆጣጠረውም የፍትህ ሚኒስቴር ነበር፤ በኋላ በ2003 መስከረም 24 ላይ የሃይማኖት ጉዳዮች ተጠሪነት ወደ ፌደራል ጉዳዮች እንዲዞር በፓርላማው ሲወሰን ፌደራል ጉዳዮች ተረክቧል፡፡ እኛ ደግሞ የመጅሊሱ አመራረጥ ግልፅ አይደለም፣ ማን ነው ሰዎቹን እየመረጠ ያለው? የሚሉ የህብረተሰቡን ጥያቄዎች ነው የያዝነው። ከዚያ ቀደም በ1992 በተመሣሣይ በመጅሊሱ ጉዳይ ጥያቄ ተነስቶ የተዳፈነበት ሁኔታ ነበር። በአንድ በኩል መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል መርህ ይቀመጣል፡፡ በሌላ በኩል፤ ለተቋማቱ አስተዳደር ፍቃድ እየሰጠ ያለው መንግስት ነው፤ ተቋሙ የስራ ሪፖርት የሚያደርገው ለመንግስት ነው፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ መንግስት ከተቋሙ እጁን ያንሣ ሲባል፣ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጉዳይ ግልፅ የሆነ፣ የጠራ ነገር በሚወጣበት ሁኔታ ላይ ስንወያይ ነበር፡፡ በሁለተኛ ደረጃ፣ አህባሽ የሚባል አስተሳሰብ ከንቲባውን ጨምሮ በበርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ አግኝቶ፣ አስተሳሰቡን ለማስፋፋት በርካታ ነገሮች ሲደረጉ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሙ ሙሉ ማስረጃ ነበር፤ በዚህ ጉዳይም ላይ ስንነጋገር ነበር፡፡ እንደዚሁም የአወልያ ተቋም በቦርድ ይተዳደር የሚሉት ላይ ነበር ውይይታችን፡፡ መጀመሪያ ጥር 18 ቀን 2004 ኮሚቴው ከተመረጠ በኋላ ጥር 23 ቀን 2004 በወቅቱ የሲቪል ሠርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሣዶ “ኮሚቴውን ላነጋግር እፈልጋለሁ” ብለው እኔ ባልኖርበትም፣ ሌሎች አባላት ሄደው አነጋገሯቸው፡፡
በወቅቱ ካነጋገሯቸው በኋላ ዶ/ር ሽፈራውን ጨምሮ እንነጋገራለን በሚል በሌላ ጊዜ ቀጠሮ ተያዘ፡፡ የካቲት 5 ቀን 2004 ወደ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሄድን፡፡ በወቅቱ ሚኒስትሩ አልነበሩም፤ ምክትሉ ነበሩ ፣ የአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ሃላፊ አቶ ፀጋዬ ማሞና ከፖሊስ የተወከሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነሱ ባሉበት ስለ ጉዳዩ ማብራሪያ ሰጠን፡፡ እነሱም “እንደ ኮሚቴ ወደኛ መምጣታችሁ ጥሩ ነው፤ ባለው ነገር ላይ ተነጋግረን መፍትሄ እንፈልጋለን” አሉን፡፡
መጀመሪያ ላይ የነበረው አዝማሚያ መጅሊስንም እኛንም አስቀምጠው ለማነጋገር ነበር። በወቅቱ እኛም አዝማሚያው ልክ አይደለም፤ እኛ ከመጅሊስ ጋር ተነጋግረን የምንጨርስ ቢሆኖ ኖሮ እናንተም ጋር መምጣት አያስፈልገንም ነበር፣ ህዝቡ መጅሊሱን አናውቀውም፤ አልወከልናቸውም እያለ ነው፤ ይባስ ብለው ከህዝቡ ፍላጎት ተቃራኒ እየሄዱ ስለሆነ እናንተ ለህዝቡ ያላችሁን ምላሽ ስጡን፤ አናናግራችሁም የምትሉ ከሆነም በግልፅ ንገሩን” ስንላቸው፣ መጅሊሱን ትተው እኛን ለማነጋገር ሞክሩ፡፡ በኋላ ላይ እኛ ከፌደራል ጉዳዮች ጋር መደበኛ ውይይት እያደረግን እያለ፣ መጅሊሱ “ህገወጥ ናቸው” ማለት ጀመረ፡፡ ከዚያም ወልቂጤን በመሣሠሉ አካባቢዎች የኮሚቴው አባላትን ማሠር ተጀመረ፡፡ በኋላ የካቲት 26 ቀን ባደረግነው ውይይት ላይ ሚኒስትሩም ተገኝተው ነበር፡፡ እኛም ውይይቱ በቴሌቪዥን ወይም በሬድዮ የቀጥታ ውይይት መደረግ አለበት የለበትም በሚል ነበር የተነጋገርነው፡፡ ይሄን ሀሣብ ያመጣንበት ምክንያት ደግሞ ሬድዮ ፋና ቀደም ብሎ እኔም የተሣተፍኩበት ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ ያንን ውይይት ቆራርጠው እነሱ በሚፈልጉት መንገድ ስላቀረቡት፣ እንደ ኮሚቴ ተሰብስበን ማንኛውም ውይይት ወይ በቀጥታ መተላለፍ አልያም እኛም የምንቀዳበት ሁኔታ መኖር አለበት የሚል አቋም ይዘን ነበር፡፡ በዚህ ላይ ውይይት ካደረግን በኋላ “በቃ የውይይቱ ቅጂ ይሰጣችኋል” ተባልን፡፡
በዚሁ ወደ መደበኛ ውይይት ገብተን፣ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እያደረግን ቆይተን፣ ከምሽቱ 1 ሰዓት አካባቢ እኛ ለሶላት ስንወጣ፣ እነሱ ወዲያው ለሬዲዮ ፋና መግለጫ ሰጡ። ከኮሚቴው ጋር ውይይት ተደርጎ፣ ለጥያቄዎች ምላሽ እንደተሰጠ አድርገው መግለጫ ሰጡ፡፡ እኛ ሰግደን ስንመለስ ሰው ቴክስት እያደረገ፣ “ምንድን ነው የተወሰነው?” በሚል ጥያቄ ነበር ያጣደፈን፡፡ እኛ ሶላት ላይ ስለነበርን የተባለውን አልሰማንም፡፡ መግለጫ እንደተሰጠም አላወቅንም ነበር፡፡ በወቅቱ በጣም ነው ያዘንነው፡፡ እንዴት የጋራ ድምዳሜ ላይ ሳንደርስ መግለጫ ይሰጣል? አልን፡፡ እነሱም “በቃ መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ የመጅሊስ ምርጫም በኡላማ ምክር ቤት አማካኝነት ይካሄዳል፤ ጥያቄያችሁም ተመልሷል ከእንግዲህ ስብሠባ መደረግ የለበትም” አሉን፡፡ “አወልያን በተመለከተም ካስፈለገ ቦርድ ይቋቋማል፤ ቦርዱም ከፌደራል ጉዳዮች፣ ከማህበራዊ ማደራጃ ተደርጎ ሊዋቀር ይችላል” አሉን፡፡ በወቅቱ እኛ ጥያቄያችን እንዳልተመለሰ ስንነግራቸው፣ “ቢያንስ እንኳ የአወሊያ ጉዳይ እንዴት ተመልሶልናል ብላችሁ አትቀበሉም?” አሉን፡፡ በኋላ “በቃ ምላሻችሁን በፅሁፍ ስጡን፤ እኛ ለወከልነው ህዝበ ሙስሊም ደብዳቤውን ወስደን በንባብ እንነግራለን፤ በአፍ ግን ለህዝቡ ተናገሩ የምትሉትን አንቀበልም” አልናቸው፡፡ ከዚያም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለተለያዩ የመንግስት አካላት ደብዳቤዎችን ፃፍን። በመጨረሻ መጋቢት 14 በወቅቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅ/ቤት ሃላፊ የነበሩት አቶ ሬድዋን ሁሴን ያናግሯችሁ ተብለው አነጋገሩን፡፡ እሣቸውም፤ “መንግስት ጥያቄያችሁ ምላሽ ማግኘት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ እኛ ከእናንተ የምንፈልገው በጉዳዩ ጊዜ ላይ ጊዜ አግኝተን ተነጋግረን ምላሽ እስክንሰጣችሁ ድረስ በአወሊያ የሚደረገው ነገር ለአንድ ወር እንዲቋረጥ ለህዝቡ እንድትነግሩልን ነው” አሉንና በዚሁ ተለያየን፡፡ በተቃራኒው በዚያ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ኮሚቴውን ማጥላላትና ኮሚቴው ላይ ተቃዋሚ ሰዎችን ለመፍጠር ነበር ጥረት ሲደረግ የነበረው፡፡ በኋላ አንድ ወሩ ሊገባደድ ሲል ሚያዚያ 11 ቀን 2004 የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል አባላት የሆኑ 5 ሰዎች፣ የፖሊስ አዛዥና ሌሎች ጠርተው አነጋገሩን፡፡ በማግስቱ ሚያዚያ 12 ቀን በአወሊያ ረብሻ ለማስነሣት አላማ እንዳለ፣ ይሄን ስራ ማን እንደሚሠራ መረጃው ነበረን፤ ይሄን ጉዳይ ይዘን የተመረጥን ሰዎች ልናነጋግራቸው ስንሄድ እነሱ ጭራሽ “ከእንግዲህ ለሚፈጠር ችግር ሁሉ ሃላፊነቱን ትወስዳላችሁ” ወደሚል ማስፈራራትና ዛቻ ገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ እኔ በግልፅ የተናገርኳቸው፤ “እኛ ምንም የመረበሽ አላማ እንደሌለን እናንተም ከኛ በላይ ታውቃላችሁ፤ ህዝቡም ያውቃል፤ ማንም ይሁን ማን ነገም ሆነ ከነገ በኋላ ረብሻ እንዳይኖር ለማድረግ እኛ ተዘጋጅተናል፤ ረብሻ ለመፍጠር ዝግጅት እንዳለም ጠንቅቀን እናውቃለን፤ እኛ እንዳይረበሽ ለማድረግ ሙሉ ዝግጅት አድርገናል” ስላቸው ተደናገጡና፤ “እንዴት መንግስትን በዚህ ትጠረጥራላችሁ?” አሉኝ፡፡ “እኛ ለሃገራችን ሠላም ለማስፈን እየሠራን ነው የምትሉት እውነት ከሆነ ጥሩ ነው፤ እኛ ያለን መረጃ ግን በተቃራኒው ነው” አልናቸው፡፡ በወቅቱ ተደናገጡ፡፡ በኋላ ውይይታችን ጨርሠን ስንወጣ፣ አነዋር መስጊድ ላይ የረብሻ ቅስቀሣ ወረቀት ተበተነ። እኛም አወሊያ ት/ቤት ጀርባ ባለ ጫካ የፀጥታ አካላት ተደብቀው እንዳለ መረጃ ነበረን፡፡ ይሄ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያም እንዲወጣ አደረግን፡፡
ሚያዝያ 12 ቀን መድረክ መሪው ኡስታዝ ሣቤር ይርጉ ነበር፡፡ እሱም “እንኳን በሠላም መጣችሁ፤ ጫካ ውስጥ ያላችሁትን ጨምሮ” በማለት ህዝቡ ጫካ ውስጥ እንዳሉ እንዲያውቅ አደረገ፡፡ በዚህ መልኩ በእለቱ ተደግሶ የነበረው ረብሻ ሳይፈጠር ቀረ፡፡ በኋላ በተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት ኮሚቴውን ማጉላላት፣ መፈረጅ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ ህዝብና ኮሚቴውን የመነጣጠል ሙከራዎች ቀጠሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ቀጥለን ሐምሌ 4 ቀን እኔና አቡበከር አለሙን ያዙን፤ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወስደው ለ4 ሰዓት ካሰሩን በኋላ፤ “ከአሁን በኋላ የመጅሊስ ጉዳይ፣ የሙስሊም ጥያቄ የምትሉትን ነገር የማታቆሙ ከሆነ በህይወታችሁ ፍረዱ” ብለው አስፈራርተው ለቀቁን፤ “የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ነው የሰጠናችሁ” አሉን፡፡
ሐምሌ 6 ምሽት ለሐምሌ 8 የሠደቃ ፕሮግራም አወሊያ ላይ የተዘጋጀ ዝግጅት ነበር። 40 ያህል በሬዎች ነበሩ፤ የታረደውን ስጋም ያልታረዱትን በሬዎችም ወስደው በርካታ ሰዎችን አሰሩ፡፡ ሐምሌ 7 አነዋር መስጊድ ሄጄ፣ ሰውን ለማረጋጋት፣ እኛ የያዝነው መንገድ ሠላማዊ ነው በሚል ንግግር አደረግሁ፡፡ የዚህን ቪድዮም ኢንተርኔት ላይ ዛሬም ማንኛውም ሠው መመልከት ይችላል። በማግስቱ ሐምሌ 8 ቀን እኔ፣ አቡበከር፣ ካሚል ሸምሱ፣ አህመድ ሙስጠፋ ወደ አወሊያ ስንሄድ መንገድ ላይ አንዲት ነጭ ኒሳን መኪና ከፊታችን ቀድማ መንገድ ዘጋችብን፡፡ ከዚያም ሌሎች መኪኖች ከኋላችን መጥተው ሰዎች ወርደው፤ “እንንቀሳቀሳለን ብትሉ ግንባራችሁ ነው የምንለው” ብለው ሽጉጥ ደቅነውብን፣ ነጯን መኪና እንድንከተል አዘዙን፡፡ “እናንተ እነማን ናችሁ? መታወቂያ አሣዩን” ስንላቸው፣ “ለእናንተ አይነት ሰዎች ነው መታወቂያ የምናሣየው” ብለው እኔን በቦክስ መቱኝ፤ በዚህ መልኩ አጅበውን ይዘውን ሄዱ፡፡ ልክ ሱማሌ ተራ ስንደርስ፤ “እነዚህ ሰዎች ህገ ወጦች ናቸው፤ መታወቂያም ሊያሣዩን አልፈለጉም ዝም ብለን መከተል የለብንም፤ ከቻልክ አምልጥ አልነው” ሹፌራችንን፤ ሹፌራችንም እንደ ምንም ብሎ አመለጣቸው፡፡ ከዚያም አንዋር መስጊድ ገባን፤ ፕሮግራሙም ተካሄደ፡፡ ከዚያ በኋላ 8 ሰዓት ላይ ሁላችንም የኮሚቴው አባላት ተሰብስበን አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሄደን “ትፈልጉናላችሁ ወይ?” አልናቸው፡፡ እነሡም፤ ”እኛ የምናውቀው ነገር የለም፣ አንፈልጋችሁም” አሉን፡፡ ከዚያ በኋላ የደህንነት ክትትል በዙሪያችን ይደረግ እንደነበር እናውቅ ነበር፡፡ በአራተኛው ቀን ሐምሌ 12 ቀን ጀምሮ አባላቱን ማሰር ጀመሩ ማለት ነው፡፡
መንግስት መጀመሪያ ላይ እውቅና ሰጥቷችሁ ሲያነጋግራችሁ ከቆየ በኋላ እንዴት ወደ ህገ ወጥነት ቀየራችሁ? ምክንያቱን ለመረዳት ሞክራችሁ ነበር?
ከታሠርን በኋላ የደህንነት አመራር ከነበረው ወልደስላሴ ጋር በእስር ቤት ተነጋግረን ነበር፡፡ እሱ የነገረኝ በወቅቱ መንግስት በማስፈራራትም በሌላም መንገድ እኛን ወደሚፈልገው ለመጠምዘዝ ሲሞክር ነበር፡፡ ይሄ ሃሳቡ ሊሣካለት አልቻለም፡፡ እንዳጋጣሚ ደግሞ እኛ መሀል ለኢህአዴግም ቅርብ የሆኑ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነሱ በቀላሉ ይመለሣሉ ተብሎ ተጠብቆ ነበር፤ ለማግባባትም ሙከራ ተደርጎ ነበር። እኛ ግን አስቀድመን ይሄ ሊመጣ እንደሚችል ገምተን እንቅስቃሴያችን በጥንቃቄና ግልፅነት በተሞላበት መልኩ እያካሄድን ስለነበር ለመከፋፈል አጀንዳው አልተመቸነውም፡፡ አንዴ በብሄር፣ አንዴ በፖለቲካ፣ አንዴ በእድሜ ለመከፋፈል ብዙ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ይሄ በኮሚቴው አባላት ፅናት ሊሣካ አልቻለም፡፡ ይሄ አልሣካ ሲል ህብረተሰቡ ጥያቄው ትክክል እንደሆነ፣ ኮሚቴው ግን ሌላ አላማ እንዳለው በግልፅ ወደ ማጥላላት ነው የተገባው፡፡ ይሄን ከወልደስላሴ ጋር በማረሚያ ቤት ካደረግነው ውይይት መረዳት ችያለሁ፡፡ በወቅቱ እስከ መጨረሻ የዘለቀው የኛ ግልፅ አቋም፤ “ለህዝቡ ያላችሁን ምላሽ በደብዳቤ ስጡን ወይም ከእናንተ የተወከለ ህዝቡ በተሰበሰበበት ተገኝቶ ያስረዳ” የሚል ነበር፡፡
የፍርድ ቤት ጉዳያችሁና የህዝቡ እንቅስቃሴስ ምን ይመስል ነበር?
እኛ የግል ጥያቄ ሳይሆን የህብረተሰቡን ጥያቄ ነበር የያዝነው፡፡ እኛም ከታሰርን በኋላ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝበ ሙስሊም ጥያቄውን ይዞ ሲቃወም ነበር፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል። ይሄ እስር ቤት ሆነን ያሳየን የነበረው፣ መንግስት ከህዝቡ ጥያቄ በተቃራኒ መቆሙን ነው፡፡
ህብረተሰቡ እኛ ያለመክዳታችንን አውቆ በዚያ መልኩ መንቀሳቀሱ ለሁሉም በግልፅ የታየ ነው። እኛ በማረሚያ ቤት ሆነን ይጎበኘን የነበረው በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ ነው፡፡ አስታውሳለሁ፤ አንድ ቀን የመጡ ጠያቂዎች መቶም ሃምሣ ብርም እየሰጡኝ ነበር የሚሄዱት፤ በመጨረሻ የሠጡኝን ገንዘብ ስቆጥረው 17 ሺህ ብር ነበር የሆነው፡፡ በኋላ ያንን ገንዘብ “እኔ አልፈልግም፤ ይሄ ሁሉ ህዝብ መጥቶ የጠየቀኝ የያዘኩትን አላማ ስለሚደግፍ ነው” በሚል ለማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች፣ ለማረሚያ ቤቱ የውሃ ችግር ማቃለያ ታንከር ይገዛ ዘንድ ብሰጥም ሃላፊዎቹ፤ “ለመቀበል ፍቃደኛ አይደለንም” ብለው ችግር የፈጠሩበትን ሁኔታ አስታውሣለሁ፡፡ በኛ የክስ ሂደት ምስክር ለመሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው በራሳቸው ፍቃድ የተመዘገቡት፡፡ የቀረበብን ክስም ግልፅ ነበር፡፡ አንደኛው፤ የኮሚቴው አባል መሆናችን ብቻ እንደ ሽብር ነው የተቆጠረው፣ ሌላው ቅስቀሣ ማድረግ የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ህዝብ ፊት የቀረቡ ንግግሮች ናቸው ያስከሰሱን፡፡ ስለዚህ ህዝቡ ለምስክርነት ለመቆም አልከበደውም። በአካባቢው የነበሩ ክርስቲያኖች ሳይቀሩ ነው የመከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡልኝ፡፡ ይሄ ሁሉ ማስረጃ ቀርቦ ባለበት ነው ፍ/ቤቱ ጥፋተኛ ነህ ያለኝ፡፡ ህብረተሰቡም በዚያ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረው አለኝታነቱን ለመግለፅ ነበር፡፡
በማረሚያ ቤት ታመው እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያም ተገልፆ፣ ህክምና እንዲያገኙ ቅስቀሳ ሲካሄድ ነበር፤ ህመምዎ ምን ነበር? አሁንስ የጤንነትዎ ሁኔታ?
እኔ ወደ ማረሚያ ቤት የወረድኩት ጥቅምት 19 ቀን 2005 ነው፡፡ ክስ የተመሠረተብኝ ቀን ማለት ነው፡፡ ከዚያ በፊት ማዕከላዊ ለ3 ወር ያህል ቆይቻለሁ፡፡ በጨለማ ቤት ታስሬያለሁ፤ የተለያዩ ማንገላታቶች ተፈፅመውብኛል። ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከገባሁ በኋላ ብዙ ክትትል ይካሄድብኝ ነበር። ቤተሠብ እንዳይጠይቀንም እንከለከል ነበር። ውስን የቤተሰብ አባላት ብቻ ነበሩ እንዲጠይቁን የሚደረገው፡፡ እኛን በተለየ መልኩ የመመልከት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ የኩላሊት ህመም በፀና ያመመኝ በመጋቢት 2009 ነበር፡፡ እዚያው ክሊኒክ ስሄድ ኢንፌክሽን ነው ተብዬ መድሃኒት ተሠጠኝ፤ ግን ብዙም አልተሻለኝም ነበር፡፡ በኋላ ወደ ውጪ ወጥቼም እንድታከም ስጠይቅ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ከቆየሁ በኋላ ነሐሴ 5 ቀን ነው ከማረሚያ ውጪ ህክምና ያደረግሁት። በወቅቱ ኩላሊትህ ውሃ ይዟል ነው የተባልኩት፡፡ ሪፈር ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ብባልም ያንን ተከልክያለሁ። ለ1 ወር ያህል ህክምና ማግኘት ሳልችል በህመም ስሰቃይ ነበር፡፡ ለነሐሴ 17 የተፃፈው ሪፈር መስከረም መጨረሻ አካባቢ ነው በብዙ ውጣ ውረድ ወደ ጳውሎስ የሄድኩት። ከዚያ በኋላ ነው ፌስቡክ ላይ ጉዳዬ የተነገረው። በወቅቱ እኔ በማህበራዊ ሚዲያ እንደወጣሁ አላወቅሁም ነበር፡፡ በኋላ የማረሚያ ቤቱ የክሊኒክ ሃላፊ ጠርታኝ፤ “ምን በድለንህ ነው በማህበራዊ ሚዲያ ህክምና ተከለከልኩ” ያልከው አለችኝ፡፡ እኔ በወቅቱ ምንም አላውቅም ነበር፡፡ ይሄን አስረዳኋት፤ እሷም “በቃ ማንኛውም ችግር ካለ ለኔ ንገረኝ” ብላ ስታግባባኝ ነበር። በኋላም ወደ ህክምና ስወሰድ ፎቶ ግራፍ እንዳልነሣ በጥንቃቄ ነበር፡፡ በማያሣይ መስታወት መኪና ውስጥ ተደርጌ ነበር ወደ ህክምና የምወሠደው፡፡ ህመሜ የሽንት ፊኛ ቱቦ መጥበብ የፈጠረው በመሆኑ ቱቦ ተገጥሞልኝ ነበር ለ1 ወር የቆየሁት፤ ለሶስት ለአራት ቀናት ሽንት ቤት መቀመጥ አልችልም ነበር፤ ደም ነበር የምሸናው፡፡ አሁን የተባለው ውሃ ወጥቷል፣ ቱቦውም ወጥቷል፡፡ ጤንነቴም እየተመለሰ ነው፡፡
ከእናንተ ጋር የአቶ ጁነዲን ሣዶ ባለቤትም ታስረው ነበር፤ ከእናንተ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ነበር?
ወ/ሮ ሃቢባ መሃመድ ትባላለች፡፡ ማዕከላዊ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የጁነዲን ሣዶ ባለቤት ተብላ ያየኋት እንጂ በስምም በአካልም ትውውቅ አልነበረንም፡፡ እሷ ላይ በነበረው ክስ፣ ምስክር ተብለው የመጡት ሹፌሯና አጃቢዎቿ ናቸው፡፡ የአቶ ጁነዲን እናት፤ “መስጊድ በቦታዬ ላይ ይሠራ” የሚል ኑዛዜ ማስቀመጣቸውን ተከትሎ፣ ያንን መስጊድ ለማሠራት ከሚደረግ ጥረት ጋር ተያይዞ እንደታሠሩ ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከእኛ ጋር ግን በወቅቱ አንተዋወቅም ነበር፡፡
ከሃይማኖት መምህርነትዎ ባሻገር የታሪክ ምሁርም እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ የሚፅፏቸው የታሪክ መጻህፍት ነባሩን የኢትዮጵያ የታሪክ መረዳት የሚያፈርስ ነው የሚል ትችት ይቀርብባቸዋል? በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
እንግዲህ እኛ የኢትዮጵያ ታሪክ ስንል መሆን ያለበት የኢትዮጵያን ሁሉ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ብለን የአንደኛውን ህዝብ፣ ሃይማኖት ወይም አካባቢ፣ ወይም ስልጣን ላይ ያለው አካል ታሪንክን የምናወራ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ካልን አሸናፊውም ተሸናፊውም የየራሱ ትርክት አለው፡፡ ይሄ እውቅና ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ታሪክ የሚፃፈው በአሸናፊው እንደሆነ ይታወቃል፤ ነገር ግን የተሸናፊውስ ታሪክ? ብለን መጠየቅ አለብን። የኢትዮጵያን ታሪክ ሙሉ ሊያደርግ የሚችለው የአሸናፊውንም የተሸናፊውንም ታሪክ አሟልቶ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ እስከ ዛሬ ስንሠማው፣ ስንማረው የነበረው ታሪክ የሁሉንም ብሄሮች ይወክላል ወይ? የሁሉንም ሃይማኖት ይወክላል ወይ? ብለን በንፁህ ህሊና መጠየቅ አለብን፡፡ እስከ ዛሬ በትምህርት ስርአቱ ተካትቶ የተማርናቸው ታሪኮች የነገስታቱን ነው፡፡ በወቅቱ የነበሩ ነገስታትን ፍላጎት መሠረት አድርገው ነው የተቀረጹት። ዛሬም በትምህርት የሚቀርበው ታሪክ የመንግስትን ፍላጎት ተከትሎ ነው፡፡ ለምሳሌ የሙስሊሙ ታሪክ ምን ነበር? የሚለው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንዴት ነው የቀረበው የሚለውን ማየት አለብን፡፡
እርስዎ የሚጠቀሟቸው የታሪክ ማጣቀሻዎች ምንድን ናቸው?
ታሪክ የጋራ መግባባትን በሚፈጥር መሠረት ላይ ካልቆመ መልካም አይደለም፡፡ የኔ ማጣቀሻዎች ትኩረት ሳይሠጣቸው የነበሩ ነገር ግን በትምህርት ስርአቱ ውስጥ የነበሩ መፅሐፍት፣ ሁለተኛ የሙስሊም ምሁራን በአረብኛና በተለያዩ ቋንቋዎች በየዘመናቸው የፃፏቸውን ማኑስክሪፕቶች፣ በእድሜ የገፉ ሽማግሌዎችንና የተለያዩ ምንጮችን በመጥቀስ ነው፡፡ ይሄንንም በግልፅ በመፅሐፎቼ አመላክቻለሁ፡፡ ሁሉም ያለውን ማስረጃ አምጥቶ መሃል ላይ የሚያግባባን ታሪክ ተቀምጦ በትምህርት ስርአቱ ውስጥ ተካትቶ ልጆቻችን ካልተማሩ ለወደፊት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ላይ አብዛኞቹ አለመግባባቶች ያሉት ስለ ትናንት እንጂ ስለ ዛሬ አይደለም፡፡ ይሄ መታረቅ አለበት፡፡ ትናንት ምን ሆኖ ነው ዛሬ ላይ የደረስነው የሚለውን መፈተሽና ወደ ጋራ መግባባት መምጣት አለብን። በታሪክ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር ለነጋችን መልካም ይሆናል፡፡
ከዚህ በኋላ ምን ለመስራት አቅደዋል?
እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ ኢትዮጵያን ይጠቅማል ባልኩት ነገር ሁሉ እሳተፋለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ማንንም የሰው ልጅ ይጠቅማል ባልኩት ሁሉ ከመሣተፍ ጎን ለጎን እንደ ሙስሊም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ እሣተፋለሁ። በብሄርም ጉዳይ እንደ አንድ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ፣ አስፈላጊውን ተሳትፎ አደርጋለሁ፡፡
እስከ ዛሬ በሙስሊምና እስልምና መንገድ ብቻ መታጠሬ ቀርቶ በሃገሬ ጉዳይ በማንኛውም መልኩ ከሌሎች ወገኖቼ ጋር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንዲሁም ሙስሊሙ ማህበረሰብ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጠንክሬ እሠራለሁ፡፡

 

ለ 5 ዓመታት ተቋርጦ ቆይቷል

የሕንፃ ግንባታው ለአምስት ዓመታት ተቋርጦ የቆየው የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ማርያም ቤተ መዘክር ግንባታ ለማስጀመር፣ የ160 ሚሊዮን ብር አዲስ ውል ተፈረመ፡፡
ጨረታውን በአዲስ መልክ በማውጣት፣ ባለፈው የካቲት 12 ቀን የግንባታ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ገሪማ እና አሸናፊ የሆነው ተቋራጭ ድርጅት የስምምነት ውል ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
ከድርጅቱ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ተክለ ሃይማኖት አስገዶም ጋር በመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት አዳራሽ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ “የቀድሞው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ፣ እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን በመተማመን ያስጀመሩት ይህ ታሪካዊ ቤተ መዛግብት፣ የኢትዮጵያውያን ሀብትና ንብረት ነው፤” ብለዋል፤ ለፍጻሜውም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተለይም የቤተ ክርስቲያን አካላት እያንዳንዳቸው ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አስተላለፈዋል፡፡
ቤተ መዘክሩን ለማጠናቀቅ 160 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የርእሰ አድባራት ወገዳማት አኵስም ጽዮን ሙዚየም ግንባታ፣ በሚያዝያ ወር 2003 ዓ.ም. በቤተ ክርስቲያኒቱ ቋሚ ሲኖዶስ ተወስኖ በቀድሞው ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ይፋ የተደረገ ቢኾንም፤ እስከዛሬ የግንባታው ሒደትና ወጪ አነጋጋሪ ሆኖ መዝለቁ ታውቋል፡፡
በአንድ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱ ልሳን የሆነው “ዜና ቤተ ክርስቲያን” ጋዜጣ፣ “ለግንባታው ፕሮጀክት በውጭ ምንዛሬ 8.9 ሚሊዮን ዮሮ እና 25 ሚሊዮን ዶላር፣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ደግሞ ከ200 ሚሊዮን እና ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ” ወጪዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሰ ሲሆን፣ የወጪው መጠን መለያየት በፕሮጀክቱ ላይ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች ሲያስነሣ ቆይቷል፡፡
ከአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት ለሙዚየሙ ግንባታ ርዳታ ለማሰባሰብ፣ በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ላለፉት 6 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየ ቢሆንም፤ በሙዳየ ምጽዋት የታቀደውን ያህል ገንዘብ በወቅቱ ማግኘት እንዳልቻለ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
እስከ አሁንም የተሰበሰበው ገንዘብ ከ25 ሚሊዮን ብር ያልበጠ እንደኾነ የጠቆሙት ምንጮች፤ መሠረቱ ወጥቶ የቆመው ግንባታ ከተቋረጠም አምስት ዓመት ማስቆጠሩን ጠቁመዋል፡፡ “ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁበት ብረቱ እየዛገ፣ ብሎኬቱ እየፈራረሰ ነው፣” ይላሉ ምንጮቹ፡፡
በሌላ በኩል ዩኔስኮ፣ “የሙዚየሙ ሕንፃ ዲዛይን መካነ ቅርሱን የሚሸፍን መኾን የለበትም፤” በሚል ማሻሻያ እንዲደረግበትና ግንባታውን ለማጠናቀቅ ጥቅም ላይ የሚውሉ ቁሳቁሶችም ከመካነ ቅርሱ (ሐውልቱና የጥንቱ ቤተ ክርስቲያን) መልኮች ጋር እንዲጣጣሙ ማሳሰቡን ምንጮቹ አክለዋል፡፡
በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ትብብር፣ የዲዛይኑ ማሻሻያ ተደርጎ ለዩኔስኮ ከተገለጸና ከተፈቀደ በኋላ ጨረታው ወጥቶ የግንባታው ውል እንደ አዲስ መፈረሙን አስረድተዋል፡፡ ከአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት የገንዘብ አስተዋፅኦውን የሚያስተባብረው ኮሚቴም በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እንደ አዲስ ተዋቅሮ በሥራ አስኪያጅ እንዲመራ የተደረገ ሲኾን፣ በሙዳየ ምጽዋት የሚሰበሰበው ርዳታም እንደ አድባራቱ የገቢ አቅም ወደ “ቁርጥ መዋጮ” መዞሩ ታውቋል፡፡
የ“ቁርጥ መዋጮው” ድልድል፣ በአድባራት በቂ ውይይት አልተካሔደበትም፤ ያሉት ምንጮቹ፣ ይህም የተፈለገው አስተዋፅኦ እንዳይገኝ ዕንቅፋት እንዳይሆን ስጋታቸው ገልጸዋል፤ የአድባራቱን አስተዳደር የማሳመን ተጨማሪ ሥራ እንደሚያስፈልግና ቀድሞውንም በቂ ገንዘብ ሳይያዝ በተለጠጠ በጀት ግንባታውን መጀመሩ አግባብነት የሌለው በመሆኑ ለቁጥጥርም ስለሚያዳግት ሊታረም ይገባል፤ ብለዋል፡፡

 

የአለማችን ቢሊየነሮችን የሃብት ደረጃ በማውጣት በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤ የ2018 የፈረንጆች ዓመት የአለማችንን ቀዳሚ ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን የ112 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያስመዘገቡት የአማዞን ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጄፍ ቤዞስ በቀዳሚነት ተቀምጠዋል።
ቤዞስ አምና ከነበራቸው አጠቃላይ ሃብት ዘንድሮ የ39.2 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሪ ማስመዝገባቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ በአንድ አመት ውስጥ ይህን ያህል የሃብት ጭማሪ በማስመዝገብ በታሪክ የመጀመሪያው የአለማችን ባለጠጋ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
ባለፉት 24 አመታት ውስጥ ለ18 ጊዜያት የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ሆነው የዘለቁት የማይክሮሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ዘንድሮ 90 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ይዘው ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያሉ ሲሆን የታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ መስራች ማርክ ዙክበርግ በ71 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አምስተኛው የአለማችን ቢሊየነር ሆኗል፡፡
የአመቱ የተጣራ ሃብታቸው 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ የተነገረላቸው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አምና ከነበሩበት የሃብት ደረጃ በ222 ደረጃዎች ዝቅ ብለው 766ኛ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አለማችን ዘንድሮ ከመቼውም በላይ በርካታ ቢሊየነሮችን ማፍራቷን የጠቆመው ፎርብስ፤አምና 2 ሺህ 43 የነበረው የቢሊየነሮች ቁጥር ዘንድሮ ወደ 2 ሺህ 208 ከፍ ማለቱንና የአለማችን ቢሊየነሮች ጠቅላላ ሃብት ድምር አምና ከነበረበት የ7.7 ትሪሊዮን ዶላር ጭማሪ በማድረግ ዘንድሮ 9.1 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ገልጧል፡፡
ከሙስና ጋር በተያያዘ ባለሃብቶቿን ስታስር የከረመቺውን የሳኡዲ አረቢያ ባለሃብቶች በዘንድሮው የባለጠጎች መዝገብ ውስጥ አለማካተቱን ያስታወቀው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፤ ባለፈው አመት በዝርዝሩ ውስጥ ተካትተው የነበሩ 10 የሳኡዲ ቢሊየነሮችን ስም ከዝርዝሩ መፋቁን አመልክቷል፡፡
ከሳኡዲ የሙስና ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከፎርብስ ዝርዝር ውስጥ ከተፋቁት ባለጠጎች መካከል አምና 18.7 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት የነበራቸው ልኡል አልዋሊድ ቢን ታላል እና 8.1 ቢሊዮን ዶላር የነበራቸው ሼክ ሙሀመድ ሁሴን አል አሙዲን ይገኙበታል፡፡

 

እንግሊዝ ናይጀሪያውያን እስረኞችን ወደ አገራቸው ልካ የእስር ጊዜያቸውን እንዲጨርሱ ለማድረግ፣በአገሪቱ ግዙፍ ወህኒ ቤት የምታስገነባበት 700 ሺህ ፓውንድ ያህል በጀት መያዟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ እንግሊዝ ኪሪኪሪ በሚባለውና በሌጎስ የሚገኘውን የናይጀሪያ ትልቁን ወህኒ ቤት ለማስፋፋት ማቀዷን የጠቆመው ዘገባው፤ ሁለቱ አገራት ከ4 አመታት በፊት በፈጸሙት እስረኞችን አሳልፎ የመስጠት ስምምነት መሰረት እስረኞች ወደ አገራቸው ገብተው እንዲታሰሩ የማድረግ ሃሳብ መያዙንም አመልክቷል፡፡
በ2016 የፈረንጆች አመት ብቻ 320 ናይጀሪያውያን በተለያዩ የወንጀል ክሶች ቅጣት ተጥሎባቸው በእንግሊዝ በሚገኙ የተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ የእስር ጊዜያቸውን በማሳለፍ ላይ እንደነበሩ የጠቆመው ዘገባው፤ በእንግሊዝ ከሚገኙ የሌሎች አገራት እስረኞች ናይጀሪያውያን 3 በመቶውን እንደሚሸፍኑም አስታውሷል፡፡

ከአመታት በፊት በአለማችን የስማርት ፎን ገበያ ከቀዳሚዎች ተርታ ይሰለፍ የነበረው የአሜሪካው ኩባንያ ብላክቤሪ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎቼን የቅጂ መብት በመጣስ ተጠቅሞብኛል ሲል በታዋቂው የማህበራዊ ድረገጽ ኩባንያ በፌስቡክ ላይ ክስ መመስረቱ ተነግሯል፡፡
ፌስቡክ ፈጠራዎቼን በመስረቅ በዋትሳፕና በኢንስታግራም አፕሊኬሽኖቹ ላይ ተጠቅሞብኛል ሲል ክስ የመሰረተው ብላክቤሪ፤ከአመታት በፊት አብረን ልንሰራ ተስማምተን ነበር፣ ውሉን አፍርሶ ፈጠራዎቼን ተጠቅሞብኛል ብሏል- ቢቢሲ እንደ ዘገበው፡፡
ብላክቤሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሽያጩ እየቀነሰና ተወዳዳሪነቱና ተወዳጅነቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከ2 አመታት በፊት ስማርት ፎን ማምረት ማቆሙን የጠቆመው ዘገባው፤ባለፈው አመትም በኖክያ ላይ ተመሳሳይ የቅጂ መብት ጥሰት ክስ መስርቶ እንደነበር አስታውሷል፡፡

አንድ በወታደሮች ካምፕ የመዝናኛ ክበብ ዙሪያ የተፃፈ ሐተታ የሚከተለውን ቀልድ ነጥቧል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን በአንድ የመኮንኖች ክበብ ውስጥ ከተራ ወታደር እስከ ጄኔራሎች ድረስ እየተዝናኑ ሳሉ፣ የዕንቆቅልሽ መሰል ጥያቄና መልስ ተጀመረ፡፡
የጨዋታ መሪው፤
“ለመሆኑ ወሲብ (የአልጋ ላይ ግንኙነት) ስንት ፐርሰንቱ ፍቅር ነው? ስንት ፐርሰንቱስ ሥራ ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
መኮንኖቹ እንደየ ማዕረግ ደረጃቸው ይመልሱ ጀመር፡-
ጄኔራሉ:- “ዘጠና ከመቶው ፍቅር፣ አሥር ከመቶው ሥራ ነው” አሉ፡፡
ኮሎኔሉ፡- “በእኔ ግምት ሰማኒያ ከመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሃያ ከመቶው ሥራ ነው፡፡” አሉ፡፡
ሻለቃው ቀጠሉ፡- “ለእኔ እንደሚሰማኝ ደግሞ ወሲብ ሰላሳ በመቶው ሥራ፤ ሰባ በመቶው ፍቅር ነው”
ሻምበሉ ደግሞ፤
“እኔ በበኩሌ አርባ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ፡፡ ስልሳ በመቶው ግን ፍቅር ነው፡፡”
መቶ አለቃው ጥቂት ስሌት ሠርተው፤
“እኔ ደግሞ ወሲብ ሃምሳ በመቶው ፍቅር፣ ሃምሳ በመቶው ሥራ ነው እላለሁ”
አለ፡፡
ሃምሳ አለቃው ተነሳና፣
“የእኔ ከሁላችሁም ይለያል፡፡ ወሲብ አርባ በመቶው ፍቅር፤ ስልሳ በመቶው ሥራ ነው” አለ፡፡
አሥር አለቃው፤
“ሰላሳ በመቶው ፍቅር ነው፡፡ ሰባ በመቶ ደግሞ ሥራ ነው” አለ፡፡
ይሄኔ ተራ ወታደሩ እጁን አወጣ፡፡
ዕድል ተሰጠው፡፡
“እኔ ከሁላችሁም አልስማማም፤ ለእኔ ወሲብ መቶ በመቶ ፍቅር ነው” አለ፡፡
ጄኔራሉም፣ ኮሎኔሉም፣ ሻለቃውም አጉረመረሙ፡፡
“እኮ ምክንያትህን አስረዳና?” አሉት፡፡
ተራ ወታደሩም፤
“ጌቶቼ፤ ወሲብ ሥራ ቢኖርበት ኖሮ ለእኛ ትተውልን ነበር!”
* * *
አስተሳሰባችን የልምዳችን፣ የትምህርታችን የተፈጥሮአችን ተገዢ ነው፡፡ ልምዳችን የቅርብ የሩቁን የማስተዋልና በትውስታችን ቋት ውስጥ የማኖር ውጤት መዳፍ ሥር ያለ ነው፡፡ ትምህርታችን ትምህርት የሚሆነው ወደ ዕውቀት መለወጥ ሲጀመር ነው! ዕውቀታችን ወደ የብልህ-ጥበብ (wisdom) የሚለወጠው አንድም በዕድሜ፣ አንድም የሚዛናዊ አመለካከት ባለቤት ስንሆን ነው! ሚዛናዊነት የጎረኝነት (Positionality) ተቃራኒ ነው፡፡ የወገናዊነት ፀር ነው! ወገናዊነት የኢ-ፍትሐዊነት መቆፍቆፊያ ሰንኮፍ ነው፡፡ ኢ-ፍትሐዊነት ከማናቸውም ህገ-ወጥ ድርጊት ጋር፤ አንዱን-ሲነኩት-ሌላው ይወድቃል ዓይነት ግንኙነት አለው፡፡ (Domino-effect እንደሚባለው፡፡) ለችግሮች የምንሰጠው አጣዳፊ መፍትሔዎች ወዴት ያደርሱናል? ብሎ መጠየቅ ትልቅ መላ ነው፡፡ “የፊተኛውን ባልሽን በምን ቀበርሽው- በሻሽ፤ ለምን- የኋላኛው እንዳይሸሽ” የሚለውን ማውጠንጠን አለብን፡፡ በየለውጡ ውስጥ የአንድ የአገራችንን ገጣሚ ስንኞች ሥራዬ ብሎ ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡-
“ዘመንና ዘመን እየተባረረ
ከምሮ እየናደ፣ ንዶ እየከመረ
ይሄው ጅምሩ አልቆ፣ ማለቂያው ጀመረ
ጀመረ”
መውጫ መውረጂያችን በሥጋት የታጠረ ከሆነ፤ ከመረጋጋት ጋር እንራራቃለን፡፡ ያለ ሥጋት የምንጓዘው ለህሊናችን ታማኝ የሆንን እንደሆነ ነው! በስሜታዊነት ምንም ዓይነት ድርጊት መፈፀም የለብንም፡፡ ፅንፈኛ ሆነንም ማሰብ የለብንም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን አሉታዊነትን
(Negativism) በፍፁምነት ማስወገድ አለብን፡፡ ለረዥም ጊዜ ሰቅዞ የያዘንን ሁሉ፣ በተቃውሞ በጋራ ከመጠርነፍ ዕምነት የግድ መላቀቅ ይኖርብናል፡፡ ነጋዴውን ሌባ ነው ብሎ አስቦ መጀመር፣ ባለሙያውን ከእኛ ጋር ካልሆነ ባለሙያ አይደለም ብሎ ማሰብ፣ ሰውን አላግባብ መፈረጅ፤ የእኔ ቦይ ውስጥ ካልፈሰስ የተሳሳተ ሰው ነው ብሎ መገምገም… እኒህና እኒህን መሰል አካሄዶች ሁሉ ከፀፀት አያፋቱንም!
ዛሬም ነገረ-ሥራችንን እንመርምር፡፡ ማህበረሰብ ለአመክንዮ እንጂ ለመላምት/ለግምት መጋለጡ ደግ አይደለም፡፡ ግለሰባዊ፣ ተቋማዊ አሊያም ፓርቲያዊ ግልፅነት (Transparency) ወደድንም ጠላንም አስፈላጊ ነው! አለበለዚያ ዳፍንተኝነት (Obscurantism) ይወርረናል፡፡ ህብረተሰብ የሀገሪቱ አካሄድ ውሉ እንዳይጠፋበት ማድረግ ያለበት አመራሩ ነው፡፡ አመራር ተመሪውን አይከተልም፡፡ ያ ከሆነ ጭራዊ እንቅስቃሴ ወይም የድሃራይ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገባል- Tailist movement እንዲል መጽሐፍ፡፡ ደራሲ በተደራሲ ከተመራ፣ ገጣሚው በአጨብጫቢ-ታዳሚ ከተመራ፣ ዋናው ባለሙያ በበታቹ ተፅዕኖ ውስጥ ከወደቀ፣ መሪው በተመሪው እጅ ከተያዘ የመንተብ- decadence አንድ ድረጃ ነው! ከዚህ ተከትሎ ምርጫ ማጣት ይመጣል፡፡ የሚፈልገው ነገር ሁሉ ጭጋግ ውስጥ ይወድቅና አጥርቶ ማየት ይሳነናል፡፡ የቱን ልያዝ ዓይነት ድንግዝግዝ ውስጥ እንጨፈቃለን፡፡
ያኔ ነው እንግዲህ “ከሞትና ከህይወት የቱ ይሻልሃል?” ቢባል ሲያስብ ዘገየ፤ የሚለው ተረት ጎልቶ የሚነበበው! ከዚህ ይሰውረን!!

 

በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አስተያየት በመስጠትና የሰሉ ሂሳዊ ጽሁፎችን በማቅረብ የሚታወቁት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ መምህር የሆኑት አቶ ስዩም ተሾመ ሰሞኑን መታሰራቸው ታውቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲ መምህሩና ጦማሪው አቶ ስዩም ተሾመ የመታሰራቸው ጉዳይ ከትናንት በስቲያ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተነገረ ሲሆን ስለ ሁኔታው ለማወቅ ወደ ቅርብ ወዳጃቸው በመደወል መታሰራቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ ስዩም ተሾመ፤ ሐሙስ ጠዋት 4 ሰዓት ገደማ ወሊሶ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች መወሰዳቸው የታወቀ ሲሆን ምንጮች በኮማንድ ፖስቱ ሳይታሰሩ እንዳልቀረ ቢገምቱም ለማረጋገጥ ግን አልተቻለም፡፡
በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችቶችን በድፍረት በመሰንዘር የሚታወቁት የዩኒቨርሲቲ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ፤በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ከአገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ጋር በተያያዘ ትንተናዎችና የመፍትሄ ሃሳቦች በመስጠት ትኩረት ስበው ቆይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ 2025 ለማሳካት ለያዘችው ሁሉንም ዜጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ የማድረግ እቅድ የሚውል የ375 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከዓለም ባንክ ማግኘቷ ታውቋል፡፡
ከዓለም ባንክ ሰሞኑን የተገኘው የገንዘብ ብድር በተለይ በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ ለአንድ ሚሊዮን የገጠር ነዋሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ለተያዘው እቅድ አጋዥ ይሆናል ተብሏል። በአጠቃላይ የ5 ዓመቱ ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚጠይቅም ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል የማምረት አቅም እንዳላት በመግለጫው የተጠቆመ ሲሆን ፕሮጀክቱም በቁርጠኝነት ከተሰራ ስኬታማ ይሆናል ተብሏል፡፡
ሀገሪቱ ካላት ሃይድሮ ኤሌክትሪክ አቅም ባሻገር ከፀሐይ፣ ከንፋስና ከጂኦተርሚናል ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም እንዳላት የዓለም ባንክ ሪፖርት ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት 10 ዓመታት ውጤታማ የኤሌክትሪክ ማዳረስ ፕሮግራም ዘርግቶ በሀገሪቱ የሚገኙ ከተሞችንና መንደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል- በመግለጫው፡፡

ከግንባር ቀደም ዓለም አቀፍ ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች አንዱ የሆነው ዎርልድ ሬሚት፣ ኒውዮርክ የሚገኙ 9 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በፈጣንና ዝቅተኛ ዋጋ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲልኩ ማድረጉን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ፣ ጊዜ ውድ በሆነበት የአሜሪካ (የውጭ አገር) ኑሮ፣ ደንበኞች ወደ አንድ ተቋም (ባንክ ወይም ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች) በአካል መሄድ ሳይኖርባቸው በማንኛውም ቦታና ሰዓት፣ የድርጅቱን ድረ - ገፅ ወይም ሞባይል ስልካቸውን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ ይችላሉ ብሏል፡፡
ዎርልድ ሬሚት በኒውዮርክ ግዛት የሚኖሩትን ጨምሮ ከ50 በላይ በሚሆኑ አገራት የሚኖሩና የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዜቶች የሚልኩትን ገንዘብ፣ እዚህ ያሉ ገንዘቡ የተላከላቸው ሰዎች በመላ አገሪቷ ከሚገኙ የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ቅርንጫፎች እንዲወስዱ ከባንኩ ጋር መዋዋሉን ገልጿል፡፡
የገንዘብ አስተላላፊው ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ኃላፊ ሻሮን ኪንያንጁይ፣ በዎርልድ ሬሚት በኩል ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች ከፍተኛ ዕድገት እያሳዩ መሆኑን መመልከታቸውን ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎችም ሆኑ ተቀባዮቹ ከዎርልድ ሬሚት ጥራት ያለው አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ማረጋገጣችንን እንቀጥላለን፡፡ ኒውዩርክን ያካተተ አገልግሎት መጀመርና የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ወደ መረባችን መግባት ወደ ኢትዮጵያ ሃዋላ ለሚልኩ ሰዎች መልካም ዜና ነው ብለዋል፡፡
በወጣት ሶማሊያዊ ኢንተርፕረነር እስማኤል አህመድ እ.ኤ.አ በ2010 የተመሰረተው ዎርልድ ሬሚት ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ መላክ የጀመረው በተመሰረተ በዓመቱ በ2011 እንደሆነ የጠቀሰው መግለጫው፣ ኒውዮርክ በመጨመሩ አሜሪካ የዎርልድ ሬሚት ትልቁ የገንዘብ መላኪያ ገበያ እንደምትሆንና ኩባንያው በ2017 ከአሜሪካ የሚላከው ገንዘብ 200 ፐርሰንት ዕድገት ማሳቱን አመልክቷል፡፡ ዎርልድ ሬሚት ከFacebook, spotify, Netfliy እና Slack እንዲሁም ቀዳሚ ኢንቨስተሮች ከሆኑት Accel እና TCV 200 ሚሊዮን ዶላር ማግነቱን ገልጿል፡፡ ዋና መ/ቤቱ በለንደን ሲሆን የአሜሪካ ዋና መ/ቤት በዴንቨር፣ ክልላዊ ቢሮዎች ደግሞ በካናዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በፊሊፕንስ፣ በጃፓን፣ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ እንዳሉት መግለጫው አመልክቷል፡፡