Administrator

Administrator

የታላቁ ገጣሚና ፀሐፌ-ተውኔት ደበበ ሠይፉን ‹‹የብርሃን ፍቅር (ለራስ የተፃፈ ደብዳቤ )›› በድጋሚ ማሳተሙን የገለጸው ሐሳብ አሳታሚ፤ከነገ ወዲያ ሰኞ በ10፡30 በተለያዩ የጥበብ መሰናዶ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ ያስመርቃል፡፡ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ በደበበ ሠይፉ ስራዎች ላይ ዳሰሳዊ ቅኝት የሚያቀርብ ሲሆን በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚከትባቸው ጥበባዊ ጽሁፎቹ የሚታወቀው ተፈሪ መኮንን፣ ስለ ደበበ ሠይፉ መምህርነት፤ ተዋናይ ተፈሪ አለሙ፣ ስለ ፀሐፌ-ተውኔት ደበበ ሠይፉ፤እንዲሁም ገጣሚ ታገል ሰይፉ ስለ ደበበ ሠይፉ አንዳንድ ትዝታዎች እንደሚያወጉ ታውቋል። አንጋፋና ወጣት ገጣሚያንም ስራዎቻቸውን ለታዳሚው ያቀርባሉ፡፡ የሥነጽሁፍ ወዳጆች በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ እንዲገኙ ሐሳብ አሳታሚ ጋብዟል፡፡  

በታደሰ ፀጋ ወ/ስላሴ የተፃፈውና “የመናፍስቱ መንደር” የተሰኘው መፅሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መፅሀፉ በዋናነት በአይን የማይስተዋሉ ስውራን መናፍስትንና የሰዎችን ዘመናት ያስቆጠረ ህቡዕ እንቅስቃሴ አሻራን በስፋት ያስቃኛል ተብሏል። በሰንሰለታማው የሰሜን ተራሮች የሰፈሩ ጥንታዊ ህዝቦች ስልጣኔ፣ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርስ እንዲሁም ያልተነገሩ ድብቅ ታሪኮችም በመጽሐፉ ተዳስሷል። በ10 ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ275 ገጾች የተቀነበበው መፅሐፉ፤በ77 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ መጽሐፉን የሚያከፋፍለው እነሆ መፅሐፍ መደብር እንደሆነ ታውቋል፡፡  

በደራሲ እንዳልካቸው ወሰን የተፃፈውና “ያልበራ ብርሐን” የተሰኘው መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
 ዓመተ ፍዳ አልፎ አመተ ምህረት መምጣቱንና በአሁኑ ወቅት የሰው ልጅ አዕምሮ የሚፈጥራቸውና የሚገልፃቸው በርካታ ምስጢራት፣ ዘመኑን ከዓመተ ምህረት ወደ “ዓመተ ግልፀት” ለውጦታል ይላል - ደራሲው በመጽሐፉ፡፡ ይህ ግን የግል አስተሳሰቡ መሆኑን አልሸሸገም፡፡
በ118 ገጾች የተመጠነው  መፅሐፉ፤በ40 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡  

ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደውና ለሀገራቸውና ለወገናቸው ላቅ ያለ አገልግሎት የሰጡ ዜጎች የሚከበሩበት የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት ሥነሥርዓት ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አበባ አቤል ሲኒማ ይከናወናል፡፡
በ10 ዘርፎች ለ2008 የዓመቱ በጎ ሰው ሽልማት መብቃት አለባቸው የተባሉ ዜጎች በሕዝቡ የተጠቀሙ ሲሆን በየዘርፉ ከተጠቆሙት ዜጎች መካከልም ሥራዎቻቸው ተመዝነው በሽልማት ኮሚቴው አማካኝነት ሦስት ሦስት ዕጩዎች ተለይተዋል፡፡
በእነዚህ እጩዎች ላይ አምስት አምስት ዳኞች (በየዘርፉ) ድምጽ እየሰጡ መሆኑ የታወቀ ሲሆን የየዘርፉ ተሸላሚዎችም ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በሚኖረው ሥነ ሥርዓት ይታወቃሉ ተብሏል። ሚዲያዎችና ሌሎች የመገናኛ አካላት፣እጩዎችን በማስተዋወቅና በማክበር፣ ለሀገራቸው በጎ የሚሠሩ ዜጎችን ለማብዛት የበኩላቸውን እንዲወጡ የበጎ ሰው ሽልማት ኮሚቴ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በታች እጩዎቹ በየዘርፋቸው ቀርበዋል፡፡
መምህርነት
ተ/ ፕሮፌሰር ዘሪሁን አስፋው
ተ/ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
መ/ር አውራሪስ ተገኝ
ንግድና ሥራ ፈጠራ
አቶ ብዙአየሁ ታደለ
አቶ ሳሙኤል ታፈሰ
አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ
ማኅበራዊ ጥናት
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ
ዶክተር አንዳርጋቸው ጥሩነህ
ፕሮፌሰር ባየ ይማም
ሳይንስ
ሎሬት ዶክተር መላኩ ወረደ
ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ
ዶክተር ውዱ ዓለማየሁ
ቅርስና ባሕል
የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም (አዲስ አበባ     
           ዩኒቨርሲቲ)
ኢንጅነር ታደለ ብጡል
መ/ር ካሕሳይ ገብረ እግዚአብሔር
መንግሥታዊ የሥራ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት
ኢንጅነር ዘውዴ ተክሉ
ዶክተር ተወልደ ብርሃን
          ገብረእግዚአብሔር
ዳኛ ስንታየሁ ዘለቀ
ስፖርት
አቶ ጌቱ በቀለ
ጋቶች ፓኖ
ዶክተር ይልማ በርታ
ኪነጥበብ (ድርሰት)
አቶ አስፋው ዳምጤ
ወ/ሮ ፀሐይ መላኩ
አቶ አውግቸው ተረፈ
ሚዲያና ጋዜጠኛነት
መንሱር አብዱልቀኒ
አቶ አጥናፍሰገድ ይልማ
አቶ ደረጀ ኃይሌ
በጎ አድራጎት
ዶክተር ቦጋለች ገብሬ
ወ/ሮ ፀሐይ ሮቺሊ
ወ/ሮ ዘውዲቱ መሸሻ

ቶታል ኢትዮጵያ ከኤም ብር ጋር በመተባበር አዲስ የተቀላጠፈ የሞባይል ክፍያ አሰራር መተግበር የጀመረ ሲሆን ደንበኞች ካሉበት ሆነው የድርጅቱን አጠቃላይ አገልግሎቶች በተመለከተ የተሟላ መረጃ የሚያገኙበት “ቶታል ሰርቪስስ” የተባለ አዲስ የሞባይል ስልክ አፕሊኬሽንም አስመርቋል፡፡
የቶታል ኢትዮጵያ የሽያጭና የማርኬቲንግ ስራ አስኪያጅ ክሪስቶፊ ፌራንድ ባለፈው ረቡዕ በተከናወነው የምረቃ ስነስርዓት ላይ እንዳሉት፣የሞባይል ክፍያ አሰራሩ የኩባንያው ደንበኞች በማንኛውም ጊዜ የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም፣ ገንዘብ መላክ፣ የሞባይል ካርድ መግዛት፣ ገንዘብ ማስቀመጥ ወይም ማውጣትና መገበያየት የሚችሉበት ነው፡፡
የኩባንያው ደንበኞች በተመረጡ የቶታል ማደያዎች ይህን አስተማማኝ፣ ጊዜ ቆጣቢና ቀልጣፋ የሞባይል ክፍያ ዘዴ በመጠቀም ነዳጅ መግዛት፣ መኪና ማሳጠብ፣ የመኪና ዘይት መግዛት፣ የሱፐር ማርኬትና የካፌ አገልግሎቶችን መጠቀም ወዘተ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤በቅርቡም ይህን አገልግሎት በሁሉም የቶታል ማደያዎች ለማስጀመር እየተሰራ እንደሚገን አስታውቀዋል። ቶታል ኢትዮጵያ ከዚህ በተጨማሪም ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት በማሰብ፣ ደንበኞች ካሉበት ሆነው የሞባይል ስልኮቻቸውን በመጠቀም የድርጅቱን አገልግሎቶች በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን ቶታል ሰርቪስስ የተባለ አዲስ የሞባይል ስልክ አፕሊኬሽን አስመርቋል፡፡  
አዲሱ የሞባይል አፕሊኬሽን፣ የቶታል ኢትዮጵያ ደንበኞች ባሉበት ሆነው በስልኮቻቸው አማካይነት ያለ ውጣ ውረድ በአቅራቢያቸው  የሚገኘውን የቶታል ማደያ ለማወቅና የሚሰጡ አገልግሎቶችን የተመለከቱ መረጃዎችን ለማግኘት የሚችሉበት ነው፡፡ ደንበኞች አዲሱን የቶታል ሰርቪስስ የሞባይል አፕሊኬሽን፣ ከጎግል ስቶር ላይ ማውረድ እንደሚችሉ በመጠቆም፣ ቶታል ኢትዩጵያ ለደንበኞቹ ያለውን ተደራሽነት ለማሳደግ ትኩረት በመስጠት በፀሐይ ብርሀን የሚሠሩ መብራቶች በማደያው እንዲሁም በህዳሴ ሱቆች ላይ ማቅረቡንም አስታውሰዋል፡፡
ኤምብር በአገሪቱ የሚገኙ አምስት ታላላቅ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን በማቀፍ የጀመረውን ዘርፈ ብዙ የሞባይል የፋይናንስ አገልግሎት በማስፋፋትና የደንበኞቹን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በማሳደግ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎቱን በስፋት እየሰጠ እንደሚገኝም በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገልጧል፡፡

 - ያለቅጥ ወፍራችኋል፤ ሸንቀጥ እስክትሉ ህዝብ ፊት አትቀርቡም ተብለዋል
   የግብጽ መንግስት የብሮድካስቲንግ ተቋም የሆነው “ኢርቱ”፤8 ሴት የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኞችን “ያለቅጥ ወፍራችኋል፣ የምትመገቡትን ምግብ መጠን ቀንሳችሁ እስክትከሱና ሸንቀጥ እስክትሉ ድረስ ከህዝብ ፊት አትቀርቡም” በሚል ለአንድ ወር ያህል ጊዜ ከስራ ማገዱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
“ዘ ኢጂፕሺያን ሬዲዮ ኤንድ ቴሌቪዥን ዩኒየን” የተባለው ተቋም ይሄን አስቀያሚ ውፍረታችሁን ይዛችሁ ከተመልካች ፊት አትቀርቡም በሚል በጋዜጠኞቹ ላይ የወሰደው ከስራ የማገድ እርምጃ፣የሴቶች መብቶች ተከራካሪ ቡድኖችን ማስቆጣቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
“ዘ ውሜንስ ሴንተር ፎር ጋይዳንስ ኤንድ ሌጋል አዌርነስ” የተባለው የአገሪቱ የሴቶች መብት ተከራካሪ ቡድን፣ ውሳኔው ህገ-መንግስትን የሚጥስና በግብጻውያን ሴቶች ላይ የተቃጣ ጾታዊ ጥቃት ነው ሲል ተቃውሞውን በማሰማት ውሳኔው እንዲሻር ጥያቄ ማቅረቡን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ተቋም ግን ውሳኔው በምንም አይነት መንገድ እንደማይሻር ማስታወቁን ቬቶ ኒውስ የተባለው የግብጽ ድረገጽ የዘገበ ሲሆን፣ የአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች በጉዳዩ ዙሪያ እየተከራከሩ እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡

   በቅርቡ ከተቃጣበት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር በተያያዘ ከ26 ሺህ በላይ ዜጎችን ያሰረው የቱርክ መንግስት፣ ባጋጠመው የእስር ቤቶች መጨናነቅ ሳቢያ፣ ከመፈንቅለ መንግስቱ ጋር ባልተያያዙ ወንጀሎች የታሰሩ ነባር 38 ሺህ ያህል እስረኞችን ሰሞኑን እንደሚፈታ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ጣይብ ኤርዶጋንን ከስልጣን ለማስወገድ የተካሄደው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎቹን እያፈሰ ወደ እስር ቤቶች ማጋዙ በእስር ቤቶች ላይ ከፍተኛ መጨናነቅ መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፤የአገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር በኪር ቦዝዳግ፣ ችግሩን ለመፍታት በማሰብ 38 ሺህ እስረኞችን ለመፍታት መወሰናቸውን እንዳስታወቁ ገልጧል፡፡በተለያዩ የወንጀል ክሶች ተጠርጥረው የታሰሩት እነዚህ 38 ሺህ እስረኞች ከእስር ይለቀቁ እንጂ ምህረት አልተደረገላቸውም ያሉት ሚኒስትሩ፤ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተመርምሮ ተገቢው ቅጣት እንደሚጣልባቸው ማስታወቃቸውን ዘገባው አስረድቷል፡፡

ለአመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየችው የመን በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ በደረሰ ውድመትና በኢኮኖሚ ድቀት ሳቢያ በድምሩ 14 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደደረሰባት ሮይተርስ ዘገበ፡፡
በየመን ላለፉት 16 ወራት በዘለቀው የእርስ በእርስ ጦርነት ከ6 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንና ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ማፈናቀሉን የሚጠቁም ይፋ ያልሆነ ሪፖርት ማግኘቱን ያስታወቀው ሮይተርስ፤ከግማሽ በላይ የሚሆነው ህዝቧም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጠቂ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በአገሪቱ የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ በርካታ መሰረተ ልማቶች መውደማቸውንና የኢኮኖሚ ድቀት መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤በአገሪቱ የሚገኙ 1 ሺህ 671 ትምህርት ቤቶች መውደማቸውንና ውድመቱ 269 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት አስረድቷል፡፡
የህክምና አገልግሎት ሲሰጡ ከነበሩ የአገሪቱ 3 ሺህ 652 ተቋማት መካከል 900 ያህሉ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን የገለጸው ዘገባው፤በዚህም 2.6 ሚሊዮን የአገሪቱ ህጻናት ለበሽታ የመጋለጥ አደጋ ላይ መውደቃቸውን አስረድቷል፡፡

    ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጌታውን ወደ ጦር ሜዳ የሚወስድ ፈረስ ነበረ፡፡ ከጊዜ በኋላ ፈረሱ ማርጀቱ እየተሰማው መጣ፡፡ ፈረሱ በራሱ ጊዜ ለጌታው ማገልገሉን ትቶ የወፍጮ ቤት አገልጋይ ብሆን፤ ምናለበት ብሎ አሰበና ወደ ወፍጮ ቤት ለመቀጠር ሄደ፡፡ ባለወፍጮ ቤቶቹ፤ ‹‹ወደዚህ ለምን መጣህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ ፈረሱም፤ ‹‹እድሜዬ አረጀ፤ ቀጣዩን ዕድሜዬን የአሁኑን ማንነቴን ማረጋገጫ ማድረግ አለብኝ፤ ራሴን፣ የትላንት ማንነቴን ማረጋገጥ ማለትም፤ ይሄ ነው፡፡ ለፈረሱ፤ የወፍጮ ቤቱ ሕይወት እምብዛም ማራኪ አልሆነለትም፡፡ እንደ ከበሮው ምቱን ማጣጣም አልቻለም፡፡ ይልቁንም እያንዳንዷን እህል ለማድቀቅ፣ የእሱ የባርነት ጉልበት አስፈላጊ ሆነ፡፡ ኩራት ቀረ፡፡ ያም ሆኖ የዚህን ሥራውን ክብደት መሠረት አድርጎ፣ የበቆሎ መፍጨት ሥራውን መቀጠል ግድ ሆነበት፡፡ ‹‹ያገለገለ ፈረስ ሁሉ ወፍጮ ቤት እንዲሄድ አይመከርም!›› ይላሉ አዋቂዎች፡፡ ፈረሱ ግን ይሄ ፍልስፍና አልተዋጠለትም፡፡ ይህን ከባድ ሥራ ብሎ በወጉ ያስተዋለው ይህ ጉልበተኛ ፈረስ፤ ‹‹ጌታዬ! ከዕለታት አንድ ቀን፤ እኔ በጦርነት ቦታ ስመ ጥር አርበኛ ነበርኩ፡፡ ሴት ወንዱ እኔን ለማየት ከየቤቱ ወጥቶ አድናቆቱን ሲገልጥልኝ ከርሟል፡፡ የዛሬው የእኔ ቅርፅና መልክ ከዱሮው
በጣም የተለየ ሆኗል! ጦር ሜዳውን ትቼ ወደ ወፍጮ ቤት መምጣቴ ዛሬ በጣም ፀፅቶኛል፡፡አለው፡፡ባለ ወፍጮ ቤቱም እንዲህ አለው፤ ‹‹ስለትላንት መፀፀት ምንም ፋይዳ የለውም፡፡ ንብረትና ባለፀግነት፤ አያሌ ላይና ታች፣ ክፉ የጥረት ውጣ-ወረድ፣ በእጅህ ሊኖር ግድ ነው! መጠንቀቅ የራሳችን ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር እንዳመጣጡ እንቀበለው፡፡ አንድ ወቅት ፈረሰኛ ነበርክ፤ አሁን ወፍጮ አስፈጪ ሆነሃል፡፡ ነገ ምን እንደምትሆን አይታወቅም፡፡ ሆኖም ነገንም በሰላም ለመቀበል ዝግጁ ሁን›› አለው፡፡

    …
የአገራችን ሁኔታ ወደድንም፣ ጠላንም አሳሳቢ ነው! ነገ ምንም ይምጣ ምን ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን፡፡ ቀውጥ እና ነውጥ ነገ የዕለት ሁኔታ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹ኃይል ሁልጊዜ አያበላም››፤ ይላሉ አበው፡፡ ምክንያቱም ውሎ አድሮ ኃይል የለሹ ኃይለኛ ሊሆን ይችላልና ነው፡፡ ሰላም ያለ ተግባር ግልፅ አይደለም - አይገባም፡፡ ሰላምን ለማምጣት ሰላም- ለሚያሳጡ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ግዴታ ነው፡፡ ጥንት የመንግሥት ለውጥ በተደረገ ማግሥት፤ አንድ መሰረታዊ ነገር በሃገሪቱ መሪ ተነግሮ ነበር፡፡ ‹‹ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር አንዲት ጥይት አትጮህም›› ተብሎ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲያ የተከተለው ነገር ሁሉ ግን፤ ግምቱንና ትንበያውን ያስተባበለ ነው፡፡ በከፊል ከማህበረሰቡ፣ በከፊል ደግሞ ከመንግስት በመነጨ ግጭት፤ ‹‹የአንድ ጥይት- አይጮህም›› ፅንሰ- ሃሳብ እንደ ከሸፈ ጥይት መሆኑ በይፋ ታይቷል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ፤ ሀሳብን መግለፅ መታቀቡ የልብን መናገር አለመቻሉ፤ ለአንድ ሀገር ፍፁም አደጋ ነው። ‹‹ተናግሮ የትም አይደርስም›› ከሚል አምባገነናዊ ዕብሪት፤ እስከ  ‹‹እኔ እያወኩለት ምን ነገር ያስባዝተዋል›› እስከሚል ክልከላ ድረስ፤ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መንሰራፋቱ ስህተት ላይ እንዳይጥለን መጠንቀቅ፤ እጅግ በጣም ወሳኝ
ነው! ሥራ- እጥነት አፍጦብናል። የኑሮ ውድነት የጥንቆላ ሳይሆን ነባራዊ ዕውነታ ነው፡፡ የቸገረው ሰው ጥያቄ ሲያነሳ መልስ እንጂ የነገ-ያልፍልሃል ራዕይ አያፅናናውም! በኃይል ሊገደብ ሲሞከር ደግሞ የባሰ ጥፋት ነው! ለማናቸውም ጥያቄ ህጋዊ መልስ ያስፈልገዋል የሚል መንግሥት፤ ህጋዊ ተቃውሞን አይንቅም። ማናቸውንም መሬት የያዘ እንቅስቃሴም ‹‹ከጀርባው የውጪ ኃይል አለበት››፣ ‹‹የአመለካከት ህፀፅ ነው››፣ ‹‹እኛ ከተነሳንበት ሀገራዊ ዓላማ ተፃራሪ ነው››፣ ‹‹ባለቤት የለውም›› ወዘተ በማለት ችግሩን እንዳናይ ሊያውረን አይገባም!! እሳት እየተቀጣጠለ እያለ፤ ‹‹እሳት የለም›› ብሎ መካድ ሳይሆን፤ አንድም እሳቱን የሚያቀጣጥሉ ኃይሎችን ልብ ብሎ ለይቶ መጠበቅና ተገቢ እርምጃ መውሰድ፤ ሁለትም ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ እንዳይሆን በወቅቱ የእሳት አደጋ ሰራተኛ
መመደብና ረጋ ብሎ ማሰብ፤ ያሻል፡፡
ከዚህ ሁሉ ባሻገር ደግሞ፤ “እኔ ብቻ ነኝ እሳቱን የማጠፋው” ብሎ ግትር ከማለት ይልቅ፤ ሌላም ለሀገር የሚቆረቆር ዜጋ አለ ብሎ ማመን ዋና ነገር ነው! የፀጥታ ኃይሎችን አቅም ከማባከን ህዝቡበሰላማዊ መንገድ አስቦ፣ ተሳስቦ፣ መፍትሔ እንዲፈልግ መላ መምታት የተሻለ ነው፡፡መስማት የሚፈለገውን ድምፅ ብቻ የሚናገሩ ማህበረሰቦችን መሰብሰብ በኃይለስላሴም፣ በደርግም፣ አሁንም አላዋጣም፤ አያዋጣምም! በመሠረቱ ሀገራችን መበታተን የለባትም የሚለው የሁላችንም መፈክር ነው፡፡ የሥልጣን ክፍፍል፣ የሀብት ክፍፍል ማመላከቻ መሆን የለበትም፡፡ ባለሙያን እናክብር! ከሥር ያመረቀዘው ቁስል እስኪፈነዳ ጊዜ በሰጠን ቁጥር የህላዌ ገመዳችን እየሰለሰለ እንደሚሄድ አንዘንጋ፡፡ አንድ በሳል ፀሐፊ ስለ ኢህአዴግ መንግሥት አተያይ ሲሰጥ፤ ‹‹እኛ ስፉ እንጂ ጥፉ አንልም›› ይላል፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል! ራስን አለማሞኘት የችግራችን ግማሽ መፍትሔ ነው፡፡ ፅንፈኝነትን ግን አውቆ፣ ነቅቶ፣ በቅቶ መከላከል፣ ግዴታ ነው፡፡ ሆኖም እክሉን ለማስወገድ ከራስ መጀመር አሌ የማይባል ጉዳይ ነው! የችግር ሁሉ አዋቂ እኔ፣ መፍትሔውም እኔ ማለት፤ L’etat, c’est moi›› (መንግስትማ እኔ ራሴ ነኝ እንደማለት) እንዳለው የፈረንሳይ መሪ፤ አባዜ ይፈጥራል፡፡ ደርግ የሰራው ስህተት ሳናውቀው
እንዳይበክለን ማስተዋል እጅግ ብልህ ያደርገናል! ገለልተኛ የፓለቲካ ሂደት እንዲፈጠር መጣጣር
ወሳኝ ነው፡፡ አንዘናጋ! መምከርና መመካከር ዛሬ የማይታለፍ እርምጃ ነው! ብልህነት ነው!
የማንነት ጥያቄ ክስተት ሳይሆን በማናቸውም ጊዜ ህዝብ ሊጠይቀው የሚችል የለውጥ ነፀብራቅ ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር በኃይል ሳይሆን በአግባቡ ጉዳዩን ማጤን ነው፡፡ ለመወያየት ዝግጁ መሆን ነው! ሁኔታዎችን እንደ ህዝብ ስሜት መከተል፤ ትላንትም፣ ዛሬም፣ ነገም ያለና የሚቀጥል ዕውነታዊ
ግዴታ ነው፡፡ እንደ ህዝቡ ዋና ስሜት ለመጓዝ እናስብ፡፡ ‹‹ሰው ቢለብስ እንደ አየሩ፤ ወፍ ቢጮህ
እንዳገሩ›› የሚለውን ተረት መቼም አንርሳ!

ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ዘንድሮ የግዕዝ ትምህርት ለመጀመር አስቧል
    ፎርብስ መጽሄት በቅርቡ ባወጣው የ2016 የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ የተካተተውና የወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ ኮከብ እንደሆነ የሚነገርለት ትውልደ ኢትዮጵያዊው አቤል ተስፋዬ፣ በካናዳ በሚገኘው ቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም ለማስጀመር የሚያግዝ 50 ሺህ ዶላር (1.2 ሚ ብር ገደማ) በስጦታ ማበርከቱ ተዘገበ፡፡
የግራሚ ተሸላሚው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፤ ቢቂላ አዋርድስ ከተባለ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ተቋም የቀረበለትን የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ በመቀበል ስጦታውን ያበረከተ ሲሆን፣ ተቋሙ በድምጻዊው ፈጣን ምላሽ መደነቁንና የገንዘብ ድጋፉ ባህላችንን ለመጠበቅና ለተቀረው አለም ለማስተዋወቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲል ምስጋናውን ማቅረቡን ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል፡፡
“እጅግ ድንቁንና ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ታሪክ ለተቀረው አለም ልናስተዋውቅ ነው፡፡ በካናዳ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራምን ለማስጀመር በሚደረገው ጥረት የበኩሌን ድጋፍ ለማድረግ በመቻሌ ኩራት ይሰማኛል” ሲል በትዊትር ገጹ ላይ የተናገረው አቤል ተስፋዬ፤ ሌሎችም ለዚህ ጅምር መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም ለማስጀመር ታስቦ እየተካሄደ በሚገኘው የገንዘብ ማሰባሰብ እስካሁን ድረስ ከ170 ሺህ ዶላር በላይ  መገኘቱን ያስታወሰው ዘገባው፤ ዩኒቨርሲቲው በዚህ አመት የግዕዝ ቋንቋ ጥናትን ለማስጀመር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝም ጠቁሟል፡፡
የቢቂላ አዋርድስ ፕሬዚዳንት አቶ ተሰማ ሙሉጌታ፣ በቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ፕሮግራም መጀመሩ የአገሪቱን ጥንታዊ ስልጣኔዎች በመመርመር እንዲሁም ቱባ ባህላችንን፣ ታሪካችንንና ባህሎቻችንን ጠብቆ በማቆየት ረገድ ተጠቃሽ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲሉ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በኦሎምፒክ ጀግናው አበበ ቢቂላ ስም የተቋቋመው ቢቂላ አዋርድ፣ በኢትዮ-ካናዳውያን መካከል የአካዳሚክ፣ ሙያዊና የቢዝነስ ትብብር የመፍጠርና በጎ ፈቃደኝነትን የማጠናከር አላማ ይዞ እንደተመሰረተ የጠቆመው ዘገባው፣ ተቋሙ ከሁለት አመታት በፊትም ለድምጻዊ አቤል ተስፋዬ የሙያዊ ልቀት ሽልማት እንዳበረከተለት አስታውሷል፡፡
ለ117 አለማቀፍ የሙዚቃ ሽልማቶች በመታጨት፣ ሁለት የግራሚና ስምንት የቢልቦርድ ሽልማቶችን ጨምሮ 36 አለማቀፍና ክልላዊ የሙዚቃ ሽልማቶችን ያገኘውና በወቅቱ የአለማችን የሙዚቃ መድረክ አብሪ ኮከብ ሆኖ የወጣው የ25 አመቱ ድምጻዊ አቤል፤ፎርብስ መጽሄት በቅርቡ ይፋ ባደረገው የ2016 ከፍተኛ ተከፋይ 100 የዓለማችን ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካተቱት 15 ዝነኞች መካከል አንዱ እንደነበርና  ከእነዚህ ዝነኞች መካከልም ከፍተኛውን ገቢ ማግኘቱን፣ ባለፉት 12 ወራት ብቻ 55 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘም መዘገባችን አይዘነጋም፡፡