Administrator

Administrator

ግንቦት 20፤ ለኪነ-ጥበቡ አበረከተ የሚባለው ነገር ቅድመ ምርመራን ማስቀረቱ ቢሆንም ቴአትርና ፊልምን ግን ከደርግ ሳንሱር አልተላቀቁም፡፡ ለምሳሌ ሥነ ጽሑፍ፣ ስዕልና ሙዚቃ ቅድመ ምርመራ አይካሄድባቸውም፤ ቀድመው አይታዩም፤ አይመረመሩም፡፡ ይሄ መጽሐፍንም ጋዜጣንም ጭምር ነው፡፡ ፊልምና ቴአትር ግን ይገመገማሉ፡፡ በደርግ ጊዜ የነበረው አሰራር በፊልምና ቴአትር ላይ እስካሁን ቀጥሏል፡፡
ለምሳሌ ቴአትር ለማሳየት ባህልና ቱሪዝም ፈቃድ ካልሰጠሽ ቴአትርሽ አይታይም፡፡ ባህልና ቱሪዝም ፈቃድ ካልፃፈ፣ ክ/ሀገር ሄደሽ ቴአትር ማሳየት አይታሰብም፡፡ ፊልምሽ ሲኒማ ቤት ለመታየት መጀመሪያ መገምገም አለበት፡፡
በአንቺ ስራ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሰዎች (ገምጋሚዎቹ) “ይህን ነገር ጨምር፤ ይህንን ነገር አውጣ” የማለት መብት አላቸው፡፡ እስካሁን በግምገማ ምክንያት የታገዱ ምን ምን የመሳሰሉ ቴአትሮችና ፊልሞች አሉ፡፡ “ወይ አዲስ አበባ” የተባለ የጌትነት እንየው ቴአትር በግምገማ ምክንያት ከታገዱት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህ ቴአትር ተገምግሞ ታግዷል፡፡ ይህ የሆነው ሊከፈት ለህዝቡ መጥሪያ ከተላከ በኋላ ነው፡፡ ኢህአዴግ ወይም ግንቦት 20፤ ፊልምና ቴአትርን ገና ነፃ አላወጣቸውም፡፡ በቃ ቴአትርና ፊልም አሁንም ባርነት ላይ ናቸው፡፡

(ሰዓሊ ሰይፈ አበበ፣ የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና
ቀራፂያን ማህበር ዋና ፀሐፊ)

  በደርግ ስርዓት እኔ ልጅ ነበርኩኝ፤ ሆኖም የደርግ ዘመን ስዕል የሞተበትና በተወሰኑ ሰዎችና በጥቂት ቦታዎች ብቻ ተወስኖ እስትንፋሱ የቆየበት ወቅት ነበር፡፡ እርግጥ በኃይለስላሴ ጊዜ የተከፈተ አቶ አለፈለገ ሠላም የሚባል የስዕል ት/ቤት ነበር፤ ልጅ ሆኜ አባቴ እዛ ልኮኛል፡፡  እኔ በቤተሰብ እውቀትና ስዕል ይወዱ ስለነበር ተላኩ እንጂ ይህን ያህል የተመቻቸ ነገር ኖሮ አልነበረም፡፡ ህብረተሰቡም ለስዕል ትኩረትና አክብሮት ነበረው ለማለት እቸገራለሁ፡፡ “አርፈህ ትምህርትን ተማር” የሚባልበት ጊዜ ነበር፡፡ አርት ት/ቤት ስገባና ኢህአዴግ ሲገባ አንድ ሆነ፡፡ ከግንቦት ሃያ በኋላ በስዕሉ በኩል የመጣው ለውጥ የሚገርም ነው፡፡ ብዙ ጋለሪዎች ተከፈቱ፣ ብዙ እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ በአሁኑ ወቅት ሰዓሊ ስቱዲዮ ከፎቶ፣ ጋለሪ ከፍቶ ስዕል እየሸጠ የሚኖርበት ጊዜ ነው፡፡ ቱሪስቶች ከውጭ ይመጣሉ፤ በጥሩ ዋጋ ስዕል ይገዛሉ፡፡ ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች፤ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ ሰዓሊው በአገር ውስጥም በውጭም የስዕል ኤግዚቢሽኖች የማዘጋጀት፣ ስዕሉን የመሸጥ፣ በስዕል የሚሰማውን የመግለጽ ነፃነት ያገኘው ከግንቦት 20 ወዲህ ነው፡፡ ስርዓቱና አካሄዱ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ እንደምንሰማው ከግንቦት 20 በፊት በነበረው ስርዓት፤ ጥቂት አርት ስኩል የመማር እድል የገጠማቸው ሰዓሊዎች ከተመረቁ በኋላ ሀገር ፍቅር ቴአትር ነው የሚገቡት፡፡ ፖስተር ምናምን ለመስራት ማለት ነው፡፡ እንደ ነጋሽ ወርቁ፣ እነ ጥበበ ተርፋ ያሉ እግዚብሔር የረዳቸው ሰዓሊያን ብቻ… እነ አፈወርቅ ተክሌ ያሉት … በትግል አቆይተውታል፡፡ እነ ገ/ክርስቶስ ደስታም ተሰድደው ህይወታቸውን ያጡበት ጊዜ ነበር፡፡
በአሁኑ ጊዜ እንደ ኤሌያስ ስሜ፣ እነ ዳዊት አበበ፣ ፍቅሩ ገ/ማርያም ያሉ ጐበዝ ጐበዝ ሰዓሊዎች አሉ፡፡ እነ ኤሊያስ ስሜን ብትወስጂ፤ እንደ ኒዮርክ ታይምስና ዋሽንግተን ፖስት ላይ ሽፋን ያገኙ ሰዓሊያን ናቸው ይሄ ግንቦት ሃያ የፈጠረላቸው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በግንቦት ሃያ፤ ቴክኖሎጂውም አስተሳሰቡም፣ ነፃነቱም አግዞናል፡፡ የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራፂያን ማህበርን መስርተን፤ ህጋዊ ሰውነት አግኝተን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህ ሁሉ የመጣው እንግዲህ በግንቦት 20 ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በአሁኑ ሰዓት የጐዳና ላይ ስዕል ሁሉ ጀምረናል፡፡ ቦሌ መንገድ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ስርዓቱ የሰጠን ነፃነት ነው፤ ስለዚህ ለስዕሉ ኢንዱስትሪ ግንቦት ሃያ በርካታ እድሎችን ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡    

ባለፉት 25 ዓመታት ከምርጫ ጋር ተያይዞ፣ ከተቃውሞ ሰልፍና ውጤታቸው፣ ከፕሬስ ነፃነትና ከጋዜጠኞች ስደት እና እስራት፣ ከብሄር ጎሳዉ ጥቃት እና ከመሳሰሉት ዲሞክራሲያዊ፣
ፍትሃዊና፣ ሰብአዊ ጊዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ አሉታዊ ሪፖርቶች በአለማቀፍ ተቋማት ቀርበዋል፡፡ መንግስት በበኩሉ የሚወጡትን ሪፖርቶች በሙሉ እንደማይቀበላቸው እየተከታተለ
ይፋ ሲያደርግ ከርሟል፡፡ ዲሞክራሲን ስናነሳ ሰብአዊ መብትን ሰብአዊ መብትን ስናነሳ የህግ የበላይነትን፣ የህግ የበላይነትን ስናነሳ ፍትህን እናነሳለን የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ
አንበሴ የህግ ባለሙያዎችን በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብትና በፍትህ ላይ ባለፉት 25 ዓታት ሀገሪቴ ምን ያህል ተራምዳለች ሲል ጠይቋቸዋል፡፡

“ዲሞክራሲ በሌለበት ነፃ ፍ/ቤት ሊኖር አይችልም”    (ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፤አለማቀፍ የህግ ባለሙያ)

በሀገራችን እንደ ሰማይ ከራቁ የሰብዓዊ መብቶች ዋነኛው ፍትህ ነው፡፡ አንድ የመንግስት ባለስልጣን ለሰራው ወንጀል ተጠያቂ ያለመሆን በሀገራች ስር የሰደደ ባህል ሆኗል፡፡
ተጠያቂ ያለመሆን ደግሞ ከፍተኛ የፍትህ ጥሰት እንደመሆኑ መጠን፣ በአለማቀፍ ህግ ከፍተኛ አፅንኦት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ዘ ሄግ የሚገኘው አለማቀፍ የህግ ፅ/ቤት የተቋቋመው በዋናነት ተጠያቂነትን ለማስፈን ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ያቋቋመው የሩዋንዳው ፍ/ቤት የተመሰረተው በዋናነት ሩዋንዳ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረው የመንግስት ባለስልጣናት ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ ያለመሆን ባህልን ለመስበር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ስንገመግመው፣ በሀገራችን አንዳንድ ባለስልጣናት ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ አልሆኑም፡፡ በኢህአዴግ ዘመን ከተቃዋሚዎቹ በስተቀር ከኢህአዴግ ሰዎች ለሰሯቸው ወንጀሎች ተጠያቂ የሆነ የለም፡፡ በወንጀል ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚችሉ 3 ምሳሌዎችን መጥቀስ ይችላል፡፡ አንደኛ፤ በ1997 ዓ.ም 300 ሰላማዊ ሰልፈኞች በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን መንግስት አምኗል፡፡ በጊዜው የደህንነትና የፖሊስ ኃይል፣ በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ቁጥጥርና እዝ ሥር ስለነበረ፣እነዚህ የፀጥታ ኃይሎች ለፈፀሙት ድርጊት አቶ መለስ ተጠያቂ ሲሆኑ አላየንም፡፡
ሁለተኛው፤ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንስቶ ምናልባትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጎሳቸው ወይም በቋንቋቸው ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለው ለከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ተዳርገዋል፡፡ ቤኒሻንጉል - ጉራፈርዳን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ከነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉት በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪዎች መውደቂያ አጥተው ተንገላተዋል፡፡ አንድን ሰው በዘሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በጎሳው ምክንያት ከኖረበት ቦታ ማፈናቀል አለማቀፍ ወንጀል ነው፡፡ በትውልድ ሃገሩ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ሀገር ሆኖ ይህ በደል የደረሰበት ሰው መንግስት ላይ ክስ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ ይህ ወንጀል በሰው ፍጡር ላይ የሚፈፀም ወንጀል እንደመሆኑ ክሱ በይርጋ አይታገድም፡፡ ከ20ም ሆነ ከ30 ዓመት በኋላም ቢሆን ክሱን ማንቀሳቀስ ወይም ክስ መመስረት ይቻላል፡፡ ቅጣቱ ብዙ ጊዜ እድሜ ልክ እስራት ነው፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ለዚህ ቅጣት የሚዳርጉ በርካታ ኢ-ሰብአዊ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ በቅርቡ ወደ 400 የሚጠጉ የኦሮሞ ሰላማዊ ወጣቶች ህይወት መጥፋት ተዘግቧል፡፡
 ለዚህ ተጠያቂ የሆነ አካል የለም፡፡ መንግስት ለወንጀሉ ሳይሆን ለድርጊቱ ኃላፊነት ወስዷል፡፡ ለተፈፀመ ድርጊት ይቅርታን በመጠየቅ ወንጀል አይታለፍም፡፡ መንግስት ከተጠያቂነት አሁንም አይድንም፡፡
ለፍትህ ትልቅ ስንቅ የሆኑት አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚንዱ አዋጆች በኢህአዴግ ተደንግገዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው የፀረ-ሽብር አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ የሚደነግጋቸው አንቀፆች ህገ-ወጥ ናቸው፡፡ እንደ ብዙ አውሮፓና አፍሪካ አገሮች፣ ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረሱ ህጐችን የሚሽር ነፃ የህገ-መንግስት ፍ/ቤት ቢኖር ኖሮ ይህ አዋጅ በቀጥታ በተሻረ ነበር፡፡ በሀገራችን ይህ ኃላፊነት የተሰጠው የፌደሬሽን ም/ቤት፣ የህገ-መንግስት አጣሪ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ አካል የፖለቲካ አካል ስለሆነ ነፃ ነው ለማለት አይቻልም፡፡
ለምሣሌ በ1997 ዓ.ም ተሠናባቹ ፓርላማ፣ ቅንጅት አሸንፎ ሊቆጣጠር ይችላል በሚል ፍራቻ፣ ተተኪውን ፓርላማ ዋጋ ቢስ ያደረገው አዋጅ ይሻርልን ብለን ዶ/ር ሃይሉ አርአያና እኔ ላቀረብነው አቤቱታ መልስ ሳይሰጠን ፋይሉ ተዘግቷል፡፡ ስለዚህ ዲሞክራሲ በሌለበት፣በአንድ ፓርቲ አምባገነንነት በሚተዳደር ሀገር ነፃ ፍርድ ቤት ሊኖር አይችልም፡፡ እስካሁንም ህብረተሰቡ የሚያምነው ነፃ የፍትህ ስርአት አልተገነባም፡፡
 ፕሬስን በተመለከተ በአንዲት ቃል ልጠቅልለው፡፡ በኛ ዘመን የትግሉና የለውጡ ጀግኖች፣ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አሁን ግን ጋዜጠኞች ናቸው፡፡  


===========================

“የሰብአዊ መብት ጥሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ነው”
(አቶ ተማም አባቡልጉ፤የህግ ባለሙያ

የፍትህ ሥርአቱ ተመስርቷል ወይ ብለን ስንጠይቅ፣ለኔ ገና አልተመሰረተም፡፡ የፍትህ ስርአት ማለት የፖሊስ፣ የፍ/ቤት የአቃቤ ህግና ከነዚህ ጋር ተያያዥ ነው፡፡ የፍትህ ስርአት ተመስርቷል ብለን ስናስብ፣ እነዚህ ተቋማት መኖራቸውን ብቻ ካሰብን ስህተት ነው፡፡ ድሮም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ተቋማት ነበሩ፡፡ ፖሊስም ሆነ ፍርድ ቤት ድሮም ነበሩ፡፡ አሁን ማየት ያለብን ከዲሞክራሲ መስፈንና ከህግ የበላይነት አንፃር ነው፡፡
በእነዚህ የፍትህ ተቋማት የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዴት እየተከበሩ ነው የሚለው ነው መታየት ያለበት፡፡ የፍትህ ስርአቱ ተቋቁሟል ወይ ስንል፣ ከነዚህ አንፃር ከነጭራሹ አልተቋቋመም፣ የለም፡፡
 ድሮ የነበሩ ስርአቶች አያያዛቸውና መሰረታቸው ይለያያል እንጂ ሁሉም ጨቋኝ ናቸው የሚል ድምዳሜ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ስርአቶች በሌላ መልኩ እንዲቀጥሉ ተደረገ እንጂ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ከማስከበር አንፃር ብዙ ርቀት አልተሄደም፡፡ ነባሩን ከማስቀጠል በዘለለ አዲስ የፍትህ ስርአት አልተቋቋመም፡፡ የዲሞክራሲ መሰረት የሆነው መድብለ ፓርቲ የሚባለውም በተግባር የለም፡፡ ኢህአዴግ መንግስት ሲሆን ኢትዮጵያን በዘር ነው የከፋፈላት፡፡
 ክልሎቹ በዚህ መንገድ ተሰርተው ካበቁ በኋላ ነው ክልሎቹን ሊያስተዳድሩለት የሚችሉ የብሄር ፓርቲዎችን ያዋቀረው፡፡ የዚህ መሃንዲስ ደግሞ ህወኃት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ የመጡ ፓርቲዎች አጃቢዎች ናቸው፡፡ በእኔ ግንዛቤ መድብለ ፓርቲ በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አልተቋቋመም፡፡ የፍትህ ስርአቱም ድሮ ከነበሩት አልተለየም፡፡
ገለልተኛ ምርጫ ቦርድ፣ ገለልተኛ ፍርድ ቤት በሌሉበት መድብለ ፓርቲ ስርአት ሊኖር አይችልም፡፡ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በሌለበት ስለ ዲሞክራሲ ማውራት አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ ከህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ይልቅ የዘር ፓርቲዎች ነው የሚፈልገው፡፡ የመድብለ ፓርቲ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አልተፈጠረም፡፡
የህግ የበላይነት አልሰፈነም የምለው በንጉሱ ዘመን ህግ ነበረ፤ነገር ግን የህግ የበላይነት ከንጉሱ በታች ነው፡፡ ዛሬም ያ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ፍትህ ተአማኒነት እንዲያጣ፣ ሰው ሁሉ የህግ የበላይነት ስህተት እንደሆነ ቆጥሮ፣ ለህግ ክብር እንዲያጣ የተደረገው በዚህ 25 ዓመት  ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
የሰብአዊ መብት ጉዳይን ካየን፣ ጥሰቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት ነው፡፡ ደርግ በግልፅ ይገድላል፣ ያስራል፡፡ አሁን ደግሞ ፍርድ ቤት እንደ ሽፋን ያገለግላል፡፡ በእስር ወቅትም ሰላም የለም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ ስርአቱን የነካ ሰው ከሁሉም አቅጣጫ ዱላ ይበዛበታል፡፡ መጠጊያ የለውም፡፡ ፖሊሱ ይጣላዋል፣ አቃቤ ህግ ይጣላዋል፤ ሁሉም ይጣላዋል፡፡ የአባት ገዳይ ተደርጎ ነው የሚታየው፡፡
እንደ ህግ ጠባቂነቴ ያስተዋልኩት፤ዛሬ አንድ ተጠርጣሪ በፖሊስ ሲያዝ መደብደብ፣ መዋከብ የመሳሰሉት ይቅሩ የተባሉ ተግባርት ሁሉ ይፈፀሙበታል፡፡ የድሮው ባህል አልተቀረፈም፤ ድሮም ፖሊስ ሰው ይደበድባል፤ዛሬም ይደበድባል፡፡ ድሮም ተጠርጣሪ በፖሊስ ይመናጨቃል፤ዛሬም ክብሩ አይጠበቅም ይመናጨቃል፡፡
እነዚህን ነገሮች አንስተን ከገመገምን፣ በፍትህና በሰብአዊ እንዲሁም ዲሞክራሲ መመዘኛዎች ኢህአዴግን የሚያህል ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ያስተናገድን አይመስለኝም፡፡ ደርግ ወታደራዊ አምባገነን ነበር፡፡ ኃይለሥላሴ ግለሰባዊ አምባገነን ነበሩ፡፡ ኢህአዴግም አምባገነን መንግስት ነው፡፡


======================

“አሁን የተገኘው የፍትህ ሥርአት የ25 ዓመት በረከታችን ነው”
አቶ በሪሁ ተ/ብርሃን (የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት)

ባለፉት 25 ዓመታት የፍትህ ስርአቱ በተለይ የዳኝነት ስርአቱ ያስመዘገባቸው አጠቃላይ ስኬቶችን ከመናገራችን በፊት የሥርአት ለውጥ ሲመጣ፣ የጥንት ስርአቱም በዚህ ትይዩ ተለውጧል፡፡ የዳኝነት ነጻነትና ተጠያቂነት ህገ መንግስታዊ እንዲሆን በህገ መንግስቱ በግልፅ ከመቀመጡም በላይ የፍ/ቤቶችን ነፃነትና ገለልተኝነት ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ፣ በዚህ ማዕቀፍ የፍትህ ስርአቱ ሊገነባ መቻሉ፣የ25 ዓመት በረከታችን ነው የሚሆነው፡፡
ሁለተኛው ይሄንን ማረጋገጥ የሚያስችል ቁመና እንዲኖረው የህግ፣ የተቋማዊ ማዕቀፍም የተቀረፀበት ሁኔታ እንዳለ ማየት እንችላለን፡፡ የፍትህ ስርአት አገልግሎቱ በእለት ተእለት ስራው የሚመራባቸው የተለያዩ ህግጋቶች ከመውጣታቸውም ባሻገር እነዚህን ህግጋቶች መሬት ከማውረድ አንፃር በርካታ ተግባራት ተከናውኗል፡፡ የዳኝነት ነፃነት ሊኖር ይገባል የሚለው በህገ መንግስት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችም ወጥቶለታል፡፡ የዳኝነት ነፃነቱን ሊያረጋግጥና  ዳኝነትን ውጤታማ ሊያደርግ የሚችል ማዕቀፍ ተዘርግቷል፡፡ ሶስተኛ ተቋማዊ ቁመናውን ስንመለከት፣ በፍትህ ስርአቱ የተደረሰበት የተቋም አቅም፣ የሰው ሃብት ልማቱና፣ የዳኞች ምልመላ እንዲሁም የዳኞች የምዘና ስርአት ከቀድሞው ባህል የራቁ ሆነዋል፡፡
በንጉሱ ዘመን የመጨረሻው የፍ/ቤቶች የበላይ የሚሆነው ዙፋን ችሎት ነበር፡፡ አሁን ይሄ የለም፡፡ ችሎቶች ነፃና ገለልተኛ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ከመጀመሪያ ደረጃ - ከፍተኛ - ብሎም ጠቅላይና ሰበር ችሎት ያሉት አደረጃጀቶች፣በራሳቸው ነጻነቱን የጠበቀ የስልጣን ተዋረድ እንዲደራጁ ተደርገዋል፡፡ ለእነዚህ ተቋማት ተመጣጣኝ የሆነ በጀት፣ የሰው ኃይል ተመድቦላቸዋል፡፡ የሰው ኃብት ልማትን ስንመለከት፤ በቅድመ 87፣ 84 በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቱ ዳኞች የቤተ ክህነት ምሁራን ናቸው ወይም ከ1-6ኛ የተማሩ ናቸው፡፡ አሁን ግን 97 በመቶ የሚሆኑት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡
ከህግ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ባለሙያ በፍትህ ስርአቱ መፈጠሩ ትልቅ እድገት ነው፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች ስልጣናቸውና ቁመናቸው የሚመሰረተው በዜጎች ፍትህ ማግኘት ላይ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ፍ/ቤት መቅረብ አለበት ብሎ ያመነበትን የማቅረብ መብት አለው፡፡ በ2008 ዓ.ም ብቻ እንኳ ስንወስድ፣ የፌደራል ፍ/ቤቶች 165ሺህ መዝገቦች በእጃቸው ላይ አለ፡፡ 165ሺህ መዝገቦችን ማስተናገድ መቻል፣ ጉዳዮችን የማስተናገድ አቅማቸው እያደገ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የህግ የበላይነት፤ የህልውና ጉዳይ እየሆነ እንደመጣም ያመላክታል፡፡
ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብትን የማስፈን ጉዳይ በህግ የበላይነት የሚመራ እንደመሆኑ፣ ፍ/ቤቶች ተገቢውን ተግባር እየተወጡ ነው፡፡ ፍ/ቤቶች ከህገ መንግስቱ በሚመነጩ ህጎች፤ ዜጎችን እኩል በማስተናገድ ላይ ናቸው፡፡ በሀይማኖት፣ በዘር፣ በፖለቲካ፣ በሀብት፣ በፆታና በመሳሰሉት ልዩነት ሳያደርጉ እያስተናገዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም “ሰማይ አይታረስ ንጉስ አይከስ” ይባል ነበር፡፡ ለንጉስ ቤተሰቦች ጥበቃ የሚሰጡ በወንጀል ህጉ ላይ በግልፅ የተቀመጡ ድንጋጌዎች የነበሩበት ስርአት አልፈን ነው እዚህ የደረስነው፡፡ በደርግ ጊዜ የሸንጎ ስርአትን በምናይበት ጊዜ በተመሳሳይ የሉአላዊነት ስልጣን ባለቤት የሆነው ሸንጎው ነው፡፡ የህግ የበላይነት ሳይሆን የሸንጎው የበላይነት፣ የዳኝነት የበላይነት ሳይሆን የሸንጎው አስፈፃሚነት የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ ራሱን የቻለ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ማየት እንችላለን፡፡
ሌላው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ከማክበርና ከማስከበር አኳያ፣ ከሰብአዊ መብት ፅንሰ ሀሳብ ስነሳ፤ እዚህ አገር ዘር የማጥፋት ወንጀል የሚፈፀምበት፣ ያለ ፍርድ የሞት ቅጣት የሚፈፀምበት ነበር፤ የሰው ልጅ ማሰቃየት ተግባር የሚፈፀምበት ሀገር ነበር፡፡ ለምሳሌ እንደ ሂውማን ራይትስዎች ሪፖርት ከሆነ፤ በቀይ ሽብር ጊዜ በ1 ዓመት ውስጥ 500ሺ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ፍርድ ተጨፍጭፈዋል፡፡ ይሄን ስናይ ዛሬ ላይ ለኛ የሰብአዊ መብት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ያ ታሪክ መደገም ፈፅሞ የለበትም፤ ስለዚህ ሰው የመግደል ወንጀል ብቻ ተብሎ አይታለፍም፡፡ በርካታ ጉዳዮች በፍትህ ይዳኛሉ፡፡ ባለስልጣናት ጭምር ስልጣንን ያለአግባብ ከተገለገሉ ትልቅ ወንጀል ሆኖ ይጠየቃሉ፡፡
በሰብአዊ መብት አያያዝ፣ ከዚህ አንፃር እየተሻሻለ መምጣቱን ማየት እንችላለን፡፡ ፍ/ቤቶች ይሄነ በማክበር፣ በማስከበር የሰብአዊ መብትን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ታምኖ እየተሰራበት ነው፡፡ ተከሳሾች ወይም ወደ ፍ/ቤት የቀረቡ ሰዎች፤ ክሳቸውን በግልፅ እያወቁ እንዲከራከሩ፣ የአቃቤ ህግን ማስረጃ የመመልከትና በመረጡት ጠበቃ የመወከል መብት፣ እንዲሁም በሚገባቸው ቋንቋ የመዳኘት መብት አግኝተዋል፡፡ እነዚህን ስራዎች በማጠናከር ቀጣይነት ያለው እየተሻሻለ የሚሄድ ስርአት መፍጠር ያሻል፡፡
ፍ/ቤቶች ባለፉት 25 ዓመታት ውስጣዊ አደረጃጀታቸው እያደገ መሄዱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ ፍትህ ለዜጋው እንዲደርስ ያደረጉት አስተዋጽኦም ተጠቃሽ ነው፡፡ ሀገሪቱ እያስመዘገበች ላለው እድገት፤ድጋፍና አጋዥ በመሆን የድርሻቸውን እየተወጡ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ይሄን ስንል እጥረቶች የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ፡፡ ለምሳሌ ወንጀል የማይሸከም ማህበረሰብ ከመፍጠር አንጻር በሁሉም ባለድርሻዎች ዘንድ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራበት ይገባል፡፡ ሌላው ወንጀል የሚሰሩ ወገኖችን አቅማቸውን በማዳከም ረገድ እየተሰራ ያለ ቢሆንም የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
የህግ የበላይነትና ዲሞክራሲ በሌለበት መልካም አስተዳደር ስለማይኖር በአፅንኦት ማስፈን ያስፈልጋል፡፡ ሙስናን፣ ስልጣንን ለግል ጥቅም አለማዋል እንዲሁም ኢ-ፍትሃዊ አሰራርን ከመዋጋት አንፃር እያደገ ሊሄድ የሚገባው መሰረት አለ፤ያንን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ጥራቱን የጠበቀ፣ ወጥነት ያለው፣እየተጠናከረ የሚሄድ ስርአት ለማበጀት፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በሰፊው ይጠበቃል፡፡ ሂደቱን ፍትሃዊ ለማድረግ የአቅም ችግርና የዳኝነት ክፍተቶች፤ እየጎለበቱና እየዳበሩ መሄድ አለባቸው፡፡ የሰው ሀብት ልማቱ ከሚፈለገው አንፃር ገና ብዙ ሊሰራበት ይገባል፡፡

“ሀገሪቱ በዲሞክራሲና በፍትህ ወደፊት አልተራመደችም”


ባለፉት 25 ዓመታት ሀገሪቱ በዲሞክራሲ፣ በሰብአዊ መብትና በፍትህ የሚጠበቅባትን ያህል ወደፊት አልተራመደችም ሲሉ አንጋፋ የህግ ባለሙያዎች የተቹ ሲሆን የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ በአሁኑ መንግስት ከምንግዜውም የተሻለ የዲሞክራሲ፣ የሰብአዊ መብትና የፍትህ ስርአት ተዘርግቷል ብለዋል፡፡ አንጋፋው የህግ ባለሙያ አቶ አብዱ አሊ ሂጅራ ለአዲስ አድማስ በሰጡት አስተያየት፤ “ዲሞክራሲ ማለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ነው፤ በአሁን ወቅት ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ስርአት አልተፈጠረም” ብለዋል፡፡
“ዲሞክራሲ በሌለበት ነፃ ፍ/ቤት ሊኖር አይችልም” ያሉት ዓለምአቀፉ የህግ ባለሙያ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም በበኩላቸው፤ ወንጀል የሰሩ ከፍተኛ ባለስልጣናት በህግ አለመጠየቃቸውን ጠቅሰው የህግ የበላይነትም እየተከበረ አይደለም ብለዋል፡፡ “ለፍትህ ስንቅ የሆኑ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን የሚንዱ አዋጆች መፅደቃቸው የፍትህ ስርአቱ ወደፊት እንዳይራመድ አድርጎታል” ሲሉም ተችተዋል፤ ዶ/ር ያዕቆብ፡፡
ሌላው የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ፤ የፍትህ ስርአቱ በሚፈለገው መጠን ገና እንዳልተመሰረተ ገልፀው፤ የፍትህ ተቋማት መኖር ብቻውን ፍትህ አለ አያስብልም ብለዋል፡፡
“የህግ የበላይነት ሠፍኗል ብዬ አላምንም” ያሉት አቶ ተማም፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ነው ብለዋል፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ም/ፕሬዚዳንት አቶ በሪሁ ተ/ብርሃን በበኩላቸው፤ የስርአት ለውጥ ሲመጣ የዳኝነት ነፃነትና ተጠያቂነት ህገመንግስታዊ እንዲሆን መደንገጉ፣ በፍትህ ስርአቱ ላይ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል፡፡
 ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብትን የማስፈን ጉዳይ በህግ የበላይነት የሚመራ እንደመሆኑ ፍ/ቤቶች በዚህ በኩል ተገቢውን ተግባር እየተወጡ እንደሆነም ም/ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡

   በየመን በኢትዮጵያ መንግስት በቁጥጥር ስር የዋሉትና በእስር ላይ የሚገኙት የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ልጅ የሆነቺው የ9 አመቷ ታዳጊ ምናበ አንዳርጋቸው፤ አባቴ ከእስር የሚፈታበትን መንገድ አላመቻቸም በሚል የእንግሊዝን መንግስት ልትከስ እንደሆነ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡ የታዳጊዋ የህግ ባለሙያዎች የእንግሊዝ መንግስት የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ የሚገባውን ያህል አለመከታተሉና ከእስር የሚፈቱበትን መንገድ ለመፈለግ እስከመጨረሻው አለመግፋቱ በህግ ያስጠይቀዋል ማለታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ የእንግሊዝን መንግስት በህግ መጠየቁ፣ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር የሚፈቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ያስችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸው መናገራቸውን ገልጧል፡፡
በእንግሊዝ የውጭና የኮመንዌልዝ ቢሮ ፤የአቶ አንዳርጋቸው እስርና አያያዝ ተቀባይነት የሌለው ነው ቢልም፣ ከእስር ተፈትተው እንዲወጡ ግፊት አላደረገም ያለው ዘገባው፣ ልጃቸው ምናበ፤ አባቷ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለመፍጠር ተጨማሪ ጥረት ያደርጋል በሚል ተስፋ መንግስትን ለመክሰስ መዘጋጀቷን ጠቁሟል፡፡

   ዲቢኤል ግሩፕ የተባለው ታዋቂ የባንግላዴሽ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራች ኩባንያ በትግራይ ክልል ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን ዴይሊ ስታር ድረገጽ ትናንት ዘገበ፡፡
በቀጣዩ አመት የካቲት ወር ላይ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የማምረት ስራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋብሪካው፤ ለ3 ሺህ 500 ሰራተኞች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር የኩባንያው ከፍተኛ የስራ ሃላፊ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ኩባንያው ለፋብሪካው ግንባታ ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካገኘው 55 ሚሊዮን ዶላር ብድር በተጨማሪ የ15 ሚሊዮን ዶላር ብድር ከስዊድን መንግስት የልማት ፈንድ ማግኘቱን የጠቆመው ዴይሊስታር፣ ምርቶቹን ወደተለያዩ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ፣  የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራትና ወደ አሜሪካ ኤክስፖርት ለማድረግ ማቀዱንም አስታውቋል፡፡

የ100ሺ ብር የፍትሃብሔር ክስም ቀርቦበታል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት፣ የፓትሪያርኩን ስም በማጥፋት ወንጀል የተከሰሰው የ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ፍ/ቤት ቀርቦ በ5ሺህ ብር ዋስ ተለቀቀ፡፡ ቤተ ክህነት ከወንጀል ክሱ በተጨማሪ ላይ የ100 ሺህ ብር ካሳ እንዲከፈላትም በጋዜጠኛው ላይ የፍትሃ ብሄር ክስ አቅርባለች፡፡
መጋቢት 25 ቀን 2008 ዓ.ም በ“ሰንደቅ” ጋዜጣ ዕትም ላይ “ፓትርያርኩ ለኢትዮጵያ የደህንነት ስጋት ለምዕመናን የድህነት ስጋት” በሚል ርዕስ የተፃፈውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፅሁፍ በማተሙ ነው ቤተ ክህነት ክሱን የመሰረተችው፡፡
ቤተክህነት ያቀረበችው የቀረበው የክስ ዝርዝር እንደሚያስረዳው፤ ለክሱ ምክንያት የሆነው የዲያቆን ዳንኤል ክብረት ፅሁፍ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋዋማዊ አሰራር ጥላሸት የሚቀባና የፓትርያርኩን ስም የሚያጠፋ እንዲሁም በመልካም ስምና ዝናቸው ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ህዝበ ክርስቲያኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማዊ አሰራር እንዳይቀበል የሚያደርግ ፅሁፍ በጋዜጣው ታትሞ እንዲወጣ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ስም የማጥፋት ወንጀል መከሰሱን ይጠቁማል፡፡ ቤተ ክህነቷ ከዚሁ የክስ ጭብጥ ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛው አድርሶብኛል ላላቸው የህሊና ጉዳት የ100 ሺህ ብር ካሳ የጠየቀችበትን የፍትሃ ብሄር ክስም አቅርባለች፡፡ ጋዜጠኛው ባለፈው ረቡዕ በፌደራል የመጀመሪያ ፍ/ቤት ቂርቆስ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ፤ በስራ መደራረብ ምክንያት ባለሙያ ለማማከር እንዳልቻለ በማስረዳት ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጠው በጠየቀው መሰረት ፍ/ቤቱ ለግንቦት 23 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ለቀረበበት የ100 ሺህ ብር የፍትሃ ብሄር ክስ ክርክር ለግንቦት 26 ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

554 እስረኞች እንዲለቀቁ ወስኗል
የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ 40 ኢትዮጵያውያን ወጣት ጥፋተኞችን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከስሰው ለተቀጡና በእስር ላይ ለሚገኙ 554 እስረኞች ባለፈው ማክሰኞ ምህረት ማድረጋቸውን ዛምቢያን ናሽናል ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገበ፡፡ፕሬዚዳንቱ ባለፈው ረቡዕ የተከበረውን የአፍሪካ የነጻነት ቀን ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የምህረት ውሳኔ፣ ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣት ጥፋተኞች መቼና በምን ወንጀል ተከስሰው ለእስር እንደተዳረጉ የታወቀ ነገር የለም ያለው ዘገባው፣ ከ2015 አንስቶ ከ100 በላይ ኢትዮጵያውያን በዛምቢያ እንደታሰሩ ጠቁሟል፡፡ምህረት የተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሁሉም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፣ ታስረውበት የነበረው እስር ቤት ግን የአዋቂዎች እንደሆነና፣ መንግስት ባወጣው የምህረት ውሳኔ ኢትዮጵያውያኑን ማካተቱ ትርጉም ያለው ነገር ነው መባሉን ገልጧል፡፡በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በዛምቢያ ሉዋንጉዋ ድንበር በኩል አድርገው ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር እንደሚሞክሩ የገለጸው ዘገባው፣ የአገሪቱ ፖሊሶችና የኢሚግሬሽን ሰራተኞችም በህገወጥ መንገድ ድንበር የሚያቋርጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን እየተከታተሉ በቁጥጥር ስር ማዋል መቀጠላቸውን አስረድቷል፡፡

         አንጋፋው ድምጻዊ ማህሙድ አህመድ፤የክብር ዶክትሬቱን ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ትላንት ተቀበለ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አርቲስቱ ላበረከተው ድንቅና የረጅም ጊዜ የኪነ ጥበብ ስራ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ፣ የክብር ዶክትሬት ከሰጣቸው አራት ሰዎች አንዱ አንደነበር የሚታወስ ሲሆን ማህሙድ በወቅቱ በአገር ውስጥ ባለመኖሩ ተወካዩ በሥነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው እንደነበረ የዩኒቨርሲቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደምሴ ደስታ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በትላንትናው እለት አርቲስቱ ራሱ በአካል ተገኝቶ ከዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬቱን ተቀብሏል፡፡ በዚህ ሥነ ስርዓት ላይ የቀድሞው የጎንደር ፋሲለደስ የኪነት ቡድን ዳግም  ምስረታም ተካሂዷል፡፡ ማህሙድ አህመድ፤ በቅርቡ 75ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ሲያከብር በማሪዮት ሆቴል ለእይታ ከቀረቡት 75 ፎቶዎቹ መካከል 40 ያህሎ በጎንደር ሥነ ሥርዓቱን ምክንያት በኤግዚቢሽን መልክ ለእይታ የቀረቡ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ለተመልካች ክፍት ሆነው እንደሚቆዩም አቶ ደምሴ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ በርካታ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  

          የአዲስ አበባ ከተማን የትራንስፖርት ችግር እንደሚፈታ የተነገረለት ሸገር የከተማ አውቶቡስ ትናንት ስራ የጀመረ ሲሆን ለአንድ አውቶቡስ 3.61 ሚ. ብር ፣ ለ50 አውቶብሶች 180 ሚ. ብር ወጪ መደረጉ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ ብረታ ብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን እንዲሰራለት ካዘዛቸው 300 አውቶቡሶች ውስጥ 50ዎቹን ተረክቦ ሥራ
ማስጀመሩን የአስተዳደሩ የትራንስፖርት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ካፓሲቲ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ
አቶ ሙሉቀን አማረ ገልጸዋል፡፡ አውቶብሶቹ ከአንድ ኪሎ ሜትር በታች የሚቆሙ ስላልሆነ፣ የረዥም ርቀት ፍላጎት የሚያሟሉ ናቸው ያሉት አቶ ሙሉቀን፤ ታሪፋቸውም ኪስ አይጎዳውም ብለዋል፡፡ እስከ 4 ኪሎ ሜትር 1.50፣ ከ4-6 ኪ.ሜ 2 ብር፣ ከ6-9 ኪ.ሜ 3 ብር፣ እስከ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት 3.50 እንደሚያስከፍሉ በመግለፅ፡፡ አውቶብሶቹ ለጊዜው የሚጓዙባቸውና የተመረጡ መስመሮች፡- ከሜክሲኮ ቦሌ፣ ከቦሌ ፒያሳ፣ ከፒያሳ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ዓለም ባንክ፣ ከሳሪስ አቦ መገናኛ እንደሆኑ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ከ3ወር በኋላ 150 አውቶብሶች ሲረከቡ የመስመሮቹ ቁጥር 21 እንደሚደርስና የቀሩትን አውቶቡሶች አጠናቀው አጠናቀቁ ሲረከቡ እንደየአስፈላጊነቱ ሌሎች መስመሮች እንደሚከፈቱ አስረድተዋል፡፡ ሸገር አውቶቡስ የተቋቋመበት ሦስት መሰረታዊ ነገሮች አሉት ያሉት ኃላፊው፣ በአንድ ኪ.ሜ የሚቆም መደበኛ አገልግሎት፣ የተማሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎትና ፈጣን የትራንስፖርት
አገልግሎት (ከአስኮ እስከ ጀሞ (16 ኪ.ሜ) እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ሸገር አውቶቡስና አንበሳ አውቶቡስ ሁለቱም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ስለሆኑ ጎን ለጎን ይሰራሉ ያሉት አቶ ሙሉቀን፤ አንበሳ አውቶቡስ 814 አውቶቡሶች፣ ሲቪል ሰርቪስ ወደ 400 አውቶቡሶች፣ ሸገር ደግሞ 300 አውቶቡሶች ይኖሩታል፣ ሆኖም ጥናቶች፤ የከተማዋ የትራንስፖርት ፍላጎት በአማካይ 3500 አውቶቡሶች እንደሆነ የሚያመለክቱ ስለሆነ ሌሎች ተጨማሪ አውቶቡሶች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት አውቶቡስ ለመጠበቅ ከአንድ ሰዓት በላይ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፤ የሸገር አውቶቡሶችን በ10 ደቂቃ ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል ቢገልፁም በምን መንገድ እንደሆነ አልገለፁም፡፡ የሸገር ዘመናዊ አውቶቡሶች የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው ሲሆን፣ አውቶብሶቹ የት እንዳሉ መቆጣጠር የሚያስችል ጂፒኤስ፣ የአየር መቆጣጠሪያ ኤሲ እንዳላቸውና፣ አውቶማቲክ ትኬት እንደሚጠቀሙ ሃላፊው ተናግረዋል፡፡