Administrator

Administrator

 የአገሪቱን የንግድ ህግና የብሄራዊ ባንክ መመሪያ በማሟላት የተቋቋመው ጸሃይ ባንክ፣ ዛሬበይፋስራእንደሚጀምርአስታወቀ።
ባንኩ ይህን ያስታወቀው ከትላንትበስቲያ ረፋድ ላይ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው። እንደባንኩሃላፊዎች ገለፃ፤ "ፀሐይ ባንክ ለሁሉም "በሚልመሪቃል፣ ዛሬ ስራውን የሚጀምር ሲሆንበ2.9  ቢሊዮን ብርየ ተፈረመ፣ በ734 ሚሊዮን ብር ሥራ ላይ የዋለ ካፒታልና በ373 ባለአክሲዮኖች መዋቀሩንም የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶታዬ ዲበኩሉ፣ምክትል የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ታደሰ አየነውና የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሬድ መስፍን

በጋራ በሰጡት መግለጫ አብራርተዋል።
   ፀሐይ ባንክ፣ የባንክ ኢንዱስትሪውን ክፍተት በተረዱና ለትውልድ የሚሸጋገር ተቋም ለመመስረት ዓላማ ባላቸው አደራጆች የተቋቋመ ሲሆን ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሊያገለግል በሚያስችል አደረጃጀት ዝግጅቱን አጠናቅቆ ዛሬ በይፋ ስራ እንደሚጀምር ሃላፊዎቹ ጨምረው ገልፀዋል። የፀሐይ ባንክ ዓላማ የባንክ ኢንዱስትሪውን መቀላቀል ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ ዘርፉ በቂ ትኩረት ያላገኙትን የጥቃቅንና አነስተኛ፣ የግብርናውን ዘርፍ ፣የአምራች የአምራች ኢንዱስትሪዎችንና አዋጭ የሆኑ የፈጠራ ሃሳቦችንና ስራ ፈጣሪዎችን ተደራሽ በማድረግ እንደ መሪ ቃሉ የሁሉም አገልጋይ እንዲሆን መትጋት ነው ብለዋል ሃላፊዎቹ። ባንኩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱን በማዘመን፣ ዘመኑን የዋጀ “ቴሚኖስ ትራንዛክትአር 21” የለቀቀውን የኮርባን ኪንግ ሲስተም በመላበስ፣ መደበኛውን የባንክ አገልግሎትና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንዲሁም የቢፒሲ ኩባንያ ምርት “ስማርትቪስታ” በመጠቀም አጠቃላይ የዲጂታል ባንክ አገልግሎት ይዞ በመቅረብ በኢንዱስትሪው ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን የቦርድ ሰብሳቢው አቶ ታዬ ዲበኩሉ ተናግረዋል።
እንደ ሃላፊዎቹ ገለፃ፤ ዛሬ ባንኩ በይፋ አገልግሎቱን መስጠት ሲጀምር 30 ቅርንጫፎቹ በተመሳሳይ ሰዓት ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን፣ በቅርቡም የቅርንጫፎቹን ብዛት ወደ 50 እንደሚያሳድግ ተብራርቷል። ባንኩ ዛሬ ስራውን በይፋ በሚያስጀምርበት ስነ ስርዓት ላይ የብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች፣ የተለያዩ
ባንኮች የቦርድ አመራሮችና ፕሬዚደንቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙም ታውቋል፡፡        ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መልካም ድምጽ ያለውና ጫማ ሲሰፋ መደብሩ ውስጥ ሆኖ ማንጓራጎር የሚወድ አንድ ሰው ነበር፡፡ ጎረቤቱ ደግሞ ገንዘብ የተረፈው ባለጸጋ ነበር። ይህ ሀብታም፣ ጫማ ሰፊው በመዝፈኑ ሁሌም ይደነቅ ነበር፡፡ ባለጸጋው አንድ ቀን ጫማ ሰፊውን ወደ ቤቱ አስጠርቶ፤
“መቼም እንዲህ የምትዘፍነው ቢደላህ ነው። ብዙ ብር ሳታገኝ አትቀርም። በዓመት ምን ያህል ታተርፋለህ?” አለው፡፡
ያም ጫማ ሰፊ፤ “ኧረ ምንም አላተርፍም፤ ትርፌ ድካሜ ብቻ ነው” አለና መለሰ። ሀብታሙም፤ “በቀንስ ስንት ታገኛለህ?” አለው።
ጫማ ሰፊውም፤ “ቀለቤን ከቻልኩ በቂዬ ነው። የችግሬን ቀዳዳ ከሸፈንኩ ተመስገን ብዬ እተኛለሁ።” ሲል መለሰለት።
ሀብታሙ ሰው ከት ብሎ ስቆ፤ ወደ ጓዳው ገብቶ፣ አንድ ከረጢት ወርቅ አምጥቶ “እንካ ለቤትህና ለትዳርህ የሚሆንህ ሀብት ነው፡፡ ተጠቀምበት፡፡” አለው።
ያ ጫማ ሰፊ እንዴት እንደሚያመሰግነው ግራ እየተጋባ፣ የተሰጠውን ይዞ ወደ ቤቱ ሮጠ፡፡ ቤት ገብቶም ጓዳውን ቆፍሮ ወርቁን ቀበረው፡፡ ባልጠበቀው የወርቅ ስጦታ እጅግ ተደሰተ፡፡ ውሎ ሲያድር ግን ጫማ ሰፊውን አንዳንድ አጓጉል ሀሳብ ያስጨንቀው ጀመር፡-
“አሁን ከረጢት ሙሉ ወርቅ መቀበሌን ድንገት የሰማና ያወቀ ሌባ ቢመጣና ገድሎ ቢቀማኝ ምን እሆናለሁ?” ይህ ሀሳብ እጅጉን እረፍት ነሳው፡፡
አይጦችና ድመቶች ኮሽ ባደረጉ ቁጥር ይባንናል፡፡ ይሸበራል፡፡ ጭራሹኑ ሌሊት መተኛትም ሆነ ማለዳ ተነስቶ መዝፈኑ ቀረ፡፡ ጤንነት አጣ፡፡ ሀሳብ ብቻ፡፡ ጭንቀት ብቻ፡፡ ስጋት ብቻ። ከዚያ ወርቅ ያገኘውን ጥቅም ማሰላሰል ጀመረ፡፡ ቢያወጣ ቢያወርደው ምንም ጥቅም አላገኘበትም - ከእንቅልፍ ማጣቱ በስተቀር፡፡ በመጨረሻም ወደ ባለጸጋው ጎረቤቱ ሄደና፤
“ጌታዬ፤ ይኸውልህ ወርቅህን ውሰድልኝ” አለው፡፡
“ምነው?” ሲል ሀብታሙ ጠየቀው፤ ሁኔታው ግራ እያጋባው፡፡
“የለም፤ የጥንት የጠዋቱ ዘፈኔና ድምፄ ይሻለኛል፡፡ ያንን የሚያክል አንዳችም ደስታ በምንም ዋጋ አላገኝም፡፡ እንቅልፌን መልስልኝ!” በማለት ሥጋቱንና ወርቁን መልሶ አስረከበው፡፡
ከዚህ በኋላ ያ ድሀ ጫማ ሰፊ፣ እጅግ ፍንድቅድቅ እያለ ሀሳቡን ሁሉ ጥሎ፤ ወደ ማለዳ ደስታው፣ ወደ ድህነቱና ወደ ሥራው እንዲሁም ወደ ዘፈኑ ተመለሰ፤ ይባላል፡፡
     ***
     ገንዘብን የጨበጠ ሁሉ፣ ሃብትን ያከማቸ ሁሉ ደስተኛ ይሆናል ማለት አይደለም፡፡ በተለይ ያለ ሥራ የሚገኝ ሀብት፣ ከፍስሐው ይልቅ የነብስ ውጪ ነብስ -ግቢ ሰቀቀኑ የበለጠ አሳሳቢ ነው፡፡ ነገን የሚፈጥረው የዛሬ ጥንካሬያችን ነው፡፡ ጥንካሬ በፖለቲካ፣ ጥንካሬ በኢኮኖሚ፤ ጥንካሬ በማህበረ- ሱታፌ፣ ጥንካሬ በራዕይ፣ ጥንካሬ በሽንፈት ባለመሰበር፣ ጥንካሬ በዕውቀት፣ ጥንካሬ ወድቆ በመነሳት ወዘተ ሊተረጎም ይችላል፡፡ በሰላም ጊዜ የምናሳየው ጥንካሬና በጦርነት ጊዜ የምናሳየው ጥንካሬ ከቶም አንድ ዓይነት አይደለም፡፡ ለሁሉም ወሳኙ የትግል መንፈስ ጥንካሬ በአንድ ወገን፤ ቅራኔን የመፍታትና የመቻቻል ጥንካሬ በሌላ ወገን መኖር ነው፡፡ ለሁሉም ጥንቃቄ አስፈላጊ ነው፡፡ ከጥንቃቄ ሁሉ ዋናው ደግሞ፤
“ወፍ ነሽ ሲሉ እዩት ጥርሴን፣ አይጥ ነሽ ሲሉ እዩት ክንፌን” ከሚሉ አድር-ባዮች የምናደርገው ጥንቃቄ ነው፡፡
ቀጣዩ ጥንቃቄ፤
“ማገርና ግድግዳ የማይረዳ፣ ሰፋ አድርገህ ሥራ” እንደሚል ነው፡፡ የሚያወራ አገር ሙሉ መሆኑን አለመርሳት ነው፡፡ “በቅሎ ግዙ ግዙ፤ አንድ አሞሌ ላያግዙ” የሚለውንም ልብ ማለት ያባት ነው። ሌላው ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ፤
“ውሻን በእግር መምታት፣ እንካ ስጋ ማለት መሆኑን” መርሳት አደገኛ መሆኑን መዘንጋት ነው፡፡ በመጨረሻም፤
“አብረው የሳቡ ጣቶች ቀርክሃ ያጎብጣሉ!” የሚለውን የአንድነት ዋንኛ መርህ ከልብ ማሰብ
ያሻል፡፡ ፈረንጅ፤ “United we stand, divided we fall” እንዲል።


  በደራሲ እስከዳር ግርማ የተጻፈው “የፈረንጅ ሚስት” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል።
መፅሐፉ ከተለያየ ሃገር የመጡና የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው ወንዶች ባገቡ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ዙሪያ የሚያጠነትን ነው።
በሞዴልነቷ አምባሳደርነቷ የምትታወቀው ደራሲዋ፤ በቅርቡ ለአንባቢያን ባደረሰችው “ኢትዮጵያዊ ሀገሩ የት ነው?” የተሰኘ መጽሐፏ አድናቆት ተችሯታል።
ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “ቁጥር እንግዳ” እና “ሰውነቷ” የተሰኙ ፊልሞችን ፕሮዲዩስ በማድረግና በመተወን የምትታወቅ ሲሆን የ”ሰውነቷ” ፊልም ደራሲም ነች።

ደራሲ ከበደ ሚካኤል በ”ታሪክና ምሳሌ ፩ኛ መጽሐፍ” የሚከተለውን ትርክት አኑረውልናል። ጥንት የጻፉት ለዛሬ አብነት አለውና ጠቀስነው።
ርዕሱ፡- “እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት
      እጅግም ብልሃት ያደርሳል ከሞት” ይላል። በአጭሩ ታሪኩ እነሆ፡-
ከዕለታት አንድ ቀን፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ መጽሐፍ በማንበብና፣ ጥበብን በመመርመር የሚኖሩ ሶስት ሰዎች ነበሩ። ሥራ ለመለመንና ደጅ ለመጥናት ወደ ቤተ-መንግስት ሄዱ። የዘመናቸው ንጉስ ጥበብ እንደሚወድ አሳምረው ያውቃሉ። እየተጫወቱ መንገድ እንደጀመሩ እነሱ ወደሚሄዱበት ከተማ የሚሄድ አንድ ሌላ መንገደኛ አግኝቷቸው አብሯቸው ይጓዝ ጀመረ። እሱ ብዙም የተማረ አልነበረም። ሆኖም ከነሱ የበለጠ የተፈጥሮ አስተዋይነት ነበረው።
ሦስቱ ሰዎች የጥበብን ነገር አንስተው እየተከራከሩና ወደፊት የሚያገኙትን ክብር እየተጫወቱ ሲሄዱ ካንድ ጫካ ውስጥ ደረሱ። እዚያ ቦታ ከብዙ ጊዜ በፊት የሞተ አንድ አንበሳ አገኙ። አጥንቱ በያለበት ተበታትኗል። ከሦስቱ አዋቂዎች አንደኛው፡-
“እንግዲህ የዕውቀታችን ልክ የሚታወቀው አሁን ነው። እነሆ ይህ ተበታትኖ የምናየው የአንበሳ አጥንት ነው። እኔ ጥቂት ቃል ደግሜ፣ ይህ አጥንት ሁሉ ተሰብስቦ ቀድሞ እንደነበረ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደርገዋለሁ” አለ።
ሁለቱ ባልንጀሮቹ፡- “እስቲ በል አድርግ እንይህ” አሉት።
እሱም እንዳለው ድግምቱን ደግሞ የአንበሳውን አጥንት ሁሉ በየቦታው ገብቶ እንዲገጣጠም አደረገው።
ሁለተኛው አዋቂ ይሄንን ባየ ጊዜ፤ “እኔ ደግሞ፣ ስጋውን መልሼ፤ ደሙን ሞልቼ ቆዳውን አለብሰዋለሁ” ብሎ ድግምቱን ደገመና እንደተናገረው አደረገ።
 ያ ብዙ ትምህርት የሌለው አራተኛው መንገደኛ፣ የአንበሳው አጥንት እንደተገጣጠመና ሥጋውን ደሙንና ቆዳውን አግኝቶ አካላቱ እንደሞላለት በዓይኑ ባየ ጊዜ፣ የነገሩ አካሄድ አላምርህ ስላለው፤ በአቅራቢያው ግራ ቀኙን ተመልክቶ አንድ ዛፍ መኖሩን አስተዋለና ልቡ ረጋ።
ሦስተኛው አዋቂ ተነሳና፤ “እናንተ ይሄንን ብታደርጉ እኔ ደግሞ የሕይወት ትንፋሽ የሚሰጥ ድግምት አውቃለሁ” ብሎ መድገም ሲጀምር፤ አራተኛው መንገደኛ፤
“ወንድሞቼ ሆይ! ይህ አያያዛችሁ ከቶ አላማረኝም። እናንተም ዕውቀታችሁን ብቻ እንጂ ይህ የምታስነሱት አውሬ አንበሳ መሆኑን ዘንግታችሁታል መሰለኝ። ነፍስ ዘርቶ የተነሳ እንደሆነ ከያዝነው በትር በቀር የምንከላከልበት ሌላ የበቃ መሳሪያ በእጃችን ስለሌለ ሁላችንንም ያበላሸናልና ተው ይቅር” ብሎ ቢያሳስባቸው፣ ያ መጀመሪያ ያንበሳውን አጥንት የገጣጠመ አዋቂ፣ ከት ብሎ ሳቀና፤ “አዬ  የኛ ጅል ደንቆሮ፣ እኛ የምንሰራውን ጥበብ እየተመለከትህ መደነቅ አነሰህና ምን ጥልቅ አርጎህ በማታውቀው ሙያ ገብተህ ምክር ልትሰጠን ደፈርህ” ብሎ  ዘለፈው። ለአንበሳው ሥጋ ደምና ቆዳ የመለሰለትም ሁለተኛው አዋቂ፤ “ምንስ አስር ደንቆሮ ብትሆን ከሞት ያስነሳነው አውሬ መልሶ እኛኑ ይበላናል ብለህ ማሰብህ ከጅልም ጅል ነህ!” ብሎ ሳቀበት።
“እንግዲያውስ ለእኔ ለደንቆሮው ፍቀዱልኝና እዚያ እዛፍ ላይ እስክወጣ ድረስ ጊዜ ስጡኝ” ብሎ  ሸሽቶ ከዛፉ ላይ ሆኖ መጨረሻቸውን ይመለከት ጀመር።
ሦስተኛው አዋቂ፡-
“ከጓደኞቼ አንሼ አልቀርም” ብሎ ድግምቱን ደግሞ ሲጨርስ፣ አንበሳው ነብስ ዘርቶ ተነስቶ፣ በተራበ አንጀቱ ዘልሎ አጠገቡ የነበረውን ነብስ የዘራለትን ሰው መጀመሪያ በላው። ቀጥሎ ሥጋ ደምና ቆዳ የሰጠውን ሰው ደገመው። ከዚህ በኋላ ራቡ ታገስ ሲልለት አጥንቱን የገጠመለትን ሰው ገድሎ ሬሳውን ጎትቶ ወደ ዋሻው ይዞት ሄደ።
***
“ደንቆሮ የተባለውን ሰው ድንቁርናው አዳነው። ሦስቱን ጥበበኞች ግን የሰሩት የጥበብ ሥራ አጠፋቸው። ማንኛውም ነገር በመጠኑ ሲሆን መልካም ነው። ከመጠን ሲያልፍ ግን ይልቁንም ፉክክር ሲጨመርበት፤ ሌላው ይቅርና ያቺ መልካሚቱ ጥበብ እንኳን ትጎዳለች፤ ከጥፋትም ታደርሳለች።”
መጽሐፍ ማንበብና ጥበብን መመርመር ታላቅ ጸጋ ነው። ዕውቀት የዚህ ፍሬ ነው። እውቀትን ወደ ተግባር ስንመነዝር ትርጓሜው ሕይወት ይሆናል። ወጣቶቻችን ይህን ሊገነዘቡ ያሻል። ከሁሉም በላይ ግን መሪዎች!!
መሪዎቻችን ህዝብን የመምራት ሃላፊነት ተቀብለዋልና፣ ሰላምን የማስከበርና ጦርነትን የመግታት የአንበሳው ድርሻ እነሱው እጅ ላይ ይወድቃል። ስለዚህ በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በማህበራዊውም ጉዳይ ላይ ሳያሰልሱ፣ ነጋ ጠባ መጨነቅ ግዴታቸው ይሆናል። በእርግጥ ለራሳቸው ህልውናም ሲሉ ነው! ወንበር ያለ ፖለቲካ ጥንካሬ፣ ፖለቲካም ያለ ኢኮኖሚ መረጋጋት ስር የለውም። ማህበራዊ ምስቅልቅል የዚህ ነጸብራቅ ነው።
የሒትለር አማካሪና የጀርመን ፕሮፓጋንዳ ዲሬክተር የነበረው ጎብልስ፤ “አንድን ውሸት ደጋግሞ በመናገር እውነት ለማድረግ ይቻላል” የሚለው ንድፈ-ሀሳቡ፣ ዛሬ መኖር የለበትም- ነፍሶበታል (Obsolete ሆኗል እንዲል ፈረንጅ)፡፡ “እውነት ቦት ጫማዋን ሳታጠልቅ እውሸት አለምን ዞሮ ይጨርሳል”፤ የሚለውን ብሂል አገር አውቆታልና ነው። የአመራሮችና የሹማምንት ውሸት እድሜ የለውም! ቢያንስ “ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባበትም” የሚለውን ተረት አለመዘንጋት ብልህነት ነው፤ እንላቸዋለን።
መጪው ጊዜ የከፋ እንዳይሆን ዛሬን ማስተካከልና ማመቻቸት ይበጃል። ዳር ዳሩን መዞር ትተን ወደ ጉዳዩ መግባት፣ ወደ ወሳኙ ለውጥ ያሸጋግረናል ብለን እንገምታለን። የተሸራረፈ ለውጥም አያዛልቀንም። ነገን በቅጡ ማስተዋል ከብዙ ችግር ያድነናል።
ዝናብ የሚመጣ ከሆነ መጠለያ ማመቻቸት፣ ድርቅ ሊከሰት ይችላል ከተባልን አስቀድመን ከእልቂት የሚያድነንን ዝግጅት ማድረግ ተገቢ ነው። ጦርነት እንኳ ሊመጣ ይችላል ተብሎ ከተጠረጠረ መዘጋጀት ያባት ነው። አለበለዚያ “ለከርሞ የሚራብ ዘንድሮ እህል-ተራ ያንዣብባል” የሚባለው ተረት ዓይነት እንሆናለን።
ከዚህ ይሰውረን! ሁሉም ነገር እንደ ቤንዚንና ናፍጣ ዋጋ ጭማሪ በየቀኑ እያሳቀቀን፣ በጥይት ሰውነታቸው የተበሳሳ ህጻናት የምናይበት አሰቃቂ ሁኔታና ኢ-ሰብዓዊ ትዕይንት ውስጥ መግባት፣ አንድም ከድጡ ወደ ማጡ ነው፣ አንድም ደግሞ “ኦ ሰላም! በስምሽ ስንት ግፍ ተሰራ!” የሚለውን ጥንተ-ንባባችንን የሚያስታውሰንን ትዝብት በመሪር ሐዘን ማሰብ ነው! በዚህ ላይ በየፖለቲካና ብሄር ድርጅቶቹ የሚታየው መንታ ገጽታ፣ ዛሬም እንደ ትላንት በቅራኔ፣ በውዝግብና በመተላለቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑ፣ ነገራችንን ሁሉ እጅጉን የእውር- የድንብር ያስኬደዋልና “ያገር ያለህ?!” ያሰኘናል። ከዚህ ቁጣም ይሰውረን!! ቀና አዕምሮና ቀና ሰብዕና ያለው ዜጋ ሁሉ፣ ሁኔታው የዕለት ሰርክ መሆኑን አውቆና ነግ-በእኔ ብሎ ቢያስብበት፤ ለሁሉም መልካም ነው።

ባለፈው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ብሔርንና ጎሳን መሰረት ያደረጉ  አስከፊ ግጭቶችና  ጥቃቶች መከሰታቸውን የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል፡፡
በመገናኛ ብዙኃን በስፋት የሚነገረው በኦሮሚያ ክልል ወለጋ አካባቢ የተከሰቱ  ብሔር ተኮተር ጥቃቶች ቢሆኑም፣ በተለያዩ  የሃገሪቱ አካባቢዎችም ከመገናኛ ብዙኃን የተሰወሩ አስከፊ ጥቃቶችና ኢ-ሠብአዊ ድርጊቶች በሠላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈፀሙ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በተከሰቱ ብሔር ተኮር ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ህይወት ከመጥፋቱም ባሻገር በ10ሺ የሚገመቱ ከሞት የተረፉ ዜጎች ሃብት ንብረታቸውን ማጣታቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የወለጋውን ጥቃት ተከትሎ 20 ሺህ 5 መቶ ያህል ዜጎች አካባቢውን ጥለው ወደ አማራ ክልል እንደገቡ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
በተጠናቀቀው የሰኔ ወር ከኦሮሚያ ውጪ ግጭቶች አይለው ከታዩባቸው አካባቢዎች፡- በአፋር ክልል አውሲ፣ ገቢ፣ ሃሪ ዞኖች፣በሶማሊ ክልል ሊበን ዞን፣በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ካማሺ እና አሶሳ አካባቢ፣ በደቡብ ክልል ደራሼ እና አሌ ወረዳዎች፣የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የደቡብ ወረዳዎች (ጌዲኦ ዞን፣ አማሮ፣ ቡርጂ) ይጠቀሳሉ፡፡
በአንጻሩ ለበርካታ ጊዜያት በግጭትና ጥቃት ቀጠናነቱ የሚታወቀው የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ባለፈው ሰኔ ወር አንጻራዊ መረጋጋት እንደታየበት እንዲሁም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንም በአንጻራዊ መረጋጋት ውስጥ ማሳለፉን የተመድ የሠብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

 የዲጂታልም ሎተሪም ሊጀመር ነው

             ኢትዮ ቴሌኮም፤ ግብር ከፋዮች ዓመታዊ ግብር በቴሌብር መክፈል የሚያስችላቸውን አሰራር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ጋር  ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ቀላል፣ ፈጣን፣ ምቹና አስተማማኝ የሆነውን  የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ቴሌብርን ተጠቅመው፣ በየትኛውም ጊዜና ቦታ ሆነው፣ የግብር ክፍያቸውን መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።
በዚህ ተግባራዊ በተደረገው የግብር ክፍያ ስርዓት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት ግብራቸውን የሚከፍሉ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች፣ ያለምንም እንግልትና ውጣ ውረድ በወቅቱ ግብራቸውን እንዲከፍሉ፣ ለከፈሉት የአገልግሎት ክፍያ ማስረጃው በቅርብ እንዲኖራቸው፣ ግብር ለመክፈል የግብር መክፈያ ጣቢያ በአካል ሲሄዱ የሚደርሰውን የገንዘብና የጊዜ ብክነት እንዲሁም፣ የትራንስፖርትና ሰነዶችን ኮፒ ለማድረግ የሚያወጡትን ወጪ እንደሚያስቀር ታውቋል፡፡
 “ግብር ከፋዮች በየትኛውም ቦታና ሰዓት በቴሌብር መተግበሪያ ወይም በአጭር ቁጥር *127# በመጠቀም ግብራቸውን በወቅቱ ለመክፈል ያስችላቸዋል” ብሏል- ኢትዮ ቴሌኮም።
በዚህም የግብር ክፍያ ስርዓት ከ300 ሺህ በላይ ግብር ከፋዮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጠቆመው ኩባንያው፤ ግብር ከፋዮች በሞባይል ስልካቸው ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በ7075 በአጭር የጽሁፍ መልእክት የሚደርሳቸውን የክፍያ ማዘዣ ቁጥርን በመጠቀም ክፍያቸውን ሲፈጽሙ፤ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ከ7075 እንዲሁም ከ127 የክፍያ ማረጋገጫ መልዕክት ይደርሳቸዋል ብሏል።
ደንበኞች ለቴሌብር አገልግሎት ያልተመዘገቡ ከሆነ መመዝገብና አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የተጠቆመ ሲሆን በዚህም መሰረት ደንበኞች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ ኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማዕከላት እንዲሁም የቴሌብር ህጋዊ ወኪሎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ ገንዘብ ተቀማጭ በማድረግ የግብር ክፍያውን በቀላሉ በቴሌብር መፈጸም ይችላሉ ተብሏል።
በተጨማሪም የባንክ አካውንት ያላቸው ደንበኞች ከቴሌብር ጋር ትስስር ባደረጉ ባንኮች ማለትም አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ብርሃን ባንክ፣ ህብረት ባንክ፣ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ አባይ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ ኦሮሚያ ባንክ፣ ወጋገን ባንክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ እና ንብ ባንክ አማካኝነት ከባንክ አካውንታቸው ወደ ቴሌብር አካውንታቸው ገንዘብ በማስተላለፍ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ ይገባቸዋል ብሏል- ኢትዮ ቴሌኮም በመግለጫው።
የቴሌብር አካውንት ያላቸው ነገር ግን የባንክ አካውንት የሌላቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ ምንም አይነት የባንክ አካውንት ሳያስፈልጋቸው በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ፣ ዳሽን ባንክ፣ እናት ባንክ፣ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ ወጋገን ባንን እና ንብ ባንክ ቅርንጫፎች በአካል በመሄድ የቴሌብር አካውንታቸው ላይ በቂ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም እና ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ በቴሌ ብር እና በ60ና አጭር የፅሁፍ መልዕክት ለመጀመር ከትላንት በስቲያ ስምምት ፈፅመዋል፡፡
የብሔረዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ መጀመሩ ከዚህ በፊት ለህትመትና ሌሎች ተያያዥ ያላቸው ሥራዎች ያወጣው የነበረውን ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንስና ለደንበኞች ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ያስችለዋል ተብሏል፡፡


የግል ሚዲያውን ለመታደግ የማስታወቂያ ህጉ መሻሻል አለበት

          አቶ ቴዎድሮስ ሽፈራው ይባላሉ። ሥራ ፈጣሪና ኢንቨስተር ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት “ናሁ“ ቴሌቪዥንን ጨምሮ የተለያዩ ኢንቨስትመንትና ኩባንያዎች  ባለቤት ናቸው፡፡ “ወደ 7 ገደማ ኩባንያዎችን ማቋቋም ችያለሁ፤ ህልሜም ሩጫዬም ገና ነው” የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች መካከል ሪልስቴት፣ ሆቴልና አፓርትመንት፣ ሪዞርት፣ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን፣ የግብርና ውጤቶች አስመጪና ላኪነት፣ እንዲሁም ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ  አዳዲስ የአገልግሎት ዘርፎች እንደሚገኙባቸው ይገልጻሉ፡፡
አቶ ቴዎድሮስ ዛሬ በተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ስኬት ቢቀዳጁም በመንገዳቸው ብዙ ፈተናዎችና ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፤ከሃገር ቤት እስከ ሩቅ ምሥራቅ፡፡ ለመሆኑ ባለሃብቱ ከምን ተነስተው ነው ዛሬ ላይ የደረሱት? ምን ዓይነት ፈተናዎችን ተጋፍጠው በድል ተወጡ? የስኬት ምሥጢራቸው ምንድን ነው? የህይወትና የሥራ ፍልስፍናቸውስ? ሁሉንም ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በስፋት አውግተውታል፡፡ እነሆ፡-


          እስቲ ስለ ትውልድዎና ዕድገትዎ ይንገሩን ?
እኔ ብዙም የተለየ ህይወት የለኝም፡፡ ቀለል አድርጌ ለመግለፅ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ የተወለድኩት ሰፈረ ሠላም አካባቢ ነው፡፡ ያደግሁት ደግሞ  ኦልድ ኤርፖርት፣ ቫቲካን ኤምባሲ አካባቢ ነው። እዚያው ያደኩበት አካባቢ ባለው ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ተማርኩ፡፡ ከዚያ ሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተግባረዕድ ተምሬ፣ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው፣ ከለውጡ በፊት ወደ ድሬድዋ ሄድኩ፡፡ ድሬድዋ ትንሽ ቆየሁና ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ።  አዲስ አበባ በስራ ላይ ትንሽ ቆይቼ ወደ ጃፓን ሄድኩ፡፡ ጃፓን እንደሄድኩ ቴክኒክ ት/ቤት ነው የገባሁት። ጎን ለጎን ለመኖር  ስራ መስራት እንዳለብኝ  ወስኜ፣ የጃፓንኛ  ቋንቋ ተምሬያለሁ፡፡ ከጃፓን በኋላ ደግሞ ወደ ቻይና ነው ያመራሁት፡፡ ቻይና ስደርስ እንግዲህ ጠቅልዬ ወደ ንግድ ዓለም ገባሁ ማለት ነው፡፡ በቻይና  ለዘጠኝ ዓመት በንግድ ስራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ ከዚያም በኛ ሚሊኒየም ላይ ሃገር ያቀረበልንን ጥሪ ተቀብዬ ወደ ኢትዮጵያ ገባሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣሁ በኋላ በተለያየ የንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ነው የተሰማራሁት፡፡ እንደገናም ወደ ትምህርት አለም ተመልሼ፣ በቢዝነስ ማኔጅመንት እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ተምሬያለሁ፡፡
አስተዳደግዎና የቤተሰብዎ ሁኔታ እንዴት ነበር?
እኔ ከነጋዴ ቤተሰብ አይደለም የመጣሁት፡፡ አባቴ ወታደር ነው፡፡ ለሃገሩ ሲሰራ የነበረ ሰው ነው፡፡ ስለ ንግድም ብዙ እውቀት አልነበረውም። እኔ ወደ ንግዱ የመግባት ፍላጎቱ ያደረብኝ በእናታችን ሞት ምክንያት ወደ ድሬድዋ በሄድኩበት አጋጣሚ፣ የንግድ እንቅስቃሴውን በመመልከቴ ነበር፡፡ ከድሬድዋ ወደ አዲስ አበባ  ስመለስም ባዶ እጄን ነበርኩ፡፡ እንደ ማንኛውም ወጣት አዲስ አበባ ላይ ስራ መፈለግ ነው የጀመርኩት፡፡ በወቅቱ ስለ አለም የተለያዩ ሚዲያዎችን አዳምጥ ነበር፡፡ ከዚያ በመነሳት ብዙ መስራት አለብኝ ብዬ አብዝቼ አስብ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ላይ በወቅቱ የቱሪስት  አስጎብኝና ጉዞ ድርጅት ውስጥ ለመስራት እፈልግ ነበር። በየቦታው መዞር ስለምፈልግ ያንን ስራ ነበር ሳፈላልግ የነበረው፡፡ ቀንቶኝ መጀመሪያ ያገኘሁት ሥራ  ሳፈላልግ የነበረው አይነት ነው። ነገር ግን ያንን ስራ ስሰራ  የነበረው ደመወዝ ተከፍሎኝ አልነበረም፡፡ ቀጣሪዬን “ግዴለህም በጣም ጠቀሚ ሠራተኛ እሆናለሁ” ብዬው ነበር የተቀጠርኩት፡፡

ሰውየው በሚዲያም ይታወቃል፡፡ ሞላ ዘገየ ይባላል፡፡ ስራውን ስጀምር ጠረጴዛና ወንበር አልተሰጠኝም። ብቃቴንም ማየት ስለሚፈልጉ እንዲሁ ነበር  የምሰራው፡፡ እንደ ኮሚሽን ሠራተኛ ስራ እያመጣሁ ነበር የምሠራው፡፡ በወቅቱ የ100 ሺህ ብር ስራ ካመጣሁ 10 ሺህ ብር ትሰጡኛላችሁ ስላቸው ስራውን ካመጣህ ምን ችግር አለው የሚል ነበር ምላሻቸው፡፡ በዚህ መልኩ ከተስማማን  በኋላ በመጀመሪያ ያሰብኩት ነገር በኢትዮጵያ ውጪ ስለመጓዝ ነበር፡፡ ያልተሞከረ ነገር መሞከር አሰብኩና ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ወደ ግብፅ ሃገር ሄደው እንዲጎበኙ እድል ማመቻቸት ጀመርኩ፡፡ አለቃዬ በሃሳቤ ተስማማ፡፡ እኔ በወቅቱ ስለ ግብፅ ከማንበብ ባሻገር ግብፅን በአካል አላውቃትም፡፡ መቼም የጉዞ አሰናጅ ሆኖ ወደ ግብፅ ለመሄድ ያሠበ ሰው ካለ፣ በመጀመሪያ  ስለ ሃገሪቱ ብዙ ማወቅ አለበት። እኔ ግን እንዲሁ በድፍረት አንድ የጉዞና የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጀሁ፡፡ ያንን ለህዝቡ ለማስተዋወቅ ማስታወቂያ ማስነገር ያስፈልግ ነበር፡፡ በወቅቱ ደግሞ በድርጅቱም ሆነ በኔ በኩል ያንን ማስታወቂያ ማስነገር የሚያስችል ገንዘብ አልነበረንም፡፡ በወቅቱ ያደረግሁት ቢኖር ከእህቴ የተሰጠችኝን አንድ ትንሽዬ መኪና ነበረችኝ፡፡ እሷን መኪና በ14 ሺህ ብር ሸጥኳትና አራት ሺህ ብር ለቴሌቪዥን ማስታወቂያ ከፈልኩኝ፡፡ ይሄን ሳደርግ ግን በወቅቱ ስራውን ለመስራት ካለኝ ጉጉት እንጂ ከቀጣሪዬ ጋር በወጉ እንኳ የስራ ቅጥር ውል አልነበረኝም፡፡ ያ የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ሲተላለፍ አለቃዬ ቤቱ ቁጭ ብሎ ይመለከታል፡፡ “ፒርስ ትራቭል ኤጀንት ወደ ግብፅ ሃገር የጉብኝት ፕሮግራም አዘጋጅቷል” የሚል ማስታወቂያ ሲያይ ደነገጠ። አልነገርኩትም ነበር፡፡ ጠዋት ስንገናኝ ማን ነው ይህን ያደረገው አለኝ፤ እኔ ነኝ አልኩት፡፡ እንዴት ገንዘብ ከየት አመጣህ አለኝ፡፡ መኪናዬን ሸጬ አልኩት… እንዴ ሰው ባይመጣስ አለኝ… ግዴለህም ይመጣል አልኩት፡፡
ያኔ ይህን ያህል ሃላፊነት ለመውሰድ ለምን ፈለጉ?
ትልቁ ቁምነገር የስራው ፍላጎት ነበረኝ፤ ህይወትን  መለወጥ የሚቻለው ዋጋ ተከፍሎ ነው በሚለው አምን ነበር፡፡ ብዙ ሰው ያለውን አጥቶም ቢሆን አዲስ ነገር መሞከርን እንደ እብደት  ሊያየው ይችላል፡፡ እኔ ግን በህይወቴ ብዙ ውጣ ውረድን ያሳለፍኩ ስለሆንኩ ብዙ ነገር ተምሬአለሁና እንዲህ አይነቱን ውሳኔ አልፈራም፡፡ ያው ግን እንዳሰብነው ብዙ ሰው ግብፅን መጎብኘት ይፈልግ ነበርና፣ ቢሮአችን በሚመዘገቡ ሰዎች ተጨናነቀ፡፡ ካሰብነው በላይ ሰው ተመዝግቦ፣ የመጀመሪያውን ጉዞ ከኢትዮጵያ ወደ ግብፅ አደረግን ማለት ነው። ግብጽን አላውቃትም ነበርና ከተጓዦች አንድ ቀን ቀድሜ ገብቼ በፍጥነት ያሉትን ነገሮች በሙሉ ተመለከትኩና እንግዶችን ደግሞ አስጎበኘሁ ማለት ነው፡፡ ያንን የጉዞ ፕሮግራም አዘጋጅተን ስንጨርስ ታዲያ 50 ሺህ ብር ትርፍ አገኘን፡፡ ያችን የሸጥናትን መኪና ተክቼ ለኩባንያውም የነበረበትን እዳ ከፈልኩ ማለት ነው፡፡ ከዚያም የኩባንያው መደበኛ ቅጥር ሆኜ በጉዞ አሠናጅነት፣ ለአንድ ለሁለት ዓመት ሠራሁኝ። እንግዲህ ትልቅ ገንዘብ እጄ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ  በዚህ አጋጣሚ ነበር የገባው። ከዚያ በኋላ ወደ ጃፓን ሃገር  ነው ያቀናሁት፡፡
ጃፓንን ለምን መረጧት? የተለየ ምክንያት ነበረዎት?
ብዙ ሰው ጃፓን ለምን ሄድክ? ይለኛል። እኔ ግን በወቅቱ አማራጭ አጥቼ ነው ጃፓን የሄድኩት፡፡ አውሮፓ፣አሜሪካ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም ነበርና ወደ ጃፓን ሄድኩ፡፡
በወቅቱ እዚህ ባለው  ስራዎ ስኬታማ ከነበሩ ለምን ስደትን መረጡ?
 አንደኛ በጣም ወጣት ነበርኩ፤ ሥራውም ያን ያህል የተፍታታ አልነበረም፡፡ እንደ እኔ አይነት ብዙ ፍላጎት ላለው ሰው ምቾት የሚሰጥ አልነበረም፡፡ ከመሄዴ በፊት የተለያዩ ቢዝነሶችን ለመስራት አየር መንገድን ጨምሮ ለማናገር ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ከልጅነቴም  የተነሳ ሊሆን ይችላል በሩን የከፈተልኝ በወቅቱ አልነበረም። ሁኔታዎች ከባድ ነበሩ፡፡ የለውጡ አካባቢም ስለነበር ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምን ወጥቼ አልሞክረውም ብዬ  ነው የወጣሁት፡፡
ጃፓን እንዴት ተቀበለችዎ?
የሚገርመው ጃፓኖች ጥሩ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች አይደሉም፡፡ የኔም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ያን ያህል አልነበረም፡፡ ጃፓንኛም አላውቅም፡፡ እዚያ የማውቀው ኢትዮጵያዊም አልነበረም፤ ገና ኤርፖርታቸው ስደርስ ኢትዮጵያውያን ያሉበትን አካባቢ ነበር ማፈላለግ የጀመርኩት፡፡ እዚያ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ናቸው የነበሩት፡፡ ጃፓንን ቶሎ ለመልመድ አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንደው ባጭሩ ለመግለፅ አጋጣሚው በህይወት ውስጥ ፍዳ ያየሁበት ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ ያ መከራ ግን አላቆመኝም፡፡ ከብዙ መቸገር በኋላ ስራ አገኘሁ፡፡ ያንን ስራ መስራት ጀመርኩ፡፡ በዚያው መላመዱ መጣ፡፡ እዚህ ላይ ባጫውትህ  ደስ የሚለኝ አንድ ገጠመኝ ነበረኝ፡፡ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ ስሰራ እሳት ይነሳል፡፡ በኛ ሃገር እሳት ሲነሳ  የለመድነው ተሯሩጠን የመብራት ቆጣሪ ማጥፋት  ነው፡፡ እኔ ይሄንን ይዤ እዚያ ፋብሪካ ውስጥ እሳት ሲነሳ ሮጬ ባልቦላውን አጠፋሁት። እሳቱም ጠፋ፡፡ በወቅቱ በኔ ቤት የሚያሸልም ስራ የሠራሁ ነበር የመሰለኝ፤ ነገር ግን በማግስቱ ቢሮ  ተጠራሁና “ለምን ይሄን አደረግህ፤ በል ከእንግዲህ ላንተ የሚሆን ቦታ የለንም” ብለው ከስራ አሰናበቱኝ፡፡
ለምን?
ምክንያቱም ጃፓኖች በባህላቸው ለአለቆቻቸው ፍፁም ታዛዥ ናቸው፡፡ እነሱ ሳያዟቸው ምንም ነገር አያደርጉም፡፡ አዛዥ 5 በመቶ ቢሆን፣ ሌላው ጠቅላላ ታዛዥ ነው። አለቃ ያለውን ነገር መፈፀም ግዴታ ሲሆን ያላዘዘውን መፈፀም ወንጀል ነው፡፡ በዚያ የተነሳ ከሥራዬ ተሰናበትኩ፡፡  የዚያች ቀን መንገድ ላይ ስሄድ፤ “እኔ በህይወት ዘመኔ ጭራ ሳልሆን ራስ ሆኜ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ” እያልኩ ለራሴ እየነገርኩት ነበር፡፡ “ስለዚህ ያለቦታዬ ነበር የገባሁት፤ እግዚአብሔር አልፈቀደውም፤ ራሴ  የምመራውን ኩባንያ መመስረት አለብኝ” ብዬ ነው ያሰብኩት፡፡ ይሄን ሣስብ ግን ምንም ነገር አልነበረኝም፡፡ ጃፓን ውስጥ ደግሞ ሲሆን በጣም ከባድ ነው፡፡ ግን በጣም ብዙ ትግሎች አድርጌ ትንሽ ኩባንያ አቋቋምኩ፡፡ ምናልባት ጃፓን ሃገር የራሱን ኩባንያ ያቋቋመ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሳልሆን አልቀርም፡፡
ኩባንያው ምን የሚሰራ ነበር?
በመጀመሪያ ያገለገሉ መኪናዎችን እየሰበሰብኩ እየጠጋገንኩ፣ ወደ ሌላ ሃገር እልክ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ ሌዘር ፕሪንተር ካርትሬጅ ማኑፋክቸር ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ መማርና መስራት ጀመርኩ፡፡ በብዙ መከራ ፋብሪካ አቋቁሜ አሮጌ እቃዎችን መልሶ በማደስ ለሽያጭ ማቅረብ ጀመርኩ፡፡ እየሰራሁ በደንብ እያደግሁ መጣሁ፡፡ ነገር ግን ስራዬ ቢያድግም ለቤት ኪራይ፣ለሠራተኞች ደመወዝ፣ ለፋብሪካ ኪራይ ከፍዬ መኖር እቸገር ነበር፡፡ ስለዚህ  ለ12 ሰዓት ያህል በፋብሪካ ከሰራተኞቼ ጋር አብሬያቸው  እሰራና ሌሊት ደግሞ ሌላ ቦታ ተቀጥሬ እሰራ ነበር፡፡ 7 ዓመት ገደማ ጃፓን ስኖር  ከአራት ሰዓት በላይ ተኝቼ አላውቅም ነበር፡፡ ሌላ ጋ ተቀጥሬ ያመጣሁትን ገንዘብ ለሠራተኞቼ ደሞዝ እከፍል ነበር፡፡ እንዲህ ባለ ሁኔታ እየሠራሁ፣ ኩባንያውም እያደገ ሲመጣ አንድ ቀን ከጃፓን መንግስት ኢምግሬሽን ቢሮ ትፈለጋለህ ተብዬ ተጠራሁ፡፡ መልካም ነገር ይገጥመኛል ብዬ ነበር ወደ ቢሮው ያመራሁት፤ የጠበቀኝ ግን ሌላ ነገር ነበር፡፡ “ከኢትዮጵያ የመጣኸው በሌላ ቪዛ  ስለሆነ ኢንቨስተር ሆነህ እዚህ ፋብሪካ አቋቁመህ መስራት አትችልም፤ ስለዚህ ከሃገር ወጥተህ እንደገና የቢዝነስ ቪዛ ይዘህ መምጣት አለብህ!” ተባልኩ፡፡ ብከራከርም አልተቀበሉኝም፡፡ እዚያው ያለኝን ንብረት ትቼ 5 ሺህ ዶላር የማትሞላ ገንዘብ ይዤ፤ ከጃፓን ተባርሬ ወጣሁ፡፡ ያለምንም ክሊራንስ ባዶ እጄን ንብረቴን ጥዬ ነበር የወጣሁት፡፡ በወቅቱ ትራንዚት ያደረግኩት ታይላንድ ነበር፡፡ በዚያ ሰዓት ብዙ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፤ ቤተሰብ የሚያውቀው ፋብሪካ እንዳለኝ፣ ጥሩ ገቢ እንደማገኝ  ነው፡፡ ታዲያ ምን ይዤ ወደ ሃገር ቤት ልመለስ? ባጋጣሚ አየር መንገድ የሚሰራ አንድ ወዳጄን አገኘሁትና  የደረሰብኝን ሁሉ ነገርኩት፡፡ እኔ እና እሱ አውሮፕላን ጣቢያ ውስጥ እያወራን ሳለ የምጓዝበት አውሮፕላን አመለጠኝ፡፡ ወዳጄ በደረሰብኝ ነገር  በጣም ስላዘነ አንድ ነገር መከረኝ፡፡ “ወደ ሆንግ ኮንግ ሄደህ ቪዛ ይዘህ ና” አለኝ፡፡ የ15 ቀን ቪዛ እንደሚሰጡ ነገረኝ። እኔም እንደተባልኩት አደረኩኝ፡፡ ወደ ሆንግ ኮንግ ሄጄ የ15 ቀን ቪዛ ይዤ  ተመለስኩ፡፡ ወደ ታይላንድ እንደተመለስኩኝ፣ እጄ ላይ በቀረችው 2 ሺህ ዶላር አንዳንድ ስራዎችን መስራት ጀመርኩ፡፡ ከቱሪስቶች ጋር የተያያዙ ስራዎች ነበሩ፡፡ በ6 ወር ውስጥ ምንም በማላውቀው ሃገር እንደገና በእግሬ መቆም ጀመርኩ፡፡ በብዙ ትግል ሰው ሆንኩ፡፡ ነገር ግን ታይላንድ ብዙም እንደማያሳድገኝ ስላየሁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና በረራ ጀመረ ሲባል፣ እንደገና ጓዜን ጠቅልዬ ወደ ቻይና ተሰድጄ ገባሁ፡፡ ቻይኖች እንግሊዘኛ አያውቁም፡፡ ትልቅ የቋንቋ ችግር ገጠመኝ፡፡ እንደአጋጣሚ አየር ማረፊያ ውስጥ ያገኘኋቸውን አረቦች ነበር እየተከተልኩ ስንቀሳቀስ የነበረው፡፡ እነሱ የሚሰሩትን የሚያደርጉትን ሁሉ በትኩረት እከታተል ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ነዴጋዎች ነበሩ፡፡ ከእነሱ ጋር ስንቀሳቀስ ባጋጣሚ ለኢትዮጵያዊም ለአፍሪካዊም የሚሆን ሰፊ የስራ እድል  እንዳለ ተረዳሁ፡፡ በቃ ይሄ ሃገር የኔ የመጨረሻ ማረፊያዬ መሆን አለበት አልኩ። የኔ የቢዝነስ መነሻ ይሄ ሀገር ነው ብዬ አመንኩ። ወዲያው ትንሽዬ ቢሮ ነገር ተከራየሁ። ያቺን ቢሮ በተከራየሁ በአመቱ ሚሊዮን ብር እጄ ገባ።
የጀመሩት ሥራ ምን ነበር?
በቻይና ፋብሪካዎችና በአፍሪካውያን ሸማቾች መካከል ትልቅ ክፍተት መኖሩን ተገንዝቤ ነበርና፣ ያንን ክፍተት መጠቀም ነው የጀመርኩት። በወቅቱ የቻይና ፋብሪካዎች በአፍሪካ አገራት ገበያ ይፈልጉ ነበር ። ይሄንን ስረዳ ቀርቤ እያናገርኩ በኮሚሽን ለብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት የገበያ እድሎችን የማመቻቸት ስራ ጀመርኩ። በኮሚሽን ስራ እንዲሁም በመርከብ የሚጫኑ እቃዎችን ሂደት የመከታተልና የማዘጋጀት ስራዎችን እሰራ ነበር። ይሄ ትልቅ ቢዝነስ ነበር። በወቅቱ ቻይናዎች እንግሊዘኛ ተናጋሪዎች ስላልነበሩ እኔ ያንን ክፍተት በመጠቀም ነው ጉድለታቸውን ስሞላ የነበረው። በዚህ ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሚሊዮን ብር ብቻ ሳይሆን ሚሊዮን ዶላር ምን እንደሆነ ማየት ቻልኩ። እውነቱን ለመናገር ፈጣንና ጠንካራ ሰራተኛ ነበርኩ። በአፍሪካውያኑም በቻይናውያኑም እታመን ነበር። በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ ስራ ኤጀንትነትን ወሰድኩ። በቀላሉ አየር መንገዳችንን በዚያ እያገዝኩ ለራሴም ገቢ አገኝ ነበር። እኔ በቢዝነስ አለም አዳዲስ ፈጠራዎች ናቸው የሚያስደስቱኝ። አሁንም ያሉት እነ “ካሽጎ” እና “ጉዞጎ” የኔ ናቸው። ፈጠራ ላይ በጣም መስራት እወዳለሁ። በትንሹ ጀምሬ ወዲያው ሌላ የቢዝነስ ፈጠራ ውስጥ ነው መግባት የምፈልገው። ቻይና ሳለሁ እንደ አልማዝ፣እንቁ፣ትልልቅ ብራንድ የሆኑ ሰዓቶችና፣ ጌጣጌጦች-- እንዴት ነው ከሃገር ሃገር የሚጓጓዙት የሚለውን ለራሴ ጠየኩና፤መቼም እነዚህ ንብረቶች እንደነ ዲኤች ኤል ባሉት ሊላክ አይችልም ብዬ ጉዳዩን ማጥናት ጀመርኩ። በኋላ ስገነዘብ እነዚህ ውድ እቃዎች ራሳቸውን ችለው የሚመላለሱበት መንገድ አልነበረም። ይሄን ክፍተት መሙላት አለብኝ ብዬ በኦንላይን የሚገበያዩ ውድ እቃዎችን የማጓጓዝ ስራ ጀመርኩ ማለት ነው። ያው የሚጓጓዘው እቃ ውድ ነው፡፡ ስለዚህ የሚያስፈልገውም የማጓጓዣ ገንዘብ ትልቅ ገንዘብ ነው የነበረው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ገንዘብ ሰራሁበት ማለት ነው። ያንን እየሰራሁ ሳለ ነው እንግዲህ በሚሊኒየሙ ጊዜ “ወደ ሀገር ግቡና ስሩ” ተብሎ ጥሪ ሲደረግ፣ ወደ ሀገር ቤት የመጣሁት።
ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ምን ገጠመዎት? በምን ሥራ ላይስ ተሰማሩ?
እውነቱን ለመናገር በወቅቱ የነበረው ነገር አልጋ በአልጋ አልነበረም። ብዙ ተግዳሮት ነበር የገጠመኝ። እንደውም በሌሎች ዲያስፖራዎች ላይ ከደረሰው የከፋ እንግልት ነበር የገጠመኝ። ግን “ብረት በተቀጠቀጠ ቁጥር ይጠነክራል” እንደሚባለው፣ ፈተናዎች የበለጠ አጠንክረውኝ ነበር። እንደመጣሁ ሪል እስቴት ቢዝነስ ውስጥ ነበር የገባሁት፡፡ በወቅቱ ብዙዎች ጉዳዬን ይዤ ወደ ቢሯቸው ስሄድ አያምኑኝም ነበር። በመጨረሻ ግን ኦሮሚያ ክልል ለገጣፎ አካባቢ ሰው አልፈልግም ብሎ የተወውን ቦታ፣ ለምን ሄዶ አይሞክርም ተብሎ ቦታው ተሰጠኝ፡፡ እዚያ ጫካ ውስጥ መዋኛ ጭምር ያለው መኖሪያ ቤት  ሰራሁኝ። በወቅቱ ከሰው ርቆ ጫካ ውስጥ በመሆኑ አንዳንዱ እንደ እብድ ይቆጥረኝ ነበር። እዚህ ውስጥ ማነው መጥቶ የሚኖረው? እያሉ ያሾፉብኝ ነበር። ግን አላማና ራዕይ ስለነበረኝ  ስራውን ቀጠልኩበት፡፡ የተወሰኑ ቤቶች ሰራሁና ጨረስኩ። ግን በዚሁ መሃል ብዙ ፈተናዎች ነበሩብኝ። መንግስትን ያኔም እተች ነበር፤ ዛሬም ሲያጠፋ እናገራለሁ። በነዚያ ንግግሮቼ አልወደድም ነበር። በየስብሰባው የምናገራቸው ነገሮች ጥላቻን አትርፈውልኝ ነበር። በዚህም ብዙ ፈተና አይቻለሁ። በወቅቱ የፖለቲካው አባል መሆን ወይም የሆነ ዘር ውስጥ ማረፍ እንዳለብኝ ይነገረኝ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ አባቴም እናቴም የማን ዘር  እንደሆንኩኝ አልነገሩኝም። “ኢትዮጵያዊ ነህ” ብቻ ብለው ነው ያሳደጉኝ። ከኢትዮጵያዊነቴ ውጭ ሌላ የማውቀው ነገር የለም። ስለዚህ ትናንትም ዛሬም የትኛውም ዘር ውስጥ መውደቅ አልችልም። በወቅቱ ለፖለቲካው የቀረበው ሰው በዘሩ ተመርጦ፣ ታክስ የማይከፍልበት፣ ሌላው ከሚገባው በላይ የሚከፍልበት፤ በዚህ ሰበብ ፍዳውን የሚበላበት ጊዜ ነበር። ሲያሻቸው የቅንጅት አባል ነህ ይሉኝም ነበር። ስለዚህ ብዙ ጊዜ ከሃገር ስወጣ ጥሩ ነገር ያለ ሲመስለኝ፣ ደግሞ ስመለስ እንዲሁ ስባክን ነበር የቆየሁት። በጣም ያንገላቱኝ ነበር። በታክስ ሰበብ ብዙ ንብረቶቼ ተሸጠውብኝ  ወደ ነበርኩበት ቻይና ለመመለስ ተገድጄ ነበር። በኋላ አቶ ሃይለማርያም ሲመጡ ደግሞ ከ3 መቶ ሺህ ብር ያልበለጠ ካፒታል ይዤ መጣሁ፤ ግን በዚያ ካፒታል የጀመርኳቸውን ፕሮጀክቶች ጨርሼ ኢንቨስትመንቴን አስፋፍቼ፣ አሁን ላይ ከ7 ያላነሱ ኩባንያዎች አሉኝ ማለት ነው። ከ1250 በላይ ለሚሆኑ ሰራተኞች የስራ እድል መፍጠር ችለናል። በቴክኖሎጂው፣ በሚድያው፣ በሆቴል፣ በሪልስቴት፣ በሪዞርት፣ በኢምፖርት፣ በኤክስፖርቱ የቢዝነስ ዘርፎች ኩባንያዎች አሉን፡፡ አሁንም ደግሞ የበለጠ ለማደግ ጠንክረን እየሰራን እንገኛለን።
በሚድያው ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ያነሳሳዎት ምንድን ነው?
እንግዲህ ወደ ሚድያው ስመጣ፣ በመጀመሪያ ከእነ አማረ አረጋዊ ጋር ሆነን አርትስ ቲቪን ማቋቋም ነበር የጀመርኩት፡፡ በኋላ እሱ ሲዘገይብኝ የራሴን ድርሻ ለሌላ ሰው ሸጥኩና ናሁ ቲቪን ገዛሁት። አገር እንድታድግ ከተፈለገ ለውጥ ያስፈልጋል፤ ለዚህ ለውጥ ደግሞ ሚድያው ወሳኝ ሚና አለው ብዬ አምናለሁ። ሚድያ አራተኛ መንግስት ነው። ይሄ የሚሆነው ግን መንግስት ሲፈቅድና ሁኔታዎችን ምቹ ማድረግ ሲቻል ነው። በወቅቱ የለውጥ ስሜት በየአቅጣጫው የሚታይበት፣ ከፍተኛ ትግል ሲካሄድ የነበረበት ጊዜ ነበር። እኔም ለውጡን ከሚፈልጉት አንዱ ነበርኩ። በወቅቱ በተለይ በንግዱ አለም ያለን ሰዎች በእኩል አንስተናገድም ነበር። ከፍተኛ መድሎ ነበረብን። ስለዚህ ያ መለወጥ አለበት የሚል ፅኑ እምነት ነበረኝ። ኋላም ወደ መባቻው አካባቢ “ካልደፈረሰ አይጠራም” በሚል በቴሌቪዥን ጣቢያው ለውጡ ወደ ኋላ እንዳይመለስ  የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ችለናል። ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሪዝን ብሬክ ፊልምን “ሳቂ ሳንቃ” ወይም “እስር ቤቱን ሰብረህ ውጣ” በሚል ተርጉመን እናስተላልፍ ነበር። ያንን ያደረግነው ለውጡ ፈፅሞ መቆም የለበትም በሚል አቋም ነበር። ፊልሙንም ወቅቱን ጠብቀን አስበንበት ነበር ያቀረብነው። በወቅቱ የነበረው አማራጭም ለውጡን ወደፊት መግፋት ስለነበር በቁርጠኝነት ነው ትግል ስናደርግ የነበረው። ያኔ ወደ ኋላ ብንመለስ አይሆንም ነበር። ወጣቱ ድንጋይ ይዞ ክላሽ ፊት ቆሞ  ሲታገል ነበር። ያ ትግል ወደ ኋላ ፈፅሞ አይመለስም ነበር፡፡ እኛም ለውጡን ወደ  ኋላ እንዳይመለስ ነው በተለያየ ጥረት የደገፍነው።
የሚድያ ስራ ትርፋማ ነው እንዴ?  
ፈፅሞ አይደለም። የህዝብ (መንግስት) ሚድያ ሲሆን የመንግስት በጀት ነው የሚጠቀመው፡፡ ያም ሆኖ ማስታወቂያውንም በብቸኝነት የያዙት እነሱው ናቸው። የግሉ ሚድያ በጀት የለውም፡፡ ማስታወቂያም አያገኝም። ታዲያ እንዴት ነው ውጤታማ የሚሆነው? የመንግስት በጀት የሚመደብላቸው ሚድያዎች፣ ማስታወቂያውንም በብቸኝነት በያዙበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። እኛ ጠንከር ያሉ ጉዳዮችን ስናነሳኮ የሳሙና ማስታወቂያ እንኳ ለማስነገር ደንበኞች ይፈራሉ። ታስፈርጀናለህ ይላሉ፡፡ ስለዚህ በሁሉም የሚጎዳው የግሉ ሚድያ ነው። በዚያው ልክ የመንግስት መስታወት የሚሆኑት ደግሞ ከመንግስት ይልቅ የግሉ ሚድያዎች ናቸው። የመንግስት ሚድያዎች እኔና አንተ በምንከፍለው ታክስ ነው የሚተዳደሩት፡፡ ይህ ብቻ አይበቃቸውም፤ ማስታወቂያውን ከጥቃቅን እስከ ከፍተኛ ያለውን ለብቻቸው ተቆጣጥረው ይይዛሉ። ጋዜጦች ዛሬ ላይ በመጥፋት ላይ ናቸው። መንግስት ታክስ እንዳይከፍሉ ማድረግ አልያም ወረቀት በነፃ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። ትውልድ ያንብብ ይወቅ እያልን በሌላ ጎን ትውልድ እንዳያነብ የሚያደርጉ እክሎችን ማብዛቱ የሚደገፍ አይደለም። የማስታወቂያ ህጉ መስተካከልና ለሁሉም ፍትሀዊ መሆን አለበት። እኔ አሁን ናሁ ቲቪን በየወሩ ከሌላው ኩባንያ ገቢ ከ1 ሚሊዮን ብር  በላይ እየደጎምኩት ነው ያለው፡፡ ግን እስከ መቼ ይደጎማል? አንድ ቀን ይደክመንና ልንተወው እንችላለን። እኔ ግርም የሚለኝ ባለሃብቱም ትክክለኛ ድምፅ ሊሆነው የሚችለው የትኛው ሚድያ እንደሆነ አልገባውም። አንድ ችግር ቢደርስበት ድምፅ የሚሆነው እኮ የግል ሚዲያ ነው፡፡ የግሉ ሚዲያ ሲዘጋ የሱም አንደበት እየተዘጋ መሆኑን አይረዳም፡፡ ጭራሽ አፉን የሚዘጋለት የመንግስት ሚዲያው ላይ ነው ሄዶ የሚያስተዋውቀው። ጉዳዩ የእውቀትም የግንዛቤም ችግር ነው። እኔ የፈለገ ቢመጣ የመንግስት ሚዲያ ላይ አላስተዋውቅም፡፡ ምክንያቱም ለእነሱ የበለጠ ጉልበት ነው የምሰጣቸው፡፡ ጉልበት በተሰጣቸው ቁጥር ደግሞ መንግስት የበለጠ የፈለገውን እንዲያደርግ ዕድል እየሠጠኸው ነው የምትሄደው፡፡ መንግስትን መግራት ከፈለግህ የግል ሚዲያን ደግፍ አበርታ፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ የአመለካከት ለውጥ ያስፈልጋል፡፡
በፈተናዎች መሃል አልፈው ለስኬት የበቁበት ምስጢር  ምንድን ነው?
ከሁሉም በላይ ምንም ቢሆን ተስፋ አልቆርጥም። ስወድቅ እልህ ይይዘኛል እንጂ በዚያው ተስፋ ቆርጬ አልቀርም፡፡ በተሻለ ጉልበት በድጋሜ እስክነሳ እንቅልፍ የለኝም። ሁልጊዜ የመሪ ሀሳብ እንጂ የተመሪነት መንፈስም ሀሳብም ፈፅሞ የለኝም። እኛ ኢትዮጵያውያን ጠንካሮች ነን፤ ሃሳባችን ትልቅ ነው። ትንሽ እንቅልፍ ቀንሰን በብዙ ማሰላሰል ከሰራን ምንም ነገር ማድረግ ይቻለናል። እኔ የተሸናፊነት ስሜት ፈፅሞ የለኝም። ስኬቴ እንጂ የዛሬው ስህተቴ አይታየኝም። ብዙ የመዝናናት ህይወት አላውቅም፤ ለኔ ህይወት ስራ ነው። ከመዝናናት በላይ የምመርጠው ቁጭ ብዬ ያሉ ክፍተቶችን ማጥናትን ነው፡፡ ወደ አንድ ቦታ ስሄድ ምን እድል አለ የሚለውን ነው ማየት የምፈልገው። ሁልጊዜ የማየው እድሎችን ነው። አንዱ ሲበላሽብኝ ወደ ሌላው አማራጭ ነው ምሄደው። የኔ ህይወት እረፍት የለውም፡፡ ዛሬም ትግል ላይ ነኝ። ገና ብዙ ማሳካት የምፈልጋቸው ነገሮች አሉኝ። ሲቀጠቅጠኝ የነበረው መንግስትም በኋላ ልፋቴንና ድካሜን አይቶ ሸልሞኛል። ለኔ ያ ቀን ልዩ ነበር፡፡  ለሁሉም ጊዜ አለው።
በእርስዎ  ህይወት ውስጥ ፈታኝ የሚሉት ጊዜ የቱ ነው?
ያለ ፈተና የሆነ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በህይወቴ የማልረሳቸው ከፍተኛ ዋጋ የከፈልኩበት የጃፓን ህይወቴ እና በመጨረሻ ከኢትዮጵያ ልሰደድ የነበርኩበት ጊዜያት ናቸው፡፡ እነዚህን በተለየ አነሳሁልህ እንጂ ብዙ ውጣ ውረዶች ናቸው በህይወቴ የገጠሙኝ፤ ግን እግዚአብሔር ቅን አምላክ ነው፡፡ እኔን በነዚያ እሳቶች ውስጥ እንዳልፍ አድርጎኛል። ዛሬ ለኔ ብዙ ነገር ብርቅ አይደለም፡፡ በ37 ዓመቴ ጥሩ ገቢ ኖሮኝ፣ አውሮፕላኖች ኖረውኝ፣ ብዙ ነገሮች አይቻለሁ፡፡ ለኔ በዓለም ላይ ምንም ነገር ብርቅ አይደለም፡፡ ያንን ህይወት እንዳልፍ ወይም እንዳውቅ ያደረገኝ ግን በብዙ የህይወት ውጣ ውረድ ማለፌ ነው፡፡ ስለ ረሃብ አውቃለሁ፤ ምክንያቱም ርቦኝ ያውቃል፡፡ ስለ ሃዘን ጭንቀት አውቃለሁ፤ ደርሰውብኝ አልቅሼ ስለማውቅ። የሰው ልጅ ቸገረኝ ሲል አውቃለሁ፤ እኔም ተቸግሬ ሰው ረድቶኝ ስለማውቅ፡፡  ያንን   አድርጌ ባላልፍ ኖሮ ዛሬ ቅልል ያለ ህይወት አይኖረኝም ነበር፡፡ በእግሬ ሄድኩኝ በመኪናም ምንም አይገደኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያን በእግሬ እሄዳለሁ፣ የትም  ቦታ  ከሰዎች ጋር ቁጭ ብዬ  የልቤን አውርቼ ወደ ቤቴ እገባለሁ፡፡ የሰውን ልጅ በገንዘቡ ባለው ሃብት ለክቼ አላውቅም፡፡ እንደዚያም እንዳደርግ አይምሮዬ አይፈቅድም፡፡ ፈጣሪዬንም ሁሌ አመሰግነዋለሁ፡፡ በብዙ ፈተና የተፈተንኩ ነኝ፤ ሰዎች ፈተና ሲገጥማቸው እኔም ያለፍኩበት ነውና በእጅጉ እረዳለሁ፡፡
የወደፊት ህልምና ራዕይዎ ምንድን ነው?
በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ፣በዓለም ደረጃ ብዙ ነገር ለመስራት አስባለሁ፡፡ በአለም ደረጃ ታዋቂ ሊያደርገን የሚችል ነገር ሰርቻለሁ። ምቀኛው በዛበት እንጂ  “ካሽጎ” የኔ ፈጠራ ነው። ዛሬ አሜሪካኖች “ካሽጎ” ተግዳሮት ሆኖባቸው በጉልበት ኢትዮጵያ መጥተው አስቁመውታል። አለምን የሚለውጥ ቴክኖሎጂ ነበረን፡፡ “ካሽጎ” አለማቀፍ የገንዘብ ዝወውርን ያለ ደላላ የሚያሳልጥ፤ ኢትዮጵያ በየአመቱ በሌሎች የገንዘብ አዘዋዋሪዎች የምታጣውን 9 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ገቢ የሚያስጠብቅላት ነበር፡፡ ማንም ሰው በያዘው የእጅ ስልክ 10 ዶላር ልኮ፤ 10ሩም ዶላር በቀጥታ ለኢትዮጵያ የሚገባበት አሠራር ነበር፡፡ ነገር ግን ኮሚሽን የሚያገኙ ሌሎች ካምፓኒዎች ተረባርበው አስቆሙት እንጂ በርካታ ጥቅም ያለው ነበር፡፡ አሁንም ተስፋ  የሚያስቆርጠን አይደለም፡፡ “ጉዞጎ” የኛ ነው፡፡ አሁን የ”ጉዞጎ” ሽያጭ ከ5 መቶ ሚሊዮን ብር በላይ አልፏል፡፡ በቀጣይ በቢሊዮን ይገባል፡፡ አሁን ወደ አሜሪካም እየወሰድነው ነው፡፡ አሜሪካን ሃገር “ጉዞጎ ኢንተርናሽናል” በሚል ተመዝግበን ልንገባ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት አሜሪካን ሃገር ይገባል፡፡ በዓለም መታወቂያችን የሆነ አገልግሎት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዓለም ላይ ሁሉ መድረስና መስራት እፈልጋለሁ፡፡ እስከዚያ ድረስ ተኝቼ አላድርም፡፡ እኔ ብጀምረው ልጆቻችን ይጨርሱታል፡፡


              በ564 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታልና በ702 ሚሊዮን ብር የተፈረመ ካፒታል፣ በ10ሺ ባለአክሲዮኖች የተደራጀው አሐዱ ባንክ፤ በመጪው ቅዳሜ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ።
በአገልግሎት አሰጣጥና በቴክሎጂ አጠቃቀም በኩል ያለውን ሰፊ ክፍተት ለማጥበብ አቅዶ የተነሳው አሐዱ ባንክ፤ ይህንን የተሻለ የባንክ አደረጃጀት ይዞ ወደ ገበያ  የሚገባ አገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው ተብሏል።
የአሐዱ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተነህ ሰብስቤና የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ ፋንታዬ በማርዮት ሆቴል ከትላንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፤ ባንኩ በየዓመቱ ከሚያቀርበው ብድር እስከ 15 በመቶ የሚደርሰውን ለስራ ፈጣሪዎችና ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚያመቻች ይሆናል ። የባንኩን አገልግሎት በስፋት ለማዳረስ የዲጂታል አማራጮችን እንደሚጠቀምም ተገልጿል።
በአገራችን ከተለመደውና ከብዙሃን ሰብስቦ ለጥቂቶች የመስጠት የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት መሆኑን ያስታወሱት የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አንተ አንተነህ ሰብስቤ፤ አሐዱ ባንክ በተቃራኒው ከብዙሃን ፋይናንስ ሰብስቦ ለብዙሃን የማያዳረስ ዕቅድ እንዳለው ተናግረዋል።
ባንኩ ቅርንጫፎቹን በስፋት በመክፈት አገልግሎቱን ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ መዘጋጀቱን የገለጹት የባንኩ የስራ ሃላፊዎች፤ በቀጣይም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ በሞባይል አማካኝነት የባንክ ሂሳብን  በቀላሉ መክፈትና ማንቀሳቀስ የሚቻልበትን አሰራር ተግባራዊ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ከሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶችን ለመስጠት በሚያስችሉ ተግባራት ላይ አተኩሮ እንደሚቆይና “አንድ ቅርንጫፍ ለአንድ ልጅ” በሚል ባንኩ በሚከፍታቸው ቅርንጫፎች ቁጥር ልክ ድጋፍና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ልጆች ዓመታዊ ወጪያቸውን እንደሚሸፍን ገልጿል።
የአገር ቅርስና እስቶችን ተንከባክቦና ጠብቆ ለትውልድ ማስተላፍ የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ሃላፊነት ነው ብሎ የሚያምነው ባንኩ የአገራችን ታላቅ ሃብትና ቅርስ ለሆነውን የቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዕድሳት የ500 ሺ ብር ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቋል፡፡
ባንኩ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት የቅርንጫፎቹን ቁጥር 50 እንደሚያደርስም ተገልጿል።