
Administrator
በልታ በልታ ጨው የለውም፣ ሄዳ ሄዳ መንገድ የለውም [በሊዓ በሊዓ ጨው የብሉን፣ ከይዳ ከይዳ መገዲ የብሉን] የትግሪኛ ተረት
እጅግ አድርገው ቀልድ ወዳጅ የነበሩ አንድ ሀብታም ጌታ ነበሩ፡፡ እንደ ጌታው ቀልድ ወዳጅ የሆነ አንድ አጋፋሪም ነበራቸው፡፡ አንድ ቀን ጌታው አንዲት ያልተገራች በቅሎ ይገዛሉ፡፡ በቅሎይቱ ለአገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ናት፡፡ ስለዚህም ጌትዬው አጋፋሪውን ይጠሩና “እቺን በቅሎ ጫንና መንገድ አሳያት” ብለው አዘዙት፡፡ አጋፋሪውም ትዕዛዙን ተቀብሎ፣ በቅሎዋን ጭኖ፣ ተቀምጦባት መጭ አለ፡፡ አንድ መንታ መንገድ ላይ ሲደርስ፣ ዱብ አለና በቅሎዋን፤
“በቅሎ ሆይ፤ ያውልሽ እንግዲህ፡፡ የሸዋ መንገድ ይህ ነው፡፡ የጎጃም መንገድ ይህ ነው፡፡ የጎንደርም መንገድ ይህ ነው፡፡ የትግሬም መንገድ ይህ ነው፡፡ ጌታሽ መንገድ አሳያት ብለውኛልና የወደድሺውን መንገድ ይዘሽ ሂጂ” ብሎ እንደተጫነች ለቀቃትና እሱ ወደ ቅልውጡ ሄዶ አምሽቶ ወደ ጌታው ተመለሰ፡፡ ጌታውም፡- “ለበቅሎዋ መንገድ አሳየሃት? ሲሉ ጠየቁት፡፡
“አዎን ጌታዬ የአራቱንም አገር መንገድ አሳይቼአት ሳበቃ የወደድሺውን ያዥና ሂጅ ብዬ ለቀቅኋት፡፡” ብሎ መለሰ፡፡ ጌትየው በጣም ተናደዱ፡፡ በነጋታው “ተነሱ ፍለጋ እንሂድ” ብለው አሽከሮቻቸውን ሁሉ አስከትለው ፍለጋ ተሰማሩ፡፡ በቅሎዋ ድራሿ ጠፋ፡፡ በመጨረሻ ያ የጣላት አጋፋሪ ራሱ መልሶ አገኛት፡፡ ዳሩ ግን ገሚስ ጎንዋን ጅብ ተጋብዟት ነው ያገኛት፡፡ በመካያው አጋፋሪው በሌላ አቅጣጫ ወደሄዱት ወደ ጌታው ዘንድ አመራ፡፡
ጌትየው፡- “እህስ ምንም ፍንጭ የለም?” አሉና ጠየቁት ገና ሲያዩት፡፡
“እንዴት ፍንጭ አይኖርም፤ አለ እንጂ ጌታዬ! ግማሿን በቅሎ አግኝቻታለሁ፡፡ ግማሿን ለጅብ አካፍላዋለች” ሲል መለሰላቸው፡፡
* * *
በማንኛውም ወቅት የጅብ ሲሳይ እንዳንሆን መንገድ የሚያሳይ እንጂ መንገድ ላይ የሚጥለን መሪ፣ ኃላፊ፣ ሹም አይጣልብን ማለት ደግ ፀሎት ነው፡፡ አቅጣጫ ሳይለዩ አለ በተባለው በተለመደው መንገድ ሁሉ ጊዜ - አለጊዜ መሄድ ትርፉ እንደ በቅሎዋ መበላት ነው፡፡ አዲስ መንገድ ማየትና መልመድ የሚቻለው በመጀመሪያ ያ መንገድ ሁነኛው መንገድ፣ ጅብ የማያስበላው መንገድ፣ መሆኑን ልብ እንድንል የሚያደርግ በአገር ጉዳይ የማይቀልድ፣ የማያስበላን አጋፋሪ ሲገኝ ነው፡፡
ወደ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት የሚያደርሰን መንገድ የቱ ነው? ከሙስና የፀዳ ሹምና ሿሚ የምናገኝበት መንገድ የቱ ነው? ፍትህ ወደሰፈነበት፣ ወገናዊነት ወዳልተንሰራፋበት፣ ሰው በሰውነቱ ወደሚከበርበት፣ በጠባብ አመለካከት ወደማንታወርበት፣ “ከእኔ በስተቀር ለሌላ ጌታ አትደር” የሚል ክፉና ቀናኢ ጌታ ወደማይኖርበት፣ ሰፊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚወስደን አውራ ጎዳና የትኛው ነው? የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ወደሚቋደሱበት የስልጣን ገበታ የሚወስደው፤ “ጎንህ እንዲያርፍ፣ የጓደኛህ ጎን ይረፍ” ለማለት የሚችሉ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ወገኖች ለሀገር ሲሉ ልዩነቶቻቸውን አቻችለው በአንድ መድረክ ወደሚነጋገሩበት የፖለቲካ ጀማ የሚያመራው፣ “አፈ-ቅቤ ልበ-ጩቤ” ወደማይበዛበት ብሄራዊ ሸንጎ የሚያቀናው ሁነኛ ጥርጊያ መንገድ የቱ ነው? አዲስ ብለን የመረጥነው አቅጣጫ፣ አዲስ ብለን የሾምነው ሹም፣ አዲስ ብለን የጠመቅነው አስተሳሰብ፣ “አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን” ወደማይሆንበት “የአካሄድ”ና “የሥርዓተ-ሲመት” እንዲሁም “የአቋቋም” ፖሊሲዎቻችን መልሰው እግ -ተወርች ወደማያስሩበት ወግ (Order) የምንደርሰውስ በምን መላ ነው? ነገ የሚታለመው ሥርዓት ሁሉ በአንድ ተውኔት ውስጥ በምፀት እንደተጠቀሰው፤ “ዐይናማው ብለነው እውር ሆኖ ቢወለድስ?”፣ “ክንዴ ብለነው ክንደ-ቆራጣ ቢሆንስ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
“የአዛውንቶች ልብ ባህር ነው፣ ግን አይዋኝበትም” እንዲል መፅሐፈ-ትግሬ፣ የአዋቂዎቻችንን፣ የብልህ አረጋውያንን እውቀት ለመጠቀም የሚያስችለን መንገድ የትኛው ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ “አስተዋይ ሰው ወይ ገለል ሲል፣ ወይ አገር ለቅቆ ሲሄድ ይታወሳል” ይባላልና በየሰበብ አስባቡ ከአገር ወጥተው በውጭ አገር የሚገኙ አስተዋይ ኢትዮጵያውያንን አእምሮስ የምንጠቀምበት ምን ዓይነት መንገድ አለ? ብሎ መጠየቅ ያሻናል፡፡ ለሀገርና ለህዝብ ሲባል የሚጠየቅ ጥያቄ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ የተመኘነው እስኪገኝ፣ የጎደለው እስኪሞላ መጠየቅ አለበት፡፡ የሚመለከተው ክፍልም ደከመኝ፣ ታከተኝ ሳይል መልስ መስጠት አለበት፡፡ ትክክለኛ መንገዶችን መጠ|ቆም፣ ማሳየት፣ እንዴትስ እንደሚኬድበት መነጋገር የግድ ነው፡፡
መቼም “አገርና አውድማ መክደኛ አለው” ይሏልና ለየጉዳዩ ሁሉ ቁልፍ ማበጀት፣ መፍትሄና መንገድ ማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ከእንግዲህ የየሥርዓቱ የቤተ-ሙከራ መፈተኛ - እንስሳ (Guinea-pig) መሆንን የምትሸከምበት ጥኑ ትከሻ የላትም፡፡ የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭቷ፣ ማህበራዊ ቀውሷ፣ የኑሮ ውድነቷ፣ የሹመኞች ሙስና፣ የዜጎች ተስፋ ማጣት ---. ሁሉም የችግር ጠርዞች መፈናፈኛ እያሳጧት ወደ ሌላ የፖለቲካና የሥነ-አዕምሮ አለመረጋጋት ወጀብ ውስጥ እንዳይከታት ብርቱ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡ የምንሰራው ሁሉ ባይሳካም እንደገና እንሞክረዋለን ወደሚልና ሌላ የሙከራ -ቅጽ ወደመሙላት የሚያስኬድ የሚያወለዳ ሁኔታ ከቶ የለም፡፡
“በልታ በልታ ጨው የለውም፣ ሄዳ ሄዳ መንገድ የለውም አለች” እንደሚባለው፤ ጉዟችን ለዕድገት ወደሚከፈት በር እንጂ ወደተገደገደ - አጥር (Dead-end) ከሆነ ለሀገር ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ከዚያ ይሰውረን፡፡
በኢትዮጵያ ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር ይካሄዳል
- ከ60 አገራት የተውጣጡ 100 እንግዶች ይሳተፋሉ
ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድር በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ሊካሄድ መሆኑ ተገለፀ። የፊታችን ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስቴዲየም በሚካሄደው ታላቅ ዓለም አቀፍ የቁርአን ውድድር ላይ ከ60 አገራት የሚመጡ 100 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች፣ የልኡካን ቡድን ተሳታፊዎች እንዲሁም ኢንቨስተሮችና ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
በዛሬው ዕለት ምሽት በዚህ ውድድር ላይ የሚሳተፉ የውጭ አገር እንግዶች ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደጀመሩ አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የውድድር መድረኩ ቱሪስቶችን ወደ አገራችን ለመሳብ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የተገለፀ ሲሆን፤ የአገር ገጽታ ግንባታ አበርክቶውም የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በዘይድ እብን ሳቢት የቁርዓን ማህበር አዘጋጅነትና በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት የበላይ ጠባቂነት የሚካሄደውን ይህን የቁርዓን ውድድር አስመልክቶ፣ ባለፈው አርብ ጥር 16 ቀን 2017 ዓ.ም በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል መግለጫ ተሰጥቷል።
ውድድሩ በሁለት መርሃ ግብር የተከፋፈለ መሆኑን ያብራሩት አዘጋጆቹ፣ የመጀመሪያው የማጣሪያ ውድድር በዛሬው ዕለት ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል የተካሄደ ሲሆን፤ ሁለተኛውና የፍፃሜው ውድድር ደግሞ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በዕለተ እሁድ በደመቀ ሁኔታ ይካሄዳል ተብሏል።
ዓለማቀፍ የቁርአንና አዛን ውድድሩ ለመስተንግዶ ከፍተኛ ባጀት እንደሚጠይቅ የተናገሩት አዘጋጆቹ፤ የዚህ ውድድር ባለቤት የኢትዮጵያ ህዝብ በመሆኑ አብዛኛው የፋይንስ ምንጭም ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው ብለዋል።
ለዚህም አጋዥ ይሆን ዘንድ አማራጭ የመግቢያ ትኬቶች መዘጋጀታቸው ተጠቁሟል። የቪአይፒ ትኬት 5ሺ ብር፣ የመደበኛ ትኬት 800 ብርና የተማሪዎች መግቢያ ትኬት ደግሞ በ400 ብር መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ታላላቅ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ትኩረት እንደሚስብ በተነገረለት በዚህ የቁርአንና የአዛን ውድድር፤ ከተለያዩ የዓለም አገራት 100 የሚደርሱ እንግዶች ይመጣሉ ተብሏል። ከአገራቱም መካከል አሜሪካ፣ ህንድ፣ ቱርክ፣ ሩሲያ፣ ኖርዌይ፣ ኳታር፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ አልጀሪያ፣ ፍልስጤም፣ ጅቡቲና ሌሎች አገራት እንደሚገኙበትም ተነግሯል።
የቁርአን ውድድሩ አዘጋጆች እንደሚያስረዱት፤ ይኼ ታላቅ ዓለማቀፍ ውድድር ከሃይማኖቱ ባሻገር ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ነው። በአንድ በኩል ብዝሃነታችንን እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብታችንን ለዓለም የምናሳይበት መልካም አጋጣሚ ነው የሚሉት አዘጋጆቹ፤ ቱሪስቶችን ወደ አገሪቱ ለመሳብም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል ብለው ያምናሉ፡፡ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያለንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርም ፋይዳው የጎላ መሆን ያስረዳሉ።
ለውድድሩ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተሳታፊዎችና እንግዶች ለሳምንት ያህል በመዲናዋ እንደሚቆዩ የገለፁት አዘጋጆቹ፤ ነዋሪው እንግዶቹን ሁሌም በሚታወቅበት ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ እንዲቀበል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የቁርዓንና የአዛን ውድድር ሽልማት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ የተካሄደው የዛሬ 3 ዓመት በ2014 ዓ.ም ሲሆን፤ ይሄኛው ዓለማቀፍ ውድድር ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
ዓለም አቀፍ የቁርአን ንባብ ውድድር ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የእስልምና ሃይማኖት ታሪክ ተመራማሪና ደራሲ የሆኑት ተሾመ ከድር ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ውድድሮች፤ ተሳታፊዎችና ታዳሚዎች ስለ ቁርአንና ኢስላማዊ አስተምህሮ ያላቸውን ግንዛቤ እንዲያሳድጉም ያበረታታል ይላሉ፡፡
በተጨማሪም፤ አስተናጋጅ ሀገራት ተሳታፊዎችን፣ ቤተሰቦችንና ተመልካቾችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን ይስባሉ። ይህም ለአካባቢው ኢኮኖሚና ቱሪዝም ዘርፍ ገቢ እንደሚያስገኝ ይገልጻሉ፡፡
መድረኩ የአስተናጋጅ ሀገር ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶችን ያሳያል፣ ወደፊትም ብዙ አለም አቀፍ ጎብኚዎችን ይስባል፤ ሲሉ መሰል የቁርአን ውድድሮች ያላቸውን ፋይዳ አስረድተዋል፡፡
አዲስ አድማስ እና ተስፋዬ ማሞ
አርቲስት ተስፋዬ ማሞ ሁለገብ የኪነጥበብ ሰው ነው፡፡ በማስታወቂያ ሥራዎቹ ይታወቃል፡፡ ደራሲና የፊልም ባለሙያም ነው፡፡ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅም ነው፤ ተስፋዬ ማሞ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ 25ኛ ዓመትን አስመልክተን ቃለምልልስ አድርገንለታል፡፡
ከአዲስ አድማስ ጋር እንዴት እንደተገናኘና እንደተዋወቀ ያወጋናል፡፡ ጋዜጣው ብዙ ዋጋ እንደተከፈለበትም ይናገራል፡፡ ሁሉንም ከባለቤቱ አንደበት እነሆ፡-
ለመሆኑ ተስፋዬ እና አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደምን ተገናኙ?
ከአዲስ አድማስ ጋር የተገናኘነው ገና ሳትወለድ በፊት ነው። መጀመሪያ የተዋወቅነው ከአሰፋ ጎሳዬ ጋር ነው። አሰፋ የዓለምን ካርታ በአማርኛ ከሰራ በኋላ ማስታወቂያዎችን ይሰራ ነበር። ለፒኤስአይ፣ ለዲኬቲ ኢትዮጵያ የሚሰራቸው ማስታወቂያዎች ነበሩ። እናም፣ እነዚህን ማስታወቂያዎች እኔ ነበርኩ በድምጽ የማነብለት። በዚህ ምክንያት ከአሰፋ ጋር የወንድም ያህል ጓደኛሞች ነበርን። የማንነጣጠል -- አብረን የምንበላ፣ አብረን የምንጠጣ፣ አብረን የምንዞር፣ አብረን የምንውል -- ጓደኛሞች፡፡ እና፣ አሰፋ ህልሙን ሲያልም ጀምሮ አውቃለሁ፤ አዲስ አድማስን። ምክንያቱም አዲስ አድማስ ከመምጣቱ ከዓመታት በፊት -- ጋዜጣው እስከሚወለድበት፣ እስከ 1992 ድረስ ጽሁፎችን ይሰበስብ ነበር። አሪፍ ጽሁፎችን ሲያገኝ ይሰበስባል፡፡ አዲስ አድማስ ላይ ይወጡ የነበሩ የባሴ ሃብቴ ጽሁፎች በሙሉ በዚያ ጊዜ የተሰበሰቡ ናቸው። ጥሩ ጽሁፍ፣ ጥሩ ሃሳብ ካገኘ አንድ ቀን አንድ ነገር “ሊሆን ይችላል” እያለ ይሰበስብ ነበር፡፡ ”አዲስ አድማስ” ተብሎ ስም አይውጣለት እንጂ የሕትመት ስራ እንደሚሰራ ያውቅ ነበር፤ አሰፋ። በዚህም ምክንያት ጽሁፎችን ሲያከማች ነው የቆየው፡፡ እየተረጎምን ጽሁፎችን እናስቀምጥ ነበር። እኔ ዘንድ የ“ሪደርስ ዳይጀስት” በጣም ብዙ ቅጾች ነበሩ፡፡ “ጉድ ሃውስ ኪፒንግ” የሚባል መጽሔቶችም ነበሩኝ። እነዚያን መጽሔቶች ይዘን፣ በእነርሱ ላይ ተመስርተን ሃሳቦችን እንከትብ ነበር። የዓመታት ድምር ሃሳቦች ውጤት ነው አዲስ አድማስን እንዲወለድ ያደረገው። አዲስ አድማስ ከአድማስ አድቨርታይዚንግ ነው የወጣው፤ የአሰፋ መሰረት አድማስ ነውና፣ “አዲስ አድማስ ጋዜጣ” የሚባል ተመሰረተ።
መንገዱ ግን እንዲህ እንደማወራልህ አልነበረም፤ በጣም ከባድና በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንግዲህ ከ1990 በፊት በነበሩት ጊዜያት፣ ገና ከጽንስ በፊት የሃሳብ መብላላቶች ውስጥ ነው አብረን የነበርነው። እንዲያውም የማልረሳው አሰፋ ወሎን በጣም ነበር የሚወደው፤ የወሎን ትውፊቶች፣ ታሪኮቹን በጣም ስለሚወድ፤ እኔም አወራው ስለነበር፤ “ሁኔታዎች ቢመቻቹ እያንዳንዱ የወሎ አውራጃ ውስጥ አንድ አንድ ወር ተቀምጠህ ታሪኮች ተጽፈው ቢመጡ” ይለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ወሎ በጣም ብዙ ትውፊትና በጣም ብዙ ታሪክ ያለበት አገር ስለሆነ፣ እዚያ ድረስ አሰፋ ለጽሁፍ ክምችት በጣም ያስብ ነበር።
እንግዲህ ይህ ሁሉ የጽሁፍ ክምችት ተሰበሰበ፣ አጠቃላይ ሂደቶች ተከናወኑና ወደ ሕትመት ሊገባ ነው። የሕትመት ቅድመ ዝግጅቱ ምን ይመስል ነበር?
የአድማስ አድቨርታይዚንግ ቢሮ ራስ ሆቴል ፊት ለፊት ነው የነበረው። በዚያ ቢሮ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ይሰሩበት ነበር፡፡ አዲስ አድማስ እንደ ጋዜጣ ስም ወጥቶለት፣ ሥራ ለማስጀመር ሲታሰብ ግን ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ፣ አንድ ቤት ለአጭር ጊዜ ተከራየ፡፡ የመጀመሪያው የአዲስ አድማስ የሥራ ቦታ እዚያ ነው የነበረው። ብዙ ሠራተኛ አልነበረውም።
ምን ያህል ሠራተኞች ነበሩ?
አሰፋ ራሱ፣ ሰለሞን ጎሳዬ፣ ሰዓሊው መስፍን ሃብተማርያም፣ የውብዳር የምትባል ጸሐፊ... እና ጌታቸው አበራ ነበረ። በተረፈ አዳዲስ -- ገና ብቅ ብቅ የሚሉ ልጆች ናቸው የነበሩት። እነ ነቢይ መኮንን ያኔ አልመጡም ነበር። ነቢይ በኋላ እዚህኛው ቢሮ ከተቀየረ በኋላ ነው የመጣው። የቅድመ ዝግጅትና የመጀመሪያዎቹ የአዲስ አድማስ ሕትመት የጀመረው እዚህ ንግድ ማተሚያ ቤት አካባቢ የነበረው ቢሮ ነው። እርሱ ቦታውም፣ ሁኔታውም ጥሩ ስላልነበር -- ሦስት ወይም አራት ወር መቆየቱን እርግጠኛ አይደለሁም -- ያን ያህል ጊዜ አልቆየም። ለአጭር ጊዜ ነው የቆየው። እርሱ ተለቅቆ ለም ሆቴል አካባቢ አንድ ሌላ ቢሮ ውስጥ ተገባ። ሲጀመር፣ እንደ ኮቴጅ (ጎጆ) ኢንዱስትሪ በቤተሰብ፣ በጓደኛና በዙሪያው ባለን ሰዎች ነው የተጀመረው። እኔ ሁለት ዓምዶችን ይዤ ነበር፤ “ካሰብነው ይገርማል” የሚል እና አንድ ሌላ “በሳምንቱ ውስጥ ምን አለ? ምን ትጠብቃላችሁ?” የሚል። በኋላ እነ ነቢይ መኮንን መጡ። እነ ሰለሞን ገብረ እግዚአብሔር መጡ፡፡ እነ ሰለሞን አበበ ቸኮል (ሰአቸ) መጡ። ከዚያ እያደገ ሄደ።
አዲስ አድማስ ጋዜጣ መታተም እንደጀመረ በቀላሉ አልተለመደም፤ በርካታ ኮፒዎች ከገበያ ይመለሱ ነበር። ይታተማል፤ ተመልሶ ይመጣል። ለማስለመድ የነበረው መከራ ቀላል አልነበረም፡፡፡ አንዳንድ ሰዎች፤ “አሰፋ፣ ይህ ብርቱካናማ ቀለም ይቀየር፣ ሰውን የሚገፋብን ቀለሙ ነው” ይሉት ነበር። አሰፋ ደግሞ፤ “የአባቴን ቤት እስከመሸጥ እሄዳለሁ እንጂ ይህንን ሎጎ አልቀይረውም። ከአቋሜ፣ ከያዝኩት ስታንዳርድ አንዲት ኢንች ዝቅ አልልም” ይል ነበር። ምክንያቱም ያኔ ጊዜው የገተር ፕሬስ (Gutter Press) -- የእነ”ጎዳናው” -- ጊዜ ነው የነበረው። አሁን ፌስቡክ ላይ እንዳለው፣ መንችፎ የመሮጥ ዓይነት ነገር የለም? በብዛት የሚነበቡት እንደእነርሱ ዓይነት ጋዜጦች ነበሩ። ሆሮስኮፕ ያላቸው፣ የፈረንጅ ታሪኮች ተተርጉመው የሚወጡባቸው ጋዜጦች ነበሩ የተለመዱት። በዚያ መሃል ቁምነገሮችና ዕውቀት የሚያስጨብጥ፣ ፍልስፍናን የተሸከሙ ሃሳቦች ያሉት አዲስ አድማስ ጋዜጣ መጣ። ያልተለመደ ነበር፤ በዚህም የተነሳ በነጻ እስከመበተን ተደርሷል፤ ለማስለመድ፡፡ ምሁሩና የማንበብ ፍላጎት ያለው ሰው ዘንድ እንዲደርስ በጣም ብዙ ተሰርቷል፤ በሸክም ወጥቶ በሸክም እየተመለሰ፣ አዟሪዎች እጅ ላይ ይቆይ ነበር፡፡ ደግነቱ አዲስ አድማስ ሳምንትም፣ ወርም፣ ዓመትም ቆይተህ ብታነብበው፣ አያልፍበትም፡፡ ሁሌም የሚነበብ ጋዜጣ ነው፡፡
እንዲህ እንዲህ እያለ ቀስ በቀስ አዲስ አድማስ በየሳምንቱ ቅዳሜ በናፍቆትና በጉጉት የሚጠበቅ ጋዜጣ ለመሆን በቃ። ግን ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታል፤ ዝም ብዬ ቀለል አድርጌ እንደምነግርህ አይደለም፡፡ ያ ሁሉ ተለፍቶ፣ ያ ሁሉ ጽሁፍ ተጠራቅሞ የሚሰራው ስራ እስኪለመድ እየተመለሰ ሲመጣ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበረ መገመት ይቻላል፡፡ ...persistence የሚባለውን ነገር እኔ ያየሁት ያኔ ነው፡፡ አሰፋ በዚህ በጣም የሚገርም ሰው ነበር፡፡ “የአባቴ ቤት ካስፈለገ ይሸጣል እንጂ አላፈገፍግም” የሚል አቋም ስለነበረው፣ በአቋሙ ጸንቶ ከደረጃው ዝቅ እንዳይል በደረጃው እንዲያድግ አድርጎ፣ በዙሪያውም ሌሎች ብዙ ሰዎች እንዲሰሩ በማድረጉ ምክንያት ነው ለተወዳጅነት የበቃው።
ከመጀመሪያው ዕትም በአዕምሮህ ውስጥ ጎላ ብሎ የሚታወስህ ዓምድ የትኛው ነው?
ጋዜጣው በቂና ሙሉ ዝግጅት የተደረገበት በመሆኑ ምሉዕ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ እያንዳንዱ ዓምድ ራሱን ችሎ የቆመ ነበር፤ አንደኛው ከሌላኛው ጋር የሚነጻጸር አልነበረም፡፡ ሁሉም በራሱ ሙሉ ነው፡፡ ከሳምንት ሳምንት የሚነበብ ጋዜጣ ነው የነበረው፡፡ የካርቱን ምስሎቹ፣ የገጽ ቅንብሩ፣ መልኩ ሁሉ የሚያምር ጋዜጣ ነው። በዝግጅት በአቀራረብና በይዘት፣ በቅንብርም ደረጃ የተስተካከለና የተሟላ እንዲሆን ብዙ ጥረት የተደረገበት ጋዜጣ ነው፡፡ ስለዚህ የምትጥላቸው ጽሁፎች አልነበሩም።
በዚህ መልኩ የጀመረው አዲስ አድማስ የዘለቀበትን መንገድ እንደ አንድ አብሮ እንደነበረና ኋላም በቅርብ ርቀት ሆኖ እንደሚከታተል ሰው የጋዜጣውን ዕድገት እንደምን ነበር የምትገመግመው?
እኔ ረዥሙን ጊዜ ከጋዜጣው ጋር አብሬ ነበርኩ፤ አልጻፍና ወደ ራሴ ስራ አልምጣ እንጂ። ምክንያቱም ከጅማሮ አንስተህ አብረህ የነበርክበት ስራ ወይም አንድ ልጅ ተወልዶ ሲያድግ ዓይንህ መከተሉ አይቀርም። ስለዚህ በተመሳሳይ ሁኔታ አዲስ አድማስን እከተል ነበር። አዲስ አድማስ እንደነገርኩህ ሲጀመር በጣም ከፍ ተደርጎ ነው የተጀመረው፡፡ ስለዚህም ሰዎች አንብበው የማይጥሉት ጋዜጣ ነው የሆነው፡፡ ብዙ ቦታዎች ላይ ክበቦች፣ ትናንሽ የጓደኛሞች ስብስብ ነበሩ፤ አዲስ አድማስን ቅዳሜ ቅዳሜ ጠብቀው ቁጭ ብለው አንብበው የሚወያዩ። አዲስ አድማስ ጋዜጣ የመወያያ፣ የመነጋገሪያ አጀንዳ ነው የነበረው፡፡ ከዚያም በናፍቆት የሚጠበቅ ጋዜጣ ሆኖ ነው የዘለቀው፡፡ በሁሉም ዘንድ የሚወደድ፣ ሁሉም ሰው ሊጽፍበት የሚፈልግ፤ ሃሳቦቹን የሚያንጸባርቅበት፣ ጽሁፎቹን የሚልክበት ጋዜጣ ነው የሆነው፡፡ አዲስ አድማስ ውስጥ ባሉ አዘጋጆችና ተባባሪ አዘጋጆች ብቻ ሳይሆን ከውጭ እንደ ጋሽ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር፣ ኤፍሬም እንዳለ፣ መስፍን ሃብተማርያም ወዘተ ያሉ በርካታ ዕውቅ የብዕር ሰዎች ይጽፉበት ነበር። እነ አብርሃም ረታ ዓለሙን የመሳሰሉ ጸሃፍት ሁሉ የሚጽፉበት ነበር፡፡ አገሪቱ ውስጥ አሉ የተባሉ ጸሃፍት በሙሉ የሚጽፉበት ትልቅ ጋዜጣ ለመሆን የበቃ ነው፡፡
ገጣሚ ነቢይ መኮንን በዋና አዘጋጅነት በጋዜጣዋ ላይ በሰራባቸው ዓመታት የነበረውን ሚና እንዴት ትገልጸዋለህ?
አየህ፣ አሰፋ አርቆ አሳቢ ነበር። አርቆ አሳቢ በመሆኑ ምክንያት አዲስ አድማስ ጋዜጣን ሲጀምር፣ እንደገና “አድማስ ፕሮዳክሽን” በሚል -- ወደ ቴሌቪዥን የማደግ ፍላጎት ነበረው---- እሱን ለማቋቋም ሲሰራ፣ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የጋዜጣውን ሃላፊነት ለነቢይ ሰጥቶት ነበር። ነቢይ ደግሞ ከአድማስ በፊት በሜጋ ኪነ ጥበባት መጽሔት ያዘጋጅ ስለነበር፣ መልክ ያለው ጋዜጣ እንዲሆን አድርጎታል። ነቢይ ጥሩ ኤዲተር ነው። የቋንቋ ችሎታው በጣም አስደማሚ ነው። ሃሳብን የማዋዛት አቅሙ የላቀ ነው፡፡ በተረት እያዋዛ የሚጽፋቸው ርዕሰ አንቀጾቹ ጎልተው ወጡ እንጂ የግጥም ጥጎቹ ራሳቸው የሚገርሙ ነበሩ። በየሳምንቱ “የግጥም ጥግ” በሚል ግጥሞች የሚያወጣበት ጥግ ነበረው፡፡ ነቢይ አትኩሮ ይሰራ በነበረባቸው ዘመናት ሁሉ ጋዜጣው መልክ ኖሮት እንዲቀጥል የሚችለውን ያህል ጥረት አድርጓል።
የኢሮብ ሕዝብ በኤርትራ ጦር በደል እየደረሰበት ነው ተባለ
የኢሮብ ሕዝብ በኤርትራ ጦር በደል እየደረሰበት መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፤ የፌደራል መንግስት ይህንን በደል ለማስቆም ምንም ያደረገው ነገር የለም ሲል ተችቷል።
“የትግራይ ሕዝብ አሳር ሊያበቃ ይገባል” በሚል ርዕስ የኢሕአፓ የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባለፈው ረቡዕ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ አንዳንድ የትግራይ ክልል ወረዳዎች ከነሐሴ 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በኤርትራ ጦር መያዛቸውን አመልክቷል። በተለይም “ከፍተኛ በደል እያስተናገደ ነው” ሲል ፓርቲው የጠቀሰውን የኢሮብ ሕዝብ ለመታደግ የፌደራል መንግስት “ምንም ዓይነት መፍትሔ” ሲሰጥ አለመታየቱን ጠቅሷል።
አያይዞም፣ የኤርትራ ጦር የኢሮብ ወጣቶችን በገፍ እያፈሰ ወደ ሳዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋም እየወሰዳቸው እንደሚገኝ የጠቆመው ኢሕአፓ፤ “የትምሕርት ስርዓቱን በመቀየር በኤርትራ የትምሕርት ስርዓት እያስተማረ ይገኛል” ሲል በመግለጫው አትቷል። “ከፍተኛ የአገር ሉዓላዊነት ወረራ” መሆኑን የጠቆመው ፓርቲው፤ የፌደራል መንግስቱ ድርጊቱን የማስቆም ሃላፊነት እንዳለበት አሳስቧል።
በሌላ በኩል፣ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈልና መወነጃጀል የትግራይ ሕዝብ ሰላምና መረጋጋትን እንዳያገኝ ማድረጉን ፓርቲው አስታውቋል። “እነዚህ በሕዝብ ስም እየማሉ ሕዝብን ለመከራ በዳረጉ ሁለት ሃይሎች የመከኑ ፍላጎቶች የተነሳ የትግራይ ሕዝብ ሁሌም ከጎረቤቶቹ ጋር ጦርነት እየተማዘዘ ሰላም ርቆት ሊኖር አይገባም” ብሏል።
“ሕጋዊ እና ፍትሐዊ” ምርጫ ተካሂዶ የትግራይ ሕዝብ በእንደራሴዎቹ እስኪወከል ድረስ ሁሉንም ሕጋዊ ፓርቲዎች ያካተተ የመማክርት ምክር ቤት እንዲቋቋምም ኢህአፓ ጠይቋል። በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው ውዝግብ የተነሳ የተፈጠሩት ሁለት አንጃዎች “በንግግርና በመቻቻል” አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀት እንዳለባቸውም ፓርቲው አሳስቧል።
“በኢትዮጵያ ያሉ ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግራይ ሕዝብን የረሱት በሚመስል ሁናቴ አንድም ቀን ስለሕዝቡ ሲጨነቁ አይታይም” በማለት የነቀፋው ኢሕአፓ፤ አገራዊ ፓርቲዎች “ስለትግራይ ሕዝብነ ሲሉ ፖለቲካዊ መፍትሔ ማበጀት” ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደገና እንዲዋቀር ወታደራዊ አመራሮች ወሰኑ
አንዳንድ ወታደራዊ አመራሮች ውሳኔውን አልተቀበሉትም
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንደገና እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፋቸውን የክልሉ ወታደራዊ አመራሮች አስታውቀዋል። አመራሮቹ ጊዜያዊ አስተዳደሩን አምርረው በመተቸት፣ የአስተዳደሩን አመራሮች “የውጭ ሃይሎች መሳሪያ ሆነዋል“ ሲሉ ከስሰዋል።
ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. ወታደራዊ አመራሮቹ በትግራይ ክልል ለሚገኙ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል። “በትግራይ ሃይሎች ላይ የሚካሄደውን የስም ማጥፋት ዘመቻ መከላከል አልቻለም” ሲሉም ተችተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ውስጥ ይስተዋላል ላሉት አጠቃላይ ችግር ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚያሻ የጠቀሱት እነዚሁ አመራሮች፤ “ማንኛውም ነገር ከትግራይ ሃይሎች አቅም በላይ አይደለም።” ሲሉ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡ “ይህንን ሰበብ በመጠቀም የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አንቀበልም” ሲሉም አክለዋል፡፡
በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው ህወሓት በጊዜያዊ አስተዳደር ያለውን ከ50 በመቶ የዘለለ (50+1) ድርሻውን እንዲረከብ ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት አመራሮቹ፤ “በትግራይ ክልል የሚገኙ ታጣቂዎች በትግራይ ሰላምና ጸጥታ ሴክሬታሪያት ስር መሆን አለባቸው። ከዚህ ውጪ በሆነ ወገን ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ባለፈው ነሐሴ ወር 2017 ዓ.ም. በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በሚመራው ህወሓት ለተካሄደው 14ኛ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔ ዕውቅና መስጠታቸውንም ወታደራዊ አመራሮቹ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም፤ በጉባኤው ውሳኔ መሰረት፣ የጊዜያዊ አስተዳደር የአመራሮች ለውጥ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
“በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ወሳኝ ስልጣን ያላቸው አመራሮችና አባላት ከተሰጣቸው ተልዕኮ ውጪ የሕዝብን ጥቅም ወደ ጎን በመተው ክህደት ፈጽመዋል። የውጭ ሃይል መሳሪያ ሆነዋል” ያሉት ወታደራዊ አመራሮቹ፤ “በፕሪቶሪያ ስምምነት መሰረት የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም” የሚል ክስ አቅርበዋል። በዚህም ሳቢያ፣ “የተዳከመ ነው” ሲሉ የሰየሙት፣ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተነስቶ በምትኩ ሌላ አስተዳደር እንዲዋቀር መወሰናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ይሁንና የወታደራዊ አመራሮቹ ጋዜጣዊ መግለጫ “አይወክለንም” ያሉ ሌሎች ወታደራዊ አመራሮች ደግሞ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ኮንነው መግለጫ ያወጡትን ወታደራዊ አመራሮች “አደገኛ አቋም ነው” በማለት ነቅፈውታል። ይህ መግለጫ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ፍጭት ከማባባስ ውጭ የሚበጀው ነገር እንደሌለ ያመለከቱት በሃሳብ “ተለይተናል” ያሉት ወታደራዊ አመራሮች፤ “ከዚህ ከፋፋይ የፖለቲካ ጨዋታ ራሳችንን በማራቅ፣ ከታሪክና ከትውልድ ተጠያቂነት ዕዳ እንድንላቀቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ፤ “ከተልዕኳቸው ውጭ ለአንድ ሕገ ወጥ ቡድን ወግነው ጊዜያዊ አስተዳደሩን የማፍረስ፣ ስርዓት አልባነት የማንገስና ሰራዊቱን የመበተን ግልጽ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸውን አሳውቀዋል” በማለት የወታደራዊ አዛዦቹን መግለጫ ወቅሷል። “ሕጋዊም ይሁን ሞራላዊ ቅቡልነት የሌለው” ሲል መግለጫውን ያጣጣለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ “የፕሪቶሪያ ስምምነትንም ለአደጋ የሚያጋልጥና ሃላፊነት የጎደለው ነው” ብሏል፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ አመሻሽ ላይ በይፋዊ የማሕበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው ማብራሪያ።
የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር የሚነቅፍ መግለጫ ያወጡት ወታደራዊ አመራሮች ከጥር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ስብሰባ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፤ በስብሰባው ላይ ሲሳተፉ የነበሩ አመራሮች ብዛት ወደ 200 ገደማ እንደሚጠጋ ለማወቅ ተችሏል። በአንጻሩ፣ ይህንን የወታደራዊ አመራሮች ጋዜጣዊ መግለጫ የነቀፉና ተጻራሪ መግለጫ ያወጡ ወታደራዊ አዛዦች ብዛት ከ12 በላይ እንደሚሆን ተነግሯል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ ነው
በቀጣይ ዓመት ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ ነው
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የተመሰረተበትን 70ኛ ዓመትና የማስተማሪያ አጠቃላይ ሆስፒታሉን የመቶኛ ዓመት ምስረታ በዓል በተለያዩ መርሃ ግብሮች ማክበር ጀምሯል። ባለፈው ረቡዕ ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በተገኙበት በይፋ የተከፈተው ክብረ በዓል፤ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል።
በ1942 ዓ.ም ኢትዮጵያ የጤና ሰራተኞች እንደሚያስፈልጋትና የጤና አጠባበቅ ትምህርት የሚቀስሙበት ማሰልጠኛ ተቋም እንዲከፈት የዓለም የጤና ድርጅት ማሳሰቡን ተከትሎ ነው የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የተቋቋመው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያዊያን የጤና ባለሙያዎች ስላልነበሩ ወጣቶች እየተመረጡ ውጪ ሐገር እንዲሰለጥኑና የጤና አጠባበቅ ሰራተኞች በሃገር ውስጥ የሚሰለጥኑበት ተቋም እንዲመሰረት የተወሰነ ሲሆን፤ መስከረም 24 ቀን በ1947 ዓ.ም የጎንደር ጤና አጠባበቅ ኮሌጅ ከሐሳብ ወደተግባር መቀየሩን የዩኒቨርሲቲው ታሪክ ይጠቁማል፡፡
ምስረታው እውን እንዲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የዓለም የጤና ድርጅትና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት የተባበሩ ሲሆን፤ በወቅቱ “የጎንደር ጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ” በሚል ስያሜ መቋቋሙ ተገልጿል። በዚሁ የምስረታው ዓመት በአገር ግዛት ሚኒስቴር ስር አንድ ዘርፍ ይዞ የነበረው የህዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በመባል ከፍ ባለ ደረጃ እንዲመራ በነጋሪት ጋዜጣ አዋጅ ቁጥር 91 መታወጁን የሚያትተው የዩኒቨርሲቲው ታሪክ፤ በ1948 ዓ.ም ደግሞ በሐገሪቱ የሚካሄደው ማንኛውም የጤና ትምህርት በሕዝብ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር እንዲተዳደር በመታዘዙ፣ ይህ የማሰልጠኛ ተቋምም በሚኒስቴሩ አመራር ስር እንዲውል መደረጉ ተመልክቷል። ማሰልጠን ከመጀመሩ በፊትም፣ የጤና ማሰልጠኛ ጣቢያ የሚል ስያሜውን በ1947 ዓ.ም ስራውን ሲጀምር፣ የጎንደር ህዝብ ጤና ጥበቃ ኮሌጅና ማሰልጠኛ ወደሚል ቀየረ። ከዚህ በኋላ ብዙ ሂደቶችን ያለፈው ኮሌጁ፤ ከጤና ዘርፍ ውጪ በርካታ የትምህርት ዘርፎችን አካትቶ፣ በ1996 ዓ.ም ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ወደሚል ስያሜ መሸጋገሩን ፕሬዚዳንቱ አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) አብራርተዋል።
ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበትን 70ኛ ዓመት እያከበረ ባለበት በዚህ ወቅት 11 ኮሌጆች ፣ 87 ቅድመ ምረቃ እና 280 ድህረ ምረቃ፣12 የምርምር ማዕከላት፣ ከተለያዩ ወረዳዎች እስከ መዲናዋ አዲስ አበባ ድረስ 22 የምርምርና የስልጠና እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት መስጫ ግቢዎች ያሉት አንጋፋና ግዙፍ የትምህርት ልህቀት ማዕከል መሆኑ ተነግሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ከ40 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ የሚገኝ አንጋፋ የልህቀት ማዕከል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያዎቹን ተማሪዎች በ1958 ዓ.ም ያስመረቀ ሲሆን፤ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እስከ 2016 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለሃገሪቱ የሰለጠነ የሰው ሃይል በማበርከትም ሚናው የጎላ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለሃገራቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 10 ሰዎች የክብር ዶክትሬት የሰጠ ሲሆን፤ በቀጣይ ዓመት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ለመሆን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝና በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚገኙ ከ150 በላይ አጋር ተቋማት እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል።
ከጣሊያን ወረራ ጊዜ ጀምሮ ታሪክ ያለው የዩኒቨርስቲው አጠቃላይ የማስተማሪያ ሆስፒታል፤ ለጎንደርና ለአካባቢው ህዝብ ጤና ታሪክ የማይዘነጋው ውለታ መዋሉ የተገለፀ ሲሆን፤ 100ኛ ዓመቱን መድፈኑ ታሪኩን ያጎላዋል ተብሏል። በጎንደር ከተማ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብቸኛው ሆስፒታል በመሆን በማከም፣ በምርምር፣ በግንዛቤ ማስጨበጥና በማስተማሪያነት ያገለገለው ይሄው ሆስፒታል፤ አሁንም ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢ ዎች ለሚመጡ ከቤኒሻንጉልና ከሱዳን ጭምር ለሚመጡ በአጠቃላይ ለ13 ሚሊዮን ህዝብ ሪፈራል ሆኖ እያገለገለም ነው ተብሏል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ልህቀትና በጤና አገልግሎት የደረሰበትን የ70 እና የመቶ ዓመት ስኬት፤ ከጥር 14 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበረ እንደሚቆይ የተገለጸ ሲሆን፤ ከመርሃ ግብሮቹም መካከል ሩጫን ጨምሮ ስፖርታዊ ውድድሮች፣ ነፃ የጤና ምርመራ፣ ደም ልገሳና ሌሎች የማህበረሰብ አገልግሎቶች ይገኙበታል፡፡ የጎንደር ቃልኪዳን ቤተሰብ ቀን፣ የህክምና ተማሪዎች ምረቃ በዓል፣ የታዋቂ ሰዎች ስኬትና ተሞክሮ ማካፈያ መድረክ፣ የፕሮጀክት ስራዎች ምርቃት፤ የአውደ ርዕይ መርሃ ግብር፣ የጥናትና ምርምር ጉባኤና ሌሎችም የመርሃ ግብሩ አካል እንደሚሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የበዓል አከባበሩ ከዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመት አከባበር ልምድና ከውጪ አገር ተሞክሮ ተቀምሮ ትላንትን፣ ዛሬንና ነገን የሚያስተሳሰር ታሪካዊ አከባበር እንዲሆን ታስቦ ከፍተኛ ዝግጅት እንደተደረገበት ፕሬዚዳንቱ አስራት አፀደወይን (ዶ/ር) አብራርተዋል።
የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር መጠን ከፍተኛ መሆኑ እንቅፋት ፈጥሯል
የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር መጠን ከፍተኛ መሆኑ እንቅፋት ፈጥሯል ተብሏል። የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት፣ ባንኮች ለአምራች ዘርፍ ሲያቀርቡት የነበረው ከ13 በመቶ የማይበልጥ የብድር አቅርቦት ድርሻ ወደ 24 በመቶ እንዲያድግ የፖሊሲ አቅጣጫ ቢሰጥም፣ የብድሩ ድርሻ ግን እስካሁን ከ16 በመቶ አልበለጠም።
ከትላንት በስቲያ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም. የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት አቶ መላኩ፤ ለከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች 28 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በብድር መልኩ ለማቅረብ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከዕቅዱ የተሳካው 24 ነጥብ 87 ቢሊዮን ብር መሆኑን አብራርተዋል። ይህ ብድር ከዕቅዱ አንጻር ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ግን 4 ነጥብ 9 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
ባንኮች ለአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ስራ ማስኬጃ የሚሰጡት ብድር ካላቸው ካፒታል ከ1 በመቶ ያልበለጠ እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት ግን ድርሻው ወደ 10 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ገልጸዋል።
“የኢትዮጵያ ባንኮች ለአምራች ኢንዱስትሪው ፋይናንስ ከማቅረብ ይልቅ በተለመደው መንገድ የአጭር ጊዜ ትርፍ በሚያስገኙና ስጋታቸው ዝቅተኛ በሆኑ ዘርፎች ላይ እንደተሰማሩ እንዳይቀጥሉ ማድረግ የሚቻልበትን አሰራር መፈተሽ ይገባናል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ በዚህ ረገድ መንግሥት በቀጣይ ሊወስድ የሚችለውን እርምጃ ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ለአምራች ዘርፉ የግብዓት አገልግሎት ለማቅረብ ታቅዶ ከነበረው 468 ሚሊዮን ዶላር ማቅረብ የተቻለው 369 ሚሊዮን ዶላር ገደማ መሆኑን በመግለጽም፣ባንኮች የሚጠይቁት ማስያዣ ብር መጨመሩ ለዕቅዱ አለመሳካት ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ባንኮች ለአምራች ዘርፍ ሲያቀርቡት የነበረው ከ13 በመቶ የማይበልጥ የብድር አቅርቦት ድርሻ ወደ 24 በመቶ እንዲያድግ የፖሊሲ አቅጣጫ ቢሰጥም፣ የብድሩ ድርሻ ግን እስካሁን ከ16 በመቶ አለመብለጡን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ባንኮች የሚጠይቁት የማስያዣ ብር መጠን “ከወትሮው ከፍ ያለ” በመሆኑ ምክንያት በታቀደው ልክ ስኬታማ ለመሆን እንቅፋት መፍጠሩን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ “ከተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘ የብር ፍላጎት መጠን በእጥፍ ስለጨመረ፣ አቅርቦቱ ‘አጥጋቢ ነው’ ተብሎ ሊወሰድ የሚችል አይደለም” ሲሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል። ዘርፉ የሚፈልገውን በቂና ውጤታማ ፋይናንስ ለማቅረብ ባንክ እና ባንክ ነክ ያልሆኑ ሌሎች የፋይናንስ ምንጮችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።
“ሰማኒያውን ነህ… ዘጠናውን ነህ ወገቤን የያዝከኝ ገላጋይ መስለህ?!”
ሁለት ዕውቅ ሽማግሌዎች ወዳጃቸው ለሆነ አንድ ሽማግሌ፤ “ሴት ልጅህን ለልጄ ስጠኝ” እያሉ በተራ በተራ መልዕክተኛ ላኩበት። ያም ሽማግሌ መልክተኞቹን በተራ በተራ አስተናገዳቸው። ለመጀመሪያው መልዕክተኛ፡- “መልካም፤ ልጄን ለልጅህ እሰጥሃለሁ ግን ቤትህን አሰናዳ ብለህ ንገረው” ብሎ ይልክበታል።
ለሁለተኛው መልዕክተኛም፤ “ና ቅረብ ወዳጄ። ለጌታህ ስትለው፤ ደግ ነው ልጄን ለልጅህ ልድራት ዝግጁ ነኝ፤ ሆኖም አስቀድመህ ቤትህን አሰናዳ” አለው። መልዕክተኞቹም-እርስ በእርሳቸው የተባሉትን ሳይነጋገሩ ወደ ጌቶቻቸው ሄዱ።
አንደኛው መልዕክተኛ ወደ ጌታው ሄዶ፤ “ጌታዬ ጥያቄውን አቅርቤ ነበር። ነገር ግን የ3 ወር ጊዜ ሰጥቼሃለው፤ ቤትህን አሰናዳ በለው” አሉ።
በመጀመሪያ መልሱን የሰማው ሽማግሌ ለልጁ፤ “በል ወዳጄ ሦስት ወር ቅርብ ጊዜ ነው፤ በያለበት መሬት እየገዛህ እልፍኝና አዳራሽ ሥራ፡፡ ለሚስትህና ላንተ መቀመጫ ይደላሃል” አለው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ መልሱን የሰማው ሽማግሌ ግን፤ “ያጅሬን ብልሃት እኔ አውቃለሁ። በል ልጄ ተነስተህ ገንዘብ ይዘህ ሄደህ ወዳጅ አብዛ። እስካሁን የምታውቀው ሰው በቂ አይደለም። ቤትህን አሰናዳ ማለቱ ትርጉሙ ይሄ ነው።”
የተባለው ቀን ሲደርስ አባት ደግሶ ይጠባበቅ ኖሯል። ሁለቱ አባቶች በሰዓቱ ከች አሉ። ከተጋበዙ በኋላም አንደኛው፤ “መሬት ገዝቼ ለልጄ ሰጥቼዋለሁ።” ሲል ተናገረ።
የሠርጉ ባለቤትም፤ “የምድር ብዛት ከቁም-ነገር አይውልም። ባንድ ስተት ቀሪ ነው። እልፍኝና አዳራሹንም አውሎ ነፋስ ይጠርገዋል። የእሳት እራትና ምሳ ነው። ውሃ ሙላት ያጠፋዋል። ጠንቅ አያጣም” አለው።
ቀጥሎም ሁለተኛው አባት፤ “ገንዘብ ይዘህ ሂድ፤ ወዳጅ አብዛ” ብዬዋለሁ አለና አስረዳ። የሠርገኛው አባትም፤ “ሌላ ሀብት ሁሉ ጠፊ ረጋፊ ነው። ብዙ ወዳጅ ግን በየቦታው ቢፈራ ሀብት ነው። ጥቅምም ካንዱ ቢጠፋ ካንዱ ይገኛል፤ አንዲት ልጄን ለዚህ ልጅ መርቄ ሰጥቼዋለሁ” አለ።
* * *
ህዘብ የሚወደው መሪ ማግኘት ታላቅ ጸጋ ነው። ወዳጅ ለማፍራት የሚችል መሪ ማግኘት መታደል ነው። ለራሱ ማረፊያ እልፍኝ - ከአዳራሽ የሚሰራ መሪ ማግኘት ከቁምነገር የሚጻፍ አይደለም። ባንድ ስተት ቀሪ-ነው፤ አውሎ ንፋስ ይጠርገዋል። ህዝብ የክብሩ ምልክት የሚሆንለት መሪ ይፈልጋል። ተናግሮ የሚያጠግበው መሪ ይፈልጋል። እምነቱን የሚጥልበት፣ ለሾመው የሥልጣን ዘመን የሚበቃ ጥንካሬ ያለው ርዕሰ-ብሔር እንዲኖረው ይመኛል። በእርግጥም ህዝብ ሆደ-ሰፊ፣ እንደ ወጣት የማይቸኩል፣ በረዥምና በበሳል አካሄድ እንጂ በቆረጣ የማይመካ፣ ብልጥ ሳይሆን ብልህ የሆነ፣ የዕውቀት-የልምድና የዕድሜ ባለፀጋ የሆነ እንደራሴ ይፈልጋል።
የሀገር መሪ ሲመረጥ እንደ ቴአትር ገፀ-ባህሪ ለአንድ ወንበር (ሚና) ሁለት ሰው የሚሰለጥንበት (Double-cast እንደሚባለው) የመጠባበቂያ ሂደትም ሆነ መለዋወጫ የለውምና፣ አካላዊና አዕምሮአዊ ይዞታውና ብቃቱ በቅጡ መጤን ይኖርበታል።
የሕዝብ ስነ-ልቦናን የሚያሸንፍ መሪ የህዝብን ተስፋ ያለመልማል። መሪው ተስፋ የማይጣልበት ከሆነ፣ ተመሪውንም ይዞት ወደ ጨለምተኛ አቅጣጫ ያመራል። ዣን ፖል ሮችተር እንዳለው፤ “የእርጅና አሳዛኙ ነገር፤ ደስታችን ማለቁ ሳይሆን፤ ተስፋችን ጨርሶ መሟጠጡ ነው”። ተስፋ ያለው መሪ፤ የሆነ እንደሆነ ለነገ መቅረዝ ያበራል። ልምዱን፣ እውቀቱን፣ ደርዙን እንደ ሻማ እያቀጣጠለ የመጪውን ቀን ተስፋ የማያሳይ መሪ፣ አለቃ ወይም ሹም ከሆነ ግን ጭል-ጭል ትል የነበረችውን ነግ- ተነግ- ወዲያ ራዕይ ይጋርዳል። እርጅና ፀፀት የሚያመጣው ያልተዘጋጁበትን ቦታ እንደማታ-ሲሳይ፣ እንደማታ-እንጀራ ቆጥረው ሲቀመጡ ነው። “ምነው እዚህ እንደምደርስ ባወቅሁ፣ ራሴን በተሻለ ጠብቄ እቆይ ነበር” እንዲል ኡቢ ብሌክ፤ በስተርጅና የሚገኝ ሥልጣን ከትፍስህቱ ጭንቀቱ፣ ከተስፋው ፀፀቱ ይብሳል፡፡ እንደ ኖስትራ ዳሙስ The man who saw tomorrow ማለታችን ይቀርና The Man who’ll see Yesterday የሚል ዓይነት፤ ምስቅልቅል ውስጥ ሊከተንም ይችላል። (ራዕያችን ነገን አስቀድሞ ማየት መሆኑ ይቀርና፤ ትላንትን ነገ ለማየት መቋመጥ ይሆናል እንደማለት ነው።)
“የአንበሳ መንጋ መሪ በግ ከሚሆን ይልቅ፣ የበግ መንጋ መሪ አንበሳ ቢሆን ይሻላል” ሲል የፃፈልን ዳንኤል ዴፎ፤ የአገርን ምልክት፣ የአገርን መኩሪያ፣ የአገርን ወኪል፣ የኢገርን እንደራሴ ጉልህ ገጽታ አበክሮ ሲገልጽልን ነው። አንድም “ምነው ወጣቱ ባወቀ፣ ምነው ሽማግሌው መሥራት በቻለ” የሚለው የፈረንሳዮች አባባል፣ የዕውቀትንና የሥራን ኅብራዊ አስፈላጊነት ሲያሳየን ነው።
የነፃነትን፣ የፍትሕን፣ የመብት መከበርን ፍቱን አስፈላጊነት ከመቼውም በበለጠ እያየች፣ በላቀ ሁኔታም እየተገነዘበች፣ በመጣችው ሀገራችን ውስጥ ለዚህ እውን መሆን ብርቱ ጥረት የሚያደርጉ ብቁ ዜጎችን እንሻለን። ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ The Young man knows the rules the old man knows the exceptions (ወጣቱ በህግ የሚፈቀደውን ያውቃል፤ ሽማግሌው በሕግ የሚከለከለውን ያውቃል) ብለን እንዳናልፍ የሀገር ክብር፣ የመንበሩ ልዕልናና የታሪክ አደራ እንቅልፍ ይነሱናል።
ለአንድ የኃላፊነት ቦታ የብቃት መመዘኛ የዚህ ወይም የዚያ ብሔር-ብሔረሰብ መሆኑ እንዳይደለ መቼም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ሳንረዳው አይቀርም፡፡ በተግባር መከወኑ ላይ ባይሳካልንም፡፡
የአእምሮ መትባት፣ የአንጎል ብስለት፣ የእውቀት ደረጃና የሙያ ክህሎትና ሥነ-ምግባር እጅግ ወሳኝ የመሆኑን ያህል፤ የእነዚህ ሁሉ ማቀፊያ የሆነው አካላዊ ውሃ-ልክና ጤነኛነት፣ እንዲሁም የእድሜ ልከኛነት የዚያኑ ያህል ወሳኝ ነው። ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ኃላፊነትና ሥልጣን አካላዊ ሸክም ሲሆን፤ ውሎ አድሮም አዕምሮአዊ ጭንቀት ወደመሆን እንዳይሄድ መስጋት ተገቢ ነው። “አይቶ ነው ገምቶ ነው…” እንዲሉ ዕድሜንም አቅምንም አገናዝቦ ኃላፊነትን መቀበል ደግ ነው። አለበለዚያ እድሜ እየገፋ ሲሄድ፤ ህዝብንም “ማንስ ቢወክልህ ምን ቸገረህ?” ብሎ እንደመናቅ ያለ ክፉ ደዌ የለም። ሌላ “ጥገኛ ዝቅጠት” መጋበዝም ይሆናል ዞሮ ዞሮ። ደግሞምም የሁሉም ኃላፊነት ነው- የአጪም፣ የታጪም፣ የ”እሰይ-አበጀህ የእኛ ሎጋ!” ባይ ታዳሚም። አለበለዚያ፤
“ሰማንያውን ነህ
ዘጠናውን ነህ
ወገቤን የያዝከኝ ገላጋይ መስለህ!”
ማለት ይመጣል። ኃላፊነቱም አጠያያቂ ይሆናል። ሁሉም ጥንቃቄ ያሻዋል።
የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ ከአገራዊ የምክክር ሂደት ራሱን አገለለ
ከአገራዊ የምክክር ሂደቱ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው የሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲ፤ “አገራዊ የምክክር ሂደቱ መደበኛ ሕዝባዊ ውይይት እየመሰለ ሂዷል” ሲል ተቸ።
ባለፈው ረቡዕ ጥር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ፓርቲው ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንደገለፀው፤ “አካታች” እና “ገለልተኛ” ምክክር የሚካሄድበት ዕድል ስለሌለ ራሱን ከምክክር ሂደቱ አግልሏል። አክሎም፣ የምክክር ኮሚሽኑ “ከገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ” ውጪ መሆን አለመቻሉን ጠቅሷል።
የምክክር ሂደቱ የሃሳብ ልዩነት ያላቸውንና “የግጭቶቹ ተዋናይ የሆኑትን አካላት ያላሳተፈ”፣ “ጦርነቶች እንዲቆሙ በማድረግ አስቻይ ሁኔታን ያልፈጠረ” መሆኑን ፓርቲው አመልክቷል። ይህም ሁኔታ ከአጀንዳ ልየታ ሂደት ጀምሮ ሲስተዋል መቆየቱን ጠቁሟል።
ምክክሩ “መደበኛ ሕዝባዊ ውይይት እየመሰለ ሄዷል” ያለው ፓርቲው፣ አሁን ኮሚሽኑ እየተከተለ ባለው መንገድ “የተወሳሰቡ” ያላቸው የአገሪቱ ችግሮች እንደማይፈቱ በጽኑ እንደሚያምንም ነው ያስረዳው። ፓርቲው ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመ ወዲህ፣ በመንግስት አካላት በተለይም የክልሉ መንግስት ከዚያ በፊት ከነበረው “በከፋ ሁኔታ” ዕመቃ እንደተፈጸመበት አብራርቷል።
በዚህ ምክክር መሳተፍ ችግሮችን የሚፈታ ውጤት ያመጣል ብሎ እንደማይጠብቅም ፓርቲው አመልክቷል። የምክክር ሂደቱ አሁን ባለው ቁመና “ከገዢው ፓርቲ ፍላጎት ውጪ ለሌሎች አስቻይ ሁኔታ መፍጠር የማይችል፣ አካታችና ሃቀኛ አገራዊ ምክክር በማድረግ ውስብስብ ችግሮቻችን በምክክር ለመፍታት የሚያስችል አቅምና ቁርጠኝነት የሌለው መሆኑን” እንዳረጋገጠ በደብዳቤው ላይ ጨምሮ አትቷል።
ኮሚሽኑ በነሃሴ ወር 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት፣ ከፓርቲው ከታገዱ ግለሰቦች ጋር በመተባበር የፓርቲው ተወካዮች ከመድረኩ ተገድደው እንዲወጡ “አድርጓል” በማለትም ፓርቲው ከስሷል። አያይዞም፣ ፓርቲው “ይህም የተደረገው በዲሲፕሊን ከተሰናበቱ የፓርቲውን ሰዎች ቀድሞውኑ በማስገባትና ከእነርሱ ጋር በማበር ነው” ያለ ሲሆን፣ ቦርዱ ችግሩን ለማስተካከል ከፓርቲው አመራር ጋር ተወያይቶ ከስምምነት ላይ የደረሰ ቢሆንም፣ በተስማማው መሰረት ምንም ዓይነት እርምጃ አለመውሰዱን ነው የጠቀሰው።