Administrator

Administrator

የኬንያ ፖሊስ በህገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ገብተዋል ያላቸውን 13 ኢትዮጵያውያን ባለፈው ረቡዕ ምሽት በመዲናዋ ናይሮቢ በቁጥጥር ስር ማዋሉንና ለፍርድ ለማቅረብ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ዥንዋ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡
በህገወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ ገብተዋል የተባሉት ኢትዮጵያውያኑ፣ በመዲናዋ ናይሮቢ በተከራዩት አንድ ቤት ውስጥ ለቀናት ተደብቀው እንደቆዩ የጠቆመው የከተማዋ ፖሊስ፤ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሊያሸጋግራቸው የተስማማን አንድ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በመጠበቅ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን ሁሉም ወንዶች ሲሆኑ በተለያዩ ወንጀሎች ተከስሰው ቅጣት እንደሚጣልባቸውና ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ ያስታወቀው ፖሊስ፣ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪውንና በወንጀሉ ተሳትፈዋል ያላቸውን ሁለት ሴቶች በቁጥጥር ስር ለማዋል ዘመቻ እንደጀመረም ገልጿል፡፡
ወደ ታንዛኒያ እና ደቡብ አፍሪካ ለመሻገር በማሰብ፣ በህገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ገብተው የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የጠቆመው ፖሊስ፤ በየአመቱ እስከ 100 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በኬንያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚውሉም አመልክቷል፡፡

    የሬድዮ እናቴሌቪዥን ፍቃድ የመስጠትና የመቆጣጠር ተግባር የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በተደጋጋሚ ለአመልካቾች ማስታወቂያ ቢያወጣም በክልል የግል የንግድ ሬድዮ ጣቢያ ለመክፈት ፍላጎት ያለው አካል አለመገኘቱን አስታውቋል፡፡
ባለስልጣኑ ከሠሞኑ የግል ሚዲያዎችን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ዳሠሣዊ ጥናቱ ላይ የሬድዮ ፍቃድ መስጠት ከተጀመረ ጀምሮ 10 የግል ሬድዮ ጣቢያዎች በአዲስ አበባ ፍቃድ የወሠዱ ሲሆን አንደኛው እስካሁን ስራ አልጀመረም ተብሏል፡፡
በተደጋጋሚ በየክፍልቹ የግል ሬድዮ ጣቢያ ለመክፈት ለሚፈልጉ ባለሃብቶች የውድድር ማስታወቂያዎች ማውጣቱን የጠቆመው ባለስልጣኑ እስከዛሬ አንድም አካል ፍቃድ ወስዶ ለመስራት ፍላጎት አላሣየም ብሏል፡፡
በአዲስ አበባ የተከፈቱ የግል የሬድዮ ጣቢያዎችም ቢሆኑ ብዙ ርቀት የማይደመጡ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የተወሠኑ ከመሆናቸውም በላይ የይዘት ችግር አለባቸው ብሏል ባለስልጣኑ፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ የኤፍ ኤም የግል ሬድዮ ጣቢያዎች የአየር ጊዜያቸውን በአመዛኙ በስፖርት እና በመዝናኛ ጉዳዮች እንደሚሸፍኑ የጠቆመው የባለስልጣኑ ዳሠሣዊ ጥናት በዚህም በሃገሪቱ የሚፈልገውን ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር በኩል የሚጠበቅባቸውን ሚና መጫወት አልቻሉም ብሏል፡፡
በይዘታቸው በማህበራዊ፣ በፖለቲካዊ፣ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ በየጊዜው ባለስልጣኑ ከብሮድካስተሮቹ ጋር እየተመካከረ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ብሮድካስት ባለስልጣን ፍቃድ ከሠጣቸው 5 የሃገር ውስጥ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሶስቱ ስራ መጀመራቸውንና ሁለቱ እስካሁን ወደ ስራ ለመግባት እንዳልቻሉ ተመልክቷል። ተጨማሪ 5 የሣተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ ተቀማጭነታቸው ከሃገር ውጭ አድርገው እየሠሩ መሆኑን ከብሮድካስት ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ፕሬሶችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት 18 ጋዜጦች እና 43 መፅሄቶች ገበያው ላይ አሉ ያለው ብሮድካስት ባለስልጣን ከ18 ያህሉ ጋዜጦች ወጥነታቸውን ጠብቀው ሣያቋርጡ በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጋዜጦች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ናቸው ብሏል፡፡


      “---አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ፣ ኢህአዴግ አዲስ፣ መሬት የረገጠ ፖሊሲም ሆነ አስተሳሰብ ሲያፈልቅ አላየንም፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፖሊሲ ገጽታ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲን” ምርኩዝ አድርጎ እየተጓዘ ነው፡፡ ግብርና መርም ሆነ በኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ፣ በእርሳቸው ዘመን የተከተበ ነው፡፡---”
                      ከተመስገን ጌታሁን ከበደ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

       ሰሞኑን የኢህአዴግ መሪና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የአቶ መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመት ሲዘከር ሰንብቷል፡፡ የፓርቲው አመራሮችና  የትግል አጋሮች፣የአቶ መለስን ሁለንተናዊ ሰብእና የሚገልጹ ምስክርነቶችን በመንግስት መገናኛ ብዙኃን ሲሰጡ አድምጠናቸዋል፡፡ በኢህአዴግ ጥላ ስር የተደራጁ የአዲስ አበባ ወጣቶችም፤ በተለያዩ ሥነ ስርአቶች ጠ/ሚኒስትሩን በየአዳራሹ ዘክረዋል፡፡ የሁሉም  ሀሳብ የሚያጠነጥነውና የሚያሳርገው ታዲያ  የመለስ ሌጋሲን ማስቀጠል በሚለው ላይ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የአቶ መለስ ዜናዊ፣ ዜና እረፍት ሲነገር፣ እውነታውን  ለመቀበል የተቸገረ አንድ የኢህአዴግ አባል አጋጥሞኝ ነበር፡፡ ይህ አባል ሞታቸውን መቀበል ከመቸገሩ የተነሳ፣ አንድ ቀን ድንገት ብቅ ብለው ሕዝቡን እንደሚያስደምሙት እስከማመን ደርሶ ነበር፡፡ አይፈረድበትም፤የመውደዱና የአክብሮቱ ጥልቀት ይመስለኛል፣ ይህን ዓይነቱን እምነት የፈጠረበት፡፡ ስለ አቶ መለስ ዜናዊ አንባቢነት፤አርቆ አስተዋይነትና እንከን የለሽ  ሰብእና በቅርብ የሚያውቋቸው የትግል ጓዶቻቸው በሚገባ ነግረውናልና፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የምለው የለኝም፡፡
ከጠ/ሚኒስትሩ ህልፈት በኋላ ስለ ፓርላማው ውሎ ዜና ሲዘገብ፣ በፓርላማው አዳራሽ መግቢያና መውጫ በር፣ በውስጥ በኩል የተሰቀለውን ግርማ ሞገስ ያለው፣ የአቶ መለስ ዜናዊ ሙሉ ፎቶግራፍ በቴሌቪዥን በመደጋገም እመለከት ነበር፡፡ የፓርላማው ውሎ የዜና ሽፋን ሲሰጠው፣ ምስሉ በቴሌቪዥን ካሜራ ያለ ጭቅጭቅ ሰተት ብሎ ነበር የሚገባው፡፡ የፎቶው ጥራት፣ በአካለ ሥጋ - በሕይወት ያሉ ነው የሚመስለው፡፡ አንዳንድ ጊዜ  ተሰብሳቢው መሀል፣ በሀሳቤ ራሴን አገኘውና፣ ፎቶውን ሰርቅ እያደረግሁ እመለከታለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በበሩ መግቢያ ላይ ቆሜ አዳራሹ ውስጥ ያለውን የስብሰባ ታዳሚ እመለከትና፣ ስሜታቸውን ለማጤን እሞክራለሁ፡፡ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያላቸውን እውነተኛ ስሜት፣እንደ ኤክስሬይ ሰርስሬ መመልከት ብችል ብዬ እመኛለሁ፡፡ ስንቶቻቸው ከልባቸው ያከብሯቸዋል፤ ስንቶቻቸው ግድ አይሰጣቸውም፤ ስንቶቻቸውስ ይፈሯቸዋል፡፡ እርግጥ ነው መፈራት መጠላት ማለት አይደለም፡፡ የፓርላማ አባላቱ፣ አፈ-ጉባኤው ሳይቀሩ፣ የአቶ መለስ ዜናዊን ፎቶግራፍ ሲያዩ፣ አእምሮአቸው ውስጥ ምን እንደሚመላለስ ባውቅ እያልኩ እመኛለሁ፡፡  
አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማው ተገኝተው የሚያቀርቡት ማብራሪያ ሁለት ገጽታዎች ነበሩት፡፡ አንዱ ተቃዋሚዎች ከሚያቀርቡት ጥያቄ ተነስተው በሚሰጡት ምላሽ፣ አብዛኛውን የኢህአዴግ ተመራጭ  የምክር ቤት አባላት፣ በሳቅ ሲያጥለቀልቁ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ በሃፍረት ይኮስሳሉ፡፡ ምንም ጥያቄ ቢነሳ ጠ/ሚኒስትሩ መልስ ቸግሯቸው አያውቅም፡፡ መልሱ ግን ሁሌም ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ለጊዜው ግን ትክክል የሚመስሉት እሳቸው ነበሩ፡፡ የሚያበሳጫቸው ሀሳብ ሲያጋጥማቸውም ብስጭታቸውን መደበቅ አይችሉበትም፡፡ ሂሳቸው ከሰይፍ የሚሰላበትም ጊዜ ነበር፡፡ በተቃዋሚዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ አባላትም ላይ የሚሰነዝሩት ሀሳብ አባላቱን የሚያስበረግግ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ በፓርላማ፣ “የመንግስት ሌቦች” ያሏቸውን ወገኖች ያሸማቀቁበት አጋጣሚ በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
ኢህአዴግ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ገብቶ፣ የሽግግር መንግሥት ከመሰረተበት ዕለት ጀምሮ ለተከታታይ አምስት አመታት የተካሄደውን የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት የዳሰሰ ጥናት የማንበብ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ አጥኚዎቹ፤ ዘጠኝ ወራት ሙሉ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ከመጀመሪያዋ ስብሰባ አንስቶ በመገኘት፣ በጉባኤው የተለያዩ ፖሊሲዎች ሲወጡና ሲጸድቁ ተከታትለዋል፤ ሰነዶችንም ፈትሸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱን ለማጽደቅ የተካሄደውን ውይይት፣ በየትኛው አንቀጽ ላይ ብዙ ሰዓት የፈጀ ክርክር እንደተካሄደ፣ ባጠቃላይ ሕገ መንግሥቱን ለማጽደቅ የፈጀውን ጊዜ በቀናትና በሰዓት እየለኩ፣ የፓርላማውን አካሄድ ዝርዝር ጉዳይ በስፋት መርምረዋል፡፡ ሕገ መንግስቱን ለማጽደቅ 12  ቀናት መፍጀቱን የጠቀሱ ይመስለኛል፡፡ ጊዜ ሳይፈጁ የጸደቁ ሕጎችንም ከነምክንያታቸው አብራርተው ጽፈዋል፡፡ በዚህ ጥናት በደቡብ አፍሪካና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ አንቱ የተባሉ ምሁራን የተሳተፉበት ሲሆን  በጣም በጥልቀት የተካሄደ ጥናት ነበር፡፡   
የጥናታቸው ትኩረት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ (Contemporary Ethiopian politics) ላይ ነበርና፣ ፖሊሲ የሚያመነጨውንና የፖሊሲ ረቂቅ ጽሑፍ የሚያዘጋጀውን የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ለማወቅም ጥረት አድርገዋል፡፡ ፖሊሲ የሚያመነጩትን ሰዎች ሚና ለመፈተሽም ሞክረዋል፡፡ የእኒህ ተመራማሪዎች ትልቁ ፈተና፣ የፖሊሲ ረቂቁን ያዘጋጀውን ሰው ማንነት ለማወቅ የሚያቀርቡት ጥያቄ መልስ አለማግኘቱ ነበር፡፡ በወቅቱ በድርጅቱ ውስጥ ሰፍኖ በነበረው አሰራር፣ ሁሉም ፖሊሲዎች የሁሉም አባላት አስተዋጽኦ ያለበት መሆኑ የተነገራቸው ሲሆን  ኢህአዴግ በግለሰቦች ትከሻ ላይ ያልተንጠለጠለ እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ ሙከራ መሆኑን ተመራማሪዎቹ የተገነዘቡ ይመስለኛል፡፡ የግለሰቦች ማንነት ላይ ማተኮር፣ የግለሰብ አምባገነንነትን ይፈጥራል ብሎ ኢህአዴግ ያምን  ነበር፡፡ ነገር ግን  የፖሊሲ መነሻ ሀሳቡ ከአንድ ግለሰብ መፍለቁ የግድ ነው፡፡
ፖሊሲ የሚያመነጨውን የኢህአዴግ ራስ ለማወቅ ያደረጉት ጥረት ይሳካላቸው አይሳካላቸው ባላስታውስም፣ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሌላ  የፖሊሲ ሀሳብ ያመነጩ የኢህአዴግ ሰዎች ቁጥራቸው ከሁለት አይዘልም፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሌላ የፖሊሲ ረቂቅ ካቀረቡት መካከል አቶ በረከት ስምዖን እንደሚገኙበት  ሰምቼአለሁ፡፡ ሌሎች ጓደኞቻቸው፣ በአቶ መለስ ዜናዊ ተነድፎ የተሰጣቸውን ፖሊሲዎች አንብበው፣ ውይይቱን ከሟሟቅ የዘለለ ሚና እንደሌላቸው በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ተገንዝቤአለሁ፡፡
ሰሞኑን የአቶ መለስ ዜናዊ አምስተኛ ሙት ዓመታቸው ሲዘከር፣ የተሰጠው ምስክርነት ይህንኑ ያረጋግጣል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የምትገዛበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና ዋና አመንጭ፣ አቶ መለስ ዜናዊ መሆናቸውን መገመት ይቻላል፡፡ በሙስና ወንጀል ተከሰው ለዓመታት ወህኒ ወርደው የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ፣ ከኢህአዴግ የታሪክ መዝገብ ላይ የተፋቁ ቢሆኑም፣ በዚያን ወቅት በርከት ያሉ የፖሊሲ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ሌላው የተዋጣላቸው የኢህአዴግ ቁንጮ ባለስልጣን እንደነበሩ ይነገራል፡፡ ይሁንና የአቶ መለስን  ያህል የጎላ ሚና የነበረው የኢህአዴግ መሪ ማግኘት ይከብዳል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ወዲህ፣ ኢህአዴግ አዲስ፣ መሬት የረገጠ ፖሊሲም ሆነ አስተሳሰብ ሲያፈልቅ አላየንም፡፡ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የፖሊሲ ገጽታ፣ “አብዮታዊ ዲሞክራሲን” ምርኩዝ አድርጎ እየተጓዘ ነው፡፡ ግብርና መርም ሆነ በኢንዱስትሪ ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሰነድ፣ በእርሳቸው ዘመን የተከተበ ነው፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ግጭት ሳቢያ፣“ጦርነት ይካሄድ አይካሄድ” የሚለው ክርክር፣ ለህውኃት መሰንጠቅ ምክንያት መሆኑ ይታወሳል፡፡ አቶ ስዬ አብርሀ በጻፉት መጽሐፍ፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፤ ባይሳካላቸውም፣ ጦርነት መካሄድ የለበትም ከሚሉት ወገኖች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡ እንደ አቶ ስዬ አባባል ከሆነ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የኢትዮጵያ ነገሥታት የጦረኝነት አባዜ፣ በአስተሳሰብ ደረጃ አሸንፈው ነበር ማለት ነው፡፡
የአቶ መለስ ዜናዊ አስተሳሰብ ጎዳም ጠቀመም፣ የ14 ዓመቱ የጫካው ዘመን ሲቆጠር፣ ላለፉት 42 ዓመታት ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታዋ የተወሰነው በእሳቸው አስተሳሰብ መሆኑ የሚካድ አይደለም። ይህ አስተሳሰብ በሥራ ዘመናቸው የተፈጠረውን ስህተትና ጥፋት አያካትትም፡፡ ምናልባት በባህላችን ሙት ወቃሽ መሆን ነውር በመሆኑ ይመስለኛል፣ በጣም የጎሉ ስህተቶች እንኳ አልተጠቀሱም። በሌላ በኩል፤ ስለ አቶ መለስ ዜናው ሰብእና እንደዚህ ጎልቶ ከተነገረ፣ የአሁኖቹ የኢህአዴግ መሪዎች፣ ሩጫቸውን ጨርሰዋል ብለን ለማሰብ ያስገድደናል፡፡ በአንድ በኩል፤ በአገራችንም ሆነ በዓለም የማያቋርጥ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ክስተት ነው የሚታየው፡፡ በሌላ በኩል፤ የአቶ መለስ ዜናዊን ሀሳብ ዘላለማዊ አድርጎ የማሰብ አዝማሚያ በስፋት ተንሰራፍቷል፡፡ የአማራ ክልል ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር በጨረፍታ በቴሌቪዥን ላይ ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ አቶ መለስ ዜናዊን የወደፊቱን የሚያውቁ ነቢይ ያህል ነበር ሰብእናቸውን አግዝፈው ሲናገሩ የሰማሁት፡፡ ዓለም በፍጥነት በምትለዋወጥበት በዚህ ዘመን እንደዚህ አይነቱ  አስተሳሰብ የሚያዋጣ ነው ወይ የሚለው ያከራክራል፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ፣
 አንድ ሀሳብ ይዞ መቆምን ፈጽሞ የሚደግፉት አይመስለኝም፡፡ አሁን ያሉት የኢህአዴግ መሪዎች አዳዲስ ሀሳቦችን እንዳያፈልቁ የሚያሰንፍ ወይም የሚገታ አስተሳሰብ እንዳይሆንም ስጋት አለኝ። የአቶ መለስ ዜናዊን ሌጋሲ ለማስቀጠልም እኮ ከጊዜው ጋር መጓዝ የግድ ይላል፡፡  

 በ2008 ዓ.ም በሀገሪቱ ተፈጥሮ ለነበረው ተቃውሞና ግጭት መፍትሄ ለመሻት ከተንቀሳቀሱ አካላት አንዱ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሲሆን ሌላኛው 120 የተለያዩ አባላት ያሉት “የሽማግሌዎች ቡድን” ነበር፡፡ እነዚህ አካላት የሀገሪቱ ችግሮች በሽምግልና እና በእርቅ ነው ሊፈቱ የሚገባው የሚል አላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ አሁን የት ነው ያሉት? ዓላማቸውስ ከምን ደረሰ? የሁለቱንም ተወካዮች የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሐፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ፤ ተቋማቸው የእርቅ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሲገልፁ፤ ሌላው የሽምግልና ቡድን አባልና ፀሐፊ የሆኑት ፓስተር ዶክተር ዘካሪስ አ/ብርሃን በበኩላቸው፤የሽምግልና ቡድኑ አላማ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ መፍትሄ እንዲሰጥ ማሳሰብ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ ምን ያህል ተሳክቶላቸው ይሆን? አሁን ስላገረሸው ውጥረት ምን ይላሉ? ቀጣይ ዕቅዳቸውስ ምንድን ነው? ተወካዮቹ ያብራራሉ፡-   

                           “የሚበጀውን ለማድረግ ማሸነፍም መሸነፍም እንዳለ መቀበል ይኖርብናል”
                                 ፓስተር ዶ/ር ዘካሪያስ አ/ብርሃን (“የሽማግሌዎች ቡድን” ፀሃፊ)

      ጀምራችሁት የነበረው አገራዊ ሽምግልና ምን ላይ ደረሰ?
ባለፈው ዓመት፣ መስከረም 17 ቀን 2009 ዓ.ም የተሰበሰብነው፣ ገለልተኛ የምንባል የዜጎች ስብስብ አካላት ነበርን፡፡ በቀላል አገላለፅ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የምንል ወገኖች፣ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍል ተውጣጥተን፣ መፍትሄ ለማፈላለግ የተሰበሰብን አድሆክ (Adhoc) ኮሚቴ ብለህ ልትጠራን ትችላለህ፡፡ መነሣሣቱን ወስዶ ያሰባሰበን፣ የኢትዮጵያ የሰላም የልማትና የዴሞክራሲ ህዝባዊ የምክክር መድረክ ነበር፡፡
መድረኩ በመጀመሪያው ቀን ያሰባስበን እንጂ፣ ይህን ጊዜያዊ የሽምግልና ሚና መጫወት የጀመርነው፣ ወደ 120 አካባቢ የምንሆን ሰዎች ነበርን ማለት ይቻላል፡፡ ከ120 ሰዎች መካከል የተወሰንነው፣ ንዑስ ኮሚቴ አዋቅረን፣ የ120 ሰዎችን ጥያቄዎች በስፋትና ጥልቀት ባለው ውይይትና ክርክር ጨምቀን፣ 16 ነጥቦች በሚሆኑ ጥያቄዎች ይዘን፣ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር በተወካዮቻችን አማካኝነት አቅርበናል፡፡ ይህ እንግዲህ የሆነው የመጀመሪያው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳይታወጅ ሲሆን ከዚያም በኋላ ቢሆን ሀሳባችንን ለተለያዩ የመንግስት አካላት አቅርበናል፡፡
የሽምግልናው መማክርት ሥራውን በዚህ መልኩ በማጠናቀቁና አድሆክ ኮሚቴ ስለነበር በጊዜው ለተፈጠረው አለመግባባት የበኩላችንን የዜግነት ግዳጃችንን ለመወጣት ሞክረናል፡፡ ያቀረብነው የህዝቡ ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ቢመለስም ባይመለስም፣ ከስብስባችን ግብ አንፃር ውጤማ ነበርን፡፡ ተልኳችን ህዝቡ እየጠየቀ የነበረውን ጥያቄ ማቅረብ እንዲሁም ሽምግልናን ያማከለ ውይይት በመፍጠር፣ ለዜጎች የሚበጀው ነገር ይመጣ ዘንድ ማሳሰብ ነበር፡፡ ያንንም አድርገናል፡፡
ቀጣይ እቅዳችሁ ምንድን ነው? ሽምግልናውስ ቀጣይነቱ ምን ያህል ነው?
ይህ የሽምግልና አካል ከላይ እንደተገለፀው፣ አድሆክ ኮሚቴ በመሆኑ፣ ብዙዎቻችን ከዚያ በኋላ ሥራችንን አቁመናል፡፡ ምክንያቱም ግባችን ጥያቄዎችን  ለውይይት ማቅረብ ነበርና ነው፡፡ አሁን እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት፣ የተሰበሰብንበትም የምንሰባሰብበትም ምክንያት ያለን አይመስለኝም፡፡ በግል የምንገናኝ ሰዎች፣ የዚህ አድሆክ ኮሚቴ ሚና ማብቃቱን አውርተንበት የምናውቅ ይመስለኛል። በርግጥ ከመንግሥት አካላት በኩል ለውይይት ቀጠሮ እንደሚሰጠንና ውይይት እንደምናደርግ በተወካዮቻችን በኩል መልዕክት ደርሶናል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለቀጣይ ውይይት ፈቃደኛነታቸውን እንዳሳዩ ተወካዮቻችን ገልፀዋል፡፡
አሁን በሀገሪቱ ላሉ ፖለቲካዊ ችግሮችና ውጥረቶች መፍትሄው ምንድን ነው?
በአሁኑ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት አሊያም በሚመጣው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በሰከነ መንፈስ በመወያየት፣ የፖለቲካ ትኩሳቱን አርግቦ፣ ለአገሪቱ የሚበጀውን መንገድ መርጦ መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ውይይት ዋናው የዲሞክራሲ መንገድ፣ የመግቢያው በር ነው፡፡ ከውይይት የሚጠቅመውን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ ደግሞ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሀሁን መጀመር ነው፡፡ ጉንጭ አልፋ ክርክር ተግባር ሲያጅበው ነው ትክክል የሚሆነው። አሁንም ፍሬ ያለው ውይይት ያስፈልጋል፡፡ በውይይት ማሸነፍም መሸነፍም ሁልጊዜ የለም፡፡ አውራነት ሁልጊዜ የለም፡፡ የሚበጀውን ለማድረግ ማሸነፍም መሸነፍም እንዳለ መቀበል ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ አሁን አንተ ላነሳኸው ሀሳብ፣ ችግር ይኑርም አይኑርም፣ በውይይት መፍትሄ መፈለጉ ይሻላል። የፖለቲካ ሥርዓት፣ የእምነት አቋም መግለጫ ወይም አላማ አይደለም፡፡ መቀየር መለወጥና ለአገሪቱ የሚበጀውን መንገድ መያዝ ይገባል፡፡ እሱን ለማድረግ የመንፈስ ልዕልና እና ቁርጠኝነት ወዳለበት ከፍታ መሸጋገር ይገባናል፡፡

------------------


                                “አንድነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል”
                                 መጋቢ ዘሪሁን ደጉ (የኢ/ሃ/ተ/ጉ ዋና ፀሐፊ)


         የሽምግልና እና የእርቅ ሂደቱን ምን ላይ አደረሳችሁት?
በአሁኑ ወቅት የዚሁ የእርቅ አካል የሆኑ ስራዎችን እየሰራን ነው፡፡ ጉዳዩ ጠዋት ተጀምሮ ማታ የሚያልቅ ነገር አይደለም፡፡ ውስብስብ ነው፡፡ በህዝቦች መካከልና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል የሚሰራ ስራ እንደመሆኑ፣ በቂ ጊዜና በጀት እንዲሁም ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ነገሮችን ተራ በተራ እያስኬድን ነው፡፡ አሁን ዲላ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር የመፍታቱን ስራ እያገባደድን ነው፡፡
በዲላ እየሰራችሁት ያለው ሥራ  ምንድን ነው?
በወረዳ ደረጃ ባሉ መዋቅሮቻችንና በክልሉ መንግስት ድጋፍ፣ በህዝቦች መካከል የተፈጠሩ ቅራኔዎችን እንዲፈቱ እያደረግን ነው፡፡ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ነው ይሄን እየሰራን ያለነው፡፡ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከወረዳ ከፍ ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ያሉ ችግሮች ላይ ጠንካራ ስራ ሰርተን እናጠናቅቃለን። ውይይት እያደረግን መጨረሻ ላይ ባህላዊውን እርቅ እያደረግን ነው የምንቋጨው፡፡ ቀጣይነት ያለው ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ እንዲፈጠር፣ ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል የሚለውን እየተመካከርን እየሰራን ነው፡፡ በአማራ፣ በኦሮሚያና በሌሎችም አካባቢዎች፣ የእርቅ ውይይትና ምክክሮችን አድርገናል፡፡ እንግዲህ ተራ በተራ ነው እየሰራን  ያለነው፡፡
እስቲ በምሳሌ ያስረዱን --- እርቁ የሚፈጠረው እንዴት ነው? ማን ከማን ጋር ነው የሚታረቀው?
 ለምሳሌ ዲላ አካባቢ በተፈጠሩ ግጭቶች፣ የብዙ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ በነዋሪዎች መካከልም መቃቃር ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖችና ጉዳት አድርሰዋል ከሚባሉ ወገኖች ጋር ውይይት በማድረግና ወደ አንድ መድረክ በማምጣት ነው፣ እርቅ የምንፈጥረው፡፡ እርግጥ እንደምናስበው ሂደቱ ቀላል አይደለም፤ ውስብስብ ነው፡፡ ንብረት የወደመበት ንብረቱ እንዲመለስ፣ ወንጀል የሰራ በህግ እንዲጠየቅ ይደረጋል፡፡ በህግ የተያዙ ጉዳዮችን ለፍትህ አካላት ትተን፣ ከህግ በመለስ ያሉ ስራዎችን ነው የምንሰራው፡፡ በዋናነት በህዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት መልሶ በመገንባቱ ላይ ነው ትኩረት የምናደርገው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሃገር ሽማግሌዎችና የመንግስት አካላትም ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
አሁንም በየአካባቢው ውጥረቶች እንዳሉ ይገለፃል፡፡ እነዚህን ውጥረቶች ለማርገብ የእናንተ ሚና ምንድን ነው ?
እኛ የምንከተለው ሁለት አቅጣጫዎችን ነው። አንደኛው አቅጣጫ፣ ከመንግስት ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ናቸው፡፡ እነዚህ አሁንም ቀጥለዋል። በቅርቡም ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር ውይይት የምናደርግበት የምክክር መድረክ እናዘጋጃለን፡፡ እንዴት ተባብረን የሃገራችንን ሠላም እናረጋግጥ? በሚል ውይይት እናደርጋለን፡፡ የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዳሉ ሆነው፣ የህዝቡን የእርስ በእርስ ግንኙነትና ሠላም እንዴት ማጠናከር ይቻላል? መንግስት ደግሞ ምን ይጠበቅበታል? የሚሉትን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ፣ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ውይይት እናደርጋለን፡፡ ከክልል መንግስታት ጋርም ተመሳሳይ ውይይት እናካሂዳለን፡፡  
ህዝቡ አካባቢም ጥያቄዎችን በሠላማዊ መንገድ ማቅረብ፣ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ እንመካከራለን። ምንም በማያውቀው ሠላማዊ ዜጋ ላይ ወይም በሃገሪቱ ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ፈፅሞ የማንቀበለው ነው። ውጤቱም ጥሩ አይደለም። ስለዚህ የተሻለውን መንገድ የማሳየት ስራ ይጠበቅብናል፤ እየሰራንም ነው፡፡ ሌላው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ነው፡፡ መንግስት በእርግጥ ከተቃዋሚዎች ጋር ውይይት እያደረገ ነው፡፡ እኛም በሂደቱ በታዛቢነት አለን፡፡ እንደ አንድ ተቋም እንግዲህ የምንችለውን ጥረት ሁሉ እያደረግን ነው፡፡
ይሄን ስራ ስትሰሩ ምን ተግዳሮቶች ገጥሟችኋል?
ከመንግስት በኩል ጥሩ ትብብር ነው ያለው፤ ጥያቄዎች በአግባቡ ቶሎ ይመለሱልናል፡፡ በተለይ ዲላ ላይ የዞኑ መንግስት ለሰላም፣ ለእርቅ፣ ለህዝቦች አንድነት ከምንጠብቀው በላይ ከፍተኛ ድጋፍ ነው ያደረገልን፡፡  የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬም ያሳዩን ትብብርም የሚደነቅ ነው፡፡ እንደ ተግዳሮት የምናነሳው፣ ስራው ከፍተኛ  ፋይናንስ የሚጠይቅ ነው፡፡ ትልቁ ተግዳሮታችን የፋይናንስ አቅም ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሌላው ጥሩ ነው ያለው፡፡  
አሁን  የሚታዩ ውጥረቶች ምን ያህል ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው?
እኔ ቁጭ ብሎ በመነጋገር አምናለሁ፡፡ ህዝባችን እርስ በእርሱ የሚዋደድ፣በጋራ የሃገሩን ሠላም ለማረጋገጥ፣ ሃገሩን ለማልማት የሚተጋ፣ ለዘመናት የቆየ የትስስሮች ታሪክ ያለው ህዝብ ነው፡፡ በቀላሉ አደጋ ውስጥ የሚወድቅና በቀላሉ ለሌላ ችግር የሚጋለጥ አይደለም፡፡
ችግሮች ቢኖሩም ህዝቡ በባህሉና በሃይማኖቱ ጠንካራ ስለሆነ፣ ይሄ እሴት እንዳይሸረሸር ከመንግስትም ከኛ የሃይማኖት ተቋማትም ብዙ መሥራት ይጠበቃል፡፡ የህዝቡን አንድነት አጠናክሮ በመሄድ ረገድ የሁላችንንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡ አንድነቱ እንዳይነካ መታገል ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የምንለው እጅግ ጠንካራው ማንነታችን ነው፡፡ መንግስትም ከህዝቡ የሚነሳለትን ጥያቄ እያደመጠና በጥልቀት እየፈተሸ የመመለስ ስራን አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡ ይሄ ከተደረገ አስደንጋጭ ችግር ውስጥ እንገባለን የሚል ስጋት የለኝም፡፡ ግን መንግስት፣ ብዙ የቤት ስራ ይጠብቀዋል፡፡ መንግስት፣ የህዝብን ጥያቄዎች ለመመለስ እስከተጋ ድረስ አገራችን ብዙ  ችግር አይገጥማትም፡፡  

  ኖርዝ ኢስት ኤቨንትስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከብሄራዊ ቤተ-መዛግብትና ቤተ- መፃህፍት ኤጀንሲ ጋር በተመባበር፣ ሲያካሂድ የቆየው የሥነፅሁፍ ውድድር፣ ሰኞ ከምሽቱ 12፡ 00 እስከ 2፡00 በሚዘልቅ የሽልማት ሥነ ስርዓት እንደሚጠናቀቅ ተገለፀ፡፡ የሽልማት ድርጅቱ፤ በረጅም ልብ ወለድ፣ በግጥም፣ በልጆች
መፃህፍት እንዲሁም ለስነፅሁፍ እድገት፤ ለንባብና ትምህርት መስፋፋት የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ተቋማት የሚሉትን ጨምሮ በዘጠኝ ዘርፎች ሥራዎችን ሲያወዳድር የቆየ ሲሆን ከነገ በስቲያ የየዘርፉ አሸናፊዎች ይፋ እንደሚሆኑና እንደሚሸለሙ ታውቋል፡፡ የሽልማት ሥነስርዓቱ በኪነ-ጥበባዊ ዝግጅቶች ታጅቦ እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ በዕለቱ የስነ ፅሁፍ ባለሙያዎች፣ የተሸላሚ ቤተሰቦች፣ የስነ-ፅሁፍ አቅራቢዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙ ሲሆን የብሄራዊ ቴአትር በር ከቀኑ 11፡00 እስከ 12፡00 ብቻ ክፍት እንደሚሆን የገለፁት አዘጋጆች፤ ታዳሚዎች በሰዓቱ እንዲገኙ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

   ”የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ለንባብ በቃ
                 • “ከንዱራ” ሰሞኑን በገበያ ላይ ዋለ

       በደራሲ ደመወዝ ጎሽሜ የተዘጋጀው “ዓሥራ ሥድሥት” የተሰኘ መጽሐፍ፣ በዛሬው ዕለት ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ፣ አምስት ኪሎ በሚገኘው በብሔራዊ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን  አዳራሽ ይመረቃል፡፡ ኢጋ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መጽሐፉ ሃይማኖታዊ ፍልስፍናዎችን የያዘ ሲሆን  የሥነመለኮት ባለሙያ ዶ/ር ዘሪሁን ሙላትና የጥበብ ታሪክ መምህርና ተመራማሪው አቶ አበባው አያሌው፣ በመጽሐፉ ውስጥ በቀረቡት ሃሳቦች ላይ የመወያያ ነጥብ ያነሳሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የመጽሐፉን ሃሳብ የሚያንጸባርቅ ዶክመንታሪ ፊልም ለዕይታ የሚቀርብ ሲሆን ለተወሰኑ ታዳሚዎችም በዲቪዲ በስጦታ ይበረከታል ተብሏል፡፡
አቤል ጋሼ የተባለ ደራሲ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ ባሰፈረው ዘለግ ያለ አስተያየት፤ “-- በእውነት ጥበብን የፈለገ ከዚህ ከደመወዜ ታዛ ይጠለላል! ያጠይቅ! ከአዋቂ ይማር! ይህ ጽሁፍ ፍልስፍና ነው፤ ይህ ጽሁፍ ቀመር ነው፤ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖት ነው፤ ይህ ጽሁፍ ስለ ሃይማኖት፣ ስለ ፖለቲካ፣ ስለ ታሪክ ነው፤ በተለይም ይኸ መጽሐፍ እውነትን የመፈለግ አንደምታ ነው--” ብሏል፡፡
 በ441 ገጾች ዳጎስ ብሎ የተሰናዳው “ዓሥራ ሥድሥት”፤ በ101 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ደራሲው ደመወዝ ጎሽሜ፣ ከዚህ ቀደም “ሶስተኛው ኪዳን” የሚል መጽሐፍ ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡
በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር በሆነው ብሩህ ዓለምነህ የተዘጋጀው፣ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የተሰኘ መጽሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል። የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎችን  ከእነ ትንታኔያቸው ያካተተው መጽሐፉ፤ ታሪክ፣ ሃይማኖትና ፍልስፍና የተዋሃዱበት ነው ተብሏል፡፡
ደራሲው ይሄን መጽሐፍ የማዘጋጀት ሃሳቡ እንዴት እንደተጠነሰሰ ባብራራበት ጽሁፉ፤”ዘርዓያዕቆብ የፍልስፍና ት/ቤት የሚል ተቋም ለማቋቋም በማደርገው ጥረት ውስጥ በ3 ዙር (በሃምሌ 2008፣ በህዳርና በጥር 2009 ዓ.ም) ወጣቶችን በሳምንት ሦስት ቀን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” እና ሌሎችንም የፍልስፍና ትምህርቶች በአማርኛ ማስተማር ጀመርኩ፡፡ ከእነዚህ ኮርሶች ውስጥ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለውን ትምህርት  የመጀመሪያው ዙር ላይ በአንድ ሳምንት ነበር የጨረስኩት፤ ሁለተኛ ዙር ላይ ደግሞ አንድ ወር ፈጀብኝ፡፡ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ከኢትዮጵያ ታሪክ፣ እምነትና ሥነ ጽሁፍ ጋር እያያያዝኩት ስሄድ ግን ነገሩ በጣም ሰፊ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡” ይላል፡፡
ከዚያስ? ደራሲ ብሩክ ዓለምነህ ማብራሪያውን ይቀጥላል፤ ”ስለ ዘርዓያዕቆብ ይበልጥ ባሰብኩና ባስተማርኩ ቁጥር አዳዲስ ዕይታዎች ሁሉ ይመጡልኝ ጀመር፡፡ በሂደትም የዘርዓያዕቆብን፣ የወልደህይወትን፣ የዶ/ር እጓለንና የዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን ትምህርቶች አንድ ላይ በመስፋት፣ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ምን እንደሚመስል ቅርጽ መስጠት እንደሚቻል እየተረዳሁ መጣሁ። እንግዲህ “የኢትዮጵያ ፍልስፍና” የሚለውን ትምህርት፣ በመጽሐፍ መልክ የማሰናዳቱ ሃሳብ የመጣው በዚህ ወቅት ላይ ነበር” ብሏል፡፡
“ትንታኔ”፣”ሀገራዊ ቁጭት” እና “የዘርዓያዕቆብና የወልደ ሕይወት ሐተታዎች” በሚሉ ሦስት ክፍሎች፣ በ352 ገጾች ተቀንብቦ የተሰናዳው የኢትዮጵያ ፍልስፍና የማስተማሪያ መጽሐፍ፤ ዋጋው 91 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡  ደራሲው ከዚህ ቀደም “ፍልስፍና-1” እና “ፍልስፍና-2” የተባሉ መጻህፍትን ለንባብ ያበቃ ሲሆን በአዲስ አድማስ ጋዜጣና ውይይት መጽኄት ላይ የተለያዩ ፍልስፍናዊ መጣጥፎችን በመጻፍ ላይ ይገኛል፡፡  
በአያሌው ወረታ የተጻፉ የወግ፣መጣጥፍ፣ ማስታወሻና ልቦለድ ስብስቦችን ያካተተው፣ “ከንዱራ” የተሰኘው መጽሐፍም በገበያ ላይ የዋለው ሰሞኑን ነው። የመጽሐፉ ታሪኮች፤ “ወዮላችሁ”፣”ቤዛ”፣ “ከንዱራ”፣ ”የኛ ቀበሌ ወጎች”፣ ”የጉዱ ጣሴ ማስታወሻ”፣ ”ናጽነት” እና “አንጎልን ውጦ” በሚሉ ርዕሶች የቀረቡ ሲሆን በ194 ገጾች የተቀነበበው ስብስቡ፤ በ70 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
“ዘመነ ኮንዶሚኒየም ሲቃረብ የህዝብ ብዛት ይጨምራል፤ ቤት አልባዎች ይበዛሉ፤ የጨረቃ ቤቶች ይስፋፋሉ፤ መሬትም እንቁነቷን ታውጃለች። አልጠግብ ባዮች እንደ አሸን ይፈላሉ፤ መንግስትንም መከታ ያደርጋሉ፤ በጉያውም ይሰገሰጋሉ፡፡ እልፍ አዕላፍ ቤት የለሾችንም ይንቁአቸዋል፤ ምሬታቸውንም ይዘባበቱበታል፡፡ ይህን ጊዜ ጭንቀትና አበሳ በመንግስት ላይ ይወድቃል። እርሱም የባሰባቸውን “ኑ ወደ እኔ” ይላቸዋል። ሽቅብ ያሰፍራቸው ዘንድም ይሯሯጣል። የተቀሩትንም አይዟችሁ ይላቸዋል፡፡ ምድርን ግን  ትመቻቸው ዘንድ ላላቸው ይመትርላቸዋል---” እያለ ይቀጥላል -”ወዮላችሁ” በሚል ርዕስ የቀረበው የመጀመርያው መጣጥፍ፡፡

• 400 የብሪጅስቶን ጎማ የገዛ፣ ታይላንድን ለ1ሳምንት በነጻ ይጎበኛል
       • 1ሺ ጎማ ለሚገዙ፣ የ160ሺ ብር ቅናሽ ይደረግላቸዋል

     በኢትዮጵያ  የታዋቂው ብሪጅስቶን ጎማ ብቸኛ አከፋፋይ  ካቤ ኃ. የተ. የግል ማህበር፣ “ባንዳግ” የተሰኘ አዲስ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ፡፡  ከጃፓኑ ብሪጅስቶን አለም አቀፍ ኩባንያ የመጡ ኃላፊዎችና የካቤ  አመራሮች፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሸራተን አዲስ፣ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ባንዳግ” ለአገራችን እንግዳ ቢሆንም  በመላው አለም ለረጅም አመታት በእጅጉ የሚታወቅ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ አዲስ አገልግሎት፣ የሥራ ጊዜው ያበቃለት ጎማን እንደ አዲስ ለመጠቀም የሚያስችል ነው  ብለዋል፡፡
የብሪጅስቶን አመራሮች እንደገለፁት፤ የ”ባንዳግ”ን አገልግሎት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር ከፍተኛ በጀት የተመደበለት  ሲሆን አገልግሎቱም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው ተብሏል፡፡ ከአገልግሎት ውጭ የሆነን አሮጌ ጎማ፣ በብሪጅስቶን “ባንዳግ” አገልግሎት በማሳደስ፣ የጎማ ግዢ ወጪን በ50 ፐርሰንት መቀነስ እንደሚቻል የጠቆሙት አመራሮቹ፤ አገልግሎቱ የሚሰጠው  ዘመኑ ባፈራው የረቀቀ ቴክኖሎጂ በመሆኑ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና አስተማማኝ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ብሪጅስቶን፣ ለደንበኞቹ አዲስ የሽያጭ ማስተዋወቂያ ስጦታ ማዘጋጀቱን ሰሞኑን አብስሯል፡፡ በዚህም መሰረት፣ 400 የብሪጅስቶን ጎማ ለሚገዙ ደንበኞች፤ ለአንድ ሳምንት ሙሉ ወጪያቸውን ችሎ፣ ታይላንድን ያስጎበኛል፡፡  በተጨማሪም፣ 1ሺ ጎማ ለሚገዙ፣ የ160 ሺ ብር ቅናሽ የሚያደርግ ሲሆን 50 ጎማ ለሚገዙ ደግሞ  የ30ሺ ብር ቅናሽ እንደሚደረግላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህ የሽያጭ ማስተዋወቂያ ስጦታ፣ ለ3 ወራት ብቻ የሚዘልቅ ሲሆን  በመጪው ህዳር ወር አጋማሽ ላይ (ኖቬምበር 30 ቀን 2017) የሚያበቃ ይሆናል ተብሏል፡፡

    ኢንተርኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል ያስገነባውና በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት 360 ድግሪ የሚሽከረከረው ሬስቶራንት ሰሞኑን አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡
ሆቴሉ በቅርቡ ግንባታውን አጠናቆ አገልግሎት ላይ ያዋለው አዲሱ ሬስቶራንት፣ 360 ድግሪ እየተሽከረከረ ደንበኞች የከተማዋን ዙሪያ እየቃኙ እንዲዝናኑ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ ከትናንት በስቲያ 11ኛ ፎቅ ላይ የሚገኘውን ተሽከርካሪ ሬስቶራንት ለጋዜጠኞች ባስጎበኘበት ወቅት፣ የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይልቃል በቃሉ እንደተናገሩት፣ ተሽከርካሪው ሬስቶራንት በአንድ ጊዜ 120 እንግዶችን ይዞ፣ 360 ድግሪ በመሽከርከር፣ የአዲስ አበባ ከተማን ዙሪያ ያስቃኛል፡፡ ተሽከርካሪው ሬስቶራንት ከተነሳበት ቦታ ተመልሶ ለመድረስ 55 ደቂቃዎች ይወስድበታል ተብሏል፡፡
ሬስቶራንቱ የተለያዩ ሀገራትንና  ባህላዊ የኢትዮጵያ ምግቦችን ለደንበኞቹ ያቀርባል ያሉት ሥራ አሥኪያጁ፤ ደንበኛው ላገኘው አገልግሎት የሚከፍለው ዋጋ ተመጣጣኝ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በቱሪዝም እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን የገበያ መቀዛቀዝ ችግር መፍትሄ እንደሚያስገኝ እምነት የተጣለበት ስብሰባ፤ የፊታችን ማክሰኞ እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እእንደሚካሄድ አቶ ይልቃል በቃሉ ተናግረዋል፡፡
አምና በዚህ ወቅት በአገሪቱ ተከስቶ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ፣ ከፍተኛ የእንግዶች የፕሮግራም ስረዛ ገጥሞን ነበር ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ዘንድሮ ግን በአንፃራዊ መልኩ የተሻለ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡  

  አጠቃላይ ሃብታቸው 1.08 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል

       ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2017 የፈረንጆች አመት፣የአለማችን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ቀዳሚ 100 ቢሊየነሮችን ዝርዝር ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገ ሲሆን በአመቱ የ6.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት የተጣራ ሃብታቸውን 84.5 ቢሊዮን ዶላር ያደረሱት  የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር የማይክሮሶፍት መስራች ቢል ጌትስ ቀዳሚውን ስፍራ ይዘዋል፡፡
የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ በ81.7 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛነትን ደረጃ ሲይዙ፣ የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ፣ በ69.6 ቢሊዮን ዶላር የአመቱ የአለማችን ሶስተኛው የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለጸጋ መሆኑን ፎርብስ ለሶስተኛ ጊዜ ባወጣው አመታዊ ዝርዝሩ አመልክቷል፡፡
በአመቱ ከፍተኛውን ገቢ ያገኘውም ማርክ ዙክበርግ ሲሆን የዙክበርግ የሃብት መጠን አምና ከነበረው በ15.6 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል ተብሏል፡፡ ዙክበርግ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱትና ዕድሜያቸው ከ40 አመት በታች ከሆነ 16 ባለጸጎች አንዱ መሆኑም ተነግሯል፡፡ ከዙክበርግ በመቀጠል በአመቱ ከፍተኛውን ሃብት ያፈሩት የአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ ናቸው ያለው ፎርብስ፤ ሰውዬው ባለፉት 12 ወራት የሃብት መጠናቸውን በ15.5 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ማድረግ መቻላቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
ከአመቱ 100 የአለማችን የቴክኖሎጂ ቢሊየነሮች ግማሹ አሜሪካውያን ሲሆኑ ስምንቱ ከአንድ እስከ አስር ባለው ደረጃ ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ 33 ያህሉ እስያውያን ባለጸጎች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቻይና እና የሆንግ ኮንግ ቢሊየነሮች መሆናቸው ተነግሯል፡፡
ከ100 የዘርፉ ባለሃብቶች መካከል 11 የሚሆኑት የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረበት ቀንሷል ያለው ፎርብስ፤ ከፍተኛውን ኪሳራ ያስተናገደው ዢያኦሚ የተባለውን ስማርት ስልክ የሚያመርተው ኩባንያ መስራችና ባለቤት ሊ ጁን መሆኑንና፣ የሰውየው የሃብት መጠን በአመቱ በ2.9 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን አመልክቷል፡፡
የአለማችን የቴክኖሎጂ ዘርፍ ባለሃብቶች አጠቃላይ ሃብት ድምር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ በማለፍ፣ 1.08 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንም ፎርብስ አስታውቋል።

   - አገሪቱ የ300 ሚ. ዶላር ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ አጥታለች
                     - የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን እስክታሻሽል ድረስ የ195 ሚ.ዶላር ድጋፍ ታግዷል

      የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ አሜሪካ ለግብጽ ከምትሰጠው አመታዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የገንዘብ እርዳታ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ያህል ቅናሽ ማድረጉንና ተጨማሪ የ195 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍ ማገዱን ባለፈው ማክሰኞ ያስታወቀ ሲሆን የግብጽ መንግስት በውሳኔው ክፉኛ መበሳጨቱ ተዘግቧል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ የትራምፕ አስተዳደር የወሰደውን የእርዳታ ቅናሽና እገዳ እርምጃ ክፉኛ የተቸ ሲሆን እርምጃው በሁለቱ አገራት መካከል ለረጅም ዘመናት የዘለቀውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነትና ግብጽን መርዳት ያለውን ጠቀሜታ በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብሎታል፡፡
አሜሪካ ለግብጽ የምትሰጠውን እርዳታ መቀነሷ፣ የሁለቱን አገራት የጋራ ጥቅሞች እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል ሲልም ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ አስጠንቅቋል፡፡
የትራምፕ አስተዳደር፣ በግብጽ የሚታየው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሁኔታ እየከፋ በመምጣቱና የሲቪክስና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ የሚደረጉ እገዳዎችና የመብት ጥሰቶች ባለመሻሻላቸው፣ ለግብጽ ሲሰጥ የቆየውን የ65.7 ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ ድጋፍና የ30 ሚሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ እርዳታ ገንዘብ፣ ለሌሎች አገራት ለመስጠት መወሰኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከዚህ በተጨማሪም ለግብጽ ልትሰጥ ያቀደቺውን የ195 ሚሊዮን ዶላር የወታደራዊ እርዳታ ማገዷን የዘገበው ቢቢሲ፤ ግብጽ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትንና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የጣለቺውን አፋኝ ህግ እስክታሻሽል ድረስ ገንዘቡ በባንክ እንደሚቆይ መነገሩን አመልክቷል፡፡
ግብጽ ከአሜሪካ ከፍተኛውን አመታዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ እርዳታ ከሚያገኙ ቀዳሚዎቹ አገራት አንዷ እንደሆነች የጠቆመው ዘገባው፤ በየአመቱ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ ስታገኝ እንደነበርም አስታውሷል፡፡