
Administrator
“ለሰላም የሚንበረከኩ ሁሉ በክብር ከፍ ይላሉ
የሰላምና የኢኮኖሚ አርበኞች 20 ሚ. ብር ተሸለሙ
ላለፉት 7 ዓመታት በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ የተሰማራው የቻይናው አንቴክስ ጨርቃጨርቅ ኃ.የተ.የግ.ማ፤ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትና ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን አወዳድሮ 20 ሚሊዮን ብር እንደሚሸልም ያስታወቀው የዛሬ ሁለት ወር ገደማ ነበር፡፡
ከትላንት በስቲያ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ተሲያት በኋላ፣ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተከናወነ ታላቅ ሥነስርዓት፣ በሁለቱም የውድድር ዘርፎች አሸናፊዎች ተለይተው ሽልማታቸው በክብር ተበርክቶላቸዋል፡፡ በሰላም ዘርፍ የጋሞ አባቶች ያሸነፉ ሲሆን፤ በኢኮኖሚ ዘርፍ ደግሞ ኢንቨስተሩ ኢንጂነር ቢጃይ ናይከር አሸንፈዋል፡፡ እያንዳንዳቸውም በነፍስ ወከፍ 10 ሚሊዮን ብርና ከ5 ኪ.ግ ንጹህ ብር የተሰራ ግዙፍ ዋንጫ ተሸልመዋል፡፡
የጋሞ አባቶች የሰላም አሸናፊ መሆናቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ አዳራሹን በባህላዊ ዜማቸው በደስታ አድምቀውታል፡፡ ሽልማታቸውን በክብር ከተቀበሉ በኋላ አንድ ተወካያቸው የተሰማቸውን እንዲናገሩ ተጋበዙ፡፡ የጋሞ አባቶች ተወካይ አንደበተ ርዕቱ ናቸው፡፡ በሰላም ዙሪያ ከፍልስፍና የማይተናነስ አጭር ንግግር አቀረቡ፡፡
“ይሄ ሽልማት እዚህ የመጣን የጋሞ አባቶች ሽልማት ብቻ ሳይሆን የመላው ጋሞ ህዝብ ነውና፣ የጋሞ ህዝብ እንኳን ደስ አለህ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ይሄን ሽልማት ያበረከተልን ድርጅት “ሰላም ከሌለ ቢዝነስ የለም” ይላል፤ ጋሞ ደግሞ “ሰላም ከሌለ ህይወት የለም ብሎ ያምናል” ሲሉም የሰላምን ፋይዳ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በጋሞ ግጭትና ሞት ወይም መፈናቀል የለም ያሉት ተወካዩ፤ ”ለዚህም ምክንያቱ እኛ በሞት መሃል ነው የምንገባው፤በሚወረወር ቀስት መሃል እንገባለን፤ ህዝብ ከሚያልቅ ሁለት ሽማግሌ ሞቶ ትውልድ ቢተርፍ ይሻላል” ብለዋል፡፡
ለሰላም የሚንበረከኩ ሁሉ በክብር ከፍ ይላሉ ያሉት የጋሞ አባቶች ተወካይ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ ሽማግሌዎች ለሰላም ይንበረከኩ ዘንድ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማቱን ላበረከቱት የአንቴክስ ኢትዮጵያ መሥራችና ባለቤት ሚ/ር ቻን ዋ፣ ምስጋናና ምርቃት ያቀረቡ ሲሆን፤ “የውጭ ሰው ቢሆንም የእግዚአብሄር መላዕክተኛ ነው” ብለዋል፡፡ እንደ ማር የሚጣፍጥ ንግግራቸውን ሲቋጩም፤ “እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ጨምሮ ጨማምሮ ይባርካት” በሚል ምርቃት ነው፡፡
በህመም ምክንያት በሽልማት ሥነስርዓቱ ላይ ያልተገኙት የኢኮኖሚ ዘርፍ አሸናፊው ኢንጂነር ቢጃይ ናይከር፣ በልጃቸው አማካይነት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በሽልማቱ ያገኙትን 10 ሚሊዮን ብር በፌስቡክ ላይ ወጣቶችን አወዳድረው ለ62 አሸናፊዎች መልሰው እንደሚያበረከቱት አስታውቀዋል፡፡
ድምጻቸውን በመስጠት ለአሸናፊነት ላበቋቸው ደጋፊዎቻቸው ሁሉ ጥልቅ ምስጋናቸውን በልጃቸው በኩል አቅርበዋል - ኢንጂነሩ ኢንቬስተር፡፡
”ሰላም ከሌለ ንግድ የለም“ (No Peace, No Business) በሚል መርህ በተዘጋጀው በዚህ ውድድር፤ እጩ ተሸላሚዎቹ የተመረጡት 30 በመቶ በህዝብ ድምጽ፣ 70 በመቶ ደግሞ በዳኞች ድምጽ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በሁለቱም ዘርፎች ለመወዳደርና እጩ ተሸላሚ ለመሆን ዘጠኝ ዘጠኝ መስፈርቶች ተቀምጠዋል፡፡ በኢኮኖሚ ዘርፍ ከተዘረዘሩት ዘጠኝ መስፈርቶች የመጀመሪያዎቹ አራቱ፡- ከትንሽ ተነስቶ በራሱ ጥረት የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ የቻለ፣ ለብዙዎች የሥራ በር የከፈተ፣ በሥራ ፈጠራ የተካነ፣ ህዝብና አገርን ለመጥቀም የሚሰራ-- ይላሉ፡፡ በተመሳሳይ በሰላም ዘርፍ ከተዘረዘሩት መስፈርቶች የመጀመሪያዎቹ አራቱ፡- በአመለካከቱ፣ በንግግሩ፣ በአኗኗሩ ሰላምን ከፍ የሚያደርግ፤ ለሰብአዊ መብት መከበር ግድ የሚለው፤ ዋጋ ከፍሎ በህብረተሰብ መካከል እርቅን ለማውረድ የሰራ፤ ይቅርታን እየኖረ፣ ይቅርታን የሰበከ-- የሚሉ ናቸው፡፡
በዚህም መሰረት የሚከተሉት የሰላም ዘርፍ እጩ ተሸላሚዎች ሆነው ተመርጠዋል፡፡
ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ
የጋሞ የዕርቅ አባቶች
የድምጻችን ይሰማ አባላት
ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ
ድምጻዊ ታሪኩ ካንጊሲ (ጂሽካጊና)
የኢኮኖሚ ዘርፍ እጩ ተሸላሚዎች ሆነው የተመረጡት ደግሞ እነሆ፡፡
ኢንጂነር ቢጃይ ናይክር
ወጣት ኢዘዲን ከሚል
ዶ/ር መሃመድ ሽኩር
ወ/ሮ በረከት ወርቁ (በረከት ገበሬዋ)
ዶ/ር ዘሩ ገብረሊባኖስ
በሁለቱም ዘርፎች የተመረጡት እጩ ተሸላሚዎች፤ ከ2 ኪ.ግ ንጹህ ብር የተሰራ ዋንጫ የተሸለሙ ሲሆን፤ በየበኩላቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ይፋ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል - በዕለቱ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ በተዘጋጀው ታላቅ ሥነስርዓት፡፡
በሚያስገርም ሁኔታ፣ የዚህ ውድድርና ሽልማት አዘጋጅ፣ የአንቴክስ ኢትዮጵያ መሥራችና ባለቤት ሚ/ር ቻን ዋ፤ ከዕለቱ እንግዶች ታላቅ ክብርና አድናቆት ጎርፎላቸዋል፡፡ በእጅጉም ተመስግነዋል፡፡
በሥነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሃፊ ቄሲስ ታጋይ ታደለ ባደረጉት ንግግር፤ “ዛሬ በጣም ደስ የሚል ቀን ነው፤ ኢትዮጵያ እንዲህ ሰላምን መፈለግ ከጀመረች ለውጥ ታመጣለች፤” ብለዋል፡፡
አንቴክስ ኢትዮጵያን በተመለከተም በሰጡት አስተያየት፤ “ሌሎች የውጭ ድርጅቶች የጸጥታ ችግር ሲፈጠር ሥራቸውን ዘግተው፣ ሠራተኞቻቸውን በትነው ሰላም ወዳለበት አገር ይሄዳሉ፤ አንቴክስ ግን የሰላም ሁኔታውን ማሻሻል ይቻላል በሚል እምነት የመፍትሄ አካል ነው የሆነው፡፡ ይሄ በእጅጉ ያስመሰግነዋል፡፡ ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው፡፡” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላዋ የክብር እንግዳ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው፤ ለአንቴክስ ኢትዮጵያ መሥራችና ባለቤት ትልቅ ክብርና አድናቆት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ በተለይ አዳማ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካን በጎበኙ ወቅት የሠራተኞቹን አያያዝ ተመልክተው መደመማቸውን ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያን ከማናችንም በተሻለ ይወዳታል፤ እንዲህ ዓይነት ቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው ማግኘት መታደል ነው፡፡” ብለዋል፤ ወ/ሮ መሰንበት፡፡
እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም ኢትዮጵያን ከጎበኟት በኋላ ከአገሪቷና ህዝቧ ጋር በፍቅር ወደቅሁ የሚሉት የአንቴክስ ኢትዮጵያ መሥራች ሚ/ር ቻን ዋ፤ ወዲያው ያለአንዳች ማመንታት ኢንቨስት ለማድረግ መወሰናቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በንግግራቸው የቻይናን ስኬት እያጣቀሱ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያስረዱት ሚ/ር ቻን፤ ለቻይና ከፍተኛ የዕድገት ስኬት ሁለት መሰረታዊ ምሰሶዎች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዱ ላለፉት 40 ዓመታት ቻይና በዘላቂ ሰላምና የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መዝለቋ ነው ለስኬት ያበቃት ይላሉ፡፡ አንዱ ምሰሶ ሰላም ነው፡፡
ሰላም ብቻ ግን ለአንድ አገር ልማትና ብልጽግና በቂ አይደለም ባይ ናቸው፤ ቻይናዊው ኢንቬስተር፡፡ ሁሉም ዜጎች (በዕድሜ፣ በጾታ፣ በዘር፣ በሃይማኖትና በአመለካከት የተነሳ ልዩነት ሳይደረግባቸው) በአገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ በእኩልነት መሳተፍ አለባቸው፤ እኩል ዕድል ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ ለዜጎች ሁሉ እኩልና ፍትሃዊ ዕድል መኖር አለበት፤ ሁለተኛው ምሰሶ ይሄ ነው ሲሉ፣ የቻይናን የዕድገትና ብልጽግና ምስጢር ያስረዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ ይሄን ማድረግ ከቻለች ከቻይናም ባጠረ ጊዜ ስኬትን እንደምትቀዳጅ በልበሙሉነት ይናገራሉ፤ ሚ/ር ቻን፡፡
አንቴክስ ኢትዮጵያ ላለፉት 7 ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በነበረው ቆይታ፣ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች በመገንዘብ፣ መፍትሄ የማፈላለግ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና ለመወጣት ባቋቋመው ፉድ ኤንድ ፕላስ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት አማካኝነት በርካታ እርዳታዎችና ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ይነገራል፡፡
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማትና ሰላም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕውቅና የሚሰጥ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሥራዎች (Best Influencer Work Prize) ሽልማትም የዚሁ እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ የBIW Prize ዓላማም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት በተለየ መንገድ ጥረት ለሚያደርጉና በህዝቡ መካከል ሰላማዊ አብሮነትን ለማጎልበት ለሚተጉ፣ በሥራቸውም ለሌሎች አርአያ መሆን የቻሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ማበረታታትና ሥራቸውንም ማገዝ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
የዛሬ ሁለት ወር ገደማ በአዳማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አንቴክስ ኢትዮጵያ በሰጠው መግለጫ፣ የBIW Prize በየዓመቱ እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡ በእርግጥም “ሰላም ከሌለ ንግድ የለም” - (ኖ ፒስ ኖ ቢዝነስ) ለሚለው ጉዳይ፣ ሁሉም በቢዝነስ ላይ የተሰማሩ ወገኖች ትኩረት ሊሰጡትና ለመፍትሄውም የድርሻቸውን ሊያዋጡ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የአንቴክስ ኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ ተግባር ለብዙዎች አርአያ እንደሚሆን ይታመናል፡፡
አንቴክስ ኢትዮጵያ በአዳማ ኢንዱስትርያል ፓርክ ከ10 በላይ ሼዶች ያሉት ሲሆን፤ ለ4500 ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ የስፖርት ልብሶችን፣ የውስጥ ልብሶችን፣ የተጠለፉና የተሸመኑ ልብሶችን፣ እንዲሁም ሁሉንም ዩኒፎርሞች እያመረተ ወደ ውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ አንቴክስ ግሩፕ፤ እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም በቻይና የተመሰረተ ኩባንያ ሲሆን፣ ከቻይና በተጨማሪም በእስያና በአፍሪካ በጨርቃጨርቅና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየሰራ የሚገኝ ድርጅት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የውድድርና ሽልማት ዝግጅቱን ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ያስተባበረው በሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ ሲሆን፤ ይሄን ፕሮጀክት በአስገራሚና አስደናቂ ብቃት በመወጣቱ ሊመሰገን ይገባዋል፡፡ በተለይ በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ የተዘጋጀው የሽልማት መርሃ ግብር ለብዙዎቹ የአገራችን ኹነት አዘጋጆች መማሪያ የሚሆን ነው፡፡ ጥንቅቅ ያለ ጥራቱን የጠበቀ መርሃግብር ነው ያዘጋጀው - በሻቱ ቶለማርያም መልቲሚዲያ፡፡
የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ በምክር ቤት አባላት ትችት ቀረበበት
“ህ ዝቡን ለተደራረበ የግብር ወጪ የሚዳርግ ነው
የታክስ አስተዳደርን እንደሚያዘምን የተነገረለት የንብረት ታክስ ረቂቅ አዋጅ ትችት የቀረበበት ሲሆን፤ አዋጁ ጸድቆ ወደ ተግባር ከመገባቱ በፊት ሕዝብ ሊመክርበት ይገባል ተብሏል።
ይህ የተነገረው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ላይ በተደረገ ውይይት ነው። በውይይቱም ከምክር ቤት አባላት የተለያዩ አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን፤ ስለ ዓዋጁ ሰፋ ያለ ማብራሪያም ተሰጥቷል።
ረቂቁን ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ያቀረቡት የገንዘብ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች መመሪያ ሃላፊ አቶ ተወዳጅ መሃመድ ናቸው፡፡ ሌሎች አገራት ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ የንብረት ታክስን እንደሚጥሉ የጠቆሙት ሃላፊው፤ ኢትዮጵያ ግን ተሽከርካሪ ወይም ተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ ታክሱን ተግብራ እንደማታውቅ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ማብራሪያ ላይ እንደተጠቆመው፣ በንብረት ታክስ አማካይነት የሚሰበሰበው ገቢ በየከተሞቹ ለሚከናወኑ የተለያዩ የልማት ስራዎች ይውላል። በተጨማሪም፣ ከሌሎች የታክስ ሥርዓቶች ይልቅ ለቁጥጥር ቀላልና ግልጽ ነው ተብሏል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ሲዘጋጅ የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በጥናት ለመዳሰስ ጥረት መደረጉ የተገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በጣሪያና ግድግዳ፣ በቤት ግብርና በመሳሰሉ አነስተኛ ገንዘብ ሲሰበሰብ እንደቆየ ተጠቁሟል፡፡ ከተሞች ከእነዚህ የተለያዩ ገቢዎች ውስጥ ለልማት ከሚያስፈልጋቸው የገንዘብ መጠን የሚያገኙት 1.8 በመቶውን ብቻ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
ይህንን ለማሻሻልና ለከተሞች ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ሲባል ረቂቅ ዓዋጁ እንደተዘጋጀና በባሕር ዳር፣ መቐለ እና ድሬዳዋ ከተሞች ለአዋጁ እንደ ግብዓት የሚያገለግል ጥናት መደረጉን ተመልክቷል። በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደሰፈረው ከሆነ፤ አጠቃላይ ንብረቱ ካለው ግምት 25 በመቶ ተወስዶ፣ ከእርሱ ላይ 0.2 በመቶ ቢጣል ተብሎ ቀርቧል።
የንብረት ታክስ ከሌሎች የታክስ ዓይነቶች የሚለየው ግብር ከፋዩ “ይህን ያህል መክፈል እችላለሁ” ብሎ የሚያቀርበው ሳይሆን፤ በከተሞች ውሳኔ ተተምኖ የሚሰበሰብ ነው ተብሏል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ ሃሳባቸውን የገለጹት የምክር ቤቱ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ “ከዚህ ቀደም የኤክሳይዝ ታክስ አሻሽለናል፤ የተጨማሪ እሴት ታክስም እንደዛው። የመንግስት ሰራተኛው ላይ ከ25 እስከ 35 በመቶ የገቢ ግብር የሚከፍል ሲሆን፤ ለሚገዛቸው የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦች ተጨማሪ ዕሴት ታክስ ተጥሎበታል። አሁን ደግሞ የንብረት ታክስ ይጠበቃል። ይህ ደግሞ ሕዝቡን ለተደራረበ የግብር ወጪ መዳረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፤ ረቂቅ ዓዋጁ “ይፈጥረዋል” ያሉትን ጫና የንግዱ ማሕበረሰብ መቋቋም እንደሚችል በመግለጽ፣ ረቂቅ አዋጁ በሌላው ማሕበረሰብ ላይ ከፍተኛ ችግርና መማረር እንዳይፈጥር ስጋት እንዳላቸው አንስተዋል።
“የንብረት ታክስ አዋጅ ግብሩ የተሻለ ገቢ ባለው ላይ ነው ‘የሚጣለው’ ይላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ገቢ ስንት ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ የተሻለ ገቢ ያለውስ ማን ነው? የገቢው መነሻስ ስንት ነው?” ሲሉ ዶ/ር ደሳለኝ ሞግተዋል፡፡ ዶ/ር ደሳለኝ አክለውም፤ “እዚህ ቤት ብዙ ሰው ስጋት አንስቷል። በተደጋጋሚ የተለያዩ ስጋቶችን እናነሳለን። ድምጽ ስንሰጥ ግን ድምጽ የሚሰጠው ሰው ምክር ቤት ውስጥ ከሚሰጠው አስተያየት ጋር አይገናኝም። አንዳንዴ እንደ ምክር ቤት አባላትና እንደ ሕዝብ ተወካይነታችን፣ ስጋታችን በምንሰጠው ድምጽ በኩል መንጸባረቅ አለበት ብዬ አምናለሁ።” በማለት መልዕክታቸውን አጋርተዋል።
ሌሎች የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ አዋጁ ጸድቆ ወደ ስራ ከመግባቱ በፊት ግልጽ በሆነ መልኩ ህዝቡን ማወያየት እንደሚገባ አሳስበዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው፤ “የታክስ ገቢን ማሳደግና የዕዳ ክምችትን መቀነስ የሪፎርሙ አንዱ አካል ከመሆኑ አንጻር ረቂቅ ዓዋጁ የታክስ አስተዳደሩን ለማዘመን ያግዛል።” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሁለት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ታገዱ
የሲቪክ ተቋማት በነፃነት የሚሰሩበት ምህዳር እንዲፈጠር ተጠይቋል
በለውጡ ማግስት የሲቪክ ተቋማት በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ የሚያግዱና የሚያፍኑ ህጎች መሻሻላቸውን ተከትሎ፤ ምህዳሩ የበለጠ ምቹና ነፃ እንደሚሆን ብዙዎች ጠብቀው ነበር፡፡ በእርግጥም ላለፉት 4 እና 5 ዓመታት በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ታይቶ ነበር፡፡ በርካታ ሲቪል ተቋማት ተመስርተዋ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ሁኔታዎች ፈፅሞ ተለይተዋል ይላሉ - የሰብአዊ መብ ተሟጋቾች፡፡
ከሰሞኑ አንጋፋው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አዳዲስ ተሟጋቾች ማዕከል ባወጡት መግለጫ፤ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶ ባለስልጣን መታገዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ ድርጅቶቹ የታገዱት “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል” በሚል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢሰመጉ ከትላንት በስቲያ ታሕሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በተሻሻለው የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሰረት ተመዝግቦ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም፣ ታሕሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ከሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በተጻፈ ደብዳቤ መታገዱን አመልክቷል። ድርጅቱ ለዕግድ የበቃበትን ምክንያት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሲገልጽ፣ ከተቋቋመለት ዓላማ ውጪ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና፣ ገለልተኛ እንዳልሆነ ጠቁሞ፣ እ.ኤ.አ. በ2023 የበጀት ዓመት የአስተዳደር ወጪ ገደብ ጠብቆ እንዳልሰራና ሃላፊነት በጎደለው መልኩ እንደተንቀሳቀሰ በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።
በአሁኑ ሰዓት ዕግዱ በሚነሳበት ሁኔታ ላይ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ የገለፀው ኢሰመጉ፣ “የገጠመንን ተግዳሮት በንግግር በመፍታት አሁንም ቢሆን ለሰብዓዊ መብት መከበር፣ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለሕግ የበላይነት የአገራችንን ሕግና ስርዓትን በመከተልና የድርጅታችን ሕገደንብ በሚፈቅድልን መሰረት እንደ ሁልጊዜው በገለልተኝነትና በሃላፊነት መንፈስ ስራችንን በትጋት ለመወጣት እንጥራለን” ብሏል፣ በመግለጫው።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል በበኩሉ፣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ታሕሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ታህሳስ 16 በደረሰው ደብዳቤ፣ ድርጅታቸው ከማንኛውም እንቅስቃሴዎች እገዳ እንደተጣለበት ማወቁን ጠቁሟል። አያይዞም፣ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተላከለት ደብዳቤ የተጻፈው ታሕሳስ 14 መሆኑን ገልጾ፣ እንደ ኢሰመጉ ሁሉ ማዕከሉ የታገደው “ድርጅቱ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ በመንቀሳቀሱና ገለልተኛ ባለመሆኑ” በሚሉ ምክንያቶችና “ግልጽ የሆነ የአደረጃጀት መዋቅር የሌለው ነው” በሚል ክስ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በባለስልጣን መ/ቤቱ በተጻፈው ደብዳቤ ማዕከሉ፤ “ሃላፊነት በጎደለው መልኩ የተንቀሳቀሰ መሆኑ በተደረገ ክትትልና ግምገማ ለማረጋገጥ ተችሏል” ብሏል። ይሁንና በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቀረቡበትን ክሶች ያጣጣለው ማዕከሉ፣ “ድርጅታችን ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ ከተቋቋመበት አላማ ውጭ በየትኛውም ያልተገባ ወይም ከህግ የሚጻረር እንቅስቃሴ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ የማያውቅ መሆኑን ገልጷል” ሲል አትቷል።
ድርጅቱ አክሎም፣ በማያውቀው መልኩ ሃሳቡ በሕግ አግባብ ባልተጠየቀበት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ክትትልና ግምገማ ያካሄደ መሆኑን በመግለጽ፣ ያስተላለፈው ዕገዳ “አግባብነት ያለውና ሕግን የተከተለ ነው” ብሎ እንደማያምን በመግለጫው ጠቅሷል። በዕግዱ ዙሪያ “በቂ ማብራሪያ” እንዲሰጠው የሚጠይቅ ደብዳቤ ለባለስልጣኑ ማስገባቱንም ማዕከሉ አመልክቷል።
ባለስልጣኑ ይህንን ደብዳቤ ተመልክቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስም ድርጅቱ ከየትኛውም ሥራዎቹ መታገዱንና ጽሕፈት ቤቱም መዘጋቱን ድርጅቱ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
ባለፈው ሕዳር ወር ውስጥ በጥቂት ቀናት ልዩነት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሞያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ በባለስልጣኑ መ/ቤት የታገደ ሲሆን፤ ከቀናት በኋላ በድርጅቶቹ ላይ የተጣለው ዕግድ ቢነሳም፤ ካርድና የሕግ ባለሞያዎች ለሰብዓዊ መብቶች በድጋሚ መታገዳቸው ይታወሳል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ላይ እየተጣለ ያለው ዕገዳ አሳሳቢ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታውቋል፡፡
በተመሳሳይ፣ “የኢትዮጵያ መንግስት፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚሰሩ ድርጅቶችን ማዋከብና፣ ማገድ ሊያቆም ይገባል” በማለት ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂዩማን ራይት ሰዎች ህዳር 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አሳስቦ ነበር። ተቋሙ አክሎም፤ በአገሪቱ የሲቪክ ተቋማት በነጻነት ሊሰሩበት የሚያስችል ምህዳር እንዲፈጠር ጠይቋል።
ይህ ዜና ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሰዓት ድረስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሰጠው መግለጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።
ኤልያስ መልካ የቅንብር አሻራውን ያሳረፈበት አልበም ሊወጣ ነው
አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ኤልያስ መልካ የቅንብር አሻራውን ያሳረፈበት የድምጻዊ አብርሃም በላይነህ (አብርሃም ሻላዬ) “ቀን በቀን” የተሰኘ አልበም ሊወጣ መሆኑ ተነግሯል። በአልበሙ ወጣትና አንጋፋ ባለሞያዎች እንደተጣመሩበት ተጠቅሷል።
የፊታችን ታኅሳስ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በድምፃዊው የዩቱዩብ ቻናል ለአድማጭ በሚደርሰው በዚሁ አልበም ላይ፣ የዚህ ትውልድ ቀለም የሆኑት ኤልያስ መልካና ሚካኤል ሃይሉ (ሚኪ ጃኖ) በላቀ ደረጃ በሙዚቃ ቅንብር የተጣመሩበት ሲሆን፤ ወንደወሰን ይሁብ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ናትናኤል ግርማቸውና አንተነህ ወራሽን የመሳሰሉ የግጥምና ዜማ ሞያተኞች በአልበሙ ላይ ተሳትፈዋል።
“ቀን በቀን” አልበምን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 9 ዓመታትን እንደፈጀ ተነግሯል።
ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት ለሙዚቃ አድማጮች ባደረሰው “ሻላዬ” የተሰኘ ባሕላዊ ነጠላ ዜማው ከፍተኛ ተወዳጅነትና ዕውቅናን ያተረፈው አብርሃም በላይነህ (አብርሃም ሻላዬ)፤ ለዓመታት በለቀቃቸው ነጠላ ዜማዎቹ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍ ያለ ዝናን ከማትረፉም በላይ፣ “እቴ ዓባይ” በተሰኘ ስራውም በ“All African Music Award" አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡
የግጥም መድበል እየተሸጠ ነው - ይዘዙን!
በዘውዴ አለልኝ የተጻፈው ‹‹ጊዜን መሸከም›› የተሰኘ የግጥም መድበል ለንባብ በቃ። መድበሉ 54 ግጥሞችን የያዘ ሲሆን በ162 ገጾች የተቀነበበ ነው፡፡
የመጽሐፉ ቅርጽ በዋሽንት አውታረ ቅኝት የተሠራ ሆኖ በጥቁር፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ነጭ ቀለማት የተከፋፈለ ነው። ቀለማቱ ከኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ዋሽንት፣ ክራር፣ ነጋሪትና ሞረሽ ከምትባል ወፍ ጋር የተቀነባበረ ነው። እያንዳንዱ ክፍል ቀለማዊና ሙዚቃዊ ፍካሬ መግቢያ አለው።
የግጥም መድበሉ ታትሞ ለሽያጭ ተዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉን ለመግዛት የምትፈልጉ በኦንላይን ይዘዙን፡፡ ዋጋው ለአገር ውስጥ 350 ብር ሲሆን፣ ለውጭ ሀገር በ20 ዶላር ተተምኗል።
የባንክ ሂሳብ ቁጥር...
አቢሲኒያ ባንክ ( bank of abyssinia) 200869327 ዘውዱ አለልኝ አራገው ( zewdu alelgn aragaw)
ዳሽን ባንክ (Dashen bank) 5472769396011 ዘውዱ አለልኝ አራጋው ( zewdu alelgn aragaw)
ንግድ ባንክ (CBE ) 1000298476936 (Daniel abreha) ዳንኤል አብርሃ
ቴሌ ብር / tellebirr፦ 0913240885 zewdu alelgn
እባክዎ ክፍያ የፈጸሙበትን የባንክ ደረሰኝ Screenshot አድርገው፣ ወይም ፎቶ አንስተው በዚህ የቴሌግራም ሊንክ @Gizienmeshekem2424 ይላኩልን፡፡
አርቲስት መስከረም አበራ የኢቭ የሕጻናት ዳይፐር የብራንድ አምባሳደር ሆነች
በተለያዩ የፊልምና የመድረክ ተውኔቶች የምትታወቀው አርቲስት መስከረም አበራ፤ የኢቭ የሕጻናት ዳይፐር የብራንድ አምባሳደር ሆና ተመርጣለች። አርቲስት መስከረም ለብራንድ አምባሳደርነቱ የተከፈላትን ክፍያ በይፋ ከመግለጽ ተቆጥባለች።
ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል በተካሄደ መርሃግብር፣ ስለ አርቲስት መስከረም አበራ ሞያዊ አበርክቶና ስነ ምግባር፣ በደራሲና ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይና በተውኔት ደራሲና አዘጋጅ ዳግማዊ “አመለወርቅ” ፈይሳ አማካይነት የቀረበ ሲሆን፤ ኢቭ ሞዴስ እና የሕጻናት ዳይፐር፣ አርቲስት መስከረምን ለብራንድ አምባሳደርነት መምረጡ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
አርቲስት መስከረም በበኩሏ፤ ከኢቭ ሞዴስ ጋር የነበራትን ቀደም ያለ መስተጋብር በማውሳት፣ “ከራሴ ሴትነት ጋር በተገናኘ የ’ኢቭ’ን ምርት አውቀዋለሁ” ብላለች። አያይዛም፣ “ልጅ የለኝም፤ ነገር ግን ልጅ ለወለዱ ወዳጆቼ በመስጠት ምርቱን እንዲጠቀሙ አደርጋለሁ” ስትል ቃል ገብታለች።
የብራንድ አምባሳደርነቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ ሲሆን፣ የቢልቦርድ፤ የቴሌቪዥንና የራዲዮ ማስታወቂያዎችን መስራት የሚያስችላት መሆኑ ተነግሯል። አርቲስቷ ከአምራች ድርጅቱ ስለተከፈላት የገንዘብ መጠን በይፋ ከመግለጽ ተቆጥባለች።
“የእኔ ደስታ በሞያዬ መቆየት ነው፤ ፍላጎቴም የሕዝቡን ስሜት መረዳት ነው። የኢቭ ዳይፐር የብራንድ አምባሳደርነት የመጀመሪያ ስራዬ ይሆናል። ወደፊት ሌሎች ስራዎች ይኖራሉ” ብላለች፤ አርቲስት መስከረም አበራ፡፡
ኢቭ ሞዴስ እና ዳይፐርን የሚያመርተው ጊዮፒዮን የንጽህና መጠበቂያ ግብዓቶች አቅራቢ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ስራውን ከጀመረ 16 ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፤ የተለያዩ የጥራት ሽልማቶችን እንዳሸነፈ ለማወቅ ተችሏል።
ዳሸን ባንክ የሴቶችን የመሪነት ሚና ለማሳደግ የሚያስችል መርሃ ግብር አስጀመረ
ዳሸን ባንክ የሴቶችን የመሪነት ሚና ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል መርሃ ግብር አስጀምሯል፡፡ መርሃ ግብሩ የሴት ሰራተኞቹን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት ያስችላል ተብሏል።
በመርሃ-ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አፋው ዓለሙ፤ “ዛሬ የምንኮራባቸው የአገራችን ታሪካዊ ድሎችን እንድንጎናፀፍ ሴቶች ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክተዋል” ብለዋል፡፡
ከታላላቅ አገራዊና ተቋማዊ ስኬቶች ጀርባ የሴቶች ሚና የጎላ መሆኑን የገለጹት አቶ አስፋው፤ ሴቶች ተገቢው ዕውቅና ሊሰጣቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዳሸን ባንክ ይህን ክፍተት በአግባቡ ተገንዝቦ የሚሰራ በመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ ሴቶችን በከፍተኛ የአመራር እርከኖች ላይ በመሾም ወደፊት በማምጣት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ባንኩ ሴቶችን በአግባቡ ያካተተ አሰራር በመፍጠር አዳዲስ ፈጠራዎችንና ውጤታማነትን እንደሚያጎለብት ተመላክቷል፡፡
መርሃ-ግብሩ ባንኩ ሁሉም ሰራተኞች ዕኩል ዕድል የማግኘትና የማደግ አጋጣሚ እንዲያገኙ ለማድረግ ካለው ራዕይ ጋር አብሮ የሚሄድ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
በዳሸን ባንክ የሰው ሐብት ዋና መኮንን ወ/ሮ ህይወቴ ከፈለኝ በበኩላቸው፤ “ፕሮግራሙ በባንካችን ወደፊት ከፍተኛ አመራር መሆን የሚችሉ ሴቶችን ከወዲሁ ለመለየትና ለማብቃት የተነደፈ ነው” ብለዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የተሻለ ልምድ ያላቸውን ሴቶች ድጋፍ ከሚሹ ሴቶች ጋር በማገናኘት ጠቃሚ የሙያ ዕድገት እንዲያገኙ የሚያስችሉ ድጋፎችን ለመስጠት ያለመ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ሐሳባቸውን ያጋሩት የ'ሴታዊት ንቅናቄ' መስራች ዶ/ር ስህን ተፈራ፤ ዳሸን ባንክ ሴቶችን በሁሉም መስክ ብቁ ለማድረግ እየሰራ ያለው ሥራ ለሌሎች ተቋማት ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል።
አዲሱ “ማይክሽን መከለሻ” ቅመም በይፋ ተዋወቀ
ባለፈው መስከረም ወር ላይ ገበያውን እንደተቀላቀለ የተነገረለት አዲሱ “ማይክሽን መከለሻ” ቅመም በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል በይፋ ተዋወቀ፡፡
“ማይክሽን መከለሻ” የተለያዩ ሃገራዊ ቅመሞችን እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈውን የሸኖ ለጋ ቃናን በውስጡ የያዘ ነው ተብሏል፡፡
ዛሬ ታህሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ረፋዱ ላይ አዲሱን ምርት በይፋ የማስተዋወቅ መርህ ግብር በሸራተን አዲስ የተከናወነ ሲሆን፤የአምራች ድርጅቱ ሎንግሪቨር አግሮ ኢንዱስትሪ መሥራችና ባለቤት ከአጋሮቻቸው ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ከተፈጥሮአዊ ግብአቶች ተቀምሞ የተሰናዳው “ማይክሽን መከለሻ”፤ ሃገራዊ ቅመሞችን ያካተተ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ቅርንፉድ፣ ከሙን፣ ቀረፋ፣ የካርዌል ዘርና ሌሎች የተለያዩ ቅመሞችን በአንድ ላይ የያዘ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ሎንግሪቨር አግሮ ኢንዱስትሪ ባወጣው መግለጫ፤ ”ለዘመናዊም ሆነ ለባህላዊ ምግቦች እንዲሁም በፍስክ ወቅት ጭምር ተስማሚ ነው ነው” ብሏል፡፡
በማናቸውም ሱቆችና ሱፐርማርኬቶች ለገበያ እንደቀረበ የተነገረለት “ማይክሽን መከለሻ”፤ አንዱ በ25 ብር እንደሚሸጥ ተጠቁሟል፡፡
የ“ማይክሽን መከለሻ” አምራች የሆነው ሎንግሪቨር አግሮ ኢንዱስትሪ እ.ኤ.አ በ2022 ዓ.ም በኢትዮጵያ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፤ የተለያዩ የምግብ ምርቶችን ለማምረት የተቋቋመ የውጭ ኢንቨስትመንት ኩባንያ ነው፡፡ ድርጅቱ በዱባይ በዓለማቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያተረፈው የዩኒግሎካል ኢንተርትሬድ አካል ነው፡፡
አሚጎስ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ
• የማህበሩ ጠቅላላ ሃብት ከ1 ቢ.ብር በላይ ደርሷል
አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበር፣ በ2016 በጀት ዓመት በአጠቃላይ 145 ሚሊዮን ብር ማትረፉንና ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የማህበሩ አባላት የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 53 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበሩ ይህን ያስታወቀው ዛሬ ታሕሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ 11ኛ የባለአክስዮኖች ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
የማህበሩ አባላት በተገኙበት ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በዚህ ወቅትም የአሚጎስ ጠቅላላ ሃብት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተነግሯል፡፡
አሚጎስ በዛሬው ጉባኤው የኅብረት ስራ ማህበሩን ጠቅላላ ጉባኤ ተወካዮች የመረጠ ሲሆን፤ በቀጣይ ያቀዳቸው ሰፋፊ ስራዎችም ቀርበዋል።
የዛሬ 12 ዓመት በሦስት ዓይን ገላጭ መሥራቾች ተጀምሮ ዛሬ ወደ 10ሺ የሚጠጉ አባላትን ያፈራው የህብረት ሥራ ማህበሩ፤ ወደ 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ አጠቃላይ ካፒታል ያለው ሲሆን፤ ከ120 በላይ ሰራተኞች ይዞ በተለያዩ የክልል ከተሞች ቅርንጫፎቹን በማብዛት ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚገኝ ከማህበሩ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡