Administrator

Administrator

በመላው አለም ጦርነትንና የእርስ በእርስ ግጭትን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 መጨረሻ ላይ 71 ሚሊዮን ያህል መድረሱንና አመቱ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛው የተፈናቃዮች ቁጥር የተመዘገበበት መሆኑን ተመድ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አለማቀፍ ሪፖርት እንዳለው፣ በአመቱ ከተፈናቀሉት 71 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 41.3 ሚሊዮን ያህሉ በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ፣ 25.9 ሚሊዮን የሚሆኑት ስደተኞች እንዲሁም 3.5 ሚሊዮን ያህሉ ጥገኝነት ፈላጊዎች ናቸው፡፡
በፈረንጆች አመት 2018 የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር አምና ከነበረው በ2.3 ሚሊዮን ጨምሯል  ያለው ሪፖርቱ፤ የተፈናቀሉት ሰዎች የአንድ አገር ዜጎች ቢሆኑ ከአለማችን አገራት በህዝብ ብዛት 20ኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጡ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡
በአዳዲስ ተፈናቃዮች ቁጥር ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ኢትዮጵያ እንደሆነች የጠቆመው ዘገባው፣ በአመቱ 1.5 ሚሊዮን ያህል ኢትዮጵያውያን መፈናቀላቸውንና ሁሉም  በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ እንደሆኑም አክሎ ገልጧል፡፡

አውሮፕላኖች ከአብራሪዎች ቁጥጥር ውጭ እየሆኑ በመከስከስ በርካታ መንገደኞችን ለህልፈተ ህይወት በሚዳርጉበትና የአቪየሽን ኢንዱስትሪ በደህንነት ስጋት ውስጥ በወደቀበት በዚህ አደገኛ ወቅት ላይ፣ ታዋቂው የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ኤርባስ፤ ያለአብራሪ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን ላመርት ነው ማለቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው፡፡
ኤርባስ ኩባንያ ያለምንም አብራሪ በቴክኖሎጂ ብቻ እየታገዙ መንገደኞችን አሳፍረው የሚበርሩ አውሮፕላኖችን ለማምረት ማቀዱን የኩባንያው የንግድ ዘርፍ ሃላፊ ባለፈው ሰኞ ማስታወቃቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ብዙዎች ሃሳቡን ቢቃወሙትም ከሰሞኑ በአሜሪካ በ22 ሺህ ሰዎች ላይ በተካሄደ ጥናት ግን 70 በመቶ ያህሉ አብራሪ በሌላቸው መሰል አውሮፕላኖች ለመጓዝ እንደሚመርጡ መግለጻቸውን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአለማችን ያለአብራሪ የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችን የሚጠቀም የንግድ ተቋም እንደሌለ የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል አውሮፕላኖችን መንገደኞችን በመደበኛነት ለማጓጓዝ በጥቅም ላይ ማዋል በህግ እንዳልተፈቀደም ገልጧል፡፡ በተያያዘ ዜናም፣ ተፎካካሪው ቦይንግ ኩባንያ፤ በ737 ማክስ ኤይት  አውሮፕላኑ ሳቢያ ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ፣ ኤርባስ ገቢው መጨመሩንና አዲስ ያመረተውን ኤ321ኤክስኤልአር የተባለ ግዙፍ አውሮፕላን በገፍ መሸጥ መጀመሩን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ኩባንያው 27 ያህል አውሮፕላኖችን ለተለያዩ ደንበኞች ለመሸጥ ትዕዛዝ መቀበሉንና ሽያጩ 15 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስገኝለት ባለፈው ሰኞ ዕለት በፓሪስ በተጀመረው አለማቀፍ የአየር መንገዶች ኤግዚቢሽን ላይ ይፋ ማድረጉን ያስታወሰው ዘገባው፣ 200 አውሮፕላኖችን ይሸጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክቷል፡፡

የተሻለ እድገት ያላቸው አገራት ክትባትን በተመለከተ ያላቸው በጎ አመለካከት ከድሃ አገራት ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ እንደሆነ ዌልካም የተባለ አንድ የጥናት ተቋም ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
በ144 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ ከ140 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ የተሰራውን ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት ለክትባት እጅግ ዝቅተኛ የሆነ አመለካከት ያላቸው ህዝቦች የሚገኙባት አገር ፈረንሳይ ስትሆን 33 በመቶ ያህል የአገሪቱ ዜጎች ክትባት ጥሩ አይደለም ብለው እንደሚያስቡ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡
በአብዛኞቹ ያደጉት አገራት ለክትባት ጥሩ ያልሆነ አመለካከት መኖሩን የጠቆመው ጥናቱ፣ ምላሻቸውን የሰጡት ሰዎች በሙሉ ክትባትን እንደሚደግፉ የገለጹባቸውን ባንግላዴሽንና ሩዋንዳን በመሳሰሉ ያላደጉ አገራት በአንጻሩ ለክትባት በጎ አመለካከት መኖሩን አስረድቷል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ 79 በመቶ ያህል ሰዎች ክትባት ችግር የለውም ብለው እንደሚያስቡ፣ 84 በመቶ ያህሉ ደግሞ ክትባት በሽታዎችን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ነው ብለው እንደሚያስቡ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ለክትባት በጎ አመለካከት አለመኖር አለማቀፍ ክስተት መሆኑንና ከአለማቀፉ የጤናው ዘርፍ 10 ዋነኛ ተግዳሮቶች መካከል ይሄው የተዛባ አመለካከት አንዱ መሆኑን በቅርቡ ይፋ ማድረጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ዘንድሮም ለ8ኛ አመት መሪነቱን ይዟል

                የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ይፋ የተደረገ ሲሆን ላለፉት ሰባት ተከታታይ አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዘለቀው የአሜሪካው ማሳቹሴትስ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ዘንድሮም ክብሩን አስጠብቋል፡፡
በምርምርና በመማር ማስተማር ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ጨምሮ የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ መስፈርቶች እያወዳደረ በየአመቱ ደረጃ የሚያወጣው ኪውኤስ የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው የአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን የያዙት የአሜሪካዎቹ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡
ካሊፎርኒያ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኦክስፎርድ፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካምብሪጅ፣ ኢቲኤች ዙሪክ፣ ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን፣ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቺካጎ እና ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች መሆናቸውንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ በየአመቱ የአለማችንን ዩኒቨርሲቲዎች እያወዳደረ ደረጃ የሚሰጠው ተቋሙ፣ በአለማችን 82 አካባቢዎች የሚገኙ 1000 የአመቱ ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎችን ባካተተበት በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች 13 ብቻ ሲሆኑ ስምንቱ የደቡብ አፍሪካ፣ አምስቱ ደግሞ የግብጽ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው፡፡
የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኬፕታውን በአለማቀፍ ደረጃ 198ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የግብጹ አሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካይሮ 395ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡


                       • በልመና የሚመጡ የህክምና ቁሳቁሶች ያለ ቀረጥ ቢገቡ መልካም ነበር
                       • ለጉንችሬ ሆስፒታል የ13.5 ሚ. ብር የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

           የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ዘላለም ጭምዴሳ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ከአሜሪካን ሀገር ያሰባሰቡትን 13.5 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ የህክምና መሣሪያዎች፣ በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ወረዳ ለሚገኘው የጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 1 ቀን 2011 ዓ.ም  ለግሰዋል፡፡
በ2007 ከጤና ጣቢያነት ወደ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያደገው የጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል፤ በወር እስከ 3ሺ ህመምተኞችን የሚያስተናግድ ሲሆን ለህክምና አስፈላጊ ከሆኑ ቁሳቁሶች ግማሽ ያህሉ እንኳ ያልተሟላለት መሆኑ በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
35 የህሙማን አልጋዎች ያሉት ሆስፒታሉ፤ ስምንት ጠቅላላ ሃኪሞች፣ ሶስት አስቸኳይ ቀዶ ጥገና ሃኪሞችና 26 ነርሶች እንዳሉት ተጠቁሟል:: ሆስፒታሉ ካለው ተገልጋይ አንፃር የሚሰጠው አገልግሎት በህክምና ቁሳቁሶች እጥረት በሚፈለገው ልክ አለመሆኑን የገለጹት የሆስፒታሉ አስተዳደሮች፤ ዶ/ር ዘላለምና አጋሮቻቸው ያበረከቱት ድጋፍ ለሆስፒታሉ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡  
የደም ማቆያ ባንክን ጨምሮ 20 ያህል አልጋዎች፣ ዊልቼሮችና ሌሎች በርከት ያሉ የህክምና ቁሳቁሶችን ለሆስፒታሉ ያበረከቱት ዶ/ር ዘላለም፤ ስለ እርዳታ አሰባሰቡና ስለ ወደፊት ዕቅዳቸው እንዲሁም ስለሚሰጡት  ነጻ የህክምና ድጋፍ ለአዲስ አድማስ አብራርተዋል፡፡  
          ሆስፒታሎችን በህክምና ቁሳቁስ የመደገፍ ሃሳብ እንዴት ተጀመረ?
በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዜሽን ከተመረቅሁ በኋላ በሲዳማ ዞን ቦና ሆስፒታል ነበር የምሰራው:: ሆስፒታሉ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነበር፡፡ እዚያ ሆስፒታል ውስጥ ከፍተኛ የህክምና መሣሪያ እጥረት ነበር፡፡ በወቅቱ ለዚህ ሆስፒታል በኔ በኩል ምን ማድረግ ነው የምችለው የሚለውን ሳስብ፣ ውጭ ሀገር ከሚገኙ ረጂ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመስራት ሃሳብ ነው የመጣልኝ፡፡ በአጋጣሚ ደግሞ የአክስቴ ልጅ አሜሪካን ነው የምትኖረው፡፡ ከእሷ ጋር ተመካከርን:: በእርዳታ የተሰጠን አንድ ኮንቴነር የህክምና እቃ ወደ ኢትዮጵያ ለማጓጓዝ 24 ሺህ ዶላር ያስፈልጋል ተባልን:: እኛም ጓደኞቻችንን እርዳታ አድርጉልን እያልን በፌስ ቡክ እየለመንን፣ 120 የሚሆኑ ሰዎች ከ10 ዶላር እስከ 4ሺህ ዶላር ከረዱን በኋላ፣ ገንዘቡ ሲሞላልን  ከፍለን ለቦና ሆስፒታል አንድ ኮንቴነር የህክምና መገልገያ መሣሪያዎች አስመጣን፤ ከአንድ አመት ከ6 ወር በፊት፡፡  
ያንን ካየንና በዚያ ከተበረታታን በኋላ ሁለተኛ ዙር እርዳታ ማሰባሰብ እንዳለብን ወሰንን፡፡ ይሄን የጉንችሬ ሆስፒታል እንድናስብ ቅድሚያ ፋውንዴሽን ከተባለ የወዳጆቻችን ድርጅቶች ሃሳብ ቀረበልን፡፡ እኛም ሄደን ስናየው ሆስፒታሉ ትልቅ ችግር ያለበት መሆኑን ተረዳን፡፡ ወዲያው የመጀመሪያውን የቦና ሆስፒታል ድጋፍ ካደረገልንና አሜሪካ ከሚገኘው “ፕሮጀክት ኪዩር” ከተሰኘው ተቋም ጋር ተነጋገርን:: እሱም በድጋሚ ድጋፉን አደረገልን ማለት ነው፡፡ ቅድሚያ ፋውንዴሽን የተባለው ተቋም፣ የማጓጓዣ ወጪ 24ሺህ ዶላሩን አሜሪካ ካሉ ወዳጆች አሰባስበው ከፍለው ነው ድጋፉ  የመጣው፡፡
ያሰባሰባችሁት የህክምና መሳሪያዎች  የዋጋ ግምት ምን ያህል ነው?
እስከ 450ሺህ ዶላር ወይም 13.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ነው፡፡ እኛ ምንም ገንዘብ አላወጣንም:: ያደረግነው ነገር ያው በቅን ልቦና ተነሳስተን፣ ጊዜያችንን በመጠኑ ሰውተን፣ ለህብረተሰቡ የተሻለ ነገር ለማድረግ ነው የሞከርነው፡፡ ሃሳብ እንጂ ገንዘብ ያወጣነው የለም፡፡
ለወደፊት ምን እቅድ አላችሁ?
ከቅድሚያ ፋውንዴሽን ፕሬዚዳንት አቶ አስቻለው ጋር በመሆን በአመት ሁለት ሆስፒታሎችን በዚህ መልኩ መደገፍ የሚል እቅድ ይዘናል፡፡ ከዚህ በኋላ በዚህ እቅድ መሠረት ለሆስፒታሎች ድጋፍ ማሰባሰባችንን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ በተለይ ከአሜሪካ የሚመጡ እቃዎች ጥራታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የህክምና መሣሪያዎች የጥራት ችግር እየተባለ የሚነሳውን ችግር ይቀርፋል ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እንዲህ ያሉ የድጋፍ ማሰባሰብ ፕሮጀክቶች፣ በሌሎች ሀገራት፣ በአብዛኛው በቀዳማዊ እመቤቶች የሚመራ ነው፡፡ ለምሣሌ በኬንያ ከፕሮጀክት ኪዩር ጋር እየተፃፃፈች፣ ገንዘቡን እየከፈለች የምታስመጣው የኡሁሩ ኬንያታ ባለቤት ነች፡፡ ስለዚህ እኛም እድሉን የምናገኝ ከሆነ ከቀዳማዊ እመቤት ጋር መስራት እንፈልጋለን፡፡ ለዚህም ፕሮፖዛል አዘጋጅቻለሁ፡፡
ከሙያ ድጋፍ አንፃርስ ምን እያከናወናችሁ ነው?
የሙያ ድጋፍ ከዚህ በፊትም አድርገናል፡፡ 16 እናቶችን በሁለት ቀናት ቀዶ ጥገና አድርገንላቸዋል:: ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ነበርን፡፡ አንድ ቡድን ከጓደኞቻችን ጋር አቋቁመን፣ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ነፃ የህክምና ድጋፎችን እናደርጋለን:: ለወደፊትም በጐ ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ጓደኞች አሉን፤ ቢያንስ 10 ያህል የቀዶ ጥገና ስፔሻሊስቶች አሉ፡፡ በየአካባቢው የነፃ ህክምና ዘመቻዎችን እናደርጋለን፡፡
የህክምና መሣሪያዎች ድጋፍ በማስመጣት ሂደት የገጠማችሁ ትልቁ ተግዳሮት ምንድን ነው?
አንዱ የጉምሩክ ጉዳይ ነው፡፡ የፍቃድና የጉምሩክ ክፍያ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ በልመና የሚመጡ የህክምና ቁሳቁሶችን በነፃ ቢያስገቡ መልካም ነበር፡፡ ለጉምሩክ ሂደት ብቻ ከ100ሺህ ብር በላይ ተከፍሏል:: ይህ ቢቀር የተሻለ ይሆን ነበር፡፡

  መዲናችን አዲስ አበባ ግዙፍ ከተማ ነች:: በአገራችን ካሉ ነባር የመንግስት መቀመጫ ከነበሩ ከተሞች ጋር ስትወዳደር ዕድሜዋ ረጅም አይባልም፡፡ 130 ዓመታት አካባቢ፣ እ.ኤ.አ በ1886 ተቆረቆረች ነው የሚባለው፡፡ በደቡብ ሕዝቦች ቤንች ማጂ፣ ከምትገኘው ከማጂ፣ በዕድሜ በጥቂት ዓመታት ነው የምትበልጠው:: የኦሮምያዋ ጅማ አሁን እንደምናውቃት አዌቱ አካባቢ ጣልያን መልሶ ያለማት ትሁን እንጂ ከአዲስ አበባ በጣም ቀድማ የተቆረቆረችና ለብዙ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ለወላይታ፣ ከምባታ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ የንግድ መናኸሪያ መተላለፊያ ነበረች፤ አሁንም ነች:: ጅማ ከአዲስ አበባ በዕድሜ የምትበልጥ ከተማ ነች፡፡ በምስራቅም ሐረር ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የከተማ በ16ኛው ክፍለ ዘመን እጅግ የገነነች የንግድና ባህል መናኸሪያ ነበረች:: በሰሜን እነ አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጐንደር መቼ አብበው፣ መቼ ገንነው፣ መቼ እንደደከሙ ብዙ አንባቢ ያውቃል፡፡ ነገር ግን እንደ ጅማ እና ሐረር፣ አዲግራት የመሳሰሉ የቆዩ ከተሞች፤ እንደ አዲስ አበባ ለምን አልገዘፉም? ለምን በአካባቢያቸው ላሉ የገጠር ነዋሪዎች የከተሜነት ተምሳሌት እየሆኑ፣ የኢትዮጵያን የከተሜነት እንቅስቃሴ ለምን አላፋጠኑም? የሚሉት ጥያቄዎች አንባቢያን ቢያነሱ፣ መልሱ እንዲህ በቀላሉ የሚሰነዘር አይደለም፡፡ የከተማ ልማትና የታሪክ ተመራማሪዎች፤ የኢትዮጵያ የከተሜነት የዳዴ ጉዞ፣ ከስር መሰረቱ ከነበረው በተስፋፊነት የተቃኘ ሂደት በመነሳት፣ የመደቦችና የሕዝቦች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ታሪክ ለዛሬውም የተዛባ የከተማ ምጣኔ መሰረት ነው የሚሉ አሉ፤ እኔም አንዱ ባይ ነኝ፡፡
“ከተማ” የሚለው የአማርኛ ቃል በመጀመሪያ “ከፍታ”፣ ቀስ እያለ ደግሞ “ከተማ” ማለት የተስፋፊው ኃይል መከማቻ ሰፈር (የጦር ካምፕ) ሆኖ መቆየቱን የዕውቀት መዛግብት ያስረዳሉ::” በተለይ በሰሜን ኢትዮጵያ ወራሪውና ጭፍራዎቹ በኅብረተሰቡ ላይ “እንደ አንበጣ መንጋ” ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እየሰፈሩበት፣ ያፈራውንና ያከማቸውን ሃብት፣ ከብቱን፣ ምንም ሳይቀር ጠራርገው እንደሚወስዱበት፣ ትዳርና ልጆቹን እንደሚደፍሩበት፣ ሲያልቅበትም ከዚህ ተነስተው ወደ ሌላ ያልተነካ ደንና ግብርና እንደሚያቀኑ ተጽፏል፤ መሰል ግፉ በመጻሕፍት ተተርኳል፡፡”
“ከተማ” ማለት በደቡብ ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜም የቆየ ትርጉሙ ማጂ፣ ሀገረማርያም፣ ጅግጅጋ እንደዚህ ነው የተፈጠሩት፡፡ ንጉሱ አፄ ኃይለስላሴ እ.ኤ.አ በ1932 በአፄ ምኒልክ እና በአባ ጅፋር መካከል ተደርጐ የነበረውን የቀድሞ ስምምነት አፍርሰው ጅማን ወደ አውራጃ፣ ያን የቆየ የኦሮሞ የገበያና የባህል መጋላ ወደ “ከተማ” ቀይረው ከጠቀለሉት ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ፣ በያኔው አውራጃ (በዛሬው ዞን) የሚኖረው ሰው ቁጥር፤ ከአዲስ አበባ የህዝብ ቁጥር ጋር የሚቀራረብ መጠን ድረስ አድጓል፡፡ ነገር ግን ከጂማ ዞን ነዋሪ ውስጥ 120ሺ አካባቢ (5 በመቶ) ብቻ ናቸው በከተሜነት የሚኖሩት፡፡ የምዕተ ዓመቱ መጀመሪያ ላይ የራሷ መሪ የነበራት፣ ለምዕራብ እና ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ንግድና ባህል መዳበር ጉልህ አስተዋጽኦ ስታደርግ የነበረችው ጅማ፤ በከተሜነት ለምን ከእህትዋ ከአዲስ አበባ ወደ ኋላ ቀረች?
(ሾተል፡ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፤
ፀደቀ ይሁኔ ወልዱ)


                 - ለ11 ተከታታይ አመታት በሰላማዊነት የሚስተካከላት አልተገኘም
                 - ኢትዮጵያ ከ163 የአለማችን አገራት 131ኛ ደረጃን ይዛለች


             ላለፉት 10 ተከታታይ አመታት በአለማቀፉ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት ውስጥ ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የዘለቀችው አይስላንድ፣ ዘንድሮም ክብሯን በማስጠበቅ የአለማችን የአመቱ እጅግ ሰላማዊ አገር በሚል ተመርጣለች፡፡
በአምናው የሰላም ደረጃ በ131ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣ የነበረችው ኢትዮጵያ ዘንድሮም ከፍም ዝቅም ሳትል በሪፖርቱ ከተካተቱት 163 የአለማችን አገራት መካከል አነስተኛ ሰላም ያላቸው ከሚለው ምድብ ውስጥ በ131ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ተነግሯል፡፡
ዜጎቿ ሰላማዊ ህይወትን የሚገፉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር በሚል አይስላንድን በአንደኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠውና ኢንስቲቲዩት ፎር ኢኮኖሚክስ ኤንድ ፒስ የተባለው ተቋም ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው የ2019 አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት እንደሚለው፣ በአገሪቱ በአመቱ የተፈጸመው ወንጀል በሚገርም ሁኔታ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡
ከአይስላንድ በመቀጠል በሪፖርቱ ውስጥ ከተካተቱት 163 የአለማችን አገራት መካከል በሰላም ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ኒውዚላንድ ስትሆን ፖርቹጋል በሶስተኛ፣ ኦስትሪያ በአራተኛነት ይከተላሉ ያለው ዝርዝሩ፤ አራቱ አገራት ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት፣ የአለማችን ምርጥ አራት ሰላማዊ አገራት ሆነው መዝለቃቸውንም አስታውሷል፡፡
ተቋሙ ለ13ኛ ጊዜ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው አመታዊው አለማቀፍ የሰላም ሁኔታ ሪፖርት ውስጥ በሰላማዊነት የመጨረሻውን ደረጃ የያዘችውና በአመቱ እጅግ በከፋ ሁኔታ ሰላም የራቃት የአለማችን አገር አፍጋኒስታን መሆኗንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሶርያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ የመን፣ ኢራቅ፣ ሶማሊያ፣ ማዕከላዊ የአፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሊቢያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩስያ ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው በሰላም እጦት ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸው ተነግሯል፡፡
አለማችን በእርስ በእርስ ግጭትና ብጥብጥ በየአመቱ 14 ትሪሊዮን ዶላር  ታጣለች ያለው ሪፖርቱ፣ በግጭትና በብጥብጥ ሳቢያ በአመቱ 28.9 ቢሊዮን ዶላር ያጣችው ሶርያ፣ ክፉኛ የተጎዳች የአለማችን ቀዳሚዋ አገር ናት ብሏል፡፡
የአለማችንን አገራት ማህበራዊ ደህንነት፣ ግጭትና ሌሎች ሁኔታዎች በመገምገም በየአመቱ ሪፖርቱን ይፋ የሚያደርገው ተቋሙ፣ በአመቱ የአለማችን አማካይ የሰላም ሁኔታ እጅግ በጥቂቱም ቢሆን መሻሻል እንዳሳየ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የ86 አገራት የሰላም ሁኔታ ቢሻሻልም 76 አገራት ደግሞ ሰላማቸው ከአምናው መቀነሱን አመልክቷል፡፡
የአለማችን ሰላም ባለፉት 11  አመታት በ3.78 በመቶ ያህል መቀነሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ለዚህም ከፍተኛውን ድርሻ አበርክተዋል በሚል በምክንያትነት የጠቀሳቸው ሽብርተኝነትና የአገራት ውስጣዊ ግጭቶችን ነው፡፡
በሪፖርቱ ከተካተቱት አገራት መካከል 104 በሚሆኑት ውስጥ የሽብር ድርጊቶች ጭማሪ ማሳየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ ከግጭት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2017 በነበሩት ጊዜያት የ140 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጧል፡፡

አፕል እና ጎግል ይከተላሉ

                    ታዋቂው የአሜሪካ ኩባንያ አማዞን፤ ካንታር የተባለው አለማቀፍ የጥናት ተቋም ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው የ2019 የፈረንጆች አመት የአለማችን ባለከፍተኛ የንግድ ምልክት ዋጋ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛነት መቀመጡ ተዘግቧል፡፡
በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አለማቀፍ የሸቀጦች ንግድ አገልግሎት በመስጠት በትርፋማነት የዘለቀውና የኩባንያ የንግድ ምልክት ዋጋውን አምና ከነበረበት 52 በመቶ በማሳደግ፣ 315 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ያደረሰው አማዞን፣ ታዋቂዎቹን አፕልና ጎግል በመቅደም ለመጀመሪያ ጊዜ የአለማችን ባለውድ ዋጋ ኩባንያ መሆኑን ፎርብስ መጽሄት በዘገባው አስነብቧል፡፡
ከአምና በስተቀር ላለፉት 12 አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው አፕል ኩባንያ ዋጋውን 309.5 ቢሊዮን ዶላር ቢያደርስም በኣማዞን ተቀድሞ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ሊል ተገዷል ያለው ዘገባው፣ አምና በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ታዋቂው ጎግል በበኩሉ፤ በ309 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዙን አመልክቷል፡፡
ማይክሮሶፍት በ251.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቪዛ በ177.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ፌስቡክ በ159 ቢሊዮን ዶላር፣ አሊባባ በ131.2 ቢሊዮን ዶላር፣ ቴንሰንት በ130.9 ቢሊዮን ዶላር፣ ማክዶናልድ በ130.4 ቢሊዮን ዶላር፣ ኤቲኤንድቲ በ108.4 ቢሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው በንግድ ምልክት ዋጋ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ደረጃን የያዙ የአለማችን ኩባንያዎች ሆነዋል፡፡

የ21 አመቷ አሜሪካዊት ሌክሲ አልፎርድ በለጋ ዕድሜዋ ሁሉንም የአለማችን አገራት በመጎብኘት አዲስ ክብረ ወሰን ማስመዝገቧን ፎርብስ መጽሄት ከሰሞኑ ዘግቧል፡፡ላለፉት ተከታታይ አመታት የአለማችንን አገራት ከዳር እስከ ዳር በማዳረስ ተጠምዳ የኖረችውና ባለፈው ሳምንት ሰሜን ኮርያ የገባችው ሌክሲ፣ በለጋ ዕድሜዋ ሁሉንም የአለማችን አገራት የጎበኘች ሴት የመሆን ዕቅዷን በድል በማጠናቀቅ በአለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ ላይ ሰፍራለች፡፡የአለማችንን 196 አገራት በሙሉ የመጎብኘት ዕቅድ ይዛ የተነሳችው ገና ህጻን ሳለች ጀምሮ እንደነበር የተነገረላት ሌክሲ፣ እ.ኤ.አ በ2013 ላይ በ24 አመቱ ሁሉንም አገራት ከጎበኘው አሜሪካዊው ጄምስ አስኪዝ ክብረወሰኑን ከመንጠቋ በተጨማሪ አገራቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ጎብኝታ በመጨረስም ታሪክ መስራቷን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ካሊፎርኒያ ውስጥ የአስጎብኝ ድርጅት ባለቤት በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ያደገችው ሌክሲ፣ በለጋ እድሜዋ ከቤተሰቦቿ ጋር ወደተለያዩ አገራት የመጓዝ ዕድል እንዳገኘችና የ18 አመት ወጣት እያለች 72 የአለማችን አገራትን እንደጎበኘች ያስታወሰው ዘገባው፣ ከሶስት አመታት በፊት ግን ቀሪዎቹን 124 አገራት በማዳረስ ክብረወሰኑን ለመስበር በትጋት አለምን መዞር መጀመሯን አመልክቷል፡፡


               “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በ1 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቀዳሚነቱን ይዟል

               በአለማችን የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ በአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” የተሰኘው ተወዳጅ ፊልም እጅግ ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን መያዙ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1939 ለእይታ የበቃው “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በወቅቱ በአገር ውስጥ ገበያ 200.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በቦክስ ኦፊስ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የዘገበው ሲኤንቢሲ ኒውስ፣ ይህ ገቢ በዛሬው የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.82 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚደርስ አስታውቋል::
እ.ኤ.አ በ1977 ለእይታ የበቃውና በወቅቱ 461 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያገኘው የመጀመሪያው “ስታር ዎርስ” ፊልም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ፊልሙ ያገኘው ገቢ በአሁኑ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ዘገባው አመልክቷል፡፡
“ዘ ሳውንድ ኦፍ ሚዩዚክ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ፊልም ለእይታ በበቃበት እ.ኤ.አ በ1965 ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 159.3 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በወቅቱ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.28 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰው ይህ ገቢ ፊልሙን በምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ የሶስተኛነት ደረጃ ላይ እንዳስቀመጠው አመልክቷል፡፡
የሳይንሳዊ ልቦለድ ዘውግ ያለውና እ.ኤ.አ በ1982 ለእይታ የበቃው ለእይታ የበቃው “ኢ.ቲ ዘ ኤክስትራ ቴሪስቴሪያል” በወቅቱ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.27 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት የአራተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ ዘመን አይሽሬው ታይታኒክ በበኩሉ በ1.22 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
“ዘ ቴን ኮማንድመንትስ” በ1.18 ቢሊዮን ዶላር፣ “ጃውስ” በ1.15 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዶክተር ዚያጎ” በ1.12 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዘ ኤክሶርዚስት” በ996.5 ሚሊዮን ዶላር፣ “ስኖው ዋይት ኤንድ ዘ ሰቭን ድዋርፍስ” በ982.1 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በአለማችን የፊልም ታሪክ ከፍተኛ ገቢ ካስገቡ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ፊልሞች መካከልም “ቤንሁር”፣ “አቫታር”፣ “ዡራሲክ ፓርክ”፣ “አቬንጀርስ - ኢንድጌም”፣ “ዘ ላየን ኪንግ”፣ “ዘ ስቲንግ”፣ “ዘ ግራጁዌት”፣ “ፋንታሲያ” እና “ዘ ጋድ ፋዘር” እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡