Administrator

Administrator

Saturday, 11 January 2020 12:32

የአድማስ ትውስታ

   ከአዘጋጁ፡- የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተመሰረተበትን 20ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 27 ቀን 1993 ዓ.ም በፊት ለፊት ገፅ ላይ የወጡ ሦስት አብይ ዜናዎችን ለትውስታ ያህል አቅርበናቸዋል አንብባችሁ ተገረሙ፤ ተደመሙ፡፡

                  የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንደኮበለለ ተነገረ

         የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ እንደኮበለለ ተነገረ
የእፎይታ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ለወንድሙ ሠርግ በሚል ከአንድ ሳምንት በፊት ከኢትዮጵያ ውጭ ሄዶ በዚያው መቅረቱን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለፁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ገ/አብ ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምሪያ ኃላፊ የነበረ ሲሆን፤ ከኢህአዴግ ከመቀላቀሉ በፊት የቀድሞው ሠራዊት የመቶ አለቃና የክፍሉም ካድሬ እንደነበር ይታወሳል ያሉት እነዚሁ ምንጮች፤ ኢህአዴግን የተቀላቀለው ደብረታቦር ላይ በ1982 በተደረገ ውጊያ ተማርኮ ነው ብለዋል፡፡ በምርኮኛ የጦር መኮንኖች የተቋቋመው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መኮንኖች አብዮታዊ ንቅናቄ (ኤዴመአን) የሚባል ድርጅት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንደነበር ምንጮች ጠቁመው፤ በወቅቱ የበረደች ጥይት እጁን መትታው የተማረከው አቶ ተስፋዬ ገብረአብ በቅርቡ በተካሄደው የካድሬዎች ኮንፈረንስ ላይ ለመገኘት ጠይቆ መከልከሉን ገልፀዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ገብአረብ “የቡርቃ ዝምታ”፤ “የቢሾፍቱ ቆሪጦች”፣ “ያልተመለሰው ባቡር” የተሰኙ መጽሐፎች ደራሲ ነው፡፡
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)

የህወሓት ካድሬዎች እንዲወያዩበት ቀረበ የተባለ የአቶ መለስ ዜናዊ ጽሑፍ፤ የሊበራል ዲሞክራሲ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መርሆች ጠቃሚ ቢሆኑም በኢንዱስትሪ ለበለፀጉ አገሮች ብቻ የሚሰሩ ናቸው፤ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው እንደሚል ተገለፀ፡፡
የመፃፍ፣ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ የዜጐችን መብት እናከብራለን የሚለው ይኸው ጽሑፍ፤ ተቃዋሚዎችንና ነፃ ፕሬስን በማፈን ሳይሆን በህብረትና በህግ በጽናት እንታገላቸዋለን የሚል ነው ተብሏል፡፡
የህግ የበላይነት መከበር አለበት፤ የዜጐች መብትና በህግ ፊት እኩል መሆናቸው መጠበቅ አለበት እንዲሁም የመንግስት ስልጣን በህግ አውጪ፣ አስፈፃሚና ተርጓሚ ተከፋፍሎ እርስ በርሱ የሚቆጣጠር መሆን ይገባዋል የሚሉ መሰረተ ሃሳቦች ዋነኛ የሊበራል ዲሞክራሲ መርሆች እንደሆኑ የዘረዘረው የአቶ መለስ ጽሑፍ፤ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እነዚህን መርሆች እንደ መነሻ በመውሰድና ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ፣ ህዝባዊና አብዮታዊ ባህርዮችን ያላብሳቸዋል ይላል፡፡
ጽሑፉ፤ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ በግለሰቦች መብት መከበር ላይ ብቻ ሳይገታ የህዝባችን መብት ማለትም የብሔር ጥያቄንም በሚገባ ይመልሳል፤ በዚህም ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ አድኗል” ካለ በኋላ፤ አሁንም ትምክህተኝነትና ጠባብነት አለ፤ እንዲያውም በአንዳንድ በኩል ተባብሷል በማለት ኢትዮጵያዊነትን የመፍጠር ስራ መጠናከር አለበት ሲል ይገልፃል፡፡
በኢኮኖሚ በኩል ሊበራል ዲሞክራሲ ነፃ ውድድርን በማስፈንና መንግስት ሙሉ ለሙሉ ከኢኮኖማው እንዲወጣ በማድረግ፣ ብልጽግና እንደሚያመጣ የተነተነው ይኸው ጽሑፍ፤ “ሊበራል ዲሞክራሲ በኢንዱስትሪ ለበለፀጉ አገሮች እንደሚጠቅም ግልጽ ቢሆንም መርሁን ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል፡፡ ነፃ ገበያ ሊሸፍናቸው የማይችሉ ቀዳዳዎችን ለመድፈን መንግስት ኢኮኖሚው ውስጥ መግባት አለበት” የሚል ሲሆን፤ የባለሀብቶች አቅም እየዳበረ ሲሄድ የመንግስት ተሳትፎ እየቀነሰ እንደሚሄድ፤ ይህም የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርህ እንደሆነ ያብራራል፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ የበላይነት እንዳላገኘ እንረዳለን የሚለው የአቶ መለስ ጽሑፍ፤ ተቃዋሚዎችንና ነፃ ፕሬስን በህግና በህብረት እንታገላቸዋለን በማለት አላማውን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ጋዜጠኞችን በማሰርና የፕሬስ ነፃነትን በማፈን በአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች በግንባር ቀደምትነት ዘወትር የሚወቀስ ሲሆን ሰሞኑን ፈረንሳይ አገር የሚገኝ ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ማህበር የፕሬስ ነፃነትን ያፍናሉ በማለት ከዘረዘራቸው የዓለም መሪዎች መካከል ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን አንዱ አድርጓቸዋል፡፡
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)
***
የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንትን ጨምሮ በርካታ ተማሪዎች የደረሱበት አልታወቀም
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ በኋላ ወደ 3ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ለ8 ቀናት ሰንዳፋ ቆይተው ቢመለሱም የተማሪዎች ህብረትን ሲያንቀሳቅሱ የነበሩ ተማሪዎች ግን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አንዳንድ ተማሪዎች ገለፁ፡፡
ከሚያዚያ 1 ቀን 1993 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎቹን የመብት ጥያቄ ሲያቀርቡና ሲያስተባብሩ የነበሩ ተማሪዎች ከስጋት የተነሳ ራሳቸውን ደብቀው እንደሚገኙ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
የቀድሞው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረው ተማሪ ተክለሚካኤል አበበ በፖሊሶች ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን አብረውት የሚማሩ ተማሪዎች ጠቅሰው፤ ፖሊሶች የተክለሚካኤል የትውልድ ቦታ ወደሆነው አሩሲ ነገሌ በሄሌኮፕተር በመሄድ ፈልገው ሲያጡት፣ ታላቅ ወንድሙን አፈወርቅ አበበን ይዘው አዲስ አበባ እንዳመጡት ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተማሪ ተክለሚካኤል ወላጆች በከፍተኛ ስጋት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት የተክለሚካኤል ጓደኞች፤ ለማረጋገጥ ባይቻልም ወደ አንድ ኤምባሲ ለመግባት ጠይቆ ተፈቅዶለት እዚያ እንደሚገኝ ወሬ መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡
ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት የነበረውና የህግ ፋኩሊቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ተክለሚካኤል አበበ፤ “የተማሪው ህገ መንግሰታዊ መብት መጠበቅ አለበት” በሚል በመታገሉና በሚያቀርባቸው ሐሳቦች ብዙ ተማሪዎች ይደግፉታል ሲሉ የቅርብ ጓደኞቹ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ቀደም የደህንነት አካላት መኝታ ክፍሉ ድረስ በመምጣት ዛቻና ማስፈራሪያ ያደርሱበት እንደበር ብዙዎቹ ተማሪዎች ያውቃሉ የሚሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፤ በፖሊሶች አድራጐት ይማረር እንደነበር፤ ሚያዝያ 8 ቀን 1993 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ተማሪዎችን ባወያዩበት እለትም ይህንኑ ተናግሮ ነበር ብለዋል፡፡
ተማሪ ተክለሚካኤል “ህሊና” በሚል ስያሜ መታተም ጀምሮ የነበረውን የተማሪዎች ህብረት ጋዜጣ ከሚያዘጋጁ ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
አሁንም በዩኒቨርሲቲው ትምህርት ያልተጀመረ ሲሆን፤ አንዳንድ የስድስት ኪሎ ተማሪዎች እንዳሉት “የመሰብሰብ ነፃነት አላችሁ” ተብለን ስንሰባሰብ በፖሊሶች ታፍሰን የምንወሰድ ከሆነ ለህይወታችን ሥጋት አለን ብለዋል፡፡   
(ሚያዝያ 27,1993 ዓ.ም)

  በዲሞክራቲክ ኮንጎ ባለፈው ሰኔ ወር የተቀሰቀሰው፣ በአለማችን እጅግ የከፋውና በፍጥነት በመስፋፋት ላይ የሚገኘው የኩፍኝ ወረርሽኝ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጉን የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የኩፍኝ ወረርሽኙ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 310 ሺህ ያህል ሰዎችን ሳያጠቃ አልቀረም መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ ወረርሽኙ ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ ባለፈው መስከረም የአገሪቱ መንግስትና የአለም የጤና ድርጅት በትብብር አስቸኳይ የክትባትና የህክምና ዘመቻ ቢጀምሩም፣ በአገሪቱ ያለው የጤና አገልግሎትና የተቋማት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አለመቻሉን አመልክቷል፡፡
በአሁኑ ሰአት ወረርሽኙ ወደ አገሪቱ 26ቱም ግዛቶች መስፋፋቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ ከ18 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአገሪቱ ህጻናት የኩፍኝ ክትባት መሰጠቱንም አስታውሷል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ክትባቱን በመጪዎቹ ስድስት ወራት ለህጻናትና ታዳጊዎች በስፋት ለማዳረስ ለተያዘው አገራዊ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ ተጨማሪ 40 ሚሊዮን ዶላር ያህል እንደሚያስፈልግ በመጥቀስ፣ ለጋሾችና አለማቀፉ ማህበረሰብ ድጋፉን እንዲያደርግ ጥሪ ማስተላለፉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በነሃሴ ወር 2018 የተቀሰቀሰው አስከፊ የኢቦላ ወረርሽኝ ከ2 ሺህ 230 በላይ ዜጎቿን የገደለባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አሁን ደግሞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በአደገኛ የኩፍኝ ወረርሽኝ መመታቷ ወደ ከፋ ቀውስ ሊያስገባት ስለሚችል አለማቀፉ ማህበረሰብ እርብርብ ማድረግ እንደሚገባውም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሚቴ የተባለው አለማቀፍ ተቋም በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2020 የእርስ በእርስ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ይፈጠርባቸዋል ተብለው የሚጠበቁ የአለማችን አገራትን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የመን እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም ከአለማችን አገራት ሁሉ እጅግ የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ያጋጥማታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ላለፉት አምስት ተከታታይ አመታት በእርስ በእርስ ግጭት የምትታመሰዋ የመን፣ 80 በመቶ ወይም ከ24 ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ህዝቧ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልገው እንደሆነ የጠቆመው ተቋሙ፤ ባለፉት 5 አመታት ውስጥ ሩብ ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች በግጭቶች ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውንና የሰብዓዊ ቀውሱ በአዲሱ አመትም በከፋ ሁኔታ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
ተቋሙ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ የእርስ በእርስ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋዎችን ጨምሮ በአገራት ውስጥ ሰብዓዊ ቀውሶችን ሊያስከትሉ ይችላሉ ያላቸውን 76 ያህል የተለያዩ መስፈርቶችን በመጠቀም ባወጣው የዘንድሮው ዝርዝር፤ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሶርያ፣ ናይጀሪያና ቬንዙዌላ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል::
የከፋ ቀውስ ያሰጋቸዋል ተብለው ተቋሙ ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ደረጃዎች የሰጣቸው አፍጋኒስታን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሶማሊያና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሲሆኑ፤ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች አገራት መካከልም ብሩንዲ፣ ካሜሩን፣ ቻድ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ማሊ፣ ማይንማር፣ ኒጀርና ሱዳን ይገኙበታል፡፡
ተቋሙ ባለፈው አመት ባወጣው የሰብዓዊ ቀውስ ስጋት ያለባቸው ዝርዝር ውስጥ ተካትተው የነበሩት ባንግላዴሽ፣ ሜክሲኮ፣ ኒካራጓና ፓኪስታን ዘንድሮ ከዝርዝሩ የወጡ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ሶስቱ አዳዲስ አገራት ደግሞ ቡርኪናፋሶ፣ ብሩንዲና ቻድ ናቸው፡፡

 የቶጎው ፕሬዚዳንት ፋውሬ ጋሴንጊቤ “ደጋፊዎቼና ፓርቲዬ ጫና አሳድረውብኛል” በሚል ሰበብ ለ4ኛ የስልጣን ዘመን በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን በይፋ እንዳስታወቁ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ዩኤንአይአር የተባለው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ባለፈው ማክሰኞ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ፓርቲውን ወክለው  በመጪው ወር በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ እንዲሳተፉ ደጋፊዎቻቸው ጫና ስላሳደሩባቸው ለቀጣይ አስር አመታት ያህል በመንበራቸው ላይ እንዲቆዩ በሚያስችላቸው ምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን ነው ፕሬዚዳንት ጋሴንጊቤ የተናገሩት፡፡
የአገሪቱ ፓርላማ ባለፈው አመት ባደረገው የህገ መንግስት ማሻሻያ አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት የስልጣን ዘመን በላይ ማገልገል እንደማይችል ቢደነግግም፣ ፕሬዚዳንት ጋሴንጊቤ ግን ዘንድሮና በ2025 በሚካሄደው ምርጫ ለመወዳደር ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1967 በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዙትና ለ38 አመታት ያህል አገሪቱን አንቀጥቅጠው የገዙት አባታቸው ጋሴንጊቤ ኢያዴማ በሞት በተለዩበት 2005 ከተካሄደ አወዛጋቢ ምርጫ አንስቶ አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ፋውሬ ጋሲንጊቤ፤ በ2010 እና በ2015 በተመሳሳይ አወዛጋቢ ምርጫ በማሸነፍ አገሪቱን በቀውስ ውስጥ ይዘዋት መዝለቃቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት በተደረገው የህገ መንግስት ማሻሻያ በስልጣን ዘመናቸው ለፈጸሟቸው ወንጀሎች ሁሉ በህግ እንዳይጠየቁ ወይም እንዳይከሰሱ ከለላ እንዲሰጣቸው ማድረጋቸውንም አስታውሷል፡፡

  የአለማችንን ከተሞች በተለያዩ መስፈርቶች በማወዳደር በየአመቱ ደረጃ የሚያወጣው ሪዞናንስ የተባለ አለማቀፍ ተቋም ከሰሞኑም የ2020 የአለማችን ምርጥ ከተሞችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን የእንግሊዝ ርዕሰ መዲና ለንደን በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ለኑሮ አመቺነት፣ የቱሪዝም ተመራጭነት፣ ጥራት፣ የመሰረተ ልማት አውታሮች መስፋፋት፣ ውበትና ንጽህናን ጨምሮ 22 ያህል መስፈርቶችን በመጠቀም የአለማችንን ከተሞች አወዳድሮ ደረጃ የሚሰጠው ተቋሙ፤ የአሜሪካዋን ኒው ዮርክ ሲቲ በሁለተኛነት፣ የፈረንሳዩዋን ፓሪስ ደግሞ በሶስተኛነት ደረጃ አስቀምጧቸዋል፡፡
የጃፓን መዲና ቶክዮ፣ የሩስያዋ ሞስኮ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬትሷ ዱባይ፣ የሲንጋፖሯ ሲንጋፖር፣ የስፔኗ ባርሴሎና፣ የአሜሪካዋ ሎስ አንጀለስ እንዲሁም የጣሊያኗ ዋና ከተማ ሮም እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የአመቱ የአለማችን ምርጥ ከተሞች መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

  ማኒካ በተባለችው የሞዛምቢክ ግዛት ሁለት ሴት ልጆቹን በ120 ዶላር ለመሸጥ ሲስማማ ነበር የተባለው አባት በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን አፍሪካን ኒውስ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
የ49 አመት ዕድሜ እንዳለው የተነገረለትና ባለፈው ቅዳሜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ሞዛምቢካዊው አባት፣ ድርጊቱን ለመፈጸም ያነሳሳው የገንዘብ እጥረት እንደሆነና ልጆቹን ሽጦ በሚያገኘው ገንዘብ ከሌላ ሰው የተበደረውን የ65 ዶላር ዕዳ ለመክፈል አቅዶ እንደነበር ዘገባው አብራርቷል፡፡
ግለሰቡ የስድስት እና የዘጠኝ አመት ዕድሜ ያላቸውን ሴት ልጆቹን ለመሸጥ ሲደራደር በአካባቢው ሰዎች ጥቆማ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን የጠቆመው ዘገባው፣ ልጆቹን ለመግዛት ዋጋ ሲደራደር የነበረው ገዢም መታሰሩን አመልክቷል፡፡
በሞዛምቢክ ህጻናትንና ሴቶችን በአገር ውስጥና ለጎረቤት አገራት ለወሲብና ለባርነት የመሸጥ ተግባር ስር የሰደደ ነው ያለው ዘገባው፣ ግለሰቡ በቅርቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ቅጣት ይጣልበታል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡

 ታዋቂው የመኪና አምራች ኩባንያ ሮልስ ሮይስ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019፣ 5 ሺህ 152 መኪኖቹን በመሸጥ በ116 አመታት ታሪኩ ከፍተኛውን ሽያጭ ማስመዝገቡን አስታውቋል::
ኩባንያው በአመቱ ኩሊናን የተባለችውን ውድ ሞዴሉን ጨምሮ የተለያዩ የመኪና ምርቶቹን ከ50 በላይ የአለማችን አገራት ውስጥ ለሚገኙ ደንበኞቹ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን ሽያጩ ካለፈው አመት በ25 በመቶ ማደጉንም አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በአመቱ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖችን የሸጠው በአሜሪካ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን፣ በቻይና እና በተለያዩ የአውሮፓ አገራትም ብዛት ያላቸው መኪኖቹን መሸጡን አመልክቷል፡፡ በብዛት ከተሸጡት የኩባንያው መኪኖች መካከል ፋንተም፣ ዳውን እና ዋሪት የተባሉት ሞዴሎቹ እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡


   የእስራኤሉ ጠ/ሚ ፍ/ቤት እንዳልቀርብ ከለላ ይሰጠኝ አሉ


           የቀድሞው የአንጎላ ፕሬዚዳንት ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ልጅ የሆነችውና የአባቷን ስልጣን መከታ በማድረግ ባካበተችው ሃብት የአፍሪካ ቁጥር አንድ ቢሊየነር እንደሆነች የሚነገርላት ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ፤ ያላግባብ አፍርታዋለች የተባለው አንድ ቢሊዮን ዶላር ያህል ሃብት እንዳይንቀሳቀስ መታገዱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አገሪቱን ለ40 አመታት ያህል ያስተዳደሩትን ኤዱዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ተክተው ከ2 አመታት በፊት ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዚዳንት ጃኦ ሎሬንኮ፤ ብሔራዊ የጸረ-ሙስና ዘመቻ መጀመራቸውንና 2.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ሃብት እንዳላት የሚነገርላት የቢሊየነሯ ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ ሃብት እንዳይንቀሳቀስ፣ ከሰሞኑ በፍርድ ቤት የተላለፈው ውሳኔም የዚህ ዘመቻ አካል እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል፡፡
የአገሪቱ መንግስት የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነቸው የ46 አመቷ ኤልዛቤል ዶስ ሳንቶስ፣ ግዙፉን የቴሌኮም ኩባንያ ዩኒቴልን ጨምሮ በበርካታ ኩባንያዎች ውስጥ ከፍተኛ የሃብት ድርሻ እንዳላቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ የአባቷን ስልጣን መከታ በማድረግ በሙስናና በምዝበራ ሃብት አፍርታለች በሚል ክስ ቢቀርብባትም፣ ምንም አይነት ወንጀል እንዳልፈጸመች ስታስተባብል መቆየቷንም ገልጧል፡፡
ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስተላለፉን ተከትሎ ኤልዛቤል በትዊተር ድረገጽ ባስተላለፈችው መልዕክት፤ ውሳኔውን በፖለቲካ ጫና የተላለፈብኝ ነው ስትል መቃወሟን የጠቆመው ዘገባው፣ የቀረቡብኝን የሃሰት ክሶች በህግ ተከራክሬ ነጻ ለመውጣት ዝግጁ ነኝ ማለቷንም አመልክቷል፡፡ የቀረበባትን የሙስና ክስ በማጣራት ላይ የሚገኘው ፍርድ ቤቱ  ባስተላለፈው ውሳኔ፤ ኤልዛቤል በባንክ ውስጥ ያላት ገንዘብና በግዙፍ ኩባንያዎች ውስጥ ያላት የሃብት ድርሻ እንዳይንቀሳቀስ ከማገዱ በተጨማሪ የባለቤቷ ሲንዲካ ዶኮሎ ሃብትም እንዳይንቀሳቀስ ማገዱን ዘገባው አክሎ ገልጧል::
በሌላ በኩል ደግሞ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በቀረቡባቸው የሙስና፣ የእምነት ማጉደልና የማታለል ክሶች ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የህግ ከለላ ይሰጠኝ ሲሉ ለፓርላማው ጥያቄ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ሶስት የወንጀል ክሶች የተመሰረቱባቸውና ምንም አይነት ወንጀል አልፈጸምኩም በማለት ምላሽ ሲሰጡ የቆዩት የ70 አመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ባለፈው ረቡዕ ለአገሪቱ ፓርላማ በላኩት ደብዳቤ፤ለተወሰነ ጊዜ ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የህግ ከለላ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ጥያቄያቸው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችለው ከፓርላማው አባላት ከግማሽ በላይ ድጋፍ ሲያገኝ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ኔታኒያሁ ቀጣዩ የአገሪቱ ምርጫ እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ የፍርድ ሂደቱ እንዳይጀመር ለፓርላማው የህግ ከለላ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ፣ የተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውንና ሰውዬው የህግ ከለላው እንዳይሰጣቸው ተግተው እንደሚታገሉ በይፋ አስታውቀዋል፡፡ እስራኤል በአንድ አመት ውስጥ ባካሄደቻቸው ሁለት ምርጫዎች ኔታኒያሁም ሆኑ ተቀናቃኛቸው ቤኒ ጋንዝ መንግስት ለመመስረት የሚያስችላቸውን ድምጽ ማግኘት ባለመቻላቸው ለሶስተኛው ምርጫ ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፤ የኔታኒያሁ የህግ ከለላ ጥያቄም የተከሰሱበት ወንጀል በፍርድ ቤት የሚታይበት ጊዜ ከምርጫው በኋላ እንዲጀመር ከመፈለግ የመነጨ ነው ብሏል፡፡


   ዶ/ር ድሬ በ950 ሚ. ዶላር ገቢ የ10 አመታት ቀዳሚው ሙዚቀኛ ሆኗል

         የአለማችን ቀዳሚዎቹ 500 ባለጸጎች ባለፈው የፈረንጆች አመት 2019 ሃብታቸው በድምሩ በ1.2 ትሪሊዮን ዶላር ወይም በ25 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 5.9 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ብሉምበርግ ሲዘግብ፤ ፎርብስ በበኩሉ ዝነኛው ድምጻዊ ዶክተር ድሬ ባለፉት አስር አመታት ከአለማችን ሙዚቀኞች መካከል ከፍተኛውን ገቢ ማግኘቱን አስነብቧል፡፡
ባለፉት 12 ወራት የሃብት መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል በሚል በአንደኛነት ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ አርኖልት ሲሆኑ ባለጸጋው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 36.5 ቢሊዮን ዶላር ያህል ተጨማሪ ሃብት ማካበታቸውን ብሉምበርግ አስነብቧል:: ከፍተኛ የሃብት ጭማሪ ካሳዩት የአለማችን ቢሊየነሮች መካከል አብዛኞቹ በቴክኖሎጂውና በቅንጦት ቁሳቁስ ምርት ዘርፍ የተሰማሩ እንደሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ የፌስቡክ መስራችና ዋና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙክበርግ የ27.3 ቢሊዮን ዶላር፣ የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ ደግሞ የ22.7 ቢሊዮን ዶላር የሃብት ጭማሪ በማስመዝገብ የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውንም አመልክቷል፡፡
በአመቱ በፍቺ ለተለያዩዋት የቀድሞ የትዳር አጋራቸው በካሳ መልክ የከፈሉትን 8 ቢሊዮን ዶላር ጨምሮ ሃብታቸው በ10 ቢሊዮን ዶላር የቀነሰባቸው የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ፣ ምንም እንኳን በ2019 የሃብት መጠናቸው በእጅጉ የቀነሰባቸው ሁለተኛው የአለማችን ባለጸጋ ቢሆኑም፣ አሁንም በ116 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአመቱ የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነርነት ክብራቸውን የነጠቃቸው የለም:: የማይክሮሶፍቱ መስራች ቢል ጌትስ በ113 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአለማችን ሁለተኛው ባለጸጋ ሲሆኑ፣ ፈረንሳዊው ቢሊየነር በርናንድ አርኖልት በበኩላቸው፤ በ106 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዛቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከአለማችን 500 ቢሊየነሮች መካከል በአመቱ የሃብት መጠናቸው ቅናሽ ያሳየባቸው 52 ባለጸጎች ብቻ ናቸው ያለው ብሉምበርግ፤ በአመቱ የ10.2 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያጡት በሚዲያው ዘርፍ የተሰማሩት አሜሪካዊው ቢሊየነር ሩፐርት ሙርዶክ ከፍተኛው የሃብት መቀነስ  ያጋጠማቸው ቀዳሚው የአለማችን ቢሊየነር መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ባለፉት 10 አመታት ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ዝነኛ ሙዚቀኞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገው ፎርብስ መጽሄት፤ ታዋቂው የሂፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ዶ/ር ድሬ በ950 ሚሊዮን ዶላር ገቢ፣ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ገልጧል፡፡ ባለፉት አስር አመታት በድምሩ 825 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠቺው ታዋቂዋ ድምጻዊት ቴለር ስዊፍት ስትሆን ቢዮንሴ ኖውልስ በ685 ሚሊዮን ዶላር በሶስተኛነት ትከተላለች፡፡
ዩቱ የሙዚቃ ቡድን አባላት 675 ሚሊዮን ዶላር፣ ፒዲዲ በ605 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤልተን ጆን በ565 ሚሊዮን ዶላር፣ ጄይዚ በ560 ሚሊዮን ዶላር፣ ፖል ማካርቲኒ በ535 ሚሊዮን ዶላር፣ ኬቲ ፔሪ በ530 ሚሊዮን ዶላር፣ ሌዲ ጋጋ በ500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም ፎርብስ በዘገባው አስታውቋል፡፡


  የቀድሞ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ እና ባለቤታቸው ባራክ ኦባማ የአመቱ የአለማችን ድንቅ ሰዎች ተብለው መመረጣቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል:: ጋሉፕ የተባለው ተቋም በአሜሪካ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ የ55 አመቷ ሚሼል ኦባማ እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም የአለማችን ቁጥር አንድ ድንቅ ሴት ተብለው ተመርጠዋል፡፡
በተቋሙ ዝርዝር ሁለተኛዋ ተደናቂ ሴት ተብለው ስማቸው የተጠቀሰው ቀዳማዊት እመቤት ሜሊኒያ ትራምፕ ሲሆኑ፣ ሄላሪ ክሊንተን እና ኦፕራ ዊንፍሬይ የሶስተኛነት ደረጃን ይዘዋል፡፡ ጋሉፕ ከአሜሪካውያን ድምጽ እየሰበሰበ በየአመቱ ይፋ በሚያደርገው የወንድ ድንቆች ዝርዝር ውስጥ ባለፉት 11 ተከታታይ አመታት በአንደኛ ደረጃ ላይ የዘለቁት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ዘንድሮም ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ተመሳሳይ ድምጽ በማግኘት በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በዘንድሮው የድንቅ ወንዶች ዝርዝር ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ሲሆኑ፣ የቴስላ ኩባንያ መስራችና ባለቤት ቢሊየነሩ ኤለን ሙስክ እንዲሁም የማይክሮሶፍት መስራችና በጎ አድራጊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በሶስተኛና በአራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡

Page 5 of 464